You are on page 1of 23

ክርስቲያናዊ ለአብነት ትምህርት

ተማሪዎች ሥልጠና
ሥነ ምግባር
ለመስጠት የተዘጋጀ
የማስተማሪያ ጽሑፍ

በቅዱሳት መካናት ልማትና


፰ ዓ.ም ማኅበራዊ አገልግሎት
ቦርድ ተዘጋጀ
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ማውጫ
ርእስ ገጽ

1. መግቢያ.................................................................................................................................................. 2
2. .ትርጉም................................................................................................................................................. 3
3. . የክርስቲያን ሥነ ምግባራት መለኪያዎች .......................................................................................... 4
4. ፫. ዐሠርቱ ቃላት ትእዛት ..................................................................................................................... 6
5. ፬. ስድስቱ ሕግጋተ ወንጌል ................................................................................................................ 11
6. ፭. ክርስቲያናዊ ግዴታዎች (ተግባራት) ............................................................................................. 14
7. ፮. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የትና እንዴት ይፈጸማል? .................................................................. 19
8. ፯. የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አስፈላጊነት ለምንድን ነው? ............................................................. 20
9. ማጠቃለያ............................................................................................................................................. 21
10. ዋቢ (ማጣቀሻ) መጻሕፍት .............................................................................................................. 22

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 1
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

1. መግቢያ
#
ክርቲያናዊ ሥነ ምግባር$ በሚለው በዚህ የትምህርት ክፍል ሰፊና ሙሉ የሆነ
ትምህርት አልቀረበም፡፡ ለመነሻ የሚሆንና ለጀማሪዎች ያህል ሊበቃ ይችላል ተብሎ የታሰበውን
ብቻ ባጭሩ አቅርበናል፡፡ ሌላውን በዚህ መጽሐፍ ዋቢ ተደርገው ከቀረቡትና ከሌሎችም ቅዱሳት
መጻሕፍት አንብቦ ማስፋፋት ከሁሉም በተለይም ከአሠልጣኞች ይጠበቃል፡፡

ትምህርቱ በ7 ሰባት ንዑሳት አርዕስት ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ እያንዳንዱንም በጣም


ጠቅለል አድርገን ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ እንደተለመደበት ጊዜ ሰዓት አጣጥሞና ጨማምሮ
ማቅረብ የመምህሩ ተግባር ነው፡፡ ሠልጣኞችም በነቃ ተሳትፎ ያልገባቸውን እየጠየቁ
በተመደበው ሰዓት ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው እንዲሄዱ ለማድረግ መምህሩ ምቹ የትምህርት
አሰጣጥ ማስተማርያ ዘዴዎችን መርጦ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ሠልጣኞች በቀናች ሃይማኖታቸው ላይ ትእዛዛትን ሕግጋገትን እንዲሁም ክርስቲያናዊ


ግዴታዎችን ወደ መፈጸም እንዲሸጋገሩ በፍቅርና በጥበብ መሳብ ይገባል፡፡ አቅልሎና አለሳልሶ
ማስተማር አስቸጋሪና ከባድ ሸክም መስሏቸው እንዳይደናገጡና ወደ ኋላም እንዳያፈገፍጉ
ለማድረግ ያስችላል፡፡ ለሚያምን የማይቻል ነገር እንደሌለና ሁሉም በእግዚአብሔር ቸርነትና
እርዳታ የሚሠሩ መሆናቸውን መግለጽ ይገባል፡፡

በጥቅሉ የክርስቲያን ሥነ ምግባራት ሁሉ መደምደሚያቸው ፍቅር ነው፡፡ ይኽውም፡-

1. #አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ፣ በፍጹም ነፍስህ ፣ በፍጹም ኃይልህ


ውደደው$ የሚለውና፤
2. #ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፡፡$ የምትለዋ ባንድነት ማለት ነው፡፡ ማቴ.22÷34-
41 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሕግጋት ታላቂቱ ፣ ፊተኛይቱ
የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ብሎ የመጀመሪያውንና የምትመስላት ብሎ ሁለተኛይቱን
ገልጦአቸዋል፡፡ በእነዚህ ሕግጋት ኦሪትና ነቢያት ትምህርታቸው እንደጸኑ
ነግሮናል፡፡

ሠልጣኞች ለራሳቸው ሲማሩም ሆነ ወደፊት ወገኖቻቸውን ሲያስተምሩ ይህን የፍቅር


ትርጉም በሚገባ በመረዳት መሆን አለበት፡፡ ሰው ለእግዚአብሔርና ለመሰሉ ለባንጀራው
ያለውን ፍቅር የሚገልጸው በአንደበት ሊሆን እንደማይችልም መገንዘብ ይገባል፡፡ #ልጆቼ ሆይ ፣
በምግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንፋቀር$ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 2
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት ይህንን ፍቅር የምንገልጥባቸው መንገዶች ናቸው፡፡1ዮሐ.3÷18


በተጨማሪም ሰው እግዚአብሔርን እወዳለሁ ካለ መውደዱ የሚታወቀው ትእዛዛቱን
በመፈጸምና በሥራ በምግባር እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ከወደዳችሁኝስ
#

ትእዛዜን ጠብቁ$ እንዲል ዮሐ.14÷15 መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ መለኪያውን


በአንደበት የሚገለጽ ፍቅር ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማቴ.7÷21-24

ስለዚህ አሠልጣኙም ሆነ ሠልጣኖቹ ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ሥልጠናው


የታቀደለትን ዐላማ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዋና ዋና
የክፍለ ትምህርቱ ዐላማዎችም ሠልጣኞች ከዚህ ሥልጠና በኋላ፡-

 የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ትርጉም ያብራራሉ፤


 የሥነ ምግባር መለኪያዎችን ይዘረዝራሉ፤
 ሥነ ምግባር በመለኪያዎቹ እንዴት እንደሚለካ ይናገራሉ፤
 ክርስቲያኖች ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን ያስረዳሉ፤
 ክርስያናዊ ሥነ ምግባር የትና እንዴት እንደሚፈጸም ያብራራሉ፤
 የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን አስፈላጊነት ይገልጻሉ የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን
ዐላማዎች መሠረት በማድረግ የእውቀት ፣ የክህሎትና የአመለካከት ለውጥ
አምጥተው ለሌሎች ወገኖቻችን እንዲተርፉ ለማድረግ የመምህሩ የአሠልጣኙ
ተግባር መተኪያ የማይገኝለት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

2. .ትርጉም
በዚህ መጽሐፍ የምንገልጸው የአጠቃላይ ርእሱ ትርጉም የተለያዩ ሦስት ቃላትን ለየብቻ
በማየትና በመፍታት ተጠቃሎ የሚቀርቡበት ሂደት ነው፡፡

 ክርስቲያን፡- የተጠመቀ ፣ በክርስቶስ ስም የተጠራ፣ የክርስቶስን ትምህርት የተቀበለ ፣


የክርስቶስ ቤተሰብ የሆነ የክርስቶስ ወገን ተብሎ ይተረጎማል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 3
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

 ሥን፡- መልክ ፣ ውበት ፣ ደምግባት ፣ ጌጥ ፣ ጥራት ፣ ጥዳት፣ መልካምነት ፣


ደግነት ፣ በጎነት ማለት ነው፡፡
 ምግባር ፡- ሥራ ፣ ፈጠራ ፣ ክንውን ማለት ነው፡፡

 ሥነ ምግባር፡- የሥራ መልካምነት መልካም ሥራ የሥራ ደግነት ደግ ሥራ


የሥራ በጎነት በጎ ሥራ ማለት ነው፡፡

 ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- የክርስቶስ ቤተሰብ ሊሠራው የሚገባ በጎ ስራ፤


o ከክርስቶስ ወገን የሚጠበቅ መልካም ሥራ፤
o ከተጠመቀና በክርስቶስ ስም ከሚጠራ አማኝ የሚጠበቅ ደግ ሥራ ማለት ነው፤

ከትርጉሙ መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያን የሆነ ሰው የሚጠበቅበት መልካም ደግ


ሥራ አለ ማለት ነው፡፡ ይህንኑ መልካምና የተወደደ ሥራ የምንማርበት ክፍለ ትምህርት
መሆኑን ጭምር የቃላቱ ትርጉም ያስረዳናል፡፡

3. . የክርስቲያን ሥነ ምግባራት መለኪያዎች


ከላይ በትርጉሙ እንዳየነው ከማንኛውም ክርስቲያን የሚጠበቀው መልካም ሥራ
መልካምነቱ የሚመዘነው ወይም የሚለካው በዓለማዊ ሚዛን አይደለም፡፡ የሚለካበት የራሱ
የሆነ መንፈሳዊ ሚዛን አለው፡፡ እነዚህንም በአጭሩ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡

ሀ. ሕገ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ሕግ


የእግዚአብሔር ሕግ የሚባለው ሰዎች እንዲያደርጉት ያዘዘበትንና እንዳያደርጉት
የከለከለበትን ነው፡፡ እንደ አጥርና እንደ ድንበር ያለ ሲሆን እንዳይጥሱትና እንዳያፈርሱት
እግዚአብሔር የወሰነውና በቅዱሳን አባቶቻተን በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ያስተላለፈው ትእዛዝ
ነው፡፡

አንድ ክርስቲያን የሠራው ሥራ በራሱም ሆነ በሌሎች ዘንድ መልካም መሆን አለመሆኑ


መመዘን የሚገባው ከእግዚአብሔር ሕግ አንጻር አኳያ ነው፡፡ የፈጸመው ተግባር አድርግ ብሎ
ካዘዘው ውስጥ ከሆነና አታድርግ ብሎ ከከለከለው ውስጥ ከሌለ ሥራው ያማረና የተወደደ ነው
ማለት ነው፡፡ የጽሑፍ ሕግ ከተሰጠበት ከኦሪት ዘመን ጀምሮ ስናይ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር
መመዘኛዎች 1ኛ. ሕገ ኦሪትና 2ኛ. ሕገ ወንጌል ናቸው፡፡ አንድ ክርስቲያን ሥነ ምግባሩ ያማረ
ነው የምንለው ከሕገ እግዚአብሔር አኳያ ከነዚህ ከሁለቱ ሕግጋት ጋር ተስማምቶ እስከተገኘ
ድረስ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የክርስቶስ ቤተሰብ ሆኖ ሳለ ሥራው ግን ከአባቱ
ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ካልተስማማ ቤተሰብነቱ ክርስቲያንነቱ ያጠራጥራል ማለት ነው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 4
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ይህንን በምሳሌ ማየቱ የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ አንድ ልጅ አባቱ የሚያዘውን ሰምቶ
የከለከለውን ትቶ የፈቀደለትን ብቻ እያደረገ ከኖረ አባቱ ደስ ይለዋል፡፡ ልጁም በአባቱ ዘንድ
የተወደደና የተመሰገነ ልጅ ይሆናል፡፡

በተቃራኒው አታደርግ ሲለው እያደገ፤ አድርግ ሲለው ደግሞ እምቢ ማለት ከጀመረ
በአባቱ ዘንድ የተጠላና የተረገመ ሆኖ ይቀራል፡፡ ተመክሮ ተመክሮ ካልተስተካከለም አባቱ ልጄ
አይደለህም ብሎ ከቤት ያባርረዋል፡፡ እግዚአብሔርም አባታችን ስለሆነ እንደዚሁ በሰጠን ትዕዛዝ
ሕግ መሠረት እንድንመላለስና ደስ እንድናሰኘው ይፈልጋል፡፡ በሕጉ መሠረት የሚሄድ ልጅ
ክርስቲያን ካገኘም እሱም ያከብረዋል፡፡ አመጸኛና የማይታዘዝ ልጅ ከሆነ ደግሞ መክሮ
አስመክሮ እንዲስተካከል ይጠራዋል፡፡ ከተመለሰና ሥራውን ካሳመረ ይወደዋል፤ ይምረዋልም፡፡
እምቢተኛ ከሆነ ደግሞ ከቤቱና ከርስቱ ከመንግሥተ ሰማያት ያባርረዋል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ሕግ ሲመዘን ዋጋ ቢስ እንዳይሆን ቀሎ


እንዳይገኝ ሥራዎቹን ሁሉ የእግዚአብሔር ሕግ በኦሪትም ሆነ በወንጌል ምን ይላል ብሎ
እየተጠነቀቀ እና ራሱን እየለካ እየመዘነ መሥራት አለበት ማለት ነው፡፡ ሥራው
እግዚአብሔርን ደስ ካሰኘ ሰዎችንም ደስ ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ደስ የማይላቸውም ሰዎች እንኳን
ቢኖሩ እነሱን ለማስደሰት ሲባል የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይገባም፡፡

ለ. የኅሊና የአዕምሮ ሕግ፡-


ሰው በተፈጥሮው ክፉውን ደጉን የሚለይበት ኅሊና አዕምሮ ከእግዚአብሔር
ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ኅሊናው ወይም አዕምሮው አውጥቶና አውርዶ የሚፈጽመው ሕግ የኅሊና
ሕግ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ሕጉን በጽሑፍ ከመስጠቱ በፊት የነበሩ ሰዎች እነ አብርሃም
ይመሩ የነበሩበት በኅሊና ሕግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ፈጣሪያቸውን እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ
ሰውንም ሳይበድሉና ሳያሳዝኑ መልካም ሥራን የሠሩ ብዙ የቀደሙ አባቶችና እናቶች አሉ፡፡
በዚህ ሥራቸውም ተጠቅመውበታልእንጂ አልተጎዱበትም፡፡ ለምሳሌ ያህልም ፡- ሄኖክ ፣ ኖኅ ፣
አብርሃም ፣ ሣራ ፣ ይስሐቅ ፣ ርብቃ ፣ ያዕቆብ ፣ ዮሴፍና የመሳሰሉትን ቅዱሳን አባቶች
ታሪክ ማንበብ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ መልካም ሥራን የሚሠራ ሰው በዚህም ምድር በሰው ዘንድ
በወዲያኛውም ዓለም በመንግሥተ ሰማያት ተጠቃሚ እንደሚሆን በማወቅ ለመልካም ሥራ
መነሣሣት ያስፈልጋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 5
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

በኅሊናችን የሚመላለሰውን ሃሳብ በመመርመር መልካም መስሎ የታየንንም ከላይ


ባየነው የእግዚአብሔር ሕግ ዳግመኛ ለክተነው መዝነነው የተስማማ ሆኖ ካገኘነው ብንሠራው
እንጠቀምበታለን፡፡ እዚህ ላይ መጠንቅቅ የሚገባው ሥጋችንን ደስ የሚያሰኝ ሐሳብ መልካም
የሆነ የኅሊና ሕግ ነው ብለን እንዳናስተናግደው እንዳንፈጽመው እና እንዳንሳሳት ነው፡፡
የኅሊና ሕግ ማለት የሥጋ ፈቃድ ማለት አይደለም፡፡ ከአዕምሮ የሚመነጭ ፣ የሥጋ ፈቃድን
የሚቃወመውና ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ተስማምቶ የሚኘውን ነው የኅሊና ሕግ የምንለው
በሌላ አነጋገር አንድ ሰው ጉቦ ሲበላ ፣ ሚስቱ ካልሆነች ሴት ጋር ሲማግጥ ሲያመነዝር ፣
በፍርድ ሲያዳላ ፣ የሰው ገንዘብ ሲሰርቅና ተመሳሳይ ተግባራትን ሲፈጽም ከውስጡ ከኅሊናው
ተው ልክ አይደለህም ተሳስተሃል እያለ የሚነግረው ነው የኅሊና ሕግ የሚባለው፡፡

ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን ውስጡን ኅሊናውን እያዳመጠ መልካም የሆነውን ሥራ


በቤተሰቡ ፣ በሥራ ቦታና በማኅበራዊ ሕይወት በሕብረተሰቡ መካከል ሁሉ ለመሥራት መቻል
አለበት፡፡ ቢሳሳትም እንኳን ንስሐ እየገባ በቀረው ጊዜ መልካም ለመሥራት መነሳሳት
ይገባዋል፡፡ ከዚሁም ጋር ከአባት ፣ ከአያት ፣ ከቅድመ አያቱ እና ከሽማግሌዎቹ በቃል
የተላለፈለት መልካም ሕግ ትዕዛዝ ካለ እንደተለመደው ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር መስማማቱን
አረጋግጦ ሊተገብረው ይገባል፡፡

4. ፫. ዐሠርቱ ቃላት ትእዛት


ከላይ እንደተመለከትነው የተጻፈው የእግዚአብሔር ሕግ በኦሪትና በወንጌል የሚገኝ
ነው፡፡ በቅድሚያ የምንመለከተው በኦሪት ዘመን ለእስራኤል በሙሴ አማካኝነት የተሰጡትን
አሥሩን ቃላት (ትዕዛዛት) ነው። እነዚህ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መለኪያዎች (መመዘኛዎች)
በመሆናቸው ባጭሩም ቢሆን ማወቅ ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ይጠበቅበታል። አሥሩ ቃላት
የሥነ ምግባር መለኪያ ብቻም ሳይሆኑ ለሃይማኖትና ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሕጎች
መሠረቶችም ናቸው። እነሆ÷ እንደሚከተለው ባጭሩ እናያቸዋለን።

ሀ/ #ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልክ$ ዘጸ.20÷3

ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ የተለያዩ ፍጥረታትን እንደ አምላክ እንዳያመልኩና


እንዳይቀበሉ የተሰጠ ትዕዛዝ ሕግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሕግ የሰጠው ለራሳችን ጥቅም
ነው፡፡ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ፍጥረት የፈጠረ ፣ አምነው ለሚያመልኩት ዋጋ
የሚሰጥ ፣ የማያምኑበትንና የሚያመልኩትን እሱን ትተው ሌሎች በሰማይና በምድር የሚገኙ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 6
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ፍጥረታትን የሚያመልኩትንና የማያመልኩትን ደግሞ ለዘለዓለም የሚቀጣ ፣ ሁሉን ማድረግ


የሚችል የሚሳነው ሊያደርገው የማይችለው የሌለ እሱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን አምነን
እንድንገዛለትና የሕይወት ባለቤት እንድንሆን ነው ይህን ትዕዛዝ ሕግ የሰጠን፡፡

ለ. #የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጠራ$ዘጸ.20÷7

ይህ ሁለተኛ ሕግ የእግዚአብሔርን ስም እንድናከብር የተሰጠ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው


ማለትም በሐሰት ፣ በመሐላ ፣ በመርገም ፣ በጨዋታ ፣ በቀልድ ፣ በድፍረትና በመሳሰሉት
ጊዜዎችና ቦታዎች ስሙን እንዳንጠራ የሚከለክል ሕግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ #አምላክህ
እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራው አያንጻውምና$ በማለት አያይዞ ነግሮናል፡፡ ይህም
ማለት ስሙን በከንቱ የሚጠራ ሰው ይቀጣል፤ ይፈረድበታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስሙን
በጸሎት ፣ በምስጋና ፣ በዝማሬ ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ጊዜዎችና ቦታዎች በክብር
በመጥራት ምሕረትና ይቅርታውን ደጅ ልንጠና ይገባናል፡፡

ሐ. #የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ$ ዘጸ.20÷8


ይህ ሕግ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ.2 ቁ2-3 በተጻፈው ላይ የተመሠረተ በስድስተኛው ቀን
ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራዉ ሥራ ሁሉ አረፈ፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛዋን
ቀን ባረካት ቀደሳትም፤ ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና፡፡ በማለት
የሰፈረውን የሚያስታውስና ሰውም ሥራውን በሌሎቹ ቀናት ሠርቶ በሰንበት ማረፍ እንዳለበት
የሚያሳስብ ነው፡፡ ሰንበትን ከሥጋዊ ሥራ በተለየ ሁኔታ መንፈሳዊ ሥራ እንድንሠራበት ነው
የተፈቀደልን፡፡ #ትቀድሳት ዘንድ አስብ$ ማለትም የተቀደሰ ሥራ ሥራባት የሚል መልእክትን
የያዘ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የተቀደሰ ሥራም፡- ምስጋና ፣ ቅዳሴ ፣ የተራበን በማብላት
፣ የተጠማን በማጠጣት እንግዳ መቀበል የታመመና የታሰረ መጠየቅ የታረዘ የተራቆተ ማልበስ
ቃለ እግዚአብሔርን መስማትና ማሰማት የመሳሉትን መንፈሳዊ ተግባራት ማከናወን ነው፡፡
ከኃጢአት ተለይቶ ንስሐ ገብቶ ቅዱስ ቁርባን ተቀብሎ የሚዋልባት ቀን ናት ሰንበት፡፡ ይቺ
ሰንበት ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜ ስትሆን በሐዲስ ኪዳን የተጨመረችን የክርስቲያኖች ሰንበት
የተባለች እሑድም ከሲኦል ባርነትና ከአጋንን ስቃይ የዳንንባትና ያረፍንባት ፣ ክርስቶስ
በትንሣኤ ያከበራት ቀን ናት፡፡ ሁለቱንም በመንፈሳዊ ተግባራት አጊጠን ውስጣችንንና
ውጪያችንን በንስሐና በቅድስና አሳምረን ልናከብራቸው የሚገቡ የተቀደሱ ዕለታት ናቸው፡፡

መ. #አባትህንና እናትህን አክብር$ ዘጸ.20÷12፡-


ወላጆች ለልጆቻቸው መገኛዎች ፣ አሳዳሪዎች ፣ መጋቢዎች ፣ አሳዳጊዎች ፣
ጠባቂዎችና አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ልጆቻቸው ሊወዷቸው ፣ ሊያከብሯቸው እና
ሊታዘዙዋቸው ይገባል፡፡ ይህ ሕግ ይህን የሚያስገነዝብ ሲሆን እግዚአብሔር አምላክህ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 7
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

በሚሰጥህ ምድር እድሜህ እንዲረዝም በሚል ማስጠንቀቂያ ያስረዋል፡፡ ይህ ማለት አባት


እናትን ማክበር በምድርም ዕድሜ ያረዝማል ነው፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን ሁሉ
የሚወስነውና መሠረት የሚሆነው የመከባበር ሕግ የሚመነጨው ከዚህ ትዕዛዝዝ ነው፡፡
ትኩረት የምንሰጥበት ዋነኛው ነገር እግዚአብሔር ወላጆቻቸውን በሚያከብሩና በሚታዘዙዋቸው
ልጆች ደስተኛ መሆኑን መግለጡ ነው፡፡ ይህን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቄላስያስ ሰዎች
በጻፈው መልእክቱ ሲገልጠው ልጆቼ ሆይ ለወላጆቻችሁ በሁሉ ታዘዙ እንዲህ ማድረግ
ይገባናል ይህም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና በማለት ነው፡፡ ቄላ.3÷20 ኤፌ 6÷1-4 ይህ
ትዕዛዝ በሥጋ የወለዱንን አባትና እናቶቻችንን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ እንደ አባትና እንደ
እናት የሚሆኑንን የዕድሜ ባለጸጋዎች ፣ የክርስትና አባትና እናት ፣ መምህሮቻችንንና
የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ትዕዛዝ ቃል ነው፡፡ እኛም ይህን አውቀን እንደሰማንና
እንደተማርን በዕለት ተዕለት ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወታችን ይህን ተግባር ለመፈጸም
መጣር ይጠበቅብናል፡፡

ሠ. #አትግደል$ ዘጸ.20÷13 ፡-
ይህ ትዕዛዝ በቀጥታ ክቡር ከሆነው ሕይወት ጋር የተገናኘ የተያያዘ ነው፡፡ ድርጊቱ ከሟች
በበለጠ የገዳዩን ዕድሜ ፣ ሕይወት 2 ኅሊና ፣ ሞራልና መጨረሻ የሚያበላሽ ታላቅ ኃጢአት
ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ሕንፃ እጅ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚገኝ ማንም ሰው
የሠራውን ሥራ ሌላው ተነስቶ ዝም ብሎ ቢያቃልልበትና ቢያፈርስበት ፀጥ የሚለው የለም፡፡
እግዚአብሔርም የእጅ ሥራውን ሕንፃውን የፈለገውን ያህል አመፀኛ እንኳን ቢሆን ከሕግ
ውጪ ማንም እንዲያፈርስበት አይፈልግም፡፡ የሚያደርጉት ሰዎች ካሉም እንኳን የፈጠራቸው
አምላክ እግዚአብሔር ይበቀልላቸዋል እንጂ ቸል ብሎ አይመለከትም፡፡ ሰው አየኝ አላኝ ተብሎ
በድብቅ እንኳን ግድያው ቢፈጸም፡-

 የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር፤


 የአጥፊው የገዳዩ ሰው ኅሊና፤
 በደሉ የተፈጸመበት ሰው ደም ነፍስ፤
 በዚያው የሚኖሩ ሥነ ፍጥረቶች ሁሉ ይመሰክሩበታል፡፡ እግዚአብሔርም እነዚህን
ምስክር አድርጎ ይቀጣዋል ይበቀለዋል፡፡

ሰው ሰውን የሚገድለው በሥጋው በአካሉ ብቻ አይደለም፡፡ ያለውን ጥራቱን በማሳጣት ፣


ሞራሉን በስደብ… በመስበር ፣ ከሃይማኖት በማውጣት በማጠራጠር ፣ ታሪኩን በሐሰት
በማበላሸ ወዘተ በመሳሰሉ ሕገ ወጥ ተግባራትም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ እነዚህ
ሁሉ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው እኛም ተመሳሳይ በሆኑና በተጠቀሱ የግድያ ተግባራት በቀጥታም ሆነ
በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳንሳተፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡

ረ. #አታመንዝር$ ዘጸ.20÷14
ይህ ሕግ የሰዎችን የኅሊና ነፃነትና የቤታቸውን ሰላም ለመጠበቅ ሲል እግዚአብሔር
የሰጠው ነው፡፡ ማመንዘር ወይም ዝሙት ማለት ነው ሰው አንድ ለአንድ በተቀደሰ ጋብቻ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 8
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ከተፈቀደለት የትዳር አጋሩ ጋር ከሚያደርገው ውጪ የሚሠራ የነውር እና የርኩሰት ሥራ


ነው፡፡ ሥጋዊ ፍላትን ካልተቆጣጠሩትና በአግባቡና በተፈቀደው መስመር ብቻ እንዲስተናገድ
ካላደረጉት ነፍስንም ሥጋንም ከሚጎዳ ዝሙት ይደርሳል፤ ወይም የዝሙት ምርኮኛ ያደርጋል፡፡

ማመንዘር በዚህ ዓለም ሥጋዊ ጤንንትንና ሕይወትን ለታላቅ ችግር ከማጋለጡም በላይ
ቤተሰብን የሚበትን ፣ ሰላምን የሚያናጋና ለማኅበራዊ ቀውስ የሚያጋልጥ አሳፋሪ ድርጊት
ነው፡፡ ከሚስት ውጪ ወንዱ የሚፈጽመውና ሴትም ከባልዋ ውጪ የምትሠራው የግብረ ሥጋ
ግንኙነት ነው ዝሙት የሚባለው፡፡ ያላገቡም ከማግባታቸው በፊት የሚያደርጉት የጾታ
የወንድና የሴት ግንኙነት በእግዚአብሔር የተፈቀደ አይደለም፡፡ ይህ ድርጊት በወዱየኛው
በሰማያዊው ዓለምም ወነደል ሆኖ መንግሥተ ተሰማይትን የሚከለክል እና ከእግዝአብሔር
ጋር የማይጣት ታላቅ በደል ኃጢአት ነው፡፡ ስለዙህ የተሳሳቱ በንስሐ ታርመው በቀጣይ
ሕይወታቸው እንዲስተካከሉ፤ ያልተሳሳቱም እንዳይሰሳቱና በቤተከርስትየን ሕግ መሠረተ
ጋብቻቸውን መሥርትው አንደሉ አንድ ተወስው በመጠንቀቅ እነዲኖር ልንነግራቸውና እኛም
ሠርተን በማሳየት ምሌ ልንሆናቸወ ይገባል፡፡

ሰ. #አትስረቅ$ ዘጸ .20÷÷15


ይህ ሕግ በዚህ ዓለም ሰዎች ሠርተው የማግኘት መብታቸውን እንዳያጡ ፣ የንብረት
የሀብት ባቤትነት መብትና ነጻነታቸውን እንዳይገፈፉ የሚከራከር ጥብቅና የሚቆም ነው፡፡
አንዱ የሌላውን ሀብትና ንብረት ባለሥልጣን ፣ ባለ ጉልበት ፣ ባለ ወገን ፣ ባለ ገንዘብ ፣ ባለ
ጊዜ ነኝ ብሎ ገፍቶ እንዳይቀማው የሚከለክል ሕግ ነው፡፡ በሌላም መንገድ አታሎም ሆነ
ተደብቆ አንዱ የአንዱን ንብረት ሀብት እንዳይወስድ ይከለክላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ
እንዳስታወቀው ሰው በላቡ በወዙ ወጥቶ ወርዶ በሚያገኘው ሀብት ብቻ እንዲተዳደር እንጂ
የሌላውን እጅ ጠባቂ እንዳይሆን የሚያሳስብ ሕግ ነው፡፡ አንድ ሰው ያልለፋበትን የሌላውን ሰው
ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ከቀማ እንደ ነፍስ ገዳይ መሆኑ ነው፡፡

እውነተኛ ሰው ክርስቲያን ለሌላው ይረዳል እንጂ የሌላውን አይቀማም ፣ አይዘርፍም


አያታልልም፡፡ አጋጣሚዎችን ተገን ምክንያት አድርጎ ጉቦ አይቀበልም፤ አራጣ ወለድ
አይቀበልም፤ በሚዛን አይበደልም የተበደረውን አያስቀርም አይክድም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የስርቆት መንገዶች ናቸውና፡፡ ስለዚህ የአንድን ሰው
አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ ንብረቶች እውቅና ሰጥቶና አክብሮ መኖርና የግድ አስፈላጊ ከሆነም
ገዝቶም ሆነ በቀጥታ ለምኖ ወይም አስፈቅዶ ባለቤቱን በማክበርና በማመስገን በሠላምና በፍቅር
መጠቀም እንጂ የስርቆትን መንገድ መከተል በዚህም ምድር በረከትን ያሳጣል፤ በወዲያናውም
ዓለም ከእግዚአብሔር ያጣላል፡፡ ክርስቲያኖችን ይህን በማወቅ ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን ከዚህ
አሳፋሪ ኃጢአት ለማራቅ መታገል አለባቸው፡፡

ሸ. #በባለእንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር$ ዘጸ.20÷16


ባልንጀራ የሚለው ቃል መሰሎቻችን የሰውን ዘር ሁሉ የሚመለከት ቃል ነው፡፡ ሐሰት
ማለት የሆነውን አልሆነም፤ ያልሆነውን ደግሞ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይህም የእውነት ተቃራኒ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 9
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ጠላት ነው፡፡ እንደሌሎቹም ሁሉ በሥጋና በነፍስ የሚያስጎዳ ኃጢአት ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን
ከገነት ያስወጣቸው ሐናንያና ሰጲራን ያስቀሰፋቸውን ሰዎችን በዓለማችን በርካታ ታላላቅ
ኃጢአቶችን ያሠራቸው ሐሰት ነው፡፡ የሰውን መብት ፣ ሕይወት ፣ ነጻነት ፣ የሚያሳጣ፣
ቤተሰብን የሚያፈርስ ማኅበራዊ ቀውስን የሚያመጣ ሀገርንም የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡
የሚወዱትን ለመጥቀም የማይወዱትን ለመጉዳት ተብሎ የሚፈጸም ምስክርነት ብቻ ሳይሆን
በእውነተኛ መሠረት ላይ ያልቆመን ክስ ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ በሐሰት ለጊዜው እውነተኞች
የተጎዱና የጠፉ ቢመስሉንም ዘላለማዊ ጥፋትን ተቀብለው የሞት ሞትን የሚሞቱት ግን ዛሬ
እንደጧት ጤዛ በማያረፍደው የሐሰት ደስታ የሚቀማጠሉት ኃጢአተኞች ናቸው፡፡ ይህንን
አውቆ እውነተኛ ሆኖ ከእውነት ጋር መከራ እየተቀበሉም ቢሆን ዘላለማዊዉን ደስታ ለማግኘት
ከሐሰት ተግባራት ሁሉ መራቅ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

ቀ. #የባልንጀራህን ሚስት ፣የባልንጀራህን ቤት አትመኝ$ ዘጸ.20÷17


አንድ ሰው የሱ ያልሆነውን ማንኛውንም ነገር ሀብት የራሱ እንዲሆን እንዳያስብ
እንዳይመኝ የሚያስጠነቅቅ ሕግ ነው፡፡ ክፉ ምኞች ከላይ በዝርዝር የያናቸውን ኃጢአቶች
ለመሠራት የሚያበቃቸው በልብ የሚጠነስስ ኃጢአት ነው፡፡ በሕግ የተከለከለውን ሁሉ
ለማድረግ የሚገፋፋ ፣ የሕግን ዳር ድንበር ለማስፈረስ አጥሩንም ለማስጣስ የሚያነሳሳ ታላቅ
በደል ነው፡፡

የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ሰው ከፍተኛውን ውጊያ እዚህ ላይ ካደረገና ካሸነፈ በሌሎች


ኃጢአቶች ላይ ድል አድራጊ ለመሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቶች በልብ ተፀንሰው በማደግ
የሚወለዱ ስለሆኑ ነው፡፡ አዳምን ከገነት ያወጣው ፣ አክአብ ናቡቴን እንዲገድል ያደረገው
ኤሳው ብኩርናውን እንዲሸጥ ያደረገውና ሌሎች ተመሳሳይና ታላላቅ ኃጢአቶች እንዲሠሩ
ያደረጋቸው የራስ ያልሆነውንና የሌላውን ሀብትና ንብረት መመኘት ነው፡፡

ስለዚህ የራሳችን በሆነው በተሰጠን መርካትን ትተን የሌላው ሚስት ፣ ሀብት ፣


ሥልጣን ፣ ዕውቀት ፣ ቤትና የመሳሰሉትን ለማግኘት መመኘት በራሱ ኃጢአት መሆኑንና ወደ
ባሰው የድርጊት ኃጢአት የሚያሸጋግር መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ በዚች ኃላፊና ጠፊ በሆነች
ምድር ላይም ሳንረካና ስንባዝን ከበረከትና ከሰላም ተራቁተን እንደምንኖርና ይቺ ዓለም ስታልፍ
እኛም ስንጠራ ዘላለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያሳጣን መሆኑን አውቀን ይህን
ከባድ ኃጢአትና የኃጢአቶች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ክፉ ምኞት በየጊዜው በመዋጋት ስንሸነፍም
ንስሐ እየገባን ልናስወግደው ይገባል፡፡

በ. #ባልንጀራህን እንደራስ አድርገህ ውደድ$ ዘሌ.19÷18


ሰው ለመሰሉ ለሰው ሊኖረው ስለሚገባ ፍቅርና አክብሮት የሚገልጽ ትዕዛዝ ነው፡፡
መቼም ራሱን የሚጠላ የለም፡፡ ሰው ራሱን የሚወደውን ያህል ሌላውን መሰሉን ከወደደ
ማኅበራዊ ቀውስ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ መለያየትና ጥላቻም ሥፍራ ቦታ አያገኙም፡፡
እግዚአብሔር በአርአያውና በመልኩ የፈጠረው የሰው ልጅ እርስ በርሱ በመዋደድ እንዲከባበርና
እንዲረዳዳ ያዘዘበት ይህ ሕግ የዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት መደምደሚያ ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 10
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ሰው መሰሉን እንደሱ ከወደደ ከላይ #አባት እናትህ አክብር$ ከሚለው ጀምሮ ያየናቸው ትዕዛዛት
ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስ #ባልንጀራውን የወደደ ግን ሕግን ሁሉ ፈጸመ…$ ያለው ሮሜ 14÷8-11

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህን በመልእከቱ ሲገልጠው #እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል
ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት ይህች ናት..$ እኛ ግን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን
እናውቃን፤ ባልንጀራችንን እንወዳለንና ባለንጀራውን የማይወድ ግን በጨለማ ይኖራል፡፡
ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነም ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ
እንዳማይኖር ታውቅላችሁ፡፡ እያለ ነው፡፡ (1ዮሐ3÷11-19) ቅዱስ ዮሐንስ እርስ በእርስ
መዋደድ የሚያስገኘውን ሰማያዊ ጥቅምና ጉዳት ገልጦ ካስቀመጠ በኋላ ቁጥር 16 ላይ
#
በዚህም ፍቅርን አወቅነው፤ እርሱ ራሱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጥቷልና፤ እኛም ስለባልንጀሮቻችን
ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል በማለት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውንም ተግባር (ሥራ)
ገልጦ አስተምሮናል፡፡

እንግዲህ ፍቅራችን ግብዝነት የሌለበት (የይስሙላ ያልሆነ) እና በሥራ የተገለጠ ሊሆን


ይገባዋል፡፡ ወገኖቻችን ተቸግረው እያለ ከንፈር መጠንና ኀዘናችንን በቃል ብቻ ገልጸን የምንሄድ
ከሆነ ክርስትናችን ከንቱ መሆኑ ነው፡፡ ክርስቲያን ተብለን ከተጠራን የክርስቶስን ምሳሌት
ተከትለን ልንሠራና የወገኖቻችንን ችግር በማቃለል ያለንን ፍቅር በሥራ መግለጥ
ይጠበቅብናል፡፡ አለበለዚያ ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ የተባልነውን አንርሳ፡፡ ነፍሰ ገዳይ ደግሞ
መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም ተብሏልና መንግሥቱን ወርሰን የዘለዓለም ሕይወት
እንድናገኝ እርስ በርሳችን በምግባርና በእውነት እንዋደድ፡፡ (ዮሐ.3÷18)

5. ፬. ስድስቱ ሕግጋተ ወንጌል


ሁለተኛው የተጻፈ ሕግ ብለን ከዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት ቀጥለን የምናየው ስድስቱን
የወንጌል ሕጎች ነው፡፡ በእነዚህ ላይ ተጨምረው እነዚያን አጥብቀውና አጠናክረው የተሰጡት
እነዚህ ሕጎች ወልደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ልጅ) ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ
ያስተማራቸው ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የቀደሙትን አስሩን ቃላተ ኦሪት በነቢዩ ሙሴ በኩል
ቢገልጣቸው እነዚህን ስድስቱን ሕግጋተ ወንጌል ግን ራሱ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ በተገለጠበት
ዘመን አስተምሮአቸዋል፡፡ እነዚህንም በአጭሩ እናያቸዋልን፡፡

ሀ. #በወንድምህ ላይ በከንቱ አትቆጣ$ (ማቴ.5÷22)


ይህ ሕግ (ትዕዛዝ) በኦሪት #አትግደል$ ተብሎ የተሰጠውን ሕግ የሚያጠብቅና ሰውን
ወደ ግድያ የሚያደርሰውን ተግባር የሚከለክል ነው፡፡ ይህም አባቶቻችን ችግር እንዳይደርስ
አርቆ ማጠር ነው የሚሉትን አባባል የሚገልጽ ነው፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የመጣው
የኦሪትን ሕግ ለመሻር ሳይሆን ለመፈጸምና ለማጥበቅ እውነተኛነታቸውምን ለማረጋገጥ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 11
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

መሆኑን ያሳያል፡፡ የሚገባ ቁጣ ስላለ #በከንቱ የሚቆጣ በማለት አስረግጦ ነገረን፡፡ የሚገባ
(ተገቢ) ቁጣ ሰዎችን ለማስተካከልና ለማረም የሚደረግና ከፍቅር የመነጨ በመሆኑ ጥቅም
እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ የሚሆነው በምቀኝነት ፣ በቅንዓት ፣ በዘረኝነት ፣ በስስት
፣ በትዕቢት እና በመሳሰሉት የጥላቻ መንፈሶች ላይ የሚመሠረት ቁጣ ግን ያንን ሰው
ማጥፋትን ወይም ማዋረድን ዓላማ ያደረገ ስለሚሆን በዚህ ዓለም ሆነ በወዲያኛውም ዓለም
ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንዳለው ማወቅ ይገባል፡፡ ቁጣው የሚያርፍበትን ሰው ለጊዜው በዚህ
ዓለም ቢጎዳውም ተቆጭው ግን በተለይም በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ኃጢአት ራሳችንን
እንድናርቅ የተሰጠን ትምህርት መሆኑን አውቀን ተግባራዊ ለማድረግ እንጣር፡፡ የተጣላው
ወይም የተጣላን ካለም በመታረቅ ሰላምን ለመመሥረት መሽቀዳዳም ይገባናል፡፡

ለ. #ወደ ሴት ተመልክተህ አትመኛት፤ አታመንዝርም$ (ማቴ.5÷28)


ይህም እንደላይኛው ሕግ አታመንዝር የሚለውን የኦሪት ሕግ የበለጠ የሚያጠብቀውና
ሰውን ወደ ዝሙት የሚያደርሰውን ምኞት እንድንዋጋ የሚያሳስበን ሕግ ነው፡፡ ምኞት ያዩትንና
የሰሙትን መውደድና መከተል ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚታየውና የሚሰማው አብዛኛው ነገር
ሰዎች ወደ ኃጢአት እንዳያዘነብሉ የሚያደርግ በመሆኑ ክፉ ምኞትን በምኞትነቱ እንዲቀር
ቢቻልም ክፉ ምኞት እንዳይፀነስ መታገሉ የክርስቲያኖች ሁሉ ተግባር እንደሆነ ነው
የተገለጸልን፡፡

ይህ ሕግ በተጨማሪ #የባለንጀራህ ሚስት ፣ ቤት አትመኝ$ የሚለውን የኦሪት ሕግ


የሚያጠናክር ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ይህንኑ አውቀን በምናውቃቸውና በምንሰማቸው ነገሮች
ተስበን ኃጢአት ወደመሥራት እንዳንደር ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ይህም ማለት ምንም ነገር
እንዳናይና እንዳንሰማ ማለት ሳይሆን ለዝሙትና ለኃጢአት ሆን ብለን በዓላማ እንዳናይና
እንዳንሰማ የሚከለክል መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡

ሐ. #ሚስትህን ያለ ዝሙት ምክንያት አትፍታት$ (ማቴ.5÷32)


ይህ ሕግ ቤተሰባዊ አንድነትን የሚያጠናክርና ቤተሰብ እንዳይበተንና ወደ ማኅበራዊ
ቀውስ ችግር እንዳያድግ የሚከለክል የደኅንነትና የሰላም ሕግ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን
ጋብቻውን በቤተክርስቲያን በተቀደሰ ብቻ እንዲመሠረት ያስተማረን አምላካችን #እግዚአብሔር
አንድ ያደረገውን ሰው አይለየውም$ በማለት ደጋግሞ ያስተማረንና ያስጠነቀቀን ከዚህኑ ሕግ
ጋር ተስማምቶ የሚሄድ ነው፡፡ (ማቴ.19÷6) ፊሪሳውያን ለጠየቁት የፍቺ ጥያቄ መድኃኒታች
ኢየሱስ ክርስቶስ በመለሰበት አንቀጹ #እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን
የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ያገባ ያመነዝራል፡፡$ በማለት ይህን
ትምህርት አጠናክሮ ገልጾታል፡፡ (ማቴ.19÷9)

ስለዚህ የባልና የሚስት ተዋሕዶ አንድነት በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነና


የዚያኑ ያህልም አንድነቱ ሲፈርስ እግዚአብሔር እንደሚያዝንና እንደሚቆጣ እንደሚፈርድም
አውቀን በትንሽ በትልቁ ጋብቻ እንዳይፈርስና እንዳይናጋ ቤተሰብም እንዳይበተን ሁላችንም
የድርሻችንን እንወጣ፡፡ የባልና ሚስት አንድነት (ትዳር) ሲፈርስ የሚከሰተውን የንብረት፣

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 12
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

የቤተሰብ ፣ የሥራ ኪሳራና ቀውስም እያሰብን ችግሮች ቢኖሩም በመቻቻል ለማለፍ ራሳችንን
እናዘጋጅ፡፡ ከምንም በላይ ሰማያዊውን ቅጣት አስበን ፈጣሪያችን እንዳያዝንብንና መንግሥቱን
እንዳይከለክለን ስንል ፍቺን ከእኛ እናርቅ፡፡ (ሚል.2÷13-17)

መ. #ፈጽመህ አትማል$ (ማቴ.5÷34)


ይህ ሕግ #የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ$ ተብሎ ከተሰጠን ሕግ ጋር
አብሮ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ በመሐላ ዙሪያ ቀደም ብሎ #መሐላችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ
እንጅ በሐሰት አትማሉ$ ተብሎ የተሰጠውን ሕግ የበለጠ ሲያጠናክረው #አዎን አዎን ወይም
አይደለም አይደለም$ በሌላ አነጋገር #እውነቱን እውነት ሐሰቱንም ሐሰት$ እንድንል የተነገረበት
አንቀጽ ነው፡፡ (ማቴ.5÷37) ከዚህ ውጪ በእግዚአብሔር በሚገለጥባቸው በሰማይ በምድርና
በኢየሩሳሌም (ቤተክርስያን) በራሳችንም እንኳን ቢሆን መማል እንደሌለብን የተሰጠ ሕግ
መሆኑን አውቀን በታዘዝነው መሠረት ብቻ መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡

ሠ. #ክፉን በክፉ አትቃወሙት$ (ማቴ.5÷39)


ይህ ሕግ ሆን ብለውም ሆነ ተሳስተው ክፉ የሚያደርጉብንን ሰዎች እንደእነሱ በክፋት
ምላሽ እንዳንሰጣቸውና ታግሰን ችለን እንድናልፋቸው አልፎ ተርፎም ለክፉ ንግራቸውም
ተግባራቸው ምላሾች በጎ መልካም ሊሆን እንደሚገባ ያሳየናል፡፡ ይህም ባልንጀራን እንደራስ
የመውደድ መገለጫ ይሆናል፡፡ ክፉን በመልካም ማሸነፍን ያስተማረን ክርስቶስ ይህን ሕግ
በተግባርም ፈጽሞ አሳይቶናል፡፡ በመስቀል እየሰደቡና እተየዘባበቱ ሊሚሰቅሉት አባት ሆይ
የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው በማለት ነው የመለሰው፡፡ #ሉቃ.23÷34$ እኛም
ልንከተለው የሚገባን ክርስቲያናዊ ሥራ ይህ ነው፡፡ ይህም ለክፉዎች ብድራት የሚከፍል
አምላክ መኖሩን ማመናችንና በቀልን ለሱ ሰጥተን ኃይላችን እሱ መሆኑን የምንመሰክርበት
አንዱ የሥነ ምግባራችን መለኪያ ነው፡፡

ረ. #ጠላቶቻችሁን ውደዱ$ (ማቴ.5÷44)


ይህ ሕግ #ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ$ የሚለውን የኦሪት ትዕዛዝ (ቃል) የበለጠ
የሚያጠብቅ ነው፡፡ ሰው ሰውን ለሚወድበት ሚዛኑ ሰብአዊ ተፈጥሮው (ሰው ሆኖ መፈጠሩ)
እንጂ ዘሩ ቋንቋው ቀለሙ ተግባሩ ዕውቀቱና የመሳሰሉት ሊሆኑ እንደማይገባ የሚገልጽ
ትዕዛዝ ነው፡፡ በኦሪት ሰው ባልንጀራውን የሚወደውን እንዲወድ የሚጠላውን እንዲጠላ ተጽፎ
ስለነበር ክርስቶስ ለበደሉን (ለጠላቶቻችን) ሊኖረን የሚገባው ምላሽ ጥላቻ ሳይሆን እውነተኛ
ፍቅር መሆኑን ገልጾ ያንን ቀላል የነበረውን የኦሪት ሕግ በጣም አጠበቀው፡፡ ወዳጅን መውደድ
ቀላል ነበርና፡፡ ዛሬ ግን (በሐዲስ ኪዳን) ጠላትንም መውደድ ቀላል ነበርና፡፡ ዛሬ ግን በሐዲስ
ኪዳን ጠላትንም መውደድ ተጨምሮ ተሰጠን፡፡ ይህን ሕግ ክርስቶስ በቃሉ ካስተማረን በኋላ
ለበደልነውና ጠላቶቹ ለነበርነው ለኛ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በመስጠት በሞቱ ይቅር
በማለት በተግባር ሕጉን ፈጽሞ አሳየን፡፡ እኛም ይጠሉናል (እንጠላቸዋለን) ለምንላቸው ሰዎች
በመልካም ንግግርና ተግባር ፍቅራችንን ልንገልጽ እንደሚገባ እናስታውስ፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 13
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

እንግዲህ ከዚህ በላይ ያየናቸውን 16 ሕግጋት (ትዕዛዛት) በዕለት ተዕለት ተግባራችን


ውስጥ ለመተግበር መነሳት (መታገል) ይጠበቅብናል፡፡

በተጨማሪም ፡-

 የተራበን ማብላት (ማቴ.25÷35)


 የተጠማን ማጠጣት (ማቴ.25÷35)
 እንግዳን መቀበል (ማቴ.25÷35)
 የተራቀተ ማልበስ (ማቴ.25÷36)
 የታመመን መጎብኘት (ማቴ.25÷36)
 የታሰረን መጠየቅ (ማቴ.25÷36)

የተባሉትን ክርስቲያናዊ ተግባራት ለመፈጸም እንትጋ፡፡ እነዚህ ከዚህ በላይ የተገለጡት


6ቱ ትዕዛዛት ሰው ሰውን እንደራሱ መውደዱ የሚመዘንባቸው የሚለካባቸው ተግባራት ናቸው፡፡
አንድ አምኖ የተጠመቀ ክርስቲያን በቤተሰቡም ሆነ በማኅበረሰቡ መካከል ሲመላለስ (ሲኖር)
እያንዳንዱ ተግባርን በነዚህ ሕግጋት መምራት ይጠበቅበታል፡፡

6. ፭. ክርስቲያናዊ ግዴታዎች (ተግባራት)


ከላይ የጠቀስናቸ ሁሉ ክርስቲያናዊ ግዴታዎች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ
ንዑስ ርእስ ልናያቸው የሚገቡ ጥቂት ነጥቦችን ክርስቲያኖች ግዴታዎች በማለት
አቅርበናቸዋል፡፡ ግዴታዎች ሰዎች መብቶቻቸውን ለማግኘት (ለማስከበር) የግድ ሊፈጽሟቸው
የሚገቡ ተግባራትን የሚገልጡ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞው እያንዳንዱ ክርስቲያን ክርስቶስ
በነፃነት የሰጠውን ሰማያዊ መብቱን (መንግሥተ ሰማያት መግባትን) ማግኘት ሊፈጽማቸው
የሚገቡ ክርስቲያናዊ ግዴታዎች አሉት፡፡ ዋና ዋናዎቹን ብቻ እንደሚከተው እናያቸዋለን፡፡

ሀ. ጸሎት ፡- ጸሎት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት መንገድ መሰላል ነው፡፡ ሰው


አምላኩን በነገሮች ሁሉ ማመስገን ይጠበቅበታል፡፡ ጸሎትሰ ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር ልዑል
ጸሎትስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሯት ቋንቋ ናት ስለዚህ ባለፊው እያመሰገንን በሚመጣው
እየለመን ስለመግቦቱና ጠብቆቱ መመስከር ይገባዋል፡፡ እያመሰገነም ይለምነዋል፡፡ ጧት በሰላም
ስላሳደረው ሲያመሰግን በሰላም እንዲያውለው ደግሞ ይማጸነዋል ይለምነዋል፡፡ በሌሎች
ጉዳዮችም እንዲሁ ነው፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነውና ይህን
መሥዋዕት ከማቅረብ ወደ ኋላ እንዳንል ያስፈልጋል፡፡

ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እሱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አውቀን በማንኛውም


ጉዳይ ወደ እሱ መጮህ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር
የሚያደርገው ግንኙነት ከተቋረጠ ከእሱ የሚጠበቀው (የሚሰጠው) ሁሉም ነገር አብሮ መቋረጡ
የግድ ነው፡፡ በተለይም ሰማያዊው ስጦታ በተቋረጠ ግንኙነት ውስጥ ይገኛል ብሎ ማሰብ ከብት
ካልዋለበት ቦታ ኩበት አገኛለሁ ብሎ የመድከም ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር በጸሎት

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 14
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ከፈጣሪያችን ጋር መገናኘት ይገባናል፡፡ እንድንጸልይ ያዘዘንም እሱው ፈጣሪያችን ክርስቶስ


ነው፡፡ (ማቴ.6÷5-16)

እንደ ቅዳሴ በመሳሰሉት የማኅበረ ጸሎቶች መሳተፍ ደግሞ ታላቅ ጸጋ የሚያስገኝ


ስለሆነ የቅዳሴውና የመሳሰለው ሁሉ ተሳታፊ በመሆን ከካህናት ጋር አብሮ መጸለይ ይገባናል፡፡
ጸልየን ፣ አስቀድሰን ፣ ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ተባርከን ስንመጣ ለመንግሥተ ሰማያት
የበለጠ ራሳችንን ማዘጋጀታችን እንደሆነ አንርሳ፡፡ የቤተሰብ ጸሎትን በጋራ በቤት ውስጥ
ማድረስ ይገባል፡፡ የግል ጸሎትም እንደ አቅማችን ስንችል በቤተክርስቲያን አለበለዚያም
በመኖሪያና በሥራ ቤታችን (አካባቢያችን) ማቅረብ ይገባናል፡፡

ለ. ጾም፡- ጾም በታወቀ (በተወሰነ) ጊዜ ሰውነታችን ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ


መከልከልና መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ግዴታ መመሪያዎቹ ሰዎች ለአባታችን
ለአዳምና ለእናታችን ለሔዋን በገነት የተሰጣቸው መመሪያ (ትዕዛዝ) ነው፡፡ ይህም ማለት
ከምስጋና ጸሎት ጋር አብረው እንዲፈጽሙት የተሰጣቸው ነው እንጅ ብቻውን አይደለም፡፡
እንዲበሉት የተፈቀደላቸው የመኖሩን ያህል እንዳይበሉ የተከለከሉትም ዕፅ ነበር፡፡ ያንን መጠበቅ
አቅቷቸው (ጾም አፍርሰው) ትዕዛዙን በመጣሳቸው አስቀድሞ እንደነገራቸው በሞት
ተቀጥተዋል፡፡ ዛሬም ጾም ለመጾም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች መቀጣታቸው አይቀርም፡፡

ስለዚህም የጾምን ጥቅም በማወቅ (በመረዳት) በሰው ዘንድ ለመታየት (ጾመኛ ነው


ለመባል) ሳይሆን እግዚአብሔር ያዘዘውና ቅዱሳን ጾመው የተጠቀሙበት ስለሆነ እኔም
ብጾመው አምላኬን ደስ አሰኝበታለሁ ብሎ መጾም ይጠቅመናል፡፡ ጾም ፡-

 የሥጋን ምኞት ፈቃድ ለማስታገስ ለማብረድ፤


 ሰውነታችን ለመልካም ሥራ የተመቻቸ እንዲሆን ለማድረግ፤
 በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ትሑት ለመሆን፤
 መብልና መጠጥን ተጠግቶ ከሚመጣ ፈተና ለመዳንና ለመሳሰሉት የሚጠቅም
የሥጋንና የነፍስን ቁስል የሚፈውስ መድኃኒት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ጾም ቶሎ
የሚታየንና የሚገባን ከሥጋ ፣ ከወተትና ከተዋጽኦዎቻቸው እንዲሁም ከሌሎች
ምግቦች ተከልክሎ መቆየት ብቻ ነው፡፡ የጾም ትርጉም ግን ከዚህም የተሰፋና የጠለቀ
ምሥጢር ያለው ነው፡፡

ጾም በውስጡ የሚይዛቸው ቁም ነገሮች ሕዋሳትን ክፉ ከሆነ ድርጊቶች ሐሳቦች


መከልከልን የሚጨምር ነው፡፡ ይህን ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊው ሊቅ በጾመ ድጓው በሚገባ
አብራርቶታል፡፡ ዓይን ክፉ ከማየት ፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት ፣ ልብ ክፉ ከማሰብና ሕዋሳት ሁሉ
እጅ ፣ እግር ፣ ምላስ ፣ አፍንጫን ሌሎችም ከክፉ ስሜቶች እንዲርቁ አሳስቧል፡፡ ጾም
የሚባለው እነዚህን ሁሉ ይጨምራል፡፡

ውጪን ያዋረዱ መስለው ከእህልና ከውሃ እየከለከሉ ግፍ የሚሠሩ ፣ ድሃ የሚበድሉ ፣


ፍርድ የሚያጓድሉ ፣ ጉቦ የሚቀበሉና የርኀራኄ ሥራን ለማድረግ የማይፈልጉ ጨካኞች የሆኑ
ሰዎች ጾም ከንቱ መሆኑን ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አስተምሮናል፡፡(ኢሳ.58÷1-13) ነቢዩ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 15
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ዘካርያስም እውነተኛውን ፍርድ በመፍረድ ፣ ምጽዋትንና ምሕረትን በማድረግ መበለቲቱንና


ድሃ አደጉን ስደተኛውንና ችግረኛውን ባለመበደል ፣ እንዲሁም አንዱ በአንዱ ላይ ክፉ ሐሳብ
ባለማሳብ የሚጾመውን ጾም እንጂ ከዚህ ውጪ የሆነውን ጾም እግዚአብሔር እንደማይቀበል
ነግሮናል፡፡ (ዘካ7÷1-ፍጻሜ)

ስለዚህ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ (ዮሐ.6÷26) ብሎ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ


እንዳስተማረን ለዚህ ዓለም ምግብ በመሳሳት እና ጣፋጭ ምግቦች በመውደድ እንዲሁም
የሥጋን ፍላጐት ሁሉ ለማሟላት በመጨነቅ ከጾም ትዕዛዝና ሥርዓት ውጪ ሆነን በሠይጣን
ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅና ከፈጣሪያችን እንዳንጣላ ጾምን ከሙሉ ትርጉምና ምሥጢሩ
ጋር እናዘውትር (እንጹም) ፡፡

ሐ. ስግደት፡- ስግደት ማለት ማጎንበስ ፣ ራስን ዝቅ ማድረግ ፣ መንበርከክ እና


ግንባርን መሬት ማስነካት (በግንባር መውደቅ) እና ስሞ መመለስ ማለት ነው፡፡ ይህም ለፈጣሪ
ክብር የመስጠትን ራስን ዝቅ የማድረግ የትሕትና ምልክት ነው፡፡ (ዕዝ.9÷15) ስግደት ፡-

1ኛ. የባሕርይ የአምልኮት ስግደትና


2ኛ. የጸጋ የአክበረት ስግደት በመባል በሁለት ይፈከላል

የባሕርይ (የአምልኮት) ስግደት የባሕርይ አምላክ ለሆነ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ
ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ሲሆን የጸጋ የአክብሮት ስግደት ደግሞ ለእመቤታችን ለቅድስት
ድንግል ማርያምና ለቅዱሳን ሁሉ የሚቀርበው ነው፡፡ ስግደቱ የባሕርይ ወይም የጸጋ መሆኑ
የሚታወቀውም በሰጋጁ (ስግደቱን በሚያቀርበው ሰው) ልብ እና ልብን በሚመረምር
በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ምልክት የለውም፡፡

ስለዚህ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ሲሰግዱ አምላክነቱን በማሰብ ለፈጣሪ የሚቀርብ


የመገዛት መገለጫ በሆነ መንገድ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ #ኑ÷ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ$
እንዲል (መዝ.94÷5) ለእርሱ የሚቀርብ ስግደት ለሌላ ለማንም ስለማይቀርብ ይህንኑ
በማመንና በልብ በማሰብ የራስን ክብር ሁሉ ለሱ አምላካዊ ክብር በማስገዛት በመስጠት
በፍርሃት መስገድ ይገባል፡፡ በዚሁ አንጻር ለቅዱሳን ስንሰግድ ደግሞ እግዚአብሔር በቸርነቱ
ያከበራቸውና የቀደሳቸው መሆኑን በማመን መስገድ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር ስለተሰጣቸው
የጸጋ ቅድስናና ክብር የጸጋ (የአክብሮት) ስግደት ነው የምንሰግድላቸው፡፡ ማኑሄ
የእግዚአብሔርን መልአክ #እንድናከብርህ ስምህ ማነው$ ብሎ ጠይቆ ማንነቱን ካወቀ በዟላ
ከሚስቱ ጋር ሰግዶለታል፡፡ (መሳ.13÷17-21) የቅዱሳንን ክብር ከምንገልጥባቸው መንገዶች
አንዱ ስግደት ስለሆነ የሚገባቸውን ስግደት በመስገድ የአማላጅነታቸውንና የቃል ኪዳናቸው
ተጠቃሚዎች መሆን የኛ ድርሻ ነው፡፡

መ. ምጽዋት ፡- ምጽዋት ማለት ስጦታ ፣ ችሮታ ፣ ልግስና ማለት ነው፡፡ ይህም


ማለት በተለያዩ ምክንያቶች ምግብ ላጡ ምግብ ፣ ልብስ ላጡ ልብስ ፣ መጠለያ ላጡ መጠለያ
እና ማናቸውንም አላስፈላጊ ነገሮች መርዳት ነው፡፡ ይህም በሚታይና በሚቆጠር (በሚሠፈር)

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 16
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ስጦታ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሰው ያጣውን የሌለውን ነገር ሁሉ መስጠትን ያካትታል፡፡


ለምሳሌ፡- ምክር ለሚያስፈልጋቸው ምክር መስጠትና የዕውቀትና የሙያ እገዛ (ድጋፍ)
ለሚያስፈልጋቸውም መርዳት ምጽዋት ነው፡፡

ይህ ተግባር ጾም ፣ ጸሎትንና ስግደትን የበለጠ የሚያሳምራቸው እና ተቀባይነት


እንዲኖራቸው የሚያስችላቸው ነው፡፡ (ኢሳ.58÷6-7፣ሆሴ6÷6) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ይህን የምሕረት ሥራ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲሠሩት ደጋግሞ አዟል፡፡ (ማቴ.5÷4
፣ማቴ.26÷11 ሉቃ.14÷12-15) ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ምንም ልዩነት ሳናደርግ ለሰዎች
ሁሉ ልንራራላቸው ይገባል፡፡ #ለድሃ የሚሰጥ አያጣም አይቸገርም ነዳያንን እንዳያይ ዓይኑን
የሚጨፍን /የሚመልስ/ ግን እጅግ ይረገማል (ይቸገራል)$ በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን
እንዳስተማረን በዚህም በዚያም በወዲያኛውም ዓለም እንዳንቸገርና እንዳይፈረድብን አዛኞችና
ለመርዳት የተዘጋጀን እንሁን፡፡ (ምሳ.28÷27 ምሳ.21÷12-14መዝ.40÷1-2) በፍርድ ቀንም
ጻድቃን እንዲፈረድላቸው ኃጥአንም እንዲፈረድባቸው የሚያደርገው መሠረታዊ ጉዳይ
ምጽዋትን መሠረት ያደረገ ሆኖ ይገኛል፡፡ (ማቴ.25÷31-ፍጻ ፣ መዝ.111÷9፣2ቆሮ 9÷6 ፍጻ)
በዚህ መሠረት ምጽዋት መስጠት ክርስቲያኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት በሚያደጉት
ጉዞ አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማወቅ በእግዚአብሔር፣ በእመቤታችን በቅዱሳንም ስም
መመጽወት ይገባናል፡፡

ሠ. አሥራት፡- ከአሥር እጅ አንዱን (አሥራት) ለቤተክርስቲያን መስጠትም የታዘዘ


ሕግ መሆኑን ማወቅና ዘጠኙን እጅ ለራስ አስቀርቶ ከአሥሩ አንዱን ከመቶው አሥሩን
ለእግዚአብሔር መስጠት ተገቢ ነው ይኽውም፡-

ሀ. በረከተ ሥጋን ለማግኘት (ምሳ.3÷9-10)


ለ. የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመፈጸም (ዘዳ.14÷22)
ሐ. ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን መፈጸሚያ
 ዘይት (ሰም) መብራት ዘጸ.27÷20
 እህል ለቁርባን (ስንዴ) ዘሌ.2÷1-3
 ዕጣን ለማዕጠንት (ዘጸ.30÷36) እና የመሳሰሉት

መ. ካናትን አገልጋዮች ለመርዳት

ሠ. ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ለሚኖሩ ችግረኞች መርጃ እንዲሁም ለመሳሰሉት


ተግባራት ሰው ጥሮ ግሮ ካገኘው ገንዘብም ሆነ እህል ወይም እንስሳ
ለእግዚአብሔር አሥራቱን እና በኩራቱን ለቤተክርስቲያን መስጠት አለበት፡፡

ከዚሁ ጋር ወደ ተቀደሱ ቦታዎች (አብያተ ክርስቲያናት) አቅም በፈቀደ መጠን ከስጦታ


ጋር በግልም ሆነ በጋራ እየተጓዙ መሳለምና በረከተ ሥጋ በከረተ ነፍስ ለማግኘት ይገባል፡፡
ይህም በሃይማኖትና በምግባር የሚያጠነክር ስለሆነ መለማመድና መተግበር ጥሩ ነው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 17
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ታላላቅና ንዑሳን በዓላትን እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ማክበር


የማይረሣ ጉዳይ ነው፡፡ በበዓላት ቀን ከሥጋዊ ሥራ ተለይቶ እየዘመሩ ፣ የእግዚአብሔርን ቃል
እየተማሩ ፣ እየቆረቡ ፣ እየጸለዩ ፣ እየሰገዱ ፣ እየመጸወቱና መልካም ሥራ አየሠሩ በመዋል
ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ መመለስ ይገባል፡፡

ቤተክርስቲያን ቅዳሜና እሑድን (ሰንበትን) ጨምሮ በርካታ የበዓል ቀናት ቢኖሩዋትም


በወር ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል በዓል በ12 ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል
በ21 እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በ29 ቀን ማንኛውም ክርስቲያን
እንዲያከብራቸው ታዛለች፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ በዓመቱ ውስጥ የሚከበሩ ዋና ዋናዎቹ በዓላትም
የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ብሥራት (ፅንሰት)፡- መጋቢት 29 ቀን ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከእሷ


እንደሚወለድ ለድንግል ማርያም የምሥራች የነገረበት ቀን ነው፡፡
2. ልደት፡- እግዚአብሔር ከእመቤታችን ሰው ሆኖ የተወለደበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም
ታህሣሥ 29 ቀን ይውላል፤
3. ጥምቀት፡- ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ቀን
ነው፡፡ በዓሉም ጥር 11 ቀን ይውላል፤
4. ደብረ ታቦር፡- ክርስቶስ የመለኮቱን ብርሃን አምላክነቱን የገለጠበት ቀን ነው፡፡
በዓሉም ነሐሴ 13 ቀን ይውላል፤
5. ሆሳዕና፡- ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ (ኢየሩሳሌም)
የገባበት ቀን ነው፡፡ በዓሉም ትንሣኤ 1 ሳምንት ሲቀረው በሚውለው እሑድ ቀን
ይውላል፤
6. ስቅለት፡- ክርስቶስ ስለ ዓለም (ስለ እኛ) ድኅነት በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለበት
መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ከትንሣኤ በፊት ያለው ዓርብ ላይ ይውላል፤
7. ትንሣኤ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ
ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን የተነሣበት ቀን ነው፤
8. ዕርገት፡- ክርስቶስ ከሙታን በተነሣ በአርባኛው ቀን የሚውል ወደ ሰማይ የወጣበት
በዓል ነው፡፡
9. ጰራቅሊጦስ፡- በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ባረገ በአስረኛው ቀን መድኃኔዓለም
ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለደቀመዛሙርቱ የላከበት ቀን ነው፡፡

እነዚህና ሌሎችም በዓላት በመማርና ከቅዱሳት መጻሕፍት አንብቦ በአግባቡ በመረዳት


ከላይ እንደገለጽነው በመልካምና መንፈሳዊ ሥራዎች ማክበር አቅም በፈቀደ መጠን የርኀራሄ
ሥራን በመሥራት ራስን ለሰማያዊው መንግሥት ማዘጋጀት የክርስቲያኖች ሁሉ ተግባር ሊሆን
ይገባል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 18
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

7. ፮. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የትና እንዴት ይፈጸማል?


በዚህ ዐቢይ ርእስ ስር ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ተራ በተራ ባጭር
እናያቸዋለን፡፡

ሀ. የት ይፈጸማሉ?
በዝርዝር ያየናቸውን ክርስቲያናዊ ተግባራት ሁሉ የምንፈጽማቸው በቅድስናው ሥፍራ
(በቤተክርስቲያን) ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ዳሩ ግን የክርስትና ሃይማኖት ማዕከላዊ
(ዋነኛ) ቦታ ቤተክርስቲያን ትሁን እንጂ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባራት ግን በሁሉም ቦታ እንደ
አስፈላጊነቱ ሊፈጸሙ ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያዊ ሥነ ምግባራትን ክርስቲያን የሆነ
ሰው፡-

 በመኖሪያ ቤት (በቤተሰቡ መካከል)


 በመኖሪያ አካባቢ
 በሥራ አካባቢ (በመሥሪያ ቤት)
 በተለያዩ ማኅበራት
 በሠርግ (ጋብቻ) ቦታ
 በሐዘን (ለቅሶ) ቤትና በመሳሰሉት ሁሉ በመፈጸም ታማኝነቱን መግለጥ (ማሳየት)
ይገባዋል፡፡

ለ. እንዴት ይፈጸማሉ?
ለዚህ መልስ የሚሆነውን በዝርዝር ለማየት በጣም ስለሚበዛ በአጭሩ እናየዋለን፡፡
ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ አፈጻጻም አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የጾም ፣ የጸሎት ወዘት ቀደም
ባሉት ገጾች የአንዳንዶቹ አፈጻጸም አብሮ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ አሁን በዚህ ክፍል ጥቅም
(የጋራ) የሆነውን አፈጻጸም ነው የምንመለከተው፡፡

 እግዚአብሔርን በመፍራትና በመውደድ፣


 የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም በማስታወስ፣
 የገሃነመ እሳትን ስቃይ በማሰብ፣
 የዚችን ዓለም ኃላፊነትና ጠፊነት ባለመርሳት፣
 በትሕትናና በታማኝነት፣
 በትዕግሥት በታታሪነት፣
 ራስን ለሰማዕትነት በማዘጋጀት፣
 በመንፈሳዊ ቅንዓት፣
 የሰይጣንን ክፋትና የእግዚአብሔርን ቸርነት በማነጻጻር፣
 ተስፋ ባለመቁረጥና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት በመታጀብ (በመታገዝ)
ሁሉንም ለእግዚአብሔር ክብር ብለን እንድናደርጋቸው ቤተክርስቲያን
አስተምራናለች፡፡ ስለዚህ እኛም ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጀምሮ ክርስትያናዊ ሥነ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 19
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

ምግባራትን በምንከውንባቸው (በምንፈጽማቸው) ቦታዎች ሁሉ ከላይ የተገለጹትን


በአዕምሮአችን እያወጣንና እያወረድን በሕይወታችንም (በኑሮአችን) ለመግለጥ
እየታገልን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡

8. ፯. የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አስፈላጊነት ለምንድን ነው?


በየርእሱ ስር መጠነኛ ጥቅሙም አብሮ ተገልጿል፡፡ ዋና ዋናዎቹን ደግመን ጥቅል በሆነ
መልኩ ባጭሩ እንደሚከተለው እናያለን፡-

 እምነት ያለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ብቻውን የሞተ ስለሆነና ምንም ጥቅም


ስለማይሰጥ፤ (ያዕ.2÷14-ፍጻ) የሰዎች ሩጫ ከንቱ እንዳይሆን፡፡
 ሥርዓት አልበኝነት እዳይስፋፋ (ሰዎች ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ እንዳይሆኑ)፤
 የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስ እንዳይስፋፋ፣
 ትዳር እንዳይፈርስና ቤተሰብ እንዳይበተን፣
 የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ፣
 ክርስቲያኖች ከቤተክርስቲያን እቅፍ እንዳይወጡ፣
 መተሳሰብና መረዳዳት ጠፍቶ ግለኝነት እንዳይነግሥ፣
 ሠላምና አንድነት ጠፍቶ ዘረኝነትና መለያየት እንዳይሰፍን ያደርጋሉ የሚሉትንና
የመሳሰሉትን ዋና ዋናዎቹ ጥቅሞች ሲሆኑ ዋናውና መሠረታዊው ጥቅሙ ሰዎች ሁሉ
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ባለቤት ሆነው የርስተ መንግሥተ ሰማያት ወራሾች
እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥቅሞች የተዘረዘሩ
በመሆናቸው እና ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም በሥጋ እንዳንጎዳና በወዲያኛውም ዓለም
ነፍሳችንን ለማዳን እንችል ዘንድ በሃይማኖታችን ጸንተን (ጠንክረን) ክርስቲያናዊ ሥነ
ምግባራትን ልንተገብራቸው ይገባል እንላለን፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 20
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

9. ማጠቃለያ
አባቶቻችን በተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳስተማሩን ሃይማኖት መሠረት ሲሆን
ሕንፃው (ግንቡ) እና ጣሪያው ደግሞ ሥነ ምግባር ነው፡፡ አንድ ቤት ጥሩ መሠረት ኖሮት
ግድግዳና ጣሪያ ከሌለው ቤት አይባልም፡፡ ምክንያቱም ከሌሊት ብርድና ከቀን የፀሐይ ግለት
ሊያድን አይችልምና፡፡ ምግባር የሌለውም ሃይማኖት እንዲሁ ከሰይጣን ፈተና ከኃጢአት
ወጥመድና ከሲኦል (ገሃነመ እሳት) ሊያድን በዚህም ዓለም በረከተ ሥጋን ሊያስገኝ አይችልም፡፡

ግድግዳውና ጣሪያው ያማረ ሆኖ መሠረቱ ያልጸና ቤትም ከነፋስ ፣ ከኃይለኛ ዝናብ ፣


ከጎርፍና ከማዕበል ሊያድንና የሚኖርበትን ሊያድን አይችልም፤ ጥሩ ሥነምግባር ይዘው
ትክክለኛ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከሰይጣን የተንኮል ነፋስ ፣ ከኃጢአትም
ማዕበል፣ ከፈቃደ ሥጋም ጎርፍ በተነሳባቸው ጊዜ ጸንተው ሊቋቋሙት አይችሉም፡፡ መልካም
ምግባራቸው ሁሉ ቢደማመር መሠረት (ሃይማኖት) ሆኖ ከጥፋት ሊያድናቸው አይችልም፡፡
(ማቴ.7÷24-28)

ስለዚህ ሁለቱንም ማለትም የቀናች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትንና የታዘዙትን


ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት አጣጥሞ መያዝና በመተግበር ራስን ከሥጋዊና መንፈሳዊ
(ምድራዊና ሰማያዊ) ጥፋት ማዳን (ማትረፍ) ይጠበቅብናል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 21
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር 2008ዓ.ም

10. ዋቢ (ማጣቀሻ) መጻሕፍት

1. መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ ፣2000 ፣አ/አ


2. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ፣ ማ/ቅ፣ 1997፣ አ/አ
3. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ፣ ማ/ቅ፣ 2001 ፣ አ/አ
4. ሥነ ምግባር ፣ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ ፣ 1995፣ አ/አ
5. ግብረ ገብነት ፣ አሥራት ገ/ማርያም ፣ 1995 ፣ አ/አ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አብነት ት/ቤቶች ክትትል ክፍል ገጽ 22

You might also like