You are on page 1of 8

ከጣራ እስከ ጉዛራ

(ክፍል አንድ)
እነሆ ከጎንደር ከተማ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ የምናመራው በአዲሱ የጎንደር ባሕር ዳር መንገድ ወደ
አዲስ ዘመን አቅጣጫ ነው፡፡ ይህ አዲሱ የአስፓልት መንገድ የገበሬዎችን እርሻና አስደናቂ የሆኑትን የሰሜንና
ደቡብ ጎንደር ተራራማ ቦታዎች እያቋረጠ የሚጓዝ በመሆኑ ዓይናችሁን ከግራና ቀኝ የተፈጥሮ ትርዒት
አትነቅሉም፡፡

በመንገድ ላይ በኩራት ከቆሙት ዐለቶች


ዐለቶች አንዱ
የሩቅ ምሥራቅ ምንጣፍ የመሰሉ እርሻዎች፣ እንደ ሞዴሊስት ወገባቸውን ይዘው የልብስ ትርዒት የሚያሳዩ
የሚመስሉ ወጥ ድንጋዮች፣ በዛፎችና ቁጥቋጦዎች የተሞሉ ተራሮች በመንገዱ ግራና ቀኝ እየተሰናበቷችሁ
ያልፋሉ፡፡ ሾፌራችን ሞላ ረጋ ብሎ ለጎብኝ በሚያመች መንገድ ይነዳል፡፡ የጎንደር ልደታው ሙሉቀን ደግሞ
እያንዳንዷን መሬት ልቅም አድርጎ ያውቃታል፡፡

ምዕራፋችን የሆነው ሦስቱ ታላላቅ ገዳማት የሚገኙባት የጣራ ገዳም አካባቢ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ጣራ ገዳም፣ ዋሻ
እንድርያስና ዋሻ ተክለ ሃይማት የተባሉ ገዳማት ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያ ጉዟችን ወደ ዋሻ እንድርያስ ነው፡፡

አዲሱ የባሕር ዳር ጎንደር መንድ የጣራ ገዳምን ቦታ ለሁለት ከፍሎት ስለሚያልፍ በግራና ቀኙ ጥቅጥቅ ያለው ደን
ይታያል፡፡ በጣራ ገዳም ተራራ ሥር ስትደርሱ ለአካባቢው የተዘጋጀውን በቧንቧ የተሳበ አንድ የምንጭ ውኃ
ታገኛላችሁ፡፡ ትምህርት ቤቱን አልፋችሁ ለአሥራ አምስት ደቂቃ ወደ ተራራው ሥር ስታመሩ እየተንደረደራችሁ
ትወርዱና የወፎችን ድምጽ ብቻ ወደ ምትሰሙበት ወደ ዋሻ እንድርያስ ትደርሳላችሁ፡፡

ዋሻ እንድርያስ በ13ኛው መክዘ ከተሠሩት የጎንደር የዋሻ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ ያነጹት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ
መዝሙር የነበሩትና ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር በሁለተኛው የኢየሩሳሌም ጉዟቸው የተገናኙት አቡነ እንድርያስ
ዘመርሐ ቤቴ ናቸው፡፡ አቡነ እንድያስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተገናኙት በደብረ በንኮል ገዳም መሆኑን ገድላቸው
ይገልጣል፡፡ አቡነ እንድርያስ በላስታ፣ ጎንደር መንገድ አልፈው፣ በጎጃም በኩል በመሻገር መጀመርያ ወደ ደብረ
ሊባኖስ ተጉዘው ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላ ወደ እብናት አካባቢ መምጣታቸውን ነው ገድሉ የሚናገረው፡፡

አቡነ እንድርያስ
ገድለ አቡነ እንድያስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክና ጉዞ በገድለ ተክለ ሃይማኖትም ሆነ በሌሎች መዛግብት
የማናገኛቸውን አዳዲስ ታሪኮች የሚገልጥልን ልዩ መጽሐፍ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከትግራይ ወደ ላስታ
ተጉዘው ከላስታ በተከዜ በኩል ወደ ጎንደር እብናት መምጣታቸውን፤ ከዚያም በዚህ በጣራ ገዳም በኩል
ማለፋቸውን ይተርካል፡፡ ይህ መንገድ ዛሬም የጎንደር ሰዎች ላሊበላን ለመሳለም ወደ ላስታ የሚሄዱበት በመልዛ
በኩል ያለው መንገድ ነው፡፡

አቡነ እንድርያስ ወደዚህ ቦታ ሁለት ጊዜ መጥተዋል፡፡ መጀመርያ ከደብረ በንኮል ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር
የተከዜን ወንዝ ተሻግረው ሲሆን በኋላም በአካባቢው ወንጌል እንዲያስተምሩ ተልከው ነው፡፡ በመጀመርያው
ጉዟቸው ወሎን ተሻግረው ዐርፈውበት የነበረው ቦታ እብናት ውስጥ ዛሬ ‹ደብር ተክለ ሃይማኖት› የሚባለው
ሥፍራ ነው፡፡

ዋሻው መልኩ የይምርሃነ ክርስቶስን ይመስላል፡፡ ከአንድ ተራራ ሥር የነበረውን የተፈጥሮ ዋሻ በመጠቀም የተገነባ
ነው፡፡ በሮቹ ከእንጨት የተሠሩ ሲሆኑ በበሮቹ አራት መዓዝን የሚገኙት ወጣ ወጣ ያሉት ነገሮች የዘመነ ላሊበላን
የሕንጻ አሠራር የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የዋሻ እንርያስ በር
ልክ እንደ ላሊበላ ውቀር አብያተ ክርስቲያናትና እንደ ይምርሃነ ክርስቶስ ሁሉ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያኑ መስኮት
አንዱ ከሌላው ጋር የማይገጥም የየራሱ ልዩ ዲዛይን አለው፡፡ በብዙዎቹ የጥንት ገዳማት ላይ የምናየው የድንጋይ
ደወል እዚህም አለ፡፡ እንዲያውም ከብዛቱ የተነሣ ሌሎች ‹አድባራት ይጠቀሙበት› ብለው ቢሰጡት በሄደበት ቦታ
ድምጽ አላወጣ በማለቱ እንደተመለሰ ገዳማውያኑ ነግረውኛል፡፡

ወደ ውስጥ ስትገቡ አያሌ ጥንታውያን ነገሮችን ታያላችሁ፡፡ መሥዋዕተ ኦሪት ይሠዋበት የነበረው የደሙ
ማቅረቢያ፣ በአካባቢው በነበረው ጥንታዊ የጣዖት አምልኮ ያገለግል የነበረ የጣዖት ቅሪት፣ የቀድሞውን ዘመን
የገበጣ ጨዋታ የሚያሳይ ጥንታዊ የገበጣ መጫወቻ፤ ከእንጨት የተሠራ የመነኮሳት መሰብሰቢያ ቃጭል፤ የቀድሞ
ነጋሪቶች፤ ወዘተ ለታሪክ ቀርተዋል፡፡
ዋሻ እንድርያስ ከተራራው ላይ ሲታይ
ዋሻ እንድርያስ የሚገኘው ከጣና ሐይቅ አጠገብ እንደመሆኑ፤ በአካባቢው በጣና ቂርቆስ ይከናወን ከነበረው
ኦሪታዊ ሥርዓት፣ የአኩስም ሥልጣኔ ባለቤቶች የነበሩት የአገው ሕዝቦች በአካባቢው ከነበራቸው ቦታ አንጻር የዋሻ
እንድርያስና የሥርዓተ ኦሪት ግንኙነት በሚገባ ቢጠና ለሃይማኖት ታሪካችን ተጨማሪ ፍንጭ የሚሰጠን
ይመስለኛል፡፡ በቦታው ያየሁት የኦሪት መሥዋዕት ማቅረቢያ በጣና ቂርቆስ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በአካባቢው የወይን እርሻ እንደነበረ የሚያሳይ የወይን ማጠራቀሚያ ጎታ፣ ለክፉ ቀን እህል ማጠራቀሚያ ያገለግል
የነበረ ጥንታዊ ጎተራ፣ የአባቶቻችንን ጥንታዊ ጥበብ የሚያሳይ ጥንታዊ ቁልፍ ይገኛሉ፡፡
ከዋሻ እንድርያስ መስኮቶች አንዱ
በግድግዳው ላይ የምታዩት ትንንሽ ጠፋጣፋ ድንጋዮችን በጭቃ እያጣበቁ ግድግዳ የመሥራት ጥበብ ልክ እንደ
ይምርሃነ ክርስቶስ ሁሉ እዚህም ጎልቶ ይታያል፡፡ በሁለቱም ቦታዎች ስለ ጥበቡ የሚተረከው ተመሳሳይ ነው፡፡
እዚያም እዚህም ጭቃው ሰባት ዓመት እንደሚቦካ ይነገራል፡፡

በገድሉ ላይ የሚገኘውን አካባቢው ከላስታ ጋር የነበረውን ግንኙነት ስናየው የጥበቡን ትሥሥር ሊያመለክተን
ይችላል፡፡ በይምርሃነ ክርስቶስ ጣራና ግድግዳ ላይ የምናየውን ዓይነት የሥዕል ጥበብ እዚህ በተሻለ ሁኔታ ተጠብቆ
እናገኘዋለን፡፡

በዋሻ እንድርያስ የምናገኛቸው ሥዕሎች የጎንደርን ዘመን ሥዕሎች የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ እንደ እኔ ግምት
ከመካከለኛው ዘመን እና ከዚያ በፊት ከነበሩት ሥዕሎች ጋር ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ በተለይም የተጠቀሙበት
ቀለምና በእንጨት ላይና በግድግዳ ላይ በጭረት ለመሳል የተጠቀሙበት ዘዴ የላስታን ዘመን የሥነ ሥዕል ጥበብ
ለመፍታት የመረጃ ምንጮች ለመሆን የሚያስችላቸው ነው፡፡
በዋሻ እንድርያስ የሚገኘው የኦሪት መሥዋዕት ማቅረቢያ የነበረ ዕቃ
አሁን ተገዝቶ መግባት ቀረ እንጂ ዋሻ እንድርያስን፣ ዋሻ ተክለ ሃይማኖትንና ዜና ማርያምን የሚያገናኝ የዋሻ ውስጥ
መንገድ አለ፡፡ ልክ ይምርሃነ ክርስቶስንና አቡነ ዮሴፍን የሚያገናኘውን መንገድ የሚመስል፡፡ አስጎብኛችን
ከአምስት ዓመታት በፊት ገብተው እንደነበር ነግረውናል፡፡ ወደ ታች መውረጃ ደረጃ፣ ከዚያም የዋሻ ውስጥ
መንገድ፣ ቀጥሎም ዘይት መሰል ነገር ያለው ኩሬ እንዳገኙ ተርከውልናል፡፡ ያ ኩሬ ጠበል መሆኑንና ብዙዎችን
ሲፈውስ በዓይናቸው ማየታቸውንም አጫውተውናል፡፡ የሚገቡበት ዋናው ምክንያትም ከዚያ ጠበል ለሰዎች
ለመቅዳት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከኩሬው በኋላ ሰፊ ሜዳ መኖሩን ሜዳው እንዳለቀም መንገድ እንደሚገኝ
ይገልጣሉ፡፡
ከእንጨት የተሠራ ቃጭል
ከእርሳቸው በፊት የገቡ አባቶች አንድ ቀን ሙሉ ሄደው ነገር ግን ከግማሽ መንገድ ማለፍ እንዳልቻሉና
እንደተመለሱ እንደነገሯቸው ተርከውልናል፡፡

የድንጋይ ደወል
ከተራራው ወደ ታች እየሰገዱ የሚወርዱት ዛፎች፤ በግራና ቀኝ የምትሰሙት የአዕዋፍ ዝማሬ፣ በመካከላቸው
ጎንበስ ብላችሁ የምታልፉት ዕድሜ ጠገብ ዛፎች እዚያው እንድትቀሩ እንጂ እንድትመለሱ አይመክሯችሁም፡፡
ከቤተ ክርስቲያኑ ስንወጣ በስተ ግራ በኩል እናቶች በድንጋይ ወፍጮ እህል ይፈጫሉ፡፡ እኛ እየራቅን ስንሄድ
ከአዕዋፉ ዝማሬ ቀጥሎ የሚሠማን ‹እርም እርም› የሚለው የወፍጮው ድምጽ ብቻ ነበር፡፡
ዋሻ እንድርያስን በዚህ ተሰናብተን ጉዞ ወደ ዋሻ ተክለ ሃይማኖት ቀጠልን፡፡ ሳምንት እንገናኝ፡፡

You might also like