You are on page 1of 7

የአብክመ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ

የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ ታዛቢ ኮሚቴ፣ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት እና ሥራ አመራር ቦርድ ማትጊያ

ክፍያ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር……../2010 ዓ.ም

ህዳር/2010 ዓ.ም
መግቢያ
መሬት የከተሞች ውስን ሀብት እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ይዞታ በማን እና በምን አግባብ እንደተያዘ
በይዞታው ላይ ያለውን መብት፣ ኃላፊነትና ግዴታ አረጋግጦ በመመዝገብ ባለመብቱ በይዞታው ላይ ያለውን
የመጠቀም መብት በማወቅ ወደ ኢኮኖሚው አስገብቶ ሊጠቀምበት የሚችልበት አግባብ በመፍጠር

0
የከተሞችን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እና ከተማው በአስተዳደር ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ይዞታዎች የተያዘበትን
አግባብ በመለየት እና ክፍት የሆነውን መሬት ለይቶ በማወቅ የህዝብ እና የመንግስት የሆነውን የመሬት ሀብት
ለይቶ በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የከተሞች
የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ህግ በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር
818/2006 ተደንግጓል፡፡ ይህን አዋጅ ተክተሎም “የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ የሚኒስትሮች
ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 324 /2006”፣ “የከተማ ካዳስተር ቅየሳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር
323 /2006”፣ “የከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007”፣“የከተማ ካዳስተር
ቅየሳ መመሪያ ቁጥር 44/2007” እና ሌሎችም ተያያዥ የሆኑ ስታንዳርዶችና ማንዋሎች የወጡ ሲሆን
በፌደራልና በክልል ደረጃም አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ስራ ተግብቷል፡፡
የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ስራው ሲከናወን ህብረተሰቡን ያሳተፈ መሆን እንደሚገባው በህግ ማዕቀፎቹ ላይ
የተገለፀ ሲሆን የሚሳተፉበት አግባብም በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “የከተማ የመሬት ይዞታ
ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007” አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ “በህብረተሰቡ የሚወከሉ
እና በታዛቢነት እንዲሳተፉ የሚደረጉት፣ በይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ፣ እንዲሁም
በኮሚሽን ውስጥ የሚሳተፉ በክልል ደረጃ በሚወሰንውሳኔ መሰረት የማትጊያ አበል እንዲከፈላቸው
መዝጋቢው ተቋም አስወስኖ ማስፈጸም አለበት” ተብሎ ተደንግጓል፡፡በመሆኑም በክልላችን በሚገኙ የይዞታ
ማረጋገጥና ምዝገባ ስራ በሚከናወንባቸው ከተሞች በስራው ላይ በቀጥታ ለሚሳተፉ የአካባቢ ታዛቢ ኮሚቴ፣
ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት እና ሥራ አመራር ቦርድ በመመሪያው መሠረት የማትጊያ ክፍያ እንዲፈፀም እና
የክፍያው መጠን ከከተሞቹ የመክፈል አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆንማድረግ በማስፈለጉ ይህ የአፈፃፀም
መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ የይዞታ ማረጋገጥ ታዛቢ ኮሚቴ ፣ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት እና ሥራ አመራር ቦርድ
ማትጊያ ክፍያ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር……../2010 ዓ.ም ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ

1
በዚህ መመሪያ ውስጥ የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር

1. “ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ”ማለት የከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007
አንቀጽ 28 መሠረት የሚሰየምና በይዞታ ማረጋገጥ ሂደት ላይ የሚነሳ ቅሬታን መርምሮ የመወሰን
ሥልጠን ያለው አካል ነው፡፡
2. “ታዛቢ ኮሚቴ” ማለት ለይዞታ ማረጋገጫነት በተመረጠ ሰፈር ውስጥ በከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ
እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007 አንቀጽ 18 መሠረት በኗሪዎች የሚመረጥና የይዞታ ወሰን
ማካለል፣ በሰነድ ማጣራት እና የይዞታ ማረጋገጥ ሥራዎችን በታዛቢነት የሚከታተል አካል ነው፡፡
3. “ማትጊያ አበል” ማለት የከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007 አንቀጽ
16 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በተገለፀው መሠረት በታዛቢነት ለሚሰሩ እና በይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ
ጉባኤ ውስጥ ለሚያገለግሉ በክልል ደረጃ በተወሰነው መሰረት የሚፈፀም የአበል ክፍያ ነው፡፡
4. “የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ” ማለት በአንድ ቁራሽ መሬት ላይ ያለ የመሬት ይዞታ መብትን በከተማ መሬት
ይዞታ ምዝገባ አዋጅ 818/2006፣ በይዞታ መረጋገጥና ምዝገባ ደንብ ቁጥር 324/2006 እና መመሪያ ቁጥር
45/2007 መሠረት ማረጋገጥ ነው፡፡
5. “ሰፈር” ማለት በአነስተኛው የከተማ አስተዳደር እርከን ውስጥ ከ 200 ያልበለጡ ቁራሽ መሬቶችን
(ይዞታዎችን) የያዘ አካባቢ ነው፡፡
6. “የአሰራር ስታንዳርድ” ማለት በከተሞች የመሬት ይዞታ መብት የማረጋገጥ እና የመመዝገብ ስራ ወጥ እና
ደረጃውን ጠብቆ እንዲከናወን ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ከተሞች ተግባራዊ የሚሆን የከተማ
መሬት ይዞታ የማረጋገጥና ምዝገባ የአሰራር ስርዓት ነው፡፡
7. አማካሪ ኮሚሽን -ማለት “የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ
ቁጥር 324 /2006” አንቀፅ 2 ን/አንቀፅ 12 የተሰጠውንስያሜ /ድንጋጌ ይይዛል
3. ተፈፃሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ ተፈፃሚ የሚሆነው የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ስራ በተጀመረባቸው የክልሉ ከተሞች ሆኖ በታዘቢነት፣
በቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባልነት፣ ሥራ አመራር ቦርድ በ“የከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ

ቁጥር 45/2007” መሠረት ተመርጠው በማገልገል ላይ ለሚገኙ አካላት ይሆናል፡፡

4. የደጋፊ አደረጃጀቶች ተግባርና ኃላፊነት

4.1 የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007 ዓ.ም አንቀፅ 19 ላይ የሰፈር
ታዛቢዎች ተግባርና ሀላፊነት እንደሚከተለው ደንግጓል፤

1) የሰፈር ታዛቢዎች በሚታዘቡበት ወቅት የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናሉ፡-


ሀ) በተመረጡበት ሠፈር ውስጥ የይዞታ ወሰን ማካለል፣ ሰነድ ማጣራት እና የይዞታ ማረጋገጥ
ሥራዎችን በታዛቢነት ይከታተላሉ፣

2
ለ) በይዞታ ማረጋገጥ ሂደቱ ላይ ሃሳብ ወይም አስተያየት ካላቸው ምክር ይሰጣሉ፣
ሐ) የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ ለማብራሪያ ከፈለጋቸው ቀርበው ማብራሪያ ይሰጣሉ፣
መ) ሰፈራቸውን ወክለው ለይዞታ ማረጋገጫነት በተመረጠው ሰፈር፣ በእያንዳንዱ በተረጋገጠ የመሬት
ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ላይ ስለመታዘባቸው ብቻ ይፈርማሉ፡፡
ሠ) ከአካባቢ ታዛቢዎች መካከል ከሶስቱ ሁለት ለመታዘባቸው ከፈረሙ ታዛቢዎች በተሟላ መልኩ
እንደታዘቡ ይቆጠራል፡፡
ረ) ከአካባቢ ታዛቢዎች መካከል አስገዳጅ በሆነ ምክንያት የተጓደለ ታዛቢ ካለ፣ በአረጋጋጭ ሹሙ
አማካኝነት ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄው ቀርቦ እንዲሟላ መደረግ አለበት፡፡
2) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የአካባቢ ታዛቢው በታዛቢነት
የሚያገለግል የይዞታ ማረጋገጫ ሰፈሩ ሥራ መጠናቀቁ በአካባቢ ማስታወቂያ ይፋ እስከሚሆን ቀን
ይሆናል፡፡ የምዝገባ ተቋሙ በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰፈር ውስጥ ላገለገሉ ለሁሉም ታዛቢዎች
የአካባቢ ታዛቢ ተግባር ለማከናወናቸው የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል መደበኛ ሥራ ያላቸውን
ታዛቢዎች በተመለከተ ክትትል በማድረግ ተገቢውን ጥቅማ ጥቅም ተጠብቆለት ወደ ቀድሞው የሥራ
ምድባቸው መመለሳቸውን ያረጋግጣል፡፡
4.2 የቦርዱ ስልጣንና ተግባር

4.2.1 በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 136/2008 ዓ.ም አንቀፅ 9
ላይ ቦርዱ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል በማለት ደንግጓል፡፡

1. በክልሉ የከተማ መሬት ይዞታ ለመመዝገብ በሚነደፉ የኘላን ዋና ዋና ግቦች ላይ ይመክራል፣ ማስተካከያ
በማድረግ ያፀድቃል፤

2. የከተማ መሬት ይዞታ ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ የመረጃ መሰረተ ልማትን የማልማት፣ የማመንጨት፣
የማምረት፣ የማሻሻልና የማስተዳደር ሂደቶችን አፈጻጸም ይገመግማል፣ በጥናትና በግብረ መልስ በተለዩ
ችግሮች ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል፣ ለተፈጻሚነታቸውም የሚመለከታቸውን
አካላት በማስተባበር ይመራል፣ ይገመግማል፣ ይከታተላል፤

3. የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባን ክልላዊ አፈጻጸምና የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱ በተገቢው ሁኔታ
እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲቻል በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅም መገንባቱን
ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ድጋፍ እንዲደረግ አቅጣጫ ያስቀምጣል፤

4. በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ተገቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ በማድረግ ይወያያል፣
ከህጋዊ ካዳስተር አተገባበር አንፃር ቅንጅት እንዲፈጠር ይሠራል፡፡
4.2.2 በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃጽ/ቤት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 137/2008 ዓ.ም አንቀፅ 10 ላይ
ቦርዱ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል በማለት ደንግጓል፡፡

1. ለከተማው የመሬት ይዞታ ምዝገባ የሚነደፉ ዋና ዋና ግቦችን ያፀድቃል፤

3
2. የአፈፃፀም ሪፖርቱን በየ 3 ወሩ ሰምቶ ያፀድቃል፣ ለቀጣይ ሥራዎች በእቅድ ተመስርቶ አቅጣጫ
ያስቀምጣል፤

3. የከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባ የማልማት፣ የማመንጨት፣ የማምረት፣ የማሻሻልና የማስተዳደር ሂደቶችን
አፈጻጸም ይገመግማል፤

4. በጥናትና በግብረ መልስ በተለዩ ችግሮች ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል፤


ለተፈፃሚነታቸው የሚመለከታቸው አካላት በመተባበር መሥራታቸውን ይቆጣጠራል፤

5. የከተማ መሬት ምዝገባ በከተማው የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በተገቢው ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን
ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅም መገንባቱን ይከታተላል፣ ይገመግማል፣
የአፈጻጸም አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
4.3 ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት ሥልጣንና ተግባራት፣

የከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር 45/2007 አንቀፅ 28፣ 29 እና 30 መሰረት
4.3.1 የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ መመልመያ መመዘኛ እና አሰያየም፤
1) የጉባኤው ሰብሳቢና ጸሐፊ አሰያየም፤
ሀ) የወረዳዉ ዋና አስተዳዳሪ የጉባኤው ሰብሳቢን ጨምሮ ሦስት አባላት ይሰይማል፤
ለ) ከእያንዳንዱ ማረጋገጫ ሠፈር ከህብረተሰቡ ከተወከሉ ከአምስት ያልበለጡ የጉባኤ አባላት
ከመካከላቸው ጸሀፊ ይሰይማሉ፤

2) ጉባኤው በይዞታ አረጋጋጭ ሹም በኩል አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ግብአቶች መዝጋቢው ተቋም ሥራ ከመጀመሩ በፊት
እንዲያሟላ ያደረጋል፡፡
3) የማረጋገጥ ጉባኤው አመላመል፡-
ሀ) በተወሰነው የይዞታ ማረጋገጫ ሰፈር ውስጥ ያሉ የማረጋገጥ ስራ ወይም ሂደት ላይ የሚነሱ
ቅሬታዎችን ለመፍታት በጥሩ ስነ ምግባር የታነጹ ለመሆቸው ከሰፈራቸው ባለይዞታዎች ድጋፍ
ያገኙ፤
ለ) የሚመረጡበት የመሬት ማረጋገጫ ሰፈር ሁለት አመት ላላነሰ ጊዜ በባለይዞታነት ወይም ነዋሪነት
መኖራቸው የተረጋገጠ፤
ሐ) በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ወይም ተሰሚነት እንዳላቸው ባላቸው የልማት ሥራ እና ማህበራዊ
ተሳትፎ ምስክርነት ያገኙ፤
መ) ከዚህ ቀደም በሙስና እና በእምነት ማጉደል የወንጀል ተጠያቂነት ያልቀረበባቸው እንዲሁም በስነ
ምግባር ብልሽት የማይጠረጠሩ፤ እና
ሠ) በአካባቢው የሥራ ቋንቋ መገልገል የሚችሉ፣ ማንበብ እና መፃፍ ችሎታ ያላቸው፤

4
4.3.2 የቅሬታ አቀራረብ

1) በይዞታ ማረጋገጥ ሂደት ላይ ቅር የተሰኘው ማንኛውም የመሬት ባለይዞታ ቅሬታውን የሚያቀርበው


በጽሁፍ ይሆናል፡፡ ቅሬታ ቅሬታ አቅራቢው የቅሬታ ነጥቦችን እና እንዲፈጸምለት የሚፈልገውን ጉዳይ
በመግለጽ ቅሬታውን ማቅረብ አለበት፡፡
2) በማንኛውም የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሰፈር ውስጥ በአረጋገጭ ሹም ውሳኔ እና የይዞታ ማረጋገጥ ሂደት
ላይ ቅሬታ ያለዉ ሰው፤ ቅሬታውን በራሱ ወይም በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካኝነት በየደረጃው
ማቅረብ ይችላል፡፡
4.3.3 የቅሬታ አወሳሰን
1) ጉባኤው የቀረበለትን ቅሬታ መርምሮ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ አብላጫ ድምጽ ያለው ውሳኔ የጋራ ሆኖ
ይጸድቃል፡፡ ነገር ግን የጉባኤ አባላት ድምጽ በውሳኔው ላይ የመደገፍ እና የመቃወም አቋም እኩል በኩል
ሲሆን፤ ሰብሳቢው የደገፈው ወገን የጉባኤው ውሳኔ ይሆናል፣ ሆኖም የሃሳብ ልዩነቱ በውሳኔው ላይ
ይመዘገባል፡፡
2) የቅሬታ ሰሚው ጉባኤ ምልዓተ-ጉባዔ 75 በመቶ ነው፡፡

3) ጉባዔው ውሳኔ የሚሰጠው ምልዓተ-ጉባዔ በተገኙበት ይሆናል፡፡


ክፍል ሁለት

5. የማትጊያ ክፍያ መጠንና አግባብ


1. ክፍያው ታሳቢ ያደረገው የታዛቢ ኮሚቴ፣ ቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ
የሚያጠፉትን የግል የስራ ሰዓትና የሚያጡትን ገቢ በተወሰነ ደረጃ መደጎም ነው፡፡
2. ለታዛቢና ለቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት የማትጊያ አበል ክፍያ የሚፈፀመው ለተሳተፉበት ቀን ብቻ
ሲሆን መገኘታቸውን የሚያረጋግጠው የይዞታ አረጋጋጭ ሹሙ በከተማው የይዞታ ምዝገባና
መረጃ ጽ/ቤት በኩል ይሆናል፡፡
3. ለታዛቢ ኮሚቴ የሚፈፀመው ጠቅላላ የክፍያ መጠን በአንድ ሰፈር በአሰራር ስታንዳርዱ
ከተገለፀው በሰነድ እና በልኬት በቅደም ተከተል በቀን 8 እና 5 ይዞታዎች ይረጋገጣል ከሚለው
ታሳቢ ማነስ የለበትም፡፡
4. በአንድ ሰፈር ለቅሬታ ሰሚ ጉባኤ አባላት የሚፈፀመው ጠቅላላ የክፍያ መጠን “የከተማ መሬት
ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 324 /2006” አንቀጽ 23
ንዑስ አንቀጽ 1 ፊደል ተራ “ሀ” ከተገለፀው 15 ቀናት የውሳኔ መስጫ ጊዜ መብለጥ የለበትም፡፡
5. የማትጊያ ክፍያ መጠን በቀን 70 ብር ይሆናል፡፡ ከተሞች ከዚህ የተሻለ መክፈል ከቻሉ የክፍያ
መጠኑን መጨመር ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የቀን ክፍያው ከ 100 ብር መብለጥ የለበትም፡፡

5
6. የበጀት/የፋይናንስ/ ምንጭ በከተማ ከከተማ አስተዳደሩ ገቢ በክልል ደግሞ ከክልሉ ገቢ ለዚህ
ተብሎ ከተመደበ በጀት ይሆናል፡፡
7. የክልሉ የስራ አመራር ቦርድ አባላት የውሎ አበል ክፍያን በተመለከተ የአብክመ ርዕሰ መስተዳድርና
የክልል መስተዳድር ምክር ቤት ህዳር 12 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው አራተኛ ዓመት የስራ ዘመን
8 ኛ መደበኛ ስብሰባ የስራ አመራር ቦርድ አበል አከፋፈልን አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ ተግባራዊ
ይሆናል፡፡
8. በከተማ ደረጃ ለሚቋቋም የስራ አመራር ቦርድ የቦርዱ አባላት የክፍያ መጠን በከንቲባ ኮሚቴ
የሚወሰን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጅ የክፍያው መጠን የአብክመ ርዕሰ መስተዳድርና የክልል
መስተዳድር ምክር ቤት ለ 4 ኛ ደረጃ የስራ አመራር ቦርድ ከወሰነው መብለጥ የለበትም፡፡
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
6. የመተባበር ግዴታ
ማንኛውም ባለድርሻ አካል ይህንን መመሪያ ለማስፈፀም የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
7. መመሪያ ስለማሻሻል
ይህ መመሪያ ማሻሻል ባስፈለገ ጊዜ የክልሉ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲው የማሻሻያ ሃሳብ
አቅርቦ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ ቀርቦ ሊሻሻል ይችላል፡፡

8. መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ
ይህ መመሪያ ክፍያውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ ከፈቀደበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ባህርዳር…………………ቀን 2010 ዓ.ም

የአብክመ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ ኃላፊ

You might also like