You are on page 1of 3

ቡድንተኝነት፣ አግላይነት እና ሴረኝነት፦ የፖለቲካችን ጥመት ዋነኛ ምክንያቶች

ሀገር ህዝብ፣ መንግስትና ሉዓላዊ ገዛትን ያካተተች አካል ናት፡፡ ሀገር በውስጧ ለሚኖሩ ዜጎች በሰባዊነት
የመኖር ዋስትና የምትሰጥ መሆን ይኖርባታል፡፡ የሀገር ገዢ የሚሆነው መንግስትም በህዝብ የሚመረጥ ሆኖ
ህዝብን በፍትሃዊነት ማገለግል ይኖርበታል፡፡ የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበር ደግሞ በአግባቡ የተከለለ ግዛት ሊኖር
ይገባል፡፡ እነዚህ ሶስት ውጥኖች የሀገርን ትርጓሜ ያሟላሉ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ 110 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ብዛት በመያዝ በአፍሪቃ 2 ኛ በዓለም 12 ኛ ላይ ትገኛለች፡፡
ከ 1 ሚሊዮን በላይ የካርታ ስፋት ያላትና የዓለም ህዝብን 1.4% የምትሸፍን ናት፡፡ በብዝሃዊዋ ሀገራችን
የተለያዩ ብሄሮች፣ ሀይማኖቶችና ባህሎች ይገኛሉ፡፡ ከ 83 በላይ ብሄሮች እና ከአስር በላይ ሀያማኖቶች ያላትና
የመቻቻልና የጥንታዊነት ተምሳሌትም ናት፡፡ ከ 3’000 ዓ.ም በላይ ታሪክ እንዳላት የሚነገርላት ሀገራችን
ኢትዮጵያ በዘመኗ ልክ እንደ ሌሎች ሀገራት ዘውዳዊና ንጉሳዊ መንግስታት አሳልፋለች፡፡ ዴሞክራሲ ባለፉት 100
ዓመታት ያደገ በመሆኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዷል፡፡ ሌሎች የዓለም ሀገራት
ከፍጥረታቸው ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበሩ ሁሉ ሀገራችንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንደሚገል መርዝ
ስትፈራ ቆይታለች፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ሀገራት ለዴሞክራሲ ከሀገራችን የከፋ መሰዋትነት ከፍለዋል፡፡

ከ 150 በላይ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ዓመታት በመላቀቅ ላይ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ


ስርዓት ለመፍጠር ጥሩ የሚባል ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ለአምስት የስለላ መረብ ተጠርንፎ
ፍዳውን ሲያይ የከረመው የኢትዮጵያ ህዝብ ሌሎች አንግብጋቢ ፈተናዎች ተደቅነውበታል፡፡ በለውጡ
አመራር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ቢመስሉም ሀገራችን ያላት ውስብስብ ችግር በቀላሉ
አይፈታም፡፡ የብሄር ክፍፍሉ፣ የኢኮኖሚ ችግሩና ሥራ-ዓጥነቱ ለመንግስት ትልቅ ፈተና ሆኖበታል፡፡
ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በልጠው አንገብጋቢ መስለው የቀረቡት ፖለቲካዊ ችግሮች ልክ እንደ
ሸርተቴ ጫወታ ከእንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ተመላልሰው እየተከሰቱ ስጋት ፈጥረዋል፡፡

የሀገራችን ኢትዮጵያ ችግሮች ረጅም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት አላቸው፡፡ የባለፉት 150 ዓመታት
ችግሮች ግብር ከማስገበር፣ መሬት ከመንጠቅና የባህል ተፅዕኖ ከማሳደር ጋር ተያያዥነት አላቸው፡፡ እነዚህ
ችግሮች ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንጂ ፖለቲካዊ መሠረት የላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ
ተመስለው ቀርበው ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም አብዛኛው ዓመታት ንጉሳዊ መሠረት ያላቸው ነገስታት የሀገር
መሪ ነበሩ፡፡

በዓለም የሀገራት ታሪክ የእኩልነት፣ የፍትህና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረጉ የህዝብ ጥያቄዎች
በሥልጣን በሚፈራረቁ መንግስታት ላይ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በማደግ ላይ ባሉና ባደጉ ሀገራት ሳይቀር
በተለያየ ደረጃ ቀርበዋል፡፡ ባደጉ ሀገራት ዋና ዋና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመቀረፋቸው ፖለቲካዊ
ጥያቄዎች ዋነኛ ተቀባይነት አላቸው፡፡ በዚህም የግለሰብ መብትን መሠረት ያደረጉ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች
በሰፊው ይቀነቀናሉ፡፡ በእነዚህ ሀገራት የዴሞክራሲ ሥርዓትና ተቋማት ስለተስፋፉ ግለሰቦች መብታቸውን
ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ትግል መንገዱ ጨርቅ ነው፡፡ ባላደጉ ሀገራት ግን የዴሞክራሲ ሥርዓትና ተቋማት
ባለማደጋቸው ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን በራሳቸው ተደራጅተው ያስጠብቃሉ፡፡

ባላደጉ ሀገራት ያለው የፖለቲካ ውስብስብነት ለቡድንተኝነት፣ ለሴረኝነትና ለአግላይነት የተጋለጠ ነው፡፡
ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ መሪዎች ለተቀናቃኝ ኃይሎች ጨለማ ሲለሚደቅኑባቸው ሌላ ያልተለመደ
የፖለቲካ ባህል መስመሩን እንዲይዝ ይረዳል፡፡ ልክ አንድ ግቢ ለመግባት በዋናው መግቢያ በር ሲከለከል
አቋራጭ በሮችን ወይም ቀዳዳዎች እንደምንጠቀም ሁሉ በተዘጋው የፖለቲካ ምህዳር አቋራጭ መንገድ
ይፈለጋል፡፡ በዚህም ቡድንተኝነት፣ ሴረኝነትና አግላይነት ምፍትሄ ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡
የባለፉት 50 ዓመታት የፖለቲካ ባህላችን አንድ መልክ ያለው ነው፡፡ ጭሰኝነት ለማስቆም በሚል የተደራጁ
ሳሻሊስት ኃይሎች አየሩን የሞሉበት ጊዜ ነበር፡፡ እነዚህ ኃይሎች አንድ የጋራ ጠላት የሚሉት መደብን
መሠረት አድርገው የተነሱ ናቸው፡፡ የሀሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም የጋራ ጠላት ግን ነበራቸው፡፡ ይህ በጠላትነት
የተፈረጀው ኃይል በጊዜው ከፍተኛ ወታደራዊ አቅም ስለነበረው የስሜት መግባባት መፍጠር ነበረባቸው፡፡
ይህን ጠላት የሚሉትን መደብ ለመታገል ከየአካባቢው የተማሪዎች ትግል በየዞጉ ተቀጣጥሎ ነበር፡፡ ታጋይ
ወጣቶች ብስለት ስላልነበራቸው ጠላት የሚሉት መደብን አሳድገው ማህበረሰብን መሠረት አድርገው ነበር፡፡
ለዚህም ይህ በጠላትነት የተፈረጀው ማህበረሰብን በሌሎች ማህበረሰቦች እንዲጠላና እንዲገፋ የሚያደርጉ
ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ትግሉ እየተፋፋመ ሲሄድ የሀገሪችንን ታሪክ ማቆሸሽ ቀጠለ፡፡ የሀገሪችንን ሀገራዊ
መሠረት ከነገስታት ብቻ ጋር ማስተሳሰር ተጀመረ፡፡ አንድን ማህበረሰብ የተለየ ጠላት ማድረግ አውዱን
ተቆጣጠረው፡፡

በጠላት መተሳሰር ተቀጠለበት፡፡ የስልጣን መደቡ ይወክለዋል የተባለው ማህበረሰብ የሚያወግዙ ተግባራት
ተበራከቱ፡፡ የማህበረሰቡ ተፅዕኖን ለማስቆም በሚል የብሄር ፖለቲካ አውዱን ሞላው፡፡ አንድን ማህበረሰብ
መሠረት ያደረጉ ጥፋቶች ተከሰቱ፡፡ ይህን ማህበረሰብ ለማንኮታኮት በሚል የብሄር ቡድኖች ፈለቁ፡፡ የብሄር
ፌደራሊዝም መስመሩን ተቆናጠጠው፡፡ ይህ ፌደራሊዝም የብሄር ቡድኖችን ፈጠረ፡፡ በብሄር ስም ብቻ
የተደራጁ ቡድኖች መፈጠራቸው አንደኛው ቡድን ሌላኛውን ቡድን አሸንፎ በማዕከላዊ ስልጣን ላይ
ለመቀመጥ ሴረኝነት ብቅ ብቅ አለ፡፡ አንዱን የብሄር ቡድን ተቀባይነት ለማሳጣት ሴራ ማቀነባበር ተጀመረ፡፡
ለሴራቸው የማይመቻቸውን ቡድኖች ደግሞ ማግለል ተጨመረ፡፡ ይህ ሁናቴ ማህበራዊና ብዙሃን ሚድያዎችን
በመጠቀም ተቀናቃኙን ቡድን ከፖለቲካው ውጪ ለማድረግ ሴራ በረከት፡፡

ከሥር መሠረቱ ውድድርን መሠረት ያላደረገው የፖለቲካ ባህላችን ተቀናቃኝ የሆነን በጥላቻ ተቀባይነት
በማሳጣት የተተበተበ ነው፡፡ ይህ በጥላቻ መነቋቀር ደግሞ አንደኛው ሌላኛውን እንዲያገል በር ከፍቷል፡፡ አንዱ
ቡድን ሌላኛው ላይ ሴራ ማቀነባበር አሸናፊ ለመሆን ሁነኝ መንገድ ሆኗል፡፡ ፍኩኩርና ውድድር ከመስመር
ሳይገቡ ወጡ፡፡ ባነስ ሁኔታ የሚጠላ ቡድን አሸናፊ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠላው ደግሞ ይገለላል፡፡ በዚህም
የተቧድኖ ክንቻ ሰፊ መሠረት አገኘ፡፡

ቡድንተኛ ፖለቲከኞች ሌላውን ቡድን እንዲገለል ለማድረግ የታሪክ ትርክትና ንግርትን መሠረት ያደርጋሉ፡፡
ነባር መጥፎ የታሪክ አጋጣሚዎችን ከታሪክ ማህደር በመበርበር ወክላለው የሚሉትን ህዝቡ በድሏል
የሚባለውን መንግስት የወጣበትን ህዝብ እና ቡድን እንዲጠላ ያደርጋሉ፡፡ ይህ የታሪክ ውዝግብ ባለፉት 50
ዓመታት የተፈጠረ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዓመታትም የተነገሩና የተፃፉ ታሪኮች የፖለቲካ ሴራን መሠረት ያደረጉ
ናቸው፡፡ የቀድሞ መንግስታትን የብሄር ማንነት ሳይቀር ካላቸው ማንነት በውሸት ገልብጦ ተቀባይነት
ለማሳጣት ሴራ ሲቀነባበር ቆይቷል፡፡ እንደ ቡድን ወክላለሁ የሚሉት ህዝብ በህጋዊ መንገድ ሳይወክላቸው
በእኔ አውቅልሃለሁ ፖለቲካ ጦዞ ነበር፡፡ ህጋዊ ውክልና ያልተላበሱ ቡድኖች በማጥላላት ፖለቲካ አየሩን
ተቆጣጥረውት ነበር፡፡

ቡድንተኛ ፖለቲከኞች ለውይይት ዝግጁ አይደሉም፡፡ የያዙትን አቋም ያለማመንታት የሚቀበል ቡድን ሲኖር
ብቻ ይወያያሉ፡፡ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ቡድኖችን በስጋት ያያሉ፡፡ ወክላለሁ የሚሉትን ህዝብ ከሌላው ህዝብ
የሀሳብ ልውውጥ እንዳያደርጉ አውዱን በጥላቻና አግላይነት ይሞሉታል፡፡ አንዱ ህዝብ የሚጠላውን ህዝብ
መልካም ሀሳብ እንኳን እንዳይቀበል ልዩነት በማስፋት እርስ በራስ እንዲገላሉ ያደርጋሉ፡፡ የእነሱ ሐሳብ ብቻ
እንዲዘወተር ዝግ ምህዳር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ቡድንተኝነት አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ
ያስፈራራሉ፡፡
ሕወሓት/ኢህአዴግ የብሄር የበላይነትን ለማስቆም በሚል የብሄር ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ሁሉም
ብሄር ተደራጅቶ የራሱን ብሄር መብት እንዲያስጠብቅ በሚል ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልልን መሠረት ያደረጉ
የብሄር አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡ ብሄርን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ አደረጃጀታችን ለእነዚህ ኃይሎች
አመቺ ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት ፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የበላይ ነበረ የሚባለውን ብሄር ማጥላላት አስፈላጊ
ነበር፡፡ ለዚህም ፖሊሲ ተቀርፆ በእያንዳንዱ የፖለቲካ ስብሰባ የውሸት ትርክት በመፍጠር ይህ የበላይ ነበረ
የሚባለውን ብሄር የማጥላለት ሥራ በሰፊው ተሰራ፡፡ ትርክቶች ተደጋግመው በመነገራቸው እውነት መስለው
ነበር፡፡ ይህ የጥላቻ አውሎንፋስ አሁን ላይ ለሚታዩ ብሄርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቶች
ናቸው፡፡ ለተቧድኖ መነቋቀር ማደግ ታርሶ የተከሸነ መሬትም ሆኗል፡፡ የቡድን መንፈስ ጀግኖ እንዲወጣና
ካልተቧደኑ መብትንና ጥቅምን ማስጠበቅ አይቻልም የሚል መፈክርን ፈጥሯል፡፡ አሸናፊ የብሄር ቡድን
ለመሆን ደግሞ ሌላው ብሄር ላይ ማሴርና በሌሎች ብሄሮች ተቀናቃኝ የሚሉትን ብሄር እንዲገለል ማድረግ
ትልቅ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል፡፡

ቡድንተኝነት ፖለቲከኞች በግላቸው የቆሙለትን ዓላማ ለማስፈፀም ስይችሉ ሲቀሩ ቡድን ፈጥረው
ለማሸነፍ የሚሆን አቅም ለማሰባሰብ እንዲረዳ ነው፡፡ የቡድን መንፈስ እንዲጠነክር ደግሞ ጠላትና ስጋት
መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቡድንተኝነት ጠንካራ መሠረት ላይ መቆም አይችልም፡፡ የቡድኑ አባላት
አብዛኛው ወጣቶች ሊሆኑ ሲገባ መሪዎች ደግሞ በሳል አዛውንቶች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አባሎች ወጣት
መሆናቸው ስጋት ፈጥሮ ስሜታዊነትን ለመቀስቀስ እንዲያስችል ነው፡፡ ሴራ ለማቀነባበርና ስልት ለመቀየስ
ደግሞ በሳል አዛውንቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህ ሁናቴ ከሀገራች ሁኔታ ጋር በሰፊው ይያያዛል፡፡ ብሄርን መሠረት
ያደረጉ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በሴረኛ አዛውንቶች የሚነዱ ስሜታዊ ወጣቶች በመኖሩ ሀገራችን የስቃይ
ዘመን ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ሁኔታውም መባባሱን ቀጥሏል፡፡

You might also like