You are on page 1of 5

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ስለሚያደርጉት ግንኙነት አስመልክቶ

የወጣ መመሪያ ቁጥር 3/2002 ዓ.ም.


አንቀፅ 1 አውጪው አካል
የምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴ በተሻሻለው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነምግባር
ደንብ ቁጥር 3/2002 ዓ.ም. አንቀፅ 116 ንዑስ አንቀፅ 11 መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
አንቀፅ 2 አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ “አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ስለሚያደርጉት ግንኙነት አስመልክቶ የወጣ መመሪያ ቁጥር 3/
2002 ዓ.ም.” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
አንቀፅ 3 ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፦
1. "ምክር ቤት" ማለት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ነው፡፡

2. "አፈጉባኤ" ማለት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ነው፡፡

3. "ደንብ" ማለት የተሻሻለው የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነምግባር ደንብ ቁጥር
3/2002 ነው፡፡

4. “አባል” የምክር ቤቱ አባል ነው፡፡

5. “መራጮች ወይም መራጭ ህዝብ” ማለት አንድ አባል በተመረጠበት የምርጫ ክልል ውስጥ የሚኖሩ
ዜጐች ናቸው፡፡

6. “የፓርቲ ተጠሪዎች” ማለት በምክር ቤቱ ውስጥ 10 እና ከዚያ በላይ መቀመጫ ያላቸው የፖሊተካ
ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ውስጥ የፓርቲያቸውን ስራዎች እንዲያስተባብሩ የሚወክሏቸው የምክር ቤቱ
አባል የሆኑ አባሎቻቸው ናቸው።
7. "ሰው" ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡

187
አንቀጽ 4. የጾታ አገላለጽ
በዚህ መመሪያ ውስጥ በወንድ ጾታ የተደነገገው የሴትንም ጾታ ያካትታል።

አንቀጽ 5. አተረጓጐም
በዚህ መመሪያ ለሚፈጠር የሕግ አተረጓጐም ክፍተት በደንቡ አንቀጽ 3 መሠረት ሊሞላ ይችላል፡፡
አንቀጽ 6. የተፈፃሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ ማንኛውም አባል ከመራጩ ህዝብ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል።
አንቀፅ 7 ዓላማ
የዚህ መመሪያ ዓላማ ፡-
1. አባላት ከመራጭ ህዝባቸው ጋር በየጊዜው በሚያደርጉት ግንኙነት ተጠያቂነትን እና ግልፅነትን
የሚያዳብሩበትን እንዲሁም በምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራቸውን የሚያጠናክሩበትን ፣ እና
2. አባላት በመራጭ ህዝባቸው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡበትን፣ አሠራር በግልፅ መደንገግ
ነው፡፡
አንቀፅ 8 አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ስለሚገናኙባቸው ጉዳዮች
1. ማንኛውም አባል በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከመራጩ ህዝቡ ጋር ተገናኝቶ ሊወያይ ይችላል።
2. የንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አባላት በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ ከመራጮቻቸው ጋር
ተገናኝተው ሊወያዩ ይችላሉ።
ሀ. ምክር ቤቱ በእቅድ በያዘውና ከመራጭ ህዝብ ጋር በሚሰራ ስራ፣
ለ. ምክር ቤቱ ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ፣
ሐ. ከመራጭ ህዝቡ በሚነሳ ጥያቄ ወይም አስተያየት ዙሪያ፣
መ. በአስተዳደሩ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደና ልማት እቅዶች አተገባበርን አስመልክቶ፣

አንቀፅ 9 አባላት ከመራጭ ህዝባቸው ጋር ስለሚገናኙበት ጊዜ


1. ማንኛውም አባል በማንኛውም ጊዜ ከመራጩ ህዝብ ጋር ተገናኝቶ ሊወያይ ይችላል።
2. የንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነበት አጀንዳ ላይ
አባላት ከህዝብ ጋር ተገናኝተውና ሃሳብ አሰባስበው እንዲያቀርቡለት ኘሮግራም ሊያዘጋጅ ይችላል፡፡
አንቀፅ 10 አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ስለሚገናኙበት ዘዴ
1. አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚከተለውን ዘዴ ሊጠቀሙ ይችላሉ።
ሀ. በየምርጫ ክልላቸው በአካል በመገኘት እና እንዳመቺነቱ መራጩን ህዝብ በመሰብሰብ፣
ለ. በስልክ፣ በፋክስ ወይም በድህረ-ገጽ በመላላክ፣ ወይም
ሐ. በሌላ በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ከመራጭ ህዝባቸው ጋር ሊገናኙ ይችላሉ።
2. የንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዱ አባል መንግሥታዊ አካላትን እና ልዩ ልዩ
የህዝብ አደረጃጀቶችን በማግኘት ከህዝብ ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል፡፡

188
3. አባላት ከመራጭ ህዝባቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥቆማዎችን ወይም ሙያዊ
አስተያየቶችን ሊያሰባስቡ ይችላቡ፡፡
አንቀፅ 11 ከመራጭ ከህዝብ በተነሱ ጥያቄዎች ወይም  አስተያየቶች ላይ አባላት መከተል ስለሚገባቸው
አካሄድ
1.አባላት ከመራጮቻቸው ጋር የሚያደርጉት ውይይት ትኩረቱ በአስተዳደሩ የሥልጣን ክልል ስር
የሚወድቅ መሆን አለበት፡፡
2.ከላይ በንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም አባል ከአስተዳደሩ የሥልጣን ክልል
ውጪ የሆነ ጉዳይ በመራጩ ህዝብ ሲቀርብለት በየደረጃው ለሚገኝ አስፈፃሚ አካል በመላክ
እንዲፈታ ሊያደርግ ይችላል፡፡
3. ማንኛውም አባል ከመራጩ ህዝብ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ከመራጩ ህዝብ የሚቀርብለት ጥያቄ
በፌደራሉ መንግስት ወይም በአስተዳደሩ ስልጣን ስር የሚወድቅ ስለመሆኑ ለይቶ መመዝገብ
ይኖርበታል።
4.አንድ አባል ከመራጩ ህዝብ የቀረበለት ጥያቄ በአስተዳደሩ ስልጣን ክልል የሚወድቅ ከሆነ ፡-
ሀ. በአስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ምን እየሰራ እንዳለ መግለጽ አለበት፣
ለ. እንዲጣራ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በጥቆማነት ሊያቀርብ ይችላል፣
ሐ. የአስተዳደሩ አስፈጻሚ አካል ሪፖርት ሲያቀርብ ጥያቄ በማቅረብ መልስ እንዲያገኝ ሊያደርግ
ይችላል። ወይም
መ. ለፖለቲካ ፓርቲው ተጠሪ በሪፖርት ሊያሳውቅ ይችላል።
5. የንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ አባል ከመራጩ ህዝብ የቀረበለት ጥያቄ በፌደራል
ስልጣን ስር የሚወድቅ ከሆነ የፌደራሉ መንግስት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ምን እየሰራ እንዳለ ለመግለጽ ወይም
ጥያቄው ለፌደራሉ እንዲላክ ለአፈጉባኤው ለማቅረብ ይችላል።
አንቀፅ 12 መራጭ ህዝቡን በማነጋገር ሂደት አባላት የሚከተሉት መርህ
1. መንኛውም አባል ከመራጭ ህዝቡ ጋር በሚገናኝበት በማንኛውም ጊዜ የአባላት ስነምግባር መመሪያ
ቁጥር 1/2002 ድንጋጌን በማክበር መሆን አለበት።
2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ አባል፡-
ሀ. የቀበሌ አስተዳደሮችን ስልጣን ማክበር እና ማስከበር ይኖርበታል።
ለ. ለመራጭ ህዝቡ መፈጸም የማይችለውን እፈጽማለሁ ማለት ወይም የሀሰት ቃል መግባት
የለበትም።
ሐ. በምርጫ ክልሉ የሚኖሩ ነዋሪዎችን በእኩል የማስተናገድና የማገልገል ኃላፊነት አለበት፡፡
መ. መራጭ ህዝቡ የሚያቀርብለትን ማንኛውንም ሀሳብ ማክበር አለበት፡፡
3.ማንኛውም አባል ፡-
ሀ. ምክር ቤቱ ባዘጋጀው አጀንዳ ላይ መራጩን ህዝብ ሲያነጋግር ምክር ቤቱ ካስቀመጠው አቅጣጫ
ውጪ ተንቀሳቅሶ ሲገኝ ፣ወይም
ለ. ማንኛውም ህዝቡን በሚያነጋግርበት ጊዜ በንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገውን የጣሰ ተግባር ሲፈጽም፣
ምክር ቤቱ በሚቀርብለት ጥቆማ ወይም ሪፖርት ላይ ተመስርቶ አስፈላጊውን ውሳኔ ያሳልፋል።

189
አንቀፅ 13 ሪፖርት ስለማቅረብ
1. ማንኛውም አባል በየጊዜው ከመራጩ ህዝብ ጋር በአካል በመገናኘት ያገኘውን ጥያቄ ወይም አስተያየት
አስመልክቶ ዝርዝር ሪፖርት በማዘጋጀት አባል ለሆነበት የፖለቲካ ፓርቲ ሊያቀርብ ይችላል።
2. አንድ አባል በዚህ አንቀጽ መሠረት የሚያቀርበው ሪፖርት በዋናነት፡-
ሀ. መራጭ ህዝቡን ያነጋገረበትን ምርጫ ክልል ወይም ልዩ ቦታ ስም እና ቀን፣
ለ. ያነጋገረውን መራጭ ህዝብ ብዛት፣
ሐ. ከመራጭ ህዝቡ የቀረቡ ጥያቀዎችን ወይም አስተያየቶችን ዝርዝር፣
መ. የአባሉን አጠቃላይ አስተያየት ፣ስምና ፊርማ፣
የያዘ መሆን አለበት።
3. እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሠረት ከአባላቱ የደረሰውን ሪፖርት በመጭመቅ እና
ምክር ቤቱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመለየት ለአፈጉባኤው ያቀርባል።
4. አባሉ በዚህ አንቀጽ መሠረት ያዘጋጀው ሪፖርት በአስተዳደሩ ስልጣን ስር ባሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን
አለበት።
5. የንዑስ ቀንቀጽ 2 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም በምክር ቤቱ ተግባር ተሰጥቶት መራጭ ህዝቡን
ያነጋገረ አባል የሚያቀርበው ሪፖርት ፡-
ሀ. መራጭ ህዝቡን ያገኘበትን ዘዴ፣
ለ. ከውይይቱ የተገኙ ዋናዋና ጭብጦች፣
ሐ. መራጭ ህዝቡን በጉዳዩ ላይ በማነጋገር ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎች፣
መ. ህዝቡን ለማወያየት ሂደት ለስራ የሚውል ገንዘብ ወይም ሌላ ቁሳቁስ ተመድቦ ከሆነ የዚህን
አጠቃቀም፣
ሠ. ምክር ቤቱ መራጩን ህዝብ ለማወያየት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ስለመከተሉ በተጨማሪነት
ማካተት አለበት።
አንቀፅ 14 የምክር ቤቱ ኃላፊነት
1. አባላት ትብብር ሲጠይቁ ከመራጮቻቸው ጋር የመገናኘት ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ
በምርጫ አካባቢያቸው ትብብር የሚያገኙበትን ሁኔታ ምክር ቤቱ ያመቻቻል።
2. እንዳስፈላጊነቱ አባላት በምክር ቤቱ የታቀደን ሥራ ከመራጭ ህዝባቸው ጋር እንዲወያዩ ሲያደርግ
ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ምክር ቤቱ ከምርጫ ክልላቸው ትብብር የሚያገኙበትን
ሁኔታ ያመቻቻል፡፡
3. አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩ እና ሪፖርት እንዲያቀርቡ አጀንዳ ያዘጋጀው
ምክር ቤቱ በሆነ ጊዜ ምክር ቤቱ ከአጀንዳው ጋር የተያያዙ ለስራ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ያሟላል።
4. አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ለመገናኘት ከምክር ቤቱ ያስፈልገናል የሚሉትን መረጃ ምክር ቤቱ
በወቅቱ እንዲደርሳቸው ያደርጋል።
5. አባላት በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ምክር ቤቱ ባዘጋጀው አጀንዳ ዙሪያ መራጭ ህዝባቸውን ለማነጋገር
ተሠማርተው ከሆነ ምክር ቤቱ ፡-

190
ሀ. ህዝቡ የሚወያይበትን ጉዳይ ፣
ለ. የጉዳዩን ዓላማ፣
ሐ. ጉዳዩን ለማወያየት የሚያስፈልገውን የጊዜ ገደብ ፣
መ. ከህዝብ ውይይት የተገኘውን ውጤት አባሉ ሪፖርት የሚያቀርብበትን ጊዜ፣
ወስኖ ዝርዝር የአሰራር እቅድ ለአባላት ያዘጋጃል።
6. ምክር ቤቱ አባላት ከመራጭ ህዝባቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ የሚያቀርቡትን አጠቃላይ ጭማቂ ሪፖርት
በመቀበል፡-
ሀ. እንዳስፈላጊነቱ አባላት ከመራጭ ህዝባቸው ላመጡት ጥያቄ መፍትሔ ይሰጣል፡፡
ለ. እንደአግባብነቱ ለምክር ቤቱ ተግባራት በግብአትነት ይጠቀምበታል፡፡
ሐ. በምክር ቤቱ የተላለፈ ውሣኔ ሲኖርም አፈፃፀሙን ይከታተላል፡፡
7. አፈጉባኤው ከላይ በንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የደረሰውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን ስልቶች
ሊጠቀም ይችላል።
ሀ. ጉዳዩን ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በመምራት ተጣርቶ እንዲቀርብ ሊያደርግ ይችላል።
ለ. አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው መንግስታዊ አካሉ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያቀርብ ሊያደርገው ይችላል።
ሐ. ጉዳዩን ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል ወይም የአስተዳደር እርከን በመላክ መልስ እንዲሰጥበት
ሊያደርግይችላል።
አንቀጽ 15 የተሻሩ መመሪያዎች እና አሠራሮች

ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም አሠራር በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ
ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

አንቀጽ 16 መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ በምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ከፀደቀበት ከሰኔ 13 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

አብዱልአዚዝ አህመድ

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት

አፈጉባኤ

191

You might also like