You are on page 1of 13

የውል ቁጥር፡------------------------

ቀን፡ / /2014 ዓ.ም

የሀበሻ ሲሚንቶ ምርት ለማከፋፈል የተደረገ የአከፋፋይነት የውል ስምምነት

ይህ ውል ዛሬ ቀን ------------------------- ዓ.ም በሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የገ/ማር


ከ------------------ ፋብሪካ ተረክቦ በጅምላ እና ችርቻሮ ወኪል አከፋፋዮች የሚያከፋፍለውን የሐበሻ
ሲሚንቶ ከዚህ በኋላ ‘‘አቅራቢ’’ እየተባለ በሚጠራው አድራሻው በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክ/ከ
በወረዳ፡----- የቤት ቁጥር፡------------ ስልክ ቁጥር+251942444440 የፖ.ሳ.ቁ፡-------- በሆነው፤

እና

ከዚህ በኋላ ‘‘አከፋፋይ’’ እየተባለ በሚጠራው/አድራሻ፡ ---------------------------------ክልል/ከተማ

----------- ክ/ከ ቀበሌ/ወረዳ፡-…………የቤት ቁጥር……………የስልክ ቁጥር ------------------


የተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር፡--------------------------- የንግድ ምዝገባ ቁጥር ---------------------የግብር
ከፋይ መለያ ቁጥር፡- -------------------------- በሆነው መካከል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ
ከተማ ወረዳ ----- የቤት ቁጥር አዲስ በሆነው አቅራቢ ድርጅት ዋና መስርያ ቤት ውስጥ የተደረገ
የአከፋፋይነት ውል ስምምነት ነው፡፡

አንቀጽ 1
የውሉ ዓላማ

ይህ ውል ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማር በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሐበሻ ሲሚንቶ ምርትን
በማከፋፈልና በማሰራጨት ቀዳሚ ለመሆን ከአምራች ድርጅቱ ጋር ባለው ፅኑ ስምምነት እና ፍላጎት
መሠረት የአምራቹ የንግድ ምልክት እና ስያሜ የሆነውን ‘‘ሐበሻ ሲሚንቶ’’ ክብርና ዝና ጠብቀው በዚህ
ውል መሠረት ምርቱን ለማከፋፈል የሚያስችል አቅምና ብቃት ያላቸውን ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ባለቤት
የሆኑ የሲሚንቶ ምርት የጅምላ ነጋዴዎችን ወክሎ በምርቱ አቅራቢነት ለአከፋፋዮች የማከፋፈል ሥራውን
ማሰራት ስለፈለገ፣ አከፋፋዩም አቅራቢው ያወጣውን የአከፋፋይነት መስፈርቶች በማሟላቱና አምራቹ
የሚያመርተውን እና አቅራቢው የሚያከፋፍለውን ‘‘የሐበሻ ሲሚንቶ’’ ከማምረቻ ቦታ በመግዛት የምርቱን
መልካም ስምና ዝና ጠብቆ ምርቱን በዚህ ውል በተጠቀሱት ሁኔታዎች መሠረት ለአገልግሎት ሰጪ
ድርጅቶችና ለቸርቻሪዎች በሽያጭ የማከፋፈል ሥራ ለመስራት በመስማማቱ ስለውል በተደነገጉት
የኢትዮጵያ ፍትሐብሄር ሕግ ቁጥሮች አንቀፅ 1675፤1679፣ 1731፣ 2005 እና 2266 መሠረት ይህ ውል
በተዋዋይ ወገኖች መካከል ተፈጽሟል፡፡

አንቀጽ 2
ትርጓሜ
2.1. “የስምምነት ውል’’ ማለት ይህንን ስምምነትና የዚህን ስምምነት አባሪዎች፣ ወደፊት በተዋዋዮች
መካከል በጽሁፍ ሊደረጉ የሚችሉ ስምምነቶችንና ግዴታዎች ጨምሮ ተዋዋይ ወገኖች ወደውና ፈቅደው
የሚስማሙትና ግዴታ የሚገቡብት ሰነድ ነው፡፡
2.2. “አምራች’’ ማለት ሐበሻ ስሚንቶን በጥራትና በመጠን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበውን ድርጅት
ማለት ነው፡፡
2.3. “አቅራቢ’’ ማለት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሆነ በመንግሥት ሕግና ደንብ የተቋቋመ
ወይም ፈቃድ ተሰጥቶት ማናቸውም የኮንስትራክሽን ምርት ውጤቶችን ለማከፋፈልና ለማሠራጨት የሕግ
ፈቃድ ያገኘ ሕጋዊ ሰውነት ያለውን ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ ማለት ነው፡፡
2.4. “አከፋፋይ’’ ማለት ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማር ጋር ውል በመፈራረም የሐበሻ
ስሚንቶን በጅምላ በመግዛት በተመደበበት ክልል ወይንም ከተማ ብቻ ምርት የሚያከፋፍለውን
----------------------------------------------------------- ድርጅት ማለት ነው፡፡
2.5. “የጅምላ ነጋዴ’’ ማለት የኮንስትራክሽን ምርት ውጤቶችን የማከፋፈል የጅምላ ሕጋዊ ንግድ
ፈቃድ ያለውና ከሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ የሚቀርቡትን የሐበሻ ስሚንቶ ምርት ተረክቦ
ለቸርቻሪ ነጋዴዎች የሚያከፋፍል ማለት ነው፡፡
2.6. “ቸርቻሪ ነጋዴ’’ ማለት ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ ለጅምላ ነጋዴው የሚሸጥለትን
ምርት ተረክቦ ለሕብረተሰቡ የሚሸጥ ማለት ነው፡፡
2.7. “ተወዳዳሪ ፋብሪካ“ ማለት የአምራች ፋብሪካው የሚያመርተውን የሲሚንቶ ምርት በተመሳሳይ
መልኩ በሌላ የንግድ ስምና የንግድ ምልክት የሚያመርትና የሚያከፋፍል ፋብሪካ ነው፡፡
2.8. “የንግድ ምልክት’’ ማለት ሐበሻ ስሚንቶ የሚለውን የታወቀ አርማ ማለት ነው፡፡
2.9. “ዓርማ ያለው ሲሚንቶ’’ ማለት ሐበሻ ሲሚንቶ አርማ በላዩ የታተመበት ከረጢት ማለት ነው፡፡
2.10. “ምርት’’ ማለት የሐበሻ ስሚንቶ ምርት ማለት ነው፡፡
2.11. “ኮታ’’ ማለት አንድ አከፋፋይ ለተመደበበት ክልል፣ ከተማ ወይም ወረዳ እንዲያከፋፍል በወርና
በዓመት የተመደበለት የምርት መጠን ነው፡፡
2.12. “የገበያ መረጃ’’ ማለት ሐበሻ ስሚንቶ የሚመለከት ወይም በአከፋፋዩ ድርጅት የሚገኝ አጠቃላይ
የገበያና የሽያጭን ሁኔታ የምርት ስትራቴጂ የሚቀይሱበት መረጃ ነው፡፡
2.13. “የሽያጭ መመሪያ’’ ማለት ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ የሽያጭ መመሪያ ማለት
ነው፡፡
2.14. “የሽያጭ ስትራቴጂ’’ ማለት ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ በሚያደርገው ጥናትና
አከፋፋዩ በሚያመጣው መረጃ ተደግፎ የሚቀየስ የሽያጭ ስልት ነው፡፡
2.15. “የሽያጭ ፕሮሞሽን’’ ማለት ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማ እና አከፋፋዩ በጋራ
የሚነድፉት ሽያጭን ለማስፋፋትና ለማዳበር በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የሚያደርጉት ምርት የማስተዋወቅ
ተግባር ነው፡፡
2.16. “ምርት ማስተዋወቅ’’ ማለት አከፋፋዩና አቅራቢው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምርት ለማስተዋወቅ
የሚያደርጉት የፕሮሞሽን/የማስተዋወቅ ሥራ ነው፡፡
2.17. “ተወካይ’’ ማለት በመንግሥት በውክልና ማስረጃ ጽ/ቤት የተፈረመና ሕጋዊ ማስረጃ ያለው
የአከፋፋዩ ብቸኛ ወኪልና በአከፋፋዩ ውክልና የተሰጠው የተፈጥሮ ሰው ነው፡፡
አንቀጽ 3
የአቅራቢው መብትና ግዴታ
3.1. አከፋፋዩ ምርቱን ለማስጫን የሚችልባቸውን ቀናት ፕሮግራም አውጥቶ ያሳውቃል፡፡
3.2. የዋጋ ለውጥ ሲያደርግ አከፋፋዩን በቅድሚያ በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡
3.3. ምርት ለመጫን በማምረቻው ቅጥር ግቢ የገቡ የአከፋፋዩን ተሽከርካሪዎች ከአመራቹ ድርጅት
ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን የጥበቃ አገልግሎት እንዲያኙ ተገቢውን ሁኔታ ያቻቻል፤ ሆኖም
ከመኪናው ላይ ከውሉ ጋር ግንኙነት የሌለው ንብረት ቢጠፋ አምራቹም ሆነ አቀራቢው ተጠያቂነት
የለባቸውም፡፡
3.4. አከፋፋዩ ምርት ለማስተዋወቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አስፈላጊ ሲሆን የባለሙያ ድጋፍ
ይሰጣል፡፡
3.5. የገበያ ማስፋፊያና ማዳበሪያ በአጠቃላይ ለገበያ ፕሮሞሽን ሲል አምራቹ ወይም አቅራቢው
የሚያዘጋጀውን ማንኛውንም ለማስታወቂያ የሚረዱ ማቴሪያሎች እንደአስፈላጊነቱ ለአከፋፋዩ እንዲደርስ
ያደርጋል፡፡
3.6. ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ የስሚንቶ ምርት ከአምራቹ ተረክቦ ያቀርባል ይሸጣል፡፡ በአጠቃላይ
የምርት ጥራት ላይ ከአምራች ድርጅት ጋር በመመካር ተገቢውን ሁሉ ያደርጋል፡፡
3.7. አከፋፋዩ በተመደበበት ክልል የገበያ ጥናት በማድረግ ከአከፋፋዩ ጋር በጋራ የሚከናወኑ የምርት
ማስተዋወቂያ ስትራቴጂዎችን ይቀይሳል፡፡
3.8. አከፋፋይ ሲጠይቅ ወይም አምራቹ/አቅራቢው ራሱ ሲያምንበት ተገቢውን የገበያ፤ የምርትና
የሥርጭት መረጃዎችን ለአከፋፋዩ ይሰጣል፡፡
3.9. የአከፋፋዩ የንግድ አሠራር የተቃና እንዲሆንለትና አከፋፋዩ እንዳይጉላላ እንደአስፈላነቱ አቅሙ
በፈቀደለት መጠን ከአምራቹ እና አቅራቢው ጋር የተዛመዱ የሥራ ግንኙነቶችን በተመለከተ መረጃ
ይሰጣል፡፡
3.10. በአከፋፋዩ ድክመት የተነሳ አከፋፋዩ የተመደበበትን ክልል፣ ከተማ ወይም ወረዳ የሰሚንቶ ምርት
ማድረስ ካልቻለ አቅራቢው ለአከፋፋዩ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አከፋፋዩ በተመደበበት ክልል ገብቶ
መሸጥ ወይም ለሌላ አከፋፋይ ውክልና መስጠት ይችላል፡፡
3.11. አቅራቢው የሚኖረውን የዋጋ ለውጥ እየገመገመ እንደ ሁኔታው የዋጋ ለውጥ የማድረግ ሙሉ
መብት አለው፤
አንቀጽ 4
የአከፋፋዩ መብትና ግዴታ
4.1. በክልሉ ውስጥ ላሉ ደንበኞች የበር ለበር ሰርጭት ያከናውናል፡፡
4.2. የሀገሪቱን የንግድ ስርአት በአግባቡ ጠንቅቀው የሚያውቁ በቂ የሽያጭ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው
የሽያጭ ሰራተኞች ሊኖሩት ይገባል፡፡
4.3. በሚያከፋፍልበት ቦታና ጊዜ የተዛባ እና የአምራቹንና የአቅራቢውን ደርጅት መብትና ጥቅም
ሊጎዳ የሚችል ማናቸውም አይነት አሰራር መፈጸም የለበትም፡፡
4.4. በየጊዜው ከአምራቹ/አቅራቢው የሚወጡትን ማናቸውንም መመሪያዎች ያለቅድመ ሁኔታ
ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
4.5. ምርቱን በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ይረከባል፡፡
4.6. አቅራቢው/አምራቹ እንዲያቀርብ የሚጠይቀውን መረጃ እና ማስረጃ ሁሉ ወዲያውኑ ያቀርባል፡፡
4.7. የአቅራቢውን እና የአምራቹን መልካም ስምና ዝና ይጠብቃል፡፡
4.8. የተመደበለትን የምርት ኮታ ለተመደበበት ክልል ብቻ ያከፋፍላል፡፡
4.9. አከፋፋዩ የግል ብልጽግናን በመሻት ከሚመጣ እና የአምራቹን እና/ወይም የአቅራቢውን ድርጅት
መብትና ጥቅም እንዲሁም መልካም ስምና ዝናውን ከሚያጎድፉ ተግባራትና ከማንኛውም የማጭበርበርና
የማታለል የወንጀል ተግባር መቆጠብ አለበት፡፡
4.10. በአቅራቢው በኩል የቀረበለትን ምርት የማከፋፈሉን ስራ ያለ አቅራቢው ፈቃድ እና ይሁኝታ
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ አይሰጥም፡፡
4.11. አቀራቢው በሚያወጣው ፕሮግራም መሠረት ገበያና ሽያጭን በተመለከተ አከፋፋዩ ስልጠና
ቢያስፈለገው ራሱን ወይም ሕጋዊ ወኪሉን መድቦ በራሱ ወጭ ስልጠናውን ይካፈላል፣
4.12. የምርት ጥራትን በተመለከተ ችግር ሲያጋጥመው ለአቅራቢው ወዲያውኑ በጽሑፍ ያሳውቃል፣
4.13. ቁመቱም ሆነ ስፋቱ ለሲሚንቶ ምርት አያያዝ ተስማሚ የሆነ መጋዘን አዘጋጅቶና አሟልቶ
ይገኛል፣
4.14. አከፋፋይ የምርት ውጤቶችን ለማከፋፈል እና ለማዘዋወር የሚያስችሉ በቁጥር ከ 1/አንድ/ ያላነሱ
ሙሉ የመድን ሽፋን የጭነት ኢንሹራንስ ጭምር የተገባለቸው ተሽከርካሪዎችን የማቅረብ ኃላፊነት
አለበት፤
4.15. በማናቸውም ሁኔታ የተፎካካሪ ድርጅት ምርትን አያከፋፍልም ወይም አያከማችም፤ይህን ፈፅሞ
የተገኘ እንደሆነ ተገቢ ባልሆነ የንግድ ፉክክር እና በአምራች/አቅራቢ ድርጅቱ ላይ ለሚፈጠሪው
ማናቸውም ኪሳራ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
4.16. አቅራቢው የሚያወጣውን የዋጋ ቁጥጥር መመሪያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
4.17. ከአቅራቢው ድርጅት ጋር በመመካከር እና በመስማማት የአምራች ድርጅቱን ብራንዲንግ እና
መልካም ስም/ዝና በጠበቀ መንገድ አስፈላጊውን የምርት ማስታወቂያ የማከናወን መብት አለው፡፡
4.18. አከፋፋዩ የምርቱ ደህንነት የሚጠበቅበትን በቂ ሁኔታ የማመቻችት እና ምርቱን አደጋ ላይ
ከሚጥሉ እንዲሁም ጥራቱን ሊቀንሱ ከሚችሉ ተግባራት ቀድሞ የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡
4.19. አከፋፋይ ምርቱን በሚያሰራጭበት ጊዜ ሁሉ የሀገሪቱን ህግ እና ደንብ እንዲሁም መመሪያዎች
በአግባቡ መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡

አንቀጽ 5
የምርት ርክክብ
5.1. አቅራቢው ከአምራች ድርጅቱ ጋር በመናበብ ምርቱን አከፋፋዩ በሚያቀርበው የጭነት መኪና ላይ
በማስጫን ያስረክባል፡፡
5.2. አከፋፋዩም ምርቱን አቅራቢው ከሚያዘጋጀው ቦታ በመረከብ በራሱ ትራንስፖርት ወጪ ወደ
ሚያከፋፍልበት ቦታ ያጓጉዛል፡፡
5.3. አከፋፋዩ በርክክብ ወቅት ምርቱን በትክክል አይቶና ቆጥሮ በግንባር ወይም በተወካይ አማካኝነት
መረከብ አለበት፡፡
5.4. አከፋፋዩ ምርቱን ለመረከብ የሚልከውን ተወካይ ሙሉ ስምና የተሸከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር በአግባቡ
መዝግቦና ተፈርሞ ይልካል፡፡
5.5. አቅራቢ ድርጅቱ አምራቹ የሚያመርተውን የምርት መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሽያጭ
ፕሮግራም በማውጣት አከፋፋዩን ያስተናግዳል፡፡ ይህም ሲሆን በምርት ሂደት ረገድ የአሠራር ችግር
ሲያጋጥም አቅራቢው ያወጣውን ፕሮግራም እንደሁኔታው ሊያስተካከለው ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ
ሁኔታ ሲያጋጥም አቅራቢው ይህንን በአቅራቢው ወይም በአምራቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው
ማስታወቂያ ሠሌዳ ላይ ማስታወቂያ በመለጠፍ ወይም እንደአስፈላጊነቱ በስልክ በማሳወቅ አስፈላጊውን
ይፈፅማል፡፡
5.6. አምራቹ ወይም አቅራቢው ወይም አከፋፋዩ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር
አከፋፋዩ በየወሩ መረከብ ያለበትን የምርት መጠን በወጣለት የማከፋፈል ፕሮግራም መሠረት በወሩ
ውስጥ አጠናቆ ማንሳት ያለበት ሲሆን በየወሩ መጨረሻም የምርት የቴክኒካል እና የፋይናንሻል ግምገማ
ሪፖርት ያቀርባል፡፡
አንቀጽ 6
ምርቱ የሚከፋፈልበት ቦታና የምርት መጠን /ኮታ/ ድርሻ
6.1. አከፋፋዩ ምርቱን አምራቹ እና አቅራቢው በሚያመቻችለት ቦታ ተረክቦ የሚያከፋፍለው
በ----------------------------------------ክልል/ከተማ ልዩ አካባቢው --------------------------------------
ተብሎ በሚጠራበት አካባቢ ብቻ ሲሆን እንደአስፈላጊነቱ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሰረት ቦታው
ሊቀነስም ሆነ ተጨማሪ የማከፋፈያ ቦታዎች ሊፈቀዱ የሚችሉ ሲሆን ይህ ሲሆን የዚህ ውል መሰረታዊ
ስምምነት አካልን መለወጥ ሳያስፈልገው አቅራቢው ቦታውን በፅሁፍ ብቻ ለአከፋፋዩ በማሳወቅ የዚህ
ውል አባሪ በማድረግ ተፈፃሚ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
6.2. አከፋፋዩ በዚህ ውል እንዲያከፋፍል ከተጠቀሱት ቦታዎች ውጭ በመውጣት ከአቅራቢው ፈቃድ
ውጭ ምርቱን ማከፋፈል አይችልም፡፡ ይህ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ አቅራቢው ወይም አከፋፋዩ
ከተፈቀደለት ቦታ ውጭ ምርቱን ያከፋፈለበት ወኪል ሲያሳውቅ በአከፋፋዩ ቸልተኛ ተግባር አቅራቢው
አሊያም ወኪሉ የደረሰበት ኪሳራ ያለ እንደሆነ በህግ አግባብ የመጠየቅ መብቱ ተጠብቆ አቅራቢው ውሉን
ያለአንዳች ቅድመ ማስጠንቀቂያ የማቋረጥ መብት አለው፡፡
6.3. አቅራቢው ለአከፋፋዩ የሚሰጠውን የምርት መጠን መጨመርም ሆነ መቀነስ ይችላል፣ ይህም
ሲሆን አቅራቢው የሚጨምረውን ወይም የሚቀንስውን የምርት መጠን አሰቀድሞ ከ 15 /አሥራ አምስት/
ቀናት በፊት ለአከፋፋዩ ያስታውቃል፡፡ በማስታወቂያው መሠረት በአከፋፋዩ በኩል ወዲያውኑ ምላሽ
ካልተሰጠ ተጨማሪውን ወይም ተቀናሹን የምርት መጠን አከፋፋዩ እንደተቀበለው ይቆጠራል፡፡
6.4. በዚህ ውል መሠረት በተጠቀሰው የአከፋፋይነት የውክልና ጊዜ ውስጥ በየወሩ 2ooo/ሁለት ሺ/
ኩንታል የመግዛት እና የማከፋፈል ኃላፊነት አለበት፡፡
አንቀጽ 7
የምርት መሸጫ ዋጋና የክፍያ ሁኔታ/አከፋፈሉ/
7.1. አከፋፋዩ ይህንን የውል ሰምምነት ሲፈፅም ጠቅላላ መጠኑ 5200/አምስት ሺ ሁለት መቶ/
ኩንታል ለሆነ ምርት የአንዱ ዋጋ /556.85̇/ ጠቅላላ ድምሩ 2,895,620.00/ ሁለት ሚሊየን ስምንት መቶ
ዘጠና አምስት ሺ ስድስት መቶ ሃያ/ ክፍያ በውል ሰጭ ድርጅት አካውንት ገቢ በማድረግ ገቢ
ያደረገበትን የገቢ ማረጋገጫ ደረሰኝ አያይዞ ሲያቀርብ በዚህ አንቀፅ ላይ የተገለፀውን የምርት መጠን
በየጊዜው ሲረከብ ተቀናናሽ እየተደረገ ምርቱን ይረከባል፡፡
7.2. አከፋፋይ በዚህ ውል አንቀፅ 7.1 በተገለፀው አግባብ የፈፀመውን ክፍያ ያህል ምርት የመረከብ
ያልተገደበ መብት አለው፡፡
7.3. አከፋፋዩ ምርቱን የሚገዛው በወቅታዊ የአቅራቢው የመሸጫ ዋጋ መሠረት ነው፡፡
7.4. በመንግሥት በኩል በኤክሳይዝና በሽያጭ ታክስ ላይ ተጨማሪ የሚደረግ ከሆነ ወይም አምራቹ
የሚጠቀምባቸው ጥሬ እቃዎች ዋጋ ከናረ የመሸጫ ዋጋውም ከዚህ ጋር እየተገናዘበ ይስተካከላል፡፡
7.5. አከፋፋዩ ቅድመ ክፍያ የፈፀመበት 5200/አምስት ሺ ሁለት መቶ/ ኩንታል ምርት ከማለቁ
800/ስምንት መቶ/ ኩንታል ያህል ሲቀረው ወዲያውኑ በተመሳሳይ ሁኔታ የ 5200/አምስት ሺ ሁለት መቶ/
ኩንታል ዋጋ በወቅቱ የክፍያ መጠን በአቅራቢ ድርጅቱ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ገቢ በማድረግ እና
ማረጋገጫ የባንክ የገቢ ደረሰኝ ይዞ በመቅረብ ውሉን ማሻሻል ሳይጠበቅ በደብዳቤ ብቻ የውሉን ቀጣይነት
ይረጋገጣል፡፡
7.6. በዚህ ውል በተገለፀው አግባብ የፈፀመውን ክፍያ በውል ዘመኑ ጊዜ ውስጥ የየአቅራቢ/አምራች
ድርጅቱን መብትና ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ያልፈፀም እና ማናቸውም አይነት ዕዳ የሌለበት
መሆኑን ከሚመለከታቸው የድርጅቱ አካላት ሲረጋገጥ እና ክሊራንስ ሲቀርብ በፋይናንስ መመሪያ
መሰረት ውሉ ሲቋረጥ የሚከፈለው እና ተመላሽ የሚደረግለት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 8
የማከፋፈያ ዋጋ
8.1. አከፋፋዩ ምርቱን የሚያከፋፍለው ጠቅላላ ወጭውን በማገናዘብና በማስላት በአካባቢው ከሚገኙ
ተወዳዳሪ ምርቶች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡
8.2. የአቅራቢው/አምራቹ የምርት የመሸጫ ዋጋ የሚጨምር ወይም የሚቀንስ ከሆነ የአከፋፋዩ የጅምላ
ተመን ዋጋም በተመሣሣይ ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡
8.3. ከምርት ማከፋፈሉ ሥራ ጋር የተዛመዱ ልዩ ልዩ የመንግስት ግብሮችና ታክሶችን አከፋፋዩ
ይችላል፡፡

አንቀጽ 9

የገበያ መረጃ ስለማቅረብና ሽያጭን ስለማዳበር


9.1. አከፋፋዩ በሚያከፋፍልበት ቦታና በአካባቢ ያለውን የታሽገ ውኃ ፍላጎት መጠን፣ እንዲሁም
የታሽገውን ውሃ ጥራት በተመለከተና በአጠቃላይ የገበያውን ሁኔታ እየተከታተለ ለአምራቹ የገበያና
ማስፋፊያ ዋና ክፍል በጽሁፍ በየወሩ መጨረሻ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
9.2. አከፋፋዩ ተገቢውን ስልትና ዘዴ ሁሉ በመጠቀም የምርት ሽያጭን ለማሳደግ አስፈላጊውን ጥረት
ያደርጋል፡፡
9.3. አከፋፋዩ በሚያከፋፍልበት ቦታ በአምራቹ/አቅራቢው የሚተከሉትን የማስታወቂያ ሰሌዳ ወይም
ተመሳሳይ እቃዎች በእንክብካቤ ይይዛል፣ አስፈላጊውን የጥገናና የቦታ ኪራይ ወጪዎች በጋራ
ይሸፍናል፡፡

አንቀጽ 10
የአከፋፋዩ የሁኔታዎች የዋስትና ማረጋገጫ
10.1. አከፋፋዩ በዚህ ውል ስምምነት መሰረት
10.1.1. በሀገሪቱ ህግና ደንብ እንዲሁም መመሪያ መሰረት አስፈላጊውን ህጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ፈጽሞ
በህግ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ያረጋግጣል፤
10.1.2. ከህግ እና ከውል በመነጨ ኃላፊነት ይህንን የውል ስምምነት ለማድረግ የሚያስችለው ያልተገደበ
መብት እንዳለው ያረጋግጣል፤
10.1.3. የድርጅቱን ህጋዊ ወኪል እና ኃላፊ የሆኑትን ግለሰብ ይህንን ውል እንዲፈፅሙ እና ይፈርሙ
ዘንድ ሙሉ ስልጣን የሰጣቸው መሆኑን በዚህ ውል ስምምነት ያረጋግጣል፤
10.2. አከፋፋዩ በዚህ ውል ስምምነት መሰረት ግዴታውን ሲፈጽም
10.2.1. የድርጅቱን መተዳደርያ ደንብ፤ መመስረቻ ፅሁፍ፤የንግድ ፈቃድ እና ሌሎች ውስጣዊ ህጋዊ
ሰነዶችን ሳይጥስ መሆኑን ያረጋግጣል፤
10.2.2. የሀገሪቱን ህግ፤ደንብ እና መመሪያ ሳይጥስ መሆኑን ያረጋግጣል፤
10.2.3. በሌላ ውል ስምምነት ላይ ከአምራች ድርጅት ጋር ተመሳሳይ የንግድ እና ምርት አቅርቦት
ካላቸው የንግድ ተቋማት ጋር ምንም አይነት ተመሳሳይ የውል ግዴታ ያልፈፀመ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
10.2.4. አከፋፋይ የአቅራቢውን ድርጅትን የሽያጭ ታሪክ ሊገዳደር የሚችል እና በጉልህ ጉዳት
ሊያደርስበት የሚችል በፍርድ ቤት፤በግልግል ዳኛ ወይም በሌላ ተቋም ያለ የህግ ክርክር የሌለው መሆኑን
ያረጋግጣል፡፡
10.2.5. አከፋፋዩ ያቀረባቸው አስረጂ ማስረጃዎች በሙሉ እውነተኛ እና ትክክለኛ እንዲሁም ስልጣን
ካለው መንግስታዊ ተቋም የተሰጡ መሆናቸውን ያረጋግጣል፤ስለትክክለኛነታቸውም ኃላፊነትም
ይወስዳል፡፡
አንቀጽ 11
አቅራቢው ለአከፋፋዩ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች
11.1. በምርት ማከፋፈል ረገድ አከፋፋዩ በሚያከፋፍልበት ቦታ የተዛባ አሠራር መፈጸሙ በማስረጃ
ከተረጋገጠ፣
11.2. አከፋፋዩ በአቅራቢው/በአምራቹ ሠራተኞች ላይ የሥነ ምግባር ጉድለት ፈጽሞ ከተገኘ፣
11.3. አከፋፋዩ የንግድ ፍቃዱን በየዓመቱ መታደስ በሚገባው ጊዜ በማሣደስ ኮፒውን ከእድሳት በኋላ
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለአምራቹ ካላቀረበ፣
11.4. አከፋፋዩ ውሉን አስመልክቶ በየጊዜው በአቅራቢው በኩል የሚወጡትን መመሪያዎች ተግባራዊ
ካላደረገ፣
11.5. ድርጅቱ በሚፈልገው የኮታ መጠን ምርቱ እየተሰራጨ ካልሆነ፡፡
አንቀጽ 11
የማከፋፈል ውክልናውን/ውሉን/ በቀጥታ ለመሠረዝ የሚያስችሉ ሁኔታዎች
11.1. በወንጀል ተጠያቂነቱ እንደተጠበቀ ሀኖ አከፋፋዩ የአምራቹን ሠራተኞች በጥቅም የደለለ ወይም
ያለአግባብ ጥቅም ለማግኘት ተመሳሳይ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
11.2. ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሐሰተኛ ሰነድ ወይም የሰው ማስረጃ ማቅረብ የማጭበርበር ተግባር
ከፈጸመ፣
11.3. ተገቢውን እንክብካቤ ባለማድረግ በምርት ላይ የጥራት ጉድለት ያደረሰ መሆኑ በማስረጃ
ሲረጋገጥ፣
11.4. በማናቸውም መንገድ ቢሆን የአምራቹን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
11.5. በዚህ ውል ስምምነት ከተደረሰበት ቦታ ውጭ ምርቱን ወስዶ ሲያከፋፍል ወይም ሲያከማች
ከተገኘ፣
11.6. የተሰጠው የንግድ ፈቃድ ከተሰረዘ፣ ወይም በዘመኑ ካልታደሰ፣
11.7. በዚህ ውል ከተዘረዘሩት ጥፋቶች ውስጥ አንዳቸውንም ቢሆን ፈጽሞ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው
በኋላ በአንድ የውክልና ዘመን ውስጥ ለሁለተኛ ወይም እንደድርጊቱ ይዘት እና ግዝፈት መሰረት
ለሦስተኛ ጊዜ ሲፈጽም ከተገኘ፣
11.8. አከፋፋዩ ከአቅራቢው የተረከበውን ምርት ወደ ሚያከፋፍልበት ክልል ያለመድረሱ እና
ያለማከፋፈሉ በማስረጃ ሲረጋገጥ፣
11.9. አከፋፋዩ በተራ ቼክ መሰረታውያን ነጥቦች ላይ ያጭበረበረ ወይም በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ቼክ
አዘጋጅቶ የሰጠ እንደሆነ፣
11.10. በአቅራቢው የቀረበወን ምርት የማከፋፈሉን ሥራ ያለአቅራቢው ፈቃድ እና ይሁኝታ በቀጥታም
ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ ከሰጠ፡፡
11.11. አምራቹ/አቅራቢው በውሉ ዘመን ውስጥ የምርቱ ሥራ ሂደት ሊስተካከል የማይችል ችግር
ሲያጋጥመውና ምርቱ ሲቀንስ፣
11.12. አከፋፋዩ ውሉን ማቋረጥ የፈለገ እንደሆነ ከ 30/ሰላሳ/ የስራ ቀናት አስቀድሞ ለአምራቹ በጽሁፍ
በተዘጋጀ ማስጠንቀቂያ በማሳወቅ ማቋረጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 12
ተፈጻሚነት የሌላቸው ድንጋጌዎች

በዚህ ውል መሠረት በአቅራቢውና በአከፋፋዩ መካከል የተመሠረተው ግንኙነት ምርትን በጅምላ


መሽጥና መግዛት ላይ ከሚያተኩር በስተቀር በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2179-2285 ስለውክልና የተደነገጉት
ድንጋጌዎች በዚህ ውል ላይ ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡

አንቀጽ 13
የቅሬታ አቀራረብ
13.1. ይህ ውል ፀንቶ በሚቆይበት ወቅት በውሉ አፈጻጸም ላይ አከፋፋዩ ቅሬታ ቢያጋጥመው
ለአቅራቢው የሽያጭ ዋና ክፍል ኃላፊ በጽሁፍ ያሳውቃል፤
13.2. የሽያጭ ዋና ክፍል ኃላፊ በአከፋፋዩ በኩል የቀረበለትን ቅሬታ መርምሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ
ውስጥ ውሣኔ ይሰጣል፣ አከፋፋዩ በተሰጠው ውሣኔ ላይ ቅር የተሰኘ ከሆነ ጉዳዩን በይግባኝ ለአቅራቢ
ድርጅተ ሥራ አስኪያጅ ያቀርባል፣
13.3. በአቅራቢ ድርጅት ሥራ አስኪያጁ ውሣኔ ቅር የተሰኘ ከሆነ ይግባኙን ለኩባንያው ዋና ሥራ
አስኪያጅ/CEO/ ማቅረብ ይችላል፡፡
አንቀጽ 14

ከአቅም በላይ ችግር

በፍትሃ ብሔር ህጉ ላይ የተገለፁት ከአቅም በላይ ምክንያቶች ለዚህ ውል አፈፃፀምም በተመሳሳይ


ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

አንቀጽ 15

የውል ስምምነትን ስለማፍረስ እና ስለመቀጮ

15.1 በዚህ የውል ስምምነት መሰረት ተዋዋይ ወገኖች ውላቸውን በስምምነት ማፍረስ እና ቀሪ ማድረግ
ይችላሉ፡፡
15.2 ከተዋዋይ ወገኖች መካከል የአንዱ መሞት ወይም መክሰር ለውሉ መፍረስ በቂ ምክንያት ነው፡፡
15.3 ሆኖም ግን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ ከተገለጹት ምክንያቶች ውጭ በሆነ ምክንያት እና
በተለይም በዚህ ውል አንቀፅ 11 ላይ ከተገለጹት ምክንያቶች መካከል አከፋፋይ ወገን ለውሉ መፍረስ
ምክንያት የሆነ እንደሆነ አምራች ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልገው ውሉን የማቋረጥ እና ለደረሰበት
ኪሳራ መጠን ልክ ካሳ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል፡፡

አንቀጽ 16

አለመግባባትን ስለመፍታት
16.1. ከተዋዋይ ወገኖች መካከል አንዱ በዚህ የውል ስምምነት ላይ በገቡት ግዴታ መሰረት ግዴታውን
ያልተወጣ እንደሆነ፤አሊያም የውሉን አፈፃፀም ያዘገዬ እንደሆነ፤
16.2. በውሉ ላይ የተጠቀሰውን መጠን አይነት እንዲሁም ጥራት ተከትሎ ያልተፈጸመ እንደሆነ በውሉ
አለመፈፀም ቅሬታ ያደረበት ወገን ጉዳዩን እንደውሉ ላልፈፀመው ወገን ጉዳዩን ባወቀው 5/አምስት/ ቀናት
ጊዜ ውስጥ በማሳወቅ ያለመግባባቱን ቀድሞ በውይይት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፡፡
16.3. በውይይት ለመፍታት ካልተቻለ እንደአስፈላጊነቱ በ 30/ሰላሳ/ ቀናት ጊዜ ውስጥ በአስታራቂ
ሽማግሌዎች/Mediation/ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ጥረት ይደረጋል፡፡
16.4. ሆኖም ግን ያለመግባባቱ በውይይትም ሆነ በሽማግልና ሊፈታ ያልቻለ እንደሆነ ቅሬታ ያለው ወገን
ጉዳዩን ስልጣን ላለው የፌዴራል ፍርድ ቤት በማቅረብ በፍርድ ያለመግባባቱ እልባት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

አንቀጽ 17
የውል አፈራረም

ይህንን የሲሚንቶ ምርት የማከፋፈል ውል አከፋፋዩ በግንባር ቀርቦ ወይም ህጋዊ ወኪሉን በመላክ
መፈረም አለበት፡፡

አንቀጽ 18
ውሉ የሚጸናበት ጊዜ
18.1. ይህ ውል ከተፈረመበት ከዛሬ ቀን ------------------------ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ------------ዓ.ም
ድረስ ለ------------------------ የሙከራ ጊዜ የጸና ይሆናል፡
18.2. በሙከራ ጊዜ ውል ውስጥ የአከፋፋዩ የሥራ አፈፃፀም አመርቂ ሆኖ ከተገኘ የሙከራ ጊዜውን
ጨምሮ ይህ ውል ለ 12/አስራ ሁለት/ ወራት የፀና ይሆናል፡፡
18.3. የውል ጊዜው ከመጠናቀቁ 30/ሰላሳ/ ቀናት በፊት አከፋፋዩ ውሉን ማራዘም የፈለገ እንደሆነ
ለአቅራቢው ቀድሞ ማሳወቅ አለበት፡፡ አቅራቢው በውል ማራዘሚያው የተስማማ እንደሆነ የዚህ
የውል ጊዜ ከማለቁ 10/አስር/ ቀናት በፊት የውል ማደሻ እና ማራዘሚያ በፅሁፍ ሊደረግ
ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ውሉ እንደተቋረጠ ይቆጠራል፡፡
18.4. ይህ ውል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1675፤1679፤1731 እና 2005 መሠረት በህግ ፊት የፀና
ነው፡፡
ስለአቅራቢው ስለአከፋፋይ
ስም፡------------------------------------- ስም፡-------------------------------------
ኃላፊነት፡------------------------------------- ኃላፊነት፡---------------------------------
ፊርማ፡------------------------------------- ፊርማ፡----------------------------------
ቀን፡------------------------------------- ቀን፡-------------------------------------

እኛም ስማችን ከዚህ በታች የተገለፅን እማኞች ተዋዋይ ወገኖች ይህንን የውል ስምምነት ፈቅደውና
ወደው ሲዋዋሉ አይተናል ሰምተናል ስንል በፊርማችን እናረጋግጣለን፡፡

እማኞች
1. ስም፡-------------------- አድራሻ፡- አ/አ ----------ክ/ከ ወረዳ፡------ የቤ/ቁ፡----ፊርማ፡-------------
2. ስም፡---------------------------- አድራሻ፡- አ/አ ----------ክ/ከ ወረዳ፡------ የቤ/ቁ፡----ፊርማ፡-----
3. ስም፡------------------------- አድራሻ፡- አ/አ ----------ክ/ከ ወረዳ፡------ የቤ/ቁ፡----ፊርማ፡--------
4. ስም፡---------------------- አድራሻ፡- አ/አ ----------ክ/ከ ወረዳ፡------ የቤ/ቁ፡----ፊርማ፡-------------

You might also like