Professional Documents
Culture Documents
መምህር ክፍሌ ወልደ ጻድቅ ‹የጽጌ ዚቅ› በሚለው፣ ዓመተ ምሕረት በሌለውና በእጅ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ በታተመው
መጽሐፋቸው ከገጽ 1 – 75 እንደ ገለጹት ከበዓለ ጽጌ ጋር የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ የእመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም፤ የቅዱን መላእክት፤ የቅዱሳም ጻድቃን እና የቅዱሳን ሰማዕታት በዓላት አብረው ይከበራሉ፡፡ ለአብነትም
የሥላሴ፤ የአማኑኤል፤ የዐርባዕቱ እንስሳ፤ የሩፋኤል፤ የኪዳነ ምሕረት፤ የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ (ፅንሰቱ)፤ የእስጢፋኖስ፤
የወንጌላውያኑ ማቴዎስና የማርቆስ፤ የዘብዴዎስ ልጆች የያዕቆብና የዮሐንስ፤ የቶማስ ዘህንደኬ፤ የሐና፤ የአቡነ አረጋዊ፤
የቂርቆስ፤ የአባ ኤዎስጣቴዎስ፤ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ፤ የአብርሃ አጽብሐ ነገሥትና የሌሎችም ቅዱሳን በዓላት
ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ ዘወትር እሑድ፣ እሑድ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማኅሌት በመቆም
ታላቅ በዓል ይደረጋል፡፡ የዐርባ ቀኑ ዘመነ ጽጌ (ወርኀ ጽጌ) መታሰቢያነቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለጌታችን መድኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እመቤታችን ልጇን ይዛ ከሰሎሜና ከዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ በተሰደዱ ጊዜ የደረሰባትን ጭንቅና
ውኃ ጥም፤ ግፍና እንግልት ለማስታወስና ከግብጽ ወደ ሀገሯ ናዝሬት መመለስዋን (ሚጠቷን) ለመዘከር ሲባል በዘመነ ጽጌ
የደመቀ አገልግሎት ይከናወናል፡፡ በዚህ ወቅት የሚቆመው የሰንበት ማኅሌቱ፣ መዝሙሩና ቅዳሴው እንደዚሁም የሚቀርበው
የክብር ይእቲና የዕጣነ ሞገር ቅኔ ሁሉ በዘመነ ጽጌ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡