You are on page 1of 3

የኢትዮጵያ

ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)


ETHIOPIAN HUMAN RIGHTS COUNCIL (EHRCO)

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ

በረሀብ ምክንያት የሚከሰት ሞት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ


አስቸኳይ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!
ጥር 21/2016 ዓ.ም

ትግራይ ክልል፡
በትግራይ ክልል የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ ከነበረው የትጥቅ ግጭት ጊዜ ጀምሮ መ ጠኑ እየጨመረ
በመቀጠል ላይ ይገኛል፡፡ በነበረው ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ
መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያደረገው የፕሪቶሪያው የሰላም
ስምምነት የጸጥታው ሁኔታ ሲፈቅድ የፌደራል መንግስት ተፈናቃዮችን ወደመጡበት የመመለስ እና ባሉበት የማዋሀድ ስራን የመስራት
እና የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለበት ቢገልጽም በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በተለያዩ ጊዜዎች ወደመጡበት
አካባቢ እንዲመለሱ ቢጠይቁም ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከፍተኛ ለሆነ ረሀብ፣ የመድሀኒት እጥረት እና ልዩ ልዩ የሰብዓዊ ቀውስ ተጋላጭ
ሆነዋል፡፡

በክልሉ በዋናነት በሽረ፣ አክሱም፣ አብይአዲ፣ መቀሌ እና አዲግራት የሚገኙ ተፈናቃዮች እና ነዋሪዎች በምግብ እና በመድሀኒት እርዳታ
ላይ የተደገፉ ሲሆን ይህ ሆኖ ሳለ ግን በዋናነት ሰብዓዊ ድጋፍ ያቀርቡ የነበሩት የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና
የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በእርዳታ ቁሳቁስ ላይ ስርቆት ተፈጽሟል በሚል እርዳታቸውን በማቋረጣቸው፣ የፌደራል
እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቂ የሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ባለመቻሉ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በ ረሀብ ምክንያት
መሞታቸውን ኢሰመጉ ባሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በትግራይ ክልል ያለው ረሀብ አሁንም ድረስ ተገቢ የሆነ መፍትሔ እና ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡
፡ የፌደራል መንግስት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት አፋጣኝ የሆነ የምግብ፣ የመድሀኒት እና ሌሎች
ሰብዓዊ ድጋፎችን በበቂ ደረጃ አሁንም ድረስ ሊያቀርቡ አልቻሉም በእዚህም ምክንያት በዋናነት የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የሆኑ ሴቶች፣
ጨቅላ ህጻናት፣ አጥቢ እናቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ከሟቾች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ሲሆን አሁንም አስከፊ አና
አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አማራ ክልል
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ በዋግህምራ ብሄረሰብ
አስተዳደር ዞን፣ ጃናሞራ እና ጠለምት አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ድርቅ የተከሰተ ሲሆን በዚህም
ማህበረሰቡ ከፍተኛ ለሆነ ረሀብ እና ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ በሽታዎች መጋለጣቸውን ኢሰመጉ ጥቅምት 02 ቀን
2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ለችግሩ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱና አሁንም ድረስ በክልሉ

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 1


የቀጠለ ግጭት በመኖሩ ምክንያት ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ያለው ረሀብ እንደቀጠለ የሚገኝ ሲሆን በእዚህ ረሀብ ምክንያት
በርካታ ሰዎች እና እንስሳት እየሞቱ ያሉ ሲሆን በአካባቢዎቹ ባለው ግጭትም ምክንያት በበቂ ሁኔታ ሰብዓዊ ድጋፍን ማቅረብ
እንዳልተቻለ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ተያያዥ የህግ ግዴታዎች


የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በግልጽ ስለ ምግብ መብት ባያስቀምጥም በተዘዋዋሪ በአንቀጽ 41 እና 43 ላይ በተጠቀሱ ሃሳቢች ውስጥ
ተካትቶ ሊታይ እንደሚቸል መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የህገ መንግስቱ በብሔራዊ ፖሊሲ መርሆችና አላማዎች ምዕራፍ አንቀጽ
90 ንዑስ አንቀጽ 1 ላ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትየጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንጹህ ውሀ፣ የመኖሪያ፣
የምግብና የማኅበራዊ ዋስትና እንዲኖረው ይደረጋል ሲል ይደነግጋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 25 ማንም ሰው ለእራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደኅንነት በቂ የሚሆን የኑሮ
ደረጃ የመኖር መብት እንዳለውና ይህም መብት ምግብን እንደሚጨምር ይደነግጋል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ዓለም
አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 11 ማንኛውም ሰው በቂ ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ለራሱና ለቤተሰቡ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ
ለመኖርና ኑሮውንም በየጊዜው ለማሻሻል መብት እንዳለው በመደንገግ የቃልኪዳኑ ተዋዋይ አገሮች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ማንኛውም
ሰው ሳይራብ ለመኖር ያለውን መሰረታዊ መብት በመገንዘብ በተናጠልም ሆነ በዓለም አቀፍ ትብብር አማካይነት ሊያደርጓቸው የሚገቡ
ነጥቦችን አካትቶ ይዟል፡፡

የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ኮሚቴ አንቀጽ 11 ላይ ስለተቀመጠው የምግብ መብት አስመልክቶ ባወጣው ጠቅላላ
አስተያየት ቁጥር 12 ላይ በቂ የሆነ የምግብ መብት በሂደት የሚፈጸም (progressively realized) መብት መሆኑን በመግለጽ ነገር
አገራት በተፈጥሮም ሆነ በሌሎች አደጋዎች ጊዜም ቢሆን በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በተደነገገው መሰረት ረሃብን ለመቀነስ እና
ለማቃለል አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ዝቅተኛ ዋና ግዴታ “minimum core obligation” እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
በተጨማሪም ይህ ጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 12 የአገራትን ግዴታ ሲያብራራ እያንዳንዱ አገር በግዛቱ ውስጥ ላለ ማንኛውም ሰው ከ
ረሀብ መጠበቁን ለማረጋገጥ በቂ የሆነ፣ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የያዘ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዝቅተኛ አስፈላጊ ምግብ እንዲያገኝ የማረጋገጥ
ግዴታ አለበት ሲል በመግለጽ በእዚህ መብት ላይ ጥሰት ተፈጸመ የሚባለው አንድ አገር ቢያንስ ከ ረሀብ ነጻ ለመሆን የሚያስፈልገውን
ዝቅተኛ የምግብ አቅርቦት ማረጋገጥ ሲሳነው እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአንቀጽ ሁለት ላይ ስምምነቱ የሚመራባቸውን የተለያዩ መርሆችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል
ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦት ማድረግ እና ሰብዓዊ እርዳታን ለሰብዊነት አላማ ብቻ መጠቀም የሚሉ
ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአንቀጽ 5 ላይ የኢፌ ዲሪ መንግስት የሴቶችን፣ ህፃናትን እና አረጋውያንን
ጨምሮ የተጋላጭ ወገኖችን ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር የሚሰጠውን
የሰብአዊ እርዳታን እንደሚያሳልጥና ተዋዋይ ወገኖቹ ሰብዓዊ እርዳታ ለሰብዊነት አላማ ብቻ እንደሚውል እንደሚያረጋግጡ
ይደነግጋል፡፡

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 2


የኢሰመጉ ጥሪ፡
 በትግራይ ክልል እና በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግርና ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድሀኒት
አቅርቦት እጥረት ተከትሎ ለረሀብ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኘኞችን፣ የአገር
ውስጥ ተፈናቃዮችን እና አረጋውያንን ጨምሮ ልዩና አፋጣኝ ትኩረት በመስጠት ነፍስ አድን የሆኑ የምግብና መድሀኒት
እርዳታዎችን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌደራል መንግስትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት እንዲያቀርቡ፣
 ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት የሆኑ እንደ የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ
ፕሮግራም (WFP) በትግራይ ክልል እና በአማራ ክልል ያቋረጡትን የምግብ እና የመድሀኒት ድጋፍ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ
የሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያስጀምሩ፣
 የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የአገር ውስጥ
ተፈናቃዮችን አስመልክቶ ያለባቸውን ኃላፊነቶች እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 3

You might also like