You are on page 1of 5

በኃይለማሪያም ይርጋ፡ ዓቃቤ ህግ

hihoney3@gmail.com
 መንደርደሪያ
ሰሞኑን የቤት አከራዮቼ ከወትሮው በተለየ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እሰጣ አገባ ውስጥ ገብተው ሲነታረኩ እሰማለሁ እኔም የፀቡ መነሻ ምን
እንደሆነ እና በተቻለኝ ለመገላገል ወደ መኖሪያ ቤታቸው ጎራ ብዬ ስለተፈጠረው ነገር ስጠይቅ ባል ቀደም በማለት “እንደምታውቀው በከተማ
ግብርና ተሰማርተን ውጤታማ ሆነናል ሆኖም ግን ባለቤቴ እንደዚህ ለፍተን ባንክ ያስቀመጥነውን ገንዘብ አውጥተን ጦማር አግሮ ኢንዱስትሪ
አክስዮን ማሕበር በግብርና የንግድ ዘርፍ በታወቁ ሙሁራን በምስረታ ላይ ስለሆነ የአክሲዮን ድርሻ እንግዛ እያለች መውጫ መግቢያ አሳጣችኝ፡፡
እኔ ግን ማህበሩ ወደፊት ቢከስር እና እዳ ከሶስተኛ ወገን ቢኖርበት ያፈራሁትን ንብረት ለእዳ መክፈያ አድርጌ ልጆቼን ሜዳ ላይ አልጥልም ነው
የምለው፡፡” እንግዲህ እኔም የህግ ባለሙያ እንደመሆኔ ይህ አይነት ክርክር በሌሎች ሰዎች ዘንድ በሰፊው ይኖራል የሚል ግምት በመያዝ 
የአክሲዮን ማህበር አጠቃላይ ይዘት ጥልቅ እና ውስብስብ ቢሆንም ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ መሰረታዊ ጉዳዮችን በ 1952 ዓ/ም ስራ ላይ ከዋለው
የሀገራችን የንግድ ህግ አንጻር እንመለከታለን፡፡

የንግድ ህጋችን አንዱ ዓላማ ለንግዱ ማህበረሰብ አማራጭ የንግድ አደረጃጀትን ማቅረብ ሲሆን ግቡም የንግድ ማህበረሰቡ ወዶ እና ፈቅዶ እንደ
ልዩ ፍላጎቱ፣እንደ ካፒታል አቅሙ፣የሽሪኮቹን አቀራረብና የሃላፊነት ወሰኑን መሰረት በማድረግ በመደራጀት የንግድ ስራ እንዲከውኑ ለማድረግ
ነው ይህንንም ለማድረግ ይቻል ዘንድ የንግድ ህጉ 6 የተለያዩ የንግድ ማህበራት አይነቶችን አስቀምጧል ከነዚህም ማሀከል የአክሲዮን ካምፓኒ
(ማህበር) አንዱ ነው፡፡ (የንግድ ህግ አንቀጽ 212 ይመለከቷል፡፡)

 የአክሲዮን ማህበር ፋይዳ


የአክሲዮን ማህበራት በሃገራችን ብሎም በክልላችን መበራከት ሀገራዊ እና ግለሰባዊ ፋይዳ አለው፡፡ ሀገራዊ ፋይዳውን ስናይ አክሲዮን ማህበር
ትልልቅና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ የንግድ ዘርፎች(ለምሳሌ ባንክ፣መድን ድርጅት፣በግብርና ዘርፍ፣በቤቶች ግንባታ ወዘተ ) ላይ
ለመሰማራት የሚረዳ የማህበር አይነት በመሆኑ የእነዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በሃገራችን መፈጠር ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ
ለመሰለፍ እያደረገች ያለውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል፤ በሌላ በኩል የግለሰቦችን ስራ ፈጣሪነት ያበረታታል፡፡ ይህ ሲባል ግለሰቦች የሀገርን
ኢኮኖሚ እድገት ሊያፋጥን የሚችል የንግድ ሃሳብ አመንጭተው ካፒታል ከህዝቡ በመሰብሰብ ለመስራት የሚያስችል በመሆኑ ሙያዊ
ብቃታቸውን ተጠቅመው የሚሰሩ ስራ ፈጣሪዎች ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ የሚያበረታታ ሲሆን ለማህበሩ መፈጠር የደም ስር የሆነውን
ካፒታል ያዋጡ ሰዎች ደግሞ ወደ ፊት ማህበሩ የሚያስገኘውን ትርፍ የድርሻቸውን በመውሰድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን
እንዲፈቱ ያስችላል፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እየተመረቁ የሚወጡ ወጣት ሙሁራኖች የእነዚህ ግዙፍ አክሲዮን ማህበራት መመስረት ሰፊ የስራ እድል
ይፈጥርላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አክሲዮን ማህበር በለሀብቱን (capitalist) ከስራ ፈጣሪ (entrepreneur) ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ጠቀሜታው
የጎላ ነው ፡፡

 ትርጉም
አክሲዮን ማህበር ማለት ቢያንስ በአምስት ሰዎች መካከል የሚቋቋም፣የህግ ሰውነት ያለው፣ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዮኖች የተከፋፈለ
እና የአባላቱ ኃላፊነት ለኩባንያው ካፒታል ባዋጡት ወይም በሚያዋጡት መጠን የተወሰነ የንግድ ማህበር ማለት ነው፡፡ (የንግድ ህግ አንቀጽ
210(2), 304, 307(1) ይመለከቷል)፡፡ ከዚህ ትርጉም ውስጥ አክሲዮን ማህበር 4 መሠረታዊ ባህሪያት እንዳሉት መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህንም
በቅደም ተከተል እናያለን፡፡

1. የአባላቱ ብዛት ከአምስት ሰዎች የማያንስ መሆኑ


አንድ የአክሲዮን ማህበር ሲመሰረት ዝቅተኛ የመስራች አባላት ብዛት አምስት ሰዎች የሚያስፈልጉት ሲሆን ከፍተኛው የአባላት ብዛት ጣሪያው
ያልተገደበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ባህሪው ደግሞ ከሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይለየዋል፡፡ ምክንያቱም የኋለኛው የአባላቱ ዝቅተኛ
ብዛት ከሁለት የማያንስ ሲሆን ከፍተኛው የአባላት ብዛቱም በ 50 ሰዎች ብቻ የተገደበ እና የካፒታሉ ዝቅተኛ መነሻ ደግሞ ከ 15 ሺህ ብር ማነስ
የለበትም፡፡ (አንቀጽ 510(2) እና 512(1) ይመለከቷል)

2. ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዬኖች የተከፋፈለ መሆኑ


የአክሲዬን ማህበሩ ካፒታል አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዬን የተከፋፈለ መሆን እንዳለበት ከትርጉሙ መረዳት ይቻላል ይህም ማለት የአክሲዮን
ማህበሩ ምስረታ ተግባር የሚጀምረው ካፒታሉን፣የአንድ አክሲዮን አቻ ዋጋ እና ካፒታሉ በስንት አክሲዮን እንደሚከፋፈል በመወሰን ቢሆንም
የካፒታሉ መነሻ ደግሞ ከ 50 ሺህ ብር ማነስ የለበትም፡፡(አንቀጽ 306 ይመለከቷል፡፡

  3.  የአባላቱ ሃላፊነት የተወሰነ መሆኑ


የአክሲዮን ማህበር ሌላኛው ገፅታ ደግሞ ማህበሩ ከሦስተኛ ወገኖች ማለትም ከአበዳሪዎች፣ከደንበኞቹ እና ከሠራተኞቹ ወ.ዘ.ተረፈ ጋር
በሚያደርገው ግንኙነት ጉዳት ሊያደርሥ ይችላል በዚህ ወቅት የማህበሩ አባላት (ባለአክሲዮኖች) ሃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለውን
ለመረዳት በንግድ ህጋችን አንቀፅ 304(2) መሰረት የማህበሩ አባላት ሃላፊነት ለማህበሩ ካፒታል ባዋጡት ወይም በሚያዋጡት መጠን ተጠያቂ
እንደሚሆኑ ይደነግጋል:: ይህም ማለት አባላቱ ማህበሩ ሲመሠረት ወይም ከተመሰረተ በኋላ ለሽያጭ ከቀረበው የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ በገዙት
የአክሲዮን መጠን ብቻ ተጠያቂ የሚሆኑ ሲሆን አባሉ የሚጠበቅበትን መዋጮ ያልከፈለ እንደሆነ አክሲዮን ማህበሩ በእዳ ሲያዝ እንዲከፍል
ይገደዳል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩ ሃብት ጉዳቱን ለመካስ በቂ ሆኖ ባይገኝ ወደ ባለአክሲዮኖቹ ንብረት መሄድ አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ
የአባላቱ የግል እዳ ከኩባንያው ሃብት አይከፈልም፡፡
የአባላቱ ሃላፊነት መወሰን ግለሰባዊ እና ሃገራዊ አላማዎችን ለማሳካት ነው፡፡ ግለሰባዊ አላማውን ስናይ ሰዎች ሃላፊነትን ፈርተው ገንዘባቸውን
ቀብረው እንዳይቀሩ እና አውጥተው ለንግድ እንዲያውሉት ለማበረታታት ነው፡፡ በመሰረቱ ካፒታል መድቦ ወደ ንግድ የሚገባ ሰው ለንግድ
የመደበው ገንዘብ እና ጉልበት ትርፍ ማስገኘቱ ቀርቶ ሲከስር ወይም ለእዳ መክፈያነት ሲውል ጉዳቱ ቀላል አይደልም፡፡ በተጨማሪም ይህ ሳያንስ
እንደገና ከንግድ ስራው ልይቶ ያስቀረውን የግል ሃብቱ ለንግዱ እዳ መክፈያ ይዋል ቢባል ፍተሃዊ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የሀላፊነት መወሰን
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ሃገራዊ ሲሆን ይህም ሀላፊነት ካልተወሰነ ሰው ወደ ንግድ እንቅስቃሴ ለመግባት ፋቃደኛ ስለማይሆን አገልግሎት
አይስፋፋም፣የስራ እድል አይፈጠርም፣ለመንግስት ግብር የሚሆን ገቢ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም ለሀገር ጥቅም ወይም ኢንቨስትመንትን
ለማበረታታት ሲባል የአክሲዮን ማህበሩ አባላት ሀላፊነት በገዙት አክሲዮን ልክ የተወሰነ ይሆናል፡፡

4. የህግ ሰውነት
በንግድ ህጋችን ውስጥ ከአሽሙር ሽርክና ማኅበር በሥተቀር የንግድ ማህበራት የህግ ሰውነት እንደሚኖራቸው በአንቀጽ 210(2) በግልፅ
ተደንግጓል፡፡ የህግ ሰውነት ዋና አላማ አንድ ግዑዝነት የሌለው ተቋም ከአባላቱ በተለየ የራሱ ህልውና(ሕይወት) እንዳለው በመቁጠር የራሱ
መብት፣ንብረት፣ግዴታ ወዘተ ባለቤት በማድረግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑበት ማህበር በአንድ ስያሜና በአንድ ውክልና እንዲሠራ ማስቻል ነው፡፡
ስለ ህግ ሰውነት ዓላማ ይሄን ያክል ካልን አንድ አክሲዮን ማህበር መቼ እና የት የህግ ሰውነት እንደሚያገኝ ቀጥለን እናያለን፡፡

አንድ አክሲዮን ማህበር እንደማንኛውም ድርጅት ጥንስሱ የሚጀምረው በአንድ ሰው አዕምሮ ነው፡፡ ይህ ሰው ሃሳቡን ለሌሎቹ አካፍሎ
የሚተባበሩትን ካገኘ በኋላ ለአክሲዮን ማህበሩ አስፈላጊ የሆኑ የህግ ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት አብረው ይሰራሉ፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ ውስጥ 
የካፒታሉን መጠን ስንት መሆን እንዳለበት፣ የአንድ አክሲዮን አቻ ዋጋ እና ካፒታሉ በስንት አክሲዮን እንደሚከፋፈል ይወስናሉ ይህ ከተደረገ
በኋላ በአባላቱ መካከል አክስዮኖቹ ይከፋፈላሉ፡፡ በመስራች አባለቱ ከተወሰነው ካፒታል ላይ ቢያንስ እሩቡ ወይም ሃያ አምስት በመቶ ከተከፈለ፣
በዝግ ሂሳብ ከተቀመጠ ለማህበሩ ምስረታ በቂ እንደሆነ እና ምዝገባውም በአንድ አመት ውስጥ ካልተፈፀመ በዝግ ሂሳቡ ውስጥ የተቀመጠው
ገንዘብ ለአዋጡት ተመላሽ እንደሚደረግ በአንቀፅ 312 በግልፅ ተደንግጓል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ እነዚህን ቅደመ ሁኔታዎች ካሟላ የት ነው
የሚመዘገበው የሚለውን ጥያቄ ደግሞ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀፅ 9 እና 5(2) መልስ ይሰጠናል ይህም አክሲዮን
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በሚተዳደር አገር አቀፍ የንግድ መዝገብ ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ በንግድ መዝገብ
ውስጥ ከመመዝገብ በተጨማሪ ማህበሩ የህግ ሰውነት ለማግኘት ሌላኛው አስፈላጊ ጉዳይ የመተዳደሪያ ደንቡ እና መመሥረቻ ፅሁፉ በሰነዶች
ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ካልተረጋገጡና ካልተመዘገቡ ህጋዊ ውጤት እንደማይኖራቸው የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 334/1995
አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀፅ 1(ሐ) ይደነግጋል፡፡ ይህ ማረጋገጥና ምዝገባ ግን በንግድ ሚኒስቴር ከሚደረገው ምዝገባ በአላማም በይዘትም የተለየ
ነው፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ምዝገባ ዓላማ ለመንግስት ቁጥጥርና ለሦስተኛ ወገኖች መረጃን አደራጅቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ ሦስተኛ ወገኖች ሲባል
ከንግድ ድርጅቱ ጋር የንግድ ሥራን የሚሰሩ ተገበያዮች፣ አክሲዮን ገዢዎች እና ተመራማሪዎች ድርጅቱ በትክክል የተቋቋመ፣ በቂ ካፒታል ያለው
መሆኑን፣ የሃብት መጠኑ(net worth)፣ታሪኩን የቀድሞ የውጤታማነት ደረጃውን፣ የወደፊት ተስፋውን፣እዳዎቹን ወ.ዘ.ተረፈ የሚያሳይ መዝገብ
ነው፡፡ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በኩል የአክሲዮን ማህበሩ መመሥረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንቡ የማረጋገጡና የማስመዝገቡ
አላማ ደግሞ የሰነዶቹ ይዘት ህግንና መልካም ጠባይን የማይቃረኑ መሆንን ማረጋገጥ ሲሆን ይህ  መዝገብ ለሦስተኛ ወገኖች ክፍት እንደማይደረግ
በአዋጅ ቁጥር 334/1995 በእንቀፅ 9(2) ላይ ተደንግጓል፡፡

በአጠቃላይ አንድ አክሲዮን ማህበር የህግ ሰውነት የሚያገኘው በንግድ ሚኒስቴር በሚተዳደር አገር አቀፍ የንግድ መዝገብ ውስጥ ከተመዘገበ እና
መተዳደሪያ ደንቡና መመስረቻ ፅሁፉ በሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ህግን እና መልካም ጠባይን የማይቃረኑ መሆኑ ተረጋግጦ ከተመዘገበ
ቡኋላ ነው፡፡

 የአክሲዮን ማህበራት አቋቋም


በንግድ ህጋችን አንቀጽ 316 እና 317 መሠረት አንድን የአክሲዮን ማህበር በሁለት አይነት    መንገድ ማቋቋም እንደሚቻል መረዳት ይቻላል፡፡
እነዚህም፡-

1. በመሥራቾች መካከል የሚደረግ መቋቋም


የአክሲዮን ማህበር ለህዝብ አክሲዮን ሳይሸጥ ከአምስት በማያንሱ መስራቾች መካከል ሲቋቋም በአደራጆች መካከል ተቋቋመ ይባላል፡፡ በንግድ
ህጋችን አንቀጽ 316 መሰረት አንድ አክሲዮን ማህበር በአደራጆች ወይም በመስራቾች መካከል ለማቋቋም አራት መሠረታዊ ነገሮችን አደራጆች
በመመስረቻ ፅሁፍ ውስጥ ማሳየት ይጠበቅባቸዋለ፡-

 ሁሉም አክሲዮኖች የተያዙ መሆናቸውን


 በአንቀጽ 312(1)(ለ) መሠረት የካፒታሉ አንድ አራተኛ ተከፍሎ በዝግ ሂሳብ በባንክ መቀመጡን
 በአይነት የተደረገ መዋጮ በባለ አክሲዮኖች ተገምቶ ግምቱ መገለጽ አለበት( አዋጅ ቁጥር 376/2003 አንቀፅ 5(11)
ይመለከቷል፡፡)
 የተለያዮ የኩባንያው አስተዳደር አካላት ለምሳሌ የማህበሩ የቦርድ አባላት፣ኦዲተሮች እና ሥራ አስኪያጅ መሾሙን መገለፅ
አለበት፡፡
2. አክሲዮን ለህዝብ በመሸጥ የሚቋቋም
በንግድ ህጋችን አንቀጽ  317 መሠረት የንግድ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በመሀከላቸው ማህበሩን ማቋቋም ካልቻሉ ለህዝብ  አክሲዮን በመሸጥ
ማህበሩን ማቋቋም እንደሚችሉ መረዳት ይችላል፡፡ የንግድ ሀሳቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ከሆነ ገንዘቡን ትንሽ ሠዎችን በማሣመን
መሠብሠብ ስለሚያሥቸግር ለሕዝብ አክሲዮን በመሸጥ አክሲዮን ማህበሩን ማቋቋም ይችላሉ፡፡ አደራጆቹ ለህዝብ አክሲዮን በመሸጥ አክሲዮን
ማህበር ሲያቋቁሙ ሊከተሏቸው ወይም መፈፀም ያለባቸውን የድርጊት ቅደም ተከተሎች አሉ( አንቀጽ 318፣ 319 እና 321 ይመለከቷል፡፡)
እነዚህም፡-
 የአክሲዮን ሽያጭ መግለጫ ማውጣት (prospectus)፡
የማህበሩ አደራጆች አክሲዮን የሚገዛው ሕዝብ ስለሚቋቋመው አክሲዮን ማህበርና ሥለአክሲዮኖቹ ትክክለኛ ዋጋ ትክክለኛውን ግንዛቤ
እንዲያገኙ የሚያስችል የአክሲዮን ሽያጭ መግለጫ ማውጣት እንዳለባቸው በንግድ ህጉ አንቀጽ 318 ተመልክቷል፡፡ ይህን መግለጫ አዘጋጅቶ
ለህዝብ መግለፅ እያንዳንዱ አክሲዮን ገዢ ከመግዛቱ በፊት እንዲያነበው መደረጉ ሕዝብን ከስህተት ይጠብቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

 የህዝቡ አክሲዮን መፈረም


የአክሲዮን ሽያጭ መግለጫ ለህዝብ ይፋ ተደርጎ ካበቃ በኋላ አክሲዮኖቹን ለመግዛት የፈለገ ሰው በመግለጫው በተገለፀው ቦታ እና ጊዜ
በመቅረብ መግለጫውን በማንበብ መፈረም ይችላል፡፡( አንቀጽ 319 ይመለከቷል፡፡)

 የፈራሚዎች ጉባኤ ማካሄድ


ህዝቡ አክሲዮን ግዢ ፈፅሞ የተፈለገው የካፒታል መጠን ከተሠበሰበ ወይም አደራጆቹ በቂ ካፒታል ተገኝቷል ብለው ካመኑ አሊያም
የመፈረሚያው ቀነ ገደብ ካበቃ አክሲዮን ለመግዛት የፈረሙ ሠዎች ወይም የፈራሚዎች ጉባኤ በመሥራቾች እንዲጠራ የንግድ ህጋችን በአንቀፅ
320 እና ተከታዮቹ ይደነግጋል፡፡ የፈራሚዎች ጉበኤ ከተደረገ በኋላ የማህበሩ አደራጆች የማህበሩን የመመሥረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ
በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ማፀደቅ አለባቸው በተጨማሪም ማህበሩ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚተዳደር ሀገር አቀፍ
የንግድ መዝገብ ውስጥ በመመዝገብ የህግ ሰውነት ማግኘት አለበት፡፡

እንግዲህ የአክሲዮን ማህበራትን ፋይዳ፣ ባህርያት እና መቋቋም በአጭሩ ከተመለከትን የአክሲዮን አይነቶችን እና አክሲዮን የገዛ ሰው የገዛውን
አክሲዮን በተመለከተ ምን መብት አለው የሚለውን ቀጥለን እናያለን፡፡

 የአክሲዮን አይነቶች
በንግድ ህጋችን አንቀፅ 328(1) እና 715 መሰረት አክሲዮን የማይከፋፈል እና ግዑዝነት የሌለው የሚተላለፍ ሰነድ ነው፡፡ አክሲዮኖች ከአንድ
ባለቤት ወደ ሌላ ከሚተላለፉበት መንገድ በመነሳት ለአምጪው የሆነ አክሲዮን “(to bearer) እና በባለቤቱ ስም የተመዘገበ አክሲዮን በማለት
በሁለት ዓይነት መልክ እንደሚከፈሉ ከንግድ ህጋችን አንቀጽ 325 መረዳት እንችላለን፡፡

1. ላምጪው የሆነ አክሲዮን፡


ላምጪው የሆነ አክሲዮን የባለቤቱን ስም በአክሲዮኑ የምስክር ወረቀት ላይ የሚይዙ ሲሆን ባለቤት ሆኖ የሚገመተው ደግሞ በማንኛውም ጊዜ
አክሲዮኑን በእጁ ይዞ የተገኘው መሆኑን እና ይህንኑ በማቅረብ ትርፍ መቀበል፣ መልሶ ገንዘብ መክፈል እና ለጠቅላላው ጉባኤ አባል መሆን 
የሚያስችሉ መሆኑን ከንግድ ህጋችን አንቀጽ 340 እና 721(1) መሰረት መረዳት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግ የሚገባው ምንም እንኳ
ላምጪው የሆነ አክሲዮን ላይ የባለቤቱ ስም ባይገለፅም በመጀመሪያ ፈርሞ የወሰደው ባለአክሲዮን ስም በባለአክሲዮኖች መዝገብ ውስጥ ስሙ
መስፈር እንዳለበት የንግድ ህጉ አንቀጽ 331 ያስገድዳል፡፡

2. በባለቤቱ ስም የተመዘገበ አክሲዮን


የንግድ ህጋችን አንቀጽ 722 እና 331 አጣምረን ስናነብ በባለቤቱ ስም የተመዘገበ አክሲዮን በእጁ የያዘ ሰው በአክሲዮኑ ላይ ለተነገረው ግዴታ
መብት ተጠቃሚ ለመሆን በአክሲዮኑ ላይና በአውጪው መዝገብ ወይም አክሲዮን ማህበሩ በሚያዘጋጀው መዝገብ ውስጥ ስሙ መፃፍ
ይኖርበታል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው የአክሲዮን አይነቶች መሠረት ያደረጉት ከአንድ ባለቤት ወደ ሌላ ከሚተላለፉበት መንገድ በመነሳት ሲሆን አሁን ደግሞ
ማህበሩ በመመሥረቻ ፅሁፉ ወይም ይህንኑ የሚለውጠው የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ልዩ ልዩ መብቶችና ጥቅሞች የሚያስገኙ የአክሲዮን
አይነቶች ማውጣት እንደሚቻል ከንግድ ህጉ አንቀፅ 335፣336፣337 እና 345  መረዳት እንችላለን በዚህም መሠረት አክሲዮኖቹን መደበኛ
አክሲዮን(ordinary share)፣ ቅድሚያ መብት የሚያስገኙ አክሲዮን(preference share) እና ትርፍ ብቻ የሚያስገኙ አክሲዮኖች (dividend
share) በማለት መክፈል ይቻላል፡፡

 መደበኛ አክሲዮን
በንግድ ህጋችን አንቀጽ 345፣406 እና 417 መሠረት መደበኛ ወይም ተራ አክሲዮን የገዛ ሰው በአመቱ መጨረሻ ከተጣራ ትርፍ
የመካፈል፣ማህበሩ ሲፈርስ ዕዳው ተከፍሎ ከሚቀረው ገንዘብ የመካፈል፣በጠቅላላ ጉባኤ ድምፅ የመስጠት ፣በያዙት የአክሲዮን ቁጥር አዳዲስ
አክሲዮኖች ሲወጡ ለመግዛት የቀደምትነት መብት እና የማህበሩን የትርፍና ኪሳራ የሂሳብ ሰነዶች እና አስተዳዳሪዎቹንና ተቆጣጣሪዎቹ ለጠቅላላ
ጉባኤው ያቀረቡዋቸውን ሪፖርቶችን የማዎቅ ወይም ቅጂዎችን የመውሰድ መብት ያስገኛሉ፡፡

 የቅድሚያ መብት የሚያስገኙ አክሲዮን


በንግድ ህጋችን አንቀጽ 336 መሠረት የቅድሚያ መብት የሚያስገኝ አክሲዮን የሚያስገኛቸው የቅድሚያ መብቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነሱም
የተለየ ጥቅም ያላቸው ወደፊት የሚወጡ አክሲዮኖችን በቀደምትነት የመግዛት፣ ትርፍ የማግኘት፣ እና ማህበሩ ሲፈርስ ከሚጣራው ሃብ ላይ
ቅድሚያ የመከፈል መብትን የሚያስገኝ ሲሆን በድምጽ መስጠት ጉዳይ ላይ ልዮ መብት ወይም ቅድሚያ የሚያሰጡ አክሲዮኖችን ማውጣት
የተከለከለ ሲሆን ማህበሩ እነዚህን አክሲዮኖች ለህዝብ የሚሸጥበት ዋና አላማ ብዙ ገንዘብ ለሚያዋጡ ወይም ብዙ አክሲዮን ለሚገዙ አባላት ልዮ
መብት በመስጠት  የተሻለ ካፒታል ለመሰብሰብ ነው፡፡ ሆኖም ግን የቅድሚያ መብት ሲባል ገደብ ያለው መሆኑን ሊጤን ይገባል፡፡ ይህም ማለት
ከትርፍ የቅድሚያ መብት ሲባል ከሚገኘው የተጣራ ትርፍ ላይ ምን ያህል ገንዘብ ወይም በመቶኛ ምን ያህል የሚለው በመመስረቻ ጽሁፉ ወይም
በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ላይ በግልፅ መገለፅ አለበት፡፡
 ትርፍ ብቻ የሚያስገኝ አክሲዮን
ይህ አይነቱ አክሲዮን በንግድ ህጋችን በአንቀጽ 337 ላይ የተደነገገ ሲሆን አክሲዮኖቹ ከተገዙ በኋላ ባሉት አመታት ኩባንው ዋጡትን ገንዘብ
የመለሰላቸው ባለአክሲዮኖች የሚይዙት አይነት አክሲዮን ነው፡፡ እንዲህ አይነነት አክሲዮን ያላቸው አባላት በአመቱ ከሚገኘው ትርፍ የመካፈል
መብት ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ማህበሩ ሲፈርስ ካፒታል ከተመለሰ በኋላ ከሚጣራው ሃብት ላይ የመካፈል መብት ያገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን
በመተዳደሪያ ደንቡ የተወሰነውን የአክሲዮን ወለድ እንዲሁም ማህበሩ ሲፈርስ ገቢ ያደረጉትን መዋጮ ለመውሰድ የላቸውም፡፡

አሁን ደግሞ በአንድ አክሲዮን ማህበር ውስጥ አክሲዮን የገዛ ሰው አክሲዮኖቹ ምን መብት ያስገኙለታል የሚለውን እናያለን፡፡ ከላይ የአክሲዮን
አይነቶቸን ከሚያስገኙት ልዩ ልዮ ጥቅሞች ወይም መብቶች በመነሳት በመደብ በንግድ ህጉ የተከፋፈሉ ሲሆን እነዚህን አክሲዮኖች የገዛ ሰው
በአመቱ መጨረሻ ከተጣራ ትርፍ የመካፈል፣ማህበሩ ሲፈርስ ዕዳው ተከፍሎ ከሚቀረው ገንዘብ የመካፈል፣በጠቅላላ ጉባእ ድምፅ የመስጠት
፣በያዙት የአክሲዮን ቁጥር አዳዲስ አክሲዮኖች ሲወጡ ለመግዛት የቀደምትነት መብት እና የማህበሩን ሰነዶች ለማወቅ የመቻል ወ.ዘ.ተረፈ መብት
እንዳለው ያየን ሲሆን አክሲዮኖቹን በማዘዋወር ረገድ ባለአክሲዮኑ አክሲዮኑን የማስተላፍ ወይም የመሸጥ፣ በመያዣ የመስጠት እና በአላባ ጥቅም
ለሌላ ሰው የመስጠት መብቶች አሉት ( 329 እና 333 ይመለከቷል) እነዚህንም በቅደም ተከተል እናያለን፡፡

    ሀ. አክሲዮኑን በሽያጭ የማስተላለፍ መብት


የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 40(1) መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት የመሆን
መብት እና የሌሎችን ዜጎች መብት እስካልተቃረነ ድረስ ንብረቱን የመያዝ፣ የመጠቀም እና የመሸጥ እንዲሁም የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ
የማስተላለፍ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ አክሲዮን የማይከፋፈል እና ግዑዝነት የሌለው ንብረት በመሆኑ ባለአክሲዮኖች መብታቸው በዚህ ህገ
መንግስታዊ ድንጋጌ ውስጥ ጥበቃ የተሰጠው እና አክሲዮናቸውን ለሌላ ሰው በሽያጭ ማስተላለፍ የሚችሉ ቢሆንም ግን ይህ የማስተላለፍ መብት
በንግድ ህጉ አንቀጽ 333(1) መሰረት በመተዳደሪያ ደንብ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የሌሎችን ባለአክሲዮኖች ወይም የኩባንያውን
መብት ለማስጠበቅ ሲባል ሊገደብ ይችላል፡፡

  ለ.አክሲዮንን በአላባ ጥቅም የማስተላለፍ መብት


ሌላው አክሲዮን ንብረት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነጥብ ባለአክሲዮኑ በአክሲዮኑ ላይ ካለው ሙሉ ባለቤትነት በመለስ የአላባ ጥቅሙን
ማስተላለፍ እንደሚችል በንግድ ህጉ በአንቀጽ 329 ላይ ተገልጻል፡፡ የአላባ መብት ምንነት እና አመሰራረትን እንዲሁም በአላባ ሰጪና ተቀባይ
መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዙት መሰረታዊ መርሆች ያሉት በፍትሐብሄር ሕግ ከአንቀጽ 1309—1358 ባሉት ድንጋጌ ውስጥ ነው፡፡ የአላባ
መብት ማለት የሚጠቀሙበትን ነገር ከመጠበቅ ግዴታ ጋር ከዚሁ ነገር ላይ በሚገኙት ፍሬዎች ወይም መብቶች ለመጠቀምና ለመገልገል
የሚያስችል መብት ነው( የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 1309(1) ይመለከቷል)፡፡ እንግዲህ አክሲዮን በአላባ ጥቅም መተላለፍ እንደሚቻል ካየን
አክሲዮኑ ለሌላ ሰው የተላለፈ እንደሆነ የባለአክሲዮኑና የአላባ መብት ተቀባዩ መብቶች ምን ምን እንደሆኑ ቀጥለን እናያልን፡፡

የአላባ ጥቅም ተቀባዮ፦


 በአላባ የተቀበለውን አክሲዮን በእጅ የማስገባት እና የሚስገኘውን ፍሬ ማለትም ትርፍ የመቀበል እና የመጠቀም መብት (
የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 1311)
 በጠቅላላ ጉባኤው ድምፅ የመስጠት መብት ( የንግድ ህግ አንቀፅ 329(1) )
 አክሲዮኑ የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም ቢኖር ለምሳሌ በአክሲዮን ማህበር የተቋቋመ ሆስፒታል ቢሆን እና ባለአክሲዮኖች
በቅናሽ ወይም በነፃ የሚታከሙ ቢሆን ይህ መብት ለአላባ ተቀባይ ይተላለፋል
 የአላባ መብት ጊዜ ሲያልቅ የከፈለው ገንዘብ እንዲመለስለት ያለው መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአክሲዮኑ የተጠየቀውን ቀሪ
ገንዘብ የመክፈል ግዴታ አለበት( የንግድ ሕግ አንቀፅ 329(4)
ሐ. አክሲዮንን በመያዣ የመስጠት መብት
አንድ ባለአክሲዮን አክሲዮን በመያዣነት በመስጠት ገንዘብ መበደር ወይም ለሌላ ግዴታ አፈፃፀም እንደዋስትና ማስያዝ እንዲሚችል ከንግድ
ህጋችን አንቀጽ 329 እና ከፍትሐብሄር ህጋችን ከአንቀጽ 2863 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መረዳት እንችላልለን፡፡ አክሲዮንን በመያዣነት
የተቀበለ ሰው የሚከተሉት መብቶች አሉት

 ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር በጉባኤዎች ድምፅ የመስጠት መብት (አንቀፅ 329(1))
 ከአክሲዮኑ የሚገኘውን ትርፍ የመቀብል መብት ያለው ሆኖ ባለመያዣው ከአክሲዮኑ የሚገኘውን ትርፍ የሚወስደው
እንዲያው በነፃ ሳይሆን ደረጃ በደረጃ ከባለአክሲዮኑ የሚጠይቀውን እዳ ለማወራረድ ነው ይህንንም ሲያደርግ መጀመሪያ
የዕዳውን ወጪ፣ ቀጥሎ ወለዱን እና በመጨረሻም ዋና እዳውን ያወራርድበታል፡፡(የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 2868(1-2)
ይመለከቷል)
 

ማጠቃለያ

አክሲዮን ማህበራት በሃገራችን አንቨስትምንትን እና ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ ዜጎች እንደ አቅማቸው የተለያየ መደብ
ያለቸውን አክሲዮኖች በመግዛት ማህበሩ በዓመት ከሚያስገኘው ትርፍ በመቀበል የተለያየ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ
ያስችላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!! 
ምንጭ፡-
 በ 1966 ዓ/ም በስራ ላይ የዋለው የኢትዮጵያ የንግድ ህግ
 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002
 የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጥ አዋጅ ቁጥር 334/1195
 1952 ዓ/ም የወጣው የፍትሐብሄር ህግ
 በፍታዱ ጴጥሮስ ገ/መስቀል ፡የኢትዮጵያ የኩባንያ ህግ ፡ የካቲት 2004 ዓ/ም, በፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር
የታተም
 Getahun Seifu, Revising company law with the advent of Ethiopian commodity exchange:an
overview, 2003 http://www.ajol.info/index.php/mlr/article/download/57150/45538
 Endalew Lijalem Enyew, The doctirine of piercing the corporate veil: its legal and judicial
recognition in Ethiopia፡http://www.ajol.info/index.php/mlr/article/download/81650/71801

You might also like