You are on page 1of 5

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት

ደቡብ ምዕራብ ነጋሪት ጋዜጣ


DEBUB MEERAB NEGARIT GAZETA
OF THE SOUTHWEST ETHIOPIA PEOPLES’ REGIONAL
STATE __________th Year No __________
__________ዓመት ቁጥ_________
__________th ______/2022
__________ ቀን_________/2014

ማውጫ

አዋጅ ቁጥር_______2014 ዓ.ም

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች


ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር_____/2014_______ገጽ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ አዋጅ
ቁጥር______/2014

መግቢያ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 6 የክልሉ መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች
እንደሚኖሩት እና የከተሞች አሰያየም እና አደረጃጀት በህግ እንደሚወሰን በክልሉ ሕገ መንግስት
በመደንገጉ፤

ከአንድ በላይ ከተሞች በክልሉ ውስጥ ለመንግስት መቀመጫነት በመሰየም ማደራጀቱ ሕዝቡ በአደረጃጀቱ
ላይ ሙሉ እምነት ኖሮት ለፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር
የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ በመታመኑ፤

የአገልግሎት ተደራሽነትን ከአገልግሎት ፈላጊ ህዝብ ስፋትና ሌሎች መመዘኛዎችን በግልጽ መስፈርት
በመመልከት ፍትሐዊ የተቋማት ስርጭት እንዲኖር በማድረግ በክልሉ ብዝሃ ከተሞች የመሰረተ ልማትና
የመንግስት አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በፍትሐዊነት መልማትንና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ
በማስፈለጉ፤

1
ክልላዊ ተቋማቱ የአካባቢዎችን ፀጋ በማጎልበት እና የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ክልሉ ከራሱ አልፎ
ለሀገር እድገትና ብልጽግና አለኝታ በመሆን የጎላ ድርሻ ለማበርከት በሚያስችል መልኩ የክልሉን የመንግስት
አካላት በአገልግሎት ፈላጊዉ ሕዝብ ዘንድ እንግልት በማይፈጥር መልኩና የአካባቢዎችን ጸጋዎችንና
የመልማት አቅምን ከግምት ውስጥ በሚያስገባ መልኩ በተለዩ የክልል ዋና ከተሞችና በዞን ዋና ከተሞች
መደልደል አስፈላጊነቱ በመታመኑ፣

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህገ መንግስት አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) መሠረት
የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ
አዋጅ ______/2014” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ
1. ክልል፤ ማለት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ነው፡፡
2. ህገ መንግስት፤ ማለት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህገ መንግስት ነው፡፡
3. ክልሉ መንግስት የስልጣን አካላት ማለት የክልሉ የህግ አዉጪ፣ ህግ አስፈጻሚ እና ህግ ተርጓሚ
አካላት ናቸዉ፡፡
4. ብዝሃ ዋና ከተሞች፤ ማለት እኩል እዉቅና ያላቸዉ የክልል መንግስት የስልጣን አካላት
ተደልድለው መንግስታዊ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው አራቱ የክልል ዋና ከተሞች ማለት ነው፡፡
5. ቢሮ፤ በክልሉ አስፈፃሚ አካት ስልጣንና ኃላፊነት ለመደንገግ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 4/2014
ክፍል ሁለት አንቀጽ 4 መሠረት የመስተዳድር ምክር ቤት አባል ሆነው የተቋቋሙ የመንግስት
መስሪያ ቤቶች ማለት ነዉ፡፡
6. ተጠሪ ተቋማት፤ ማለት በክልሉ አስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመደንገግ በወጣዉ አዋጅ
ቁጥር 4/2014 አንቀጽ 40 ላይ የተዘረዘሩና ለመስተዳድር ምክር ቤት አባል ለሆኑ ቢሮች
ወይም በቀጥታ ለርዕሰ መስተዳድሩ ተጠሪ የሆኑ ወይም በሌሎች አግባቢነት ባላቸዉ ሕጎች
ለክልሉ ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ፣ ኢንስቲትዩቶች፣ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶች፣ ኤጀንሲዎች፣
ኮሚሽኖች፣ ጽህፈት ቤቶች፣ የስልጠናና ምርምር ማዕከላትን፣ ኮርፖሬሽኖችንና ሌሎች የልማት
ድርጅቶችን ያካትታል፡፡
3. የተፈጻሚነት ወሰን
በክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞች እና በዋና ከተማነት ባልተካተቱ የዞን ዋና ከተሞች ላይ ተፈጻሚ
ይሆናል፡፡
4. የጾታ አገላለፅ፣
በዚህ አዋጅ በወንድ ፆታ የተገለፀው የሴት ፆታንም ያካትታል፡፡

2
ክፍል ሁለት

አደረጃጀትና አሠራር

5. መቋቋም
1. በክልሉ የሚከተሉት ብዝሃ ዋና ከተሞች በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

ሀ. ቦንጋ ከተማ የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳደር መቀመጫ ፣

ለ. ታርጫ ከተማ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ፣

ሐ. ሚዛን አማን ከተማ የክልሉ ዳኝነት አካል መቀመጫ፣

መ. ቴፒ ከተማ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫ ናቸወ፡፡

2. በአንቀጽ 5(1) ስር የተጠቀሱት ብዝሃ ዋና ከተሞች የተዘረዘሩ የመንግስት አካላት


እንደተጠበቁ ሆኖ የክልሉ መንግሥት አስፈፃሚ ተቋማት የተገልጋዩን ሕዝብ መልክዓ
ምድራዊ ስርጭት፣ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ እና የመልማት እምቅ
አቅም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መስተዳደር ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት
ይደለደላል፡፡
3. በአንቀጽ 5 (1) እና (2) የተመላከተዉ እንደተጠበቀ ሆኖ የጀሙና አመያ ከተሞች በተጠሪ
ተቋማት ድልድል ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ዝርዝሩ በደንብ የሚወሰን ይሆናል፡፡
6. የተደለደሉ ተቋማት ለስራ አመቺነት ሲባል ስለማሻሻል

በተመረጡ የክልሉ ዋና እና በዞን ከተሞች ተቋማት ከተደለደሉ በኋላ ከአሰራር አንጻር ተሞክሮ ለስራ
ዉጤታማነት አመቺ ያልሆነ እንደሆነ በመስተዳድር ምክር ቤቱ ማሻሻያ ሊደረግ ይችላል፡፡

7. በሂደት ሊደራጁ የሚችሉ እና የሚታጠፉ ተቋማትን በተመለከተ፣

በአንቀጽ 5 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ መንግስት ስልጣን አካላት ዉስጥ የሚደራጁ አዳዲስ
መስሪያ ቤቶችን እና ከአንድ በላይ ቢሮ ደረጃ ተቋቁሞ ስራ ላይ የነበሩ ተቋማት ለስራ አመቺነት ወደ
አንድ መታጠፍ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ በጥናት ላይ ተመስርቶ በብዝሃ ዋና ከተሞችና በዞኖች
ዋና ከተሞች የመደልደል ስልጣኑ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ይሆናል፡፡

8. የክልሉ ከተሞችና የተደለደሉ ተቋማት እርስ በርሳቸዉ ሊኖራቸዉ ስለሚገባ ግንኙነት፣


1. ተቋማት በተመደቡባቸዉ ዋና ከተሞች ተልዕኳቸዉን የሚተገብሩ ሆኖ ስብሰባዎች፣ ስልጠናዎችና
ኮንፍራንሶችን እንደአመቺነቱ በተለያዩ የክልሉ ከተማዎች አፈራርቀዉ ማካሔድ ይችላሉ፡፡
2. ተመጋጋቢ አገልግሎቶችን የሚሠጡ ተቋማት በተመሳሳይ ወይም በተቀራረቡ ከተሞች ይዘረጋሉ፡፡
3. የመስተዳድር ምከር ቤቱ ተቋማትን አራርቆ መመደብ አስገዳጅ በሚሆንበት ጊዜ የተገልጋዩን
እንግልት በሚቀንስና አገልግሎት በሚያቀላጥፍ መልኩ አሰራሮችን መዘርጋት አለበት፡፡

3
9. የክልሉ ከተሞች ፍትሐዊ ልማትና እድገትን በተመለከተ፣
ለክልሉ መቀመጫ ከተማነት በተመረጡ እና በሌሎች የዞን ዋና ከተሞች ፍትሐዊና ተመጣጣኝ
ልማት እንዲኖር የክልሉ መንግስት የአሠራር ማዕቀፍ በመዘርጋት ይሠራል፣አፈጻጸሙንም
ይከታተላል፡፡
10. በብዝሐ ዋና ከተሞች የሚደለደሉ ተቋማት የስራ የግንኙነት ስርዓት፣
1. በብዝሃ ዋና ከተሞች የተደለደሉ የአስፈጻሚ አካላት ተጠሪነታቸው የአስፈፃሚ አካት ስልጣንና
ተግባር ለመደንገግ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 4/2014 አንቀጽ 41 መሰረት ለርዕሰ መስተዳድሩና
ለመስተዳድር ምክር ቤት ይሆናል፡፡
2. አንቀጽ 10(1) እንደተጠበቀ ሆኖ ለስራ ክትትል እንዲያመች በብዝሃ ዋና ከተሞች ደረጃ
ከተደለደሉ የመስተዳደር ምክር ቤት አባል ተቋማት ኃላፊዎች ለስራ ቅልጥፍና ሲባል ተቋማትን
የሚያስተባብር የስራ ኃላፊ ርዕሰ መስተዳድሩ ሊወክል ይችላል፡፡
3. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በብዝሃ ዋና ከተሞች የተደለደሉ
ተቋማት የክልል ምክር ቤት ወይም የዳኝነት ክፍሉ ወይም ብሔረሰቦች ምክር ቤት እና ሌሎች
ከመስተዳደር ምክር ቤት ውጪ የሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት በህግ ተጠሪ ለሆኑባቸው አካላት
ተጠሪ ሆነው ይሰራሉ፡፡
4. የመስተዳድር ምክር ቤቱ አባላት እንደአስፈላጊነቱ በአካልና በተለያዩ ቴክኖሎጂ አማራጮች
መደበኛና አስቸኳይ ጊዜ ሰብሰባዎችን፣ የምክክርና ዉይይት መድረኮችን ያካሂዳሉ፣ የጋራ
ወሳኔዎችንም ያስተላልፋሉ፡፡
11. ብዝሃ ዋና ከተሞች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት
1. በብዝሃ ዋና ከተማነት የተመረጡ ከተሞች ተጠሪነታቸው ላሉባቸዉ የዞን አስተዳደር ይሆናል፡፡
2. በብዝሃ ዋና ከተሞች የተደለደሉ የክልል ተቋማት ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግሥት ይሆናል፡፡
3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ መንግሰት ከተማውን
ለማስፋፋት፣ ለክልላዊ ፕሮግራሞች እና ለልዩ ልዩ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሲፈለግ የዞኑ ወይም
የከተማዉ አስተዳደር አስፈላጊውን የመሬት አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎችን ያደርጋል፡፡
4. ብዝሐ ዋና ከተማዉ ያለበት ዞን ወይም የከተማዉ አስተዳደር ለክልሉ ተቋማትና ሠራተኞች
አስፈላጊዉን ማሕበራዊ አገልግሎቶችንና መሰረተ ልማትን ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በእኩል
እንዲጠቀሙ ያመቻቻል፡፡
5. የክልል ብዝሃ ዋና ከተሞች ጸጥታና ደህንነት ተግባራትን በተመለከተ የክልሉ ጸጥታ ተቋም
ከዞኑና በተዋርድ ካሉ ከራሱ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት የመተግበር የጋራ ኃላፊነት አለበት፡፡
ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
ክፍል ሶስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
12. ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣን
1. ይህንን አዋጅ ለማስፈፀም የመስተዳድር ምክር ቤት ደንብ ያወጣል፡፡
2. ይህን አዋጅ ተከትሎ የሚወጣውን ደንብ ለማስፈፀም የመስተዳድር ምክር ቤት መመሪያ
ሊያወጣ ይችላል፡፡

4
13. ተፈጻሚነት የሌላቸው ህጎች
በዚህ አዋጅ በተደነገጉ ጉዳዮች ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ህግ ወይም ልማዳዊ አሰራር
ተፈፃሚነት የለውም፡፡
14. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በክልል ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ቦንጋ ከተማ
ነሐሴ____ቀን____/2014 ዓ.ም
ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

You might also like