You are on page 1of 11

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ

የእምነት ተቋማት የአምልኮና የመቃብር ቦታ


አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 15/2006

መጋቢት 2006
ኢ/ከ/ል/ቢሮ
ባህር ዳር
መመሪያ ቁጥር 15/2006 ዓ.ም
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የእምነት ተቋማት
የአምልኮና የመቃብር ቦታ አሰጣጥ መመሪያ
የከተሞችን የመሬት ሃብት አጠቃቀም ከብክነት የጸዳ በማድረግ ውስን የሆነውን ይህንኑ
ሀብት በቁጠባና በተፈቀደው ፕላን መሰረት መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ፣

ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ለማምለኪያ ያውሉት ዘንድ ለእምነት ተቋማት የሚሰጣቸው


እጅግ ሰፋፊና ከክፍያ ነጻ የሆነ ቦታ አጠቃቀም በየከተሞቹ የፋይናንስ አቅም ላይ
ይፈጥር የነበረውን ጫና ለመቀነስ ይቻል ዘንድ አሰጣጡን ከከተማ ቦታ ሊዝ አዋጅ
ቁጥር 721/2004 ዓ.ም አንቀጽ /20/ ንኡስ አንቀጽ /7/ ድንጋጌ ጋር የተጣጣመ መመሪያ
ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

የሃይማኖት ተቋማት ያላቸውን ውስብስብ ጠባይ ግምት ውስጥ በማስገባት


የሚጠቀሙበትን የአምልኮ ስፍራ መስተንግዶ አግባብ፣ የቦታ መጠንና ሌሎች ሌሎች
ተዛማጅ ጉዳዮችን ግልጽና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መወሰንና ከነዚሁ ጥያቄዎች ጋር
ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት ተገቢ
በመሆኑ፣

በተሸሻለው የብሔራዊ ክልሉ ህገ-መንግስት አንቀጽ /27/ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሰረት
የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት የተከበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ
የእምነት ተቋማት የአምልኮ ቦታ ጥያቄ እየተበራከተ በመምጣቱ በክልሉ ከተሞች ውስጥ
አሁን በተዘበራረቀ መንገድ እየተሰጠ ያለውን የአምልኮ እና የመቃብር ቦታ አሰጣጥ
ወጥነት ባለው መንገድ ማስተናገድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

የከተማን ቦታ በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004ዓ.ም አንቀጽ /12/ ንዑስ
አንቀጽ /1/ ፊደል ተራ ቁጥር /መ/ እና በተሻሻለዉ የከተማ ቦታ ሊዝ ይዞታ ማስተዳደሪያ
ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 103/2004 ዓ.ም አንቀጽ /23/ ንዑስ አንቀጽ
/4/ መሰረት የእምነት ተቋማት ቦታ አሰጣጥ የክልሉ መስተዳድር ም/ቤት በሚሰጠው ውሳኔ
መሰረት እንደሚስተናገድ አስቀድሞ የተደነገገ በመሆኑ፤
የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ-መንግስት
አንቀጽ /58/ ንዑስ አንቀጽ /7/ እና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር
721/2004 ዓ.ም አንቀጽ /33/ ንዑስ አንቀጽ /2/ ስር በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን
መመሪያ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ፡
ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ “የእምነት ተቋማት የአምልኮ እና የመቃብር ቦታ አሰጣጥ ክልል
መስተዳድር ምክር ቤት መመሪያ ቁጥር 15/2006ዓ.ም ”ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-

1) “አዋጅ” ማለት የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም

ነው፡፡
2) “ከተማ” ማለት ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመበት ወይም ሁለት ሺህ ወይም ከዚያ በላይ
የህዝብ ቁጥር ያለውና ከዚህ ውስጥ ከሃምሳ በመቶ (ከ50%) በላይ የሚሆነው ነዋሪ
ከግብርና ውጭ በሆነ ሥራ ላይ የተሰማራ ሆኖ የሚገኝበት አካባቢ ነው፤
3) "የአምልኮ ቦታ" ማለት ህጋዊ እውቅና ባገኙ የክልሉ ከተሞች ውስጥ የሚገኝ ስፍራ
ሆኖ አግባብ ባለው ከተማ ፕላን መሰረት ለአምልኮ አገልግሎት እየዋለ ያለ፣
የተመደበ ወይም የሚመደብ ቦታ ነው ፤
4) " የሃይማኖት ተቋም" ማለት የአምልኮና የእምነት አገልገሎቶችን ለማካሄድ የተቋቋመ
ማናቸውም አካል ነው ፤
5) " የመቃብር ቦታ " ማለት በአንድ ከተማ የእድገት ፕላን ላይ ለቀብር አገልግሎት
የተመደበ ወይም ለዚሁ አላማ በመዋል ላይ ያለ ማናቸውም ስፍራ ነው ፤
6) “አግባብ ያለው አካል’’ ማለት የከተማ መሬትን ለማስተዳደር እና ለማልማት በህግ ስልጣን
የተሰጠው አካል ነዉ፤
7) “ምክር ቤት’’ ማለት የክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ነው፤
8) "ቢሮ" ማለት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ነው፡፡

3. የተፈፃሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

4. ዓላማ

ይህ መመሪያ በተለያዩ የእምነት ተቋማት የሚቀርቡ የአምልኮና የመቃብር ቦታ ጥያቄዎችን


ግልጽነት፣ ፍትሃዊነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መንገድ የማስተናገድና የመምራት አላማ
ይኖረዋል ፡፡
ክፍል ሁለት

የአምልኮና የመቃብር ቦታ ጥያቄ ስለሚቀርብበት፣ ስለሚጣራበትና ስለሚረጋገጥበት ሁኔታ

5. ስለአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ጥያቄ አቀራረብ

የአምልኮ ቦታ መጠየቂያ ማመልከቻ በዚህ መመሪያ መሰረት በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ


ለከተማው ኢንዱስትሪ ልማትና ከተማ አገልግሎት መምሪያ፣ በማዘጋጃ ቤት ከተሞች ሲሆን
ለከተማው ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት፣ በታዳጊ ከተሞች ውስጥ ደግሞ ለስራ አስኪያጁ ጽ/ቤት
ሊቀርብ ይችላል ፡፡ ይኸው የቦታ ጥያቄ ከእምነት ተቋማት በኩል ሲቀርብ ከዚህ በታች
የተዘረዘሩት ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት ይኖርባቸዋል፡-

1) ነባር የአምልኮ ተቋማትን ሳይጨምር ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ


የእምነቱ ተከታዮች ብዛት በእምነት ተቋሙ ማህተም ተረጋግጦ በሚከተለው ምድብ
መቅረብ ይኖርበታል፡-

ሀ/ በሜትሮፖሊታን ከተሞች ዝቅተኛው ቁጥር1000 ፤

ለ/ በመካከለኛ ከተሞች ዝቅተኛው ቁጥር 600 ፤ እና


ሐ/ በማዘጋጃ ቤት፣ በታዳጊና በአነስተኛ ከተሞች ዝቅተኛው ቁጥር 100፡፡
2) ከዚህ በላይ በንዑስ አንቀጽ /1/ ስር የተወሰነው ቢኖርም የእምነት እና የመቃብር
ቦታ ጥያቄው የቀረበው ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ እንደሆነ ከ18 አመት በላይ
የሆናቸው የእምነቱ ተከታዮች ብዛት እንደሚከተለው ይሆናል፡-
ሀ. በሜትሮፖሊታን ከተሞች ዝቅተኛው ቁጥር 200፤
ለ. በመካከለኛ ከተሞች ዝቅተኛው ቁጥር 150 እና
ሐ. በሌሎች የከተማ ደረጃዎች ዝቅተኛው ቁጥር 100፡፡
3) ጥያቄውን ያቀረበው የእምነት ተቋም በህጋዊነት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ስለመሆኑ
የምዝገባ ሰርቲፊኬት ኮፒ ተያይዞ መቅረብ ይኖርበታል፤
4) ተቋሙን እና አማኙን በቋሚነት በሚመሩት አመራሮች የተፈረመ ቃለጉባኤ ቅጅ
መያዝ ይኖርበታል፤

5) የእምነቱ አመራሮችና ተከታዮች ገንዘባቸዉን እና ጉልበታቸዉን በማስተባበር

ህንጻዉን በዉሉ መሰረት በአምስትዓመት ጊዜ ዉስጥ ለመገንባት እና


ለማጠናቀቅ የሚችሉ ለመሆኑ በደብዳቤ መረጋገጥ ይኖርበታል፤

6) ይየእምነቱ ተከታዮች ለሚሰጣቸው ቦታ የሚጠበቅባቸውን የካሳ ክፍያ በአንድ

ጊዜ አጠቃለው ለመክፈል ዝግጁ ስለመሆናቸው በፁሁፍ መስማማት ኖርባቸዋል


7) የእምነቱ ተከታዮች በከተማዉ ውስጥ የአምልኮ ማከናወኛ የሌላቸው ወይም


የሚወከሉበት የእምነት ተቋም በአቅራቢያው የራሱ የሆነ ይዞታ የሌለው መሆኑ
አስቀድሞ መረጋገጥ ይኖርበታል፤

8) በዚህ መመሪያ መሰረት አገልግሎት የሚሰጥ የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ፡-

ሀ/ በሜትሮፖሊታን እና በመካከለኛ ከተሞች ውስጥ ሲሆን በተመሳሳይ


የእምነት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ከ2 ኪሎ ሜትር እና፤

ለ/ በሌሎች ከተሞች ውስጥ ሲሆን ደግሞ በተመሳሳይ የእምነት ተቋማት


መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ከ1.5 ኪሎ ሜትር ያላነሰ መሆን
ይኖርበታል፡፡
6. ለአምልኮ ወይም ለመቃብር የሚዉል ቦታ ምደባ ጥያቄን ስለማጣራት፣ስለማረጋገጥ
እና ስለመመዝገብ፣

1) የአምልኮ ወይም የመቃብር ቦታ ጥያቄ የቀረበለት ከዚህ በላይ በአንቀጽ /5/


የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠና ከመዘገበ በኋላ ጉዳዩ
ይደገፍ እንደሆነ ለማወቅ እንደተገቢነቱ የከንቲባ ኮሚቴውን ወይም የወረዳውን አስተዳደር ምክር ቤት በፁሁፍ
ይጠይቃል፤
2) ቀድሞውኑ ለአምልኮና ለመቃብር የተመደበ ቦታ በከተማው መሪ ፕላን ላይ የሌለ

መሆኑ በታወቀ ጊዜ የቦታ ጥናትና ዝግጅት እንዲከናወን ይህንኑ ተግባር


ለሚፈጽሙ አከላት በደብዳቤ ሲያሳውቅ እንደተገቢነቱ የከንቲባ ኮሚቴው ወይም
የወረዳ አስተዳደር ም/ቤቱ በግልባጭ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፤
3)በሜትሮፖሊታን ከተሞች ውስጥ የሚቀርቡ የአምልኮና የመቃብር ቦታ ጥያቄዎች

ተፈላጊውን መስፈርት ስለሟሟላታቸው በዚህ መመሪያ መሰረትየሚያጣራውና


የሚያረጋግጠው ቢሮው ይሆናል፤
4) በሌሎች ከተሞች ውስጥ የሚቀርቡት ጥያቄዎች በየዞኑ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት
መምሪያዎች አማካኝነት የሚጣሩ ሆኖ ውሳኔ የሚሰጠው ግን ትክክለኝነታቸው ለቢሮው
ቀርቦ ከተረጋገጠ በኋላ ይሆናል፡፡
7. ለአምልኮ እና ለመቃብር አገልግሎት የሚዉልን የከተማ ቦታ ዝግጅትን በእቅድ
ስለመያዝ
1) አግባብ ያለዉ አካል ከእምነት ተቋማቱ የሚቀርብለትን ጥያቄ በማጥራትና
የከተማውን ፕላን መሰረት በማድረግ አመታዊ እቅድ ይይዛል፤ይኸውም፡-
ሀ/ የአምልኮና የመቃብር ቦታ እቅድ የሚያዘው በከተማዉ ዝርዝር የአካባቢ ልማት
ፕላን ወይም በመሰረታዊ ፕላን ላይ ለዚህ ተግባር የሚዉል ቦታ መኖሩ
ሲረጋገጥ የሆናል፤
ለ/ ከዚህ በላይ በፊደል ተራ ቁጥር “ሀ’’ስር የተደነገገው ቢኖርም በከተማዉ ዝርዝር
የአካባቢ ልማት ፕላን ወይም በመሰረታዊ ፕላን ላይ ለዚህ ተግባር የሚዉል
ቦታ የሌለ እንደሆነ ጥያቄው የቀረበለት አካል ባደረገዉ ጥናትና ማጣራት
መሰረት የእምነት ተቋሙ ቦታ ማግኘት የሚገባው መሆኑን
ለከንቲባ ኮሚቴው ወይም ለወረዳው አስተዳደር ምክር ቤት ቀርቦ እና ተገምግሞ
በቃለ-ጉባኤ የተደገፈ የስምምነት ውሳኔ ሃሳብ ሲሰጥበት በእቅድ ሊያዝ
ይችላል፡፡
2) ጥያቄው በቀረበለት አካል በኩል በተደረገዉ ማጣራት በዚህ አንቀጽ ንኡስ
አንቀጽ /1/ ፊደል ተራ ቁጥር “ሀ’’ ሥር የተመለከተዉ ያልተሟላ ሆኖ ሲገኝ እና
በፊደል ተራ ቁጥር “ለ’’ መሰረት የውሳኔ ሃሳብ ሲሰጥበት የውሳኔ ሃሳቡ ቃለ-ጉባኤ
ተያይዞ ፕላን ለሚያዘጋጀውና አፈጻጸሙን ለሚከታተለው አካል ይቀርባል፡፡

8. በአምልኮ እና በመቃብር ቦታ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ስለመስጠትና ስለማሳወቅ

1) በሜትሮፖሊታን ከተሞች ውስጥ በከንቲባ ኮሚቴዎች አማካኝነት የውሳኔ ሃሳብ


ተሰጥቶባቸው ለቢሮው የሚቀርቡ የአምልኮና የመቃብር ቦታ ጥያቄዎች ተገቢውን
መስፈርትና ሰነዶች አሟልተው ስለመቅረባቸው ከተጣራና ከተረጋገጥ በኋላ ለክልሉ
መስተዳድር ም/ቤት እየቀርቡ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ይደረጋል፤
2) በሌሎች ከተሞች ውስጥ በከንቲባ ኮሚቴ ወይም በወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት
በኩል የውሳኔ ሃሳብ ተሰጥቶባቸው በኢ/ከ/ል መምሪያዎች በኩል እየተጣሩና ተረጋግጦ
በየዞኑ አስተዳደር ምክር ቤቶች በኩል ስምምነት እየተሰጠባቸው በቢሮው አማካኝነት
ለክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ቀርቦው ይወሰናሉ ፡፡

ክፍል ሶስት

ስለአምልኮ እና ስለመቃብር ቦታ ፕላን ጥናት፣ የመሬት ዝግጅት፣ የቦታ መጠንና አጠቃቀም


ስታንዳርድ

9. ስለአምልኮ ቦታ ፕላን ጥናት

በሌሎች የከተማ ፕላን ህግጋት ውስጥ የሰፈረው እንደተጠበቀ ሆኖ የአምልኮ ማከና

ቦታ ፕላን ጥናት፡-
ሀ/ በአንድ ከተማ ዉስጥ በጥናት የሚመላከት የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ድንበር/ወሰን
ከሌላ እምነት የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ያለው ርቀት ቢያንስ ከ500 ሜትር ሬድዬስ
በላይ መሆኑን፤

ለ/ ከጤና፣ ከትምህርትም ሆነ ከአስተዳደራዊ ተቋማት ያለው እርቀት ቢያንስ ከ200


ሜትር ራድዬስ በላይ መሆኑን ፤

ሐ/ ከዚህ በላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለምዕመናኑ ተደራሽ መሆኑን


በመሰረታዊነት ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

10. ስለአምልኮ ቦታ ስፋት እና አጠቃቀም

1) ለየትኛዉም አምልኮ ማከናወኛ የሚፈቀደው ቦታ ስፋት የመቃብር ስፍራን


ሳይጨምር ከ2000 ካሬ ሜትር ሊያንስና ከ3000 ካሬ ሜትር ሊበልጥ አይችልም፤
2) የአምልኮ ማከናወኛ ቦታው 40 ከመቶ ለአምልኮ ማከናወኛዉ ህንጻ እና ተያያዥ
አገልግሎቶች ግንባታ የሚዉል ሆኖ ቀሪው 60 ከመቶ የሚሆነው ለምዕመናኑ
አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና ለአረንጓዴ ልማት የሚዉል ይሆናል፤

3) ከግንባታ ነጻ እንዲሆን ከተደረገው የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ውስጥ ሶስት አራተኛ


የሚሆነው በአረንጓዴ ሳር ወይም ዕፅዋት መሸፈን አለበት፤

4) የእምነት ተቋሙ የተሰጠውን ቦታ ለተፈቀደለት አገልግሎት ብቻ የማዋል


ኃላፊነት አለበት ፣

11. ስለመቃብር ቦታ አወሳሰንና አሰጣጥ


1) ማንኛውም የከተማ አስተዳደር ወይም ማዘጋጃ ቤት በእምነቶች የቀብር ስነ-ስርዓትና
በመሪ ፕላኑ መሰረት የመቃብር ቦታ እንዲከለል ያደርጋል ፤
2) የከተማ አስተዳደሩ ወይም ማዘጋጃ ቤቱ የቦታውን መጠን ከከለለ በኋላ በዞኑ ኢንዱስትሪና
ከተማ ልማት መምሪያ አማካኝነት ለቢሮው እንዲቀርብ ያደርጋል፤
3) ለተለያዩ እምነቶች የሚሰጠው የመቃብር ቦታ በካርታ ተደግፎ መሰጠት ይኖርበታል፡፡
የአምልኮና የመቃብር ቦታ በአንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ የሁለቱ ስፍራዎች መጠን ተለይቶ
መመላከት አለበት፤
4) በከተማው ፕላን ላይ የተቀመጠው የቦታ መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ አዲስ ቦታ የሚጠና
ሲሆን፣ ከአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ጋር የመቃብር አገልግሎለት ለሚሰጡ የእምነት ተቋማት
እና የመቃብር ቦታ በፕላን ላልተመደበላቸው እምነቶች ከ1000- 3000 ካሬ ሜትር ሊደርስ
የሚችል ቦታ ከማናቸውም አይነት ክፍያ ነጻ ሆኖ ሊሰጥ ይችላል፤

5) በከተማው ውስጥ ባሉት የመቃብር ቦታዎች ቀብር የማይቻልበት ሁኔታ ሲያጋጥም በከተማ
አስተዳደሩ ባለቤትነት የሚተዳደር ሌላ የመቃብር ቦታ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

ክፍል አራት

ስለአምልኮ እና ስለመቃብር ቦታ ዝግጅት እና የካሳ ክፍያ

12. የቦታ ዝግጅት

1) የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ የሚዘጋጀዉ በከተማው ፕላን ላይ በተመለከተዉ እና በዕቅድ


በተያዘዉ መሰረት ይሆናል፤

2) ለአምልኮ ማከናወኛ የሚዘጋጀዉ ቦታ መሰረታዊ የመዳረሻ መንገድ ያለዉ እና

ከሶስተኛ ወገኖች ይዞታ ነጻ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፤

3) ማናቸውም የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ለዚሁ በወጣው ስታንዳርድ መሰረት በየራሱ


ተሸንሽኖ የወሰን ድንጋይ የተተከለለትና ሳይት ፕላን የተዘጋጀለት መሆን ይኖርበታል፤

4) በፕላኑ ላይ የተመላከተው ወይም አዲስ የተጠናው ቦታ ያልተዘጋጀ ሆኖ ሲገኝ


በሚመለከተው የመሬት ዝግጅት አካል በኩል በዕቅድ ተይዞ እንዲዘጋጅ
ይደረጋል፡፡

13.የአምልኮ ማከናወኛ ቦታ ዝግጅት ወጭና የካሳ ክፍያ አሸፋፈን


1) ለአምልኮ እና ለመቃብር ቦታ ዝግጅት የተከለለዉ ቦታ ለዚሁ ተግባር ተብሎ
የሚለቀቅ ሲሆን ቦታዉን የሚያዘጋጀዉ አካል ንብረቱን ለማስለቀቅ ያወጣዉን ወጪ
በዝርዝር መዝግቦ መረጃዉን መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይህንኑ መሰረት በማድረግም የከተማ
አስተዳደሩ ወይም ማዘጋጃ ቤቱ ለባለመብቶች ተገቢውን የካሳ ክፍያ በመፈጸም ቦታውን
ነጻ ያደርጋል፤
2) የመቃብር ቦታን በተመለከተ የሚጠየቀውን የካሳ ወጭ የእምነት ተቀማት ሳይሆኑ
የከተማ አስተዳደሩ ይሸፍናል፤

3) ማናቸውም የሀይማኖት ተቋም ለሚፈቀድለት የአምልኮ ቦታ ሚጠየቀውን የካሳ ክፍያ


በአንድ ጊዜ አጠቃሎ ይከፍላል፡፡ይህንኑ ክፍያ ውሳኔው በተገለጸለት በአንድ ወር ጊዜ
ውስጥ ለሚመለከተው አካል ገቢ ካደረገ በኋላ ስለዚሁ ደረሰኙን ይዞ መቅረብ
ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በላይ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይከፍል ቢቀር
ለመጀመሪያዎቹ 3 ወራት የጠቅላለውን የካሳ መጠን 10 ከመቶ እንዲሁም ለሚቀጥሉት
3 ወራት 15 ከመቶ ቅጣት ተጨማሪ ይከፍላል ፡፡ ከዚህ ውጭ ግዴታውን ከናካቴው
ያልፈጸመ እንደሆነ ውሳኔው ተሰርዞ ቦታው ለሌላ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል
ይደረጋል፤
4) ለአምልኮ ማከናወኛ የተከለለዉ ቦታ ክፍት መሬት በሚሆንበት ጊዜ የእምነት ተቋማት
የተባለውን የካሳ መጠን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ ስለሚለቀቅበትና ካሳ
ስለሚወሰንበት ሁኔታ በወጡ ህጎች መሰረት እንደተመለከተው ለአርሶ አደር
ባለይዞታዎች በሚከፈልበት የመፈናቀያ ካሳ ስሌት መሰረት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡

ክፍል አምስት፡
የአምልኮ እና የመቃብር ቦታ ስለማስረከብና ስለግንባታ ክትትል

14. የአምልኮ ቦታ ስለማስረከብ

የእምነት ተቋማት ከዚህ በላይ በተወሰነው መሰረት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ፈጽመው


ማረጋገጫ ሲያቀርቡ ቦታው ተዘጋጅቶና ተለክቶ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው
ይሰጣቸዋል፡፡

15. ስለህንጻ ደረጃና ግንባታ ክትትል

1) በየትኛዉም ከተማ ለአምልኮ ማከናወኛ የሚዉል ህንጻ ፕላን እና ዲዛይኑ

ደረጃዉን የጠበቀ እና ፈቃድ ባለዉ ባለሙያ የተዘጋጀ መሆን አለበት፤

2) የአምልኮ ማከናወኛ ህንጻ ስራው ከመጀመሩ አስቀድሞ ፕላኑ እና ዲዛይኑ አግባብ ላለዉ
አካል ቀርቦ መረጋገጥና መፈቀድ ይኖርበታል፤

3) ግንባታው ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ የሚኖርበት ሲሆን በሂደቱ


አማኞች የሚያመልኩበት ጊዜያዊ መጠለያ ከፈለጉ ዋናውን ግንባታ በማያዉክ
አኳሀን ጉዳዩ በሚመለከተዉ አካል ፈቃድ በጊዜያዊነት ሊገነቡና ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡
ሆኖም በጊዜያዊነት የተገነባዉ ይኸው ህንጻ ለቋሚ አገልግሎት መዋሉ በፕላኑ ላይ
እስካልተመለከተ ድረስ ከአምስት ዓመት ለበለጠ ጊዜ በጥቅም ላይ ሊውል አይችልም፤

4) ለአምልኮ ማከናወኛ አገልግሎት በተሰጠ ቦታ ላይ ለገቢ ማስገኛ ተግባራት የሚዉሉ


ግንባታዎችን በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት መስራት የተከለከለ ነው፤

5) አግባብ ያለዉ አካል በዚህ አንቀጽ ከንኡስ አንቀጽ /1/ እስከ /4/ የሰፈሩትን ድንጋጌዎች
አፈፃፀም በቅርብ የመከታተል እና የመቆጣጠር ሀላፊነት ይኖርበታል፡፡

ክፍል ስድስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
16. የመተባበር ግዴታ
ማንኛውም ሰው ይህንን መመሪያ ለማስፈጸም በሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ አስፈጻሚውን
አካል የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
17. ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው መመሪያዎች
ቀደም ሲል ወጥተው በክልሉ ውስጥ በስራ ላይ የቆዩ የአምልኮና የመቃብር ቦታ ምደባ
መመሪያዎች በዚህ መመሪያ የተተኩ በመሆናቸው በመመሪያው ውስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ
ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

18. መመሪያው ስለሚፀናበት ጊዜ ፡-


ይህ መመሪያ በክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ታይቶ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ባህርዳር

መጋቢት 30 ቀን 2006 ዓም

የአማራ ብሔራዊ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት

You might also like