You are on page 1of 26

በኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደህንነት ቻርተር አተገባበር

ሁኔታ ላይ በቀረበ የመጀመሪያ ወቅታዊ ሪፖርት ላይ በአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደህንነት የባለሙያዎች
ኮሚቴ የተሰጠ የማጠቃለያ ምክረ ሀሳብ

የካቲት/2022
I. መግቢያ

1. የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደህንነት የባለሙያዎች ኮሚቴ (ACERWC/ ኮሚቴዉ) ከሁሉ በማስቀደም

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዺሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በቻርተሩ አንቀፅ 43 በተቀመጠዉ የተዋዋይ ሀገራት

ግዴታ መሰረት የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አፈፃፀም ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ላቀረበዉ

የመጀመሪዉ ወቅታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ምስጋናዉንና አድናቆቱን ያቀርባል፡፡ ኮሚቴው ሁለተኛዉን

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዺሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ወቅታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ከህዳር 15 እስከ ህዳር

26/2021 በበይነመረብ መስኮት በተካሄደዉ 38 ኛ መደበኛ ጉባኤ ተመልክቷታል፡፡

2. ኮሚቴው የኢትዮጵያ መንግስት በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተመራዉን
ልኡካን ቡድን ከኮሚቴዉ አባላት ጋር ዉጤታማ ዉይይት እንዲደረግ ላደረገዉ ድጋፍ ኮሚቴዉ ምስጋናዉንና

አድናቆቱን ያቀርባል፡፡ በእርግጥም ውይይቱ ኮሚቴው በአባል ሀገሯ ቻርተሩን ለመተግበር የተወሰዱትን

እርምጃዎችን እና በአባል ሀገሯ መነሻ ሪፖርት ላይ በኮሚቴዉ የተሰጡትን ምክረ ሀሳቦች አተገባበር እንዲሁም

ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲረዳ አስችሎታል፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ ያሉትን እውነታዎች እና
በተደረገዉ ገንቢ ዉይይት የቀረቡትን መረጃዎች በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ ኮሚቴው የሚከተሉትን
የማጠቃለያ ምልከታዎች እና ምክረሀሳቦች አዘጋጅቶ አፅድቋል፡፡ ይህም እንደ ኮሚቴዉ እይታ የአፍሪካ ሕፃናት
መብቶች እና ደህንነት ቻርተር ድንጋጌዎችን አፈፃፀም የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል መመሪያና አቅጣጫ
የሚያሳይ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

II. በቻርተሩ አተገባበር ላይ የታዩ መሻሻሎች

3. ኮሚቴው ሀገራዊ የአፈፃፀም ሪፖርቱ በሚሸፍነው ወቅት በአባል ሀገሯ የሕፃናት መብቶችና ደህንነትን

በማሰከበርና በማስጠበቅ ረገድ ያለውን እደገትና መሻሻል ያስተዋለ እና ያደነቀ ሲሆን እነዚህም የሚከተሉትን

ያጠቃልላሉ፦

ሀ. የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አካል የሆነው የአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል፣የአፍሪካ

ኅብረት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመጠበቅ እና ለመደገፍ የተደረገውን ስምምነት (የካምፓላ

ስምምነት)፣ እንዲሁም ሁለቱንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብቶች ስምምነት አማራጭ

2
ፕሮቶኮሎች (በሕፃናት ሽያጭ ፤ ሕፃናትን ለወሲብ ንግድ ማሰማራት እና የወሲብ ፊልም ማሰራትን ለማስወገድ

የተደረገ አማራጭ ፕሮቶኮል እና በግጭቶችና ጦርነት ውስጥ የሕፃናት ተሳትፎ የተመለከተውን አማራጭ

ፕሮቶኮል) መፅደቅ፤

ለ. የሀገሪቱ ሕጎች ከዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና መስፈርቶች ጋር

ለማጣጣም የተካሄደውን መጠነ ሰፊ የሕግ ኦዲት እና ግምገማ፤

ሐ. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ተሃድሶና በዚህ ምክንያት ኮሚሽኑ በአለም አቀፍ የብሔራዊ

የሰብአዊ መብት ተቋማት ህብረት (the Global Alliance of National Human Rights Institutions) የተሰጠው

ደረጃ ከፍ ብሎ ወደ “ኤ” ማደጉ፤

መ. የሕጻናት ፓርላማዎች ማቋቋሚያ መመሪያዎች መሻሻል እና በሁሉም ክልሎች የሕጻናት ፓርላማዎች

አደረጃጀቶች መፈጠር እና

ሠ. የሲቪል ማኅበራት ሕግ መሻሻሉና የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በሕጻናት መብቶች ላይ እንዲሠሩ እና

ከመንግሥት ጋር እንዲስተጋበሩ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑ፡፡

III. የትኩረት አቅጣጫ እና ምክረ-ሃሳቦች

ሀ. አጠቃላይ የአተገባበር እርምጃዎች


4. ኮሚቴው የህፃናት መብቶችን ጉዳይ የሚመለከቱ በርካታ አለም አቀፍ ሕጎች መፅደቃቸውን፤ ሕጎች
መሻሻላቸውን፤ እንደ ብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲ ያሉ ፖሊሲዎች፤ስትራቴጂዎችና የድርጊት መርሐ ግብሮች
መውጣታቸውን እና መፅደቃቸውን ተገንዝቧል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴው አባል ሃገሯ በመነሻ የአፈፃፀም ሪፖርቱ
ላይ የተሰጡት ምክረሀሳቦችን ከግምት ዉስጥ በማስገባት ሁሉን አቀፍ የህጻናት ህግ ለማርቀቅ ዉይይት
መጀመሯን ያደንቃል፡፡ ያሉትን ህጎች በመገምገም ከቻርተሩ ጋር እንዲጣጣሙ ለማስቻል እየተወሰደ ያለውን
እርምጃ የሚደነቅ ቢሆንም፣ ኮሚቴዉ አባል ሀገሯ ቻርተሩን እና ሌሎች ሀገሪቷ የፀደቀቻቸዉን የሕፃናት
መብቶች አለም አቀፍ ሕጎችን በስራ ላይ ሊያዉል የሚችል ሁሉን አቀፍ የሕፃናት መብቶች ሕግ እንድታወጣ

ደጋግሞ ያሳስባል፡፡ ኮሚቴው የሕጻናት ሕግን የማውጣት ጉዳይ የክልሎች ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል፣ በመሆኑም
አባል ሀገሯ የፌደራል የሕፃናት ሕግ በማዉጣት እና ክልላዊ መንግስቶችም የፌደራል ሕጉን ተምሳሌና ተሞክሮ
በመውሰድ በክልላቸው ተፈጻሚ የሚሆን የሕጻናት ሕግ እንዲያወጡ አባል ሀገሯ እንድታበረታታ ኮሚቴዉ
ይመክራል፡፡ ኮሚቴው ሁሉንም የሕፃናት መብቶች የሚሸፍን እና ከቻርተሩ እና ከሌሎች አለም አቀፍ

3
ድንጋጌዎች ጋር የሚስማማ ሁሉን አቀፍ የሕፃናት መብቶች ሕግ መውጣቱና መፅደቁ በአባል ሀገሯ ዉስጥ
ለሚገኙ የሕፃናቶች መብት መጠበቅ ጠንካራ የህግ ማእቀፍ መፍጠር እንደሚያስችል እና ፍትሕን ለማረጋገጥ

እና በቻርተሩ ውስጥ የተካተቱትን የሕፃናትን መብቶችን በሃገራዊ ደረጃ ለማረጋገጥ እንደሚረዳቸው በጽኑ
ያምናል፡፡

5. ኮሚቴው በሀገሪቱ በተደረገው ተቋማዊ ሽግሽግ የተነሳ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕጻናት
መብቶች ጉዳይን የሚመለከተው የሚኒስተር የመስሪያ ቤት መሆኑን ተረድቷል፡፡ ኮሚቴው አባል ሃገሯ
በሚኒስቴር መ/ቤቱ ላለው የሕፃናት መብቶች ዳይሬክቶሬት በቂ የገንዘብ እና የሰው ሃይል አቅርቦት
እንድትመድብ እና የሕፃናት ጉዳዮችን በሚኒስተር መስሪያ ቤቱ ዋና ዋና ስራዎች መካተታቸዉን እድታረጋግጥ
እና ተቋሙ በተሰጠዉ አዲስ ሀላፊነት መሰረት የሕጻናት መብቶች ላይ ያለምንም እንቅፋት እንዲሰራ በቂ
በጀት ሊመደብለት እንደሚገባ ኮሚቴዉ ምክረሀሳቡን ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴው የሚኒስትር መስሪያ
ቤቱ አዲስ የተሰጠውን ሃላፊነት እንደመልካም እድል በመጠቀም በሁሉም ሴክተሮችና ክልሎች ያለውን

የሕፃናት መብቶች ክትትልና የተቀናጀ አሰራር ለማጠናከር ሊጠቀምበት እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ኮሚቴው
ይህንን እድል በመጠቀም ሚኒስቴሩ የሕፃናት መብቶች አተገባበርን የሚከታተል ከሁሉም ተያያዥነት ካላቸዉ
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከሲቪክ ማህበራት ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና ከተለያዩ
ባለድርሻ አካላት የተዉጣጣ ቋሚ ግብረሀይል ወይም ኮሚቴ የሚቋቋምበትን በጀት በመመደብ የሕፃናት
መብቶች አተገባበር ላይ በሁሉም መስኮች የተሻለ ክትትል እንዲደረግ ምክረሀሳቡን ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት
የተለያዩ ኮሚቴዎች እና ግብረ ሃይሎች ቢኖሩም እነዚህ ኮሚቴዎች በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ
በመሆናቸው ኮሚቴው ሰፋ ያለ ስልጣን ያለው እና መንግስት የሕጻናትን መብት ማስከበር እንደ ዋና ጉዳይ
እንዲያዝና እንዲካተት የሚያደርግ ፣ መረጃ የሚሰበስብ ፣ በሁሉም ሴክተሮች ህግ እና መመሪያ መተግበሩን
የሚያረጋግጥ ኮሚቴ ወይም ግብረሃል መኖር እንደሚገባዉ ኮሚቴዉ ይመክራል፡፡

6. የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረጉን እና በኮሚሽኑ ዉስጥም የሴቶች እና ሕፃናት
ስራ ክፍል መቋቋሙን አድንቋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጲያ እንባ ጠባቂ ተቋም ባደረገዉ ተቋማዊ ማሻሻያ
ደስታዉን ይገልፃል፡፡ ኮሚቴዉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና እንባ ጠባቂ የበለጠ ተቋማዊ ነፃነታቸዉን እና
ጥንካሬያቸዉን አረጋግጠዉ በአባል ሀገሯ ዉስጥ የሰብአዊ መብቶችን ጉዳይ መከታተል እንዲችሉ በቂ በጀት
እንዲመደብላቸዉ ፣ ለግኝቶቻቸዉ፣ ለዉሳኔዎቻቸዉ እና ለምክረ ሀሳቦቻቸዉ በቂ ግምት እንዲሰጥ እና ስለ
ሕፃናት መብቶች ጥበቃ ስልቶቻቸውና የአቤቱታ ቅበላ ስርአታቸው ጨምሮ ስለ ኃላፊነታቸው ግንዛቤ
አንዲያድግና እንዲስፋፋ ለአባል ሀገሯ ኮሚቴዉ ምክረ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡

4
7. ኮሚቴዉ በተለያዩ ሴክተሮች ላይ የበጀት ድልድል ጭማሪ መደረጉን በመገንዘብ አድናቆቱን እየገለፀ፣ ባንፃሩ
መንግስት ድሀ-ተኮር ለሆኑ ሴክተሮች የሚያወጣዉ ወጪ ከ 2012/2013 ከነበረዉ 69% በማሽቆልቆል
በ 2017/2018 ወደ 62% የቀነሰ መሆኑን ከአባል ሀገሯ ሪፖርት ለመረዳት ችሏል፡፡ አባል ሀገሯ ዉስጥ ያሉትን
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሕፃናት እና ወጣቶች ከግምት ዉስጥ ባስገባ መልኩ መንግስት በሕፃናት ጉዳይ ላይ
ያለዉን በጀትና ወጪ መከታተል የሚያስችል እንዲሁም በየጊዜዉ የሚሻሻል የመዋእለ ንዋይ ፍሰት
መኖሩን የሚያረጋግጥ እና መከታተል የሚያስችል የበጀት ቀጥጥር ስልት እንዲነድፍና ተግባር ላይ
እንዲያውል ኮሚቴዉ ይመክራል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴዉ አባል ሀገሯ ህጻናትን በቀጥታ እና በዘላቂነት
ሊጠቅሙ በሚችሉ ሴክተሮች ለምሳሌ እንደ ጤና፣ ትምህርት እና መሰል ተቋማት ላይ የበጀት
ድልድል ጭማሪ መደረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳቡን ያቀርባል ፡፡

8. ኮሚቴው የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ሕግ መከለሱን እና መንግስት ለሲቪል ማህበራት የገቢምንጭ


ሳያስጨንቃቸው በሕጻናት መብት ዙሪያ እንዲሰሩ አመቺ ሁኔታን መፍጠሩን አመስግኗል፡፡ አባል ሀገሯ
ከዚህ በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ የሲቪል ማኅበራት በሕፃናት መብቶች መከበር ላይ እንዲሰሩ፤
በሕፃናት መብቶች ላይ በሚያተኩሩ የቅንጅትና የትብብር ፕሮግራሞች ትግበራ ላይ እንዲሳተፉ ፣አባል
ሀገሯ በምትወስዳቸዉ የህግ ማዉጣት እና የአስተዳደራዊ እርምጃዎች ቀረፃ ላይ የሲቪል ማህበራት
እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተያየት እድትቀበል ፣በተለያዩ የመንግስት ግብረ ሀይሎች እና
አወቃቀሮች የሕፃናት መብቶች ማስተባበርያ እና ትግበራ ስርአቶች ላይ የሲቪል ማህበራትን
እንድታካትት ኮሚቴዉ ያበረታታል፡፡
9. የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃ አሰባሰብ እና በስርዓተ-ፆታ፣ በእድሜ እና በክልል የተከፋፈሉ
መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራ በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራ መሆኑን ኮሚቴው አድንቋል። በዚህ ረገድ አባል
ሀገሯ በመረጃ አሰባሰብ ላይ የምታደርገዉን ጥረት የበለጠ አጠናክራ እንትቀጥል እና የሕጻናት ደህንነት
አስተዳደር ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንዲገባ እንድታረግ፤ ይህም ከኮቪድ-19 መከላከል እና
መቆጣጠር ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ጨምሮ ከልጆች መብት እና ደህንነት ጋር በተገናኘ ሁሉንም አስፈላጊ
መረጃዎችን ለመያዝ የሚያስችል እንዲደረግ ኮሚቴው ይመክራል።ኮሚቴው በተጨማሪ አባል ሀገሯ በበጀት
አመዳደብ ውስጥ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ልዬታና ፖሊሲ ቀረፃ ሂደት የሚመነጩ መረጃዎችን
በቀጣይነት በሚወሰዱ ህፃናት-ተኮር ውሳኔዎች በሚጠቅም መልኩ በሙሉ በሙሉ እንድትጠቀም ያበረታታል።
10. አባል ሀገሯ የአፍሪካ የሕፃናት ቀንን በማክበር ስለ ቻርተሩ ግንዛቤ እያስፋፋች መሆኑን ኮሚቴው አመስግኗል።
ኮሚቴው አባል ሀገሯ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ የህፃናት ዳይሬክቶሬቶች
ስለ ቻርተሩ እና አተገባበሩ እንድታሰለጥን እንዲሁም በዚህ ሰነድ ውስጥ ስለተካተቱት ምክረ ሀሳቦች ያላቸውን
ግንዛቤ እንድታሳድግ ያበረታታል።ኮሚቴው አባል ሀገሯ ቻርተሩን ለበለጠ ግንዛቤ እና ትግበራ በሁሉም ክልሎች
የስራ ቋንቋዎች እንድትተረጉም ያበረታታል።

5
ለ. የሕፃናት ትርጉም
11. በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ድንጋጌ መሰረት በ 16 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህጻናት በፍትህ ሚኒስቴር
ፍቃድ እንደ አዋቂ ተቆጥረዉ እንዲያገቡ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ እና የወንጀል ሃላፊነት ዝቅተኛዉ የእድሜ በ
9 አመት ሆኖ መቀመጡ ላይ በኮሚቴዉ የተሰጠዉ ምክረሀሳብ በሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ ውስጥ አለመተግበሩ
ኮሚቴዉ ቁጭት የሚታወስ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ኮሚቴው ይህንን ጉዳይ ኮሚቴው በጥቅምት ወር 2018
ባደረገው የክትትል ጉብኝት ወቅት ደግሞ ያነሳው ቢሆንም እስካሁን ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃዎች
እንዳልተወሰዱ አስተዉሏል። በመሆኑም ኮሚቴው አባል ሀገሯ በጋብቻ ዕድሜ ላይ ያለውን ልዩ ሁኔታ
ለማስወገድ እና የወንጀል ተጠያቂነትን ዝቅተኛ ዕድሜ ለማሳደግ ፈጣን የሕግ እርምጃዎችን እንድትወስድ
ይመክራል።

ሐ. አጠቃላይ መርሆዎች

ከአድልዎ የመጠበቅ
12. ኮሚቴው አባል ሀገሯ በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋለውን የሥርዓተ-ፆታ ልዩነት ለማጥበብ፣ የአካል ጉዳተኛ
ሕጻናትን መካተት በተለያዩ መድረኮች ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግን ጨምሮ ለማረጋገጥ የተለያዩ
ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን በአድናቆት አስተዉሏል።ሆኖም በክልሎች መካከል እንዲሁም በከተማና
በገጠር ያለው የአገልግሎት አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና ጥራት ልዩነት እንዳለው ኮሚቴው ተመልክቷል። ከዚህም
በላይ በትምህርት ላይ ያለው የፆታ ልዩነት እና በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸመው መድልዎ በልጅነት ጋብቻ፣ ጥቃት፣
የሴት ልጅ ግርዛት እና ሌሎች ድርጊቶች የሚንፀባረቅ ተግዳሮት ሆኖ እንደሚቀጥል ኮሚቴው ተመልክቷል።
ኮሚቴው የአካል ጉዳተኛ ሕጻናት አገልግሎት ተደራሽነት ውስን መሆኑንና ይህም ትምህርታቸውን፣
ጤናቸውን እና ደህንነታቸውን ባልተመጣጠነ መልኩ እንደሚጎዳ ተረድቷል። በተጨማሪም የተፈጥሮ
አደጋዎችና ግጭቶች በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕፃናትን በከፋ ሁኔታ እንደሚጎዱ ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም
ኮሚቴው በሀገሪቷ በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ ሕጻናት እኩል የአገልግሎት እድሎች እንዲኖራቸው ለማድረግ
አባል ሀገሯ ዝቅተኛ እመርታ ላላቸው ክልሎች እንዲሁም ለገጠር አካባቢዎች ተጨማሪ በጀት እና ግብአት
እንድትመድብ ያበረታታል። አባል ሀገሯ አካል ጉዳተኛ ሕጻናት እና ልጃገረዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ
ለማስቻል፣ አካል ጉዳተኛ ሕጻናት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዳይካተቱ እንቅፋት የሚሆኑትን
የተለያዩ መገለሎች እና አሉታዊ አመለካከቶችን ለመፍታት እና አገልግሎቶች በአካል እና በኢኮኖሚ ተደራሽ
እንዲሆኑ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ተቆርቋሪነትን የሚያጎለብቱ የድጋፍ እርምጃዎችን እንድትወስድ
ኮሚቴው ይመክራል። አባል ሀገሯ በድርቅና በግጭት የተጎዱ ሕጻናትን ችግር ለመፍታት ልዩ መርሃ ግብሮችን
በማዘጋጀት እና በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅእኖ ለማካካስ የሚስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን
እድትወስድ ኮሚቴው ያበረታታል። በተጨማሪም አባል ሀገሯ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ በምትሰጥበት

6
ወቅት ለሴት ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ጨምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ባሉ ሕጻናት ላይ የሚደርስ
መድልዎ ከግምት ዉጥ እንድታስገባ እና እንድትከላከል ኮሚቴው አሳስቧል።

ለሕፃናት ጥቅም ቅድሚያ መስጠት

13. ኮሚቴው አባል ሀገሯ ለሕፃናት ጥቅም ቅድሚያ የመስጠት መርህን በሕግ ማዕቀፎች እና ሌሎች እርምጃዎች
ውስጥ ማካተቱን በአድናቆት ተገንዝቧል። ኮሚቴው በፍርድ ቤት ሂደት ለሕፃናት ጥቅም ቅድሚያ መስጠት
መርህን በሚመለከት መሻሻል እንደታየ ከምንጮቹ መገንዘብ ችሏል። ኮሚቴው አባል ሀገሯ ሁሉም ሴክተሮች
በፖሊሲዎቻቸው እና በውሳኔዎቻቸው ውስጥ የህፃናትን ጥቅም ማስቀደምን በቂ ትኩረት እንዲሰጡ

ያበረታታል። ኮሚቴው እንደ ዳኞች፣ ፖሊስ፣ ዐቃብያነ ህጎች፣ ማኅበራዊ ሰራተኞች፣ የስራ ስምሪት
ተቆጣጣሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎችና መኮንኖች በሕፃናት መብት እና ለሕፃናት ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን
በሚመለከት የሰለጠኑ እንዲሆኑ ይመክራል። እንዲሁም ኮሚቴው የበጀት አመዳደብ፣ የሰው ሃይል ስምሪት እና
ሌሎች የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች የሕፃናት ጥቅም ቀዳሚነትን ታሳቤ ያደረጉ እንዲሆኑ፣ እና የተለያዩ የሕግ
ማዕቀፎች በሕፃናት ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖ ግምገማ እንዲደረግበት ኮሚቴው ያበረታታል። በተጨማሪም
ኮሚቴው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አውድ ውስጥ የሕፃናትን ጥቅም የማስቀደ መርህን በተግባር እንድታረጋግጥ
አባል ሀገሯን ይመክራል።

በሕይወት የመኖር፣የህልውና እና የዕድገት መብት


14. ኮሚቴው በሰሜናዊው የሀገሪቷ ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተከሰቱትን የሕፃናት ግድያዎችን
የሚያሳዩ የተለያዩ ሪፖርቶችን ተመልክቷል። በተጨማሪም ኮሚቴው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቁጥራዊ
መረጃ መሰረት ከ 5.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በከባድ ድርቅ የተጠቁ መሆኑን ከእነዚህም ውስጥ ብዙ ሕፃናት
በምግብ እጥረት የተጎዱ እና የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ኮሚቴዉ በተቆርቋሪነት ይገነዘባል።
ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ 2011 እና 2016 መካከል ከተመዘገበው እድገት ጋር ሲነፃፀር በ 2016 እና 2019
መካከል የሕፃናት ሞት ፣ የመቀንጨር እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላይ የታየዉ መሻሻል ጉልህ አለመሆኑን
ኮሚቴው አስተዉሏል።
በመሆኑም ኮሚቴው ለአባል ሀገሯ የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች ያቀርባል፡-
 በሰሜናዊው ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተጨማሪ የሕፃናት ግድያ እንዳይኖር ተጨባጭ
የመፍትሄ እርምጃዎች መወሰዳቸውን እንድታረጋግጥ እና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ
የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑ እንድታደርግ፤

7
 የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን፣ መቀንጨርን እና የሕፃናትን ሞትን በመቀነስ ረገድ ያለውን ጥረት
ከፍ በማድረግ በተለይም የምርት አቅርቦትንና ቅበላ በማሻሻል፣ በግብርና ምርቶች ላይ
መመሪያዎችን በመስጠት፤ የተመጣጠነ ምግብን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የምግብ አቅርቦቱን
ፍትሃዊ ስርጭት በማረጋገጥ፣ለቤተሰቦች እና ገበሬዎች የስነ-ምግብ ትምህርት መስጠትን
ጨምሮ በቤተሰብ ደረጃ የሚገኙ ምርቶችን ያማከለ የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት
መመሪያዎችን በማቅረብ እና በልዩ ትኩረት ለመጀመሪያው ስድስት ወር ጡት ማጥባትን እና
ከስድስት ወር በኋላ ተጨማሪ ምግብ ያለውን አስፈላጊነት በማስተዋወቅ የሕፃናትን ህልውና
ስትራቴጂ እንዲተገበር፤
 የወባ ትንኝ አጎበር መሰራጨቱን በማረጋገጥ፣ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት በከባድ
የመተንፈሻ አካላት ህክምና የሰለጠነ የሰው ሃይል መመደቡን በማረጋገጥ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣
ንፅህና እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች አቅርቦትን በማሟላት፣ በክትባት በሽታን የመከላከልና
የመቋቋም አቅምን በማሳደግ፣የሰዉነትን ፈሳሽ የሚተካ (ORS) አቅርቦትን በማስፋት እንዲሁም
በሽታን ለመከላከል እና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ
እርምጃዎችን በመውሰድ ሕፃናት በሚድኑ በሽታዎች ምክንያት እንዳይሞቱ እንድታደርግ፤

 ከአጋር አካላት እና ከለጋሾች ጋር በመተባበር እንዲሁም ተገቢውን አቅርቦት በመመደብ በድርቅ


ለተጎዱ አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ እና አፋጣኝ የምግብ እርዳታ በመስጠት፤ በአካባቢው
የትምህርት ቤቶችን የምገባ መርሃ ግብር በማስፋትና ብዙ ሕፃናትን ተጠቃሚ በማድረግ እና
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለሕፃናት ጥበቃ የሚሰጠው ምላሽ በግጭቱ የተጎዱ ሕፃናትን ልዩ
ፍላጎትና ተጋላጭነት ያገናዘበ መሆኑን እንድታረጋግጥ።

የሕፃናት አመለካከት
15. ኮሚቴው በ 2017 የብሔራዊ የሕፃናት ፓርላማ ማቋቋሚያ መመሪያዎች ለማሻሻል የተደረገውን ክለሳ እና

በሁሉም ክልሎች የሕፃናት ፓርላማዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሕፃናት ተሳትፎ መድረኮችን መቋቋሙን

ያደንቃል። ሆኖም ኮሚቴው በፌዴራል ደረጃ የሕፃናት ፓርላማ አለመኖሩን እና ይህም ሕፃናት በውሳኔ አሰጣጥ

ላይ ያላቸዉ ሚናና አስተዋፀዖ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና ለሕፃናት ፓርላማዎች የበጀት ድልድል

አለመኖሩን ተገንዝቧል፡፡ ኮሚቴው በሕፃናት ተሳትፎ ላይ የባህል ማነቆዎች እንዳሉ እና የሕጻናት አስተያየቶች

እና የውሳኔ ሃሳቦች ተገቢውን ዋጋ እንዳልተሰጣቸውም ተመልክቷል። ኮሚቴው አባል ሀገሯ ከሁሉም ክልሎች

የተውጣጡ ሕፃናት የሚወከሉበት እና በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን የሚገልጹበት የሕፃናት

ፓርላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲቋቋም ይመክራል። አባል ሀገሯ ለሕፃናት ፓርላማዎች ተግባራቸውን

8
እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸዉን በቂ በጀት እንድትመድብ፤ በማኅበረሰብና እና ቤተሰብ ደረጃ ስለ ሕፃናት

ተሳትፎ ጠቀሜታ ግንዛቤ ማሳደጊያና ማንቂያ ስራዎቸን እንድታካሂድ፣ ሕፃናት ትርጉም ያለው ተሳትፎ

እንዲኖራቸው ለማስቻል; እና የተሰበሰቡት ሕፃናት አስተያየቶች እና የውሳኔ ሃሳቦች በፖሊሲዎች ህጎች እና

ሌሎች ውሳኔዎች ውስጥ ከግምት ዉስጥ መግባታቸዉን እንድታረጋግጥ ኮሚቴዉ ይመክራል ።

መ. የሲቪል መብቶች እና ነፃነቶች

ስም የማግኘት፣ የዜግነት እና የልደት ምዝገባ መብት


16. ኮሚቴው ሀገሪቷ በ 2017 የወሳኝ ኹነቶችን እና ዜግነትን የሚመራውን አዋጅ ማሻሻያ ማደረግዋን እና
በወሊድ ምዝገባ ላይ ያደረገቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች በደስታ ይቀበላል። ይህ ጥረት
ቢደረግም የወሊድ ምዝገባው በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ ለአንዳንድ የልደት ምዝገባዎች የልደት የምስክር ወረቀት
አለመሰጠቱ፣ የወሊድ ምዝገባዉ በክፍያ መሆኑ እና ዘግይተዉ ለሚመዘገቡ የገንዘብ መቀጮ እንደሚከፈል

መደረጉና እና ሁለቱም ወላጆች ለምዝገባ መቅረባቸዉ ግዴታ መሆኑ ኮሚቴውን አሳስቦታል። ስለሆነም
ኮሚቴዉ ሀገሪቷ የሚከተሉትን እንድትፈፅም ያበረታታል፡፡

 ከመመዝገቢያ ጋር የተያያዘውን ክፍያ በማስወገድ እንዲሁም ዘግይቶ በመመዝገቢያ ላይ


የተጣሉትን ቅጣቶች በማስወገድ የልደት ምዝገባ ለሁሉም ነጻ መሆኑን እንታረጋግጥ;
 ሁለቱም ወላጆች ለምዝገባ መገኘት አለባቸው የሚለው መስፈርት እንዲነሳ ወይም በተለዬ
ሁኔታ ከነጠላ ወላጆች የተወለዱ ሕፃናት፣ ወላጅ አልባ ታዳጊዎች፣ ስደተኛ እና ተፈናቃይ
እንዲሁም ከቤተሰብ የተለያዩ ሕፃናት መስተናገድ የሚችሉበት ስርዓት እንድታስቀምጥ
 የልደት የምስክር ወረቀቶች ከምዝገባ በኋላ ወዲያውኑ መሰጠቱን እንድታረጋግጥ;
 ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ለማበረታታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን
እንድታጠናክር; እና
 የጤና ተቋማት ወይም የወሳኝ ኹነት መዝገብ ቤቶቸ ተደራሽ ባልሆኑባቸዉ ሩቅ አካባቢዎች
ለሚኖሩ ሕፃናት ተንቀሳቃሽ የወሊድ ምዝገባ አገልግሎት እንድትሰጥ ኮሚቴዉ ያበረታታል።

ሀሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት፣ አግባብ ያለው የመረጃ ተደራሽነት፣ የሀሳብ፣ የህሊና እና የኃይማኖት ነጻነት ፣ የግል
ህይወት የመጠበቅ መብት
17. ኮሚቴው ሕፃናት ሃሳባቸውን በሕፃናት ፓርላማዎች እና በሕፃናት ክበቦች መግለፅ መቻላቸውን እና በፍርድ

ቤት ሂደቶች ግላዊነታቸው የተጠበቀ መሆኑን መዝግቧል። ኮሚቴው ሀገሪቷ በሕፃናት የሚመሩ አደረጃጀቶች

9
ለመመስረት እና የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል መብታቸውን የበለጠ እንድታረጋግጥ

ያበረታታል። ሀገሪቷ ሕፃናት ሀሳባቸውን ትርጉም ባለው መልኩ እንዲገልጹ የሚያስችሉ የሕፃናት ክለቦችን እና

ፓርላማዎችን ጨምሮ በሕፃናት የሚመሩ ተቋማት የሚጠናከሩበት የአቅም ግንባታ ስራዎች እንድትወስድ፤

እና ሕፃናት እራሳቸውን ችለው እንዲያስቡ እና በየጊዜው እያደገ የሚሄድ አቅማቸውን ያገናዘበ መሰረታዊ

ነፃነታቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል ትምህርት በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንድታካትት ኮሚቴው

ያበረታታል። በተጨማሪም ኮሚቴው አባል ሀገሯ ከየትኛውም ሃይማኖት የተውጣጡ ሕፃናት በዚህ ዓይነት

ሃይማኖት ተኮር ውጥረት ውስጥ እንዳይገቡ በትምህርት ቤቶች እና በመገናኛ ብዙሃን ስለ መቻቻልና አብሮ

መኖር እንዲማሩ እድታረግ ያበረታታል። ከዚህ በተጨማሪ አባል ሀገሯ በፍርድ ቤቶች ሂደቶች እና ሌሎች እንደ

መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እና ሌሎች አስተዳደራዊ ሂደቶች ያሉ አውዶች ውስጥ የሕፃናትን ግላዊነት ነፃነት

እንድትጠብቅ እና የልጆችን ግላዊነት መብት በሚጥሱ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ኮሚቴው ይመክራል።

ከጥቃት እና ማሰቃየት መጠበቅ


18. ኮሚቴው ማንኛውም አይነት ጥቃቶች በሕግ መከልከላቸውን እና በመመሪያ የአካላዊ ቅጣት በትምህርት

ቤቶች የተከለከለ መሆኑን ተገንዝቦ አድንቋል።ሆኖም ኮሚቴው በአባል ሀገሯ ውስጥ የሕቫናት ጥቃቶች

መቀጠል ፈታኝ ሆኖ እንደቀጠለና አካላዊ ቅጣት አሁንም በስፋት በትምህርት ቤቶች፣ በእንክብካቤ ተቋማት

እና በቤት ውስጥ በስፋት መተግበር መቀጠሉ አሳስቦታል፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው በሚከተሉት ጉዳዮች ምክረ

ሀሳቡን ለአባል ሀገሯ ያቀርባል፡-

 በሁሉም ቦታዎች በቤት ፣ በትምህርት ቤቶች እና በእንክብካቤ ተቋማት ጭምር ሁሉንም ዓይነት
የአካል ቅጣትን የሚከለክል ሕግ እንዲወጣ
 ለመምህራን፣ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኃላፊዎች፣ እና በእንክብካቤ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ
እና ለሌሎችም የአካላዊ ቅጣት ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ እና ስለአማራጭ
የማረሚያ/የስነምግባር ዘዴዎች ሰፊ እና ተከታታይ ስልጠናዎችን እንዲሰጥ።
 ስለ መልካም አስተዳደግ እና አካላዊ ቅጣት ማኅበረሰባዊ መዋቅሮችን እንዲሁም እንደ
ቴሌቪዥን, ሬድዮ እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ለማኅበረሰቦች እና ቤተሰቦች
የግንዛቤ ማስጨበጫና የማንቂያ ስራዎች እንዲከናወኑ፤ በዚህም ሩቅ አካባቢዎችን ጨምሮ
ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ
 ሕፃናት ወይም ማንኛዉም ሰው እነሱን ወክሎ የሚደርስባቸውን ጥቃት እና ማሰቃየትን ሪፖርት
ለማድረግ እንዲችል ለሕፃናት ተስማሚ የሆነ የጥቆማ አቀራረብ አሰራርን እድታቋቁም፣ እና
አጥፊዎችን ክስ ተመስርቶባቸዉ መቀጣታቸዉን እንድታረጋግጥ።

10
ሠ. ቤተሰባዊ አካባቢ እና አማራጭ እንክብካቤ የወላጅ መመሪያ እና የወላጅ ኃላፊነቶች

19. አባል ሀገሯ በአዎንታዊ የወላጆች አስተዳደግ ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እና ማኅበረሰብ ተኮር

ትምህርት መስጠቷን ኮሚቴው በአድናቆት ተገንዝቧል፡፡ በሪፖርት ዓመቱ የመንግሥት ሠራተኞችን እና

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጆችን በማሻሻል የወሊድና የአባትነት የሥራ ፈቃድ ቀናት እንዲጨመር መደረጉ እና

በአዋጅ ቁ. 1064/2009 መሠረት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ ማዕከሎች መቋቋማቸውን

ኮሚቴው በደስታ ተቀብሎታል፡፡ በተጨማሪም ኮሚቴው የገጠር እና የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችን

በማዘጋጀት በኢኮኖሚ የተቸገሩ ቤተሰቦች የገንዘብ እና የምግብ አቅርቦቶችን እና የሕፃናት ድጋፍ ፕሮግራምን

ያደንቃል። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ጥረቶች ቢደረጉም ቤተሰቦች አሁንም በድህነት ምክንያት በገንዘብ ችግር

ውስጥ እንደሚገኙና በዚህም ምክንያት የቤተሰብን አካባቢ ሁኔታ ለማጣት የሚጋለጡ ሕፃናት ቁጥር ከፍ ያለ

መሆኑን ገልጿል።

20.የአባል ሀገሯ የደህንነት መረብ (የሴፍቲኔት) ፕሮግራሞችን በማስፋፋት በገጠርም ሆነ በከተማ ፕሮግራሞች

ተጨማሪ ቤተሰቦች እንዲሸፈኑ፣ የሕፃናት የድጋፍ ፕሮግራምን ማስተዋወቅ እና ከግሉ ሴክተር ጋር በመቀናጀት

ድጋፎች እንዲጨምሩ እና ተጨማሪ ድህነትን የማጥፋት ፕሮግራሞችን እንዲትተገብር ኮሚቴው ይመክራል።

አባል ሀገሯ በአዎንታዊ አስተዳደግ ፣ በወላጅ እና በልጆች ግንኙነት፣ በግጭት አፈታት ክህሎት እና የቤት

ውስጥን ሁኔታ ለሕፃናት ተስማሚ ለማድረግ ከቤተሰቦች ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክር ኮሚቴው

ይመክራል። በተጨማሪም ኮሚቴው በ 2009 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሠረት በሁሉም የመንግሥት መስሪያ

ቤቶች ውስጥ የሕፃናት ማቆያ ማዕከሎችን ለማቋቋም አባል ሀገሯ በቂ በጀት በመመደብ የወላጆችን ኃላፊነት

እንድትደግፍ ይመክራል።

ከቤተሰብ ስለመለያየት እና ከቤተሰብ ጋር መልሶ ስለማገናኘት


21. ልጆች ከአንዱ ወይም ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር በሚለያዩበት ጊዜ አባል ሀገሯ መልሶ ማገናኘትን ጨምሮ
ሌሎች በርካታ አማራጭ ሂደቶችን ጥቅም ላይ እንዳዋለች ተገንዝቧል። አባል ሀገሯ የሕፃናት ቀለብ አወሳሰን
መመሪያን እያረቀቀች መሆኗን ከአንድ ወይም ከሁለት ወላጆቹ የተለዩ ሕፃናትን በተመለከተ በቀለብ ውሣኔ
አሰጣጥ ላይ ለዳኞች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተገንዝቦ ኮሚቴዉ አድናቆቱን ይገልፃል። በዚህ ረገድ ኮሚቴው
አባል ሀገሯ የልጆችን ጥቅም እና ደኅንነት የማስቀደም መርሕን በመመሪያው ውስጥ በመሠረታዊ መርሆነት
መካተቱን እና መመሪያው የፍርድ ቤት የተሰጡ የቀለብ ውሳኔዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ አሠራረሮችን
ያካተተ ስለመሆኑ እንድታረጋግጥ ይመክራል፡፡ ረቂቅ መመሪያውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
ኤጀንሲዎች ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማጋራት ማናቸውም አስፈላጊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ

11
ተቀባይነት ያላቸው መመዘኛዎች መካተታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ኮሚቴው አሳስቧል። ኮሚቴው አባል
ሀገሯ የልጆችን ከቤተሰብ መለየትን እንደ የመጨረሻ አማራጭ እንድትወስድ እና የልጆችን መለየት፣ መቀላቀል
ወደ ቤተሰባቸው መመለስን ለሚወስኑ የማኅበራዊ እና ሌሎች ባለሙያዎችን እና ሠራተኞችን እንድታሰለጥን
ኮሚቴው ይመክራል። ኮሚቴው ለታዳጊዎች ስለ ግጭት አፈታት፣ የሕፃናት ከወላጆቻቸው መለየትን እና
የውሣኔ አሰጣጥ ክህሎትን በተመለከተ የአባል ሀገሯ ስልጠና እና መረጃ እንድትሰጥ ይመክራል።

አማራጭ (ተለዋጭ) እንክብካቤ እና ጉዲፈቻ


22. ኮሚቴው የአባል ሀገሯ ፍላጎት ሕጻናት በእንክብካቤ ተቋማት የማይገቡበት (deinistitutionalization of children)
ሂደትን፣ የማኅበረሰብ አቀፍ እንክብካቤን፣ የማኅበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ ጥምረትን እና የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ማሳደግ
እንደሆነ በዚህም መሰረት የፎስተር አገልግሎት እና የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን የሚመለከት ብሔራዊ መመሪያ ያላት ስለመሆኑ
ኮሚቴው አመስግኗል። ኮሚቴው ከ 2010 ዓ.ም ጀምሮ የአባል ሀገሯ ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን እንደከለከለችም ተመልክቷል፡፡
እነዚህ ጥረቶች የሚያስመሰግኑ ቢሆንም በሪፖርት ዓመቱ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ቁጥር እድገት እንዳላሳየ ኮሚቴው
ተገንዝቧል። እንደ የአባል ሀገሯ ሪፖርት (ገጽ 60) በ 2010/2011 የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ቁጥር በ 2008 እስከ 2010
ዓመታት ውስጥ ከነበረው የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል። በተጨማሪም ኮሚቴው የአማራጭ
እንክብካቤ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ የሕፃናት ምደባን እና አማራጭ እንክብካቤን ለመምረጥ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ
እንደሌለ ተገንዝቧል።
23. ኮሚቴው አባል ሀገሯ ከቻርተሩ፣ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና መመዘኛዎች በተለይም ከተባበሩት
መንግሥታት የአማራጭ እንክብካቤ መመሪያዎች ጋር የተጣጣመ ሁሉን አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ እንድታወጣ
ይመክራል። ኮሚቴው አባል ሀገሯ ሰራተኞቿ ተገቢውን ግምገማ እንዲያካሂዱ እና ከቤተሰብ ጋር ለመኖር
ያለታደሉ ሕፃናትን አስተዳደግ ሁኔታ ስልታዊ በሆነ መልኩ ለመለየት እንዲችሉ የሚያደርግ ስልጠና እንዲሰጥ
ይመክራል። አባል ሀገሯ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን እና ቀደም ብለው የነበሩት ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻዎችን
ጨምሮ ሁሉንም የአማራጭ እንክብካቤ ዓይነቶችን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል የሚያስችሉ ግብአቶችን
እንድታሳድግ ያበረታታል። ኮሚቴው አባል ሀገሯ የሔግ የውጭ ጉዲፈቻ የሕፃናት ጥበቃ እና ትብብር ዓለም
አቀፍ ስምምነትን እንድታፀድቅ ኮሚቴው ያበረታታል፡፡ አባል ሀገሯ የሕፃናትን ተቋማዊ እንክብካቤ ለማስቀረት
የምትሰራው ስራ እንዳለ ሆኖ ሕፃናት በአማራጭ የቤተሰብ ሁኔታ እንክብካቤ ማዕቀፍ ውስጥ እስኪካተቱ ድረስ
አባል ሀገሯ የሕፃናት ተንከባካቢ ተቋማትን እንድትከታተል ኮሚቴው ይመክራል። የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን፣
የፎስተር አገልግሎት እና ሌሎች ቤተሰብን መሰረት ያደረገ አማራጭ እንክብካቤን በማስተዋወቅ እና ግንዛቤን
በማሳደግ ቤተሰባዊ አካባቢ ሁኔታን የተነፈጉ ሕፃናትን እንድትደግፍ ኮሚቴው አባል ሀገሯን ይመክራል።

መሰረታዊ ጤና እና ደህንነት
24. ኮሚቴው የአምስት ዓመቱን የጤና ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ የሕፃናት ህልውና ስትራቴጂ፣ የሕፃናት ጤና፣ የእድገት እና
ልማት ፍኖተ-ካርታ እንዲሁም ብሔራዊ የስነ-ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂን በደስታ ይቀበላል። ኮሚቴው የጤና ኤክስቴንሽን
መርሐ-ግብር ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተጨማሪ በማኅበረሰብ አቀፍ ደረጃ በጎ ፈቃደኞችን በማካተት እንዲሁም
12
የጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመስግኗል። የአባል ሀገሯ ዘገባ በተጨማሪም
ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣ የጨቅላ እና አራስ ሕፃናት ሞት መቀነስ፣ የሰለጠነ የቅድመ ወሊድ እና የወሊድ
አገልግሎት ተደራሽነት መጨመር፣ የሕፃናት የክትባት መጠን መጨመር እና የመቀንጨር እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
መቀነስን ተገንዝቧል፡፡ ኮሚቴው የአባል ሀገሯ የእናቶች እና አራስ መንጋጋ ቆልፍ በሽታን ለማጥፋት መቻሉን
አመስግኗል።ይሁን እንጂ ኮሚቴው ባለፉት ዓመታት የጤና በጀት የነፍስ ወከፍ ወጪ መቀነሱን ተገንዝቧል። የክትባት መጠን
እየጨመረ ቢሄድም፣ የተከተቡ ሕፃናት መጠን በጣም ዝቅተኛ ሆኖ 43% ሆኖ ሲገኝ 20% ሕፃናት ምንም ዓይነት ክትባት
ያልወሰዱ በመሆኑ በቅርቡ በሀገሪቷ የፖሊዮ በሽታ መከሰቱን ተመልክቷል። ኮሚቴው በጤና አገልግሎት ተደራሽነት፣የጤና
ኬላዎች፣የማዕከል እና የሆስፒታሎች አቅርቦት፣የክትባት መጠን፣እንዲሁም የቅድመ ወሊድና የወሊድ አገልግሎትን
በተመለከተ ያለውን ትልቅ ክልላዊ ልዩነት አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል።በመሆኑም ኮሚቴው የአባል ሀገሯን የሚከተለዉን
ይመክራል።

 ለጤና ሴክተር የሚሰጠውን የበጀት ድልድል እንድታሳድግ እና የአቡጃ መግለጫን መስፈርት በማሟላት ከበጀቷ
ቢያንስ 15% ለጤና ዘርፍ በመመደብ እና ለጤና ሴክተሩ የበጀት ድልድል በመጨመር ከዋጋ ግሽበት እና
የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የተመጣጠነ መሆኑን እንድታረጋግጥ
 እንደ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ባሉ አነስተኛ አፈጻጸም ባላቸው ክልሎች ላይ
ያነጣጠሩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ በኮቪድ-19 ጊዜም ቢሆን መሰል አገልግሎቶች መኖራቸውን እና
ሕብረተሰቡም ኮቪድ-19 ቢኖርም አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለባቸዉ ግንዛቤ እንድትፈጥርና
የጤና ተቋማት ብዛት፣ከክትባት፣የሰለጠነ የቅድመ ወሊድና የወሊድ አገልግሎት ተደራሽነት፣የጤና
አገልግሎት ጥራትን በተመለከተ ክልላዊ ልዩነቶች እንድታስተካክል
 በጉርምስና ዕድሜ ላይ ባሉ ወጣቶች መካከል ስለ ፆታዊ ሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ያለውን
ግንዛቤ ማሳደግ እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን አገልግሎቶች በጉርምስና ዕድሜ ላሉ
ወጣቶች ተስማሚና ተደራሽ መሆናቸውን እንድታረጋግጥ።
 ስለ ኤችአይቪ እና ከእናቶች ወደ ሕፃናት ስለሚተላለፉ ኤችአይቪ ግንዛቤን በማሳደግ ወደ ህክምና
ማእከላት የሚመጡ ነፍሰጡር እናቶች በሙሉ ምርመራ እንዲደረግላቸው፣ የምክር እና ከወሊድ
በኋላ ያሉ የቫይረስ መከላከያና መቆጣጠሪያ (ARV) ህክምናዎች እንዲደረግላቸው ፣
 የክትባት አገልግሎቶቸ በማኅበረሰብ ደረጃ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መሰጠቱን
፣በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለክትባት ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም መሰጠቱን፡ ሕብረተሰቡ
በአቅራቢያው በሚገኙ ጤና ኬላዎች የክትባት አገልግሎት ማግኘት መቻሉን ፣ ራቅ ባሉ
አካባቢዎች የተንቀሳቃሽ የክትባት አገልግሎት መሰጠቱን እንድታረጋግጥና እና የፖሊዮ ወረርሽኝን
የክትባት ዘመቻ በሁሉም ክልሎች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲካሄድ እና

13
 በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ውስጥ አስፈላጊ
የሆኑ መገልገያዎችን፣ መሳሪያዎችና መድሃኒቶችን በማቅረብ እንዲሁም በጤና ተቋማት ያሉ
የጤና ባለሙያዎችን እና ዶክተሮችን ቁጥር በመጨመር የጤና አገልግሎትን ጥራት እንድታሳድግ
 ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተስማሚ የጤና አገልግሎት በመስጠት አገልግሎቶችን ተደራሽ
እንድታደርግ፤ የጤና ባለሙያዎችን ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት እንክብካቤ መስጠት እንዲችሉ
በማሰልጠን እና በተቻለ መጠን የአካል ጉዳትን የመከላከል ስራ መሰራቱን እድታረጋግጥ እና የአካል
ጉዳተኛ ሕፃናትን ችግሮች የሚያወሳስቡ ችግሮችን ለመቀነስ እና የሕይወታቸውን ስምረትና
ጥራትን ለመጨመር የሚያስችሉ የቅድመ መከላከልና ልዬታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን
እንድታረጋግጥ፤ እና
 ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሕፃናት የአደጋ ጊዜ ሕክምና እንዲያገኙ
ስትራቴጂዎችንና መርሐ ግብሮችን በመንደፍ እንዲሁም በግጭት አካባቢዎች ለረጂም ጊዜ
ያልተሰጡ የተለያዩ የሕፃናት በሽታ መከላከያ እርምጃዎችን፤ የክትባት ዘመቻዎችን፣ እና
ከኤችአይቪና ከሌሎች በሽታዎች ጋር የተያያዙ ሕክምናዎችን የማያካክሱ ስራዎች እንዲሰሩ

ትምህርት፣ መዝናኛ እና ባህላዊ እንቅስቃሴዎች


25. መንግስት የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብርን እና የትምህርት ልማት ፍኖተ ካርታ እና የቅድመ ልጅነት እድገት ትምህርት፣
ትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት የጀመረውን ሂደት ኮሚቴው አድንቋል።ኮሚቴው የሁሉም ደረጃ ትምህርት
ቤቶች ቁጥር መጨመሩን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ነፃ መሆኑን እና መንግሥት ለታዳጊ ክልሎች 5% የድጎማ በጀት
በመመደብ የክልሎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲደገፍ ማድረጉን አድንቋል።የአባል ሀገሯ ከበጀቷ ከ 20% በላይ
ለትምህርት ሴክተሩ በመመደብ በ 2012/2003 የመንግስት ወጪ 27% ለትምህርት ዘርፍ እና በ 2017/2018 ከሀገር አቀፍ
በጀት 25% ለትምህርት ዘርፍ መመደቡን ኮሚቴው አመስግኗል።በሁሉም ክልሎች አካታች የትምህርት መርጃ ማዕከላት
መስፋፋታቸውንም ኮሚቴው ተገንዝቦ አድናቆቱን ገልጿል።

26. ነገር ግን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በሕግ የግዴታ አለመሆኑን፣ የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ መጠን እየቀነሰ
መምጣቱን፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በሁለተኛ ዙር ከፍተኛ የማቋረጥ ችግር መኖሩ እና በትምህርት ቤቶች
ብዛት፤በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በተመዘገቡ የተማሪዎች ቁጥር፣ በሥርዓተ-ፆታ ስብጥር እና በትምህርት ጥራት ከፍተኛ
ክልላዊ ልዩነት መታየቱ በተለይም ሶማሌ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች ዝቅተኛ እድገት ያላቸው ክልሎች መሆናቸዉ
ኮሚቴዉን አሳስቦታል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከመጀመሪያ ሳይክል ወደ መደበኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቀጥሎም ወደ ሁለተኛ
ደረጃ ትምህርት የማለፍና የመሸጋገር ምጣኔ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ትምህርት የማቋረጥ እና ክፍል የመድገም ምጣኔ ከፍተኛ
መሆኑ ኮሚቴውን አሳስቦታል። ትምህርት የማቋረጥ መጠን ከፍተኛ ሆኖ እያለ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ያለው
ተሳትፎ ከ 2017 ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ ነው። ኮሚቴው ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ተማሪዎችን
በትምህርት ላይ ለማቆየት ትምህርት ቤቶች ያላቸው ደረጃና ዝግጅት በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና 30% የማይሞሉ ትምህርት

14
ቤቶች ብቻ የመብራት አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑን፣ 27%ቱ ብቻ ውሃ የሚያገኙት መሆኑን እና በሁለተኛ ደረጃ የመማሪያ
መጽሀፍት ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱንም ኮሚቴዉ ተገንዝቧል። የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ትምህርት በተመለከተ በቅድመ
መደበኛ ትምህርት የተመዘገቡት አካል ጉዳተኞች 1.3 % ፣በአንደኛ ደረጃ 11% ፣በሁለተኛ ደረጃ 2.8% ብቻ መሆናቸዉን
እና 36% ትምህርት ቤቶች ብቻ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ምቹ መፀዳጃ ቤት እንዳላቸው ተገንዛቧል። በመሆኑም ኮሚቴው
የአባል ሀገሯን የሚከተለዉን ይመክራል።

 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነፃ እና የግዴታ መሆኑን በማረጋገጥ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ


ትምህርት ቤት እንዲልኩ በሁሉም ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንዲሰራ።
 በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ መዋእለ-ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በሁሉም ክልሎች ተጨማሪ
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን እንድትገነባ፣ ተማሪዎችን ክፍል እንዳይደግሙ ስለሚከላከል
እና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ
ተጽእኖ ስላለው መምህራንን በቅድመ ልጅነት እድገት ላይ እንድታሰለጥን
 መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመወሰን እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ የሚመዘገቡ
ተማሪዎች ቁጥር የመቀነስ ምጣኔን እና እየጨመረ ያለውን ከአንደኛ ደረጃ እና ከሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት የማቋረጥ ምጣኔን መንስኤዎች እንድትለይ
 በሁሉም ክልሎች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣የዩኒፎርም አልባሳትን
በሁሉም ክልሎች በነፃ ማቅረብ፣የተዛማጅና ቀጥተኛ ያልሆኑ የትምህርት ወጪዎችን
ማስወገድ፣የትምህርት ቤቶችን የአካል ተደራሽነት ማሳደግ፣ንፅህና፣ውሃ፣ንፅህና መጠበቂያ ፓድ
የመሳሰሉ ግብአቶችን ማቅረብ የመሳሰሉ ተማሪዎችን በትምህርት ላይ ለማቆየት የሚያስችሉ
ስልቶችን እንድትተገብር።
 ከተለያዩ የስራ ዘርፎች ጋር በመተባበር ትምህርትን ለማቋረጥ የሚዳርጉ ውጫዊ ሁኔታዎችን
በትምህርት ቤቶች ለመፍታት የሚያስችሉ የፆታዊ ሥነ ተዋልዶ ትምህርትን መካተትን፣
ለአብዛኛዎቹ የተቸገሩ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን እና እንደ ሕፃናት ጋብቻ፣ ጾታዊ
ጥቃት፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ እርግዝና እና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ
ፕሮግራሞችን እንድታከናውን።
 ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ በመመደብ፣ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና የግንዛቤ
ማስጨበጫ ስራዎችን በማሳደግ አነስተኛ እድገት ላሳዩ ክልሎች የፕሮግራም እና የድጋፍ
ስልቶችን እንድትዘረጋ።
 በሁሉም ቦታዎች እየተገነቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ተስማሚ መሆናቸውን
እንድታረጋግጥ፣ እና የስርአተ ትምህርቱ ሁሉን አቀፍና አካታችነትን የሚፈቅድ እና የሚያመቻች
መሆኑን እንድታረጋግጥ።

15
 በአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ትምህርት ላይ የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት
በትምህርት ቤት ለሚመዘገቡ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሸጋገሩ
እና እንዲያጠናቅቁ ተጨማሪ ድጋፍ እና አዎንታዊ እርምጃ እንድትሰጥ።
 በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ቤቶች የተቀመጠውን ዝቅተኛ
መመዘኛ ማሟላታቸዉን እንድታረጋግጥ እና ስደተኛ እና የተፈናቀሉ ሕፃናትን በመደበኛ
ትምህርት ቤቶች በማዋካተትና ተጨማሪ ድጋፍ በማድረግ ያመለጡ ክፍለ ግዜያትን ወይም
አመታትን ለማካካስ እንድትሰራ።
 ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ፣ ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት ውጤት እንዲያመጡ
እንዲያግዙ እና የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ፍላጎቶችን ማካተት እንዲችሉ ለመምህራን ቀጣይነት
ያለው ስልጠና እንዲሰጥ፡፡

27. ከመዝናኛ እና ከመዝናኛ ተግባራት ጋር በተያያዘ ኮሚቴው የአባል ሀገሯ በግል እና በመንግስት ትምህርት ቤቶች
ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ አገልግሎቶችን ዓይነት እና እነዚህ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተደራሽ
መሆናቸውን የሚያረጋግጡ መስፈርቶቸንና ደረጃዎችን እንድታወጣ ኮሚቴው ይመክራል ። ኮሚቴው የአባል
ሀገሯ “ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ የከተማ መመሪያዎችን” ሙሉ በሙሉ እንድትተገብርና የመዝናኛ እና
የእረፍትና ቦታዎች እና የደህንነት ስሜት የሚፈጥሩ ስፍራዎች ከትምህርት ቤት ውጭ ላሉ ሕፃናትም ተደራሽ
እንዲሆኑ ምክረ ሃሳቡን ያቀርባል።
28. ኮሚቴው በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተዘጉበት ወቅት ያቋረጡ ሕፃናትን እንዲሁም በግጭቱ
ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ያልቻሉ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አባል ሀገሯ ልዩ
ዕርምጃዎችን እንድትወስድ ይመክራል።ኮሚቴው አባል ሀገሯ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 ፕሮቶኮሎችን
መከተላቸውን በማረጋገጥ፣ በግጭቱ ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ተጨማሪ በጀት
እንድትመድብ እና ትምህርት ቤቶች እስኪገነቡ ድረስ ጊዜያዊ የመማሪያ ቦታዎችን እንዲሰጥ
ይመክራል።ሀገሪቷ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የጠፋውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ የማካካሻ እርምጃ
እንድትወስድ፣ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመክፈት እቅድ ማውጣትን ጨምሮ ሁሉም ልጆች
(በተለይም ልጃገረዶች እና ሌሎች ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉትን) ትምህርት እንዳያቋርጡ
የሚያስችል ዘዴን በመዘርጋት እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ-ልቦና ድጋፍን እንድታከናዉን ያበረታታል፡፡

16
IV. የልዩ ጥበቃ እርምጃዎች

ስደተኛ እና የሀገር ዉስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት


29. ኮሚቴው አባል ሀገሯ ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍን በ 2017 ማፅደቋን፣ የስደተኞችን ስነ-አካላዊ
ዝርዝር ሁኔታ መመዝገቢያ የመረጃ ቋት በ 2017 ማስጀመርዋ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለስደተኛ ሕፃናት
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት እና ልደት ምዝገባ መብት የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም
ለወላሦቻቸው የመኖሪያ ቦታ የመምረጥ መብት፤ የመስራት መብት እና የቤተሰብ አባላት ተመልሰው ቤተሰብን
የመቀላቀል መብትን የሚሰጥ አዲስ የስደተኞች አዋጅ ቁጥር 1110/2019 መጽደቁን ያደንቃል። እንዲሁም
ኮሚቴው በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ መቋቋሙን እና በስደተኞችና
ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ውስጥ የሴቶች እና ሕፃናት ዴስክ መቋቋሙን ያወድሳል።መሰል የመሻሻል
እርምጃዎች የሚያስመሰግኑ ቢሆንም፣ የፖሊሲዎቹ አተገባበር ላይ ክፍተት መኖሩና በባለሥልጣናት ወጥነት
የጎደለው አሰራር እንዳለ ኮሚቴው ከተለያዩ ምንጮች ተገንዝቧል።ከዚህም በላይ በወሳኝ ኹነት ምዝገባ ወቅት
ሁለቱም ወላጆች እንዲገኙ የተቀመጠዉ መስፈርት ከወላጅ መሄድ ያልቻሉ ወይም ከአንዱ ወላጅ ጋር የሚሄዱ
ታዳጊዎችን ፈተና ላይ የጣለ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

30. የአባል ሀገሯ አስፈላጊውን ስትራቴጂ በማውጣት እና በቂ በጀት በመመደብ አዲሱን የስደተኞች አዋጅ ሙሉ
በሙሉ ተግባራዊ እንድታረግ ኮሚቴው ይመክራል። አዋጅ በተጣጣመ እና ወጥ በሆነ ደረጃ በባለሥልጣናት
እንዲተገበር፤ መንግሥት የሲቪል ኹነቶች ምዝገባ ጽ/ቤት ኃላፊዎችን እና ሌሎች ከስደተኞች ጋር ግንኙነት
ያላቸዉን ባለሙያዎችን ስለ አዲሱ አዋጅ እና ስለ ስደተኛ ሕፃናት እና ወላጆቻቸው መብት እንዲያሰለጥን
ኮሚቴው ይመክራል። ኮሚቴው የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ያለውን የጤና እንክብካቤ፣ የተመጣጠነ
ምግብ፣ የክትባት፣ የልደት ምዝገባ፣ የንፅህና አጠባበቅ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እና ሌሎች
አገልግሎቶችን ጥራትን እና ተደራሽነትን እንድታሳድግ ኮሚቴው ያበረታታል።ሀገሪቷ ከቤተሰብ ጋር መልሶ
በመቀላቀል እና አሳዳጊ (ወላጅ) ለሌላቸው ሕፃናት አማራጭ እንክብካቤ፣ ስደተኛ ሕፃናት በተቀባይ
ማኅበረሰቦች ውስጥ በማዋሃድ እና የተፈናቀሉ ሕፃናትን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በማድረግ ለስደተኞች እና
ለተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ እንድትሰጥ ይመክራል፡፡

ግጭቶች ውስጥ ያሉ ሕፃናት


31. በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተፈጠረው ግጭት የአባል ሀገሯ አቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ኮሚቴው

ተገንዝቧል።በትግራይ ክልል በ 2020 የተቀሰቀሰው ግጭት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎ አለመረጋጋት

እንደተፈጠረና በተለይም በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለሕፃናት መብቶች ጥሰቶች ምክንያት

መሆኑን ኮሚቴው ተገንዝቧል።በግጭቱ ምክንያት በርካታ ሕፃናት መፈናቀላቸውን፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና

17
ተቋማት መውደማቸውን፣ ሕፃናት ለትጥቅ ትግል መመልመላቸውን፤ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን እና

ሕፃናት ለፆታዊ ጥቃትና ብዝበዛ መጋለጣቸውን ኮሚቴው ተመልክቷል።ኮሚቴው የተባበሩት መንግስታት

ድርጅት ኤጀንሲዎች የተለያዩ ሪፖርቶችን እና የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ

ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ምርመራ በትግራይ ክልል የሕፃናትን ሁኔታ አስመልክቶ ያቀረቡትን ሪፖርት

ተመልክቷል።ኮሚቴው ከሪፖርቶቹ በጦርነቱ ወቅት በርካታ ትምህርት ቤቶች መዘረፋቸውንና

መውደማቸውን፣ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ወታደራዊ ጣቢያ ሆነው መቆየታቸዉን፣ የጤና ተቋማትም

በአቅርቦት እጥረትና የሆስፒታል ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የትራንስፖርት መንገዶች በመዘጋታቸው በአግባቡ

እየሰሩ እንዳልቆዪ ተገንዝቧል።በክልሉ እንዲሁም በአማራ እና አፋር ክልሎች የፆታ ጥቃት ግጭቱ (ጦርነቱ)

ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እየተባባሰ መምጣቱን ኮሚቴው ተገንዝቧል።በተጨማሪም በክልሉ ከ 5.5 ሚሊዮን

በላይ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጡ እንደሆኑ፣ ከ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ አስቸኳይ

የምግብ እጦት ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ይህም ሰብዓዊ እርዳታን አንገብጋቢ እንዳደረገው ኮሚቴው ተረድቷል

። እንዲሁም ግጭቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ወላጅ (አሳዳጊ) አልባ እንዳደረገ፤ ጠባቂ የሌላቸዉ እና

ያላቸዉ ታዳጊዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲፈናቀሉ ምክንያት እንደሆነ ተረድቷል።ከዚህም በላይ በግጭቱ

በተከሰተባቸው አካባቢዎች በተለይም በትግራይ ክልል ሕፃናት በሰብአዊ እርዳታ፣ በመብራት እና ሌሎች

መሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እጦት ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጋቸውን ኮሚቴው ተገንዝቧል።የአባል ሀገሯ

አንዳንድ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ኮሚቴው ቢገነዘብም፣ ኮሚቴው

የሕፃናት መብት ጥሰቱ መቀጠሉ አሳስቦታል፡፡

በዚህ ረገድ ኮሚቴው ለአባል ሀገሯ የሚከተሉትን ያሳስባል፡-

 ማንኛውም ሕፃን በየትኛውም የታጠቁ ቡድኖች እና ወታደራዊ ስርዓት ውስጥ እንዳይመለመል እና


በማናቸውም ሃይሎች የተመለመሉ ሕፃናት አስቸኳይ እና በቂ ማገገሚያ እንዲሰጣቸውና ወደ
ማሕበረሰቡ እንዲመለሱ እንድታረግ፤
 በግጭቱ አውድ ውስጥ ወሲባዊ በደል እና ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ። በኮሚቴው
ዝርዝር መረጃ ላይ አባል ሀገሯ በሰጠችዉ ምላሽ አንዳንድ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ጥፋተኛ
ሆነው በመገኘታቸው መቀጣታቸዉን የሚያሳይ ቢሆንም፣ እነዚህ ጥቂት ቁጥሮች ከተፈጠረው
ጥፋት ጋር የማይመጣጠኑ መሆናቸውን ኮሚቴው ተገንዝቧል።ስለሆነም መንግስት ይህንን ጥረት
አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በግጭቱ አውድ ውስጥ የፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን በጥልቀት

18
በመመርመር፣ በሕግ እንዲጠየቁ እና እንዲቀጡ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ኮሚቴው
ያበረታታል።
 ለሰላም የመደራደር ጥረቱን በማጎልበት በሁሉም ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ያልተገደበ
ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲዳረስ እንድታደርግ፤
 በግጭቱ ወቅት ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የስደተኞች እና የተፈናቃዮች ካምፖች እና
ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰቡ ያለባቸው አካባቢዎች ዒላማ አለመሆናቸውን እንድታረጋግጥ፤
 ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደ ኤሌክትሪክ፣ የባንክ አገልግሎት እና ሌሎች
አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እርምጃዎችን እንድትወስድ፤
 በግጭቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን
መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንድታሳድግ፤
 ከአንድ አመት በላይ ከትምህርት ቤት የራቁ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ፤ አማራጭ
የመማሪያ ዘዴዎችን እና ቦታዎችን ለማግኘት የአጭር ጊዜ ግብ እንድትቀርጽ፡፡ እንዲሁም የተጎዱ
ትምህርት ቤቶችን ወደነበረበት ለመመለስ እና ሰላም ለማስፈን የረጅም ጊዜ ግቦችን
እንድታፈላልግ፡፡
 ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ያለ ጠባቂ ያሉ ሕፃናትን ቤተሰብ የመፈለግእና የማገናኘት አገልግሎት
መስጠትን እና ወላጆቻቸው ካልተገኙ የቤተሰብ ሁኔታ የሚመስል አማራጮችን መመቻቸቱን
እንድታረጋግጥ።

በወንጀል ነገር ውስጥ የገቡ ሕፃናት


32. ኮሚቴው የሕፃናት ፍትሕ ስትራቴጂን ለመቅረፅ የተጀመረውን ሂደት፣አራት የሕፃናት የማገገሚያ/ተሃድሶ
ማዕከላት መቋቋማቸውን እና በወንጀል ወስጥ ለገቡሕፃናትልዩ የምርመራ ክፍሎች መኖራቸውን እና ለሕፃናት
ተስማሚ ችሎቶች መኖራቸውን በደስታ ይቀበላል፡፡ ኮሚቴው ባደረገው ገንቢ ውይይት የወንጀለኛ መቅጫ
ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እየተከለሰ መሆኑንና ማሻሻያው በወንጀል ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናትን ከመደበኛ
የፍርድ ቤት ሂደት ውጪ የሚታዩበትን አካሄድ /diversion/ ያካተተ መሆኑን ተረድቷል። ይሁን እንጂ ኮሚቴው
ሕፃናት በአብዛኛው የሚታሰሩት በቅድመ ክስ ደረጃ ላይ መሆኑን እና የሚታሰሩትምከአዋቂዎች ጋር
ተቀላቅለዉ መሆኑን፣ እና 4 ተሃድሶ ተቋማት ብቻ እንዳሉ እና አራቱ ተሃድሶ ተቋማት ካሉበት ቦታዎች ውጭ
የሚኖሩ ሕፃናት በአብዛኛው ከአዋቂዎች ጋር ተቀላቅለዉ የሚታሰሩ መሆኑን ተገንዝቧል። በተጨማሪም
ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ባደረገው የማጠቃለያ ምልከታ እና የውሳኔ ሃሳቦች የወንጀል ተጠያቂነት እድሜ እና
ከ 15 አመት በላይ የሆኑ ሕፃናትን በወንጀል ህግ እንደ አዋቂዎች የመያዛቸዉ ጉዳይ ላይ የተነሱት አንዳንድ
ስጋቶች ባለመቀረፋቸው አዝኗል።በተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ የወንጀል ሃላፊነት እድሜ
እና የሕፃናት ከአዋቂዎች የተለየ እስርና አያያዝ ጉዳይ መነሳቱንም ኮሚቴው ተገንዝቧል።
ስለዚህ ኮሚቴው የአባል ሀገሯን የሚከተሉትን ይመክራል፡-
19
 የሕፃናት ፍትሕ ስትራቴ የመቅረጽ ሂደት እንዲፋጠን እና ሕፃናት ከመደበኛ የፍርድ ቤት ሂደት ውጪ
የሚታዩበትን አካሄድ /diversion/፣ ሕፃናቱ ወደ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ለማዛወር ፣ የመፍሄ
መርሃ ግብሮችን እና በወንጀል ውስጥ ገብተው ለተገኙ ሕፃናት የተፋጠነ የፍርድ ሂደቶችን እንደሚሰጥ
የሚያስችሉ ስልቶች በስትራቴጂው ውስጥ መካተቱ እንዲረጋገጥ፤
 የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ማሻሻያ ከክስ በፊት እና በፍርድ ሂደት ደረጃዎች ውስጥ ወንጀል ውስጥ የገቡ
ሕፃናትን ከእስር ዉጪ ያሉ አማራጮችን እንደሚሰጥ እንድታረጋግጥ፤
 አዲስ በተቋቋመው የማኅበረሰብ አቀፍ የእርምት አገልግሎት ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበት
እና ፕሮግራሙን በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ፤
 ዝቅተኛውን የወንጀለኛ መቅጫ ዕድሜ ተቀባይነት ወዳላቸዉ የእድሜ ደረጃዎች ከፍ እንዲደረግ እና ከ 15
እስከ 18 ዓመት የሆኑ ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ውስጥ እንደ አዋቂ እንዳይታዩ ለማስቻል የወንጀል
ሕጉን የማሻሻያ ሂደት እንዲጀመር፤
 በወንጀል ውስጥ የገቡ ሕፃናት ሁሉ የተሃድሶ እና የማኅበረሰብ ጋር መልሶ የመቀላቀል አገልግሎት እንዲያገኙ
በሁሉም ክልሎች ተጨማሪ የተሃድሶ ማዕከላት እንዲቋቋሙ እንድታደርግ፤
 የተሃድሶ ማዕከላት በሁሉም አካባቢዎች እስኪቋቋሙ ድረስ የአባል ሀገሯ ሕፃናት በምንም መልኩ
ከአዋቂዎች ጋር እንዳይታሰሩ ለማድረግ እርምጃዎችን እንድትወሰድ፤ እና
ለዓቃብያነ-ሕግ፣ ለፖሊስ፣ ለዳኞች፣ ለማረሚያ ቤት አስተዳደር እና ለማኅበራዊ ጉዳይ ሰራተኞች በወንጀል
ውስጥ ገብተው ለተገኙ ሕፃናት የሚያስፈልገውን ጥበቃ እና በአለምአቀፍ መደበኛ መስፈርቶችና
ደረጃዎች መሰረት ሊከተሏቸው ስለሚገባቸው ሂደቶች ተከታታይ ስልጠና እንዲሰጥ ኮሚቴው ምክረ-
ሃሳቡን ያቀርባል፡፡

ከወላጆቻቸው ወይም ከተንከባካቢዎቻቸው ጋር የታሰሩ ሕፃናት

33. በሪፖርቱ ወቅት መንግስት ተንከባካቢዎቻቸው የታሰሩ ሕፃናትን እንክብካቤ በተመለከተ ከሕፃናት ማቆያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ
ባለድርሻ አጋሮች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ኮሚቴዉ ተመልክቷል። አባል ሀገሯ በዝርዝር በሰጠችዉ ምላሽ ኮሚቴው በእስር
ውጪ ያሉ አማራጮችን እንዲኖር የሚያረግ በማኅበረሰብ ላይ የተመሰረተ የእርምት ረቂቅ አዋጅ እንዳለ በመገንዘቡ ኮሚቴዉ
አድናቆቱን ይገልፃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተነሳሽነት ቢደረግም ሕፃናት አሁንም በመደበኛ እስር ቤት ከተንከባካቢዎቻቸዉ ጋር ታስረው
የሚገኙ መሆናቸዉ ኮሚቴዉን የሚያስቆጭ ሆኖ አግኝቶታል። ኮሚቴው ሀገሪቷ የቻርተሩን አንቀጽ 30 እንዲሁም በአንቀጽ 30 ላይ
የሰጠዉን አጠቃላይ አስተያየቱን ተግባራዊ እንድታደርግ እና በቻርተሩ መስፈርት መሰረት ሕፃናት ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር በእስር ቤት
እንዳይታሰሩ ለማድረግ እንድትሰራ ያበረታታል። በተጨማሪም የአባል ሀገሯ ዋና ተንከባካቢዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከእስር
ዉጪ ያለ ቅጣትን ተግባራዊ እንድታረግ እና የእስር ቅጣት አስገዳጅ በሚሆንበት ጊዜም ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር በእስር ላይ የሚገኙ
ሕፃናት ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ እና የተለዩ ክፍሎች እንዲመቻቹ ኮሚቴው ይመክራል። ኮሚቴው የአባል ሀገሯ ተንከባካቢዎቻቸዉ
በእስር ላሉ ሕፃናት በማደጎ ወይም በሌላ አማራጭ የቤተሰብ አያያዝ መንገዶች በማስቀመጥ ለሕፃናት እንክብካቤ ለመስጠት
የምታረገዉን ጥረት እንድታጠናክር ያበረታታል።

20
የሕፃናት ብዝበዛ
34. የአባል ሀገሯ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሕጉን በማሻሻሏ እና የስራ እድሜን ወደ 15 አመት በአዋጅ ቁጥር 1156/2019 ማሳደጓን፣እጅግ
አስከፊ የሆነ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ሀገር አቀፍ የድርጊት መርሃ ግብር ማፅደቋን እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል እና
ለማስወገድ የተዘረጋውን የ 5 አመት ስትራቴጂ ማፅደቋን ኮሚቴው ያመሰግናልል። ኮሚቴው በአባል ሀገሯ ሪፖርት ላይ በተገለጸው

መሰረት በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ሀገሪቷ እያደረገች ያለውን ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራ አድንቋል። ይሁን እንጂ በአባል ሀገሯ
ውስጥ ያለው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ደረጃ በጣም ከፍተኛ ሆኖ እንደቀጠለ፣ በስራ ውስጥ ያሉ ሕፃናትን የሚደግፉ የሰራተኛ የስራ
ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች እና የማኅበራዊ ሰራተኞች እጥረት መኖሩን እና በአጥፊዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ጥቂት መሆናቸዉን

በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምክንያት በ 5 ድርጅቶች ላይ ብቻ እርምጃ እንደተወሰደ ኮሚቴዉ ተገንዝቧል፡፡


35. አባል ሀገሯ አዲሱን አዋጅ፣ የትግበራ እቅዶቹና ስትራቴጂዎቹ ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሆኑና የሰራተኛ ተቆጣጣሪዎችና የማኅበራዊ
ሰራተኞች ቁጥር እንዲጨምር ሀገሪቱ በቂ በጀት እንድትመድብ ኮሚቴው ያሳስባል። አባል ሀገሯ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ፈጻሚዎች እና
የስራ አካበቢ ጤና እና ደህንነት መስፈርቶችን በማያሟሉ ቀጣሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የምታደርገውን ጥረት እንድታሳድግ
ኮሚቴው ይመክራል።መደበኛ ያልሆነው የሥራ ሴክተር ለከፋ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዋና መንገዶች አንዱ በመሆኑ የአባል ሀገሯ
በእነዚህ መደበኛ ያልሆኑ የሥራ ሴክተሮች ላይ የመቆጣጠር ስራዋን እንድታጠናክር ኮሚቴው ያበረታታል። ኮሚቴው ሕፃናትን ወደ
ባህር ማዶ ወስዶ መቅጠር በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2016 የተከለከለ መሆኑን ቢመለከትም፣ ሁሉም
ሕፃናት የወሊድ ምዝገባ እንዲኖራቸው በማድረግ፤ የባህር ማዶ ቅጥር ውስጥ የሚሳተፉትን በመቆጣጠር እና ሕፃናትን ለባህር ማዶ
ቅጥር የሚልኩ አካለትም ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ ተፈጻሚነትን ለማረጋገጥ የአባል ሀገሯ የጥበቃ እርምጃዎችን እንድትወስድ
ኮሚቴው ያሳስባል።የአባል ሀገሯ እያከናወነች ካለው የግንዛቤ ማስጨበጫና የመከላከል ስራ በተጨማሪ ችግር ዉስጥ ያሉ ሕፃናትን
ጨምሮ ሁሉንምነ ሕፃናትን እጅግ አስከፊ ከሆነ ጉልበት ብዝበዛ በማውጣት ለሕፃናቱ የትምህርትና የሙያ ስልጠና በመስጠትና
ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ኮሚቴው ይመክራል።በተጨማሪም የአባል ሀገሯ የቤተሰቦች የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ እና
ልጆቻቸውን ከሕፃሸናት ጉልበት ብዝበዛ ለመጠበቅ ማበረታቻዎችን በመስጠት ከቤተሰብ ጋር በቅርበት እንድትሰራ ኮሚቴው
ያበረታታል። አባል ሀገሯ ሕፃናት ለልመና የሚጠቀሙትን ለሕግ በማቅረብ እና ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ሕፃናትን
ለልመና መጠቀም ዙርያእርምጃ እንድትወስድ ኮሚቴው ይመክራል።

የሕፃናት የሕገ ወጥ ዝውውር፣ ጠለፋ እና ንግድ


36. ኮሚቴው በ 2020 የሀገሪቱን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የመቆጣጠር እና የመከላከል ሕግ መሻሻልን፣ ከፍተኛ
የሔሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ እና ግብረ ሃይል ከተለያዩ ሚኒስቴሮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በማዋቀር እና
የተጎጂዎችን ሪፈራል/የመልሶ ማቋቋም መመሪያ በ 2018 በሪፖርት ወቅት ማጽደቋን በደስታ ይቀበላል።
በተጨማሪም አባል ሀገሯ በኮሚቴው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በሰጠችው ምላሽ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ
ግንኙነት በማድረግ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን ለመመለስ የምታረገዉን
ጥረት ኮሚቴዉ ተገንዝቦ አድናቆቱን ይገልፃል፡፡ ሆኖም ግን ኮሚቴው አሁንም የሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭ
የሚደረጉ የሕፃናት ሕገ-ወጥ ዝውውር መጨመሩንና ይህም በግጭት፣ መፈናቀልና ሌሎች ምክንያቶች

21
እየተባባሰ መምጣቱን ተመልክቷል።ኮሚቴው የአባል ሀገሯ የሕጎቿን እና ፖሊሲዎቿን አፈፃፀም እንዲታጠናክር
እና በተለይም የሚከተሉት ጉዳዮች እንዲጠናከሩ ያበረታታል።
 በሕገወጥ የሕፃናት ዝውውር ፣በሕገ ወጥ መንገድ ሕፃናትን ድንበር ማሻገር ፣ ጠለፋ እና የሕፃናት ንግድ
ላይ የተሳተፉ አካላት ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ክስ እንዲመሰረት እና የጥፋተኝነት ውሳኔ
ለማሰጠት የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር፤
 በጠፉ ሕፃናት ላይ በሚቀርቡ ጥቆማዎች ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ
 የ=ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወርን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን ሕግ አፈፃፀም በቂ በጀት እና የሰው
ሃይል በመመደብ እንዲጠናከር እንዲሁም ለተጎጂዎች የማገገሚያ ፣የመልሶ ማቋቋም እና ሌሎች
አገልግሎቶችን እንዲሰጥ፤
 በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሌላ ሀገር የተዘዋወሩ ሕፃናትን ፈልጎ ለመለየት እና ለመመለስ ቀድሞ እየተሰራ
የነበረውን ጥረት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ስምምነቶች እና ግንኙነቶች እንድጠናከር፤
 እንደ ስነ-ልቦና፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ድጋፍ ለሚሹ ተጎጂዎች አስፈላጊው መገልገያዎች እና
አገልግሎቶች ያሏቸው መጠለያዎች እንዲቋቋሙ፤
 የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥረቶችን እንዲቀጥሉ እና እንዲጠናከሩ፤
 ለተጎጂዎች የተቀናጀ ምላሽ እንዲኖር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢውን የቅንጅት ዘዴን
እንዲመሰረት፤ እና
 እንደ ቱሪዝም ዘርፍ ያሉ የግል ዘርፎችን በማሳተፍ የሕፃናትን ሕገ ወጥ ዝውውር፣ጠለፋ እና ንግድ
ለመከላከል የሚያስችሉ የትብብር ስራዎች እንዲጠናከሩ ኮሚቴዉ ያበረታታል፡፡

ወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃት


37. ኮሚቴው የአባል ሀገሯ ጾታዊ ብዝበዛና ጥቃትን ለመከላከልና ለመቅረፍ ያደረገቻቸውን ልዩ ልዩ ጥረቶች በመከላከል እና
በመፍትሔ አቅጣጫ የሚሰጥ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሁም የስልክ መስመሮችን፣ ለሕፃናት ምቹ የሆኑ
ፍርድ ቤቶችን፣ የአንድ አገልግሎት ማእከላትን እና ጥቃት ለደረሰባቸዉ ማቆያ ማእከላት ማቋቋም ላይ ያደረጋቸውን ጥረቶችን
ተመልክቶ አድንቋል።ነገር ግን የአባል ሀገሯ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኮሚቴው በሕፃናት ላይ የሚደርሰው የፆታዊ ብዝበዛ
እና በደል መጠን በጣም ከፍተኛ ሆኖ እንደቀጠለና ከአራት ሕፃናት ውስጥ ከአንድ በላይ የሚሆኑት ወሲባዊ ጥቃት
እንደተፈጸመባቸው ወይም እንደተበዘበዙ ተመልክቷል። በተጨማሪም ከ 8 ቱ የስልክ መስመሮች 5 ብቻ የሚሰሩ እንደሆነ
ከ 34 ቱ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከላት 4 ቱ ብቻ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የአባል ሀገሯ ዘገባ ያመለክታል።
ከዚህም በላይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሰሜናዊ እና በሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በሕፃናት
ላይ የሚደርሰው ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደል በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው
የአባል ሀገሯ ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንድትወስድ ለማበረታታት ይፈልጋል።
ኮሚቴው የአባል ሀገሯን የሚከተሉትን ይመክራል፡-

22
 ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የጥቆማ ማቅረቢያ ስርአት መኖሩን እንድታረጋግጥ። በዚህ ረገድ ኮሚቴው የአባል
ሀገሯ 8 ቱ የስልክ መስመሮች እና ለ 34 ቱ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከላት በቂ በጀት በመመደብና ግብአት
በማሰባሰብ ወደ ተግባር እንዲገቡ እና የሚቀጠሩት ሰራተኞች በሕፃናት መብትና ሕፃናትን ላይ ያተኮሩ አገልግሎቶች
ላይ የሰለጠኑ እንዲሆኑ ያበረታታል።
 የተጠቆሙ የመብት ጥሰት ጉዳዮች በተገቢው መንገድ ተመርምረው ለሕግ እንዲቀርቡ እና ተመጣጣኝ
ቅጣት እንዲጣልባቸው በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲሰፍን እንድታደርግ።
 የፖሊስ መኮንኖችን፣ ዐቃብያነ ሕጎችን እና ዳኞችን ስለ የሕፃናት ጥቅምን ማስቀደም ፣የሕፃናትን
ግላዊነት ስለመጠበቅ እና ስለ ሕፃንት ሌሎች መብቶች በማሰልጠን ከጥቃት የተረፉት ተጠቂዎች
የስነልቦና ጉዳት ዳግም እንዳይደርስባቸዉ ለማስቻል እና የተበደሉ እና የተበዘበዙ ሕፃናት ጉዳዮች የሕፃናት
ጥቅምን ማስቀደምን ትኩረት በመስጠት እንዲያዙ ማሰልጠን ።
 ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና የጥቆማ መቅረቡን ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡን ንቅናቄ እና የግንዛቤ
ማስጨበጫ ስራዎችን እንዲሰሩ
 የወሲብ ጥቃትን እና ብዝበዛን በሚመለከት ጥቆማ ማቅረብን የሚከለክሉ ባህላዊ እና ሌሎች
መሰናክሎችን ለመቅረፍ ከማኅበረሰብ አቀፍ የሪፖርት አቀራረብ ዘዴዎች ጋር ትብብር እንዲፈጠር
 በመንግስት የተቋቋሙት የተጠቂዎች ማቆያ ማእከላት የተጎጂዎችን የስነ-ልቦና ማኅበራዊ እና የጤና ድጋፍ
እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም እና መልሶ ማቀላቀል አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲችሉ በቂ የገንዘብ
ድጋፍ እና የሰው ሃይል ማግኘታቸውን እንድታረጋግጥ።
 በግጭቱ እና ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የወሲብ ጥቃት እና ብዝበዛ ሰለባ ለሆኑ ሕፃናት የተለያዩ
ስትራቴጂዎችን እና ፕሮግራሞችን እንድትቀርፅ ኮሚቴዉ ይመክራል።

በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት
38. በአባል ሀገሯ ውስጥ የሕፃናትን የጎዳና ላይ ችግር ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ
ቤቶችን እና የሲቪል ማህበራትን ያካተተ ግብረ ሃይል በማቋቋም፣ አባል ሀገሯ ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር
በመቀናጀት አገልግሎት ለመስጠት በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተመረጡ ከተሞች
የቤተሰብ ፍለጋ እና የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት የተወሰዱ እርምጃዎችን ኮሚቴው አድናቆቱን ይገልፃል።እንዲህ
ዓይነት ጥረቶች የሚታወቁ ቢሆኑም፣ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በአባል ሀገሯ ሪፖርት ውስጥ
እውቅና እንደተሰጠው የእነዚህ ሕፃናት አገልግሎት እጦት ኮሚቴው ያሳስበዋል።እንደ ድህነት፣ ግጭት፣ የጓደኞች ግፊት እና
የወላጆች መለያየት እና አለመግባባቶች ያሉ ምክንያቶች ሕፃናት ወደ ጎዳና ላይ እንዲወጡ የሚያደርጉ ዋና ምክንቶችን
ለመቅረፍ የአባል ሀገሯ እርምጃዎችን እንድትወስድ እና በመንገድ ላይ ላሉ ሕፃናት የሙያ ስልጠና፣ በአማራጭ ስልቶች
መደበኛ ትምህርት የመስጠት፣ በጎዳና ላይ ላሉ ሕፃናት የፆታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ጨምሮ የጤና
እንክብካቤ አገልግሎት የመስጠት እና በቤተሰብ ፍለጋ እና ውህደት ላይ ጥረቷን እንድትቀጥል ኮሚቴዉ ይመክራል። በጎዳና
ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ለሚኖሩባቸው ከተሞችም ትኩረት በመስጠት መጠለያዎችን በመገንባት ለተጎጂዎች
ቀጣይነት ያለው የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞችን እና አገልግሎቶችን በማቅረብ አባል ሀገሯ ጥረቷን እንድታሳድግ እና

23
በትምህርት ቤቶች፣ ቤተሰቦች እና በመገናኛ ብዙኃን በጎዳና ላይ መኖር ስለሚያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ ግንዛቤ የመፍጠር
ስራ እንዲሰራ ኮሚቴው ይመክራል።

በአደገኛ ዕፅ ሱስ ውስጥ ያሉ ልጆች


39. ሕፃናትን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትና ተጠቃሚነት ለመከላከል የተወሰዱትን ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ለምሳሌ
ሕፃናት ማንኛውንም እፅ ወይም አልኮል እንዳይጠቀሙ የሚከለክሉ ሕጎች ማውጣትን፣ ሕፃናትን ዒላማ
ያደረግ አደንዛዥ እፅ እና አልኮል ማስተዋወቂያ ክልከላን እና የትምህርት ቤቶችን አከባቢዎች ከዚህ አንፃር
ለመቆጣጠር የወጡትን ደንቦች ኮሚቴው እያደነቀ አሁንም ቢሆን ሕፃናት ገና በለጋ እድሜያቸው ጭምር
አደንዛዥ እፆችን የመጠቀም አዝማሚያ ማሳየታቸው እየጨመረ መሆኑን ተገንዝቧል። ኮሚቴው አባል ሀገሯ
በሕፃናት ላይ እየጨመረ የሚሄደውን የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ለመቅረፍ ትኩረት እና ጥረቷን እንድታሳድግ
ይመክራል።ኮሚቴው ለሕፃናት አልኮል እና አደንዛዥ እፆችን በሚያቀርቡ ግለሰቦች እና አገልግሎት ሰጪዎች
ላይ እርምጃ ለመውሰድ አባል ሀገሯ ያለማቋረጥ የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ሁኔታ መከታተል እንዳለባት
ይመክራል። በተጨማሪም ኮሚቴው የአባል ሀገሯ ለአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት የተጋለጡ ህጻናትን የማገገሚያ
አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት እና እንደዚህ ላሉት ህፃናት የቤተሰብ መልሶ መገናኘት (እንደ
አስፈላጊነቱ) ፣ የሙያ ስልጠና ፣ የትምህርት እና የስራ ዕድሎች የሚቀርቡበት የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞች
ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይመክራል፤፤ኮሚቴው ምላሹን ለማሳደግ እና ለምንጩ ተደራሽ ለመሆን ከሲቪል
ማህበራት ጋር በቅርበት እንዲሰራ ኮሚቴው ያበረታታል።

የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች


40. ኮሚቴው በ 2025 የህፃናት ጋብቻን እና የሴት ሕፃናት ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ለማቆም በቁርጠኝነት ቃል መግባቱን
እንዲሁም የሕፃናት ጋብቻን ለማስወገድ ሀገራዊ ጥምረት መመስረቱንና በ 2017 በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በወጣው ሰርኩላር
አማካኝነት በሴት ሕፃናት ግርዛት መሳተፍ በወንጀለኝነት መፈረጁን እና በአባል ሀገሯ ውስጥ የሴት ሕፃናት ግርዛትን
በሕክምና ተቋማት ማከናወን መከልከሉን አድንቋል። ከ 2005 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የሕፃናት ጋብቻ ምጣኔ ቅናሽ
ማሳየቱን እና የሴት ሕፃናት ግርዛት የተሻለ መቀነሱን ኮሚቴው ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ኮሚቴው በ 2016 የሴት ሕፃናት
ግርዛት እና ሕፃናት ጋብቻ መጠን በጣም ከፍተኛ መሆኑን ተመልክቷል፣ የሴት ሕፃናት ግርዛት ከ 15-19 አመት እድሜ
ክልል ውስጥ ካሉ ልጃገረዶች 47%፣ ከ 0-14 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ 16% እና በ 14 አመት እድሜ ክልል ባሉ
በሴቶች 38% በተጨማሪም በ 2016 የህፃናት ጋብቻ መጠን 58% እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሕፃናት
ጋብቻ ከሕፃናት ጠለፋ ጋር የተያያዘ መሆኑን ኮሚቴው አሳስቦታል።

በመሆኑም ኮሚቴዉ የአባል ሀገሯ እነዚህን ተግባራት በመቀነስ እና በማስወገድ ረገድ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክራ
እንድትቀጥል የሚከተሉትን ይመክራል፡-

 የሕፃናት ጋብቻ የሚፈጸሙበት ወቅት በመሆኑ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት
በልጃገረዶች ትምህርት ላይ ከፍተኛ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ እንድታረግ

24
 ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን በትምህርት ቤት እንዲቆዩ እና ለሕፃናት ጋብቻ እንዳይሰጡ ወይም የሴት
ሕፃናት ግርዛትን እንዳይፈጽሙ ማበረታቻ እንድትሰጥ
 የሕፃናት ጋብቻ እና የሴት ሕፃናት ግርዛት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ለልጃገረዶች ለቤተሰቦች የተሻለ
የስራ እድል መፍጠር
 ለወላጆች፣ ለሃይማኖት እና ለማኅበረሰብ መሪዎች እና ለልጃገረዶች የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ
እርምጃዎችን እንዲከናወን
 በጎጂ ልማዶች ላይ ለሴቶች ልጆች የአቻ ትምህርት መድረክ እንዲፈጠር
 ከግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ ድርጊቶች ላመለጡ ሕፃናት መጠለያ እና ሁሉንም የስነ-ልቦና-ማህበራዊ
ድጋፍ እንዲሰጥ
 ሕፃናትን ለጋብቻ አላማ የሚጠልፉን እና ግርዛትን የሚፈፅሙ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ
የሕፃናት ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክሉትን ሕጎች ተግባራዊ ማድረግ
 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የሕፃናት ጥበቃን ማረጋገጥ የሁሉም ሕፃናት ልዩ ፍላጎቶች እና ተጋላጭነቶች
በተለይም በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት የተጋለጡ ልጃገረዶችን ግምት ውስጥ ያስገቡ ስራዎች እንዲሰሩ
ኮሚቴዉ ይመክራል፡፡

የሕፃናት ኃላፊነት
41. ኮሚቴው የሕፃናት ኃላፊነት ጉዳይ በብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲ ውስጥ የተካተተ መሆኑን በመመልከቱ
ምስጋናዉን ይገልፃል ። በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ውስጥ ሕፃናት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስላላቸው
ኃላፊነት እንዲማሩ መደረጉንም አመስግኗል።ኮሚቴው በተጨማሪ በቻርተሩ አንቀጽ 31 ላይ የሰጠውን ቁጥር
3 አጠቃላይ አስተያየት በመጠቀም ሀገሪቷ የሕፃናትን ሀላፊነቶች አፈፃፀም ላይ የተሻለ መመሪያ እንድትሰጥ
ያበረታታል።ኮሚቴው በተጨማሪም የአባል ሀገሯ ሕፃናት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለአላስፈላጊ ጫናና ስራ
እንዳይዳረጉ እና አንቀፅ 31 የሚተገበረው በቻርተሩ አጠቃላይ መርሆዎች መሰረት እና ከሌሎች የቻርተሩ
ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡

V. ማጠቃለያ
42. የአፍሪካ የሕፃናት መብትና ደህንነት ኤክስፐርቶች ኮሚቴ የኢትዮጵያ መንግስት ለአፍሪካ ሕፃናት ቻርተር እና
ኮሚቴው በመነሻ ሪፖርቱ ላይ የሰጣቸውን ምክረሀሳቦች ለመተግበር የወሰዳቸዉን እርምጃዎች እና ጥረቶችን
አድንቋል።

25
43. ኮሚቴው በዚህ ሰነድ ላይ የተመለከቱት ምክረሀሳቦች ተተርጉመው በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ለሚገኙ
ለሁሉም የመንግስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በስፋት እንዲሰራጩ
ይመክራል። አባል ሀገሯ እና ባለድርሻ አካላቱ እነዚህን የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳቦች በሀገሪቱ በሚወጡ እቅዶች፣
ስትራቴጂዎች እና ፖሊሲዎች በማካተት ተግባራዊነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሰሩ ኮሚቴው ይመክራል። በዚህ
አጋጣሚም ኮሚቴው የመፍትሄ ሀሳቦቹ መተግበራቸውን ለማረጋገጥ በቅርብ ጊዜ የክትትል ተልዕኮ እንደሚኖረው
ለማስታወቅ ይወዳል፡፡ ኮሚቴው በአፍሪካ ሕፃናት ቻርተር አንቀጽ 43 መሰረት የአባል ሀገሯ ሁለተኛውን
ወቅታዊ ሪፖርቷን የካቲት 2025 እንድታቀርብ ግብዣዉን ያቀርባል።የአባል ሀገሯ የሁለተኛ ወቅታዊ ሪፖርቷን
ለማዘጋጀት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሕፃናት፣ ከተመድ ኤጀንሲዎች፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከሌሎች
ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ምክክር እንድታርግ ኮሚቴው ይመክራል።
44. የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደህንነት የባለሙያዎች ኮሚቴ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ
ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ያለውን አክብሮት በድጋሚ ማረጋገጥ ይወዳል፡፡

26

You might also like