You are on page 1of 20

 ስለ ኤቲስቶች እና ሳይንስ

 ለሀልዎተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔርን መኖር የሚያስረዱ) ማስረጃዎች

 በሀልዎተ እግዚአብሔር ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች

 የክፉ ነገር ምንነትና ጥቅም

 ክፋት (ኃጢአት) በእግዚአብሔር ተፈጥሯልን?

 ክፉ ነገር ለምን አይጠፋም?

 እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ገሃነመ እሳት ይልካልን?

 ክፋት ከሚኖር እግዚአብሔር ዓለምን ባይፈጥርስ?

 እግዚአብሔር ወደ ገሃነመ እሳት የሚገቡ ሰዎችን አስቀድሞ ካወቀ


ባይፈጥራቸውስ?

 ሰይጣን ብዙዎችን የሚያስት ስለሆነ ለምን አይጠፋም?


ስለ ኤቲስቶች እና ሳይንስ
Atheism የሚለው ቃል 'a- አሉታዊነትን የሚገልጽ' እና 'theos-አምላክ' ከሚሉ ቃላቶች የመጣ ሲሆን "አማልክት
የሉም" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል። ለዚህ ዓለም ሠራዔ መጋቤ የለውም ብሎ የሚያምን ነው። ይህም አማልክት የሉም
ብለው የሚያምኑ ወገኖች ደግሞ "Atheist" ይባላሉ። Atheistኦች እግዚአብሔር ለመኖሩ ማስረጃ የለም የሚሉና ያለው
ማስረጃ እግዚአብሔር መኖሩን ይቃረናል በማለት አስተሳሰባቸውን ይገልጻሉ። በ5ኛው መቶ ዓመት ቅ.ል.ክ በግሪክኛ
የተጀመረ ሲሆን እግዚአብሔር (አማልክት) የለም የሚል አስተሳሰብ ነው። ይህ እግዚአብሔር የለሽነት እምነት በተለያየ
ዘመንና ቦታ ግለሰባዊ አቋም ሆኖ የኖረና እየኖረ ያለ ቢሆንም በስፋት የተሰራጨውና በተቋማዊ አደረጃጀት መልኩን ቀይሮ
የሃይማኖት ጠላት ሆኖ የተነሳው በምዕራቡ ዓለም ከ 17ኛው ክ/ዘመን ወዲህ ነው። በተለይ ከ 18ኛው ክ/ዘመን -20ኛው
ክ/ዘመን ድረስ እግዚአብሔር የለሽነት እንደ ዘመናዊነትና የአዋቂነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድባቸው ዘመናት ነበሩ።
Atheism የሚለው ቃል ለመጀመርያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ 16ኛው ክ/ዘመን ሲሆን ቃሉ የተስፋፋውም ነጻ ሃሳብና
ሃይማኖትን መተቸት እጅጉን በሰፈነበት በ 18ኛው የመገለጥ (Enlightment) ዘመን ነበር። በ 19ኛውና በ20ኛው
ክ/ዘመን በፈጣሪ አለማመን የአዋቂነትኔ የስልጡንነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድባቸው ዘመናት ነበሩ። [WIKIPIDEA]

ኤቲስቶች በመሠረታዊነት የማያውቁትን ሁሉ ይክዳሉ። ስለ እግዚአብሔር እርግጥ የሆነ ዕውቀት ስለሌላቸው ሌላውም
አይኖረውም ብለው ያስባሉ። ይህም ድምዳሜያቸው ዕውቀት በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ የሚል ትምህርታቸው ነው። ሳይንስ
ስለማንኛውም ነገር ዕውቀት ለማግኘቴ የሚችለው የስሜት ሕዋሳት በሚያቀርቡለት መረጃ [Emperical Evidence] ላይ
ተደግፎ በንጻሬ አስተውሎታዊ ምልከታ (Reflective observation)ና በትንተናዊ ገለጻ (Analytic description)
ተመርቶ ነው። መሠረታዊ የሕልውና ጥያቄዎች ግን ትክክለኛ መልሳቸው በስሜት ሕዋሳት ብቻ ተመርተ ን የምንደርስባቸውና
የምንጨብጣቸው አይደሉም። ሳይንስ ሰው መሆኔን ተቀብሎ ለመኖር የሚያስችሉኝን ነገሮች በማመቻቸት ኑሮዬን የተሟላ
ያደርገዋል እንጂ ሰው ሆኜ የተፈጠርኩበትን ወይም የተገኘሁበትን ምክንያት ወይም የመኖሬን ትርጉም አይነግረኝም። ሌላው
ቢኖር ሳይንሳዊ ዕውቀት መልካም ሰውነት ወይም ስነ ምግባራዊ ማንነት አይፈጥርም። ምንም ያህል የሳይንሳዊ ዕውቀታችን
ቢሰፋና የቴክኖሎጂ ምጥቀታችን ቢንሰራፋ በስሜት ሕዋሳታችን ላይ ተደግፈን የምናገኘው ዕውቀት የስነ-ምግባር ችግራችንን
የመንፈስ ጉድለታችንን አይሞላውም። ሳይንሳዊ ዕውቀት ኃጢአትን አያፀዳም። ርኩሰትንም አያስወግድም። ሳይንስ ንፁህ
አነዋወርን የቅድስና ሕይወትን መፍጠር አይችልም። ሳይንስ በውሱን የስሜት ሕዋሳቶቻችን ልናውቅ የምንችላቸውን
ለማጥናት ይረዳል። ነገር ግን እጅግ የረቀቀውንና ከስሜት ሐዋሳቶቻችን ውጪ ያለውን ሁለንተናዊ እውነታ ለመረዳት ግን
አይጠቅመንም።

አብዛኞቹ የሳይንስ ባለሙያዎች የሳይንስ ስኬት የነገረ መለኮት ድክመት የሚያሳይ ይመስል የሒሳብና የፊዚክስ ውጤቶችን
በማሳየት የሃይማኖትንና የነገረ መለኮትን አለመታመን ሊነግሩን ይሞክራሉ። ስለ ዕቃው ጥራት ስንጠይቅ ብዛቱን እያሳየ
እንደሚያታልል ነጋዴ የሕይወትን ምንነትና የመኖርን ትርጉም ስንጠይቅ ያስገኘውን የቴክኖሎጂ ውጤትና የቁሳዊ ንብረት
ብዛት እያመለከተን በሕልውናችን ላይ የሚያተኩሩ መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንዳናስተውል ሊጋርደን ይሞክራል።

😁 ቀልድ:- "የታወቀ የሳይንስ ሊቅ ከሞት በኋላ ነፍሱ በእግዚአብሔር ፊት ቀረበች። ሊቁም በእውቀቱ ተመክቶ በትዕቢት
ቃል "እኛ የሳይንስ ሰዎች ፈጣሪ እንደማያስፈልገን ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። ያንተን ምስጢር ዕውቀት ሁሉ ተረድተናል።
የአንዱን ልብ አውጥተን ወደ ሌላው መትከል እንችላለን።... በአጠቃላይ በአንድ ወቅት ተአምር ተብሎ የተቆጠረውን ጥበብና
ሁሉን ቻይነትህን ይገልጻል የተባለውን ሁሉ መስራት ችለናል በማለት ተናገረ። እግዚአብሔርም "የሰው ልጅ ይፈልገኛል
ወይስ አላስፈልገውም የሚለውን እናይ ዘንድ በመፍጠር ላይ ትንሽ ውድድር ለምን አናደርግም።" በማለት ጠየቀው። ሊቁም
ተስማምቶ "ምን ላድርግ" ሲል "ወደ መጀመርያው ፍጥረት ተመልሰን አዳምን እንፍጠር" አለው። ያም ሊቅ "ከምድር ላይ
አፈርን ሊያሳ ዝቅ ሲል እግዚአብሔርም "የራስህን አፈር ተጠቀም እርሱ የኔ ነው" በማለት መለሰለት።" ከዚህም ቀልድ
የቱንም ያህል ሳይንስ ቢራቀቅ እጅግ ውሱን መሆኑን ያሳየናል።

ኤቲስቶችን በጠቅላላው በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን።

1. ፍጹም አምላክ የለሽ (Absolute Atheists)

እኚህ ሀልወተ እግዚአብሔርን (የእግዚአብሔርን መኖር) ጨርሰው የሚክዱ የሃይማኖት ተቃዋሚ ሆነው የሚመላሱ ናቸው።

2. በግብራቸው አምላክ የለሽ የሆኑ (Practical Atheists)

እኚህ ደግሞ እግዚአብሔርን አለ ብለው ቢያምኑም ቢቀበሉም በዕለት ተዕለት አኗኗራቸው ከእግዚአብሔር ጋር አይገናኙም
መንገዱንም አይፈልጉም። የእግዚአብሔርን መኖር ባይክዱም በግብራቸው (በስራቸው) በአኗኗራቸው ከእግዚአብሔር የተለዩ
ርሱንም የተዉ ናቸው። ልክ እግዚአብሔር እንደሌለ ያህል ሆነው ይኖራሉ። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጸው "እግዚአብሔርን
እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ። ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ስራም የማይበቁ ስለሆኑ በሥራቸው ይክዱታል።"
ቲቶ. 1:16 ብሏል፡፡

ብጹዕ አብነ ሺኖዳም ወደ ኤቲይዝም በገቡበት መንገድና በአይነታቸው ይከፍሏቸዋል።

በኮሙኒስት ሐገራት የነበረው Atheism መነሻ በተሳሳተ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ምክንያት የመጣ ነው። በመንግስት በኩል
ባለው ግፊትና በሕዝቡም ዘንድ ባለው ፍርሃት ነው። የፖለቲካዊው ግፊት ከራቀ የሕዝቡም ፍርሃት ከተወገደ በኋላ በራሺያ
በፖላንድ ሮማንያ በመሳሰሉ ሀገራት ክርስትናን ዳግም አጽንተዋል።

ሌላው Atheism ደግሞ ማርኪሲዝም(Marxcism) ነው። ይህም ኤቲይዝም እግዚአብሔርን መቃወም እንጂ ሕልውና
መካድ አይደለምተ በኢኮኖሚያዊ ችግሮችና በድህነት ም/ት የሚሰቃዩና በቅንጦት ከሚኖሩ ሰዎች አንፃር ሲመለከቱ
እግዚአብሔር በሰገነት ላይ የሚኖር ለድሆችና ለሚለፉት የማያስብ አድርገው ያስተምራሉ። ሃይማኖትንም ለሕብረተሰቡ
አደንዛዥ ዕፅ ነው እስከ ማለት ደርሰው ተናግረዋል። በዚህም ሃይማኖት ሰዎች በሕይወት ውስጥ ያለን ችግሮች ምስቅልቅሎች
እንዳይሰማቸው የሚያደርግ አደንዛዥ ዕፅ ነው ይላሉ።ሰው ያለ ሃይማኖት ሊኖር አይችልም። ሰው እንስሳዊ ብቻ ስላይደለ
ማንነቱንና የመኖሩን ትርጉም ለማግኘት ይሄዳል። እግዚአብሔርንም ሲክድ ሃሳባዊ አምላክ በአዕምሮው ያኖራል። "ለአንተ
የሰራሃቸው አማልክትህ ውዴት ናቸው?" ኤር. 2:28::

Existentialist የሚባሉት ደግሞ በእግዚአብሔር በተከለከለው የኃጢአት ምኞታቸው መዋኘተ የሚፈልጉ ናቸው።
እንደውም "እኛ እንድንኖር እግዚአብሔር ባይኖር ይሻላል።" እስከማለት የደረሱ ናቸው። የሥጋ ፈቃዳችንን እየፈፀምን
የምንኖርበት የምንኖርበት ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሔር አለመኖር ነው ይላሉ። "አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር"
የሚለውን የጌታን ጸሎት ይዘውም "በሰማይ ቆይ ምድርንም ለኛ ተዋት" በማለት ይናገራሉ። "ክፉን የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን
ይጠላልና። ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም።" ዮሐ. 3:20 እንዲል።

ኤቲስቶች እግዚአብሔር ስለ መኖሩ ማስረጃ የለም በማለት ሲናገሩ በነርሱ ዘንድ ማስረጃው መዳሰስና መታየት
(Emperical Evidence) ሊኖርበት ያስፈልጋል። በጊዜና በቦታ የማይወሰን አምላክን ለሚያምን ክርስቲያን ደግሞ እንዲህ
ያለ ማስረጃን ሊያቀርብ አይቻልም። ለማረጋገጥ መሞከርም በቦታ የማይወሰነውን አምላክ በቦታ መወሰን ይሆንብናል።
ፈጣሪን ከመፈለግ ይልቅ እኛው ራሳችን ፈጣሪዎች ሆነን እንገኛለን።

ሳይንስ ወደ እውነት ለመድረስ አንዱ መንገድ ነው። እኚህ ኢ-አማንያን ሳይንስን ከእውነት ጋር ሊያስተካክሉት የዕወቀቶች
ሁሉ ጥግ አድርገው ሲያቀርቡ እንመለከታለን። ይህንም የተሳሳተ እሳቤ ይዘው ሳይንስ የእግዚአብሔርን አለመኖር አረጋገጠ
በማለት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። እኛ ግን ሐልዎተ እግዚአብሔርን በ Laboratory ለማረጋገጥ አንሞክርም።
ሳይንሳዊ መንገድ ወደ እውነት ሊያደርሱን ከሚችሉ መንገዶች አንዱ መሆኑን እንጂ ብቸኛው አለመሆኑን መረዳት
ያስፈልጋል። የሳይንስ በ Matter and Energy (በቁስ አካልና ጉልበት) መልኩ የተገለጡትን የሚያጠና ነው። ከዚህ ውጪ
ያሉትን ግን ለማጥናት አይቻለውም።

 ለምሳሌ:- ፍቅርን ልንክደው የማንችል በሕይወታችን ውስጥ ያለ እውነታ ነው። ቤተሰቦቻችንን እንወዳለን።
በተቃራኒ ጾታ መካከል ያለም መዋደድ ፍቅር አለ። ፍቅር ቁስ አካልም ጉልበትም ስላልሆነ በሳይንሳዊ መንገድ
ሊመረመር አይችልም። የፍቅር ርዝመት ክብደት ብለን ልንለካም አንችልም። ከዚህ በተጨማሪ ርሕራሔ ፍትሕ
የመሳሰሉትንም በሳይንስ አይመረመሩም። እግዚአብሔርም ደግሞ ቁስ አካል ወይም ጉልበት አይደለም። ስለዚህም
በሙከራ ሳይንስ ልናረጋግጠው አንችልም።
 ታሪክን በሳይንሳዊ መንገድ ልናረጋግጠው አንችልም። በሳይንሳዊ መንገድ ተጠቅመን የንጉስ ቴዎድሮስን በንግስና
መምራቱን የአደዋ ጦርነት መካሄዱን ማረጋገጥ አንችልም። ምክንያቱም ታሪክ በባሕሪይው የሚደገም አይደለምና።
እኚህን ግን በሳይንስ ስለማይረጋገጡ መከሰታቸውን ማንም ሊክድ አይችልም።
 ነፍስ አትታይም ነገር ግን በስጋ አድራ አካልን ስታንቀሳቅስ ስራ ስታሰራ ትታያለች። ስላላየናት ግን የለችም
አያሰኝም። የመሬት ስበት አለ የመሬት ስበትን በአይን ባናየውም ዕቃ ሲወድቅ በስራው እናስተውላለን። አዕምሮ
(mind) አለ ብለን እንናገራለን። አዕምሮን ግን አናየውም አንዳስሰውም። የማናየው ስለሆነ አዕምሮ የለም ወደ
ሚል ድምዳሜ አንሄድም።

ሳይንስ የተለያዩ መሳርያዎችን ወደ እውነት ለመድረስ እንደሚጠቀም [በኬሚስትሪው Test tubeን በአስትሮኖሚው ዘርፍ
Telescopeን ለባዮሎጂ Microscopeን ይጠቀማል።) በሃይማኖት የሚኖርም ሰው የእግዚአብሔርን መኖር ለማወቅ
የሚጠቀመው መንፈሳዊ መሳርያዎች አሉ። እኚህም በቃለ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት በንስሐ በልብ ንጽህና ናቸው።

Blaise Pascal የተባለ ፈረንሳዊ የሂሳብ ሊቅና ሳይንቲስት የእግዚአብሔርን መኖር መቀበል አትራፊ እንጂ የሚያከስር
እንዳልሆነ በ ውርርድ (wager) በምሳሌ አስረድቷል። አንድ ጤናማና ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሁለት አማራጮች ቢሰጡት
ሽልማትን ለማግኘት የተሻለ ዕድል ያለውን አማራጭ ይመርጣል። ለምሳሌ:- አንድ ሰው ቤትህ በእሳት እየነደደ ነው ብሎ
ቢነግርህ ሁለት አማራጮች አሉህ። ወይ እውነቱን ነው ወይም ሐሰት ሊሆን ይችላል። ተቃጥሎ ይሆን? ብሎ ለማረጋገጥ
ቤቱን ለማየት መሄድ ሐሰቱን ነው ብሎ ካለመጨነቅና በኋላ እውነቱን ሆኖ ንብረቱ ወድሞ ከምናገኘው ኪሳራ አንጻር የተሻለ
ምርጫ ነው።

በዚህም መሰረት እግዚአብሔር አለ ወይንም የለም ብለን አማራጮችን ይዘን ብንነሳ:-

 እግዚአብሔር አምነንና ታምነን ኖረን እግዚአብሔር ቢኖር በመንግስተ ሰማያት ሽልማትን እናገኛለን።
 በእግዚአብሔር አምነን ኖረን እግዚአብሔር ባይኖር የምናጣው የለም። በምድርም ያጣነውም ቢኖር በኃጢአት
እንደፈቃዳችን መኖርን ነው።
 በእግዚአብሔር ሳናምን ኖረን እግዚአብሔር ቢኖር ዘላለማዊ ሞት ይጠብቀናል።
 በእግዚአብሔር ሳናምን ኖረን እግዚአብሔር ባይኖር በኃጢአታችን ምክንያት ፍርድ አይኖርብንም።

ስለዚህ እግዚአብሔር አለ ብለን ተወራርደን ከዚያም ልክ ብንሆን አሸናፊዎች እንሆናለን። እግዚአብሔር አለ ብለን
ተወራርደን ከዚያም እግዚአብሔር ባይኖር ያጣነው አንዳች ነገር አይኖርም። ነገር ግን እግዚአብሔር የለም ብለን ብንወራረድና
ከዚያም ልክ ብንሆን አሸናፊ አንሆንም [በዚህ የሚገኝ ሽልማት የለምና] እግዚአብሔር የለም ብለን ተወራርደን ከዚያም ልክ
ባንሆን ሁሉን እናጣለን። ታዲያ ሁሉን ለማጣት ወይም ምንም ላለማሸነፍ የሚወራረድ ምክንያታዊ ቆማሪ ይኖራልን?
በማለት ይጠይቃል። በዚህ የውርርድ (Betting) ምሳሌ መሰረት በእግዚአብሔር መኖር የሚወራረደው ሰው ምክንያታዊ
የሆነና ሁሉን የሚያተርፍበት ምንም የማያጣበት ነው።

ለሀልዎተ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ማስረጃዎች


አብርሃም ፈጣሪውን ለማግኘት ባደረገው ጉዞ ፍጥረታትን ይመለከት፥ ይመረምር ጀመር። ተራራውን ከፍ ብሎ ቢያየው፦
«አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ይህንንም፦ አንዱ ተራራ ሌላውን ሲበልጥ አይቶ፦ «በፈጣሪ መብለጥ መበላለጥ የለበትም፥
ስለዚህ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሁለተኛም ነፋስ፦ ባሕር ሲገሥጽ፥ ዛፍ ሲያናውጥ አይቶ፥ «አምላክስ ይህ ነው፤»
አለ። ነፋስንም፦ ተራራ ሲገታው፥ መዝጊያ ሲመልሰው አይቶ፦ «ፈጣሪንስ የሚገታው የለም፥ ይህም አምላክ አይደለም፤»
አለ። ሦስተኛም፦ የባሕሩን ማዕበልና ሞገድ አይቶ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ባሕርም ሲሞላና ሲጐድል አይቶ፦
«በፈጣሪስ ሕፀፅ (ጉድለት) የለበትም ፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አራተኛም፦ እሳት፦ ደረቁን ከርጥቡ ለይቶ ሲበላ፥
ቋያውን ሲያቃጥል አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። እርሱንም ውኃ ሲያጠፋው፥ መንገድ ሲከለክለው አይቶ፦ «ይህም
አምላክ አይደለም፤» አለ። አምስተኛም፦ ፀሐይ በዓለሙ መልቶ ሲያበራ አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» ብሏል። እርሱም፦
በምሥራቅ ወጥቶ በምዕራብ ሲገባ አይቶ «በፈጣሪስ መውጣት መግባት የለበትም፥ ቀን ቢመግበን ማታ ማን ይመግበናል?
ለዚህም ፈጣሪ አለው፤» አለ። ከዚህ በኋላ፦ «አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ፤ የፀሐይ አምላክ አነጋግረኝ፤» ብሎ ጮኸ።
እግዚአብሔርም ድምፁን አሰምቶታል። እኛም እንደ አብርሃም ባለ ሕሊና ብንመረምር ወደ እውነት እንደርሳለን።

የእግዚአብሔርን መኖርና መረዳት በነዚህ በ4ቱ መረዳትና ማስተዋል እንችላለን።

1ኛ. የቅዱሳት መጻህፍት ምስክርነት [መዝ. 14:1፣ ሮሜ. 1:20]

2ኛ. ቅዱስ ትውፊት

3ኛ. የግል ሕይወት ተሞክሮ (በሕይወታችን ውስጥ የሚሰራው ድንቅ ስራ)

4ኛ. በአመክንዮ [Reasoning)

በቅዱሳት መጻሕፍና በቅዱስ ትውፊት የእግዚአብሔርን መኖር ብቻ ሳይሆን ፈቃዱም የተገለጡባቸው ናቸው። ዘላለማዊ
ሕይወትን ለማግኘት ልንከተል የሚገባውን መንገድ ያስታውቁናል። በግል ሕይወት ተሞክሮአችን ከሁሉ በላይ
የእግዚአብሔርን መኖር በሕይወታችን ያደረገውን ድንቅ ነገር ተመልክተን ለሰዎችም በእግዚአብሔር የተደረገውን ሰምተን
የምናውቅበት ነው። በቀጣይ ማስረጃዎች የምናቀርበው በአመክኖዮአዊ (Reasoning) መንገድ ነው። በዚህም ስር አራት
ማስረጃ መንገዶች አሉ።

1ኛ. Cosmological Argument (የስነ ፍጥረት ማስረጃ)


ይህ ሙግት መሰረት የሚያደርገው የምክንያትና የውጤት ሕግ (The law of Cause and Effect) ላይ ነው። በዚህም
ሕግ መሰረት አንድ ውጤት በቂ የሆነ ምክንያት ሊኖረው ይገባል የሚል ነው። (Every effect should have sufficient
cause which is quantitatively and qualitatively superior to it)

ቁሳዊ የሆነ ውጤት [Effect] በቂ ምክንያት[Cause] ሊኖረው ይገባል ያለ በቂ ምክንያትም የሚገኝ ውጤት የለም።
ዳግመኛም ከውጤቱ ተከትሎ የሚመጣ ምክንያት የለም ምክንያትንም የሚቀድም ውጤት ውጤትንም የሚከተል ምክንያት
የለም ይላል። ይህ ሕግ በሳይንሱም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ተቀባይነት ያለው ነው። ከውጤቱ የሚበልጥ በቂ የሆነ ምክንያት
ስንልም ብቁ ካልሆኑ ምክንያቶች ስንለይ ነው። ለምሳሌ፦ አንዲት ዝንብ ጠረጴዛ ላይ ባለ መጽሐፍ ላይ አርፋ መጽሐፉን
ጣለችው ማለት ልክ አይሆንም ዝንቧ መጽሐፉን ለመጣል በቂ ምክንያት አይደለችምና። ዳግመኛም አንዲት እንቁራሪት
ወንዝ ውስጥ ገብታ ውሃውን አደፈረሰችው ማለትም በቂ ምክንያት አይደለም ምክንያትም ከውጤት አልበለጠም።

በዚህም መሰረት የዓለም [Universe] መኖር ከራሷ በላይ በሆነ ኃይል ስለተገኘች ነው ይህም በእግዚአብሔር ስለተፈጠረች
ነው ይላል። በዚህም ውስጥ ዓለም ውጤት ስትሆን በቂ የሆነ ምክንያት (አስገኚ) ሊኖራት ይገባል ማለት ነው።

ስለ ዓለም መገኘትም በዋናነት ሁለት አስተያየቶች ይነሳሉ።

A. ዓለም ዘላለማዊ ናት (Universe is Eternal)

ይህን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሳይንቲስቶች ዓለም ሁሌም ነበረች ዘላለማዊት ናት እንጂ አስገኚ ያስፈልጋት ዘንድ መጀመርያ
(Beggening) ያላት አይደለችም በማለት ይናገራሉ። ሃሳቡም 'Steady State Theory' ይባላል። የዚህ አስተሳሰብ
አራማጆች ለዓለም መነሻ (መጀመርያ) የሚለውን ጥያቄ ስለሚያስቀርላቸው ለነርሱ የተመቸ ነው። ምክንያቱም ዘላለማዊት
ናት ብለው ከተነሱ 'First cause (የመጀመርያው ምክንያት)' የሚሉትን ጥያቄዎች አያስከትልምና ነው። ይህ አስተሳሰብ
የተሳሳተ መሆኑን በራሱ ሳይንስ ይቃወመዋል። ይህንም በሳይንቲስቶች አመለካከት ስንመለከተው

 ሳይንሱ ዓለም በየጊዜው እየሰፋች እያደገች ነው በማለት ይናገራል ። (There is an Expanding


Universe) ይህ እየሰፋች መሄዷ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሰን ስንሄድ አንድ ነጥብ እንደነበረች እናስተውላለን
ይላሉ ይህም Singularity ይባላል። ይህም ዓለም መጀመርያ እንዳላት ያስረዳናል። በስዕል ስንገልጠው (The
Expanding universe)

⬛➡◼➡◾➡▪➡. (ሳጥኑ እየሰፋች ያለችውን ዓለምን [Expanding universe] ቢወክል ወደ ኋላ ብንመለስ


እንደ ነጥቡ ያለ መጀመርያ እንዳላት እንረዳለን።)

[ማስታወሻ ይህን ማስረጃ ማቅረባችን እሾህን በእሾህ በሚለው አካሄድ ነው ሳይንስን እንቀበላለን ስለ ዓለምም መገኘት ሳይንስ
ይነግረናል ብለው ሳለ ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ ሆነው መገኘታቸውን ለማሳየት ነው።]

 በሁለተኛው የ ፊዚክስ ቴርሞዳይናሚክስ ሕግ (The second Law of Thermodynamics) መሰረት


ዓለም ዘላለማዊ ናት የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት የለውም። Robert Jastrow የተባለው የናሳ ዳይሬክተር
የነበረው ሳይንቲስት "የሳይንስ የኋለኛው ፍለጋ በስነ ፍጥረት ላይ ያበቃል" በማለት የቱንም ያህል ቢራቀቅ
ስነፍጥረትን በሳይንሳዊ መንገድ ልፈልግ ማለት ድክመት መሆኑን ገልጿል። የፊዚክስ መርሕን (Principle of
Physics) የሚንድ ነው። ይህም ሕግ (Second law of Thermodynamics) በዝግ ሥርዓት (Closed
System) ነገሮች ሁሉ ወደ ስርዓት አልበኝነት ወይም ቀውስ (Disorderness) ይሄዳሉ ይህም State of
Entropy ይባላል። አንድ መኪና ብዙ ካገለገለ በኋላ መሥራት ያቆማል። ማሽኖችም ከጊዜያት በኋላ ይሰበራሉ።
ሕንጻዎችም ይፈራርሳሉ። የአንድን ነገር ማርጀትም እንዲሁ ይህ ሕግ ይገልጸዋል። እየሰፋች ያለችው ዓለም
(Expanding Universe) በምትሰፋበት ሂደት ጉልበትን (energy) እያጣች (It would lose Heat
and light) ትሄዳለች። ዓለማችን በውስጧ ያለውን ጉልበት ( Energy) እያጣች ትሄድና በመጨረሻም
ሕይወታችንም ሆነ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ይቆማሉ ዓለምም ትሞታለች ይላሉ። ምናልባት ይህ የሳይንቲስቶቹ
አገላለጽ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር የተስማማ ይመስላል።

ስለዚህ ዓለማችን ጉልበት (Energy) እያጣች ያላት ጉልበት እያለቀ የሚሄድ ከሆነ ዘላለማዊ (Eternal) ልትሆን
አትችልም። ምክንያቱም ዘላለማዊ እንድትሆን እያለቀ (እያጣች) ያለው Energy መተካት ይኖርበታል Energyው ግን
እያለቀ ነውና ዘላለማዊ ልትሆን አትችልም። ወይም በሌላ በኩል ዓለም ዘላለማዊ ሆና መጀመርያ የሌላት ወሰን የለሽ እድሜ
ቢኖራት ኖሮ State of Entropy ላይ ከብዙ ዓመታት በፊት በደረስን ነበር። በ State of Entropy ላይ ስላልደረስን
(ዓለም ስላልሞተች) ዓለም መጀመርያ ሊኖራት ይገባል ማለት ነው።

ብጹዕ አቡነ ሺኖዳም ዓለም ዘላለማዊ ናት ለሚሉት ሲመልሱ ተፈጥሮ ወይም ቁስ አካል ዘላለማዊ ነው ልንል አንችልም። ቁስ
አካል ዘላለማዊ ይሆን ዘንድ አይችልም። ዘላለማዊ መሆን ኃያል መሆኑን ያሳያል። ቁስ አካል ደግሞ ደካማ ነው። ከአንዱ ወደ
ሌላ ሁነት (State) ይቀየራል። ውሃ ወደ ትነት ይቀየራል። በኋላም ቀዝቅዞ በረዶ ይሆናል። እንጨትም ተቃጥሎ ከሰል
ይሆናል ወይም ጢስ ሆኖ ወደ አየር ይወጣል። ውህደቶች (Compounds) ወደ ቀደሙ ንጥረ ነገሮች (Elements)
ሊመለሱ ይችላሉ። ስለዚህም ተፈጥሮ ለውጥ የሚስማማው ነው። ይህ መለዋወጡ (አቋም አለመኖሩ) ጽኑዕ አለመሆኑ
ደካማነቱን ይገልጻል። ስለዚህም አዲስ ቁስ አካልን ለመፍጠር የሚችል አይሆንም።

B. ዓለም መጀመርያ ያላት ናት (Universe has a beginning)

ያሉት ማስረጃዎች በሙሉ ዓለም መጀመርያ (Beginning) እንዳላት የሚያሳዩ ናቸው። በምክንያትና ውጤት ሕግ (The
law of cause and Effect) መሰረት ደግሞ ለጅማሮዋ በቂ የሆነ ምክንያት ያስፈልጋታል። ይህም ምክንያት ከውጤቱ
የሚበልጥ መሆን ይኖርበታል። ከዓለም በላይ የሆነ ጅማሬ የሌለው ሊሆን ያስፈልጋል። እርሱም ምክንያት የሌለው ምክንያት
ወይም የመጀመርያው ምክንያት Uncaused Cause (First Cause) ነው። አስገኚ (ፈጣሪ አላት) የሚለውን ለመሸሽ
ደግሞ ዓለም መጀመርያ አላት ነገር ግን ራሷን በራሷ ያስገኘች (Self Existed) ናት በማለት የሚናገሩ አሉ። ይህ አስተሳሰብ
የሽሽት እንጂ ውሃ የሚያነሳ አይደለም። አንድ ነገር ራሱን ለማስገኘት በራሱ ውስጥ ኃይል ሊኖረው ይገባል። ይህን ኃይሉን
ደግሞ ከሌላ ምንጭ ከወሰደው በራሱ ተገኘ ሊባል አይችልም ራሱ ውጤት (Effect) ይሆናል እንጂ። ራሷን በራሷ አስገኘች
ማለት ምክንያታዊ አይደለም። አንድ ነገር ራሱን ለማስገኘት ከራሱ በፊት መገኘት አለበት። ይህ ደግሞ በአመክንዮ የማይቻል
(Logically Impissible) ነው። አንድ ቁስ አካል ራሱን አልፈጠረም (አላስገኘም) ትርጉምም አይሰጥም። ራሱ ሳይኖር
እንዴት ሁሉን ሊያስገኝ ይችላል። ከመፈጠሩ በፊትስ ለመፍጠር ምን ኃይል ሊኖረው ይችላል።

2. Telological Argument (The Argument from Design -የስነ ዲዛይን ሙግት)


"ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።" መዝ. 139:13-14

ከውብና ድንቅ ፍጥረታት (Design) በመነሳት ይህን የሰራ ፈጣሪ (Designer) መኖሩን የሚያስረዳ ነው። ድርጊት ያለ
አድራጊ ስሜት ያለ ምክንያት ስለማይኖር የዐዋቂነቱን፣ የኃያልነቱን የደግነት ባሕርዩን ምልክቶች በማሳየት ህልውናውን
ገለጧል። በአስደናቂ ሁኔታ ትልቅና በአሰራሩም አይንን የሚማርክ ሆኖ የተሰራ አንድ ቤት በምናይበት ጊዜ ያን ቤት የሰራ
መሐንዲስ ብልኅና ጎበዝ መሆኑን ያንንም ቤት ለአንድ አላማ የሰራው መሆኑን ወደ ሀሳባችን አይመጣምን? የአሰራሩንም
ትክክለኛነት አስደናቂነት በምናይበት ጊዜ እንዲህ አስተካክሎ ለመስራት መሳርያዎች ያሉት ብልህ ሰው መሆን አለበት
ማለታችን አይቀርም። ይህም መሳርያም የሰራ ታላቅ ዕውቀት ያለው ሰው መሆን አለበት ብለን በሃሳባችን እንወስናለን? ወይስ
ያ መሳርያና ያ ሥራ በአጋጣሚ የተገኘ እንደሆ እንገምታለን? በአዕምሮዋችን እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ይቀበለዋል? የሰው
አዕምሮ አንድ የተሰራ ስራ ባየ ጊዜ ለዚያ ስራ ሰሪ እንዳለው በፍጥነት ወደ ሃሳቡ ይመጣል። እንግዲህ በትልቁ ቤት አሰራርና
በመሳርያው ጉዳይ አንድ ብልኅና አስተዋይ ሰሪ ያለ መሆኑን የሰው አዕምሮ የሚገምት ከሆነ አዕምሮ ሊረዳውና ሊያብራራው
የማይችለውን የዚህን ዓለም አስደናቂ አፈጣጠር በሚመለከትበት ጊዜ ሰው የእግዚአብሔርን ሕልውና ሊያረጋግጥ
አይችልምን?

 በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን የአካል ክፍሎች አዘገጃጀት፣ በዐይኖቻችን ለማየት በጆሮዎቻችን ለመስማት
በእግሮቻችን ለመራመድ በአፍንጫችን ለማሽተት በእጆቻችን ለመስራት ለመያዝ መመቻቸታቸው በአጋጣሚ የሆነ
ነገር ነው ማለት ይቻላልን? እነዚህ እያንዳንዳቸው የአካል ክፍሎችም ዝም ብለው በሰውነታችን ላይ ተሰክተው
የሚገኙ ተለጣፊ ነገሮች ሳይሆኑ ከውስጣዊ አካላችን ጋር በቀላሉ ልንረዳው በማንችለው በአስደናቂ ሁናቴ የተያያዙ
ናቸው። ታዲያ ይህንን የተወሳሰበ አስደናቂ ሁናቴ የተያያዙ ናቸው። ታዲያ ይህን የተወሳሰበ አስደናቂ ሥርዓት
በአጋጣሚ የተገኘ ነው ለማለት እንደፍራለን? እነዚህ ሁሉ ነገሮች መነሻና መጀመርያ የሌለውን አንድ ትልቅ ብልኅ
(ጠቢብ) ፈጣሪ አይገልጡምን?

 እስቲ በመተንፈስ አማካይነት ስለምንኖርበት አየር እናስተውል። ይሄ አየር በውስጡ ኦክሲጅን አለው። በአየሩ
ውስጥ ያለው ኦክሲጅን ብቻ ቢሆን ኖሮ በቅጽበት ዓለምን በሙሉ ባቃጠለ ነበር። ድንቅና ብልኅ (Wise) ፈጣሪ
ግን ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ የተቃጠለውን የሚያጠፋ ናይትሮጂን የተባለውን ንጥረ ነገር ፈጠረለት። በሁለቱ
ንጥረ ነገሮች መዋሐድ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው አየር ተገኘ። በከባቢ አየር ያለው ኦክሲጅን 21% ነው። ይህ
የኦክሲጅን መጠን በ 2% ቢጨምር ኖሮ በዙርያችን ያሉ ቁስ አካል ሁሉ ተቃጥሎ ያልቅ ነበር። ይህ ጥበባዊ ስራ
የሆነው ረቂቅ ስነ ስርዓት በአጋጣሚ ተገኘ ለማለት ይቻላልን?

 አንድ የ DNA Molocule መሠረተ ሕይወት ብለው የሚጠሩት አንድ Encyclopedia የሚይዘውን መረጃ
ይይዛል። አንድ Encyclopedia በመሬት ወድቆ ብናይ መጽሐፉን ያዘጋጀ ጠቢብ እንዳለ እናውቃለን። አንድ
ፍጡር ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ DNA ዎች መኖሩን ስንረዳ ጠቢበኛ እንደሰራው ይነግረናል።

 በሰው አዕምሮ ያለው መረጃ በቢት (Bit) ሲገለጽ 100 ትሪሊዮን 14 bit መረጃ ነው። ይህ መረጃ በእንግሊዘኛ
ፊደላት ቢጻፍ መረጃው 20 Million መጽሐፍ የሚሆን ነው። ይህም 20 million ያህል መጻሕፍት የሚያህል
መረጃ በእያንዳንዳችን ጭንቅላት ውስጥ አለ ማለት ነው። ይህ ድንቅ ነው። ታዲያ ለዚህ ፍጥረት አስገኚ የለውም
እንዴት ሊባል ይችላል?

 ሰዎች ከአንዱ ከሌላው የሚለይበት የተለያየ አሻራ (Fingerprint) አላቸው። ለዚህ ሁሉ የተለያየ አሻራን የሰራ
አስገኚ ፈጣሪ መኖርን ይነግረናል።

 ምድር አሁን ካላት መጠነ ቁስ ትንሽ ብትተልቅ ኖሮ የመሬት ስበትን በመጨመር የሐይድሮጂን አቶሞችን ከከባቢ
አየር እንዳይወጡና እንዲከማች በማድረግ ለመኖር ተስማሚ አይሆንም ነበር። ምድራችን ትንሽ ብታንስ ደግሞ
ኦክሲጅን ከከባቢ አየር ይወጣ ነበር።

 ምድር በሕዋ ላይ በ 66,000 ማይል በሰዓት በፀሐይ ዙርያ ትዞራለች። ይህ ፍጥነቷ የፀሐይ ስበትን በመጠበቅ
በምሕዋሯ ከፀሐይ ባላት ርቀት እንድትዞር ያደርጋታል። የምድር ፍጥነቷ ትንሽ ቢሆን ኖሮ ወደ ፀሐይ ተስባ ትሄድ
ነበር ሕይወት ያለው ሁሉም ይጠፋ ነበር። እንዲሁ ከመሬት እስከ ፀሐይ ያለው ርቀት በ 2% እንኳ ቢቀየር
ሕይወት ሁሉ ይጠፋ ነበር።
ሌሊትና ቀን በቋሚ ስነ ስርዓት ይቀያየራሉ። የዓመቱ ወቅቶችም ሁናቴአቸው ሳይለወጥ ጊዜአቸውን ጠብቀው ይፈራቃሉ።
ወንዞች ሞልተው ወደ ባህር ይመለሳሉ። በዚህም ፍጥረታትን ያስገኛቸው እግዚአብሔር መኖሩንና በስነ ስርዓት
ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸው መሆኑን ይመሰክራሉ። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ "ደግሞም አምላክነቱ
ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሰሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።" ሮሜ. 1:20 ብሏል። ቅዱስ ዳዊትም "ሰማያት
የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ። የሰማይ ጠፈሮችም የእግዚአብሔርን ስራ ያውጃሉ።" መዝ.19:1 ብሏል። ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅም "እግዚአብሔር ስለ ሕልውናው ያስተማረን በመጻሕፍት አማካይነት ብቻ ቢሆን ኖሮ እርሱን ማወቅ የሚቻላቸው
መጻሕፍትን ማንበብ የሚችሉ ብቻ ሰዎች በሆኑ ነበር። መጻሕፍትን ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ማንበብ በሚችሉ ሰዎች ገለጣ
ካልተደረገላቸው በቀር እግዚአብሔርን ማወቅ ባልተቻላቸውም ነበር። ስለ እግዚአብሔር የተጻፉትን መጻሕፍትም ለማግኘት
የሚችሉት ባለጸጎች ብቻ ስለሚሆኑና ድሆች መጻሕፍቱን ለመግዛት አቅም ስለማይኖራቸው እግዚአብሔርን ማወቅ በባለጸጎች
በተወሰነ ነበር። ከዚያም በላይ በነዚያ መጻሕፍት የሚችል እነዚያ መጻሕፍት የተጻፉበትን ቋንቋ የሚያውቅ ሰው ብቻ በሆነ
ነበር። እነዚህ ችግሮች ግን በተፈጥሮ መጻሕፍት ውስጥ የሌሉ ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት ተፈጥሮ የሚናገረው
የተማሩና ያልተማሩ ሀብታሞችና ድሆች ሊረዱ በሚችሉት በትርዒት ቋንቋ እንጂ በጽሁፍና በአንደበት ንግግር ቋንቋ ስላልሆነ
ሁሉም ይህን ትልቅ መጽሐፍ በመመልከት የዚያን ሠሪ (ፈጣሪ) ትልቅነትና ክብር ለማንበብ ይችላል። በርግጥም ተፈጥሮ
የሚናገርበት ድምጽ አለው። ተፈጥሮን መመልከት ከአንደበት ከሚነገር ንግግር ይበልጣል።” ብሏል።

ይህ ሁሉ ድንቅ የስነ ፍጥረት አሰራር አስገኚ እንዳለው አፍ አውጥቶ ይናገራል። ይህን ለመቃወም በዕድል (Chance)
የተፈጠረ እንደሆነ የሚናገሩ አልጠፉም። ሳይንስ የሚመሰረተው በዕድል ሳይሆን በተደጋጋሚ ሙከራዎች እንደሆነና
ይነግረናል ስለዚህ ይህ ሙግት ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም። በዕድል የመገኘትን ነገር ጥናት ሲያደርጉ አንድ የእንስሳ ሕዋስ
(Animal cell) በዕድል መገኘቱ 1 በ 104,000 ነው። አንዷ Cell እንኳ በዕድል መገኘቷ ይህን ያህል ከሆነ አንድ ፍጥረት
በዕድል ተከሰተ ብሎ መናገር አያስደፍርም። ብጹዕ አቡነ ሺኖዳም ዕድል ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-አመክንዮአዊ ቃል ነው። ዕድል
ምንድነው? የዕድል ኃይሉስ ምንድነው? ዕድልስ ለመፍጠር የሚያስችል ባሕሪያት አሉት? በማለት ይጠይቃሉ።

3. Axiological Argument (The Argument from Moral-- የኅሊና ማስረጃ)


ይህ ሙግት መሰረት የሚያደርገው በነገሮች ጥሩና መጥፎ ወይም ትክክልና ስሕተት መሆን ላይ ነው። ሁሉም ሰው የሞራል
ሕግ እንዳለ ያውቃሉ። የሞራል ሕግ መኖሩ የሞራል ሕግ ሰጪ መኖሩን ያሳያል። አንድ ሰው ነገሮችን ጥሩና መጥፎ ብሎ
ለመፈረጅ በመጀመርያ ደረጃ ቋሚ የሆነ የሞራል ሕግ ሊኖረው ያስፈልጋል። ይህ ቋሚ የሆነውም የሞራል ሕግ እግዚአብሔር
የሰራው ሕሊና ነው። ሕሊናም በሰው ውስጥ የሚገኝ የስሜት አባል ነው። ዐይን በማየት አንድን ነገር ከሌላው እንደሚለይ
በዚህም ዓይነት ኅሊና ትክክለኛውን ስራ ከስሕተት ሥራ ይለያል። አውግስጢኖስ የተባለው ሊቅ "እግዚአብሔር ክብሩ
ይስፋና በሰው ልብ ውስጥ ፍርድን ሲመሰርት አዕምሮን ዳኛ ሕሊናን ዓቃቤ ሕግና ሐሳብን ምስክር አድርጓቸዋል። በተወዳጅ
ጣቶቹም በልብ ወረቀትነት ላይ የሕላዌው ምልክቶች አንድነቱ፣ዘላለማዊነቱ፣ ዓለምን መፍጠሩ ተጽፏል።’’ ብሏል፡፡

አባ ዶሮቴዎስም "እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር አዕምሮን የሚያበራ ክፉና ደጉን የሚያመለከተውን ሐሳብን ተከለበት።
ይሀውም ኅሊና ይባላል። ይህም የተፈጥሮ ሕግ ነው። የተጻፈው ሕግ ከመሰጠቱ በፊትም ይህንን ሕግ (ሕሊናን) ተከትለው
አባቶች ና ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተዋል::" ብሏል።

ይህ የሞራል ሕግ ቋሚ (Objective) ሳይሆን አንጻራዊ (Subjective) ነው ብለው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ። ሁሉም ሰው
የማይቀበለው መጥፎ ነገር አለ።

ለምሳሌ:- ግድያ ስርቆት ውሸት በሁሉ ዘንድ መጥፎ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። በመዋሸትና በመስረቁ የሚወደስ
የሚመሰገንበት ማሕበረሰብእ የለም። መግደልንም የሚያወድስ ማሕበረሰብ እንዲሁ። እዚህ ጋር የ አዶልፍ ሂትለር 6 ሚሊዮን
አይሁዳውያንን መጨፍጨፉ ሌሎችም የተፈጸሙትን የግድያ ተግባራት እንዴት ይታያል ሊባል ይችላል። አዶልፍ ሂትለር
ሰውን መግደል መጨፍጨፍ ልክ ነው በማለት ሳይሆን አይሁድን ከሰውነት የጎደሉ (Sub Human) አድርጎ ስለሚያምን
ነበር። ውርጃን የሚደግፉም ሰዎች ነፍስን ማጥፋት የሚደግፉ ሆነው አይደለም። ይልቁኑ ያልተወለደው ልጅ ሰው አይደለም
ብለው ስለሚያምኑ እንጂ።

ቋሚ የሞራል ሕግ የለም የሚሉ ሰዎች እንኳ በፍትሐዊ በክብርና በትሕትና መንገድ መስተናገድ የሚፈልጉ ናቸው። እኚህን
ሰዎች "አፍህን ዝጋ አንተ ስለምታስበው ምን አገባኝ" በማለት ብንናገረው በሞራል መደረግ አለባቸውን የሚባሉ እንዳሉ
ከፊቱ እናስተውላለን። ምንም ሊክዱ ቢሞክሩም የሞራልን ሕግ የማንክደው ሐቅ ነው።

C.S Lewis የተባለው በቀድሞ ሕይወቱ ኤቲስት የነበረ ሰው ስለሞራል ሕግ ሲናገር " በፊት ኤቲስት እያለሁ
በእግዚአብሔር ላይ የነበረኝ ሙግት ዓለም ጨካኝ ኢ ፍትሐዊ ነው የሚል ነበር። ነገር ግን ፍትሐዊና ኢ ፍትሐዊ የሚለውን
ከየት አገኘሁት? አንድ ሰው አንድን መስመር የተጣመመ ነው ለማለት ቀጥ ያለን መስመርን ሊያውቅ ይገባልና።" ብሏል።
ይህም ሞራላዊ ሕግን የሰጠ ፈጣሪ መኖሩን ያመለክታል። ነገሮችን ጥሩና መጥፎ ብለን የምንመለከትበት ቋሚ የሞራል ሕግ
በመኖሩ ነው።

4. Ontological Argument (The Argument from being- ስነ-ኑባሬ)

ስለ እግዚአብሔር ያለን ሐሳብ ይህ ሐሳብ መኖሩ በራሱ የእግዚአብሔርን መኖር ያስረዳል የሚል ሙግት ነው። ይህ ማስረጃ
የሚያተኩረው በሃሳብና በሕልውና ዝምድና ላይ ሲሆን ማስረጃውም እኚህ ሁለቱ ሐሳብ (Idea) እና ሕልውና (Existence)
አይነጣጠሉም። ሐሳብ ተዛማች የሆነ ሕልውና አለው። ሕልውና የሌለውን ነገር ማሰብ አንችልም የሚል ነው። C.S Lewis
"ምኞት (ፍላጎት) ከምንም አይመጣም። በማለት መልሱን ይጀምራል። ተፈጥሮ በራሱ ምኞት (Desire) እውናዊ በሚያደርግ
ሕልውና (Existence) ሳትሞላ አትፈጠርም ይለናል። ከመጀመርያ ስንጀምር በአንድ ሕፃን የሚበላ ነገር (ምግብ) በሌለበት
ሁኔታ የርሃብ ስሜት አይፈጥርም። የርሃብ ስሜት የሚኖረው ለርሃብ መልስ መሆን የሚችል ሕልውና ማለትም ምግብ ካለ
ብቻ ነው። ዋና ባይኖር ኖሮ የዋና ፍላጎት (ስሜት) አይፈጥርም ነበር። እናም ይላል ሌዊስ እግዚአብሔር የሚለው ሐሳብ
ሲጀመር የሚኖረው እግዚአብሔር ካለ ብቻ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር አለ ማለታችን ምናባዊ ወይም ምኞት ብቻ
የወለደው ፍላጎት ሳይሆን እውነትን መሠረት ያደረገ ነው በማለት ይሞግታል።

❓ጥያቄዎች❓

❓1⃣. ለሁሉ ምክንያት (አስገኚ) ካለው እግዚአብሔርን ማን አስገኘው?


በመጀመርያ ደረጃ ሁሉም ነገር ምክንያት ያስፈልገዋል አልተባለም። ይልቁኑ ሁሉም መጀመርያ (መነሻ) ያለው ነገር ምክንያት
አስገኚ አለው አልን እንጂ። ዓለም ዘላለማዊ ናት (Universe is Eternal) የሚለውን ሐሳብ ስንሞግት ዓለም መጀመርያ
እንዳላትም ያስረዳነው ምክንያት የሚያስፈልጋቸው መጀመርያ ያላቸው ነገሮች በመሆናቸው ነው ምክንያቱም መጀመርያ
ያላቸው አካላት ውጤት ናቸውና። ውሱንና ጥገኛ የሆኑ አካላት ለሕልውናቸው ምክንያትን ይፈልጋሉ። እግዚአብሔር ግን
ወሰን የለሽ ነውና አስገኚ አያስፈልገውም። የምክንያትና የውጤት ሕግ ከጊዜ ውጪ አይሰራም። (The law of cause and
effect doesn't apply in the abscence of time) እግዚአብሔር ደግሞ ከጊዜ በላይ (በጊዜ ውስጥ ስላልሆነ) ስለሆነ
ምክንያት (አስገኚ) የለውም። በሌላ በኩል ጥያቄው ራሱ illogical ነው። ለምሳሌ:- የወንደላጤው ሚስት ማናት?
የሚለውን ጥያቄ ብንመለከት illogical ነው። ምክንያቱም ቀድሞም ወንደላጤ ሚስት የለውማ! እግዚአብሔርን ማን
ፈጠረው? የሚለውም ጥያቄ አስገኚ (ምክንያት) የሌለውን ማን አስገኘው? ብሎ እንደመጠየቅ ያለ ነው።

❓2⃣. እግዚአብሔር ማንቀሳቀስ የማይችለውን አንድ ተራራ መፍጠር ይችላልን?


ጥያቄው የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ከሁሉ አስገኚነቱ ጋር ለማምታታት የቀረበ ነው። በመጀመርያ ደረጃ እግዚአብሔር
ሁሉን ቻይ ብቻ አይደለም ሁሉን አዋቂ በሁሉ የሚገኝ ሁሉን የሚያደርግ...አምላክ ነው። እኚህ ባሕርያቱ እርስ በርስ
የሚጋጩ አይደሉም። ይህን ጥያቄ መጠየቅ እንዲ ብሎ እንደመጠየቅ ያለ ነው። "ወሰን የለሽ ከሆነ በላይ ያለ ነገር አለን?"
ብሎ እንደመጠየቅ ነው። ወሰን የለሽ ካልን ለምን ገደብ እናበጅለታለን? ገደብ ወሰን ካለበትማ ቀድሞውኑ ወሰን የለሽ
አይባልም ነበር። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ካልን በኋላ ማንቀሳቀስ የማይችለውን ማለት በራሱ ዓርፍተ ነገሩ የሚጋጭ
ነው። በሌላ በኩል "እግዚአብሔር አራት መአዘን የሆነ ክብ መስራት ይችላልን?" ፣ "የሰማያዊ ሽታው ምንድነው?" ብሎ
እንደመጠየቅ ነው። ሰማያዊ ሽታ የለውም ምክንያቱም ይህ የመደብ (Catagory) ስህተት ነውና። ክብ ነገርም አራት መአዘን
መሆን አይችልም። በአመክንዮ የማይቻሉ ነገሮች (Logically Impossible) ናቸው። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ማለት
Logically የማይቻሉ ነገሮችን እንዲያደርግ መናገር ማለት አይደለም። ለኛ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ የተቻለ ነው
ሁሉን ማከናወን ማኖር ማጥፋት ጊዜና ቦታ ሳይገድበው መስራት ለርሱ ይቻለዋል።
❓ 3⃣. እግዚአብሔር ወሰን የለሽ ከሆነ በአንዴ በጎም መጥፎም ጠንካራም ደካማም መሆን አይችልም
ወይ? የወሰነው የለሽ ከሆነ ኃጢአትን ማድረግ አይችልም ወይ?
እግዚአብሔር ወሰን የለሽ ነው ስንል በፍጽምናው ወሰን የለበትም (Unlimited In His Perfection) ማለታችን ነው።
ኃጢአት ደግሞ ፍጽምና አይደለም። ይልቁኑ ፍጹም ያለመሆን (Imperfection) ነው እንጂ። ደካማ መሆንም እንዲሁ
ውሱንነት ወይም ፍጹም ያለመሆን ናቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር ወሰን የለሽ ነው የምንለው በፍጽምናው ነውና ክብር
ይግባውና እንደ ፍጡራን ኃጢአት ማድረግ ድካም አይስማማውም።
The Problem of Evil (የክፉ ነገር ጣጣን)
እግዚአብሔር መልካምና ኃያል ከሆነ እንደ መልካምነቱ ክፋትና መከራ እንዲኖር አይወድም። ኃያልም እንደመሆኑ ክፋ ነገርና
መከራን ማጥፋት ይቻለዋል። ክፉ ነገርና መከራ ግን በዚህ ምድር ላይ ስላሉ እግዚአብሔር የለም በማለት ይናገራሉ። በምድር
ላይ የሚታዩትን መከራዎች ኢፍትሐዊነትና የክፋት ስራዎችን በማንሳት ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ክፉ ነው
እግዚአብሔርም የለም ይላሉ። በመሰረታዊነት ጥያቄውን ልብ ካልነው በእግዚአብሔር መኖር ላይ ሳይሆን በመልካምነቱ ላይ
የተነሳ ጥያቄ መሆኑን እንረዳለን። ቋሚ የሞራል ሕግ የለም የሚሉ ኤቲስቶች ፍትሐዊና ኢፍትሐዊ ብለው ለማማረር እንዴት
ቻሉ? በአስተውሎት ብንመለከተውማ የእግዚአብሔርን አለመኖር ሳይሆን መኖሩን የሚያስረዳ ነው::

በፍልስፍናው ዓለም ክፋት የሚባሉትን በ 3 ከፍለው ይመለከታሉ።

1ኛ. አካላዊ ክፉ (Physical Evil)

እኚህም ክፋት የሚባሉት የሰውን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ናቸው። ሕመም፣ በሽታ፣ ስቃይ፣ ጭንቀት ሞት የመሳሰሉት
ናቸው።

2ኛ. ስነ ምግባራዊ ክፉ (Moral Evil)

እኚህ ደግሞ ከማሕበረሰቡ ውጪ ያሉ ማፈንገጦች ናቸው። ስርቆት ዝሙት ውሸት ማጭበርበር...የመሳሰሉት ናቸው።

3ኛ. ሜታ ፊዚካላዊ ክፉ (Metaphysical Evil)

እነዚህ ደግሞ ከተፈጥሮ በላይ በሆኑ ክስተቶች የሚደርሱ ናቸው። ረሃብ ቸነፈር የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ይህን ሜታፊዚካል ክፉ ሳይንቲስቶች በራሳቸው ክፉ አይደሉም በማለት ይሞግታሉ። ምክንያቱም እኚህ ዓለምን ምሉዕ
የሚያደርጓትና የሚጠቅሙ ስለሆኑ ነው በማለት ያስተምራሉ። ለምሳሌ:- በአንድ የክዋክብት ፍንዳታ የሚፈጠሩ አደጋዎች
አሉ። በዚህ ውስጥ ግን የሚገኙ እንደ ዚንክ ወርቅ ያሉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች (Elements) ይፈጠራሉ እኚህ ደግሞ ስነ
ምሕዳሩን የሚጠብቁ ናቸው ለእንስሳቱና ለእጽዋቱ ሕልውና የሚያስፈልጉ ናቸው ይላሉ ።

በክርስትናው ደግሞ አኚህ ክፉ የሚባሉት በሁለት ተከፍለው ይታያሉ።

1ኛ. ተፈጥሮአዊ ክፉ (Natural Evil)

በተፈጥሮአዊ ሒደት የሚከሰቱ ናቸው። ረሃብ በሽታ መከራዎች የመሳሰሉት... ናቸው።

ጻድቁ ኢዮብ ሰይጣን መከራን ካደረሰበት በኋላ "ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን ክፉ ነገርንስ አንቀበልም። አላት"
ኢዮብ. 2:10 በማለት መከራውን ያደረሰው ሰይጣን ቢሆንም የፈቀደው እግዚአብሔር በመሆኑ ክፉን ከእግዚአብሔር
አንቀበልምን? በማለት ተናግሯል። ስለ ክፉ ነገር ስንናገር የሰውንም ድርሻ መመልከት ያስፈልጋል። ሰው ይህ ሁሉ መከራ
የሆነው በእግዚአብሔር ነው በማለት ያማራል በዝሙት በመመላለስ AIDS የተባለ ብዙዎችን የቀጠፈ በሽታ አመጥቷል።
ለAIDS በሽታ የሚውለው ገንዘብ ለተቸገሩት ይውል ነበር። ሀገራት ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ለጦር መሳርያ መግዣ
እየተጠቀሙ በኋላ ደግሞ ለሚፈጥሩት ጦርነት እግዚአብሔርን ይከሳሉ። የተሰጠንን ተፈጥሮ በአግባቡ ሳንይዝ የአየር
ብክለትን እኛው ፈጣሪዎች ሆነን ሳለ በኋላ የአየር ንብረት መለወጥ እያልን እንጮሃለን እግዚአብሔርን እንከሳለን። ሰው
ራሱን ከመክሰስ ይልቅ ከጥፋት ከመራቅ ይልቅ ለጥፋቱ እግዚአብሔርን ተጠያቂ ማድረግ እግዚአብሔርን ለመቃወም
ይነሳል። እግዚአብሔር መከራን ሲፈቅድ የተፈጥሮ አደጋ እንዲሆን ቢያደርግ ፍቅር ሰላምን እንድናጸና ለመልካም ዓላማ ነው
ነው።
2ኛ. ስነ ምግባራዊ ክፉ (Moral Evil)

ነጻ ፈቃድ ባላቸው ፍጥረታት የሚፈጸሙ የስነ ምግባር ጉድለቶች የኃጢአት ሥራዎች ናቸው። ስርቆት ስግብግብነት
ውሸት...የመሳሰሉ የኃጢአት ሥራዎች ናቸው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የሁለቱን ልዩነት ሲያስቀምጥ “በራሱ ክፋት የሆነ ነገር አለ። እነዚህም አመንዝራነት፣ዝሙት፣
ስስታምነት፣ ፍቅረ ንዋይና ስፍር ቁጥር የሌላቸው የመጨረሻ ውግዘትና ቅጣት የሚገባቸው አስፈሪና አሳፋሪ የሆኑት
ተመሳሳይ ነገሮች ሁሉ ናቸው። በሌላም በኩል ረሃብ፣ በሽታ፣ሞት፣ ሕመምና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎችም "ክፉ" ተብለው
ይጠራሉ። እነዚህ እንደ መጀመርያዎቹ ዓይነት ክፉዎች አይደሉምና ለዚህ ነው "ክፉ" ይባላሉ ያልኩት። ምክንያቱም
በራሳቸው ክፉዎች ቢሆኑ ኖሮ ትዕቢታቸውን በመገሰጽ፣ ከስንፍናችን በማንቃት፣ ጥንካሬያችንን በመጨመርና የበለጠ ትጉኃን
እንድንሆን በማድረግ የመልካም ነገር ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም ነበር። በራሱ ክፉ የሆነ ኃጢአት ግን የእግዚአብሔር ስራ
አይደለም። እግዚአብሔር ፈጽሞ ኃጢአትን አልፈጠረም። ኃጢአት የኛ ነጻ ፈቃድ የፈጠራ ውጤት ነው። ያ ግን ይህን
ለማስታገስና ለማጥፋት ከእግዚአብሔር የሚመጣ ነው።” ብሏል።

ሙግት 1
መነሻ ሐሳብ 1 (Premise 1) :- ክፉ ነገር መልካም አላማ የለውም።

መነሻ ሐሳብ 2 (Premise 2) :- መልካም የሆነ እግዚአብሔር የሆነው እግዚአብሔር ደግሞ መልካም አላማ አለው።

ስለዚህ እግዚአብሔር ሊኖር አይችልም ይላሉ።

መከራ ሕመም ክፉ የተባሉት ነገሮች መልካም አላማ የላቸውም ማለት ወሰን የለሽ ዕውቀት ነው ያለኝ ብሎ መናገር ነው።
ፍጡራን ሆነን ውስን እውቀት ኖሮን የእግዚአብሔርን ሥራ ዓላማ ካልተረዳን መልካም ዓላማ የለውም ማለት አይገባም።
"የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው። ፍርዱም እንዴት የማይመረመር ነው ለመንገዱም ፍለጋ
የለውም።" ሮሜ. 11:33 ተብሏልና።

የሕመም የመከራ ጥቅሞች


1ኛ. ሕመም ከሚመጣው የባሰ ጥፋት እንዳይደርስብን የሚሰጡ ናቸው። አባት ልጁን የሚቀጣው ስለሚወደው ነው እንጂ
በጭካኔና በጥላቻ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ “ለመቀጣት ታገሡ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና።
አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማነው? ነገር ግን የሁሉ ቅጣት ተካፋይ ሆኗል። ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጂ ልጆች
አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩ እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት
አብልጠን ልንገዛና ልንኖር በተገባን ነበር። እነርሱ መልካም ሆኖ እንደታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና እርሱ ግን
ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም። ዳሩ
ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።" ዕብ. 12:7-11 ብሏል፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ጳውሎስ
"ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋ መውጊያ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልዕስተኛ ተረጠኝ::" 2ኛ ቆሮ.
12:7 በማለት የተሰጠው መገለጥ ትዕቢት እንዳይሆንበት ትዕቢት ሆኖበትም እንዳይጎዳው የጎን ውጋት በሽታ ተሰጥቶት
ነበር። ይህም ራሱን ደካማ መሆኑን አውቆ ከትዕቢት ይርቅ ዘንድ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሐኪም የሚመሰገነው በሽተኛውን ወደ መስክና ደስ ወደሚሉ የአትክልት ቦታዎች ሲወስደውና ጥሩ
ምግብ ሲያቀርብለት ብቻ ሳይሆን ያለ ምግብ እንዲቆይ ሲያዘውም፣ እንዲህ ያለውን አትብላ፣ እንዲህ ያለውን አትጠጣ ብሎ
ሲከለክለውም፣ ከአልጋው እንዳይነሳ ሲያዘውና አልጋውን እንደ እስር ቤት ሲያደርግበትና ፀሐይን እንኳ እንዳያያት
ሲከለክለውም፣ ቤቱን በሁሉም አቅጣጫ በመጋረጃ ሲጋረደውም፣ የሚቆረጥ አካል ካለ ያንን ጨክኖ ሲቆርጥና ስለት ሰውነቱ
ላይ ሲያሳርፍበትም፣ የሚመርሩ መድኃኒቶችንም ሲያመጣና በሽተኛውን እንዲወስድ ሲያዘውም በእነዚህ ሁሉ አሁንም
እንደዚያኛው እኩል ሐኪም ነው። ይህን ያህል ከባድና አስጨናቂ ነገር የሚያደርገውን ሐኪም እያሉ እየጠሩና ድርጉቱንም
ለሰውዬው ጤንነት ከማሰብ እንደሆነ በመረዳት እያመሰገኑና እያወደሱ እግዚአብሔር ግን ከነዚህ ነገሮች ረሃብ ወይም ሞት
አንዱን እንኳ ቢደረግ ማማረርና መግቦቱን እስከ መካድ ደርሶ በርሱ ላይ የማይገባ መናገር ምን ያህል የሚያበሳጭና
የሚያሳዝን ነገር ነው?” በማለት ገልጾታል፡፡

2ኛ. የስጋ ደዌን በሽታን (Leprosy) ብንመለከት በዚህ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች የጥናቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሕመም
ስለማይሰማቸው (loss of sensation and pain) ራሳቸውን ይጎዳሉ። እኛ የሚጎዳ የሚያቃጥል ነገርን ስንነካ ሕመም
ይሰማናል በስጋ ደዌ በሽታ ታማሚዎች ዘንድ ግን ይህ ሕመም ስለማይሰማቸው የጋለና የሚያቃጥል ነገር ላይ በመቆየት
በእጆቻቸው ላይ የመቆረጥና የመቆመጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል። እኛ የምናማርረው ሕመም እነርሱ የሚናፍቁት ነው። ስለዚህ
ሕመምን መከራን ይዘን ጠቃሚ አይደለም ልንል አይቻለንም።

3ኛ. በክፉ ነገሮች እግዚአብሔር ታላቁን መልካም ነገር ያመጣል። ሕመም መከራውንም እግዚአብሔር ለበጎ ይለውጠዋል።

 አይሁድ ጌታችን መከራ ባደረሱበት ፍትሕ በታጣበት ሁኔታ በሰቀሉት ጊዜ እግዚአብሔር የሰቃዮቹን ክፉ
ድርጊታቸውን ለበጎ በመለወጥ ለሁላችን ድኅነት ለክርስትናም መሰረት ሆኗል።
 ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስን ስለ እውነት በመመስከሩ ተቃውመውት ወግረው በገደሉት ጊዜ ክርስቲያኖች በስደት
በዓለሙ ተበትነዋል። ይህ የገዳዮቹን ክፉ ተግባራቸውን እግዚአብሔር ወደ በጎ በመለወጥ የተበተኑት ክርስቲያኖች
በዓለም ወንጌልን በማስተማር ክርስትናን አስፋፍተዋል።
 ዮሴፍን ወንድሞቹ በሸጡት ጊዜ ወደ ምድረ ግብጽ ደርሶ ሹመትን አግኝቶ በረሃብ ምክንያት ተሰደው የመጡ
ቤተሰቦቹን ታድጓቸዋል። ይህን ሲገልጥ "እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሆነው ብዙ
ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው::" ዘፍ.50:20
 በአንዳንድ የሱስ ማገገሚያዎች አልኮል ሲጋራን Cocaine ይሰጣቸዋል። በቃኝ እስኪሉ ድረስ እኚህን እጾች
በመውሰድ ከዚያም በኋላ ወደ ማገገም ይደርሳሉ።

4ኛ. እግዚአብሔርም በልዩ ጥበቡ ክፋት ይኖር ዘንድ የፈቀደው ታላቅ የሆነ መልካም ነገር ሊያመጣ ነው። ምክንያቱም ታላቁ
መልካም ነገር ያለ ክፋት መኖር አይኖርምና። የክፋት መኖሩ ለመልካም ነገር መምጣት አስተዋጽኦ አለው ማለት ነው።
ለምሳሌ:- አንዳንድ ምግባራት ያለ ክፉ ነገር መኖር ትርጉም የላቸውም። አንዳንድ ምግባራት በመከራና ክፉ ነገር መኖር ነው
ትርጉም የሚያገኙት ያለ አደጋ ብርታት ያለመሰናክል ጽናት ያለ መከራ ትዕግስት የለም።

 " ወንድሞች ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስት እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ
ሙሉ ደስታ ቁጠሩት።" ያዕ. 1:2-3
 "ነገር ግን መከራ ትዕግስትን እንዲያደርግ ..." ሮሜ.5:3

መከራ በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር የምናሳይበት ነው። "ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም
የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።" ገላ. 6:2

ስለማናውቀው ጉዳይ እግዚአብሔር ኢ-ፍትሃዊ ነው ለሚሉ ወገኖች የእግዚአብሔርን ጠባቆት ለመረዳት ይህን ታሪክ
እንመልከት

የእግዚአብሔር ፍትሕ (Divine Justice) ለማወቅ የሚጨነቅ የነበረ አንድ ሰው መንፈሳዊ አባቱ ጋር ቀርቦ ይጠይቀዋል።
የሰውን የዕለት ኑሮ ከአንድ ቦታ ተደብቆ ይከታተል ዘንድ ይነግረዋል። የተመለከተውም ይህን ነበር። በመጀመርያ በመንገድ
የሚያልፍ አንድ ባለጠጋ ከፈረሱ ወርዶ ለማረፍ ወደ አንዲት ምንጭ ዳር ይቀመጣል። ከቦርሳውም 100 የወርቅ ሳንቲሞችን
አውጥቶ ቆጠረ። ወደ ፈረሱ ሲወጣ ቦርሳውን ረስቶ ይሄዳል። በኋላም ሌላ ሰው ወደዚያች ምንጭ ዳር ይመጣና ቦርሳዋን
አግኝቶ ይሄዳል። ቀጥሎም አንድ ድሃ በምንጩ ዳር ተቀምጦ ዳቦ እየተመገበ ሳለ ቦርሳውን የጣለው ባለጠጋ ቦርሳውን
ሊፈልግ ወደዚያች ምንጭ ዳር ተመልሶ ሲሄድ ድሃውን ተቀምጦ ያገኘዋል። ስለቦርሳውም ሲጠይቀው ድሃው ምንም
እንደማያውቀው ይነግረዋል። ገንዘቡንም የወሰደ መስሎት ይደበድበዋል ድሃውም ክፉኛ ከመደብደቡ የተነሳ ይሞታል። በኋላ
ኪሱን ቢፈትሸው ቦርሳውን አላገኘም። ይህን የሰዎቹን ሁኔታ ተደብቆ ይከታተል የነበረው ሰው "ጌታ ሆይ የፈቃድህ ነገር
አሳውቀኝ? ቅንነትህ ይህን ኢ-ፍትሐዊነት ይታገሳልን?" በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። የእግዚአብሔር መልአክም ተገልጦ
እንዲህ ሲል መለሰለት። "ከተመለከትካቸው ውስጥ አንደኞቹ በፈቃደ እግዚአብሔር ሌላው ለትምህርትና በጠባቆቱ የተደረጉ
ናቸው። ገንዘቡን የጣለው ሰው ገንዘቡን ላገኘው ሰው ጎረቤቱ ነበር። ገንዘቡን ያገኘው (2ኛው ሰው) 100 የወርቅ ሳንቲም
የሚያወጣ የፍራፍሬ ቦታ ነበረው። ገንዘብ ወዳድ የነበረው ባለጠጋው (ገንዘቡን የጣለው) በ 50 የወርቅ ሳንቲም እንዲሸጥ
አስገደደውና ገዛው። ይህ የተበደለው ሰውም ወደ እግዚአብሔር ፍትሕን ይሰጠው ዘንድ ለመነ። ስለዚህም 100 የወርቅና
ሳንቲም ያለበትን ቦርሳ ማግኘቱ ለጸሎቱ መልስ በእግዚአብሔር ጠባቆት የተደረገ ነበር። ገንዘቡንም እጥፍ ሆኖ አግኝቷል።
"ያለ ፍትሕ የሞተው ድሃ ደግሞ ከዚህ በፊት ከዚህ በፊት ሰውን ገድሎ ነበር። ንስሐ ከገባ በኋላም እግዚአብሔር ደስ
በሚያሰኝ መንገድ ይጓዝ ነበር። ዘወትርም ለፈጸመው ኃጢአት (ሰውን ስለ መግደሉ) እግዚአብሔር ይምረው ዘንድ እርሱ
እንደገደለው አይነት ባለው አሟሟት ይሞት ዘንድ ይለምን ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ በተመለሰ ጊዜ ይቅር ቢለውም ከልብ
ለመነጨ ልመናውና ለፈጸመው ወንጀል መክፈልን በመሻቱ እንደወደደው ይሞት ዘንድ ፈቀደለት በኋላም ወደ እግዚአብሔር
እቅፉ ሄዷል። በመጨረሻም የወርቅ ሳንቲሞቹ የጠፉበትና ሰውን የገደለው ባለጠጋ በገንዘብ ወዳድነቱ ምክንያት ፍጻሜው
ጥፋት ስለሆነ ሰውን በመግደል ኃጢአት ተጸጽቶ ንስሐ ይገባ ዘንድ ሰውን እንዲገድል ፈቀደ። በመጨረሻም ይህ ባለጠጋ ንስሐ
ገብቶ ዓለማዊ ደስታን ትቶ መነኩሴ ይሆናል። ታዲያ በየትኛው ላይ ነው እግዚአብሔር ጨካኝና ኢ-ፍትሐዊ የሆነው? ሲል
መልሶለታል።

ክፉ ነገሮች ቢሆኑ እንኳ ለበጎ እንዲደረጉ ማወቅ


ታሪክ

አንድ ንጉስ ከ አጃቢው ጋር በመሆን ለ አደን ይወጣል። ለ አደን ሲወጡ ንጉሱ ወጥመድ እያጠመደ እያለ ወጥመዱ አምልጦት
እጁን ቆረጠው ። በዚያም አጃቢው በማዘን "አይዞህ ንጉስ ሆይ ሁሉ ነገር ለበጎ ነው!" ይለዋል። በዚህም ንጉሱ በንዴት
እየጦፈ "የኔ እጅ መቆረጥ ነው ለበጎ?" ይለውና እስር ቤት አሳሰረው።

ከብዙ ጊዜ በሗላ ንጉሱ ብቻውን ሀገሩን ሲዞር ሰው አርደው ለጣዖት መሰዋት የሚያደርጉ ጨካኝ ሰዎች ያዙትና አርደው
መሰዋት ሊያደርጉት ሲሉ ቆራጣ እጁን አዩት። በእነሱ ህግ መሰዋት የሚያደርጉት ሰዉ ሙሉ ጤነኛ መሆን ስላለበት ለቀቁት።
ንጉሱ አጃቢው 'ሁሉ ነገር ለበጎ ነው! ያለው ትዝ አለውና' እስር ቤት ሄዶ ስላሰርኩህ ይቅርታ አርግልኝ!..ብሎ ታሪኩን
አጫወተው።

አጃቢውም "ማሰርክ ለበጎ ነበር! እኔም መታሰሬ ጠቅሞኛል።" አለው።

ንጉሱ-"እንዴት?"

አጃቢ-"ባልታሰር ኖሮ ከአንተ ጋር እሄድና አንተ ቆራጣ መሆንህን ሲያውቁ ይለቁህና እኔን ይገሉኝ ነበርኩ " አለው።
ሙግት 2 (ክፋት (ኃጢአት) በእግዚአብሔር ተፈጥሯልን?)

መነሻ ሐሳብ 1 (Premise 1) :- እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ሠሪ (ፈጣሪ) ነው። (God is The Author of
Everything)

መነሻ ሐሳብ 2(Premise 2) :- ክፉ ነገር ደግሞ አንዳች ነገር ነው። (Evil is Something)

ስለዚህ ክፋትንም የፈጠራት እግዚአብሔር ነው ይላሉ።

መልስ

አውግስጢኖስ ሲመልስ "በመጀመርያ ክፋት አንዳች ነገር ነው ወይ ብለን ልንጠይቅ ያስፈልጋል። ክፋት አንዳች ነገር
አይደለም። (Evil is not a thing) ስለዚህም መፈጠር አያስፈልገውም ማለት ነው።" ክፋት ራሱ የመልካም ነገር
አለመኖር ስለዚህም ነው ክፋት የሚል ስያሜን ያገኘው ይለናል። ክፋት በራሱ ያለ ነገር አይደለም። የመልካም ነገር መጉደል
እንጂ። እግዚአብሔር ሁሉን ፈጠረ የፈጠረውም መልካም ነው። ክፋት ግን የመልካም አለመኖር ነው። ልክ ቅዝቃዜ የሙቀተ
አለመኖር እንደሆነ ክፋትም የመልካም ነገር ጉድለት ነው።

እግዚአብሔር ሁሉን መልካም አድርጎ ሰርቶታል። እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጠው ነገሮች አንዱ ነጻ ፈቃድን ነው። ሰው
በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነውና ነፃነት አለው። እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ ስለ ሥራውም ሁሉ ፍጹም ነጻ ነው።
ለሰውም ነጻ ፈቃድን ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ሰውን ከነጻና ከነጻ ፈቃድ ጋር ፈጥሮታል። ነፍሱ የተሳበችበትንና
የወደደችውን መርጦ መፈጸም በዚያም መኖር ይችላል። ይህም ደግሞ ከእንስሳት ይለየዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም
"እግዚአብሔር ማንንም በኃይልና በግድ ወደራሱ ፈጽሞ አይስብም። ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ቢፈለግም በድንቅ አጠራሩ
ይጠራል እንጂ ማንንም አያስገድድም" ብሏል። ሰው ነጻነት የተሰጠው በፈቃዱ ከሞትና ሕይወት አንዱን ይመርጥ ዘንድ
ነው። መምረጥ መቻሉ ደግሞ ለነጻነቱ ማረጋገጫ ነው። አንድ ሰው በበረሃ ላይ ቆሻሻ ውሃ ቢያገኝ እንኳ ይጠጣል አማራጭ
የለውማ! ስለዚህ ነጻነት ይገለጥ ዘንድ መምረጥ መቻል ያስፈልጋል። ነጻ አድርጎ የፈጠረን አምላክ በነጻነት እንድንወድ ነው።
ሰውች ነጻ ናቸው ሲባል እግዚአብሔርን በነጻነት (በነጻ ፈቃዳቸው) የሚወዱትና ፈቃዱንም ያለ አስገዳጅነት ማድረግ ሲችሉ
ነው። ፍቅር አምልኮና መታዘዝ የምንላቸው በፈቃድ የሚደረጉ መስማማቶች ናቸው። በአስገዳጅነት ከተደረጉ ፍቅር
አምልኮና መታዘዝ አይባሉም። እኚህ ነጻ ፍጥረታትም ወደው ፈቅደው እግዚአብሔርን የሚወዱት እርሱንም ለመቃወም ነጻ
ፈቃድ ያላቸው ሊሆን ይገባል።

በግድ የሆነ ፍቅር ራሱ በራሱ ፍቅር አይደለም። እንዲህ አድርጎ እኛን በመፍጠሩ ክፋትን የሚቻል አድርጎታል። ነጻ በመሆን
መልካሙን የመምረጥ ብቻ ሳይሆን ክፉውንም የመምረጥ ፈቃድ አለን። ይህ ለሰዎች የተሰጠው ነጻ ፍቃድ ደግሞ የክፋት
መነሻ ሆኗል። ስለዚህም በነጻ ፍቃድ ምክንያት እግዚአብሔር ክፋትን የሚቻል አድርጎታል። ሰው ደግሞ ክፋትን የሚሆን
አደረገው። [God made Evil Possible and Man evil actual.] ክፋትን እግዚአብሔር አልፈጠራትም። በነጻ ፍቃዱ
ምክንያት ከልቡ ያመነጫት ዲያብሎስ ነው። ሰይጣን ድንጋይ ከድንጋይ ተሰብቆ እሳት እንዲፈጥር ዲያብሎስም ሐጢአትን
አደረጋት። ( ሕዝ.28:15፤ ኢሳ. 14:7) ጌታችንም በወንጌል "ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል። ሐሰተኛ የሐሰትም አባት
ነውና።" ዮሐ. 8:44 ብሎአል። የኃጢአት ምንጭ እግዚአብሔር ነው ማለት እንዴት ይቻላል? አንድ ተጻራሪ ነገር ሌላ
ተጻራሪን ነገር ማድረግ ስለማይችል ሕይወት ሞትን ጨለማም ብርሃንን አታስገኝም። በሽታም የጤና ምንጭ አይሆንም።
ሙግት 3 :- ክፋት ለምን አይጠፋም?
መነሻ ሐሳብ (Premise 1) :- እግዚአብሔር መልካም ከሆነ ክፋትን ያጠፋል።

መነሻ ሐሳብ 2 (Premise 2) :- ሁሉን ማድረግ ስለሚቻለውም ክፋትን ማጥፋት ይቻለዋል።

ክፋት ደግሞ አልጠፋችም። ስለዚህ እግዚአብሔር የለም ይላል።

መልስ

ክፋትን ነጻነትን ሳናጠፋ ማጥፋት አንችልም። ክፋት በነጻነት ምክንያት የመጣ ነውና። ነጻነት ደግሞ የተሰጠን በነጻነት ፈቅደን
ወደን እንድንወድ እንድናፈቅር ነው። ፍቅር ለሰው ፍጥረት ትልቁ ገንዘቡ (ሀብቱ) ነው። ፍቅር ደግሞ ያለ ነጻነት አይሆንም።
ስለዚህም ነጻነትን ማጥፋት ክፋትን ማሸነፍ የሚቻለውን ፍቅርን ማጥፋት ይሆንብናል። ስለዚህ ክፋትን ለማጥፋት ነጻነትን
ማጥፋት በራሱ ክፉ ይሆናል። እግዚአብሔር ነጻ ፈቃድ ያላቸውን ፍጥረት ፈጥሮ ኃያል ስለሆነ ክፋት የሌለበትን ዓለም
መፍጠር አይችልም ወይ ብሎ መጠየቅ ሁሉን ቻይነቱ ላይ ሎጂካዊ ተቃርኖ (Logical Contradiction) ያመጣል ማለት
አይደለም። ክብ የሆነ 4 መዓዘን አይሰራም። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ስለሆነ ይዋሽ ማለት አይደለም። C.S Lewis
"እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ነጻ ፈቃድን ሰጥቶ በተመሳሳይ ደግሞ ነጻ ፈቃዱን መያዝ ይችላል በማለት መናገር ትርጉም የለሽ
የቃላት ስብስቦችን "እግዚአብሔር ይችላል" የሚል ቅጥያን በመጠቀም ድንገት ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ አይቻልም።”

እግዚአብሔር ክፋት ( ኃጢአትን) ማጥፋት ይቻለዋል። አሁን ክፋት ስላልጠፋ ድል ስላልተነሳ አይጠፋም ማለት ግን
አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ "ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል" 2ኛ ጢሞ. 4:8 እንዳለ ኃጢአት የሌለበት ኃጢአት
ድል የሚነሳበት ጊዜም ይመጣል።

ጥያቄ:- እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ገሃነም ለምን ይልካቸዋል?


ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። "ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ
ስለእናንተ ይታገሳል።" 2ኛ ጴጥ.3:9 እንዲል ሁሉ ይድን ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃዱ ነው። ሁሉም በመንግስተ ሰማያት
እንዲኖር እግዚአብሔር ቢወድም ሰዎች እርሱን ማመንና መውደድ አለባቸው። እግዚአብሔር ሰዎችን እንዲወዱት (ማንም
እንዲወደው) አያስገድድም። በግዳጅ የሆነ ፍቅር ፍቅር አይባልም። ፍቅር ነጻ ምርጫ ነውና። እግዚአብሔር ቢወድም
አንዳንዶች ግን እርሱን ለመውደድ አይመርጡም። "ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ
ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም::" ማቴ. 23:37 እንዲል። ወደ ገሃነመ እሳት ሰዎች የሚገቡት እግዚአብሔር
ስለሚልካቸው ሳይሆን ስለመረጡትና እግዚአብሔርም ምርጫቸውን ስለሚያከብር ነው። ወደ ገሃነመ እሳት መሄድ አይፈልጉ
ይሆናል። ነገር ግን እርሱን ላለመቀበል ወስነዋል።

C.S Lewisም "በመጨረሻም ሁለት አይነት ሰዎች አሉ። የመጀመሪያዎቹ እግዚአብሔርን "እንደ ፈቃድህ ይሁን" ይሁን
የሚሉና ሌሎቹ ደግሞ እግዚአብሔር በመጨረሻ "እንደ ፈቃዳችሁ ይሁን" የሚላቸው ናቸው ብሏል። ወደ ገሃነመ እሳት
የሚገቡትም ስለመረጡት ነው። ቅዱስ ሄሬኔዎስም "ሰው ኃጢአትን በማድረግ የራሱን ቅጣት ያመጣል። ልክ የራሱን ጉድጓድ
ቆፍሮ እንደመግባት ነው። ክፉ ስራውም ወደ ራሱ ይሄዳል። ራሳችን ፈቅደን ኃጢአት ስናደርግ ቅጣትን እንመርጣለን። ከርሱ
ራሳቸውን ለሚለዩት የመረጡትን መለየት ይሰጣቸዋል። ከእግዚአብሔር መለየት ሞት ነው ከብርሃንም መለየት ጨለማ
ነው..." በማለት ተናግሯል።
ጥያቄ:- እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ክፋት መፍጠር አይችልም ወይ?
እግዚአብሔር የፈጠረውን መልካም እንደሆነ አየ እንደተባለ ፍጥረት በዚህ መልኩ መፈጠሩ መልካም ነው። ሌሎች ኤቲስቶች
የሚያቀርቧቸው አማራጮች ልክ እንዳልሆኑ ለማሳየት ስንነሳ አሁን ያለው ፍጥረት ትክክለኛና እንከን የሌለበት
የእግዚአብሔር ስራ እንደሆነ በማመን ነው እንጂ ፍጥረትን እንዲህ ቢያደርገው ይሻላል እያሉ አስተያየት ለመስጠት
አይደለም።

አማራጮች ብለው የሚያቀርቡትም

1ኛ. ምንም ባይፈጠር

አሁን ያለው ዓለም ከሚኖር ምንም ባይፈጠር ይሻላል የሚሉ አሉ። ይህ አስተሳሰብ ከአንዳች ነገር (Something) ምንም
(nothing) ይሻላል የሚል ነው። ክፉ ነገር ከሚኖር ምንም ባይኖር ይሻላል ይላሉ። ይህ ሙግት በመጀመርያ ሁሉም ነገሮች
መልካም ሆነው እንደተፈጠሩ የሚዘነጋ ነው። "መልካም እንደሆነ አየ" እንዲል። ይህ መልካምነት እግዚአብሔር ባይፈጥረው
ኖሮ አይኖርም። በተጨማሪ ይህ አስተሳሰብ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም። ይህም አስተሳሰብ በውስጡ "ሞራል (ክፉና ደግ)
የሌለበት ዓለም መልካም ነው።" የሚል ነው። የሞራል ሁኔታ (Moral status) የሌለው ነገር መልካም ወይም መጥፎ
ሊባል አይችልም። የሞራል ሁኔታ የለውማ። ይህም ልክ "ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሀገር ሰላማዊ ነው" እንደማለት
ትርጉም የማይሰጥ ንግግር ነው። የሞራል ሁኔታ (Moral status) ብቻ ሳይሆን እውነታ (Reality) እንኳ የለውም።

2. ያለ ነጻ ፍጥረት ዓለምን ቢፈጥር

ይህም ማለት ዓለም ሁሉ በእንስሳትና የርሱን ፈቃድ በሚፈጽሙ ነጻነት በሌላቸው ሮቦቶች መሙላት ማለት ነው። ነገር ግን
ይህ አማራጭ እንደ መጀመርያው የሞራል ሁኔታ (Moral status) የለውም። ሞራል የሌለበትን ዓለም ደግሞ መልካም ነው
ማለት አንችልም። (That is non moral world can't be morally good world) ሌላው በዚህ አማራጭ ነጻ
ፍጥረታት ባሉበት ያለው የሞራል ዝቅጠት ክፉ ስራዎች ባይኖርም አካላዊ መበስበስ ሞት ግን አለ። እንስሳት ሞተው
ይበሰብሳሉ። ስለዚህም ነጻ ፍጥረት የሉም በማለት ብቻ አካላዊ ክፉ ነገር (Physical evil) አልቀረም። ይህም አንዱን ክፉ
ነገር በሌላው ክፉ ነገር መለወጥ እንጂ ክፉ ነገርን ያጠፋ አማራጭ አይደለም።

3. ነጻ ፍጥረት ሆነው ኃጢአትን የማያደርጉ መፍጠር አይችልም ወይ?

ነጻ ፈቃድ ኖሮ ኃጢአት አለመኖር ይቻላል። አዳም ከውድቀት በፊት በዚህ ኖሮ ነበር። ነገር ግን በዚሁ አልቀጠለም። በሎጂክ
የሚቻሉ (Logiaclly Possible) ያልናቸው ሁሉ ይደረጋሉ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የአደዋን ጦርነት ትሸነፍ ነበር
ማለት የሚቻል ነበር ጣልያን በጦር የተደራጀች ነበረችና በእውነታው ግን ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች። እንዲሁ ነጻ ፍጥረት
ሰው ኃጢአት አለመስራት ይችል ነበር ልክ በገነት እንደነበረው መስራቱ ግን እውነታው ነው። ኃጢአት እንዳይሰሩ
እግዚአብሔር መስጠት የሚችለው ዋስትና ምን ይሆን ነበር? ክፉን ነገር ለማድረግ ሲሉ ውሳኔያቸውን ማስቀየር ወይም
መልካሙን እንዲያደርግ ብቻ Programme ማድረግ። ሰው መልካሙን ለማድረግ ብቻ Programmed ቢሆን ኖሮ ነጻ
ፍጥረት ይባላልን? Programmed ከሆነና አማራጭ ከሌለው ነጻ ፈቃድ አለው ማለት አይቻልም። ክፉን ለማድረግ ሲል
ውሳኔውን እንዲቀይር ማድረግም ነጻነትን ይጋፋል። ወደ ተግባር ልንለውጠው ቀድመው የተጸነሱ ክፉ ሐሳቦች አልነበሩምን?
ይህም ነጻ ፈቃድን መጋፋት ነው። ነጻ ፍቃድ በጎውን ይሁን ክፉ በመምረጥ የሚደረግ ነውና።

4. ነጻ ፍጥረታትን ፈጥሮ ኃጢአትን የሚያደርጉ በኋላ ሁሉም የሚድኑ መንግስተ ሰማያትን እንዲወርሱ ማድረግ

ይህ አስተሳሰብ መሰረታዊ ስህተት አለበት። እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ መልካሙን እንዲመርጥ በማድረግ የሚቀይር
አድርጎ ያቀርባል። እግዚአብሔር ወደው ፈቅደው እንዲከተሉት እንጂ አስገድዶ እንድንወደው አያደርግም። ይህ ነጻ ፈቃድን
ማፍረስ ነውና። እግዚአብሔር የሰውን ምርጫን አክብሮ ይሰጣቸዋል። እርሱን ሳይወዱት ወደራሱ አስገድዶ የሚያመጣቸው
መንግስተ ሰማያት የሚያስገባቸው አይደለም። የገሃነመ እሳት ቁልፍ ከውስጡ በሰው ነጻ ፈቃድ ተቆልፏል እንዲሉ ነጻ
ፈቃዳችን ነው ወደ ሕይወት ይሁን ወደ ሞት የሚወስደን። "እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ"
ዘዳ. 30:19 ተብሏል።

ጥያቄ:- እግዚአብሔር ሰዎች ገሃነመ እሳት እንደሚገቡ አስቀድሞ እያወቀ ለምን ፈጠራቸው?
በመጀመርያ አስቀድሞ ማወቅ ማለት መወሰን ማለት አይደለም። እግዚአብሔር በጊዜኔ በቦታ ስለማይወሰን ሁሉን ነገር አሁን
የተደረገ ያህል ያውቃል። ለምሳሌ:- አንድ ሐኪም በሽተኛው የመሞቻው ጊዜ መድረሱን በማወቁ ለበሽተኛው መሞት
ተጠያቂ አናደርገውም። የእግዚአብሔርም ሁሉን አዋቂነት በነጻ ፈቃዳችን ለምናደርገው ስራ ተጠያቂ አያደርገውም።
ምርጫዬን አስቀድሞ ቢያውቅም እኔ መምረጥ አለብኝ። አስቀድሞ በማወቁ ምርጫዬ ላይ ተጽዕኖ የለውም። ነገር ግን
የምንመርጠውን አስቀድሞ ያውቃል ከጊረ በላይ ነውና። ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ሰው ገሃነመ እሳት እንደሚገባ ማወቁ ያ
ሰው ወደ ገሃነም እንዲወርድ የሚያደርግ አይደለም። ተጽፎልኛል የሚባል ነገርም የለም። የራሴን ሕይወት በነጻ ፈቃዴ
የምጽፈው ራሴው ነኝ። እግዚአብሔር ግን የምጽፈውን ወሰን የለሽ በሆነ ዕውቀቱ (ከጊዜ በላይ ነውና) ያውቀዋል። ስለዚህ
በመጀመርያ ማወቅ መወሰን አለመሆኑን እንረዳ። አንድ አስተማሪ አምና ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን ተማሪዎች ዘንድሮ
ቢያስተምርና የተማሪዎቹን ሁኔታና ደረጃ ስለሚያወቅ በዓመቱ መጀመርያ የሚያልፈውንና የሚወድቀውን ተማሪ ቢወስን
ፍትሐዊ ሊባል ይችላልን? ይህ ጥያቄው እግዚአብሔርን ኢ ፍትሐዊ አድርጎ በመሳል ነው የሚነሳው እግዚአብሔር ክፉ
እንድንሆን (ገሃነመ እሳት እንድንገባ) አስቀድሞ የወሰነ እንደሆነ ነው የሚገልጸው በራሳችን ሕይወት ውሳኔ የሌለን አድርጎ
የሚያቀርብ ነው። እግዚአብሔር ግን በእውነት የሚፈርድ ነው። ወደ ርሱ ርዳታን ሽተው የሚመጡትን ይረዳቸዋል። ያለ
ፈቃዳቸው ግን በዚህ መንገድ ተጓዙ ብሎ ነጻነታቸውን አያጠፋም። "እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ። ማንም ድምጼን ቢሰማ
ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከኔ ጋር ይበላል።" ራዕ.3:20 እንዲል
እግዚአብሔር ወደርሱ እንድንመጣ ነጻነታችን አውሮን እንዳንጠፋ ዘወትር የልባችንን በር ያንኳኳል። እግዚአብሔር ፍቅር
ነውና ወደ ህይወት እንድንደርስ የሚወድ ነው ምርጫውም ያለው በእጃችን ነው።

አንድ "A" የተባለ ሰው "B"ን ቢወልድ "B' ደግሞ "C" ን ቢወልድ አቶ ''A'' በነጻ ፈቃዱ እግዚአብሔርን ሳይከተል
የጥፋት መንገድን ቢመርጥና ከ "A" የተወለደው "B" ደግሞ እግዚአብሔርን ፈልጎ የሕይወትን መንገድ ቢከተል "C" ም
እንደ አባቱ የእግዚአብሔርን መንገድ ቢከተል "A" በፈቃዱ እግዚአብሔርን ስላልመረጠ አይፈጠርና "B" ና "C"
አይወለዱ ማለት ፍትሐዊ ይሆናልን? የአብርሃም አባት ታራ ጣኦትን የሚያመልክ ነበር:: ልጁ አብርሃም ግን እግዚአብሔርን
ፈልጎ አገኘ። ይስሐቅንም ወለደ ይስሐቅም የእግዚአብሔርን መንገድ የሚከተለውን ያዕቆብን ወለደ። ታራ በፈቃዱ አምልኮተ
ጣዖትን መርጦ ስለኖረ አይፈጠር ብለን በፈቃዳቸው እግዚአብሔርን የተከተሉ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብን እንዳይፈጠሩ
(እንዳይወለዱ) ማድረግ ፍትሐዊ ነውን?

ሌላው ገሃነመ እሳት እንደሚገባ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ አይፈጠር ምንል ከሆነ ለምን ያለ ሰው ፍጥረት እንድትኖር
ማድረግ ነው። ቃየን ባይፈጠር ኤሳው ባይፈጠር እያልን ምንሄድ ከሆነ ዓለምን ባዶ መሆኗ ነው። ይህ ደግሞ ምንም ባይፈጠር
ይሻላል ወደ የሚለውን አስተሳሰብ ይወስደናል። [ምንም ባይፈጠር የተሻለ ነው ለሚለው ከላይ ተመልሷል]

ጥያቄ:- ሰይጣን ብዙዎችን ያስታልና ለምን አይጠፋም?


ሰይጣን ሰውን ከአቅም በላይ በሆነ ነገር በማስገደድ ማሸነፍ አይችልም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ሰውን ሁሉ አንድም ሳያስቀር
ባጠፋ ነበር። ለዚህም ምስክር እርሱ (ጌታችን) እስኪፈቅድላቸው ድረስ ምንም ሊያደርጓቸው ያልቻሉትን እርያዎችን
ተመልከቱ። በማታለልና በተንኮል እጅ ሲያደርግ እንኳ ሁሉንም ድል አያደርግም። ሁል ጊዜም ድል አይቀናውም። ዲያብሎስ
ራሱ ዋና ተዋናይ ሆኖ ያለ የሌለ ኃይሉን አሰልፎ ተዋግቶት እንኳ ድል ሊያደርገው አልቻለም። ተሸንፎ አፍሮ ከጦርነቱ ተባረረ
እንጂ። በኃይል ድል ማድረግ ባይችልም በማታለልና በተንኮል ያስታል ስለዚህም ምክንያት ቢጠፋ ይሻል ነበር። ኢዮብ
ቢያሸንፈውም ቢከብርበትም አዳም ግን ተታልሎ ወድቆበታል። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዘሰ ከዚህ ዓለም ተወግዶ ቢሆን ኖሮ
ግን አዳም ፈጽሞ አይስትም ነበር። አሁን ግን ዲያብሎስ በዚህ ዓለም ስላለ አንዱ ቢያሸንፈው እንኳ ብዙዎችን ድል ያደርጋል።
አሥር ቢያሸንፉት እልፍ አእላፋትን ድል አድርጎ ይማርካል። እግዚአብሔር አጥፍቶት ቢሆን ኖር ግን እነዚህ እልፍ አእላፋት
ባልጠፉ ነበር ይላሉ። ስለዚህ ምን እንላለን? በመጀመርያ ደረጃ ድል ከሚሆኑት ይልቅ ድል የሚያደርጉት ቁጥራቸው ከእነዚያ
ያነሰ ቢሆንም እንኳ በጣም ከፍ ያለ ዋጋ አላቸው። "ትእዛዙን ከማይጠብቁ ከሽህ ሰዎች ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ
የሚያደረግ አንድ ይበልጣል።" ይላልና። ሢራ. 16:3::

ቀጥሎም ተቃዋሚው ቢወገድ ኖሮ ድል የሚያደርጉ ይጎዱ ነበር። ዲያብሎስ እንዳለ ብትተወዎ ሰነፎቹ የሚጎዱት ከጥንቁቆቹ
የተነሳ አይደለም በራሳቸው ስንፍና እንጂ። ስለ ሰነፎቹ ስትል ጠላትን እንዳይኖር ብታደርገው ግን ትጉሃኑ ስለ ሰነፎቹ
የመንፈሳቸውን ጥንካሬ በእግዚአብሔር ርዳታ የሚያሳዩበትን ዕድል አሳጣሃቸው፣ የክብርንም አክሊል እንዳያገኙ መንገዱን
ዘጋህባቸው ማለት ነው:: እስኪ ምንም ተቃዋሚ (ሰይጣን) የለም እንበል። ከርሱ ጋር የሚወዳደሩ ሁለት አትሌቶች አሉ
እንበል። ከእነዚህ አንዱ አብዝቶ የሚበ፣ ያልተዘጋጀ፣ ጥንካሬ የሌለው ደካማ ነው እንበል። ሌላኛው ግን ትጉህ ብዙ ጊዜውን
በልምምድና በሥልጠና ላይ ያጠፋና ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ በማድረግ ሲዘጋጅ የቆየ ነው እንበል። ከዚያም
ተቃዋሚውን ብታጠፋው (ውድድሩን ብትሰርዘው) ከነዚህ ከሁለቱ የጎዳሀው የትኛውን ነው? ያልተዘጋጀው ሰነፉን ነው?
ወይስ በመዘጋጀት ያን ያህል የደከመውን ትጉሁን? የተዘጋጀውን እንደሆነ ግልጽ ነው። ተቃዋሚው ቢወገድ ጠንካራው
በሰነፉ ተጎድቷልና። ሰነፉ ግን ከጎበዙ የተነሳ ምንም አይጎዳም። የሰነፉ አለመዘጋጀትና ስንፍና እንዳይገለጥ ሲባል ብቻ
ተቃዋሚው እንዳይኖር ቢደረግ ጠንካራው ስለ ሰነፉ ሲባል በሚደረገው ነገር ተጎዳ ማለት ነው። ምክንያቱም እርሱ ያን ያህል
ተዘጋጅቶ ለውድድር ቀርቦ ሳለ የሰነፉ ስንፍና እንዳይገለጥ ስትል ብቻ ውድድሩን በማስቀረትህ የድካሙን ፍሬ ሊያይ
የሚችልበትን ዕድል አሳጣኸው ማለት ነው። ስለዚህም ይህ አካሄድ ስንፍናን የሚያበረታ፣ ጥንካሬንና ራስን መግዛትን
የሚያዳክም ነው። ሰነፉ ውድድር ኖረም አልኖረም ጥንቱኑ በራሱ ስንፍና ወድቋልና። የተዘጋጀው ግን ተወዳድሮ በማሸነፍ
ዝግጅቱንና ድካሙን የሚያካክስበት ሽልማትና ክብር ያገኝ ነበር። የማይጠነቀቁት ሰዎች የሚጎዳቸው ዲያብሎስ ሳይሆን
የራሳቸው ስንፍና መሆኑን የበለጠ ትረዳ ዘንድ ለዚህ ጉዳይ ሌላ አስረጂ አመጣለሁ።

ዲያብሎስ በተፈጥሮው ሳይሆን በራሱ ምርጫና ድርጊት በጣም ክፉ ነው። ዲያብሎስ በተፈጥሮው ክፉ እንዳልሆነ ከስሙ
እንኳ ማወቅ ትችላለህ። (የመጀመርያ ስሙ ሳጥናኤል ነበር ትርጉሙም ቅሩበ እግዚአብሔር ማለት ነው) ዲያብሎሰሰ
ሐሰተኛና ሐሜተኛ ነው ሰውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲህ ብሎ አምቷልና:- "በውኑ ኢዮብ አንተን የሚያመልክ በከንቱ
ነውን? ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ዳብስ፣ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።" ኢዮ. 1:9-11:: እንደ ገናም
እግዚአብሔርን ለሰው አምቷል እንዲህ በማለት "የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች በጎቹንም አቃጠለች።" ኢዮ. 1:16::
ይህ መከራ የመጣበት ከሰማይ እግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ለማሳመንና አገልጋዩን ከጌታው ጌታውን ከአገልጋዩ ጋር
ለማጣላትና ለማለያየት ሞከረ። ነገር ግን አዳም ከእግዚአብሔር ጋር እንዳደረገው ሌላ አገልጋይ ከጌታው ጋር ሲጣላና ሲለያይ
ብታይ ዲያብሎስ ይህን ለማድረግ የቻለው በራሱ ኃይል ሳይሆን ከሰውዬው የግል ስንፍናና አለማስተዋል የተነሳ እንደሆነ
ታውቅ ዘንድ እዚህ ላይ ሞከረ እንጂ አልቻለም። (ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ ገጽ 141-143 የተወሰደ)

አዘጋጅ:-ተክለ ማርያም (ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት)

ተክለ ማርያም ነኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ!

You might also like