You are on page 1of 7

ደንብ ቁጥር 108/2ዐ11

የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ ማቋቋሚያ

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ደንብ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተረጋግጦ የተመዘገበ የመሬት ይዞታ ባለመብት የሆነ
ሰው የመሬት ይዞታ መብቱ ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፤
በተከናወኑ ምዝገባዎች መሠረት በሚሰጡ የምዝገባ ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶች ላይ ዋስትና
በመስጠት ሕብረተሰቡ በመሬት ይዞታ ምዝገባ ስረዓት ላይ እምነት እንዲኖረው ማደረግ
በማስፈለጉ፤በተሰጡ የምዝገባ ማረጋገጫ ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ ሦስተኛ ወገኖች
በቅን ልቦና በሚፈጽሙት ተግባር ምክንያት ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሣ ለመክፈል
የሚያስችል የዋስትና ፈንድ ማቋቋም ስለአስፈለገ፤

በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 818/2ዐዐ6 አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ
/1/ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር
64/2ዐ11 አንቀጽ 97 መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ ደንብ “የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ ማቋቋሚያ የአዲስ አበባ ከተማ
ካቢኔ ደንብ ቁጥር 108/2ዐ11” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ

በዚህ ደንብ ውስጥ፣

1. “ከተማ” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ነው፤


2. “ከተማ አስተዳደር” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፤

1
3. “ቢሮ” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ነው፤
4. “ኤጀንሲ” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የመሬት ይዞታ ምዝገባና
መረጃ ኤጀንሲ ነው፤
5. “አዋጅ” ማለት የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 818/2ዐዐ6 ነው፤
6. “ደንብ” ማለት የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ
ቁጥር 324/2ዐዐ6 ነው፤
7. “መመሪያ” ማለት የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ በከተማ
ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተሻሽሎ የወጣ መመሪያ ቁጥር 61/2ዐ1ዐ ነው፤
8. “የመሬት ይዞታ” ማለት የሊዝ ሥሪት በሚመራበት ህግ መሠረት በሊዝ
የተያዘ ወይም በሊዝ ሕግ መሠረት ዕውቅና የተሰጠው የከተማ ነባር የመሬት
ይዞታ ላይ የተገኘ የተጠቃሚነት መብት ነው፤
9. “መዝጋቢ ሹም” ማለት በአዋጁ መሠረት የመሬት ይዞታ መብትን፣ ክልከላንና
ኃላፊነትን እንዲመዘግብ እና ማረጋገጫዎችን እንዲሰጥ ሥልጣን የተሰጠው
ሰው ነው፤
10. “የማይንቀሳቀስ ንብረት” ማለት የከተማ መሬትንና በመሬቱ ላይ የሚገኘውን
መሬት ነክ ንብረት፣ በመሬት ላይ በቋሚነት የተገነቡ ግንባታዎችን ወይም
የተተከሉ ቋሚ ተክሎችን የሚያካትት ሲሆን ሌሎች ተነሺ ንብረቶች አንደ
ሰብል፣ ሣር እና ቋሚ ያልሆኑ ተክሎችን አይጨምርም፤
11. “የዋስትና ፈንድ” ማለት ኤጀንሲው ላረጋገጣቸውና ለመዘገባቸው የከተማ
መሬት ይዞታዎች በተቋሙ ስህተት በተፈጠሩ የመሬት ይዞታ መብት
መዛባቶች ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ካሣ ክፍያ እንዲውል በየጊዜው
ከሚደረግ የከተማ መሬት ይዞታ የመጠቀም መብት ዝውውር ከግብይቱ ዋጋ
አንድ መቶኛ ሣይበልጥ የሚሰበሰብ ክፍያ ነው፤
12. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል
ነው፤
13. በዚህ ደንብ ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡

3. የተፈፃሚነት ወሰን፣

2
ይህ ደንብ በኤጀንሲው በሚፈፀም የመሬት ይዞታ መብት የስም ዝውውር ላይ
ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

ክፍል ሁለት
ስለ ከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ መቋቋም

4. የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ ስለመቋቋሙ

የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ የዋስትና ፈንድ /ከዚህ በኋላ “ፈንዱ” እየተባለ
የሚጠራ/ ቢሮው በሚከፍተው ልዩ የባንክ ሂሣብ ውስጥ ተቀማጭ እንዲሆን በዚህ
ደንብ ተቋቁሟል፡፡

5. የፈንዱ ምንጮች
የሚከተሉት ምዝገባዎች ለፈንዱ የሚውል ተጨማሪ ክፍያ ይከፈልባቸዋል፤
1. የመሬት ይዞታ መብት በሙሉ ወይም በከፊል በሽያጭ፣ በስጦታ፣ በዓይነት
መዋጮ ወይም በሌላ ህጋዊ መንገድ በመተላለፉ፣
2. የመሬት ይዞታ መብት በውርስ በመተላለፉ ፣

ምክንያት የስም ዝውውር ሲፈጸም ፡፡

6. የፈንዱ ዓላማ
የፈንዱ ዓላማ፣
1. በኤጀንሲው ተረጋግጦ የተመዘገበ የመሬት ይዞታ ባለመብት የሆነ ሰው
የመሬት ይዞታ መብቱ እና በይዞታው ላይ ያረፈ የማይንቀሳቀስ ንብረቱ
ባለቤትንት መብቱ ዋስትና እንዲኖረው ለማድረግ፣
2. በኤጀንሲው ተረጋግጠው ለተመዘገቡ ምዝገባዎች በተሰጡ የምዝገባ ማረጋገጫ
ሰርተፊኬቶች ላይ ዋስትና በመስጠት ሕብረተሰቡ እምነት እንዲኖረው
ለማድረግ፡
3. ኤጀንሲው በሰጠው የምዝገባ ማረጋገጫ ማስረጃ ላይ በመደገፍ ሦስተኛ
ወገኖች በቅን ልቦና በሚፈጽሙት ተግባር ምክንያት ለሚደርስባቸው ጉዳት
ካሳ ለመክፍል ፡

3
ይሆናል፡፡

7. ስለክፍያዎች

ከፈንዱ ሂሣብ ገንዘብ ወጭ ሆኖ የሚከፈለው በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር፤


በመዝጋቢ ሹም እና በኤጀንሲው የክፍያና ሂሣብ ኃላፊ ፊርማ ይሆናል፡፡

8. የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሥልጣን


የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር፡-
1. ፈንዱ የሚቀመጥበት ልዩ የባንክ ሂሣብ በቢሮው እንዲከፈት ያደርጋል፤
2. በዚህ ደንብ መሠረት የተሰበሰበው ገንዘብ በፈንዱ ልዩ የባንክ ሂሣብ ውስጥ ገቢ
እንዲደረግ ያደርጋል፤
3. የፈንዱን ሂሣብ ይይዛል፤ በዚህ ደንብ መሠረት ፈንዱን ሥራ ላይ ያውላል፤
ያስተዳድራል፡፡
9. የፈንዱ ክፍያ ተመን
በዚህ ደንብ አንቀጽ 5 ሥር በተመለከተው በእያንዳንዱ ግብይት ወይም አገልግሎት
ለፈንዱ እንዲውል የሚከፈለው ተጨማሪ ክፍያ ተመን የሚከተለው ይሆናል፤
1. የከተማ መሬት ይዞታ መብት ከውርስ በስተቀር በማናቸውም ሕጋዊ መንገድ
ለሌላ ሰው በመተላለፉ የስም ዝውውር ሲፈፀም ከግብይቱ ዋጋ ዜሮ ነጥብ
ሦስት ከመቶ /ዐ.3%/፤
2. የመሬት ይዞታ መብት በውርስ የስም ዝውውር ሲፈፀም በውርስ በተላለፈው
ይዞታ ላይ ካለው የማይንቀሣቀስ ንብረት ዋጋ ግምት ዜሮ ነጥብ አንድ
ከመቶ /ዐ.1%/፣ /ወራሽ ከአንድ በላይ ከሆኑና ውርሱን ከተከፋፈሉ
በሚደርሣቸው የውርስ ድርሻ አግባብ/፡፡

10. የክፍያ ግዴታ


1. የመሬት ይዞታ መብት በሙሉ ወይም በከፊል በሽያጭ፣ በስጦታ፣ በዓይነት
መዋጮ ወይም በሌላ መንገድ ለሌላ ሰው የሚያስተላልፍ ማንኛውም ሰው

4
በዚህ ደንብ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ /1/ በተወሠነው የክፍያ ተመን
መሠረት ለፈንዱ የሚውል ተጨማሪ ክፍያ መፈፀም አለበት፡፡

2. የመሬት ይዞታ በውርስ የስም ዝውውር ሲፈፀም፣ እንደአግባብነቱ ወራሹ


ወይም ወራሾቹ በዚህ ደንብ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ /2/ በተወሠነው የክፍያ
ተመን መሠረት ለፈንዱ የሚውል ተጨማሪ ክፍያ መፈፀም አለበት፡፡

11. የፈንዱ ክፍያ የሚከፈልበት ጊዜና ሁኔታ

1. በዚህ ደንብ መሠረት ለፈንዱ እንዲውሉ የሚከፈሉ ተጨማሪ ክፍያዎች


በተናጠል እና አገልግሎቶቹ በተጠየቁ ጊዜ መከፈል አለባቸው፡፡

2. ለእያንዳንዱ የአገልግሎት ዓይነት የሚፈፀም ክፍያ ለእያንዳንዱ አገልግሎት


ለየብቻ የስም ዝውውሩ ከመፈፀሙ በፊት መከፈል አለበት፡፡

3. ስለ ኤጀንሲው ተጠያቂነት፣ ስለኃላፊነት መጠን፣ ስለጉዳት ካሣ ስሌት፣ ስለ


ጉዳት ካሣ አከፋፍል የአዋጁ፣ ደንቡና መመሪያው ድንጋጌዎች ተግባራዊ
ይደረጋሉ፡፡

12. ስለፈንዱ የባንክ ሂሣብ

የቢሮው ኃላፊ ፈንዱ የሚቀመጥበትን ልዩ የባንክ ሂሣብ ይከፍታል፡፡

13. ፈንዱን ለልማት ስለማዋልና ኢንቨስት ስለማድረግ፣

1. ፈንዱ ለጊዜው ለክፍያ የማይፈለግ መሆኑን ኤጀንሲው ሲያረጋግጥ፣ ፈንዱ


ካቢኔው ተገቢ ናቸው ለሚላቸው የከተማ የልማት ሥራ ሊውል ይችላል፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት ለከተማ ልማት ሥራ የሚውለው


ገንዘብ ከጠቅላላ የፈንዱ ገንዘብ ከአሥር በመቶ /1ዐ%/ ሊበልጥ አይችልም፡፡

3. ኤጀንሲው ፈንዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለክፍያ የማይፈለግ መሆኑን በቅድሚያ


እያረጋገጠ ቢሮው ከፈንዱ ጠቅላላ ገንዘብ ከሃምሣ በመቶ /5ዐ%/ ሣይበልጥ

5
ፈንዱን ካቢኔው ተገቢ ናቸው በሚላቸው በዋስትና ሰነዶች ላይ ኢንቨስት
ሊያደርግ ይችላል፡፡

ክፍል ሦስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

14. የመዝግብና ሂሳብ አያያዝ

የፈንዱ የመዝገብና የሂሣብ አያያዝ ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር


የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያን የሚከተል ይሆናል፡፡

15. ኦዲት

የፈንዱ ሂሣብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት


ይመረመራል፡፡

16. የመተባበር ግዴታና ተጠያቂነት

1. ማንኛውም ሰው ለዚህ ደንብ ተፈፃሚነት የመተባበር ግዴታ አለበት፤

2. ማንኛውም ሰው የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች የጣሰ ወይም አፈፃፀሙን ያሰናከለ


ወይም የፈንዱን ገንዘብ ያባከነ ወይም ያጐደለ እንደሆነ በሀገሪቱ የወንጀል
ሕግ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

17. ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ህጎች

ከዚህ ደንብ ጋር የሚቃረን ማንኛውም የከተማው ካቢኔ ደንብ ወይም መመሪያ፣


እንዲሁም ማንኛውም ልማዳዊ አሠራር በዚህ ደንብ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ
ተፈፃሚነት አይኖራቸውም፡፡

18. መመሪያ የማውጣት ሥልጣን፣

ኤጀንሲው ይህንን ደንብ በሚገባ ለማስፈፀም የሚያስፈልገውን መመሪያ ሊያወጣ


ይችላል፡፡

6
19. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ ደንብ ከሚያዝያ 1 ቀን 2ዐ11 ዓመተ ምህረት ጀምሮ የፀና ይሆናል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1 ቀን 2ዐ11 ዓ/ም

ታከለ ኡማ በንቲ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ

You might also like