You are on page 1of 31

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች ፍትሃብሔራዊ መፍትሔዎች

በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ

ይበልጣል ይመር

አፅሮተ-ይዘት

በአሁኑ ወቅት ፆታዊ ጥቃት የሚለዉ ሐረግ ለጆሮ አዲስ አይደለም፡፡ ይሁንና ፆታዊ ጥቃት
ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም የሚያስቀምጥ የህግ ድንጋጌ በኢትዮጵያ የለም፡፡ ፆታዊ
ጥቃት፤ ፆታዊ ትንኮሳና አስገድዶ መድፈር የሚሉት ሃረጎች በተግባር ሲደበላለቁ ይስተዋላል፡፡
እነዚህ ሃረጎች በተወሰነ መልኩ የሚገናኙ ግን የሚለያዩም ናቸዉ፡፡ የፆታዊ ጥቃት ትርጉም
ከፅንሰ ሃሳቡ ጋር ሲጣመር ፆታን መሰረት ያደረጉ በሴቶች ወይም በወንዶች ላይ የሚፈፀሙ
ጥቃቶችን ሁሉ ያካትታል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ፆታዊ ጥቃትን የሚተረጉም ድንጋጌ
ባይኖረዉም በተበታተነ ሁኔታ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን አካቷል፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙት ፆታዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ደረጃ የስነ ልቦና ወይም የአእምሮ ጉዳት
በማድረስ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ቅፅፈት ጀምሮ እስክ ህይወት ፍፃሜ ድረስ የሚዘልቅ ጠባሳ
ይጥላሉ፡፡ ጉዳቱ ከድብርት እስከ ራስን መጥላትና ራስን ማጥፋት እንደሚደርስ ጥናቶች
ያሳያሉ፡፡ በጤና ላይ ስነ ህይወታዊና አካላዊ መቃወስ ያስከትላሉ፡፡ እነዚህ የስነ ልቦናና የጤና
ጉዳቶች ያለን ንብረት የማጥፋት፤ ስራን መልቀቅ፤ የስራ ችሎታና ፍላጎትን ወዘተ በማሳጣት
የገንዘብ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የገንዘብ፤ የጤናና የህሊና ጉዳት የደረሰበት ሰዉ ለጉዳቱ ከተቻለ
በተመዛዘነ መልኩ ካልተቻለ በርትዕ ካሳ ማገኘት የሰዎች ተፈጥሮዊ መብት ሲሆን
የመንግስታት ደግሞ ጉዳት ለደረሰበት ሰዉ ፍትህና ካሳ ማስከፈል ወይም መክፈል ግደታ
ነዉ፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ጉዳቶች በተሟላ መልኩ የሚያስከፍል የህግ ድንጋጌ የለም፡፡ ይህ
ጥናት የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ያሏቸዉን ፍትሃ ብሔራዊ የህግ ማዕቀፎች ብቻ
የሚዳስስ በመሆኑ የጥናቱ ዘዴ ፅንሰ ሃሳባዊ (Doctrinal) ነዉ፡፡

LLB,LLM በአብክመ የፍ/ባ/ማ/ህ/ም/ኢ/ተመራማሪ email yibeeyimer@yahoo.com


1

1. መግቢያ

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች (Violence against Women) እስከ 1980ዎቹ ድረስ በዓለም
አቀፍ ደረጃ ትኩረት ያልተሰጠዉ ጉዳይ ወይም ችግር ነበር፡፡1 ይሁንና በ1980ዎቹ መጀመሪያ
ጀምሮ በየአገራቱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደራጁ የሴቶች ማህበራት በሴቶች ላይ
የሚፈጸሙ ፆታዊ፤ አካላዊ፤ ስነ ልቦናዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ
ትኩረት እንዲሰጣቸዉ ጥረት አድርገዋል2፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምንድን እንደሆነ
እስከ አሁን ድረስ ሁሉን የሚያግባባና ወጥ የሆነ ትርጉም የለዉም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች
እንዲሁም አካባቢዎች የተለያዩ ቃላቶች ይሰጡታል፡፡ ለምሳሌ Family Violence, Gender Based
Violence, Domestic Violence, Spose Abuse, Sexualized Violence, Intimate/ non-intimate partner
Violence…በሚል ይገለፃል፡፡ በዚህ ፅሁፍ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ሁሉንም ዓይነት ጥቃቶች
ሳይሆን ከሴትነት ጋር የተያያዙትን ጥቃቶች ማለትም Sexual Violence3 ብቻ እንመለከታለን፡፡

1.1. ፆታዊ ጥቃት ምንድን ነው?

ፆታዊ ጥቃት በ መዝገበ ቃላቶች ውስጥ ትክክለኛ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ማወቅ አዳጋች
ነው4፡፡ የህግ ትርጉሙን በተመለከተ በኢትዩጵያ ህግጋት ውስጥ ፆታዊ ጥቃት ማለት ምን

1
Ellsberg Mary and Heise Lori, Researching Violence against Women; A Practical Guide for Researcher and
Activists, USA, World Health Organization, 2005, page, 5 available at
https://patth.azureedge.net/media/documents/GBV_rvaw_front.pdf
2
ዝኒ ከማሁ ገፅ 5
3
ለምሳሌ አንድ ወንድ አንዲት ሴትን ቢደበድባት የአካል ጉዳት ወንጀል ነዉ፡፡ ይህም ተራ ወይም ደረቅ ወንጀል ሲሆን አንድ
ወንድ አንዲትን ሴት ቢደፍራት ይህ አድራጎቱ በሴትነቷ ምክንያት የተፈፀመባት ድርጊት በመሆኑ በሴትነት ላይ የተፈጸመ
ወንጀል ወይም ጥቃት (Sexual Violence) በሚል ለመግለፅ ተሞክሯል፡፡
4
ለምሣሌ ዘርጋው ከፍተኛ የአማረኛ መዝገበ ቃላት፡- ጥቃት ማለት 1.ግፍ፣ ጭቆና፣ በደል፣ ወረታ፣ የሃይል እርምጃ ሢለው፡፡
Sexual Violence ምንድን ነው ስንል ደግሞ የተለያዩ መዝገበ ቃላቶች እንደሚከተለው ይተረጉሙታል፡፡ ለምሣሌ፡- Black’s

law Dictionary Sexual Violence The use of physical force, usually accompanied by fury Vehemence or
4
outrage, especially physical force, unlawfully exercised with the intent to harm.

ይህም ወደ አማረኛ ሢመለስ ብስጭት ና በደል የተቀላቀለበት አካላዊ ጐልበትን በመጠቀም ሌሎችን ለመጉዳት በማሠብ

በጉልበት ከህግ ውጭ የፈፀመ ጥቃት ነው ማለት ይቻላል፡፡ Oxford Dickonary በበኩሉ Violence Behavior involving

physical force intended to hurt damage or kill some one or something. በማለት ተርጉሞታል፡፡


2

ማለት እንደሆነ በግልፅ ትርጉም አልተቀመጠለትም፡፡ የኢ.ፊ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግን ብንመለከት
በመፅሃፍ አምስት ስር በሌሎች ሠዎችና በቤተዘመድ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከአንቀፅ
538 - 661 ደንጓል፡፡ በውስጡ አራት ርዕሶች፣ በእያንዳንዱ ርዕሰ ስር ምዕራፎች፣ በየምዕራፎቹ
ስር ክፍሎች ተዋቅረዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃት እየተባሉ በልምድ የሚታወቁ
ወንጀሎች በየርዕሶች፣ ምዕራፎችና ክፍሎች ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ ለማሣያ ያህል የቤት ውስጥ
ጥቃት /አንቀፅ 564, የሴትን ልጅ ብልት መስፉት አንቀፅ 566 በርዕስ 1 በምዕራፍ 3 ስር
ሢገኙ አስገድዶ መደፈር (አንቀፅ 620) በርዕሰ 4 ምዕራፍ 1 ክፍል 1 ይገኛል፡፡5 በመሆኑም
ፆታዊ ጥቃት ማለት ምን እንደሆነ ትርጉም ካለማስቀመጡም ባሻገር በተበታተነ ሁኔታ
መደንገጉ ድርጊቱን ለመረዳት አደጋች ያደርገዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፆታዊ ጥቃት ትርጉምን ስንመለከት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)
Sexual Violence is ‘Any sexual act, attempt to obtain a sexual act, unwanted sexual comments or
advances, or acts to traffic or otherwise directed against a person’s sexuality using coercion, by
any person regardless of their relationship to the victim, in any setting, including but not limited
to home and work’6 በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ይህም በግርድፉ ወደ አማርኛ ሢመለስ
“ፆታዊ ጥቃት ማለት ማንኛውም ፆታዊ ድርጊት፡- ፆታዊ ድርጊት ለማግኘት መሞከር፣
ያልተፈለገ ፆታዊ አስተያየት ወይም ሙገሣ ወይም ለማዘዋወር የሚደረግ ድርጊት፡- ወይም
የሰዎችን ፆታዊ ጥቅም በሃይል ለማግኘት የሚደረጉ አድራጐቶች ሆነው፤ ከተጐጅው ጋር
ያለው ግንኙነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ በማናቸውም ሁኔታና በስራና በመኖሪያ ቤት ሣይገደብ
የሚፈፀም ድርጊት ነው፡፡” የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

በሌላ በኩል የጥናትና ምርምር ድርጅቶች7 Sexual violence is defined as: being physically
forced to have sexual intercourse when you did not want to, having sexual intercourse because
you were afraid of what your partner might do, and/or being forced to do something sexual that
you found humiliating or degrading በማለት የስራ ትርጉም ሰጥተዉታል፡፡ ሌላዉ በሴቶች ላይ
የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃት ምን እንደሆነ ትርጉም የሠጠው ህግ በ1993 (እ.ኤ.አ) በተባበሩት
መንግስታት ዉሳኔ የፀደቀዉ (Declaration on the Elimination of Violence against Women)


5
የአ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አዋጅ ቁጥር 414/1996፤
6
The World Health Organization (WHO), report, Understanding and addressing violence against women, 2013,
page 2
7
Global and regional estimates of violence against women, page 13

3

/DEVAW/ በሚባል የሚጠራው መግለጫ ነው፡፡ በዚህ ህግ አንቀፅ 1 ላይ “Violence against
women” means any act of gender-based violence that results in, or is likely to result in, physical,
sexual or psychological harm or suffering to women, including threats of such acts, coercion or
arbitrary deprivation of liberty, whether occurring in public or in private life.8
በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ማለት ፆታን መሰረት ያደረገ ማንኛውም ድርጊት ሆኖ አካላዊ፣
ፆታዊ ወይም ስነ-ልቦናዊ ጉዳትን ወይም ስቃይን በሴቶች ላይ ያስከተለ ወይም ሊያስከትል
የሚችሉ ድርጊቶች፣ ማስገደድ ወይም የጋራ ና የግል ህይወት ነፃነትን ያለህግ መቀማት ነው፡፡
በሚል ሊተረጐም ይችላል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ህግ በአንቀፅ ሁለት ላይ Violence against
women shall be understood to encompass, but not limited to, the following (a) Physical, sexual
and psychological violence occurring in the family, including battering, sexual abuse of female
children in the household, dowry- related violence. Marital rape, Female genital mutilation and
other traditional practices harmful to women, non-spousal violence and violence related to
exploitation.

(b) Physical, sexual or psychological violence with in the general community, including rape,
sexual abuse, sexual harassment and intimidation at work in educational institutions and
elsewhere, trafficking in women and forced prostitution.9 በማለት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ
ጥቃቶችን ስንረዳ ማካተት ያለባቸውን ብቸኛ ያልሆኑ ድርጊቶችን ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም
በቤተሠብ ውስጥ የሚታዩ አካላዊ፣ ፆታዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት ስንል መጐንተልን ጨምሮ
እንደ በቤት ውስጥ ያሉ ህፅናት ሴቶች ላይ የሚደረጉ ፆታዊ በደሎች፣ በከጥሎሽ ጋር የተያያዙ
ጥቃቶች፣ የጋብቻ ላይ አስገድዶ መደፈር፣ የሴት ልጅን ብልት መተልተል፣ እና ሌሎች ሴቶች
ላይ የሚያደርሱ ጐጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም ከጋብቻ ዉጭ ያሉ ጥቃት ነክ
ብዝበዛዎችን ያካትታል፡፡ በማህበረሠቡ ውስጥ ያሉ አካላዊ፣ ፆታዊ ና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች
ስንል በስራ ቦታ ና በትምህርት ተቋማቶች የሚታዩ የአስገድዶ መደፈር፣ ፆታዊ ጉዳትና ፆታዊ
ትንኮሣና ማስፈራሪያዎችን ያካትታል፡፡ እንዲሁም የሴቶች ህገወጥ ዝውውርና የግዳጅ ሴተኛ
አዳሪነትንም ይጨምራል፡፡


8
.Declaration on the Elimination of Violence against Women Proclaimed by General Assembly resolution

48/104 of 20 December 1993


9
ዝኒ ከማሁ አንቀፅ 5 2(1)እና(2)

4

ሌላዉ መገለፅ ያለበት ነጥብ አንዳንድ የፆታዊ ጥቃት ዓይነቶች በዋነኝነት አስገድዶ መድፈር
በሰዉ ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (Crime against Humanity) አካል ሊሆን የሚችልበት
እድል አለ፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ህግ (International Criminal Court Statute
10
ዉስጥ ተካቷል፡፡ በእርግጥ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቱ የተፈጸመዉ በስፋት ወይም በተጠና
መልኩ ሲሆን በሰዉ ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ክፍል ሊሆን እንደሚችል የዚህ ህግ
አንቀፅ 7(1) በግልፅ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በሰዉ ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች አካል
የሚያደርገዉ ገፅታ በዚህ ፅሁፍ የሚሸፈን አይሆንም፡፡

1.2. በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች

ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለያዩ መልኩ ይገለፃሉ፡፡ ከእነዚህም ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ
sexual violence, Sexual harassment, Sexual assault, Sexual abuse ,rape ናቸዉ፡፡ እነዚህ
አገላለፆች በመለዋወጥ ስንጠቀምበት ይስተዋላል፡፡11 በተለይም Sexual Violence, Sexual
Harassment, Sexual Assault የሚሉትን ቃላቶች ልዩነቶች መረዳት ጠቀሜታዉ ከፍ ያለ
በመሆኑ በዚህ ፅሁፍ እንደሚከተለዉ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

ፆታዊ ጥቃት ምን እንደሚመስል ከፍ ሢል በትርጉሙ ክፍል ተመልክቷል፡፡ ፆታዊ ትንኮሣ


(Sexual Harassment) ፆታዊ ጥቃት ጋር ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ብላክስ ሎዉ
መዝገበ ቃላት Sexual harassment “A type of employment discrimination consisting in verbal or
physical abuse of sexual nature ይለዋል፡፡ ይህም ፆታዊ ትንኮሳ ፆታ ነክ ልዩነት ሆኖ ያልተፈለገ
ወሲባዊ ሙገሳ፤ጥያቄና መድልኦ እንዲሁም ሌሎች ወሲባዊ ተፈጥሮ ያላቸዉ ቃላዊ እና
አካላዊ ድርጊቶች ያካትታል፡፡ በተጨማሪም Sexual harassment is a form of sex discrimination
that involves unwelcome sexual advances, requests for sexual favors, and other verbal and
physical conduct of a sexual nature12. በሌላ መልኩ ፆታዊ ትንኮሳ Sexual Harassment can be a
conduct which is unwelcome to its recipient allows a distinction to be drawn between inoffensive

10
For the purpose of this Statute, "crime against humanity" means any of the following acts when committed as
part of a widespread or systematic attack directed against any civilian population, with knowledge of the attack:…
(g) Rape, sexual slavery, enforced prostitution, forced pregnancy, enforced sterilization, or any other form of
sexual violence of comparable gravity;
11
Sexual violence: prevalence, dynamics and consequences, page,6
www.who.int/violence_injury_prevention/resources/.../en/guidelines_chap2.pdf,
12
Deirdre McCann, Sexual harassment at work: National and international responses,International Labour
Organization 2005,page 3

5

and unacceptable behaviour according to the context in which it takes place13 በሚል ይገለፃል
ይህም ሲተረጎም “ማንኛዉም ዓይነት ያልተፈለገ ባህርይ ሆኖ በተለይም ትንኮሳ የተደረገበትን
ሰዉ በሚያስከፋና ባልተቀበለዉ ሁኔታ ሲከናወን ነዉ”፡፡ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

ፆታዊ ትንኮሳ በአለም አቀፍ ደረጃ እዉቅና እየተሰጠዉ የመጣዉ ከ1970ዎቹ በኃላ ነዉ፡፡ እስከ
1970ዎቹ ድረስ ስም እንኳን አልነበረዉም፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ገደማ የአሜሪካ ሴቶች
በሚያደርጉት የሴቶች መብት እንቅስቃሴ (feminist movement) ዉስጥ ፆታዊ ትንኮሳን
በፌዴራሉ የፀረ- ልዩነት ህግ ስር እንዲካተት ጥያቄያቸዉን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በዚሁ መሰረት
በ1970ዎቹ አጋማሽ በወጣዉ የአሜሪካ የፌደራል ሰብዓዊ መብቶች ህግ (federal civil rights
act) ፆታዊ ትንኮሳ ፆታን መሰረት ያደረገ ጉዳት እንደሆነ እዉቅና በመስጠት የህጉ አካል
ተደረገ፡፡ ይሁንና ፆታዊ ትንኮሳ በአለም አቀፍ ደረጃ ብዙም እዉቅና ያልተሰጠዉና ገና በጅምር
ላይ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል በተባበሩት መንግስታት በ1979 የፀደቀዉ በሴቶች ላይ
የሚደረግ ማንኛዉንም አድሏዊ ልዩነት ማስወገድ ስምምነት ( Conventions on the Elimination
of all forms of Discrimination Aganst Women) /CEDAW/ ላይ ፆታዊ ትንኮሳን አስመልክቶ
ግልፅ ክልከላ ያላስቀመጠዉ፡፡ የኃላ ኃላ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛዉንም አድሏዊ ልዩነት
ማስወገድ ስምምነት ኮሚቴዎች ፆታዊ ትንኮሳን እየተገነዘቡትና በሪፖርታቸዉ እያካተቱት
መጡ፡፡ በመጨራሻም በ1989 ፆታዊ ትንኮሳ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትና የእኩልነት
መብታቸዉን በእጅጉ እየጎዳ ያለ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖረት አሳሰቡ፡፡ በዚሁ መሰረት
በተባበሩት መንግስታት ዉሳኔ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ማስወገድ ድንጋጌ
(Declaration on the Elimination of Violence Against Women) /DEVAW/ ፀደቀ፡፡ በዚህ ድንጋጌ
አንቀፅ 2 (ለ) … sexual harassment and intimidation at work in educational institutions and
elsewhere,… በሚል ተካተተ፡፡ ይህም ፆታዊ ትንኮሳና ማስፈራሪያ በትምህርትም ተቋማት፣
በስራ ቦታና በየትኛዉም አካባቢ መፈፀም በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትና አካል ሆኖ ተቆጠረ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) በ1999 ባንግ ኮክ ላይ በካሄደዉ
4ኛዉ የሴቶች ስብሰባ ላይ ፆታዊ ትንኮሳን እዉቅና ሰጠ፡፡ ከዚህ ባሻገር የተባበሩት መንግስታት
ጠቅላላ ጉባኤ በቤጅንግ ቃልኪዳንና የድርጊት ምቹ ሁኔታ The Beijing Declaration and Platform
for Action በ1995 የፀደቀዉ ፆታዊ ትንኮሳ የሴቶችን የእኩልነት መብት የሚጋፋ ድርጊት ነዉ፡፡
ስለሆነም ይህን ድርጊት ለመዋጋት መንግስታት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሠሩ

13
ዝኒ ከማሁ ገፅ 2

6

ተስማምተዋል፡፡ ፆታዊ ትንኮሳ በብዙ መልኩ ይገለፃል14፡፡ እነዚህም በአካል ከመንካት እስከ
መጉዳት፣ ምልክት ከማሳየት እስከ ፆታ ነክ ግብዣ፣ በቃላት ወሲባዊ ቀልድ ከመቀለድ እስከ
ወስብ ነክ ስድቦች፣ እንዲሁም በማሞገስ፣ በማድነቅና ልዩ ስጦታ መስጠትን ያካትታል፡፡ ከዚህ
የምንገነዘበው ፆታዊ ትንኮሣ በአካል ወይም በምልክት የሚገለፀው ፆታዊ ፍላጐቶች
(ድርጊቶችን) በሌላኛው ሠው ላይ ማሣደር ነው፡፡ በመሆኑም ፆታዊ ትንኮሣ ድርጊቶች ወንጀል
ናቸው ተብለው በኢትዩጵያ የህግ ሥርዓት አልተካተቱም፡፡

አሁን በቅርቡ የወጣዉ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር1068/2010 ፆታዊ ትንኮሳን
እንደሚከተለዉ ተርጉሞታል፡፡ “ፆታዊ ትኮሳ ማለት በስራ ቦታ የሚፈፀም ሆኖ ከሌላዉ ወገን
ፈቃድ ወጭ የሚቀርብ የወሲብ ሃሳብ ወይም ጥያቄ ወይም ሌላ ወሲባዊ ተፈጥሮ ያለዉ የቃል
ወይም የአካል ንክኪ ተግባር ሲሆን የሚከተሉትን ያካትታል፡፡

ሀ/ ከሌላዉ ወገን ፈቃድ ዉጭ የመሳም፤ የሰዉነት አካልን የመዳሰስ፤ የመጎንተል፤ወይም


የመሳሰለዉን የሰዉነት ንክኪ የመፈፀም ድርጊት

ለ/ ወሲብ አዘል በሆነ ሁኔታ ተጠቂዉን መከታተል ወይም እንቅስቃሴዉን መገደብ

ሐ/ ለቅጥር፤ ለደረጃ ዕድገት፤ ለዝዉዉር፤ለድልድል፤ለስልጠና፤ ለትምህርት፤ለጥቅማ ጥቅም


ወይም ማንኛዉንም የሰዉ ሃብት አመራር ተግባር ለመፈፀም ወይም ለመፍቀድ ወሲብን
እንደቅደመ ሁኔታ ማስቀመጥ”15 ወሲባዊ ትንኮሳን ሊያካትቱ የሚችሉ ተግባራቶች ናቸዉ፡፡

Sexual Assault ከ Sexual Violence ጋር በተመሣሣይነት ስንጠቀምበት ይስተዋላል፡፡ ብላክስ ሎዉ


መዝገበ ቃላት Assault ትርጉም ሢሠጠው ‘The threat or use of forceon another that causes that
person to have a reasonable apprehension of imminent harmful or offensive conduct: the act of
putting on another person in reasonable fear or apprehension of an immediate battery by means
of an act amounting to an attempt or threat to commit battery.’ በመሆኑም Assault ከትንኮሣ ጎላ
ያለ አካላዊ ና ስነልቦናዊ ጫና በግለሠቡ ላይ ያስከትላል፡፡ በህግ ረገድ በአትዮጵያ ወንጀል ህጉ


14
Physical conduct • Physical violence • Physical contact, e.g. touching, pinching • The use of job-related threats or
rewards to solicit sexual favours Verbal conduct • Comments on a worker’s appearance, age, private life, etc. •
Sexual comments, stories and jokes • Sexual advances • Repeated social invitations • Insults based on the sex of
the worker • Condescending or paternalistic remarks Non-verbal conduct • Display of sexually explicit or
suggestive material • Sexually-suggestive gestures • Whistling
15
የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር1068/2010 አንቀፅ 2/13 በተመሳሳይ አድሱ የአ.ብ.ክ.መ መንግስት ሰራተኞች
አዋጅ ቁጥር 253/2010 አንቀፅ 2/13

7

አንቀፅ 560 የእጅ እልፊት፤ እንዲሁም በአንቀፅ 840 የእጅ እልፊትና ቀላል ሃይል ድርጊት
በሚል ያካተታቸዉን ወንጀሎች የእንግሊዝኛወ ቅጅ አንቀፅ 560 assault; ሲለዉ በአንቀፅ 840
assault and minor acts of violence በሚል ተክቶታል ወይም ተጠቅሟል፡፡ በአንቀፅ 560 ላይ
የተመለከተዉ የእጅ እልፊትን ወይም assault ይዘት ስንመለከት “ማንም ሰዉ የአካል ጉዳት
ወይም የጤንነት ጉድለትን ሳያደርስ በሌላዉ ሰዉ ላይ የእጅ እልፊት ወይም የመግፋት ድርጊት
መፈፀመ” እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ቀላል የሆኑ ሰንበሮች የደም መቋጠር ምልክቶች
ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ስቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም እንደ ጤና ጉድለት
እንደማይቆጠር ድንጋጌዉ ይናገራል፡፡ በደንብ መተላለፍ ረገድ የተመለከተዉ አንቀፅ 840
እንዲሁ ማንም ሰዉ ሌላዉን ሰዉ ሳይመታ ወይም ሳያቆስል የእጅ እልፊት ወይም ቀላል
የሃይል ድርጊት መፈፀም እንደሆነ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በኢትዩጵያ የፍትሃብሔር ህግ አንቀፅ 2038 በእንግሊዝኛው ቅፅ physical assault


በሚል ርዕስ (1) A person commits an offence where he intentionally makes contact with the
person of another against the latter;s will. ተደንግጓል፡፡ የዚህም የአማርኛ ቅጅ ሰውነትን
ስለመጉዳት በሚል ርዕስ (1) አንድ ሰው ሆነ ብሎ ሌላው ሰው ሣይፈቅድ በሚያደርገው
መንካት በዚህ በመንካቱ ጥፉተኛ ነው በሚል ተደንግጓል፡፡

የዚህ ድንጋጌ ይዘት እንደሚነግረን ሰውን ያለፈቃዱ መንካት ጥፉት እንደሆነ ነው ይህ


ማለትም መንካቱ ጉዳት ቢያደርስም ባያደርስም ጥፉት ነው፡፡ ይህም የሰወችን የግል ነፃነት
/ለመጠበቅ ያሰበ ይመስላል፡፡ በመሆኑም assault ከ violence ያነሠ ክብደት እንዳለው ያሳያል፡፡
በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ በሴቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች የሚለውን ሃሣብ በእንግሊዝኛው
violence ማለታችን ነው፡፡

1.3 በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ የተካተቱ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ


ጥቃቶች

የወንጀል ህግ የአንድን ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማስጠበቅ


የሚያስችል፣ የግለሰቦችን ሁለንተናዊ መብት እና ነጻነት የሚያስከብር መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ቀደም ሲል ስራ ላይ የነበረውና የተሻረው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በጊዜና በተለያዩ ምክንያቶች
ህጉ ከወጣ በኃላ የመጣውን ዓለማቀፋዊ እድገት፣ አስተሳሰብ እና ሌሎች ሁለንተናዊ ለውጦችን
ያገናዘበ አልነበረም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሴቶችን መብት ጨምሮ ሌሎች አሁን ስራ ላይ

8

የዋለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ካካተታቸው እና ሀገሪቱ ካጸደቀቻቸው አለምአቀፍ የሰብአዊ
መብት ስምምነቶች እና ሰነዶች ጋርም የተጣጣመ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ይህ ህግ እንዲሻሻል
ከሆነ በኋላ በ1996 በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ እንዲተካ ተደርጓል፡፡ በዚህ አግባብ
የተሻሻለው የወንጀል ህግ በተለይም ለሴቶችና ህጻናት መብትና ደህንነት ጥበቃ የሰጡ
ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በዋናነት እንደ በግብረ-ሥጋ ነፃነትና ንጸህና ላይ የሚፈጸሙ ወጀሎችን
(አንቀጽ 620-628)፣ ለተፈጥሮ ተቃራኒ ባህሪይ የሆኑ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ድረጊቶችን
(አንቀጽ 629-632)፣ የተለያዩ ጎጅ ልማዳዊ ድረጊቶችን (አንቀጽ 561-562)፤ ጠለፋ (አንቀጽ
587-590)፣ ያለእድሜ ጋብቻ (አንቀጽ 647-648)፣ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ (አንቀጽ 555-560)
፣ በትዳር ጓደኛ ወይም ከጋብቻ ዉጭ በሆነ ግንኙነት ባላቸዉ ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጥቃት
(አንቀጽ 564)፣ የዝሙት ተግባር (አንቀጽ 635-638)፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናትን
መጉዳት (አንቀጽ 576) እና የመሳሰሉትን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

Ø በግብረ ስጋ ንጽህና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

በግብረ ስጋ ንጽህና ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን ስንመለከት


ከእለት ወደ እለት እየተበራከተ በመምጣቱና ቅጣቱ የማስፈራራት ሀይል እንዲኖረውና
ፈጻሚውም በቀላል ቅጣት እንዳይታለፍ በሚል ህግ አውጭው ቀድሞ ለድንገጌው ከተቀመጠው
የቅጣት መነሻ ወደ አምስት አመት ክፍ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ማንም ሰው የሀይል ድርጊት
በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም ህሊናዋን እንድትስት ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ
መከላከል እንድትችል በማድረግ ከጋብቻ ውጭ አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር የግብረ ስጋ
ግንኙነት የፈጸመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት
እንደሚቀጣ አንቀጽ 620(1) ስር ተመልክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአዲሱ የቤተሰብ ህግ
ዝቅተኛው የጋብቻ እድሜ አስራ አምስት አመት መሆኑ ቀርቶ አስራ ስምንት አመት ሆኗል፡፡
ስለሆነም ወንጀሉ የተፈፀመዉ እድሜያቸው አስራ ሶስት አመት በሆና አስራ ስምንት አመት
ባልሞላት ሴት ልጅ ላይ ሲሆን ወይም ወንጀሉ የተፈመጸው በጥፋተኛው መሪነት ቁጥጥር
ወይም ስልጣን ስር በሆነ የመጦሪያ ቤት የመማጠኛ፣ የህክምና፣ የትምህርት ፣የጠባይ
ማረሚያ፣ የመታሰሪያ ወይም የተያዙ ሰዎች መቆያ ተቋማት ውስጥ በምትገኝ ወይም በተከሳሹ
ጥበቃ ወይም ቁጥጥር ስር በምትገኝ ወይም የእሱ ጥገኛ በሆነች ሴት ላይ ሲሆን ወይም
በእድሜ መግፋት በአካል ወይም በአዕምሮ ህመም፣በመንፈስ ድክመት ወይም በማናቸውም ሌላ
ምክንያት የድርጊቱን ምንነት /ባህሪይ/ ወይም ቁጥጥር ስር በምትገኝ ወይም የእሱ ጥገኛ በሆነች

9

ሴት ላይ ሲሆን ወይም በዕድሜ መግፋት በአካል ወይም በመንፈስ ድክመት ወይም በሌላ
ምክንያት የድርጊቱን ምንነትም ሆነ ውጤትም ለማወቅም ሆነ ለመከላከል በማትችል ሴት ላይ
ከሆነ ወይም ይህ ድፍረት የተፈጸመው በጭካኔ በማሰቃየት ወይም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ
በሆኑ ወንዶች ከሆነ ቅጣቱ ከብዶ ከአምስት አመት እስከ ሀያ አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ
እስራት ያስቀጣል16፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንቀጽ 620 (4) ስር አስገድዶ ከደፈራት በኃላ ከህግ
ውጭ ተበዳዩዋን ይዞ ካቆየ ወይም ጠለፋ ካለ ወይም በድፍረቱ ምክንያት በሽታ የተላለፈባት
ከሆነ እነዚህን የሚመለከቱ የዚሁ ህግ ድንጋጌዎች በተደራቢነት ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

ሌላው በአንዲት ሴት ላይ የደረሰውን ከፍ ያለ ቁሳዊ ችግር ወይም የህሊና ሃዘን ምክንያት


በማድረግ ወይም በጠባቂነት፣ በአሰሪነት፣ አስተማሪነት ፣በአሳዳሪት ይህንን በመሰለ ግንኙነት
ምክንያት ያገኘውን ስልጣን እና ሀላፊነት በመጠቀም ከተባለችው ሴት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙት
የፈጸመ ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት የመሰለ ድርጊት ወይም ለንጽህና ተቃራኒ የሆነ ድርጊት
ከፈጸመባት እና ሴትዮዋም ድርጊቱን በመቃወም አቤቱታ ካቀረበች በቀላል እስራት እንደሚቀጣ17
ይደነግጋል፡፡

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ከፈረመቻቸውች የህጻናት መብቶች ኮንቬንሽን እና ከህገ መንግስቱ


አንጻር ማናቸውም አካለ መጠን ያላደረሱ ማለትም አስራ ስምንት አመት ያልሞላቸው ህጻናት
ሁለንተናዊ የህግ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመሆኑም ይህንንን ልዩ ትኩረት ከግምት ውስጥ
ያስገቡ የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ የመጀመሪያው እድሜያቸው አስራ
ሶስት አመት አመት በላይ ሆኖ አስራ ስምንት አመት ካልሞላት ሴትም ሆነ ወንድ ልጅ ጋር
ፈቅደው ይሁን በማታለል ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት
ከወንጀሉ አደገኛነትና ከልጆች ጥበቃ አንጻር ከፍተኛ ቅጣት ተመልክቷል፡፡ በቅጣት ረገድ
በተለይም ድርጊቱ የተፈጸመው በሴት ህጻን ላይ ከሆነ ግን ከሶስት አመት እስከ አስራ አምስት
አመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል18፡፡

በመሰረቱ የወንጀል ህጉ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህጻናት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት
መፈጸምን ብቻ በመቅጣት አልተወሰነም፡፡ ይልቁንም የግብረ ስጋ ግንኙነትም ባይሆን ይህን


16
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5፣ አንቀፅ 620(1)ና (2)
17
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 625
18
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 626(1)ና (2)


10

የመሰለ ድርጊት ወይም ለንጽህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ማናቸውም አይነት ድርጊት የፈጸመ
ወይም በፊታቸው እንዲህ አይነት ተግባርን ያደረገ ወይም ይህ አይነት ድርጊት እንዲፈዕም
/እንድትፈጽም የገፋፋ ማንም ሰው ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም እስከ አምስት
አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ጨምሮ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ስር
አስቀምጦ እናገኛለን፡፡ በተለይም የግብረ ስጋ ድፍረቱ የተፈጸመበት ህጻን የአጥፊው ተማሪ
፣የቤት ሰራተኛ፣ በሞግዚትነት ወይም በአደራ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በእርሱ ቁጥጥር
ስር በሚገኝ ልጅ ላይ ከሆነ አጥፊው ከሶስት አመት እስከ አስር አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ
እስራት የሚቀጣ ሲሆን በሌላ በኩል ተበዳዩዋ ሴት ከሆነች ደግሞ ቅጣቱ ይበልጥ ከብዶ
ከአምስት አመት እስከ ሀያ አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን ከንዑስ
አንቀጽ 4 ለመረዳት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የተፈጸመው ድርጊት በንዑስ አንቀጽ 3 የተገለጸው
ከሆነ አጥፊው ከሰባት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት ከዚህ
አልፎ በተበዳይ ላይ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ እንደሆነ እነዚህን
ድርጊቶች የተመለከቱ ድንጋጌዎች በተደራቢነት ተፈጻሚ እንደሚሆኑም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡19
በእርግጥ እድሜቸው አስራ ሶስት አመት ያልሞላቸው ሴት ልጆች የአካላቸውም ሆነ የአዕምሮ
ብቃታቸው እድሜያቸው በአስራ ሶስት እና በአስራ ስምንት አመት መካከል ከሚገኙ ሴት ልጆች
ጋር የማይመጣጠን እና የሚፈጸምባቸውም ድርጊት የበለጠ ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡ በዚህም
ምክንያት ይህ ድፍረት የተፈጸመው እድሜዋ አስራ ሶስት አመት ባልሞላት ህጻን ላይ ከሆነ
አድራጊው ከአስራ አምስት አመት እስከ ሀያ አምስት አመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት
ከብዶ የሚቀጣ ሲሆን ፈጻሚዋ ሴት ከሆነች ደግሞ ከአስር አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት
እንዲሆን ተደርጓል፡፡20 ይህ አድራጎት በተለይም ሞትን አስከትሎ ከሆነ ደግሞ ሞትን
የሚመለከተው የዚሁ የወንጀል ህግ ድንጋጌ በተደራቢነት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ
የአስገድዶ መድፈሩ ወይም በግብረ ስጋ ድፍረቱ ድርጊት እርግዝና ከመጣ ፤ፈጻሚው በአባላዘር
በሽታ መያዙን እያወቀ ተበዳዩዋን /ተበዳዩን ካስያዘ ወይም ደግሞ በደረሰው በደል ጭንቀት
ምክንያት ተበዳይዋ/ተበዳዩ ራሷን/ራሱን ካጠፋ ደግሞ ህጉ ለድፍረት ወንጀሉ ከፍ ያለ ቅጣት
ካላስቀመጠ በቀር ከአምስት አመት እስከ ሀያ አምስት አመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ21
ተቀምጧል፡፡ አስገድዶ መድፈር ወይም ሌሎች የግብረስጋ ግንኙነት በደል ወንጀል የፈጸመ ሰው

19
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 626(4)ና (5)
20
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5አንቀፅ 627(1)ና (2)
21
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 628


11

ብዙውን ጊዜ ከድርጊቱ በኋላ ከተበዳይዋ ጋር ጋብቻ ለመፈጸም የሚያደርገው መስማማት ከክስና
ከቅጣት ለመዳን በመሆኑ በነባሩ ህግ በዚህ አግባብ በሚደረገው ጋብቻ መሰረት የነበረው የክስና
የቅጣት ስረዛ ድንጋጌ ተሽሯል፡፡

Ø ከሴቶች እና ህጻናት ስነ ምግባር

በሴቶች እና ህጻናት ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀሎች ውስጥ ህጉ በተለይም ከስነ ምግባር ብልሹነት


ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን በክፍል ለይቶ በወንጀልነት የፈረጀ ሲሆን የተወሰኑትን ለማየት
እንሞክራለን፡፡ በህጉ አንቀጽ 635 እና ተከታይ ድንጋጌዎች እንደተመለከተው ማንም ሰው
ለጥቅም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ስጋ ለማርካት ሴቶችን ወይም አካለ መጠን
ያላደረሱ ልጆችን በፈቃዳቸውም ቢሆን ወደ ዝሙት አዳሪነት እንዲሰማሩ በማነሳሳት ፣በማባበል
ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ በመገፋፋት በማቃጠር የነገደ ከቦታ ቦታ ያዘዋወር ወይም
ለዝሙት ለማቅረብ በዝሙት አዳሪ ቤት ካስቀመጠ ከአምስት አመት ባልበለጠ ጽኑ እስራት እና
ከአስር ሽህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ በዚህ በኩል ህጉ በተለይም ለሴቶች
እና ህጻናት ከሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተነሳ ይህ አድራጎት የሚያስከትለው ቅጣት
የሚከብድበትን ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ የተበዳዩ አካለ መጠን ያደረሰች መሆን፣ በወንጀል ፈጻሚው
እና በተበዳይ መከከል ያለው የጋብቻ፤ የደምም ሆነ በህግ ያሉ እንደ ጉዲፈቻ፤ ሞግዚትነት እና
የመሳሰሉት ግንኙነቶች መኖር እንዲሁም ይህንን ተግባር እንደሙያ አድርጎ መያዝና የማታለል
እና የሀይል ድርጊቶች መኖር ቅጣቱን ከሶስት አመት እስከ አስር አመት ሊደርስ የሚችል ጽኑ
እስራት እና ከሀያ ሽህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ከሚያስቀጡ ሁኔዎች ውስጥ ይገኙበታል22፡፡

Ø ከጋብቻ ስርዓት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች

የወንጀል ህጉ በምእራፍ ስድስት ስር ከጋብቻ ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶችን አስመልክቶ


ዝርዝር ድንጋጌዎችን በጋብቻ ስርአት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ክፍል አስቀምጦ
ይገኛል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ በተለይም ከፍ ሲል የተመለከትናቸውንና ህገ መንግስቱ ሆነ
የቤተሰብ ህግ ማዕቀፎች ለጋብቻና ሴቶች ከሰጧቸው ጥበቃ ጋር የሚጣጣሙ ድንጋጌዎችን
ማየት ይቻላል፡፡ በመሰረቱ የተከለከለ ጋብቻን በመፈጸም እና በማስፈጸም ረገድ ህጉ ሚና
ያላቸውን ማለትም ከህግ ውጭ የተጋቡ፣ ለጋብቻው ፈቃዳቸውን የሰጡ፣ በምስክርነት የቀረቡ
እና ጋብቻውን ያስፈጸሙ አካላትን መቅጣት ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው ጋብቻውን

22
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 636

12

አስቀድሞ ጋብቻውን ለማፍረስ ወይም እንዳይጸና ለማድረግ የሚያስችሉ ህጋዊ ምክንያቶች
መኖራቸውን አስቦ ከሌላው ተጋቢ ከደበቀ ወይም ማንነቱን ለሌላው ተጋቢ በመደበቅ፣
በማሳሳት፣ በማታለል ወይም በማጭበርበር ጋብቻ ከፈጸመ በእስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ
እንደሚቀጣ ህጉ አስቀምጧል23፡፡ በህግ የተከለከለ ጋብቻን አስቦ ያስፈጸመ ማንም ሰው ፤አስቦ
ጋብቻውን የፈጸመ ተጋቢ ወይም ለዚህ አይነቱ ጋብቻ ምስክር የሆነ ሰው ከሶስት አመት
በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሽህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ሆኖም ይህ
የሆነው በቸልተኛነት መሆኑ ከተረጋገጠ ቅጣቱ ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም
በመቀጮ ሊሆን ይችላል24፡፡ ይሁን እንጅ ህገ ወጥ ጋብቻን መፈጸምም ሆነ ማስፈጸም በዚህ
አግባብ በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችለው ጋብቻው ከፈረሰ ብቻ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ያለእድሜ ጋብቻን አስመልቶ አንቀጽ 648 ማንም ሰው አስቦ አግባብነት ያለው የቤተሰብ ህግ
ካስቀመጠው ዝቅተኛ የጋብቻ እድሜ በታች አካለመጠን ያላደረሰችውን ልጅ ያገባ ሰው
የተበዳዩዋን እድሜ መሰረት ያደረገ ቅጣትን በሁለት መልኩ አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው
ተበዳይዋ እድሜዋ አስራ ሶስት አመት ወይም ከዛ በላይ ከሆነ ከሶስት አመት በማይበልጥ ጽኑ
እስራት የሚያቀጣ ሲሆን ሁለተኛው እድሜዋ ከአስራ ሶስት አመት በታች ሲሆን ግን ቅጣቱ
ከሰባት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ከፍ ተደርጎ የተቀረጸ ነው፡፡

Ø በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሴቶች እና ህጻናት ሕይወት ፣አካል እና


ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

የወንጀል ህጉ በቀድሞው ህግ ትኩረት ያልተደረገባቸውንና በሴቶች እና ህጻናት ህይወት ፣አካል


እና ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለይቶ በማወቅ ትኩረት እንዲያገኙ
ለማድረግ አሰባስቦ በምዕራፍ ሶስት ስር እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የመጀመሪያው ድርጊት እርጉዝ
ሴትን በማሸት ወይም በመውለድ ላይ ያለች ሴትን አካል በማርገፍገፍ ወይም አዲስ የተወለደን
ህጻን ግግ ማስወለቅ፣ክትባት እንዳይከተብ በማድረግ ወይም ይህንን የመሳሰሉ ጎጂነቱ በህክምና
ሞያ የታወቀ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመፈጸም እርጉዧ ሴት ወይም ህጻን ህይወት እንዲያልፍ
ማድረግ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት ያደረሰ ሰው እንደሚቀጣ የህጉ አንቀጽ 561፣562 እና
563 ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ወስጥ እንዲካተት የተደረገው


23
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 646 (1)ና (2)
24
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 647(1-3)


13

ደግሞ ሴትን መግረዝ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ከህጻናት ሴቶች በተጨማሪ በትላልቅ ሴቶች ላይም
ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ የድንጋጌው ይዘት ጥበቃውን ሰፋ አድርጎ በየትኛውም የእድሜ ክልል
ያለችን ሴት ሁሉ የሚመለከት ሲሆን ቅጣቱም ከሶስት ወር በማያንስ ወይም ከአምስት መቶ ብር
በማያንስ መቀጮ ተደርጎ ተደንግጓል፡፡ የሴትን ብልት መስፋትም ሴቶችን ለከፍተኛ ስቃይና
ጉዳት የሚዳርግ ጎጂ ልማድ በመሆኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ጠንከር ቢል
ውጤት ያስገኛል በሚል ግምት ከአምስት እስከ አስር አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ከፍ
ብሏል፡፡ በዚህ ድርጊት ሳቢያም አካላዊ ሆነ የጤና ጉዳት ከደረሰም በወንጀል ሕጉ ከፍተኛ ቅጣት
የሚጥል ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስር አመት የሚደርስ ጽኑ
እስራት ይሆናል25፡፡ ህጉ ከእነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች ውጭ ያለ፤ ኢ-ሰብአዊና ጎጂነቱ በህክምና
በተረጋገጠ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ምክንያት የአካል፣ የአዕምሮ ጉዳት ወይም ሞት እንዲደርስ
ያደረገ ሰውም በጉዳቱ ቅለትና ክብደት መሰረት እንደሚቀጣ በተጨማሪነት መገንዘብ ይገባል26፡፡

Ø በሴቶች የግል ነጻነቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

የወንጀል ህጉ በሰው የግል ነጻነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የተመለከቱ በርካታ ዝርዝር


ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ በዚህ ረገድ ሰውን መጥለፍ በጠቅላላው እንደሚያስቀጣ ከማስቀመጡ
በተጨማሪ ሴትን መጥለፍ ደግሞ ግልጽ ስያሜ ተሰጥቶት ራሱን የቻለ ድንጋጌ እንዲይዝ
ተደርጓል፡፡ ማንም ሰው አንዲትን ሴት አገባታለሁ በሚል ሀሳብ በሀይል የጠለፈ ወይም
ድርጉቱን የፈጸመው በማስፈራራት ፣በዛቻ ፣በተንኮል ወይም በማስፈራራት ፈቃደኛ እንድትሆን
በማድረግ ከሆነ ከሶስት አመት እስከ አስር አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ነገር
ግን አድራጊው ከጠለፋውም በኋላ ሴትዮዋን አስገድዶ የደፈራት መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ
ይህንን የድፍረት ወንጀል በሚመለከተው ህግ አግባብ ተጨማሪ ቅጣት እንደሚወሰንበት
ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ አዲሱ ህግ በነባሩ ህግ ያልነበረ እና ተበዳይዋ በጠላፊው ድርጊት
ለደረሰባት የህሊናና የማቴሪያል ጉዳት አግባብነት ባላቸው የፍትሃብሔር ህግ ድንጋጌዎች
መሰረት ካሳ የመጠየቅ መብቷን የሚጠብቅ ድንጋጌ ተካቷል፡፡ ጠላፊው የተጠላፊዋ ሴት
የአዕምሮ ህመምተኛ ወይም ራሷን መከላከል የማትችል ወይም እንዳትችል የተደረገች መሆኑን
እያወቀ ከሆነ ቅጣቱ ከቀድሞው ህግ ከብዶ ከአምስት አመት እስከ አስራ አምስት አመት


25
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 566
26
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 5 አንቀፅ 567


14

የሚደርስ ጽኑ እስራት ተደርጓል፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ሴትን መጥለፍ የተመለከቱ ድንጋጌዎች
በየትኛው የእድሜ ክልል የሚገኙትን ሴቶችን እንደሚመለከት ያስቀመጠ አይደለም፡፡ ከዚህም
በመነሳት ተጠላፊው ሴትም ሆነ ወንድ ድርጊቱ የተፈጸመው በእድሜያቸው የተነሳ ልዩ ጥበቃ
የሚያስፈልጋቸው አካለ መጠን ያላደረሱ ህጻናት (ማለትም ከአስራ ስምንት አመት በታች
የሆኑትን) ላይ በሆነ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆን ድንጋጌ በአንቀጽ 589 ተለይቶ ተቀምጧል፡፡
ድንጋጌው ከአምስት እስከ አስራ አምስት አመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን እንደወንጀሉ
የአፈጻጸም ሁኔታ፤ ክብደት እና ቅለት መሰረት ያደረጉ ቅጣቶችም በዝርዝር ተደንግገዋል፡፡

2. በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚያስከትሉት ጉዳት


2.1 የስነ ልቦና ጉዳት

የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት (WHO) የ2013 ሪፖርት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች
በየትኛውም የአለም ክፍል እየጨመሩ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ግኝት ከሆነ በዓለም
ላይ ካሉ ሴቶች ውስጥ 35% ያህል በቅርብ ጓደኞቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ባልሆኑ ሠዎች
ጥቃት ይፈፀምባቸዋል27፡፡ እንደዚህ ሪፖርት ገልፃ በዓለም አቀፍ ደረጃ 38% የሚሆኑት ሴቶች
ግድያ የተፈፀመው በቅርብ ጓደኞቻቸው ነው28፡፡ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት ከተፈፀመባቸው ጊዜ
ጀምሮ ተጎጅዎች የአካል፤ የስሜት፤ የአእምሮና የፀባይ መለዋወጥ እንዲሁም ያልተለመደ
ምልክት ይታይባቸዋል፡፡ በስሜታቸዉ ላይ የሚታዩ መለዋወጦች ከትንሹ ፍርሃት ጀምሮ ራስን
እስከ ማጥፉት29 ይደርሣል፡፡

የፆታዊ ጥቃት ሠለባ የሆኑ ሤቶች ቀድሞ ባልነበረባቸው ሁኔታ ፍርሃት (fear)
ያደርግባቸዋል፡፡ በተለይም ድጋሜ ጥቃት ይደርስብኛል በሚል መፍራት፣ ድርጊቱ
የተፈፀመበትን ሁኔታ መፍራት፤ ምሣሌ ጥቃቱ የተፈፀመው በማታ ቢሆን ማታን መፍራት፣
ማህበራዊ ግንኙነቶችን መፍራት ጥቃቱ የተፈፀመው ገበያ እሄደች ባለች ሴት ላይ ቢሆን ገበያ
መሄድን መፍራት በጥቃቱ የተነሣ የጤና ችግር ያደርስብኛል ብሎ መፍራት ሊሆኑ ይችላል30፡፡


27
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 7 ገፅ 9
28
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 7 ገፅ 9
29
Gender based violence, Health and the role of health sector, 2009, page3 available at
siteresources.worldbank.org/INTPHAAG/Resources/AAGGBVHealth.pdf
30
Evelyne Josse, “They came with two guns” The Consequences of Sexual Violence for the Mental Health of
Women in Armed Conflicts, 2010, The International Review of the Red Cross, Volume 92, Number 877, page 184

15

ሌላው ከፍርሃት ከፍ ያለው ደረጃ ስጋት (Anxity) የሚባለው ነው፡፡ ስጋት ከፍርሃት የሚለየው
ምንም ዓይነት የጥቃቱን አስታዋሽ ነገሮች በሌሉበት ደህንነት አለመሠማት ነው፡፡ ፆታዊ ጥቃት
የደረሰባቸው ሴቶች ሌላ ጥቃት በቤተሠቦቸ (በልጆቼ፣በእህቶቼ፣ በጓደኞቸቼ ወዘተ) ይደርሣል
ብሎ መስጋትም ሌላኛው አስከፊ ገፅታ ነው፡፡ ስጋቱ እየዋለ ሢያድር ትኩረት ማጣትና
እንቅልፍ ማጣትን ያስከትላል31፡፡

ከፍ ሢል ከተመለከትናቸው ከፍርሃትና ከስጋት ከፍ ያለው ደረጃ ጭንቀት (Anguish)


የሚባለው ነው፡፡ የፆታዊ ጥቃት ሠለባ የሆነች ሴት የተፈፀመባትን ጥቃት በማሰብ በጭንቀት
ውስጥ ትኖራለች፡፡ የጭንቀት ደረጃውም የሠውነቷን ስነ-ህይወታዊ ተግባራት ያቋውሣል32፡፡
በጭንቀት ጫና ወይም ደረጃ ውስጥ ያለች ሴት የልብ ምቷ መደበኛ አይሆንም፡፡ የአተነፉፈስ
ሥርዓቷ የተዛባ ይሆናል፡፡

በሌላ መልኩ መገለፅ ያለበት ስነ-ልቦናዊ ጫና ድብርት (depression)33 ነው፡፡ ድብርት ውስጥ
ያለች የፆታዊ ጥቃት ሠለባ ሤት ተስፉ መቁረጥና ሀዘን ይታይባታል፡፡ በህይወት ለመኖር
ፍላጐት አይኖራትም ማልቀስ፣ ራስን ስለማጥፋት ማሠብ፣ ወዘተ የመሣሠሉ ምልክቶች
ይታዩባታል፡፡

የፆታዊ ጥቃት የደረሠባቸው ሴቶች በአብዛኛው ማፈር፣ራስን መውቀስ ለራስ ያለን ዋጋ ዝቅ


አድርጐ ማየት (ለምሣሌ እኔ ሚስት መሆን አልችልም፣ እናት መሆን አይገባኝም ወዘተ
ማለት) ሌላኛው ገፅታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ራስን እንደጥፉተኛ መቁጠር፣ በራስ ባህርይ
መበሣጨት፣ ራስን ያልታደልኩና የተረገምኩ ነኝ ብሎ ማሠብ ይታያል፡፡ ከዚህ ባሻገር መናደድ
ይስተዋላል፡፡ የፆታዊ ጥቃት ሠለባ የሆኑ ሴቶች በጉዳት አድራሹ ላይ እጅግ ይናደዳሉ፡፡
ከዚህም አልፎ በቤተሠብ ላይ፣ ወይም በጠቅላላ በወንዶች ላይ መናደድ ይታያል34፡፡

በመጨረሻ ሊታይ የሚገባው ሄድ-መጣ የሚባለው የደስታ ስሜት (Euphoria) በጾታዊ ጥቃት
ተጐጅዎች ላይ ይስተዋላል፡፡ እንዲሁም ለሌላው ዓለም አለመጨነቅ በተለይም ለስራ፣
ለትምህርት፤ ለጓደኛ ግዴለሽ መሆን ያጋጥማል፡፡


31
ዝኒ ከማሁ ገፅ 185
32
ዝኒ ከማሁ ገፅ 186
33
ዝኒ ከማሁ ገፅ 184
34
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 1 ገፅ 23

16

ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው የስነ-ልቦና ጉዳቶች የአካላዊ ምቾት ማጣት ምልክቶች
(Physiological Symptoms) ያመጣሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋነኞቹ የውስጣዊ የአካል ክፍሎች
አሠራር ማዛባት፤ ማለትም የአተነፉፈስ፣ የደም ዝውውር፣ የምግብ መፈጨትና መወገድ
ሥርዓት ላይ ተፅእኖ ይፈጥራሉ፡፡ በፍርሃት፣ ስጋት፣ ጭንቀትና ድብርት ውስጥ ያሉ ሴቶች፣
ማስተወክ፣ ማላብ፣ ማስቀመጥ የመሣሠሉ ህመሞች ይታዩባቸዋል፡፡ ሌላኛው ጉዳት ወሢብ
የመፈፀም እክል (Sexual dysfunctions)35 ናቸው፡፡ የፆታዊ ጥቃት የደረሠባት ሴት የወሲብ
ፍላጐት የላትም ከዚህም አልፎ ወሲብን መጥላት፣ በወሲብ አለመርካት ይታይባታል፡፡ በሌላ
መልኩ ከወር አበባ አለመኖር፣ የወር አበባ መብዛት፣ እንዲሁም የተዛባ የወር አበባ (Menstrual
disorders) ያጋጥማታል፡፡

2.2. የጤና ችግር

በእርግጥ የስነ-ልቦና ችግር የጤና ችግር ነው፡፡ የጤና ችግር ከዚህ በተጨማሪም በአካል ላይ
የሚታዩ የጤና መጓደሎችን ለማለት ነው፡፡ ፆታዊ ጥቃት የደረሠባቸው ሴቶች ውስብስብ ለሆኑ
የአካል ነክ ጤና ችግሮች ያደርጋሉ፡፡ በተለይም የአስገድዶ መደፈር ጥቃት የደረሠባቸው ሴቶች

§ ያልተፈለገ እርግዝና
§ ላልተፈለገና ያለጥንቃቄ ለሚፈፀም ውርጃ
§ ኤች አይ ቪ ኤዲስን ጨምሮ ለሌሎች በግብረ ስጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች
§ ግብረ ስጋ ግንኙነትን የመፈፀም እክል (Sexual dysfunctions)
§ መካንነት
§ ለሽንት ባንባ ቁስለት
§ የወገብ ህመምና /የወገብ አጥንት የሚያስቆጣ በሽታ36 (pelvic pain and pelvic
inflammatory disease) በሴቶች ላይ የሚፈፀም የአስገድዶ መደፈር ጥቃት በሴቶች
የመራቢያ አካላት (ብልት) ላይአካላዊ የሆነ የጤና ችግር ያስከትላል፡፡

በተለይም እንደ

v የብልት መቀደድ
v የብልት መላላጥ

35
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 30 ገፅ 3
36
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 11 ገፅ 12

17

v የብልት መቅላት
v የብልት ማበጥ (ደም መቋጠ)
v ሰንበር ማውጣት
v ራስ ምታት
v ድካም37፣ ወዘተ ህመም ያስከትላል::

የክብደት መቀነስ (በተጠቂዎችም ሆነ እርግዝና ከተፈጠረ በህፃናት ላይ) ከዚህ በተጨማሪ


የፆታዊ ጥቃት ተጐጅ የሆኑ ሴቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሣዩት38 በርካታ ሤቶች
የአደንዛዥ ዕፅና የአልኮል መጠጥ ሡስ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንድ ጥናት “violence against women
is the most pervasive yet underrecognized human rights violation in the world. It is also a
profound health problem that saps women’s energy, compromises their physical and mental
health, and erodes their self-esteem. In addition to causing injury, violence increases women’s
long-term risk of a number of other health problems, including chronic pain, physical disability,
drug and alcohol abuse, and depression”39 በማለት ያስቀምጣል፡፡ ወደ አማርኛ ሲመለስ በሴቶች
ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች እጅግ ስር የሰደዱ ግን ገና በቅጡ ዕዉቅና ያልተሰታቸዉ
የሰብዓዊ መብት ጥሰትቶች ናቸዉ፡፡ የሚያሰከትሉት የጤና ጉዳት የሴቶችን የአካልና አእምሮን
ጤንነት በማወክ ሙሉ አቅማቸዉን የሚሰልብና በራሳቸዉ እንዳይቆሙ የሚያደርግ ነዉ፡፡
በተጨማሪም የሚደርሰዉ ጉዳትና ጥቃት በጨመረ ቁጥር የረጅም ጊዜ ጤና ነክ ቀዉሶችን
እንደ ፅኑ ህመም፤ የአካል ጉዳተኝነት፤ የአደንዛዥ እፅና መጠጦች ሱሰኝነታና ድብርትን
ያስከትላል የሚል ይሆናል፡፡
አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ፆታዊ ጥቃት የደረሠባቸው ሴቶች ራሣቸውን ማጥፉት መሞከራቸዉ
ሌላው ገፅታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክብራችን ተነካ የሚሉ ቤተሰቦች ፆታዊ ጥቃት
የደረሠባቸው ሴቶች ይገሏቸዋል፡፡ በአንዳንድ ሃገራት ፆታዊ ጥቃት የተፈፀመባቸዉ ሴቶች
የቤተሰባቸዉን ክብር ነክተዋል በሚል ግድያ (Honour Killing) ይፈፀምባቸዋል40፡፡


37
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 11 ገፅ 12
38
Non fatal and Fatal Outcomes of sexual violence ( Direct & Indirect Physical and Mental Health proplems)
Injury, Post traumatic stress, Femicide , Functional impairment, Depression, Suicide, Physical symptoms,
Anxiety, Maternal mortality, Poor subjective health, Phobias/panic disorders, AIDS-related , Permanent
disability
39
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 1 ገፅ 9
40
Wafaa Abdelhadi Honour Crimes and Violence against Women Preventing and Punishing Honour Crimes 2016,
Tilburg University available at arno.uvt.nt/show.cgi?fid=139874, page 10

18

3. በኢትዮጵያ ህግጋት የተካተተ የፆታዊ ጥቃት መፍትሔዎች
3.1. በወንጀል የፍትህ አስተዳደር የተደነገጉ መፍትሔዎች

በወንጀል ህጉ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ በበርካታ መፅሃፎች፣ ምዕራፎችና ክፍሎች የተካፈፋለ ነው፡፡ የዚህ


ህግ መፅሃፍ አምስት በሌሎች ሠዎችና በቤተዘመድ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከአንቀፅ 538-
661 ደንግጐ ይዟል፡፡ በተለይም በመፅሃፍ አምስት ምዕራፍ ሁለት በሠው አካልና ጤና ላይ
የሚፈፀሙ ወንጀሎች ከአንቀፅ 553-560 ተመላክተዋል፡፡ አንቀፅ 553 መርህ ነው፡፡ ይህ መርህ
ማንም ሠው አስቦ ወይም በቸልተኛነት በማናቸውም ነገር ወይም ዘዴ የሌላውን ሠው አካል
ያጐደለ ወይም ጤንነቱን የጐዳ እንደሆነ በዚህ ምዕራፍ በተመለቱት ድንጋጌዎች መሠረት
ይቀጣል ይላል፡፡ ድንጋጌዎቹ ማናቸውንም በሰውነት ላይ የሚፈፅሙትን የእጅ እልፊቶችን፣
መምታትን፣ ማቁሠልን፣ የአካል ማጉደልን፣ ጉዳቶችን ወይም ጥፉቶችን እንዲሁም በሰው
አካል ወይም የአእምሮ ጤንነት ላይ የሚፈፀሙትን ጉዳቶች ሁሉ ያጠቃልላሉ፡፡ ድንጋጌዎቹ
የሚያመለክቱት ማንም ሠው በሌላ ሠው አካል ወይም ጤንነት ላይ አስቦም ይሁን
በቸልተኝነት በምንም መልኩ ጉዳት ያደረሠ እንደሆነ እንዳደረሰው ጉዳት ልክ እንደሚቀጣ
ነው፡፡ የሚፈፅማቸው ወንጀሎችም ታስቦ የሚፈፀም ከባድ የአካል ጉዳት፣ ቀላል የአካል ጉዳት፣
በቸልተኛነት የሚፈፀም የአካል ጉዳት እና የእጅ እልፊት እንደሆኑ ከአንቀፅ 555-560 ያሉት
ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥ የእነዚህ አንቀጾች ርዕስ የአካል ጉዳት በሚል የተቀመጠ
ቢሆንም በይዞታቸው የአካል ጉዳቶች ብቻ ሳይሆኑ የአእምሮ ጤንነትን ጉዳት ተካቷል፡፡ ከዚህ
በተጨማሪ ፆተዊ ጥቃቱ ሞትን ካስከተለ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 538-541 ተፈፃሚ ሊሆን
ይችላል41፡፡ ሲጠቃለል እነዚህ ድንጋጌዎች በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የፈፀሙ ሰዎችን
በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ያስችላሉ፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 553 (2) “ፍርድ ቤቱ ለተበዳዩ
የሚከፈለውን የጉዳት ካሣ የሚወሰነው የጉዳቱን ከባድነትና የተከራካሪ ወገኞችን ሁኔታ ከግምት
ውስጥ በማስገባት በዚህ ህግ ስለ ጉዳት ካሣ በተደነገገው ጠቅላላ ድንጋጌ መሠረት ይሆናል”
በሚል አስቀምጧል፡፡ እነዚህን ሁለት ንዑስ አንቀጾች ስናያቸው በሰው የአካል፣ የአእምሮ
ጤንነት ላይ ጉዳት ያደረሠ ሠው ጉዳቱም ከከባድ የአካል ጉዳት እስከ ቀላሉ የእጅ እልፊት


41
የወንጀል ህግ አንቀፅ 620(3)፤ 626(5)፤ 627(5) የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ሞትን ያስከተለ እንደሆነ ቅጣቱ የእድሜ ልክ
እንደሚሆን ያሳያል፡፡

19

ቢሆንም እንዲሁም በአካል ከሚታዩ ጉድለቶች እስከ የአእምሮ ጠንቅ እስከሚሆኑት ጉዳቶች
ሁሉ ተበድያለሁ የሚል ሠው የጉዳት ካሣ የሚያገኝበት ሥርዓት ተዘርግቷል ማለት ነው፡፡

3.2 በወንጀል ህጉ የተካተቱ ፍትሃብሔራዊ መፍትሔዋች

የጉዳት ካሣ እንዴት እንደሚከፈል የሚነግረን የወንጀል ህጉ አንቀፅ 101 እና 102 ነው፡፡


አንቀፅ 101 ንብረትን መተካት ወይም የጉዳት ካሣና ኪሣራን መክፈል የሚል ርዕስ ኖሮት፤
“ወንጀሉ በተበዳዩ ወይም በተበዳዩ ባለመብቶች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ባደረሠባቸው ጊዜ ተበዳዩ
ወይም ስለተበዳዩ መብት ያላቸው ሠዎች በዳዩ ያደረሠባቸውን ጉዳት እንዲከሣቸው፣
ያጠፉውን ወይም ያፈረሠውን እንደነበረ እንዲመልስ እንዲሁም ለደረሠባቸው ጉዳት
ተመዛዛኝነት ያለው ካሣ በኪሣራ ስም እንዲከፍላቸው እንዲፈረድበት ሊጠይቁ ይችላሉ” በማለት
ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም ይህንን ለማድረግ የፍትሃብሔር ክስ ከወንጀል ክሱ ጋር አጣምረው
ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህም በወንጀል ስነ-ስርዓት ህጉ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት
ይመራል ይላል፡፡ እዚህ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት በደረሠባቸው ጊዜ ማለቱ ምን ማለት ነው? ከፍ
ያለ ጉዳት የሚባለው የትኛው ጉዳት ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህን
ጥያቄዎች ለመመለስ የዚህን አንቀፅ እንግሊዝኛ ቅጅ እንመልከት፡፡ Article 101- Restitution of
property, compensation for damages and costs “where a crime has caused considerable
damage to the injured person or to those having rights from him, the injured person or the
persons having rights from him shall be entitled to claim that the criminal be ordered to make
good the damage or to make restitution or to pay damages by way of compensation. To this
end they may join their civil claim with the criminal suit. Such claim shall be governed by the
provisions laid down in the criminal procedure code.” ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከፍ ያለ
ጉዳት በእንግሊዝኛው Considerable damage ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም ከፍ ያለ ጉዳት ማለቱ
ዝቅተኛ ጉዳት ከሆነ የጉዳት ካሣ አያስጠይቅም ማለት ሣይሆን ከግምት ውስጥ የሚገባ
(Considerable) ጉዳት ከደረሠ በሚል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አገላለፅ ከፍ ያለ ጉዳት
(Considerable damage) የጉዳቱን መጠን እንጂ የሚከፈለዉን የጉዳት ካሳ ልክ ለማሳየት
አይደለም፡፡ ካሳዉ በፍትሃብሔር ህጉ በተመለከተዉ መሰረት ተመዛዛኝ ወይም ርዕትን ከግምት
ዉስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሃተታ ዘምክንያት ላይ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ከግምት
ውስጥ የሚገባ ጉዳት በሚል ካልተረዳነው ከላይ በአንቀፅ 553 ላይ የተመለከቱት የእጅ


20

እልፊት፣ ማቁሠል ወዘተ እንደቀላል ጉዳት ተቆጥረው ካሣ አያስጠይቁም ወደሚል
ማደማደሚያ ያደርሠናል፡፡ ይህም ትክክል አይመስልም፡፡

በተጨማሪም የፍትሃብሔር ክስ ከወንጀል ክሱ ጋር ተጣምሮ ይቀርባል፤ የሚመራው በወንጀል


ስነ-ስርዓት ህጉ ነው ማለቱ ምን ማለት ነው? እንደሚታወቀው በብዛት የወንጀል ክሱን
የሚያቀርበው ዓቃቤ ህግ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ላይ ግን ተበዳዩ ከወንጀሉ ክስ ጋር የፍትሐብሄር
ክሱን አጣምሮ ሊያቀርብ ይችላል ሲል ምን ማለቱ ነው፡፡ የወንጀሉን ክስ እኮ ተበዳዩ
የሚያቀርብበት ሁኔታ ውሱን ነው፡፡ አገላለጹ ጉዳይን ማጣመር ከሆነ ከሳሹ አንድ መሆን
አለበት፡፡ ከሳሾቹ የተለያዩ በሆኑበት ሁኔታ ጉዳይን እንዴት አድርገን ነው የምናጣምረው?
የሚለዉም ግልፅ አይደለም፡፡ በእርግጥ ድንጋጌዉ ፈቃጅ ነዉ፡፡ ተበዳዩ ከፈለገ ራሱን በቻለ
የፍትሃብሔር መዝገብ የጉዳት ካሳ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከወንጀል መዝገቡ ጋር
የጉዳት ካሳ ጥያቄ ማቅረብ የሚችልበትም እድል ሊኖር እንደሚችል የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ
ሥርዓት ህጉ ከአንቀፅ 154-159 አስቀምጧል፡፡ አንቀፅ 154(1) በወንጀሉ የተበደለዉ ሰዉ
ወይም እንደራሲዉ የነገሩ መሰማት ሲጀምር ነገሩን የሚሰማዉ ፍርድ ቤት (to the court trying
the case ይላል የእንግኒዝኛዉ ቅጂ) ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲያዝለት መጠየቅ ይችላል፡፡
የሚፈለገዉ ካሳ አይነትና ልክ በፅሁፍ ወስኖ ያመለክታል፡፡ ማመልከቻዉን ሲያቀርብ በህግ
የተወሰነዉን የዳኝነት እንደ ፍትሃብሔ ነገር መክፈል የለበትም ይላል፡፡ በመሆኑም የወንጀል
ክሱ በወንጀል ዐ/ህግ በቀረበበት መዝገብ ጭምር ተበዳዩ ወይም እንደራሲዉ ወይም ስለተበዳዩ
መብት ያላቸው ሠዎች የጉዳት ካሳ ጥያቄ አጣምረዉ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ በግልፅ ያሳያል፡፡
ነገር ግን ይህ የክስ መጣመር በፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓት ህጉ አንቀፅ 11(1) ላይ ካለዉ
የተለየ ነዉ፡፡ ምክንያቱም በፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓቱ አንቀፅ 11(1) አነጋገር መሰረት ክሱ
የሚጣመረዉ ተከራካሪዎቹ በአንድ ዘንግ የተመደቡ (…the same parties in the same court…
ይላል የእንግሊዝኛዉ ቅጂ) ሲሆኑ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት
ህጉ አቀራረብ ከፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓቱ አንቀፅ 11(1) ሃሳብ በተለየ መልኩ ነዉ፡፡ በሌላ
መልኩ ዐ/ህግ በራሳቸዉ መከራከራ የማይችሉ ሴቶችን ወክሎ ፍትሃብሔራዊ ክርክር
የሚያደርግበት አሰራርና የህግ መዕቀፍ ተዘርግቷል፡፡ ስለዚህ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች
የጉዳት ካሳ ጥያቄ ዐ/ህግ ከወንጀል መዝገቡ ጋር አብሮ ቢያቀርብ የወንጀል ሃላፊነቱን
በተረጋገጠዉ መዝገብ ላይ የፍትሃብሔር ሃላፊነትና ካሳ ለማስወሰንና የካሳ ጥያቄዉ ሳይጓተት
መፍትሔ ለመስጠት የተሻለ ይሆናል፡፡


21

ሌላው በዚህ ድንጋጌ መታየት ያለበት የካሣዎቹ ዓይነት ምንድን ናቸው የሚለው ነው፡፡
በድንጋጌው በግልፅ እንደሚታየው፡-

Ø ንብረትን መተካት (Restitution of property)


Ø የጠፉውን ወይም የፈረሠውን እንደነበር መመለስ (Making good the damage)
Ø ኪሣራ መክፈል (to pay cost)
Ø ለጠፉ ለፈረሠ ነገር የጉዳት ካሣ መክፈል (to pay damage by way of
compensntion

የጉዳት ካሣ ደግሞ በፍትሃብሔር ህጉ 2090ና 2092 ግልፅ የሆኑ ጉዳቶች (ዕለታዊና ለወደፊት
ሊደርስ የሊችሉ ጉዳቶች እንዲሁም 2105 የህሊና ጉዳት) ሁሉ ሊያካትት ይችላል፡፡

አንቀፅ 102 ደግሞ ለተበዳዩ የሚሠጠው ካሣ አፈፃፀም ያሣያል፡፡ ይህውም፡-

“(1) ወንጀለኛው ወይም ስለ እርሱ ተጠያቂ የሆኑት እንደነገሩ ሁኔታና ወይም በኑሮአቸው
ምክንያት በተበዳዩ ላይ ለደረሠው ጉዳት ሊክሱ የማይችሉ መሆናቸው በታወቀ ጊዜ
ከወንጀለኛው ላይ ከተያዘው ገንዘብ ውስጥ ወይም ከመቀጮው ውስጥ ወይም በጉልበት ሥራ
ተለውጦ ከሚያገኘው ገቢ ሂሣብ ውስጥ ወይም ከተወረሠው ንብረት ሂሣብ ውስጥ ለተበዳዩ
እንዲከፈል ፍርድ ቤቱ ለማዘዝ ይችላል፡፡

(2) መንግስት ለተበዳዩ በከፈለው የካሣ ገንዝብ ልክ ለተበዳዩ መብት ተተክቶ ጉዳቱን ባደረሠው
ወንጀለኛ ላይ በቀጥታ ሊጠይቅና ሊቀበል ይችላል” በሚል ተደንግጓል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ የምንገነዘበው በዳዩ መካስ የሚችል ከሆነ በጉዳቱ ልክ እንዲከስ ማድረግ መርህ
ሆኖ በዳዩ መካስ የማይችል መሆኑ ከታወቀ ግን ከተያዘው ዕቃ፣ ከዋስትና መያዝ፣ ከመቀጮ፣
በጉልበት ስራ ከተገኘው ንብረትና ከተወረሠው ንብረት ላይ ለተበዳዩ ካሣ ሊካፈል እንደሚገባ
ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ባይኖሩስ እንዴት ይሆናል? የሚል ጥያቄ ማንሳት
ይገባል፡፡ በተጨማሪም ንፁስ ቁጥር ሁለት መንግስት በተበዳዩ በከፈለው የካሣ ገንዘብ ልክ
በተበዳዩ መብት ተተክቶ በወንጀለኛው ላይ ጥያቄ እንደት ያቀርባል? ማለትም መንግስት ስለ
ወንጀለኛው ሆኖ ለተበዳዩ ካሣ የሚከፍልበት አጋጣሚ አለን? ወይስ ከላይ ከተዘረዘሩት
ማለትም ከዋስትና ገንዘቡ ከመቀጮው ከተወረሠው ወዘተ ንብረት ላይ ለተበዳዩ ስለተከፈለ
ይህንን ገንዘቡን ነው መንግስት ተተክቶ የሚጠይቀው የሚሉት ነጥቦች ምላሹ ያስፈልጋቸዋል፡፡


22

በሃተታ ዘምክንያቱ ላይ “በቁጥር 105 (2) በዳዩ ወይም ስለእርሱ መብት ያላቸው ለበዳዩ
ሊክሱ በማይችሉ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሊያዝባቸው ከሚችሉት አማራጮች ውስጥ በዋስትና መያዝ
ስም ካስያዘው ገንዝብ ውስጥ በሚለው ሀረግ በተጨማሪ “ከመቀጮው ውስጥ” የሚል ሃረግ
ተጨምሯል፡፡ ይህም ተበዳዩ ሊካስበት የሚችለው አማራጭ መንገድ ከፍ እንዲያደርግለት
ያስችላል በማለት ነው የሚል ምክንያት ተቀምጧል፡፡” ከዚህ ውጭ መንግስት ለተበዳዩ በአንቀፁ
ከተመለከቱት ውጭ ስለመክፈሉ ወይም ስላለመክፈሉ የተገለፀ ነገር የለም፡፡

በፀሃፊዉ እምነት የአንቀፀ 102 (2) መንግስት ለተበዳዩ በከፈለው የካሣ ገንዝብ ልክ ለተበዳዩ
መብት ተተክቶ ጉዳቱን ባደረሠው ወንጀለኛ ላይ በቀጥታ ሊጠይቅና ሊቀበል ይችላል የሚለዉ
አገላለፅ ከተያዘው ዕቃ፣ ከዋስትና መያዝ፣ ከመቀጮ፣ በጉልበት ስራ ከተገኘው ንብረትና
ከተወረሠው ንብረት ላይ ለተበዳዩ ካሳ በተከፈለዉ ጊዜ መንግስት ከእነዚህ ጉዳዮች ላይ
የሚያገኘዉ ገቢ ስለቀረበት (ማለትም ለተበዳዩ በካሳ መልክ ስለተከፈለ) ይህንን የቀረበትን ገቢ
ከጉዳት አድራሹ ላይ እንዲያገኝ ያለመ ነዉ፡፡ በመሆኑም አንቀፀ 102 (2) መንግስት ስለ
ወንጀለኛው ሆኖ ለተበዳዩ ካሣ የሚከፍልበትን ስልት የፈጠረ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር የተያዘ
ዕቃ ወይም የዋስትና የመቀጮ ገንዘብ ወይም በጉልበት ስራ የተገኘና ከተወረሠው ንብረት በሌለ
ጊዜ መንግስት ለተበዳዩ ካሳ የሚከፍልበት ህግ አይደለም፡፡

3.3 የወንጀል ፍትህ ፖሊሲና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ህግጋት

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትህ ሚኒስቴር በ2003 ዓ.ም የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ አዘጋጅቷል፡፡ ምንም እንኳ
ፖሊሲዉን መሰረት ያደረገ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ስራ ላይ የዋለ የወንጀል ህግ ባይወጣም
የወንጀል ጉዳት የደረሰባቸዉ ሰዎች ካሳ እንዲያገኙ የሚያስችሉ የህገ ማዕቀፍ ሊኖሩ እንደሚገባ
ተመልክቷል፡፡ በፍትህ ፖሊሲዉ ክፍል ስድስት ስር በወንጀል ጉዳት የደረሰባቸዉን ሰዎች
መብት ስለማክበር በሚል ንዑስ ርዕስ ስር በወንጀል ጉዳት የደረሰባቸዉን ሰዎች መብት
በአግባቡ ማስከበር እንዲቻል የተፈፀመዉ የወንጀል ዓይነት ወይም የተጎጂዉን ግላዊ ሁኔታ
መሰረት ያደረገ እና ለልዩ ለልዩ ፍላጎቶቻቸዉም ተገቢዉን ምላሽ በመስጠት ላይ ያተኮረ
አሰራር በወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ ዉስጥ እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡ ሕፃናትን ጨምሮ በሌሎች
ሁኔታዎች በወንጀል ድርጊት ለሚደርስ ጉዳት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ተገቢዉን ጥበቃ
እና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ የድጋፍ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ በወንጀል ድርጊት
ጉዳት የደረሰባቸዉ ሰዎች ለደረሰዉ ጉዳት በፍርድ ቤት ወይም በሌሎች አማራጭ ዘዴዎች


23

የካሳ ጥያቄ በማቅረብ ተገቢዉን ካሳ በአፋጣኝ እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል አመች የሆነ
የአሰራር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የወንጀል ተጎጂዎች በተፈፀመባቸዉ የወንጀል ድርጊት
ሳቢያ ከደረሰባቸዉ ሥነ ልቦናዊ ቀዉስ እና ካጋጠማቸዉ ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች በአግባቡ
እንዲላቀቁ ተገቢ የሆነ ድጋፍ እና የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋት
ይኖርበታል በሚል ተመልክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሃ ግብር የፆታዊ
ጥቃት ተጎጂ ሴቶችን የሚደግፍና የሚንከባከብ ጊዜያዊ መጠለያ በሁሉም ክልሎችና የከተማ
አስተዳደሮች ቢያንስ አንደ መጠለያ ማዕከል ሊዘጋጅ እንደሚገባ ተቀምጧል፡፡
እዚህ ላይ የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ እንመልከት

እንግሊዝና ዊልስ

እንግሊዝና ዊልስ የወንጀል ጥቃት ሠለባ የሆኑ ዜጐች በመንግስት የሚካሱበት ሥርዓት አለ፡፡
ይህ ሥርዓት የሚተገበረውም የወንጀል ጉዳት ካሣ ባለስልጣን (Criminal Injuries Compensation
Authority (CICA)42 በሚባለው የመንግስት አደረጃጀት ነው:: ይህ መስሪያ ቤት የአካል
ጉዳቶችን እና የሚካሱበትን ታሪፍ በመዘርዘር ለተጐጅዎች ካሣ ይከፍላል፡፡ የአእምሮ ጉዳት
መነሻው የአካል ጉዳት ወይም የፆታዊ ጥቃት ከሆነ ካሣ ይወሠንለታል፡፡ በዚህ ህግ የአካል
ወይም የአእምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ሠዎች እንደ ንፁሃን ተጐጅዎች ተቆጥረው ወንጀለኛዉ
ቢቀጣም፣ ባይጠየቅም ወይም ቢከሰስም ባይከሠስም እንዲሁም ቢታወቅም ባይታወቅም ካሣ
የማግኘት መብት አላቸው43፡፡ የተጐጅዎች ግዴታ ጥቃቱ በተፈፀመባቸው ጊዜ ለፖሊስ
ማሣወቅና ለምርመራ መተባበር ነው፡፡ የአእምሮ ጉዳት ደርሷል የሚባለውም በህክምና
የተረጋገጠ የሣይካትሪክ ወይም የሳይኮሎጅካል ህመም ሢኖር ነው44፡፡ እነዚህም ከጥቃት በኃላ
የሚከሰት የአእምሮ መታወክ (Post Traumatic Stress Disorder)፣ ድባቴና የመሣሠሉትን45


42
The Criminal Injuries Compensation Schame, 2012, Ministry of Justice available at
http://www.nationalarchives.gov.uk/doc/open-government-licence
43
Vinson and Elkins, Compensation for the Mental Suffering of Rape Victims and Rape and Prostitution Laws
Relating to Minors: A Comparative Study, 2013, Beijing Zhongze Women’s Legal Counseling and Service Center,
page 20
44
ዝኒ ከማሁ ገፅ, 18
እንደ
45
Anxiety, tension, insomnia, irritability, loss of confidence, agoraphobia and
preoccupation with thoughts of guilt or self-harm

24

ያካትታል፡፡ ድባቴው የሚቆይበት ጊዜን በግምት ውስጥ ያስገባ ካሣ እንደሚከፈል ታሪክ
ያሳያል46፡፡

የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ወይም ሙከራ የደረሠባቸው ሴቶች ጥቃቱ ወይም ሙከራዉ
ሊያስከትልባቸው የሚችልው የስነ-ልቦና ከፍተኛ ነው በሚል ምክንያት በቂ ካሣ መንግስት
ይክሣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአስገድዶ መድፈር ጉዳት የደረሠባቸው ሴቶች በበዳዩ ላይ
የፍትሃብሔር ክስ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ እንድሁም የወንጀሉን ጉዳይ ለሚያየው ፍርድ
ቤቱ ለደረሠባቸው ጉዳት ካሣ እንዲከፈላቸው መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ይሁንና የወንጀሉን ጉዳይ
በሚያየው ፍርድ ቤት አማካኝነት ወንጀለኛው ወደ ማረሚያ ቤት ከተላከ በዚሁ ችሎት ካሣ
መጠየቅ አይችሉም47፡፡

ካናዳ

ካናዳ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የፌደራል ስርዓት የምትከተል ሃገር ነች፡፡ በመሆኑም በሁሉም
የሃገሪቱ ክልሎች ተፈፃሚነት ያለው የወንጀል ህግ አላቸው48፡፡ ይሁንና ክልሎች የራሣቸው
የሆነ የወንጀል ድርጊት ሠለባዎች ካሣ ህግ አላቸው፡፡ በተለይም የአልበርታና የኦንታርዮ
የተባሉትን ግዛቶች የወንጀል ፍትህ ሥርዓት በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ በአልበርታ ግዛት
የተጐጅዎች ወንጀል ህግ (Victims of Crime Act) ወይም የAlberta Compersation Act የሚባል
ህግ አለ፡፡ በዚህ ህግ የስነ-ልቦና ጉዳቶች ውስጥ በአስገድዶ መደፈር ጥቃት ስነ ልቦናቸዉን
የተጐዱ ሴቶች የሚካሡበት ደንብ ሲኖር ይህም የተጀመረው የወንጀል ተጠቂዎችን በገንዘብ
የመደገፍ ዕቅድ (The Victims of Crime Financial Benefits Program) አካል ነው49፡፡ ይህም
በግዛቷ የፍትህ ቢሮ የህዝብ ደህንነት ክፍል ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ በመሆኑም ጥቃት የደረሠበት
ሠው ወንጀሉን በተገቢው ጊዜ ለፖሊስ ማመልከት ይኖርበታል፤ እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ
መረጃዎችን፣ ሠነዶችን፣ የምርመራ ውጤቶችን ወዘተ ለፖሊስ ለመስጠት ተባባሪ መሆን
አለበት50፡፡ ካሣ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደማይቀርብ
ተደንግጓል፡፡ የጥቃቱ አደገኛነትና ጐጅነት ከግምት ውስጥ እየገባ እንደየ ጉዳዬች የሚከፈል


46
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 43 ገፅ 18
47
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 43 ገፅ 19
The Criminal Code of Canada, 1985
48

49
The Alberta Compensation Act established the Victims of Crime Fund and introduced the Victims of
Crime Financial Benefits Program.
50
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 43 ገፅ 12

25

የካሣ ገንዘብ አለ፡፡ የአስገድዶ መደፈር ወንጀልን አስመልክቶ በመንግስት ከሚከፈለው የጉዳት
ካሣ በተጨማሪ ተጐጅዎች በፍርድ ቤት ተጨማሪ ካሣ የሚጠይቁበት ሥርዓት አለ፡፡
በመሆኑም የግዛቱ ዐ/ህግ በወንጀለኛው ላይ ማንኛውንም ጉዳትና ኪሣራ አስመልክቶ ካሣ
ለተጐጅዎች እንዲከፈል መጠየቅ ይችላል፡፡ ጉዳቱም የስነ-ልቦና ችግሮች ጨምሮ ሌሎች
ጉዳቶች ሁሉ እንዲካሡ የሚደረግ ነው51፡፡

ሌላኛው የካናዳ ክልል (ግዛት) ኦንታርዮ ነች፡፡ በአንታርዬ የካሣ ህግ መሠረት የተቋቋመው
የወንጀል ተጠቂዎች የካሣ ቦርድ አለ፡፡ ይህ ቦርድ የወንጀል ጥቃት ያደረሡ ድርጊቶችን
በመዘርዘር እንዴት እንደሚካሱ ይሠራል፡፡ በዚህ ህግ መሠረት ፆታዊ ጥቃት በቀጥታም ይሁን
በተዘዋዋሪ መልኩ በሴቶች ላይ ጉዳትና ህመም እንዲሁም ሞት ያስከተለ እንደሆነ ካሣ
እንደሚከፈላቸው ይወሰናል52፡፡

3.4 በፍትሃብሔር ህጉ የተደነገጉ መፍትሔዎች

ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸዉ ሴቶች በዋናነት ፍትሃብሔራዊ መፍትሔ ያሰቀመጠዉ በከዉል


ዉጭ አላፊነት ህግ ነዉ፡፡ የዚህ ህግ ዋና ዓለማ ጉዳት ለደረሰበት ሰዉ ካሳ ማስከፈል ነዉ፡፡
ይህም በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት የዉል ግንኙነት ሳይኖር በሌላ ሰዉ ለሚደርስ ጉዳት
ሃላፊነት በህግ የተጣለበት ሰዉ ጉዳት ለደረሰበት ሰዉ የሚከፍላቸዉን ፍትሃብሔራዊ ካሳዎችን
ያካትታል፡፡ በኢትዮጵያ የከዉል ወጭ አላፊነት ህግ53 መሰረት ካሳ ለማገኘት ጉዳት መድረሱን
ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳት በሰዉ ጥቅም ላይ የሚደርስ ኪሳራ ሲሆን እሱም የገንዘብ ወይም
የህሊና ጥቅምን የሚነካ ወይም የሚጎዳ ሊሆን ይችላል፡፡54 የገንዘብ ጉዳት አሁኑኑ የደረሰ
ወይም ገና ወደፊት የሚደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም የህሊና ጉዳት በሚል
ተመልክቷል55፡፡ የገንዘብ ጉዳት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተጎጂዉን ጥቅም ወይም ገቢ
ያራቁታል፡፡ ሃብቱን ያሳጣዋል፡፡ ገቢዉ እንዳይጨምር ያደርጋል፡፡ ሃብቱ እንዳያድግ
ያደናቅፋል፡፡ ስራዉን እንዲያጣ ያደርጋል፡፡ የካሳ ዓይነቶች በሁለት መልኩ ይፈፀማሉ፡፡
እነዚህም በገንዘብ መካስ (pecuniary compensation) እና በሌላ አኳኃን መካስ (other modes of


51
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 43 ገፅ 12
52
የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 43 ገፅ 13
53
የኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ (1952)፣ 4ኛ መፅሃፍ ስለግደታዎች በሚለዉ 13ኛ አንቀፅ ከቁጥር 2027-2161 ተደንግጓል፡፡
54
ንጋቱ ተስፋዬ ከዉል ዉጭ አላፊነት እና አላግባብ መበልፀግ ህግ፤ 1999 ዓ.ም ሁለተኛ እትም፤ ገፅ 129
55
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ) አንቀፅ 2090፤ 2092፤ የህሊና ጉዳት አንቀፅ 2105

26

compensation)56ናቸዉ፡፡ በእነዚህ ዘዴዎች የሚካሱት የገንዘብ ወይም የህሊና ጉዳት
የደረሰባቸዉ ተጎጅዎች እንደሆኑ የኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ ከአንቀፅ 2090-2123
ያስገነዝባል፡፡ የካሳ አከፋፈል ስርዓቱም ለደረሰዉ የገነዘብ ጉዳት የተመዛዘነ ወይም የተመጣጠን
ካሳ መክፈል57፤ በርትዕ ካሳ መክፈል58፤ ዕቃን በመመለስ፤ በዓይነት በመተካት፤ የማደሻና
የማገጃ ትዕዛዝ በመስጠት59 መካስ እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ በኢትዮጵያ የፍትሃብሔር ህግ


የተደነገጉትን ሁኔታዎች ስንመለከት በአንቀፅ 2038 ሰውነትን ስለመጉዳት (physical assault)
በሚል ርዕስ

(1) አንድ ሰው ሆነ ብሎ ሌላው ሰው ሣይፈቅድ በሚያደርገው መንካት በዚህ በመንካቱ


ጥፉተኛ ነው፡፡
(2) እንዲህ በሆነ ጊዜ ሰዉየዉን በቀጥታም ሆነ ወይም በሌላ ህይወት ባለዉ ወይም
በሌለዉ ነገር አማካይነት ቢነካዉም ጥፋተኛ ነዉ፡፡
(3) በሌላ ሰዉ ላይ ጉዳት ለማድረግ የተደረገ የመዛት ሁኔታ ብቻ በጠቅላላዉ ጥፋት
አይባልም በሚል ተደንግጓል፡፡

ከዚህ እንደምንገነዘበዉ አንድ ሰዉ ሌላዉን ለመጉዳት ወይም ለማስቀየም አስቦ ያለፈቃዱ


ከነካዉ በመንካቱ ብቻ ጥፋተኛ እንደሚሆን ነዉ፡፡ ይህ ድርጊት ድብደባ ወይም የእጅ እልፊት
ሊባል ይችላል፤እንዲህ አይነቱ አድራጎት በሰዉነት ላይ ጉዳት ባያስከትልም ሶስቱ ሁኔታዎች
ማለትም ንክኪ፤ የተፈፀመዉ ንክኪ ያለፈቃድ መሆንና ታስቦ የተፈፀመ ንክኪ መሆን
እስከተሟሉ ድረስ ጥፋት ይሆናል60፡፡ በድንጋጌዉ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተመለከተዉ ሃሳብ
ደግሞ የሚነግረን ንክኪዉ በቀጥታ ወይም በሌላ ሕይወት ባለዉ ወይም በሌለዉ ነገር
አማካኝነት ሊፈፀም እንደሚችል ነዉ፡፡


56
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ)፣ በገንዘብ መካስ ከአንቀፅ 2090-2117 እንዲሁም በሌላ አኳኃን
መካስ ከአንቀፅ 2118-2123 ተመልክተናል፡፡
57
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ)፣ አንቀፅ 2090፤ 2091
58
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ)፣ ከአንቀፅ 2099- 2104
59
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ)፣ ከአንቀፅ 2118-2123
60
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 54፤ (ንጋቱ ተስፋዬ)፤ ገፅ 54

27

ይሁንና የዚህን አንቀፅ ልዩ ሁኔታዎች ህጉ በዝርዝር በአንቀፅ 2039 ላይ ሰውነትን መጉዳት
በሚል ተከሳሽ የሆነ ሰዉ ጥፋተኛ የማያስብሉት በቂ ምክንያቶች ናቸዉ የተባሉትን ከዚህ
በታች በተመለከተዉ መልኩ በዝርዝር አስቀምጧቸዋል፡፡

ሀ/ ከሳሹ ሥራዉን የሚቃወም መሆኑን ተከሳሹ በአዕምሮዉ ግምት ሊያስገባዉ የማይችል


መሆኑ የታወቀ እንደሆነ
ለ/ ስራዉ የተፈፀመዉ በሚገባ አኳኃን ለራሱ ወይም ለሌላ ሰዉ ለመከላከል ወይም በደንብ
በእጁ ያለዉን ወይም የያዘዉን ንብረት ለመጠበቅ ሲል እንደሆነ
ሐ/ ስራዉ የተፈፀመዉ ተከሳሹ ልጁን የአደራ ልጁን ተማሪዉን ወይም አሽከሩን በሚገባ
ለመቅጣት ሲል በሰዉነቱ ላይ ተገቢ የሆነዉን አቀጣጥ ፈፅሞበት እንደሆነ
መ/ ከሳሹ አደገኛ እብድ በመሆኑ ጉዳት እንዳያደርስ በሌላ አኳኃን ለመከላከል
ስላልተቻለዉና ተከሳሹ ስራዉን የፈፀመዉ በሚገባ አኳኃን እንደሆነ
ሠ/ የተከሳሹ ስራ አዕምሮ ባለዉ ሰዉ ግምት የሚገባ ነዉ የሚያሰኝ ሌላ ማናቸዉም
ምክንያት በተገኘ ጊዜ ሁሉ ነዉ፡፡

ሌላዉ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃት የተመለከተዉ በአንቀፅ 2114 ላይ ያለዉ የንፅህና
ክብር ስለመድፈር (sexual outrage) ነዉ፡፡

ይህም ፡- (1) ማንኛዉም ሰዉ በመድፈር ስራ ወይም ለክብር ንፅህና ተቃራኒ በሆነ ተግባር
በወንጀል የተቀጣ እንደሆነ ዳኞቹ ለተደፈረችዉ ሴት ለደረሰባት የህሊና ጉዳት ማካካሻ
የሚሆን ተገቢ ካሳ ለመቁረጥ ይችላሉ፡፡
(2) አንዲት ሴት ወይም ልጃ ገረድ በሃይል የተደፈረች እንደሆነ ለሴቲቱ ባል ወይም
ለተገሰሰችዉ ልጃ ገረድ ቤተዘመዶች ተገቢ የህሊና ጉዳት ካሳ ሊቆረጥ ይቻላል፡፡

በመሰረቱ የንፅህና ክብር መድፈር (sexual outrage) ድርጊት ፍትሃብሔራዊ ሃላፊነት


የሚያስከትለዉ የህሊና ጉዳት ያስከትላል በሚል እሳቤ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ይህ ድንጋጌ የሰፈረዉ
የህሊና ጉዳት ካሳ በሚያስፈልጋቸዉ ከአንቀፅ 2105-2117 ክፍል ነዉ፡፡ የህሊና ጉዳት ካሳ
መጠንም እጅግ ቢበዛ እስከ አንድ ሺህ ብር61 ብቻ የሚደርስ ነዉ፡፡ ከላይ በዝርዝር ለማመላከት
እንደተሞከረዉ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈፀመባት ሴት የደረሰባትና በዕድሜዋ ሙሉ


61
ግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 53፤ (ኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ህግ)፣ አንቀፅ 2116(3)

28

ሊደርስባት የሚችለዉን የስነ ልቦና ጠባሳ (እንደ ፍርሃት፤ ጭንቀትና ድብርት የመሳሰሉትን)
ሙሉ በሙሉ ፍትሃብሔራዊ መፍትሔ አግኝቷል ለማለት አይቻልም፡፡

የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ከዚህ በላይ ለማመላከት እንደተሞከረዉ በተጠቂዎች ላይ የአካል፤


የስነ ልቦናና የጤና ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል፡፡ እነዚህ ጉዳቶች በተጠቂዎች ላይ ስለመድረሱ
የሚያሳይ የጤና ምርመራ ልምድ እንኳን በብዛት አይታይም፡፡ ይህ ፅሁፍ ህጉን ብቻ እንጂ
የህጉን አተገባበር የሚፈተሺ ባይሆንም ለግንዛቤ ይረደኝ ዘንድ አጋዥ የሚሆኑ መዝገቦችን
ለመመልከት በባህር ጋር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ፅ/ቤት በ2010 ዓ.ም ዉሳኔ ያገኙ መዝገቦችን
አይቼ ነበር፡፡ በሁሉም የአስገድዶ መደፈር ወንጀል መዝገቦች ላይ የፍትሃብሐር ጉዳት ካሳ
ጥያቄ አልቀረበም62፡፡ በመሰረቱ ይህ የህክምና ማስረጃ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያቱ የተጠቂዋን
ጉዳት ለማወቅ ሳይሆን ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ማስረጃ ለማገኘት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር
ዐቃቢ ህግ ስለ ተጎጅዋ የአካል፤ የጤናና የስነ ልቦና ጉዳት አላሳሰበዉም፡፡ የየኤች አይ ቪ፤
የጉበት ቫይረስ፤ የአባለዘርና የእርግዝና ምርመራ የተገረገዉም በወንጀለኛዉን ላይ የሚቀርበዉን
ክስ ለማክበድ ነዉ፡፡ የወንጀል ህጉም እንደዚህ ዓይነት ድንጋጌ ስለያዘ፡፡ ዐቃቢ ህግ ወይም
ፖሊስ ለወንጀል ክሱ የህክምና ማስረጃ ባያስፈልገዉ ኖሮ የህክምና ምርመራ ላይደረግ ይችላል፡፡
እጅ ከፍንጅ በቀረበ ክስ63 የህክምና ምርመራ አልተደረገም፤ተከሳሹም በአምስት አመት ፅኑ
እስራት ተቀጥቷል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ (ፖሊስ ወይም ዐቃቢ ህግ) ያለኝ ማስረጃ ተከሳሽን
በወንጀል ለማስቀጣት በቂ ነዉ ብሎ ካሰበ የህክምና ምርመራ አያስደርግም፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች
በመነሳት የከሳሽ ዋነኛ ትኩረትና ግብ ወንጀል ፈፃሚን ማስቀጣት እንጂ የጥቃት ሰነባ
የሆነችዉን ሴት ፍትህ እንዲታገኝ ማድረግ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

1. ማጠቃለያ


62
የባህር ዳር ከተማ ፍትህ ፅ/ቤት ዐ/ ህግ ከአቶ ዮሃንስ…. (መዝገብ ቁጥር 428/10 በቀን 3/02/10 ዓ.ም የቀረበ ክስ)
በአንድ የህክምና ምርመራ ዉጤት የተገለፁት ፍሬ ነገሮች የሚያሳየዉ “…በተደረገዉ የማህፀን አካላዊ ምርመራ
በታችኛዉ ብልቷ ጫፍ 2 ሴንቲ ሜትር የሚሆን የድንግልና ንጣፍ መሰንጠቅ ታይቷል፡፡ ይህም የክብረ- ንፅህና
መገርሰስን ያረጋግጣል፡፡ ብልቷም በደም ተነካክቷል፡፡ የኤች አይ ቪ፤ የጉበት ቫይረስ፤ የአባለዘርና የእርግዝና
ምርመራ ዉጤቱ ለጊዜዉ ነፃ እንደሆነች ያሳያል” ይላል፡፡ በዚሁ ክስ ዝርዝር ላይ ….ተከሳሹ የሃይል ድርጊት በመጠቀም
አስገድዶ በመድፈር ክብረ ንፅህናዋን የገሰሰና ግራ ጡቷንና ግራ ጆሮዋን ነክሶ ጉዳት ያደረሰባት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይሁንና
የተከሰሰዉ በአስገድዶ መድፈሩ ብቻ ነዉ፡፡ የህክምና ምርመራዉና ዉጤቶም እነዚህን ሁሉ ጉዳቶች አላከተተም፡፡
63
የባህር ዳር ከተማ ፍትህ ፅ/ቤት ዐ/ ህግ ከአቶ ደርባቸዉ…..(መዝገብ ቁጥር 98/10 በቀን 6/11/09 የቀረበ ክስ) “ተከሳሹ የሃይል ድርጊት
በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ግል ተበዳይን በግምት 5፡30 ፀጉሯን ይዞ በመጎተት ባጃጅ ዉስጥ አስገብቶ ወደ
ሆቴል ወስዶ አልጋ ይዞ አስገድዶ ደፍሯታል…”63 ይላል፡፡

29

ፍትህ ላንዱ ጉዳት ያደረሰበት ሰዉ በፈፀመዉ ጉዳት በወንጀል ተቀጥቶ ማየት ሲሆን ለሌላ
ፍትህ አገኘሁ የሚለዉ በወንጀል ድርጊቱ የተነሳ ያጣዉን ገንዘብና ጥቅም ወይም የተጎዳዉን
አካሉንና አእምሮዉን የሚጠግን ማካካሻ በካሳ መልክ ሲያገኝ ነዉ፡፡ ለሌላዉ ጉዳት አድራሹ
በፈፀመዉ ድርጊት ተፀፅቶና ደንግጦ ተጎጅዉን ይቅርታ ሲጠይቀዉ ፍትህ አገኘሁ ሊሆን
ይችላል፡፡ እንዲሁም አንዳዱ እዉነታዉን ለማህበረሰቡ ወይም ጉዳት አድራሹ በቀጥታ መናገር
ነዉ64፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ዓላማ ለጠቅላላዉ ጥቅም ሲባል የህዝቦቹንና የነዋሪዎቹን
ሰላምና ደህንነት መጠበቅና ማረጋገጥ በመሆኑ ወንጀል ሲፈፀም ወንጀለኛዉ የሚቀጣዉ
ለጠቅላላዉ ጥቅም ሲባል (ማለትም ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈፅም ወይም ለሌላዉ
ማስተማሪያ እንዲሆን) በመሆኑ ተጎጅዎችን ያረካ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ስለመረጋገጡ
ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ምንም እንኳ ይህ ፅሁፍ ተግባሩን ሳይሆን ህጉን ብቻ የዳሰሰ ቢሆንም
ህጉን ለመዳሰስ ያነሳሳን ነገር ግን የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ከጉዳቱ በኃላ
ለንፅህና መጠበቂያ፤ ለመጠለያ ና ለህክምና ምርመራ የሚሆነ ገንዘብ ባለመኖሩ ባሰቃቂ ሁኔታ
በጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማገኘታችን ነበር፡፡ ዐ/ህግ ተጎጂዎቹ ምን መፍትሔ ያግኙ
የሚለዉ ብዙም አያሳስበዉም፡፡ ይልቁንም ትኩረቱ ወንጀል ፈፃሚዉን ማስቀጣት ነዉ፡፡
የተጎጅዎችም አስፈላጊነት ለምስክርነት እንጂ እነሱ ፍትህ ስለማገኘታቸዉ የሚጨነቅ አካል
የለም ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ለሚደርስባቸዉ
የስነ ልቦና ጉዳት በሥነ ልቦናና ሥነ አእምሮ ባለሙያዎች እየተረጋገጠ እንደጉዳቱ ልክ የገንዘብ
ካሳ የሚከፈልበት ስልት ያስፈልጋል፡፡ የፆታዊ ጥቃት የተፈፀመባቸዉ ሴቶች በተለይም
የአስገዲዶ መድፈር ድርጊት ተጠቂ ሴቶች ድርጊቱ ሊያስከትልባቸዉ የሚችለዉ የጤና
ችግሮችን በህክምና በመለየት ወይም ሙያዊ ግምት በማስቀመጥ የገንዘብ ካሳ የሚያገኙበት
ስርዓት ሊዘረጋ ግድ ይላል፡፡ የፍትሃብሔር ህጉ በአንቀፅ 2114 ላይ ያለዉ የንፅህና ክብር
ስለመድፈር የሰፈረዉ ድንጋጌ የሚያስክሰዉ የህሊና ጉዳት ብቻ ነዉ፡፡ ይሁንና የአስገዲዶ
መድፈር ድርጊት በርካታና የተወሳሰብ የጤና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ


64
Amy Kasparian የተባለች ፀሃፊ በ2014 Justice beyond bars በሚለዉ ፅሁፏ “For some [‘victims/survivors’],
justice is simply the perpetrator’s conviction and incarceration. For others, justice is receiving
compensation from the offender or the state to help with civil matters like securing safe housing,
affording counseling, or repairing property damage. To others, it is having a meaningful opportunity to
tell one’s story to the community, or perhaps directly to the offender. And yet still, to other victims,
justice is having the offender publicly acknowledge and apologize for the harm caused. In short, justice
to rape victims can manifest itself in many diverse forms that often do not necessarily rely on the
traditional criminal justice idea of punishment” በማለት ትገልፃለች

30

ጉዳቶች የሚካሱበት ህግ ተሻሽሎ ሊወጣ ይገባል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጅል ህግ ከወንጀል ፍትህ
ስርዓቱ ጋር የጉዳት ካሳ ጥያቄዎች ተጣምረዉ እንዲቀርቡ የሚፈቅዱ በመሆኑ በሴቶች ላይ
በሚፈፀሙ የፆታዊ ጥቃት ክርክሮች ጊዜ የጉዳት ካሳ ጥያቄዎችን አካቶ በማቅረብ ተጠቂዎች
ካሳ እንዲያገኙ የሚያስችል ስራ ዐቃቢ ህግ ሊሰራበት ይገባል፡፡ የአብክመ
ፍ/ባ/ማ/ህ/ም/ኢንስቲትዩት ይህንን ፅሁፍ በማዳበር ለዳኞች፤ ዐቃቢያን ህጎችና መርማሪ
ፖሊሶች ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስችል ስልጠና ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡


31

You might also like