You are on page 1of 24

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክርክር ስለማድረግ፡ ህጉና አፈፃፀሙ በአማራ ክልል

ፍርድ ቤቶች

ታፈሰች ወልዴ*

አህፅሮተ ይዘት

በመሰረቱ ተከሳሽ በተከሰሰበት ጉዳይ ቀርቦ መከራከር ዋነኛው የወንጀል ስነ ስርአት ፅንሰ ሃሳብ
መሰረት ነው፡፡ ከዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት በሚለይ ሁኔታ ልዩ የወንጀል ስነ ስርአት ህጎች
ተግባራዊ የሚደረጉበት ሁኔታ በብዙ ሃገራት ህግ ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡ በክርክር ወቅት
የተከሳሽ የመገኘት መብት ከፍታሃዊ የሙግት ስርአት ጋር በእጅጉ ተቆራኝቶ የሚታይ ሲሆን
ነገር ግን ይህ መብት ምሉእ(ABSOLUTE) አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ መብት የማህበረሰቡን
ደህንነት ባሳካ መልኩ ተግባራዊ መሆን ስላለበት ጭምር ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ፅንፎች
ሊያማክል በሚችል ልዩ ሁኔታ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክርክሮች ማካሄድም በሃገራችን
የወንጀል ስነ-ስርአት ህግ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ የፅሁፉ አላማም ተከሳሽ በሌለበት የሚደረጉ
የክርክር ሂደቶች ላይ እየታዩ ያሉትን ችግሮች ይዳስሳል፡፡ የጥናቱም ዘዴ አይነታዊ ሆኖ ውሳኔ
ያረፈባቸውን የፍርድ ቤት መዝገቦች ሆን ብሎ በመለየት የተመረመሩ ሲሆን ተግባራዊ
አፈጻፀም ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመለየት ከባለሙያዎች ጋር ቃለ-መጠይቆች ተደርገዋል፡፡
በመሆኑም ይህን የጥናት ዘዴ በመመርኮዝ በተሰበሰቡ ዳታዎች መሰረት ተከሳሽ በሌለበት
የሚደረጉ ክርክሮች ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎች ልዩነቶች ያለባቸው ሲሆኑ በተለይም በወንጀለኛ
መቅጫ ስነ-ስርአት ህግ አንቀጽ ቁጥር 161 ዙሪያ የሚነሱ የትርጉም ልዩነቶች በፍርድ ቤቶች
የሚሰጡ ውሳኔዎች ወጥና ተገማች እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡


*
LLM,LLB,በአብክመ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ
1.ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት አስፈላጊነት
በወንጀል የሙግት ስርአት ውስጥ ተከሳሽ በተገኘበት ክርክር ማካሄድ መሰረታዊው ጽንሰ ሃሳብ
ነው፡፡ ሆኖም ተከሳሽ መጥሪያ ደርሶት በክርክር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ያለመሆኑ የተበደሉ
ሰዎች ፍትህ እንዳያገኙ ብሎም ፍትህን በእጃቸው እንዲያስገቡ የሚገፋፋ ምክንያት ከመሆኑም
ባሻገር መንግስት የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ፍትህ መረጋገጥ እንዳይችል
ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮች የተፋጠነ ውሳኔ በመስጠት የህግ
ስርአቱን ከማቀላጠፍ ባሻገር ተከሳሽ ባለመቅረቡ ምክንያት የሚጠፉ፣ የሚበላሹ ማስረጃዎች
፣በምስክርነት የሚቀርቡ ሰዎች የሚሰጡትን የምስክርነት ቃል ከመዘንጋት የሚታደግ ሲሆን
ተከሻሹ ጭራሹኑ እንዳይቀጣና የወንጀል ህግ አላማ የሆነውን የማረምና የማነጽ አላማን ሳይሳካ
እንዳይቀር ያደርጋል፡፡1 በሌላ ጎኑ የግለሰብ ነጻነትን ስንመለከት በክርክር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ
እንዲሆን ተፈቅዶለት ከህግ በመሸሽ በክርክሩ ተሳታፊ ሳይሆን ሲቀር በልዩ ሁኔታዎች ተከሳሽ
በሌለበት ክርክሩ ይካሄዳል፡፡ በአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች የቃልኪዳን ሰነድ
በአንቀፅ 14 ንኡስ ቁጥር 3 ላይ እንደተመለከተውም ‹‹ማንኛውም ሰው በተከሰሰበት የፍርድ
ሂደት ላይ በአካል የመገኘት መብት አለው ፣ራሱም በመገኘት የቀረበበትን ክስ የመከላከል
መብት ወይም በጠበቃው እርዳታ እየታገዘ የመከላከል መብት አለው፡፡›› የሚለውን የዚህን
ድንጋጌውን ትርጉም የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚቴ በጄነራል ኮሜንት ቁጥር
13 (General Comment No.13) ሲያብራራ2
“When exceptionally for justified reasons trials in absentia are held, strict
observance of the rights of the defense is all the more necessary.”
ይህም በግርድፉ ሲተረጎም ‹‹በተወሰኑና ምክንያታዊ በሆኑ ሁኔታዎች ተከሳሽ በሌለበት የክስ
ጉዳዮች ሲታዩ የተከሳሽ መብቶች ጥብቅ በሆኑ ሁኔታዎችም ሊታዩ ይገባቸዋል›› በማለት
አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታዎች ተከሳሽ በሌለበት ክርክሮች የሚታይበት ሁኔታ
እንዳለ ሲገልጽልን ነገር ግን ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ሊካሄድ የሚችሉባቸው ምክንያታዊ
ሁኔታዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ይኋው ኮሚቴ አላስቀመጠም፡፡3


1
Lucas Tasar, ‘Trial in Absentia: Rescuing the "Public Necessity" Requirement to Proceed With
a Trial in the Defendant's Absence’ (2009) Barry Law Review Vol. 12, p. 153, 165
2
General Comment No. 13: Equality before the courts and the right to a fair and public hearing
by an independent court established by law (Art. 14) 04/13/1984.
file:///C:/Users/pc/AppData/Local/Temp/UN_Equality_before_courts_General_Comment_13_1984-
1.pdf
3
ዝኒ ከማሁ
2. በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ጉዳያቸውን ለመከታል ስላላቸው መብት

2.1. በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ስር

የተከሰሱ ሰዎች መብቶችን በተመለከተ በህገ መንግስት አንቀጽ 204 ላይ በዝርዝር የተመለከተ
ሲሆን አጭር በሆነ ግዜ ውስጥ ጉዳያቸው እንዲታይ ከመደንገግ አንስቶ የቀረበባቸውን ማስረጃ
የመመልከት፣የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ ማቅረብ
ወይም የማስቀረብ ፣ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙ ማድረግ፣በመረጡት ጠበቃ የመወከል
ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትህ የሚጓደልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግስት
ጠበቃ ስለሚያገኙበት ሁኔታ በህገ-መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም ክስ የቀረበባቸውን ሰዎች
መብት የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ መንግስቱ በዝርዝር ሲያስቀመጥ በክስ ሂደት ውስጥ የተከሳሽን በአካል
የመገኘት መብትን በግልጽ ደንግጎ አላስቀመጠውም፡፡ ነገር ግን በህገ መንግስቱ አንቀፅ
9(4)5መሰረት ሃገራችን የተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች የህግ አካል ተደርገው
የሚወሰዱ መሆናቸው በዚሁ ህገመንግስት ላይ የተቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸውና
አባል ከሆነችባቸው ሰነዶች አንዱ የሆነው የሲቪልና የፖለቲካ የቃልኪዳን ሰነድ ተከሳሽ በአካል
የመገኘት መብትን አካቶ በውስጡ ይዟል፡፡ የዚሁ ህገ መንግስት አንቀጽ 13(2)6 በህገ መንግስቱ
የተቀመጡት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው አለም አቀፍ
ህግጋቶች፣ከአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ስምነቶች እንዲሁም አለም አቀፍ ሰነዶች ጋር
ተጣጥመው መተርጎም እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም በአካል የመገኘት መብትን በህገ
መንግስቱ ስር አልተካተተም ለማለት አይቻልም፡፡

2.2. ፍትሃዊ የክስ ስርአት (Fair trial)


በአንድ ሃገር የወንጀል ሙግት ስርአት ውስጥ መኖር እና መረጋገጥ ከሚገባቸው መርሆች
አንዱ ፍትሃዊ የክስ ስርአት ነው፡፡ ፍትሃዊ የክስ ስርአት( Fair trial) ትርጉምን የብላክስ ሎው
መዝገበ ቃላት በሚመለከተው መልኩ ያስቀምጠዋል፡፡ Fair trial ‹‹a trial by impartial and
disinterested tribunal inaccordance with regular procedure››7ይህም በግርድፉ
ሲተረጎም ፍትሃዊ ክርክር ማለት ገለልተኛ እና የማይመለከተው ትሪቢውናል መደበኛ ህግና


4
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክሪያሳዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 1/1987፣1ኛ
አመት ቁጥር 1፣አዲስ አበበባ
5
ዚኒ ከማሁ
6
ዝኒ ከማሁ
7
Bryan.A.Garner, Blacks law dictionary, 2004,8th edition,west a Thomson business, p.634
ስርአትን ተመርኩዞ ክርክር ማካሄድ እንደ ማለት ነው፡፡ በፍትሃዊ የክስ ስርአት ውስጥ
የተከሳሽ በክርክር ወቅት መገኘት ዋነኛው መሰረት ጽንሰ ሃሳብ ከመሆኑ አንጻር ተከሳሽ
በሌለበት ክርክር በማካሄድ የተሰጠ ውሳኔስ እንዴት ፍትሃዊ ሊባል ይችላል የሚል ጥያቄ
ይነሳል፡፡
የፍትሃዊ ክርክር ስርአት መብት በውስጡ የተለያዩ ዘርፎች ያጠቃለለ ቢሆንም እንደ አጠቃላይ
መርህ ተከሳሽ ሁልግዜም ቢሆን የተከሰሰበትን ፍርድ የመመለስ፣የቀረበበትን ማስረጃ
ማስተባበል እንዲሁም የቀረቡበትን ምስክሮች የመጠየቅ መብቶችን በተመቻቹ ሁኔታዎች
ሊተገበርለት የሚገባበትን ሁኔታዎችን የሚያካትት መርህ ነው፡፡8 ፍትሃዊ የክስ ክርክር ስርአት
በአንድ የወንጀል ስርአት ውስጥ አለ ለማለት ተከሳሹ እንደ ንጹህ የመገመት መብት መኖር
፣ያለምንም መጓተቶች መዳኘት መቻል፣በአካል ተገኝቶ መከራከር ወይም በጠበቃው በኩል
መከራከር፣የቀረቡበትን ምስክሮችን መመርመር እና ለመከላከያ የሚሆኑትን ምስክሮች መጥራት
የሚያስችል መብቶችን በውስጡ አካቶ ሲይዝ ነው፡፡
አለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች የቃልኪዳን ሰነድ አንቀፅ 14 ንኡስ ቁጥር(3)9ስር
አንድ ተከሳሽ ክስ ሲቀርብበት ዝቅተኛ የሆኑ የመብት ጥበቃዎች (minimum safeguard)
ሊደረጉለት ይገባል በማለት ሰነዱ ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም ዝቅተኛ ጥበቃዎች ተፈፀሚነታቸው
እኩል በሆነ መልኩ
• ተከሳሽ በአካል በተገኘበት ክሱን ማካሄድ
• ተከሳሹ ራሱን እንዲከላከል ወይም በጠበቃ አማካኝነት ክሱን እንዲከላከል ማድረግ
እንዲሁም ጠበቃ ማቆም የማይችል ከሆነና ፍትህ መጓደልን ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ
ከሆነ በነጻ ጠበቃ ሊቆምለት እንደሚገባ ይኸው የቃል ኪዳን ሰነድ ያስቀምጣል፡፡ በሰነዱ
ላይ የተቀመጡትንም ዝቅተኛ ዋስትናዎች እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
2.2.1.ተከሳሽ በአካል በተገኘበት ክሱን ማካሄድ (the right to be present)
በክስ ክርክር ወቅት የተከሳሽ በአካል የመገኘት መብት ከከሳሹ አካል ተከሳሽን ክሱ የሚሰማበትን
ቦታ፣መቼ እና የት እንደሚሰማ አስቀድሞ ከማሳወቅ ግዴታ ጋር የሚቆራኝ ነው፡፡ ይህም
ተከሳሽም በተባለው ግዜ እንዲቀርብ ማድረግ የሚያስችል እና ተከሳሽን ያለበቂ ምክንያት
ከክርክሩ ውጭ እንዳይሆን የሚረዳ መብት ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት


8
Sarah J. Summers, Fair Trials (Hart Publishing 2007) ገጽ 113 እንዲሁም
9
The International Covenant on Civil and Political Rights (adopted on 16 December 1966,
entered into force on 23 March 1976 art. 14(3)
ኮሚቴ በጄኔራል ኮሜንት ቁጥር 3210ስር ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ለማካሄድ መወሰድ
ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ሲያስቀምጥ ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ከመደረጉ በፊት ዐቃቤ ህጉ
አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ ተከሳሽ የተከሰሰበትን ጉዳይ ለማሳወቅ ጥሪ እንዲደርሰው
ማድረጉን ለፍርድ ቤቱ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሲቪልና የፖለቲካል
የቃል ኪዳን ሰነድ አንቀፅ14(3)መ11 ላይ እንደተቀመጠውም ከሳሽ ለተከሳሽ የተከሰሰበትን ክስ
አስቀድሞ በማሳወቅ ክሱ መቼና የት እንደሚካሄድ መግለፅ መቻል ያለበት መሆኑን በግዴታነት
ያስቀምጣል፡፡ ይህ ሳይሆን ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ማካሄድ ተከሳሽ በክርክር ወቅት በአካል
የመገኘት መብቱን የሚጣረስ ነው በማለት በጄኔራል ኮሜንቱ ላይ አስፍሯል፡፡
2.2.2. ተከሳሹ ራሱን እንዲከላከል ወይም በጠበቃ አማካኝነት የመወከል መብት(the right to
defend onself or to be represented by legal council)
ይህ መብት ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ እና ማስረጃ አውቆ ራሱን እንዲከላከል የሚያስችል መብት
ሲሆን በህገ-መንግስቱም በአንቀፅ 20(5)12 ላይ ተደንግጎ እናገኛዋለን፡፡ ይህ መብት ተከሳሽ
ከአድሎ በጸዳ መልኩ የቀረቡበትን ምስክሮች የመመርመር እድል ማግኘትና ለመከላኪያ
የሚሆኑትንም ምስክሮች አቅርቦ የማሰማት መብትንም በውስጡ ያካትታል፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር
ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ተከሳሽ በአብዛኛው የህግ እውቀት የሌለው በመሆኑ ጉዳዩን አይቶ
የሚከራከራከርለት ጠበቃ ማቆም የተከሳሽ ሙሉ መብት ነው ፡፡ በዚህ መብት ስር በፈለገው
ጠበቃ የመወከል፣ችሎታ ባለው ጠበቃ የመወከል መብት በተለይም ይህን ማድረግ አቅም
ከሌለው ፍትህ እንዳይጓደል በሚል በመንግስት ጠበቃ ሊቆምለት የሚያስችል ድንጋጌ በውስጥ
ያካትታል፡፡ ሆኖም በሃገራችን ተከሳሽ በሌለበት በሚደረጉ ክርክሮች ላይ የክርክሩን ሚዛናዊነት
ለማስጠበቅ በጠበቃ የመወከል ስነስርአት የለም፡፡
አሁን አሁን እየዳበሩ የመጡ እይታዎች ተከሳሽ በክርክር ላይ ሳይገኝ ቢቀር እንኳን ሳይወከል
እንዳይቀርና ተከሳሹ ራሱ ባለመገኘቱ ምክንያት የቀረቡበትን ማስረጃዎች መከላከል ባይችልም
የተከሳሹን መብት እንዲሁም የክርክሩን ሚዛን ለማስጠበቅ ሲባል ጠበቃ ሊቆምለት ይገባል
የሚሉ እይታዎች ብቅ ብለዋል፡፡13 በተለይም ይህ አሰራር በፈረንሳይ በቀላል ወንጀሎች


10
UNHRC General Comment No. 32 Right to equality before courts and tribunals and to a fair
trial
11
ከላይ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 9
12
ከላይ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 4
13
N.W. Taylor, ‘Trial: defendant voluntarily absenting himself from trial – representatives
withdrawing from trial’ (October 2006) Criminal Law Review 952.
የተከሰሱ ሰዎች መብታቸውን በመተዋቸው ምክንያት በሌሉበት ጉዳያቸው ሲታይ በጠበቃ
እንዲወከሉ የሚደረግበት አሰራር አለ፡፡14 ከዚህ በተጨማሪም በአለምአቀፍ ትሪቡናልስ15ይህ
አሰራር በመጠኑ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በክርክር ሂደቱ ላይ ባይገኝም ጠበቃ
ተገኝቶ እንዲከራከር መፍቀድ የፍታሃዊነትን ሚዛን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ
በሃገራችንም ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮች በጠበቃ መወከል የሚያስችል የስነስርአት ህግ
ቢዳብር መልካም ነው፡፡
3.የተከሰሱ ሰዎች ጉዳያቸው በሌሉበት ስለሚታይበት ሁኔታ

3.1.ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክርክር ማድረግ ትርጉም

ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ማድረግ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ መነሻ ነው ተብሎ የሚወሰደው
በተለይም ለወንጀል ጉዳዮች አጠቃቀም በዋነኝነት ተለይቶ በመዋል ሰፊ እውቅና ያገኘው
አብሰንሺያ ‹‹absentia›› የሚለው የላቲን ቃል ነው፡፡16 ይህ ቃል በግርድፉ ወደ አማረኛ
ሲተረጎም ባልተገኘበት (በሌለበት) ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በሃገራችን የወንጀለኛ መቅጫ
ስነስርአት ህግ አንቀጽ 16017 ላይ ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮችን የገለጸበት አግባብ ከዚህ
ቃል የሚለይ ቃል መርጧል፡፡ በሌለበት(default) የሚለው ቃል ትርጓሜ ብላክስ ሎው መዝገበ
ቃላት ሲያስቀምጠው፡- ‹‹default ፡- to fail to appear or to answer›› በሚል ነው፡፡ ይህም
ወደ አማረኛ ሲተረጎም ሊቀርብ ያለመቻል ወይም መልስ ለመስጠት ያለመቻል የሚል ትርጓሜ
አለው፡፡18 ተከሳሽ በሌለበት ክርክር የማድረግ ፅንሰ ሃሳብም ተከሳሹ በፍርድ ቤት በአካል ሳይገኝ
በሌለበት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ መስጠት ነው፡፡ ሆኖም የወንጀል ስነስርአት ህጋችን
የተጠቀመበት በሌለበት(default) የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከ‹‹absentia›› ከሚለው ፅንሰ ሃሳብ ጋር
መሰረታዊ ልዩነት አለው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህጋችን
ከጅምሩም ይሁን በክርክር ሂደት ላይ ለማይቀርቡ ተከሳሾችን በተመለከተ ልንከተል ስለሚገባን
ስነ ስርአታዊ አካሄድ እንደ ፍትሃብሄር ስነስርአት በውስጡ አላካተተም፡፡ ይህንንም ለመመለስ

14
የፈረንሳይ የወንጀል ስነስርአት ህግ አንቀጽ 411(1), Aaccused charged with an offense punishable by
a fine or less than two years' imprisonment may waive appearance upon proper application to
the court, and still be represented by counsel.
15
Evert F. Stamhuis,Absentia trials and the right to defend ,University of Western Ontario,
London Ontario, Canada ,2001 p.727
16
IBA Report on the ‘Experts’ Roundtable on trials in absentia in international criminal justice,
International Criminal Court and International Criminal Law Programme, September 2016
17
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 1/1954 ዓ.ም ነጋሪት ጋዜጣ
፣አዲስ አበባ አንቀጽ ቁጥር160 (ከዚህ በሃላ የወ/መ/ስ/ስ/ህግ) በሚል ሊጠቀስ ይችላል፡፡
18
የግርጌ ማስታወሻ 7፣449
የሌሎች ሃገሮችን ልምድም ስንመለከት አብሰንሺያ ‹‹absentia›› የሚለውን ቃላት በተለይ
ሁኔታ ለወንጀል ጉዳዮች የሚጠቀሙ ሲሆን ለፍታብሄራዊ ጉዳዮች ደግሞ በሌለበት(default)
የሚለውን ቃላት ይጠቀማሉ፡፡ በሃገራችን ተከሳሽ በሌለበት የሚደረግ ክርክር በሌለበት(default)
ተብሎ የመቀመጡን ምክንያት በግልፅ የሚመልስልን ፅሁፍ ባይገኝም እንደ ፍትሃብሄር
ህጋችን የተከሳሽን ያለመቅረብ ውጤት አለማንሳቱ አንደ አንድ የህግ ክፍተት ከመውሰድ ባሻገር
ከፍታብሄር ህጉ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም (ውጤት) አለው ለማለት ግን አያስደፍረንም፡፡
3.2. አንድ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ እዲታይ የሚወሰነው መቼ ነው?
የወንጀል ህግ መርህ ተከሳሽ ባለበት ክርክር ተደርጎ ውሳኔ መስጠት ቢሆንም ይህ መርህ
በልዩ ሁኔታ ሊታለፍ ይችላል፡፡ በተግባርም ከክርክሩ ጅምር ካልቀረቡ ተከሳሾች አንስቶ
በክርክር መሃል የሚቀሩ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክርክር በማድረግ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
በስነስርአት ህጋችን ስር በክርክር መሃል የሚቀሩ ተከሳሾችን በተመለከተ የመዝገቡ ውጤት
ምን ይሆናል በሚል በግልጽ ባለመመላከቱ ምክንያት የተለያየ የአሰራር ልዩነት ፈጥሯል፡፡
ሆኖም ይህንን እና ተያያዥ ጥያቄዎችን በሚፈታ መልኩ ሰበር ተከታዩን ውሳኔ ወስኗል፡፡
19
የዚህ ክርክር አመጣጥ ባጭሩ ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 555(1)ለ በመተላለፍ በሰው
አካል ላይ ከባድ ጉዳት የማድረስ ወንጀል ፈጽሟል በማለት ክስ ቀርቦበት ድርጊቱን
አለመፈፀሙን ክዶ ተከራክሯል፡፡ ዐቃቢ ህግም ምስክሮቹን አቅርቦ ካሰማ በኋላ ተከሳሽ
እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ መከላኪያ ምስክሮቹን እንዲያሰማ በተደጋጋሚ ቀጠሮ
ቢሰጥም ተከሳሽ ሊቀርብ ባለመቻሉ ምክንያት ዐቃቢ ህግ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/161 መሰረት ጉዳዩ
በሌለበት እዲታይለት ለፍርድ ቤቱ አሳስቧል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ የተከሰሰበት ድንጋጌ
በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/161 የሚታይ አይደለም በማለት ፖሊስ ተከሳሽን ካለበት ቦታ አፈላልጎ
ሲያቀርበው የዐቃቤ ህግ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብቱን ጠብቆ ዘግቶታል፡፡ በዚህም ውሳኔ
አቃቤ ህግ ቅር በመሰኘቱ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣እንዲሁም ሰበር
ሰሚ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም አቤቱታውን ባለመቀበል ሰርዘውታል፡፡
ጉዳዩ ለፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት20 ሲቀርብ ተከታዩን ጭብጥ በማንሳት ያስቀርባል ብሏል፡፡
‹‹ተከሳሽ መከሰሱን አውቆ ምስክር ከተሰማበትና መከላክያ ምስክር ይዞ ባለመቅረቡ የመከላከል
መብቱ ታልፎ ውሳኔ እንዲሰጥ የቀረበው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ያለመቀበሉ ተገቢ ነው ወይስ


19
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ.የወንጀል ህግ ፣አዋጅ ቁጥር 414/1996 ፣አንቀጽ 596
20
የፍደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር የመ/ቁጥር 127813 አቃቤ ህግ እና አንዱአለም ገናናው
መስከረም 22/2010 የተሰጠ ውሳኔ(ያልታተመ)
አይደለም›› በማለት በዚህ ጭብጥ መሰረት ጉዳዩን ሲመረምር ‹‹ ተጠሪ ክሱ በሚሰማበት ቀን
ቀርቦ የዐቃቢ ህግ ምስክሮች ከተሰሙና መከላኪያ ምስክር አቅርቦ እንዲያሰማ በተቀጠረበት ቀን
ሳይገኝ የቀረ በመሆኑ በህገመንግስቱ አንቀፅ20(4) ተከሳሽ የተሰጠውን ምስክሮችን የመመርመር
እና የመጠየቅ መብቱ ሙሉ በሙሉ በተከበረበት ሁኔታ ተጠሪ በራሱ ፍቃድ የተጠበቀለትን
የመከላከል መብት የተወው ሲሆን ይህም መሆኑ ዳኞች የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ውሳኔ
ከመስጠት የሚያግዳቸው አይደለም›› በማለት መዝገቡን የስር ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በተገኘ ግዜ
ይንቀሳቀስ ማለቱ አግባብነት የለውም የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይኸው ፍርድ ቤትም በፍርድ
ሃተታው ላይ በስር ፍርድ ቤቶች ሲነሳ የነበረውን ጉዳዩ በሌለበት መታየት አለበት የለበትም
የሚለውን ክርክር በማንሳት ‹‹ፍርድ ቤቱ አንድን ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ማየት እንዲችል
ተከሳሹ በቀጠሮው ቀን ቀርቦ ያለ በቂ ምክንያት መቅረቱ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን
በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/161(1)እና (2)ሀ ንባብ የሚያሳየን ነው፡፡ አንድ ጉዳይ በሌለበት ታየ የሚባለው
መቼ ነው? ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ የሚታይበት ሁኔታ የሚደነግጉት ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/
161እስከ 16421 የተደነገጉት ድንጋጌዎች ይዘት ትርጉምና ተፈፃሚነት ውጤት እንዲሁም
በወንጀል የተከሰሰ ሰው በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት በሌለበት ታይቶ ከሚሰጥ ፍርድ እንዴት
አይነት ጉዳይ ነው የሚለውን የህገመንግስቱ አንቀፅ 20(4) እና ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/149(1)እና(4)
ድንጋጌ ይዘት መንፈስ ጋር መታየት አለበት፡፡›› በማለት አስቀምጧል፡፡ ይህ ውሳኔ የሃተታ
ግልጽነት የጎደለው ቢሆንም ካጠቃላይ የሃተታው መንፈስ የምንረዳው ጉዳዩ በሌለበት
የሚታየው ተከሳሽ ክስ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ሲቀር (ከጅምሩ) ሲሆን በክርክር መሃል
የሚቀሩ ተከሳሾችን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን በአካል
የመገኘት መብት መጠቀም እንዳልፈለገ ተቆጥሮ ውሳኔ መስጠት ያለበት መሆኑን ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ ውሳኔ ከሀታታዎቹ መንደርደሪያ እና ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች ይዘት
የምንረዳው ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዮች መታየት ያለባቸው ከጅምሩ በክርክር ላይ ያልተገኙ
ተከራካሪዎችን የሚመለከት መሆኑን እንዲሁም በክርክር መሃል የሚቀሩን ተከሳሾች
በተመለከተ በህገመንገስቱ የተሰጠውን የመደመጥ መብት ያልተጠቀመበት ተከሳሽ መብቱን
እንደተወ ተቆጥሮ በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤቱ የመሰለውን ከመወሰን የሚያግደው አለመሆኑን
የሚያሳይ የትርጉም ይዘት አለው፡፡


21
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ 17፣አንቀጽ 161 እስከ 164
በአሜሪካ ፍርድ ቤት22 እ.አ.አ.1912 የተሰጠ የመጀመሪያ ውሳኔ ተከሳሽ ፍርድ ቤት መቅረብ
ካልፈለገ መብቱን በፍቃዱ እንደ ተወ ተቆጥሮ ውሳኔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተወስኗል፡፡ ይህም
ውሳኔ የአሜሪካ የፌደራል ህግ የወንጀል ስነስርአት አዋጅ ላይ ተካቶ መብትን መተው የሚል
ጽንሰ ሃሳብን እንዲዳብር አድረጓል፡፡ ሆኖም ተከሳሽ ይህን መብቱን ስለመተው በጽሁፍ ወይም
በችሎት ቀርቦ የሚገልጽ ሲሆን በክርክር ወቅት የመቅረብ መብትን መተወ በሚለውም ጽንሰ
ሃሳብ በአሜሪካ ህግ ስርአት ውስጥ በኬዝ ሎውም ሆነ በህግ የዳበረ ስርአት ነው፡፡23 ነገር ግን
በሃገራችን መብትን መተው የሚል ጽንሰ ሃሳብ ተካቶ የማይገኝና ከተከሳሽ ድርጊት በመነሳት
ግምት ለመውሰድ የሚያስችለን የህግ ማዕቀፍ የሌለ ሲሆን ከላይ የተጠቀሰውም የሰበር
ውሳኔም ዓላማ ውሳኔዎችን ከመቋጨት እና የተከሳሽን መብት ከህዝብ ጥቅም ጋር በመመዘን
የተሰጠ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡
4.በተግባር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች

4.1.የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር161 አተረጓጎም በፍርድ ቤቶች

Ø የመጀመሪያው አተረጓጎም

የዚህ ድንጋጌ ትርጉም ዋነኛ መከራከሪያ ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ
የተቀመጡ በመሆናቸው መተርጎም ያለባቸው በጠባቡ ነው፡፡ ሌላኛው መከራከሪያ ሃሳባቸው
በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ161 ላይ እንደተቀመጠው ተከሳሽ በሌለበት ክርክር ሊደረግ የሚገባው የቅጣት
መነሻቸው 12 አመትና ከዚያ በላይ ጽኑ እስራት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን በሚመለከት ብቻ
ነው፡፡ ለዚህ ትርጉም እንደ ምክንያቱን የሚያስቀምጡት ይህ ልዩ ስነስርአት የተቀመጠበት
አላማ ከወንጀሉ ከባድነት አንፃር ሲሆን ተከሳሾች ባለመገኘታቸው ብቻ ጉዳያቸው ሳይታይ
እንዳይቀር ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአትም የቅጣት መነሻቸው 12 አመት እና ከዚያ


22
Diaz v. United States, 223 U.S. 442 (1912).
23
Eugene L. Shapiro, ‘Examining an Underdeveloped Constitutional Standard: Trial in Absentia
and the Relinquishment of a Criminal Defendant's Right to be Present’ (2012) Marquette Law
Review Vol. 96, ገጽ.593, 616 እንዲሁም የአሜሪካው
FEDREAL RULE CRIMINAL Procedure 43, advisory committee notes n.1–3 (1944). Rule 43
was rephrased, effective December 1, 2011, retaining the consequence that the right to be
present is waived by a defendant who is voluntarily absent from trial. According to Rule 43 (c);
the defendant should be present at the beginning of the process then s/he can waive this right,
or because of her or his disruptive behavior, the court can order the removal the defendant from
the courtroom.
በላይ የሆኑ ወንጀሎችን የሚመለከት ብቻ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ በአጠቃላይ በዚህ
አተረጓጎም መሰረት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ161 ላይ የተቀመጠው የቅጣት መስፈርት መነሻ እንጂ
መድረሻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም ብለው ክርክራቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ይህንም አቋማቸውን
በሚከተሉት መዝገቦች ላይ ለአብነት ማየት እንችላለን፡፡
ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(1) እና 540 በመተላለፍ24 የመግደል ሙከራ አድርጓል በሚል
ክስ የቀረበበት ሲሆን ተከሳሽ የተከሰሰ መሆኑን አውቆ እንዲቀርብ መጥሪያ እንዲላክለት
ቢደረግም ባለመቅረቡ እንዲሁም የጥሪ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲወጣ ቢደረግም
አሁንም ተከሳሹ ሊቀርብ ባለመቻሉ ምክንያት ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ
ባቀረበው ማሳሰቢያን መሰረት ፍርድ ቤቱ የቅጣት መነሻቸው 12 አመት በታች ሆነው
ጣሪያቸው ግን ከ12 አመት በላይ የሚያስቀጡ ወንጀሎችን ሊያካትት ይገባል ወይስ አይገባም
የሚለውን ጭብጥ በመያዝ በአብላጫ ድምጽ የሚከተለውን ብይን ሰጥቷል፡፡ የውሳኔው
ዝርዝርም፡-
‹‹ የአንድ ወንጀል ከባድነት ቀላልነት የሚወሰነውም በሚያስቀጣው ቅጣት በመሆኑ ህጉም 12
አመትን እንደ መለያ አድርጎ ያስቀመጣቸው መነሻቸው ከ12 ዓመት እና ከዚያ በላይ
ለሚያሳስሩ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ነው፡፡ በመሆኑም የቅጣት መነሻው ከ12 አመት በታች
ቢሆንም ጣሪያቸው 12 አመት በላይ በሚሆንበት ግዜ ጉዳዩ በሌለበት ይታይ የሚያስብል
አይደልም፡፡ ለምሳሌ የወንጀል ህግ 67025 የወንብድና ወንጀል ከ1 አመት እስከ15 አመት
ሊደርስ በሚችል እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ጣሪያው 15 አመት ስላለ ብቻ ተከሳሽ በሌለበት
እንዲካሄድ ማድረጉ ተከሳሽ አንድ አመት ሊቀጣ የሚችል እድል ያለው ከመሆኑ አንፃር
በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.161(2)(ሀ)ስር የተቀመጠውን ከ12 አመት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት
የሚያሳስር የሚለውን ሀረግ የሚያሟላ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች
በሚተረጉሙበት ግዜ ድንጋጌዎቹ ሊሳኩ ከሚፈልጉት አላማ በተጨማሪ የተከሳሹን መብት
በማያጣብብ መልኩና ተከሳሹን በሚጠቅም ሁኔታ መተርጎም አለባቸው፡፡ ስለዚህ ተከሳሹ ላይ
የቀረበው የወንጀል ድንጋጌ መነሻ 12 አመት በታች በመሆኑ በሌለበት ሊታይ አይገባም››
በሚል በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡


24
ዐቃቤ ህግ እና አንዱአለም እሸቴ በአ.ብ.ክ.መ.የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል መዝገብ ቁጥር
02-10929 በቀን 26/04/2008 የተሰጠ ውሳኔ እንዲሁም የግርጌ ማስታወሻ 20፣አንቀጽ 27 እና 540
25
የግርጌ ማስታወሻ 20፣አንቀጽ 670
በሌላ ጉዳይም በቁጥር 3 ተከሳሾች በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ዐቃቤ ህግ አንቀፅ 32(1)ሀ
እና 620(2)ሀ በመጥቀስ በተከሳሾች ላይ ክስ አቅርቦባቸው26 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ሊቀርቡ
ባለመቻላቸው ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ዐቃቤ ህግ ባሳሰበው መሰረት ፍርድ ቤቱ የሚከተለው
ብይን ተሰጥቷል፡፡
‹‹1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ በአማራጭ ሲሆን የተጠቀሱበት ድንጋጌም በአንደኛው ክስ ከ5
አመት እስከ 20 ዓመት በሌላው ክስ ደግሞ 3 አመት እስከ 15 የሚያስቀጣ ሲሆን በ3ተኛ
ተከሳሽ ላይ የተጠቀሰውም የህግ ድንጋጌ ከ 5አመት እስከ 20 አመት ሊደርስ የሚችል ጽኑ
እስራት የሚያስቀጣ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለሆነም ተከሳሶች ጥፋተኛ ተብለው ቢቀጡ
ቅጣቱ ከአምስት አመት ጀምሮ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 161(2)ሀ
ደግሞ ተከሳሽ በሌለበት ክሱን ለመስማት እና ክሱ ሊቀጥል የሚችለው ቅጣቱ 12 አመት
በታች በማያንስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ድንጋጌ
አንጻር እና ተከሳሾች ክስ የቀረበባቸው ድንጋጌ ጋር በመመርመር ክርክሩ ተከሳሾች በሌሉበት
ሊቀጥል አይገባም›› በማለት ብይን ተሰጥቷል፡፡
Ø ሁለተኛው ትርጓሜ
ይህ መከራከሪያ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ161 ስር የተቀመጠው የቅጣት መስፈርት ሊታይ የሚገባው
የቅጣት መነሻው ሳይሆን የቅጣት መድረሻው መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ምክንያት ብለው
የሚያስቀምጡትም የወንጀል ቅጣት አቀማመጥ ከ-እስከ በሚል የተቀመጠ በመሆኑ አብዛኛውን
ድንጋጌዎች ጥቅም አልባ ያደርጋል፡፡ ስለዚህም መነሻው ምንም ይሁን ምን መድረሻው 12
አመት ጽኑ እስራትን የሚያስቀጣ ከሆነ ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ ውሳኔ ሊሰጥ ይገባዋል በሚል
የሚቀመጥ ክርክር ነው፡፡ ይህን ትርጓሜ የሰፋ ተግባራዊነት ያለው ሲሆን ለአብነትም
ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(1) እና 54027 በመተላለፍ ተራ የሰው መግደል ሙከራ
ወንጀል ፈጽሟል በሚል ክስ ቀርቦበት የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ በሌለበት የሚታይ አይደለም
በሚል መዝጋቱን አስመልክቶ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ይግባኝ28 መሰረት ጉዳዩ በሌለበት መታየት
የለበትም የተባለው በአግባቡ ነው ወይ የሚለውን ጭብጥ ፍርድ ቤቱ በመያዝ እንደሚከተለው


26
አቃቤ ህግ እና እነ ዝናቤ ሞላ በቁጥር 3 ሰዎች፣በአ.ብ.ክ.መ. የራያ ቆብ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል መዝገብ
ቁጥር 0202509 20/03/2008 ዓ.ም.የተሰጠ ውሳኔ
27
የግርጌ ማስታወሻ 20፣አንቀጽ 540
28
ዐቃቤ ህግ እና ይመር ሰይድ በአ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደቡብ ወሎ ዞን እና አካባቢዋ የይግባኝ ወንጀል
መዝገብ ቁጥር 02-03683 13/11/2008 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ
መርምሮታል፡፡ የፍርድ ውሳኔውም ከላይ በአብይነት የተጠቀሰው መዝገብ ውሳኔን የሻረ
በመሆኑ የውሳኔውን ዝርዝር እንደሚከተለው እናያለን ፡፡
‹‹በመርህ ደረጃ የወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ ባለበት ሊካሄድ እንደሚገባው ግልጽ ነው በልዩ ሁኔታ
ግን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/ 193፣160እና ተከታዮቹ ባሉት ድንጋጌዎች ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል
ሙግት እንደሚካሄድ ተቀምጧል፡፡ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/161(2) ስር ተከሳሽ በሌለበት ሊታዩ
የሚችሉ ጉዳዮች ሲያስቀምጥ ከአስራ ሁለት አመት በታች በማያንስ የሚያሳስር በሚል
የተቀረጸ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ድንጋጌ ከወንጀል ህጉ ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች እና ስነ-
ስርአቶች ሊያሳካ ከፈለገው ዓላማ እና ግብ ጋር አስተሳስሮ ማየት ይጠይቃል፡፡ በዚህም
የወንጀል ህጉ ላይ ከተጠቀሱት የወንጀል ድንጋጌዎች መነሻ ቅጣት 12 አመት የሆነ የለም፡፡
በመሆኑም ይህ ድንጋጌ ሊተረጎም የሚገባው ህግ አውጭው ያስቀመጠውን የቅጣት ጣሪያ
እንጂ ወለሉን በማየት አይደለም፡፡›› በማለት ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡
እንዲሁም በሌላ ጉዳይ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 27(1) እና 597(1) ስር
የተመለከተውን በመተላለፍ በሴት ልጆች መነገድ ሙከራ ወንጀል29 ክስ ቀርቦበት በአካባቢው
ተፈልጎ ሊቀርብ ባለመቻሉ የጋዜጣ ጥሪ የተደረገለትና ያልቀረበ በመሆኑ ጉዳዩ በሌለበት
በመታየት የጥፋተኝነትና እና የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይም ተከሳሽ የኢ.ፈ.ዲ.ሪ
የወንጀል ህግ አንቀፅ 27(1) እና 696(ሐ)በመተላለፍ ከባድ ማታለል ሙከራ30 ወንጀል ፈጽሟል
በሚል ክስ ቀርቦበት በጋዜጣ ጥሪ የተደረገለት ቢሆንም ሊቀርብ ባለመቻሉ ምክንያት በሌለበት
እንዲታይ ትዕዛዝ ቢሰጥም ተከሳሽ ሊገኝ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በተከሳሽ ላይ
የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም የቅጣት መነሻ ወለላቸው ዝቅ ብሎ የቅጣት መድረሻ ጣሪያቸው ከፍ ብሎ የተደነገጉ
ድንጋጌዎችን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ161 መሰረት ተከሳሽ በሌለበት የሚታይበት አሰራር አለ፡፡
4.2. ተከሳሽ በሌለበት የሚካሄዱ ክርክሮች በይግባኝ ስርአት ስር

በይግባኝ ክርክር ወቅት በፍርድ ቤት መገኘት(appearance) ከመጀመሪያ ደረጃ ክርክር በተለየ


ሁኔታ የመልስ ሰጭ መቅረብ አስገዳጅ አይደልም፡፡ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 193(2)31 ስር ተደንግጎ


29
በአ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ወሎ እና አካባቢዋ ምድብ ችሎት የወንጀል መዝገብ ቁጥር 0202991
ጌትዬ ተድላ እና ዐቃቤ ህግ ፣መጋቢት 8/2008 የተሰጠ ውሳኔ፡፡
30
በአ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ወሎ እና አካባቢዋ ምድብ ችሎት የወንጀል መዝገብ ቁጥር 02-03979
ዐቃቤ ህግ እና እንድሪስ ዓሊ፣ታህሳስ 20/2009 የተሰጠ ውሳኔ፡፡
31
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር17፣አንቀጽ 193(2)፣
እንደሚገኘው ‹‹መልስ ሰጭው ወይም ጠበቃው ያልቀረቡ እንደሆነ ነገሩ በሌሉበት ይቀጥላል››32
በሚል የተቀረጸ ነው፡፡ በይግባኝ ወቅት ጉዳዩ በሌለበት ሊታይ የሚችለውም መልስ ሰጭ
ካልቀረበ ወይም በጠበቃ መወከል ሳይችል ሲቀር ብቻ ይሆናል፡፡ ዐቃቤ ህግ ይግባኝ
በሚልባቸው ጉዳዮች ላይ መልስ ሰጭ(የስር ተከሳሽ) መቅረብ ሳይጠበቅበት ጉዳዩን በጠበቃው
አማካኝነት እንዲከታተል ህጉ መፍቀዱ በባለሙያዎች ዘንድ የአቋም ልዩነቶች ፈጥሯል፡፡
አንዳንዶች ህጉ ግልጽ በሚሆንበት ግዜ ምንም አይነት ትርጓሜ አያስፈልገውም፡፡ በመሆኑም
መልሰ ሰጭ ባይቀርብም ጠበቃው እስከቀረበ ድረስ መስተናገድ አለበት እንጂ እንደ መጀመሪያ
ክርክር ተገዶ ሊቀርብ አይገባውም የሚል አቋም የሚያንጸባረቁ ሲሆን በሌላ በኩል በወንጀል
ጉዳዮችን ላይ ተከሳሹ መገኘት አለበት ምክንያቱም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጉዳዩን
ያስቀርባል ማለቱ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ የሚያርምበት አግባብ ስለሚኖር መልስ ሰጭው
እራሱ በአካል መገኘት አለበት እንጂ የጠበቃው መገኘት ብቻ በቂ አይደለም የሚል መከራከሪያ
ያቀርባሉ፡፡33 ይህንንም ክርክር በዚህ መዝገብ ስር ማየት እንችላለን፡፡
ይግባኝ ባይ በስር ፍርድ ቤት የወንጀል ህግ አንቀጽ 539(1)ሀ34 በመተላለፍ ከባድ የግድያ
ወንጀል ፈጽሟል በሚል ክስ ቀርቦበት የስር ፍርድ ቤት ክሱን ተከላክሏል በማለት ተከሳሽን
በነጻ ማሰናበቱ አግባብ አይደለም በማለት ዐቃቤ ህግ የይግባኝ አቀረበ፡፡ የመልስ ሰጭም ጠበቃ
(መልስ ሰጭው ሳይቀርብ) በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.193 መሰረት ያቀረብነው የፅሁፍ መልስ
ይያያዝልን በማለታቸው ዐቃቤ ህግ ጉዳዩ የግድያ ወንጀል በመሆኑ መልስ ሰጭ ተገዶ ሊቀርብ
ይገባል ጠበቃውም ብቻውን ቀርቦ መልስ ይያያዝልኝ ማለቱ ተገቢነት የለውም በማለት
ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ የሚከተለውን ብይን ሰጥቷል፡፡
‹‹የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/193 መልስ ሰጭው ወይም በጠበቃው አማካኝነት ቀርቦ መልስ እንዲያቀርብ
በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ህጉም ግልጽ በመሆኑ መተርጎም አያስፈልገውም››፡፡35 በማለት የአቃቤ
ህግን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ የመልስ ሰጭን ጠበቃ መልስ ከመዝገቡ ጋር በማያያዝ
በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡
4.3. ክርክር መሃል ስለሚቀርቡ/ስለሚቀሩ ተከሳሾች


32
ዝኒ ከማሁ
33
አቶ ወልደኪሮስ አድማሱ የደቡብ ወሎ እና አካባቢዋ የፍትህ ቢሮ ቋሚ ምድብ ችሎት የስራ ሂደት አስተባበሪ
በቀን 3/8/2010 ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ
34
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 20፣አንቀጽ 539(1)ሀ
35
ዐቃቤ ህግ እና አቶ ገብሬ መስፍን በጠቅላይ ፍርድ ቤት የጎንደር ቋሚ ምድብ ችሎት የወንጀል ይግባኝ ቁጥር
02- 01303 በቀን11/04/2010 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ
በተግባር የሚታዩ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ መታየት
ከጀመረ በኋላ ተከሳሽ በፖሊስ ተይዞ ወይም በራሱ አነሳሽነት ቢቀርብ ጉዳዩ እንዴት ሊወሰን
ይገባል የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ተከሳሽ ከመጀመሪያውኑ ሳይገኝ በመቅረቱ ወይም በክርክሩ
መሃል ባለ በአንዱ ሂደት ሲቀር የመዝገቡ ውጤት ምን ይሆናል የሚለው ነጥብ
በባለሙያዎች ዘንድ የተለያዩ አቋሞች ፈጥሯል፡፡36 ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው
አሳማኝ በሆነ ምክንያት መቅረቱን የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረቡ ምክንያት ክርክሩን ወደ ኋላ
ሊመለስበት የሚያስችል የስነስርአት አካሄድ በህጋችን ማእቀፍ ስር አለ ወይ ይህስ በተግባር
በሚገጥምበት ግዜ እንዴት ተደርጎ ክርክሩ ወደኃላ ሊመለስ ይገባዋል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ባለበት የክርክር ሂደት መሀል ላይ ተከሳሽ በመቅረቡ ምክንያት
የተሰጠ ውሳኔን ለማሳየነት እንመልከት፡፡
37
ተከሳሾች የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)ሀ እና 671(1)ሀእናለ በመተላለፍ ግምታቸው 30,000
የሚያወጡ ከብቶችን በመሳሪያ በማስፈራራት ከግብረአበሮቻቸው ጋር የወሰዱ በመሆናቸው
ከባድ ውንብድና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው አንደኛው ተከሳሽ በአድራሻው ሊገኝ
ባለመቻሉ የጋዜጣ ጥሪ ከተደረገለት በኋላ ፍርድ ቤቱ በሌለበት ጉዳዩ እየታየና ተከሳሽ
እንዲከላከል ብይን በተሰጠበት የክርክር ሂደት ላይ ፖሊስ ተከሳሽን አድኖ በመያዙ ምክንያት
ፍርድ ቤት ተከሳሹን በክርክሩ ውስጥ በማስገባት እና ክርክሩ ከደረሰበት እንዲቀጥል በማድረግ
በብይኑ መሰረት ተከሳሹ የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ እንዲያሰማ አድርጓል፡፡ ተከሳሽም ላይ
የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽም በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ38
ቅሬታውን በማቅረብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች በሌለሁበት የተሰሙ በመሆኑ የተሰጠው ውሳኔ
አግባብነት የሌለውም በመሆኑ እንዲሻርልኝ በማለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ተመልክቶ
የሚከተለውን ወስኗል፡፡
‹‹ በሌለበት ታይቶ ውሳኔ እንዲወሰን ብይን የተሰጠበት ተከሳሽ ጉዳዩ ፍጻሜ (ፍርድ)ከማግኘቱ
በፊት ቢገኝ በፖሊስ ተገዶ ወደ ፍርድ ሊገባ ይገባል ወይ የሚለውን የሚገዛ ግልጽ ድንጋጌ


36
አቶ ቸርነት ተገኘ የሰሜን ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት 15/05/2010ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ ፡፡
ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮችን በተመለከተ የአሰራር ክፍተቶች በዞኑ በመኖራቸው ከጠቅላይ ፍርድ ቤት
የሰበር ዳኞች ባለሙያዎችን በማስመጣት ፍርድ ቤቱ ስልጠና የሰጠ መሆኑና ይህም ስልጠና በአሰራር ላይ
የሚታዩ የትርጉም ልዩነቶችን በማንሳት ለባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
37
ዐቃቤ ህግ እና በላይ መንጌ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል መዝገብ ቁጥር 02-10881
20/10/2009 ዓ.ም የተሠጠ ውሳኔ እንሁም የግርጌ ማስታወሻ 21
38
በላይ መንጌ እና ዐቃቤ ህግ(ይግባኝ) በወንጀል ይግባኝ መዝገብ ቁጥር 02-04202 በቀን ህዳር 19/2009ዓ.ም
የተሰጠ ውሳኔ
የለም እንዲህ ከሆነ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የተከሳሽን መብት በማያጣብብ መልኩ ህጉ ፍፃሜ
የሚያገኝበትን (የተሻለ ውጤት) አተረጓጎም ሊከተል ይገባው ነበር፡፡ ይግባኝ ባዩ በችሎት ተገኝቶ
በሌለሁበት የተደረገው ክርክር ተሰርዞ ባለሁበት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ይሰሙ በማለት
ያቀረበው ክርክር አግባብነት ያላቸውን ስነ ስርአት ህግ ድንጋጌዎች ባማከለ ሁኔታ አይቶ
ማስተናገድ ሲገባው ክርክሩ ወደ ኋላ አይመለስም ነገርግን የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል
ተገልብጦ ለይግባኝ ባዩ ደርሶት እና መከላኪያ ማስረጃ ያሰማ በማለት ብይን መስጠቱ ክርክሩ
በዘፈቀደ በሆነ የፍርድ ሂደት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ ክርክሩ ከፊሉ ተከሳሽ
በሌለበት ከፊሉ ተከሳሽ ባለበት መሆኑን መዝገቡ የሚያሳይ በመሆኑ ይህ ደግሞ በወንጀል ስነ
ስርአት ህጉም ሆነ በወንጀል ሙግት ስርአት ውስጥ እውቅና ያልተሰጠው ኢ-ስነ ስርአታዊ
የሆነ የፍርድ ሂደት ሆኖ አግኝተነዋል›› በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር
የአሁን ይግባኝ ባይ ባለበት የአቃቤ ህግ ምስክሮች እንዲሰሙ እና ቀጣይ ሂደቱም ስነስርአታዊ
ህጉን ተከትሎ በይግባኝ ባይ ላይ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ እንዲሰጥ በነጥብ መልሷል፡፡
4.4.ጉዳያቸው በሌሉበት የታየ ተከሳሾች ያላቸው መፍትሄዎች ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች
Ø ጉዳያቸውን ሊታይ የሚገባው በየትኛው ፍርድ ቤት ነው
ተከሳሽ በሌለበት የተደረጉ ውሳኔዎች እንዲነሱ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.198
መሰረት ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ የቀረበውን ምክንያት አሳማኝ መሆኑን ይኸው
ፍርድ ቤት ከተቀበለው በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.202 መሰረት ጉዳዩን ስልጣን ላለው ሌላ ፍርድ ቤት
እንዲወስንበት እንደሚያስተላልፍ በስነስርአቱ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በአሰራር ደረጃ ጉዳዩን ያየው
ፍርድ ቤት ተከሳሽ አሳማኝ የሆነ ምክንያት አቅርቦ ሲገኝ እንደገና ጉዳዩን በዚያው ፍርድ ቤት
የማየት አሰራር አለ፡፡39
ጉዳዩን እንደገና ማየት
በሌለበት ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ የተሰጠው ማንኛውም ሰው ውሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት
አቤቱታ ማቅረብ (opposition) ይችላል፡፡ ይሁንና ነገሩ እንደገና ታይቶ ከዚህ በፊት የተሰጠበት
ውሳኔ እንዲነሳለት ለማድረግ በቂ ምክንያት (just cause) ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ በመሆኑም
ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ199 መሰረትም በሌለበት የተሰጠው ውሳኔ እንዲነሳ አመልካች ማሳየት ያለበት
ምክንያቶች (just cause) ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ፡-
Ø እንዲቀርብ መጥሪያ ያልደረሰው እንደ ሆነ ማሳየት


39
ወንዳቸው ሰራው የማዕከላዊ ጎንደር አስተዳደር የወንጀል የስራ ሂደት የወንጀል ዐቃቤ ህግ ጋር
በቀን12/05/2010 የተደረገ ቃለ መጠይቅ
አንድ ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል በግልፅ በሚያሳይ ሁኔታ እንዲሁም በተባለው ግዜና ቦታ
ባይገኝ የሚያስከትልበትን የወንጀል ተጠያቂነት በማሳወቅ ከሳሽ ግዴታውን መወጣቱን ለፍርድ
ቤቱ ማሳየት አለበት፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው እና ካጸደቀቻቸው ስምምነቶች አንዱ
የሆነው የሲቪልና የፖለቲካል የቃል ኪዳን ሰነድ አንቀፅ 14(3)መ40 ላይ ከተጠቀሱት መብቶች
ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ በጄኔራል ኮሜንት
ቁጥር 32 ላይ በሰጠው ትንታኔ41 ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዮች ከመታየታቸው በፊት ከሳሹ አካል
ተከሳሽ በፍርድ ቤት እንዲቀርብ ጥረት ማድረጉን ለፍርድ ቤቱ ማሳየት ሊወሰዱ ከሚገባቸው
የጥንቃቄ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በኮሜንቱ አስቀምጧል፡፡
በሃገራችን ብሎም በክልላችን ያለው የመጥሪያ አደራረስ መንገድ ኃላ ቀር ሊባል የሚችልና
የመጥሪያ አደራረስ ስርአት ለማስፈጸም የሚያስችል የራሱ የሆነ ተቋም የሌለው እና
በአብዛኛውም በፖሊስና በቀበሌ አስተዳደር ድጋፍ ላይ ያተመረኮዘ ነው፡፡ ምንም እንኳን
ሃገራችን ተቋሞችን ለማጎልበት የሚያስችል ሰፊ ነዋለ መዋይ ባይኖራትም የመጥሪያ አደራረስ
ስርአቱን በማሻሻል አሁን አሁን ሃገራችን ተጠቃሚ እየሆነች ያለችባቸውን የመገናኛ መንገዶች
ከመጠቀም አንጻር ሰፊ እጥረቶች ይታያሉ፡፡ ለአብነትም አመልካች42 በሌለበት የተሰጠው ውሳኔ
እንዲነሳለት አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ለዚህም አመልካች እንደ ምክንያት ያነሳው ከአድራሻው
ያልጠፋ እና መጥሪያ በአግባቡ ያልደረሰው መሆኑን በተጨማሪም የጋዜጣ ጥሪ ሳይደረግለት
የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ 20(4) በመጥቀስ በክሱ ወቅት
ሳይገኝ የቀረቡበትን ምስክሮች ሳይመረምር፣ የመከላኪያ ምስክርም ሳያሰማ የተሰጠው ውሳኔ
እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡43 ይህንኑ አቤቱታ መሰረት በማድረግም ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ መልስ
እንዲሰጥበት ያደረገ ሲሆን ዐቃቤ ህግም44 ተከሳሽ በአስመዘገበው አድራሻ የክፍሉ ፖሊስ
አፈላልጎ ሊያገኘው ያልቻለ በመሆኑ የጋዜጣ ጥሪ እንዲቀርብ በተደረገው መሰረትም ሊቀርብ
ባለማቻሉ የተሰጠው ውሳኔ የሚነቅፍ አይደለም በማለት ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ
ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች መጥሪያ በአግባቡ እንዳልደረሰው በበቂ
ሁኔታ ያላስተባበለ በመሆኑ ውሳኔውን አጽንቶታል፡፡

40
ከላይ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 9
41
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ በጄኔራል ኮሜንት ቁጥር 32
42
የወንጀል መዝገብ ቁጥር 02-03136 ፣በሌለበት የተሰጠ ውሳኔ እንዲነሳለት አመልካች ሄኖክ አለማየሁ በለጠ
ለአ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ችሎት በቀን 17/11/2009ዓ.ም. ማመልከቻ ያቀረበው
43
በአ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ችሎት የወንጀል መዝገብ ቁጥር 0203136 በቀን የተሰጠ ውሳኔ
44
በአብክመ ፍትህ ቢሮ የደሴ የወንጀል የስራ ሂደት በቁጥር ወ/የ/ሂ 241/2010 በቀን 20/02/2010ዓ.ም ለፍርድ
ቤቱ የጻፈው መልስ
በሌላ በኩል አቃቤ ህግ45 ተከሳሽ በስር ፍርድ ቤት የቀረበበትን ከባድ ውንብድና ወንጀል ፍርድ
ቤቱ ተከላክሏል በሚል በነጻ ማሰናበቱ በአግባቡ አይደለም በሚል ባቀረበው ይግባኝ ላይ መልስ
ሰጭን ፖሊስ በአድራሻው ፈልጎ ባለመቅረቡ እንዲሁም በአድራሻው አለመገኘቱንም ፖሊስ
በድብዳቤም ሆነ በአካል ቀርቦ እንዲያስረዳ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ቢሰጥም ቀርቦ ሊያስረዳ
ባለመቻሉ ምክንያት ተከሳሽ በተገኘ ግዜ አቃቤ ህግ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብቱን ጠብቆ
መዝገቡ እንዲዘጋ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም ውሳኔ መጥሪያ ለተከሳሽ በአግባቡ መድረሱን
ካልተረጋገጠ በስተቀር ጉዳዩ ማየት እንደማይቻልና ለተከሳሽ መጥሪያ የማደረስ ሃላፊነት
ያለበት አካል በአግባቡ ግዴታው እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ መጥሪያ በአግባቡ አልደረሰኝም
በሚል የሚቀርቡ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚደረገው ምዘና ከጉዳይ ጉዳይ የሚለይ እና ለአንዱ
ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያለው ጉዳይ በሌላ ፍርድ ቤት ተቀባይነት የሚያጣበት አግባብ አለ፡፡
በተለይም የጋዜጣ ጥሪን በተመለከተ ተከሳሽ አርሶ አደር በመሆኑ ማንበብም ሆነ መጽፍ
የማይችል፣ በሚኖርበት አካባቢ ጋዜጣ የማይደርስ እና ጋዜጣ የማንበብ ልምድ የለም በሚሉ
ምክንያቶች ጉዳዩች እንደገና እንዲታይ የሚደረጉበት አሰራሮች አሉ፡፡46
Ø ራሱ ወይም ጠበቃው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መቅረብ ያልቻሉ እንደሆነ
ከዐቅም በላይ የሆነ ችግር ተብለው የተጠቀሱት ምክንያቶች አሁንም ለፍርድ ቤቶች የተሰጠ
ፍቁደ ስልጣን ነው፡፡ በመሆኑም ከጉዳይ ጉዳይ የሚቀርቡላቸውን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር
ተብለው ሊወሰዱ የሚገቡ ምክንያቶች መዝነው ውሳኔ እንደሚሰጡባቸው የድንጋጌው መንፈስ
ያሳየናል፡፡47 በተለይም ለፍርድ ቤቱ በአመልካቹ ከሚቀርቡ ከአቅም በላይ ተብለው ሊጠቀሱ
የሚችሉ ምክንቶች ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ መቆየት፣ጸበል መክረም እንዲሁም ከሃዘን ጋር
የተያያዙ ጉዳዮች በአብዛኛው በምክንያትነት እንደሚቀርቡና የሚቀርቡትንም ምክንያቶች
በጥንቃቄ መመዘን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡48

5.ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ

5.1.የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.161 አተረጓጎም በፍርድ ቤቶች


45
አ.ብ.ክ.መ. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባህር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፣ዐቃቤ ህግ እና መከተ አድማሱ
የመዝገብ ቁጥር 02-05173 በቀን 28/05/2010 የተሰጠ ውሳኔ ባህር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት
46
አቶ በሪሁን አዱኛ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በደቡብ ወሎ ዞን የወንጀል የስራ ሂደት አስተባባሪና ዳኛ ጋር ሚያዝያ
4/2010ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ
47
የግርጌ ማስታወሻ ፣199
48
የግርጌ ማስታወሻ 46
በዚህ ድንጋጌ ዙሪያ የሚቀርቡ አከራካሪ ትርጉሞችን የተመለከትን ሲሆን የህጎች የቃላት
አጠቃቀም አሻሚ በሚሆን ግዜ ድንጋጌውን ትርጉም በሚሰጥ መልኩ መተርጎም አንዱ
መፍትሄ ነው፡፡ ህግን ለመተርጎም ከሚረዱን ዘዴዎች አንዱ የህግ አውጭው አሳብ ምንድን
ነው የሚለውን መረዳት ቢሆንም ይህ ስነ-ስርአት ሲቀረፅ የነበሩ ውይይቶች ወይም ሃሳቦች
ምንድናቸው የሚለውን የሚመልሱልን ተደራጅተው የተቀመጡ ጽሁፎች አናገኝም፡፡49ሆኖም
የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ.160 ይዘት ከልዩ ስነ ስርአቱ ጠቅላላ አላማ አንጸር በማየት ትርጉም ሊሰጠው
ይገባል፡፡ እንዲህም ሲሆን በወንጀል ህጉ የድንጋጌዎች አቀራረጽ ከ-እስከ በሚል የተቀመጡ
ከባድ ተብለው የሚጠቀሱትም ወንጀሎች ለምሳሌ እንደ ውንብድና፣ ተራ ሰው መግደል
መነሻቸው ዝቅ ብለው ተደንግገው የሚገኙ በመሆናቸው የቅጣት መነሻ ወለሉን በመተው
የቅጣት መድረሻውን ጣሪያውን በመመልከት በልዩ ስነስርአት ህጉ የሚታዩ ጉዳዮች እንዲሰፉ
ያደርጋል፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ አብሮ መነሳት ያለበት ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ
የሚፈለግበት አመክንዮ ሲሆን ይህም ውሳኔዎችን ከመቋጨት ጀምሮ የተፋጠነ የፍትህ አሰጣጥ
ስርአት በማስፈን ተከሻሹ ጭራሹኑ ሳይቀጣ እንዳይቀር በማድረግ የማህበረሰቡን ደህንነት
የማስጠበቅ አላማ እንዲሳካ የሚያደርግ ከመሆኑ አንፃር ድንጋጌውን በጠባቡ መተርጎም እና
ለጥቂት አናቅጽት ብቻ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ የዚህን ልዩ ስነስርአቱን ዓላማ የሚያጠብ
ይሆናል፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የሚካሄድ የወንጀል ስነ-ስርአት ያላት ሃገር ተብላ የምትጠቀሰው
ፈረንሳይ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩን ለማየት መለኪያ መስፈርት አድርጋ የምትገለገለው
የተፈፀመው ወንጀል ከባድ ወንጀል (FELONY) መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤቱ
ማጅስትሬት (magistrate) አማካኝነት ከባድ ወንጀል ይዘት አላቸው ተብለው በወንጀል ህጉ
የተደነገጉትን ብቻ ሳይሆን የወንጀሉን አፈጻፀም በመለካት አሲዝ (Assize) ለተባለው የፈረንሳይ
ከፍተኛው የመጀመሪያ ፍርድ ቤት( highest court of first instance) አጣርቶ በመላክ
ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ ይደረጋል፡፡50 በሌላ በኩል በእንግሊዝ ተከሳሽ በሌለበት
ክርክሮች የማድረግ ስርአት በኬዝ ሎውም ሆነ በህግ ዳብሮ ባናገኘውም መብታቸውን
በፍቃደኝነት ለሚተው( waiving of rights consensually) ሰዎች በሌሉበት ጉዳያቸውን


49
Ethiopian Criminal Procedure Teaching Material ,History of Ethiopian Criminal
Procedure,Aderajew Teklu and Kedir Mohammed, Justice and Legal System Research Institute
https://chilot.me/wp-content/uploads/2011/06/criminal-procedure.pdf Accessed at 20/7/2018
4:30a.m.
50
ከላይ በግረጌ ማስታወሻ ቁጥር 14፣እንዱሁም Ade'har Esmein, A history of continental criminal
procedureP.62-63(1913).
የሚታይበት ስርአት የተዘረጋ ሲሆን ይህም ስነስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚፈቀደው ቀላል
ለሆኑ ወንጀሎች ብቻ ነው፡፡51 ከላይ የጠቀስኳቸው የሃገራቱ ልምድ የሚያሳየን ተከሳሽ
በሌለበት ጉዳዮችን ለማየት መስፈርት ተደርጎ የሚወሰደው ከሚያስቀጣው የቅጣት መጠን
ይልቅ የወንጀሉ ከባድነት ወይም ቀላልነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም
በሃገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነስርአት ላይ የተጠቀሰው የቅጣት መጠን የወንጀሉን
ከባድነት ወይም ቀላልነት ከመለካት አኳያ ተደርጎ ቢወሰድ በተሻለ መልኩ ድንጋጌዎችን በስራ
ላይ የሚያውል አሰራር ይፈጥራል፡፡ አሁን በረቂቅ ላይ ያለው የወንጀል ስነስርአትም ይህን
መመዘኛ የተጠቀመ መሆኑን ማየት እንችላለን፡፡52
ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ሲያገለግል የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከተቀየረ እና
በአዲስ የወንጀል ህግ ከተተካ በኋላ እሱን ተከትሎ መቀየር የነበረበት የወንጀለኛ መቅጫ
ስነስርአት ህግ ሳይሻሻል በመቅረቱ ምክንያት በስነስርአቱ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎችን ወደ
ድሮው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ድንጋጌዎች ጋር ወስዶ በማያያዝ ሲተረጎሙ ይታያል፡፡ ይህም
በመሆኑ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በአዲሱ የወንጀል ህግ የተሻሻሉና የተለወጡ ሁኔታዎች
በተመለከተ ከወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ድንጋጌዎች ጋር ያላቸውን ተፈጻሚነትና ፍርድ
ቤቶች ሊከተሉት የሚገባ የህግ አተረገጓም ምን መሆን አለበት የሚለውን እንደሚከተለው
አስቀምጧል፡፡53
‹‹ …ሆኖም ህግ አውጭው በአዲሱ የወንጀል ህግ ያወጣቸውና ያሻሻላቸውን ጉዳዮች ባሉበት
ሁኔታ በቀጥታ ከነበረው የስነስርአት ህግ ድንጋጌዎች ጋር ተጣጥመው ተፈፃሚ እንዲሆኑና
እንዲተረጎሙ ፍላጎትና ሃሳብ አለው ተብሎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በአዲሱ የወንጀል
ህግ ቅጣታቸው ከፍ ብሎ የተደነገጉ ወንጀሎች የዋስትና ጥያቄና ተከሳሽ በሌለበት እንዲታይ
የሚቀርቡ ስነስርአት ጥያቄዎች 1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ


51
Criminal Justice Act 1988, s.134.፣እንዲሁም Kenneth A. Goldman ,Criminal Waiver: The
Requirements of Personal Participation, Competence and Legitimate State Interest, California Law
Review vol.54 p.1275
52
የኢፌድሪ የወንጀል ስነስርአት ህግ ረቂቅ አዋጅ
በዚህም ረቂቅ የወንጀል ስነስርአት ህግ ላይ ለአምስት ተከታታይ ቀጠሮ ተከሳሽ መቅረብ ያልቻለ እንደሆነ ፍርድ
ቤቱ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ እንደሚወስንና በሌለበት ሊታዩ የሚገባቸውም ወንጀሎች ከቀላል ወንጀሎች ውጭ
መሆን አለባቸው በሚል ያስቀምጣል፡፡
53
የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ እና አቶ ተመስገን አዲስ የሰበር መዝገብ ቁጥር 35695 ፣ቅፅ 9፣ህዳር 11/2001
ዓ.ም ውሳኔ ያገኘ፡፡
የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ትርጓሜ መስጠት ሳያስፈልግ የስነስርአት ህጉን
ከአዲሱ የወንጀል ድንጋጌዎች ጋር በቀጥታ አጣምሮ ማየት ይኖርባቸዋል፡፡››
የዚህም የሰበር ውሳኔ ይዘት የአዲሱን የወንጀል ህግ እና የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አጣጥሞ
መተርጎም ማስቻል እና ተከሳሽ በሌለበት የሚታዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ወደ ድሮ የወንጀለኛ
መቅጫ ህግ ጋር ሄዶ ማጣቀስ ሳያስፈልግ በአዲሱ የወንጀል ህግ የተቀመጡ የቅጣት
ድንጋጌዎችን ከስነስርአት ህጉ ድንጋጌዎችን ጋር ተጣጥመው በመተርጎም እንዲሰሩ ነው፡፡
በአጠቃላይ ‹‹12 አመት በታች በማያንስ የሚያሳስር ወንጀል የሰራ›› የሚለው የድንጋጌው
የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ያለበት ቢሆንም ከድንጋጌው ጠቅላላ መንፈስ የምንረዳው የተፈጸመው
ወንጀል ከባድነት ለማሳየት የቅጣቱ መጠን መቀመጡን ነው፡፡ ሌላው በወንጀል ህጉም ሆነ
በሌሎች አዋጆች የተቀመጡት ድንጋጌዎች አቀራረጽ ከጥቂት ወንጀሎች በስተቀር መነሻ
ቅጣታቸው ዝቅ ያለ በመሆኑም 12 አመት ቅጣትን መነሻ አድርጎ መውሰድ የልዩ ስነስርአት
ህጉን አላማ እንዲሳካ አያደርገውም፡፡
5.2. በይግባኝ ስርአት ስር ተከሳሽ በሌለበት የሚካሄዱ ክርክሮች
በይግባኝ ስነ ስርአት ጉዳዩ በሌለበት መታየት የሚችለው መልስ ሰጭ ራሱ ወይም ጠበቃው
መቅረብ ካልቻሉ ነው፡፡ ይህም ከመደበኛ ክርክሮች በተለየ በጠበቃ መወከል ከቻለ በግዴታ
መቅረብን ከማስቀረቱም ባሻገር በሌለበት የሚደረግ ክርክር (default) ተግባራዊ አይደረግም፡፡
በይግባኝ ግዜ ጉዳዩ ልክ እንደ መጀመሪያ ክርክር በሌለበት ታይቶ ሊወሰን የሚችለው መልስ
ሰጭው ወይም ጠበቃው መቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ ብቻ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትንው በዚህ
ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮች ውስጥ የወንጀል ጉዳይ ግላዊ በመሆኑ ራሱ ተከሳሹ በአካል መገኘት
አለበት የሚል እና የክርክሩን የመጨረሻ ውጤት አይቶ ሊጠፋ የሚችልበት አግባብ ስለሚኖር
በይግባኝ ወቅት መልስ ሰጭ መቅረብ አለበት፡፡ ምንም እንኳን የተጠቀሰው ምክንያት በተግባር
የሚታይ ችግር ቢሆንም ተገዶ እንዲቀርብ ለማድረግ ግን አያበቃም፡፡ ምክንያቱም በስነስርአት
ህጉ በአማረኛውም ሆነ በእንግሊዘኛው ትርጉም በማያሻማ መልኩ በአማራጭ በጠበቃው በኩል
የይግባኝ ክርክሩን መከታተል መልስ ሰጭ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾችን
በአድራሻ በማፈላለግ የተላለፈባቸውን ውሳኔ ተግባራዊነት የሚያስፈጽም የፖሊስ አካል በበጀት
እና በሰው ሃይል በማደራጀት ከህግ የመሸሸግ ችግር መቅረፍ የሚቻል ሲሆን
የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ/193(2) ግን መተርጎም የማያስፈልገው ግልጽ ድንጋጌ በመሆኑ እንዲሁ
ተግባራዊ ማድረጉ የተሻለ አሰራር ይፈጥራል፡፡
5.3.በክርክር መሃል ተከሳሾች ስለመቅረብና ስለመቅረት

ተከሳሾች በክርክር መሃል ቢቀርቡ ወይም በክርክር መሃል ቢቀሩ ጉዳያቸው እንዴት
መስተናገድ ይችላል የሚለውን የሚገዛ ድንጋጌ በስነ ስርአት ህጋችን ስር የለም፡፡ በተለይ
ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ከፍርድ በፊት ቢቀርቡና ላለመቅረባቸውም በቂ ምክንያት ያላቸው
ከሆነ ተጀምሮ በነበረው ክርክር ላይ ውሳኔ ማሳረፍ ሳያስፈልግ ተከሳሽ ባለበት እንደገና ክርክር
ማድረግ የተሸለ አሰራር ይፈጥራል፡፡ ይህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን ሳያስገባ ውሳኔ በጉዳዩ ላይ
ቢሰጥበትም ተከሳሽ በቂ ምክንያት እስካቀረበ ድረስ ጉዳዩ እንደገና የሚታይበት የህግ ማዕቀፍ
በመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም ክርክሩ አንዴ ከተጀመረ በሚል ማስቀጠሉ የተፋጠነ ፍትህ
ከመስጠት እንዲሁም ውሳኔዎችን ሳይንዛዙ መቋጨት ያስችላል፡፡

5.3.በክርክር መሃል ተከሳሾች ስለመቅረብና ስለመቅረት

በመሰረቱ ተከሳሽ በክርክር መሃል ቢቀርብ ወይም በክርክር መሃል ቢቀሩ ጉዳያቸው እንዴት
መስተናገድ ይችላል የሚለውን የሚገዛ የስነስርአት ድንጋጌ የለም፡፡ በተለይ ጉዳያቸው በሌሉበት
እየታየ ከፍርድ በፊትም ቢቀርቡና ላለመቅረባቸው በቂ ምክንያት ያላቸው ከሆነ ተጀምሮ
በነበረው ክርክር ላይ ውሳኔ ማሳረፍ ሳያስፈልግ ተከሳሽ ባለበት እንደገና ክርክር ማድረግ
ይቻላል፡፡ ይህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን ሳያስገባ ውሳኔ በጉዳዩ ላይ ቢሰጥበትም ተከሳሽ በቂ
ምክንያት እስካቀረበ ድረስ ጉዳዩ እንደገና የሚታይበት የህግ ማዕቀፍ በመኖሩ ነው፡፡
በመሆኑም ክርክሩ አንዴ ከተጀመረ በሚል ማስቀጠሉ የስነ ስርአት ህጉን አላማ እንዲሳካ
አያደርገውም፡፡

በሌላ በኩል በቂ ምክንያት ሳይኖራቸው ጉዳያቸው በሌሉበት በመታየት ላይ እያለ ተከሳሾች


ቢቀርቡ ሊደረግ የሚገባው ምንድን ነው የሚለው በተግባር የሚገጥም ችግር ነው፡፡ ተከሳሹ
በፖሊስ ተይዞም ይሁን በራሱ ተነሳሽነት በክርክር መሃል ከቀረበ ከደረሰበት የክርክር ሂደት
ጀምሮ ተሳታፊ ማድረግ ሊወሰድ የሚገባ አማራጭ ነው፡፡ ይህም የተከሳሽን የመከላከል እና
በክርክር ወቅት የመገኘት መብቱን አስፍቶ በማየት በህጉ ያልተሸፈነውን ይህን የስነስርአት
ክፍተት መሙላት ይቻላል፡፡ በክስ ሂደት ላይ የመገኘት መብት እና የመከላከል መብት ህገ
መንግስታዊ መብት ሲሆኑ እነዚህን መብቶች ያለበቂ ምክንያት ያልተጠቀመበት በመሆኑ
እስከመጨረሻው የክርክሩ አካል ልትሆን አይገባም ሊባል ግን አይችልም፡፡ አንድ ተከሳሽ
በሌለበት የተሰጠበት ውሳኔ እንደገና ሊታይለት የሚቻልባቸው ምክንያቶች በስነስርአት ህጉ
የተቀመጡ ሲሆን ይህን አሟልቶ ካልተገኘ በቅጣቱ ላይ ካልሆነ በቀር ምንም አይነት አማራጭ
አይኖረውም፡፡ በመሆኑም በደረሰበት የክርክር ሂደት ገብቶ መከራከሩ እራሱን እንዲከላከል
የሚያግዘው ሲሆን ሌላው የቅጣት ማቅለያዎችንም እንዲያቀርብ ይረዳዋል፡፡ እነዚህ መብቶች
ደግሞ ለተከሳሹ የተሰጡ መብቶች በመሆናቸው በስነስረአታዊ ህጎች አመራር ሊሸረሸሩ
አይገባም፡፡ ምክንያቱም የስነስርአት ህጎች ጠቀሜታም ክርክሮችን ከማሳለጥ ባሻገር መብቶችም
ተፈጻሚ እንዲሆን ማስቻል በመሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ተከሳሽ በመብቱ ያልተጠቀመበትን የክርክር ሂደት እንዲያልፈው በማድረግ ከደረሰበት
እንዲቀጥል ማስቻል ለተከሳሽ የተሻለ መብት የሚሰጥ በመሆኑ ተግባራዊ ቢደረግ የሚታየውን
ክፍተት የሚሞላ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩ በሌለበት በመታየት ላይ እያለ የተያዘ ተከሳሽ
በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቶ ባለበት እንዲታይ ሊወስን እንደሚችል ረቂቅ
የስነስርአት ህጉ ሲያስቀምጥ ይህም ለፍርድ ቤቱ ፍቁደ ስልጣን ላይ የተመረኮዘ መሆንኑን
የድንጋጌው መንፈስ ያሳየናል፡፡54 ይህም አሁን በተግባር እየታየ ያለውን ተግባራዊ ችግር ረቂቅ
አዋጁ ወደስራ ሲገባ እንደሚቀርፈው ይገመታል፡፡
በሌላ በኩል ጉዳያቸው ባሉበት ሲታይ ቆይቶ የክርክሩን አዝማሚያ በማየት የሚቀሩ ተከሳሾችን
በተመለከተ መብታቸውን እንደተው ተቆጥሮ ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት
የሚችሉ መሆኑን የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 12781355 ውሳኔ
ሰጥቶበታል፡፡
5.4.በሌሉበት የተሰጡ ውሳኔዎች ከተነሱ በሃላ ማየት ያለበት አካል
የዚህ ድንጋጌ አላማ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩን ያያው ፍርድ ቤት ነገሩን እንደገና ተከሳሽ ባለበት
ቢያየው ከአድሎ ነጻ አይሆንም በሚል እሳቤ የተቀረፀ መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት መረዳት
ይቻላል፡፡ አሁን በተግባር ያለው አሰራርም በዚያው ፍርድ ቤት ጉዳዩ እየታየ ያለበት አግባብ
በመኖሩ በህግ አውጭው ሃሳብ እና በተግባራዊ አፈጻጸም ላይ ክፍተት ያለ በመሆኑን ይህን
ሊያርም የሚችል አሰራር በፍርድ ቤቶች አስተዳደር ተግባራዊ ሊደረግ ይገባዋል፡፡
5.5.የመጥሪያ አደራረስ ስርአትን ማሻሻል
የመጥሪያ አደራረስ ስርአት በአግባቡ ለተከሳሽ ለማድረስ በሚያስችል መልኩ ያልተቀረፀና
የጋዜጣ ጥሪንም አስመልክቶ ከሚቀርቡ አቤቱታዎች መሃከልም በስርጭትም ይሁን ጋዜጣ
በማንበብ ልምድ እጥረት ሊያስተላልፈው የሚገባው መልክት ለተፈላጊው ሰው ሳይደርስ
ይቀራል፡፡ በተለይም ፖሊስን፣ቀበሌ አስተዳደርን በመጠቀም መጥሪያ የማስተላለፍ ስርአትም


54
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ 44፣ አንቀጽ 291.
55
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 22
ከሰው ሃይል ማነስ፣ከበጀት ችግር አንጻር ተደራሽነቱ አናሳ በመሆኑ በአግባቡ የመጥሪያ
አደራረስ ስርአት እየተከናወነ ነው ለማለት አይስደፍርም፡፡ ይህንንም ችግር አሁን ካለበት ኋላ
ቀር አሰራር ለመቀየር በማሰብ በረቂቅ አዋጁ ላይ የመጥሪያ አደራረስ ስርአት ተከሳሽ
ከሚኖርበት ቀበሌ አማካኝነት መጥሪያ እንዲደርሰው ማድረግ፣ በአጭር የጽሁፍ መልእክት፣
በስልክ፣ በፋክስ ፣በድህረ ገጽ ወይም በፖሰታ በእነዚህ መንገዶች ማድረስ ካልተቻለ መገናኛ
ብዙሃን በመጠቀም ለተከሳሹ መጥሪያ እንዲደርሰው ማስቻል ሲሆን በሌላ በኩል ላቅመ አዳም
ለደረሰ የቤተሰቡ አባል መጥሪያ የማድረስ ስርአትን በውስጡ አካቶ ይዟል፡፡56 በመሆኑም ይህ
አሰራር አሁን ካለው የመጥሪያ አደራረስ ሰፋ ያለ አማራጮችን ይዞ በመቅረቡ በዚህ ዙሪያ
እየተፈጠሩ የሚገኙ ችግሮችን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ስለ
መጥሪያ አደራረስ ስርአት መርህ በአንቀፅ 276(3) ሲያስቀምጥ ‹‹ፍርድ ቤቱ በዚህ ሕግ
መሰረት መጥሪያ ባልደረሰውና ባልቀረበው ተከሳሽ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ወይም ሂደት
በሌለበት እንዳልተሰጠ ይቆጠራል››57በማለት የሚደነግግ ሲሆን ይህም መጥሪያ እንዲሰጥ
ሃላፊነት የተጣለበት አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ (due diligence) እንዲወጣ ከፍተኛ ግዴታ
የሚጥል ነው፡፡ በአጠቃላይ መጥሪያ አደራረስ ስርአት ላይ የሚታዩትን ከፍተኛ የተግባር
ክፍተቶች የመጥሪያ አደራረስ ዘዴዎችንም ዘመኑ ወደደረሰባቸው ግኝቶች መቀየር መፍታት
ይገባል፡፡
6.ማጠቃለያ
ተከሳሽ በሌለበት የሚካሄዱ ክርክሮች በአንድ በኩል የተከሳሹን መብት በሌላ በኩል
የህብረተሰቡን መብት ባማከለ ልዩ ሁኔታ የሚፈቀድ የክርክር ስርአት ነው፡፡ በዚህ ልዩ
የስነስርአት ህግ ስር የተቀመጠው ድንጋጌ ይዘት ግልጽነት ችግር ያለበት ሲሆን የተዘበራረቁ
አሰራሮችንም ፈጥሯል፡፡ እነዚህን የትርጉምና ብሎም የአሰራር ልዩነቶች ለማጥበብ የሚያስችል
የስነስርአት ህግ ማሻሻልም ሆነ ገዢ የሆነ ወጥ ትርጉሞች እስካሁን አልተሰጠም፡፡ በክልሉም
በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ስር ተከሳሽ በሌለበት የሚደረጉ ክርክሮች ላይ የሚንጸባረቁ የስነስርአት
ድንጋጌዎች አተረጓጎም እና አተገባበር መለያየት ተገማች እና ወጥነት ያላቸውን ውሳኔዎች
ለመስጠት ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡


56
የግርጌ ማስታወሻ 44
57
ዝኒ ከማሁ

You might also like