You are on page 1of 3

የኢትዮጵያ

ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)


ETHIOPIAN HUMAN RIGHTS COUNCIL (EHRCO)

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ

በትግራይ ክልል ለተከሰተው ርሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድሀኒት እጥረት


አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ከኢሰመጉ የቀረበ ጥሪ!
ሀምሌ 21/2015 ዓ.ም
መግቢያ፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የጀመረ ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያስተናገደ የትጥቅ ግጭት
እንደነበረ ይታወሳለ፡፡ ይህ ግጭት በዋናነት ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን የሸፈነ ነበር፡፡ በግጭቱ ወቅት የተወሰኑ የተኩስ አቁም
ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም ለሁለት ዓመታት ሊዘልቅ ችሏል፡፡ ይህ ግጭት ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ የሰላም ስምምነት ሊቆም ችሏል፡፡ ኢሰመጉ ይህ ግጭት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጊዜ ባወጣቸው
መግለጫዎች እና ጥሪዎች ሲወተውት የቆየ ሲሆን የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለግጭቱ መቆም ላደረገው አስተዋጾ እውቅና ይሰጣል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በውስጡ የሰላም እና የፍትህ ሀሳቦችን የያዘ ሲሆን ለሁለቱም ተዋዋይ አካላት ኃላፊነቶችን ያስቀመጠ
ስምምነት ነው፡፡ ከመርሆቹም መካከል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦት ማድረግ ነው፡፡ ከእነዚህ ኃላፊነቶች
አንዱ ለኢፌዲሪ መንግስት የተሰጠው በትግራይ ክልል እና በተጎዱ አካባቢዎች ላሉ ሁሉ ሰብዓዊ እርዳታን ማሰባሰብ፣ ማስፋፋት እና
ያልተደናቀፈ የሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ሲሆን ሁለቱም የስምምነቱ ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ ለሰብዊነት አላማ ብቻ እንደሚውል
እንደሚያረጋግጡ ይገልጻል፡፡

ትግራይ ክልል ያሉ ሰብዓዊ ቀውሶች፡


በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለሁለት ዓመታት የቆየው የትጥቅ ግጭት ፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት ቢቆምም ግጭቱ ያስከተለው
ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ምንም እንኳን ኢሰመጉ በአካባቢው በመገኘት የትጥቅ
ግጭቱ ያስከተለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በወቅቱ ለመርመር ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርግም ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድና
ተባባሪነትን ባለማግኘቱና በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው የኢሰመጉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመዘጋቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት
በእዚህ ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን (1,000,000) በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለጸ ሲሆን1
የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት የትጥቅ ግጭቱ በክልሉ ያስከተለውን
ቀውስ ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪ የምግብ እርዳታ ላይ የተደገፈ መሆኑን በመግለጽ በክልሉ ኮሌራና መሰል በሽታዎች
መከሰታቸውን ገልጿል፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ የትጥቅ ግጭቱ ላስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ በትግራይ ክልል በዋናነት ሰብዓዊ ድጋፍ ያቀርቡ የነበሩት የአሜሪካ ኤጀንሲ
ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID)2 እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP)3 በእርዳታ ቁሳቁስ ላይ ስርቆት ተፈጽሟል በሚል

1 https://reports.unocha.org/en/country/ethiopia/card/5EhBh4Xf5z/
2 https://www.usaid.gov/news-information/press-releases/may-03-2023-pause-us-food-aid-tigray-ethiopia
3 https://www.wfp.org/news/wfp-statement-diversion-food-aid-ethiopia-0

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 1


እርዳታቸውን ያቋረጡ ሲሆን በእዚህም ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድሀኒት እጥረት ያጋጠመ ሲሆን የክልሉ አደጋ ስጋት
ስራ አመራር ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የእርዳታዎቹን መቆም ተከትሎ እየተከሰተ ባለ ርሀብ እና የመድሀኒት እጥረት ከአንድ
ሺህ (1000) በላይ ሰዎች መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ
ሰዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል ይህም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግስታት
ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ባደረገው መረጃ መሰረት በትግራይ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ወደ
ሆስፒታል እየገቡ ያሉ ህጻናት ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ196% መጨመሩን ያሳይል፡፡4 በእዚህ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግር፣
ርሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድሀኒት እጥረት ምክንያት በዋናነት አጥቢ እናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን
ኢሰመጉ በተጨማሪነት ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በትግራይ ክልል ለተከሰተው ርሀብ፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድሀኒት
እጥረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም የፌደራል መንግስት ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን ሁለቱም አካላት ይህ ሰብዓዊ ቀውስ
ከእዚህ የከፋ ጉዳትን ሳያደርስ ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡
በተጨማሪም የምግብ እጥረቱ ካስከተለው ርሀብ ጎን ለጎን በክልሉ የነበሩ የህክምና ተቋማት በትጥቅ ግጭቱ ምክንያት ከደረሰባቸው ጉዳት
ለማገገም እየሞከሩ ቢሆንም አሁን ድረስ ተቋማቱ ያለባቸው የህክምና ባለሙያዎች እጥረት፣ የህክምና ቁሳቁስ እጥረትና የህክምና አቅርቦት
እና ፍላጎት ተመጣጣኝ አለመሆን ከፍተኛ ችግር መሆኑን እንዲሁም ተላላፊ ለሆኑ እና ላልሆኑ በሽታዎች ያለው የመድሀኒት አቅርቦት
በዋናነት የስኳር፣ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ እና ሌሎችም መሰል በቋሚነት መድሀኒት አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ህመሞች ያለው የመድሀኒት
አቅርቦት እጅግ አናሳ መሆኑን፣ ለጨቅላ ህጻናት፣ ለአጥቢ እናቶች እና ለነፍሰጡር እናቶች የሚደረጉ ህክምናዎች ከቁሳቁስ፣ ከሰው ኃይል
እና ከመድሀኒት አቅርቦት እጥረት የተነሳ እጅጉን አነስተኛ መሆኑ እና በእዚህም ምክንያት የተለያዩ መድሀኒቶች ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች
ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡


ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 25 ማንም ሰው ለእራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደኅንነት በቂ የሚሆን የኑሮ
ደረጃ የመኖር መብት እንዳለውና ይህም መብት ምግብን እንደሚጨምር ይደነግጋል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ዓለም
አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 11 ማንኛውም ሰው በቂ ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ለራሱና ለቤተሰቡ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ ለመኖርና
ኑሮውንም በየጊዜው ለማሻሻል መብት እንዳለው በመደንገግ የቃልኪዳኑ ተዋዋይ አገሮች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ማንኛውም ሰው ሳይራብ
ለመኖር ያለውን መሰረታዊ መብት በመገንዘብ በተናጠልም ሆነ በዓለም አቀፍ ትብብር አማካይነት ሊያደርጓቸው የሚገቡ ነጥቦችን አካትቶ
ይዟል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ኮሚቴ አንቀጽ 11 ላይ ስለተቀመጠው የምግብ መብት አስመልክቶ ባወጣው ጠቅላላ
አስተያየት ቁጥር 12 ላይ በቂ የሆነ የምግብ መብት በሂደት የሚፈጸም (progressively realized) መብት መሆኑን በመግለጽ ነገር አገራት
በተፈጥሮም ሆነ በሌሎች አደጋዎች ጊዜም ቢሆን በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በተደነገገው መሰረት ረሃብን ለመቀነስ እና ለማቃለል
አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ዝቅተኛ ዋና ግዴታ “minimum core obligation” እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
በተጨማሪም ይህ ጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 12 የአገራትን ግዴታ ሲያብራራ እያንዳንዱ አገር በግዛቱ ውስጥ ላለ ማንኛውም ሰው ከርሀብ
መጠበቁን ለማረጋገጥ በቂ የሆነ፣ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የያዘ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዝቅተኛ አስፈላጊ ምግብ እንዲያገኝ የማረጋገጥ ግዴታ
አለበት ሲል በመግለጽ በእዚህ መብት ላይ ጥሰት ተፈጸመ የሚባለው አንድ አገር ቢያንስ ከርሀብ ነጻ ለመሆን የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ
የምግብ አቅርቦት ማረጋገጥ ሲሳነው እንደሆነ ያስረዳል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአንቀጽ ሁለት ላይ ስምምነቱ የሚመራባቸውን የተለያዩ መርሆችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል
ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦት ማድረግ እና ሰብዓዊ እርዳታን ለሰብዊነት አላማ ብቻ መጠቀም የሚሉ
ይገኙበታል፡፡

4https://reports.unocha.org/en/country/ethiopia?ct=t%28EMAIL_CAMPAIGN_11_May_2023_COPY_04%29&goal=0_82a80d2ffe-

b21fbbd1d1-109596177

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 2


በተመሳሳይ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአንቀጽ 5 ላይ የኢፌዴሪ መንግስት የሴቶችን፣ ህፃናትን እና አረጋውያንን ጨምሮ የተጋላጭ
ወገኖችን ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር የሚሰጠውን የሰብአዊ እርዳታን
እንደሚያሳልጥና ተዋዋይ ወገኖቹ ሰብዓዊ እርዳታ ለሰብዊነት አላማ ብቻ እንደሚውል እንደሚያረጋግጡ ይደነግጋል፡፡

የኢሰመጉ ጥሪ፡
 በትግራይ ክልል የተከሰተውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግርና ከፍተኛ የሆነ የምግብና የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት ተከትሎ
ለኢሰባዊ ቀውስ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኘኞችን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና
አረጋውያንን ጨምሮ ልዩና አፋጣኝ ትኩረት በመስጠት ነፍስ አድን የሆኑ የምግብና መድሀኒት እርዳታዎችን የክልሉ ጊዜያዊ
አስተዳደር፣ የፌደራል መንግስትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት እንዲያቀርቡ፣
 ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ሰብዓዊ እርዳታዎች ምግብን እና መድሀኒትን ጨምሮ በተገቢው መንገድ ለተጎጀዎች እና እርዳታው
ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ላይ የሚደረጉ ስርቆቶችን እና ህገ-ወጥ
ንግዶችን እንዲቆጣጠር እና በእዚህም የፌደራል መንግስቱ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ፣
 በትግራይ ክልል ዋነኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቀርቡት የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ
ፕሮግራም (WFP) ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ ምክንየት የሆነውን የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ስርቆት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር
እንዲሁም የፌደራል መንግስት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በህግ እንዲጠይቁ እና በሰብዓዊ እርዳታ
ቁሳቁሶች ላይ ተገቢውን በቂ ቁጥጥር እንዲያደርጉ፣
 በትግራይ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ከፍተኛ ርሀብ የፌደራል መንግስት እንዲሁም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር
ተገቢውን በቂ ትኩረት በመስጠት ካስከተለው ጉዳት የከፋ ጉዳትን እንዳያደርስ እና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ተቀናጅተው
በመስራት አፋጣኝ ምላሽ እንደሰጡ፣
 ሰዎች ምግብ የማግኘት መብት እንዳላቸውና የእዚህም መብት ዝቅተኛ ዋና ግዴታ ከርሀብ የመጠበቅ መብት መሆኑን በመረዳት
መንግስት ይህንን መብት የማሟላት ተቀዳሚ ኃላፊነቱን እንዲወጣና በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የፌደራል መንግስት
ድጋፍ ሰጪ የሆኑትን USAID እና WFP በማስተባበር ቀድሞ ከሚሰጠው የተሻለ፣ ወቅቱን እና ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ
ድጋፍ እንዲሰጡ በማስተባበር ረገድ የበኩሉን ግዴታ እንዲወጣ፣
 የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በትግራይ ክልል ያቋረጡትን
የምግብ እና የመድሀኒት ድጋፍ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያስጀምሩ፣
 አገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሆኑ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት በትግራይ ክልል ያለው ከፍተኛ የምግብና መድሀኒት እጥረት
እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛና አጣዳፊ መሆኑን በመረዳት አቅም በፈቀደ መጠን እርዳታዎችን በፍጥነት እንዲያቀርቡ እና
የፌደራሉም መንግስት ይህንን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ይህን አስቸኳይ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 በመጨረሻም ኢሰመጉ በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የክትትልና የምርመራ ስራ ለመስረት
እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዳግም ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን በእዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ሀምሌ 21/2015 ዓ.ም


አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የኢሰመጉ ጋዜጣዊ መግለጫ / www.ehrco.org 3

You might also like