Professional Documents
Culture Documents
ጸጋ
ጸጋ
በተለምዶ ፀጋ ሲባል ወደ አእምሮአችን የሚመጣ ሃሳብ አለ። ይህ ሃሳብ እንደ አደግንበት ማህረሰብ አስተሳሰብና እይታ ይወሰናል።
የእግዚአብሔር ቃል በሮሜ 12፡1 እንደሚነግረን ግን በአእምሮአችን መታደስ መለወጥ ይኖርብናል። ማለትም በተለምዶ የምናውቀውን
ነገር በእግዚአብሔር ቃል እውቀት መቀየር አለብን ማለት ነው። ሰው ፀጋ ማለት እንዲህና እንዲህ ነው ከሚለን ወጥተን የእግዚአብሔር
ቃል የሚለንን መቀበል አለብን።
ቃሎች ወሳኝ ናቸው። ሃሳብ ከቃላት ጋር የተያያዘ ነው። ድርጊትና እምነት ሃሳባችንን ይከተላል። የተሳሳተ መረዳት የተሳሳተ ልምምድን፤
የተሳሳተ ልምምድ ደግሞ የተሳሳተ ኑሮን ይወልዳል። የተሳሳተ ኑሮ ስንል እግዚአብሔር ልንኖረው ያላቀደልን ማለታችን ነው።
ፀጋን በእግዚአብሔር ቃል በመመልከት እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀልን የፀጋ ሙላት እንገባለን። ስለዚህ ፀጋ ምንድን ነው የሚለውን ቃል
በቃልነቱ ሳይሆን በተሸከመው ሃሳብ እንመልከተው።
2 ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡9 ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ
እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
10-11 አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም
አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።
ሐዋርያው ጳውሎስ መከራን እየተቀበለ ያለው ስለሚሰብከው ወንጌል እንደሆነና ይህ ወንጌል ምን እንደሆነ ለመንፈሳዊ ልጁ ጢሞቲዎስ
ሲነግረው፤ ወንጌል ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ለእኛ የተሰጠንን አሁን በጌታ በኢየሱስ መገለጥ እየታየ ያለውን የእግዚአብሔርን
ፀጋ የሚገልጥና ወደመታየት የሚያመጣ ነው ይላል። በዚህ ክፍል መሰረት ፀጋ የተሰጠን ከዘላለም ዘመናት በፊት እኛ በሌለንበት ጊዜ፤
ክፉም ሆነ ደግ ባላደረግንበት ጊዜ ነው።
ፀጋ እግዚአብሔር ለያዘልን የከበረ አሳብ እንድንበቃ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲያው የተሰጠን ሃብት ነው። እግዚአብሔር ሲጠራህ
አሁን ያለህበትን ሁኔታ አመሳክሮ ሳይሆን አስቀድሞ ከያዘልህ አሳብ አንፃር ነው። መጠራትህ በእርሱ ዘንድ እንደተያዘልህ አሳብና ፀጋ
መጠን ነው እንጅ እንደ አንተ ፍላጎት፤ እውቀት ወይም ችሎታ መጠን አይደለም። “ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ
እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤”
አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች በአለም በሃብት ወይም በተሰጥኦ የታወቁ ሰዎችን ያዩና ይህ ሰው ወይም ይህች ሴት ወደጌታ ቢመጡ
እንዴት ጌታን ያገለግሉ ነበር ብለው ይቀናሉ። ይህ ድንቅ የእግዚአብሔር ቃል ግን የሚነግረን ጥሪ የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ነው።
ሲጠራህ ስለአንተ ላሰበው አሳብ የሚያበቃህ ነገር ሁሉ በነፃ ያኔ ተዘጋጅቶልሃል። ጥሪው እንደ አሳቡና ፀጋው መጠን ነው።
እግዚአብሔር የሰውን የታመቀ ችሎታና ብቃት አስቀድሞ አይቶ ሳይሆን ሰውን የሚጠራው ለጠራው ሰው ምን እንደሚሰጠውና
በሰጠው ነገር ምን እንዲሆን አስቦ ነው።
2. ፀጋ የእግዚአብሔር አምላክ ብቻ የነበረውን ነገር አንተ በክርስቶስ እንድትካፈል የተዘጋጀ መንገድ ነው።
ጳውሎስ እንዳለው ሕይወትና አለመጥፋት የፀጋው ውጤቶች ናቸው። ሕይወትና አለመጥፋት ወይም ኢመዋቲነት የአምላክ ባህሪ እንጅ
የፍጡር ባሕሪ አይደለም። ይህን ባህሪ ለአንተ በነፃ ሲያካፍልህ ፀጋ ይባላል።
እግዚአብሔር በባህሪው ጻድቅ ሆኖ ሳለ በክርስቶስ ስራ አማካይነት ይህንን የጽድቅ ባህሪውን ሲያካፍልህ አንተ ጻድቅ ትሆናለህ።
የተካፈልከው ጽድቅ ፀጋ ይባላል። የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ ስትካፈል በጸጋው ጸደቅህ። ቀጥሎ ያለውን ክፍል እንመልከት፡
ወደ ሮሜ ሰዎች 3፡21 አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ 22 እርሱም፥ ለሚያምኑ
ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤
23 ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤
24 በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።
እግዚአብሔር ዘላለማዊ አምላክ ሆኖ እያለ አንተ በክርስቶስ አማካይነት ይህን የዘላለም ሕይወት ስትቀበል ዘላለማዊ ትሆናለህ።
ዘላለማዊ ሕይወት ጸጋ ነው። “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ
ከእናንተ አይደለም፤” ኤፌ 2፡8 በአጠቃላይ እግዚአብሔር የሆነውንና ያለውን እንድትካፈል የሚያስችልህ ፀጋ ይባላል። ይህም ጸጋ
የተሰጠን እግዚአብሔር ለእኛ አስቀድሞ እንደአሰበልን አሳብ መጠን ነው። ይህ አስቀድሞ የታሰበ አሳብ ምንድን ነው ? የእግዚአብሔርን
በጸጋው በመካፈል እርሱን መምሰል ነው።
በዚህ ክፍል ያለውን እውነት ጠቅለል አድርገን ብናየው እንዲህ ማለት እንችላለን
እግዚአብሄር እኛን እጅግ ትልቅ በሆነ ፍቅር ወዶናል። ሆኖም ግን በበደላችን ሙታን ስለነበርን ይህን ፍቅሩን ለማርካት አልቻለም ።
ከቸርነቱ ብዛት የተነሳ ልጁን በእኛ ቦታ እንዲሞትልን አሳልፎ በመስጠት ከሞት አዳኖን አስቀድሞ ለአሰበልን አሳብ አበቃን። ይህን
ያደረገው ሞት ለሚገባን ለእኛ እንዲሁ ባደረገው ነገር የፀጋውን ብዛት ያሳይ ዘንድ ነው።
አጋፔ ፍቅር ከተወዳጁ ለመወደዱ ምንም ምክንያት ሳይኖር ከወዳጁ ፍላጎት የመነጨ ፍቅር ነው። የአንድ አቅጣጫ ፍቅር ነው።
ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ያለ ፍቅር ነው። እግዚአብሔር ሰውን ለመውደድ ከሰው አስቀድሞ ያየው ምክንያት የለም። ሰው
የሚጠበቅበት ለዚህ ፍቅር ምላሽ መስጠት ብቻ ነው።
ፀጋም እንዲሁ ነው። በጎነት የተደረገለት ሰው በጎነት እንዲደረግለት የሚያስችል ምንም ምክንያት ሳይኖር የሰጪው ፍቅር ምክንያት ሆኖ
የሚደረግ ቸርነት ነው።
የመወያያ ጥያቄዎች
የማዛመድ ጥያቄዎች
1. በሮሜ 6፡14 ከፀጋ በታች እንጅ ከህግ በታች አይደላችሁም ይላል። ይህን ከአንተ የክርስትና ሕይወት ኑሮ ጋር እንዴት
ታየዋለህ?
2. እግዚአብሔር ከእርሱ በሆነ ነገር ለእርሱ እንድንኖር ከፈለገ አሁን ከእርሱ በሆነ ነገር እየኖርክ ነው?
3. ከእርሱ በሆነው ነገር በሁሉም የሕይወት ዙሪያህ መኖር ብትጀምር ምን አይነት ሰው የምትሆን ይመስልሃል?