You are on page 1of 28

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ


የቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት ክፍል
General Church History
Group Assignment
Council of Chalcedon-ጉባኤ ኬልቄዶን
Group Members
1. Endalkachew Muket
2. Shimekit Lemma
3.Takele Birhanu
4. Yonas Desta

Submitted to- Mhr. Getachew


Submission Date- 22/05/2015 E.C

Holy Trinity University Group Assignment 1


ማውጫ
ምዕራፍ አንድ - ታሪካዊ ዳራ .................................................................................................................................. 3
1.1 መግቢያ ................................................................................................................................................ 3
1.2 ቤተ ክርስቲያን ከጉባዔ ኬልቄዶን በፊት የነበረችበት ሁኔታ ...................................................................................... 4
1.3 የቅዱስ ዲዮስቆሮስ በኬልቄዶናውያን መወገዝ ..................................................................................................... 7
1.4 አውጣኪና ትምህርቱ .................................................................................................................................. 8
1.5 ሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ መካሄድ (449) ..................................................................................................... 9
ምዕራፍ ሁለት - የጉባዔው መደረግ ......................................................................................................................... 13
2.1 መነሾ .................................................................................................................................................... 13
2.2 የጉባዔው ምክንያቶች ................................................................................................................................ 13
2.3 በጉባዔው ውስጥ ሚና የነበራቸው ሰወች ........................................................................................................ 14
2.4 የሊዮን ደብዳቤ ....................................................................................................................................... 14
2.5 የጉባኤው ሂደት ....................................................................................................................................... 15
ምዕራፍ ሶስት- ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔወች .......................................................................................................... 20
3.1 በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔወችና ስህተቶቻቸው ................................................................................................. 20
3.2 ቤተክርስቲያን ከጉባዔ ኬልቄዶን በኋላ ........................................................................................................... 24
3.2.1 የተፈጠሩ የሃይማኖትና የሥርዓት ልዩነቶች ............................................................................................... 24
References .................................................................................................................................................. 28

Holy Trinity University Group Assignment 2


ምዕራፍ አንድ - ታሪካዊ ዳራ

1.1 መግቢያ
በክርስትና እምነት ተከታዮች መሃል በተለይም ከ 4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተፈጠረው በምሥጢረ ሥላሴ ላይ

የተሰጠ የተሳሳተ አስተምህሮ አብዛኖቹን ወዳልተፈለገ መከፋፈልና የእምነት መበረዝ መርቷቸዋል።

ከዚህ የክህደት ትምህርት በጎላ ከሚታወቁት መሃል አንዱ አርዮስ ከእስክንድርያዊው መምህሩ ከአርጌኒስ በቀሰመው ትምህርት

በዘዴ ‹‹ ወልድ ፍጡር ነው፤ አምላክም አይደለም፤›› ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሃሎ ወልድ›› (ወልድ ያልነበረበት ጊዜ

ነበር) በግሪክኛ፡- ‹‹ኢን ፖቴ ኦቴ ኡክ ኢን›› ብሎ የክሕደት ትምህርት በማስተማሩ መላው የክርስትናው ዓለም ታውኮ ነበር

(ጎርጎርዮስ, 2015)። ይህ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ አርዮስና ኑፋቄው በመወገዙ ችግሩ መፍትሔ አግኝቶ ነበር፡፡ ከ106

ዓመታት በኋላ ደግሞ ንስጥሮስ ከአንጾኪያ ባገኘው ትምህርት በቊስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በምሥጢረ ሥጋዌ እምነት ላይ

ስለ ክርስቶስ የተሳሳተ ትምህርት ማስተማር ጀመረ፡፡ በትምህርቱም 1ኛ ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው፤ 2ኛ/

ክርስቶስ ፍጹም ሰው እንጂ ፍጹም አምላክ አይደለም፤ እንዲሁም 3ኛ/ እመቤታችን ሰውን እንጂ አምላክን አልወለደችም፤

ስለዚህ እመቤታችን ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም ብሎ በማስተማሩ ይህ ኑፋቄ በ431 ዓ.ም. ላይ

በታላቁ መምህር በእስክንድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ ቄርሎስ አማካኝነት በኤፌሶን ጉባኤ ተወግዞ ችግሩ ተወግዶ ነበር

(ማህበረቅዱሳን, 2015) ፡፡ ሆኖም የንስጥሮስ የክህደት እምነት ጨርሶ ሳይጠፋ በዚያው በመካከ ለኛው ምሥራቅ በተለይ

በፋርስና በባቢሎን እንዲሁም በኤዴሳ ሲስፋፋ ቆይቷል፡፡ እንዲሁም ንስጥሮሳውያን በኤፌሶንና በቊስጥንጥንያ በብዛት ይገኙ

ነበር (Davis, 1990) ፡፡

በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን, ባሁኗ ኢስታንቡል, ከ500-600 በሚጠጉ ጳጳሳት ቱርክ ላይ የተደረገው የኬልቄዶን ጉባኤ (ዊኪፔድያ,

2015) የሮም ነገስታትን ፍላጎት ለማሟላት የተጠራ ጉባኤ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ፓፓ ልዮን የተባለው ጳጳስ በነገስታቱ

በነመርቅንያና ብርክልያ ታጅቦና የንስጥሮስን የስህተት ትምህርት ይዞ ብቅ ያለበት ስብሰባ ነበር። ንስጥሮስ የሁለት ባህርያትን

ቅድመ አለምና ድህረ አለም በማለት በመነጣጠል በስጋ የወለደችው ወልድ ሁለት ባህርያት አሉት በማለት (ዲኦፍሳይት)

ሲያስተምር በዚህ ትምህርቱም በአምላክነቱ የፈጣሪን ስራ ሲሰራ በስጋ ባህርዩ ደግሞ የስጋን ስራ ይሰራል በማለት ተዋሕዶን

የካደ መናፍቅ ነበር። አውጣኬ የሚሉት ደግሞ ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ነበረው ነገር ግን የመለኮት ባህሪው ከሰው ባህሪው

Holy Trinity University Group Assignment 3


ስለሚበልጥ ያንን ውጦታል/ መጦታል /ስለዚህ አንድ ባህሪይ (ሞኖፈሳይት) ነው አሁን ያለው የአምላክነት ባህርዩ ብቻ ነው

በማለት ያስተምር ነበር (ቤተ ሃዋርያት, 2006) ።

በወቅቱ በመምህሩ በአቡነ ቄርሎስ መንበር ተተክቶ አሌክሳንድርያን ሲያስተዳድር የነበረው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን አውጣኬ

እንደሚለው የአምላክነት ባህርዩ የሰው ባህርዩን በመዋጥ/ በመምጠጥ አንድ ባህርይ የሆነ ሳይሆን እንዲሁም ንስጥሮስ

እንደሚለው ቅድመ አለምና ድህረ አለም በመነጣጠል ሁለት ባህርይ / ዲዮፍሳይት ሳይሆን በፍፁም ተዋህዶ ከሁለት ባህርይ

አንድ ባህርይ የሆነ አምላክ ነው በማለት ትክክለኛውን አስተምህሮ አስቀምጧል።

1.2 ቤተ ክርስቲያን ከጉባዔ ኬልቄዶን በፊት


ቅዱስ ቄርሎስ የእስክንድርያን መንበረ ማርቆስ ለ32 ዓመታት ያህል አገልግሎ በ444 ዓ.ም ዐረፈ። በመንበሩም ሊቀ ዲያቆኑ

የነበረው ወዳጁና ደቀመዛሙሩ ዲዮስቆሮስ ተመርጦ 25ኛ ፓትሪያርክ ሆኖ ተሾመ፡፡ በሃይማኖቱ የቅዱስ አትናቴዎስንና የቅዱስ

ቄርሎስን ፈለግ ይከተል ስለነበር ለተዋሕዶ ሃይማኖት ቀናተኛና ተቆርቋሪ መናኝ መነኵሴ ነበር። ሊቀ ዲያቆን በነበረበት ጊዜም

መምህሩን ቄርሎስን ተከትሎ ንስጥሮስ የተረታበትን የኤፌሶን ጉባኤ ተካፍሏል፡፡ዲዮስቆሮስ በመንበረ ማርቆስ እንደተሾመ

የታናሽ እስያ ግሪኮች ይልቁንም ቄርሎስን ሲቃወሙ የኖሩ እነ ቴዎዶሪጦስ በውዳሴ ከንቱ ለማግባባት ቄርሎስን እያኮሰሱ እሱን

እያሞገሱ የሹመት ያዳብር መልእክቶች ላኩለት (ኅሩይ ኤርሚያስ, 2010 ዓ/ም)። ዲዮስቆሮስ ግን ከእምነቱ ወደኋላ የማይል

በውዳሴ ከንቱ የማይጠለፍ መንፈሳዊና ታማኝ አባት ስለነበር ሐሳባቸውን አልተቀበለውም እነሱም በዲዮስቆሮስ ዘንድ

ተሰሚነት ስላላገኙ የዲዮስቆሮስንና የመንበረ ማርቆስን ስም የሚያጎድፉበት ምክንያት መፈለግ ጀመሩ፡፡

በኤፌሶን ጉባኤ 431 ዓ.ም የንስጥሮስ የኹለት ባሕርይ ትምህርት ከተወገዘና የተዋሕዶ ሃይማኖት ከተደላደለች በኋላ ምንም

እንኳ ውስጥ ውስጡን ሽኩቻ ባይቀርም ለ17 ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያን አዲስ ክሕደት አልተሰማም ነበር፤ ከዚህ በኋላ

(ከ447-449) በቊስጥንጥንያ ያንድ ገዳም አበ ምኔት የነበረ፣ ንስጥሮስ የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ በነበረበት ጊዜ ትምህርቱን

ሲቃወምና ሲከራከር የኖረ ፣ አውጣኪስ የተባለ ግሪካዊ መነኲሴ የስህተት ትምህርቶችን በማስተማር ቤተክርስቲያንን ረፍት

መንሳት ጀመረ ። ይህም አውጣኪስ የተባለ መነኩሴ ‘’ኹለት ባሕርያት ወይም የሥጋና የመለኮት ባሕርያት ተቀላቅለው

ተጣፍተዋል’’ እያለ ያስተምር ነበር። በኣውጣኪ ዘመን የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች በእስክንድርያ ፓትርያርኩ

ዲዮስቆሮስ፣ በሮም ፓፓ ልዮን፣ በቊስጥንጥንያ ደግሞ ፍላብያኖስ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ፍላብያኖስ አውጣኪንና ትምህርቱን

በቅርብ ቢያውቅም የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ሳይጠራ የህገረ ስብከቱን ኤጲስ ቆጶሳት ብቻ በጉባኤ አድያም ሰብሰቦ

አወገዘው (አቡነ ጎርጎርዮስ, 2015)።ይህ አውጣኪስም እንደ አርዮስ እንደ መቅዶንዮስና እንደንስጥሮስ በመላው የአብያተ

Holy Trinity University Group Assignment 4


ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች ፊት ቀርቦ ካለመወገዙ የተነሣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጉዳዩን ስላላወቁት አውጣኪ ‘’የቄርሎስን

ሃይማኖት ስለ መሰከርኩ በከንቱ ተወገዝኩ’’ ብሎ ለቤተ መንግሥት ይግባኝ አለ (አቡነ ጎርጎርዮስ, 2015)፡፡

ከይግባኙ በኋላ ጠቡ አሁንም የተነሣው በዚያው በቊስጥንጥንያ ስለኾነ እንደ ተለመደው በእስክንድርያ ፓትርያርክ በዓለም

አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ እንዲታይስት ሲል ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ለእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንና ለሌሎችም አብያተ

ክርስቲያናት መልእክት ላከ፡፡ በዚህ ጊዜ ዲዮስቆሮስ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ እንደመኾኑ መጠን ጉባኤ ሰብሳቢ ነበር:

የጉባኤውም ሰብሳቢ እንደመኾኑ መጠን ቀደም አድርጎ ወደ ኤፌሶን መጣ፡፡ አብረዉት ከእስክንድርያ የመጡት 23 ኤጲስቆጶሳት

ሲኾኑ አነዚህ አምስቱ በጉባኤ ኤፌሶን (431) የነበሩ ናቸው። ከነዚህም ሌላ ከሶርያ በአባ በርሶማ የሚመሩ አያሌ ኤጲስ ቆጶሳትና

ከሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ነበሩ። ኹሉም ሰዓቱን አክብሮ በጉባኤው ላይ ሲገኝ የሮማው ፓፓ እንደራሴዎች ግን

ዘግይተው ደረሱ፤ በጊዜውም የቊስጥንጥንያው ፍላብያኖስም አልመጣም ነበር፤ ዲዮስቆሮስ በጊዜው የሙጡትን 135

ኤጲስቆጶሳት ይዞ ነሐሴ 8 ቀን 449 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ አደረገ:፡ ይህች ኤፌሶን ከ18 ዓመት በፊት በቄርሎስ መሪነት 200

ሊቃውንት ተሰብስበው የንስጥሮስን የኅድረት ትምህርት ያወገዙባት የተዋሕዶን እምነት ያጸባት ቦታ ናት: ጉባኤው የተደረገው

ያን ጊዜም አኹንም በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው (አቡነ ጎርጎርዮስ, 2015) ። አውጣኪ ወደ ጉባኤው ቀርቦ

ስለሚያምነው እምነት ሲጠየቅ የተወገዝኹት በሃይማኖቴ ጉድለት ተገኝቶብኝ ሳይኾን ንስጥሮስን እቃወም ስለነበር በግል ቂም

ነው እንጂ እምነቴም ትምህርቴም የሠለስቱ ምእትና የቅዱስ ቄርሎስ ነው ሲል ቃሉን በመሐላ ሰጠ ። ጉባኤውም ይህንን መልሱን

አይቶ ለጊዜው አውጣኪን ከግዝቱ ፈትቶ በቤተ ክርስቲያን የነበረውን ሥልጣን መለስለት፡፡

ከዚህ በኋላ ዲዮስቆሮስ የሚከተለውን ቃል ለጉባኤው አሰማ: ’’ከኒቅያ እስከ ኤፌሶን በጉባኤ ተሰብስበው አባቶቻችን ከወሰኑት

ሃይማኖት ሌላ የሚጨምር የሚቀንስ ወይም የሚያሻሻል ቢኖር የተወገዘ ይኹን’’ አለ ፡፡ በዚህ ጊዜ የነበሩት አባቶች ኹሉ

«ዲዮስቆሮስ የተዋሕዶ ሃይማኖትና የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ዲዮስቆሮስ ታላቁ ዲዮስቆሮስ ገናናው እያሉ አመሰገኑት፡

ይህን የዲዮስቆሮስን ውሳኔ ሲሰማ በስብሰባው ላይ ያልነበረው ፖፕ ልዮን ጉባኤውን ጉባኤ ፈያት ብሎ ስየመው፡፡ ይህንም

ያለበት ምክንያት የሱ መልእክተኞች ስላለተሳተፉበት ነው:፡ የጉባኤው መሪ ሊቀ መንበር የነበረውን ዲዮስቆሮስንም አወገዘው።

ልዮን በዚህ ብቻ አልተወስነም በቊስጥንጥንያው ፍላብያኖስም የመንፈቀ ንስጥሮሳውያንን የኹለት አካል ኹለት ባሕርይ

ትምህርት መልኩን ለውጦ ጽፎ ላከለት። መልእክቱም እንዲህ የሚል ነበር «የክርስቶስ ኹለት ባሕርይ ኹለት ህላዌ አንድ አካል

አለው ብለን እናምናለን: duae naturae et substantiae in unan personam አካልና ባሕርይ የተለያዩ ናቸው። ከአካል

Holy Trinity University Group Assignment 5


የተለየ ባሕርይ አባሕርይ የተለየ አካል የለም ካልን ግን ባሕርይን ኹስት እንዳልን አካልን ኹለት ማለት ይኖርብናል፧ ይኸውም

እንደ ንስጥሮስ ማለት ነው:፡ ወይም አካልን አንድ እንዳልን ባሕርይንም አንድ ማለት ይኖርብናል፧ ይኸውም እንደ ቄርሎስ

ማለት ነው: ኹለቱ ባሕርያት በመተባበር የየራሳቸውን ድርሻ ይሠራሉ፡፡ «መለኮት ይገብር ግብረ መለኮት ትስብእት ይገብር

ግብረ ትስብእት» መiኮት የመለኮትን ሥጋም የሥጋን ሥራ ይሠራል፡» የሚል ጦማር ነበር፡፡

በጦማሩም መከራ የተቀበለው ሥጋ፤ ተአምራት ያደረገው መለኮት እንደኾነ ታትቶ ቀርቧል:፡ ፍላብያኖስ ግን የቊስጥንጥንያ

መንበር ከፍ ለማድረግ በነበረው የግሪኮች ጥረት ልዮንን ተባበረን ለማለት ከሱም ላለመቃቃር እሱ የሚለውንም ላለመቃወም

ብሎ ተጠንቅቆ መልስ ሲሰጥ የቄርሎስን ትምህርት በማይቃወም ኹኔታ ተናግሯል። የፍላብያኖስ መልስ «ከሥጋዌ በኋላ ባንድ

አካል፤ ባንድ ከዊን ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የኾነውን አንድ ክርስቶስን እናምናለን ብሏል»።

ከዚህ በኋላ ፍላብያኖስ ሙቶ በመንበሩ አናቶሊዮስ ተተካ። ዲዮስቆሮስም ልዮን ለፍላብያኖስ የላከውን መልእክት (ጦማር)

በሰማ ጊዜ ንስጥሮሳዊ ነህ ብሎ አወገዘው። ከዚህ በኋላ ላቲኖችና ግሪኮች አንድ ላይ ኹነው በእስክንድርያ የቅዱስ ማርቆስ

መንበር ላይ ማሴር ጀመሩ: ይኽ ሁሉ ግር ግር በፊት የነበረውን የመንበር አቀማመጥ ተራ አፋልሶ ማለት «ሮም እስክንድርያ

አንጾኪያ» የነበረውን «ሮም ቊስጥንጥንያ እስክንድርያ» ለማለት ቊስጥንጥንያን ሥርዋጽ ለማስገባት ነው:

አውጣኪ ለጊዜው በተንኮል ሃይማኖቴ ኦርቶዶክስ ነው ቢልም ትንሽ ቆየት ብሎ የውላጤ ትምህርቱን ለማስፋፋት የውስጥ

ለውስጥ ዘመቻ ያካሔድ ጀመረ፤ የቃል ለሥጋ የሥጋም ገንዘብ ለቃል የሆነው በተዋሕዶ መኾኑን ሳይገነዘብ አውጣኪ መላልሶ

አክሮና አመንችኮ የሚናገረው ’’የቃል ገንዘብ ለሥጋ የኾነው በውላጤ ነው’’ እያለ ነበር፡፡ ይህም ማለት መለኮት ሥጋን ዋጠው

መጠጠው ማለት ነው። ልዮንና ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ተወጋግዘው እንዳሉ ግሪኮችም በሁለቱ መጣላት ቊስጥንጥንያን ከተራ

ቊጥር ለማስገባት አሰፍስፈው ሳሉ በ450 ዓ.ም ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ከፈረስ ላይ ወድቆ ሞተ፡፡ እሱ ሲሞት እኅቱ ብርክልያ

የአባቷን ጀኔራል መርቅያንን አግብታ ነገሠች: ይህች ሴት ብልጣ ብልጥ ስለ ነበረች ወንደሟ በሕይወት ሳለም የመንግሥቱን

አስተዳደር የምትመራው እሷው እንደ ነበረች ይነገርላታል፡ ቴዎዶስዮስ በተፈጥሮው ፈዛዛ ነበርና፤ ኋላ ግን አውዶክያስን ሲያገባ

ሚስትና እኅት ባመስማማት እኅቲቱ ከቤተ መንግሥት ወጥታ እንደ ግዞተኛ ሁና ትኖር ነበር፡ ወንድሟ በሞተ ጊዜ ልጅ

ስላልነበረው አልጋው ወደሷ ተዛወረ። ብርክልያም ሆነች ባሏ መርቅያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቴዎዶስዮስ ጊዜ የነበረውን

ለማፍረስና የራሳቸውን ስም የሚያስጠራ አንድ ሥራ ለመሥራት ቸኵለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ የነበረው የነገሥታት ጀብዱ በቤተ

ክርስቲያን ጣልቃ እያገቡ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ማፋለስና ለሐሳባቸው የሚስማማቸውን መሾም አልስማማም ያለውን ግን

Holy Trinity University Group Assignment 6


ማዋረድ ማጋዝና መግደል ነበር፡ ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ባልና ሚስት አልጋውን እንደያዙ የሮማው ፓፓ ልዮን

ቀዳማዊ ጋር የደብዳቤና የመልእክተኞች ልውውጥ ማድረግ ጀመሩ። ልዮንም ንስጥሮሳዊ ትምህርቱን ለማደላደል አመች ጊዜ

ሆነለት። ወዲያውም በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን (ታናሽ እስያ) ጉባኤ እንዲደረግ የቊስጥንጥንያ ቤተ መንግሥትና እነልዮን

ስምምነት አደረጉ። ከጉባኤው ጥቂት ቀደም ብሎ ልዮንና መርቅያን የቊስጥንጥንያውን አናቶሊዮን ጨምረው ተወያይተው

ነበር፡፡

1.3 1.3 የቅዱስ ዲዮስቆሮስ በኬልቄዶናውያን መወገዝ


የሮሙ ፖፕ ልዮን፣ የሮም የምሥራቁ ክፍል ንጉሠ ነገሥት የመርቅያንና የንግሥቲቱ የብርክልያ ታላቅ ተጽእኖ የነበረበት ይህ

የኬልቄዶን ጉባኤ መጀመሪያም የተሰበሰበው ዲዮስቆሮስን ለማውገዝና ከሥልጣኑ ለማውረድ ስለነበረ፣ እሱን ለማውገዝ ብዙ

ምክንያቶች ይፈልጉ ነበር፡፡ በሃይማኖት በኩል ምንም ስሕተት ስላላገኙበት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል በማለት ጉባዔው

ላይ የተሰበሰቡት ሁሉ በአንድ ድምፅ አውግዘውታል፡፡ ለዚህ ሃሰተኛ ውግዘታቸውም ሦስት የውሸት ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፤

1ኛ/ በመናፍቅነት የተከሰሰውንና የተወገዘውን አውጣኪን ነጻ አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት መልሷል፡፡ 2ኛ/ የሮሙ

ፖፕ ልዮን የላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ (The Tome of Leo) ሳይቀበል ደብዳቤውንም ፖፕ ልዮንንም

አውግዟል ፡፡ 3ኛ/ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሦስት ጊዜ ተጠርቶ አልተገኘም የሚል ነበር፡፡ ይህ የኬልቄዶን ጉባዔ እንደሌሎቹ

ጉባኤያት ሁሉም ተሳታፊዎች የሚስማሙበትን ውሳኔ ማሳለፍ ያልቻለ ቤተክርስቲያናችንም ጉባዔ ከለባት/ጉባዔ ዓብዳን ብላ

ያልተቀበለችው ጉባዔ ነው ፡፡ በጉባዔው ላይ በኃይል የተላለፈው ውሳኔ የቅዱስ ቄርሎስን (በጉባኤ ኤፌሶን) የተወሰነውን ውሳኔ

የሚቃረን ስለነበር የእስክንድርያና አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም አልተቀበሉትም፡፡ በስብሰባውም ፓትርያርክ ቅዱስ

ዲዮስቆሮስ ከተወገዘና ከሥልጣን እንዲወርድ ከተወሰነበት በኋላ ንግሥት ብርክልያ በግል አስጠርታ ሐሳቡን ለውጦ በልዮን

ጦማር (Tome of Leo) ላይ እንዲስማማና እንዲፈርም ትእዛዝ አዘል ምክር ሰጥታው ነበር፡፡ እሱ ግን መንፈሰ ጠንካራ ስለነበር

የንግሥቲቱን ትእዛዝና ምክር አልተቀበለም፡፡ በዚህ ምክንያትም ንግሥቲቱ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን በወታደሮች በሚያሰቅቅ ሁኔታ

ጥርሶቹ እስኪወልቁ ጽሕሙም እስኪነጫጭ ድረስ አስደበደባው ነበር፡፡ እሱም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቁትን ጥርሶች በአንድ

ላይ ቋጥሮ ‹‹ይህ የሃይማኖት ፍሬ ነው፤›› የሚል ጽፎበት ለግብጽ ምእመናን አንደላከላቸው በጉዳዩ ዙርያ የተጻፉ ማስረጃወች

ያሳያሉ ፡፡ ይህ ቅዱስ ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ አምስት ዓመት በግዞት ግፍና ሥቃይ እየተቀበለ ከቆየ በኋላ በ456 ዓ.ም. አርፏል።

ቅድስት ቤተክርስቲያንም የዚህን ታላቅ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በዓለ ልደቱና ዕረፍቱን በማስመልከት መስከረም 7 ታከብራለች፡

የንጉሡ ወገኖች በተለይም ንግሥት ብርክልያ የእስክንድርያን ቤተ ክርስቲያን የወከለውን የቅዱስ ቄርሎስ ደቀ መዝሙር

Holy Trinity University Group Assignment 7


በነበረው ታላቅ አባት በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ መከራ የደረሰበትን ጽኑ መከራ አብሮ ለመቀበልና ከእውነት ጋር ለመተባበር

ያልቻሉት መለካዊያን የንጉሱንና የሊዩንን ውሳኔ ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም ስብሰባ በኋላ እስክንድርያ ላይ የግብጽ ምዕመናን

ያልተቀበሉት የንጉሡ ወገኖች ግን የተቀበሉት ፕሮቴርዩስ የሚባል ሰው ተሹሞነበር፡፡በዚህም ምክንያት የእስክንድርያ ቤተ

ክርስቲያን የተዋሕዶ አማኞችና የንጉሣዊያን (መለካዊያን) በመባል ለሁለት ተከፍላለች። መለካዊያኑ በ1054 ዓ.ም.

ከምዕራባዊያኑ ካቶሊካዊያን ተገንጥለዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በዋነኝነት ካቶሊካዊያኑ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ

የሰረጸ ነው የሚለውን ትምህርት በማስተማራቸው ይህንንም የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በመቃወሟ ነው፡፡

1.4 1.4 አውጣኪና ትምህርቱ


የንስጥሮስን ትምህርት በጥብቅ ይቃወሙ የነበሩት የግብጽ መነኰሳትና ካህናት ነበሩ፡፡ በቊስጥንጥንያም ቢሆን አያሌ የንስጥሮስ

ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ ይቃወም የነበረና ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት እጅግ ቀናኢ የነበረ አውጣኪ

የተባለ በቊስጥንጥንያ የአንድ ትልቅ ገዳም አበምኔት (መምህር) ነበር፡፡ አውጣኪ ‹‹ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ

አለው›› የሚለውን የንስጥሮሳውያንን ትምህርት አጥብቆ በመቃወም እሱ ወደ ተቃራኒው የባሰ ክህደት ውስጥ ገባ፡፡ አውጣኪ

በቊስጥንጥንያ ‹‹ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብቻ አለው፤›› እያለ ያስተምር ጀመር፡፡ አባባሉ የቅዱስ ቄርሎስን

ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ይመስላል፡፡ አውጣኪ ግን ‹‹አንድ ባሕርይ›› ሲል የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ብቻ ማለቱ ነበር፡፡

በአውጣኪ አባባል ‹‹ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ

ውጦታል፤ አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ

የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፤›› ይል ነበር፡፡ ይህ አባባል በእኛም ቤተ ክርስቲያን ማለት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው፡፡ አውጣኪ በተጨማሪ ከሥጋዌ በኋላ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው

ለማለት ‹‹ክርስቶስ ዘዕሩይ ምስሌነ በትስብእቱ›› ማለት ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ (በሥጋው) ከእኛ ጋር አንድ ነው›› የሚለውን

ኦርቶዶክሳዊ አነጋገር አይቀበልም ነበር (Encyc Bri, 2015) ፡፡

‹‹በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ ወይም ጠፍቶ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው›› የሚለውን የአውጣኪን የኑፋቄ

(የክህደት) ትምህርት የሰማው የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፎ ስሕተቱን በማስረዳት አውጣኪ

ከስሕተቱ እንዲታረምና ይህን ትምህርት እንዳያሰራጭ አስጠነ ቀቀው፡፡ አውጣኪ ግን የኑፋቄ ትምህርቱን አላቆመም፡፡ ከዚህ

ላይ አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ይኸውም አውጣኪ ክሪሳፍዮስ ለተባለው ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ኃይለኛ

Holy Trinity University Group Assignment 8


ጠቅላይ ሚኒስትር የንስሓ አባት ስለነበር የልብ-ልብ የተሰማው ይመስላል፡፡ ፓትርያርክ ፍላብያኖስም ይህንን ስለሚያውቅ

ይመስላል አውጣኪን በጣም ሊጫነው አልፈለገም፡፡

ሆኖም ኃይለኛ የነበረ የዶሪሊያም ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውሳብዮስ አውጣኪን አጥብቆ ስለ ተቃወመውና ስለ ከሰሰው፣

የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ እንደተለመደው የመላው አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ተጠርተው ጉባኤ በማድረግ

ፈንታ፣ በእርሱ ስር የሚተዳደሩትን ሃያ ዘጠኝ ጳጳሳትንና ሠላሳ ሦስት የገዳማት አበምኔቶችን ብቻ ሰብስቦ በእርሱ ሰብሳቢነት

በ448 ዓ.ም. በቊስጥንጥንያ አህጉራዊ ሲኖዶስ አድርጎ የአውጣኪን የክሕደት ትምህርት መመርመር ጀመረ (Jhonson,

2012) ፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ላይ እንዲቀርብ ሁለት ጊዜ ተጠርቶ ለመቅረብ አልፈለገም፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጠራ ብቻ ቀርቦ

ስለ ኑፋቄ ትምህርቱ ሲጠየቅ ግልጽ ያልሆነ የሃይማኖት መግለጫ በጽሑፍ አቀረበ፡፡ መግለጫው ግን ስለተከሰሰበት የክህደት

ትምህርት ምንም አይገልጥም፡፡ ሆኖም የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ ግልጥ አድርጎ ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ ከእኛ ጋር አንድ

ነው?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ አውጣኪ አንድ አይደለም በማለት ካደ፡፡ ከክህደቱም እንዲመለስ ቢጠየቅ አሻፈረኝ አለ፡፡ ስለዚህ

ጉባኤው አውጣኪን አወገዘው፡፡ ከአበምኔት ሹመቱና ከክህነት ሥልጣኑም ሽሮ ተራ ሰው አደረገው፡፡ የሮሙ ፖፕ

ለቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› የሚል የሃይማኖት ፎርሙላ የያዘ

ደብዳቤ ልኮለት ስለነበረ፤ አውጣኪ ይህንንም ነበር እንዲቀበል የተጠየቀው፡፡ ይህ ደግሞ ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር የተዛመደ

ስለነበረ አውጣኪ አልቀበልም አለ፡፡

ስለዚህ አውጣኪ ‹‹የቅዱስ ቄርሎስን ሃይማኖት ስለመሰከርኩ እንጂ አንዳች የሃይማኖት ስሕተት ሳይኖርብኝ ያለ አግባብ

ተወገዝኩ፤›› ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ አመለከተ፡፡ እንዲሁም ለሮም ፖፕ ለልዮን ቀዳማዊና ለእስክን

ድርያው መንበረ ፓትርያርክ ለዲዮስቆሮስ ለሌሎችም ጳጳሳት ደብዳቤ ላከ፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም

በበኩሉ የአውጣኪን ኑፋቄና ጉባኤው ስለ እርሱ የወሰነውን ውሳኔ ለፖፕ ልዮን ላከለት፡፡ ፖፑም የጉባኤውን ውሳኔ በማጽደቅ

ምሥጢረ ሥጋዌን የያዘ ደብዳቤ ለፍላብያኖስ በድጋሚ ላከለት፡፡ በደብዳቤውም ውስጥ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያትና አንድ አካል

እንዳለው በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይህም አባባል ከላይ እንደተገለጸው መንፈቀ ንስጥሮሳዊ ነው፡፡

1.5 1.5 ሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ መካሄድ (449)


አውጣኪ በቊስጥንጥንያ እጅግ የተከበረ ሰው ስለነበረና ብዙም ደጋፊዎች ስለነበሩት የእርሱ በ448 ዓ.ም. ጉባኤ መወገዝ

ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ እንደውም ያወገዘው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ንስጥሮሳዊ ነው እየተባለ ይወራና ይወቀስ ጀመር፡፡

ንጉሠ ነገሥቱም የነገሩን ክብደት ተመልክቶ ምናልባትም በአውጣኪ ንስሓ-ልጅ በጠቅላይ ምኒስትሩ ተጽእኖ ይሆናል ዓለም-
Holy Trinity University Group Assignment 9
አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ሲኖዶስ በኤፌሶን እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ (አቡነ ጎርጎርዮስ, 2015) ፡፡

ስብሰባውም በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. በኤፌሶን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ባለፉት ሲኖዶሶች እንደተደረገው ሁሉ የእስክንድርያው

ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ወሰነ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ በመሆኑ ሃያ ሦስት ከሚሆኑ ከግብጽ

ጳጳሳት ጋር ቀደም ብሎ ኤፌሶን ደረሰ፡፡

ፖፕ ልዮን ግን ይህ ስብሰባ እንዲደረግ አልፈለገም ነበር፡፡ እንደውም ለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ እኅት ለብርክልያ ንጉሡ ጉባኤውን

እንዳይጠራ እንድታግባባው ጠይቋት ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ በሐሳቡ ጸንቶ ጉባኤውን ስለጠራ ፖፑም ሦስት

መልእክተኞች ላከ፡፡ በጉባኤው ላይ አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ተሰብስበው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጉባኤው ስብሰባውን

የጀመረው አንድ ሳምንት ዘግይቶ ቢሆንም የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች በዚህ ጊዜ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ የቊስጥንጥንያው

ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ተጠርቶ አልመጣም፡፡ የቀረበትንም ምክንያት አልገለጠም፡፡ ምናልባትም

በእሱ ሰብሳቢነት የተሰበሰበው አህጉራዊ ሲኖዶስ ያወገዘው የአውጣኪ ጉዳይ እንደገና እንዲታይ በመደረጉ ቅር ብሎት ሳይሆን

አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊትም ብዙ መናፍቃን አርዮስም ጭምር መጀመሪያ በአህጉራዊ

ሲኖዶሶች ከተወገዙ በኋላ ነበር ጉዳያቸው እንደገና በዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች እንዲታዩ የተደረገው (ቤተ ሃዋርያት, 2006)፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጳጳሳት ተጠብቀው ባይመጡም ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ የተገኙትን አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ይዞ

በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. ስብሰባውን ጀመረ፡፡ ጉባኤው የተደረገው እንደበፊቱ በኤፌሶን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ

ክርስቲያን ነበር፡፡ ጉባኤውም እንደተጀመረ አውጣኪ ተጠርቶ ስለተከሰሰበት ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ አውጣኪ

በጉባኤው ፊት ቀርቦ በራሱ እጅ የተጻፈና የፈረመበት የእምነት መግለጫ አቀረበ፡፡ መግለጫውም ከመነበቡ በፊት ራሱ እንዲህ

ሲል ጮኾ ተናገረ፡- ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ በግልጥ በምነና (በብሕትውና) ለመኖር ነበር የምፈልገው፡፡ ዛሬ በሕዝብ መካከል

በመገኘቴ ታላቅ ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ሆኖም እምነቴን ለመመስከር ስለሆነ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውንና

አባታችን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ ያስተማረውን እምነት በትክክል እቀበላለሁ፤›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ

የጉባኤው ጸሓፊ የሚከተለውን የአውጣኪ የእምነት መግለጫ ማንበብ ጀመረ፤ መግለጫውም እንዲህ ይላል፡-‹‹ሁሉን በያዘ፣

የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ አምናለሁ፡፡ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ በሚሆን በአንድ ልጁ በጌታ

በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፤ ለእኛ ለሰዎች ሲል ለድኅነታችን ከሰማይ ወረደ፡፡ ሥጋ ለበሰ፤ ሰውም ሆነ፡፡ ታመመ፤ ሞተ፤

በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ይመጣል፡፡

እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚሉ፣ ከመወለዱም በፊት አልነበረም፤ ካለምንም ተፈጠረ የሚሉት፣ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተለየ

Holy Trinity University Group Assignment 10


ነው የሚሉት፣ የእርሱ ሁለቱ ባሕርያት ተቀላቅለዋል ወይም ተዋውጠዋል የሚሉት፣ እነዚህ ሁሉ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ

ክርስቲያን የተወገዙ ናቸው፡፡ እኔም የምከተለው እምነት ይህ ነው፡፡ በዚህ እምነት እስካሁን ኖሬአለሁ፤ ወደፊትም እስክሞት

ድረስ በዚሁ እኖራለሁ፡፡›› የሚል ነበር፡፡

አውጣኪ ይህንን ለጉባኤው ሲያስረዳ ተከትለዉት የመጡትም መነኰሳት አውጣኪ ያቀረበውና የተናገረው ትክክል መሆኑን

ከዚያው በጉባኤው ፊት አረጋገጡ፡፡ ስለዚህ ይህን የሃይማኖት መግለጫ ከአዩና ከሰሙ በኋላ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ማለት

የኢየሩሳሌሙ፣ የአንጾኪያው፣ የኤፌሶኑና የቂሣርው ዘቀጰዶቅያ አውጣኪ በእምነቱ ኦርቶዶክስ ነው በማለት ለጉባኤው

አጽንተው ሲናገሩ ሁሉም አውጣኪ ከተከሰሰበት ኑፋቄ ንጹሕ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰኑ፡፡ ከተላለፈበትም ውግዘት ፈቱት፡

፡ ሥልጣነ ክህነቱንም መልሰውለት ወደ ቀድሞው የሓላፊነት ሥራው እንዲመለስ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሁለት ባሕርይን ሐሳብ

ይቀበል የነበረው የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ አውጣኪን በመወንጀል መግለጫ ሲያቀርብ በዚያ የተሰበሰቡት መነኰሳትና

ምእመናን በታላቅ ድምፅ ‹‹አውሳብዮስ ይቃጠል! አውሳብዮስ በሕይወቱ ይውደም! ክርስቶስን ለሁለት እንደ ከፈለ እሱም

ለሁለት ይከፈል!›› እያሉ ይጮኹ ጀመር፡፡

የቊስጥንጥንያን ፓትርያርክ ፍላብያኖስንና አውጣኪን ያወገዙትን ጳጳሳት የሮሙን ፖፕ ልዮን 1ኛን ጭምር አውጣኪን ያለ

አግባብ በማውገዛቸውና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸው ጉባኤው ካወገዛቸው በኋላ፣ የሚከተለውን አጭር

መግለጫ አወጣ፡- ‹‹ከኒቅያ እስከ ኤፌሶን አባቶቻችን በጉባኤ ተሰብስበው ከወሰኑት ሃይማኖት ሌላ የሚጨምር፣ የሚቀንስ

ወይም የሚያሻሽል ቢኖር የተወገዘ ይሁን፡፡›› ዘግይተው የደረሱት የፖፑ መልእከተኞች ዩልዮስና ሬናቱስ የተባሉት ጳጳሳትና

ዲያቆን ሂላሩስ ከፖፑ የተላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ እንዲነበብ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው ‹‹ክርስቶስ

ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ስለሚልና ይህም ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር ስለሚመሳሰል ጉባኤው እንዲነበብ አልፈቀደም፡፡

በዚህም ምክንያት የፖፑ መልእከተኞች ተቀይመው ወዲያውኑ በድብቅ ከጉባኤው ወጥተው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡

የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ጸደቀ፡፡ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በኤፌሶን 2ኛ ጉባኤ

እንደተወገዘ ወዲያውኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ የዚህን ጉባኤ ውሳኔ ሲሰማ የሮሙ ፖፕ ልዮን ቀዳማዊ እጅግ ተናዶ

ጉባኤውን ‹‹ጉባኤ ፈያት (የወንበዴዎች ጉባኤ)›› ብሎ ጠራው፡፡ የጉባኤውንም ሊቀ መንበር ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አወገዘው፡

፡ ከእስክንድርያ ጋር የነበረውንም ግንኙነት ጨርሶ አቋረጠ፡፡ ፖፑ ይህን ሁሉ ያደረገው እሱ የላከው የሃይማኖት ነክ ደብዳቤ

በጉባኤው ላይ ስላልተነበበና የእርሱም መልእክተኞች በጉባኤው ላይ በሙሉ ባለመካፈላቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ፖፑ ለንጉሠ

ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ የኤፌሶኑን ጉባኤ የዲዮስቆሮስ ጉባኤ ብሎ በመጥራት በጉባኤው ላይ ያለውን ቅሬታ ከገለጸ በኋላ፣

Holy Trinity University Group Assignment 11


ሌላ ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ (ጉባኤ) እንዲጠራ ጥብቅ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እንዲረዳውም የምዕራቡን ክፍል ገዥ (ንጉሥ) የነበረውን

ሣልሳዊ ዋሌንቲኒያኖስን (Valentinianus III) እና ሚስቱን ንግሥት አውዶቅሲያን አጥብቆ ለምኖ ነበር፡፡

እነዚህም ባለሥልጣኖች እያንዳንዳቸው ሐሳቡን በመደገፍ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡

ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ግን ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው የቅዱሳን አባቶች ጉባኤ መሆኑን ገልጦ በመጻፍ

ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን ገልጦ አሳስቧቸዋል፡፡ በተጨማሪም የምዕራቡን ንጉሥና ንግሥት

በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መክሯቸው ነበር፡፡ ፖፕ ልዮን ግን ሌላ ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ዳግማዊ

ቴዎዶስዮስን አጥብቆ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ ሆኖም የፖፑ ጥረት ሁሉ ውጤት አላስገኘም፡፡ ምክንያቱም ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ

ለ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ ታላቅ አክብሮት ስለነበረውና ውሳኔውንም በሚገባ ስላጸደቀው ነበር፡፡

Holy Trinity University Group Assignment 12


ምዕራፍ ሁለት - የጉባዔው መደረግ

1.6 2.1 መነሾ


አስቀድሞ በ325 ዓ.ም በኒቂያ ፤ በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥኒያ ፤ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን የተደረጉት ጉባኤዎች (ሲኖዶስ)

ቤተክርስቲያን የገጠማትን ፈተና በመጋፈጥና በአንድ ድምጽ በመወሰን የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ ጉባኤዎቹ የሚጠሩበት

ምክንያትም ሐዋርያዊ ያልሆነ አዲስ የክህደት ትምህርት ተከሰተ ሲባል ነበር፡፡ አራተኛው ጉባኤ(ሲኖዶስ) ሲጠራ ግን የተጠቀሰ

ምክንያት አልነበረም፡፡ ውጤቱም የዶግማ ልዩነት የፈጠረና ለሁለት መከፈልን ያስከተለ ነበር፡፡ ለስልጣን ሽኩቻው መነሻ

የነበረው የእስክንድርያን መንበር ነጥቆ ለቁስጥንጥንያ ለመስጠት እና የበላይ ነን ያሉ የነበሩ የሮማው ጳጳስ በእስክንድርያው

ፓትርያርክ መወገዝ የፈጠረው የመበቀል ፍላጎት ነበር።

1.7 2.2 የጉባዔው ምክንያቶች


የኬልቄዶን ጉባኤ ዓላማው ምን እንደሆነ እንዳለፉት ጉባኤዎች ግልጥ ምክንያት አልነበረውም: ከውጤቱ እንደምንረዳው ግን

ሁለት ነገሮች አሉበት።

❖ ሮም ፤ እስክንድርያ ፤ አንጾኪያ የነበረውን የፕትርክና መንበር ወደ ሮም ፤ቁስጥንጥንያ ፤ እስክንድርያ በማድረግ

የቁስጥንጥንያን ስርዋጽ ለማስገባት ይህም የእስክንድርያን መንበር ዝቅ አድርጎ ተራ ያልነበረውን ቊስጥንጥንያን ባለ

መንበር ለማድረግ ነው

❖ አውጣኪን የኑፋቄ ትምህርት ከሊዮን ጋር በሁለት በሕርይ የኑፋቄነት ስለሚስማማ የሁለት ባሕሪን ኑፋቄ ትምህርት

ለማስፋፋት ይህ ደግሞ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘውን የንስጥሮስ ትምህርት በአዲስ ስም ሰይሞ ለማደስ

ሲሆን

❖ ዲዮስቆሮስ ቀድሞ አውጣኪን ስላወገዘው ዲዮስቆሮስን ለመበቀል ነበር።

በስብሰባው ላይ ከነበሩት ሌሎች ተጨማሪ ክንውኖች በካከል የቤተክርስቲያንን የስልጣን ተዋረድና ክፍፍሎችን ለመዳሰስ፣

የኒቅያ ጉባዔ ሃይማኖታዊ ውሳኔወችን ፣ ለኣውግዞ ንስጥሮስ በቅዱስ ቄርሎስ የተጻፉትን ሁለት መልዕክቶችን እንዲሁም የፖፕ

ሊዮንን ሃይማኖታዊ መግለጫ ለማጽደቅ ነበር።

Holy Trinity University Group Assignment 13


1.8 2.3 በጉባዔው ውስጥ ሚና የነበራቸው ሰወች
በተለያዩ ጊዜያትም የተለያዩ ሰዎች የስህተት ትምህርትን ይዘው ተነስተዋል ንስጥሮስም ሙሉ በሙሉ ከቤተክርስቲያን

አልተለየም ነበርና የሁለት ባህርይን ሀሳብ ይዞ ተነሳ። የሁለት ባህርያትን ቅድመ አለምና ድህረ አለም በማለት በመነጣጠል በስጋ

የወለደችው ወልድ ሁለት ባህርያት አሉት በማለት (ዲኦፍሳይት) ሲያስተምር በዚህ ትምህርቱም በአምላክነቱ የፈጣሪን ስራ

ሲሰራ በስጋ ባህርዩ ደግሞ የስጋን ስራ ይሰራል በማለት ተዋሕዶን የካደ መናፍቅ ነበር ።

ሌላው አውጣኬ የሚሉት ደግሞ ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ነበረው ግን የመለኮት ባህሪው ከሰው ባህሪው ስለሚበልጥ ያንን

ውጦታል/ መጦታል / ስለዚህ አንድ ባህሪይ (ሞኖፈሳይት) ነው አሁን ያለው የአምላክነት ባህርዩ ብቻ ነው በማለት ያስተምር

ነበር።

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን ትክክለኛውን አስተምህሮ ያስቀመጠ ሲሆን አውጣኬ እንደሚለው የአምላክነት ባህርዩ የሰው ባህርዩን

በመዋጥ/ በመምጠጥ አንድ ባህርይ የሆነ ሳይሆን እንዲሁም ንስጥሮስ እንደሚለው ቅድመ አለምና ድህረ አለም በመነጣጠል

ሁለት ባህርይ / ዲዮፍሳይት ሳይሆን በፍፁም ተዋህዶ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የሆነ አምላክ ነው በማለት ትክክለኛውን

አስተምህሮ አስቀምጧል ። ይህም ( ሚዮፍሳይት) ይባላል። በዘመናችንም ይህ አስተሳሰብ ፈፅሞ የቆመ አይደለም ። በተለያየ

መልኩ እየተገለፀ ይገኛል።ነገር ግን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደው

ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፅንሰት ጀምሮ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የሆነ

አምላክ ነው ። ሰው ስጋና ነፍስ የተዋህዱበት ፍጥረት ሲሆን አንድ ሰው በስጋውና በነፍሱ ተለያይቶ አይጠራም ። እገሌ ተብሎ

በጥቅሉ ይሰየማል እንጅ። አንድ ነገር ሲያከናውንም እገሌ እንዲህ አደረገ ይባላል እንጅ በስጋው እንዲህ አደረገ በነፍሱ ደግሞ

እንዲህ አደረገ እንደማይባል ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከተዋህዶ በኋላ በሰውነቱ እንዲህ አደረገ በመለኮቱ ደግሞ እንዲህ አደረገ

ብሎ በሁለት ከፍሎ ማየት ስህተት ነው። ይህ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቀጥተኛ ትምህርት ነው (Philip Henry, 1900)።

1.9 2.4 የሊዮን ደብዳቤ


የሊዮን ደብዳቤ እና አቋሙ አምስት ነጥቦች አሉት

❖ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ኋላም ሰው ሆኖ ተወለደ

❖ መለኮት እና ስብእና ያለመቀላቀል በሱ ይኖአሉ

❖ እያንዳንዱ ባሕሪ (አምላካዊ ባሕሪ መለኮትነት ፣ ሰዋዊ ባሕሪ ስጋዊነት) ያለመቀላቀል የግል ባሕሪውን ይዞ ይኖራል

❖ የሁለቱም ባሕሪ ሀብት ላንዱ አካል በእኩልነት ይገኛል


Holy Trinity University Group Assignment 14
❖ ከመዋሀድ በፊት 2 ፤ ከተዋሀደ በሁላ 1 ማለት ሞኝነት ነው የሚል ነበር ።

1.10 2.5 የጉባኤው ሂደት


የኬልቄዶን ጉባኤ ጥቅምት ስምንት ቀን 431 ዓ.ም እንዲሆን ተወሰነ፡ በተባለው ቀን 636 ሰዎች ተሰበሰቡ: (ይህ ቊጥር

የ318ቱን ሊቃውንት ቊጥር ያጥፋል ይህም የኾነው ጉባኤው ከኒቅያ ይበልጣል ለማለት ነው፡) ጉባኤውን ያዘጋጁትም የቤተ

መንግሥት ባለ ሥልጣኖች የጦር አለቆች ናቸው። የጉባኤው ሊቃነ መናብርት የነበሩት የልዮን እንደራሌዎች የቊስጥንጥንያው

ሊቀ ጳጳስ አናቶሊዮስና ሌሎች የመንግሥት ሹማምንትና የጦር አለቆችም ነበሩበት፡፡ በዚህ ጉባኤ ለመገኘት ዲዮስቆሮስም

ከእስክንደርያ መጣ፤ 25 ኤስ ቆጶሳት ተከትለዉት ነበር: ከነዚህም ብዙዎቹ ከ20 ዓመታት በፊት ከቄርሎስና ከሱም ከራሱ ጋር

አብረው በኤፌሶን ጉባኤ የተሳተፉና የተዋሕዶን ምሥጢር አጣርተው የሚያውቁ ነበሩ ይህን ጉባኤ በንስጥሮሳዊነት ሲያሳሙት

የሚኖሩ ምክንያቶች አሉ: እነሱም ሀ/ 431 ዓ.ም በኤፌሶን በንስጥሮስነታቸው የተወገዙ ሰዎች ወደዚህ ጉባኤ እንዲመለሱ

መደረጉ ለ/ የልዮን ጦማር ያዘለው መልእክት ግልጥ ያለ ንስጥሮሳዊ ስለኾነ ነው። ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት የጉባኤው

ተሳታፊዎች ሁሉ ቦታ ቦታቸውን ይዘው እንደ ተቀመጡ በሊቀ መንበርነት የተሠየሙት የሮም መልእክተኞች የሚከተለውን

ተናገሩ «የክርስቶስ እንደራሴ የጴጥሮስ ወራሽ የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ራስ ቅዱስ ቅዱሳን አባታችን ልዮን ቀዳማዊ ያዘዙን

ትእዛዝ ኣለ፧ ይኸውም ከአመጸኛውና ከአሐዲው አባታችንን በድፍረት ካወገዘው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ከዲዮስቆሮስ ጋር

አብረን በጉባኤ እንዳንቀመጥ ነው። ዲዮስቆሮስ በዚህ ጉባኤ ከተቀመጠ እኛ ወጥተን እንኼዳለን አሉ ይህን ተናግረው ሲጨርሱ

በግልምጫና በደም ፍላት የልዮን ደጋፊዎች ሁሉ ተነሥ እዚህ መቀመጥ የለብሀም፤ ተከሳሾች የሚቆሙበት ቦታ ቁም ብስው iዲ

ቆስ ïîት ዲዮስቆርስም 1ü ጊ ተቀመጠት ተነቶ የሚከተውን ተረ። አንድ qሕርይ ታችን ሁለቱን አጣፍተን አይደለም (አንደ

አውጣኪ) ወይም አንዱን ከሌላው ለይተን ገንጥለን አይደለም (እንደ አቡሊናርዮስ) ለውጠንም አይደለም ሰት ሚጠት ቱሳሔ

የሚል ቢኖር የተወገዘ ነው አለ: ይህን በተናገረ ጊዜ ሳቲኖችና ግሪኮች አውጣኪም ያለው ይህንኑ ነበር ዲዮስቆሮስም ይህንኑ አለ

ውጣ! ውጣ እያሉ ጮሁበት፡፡ በዚህ ጊዜ እሱም የምንነቀፈው በንስጥሮስ ዘንድ ብቻ ነው ብሎ መንበሩን ላለማስደፈር

ውጣላቸው፤ ሁለተኛም ወደነሱ አልተመለሰም፡፡ ዲዮስቆሮስ ከወጣ በኋላ ከ20 ዓመታት በፊት በ3ኛው ጉባኤ ከንስጥሮስ ጋር

የተወገዙት እነ ቴዎዶሪጦስና እነ ኢባን በጉባኤው ሙሉ የአባልነት መቀመጫ እንዲሰጣቸው ተፈቀደላቸው፤ ይልቁንም

ቴዎዶሪጦስ በዲዮስቆሮስ ላይ የማቀርበው ልዩ ክስ አለኝ ብሎ ተናግሮ ስለ ነበር ግሪኮችም ሆኑ ለቲኖች እንደ ጠላት የቆጠሩት

ዲዮስቆሮስን የሚያጋልጥልን መስሏቸው «አክሲዮስ አክሲዮስ» ይደልዎ! ይደልዎ! እያሉ ተቀበሉት፡፡ ጉባኤውን ንስጥሮሳዊ

ካሰኙት ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው (ንስጥሮሳውያን የጉባኤው አባል በመኾናቸው)፡፡ በዚህ ጊዜ ማስት ንስጥሮሳውያን እነ ኢባን

Holy Trinity University Group Assignment 15


የጉባኤው አባላት እንዲሆኑ በተፈቀደ ጊዜ ከቄርሎስ ጋር በኤፌሶን ጉባኤ የነበሩት አረጋውያን ጳጳሳት በሙሉ ድምፅ በአንድ ላይ

ሁነው ቴዎዶሪጦስና ኢባን እንዲወጡላቸው «የንስጥሮስ መምህር ቴዎዶሪጦስ ይውጣ ቄርሎስ ኣውግዞታልና ቴዎዶሪጦስን

ካስገባን ቄርሎስን እናስወጣ» እያሉ ተቃውሟቸውን ገለጡ ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ ጉባኤው በጩኸት ስለቀለጠ የቤተ

መንግሥቱ ጸጥታ አስከባሪ ጓድ ገብቶ ዝም አስኛቸው:

ከዚህ በኋላ ልዮን በፊት ወደ ፍሳብያኖስ የላከውና አሁን ወደዚህ ጉባኤ የላካቸው መልእክቶች ተነበቡ: በዚህ ጦማር ውስጥ

ከአንድ እስከ አምሰት ተራ ቊጥር በዘረዘርናቸው ዐረፍተ ነገሮች ውስጥ ከመጀመሪው በቀር አራቱ የሁለት ባሕርይን ትምህርት

በይፋ የሚደግፉ ናቸው፡፡

የልዮን ጦማር በተነበበ ጊዜ ከግሪኮች እንዳንዶቹ በችኮላ ፤ ሳቲኖችም «ይህች ሃይማኖት የአባቶቻችን ናት: ይህች ሃይማኖት

የሐዋርያት ናት: ጴጥሮስ በልዮን አንደበት ትክክለኛይቱን ሃይማኖት መሰከረ እያሉ ጮሁ። ነገር ግን ይህ ትምህርት የንስጥሮስና

የልዮን ነው እንጂ የጴጥሮስ አልነበረም (ኤፍሬም, 2013)።

ይህ ጦማር ሲነበብ ያጨበጨቡ ቢኖሩም ባንጻሩ ከግብጽ ከሶርያና ከአርመን የመጡት ደግሞ በዚህ ንስጥሮሳዊ ትምህርት

የማይስማሙ መሆናቸውን እየገለጡ ጉባኤውን አቋርጠው ወጥተው ሔዱ ግሪኮችና ላቲኖች ባንድ ወገን የቤተ መንግሥቱ ባለ

ሥልጣኖች በሌላ ወገን እየሆኑ መስማት አለባችሁ እያሉ ቢያስፈራሯቸውም የልዮንን ጦማር የተቃወሙት ክፍሎች

የሚመልሱት መልስ «ክርስቲያን ማንንም አይፈራም፤ አእሳት ብትጥሉንም ለምደነዋል፣ ሰው ከተፈራ ሰማዕታት በቤተ

ክርስቲያን ባልነበሩም ነበር፡» የሚል ነው፡፡ ለነገሩማ እንዲያው ግሪኮችና ላቲኖች አፋቸውን fውሸት አበላሹ እንጂ የልዮን

ጦማር ንስጥሮሳዊ ለመሆኑ ምስክሩ ራሱ ንስጥሮስ ነው። ንስጥሮስ ከመሞቱ ቀደም አድርጎ ይህን የልዮን ጦማር አይቶ

የሚከተለውን ተናግሮ ሙቷል፡፡ «ይህችን ጦማር አግኝቼ ባነበብሁ ጊዜ ደስ አለኝ እግዚአብሔርንም kመሰገንሁት የሮም ቤተ

ክርስቲያን አስን ነ÷ የበትን ትmኛ ሃይማኖት ተnችና» iል፡፡ Fው የራሱ7 እምነት ልዮን ገልብቦ ስላጸደቀለት ነው፤ ነቀፋ

የሌለበት ትክክለኛ ሃይማኖት ያለው፡: ነገር ግን ሞት ቀድሞት የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔ አልሰማም።

ግሪኮች ያን ጊዚ ጓጉተው የሚጠባበቁት በማንኛውም መንገድ ልዮንን አስደስተው የእስክንድርያን ሊቃነ ጳጳሳት ስም

አጥፋፍተው አክፋፍተው የኛ ነው የሚሉትን በመንበር ተራ ቊጥር ያልነበረውን የቊስጥንጥንያ መንበር ከቊጥር ለማስገባት

ስለነበር ነው: አንዳንድ የተከራከሩ ቢኖሩም የቊስጥንጥንያ ቤተ መንግሥትና የልዮንን ኃይል ስለ ፈሩ አልገፉበትም። ደፍረው

በልዮን ጦማር አንስማማም ያሉትም ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል፡፡ በጉባኤው የመጀመሪያ ስብሰባ ዲዮስቆሮስ ተወገዘ። ስለ

Holy Trinity University Group Assignment 16


ተወገዘበትም ምክንያት በተሰጠው መግለጫ ዲዮስቆሮስ የተወገዘው በሃይማኖት ሳይሆን በሌሎች ሁለት ምክንያቶች መሆኑ

ተገለጠ፡፡ እነዚህ አንደኛ ከሊቀ ጳጳሳት ልዮን ጋር ባለ መስማማቱና ሁለተኛ ወደ ጉባኤው ሁለተኛ ተጠርቶ ባለ መምጣቱ

እንደሆነ ተነግሯል: ከአውጋዦቹ አንዱ የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ አናቶልዮም ይህንኑ ገልጧል፡ ፡

ሲያያዝ በመጣው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንድ የቤተ ክርስቲያን መምህር አባት፤ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ የሚለየው ወይም

ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመለሰው የሚከተሉት ሁኔታዎች ክተፈጸሙ በኋላ ነው:፡ ጉባኤ ይሰበሰባል ባለ ጉዳይ ይቀርባል፤ የባለ

ጉዳይን ሃሳብ ስምቶ ጉባኤው ይነጋገርበታል፤ ውሳኔ በድምፅ ብልጫ ይሰጣል፤ ውግዘቱ ወይም ይቅርታው ከዚያ በኋላ ነው

(ኅሩይ ኤርሚያስ, 2010 ዓ/ም)፡፡ በኬልቄዶን ጉባኤ ግን ይህ ሁሉ አልነበረም። ዲዮስቆሮስ ተከሳሽ መሆኑን አላወቀም፣

ሃይማኖቱንም አልተጠየቀም፤ ወደ ጉባኤው መጣ ጉባኤው ሥራ ከመጀመሩ በፊት እንዲወጣ ታዘዘ፤ ሃይማኖቱን መስክሮ ወጥቶ

ሔደ፤ ከዚህ በኋላ በሌለበት ተወገዘ የተወገዘውም በሃይማኖት ሳይሆን ከልዮን ባለ መስማማቱና ወደ ጉባኤው ሲጠሩት አሻፈረኝ

በማለቱ ነው የሚል መግለጫ ወጣ፡ እዚህ ላይ ጉባኤ ኬልቄዶን በቤተ ክርስቲያን ያልተለመደና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን

የሚያፈርስ ወንጀል ፈጽሟል ለማለት ይቻላል (አቡነ ጎርጎርዮስ, 2015)። ይኸውም አንደኛ ከጉባኤ ማባረር ሲሆን ሁለተኛ

ደግሞ ውግዘት በሌለበት መፈጸም ነው።

ዲዮስቆሮስ ከተወገዘ በኋላ ንግሥት ብርክልያ በግል አስጠርታ ሐሳቡን እንዲለወጥ በልዮን ጦማር እንዲስማማ መከረችው፡፡

ዲዮስቆሮስ ግን የሚያምነውን የሚያውቅ መንፈስ ብርቱ ነበርና እሺ አላላትም:።በዚህ ጊዜ ጽሕሙ እስኪነጫጭና ጥርሶቹ

እስኪወልቁ አስደበደበችው። እሱም መደብደቡን በአኮቴት ተቀብሎ የተነጨውን ጽሕሙንና የወለቁት ጥርሶቹን ባንድ ላይ

ቋጥሮ «ዝንቱ ውእቱ ፍሬ ሃይማኖት» ይህ የሃይማኖት ፍሬ ነው» ብሎ በግብጽ ለሚኖሩ ምእመናን ልኮላቸዋል።

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ዐቢይ ዓምደ ሃይማኖት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አርበኛ የሚል ቅጽል

ተሰጥቶታል፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ማለት ስድቡም መወገዙም መደብደቡም ካበቃ በኋላ በደሴተ ጋግራ እንዲታሰር ከንጉሡ

ከመርቅያም ትእዛዝ ወጣ። በስደቱም ጊዜ ጴጥሮስና ቴዎፒስቶስ የሚባሉ ሁለት መነኮሳት ዲቆናት ብቻ ተከትለዉት ነበር:

በስደትም እንዳለ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሥራ አልፈታም ትምህርት ኣዘል መልእክቶችን እየጻፈ በመላክ የእስክንድርን ቤተ ክርስቲያን

ሲያጽናናት ቆይታል። ምእመናንና መነኮሳትም በመምህራቸው ላይ የደረሰውን ግፍ እያስታወሱ በተዋሕዶ ይማኖታቸው ጸኑ፡

ዲዮቆሮስን ያወገዘውና እንዲሰደድም የተስማሙ ይህ ጉባኤ በልዮን ጦማር ላይ ብቻ ተፈራርሞ ለመበታተን አስቦ ነበር: ነገር

ግን ንጉሡ መርቅያን የለም፤ ከተሰበሰባችሁ በኋላ የራሳችሁንም የጋራ መግለጫ ሳታሰሙ ልትሔዱ አትችሉም ስላላቸው

ደንግጠው የጉባኤው ውሳኔ ነው በሚል ስያሜ አንድ አርቃቂ ቡድን ተቋቋመ። ይህ የመጀመሪያው አርቃቂ ቡድን የተስማማበት

Holy Trinity University Group Assignment 17


«ክርስቶስ ከሁለት ባህርያት የተገኘ ነው» የሚል ሐረግ ነበረበት:፡ ነገር ግን ይህ ሐረግ ቄርሎስና ዲዮስቆሮስ የሚሉት ስለሆነ

መኳንንቱ ተቃወሙ። በዚህ ጊዜ ረቂቁ እንደገና ወደ ንጉሡ ቀረበ: ንጉሡም ባስቸኳይ ይህ ተሠርዞ ሌላ ረቂቅ እንዲወጣ አዘዘ

መጨረሻም ከዚህ በሚከተለው ረቂቅ ተስማሙ።

1. አምላክ ፍጹም ወሰብእ ፍጹም፤ ኅቡር ህላዌ ኣብ በመለኮቱ፤ ኅቡረ ህላዌ ምስሌነ በትስብእቱ፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ፤

በአምላክነቱ ከአብ ጋር አንድ ነው በሰውነቱ ከኛ ጋር አንድ ነው፡፡

2. እሙረ በክልኤቱ ህላዌያት (ሕርያት) ዘእንበለ ፍልጠት ውላዌ ወቱስሕት፡

በሁለት ባሕርያት የሚታወቅ፤ ያለመለየት፤ ያለ መለወጥ ያለ መቀላቀል

3. በተዋሕዶ ኢያእተተ ፍልጠተ ማእከለ ክልኤቱ ህላዌያት (ባሕርያት)

ተዋሕዶው በባሕርያት መካከል ያለውን ልዩነት አላጠፋውም።

4. ወህብታተ ክልኤቱ ሕላዌያት ይትዐቀቡ በበህላዌሆሙ፤ ወእምክልኤሆሙ ይትረከብ አሐዱ ኣካል።

የሁለቱ ባሕርያት ገንዘቦች ሀብቶች) በየባሕርያቸው ተጠብቀው ሁለቱም አንድ አካልን ያስገኛሉ፡፡

ከዚህ በላይ ከአንድ እስከ አራት ተራ ቊጥር የተመለከቱት ነጥቦች ያሉበት አንድ ረቂቅ አውጥተው ተፈራርመው ለንጉሡ

አቅርበዋል። ይህ የሃይማኖት ረቂቅ ንባቡም ምሥጢሩም በዚህ ጉባኤ የተሰበሰቡት ሰዎች አይደለም፤ ንስጥሮስ ግልጥ አድርጎ

«ሁለት አካል፤ ሁለት ባሕርይ፧ ሁለት ግብር አምላክ በማርያም ልጅ አደረ። በተራክቦተ መለኮት፤ ወልደ ማርያም ወልደ አብ

የመባልን ትርሲት አገኘ፤» ያለውን ልዮን ለማደናገር አንድ አካል ሁስት ባሕርይ ሁለት ግብር ብሎ ያቀረበላቸውን እነሱም በባለ

ሥልጣኖች ተጎትጉተው ግማሹን ከቄርሎስ ግማሹን ከልዮንና ከንስጥሮስ ወስደው አቅርበውታል።

በጉባኤው መጨረሻ ላይ ንጉሡ መርቅያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ ወደ ጉባኤው አዳራሽ ገቡ። በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡት ሁሉ

በደስታና በዕልልታ ተቀበሏቸው:፡ ንጉሡ ከዚህ አያይዞ የሚከተለው ተናገረ:፡ «በነገሥታቱ ሲደረግ እንደ ነበረው ሁሉ እኔም

የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ከያዝሁ ጀምሬ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲደረግ ምኞቴ ነበር» ሲል ለጉባኤው አሰማ፡: ጉባኤውም

ለንጉሡና ለንግሥቲቱ ውሳኔው ካስረዳ በኋላ ንጉሡን የሃይማኖት የበላይ ጠባቂ አድርገው ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ ብለው

ሰይመውታል።

Holy Trinity University Group Assignment 18


ይህ ጉባኤ በምሥራቃውያን ዘንድ ጉባኤ አብዳን ጉባኤ ከለባት ይባላል። ውሳኔውን የተቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትም

መለካውያን ይባላሉ፤ ንጉሣውያን፤ ፈጻምያነ ፈቃደ ንጉሥ፤ ንጉሥ ያሉት ትክክል ነው ባዮች የቤተ መንግሥት ራት አግባዎች

ማለት ነው። አብዳን ከለባት መባላቸውም በፊት ሐዋርያት ኋላም ሊቃውንት እነ አትናቴዎስ፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ እነ ቄርሎስ

ጠብቀው ያቆዩትን የቤተ ክርስቲያን መብት በቊስጥንጥንያ ቤተ መንግሥት አስረክበዋልና እነዚህ መለካውያን 30 አንቀጾች

ያለው ቀኖናም ሠርተዋል፤ በዚህ ቀኖና በ28ኛው አንቀጽ «የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ለሮሙ ሁለተኛ እንዲሆን

ተፈቅዶለታል። ቊስጥንጥንያ አዲስ ሮም ስለሆነች» ይላል (newadvent, 2015)። በዚህ ንባብ ግሪኮች የተመኘነውን አገኘን

ብለው ደስ ሲላቸው ልዮን ግን ይህንን ቀኖና አልተቀበለውም።

ወደ እስክንድርያ እንመለስና ዲዮስቆሮስ በደሴተ ጋግራ በእሥር እንዳለ የቊስጥንጥንያ ቤተ መንግሥት ከሮማው ፓፓ ጋር

በመነጋገር ፕሮቴሪዮስ የሚባለውን መለካዊ መነኲሴ የእስክንድርያ ፓትርያርክ እንዲሆን ሹሞ ላከው። ነገር ግን ዲዮስቆሮስ

ቢታሰርም ምእመናኑና ካህናቱ አባታችን ነው ብለው የሚያምኑት ዲዮስቆሮስን ስለሆነ አዲሱን ፓትርያርክ አንቀበልም ኣሉ፡፡

በዚህ ምክንያት መርቅያን ተናዶ እሱ የሾመውን ያለ ምክንያት በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ 2ሺህ ጦር ወደ ግብጽ ላከ። ነገር

ግን የሕዝብን ተቃውሞ የጦር ኃይል ስለማይመልሰው የምእመናኑ ኃይል እየበረታ ሔደ: ብጥብጡም ውስጥ ፕሮቴሪዮስ

ተገደለ። በመካከሉ በ454 ዓ.ም የተዋሕዶ አርበኛው ዲዮስቆሮስ በእስር እንዳለ ዐረፈ። እሱ ካረፈ በኋላ ሦስት ዓመት ቆይተው

የግብጽ ምእመናን ራሳቸው መርጠው ጢሞቴዎስ የተባለውን አባት ፓትርያርክነት ሾሙት። እሱም ለተዋሕዶ እምነት ተቆርቋሪ፤

የቄርሎስ የዲዮስቆሮስ ተከታይ ስለ ነበር በዲዮስቆሮስ መታሰር ታውካና ተበጥብጣ የነበረችው እስክንድርያ በእርሱ መሾም

ተጽናናች፤ ተረጋጋች።

Holy Trinity University Group Assignment 19


ምዕራፍ ሶስት- ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔወች

1.11 3.1 በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔወችና ስህተቶቻቸው


በተራ ቊጥር ኣንድ ያለው ንብብ ከቄርሎስ የተወሰደ ነው፡፡ እነሱ ግን «አምላክ ወሰብእ» የሚለውን ንባብ ለሁለት ባሕርይ

ምስክር አድርገው ወስደውታል፡ ዘይቤውን ከነምሥጢሩ ከነምስክሩ ለሚያውቅ ግን «አምላክ ወሰብእ» የሚለውን ንባብ ሁለት

ባሕርይ አይነካካውም «ወ» እዚህ ላይ አጫፋሪ አይደለም: «ሰማይ ወምድር» ሰማይና ምድር፤ «መላእክት ወሰብእ» ሰውና

መላእክት፤ እንዳለው «ኣምላክ ወሰብእ« የሚለውም ንባብ» አምላክና ሰው» ተብሎ በምሥጢረ ሥጋዌ አይፈታም «ወ» እዚህ

ላይ «ዋዌ» ነው፡፡

«ድንግል ወእም» እንዳለው፤ ፍችው እናትም ድንግልም ማለት ነው፤ እናትና ድንግል አይባልም በምሥጢረ ሥጋዌ «አምላክም

ሰውም» ተብሎ ይፈታል እንጂ «አምላክና ሰው» ተብሎ አይፈታም፡: ጽርዓውያን ግን አገባባቸው ሰፊ «አምላክ ወሰብእ»

ማለትም ስለሆነ በዋዌው ፈንታ ከሁለቱ ስሞች አንዱን ጎርደው «ቴዎስ (አምላክ) አንትሮፓስ (ሰው) «ያስውን ቴአንትሮ

ፓስብለው ያናብቡና በቅጽልም በዋዌወም ይፈቱታል: በዋዌ ሲፈታ እንደ ግእዙ ነው። በጥቅልነት ሲፈታ ግን ስው የሆነ አምላክ

ማለት ነው። ይሀን የመሰለ ብዙ ንባብ አላቸው ክርስቶስ፤ ሰው የኾነ አምላክ እንጂ አምላክ የሆነ ሰው አይባልም። ይ ከሆነ

ጳውሎስ ሳምሳጢና ንስጥሮስ እንዳሉት በገድል በትሩፋት የከበረ ዕሩቅ ብእሲ ነው ያሰኛልና።

በሁለተኛው ተራ ቊጥር ያየነው «ተገናኙ» «ተራከቡ» «አብረው ይኖራሉ» የሚለው ቃል ተዋሐደ በሚለው ግሥ የተለወጡ

የንስጥሮስ ግሶች ናቸው:፡ እነዚህ ግሶች የሚያሳዩት የአምላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መኾን አይደለም፡፡ ጽምረት ነው

እንጂ፤ እንደ ኀዳሪና ማኅደርና እንደ ባልና ሚስት «ተዋሕዶ» ግን እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ ነው። በሦስተኛው ተራ ቊጥር

እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል ያለው በተዋሕዶ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ለቃል መሆኑንና

መገናዘቡን፤ መወራረሱን ሲገልጥ ቅዱስ ቄርሎስ «እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል» ያለውን

ለማስተባበል ነው። ይህን የቅዱስ ቄርሎስን ትምህርት መለወጥ የሥጋዌን ምሥጢር ያፋልሳል፤ ግብር ይከፋፍላል። በአራተኛው

ተራ ቊጥር «የሁለቱም ባሕርያት ህብታት ላንዱ አካል በእኩልነት ይገኛሉ» ማለት ደግሞ እንደ ሁለት እጅ እንደ ሚዛን ጆሮ

ማለት ነው:፡ ይህንንም ልዮን በመደጋገም ክርስቶስ እንዷ ጊዜ እንደ አምላክነቱ ሌ4 ጊዜ እንደ ሰውነቱ ይሠራ ነበር እንጂ ንድ

ጊዜ የአምላክነትንም የሰውነትንም ሥራ አልሠራም ብሏል: ይህም አስተሳሰብ በቃሉ ኣዞ በእጁ ይዞ የሠራውን የሥግው ቃል

ተአምራት የሚያናውጠው ሁኖ ተገኝቷል። ጴጥሮስ አካል ከህልውና ተገልጦለት «አንተ ውእቱ ወስደ እግዚአብሔር ሕያው»

Holy Trinity University Group Assignment 20


የሕያው እግዚአብሔር ልጅ አንተ ነህ ብሎ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን በቂሳርያው ጉባኤ መስክሮ ፈተናውን

ያለፈ አርበኛ ነው፡: እንደ ልዮን የመለኮትህ ባሕርይ የእግዚአብሔር ልጅ ነው አላለም፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም «ቃል በሥጋ ሞተ»

ብሎ ያስተማረው ከቅዱስ ጴጥሮስ ያገኘውን ትምህርት ነው:፡ «ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ» ብሎ ያስተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ

ነው «የሞትም የሐይወም ባለቤት ራሱ ሥግው ቃል ነውና ማለት ሞትም ትንሣኤም የሥግው ቃል ነው:፡ የልዮን ጦማር ግን

የሚለው «ሥጋ ሞተ በኅድረተ አምላክ ቃል» ነው። ይህም ማለት «ሞተ» የሚለው አንቀጽ ሥጋን ለይቶ ይመከታል ማለት

ነው፡፡ ይህንንም ትምህርት ሐዋርያት ፈጽመው ያላስተማሩት መሰረት የሌለው ትምህርት ነው (ሉሌ መላኩ, 1986 ዓ/ም )።

በሁለተኛው ተራ ቊጥር ሁለት ባሕርያት የታወቀ የሚለው በግልጥ መልኩን ሳይለውጥ የገባ የንስጥሮስ ንባብ ነው፡፡ ያለ መለየት

ያለመለወጥ፤ ያለ መቀላቀል የሚለው ምንታዌን ለመሸፈን የገባ ነው።

በሦስተኛው ተራ ቊጥር ያለው ንባብ «ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ» «በተዋሕዶ ሁለትነት ጠፋ» የሚለውን ትምህርት

የሚያፋልስ ነው:፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ

የተወለደው ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፅንሰት ጀምሮ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ

የሆነ አምላክ ነው ።

ሰው ስጋና ነፍስ የተዋህዱበት ፍጥረት ሲሆን አንድ ሰው በስጋውና በነፍሱ ተለያይቶ አይጠራም ። እገሌ ተብሎ በጥቅሉ

ይሰየማል እንጅ። አንድ ነገር ሲያከናውንም እገሌ እንዲህ አደረገ ይባላል እንጅ በስጋው እንዲህ አደረገ በነፍሱ ደግሞ እንዲህ

አደረገ እንደማይባል ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከተዋህዶ በኋላ በሰውነቱ እንዲህ አደረገ በመለኮቱ ደግሞ እንዲህ አደረገ ብሎ

በሁለት ከፍሎ ማየት ስህተት ነው።

" ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና።" " ሂድና በሰሊሆም

መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ።" ዮሐንስ 9:6-7. በዚህ ቃል ውስጥ

እንደምንመለከተው በምራቁ እንትፍ ብሎ በጭቃው የቀባውም አይኑን ያበራውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። የሰው ምራቅ

አያድንም ነገር ግን መለኮትና ትስብእት በፍፁም ተዋህዶ ስለተዋሀዱ የእውሩ አይን በርቷል።

በዮሀንስ ወንጌል ምእራፍ 2 ላይ እንደምናየው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከሀዋርያት ጋር በቃና

ገሊላ የሰርግ ቦታ ታደመ። በዚያም የወይን ጠጅ ባለቀባቸው ጊዜ ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው። በዚህ ላይም ኢየሱስ

ክርስቶስ በስጋ / በሰውነቱ ወደ ቃና ገሊላ የሰርግ ቦታ ሄደ በመለኮቱ ደግሞ ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው ማለት በሁለት

Holy Trinity University Group Assignment 21


አካልና በሁለት ባህሪይ ማየት ነው ። ነገር ግን ወደ ሰርጉ ቦታ የታደመውም ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠውም አንዱ

ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ምክንያቱም መለኮት የስጋን ባህሪይ ገንዘቡ አድርጎል ስጋም የመለኮት ባህሪይን ገንዘቡ አድርጎልና።

በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 11:43 ላይ የማርያምና የማርታ ወንድም አልዓዛር ሞቶ ነበር ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

አስነሳው። በዚህም ወደ አልአዛር የሄደውም ከሞት ያስነሳውም በተዋህዶ አንድ ባህሪይ አንድ አካል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ

ነው ።

ቅዱሰ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲፅፍ " ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም

ተጠመቃችሁን?" 1ኛ ቆሮንቶስ 1:13. ይላል። አዎን ክርስቶስ በአካሉም በባህሪዩም አንድ ነው መከፈል የለበትም። በመስቀል

ላይ የተሰቀለውና ያዳነን ትስብእት ብቻ አይደለም የትስብእትና የመለኮት ተዋህዶ እንጅ። ሲሰቀልም መለኮት አልተለየውም።

ሲነገርም በተዋህዶ ባህርዩ እንጅ በመነጠል መሆን አይገባውምና። የመጨረሻውና አራተኛው ደግሞ በልዮን ጦማር ላይ

የተጠቀሰው ነው።

ይህንን ጉባኤ አምስቱ እህት(ኦርየንታል) ቤተ ክርስቲያናት ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን፣ የእስክንድርያ

(ግብጽ) ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን፣ የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን፣የህንድ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን

እንዲሁም ፣ የአርመን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን አይቀበሉትም ። ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላ እነዚህ አብያተ ክርስትያናት

ለመጀመሪያ ግዜ በድጋሚ በ1957 ዓ/ም ጥር 7 ቀን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ውስጥ

ተሰብስበዋል ። በዚህም ጉባኤ ሰባት ዋና ዋና ነጥቦችን አጽድቀው ተለያይተዋል ከነዚህም ዋና ዋና ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው

። [19]

❖ ዘመናዊው ዓለም እና አብያተ ክርስቲያናት

❖ በመንፈሳዊ ትምህርት ተባብሮ መስራት

❖ ተባብሮ የወንጌል ሥራ መስራት

❖ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስላለው ግንኙነት

❖ ስለ ዓለም ሰላምና ፍትህ ወዘተ...... ተወያይተዋል ።

Holy Trinity University Group Assignment 22


የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በጉባኤ ኬልቄዶን ላይ ሰባት ጉባኤያትን ጨምረው ጉባኤ ኬልቄዶንን ይቀበሉታል ። ስለሆነም

የሮም ቤተክርስቲያን እና የግሪክ ቤተክርስቲያን የሁለት ባሕሪ አማኝ በመሆን ከአሐቲ ቤተክርስቲያን ራሳቸውን ነጥለው

ወጥተዋል።

Holy Trinity University Group Assignment 23


1.12 3.2 ቤተክርስቲያን ከጉባዔ ኬልቄዶን በኋላ

3.2.1 የተፈጠሩ የሃይማኖትና የሥርዓት ልዩነቶች

በክሕደት ምክንያት ከቤተ-ክርስቲያን አባልነታቸው በጉባዔ ተወግዘው ከተለዩት ከአርዮስ ከመቅዶንዮስ ከንስጥሮስ እና

ከተከታዮቻቸው በስተቀር እስከ ኬልቄዶን ጉባኤ ድረስ በአብያተ-ክርስቲያናት መካከል የእምነት ልዩነት አልነበረም።

ከኬልቄዶን ጉባኤ ጀምሮ ግን በዓለም አብያተ-ክርስቲያናት ልዩነቶች ተከስተዋል። ጥቂቶቹን ከዚህ እንደሚከተለው ናቸው፡

❖ የካቶሊክና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት ለኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ሲሉ የኦርየንታል

(የተዋህዶ) ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ ነው እንላለን

❖ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድም ሠረጸ ስትል የኦርየንታል (የተዋህዶ) እና የግሪክ ኦርቶዶክስ

አብያተ-ክርስቲያናት መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ሠረጸ እንላለን

❖ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ብዙ ሰዎች ስለሠሩት ኃጢአት በመፀፀት ንስሐ ገብተው ሳይፈጽሙት ቢሞቱ በመንግስተ-

ሰማያትና በገሃነመ-እሳት መካከል ልዩ የሆነ ቦታ (መካነ-ንስሐ (Purgatory)) ስላለ ነፍሶቻቸው ወደዚያ ሄደው

ከኃጢአታቸው እስኪነጹ ድረስ መከራ እየተቀበሉ ቆይተው ኋላ ወደ መንግስተ-ሰማያት ይገባሉ በማለት

የምታስተምረውን ትምህርት የኦርየንታል (የተዋህዶ) እና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት አንቀበለውም

❖ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የሮም ፖፕ የክርስቶስ እንደራሴና የአብያተ-ክርስቲያናት ሁሉ በላይ ስለሆነ በመንበሩ ተቀምጦ

(ተሰይሞ) በሚወስነው ሁሉ አይሳሳትም ብላ በ1870 ዓ.ም. በቫቲካን አንድ ጉባኤ የወሰነችውን የኦርየንታል

(የተዋህዶ) እና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት አንቀበልም። ይልቁንም የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች በጉባኤ

ተሰብስበው በተገኙበት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተወሰነውና ለወደፊትም የሚወሰነው ውሳኔ (ድንጋጌ) ነው

የማይሳሳት።

❖ የተዋህዶ ኦርቶዶክሳውያን የምንቀበለው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሃደው ነው ስንል የካቶሊክ

ቤተ-ክርስቲያን ግን ነፍስ ያለው መለኮት የተዋሃደው ነው ትላለች።

❖ በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ሕጻናት ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበሉት ነፍስ ዐውቀው ሜሮን ከተቀቡ በኋላ ሲሆን በኦርየንታል

(የተዋህዶ) እና በግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት ከተጠመቁና ሜሮን ከተቀቡ በኋላ ወዲያው ይቆርባሉ

❖ ለጌታ ሁለት ባሕርያት አሉት መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ሠረጸ ብለው ያምናሉ።

Holy Trinity University Group Assignment 24


❖ የኦርየንታል (የተዋህዶ) የግሪክ ኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ አብያተ-ክርስቲያናት ቄሱ በሚፀልይበት ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ

ተለውጦ ሥጋ አምላክ ደመ አምላክ ይሆናል ሲሉ ፕሮቴስታንቶች አይለወጥም ብለው ያምናሉ።

❖ የኦርየንታል (የተዋህዶ) የግሪክ ኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ አብያተ-ክርስቲያናት ድኅነት የሚገኘው ከእምነትና ከደጋግ

ሥራዎች ነው ሲሉ (ያዕ 2÷14-26፤ ማቴ 7÷21) ፕሮቴስታንቶች ግን ድኅነት የሚገኘው ከእምነትና ብቻ ነው ይላሉ።

ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላ ለሚቀጥሉት 150 ዓመታት ያህል የነገሡ የቊስጥንጥንያ ነገሥታት ቤተ ክርስቲያንን ለማዋሐድ ብዙ

ጥረት አድርገዋል ለምሳሌ ከ474 491 ዓ.ም የነገሰው ዘይኑን (ኖን) ከ491 - 518 ዓ.ም የነገሠው አንስታሲዮስ በተዋሕደ አንድ

ባሕርይ የሚለውን የተዋሕዶ እምነት ተቀብለው ቤተ ክርስቲያን በስላም የምትመራበትን መንገድ ለመፈለግ ተነሳስተው ነበር፡፡

ለዚህም በጎ ፈቃድ መሰናክሉ የኬልቄዶን ጉባኤ ውሳኔና የልዮን ጦማር መኾኑን በመገንዘብ የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ አባ

አጋግዮስ (አካኪያስ) እና ንጉሡ ዘይኑን ተስማምተው ይህን ለመሠረዝና ቤተ ክርስቲያንንም ወደ ጥንታዊ የተዋሕዶ እምነቷ

ለመመለስ ከአንጾኪያውና ከእስክንድርያው ፓትርያርኮች ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡

በዚህ የአጋግዮስ የዕርቅ ድርድር የእስክንድርያውም የአንጾኪያውም ፓትርያርኮች ተስማምተው ፈርመዋል: በዚህ ጊዜ የሮማው

ፓፓ እኔ ሳልጠየቅ ይህ እንዴት ይሆናል? በማለት ተቆጥቶ ሊቀ ጳጳሱን አጋግዮስንና ንጉሡን ዘይኑን አወ7ዛቸው 488 ዓ.ም

በዚህ ምክንያት የሮምና የቊስጥንጥንያ አብያተ ክርስቲያናት 30 ዓ.ም ያህል ተኳርፈው ረዋል በነዚህ 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ

0ሶርያና በአንጾኪያ የቄርሎስን ትምህርት የሚደግፉ በሙያ የበስሉ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ተቆርቋሪዎች እነ ሳዊሮስ lአንጾኪያና

እነፍልክስዩስ (ፊሎክሴኖስ) ዘሶርያ ለተዋሕዶ እምነት ለመመስከር በቆራጥነት ተነስተው ነበር። ሳዊሮስ ከ465 538 የ.ንጾኪያ

ሊቀ ጳጳስ ኾኖ የመለካውያንን ብዛትና ዛቻ ሳይፈራ ሳያፍር ምሥጢረ ተዋሕዶን ያስተምር የነበረው ነው:

ፊልክስዩስ (ፊሎክሴኖስ) ደግሞ 512 518 በማቡግ ሶርያ ኤጲስቆጶስ ሁኖ መለካውያን ከተዋሕዶዎች ጋር አፍላ ጦርነት

ባደረጉበት ጊዜ በትምህርት ተዋግቶ በከፊልም ቢኾን መለካውያን የማረኳቸውን ምእመና መልሷል በ491 ዓ.ም በቫግሃፕት

የተደረገው ጉባኤ የተዋሕዶ እምነት የአርማንያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን የተወሰነው እነዚህን በመሳሰሉ የሃይማኖት

አርበኞች ትግል ነው።

የተዋሕዶ ሃይማኖት በነዚህ ጊዜያት አልፎ አልፎ ድል ቢያጋጥመውም፤ አንዳንድ መሰናክልም አላጣውም ነበር፤ የቤተ

ክርስቲያንን አንድ መሆን የማይደግፉ መለካውያን ከላይ የሮማውን ፓፓ ትራስ አድርገው በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ብጥብጥ

Holy Trinity University Group Assignment 25


ከመፍጠር አልተቆጠቡም፡ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ማለት ከኬልቄዶን ጉባኤ በፊት በማንኛውም የጸሎት ጊዜ» ቅዱስ

እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃይል፤ ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ከተባለ በኋላ በየእርከኑ ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል

ተሣሃለነ እግዚኦ ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተስቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሠሣለነ እግዚኦ:፡ ዘተንሥአ እሙታን ኣመ ሣልስት ዕለት

ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ፤ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት፤ ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሠለነ እግዚኦ»

እየተባለ ምሥጢረ ሥጋዌን ከልደት እስከ ዳግም ምጽአት የተደረገውን ሁሉ ያነሣል ቅዱስ እግዚአብሔር ኃያል ቅዱስ ሕያው

ዘኢይመውት የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች እንደሚተረከው ዮሴፍና ኔቆዲሞስ ጌታን በሚገንዙበት ጊዜ ሲጸልዩት

የነበረ ነው፡፡ ሌላው መርገፉ የኒቅያ አንቀጸ ሃይማኖት ነው። መለካውያን ግን ቆነጻጽለው ጥሰው ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ

ኃይል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ካሉ በኋላ ተሠሣለነ እግዚኦ ይላሉ። ቅዱስ እግዚአብሔር ተወለደ፤ ተጠመቀ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ

ማለት ወደ ቄርሎስ ትምህርት እንዳይወስዳቸው ነው።

ከብዙ ፈተናና ውጣውረዶችም በኋላ የተዋሕዶ እምነት በመጥፋት ፈንታ እየተስፋፋች ከታናሽ እስያ ጀምሮ ማለት ከጥቁር

ባሕር ጀምሮ እስከ ዓባይ ወንዝ ድረስ ብዙ ተከታዮችን አፈራች። በኢትዮጵያም የተዋሕዶ ሃይማኖት ብሔራዊት ሁና እስካሁን

ቆይታለች መለካውያን ከኬልቄዶን ውሳኔ በኋላ የርስ በርስ ትርምስና አለመግባባት ጋጥሟቸዋል: በተለይም በኬልቄዶን ውሳኔ

ቀኖና 28 ላይ የሠፈረውን ልዮን አላጸድቅላቸውም በማለቱ ግሪኮች የልዮንን ጦማር በመደገፋቸው ብዙ ጸጸት አጋጥሟቸዋል

(ZA Blog, 2018)። ይሁን እንጂ ከላይ እንዳየነው የዘርና የፖለቲካም ጉዳይ ስላለበት ጠቡ አልተፋፋመም ከኬልቄዶን በኋላ

ሁሉም ባንድ ላይ ሦስት ጊዜ ጉባኤ አድርገዋል፡፡ እነዚህም ሦስት ጉባኤያት አንደኛ በ553 ዓ.ም የተደረገው ሁለተኛው

የቊስጥንጥንያ ጉባኤ በመባል የታወቀው ነው፡፡ ሁለተኛ ከ680 - 681 ዓ.ም በቊስጥንጥንያ የተደረገው ሦስተኛው

የቊስጥንጥንያ ጉባኤ በመባል የታወቀው ነው። ሦስተኛ በ787 ዓ.ም በኒቂያ የተደረገው ሁለተኛው የኒቅያ ጉባኤ በመባል

የታወቀው ነው: ባጠቃላይ መለካውያን ባንድነት የሚቀበሏቸው ሰባቱ ጉባኤያት እነዚህ ናቸው:፡ እኛ ግን ከኬልቄዶን ጉባኤ

በፊት የተደረጉትን ሦስቱን ጉባኤት ብቻ እንቀበላለን እነሱም የኒቅያ የቊስጥንጥንያና የኤፌሶን ጉባኤያት ናቸው።

በኬልቄዶን ጉባኤ ከተወሰነው ኢሕጋዊ ውሳኔ በኋላ የመለካውያንና የተዋሕዶዎች አቅዋም በዘመናት ሁሉ በጠላትነትና

በመነቃቀፍ ነበር፡ ከኬልቄዶን ውሳኔ በኋላ እኛም እነሱም ንስጥሮሳውያን መለካውያን ሁለት ባሕርይ ባዮች ይሉናል: አንድ

ባሕርይ ባዮች የሚሉንም ከሁለት መናፍቃን ጋር አጣምረው ነው። አንደኛ «የእግዚአብሔር ቃል ሥጋን እንጂ ነፍስን

አልተዋሐደም» ከሚል ከአቡሊናርዮስ (አፓሊናርዮስ) ጋር አዛምደው ነው፡፡ በነሱ አባባል ክርስቶስን አንድ ባሕርይ የሚለው

ትምህርት የአቢሊናርዮስ ነው፤ ቄርሎስም አንድ ባሕርይ ማለቱ በጥቅሱ ሳይጠነቀቅ ቀርቶ ነው ይላሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ቃልና
Holy Trinity University Group Assignment 26
ሥጋ በተዋሐዱ ጊዜ ቃል ሥጋን መጦታል፤ ለውጦታል ከእሳት እንደ ገባ ቅቤ አቅልጦታል፤ ከሚለው ከአውጣኪ ጋር አጣምደው

ነው። ግሪኮች ዛሬም እኛን ባዩ ቊጥር አንድ ባሕርይ ባዮች ናችሁ ይሉናል ሌሎች ግን አምስቱንም እኅት አብያተ ክርስቲያናት

በተንኮል ለመከፋፈልና ለመለያየት የእኛን ተማሪዎችና መነኮሳት ሲያገኙ ሌሎች ናቸው እንጂ እናንተ ሞኖፊሴት አይደላችሁም

በማለት ያንዳንድ የዋሆችን ልቡና ከፋፍለውታል: በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ከራሳችን ሊቃውንት የተጻፉ መጻሕፍትን

ሳንመለከት ወደ ውጭ ስለምንላክ እነሱ የሚሉት እውነት የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ፣ የሶርያ፣

የአርመንና የሕንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው በማለት ከኬልቄዶን ጉባኤ የተለዩ

ናቸው፡፡ ክርስቶስን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው የምንለውም እንደ አቡሊናርዮስ ከፍለን፤ ቀንስን እንደ ኣውጣኪ አጣፍተን

ሳይሆን እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ በባሕርይ ተዋሕዶ ነው።

Holy Trinity University Group Assignment 27


ዋቢ መጻህፍት
Davis, L. D. (1990). The First Seven Ecumenical Councils. Liturgical Press.

Encyc Bri. (2015, Feb). Encyclopedia Britannica. Retrieved from Encyclopedia


Britannica.: https://www.britannica.com/biography/Eutyches

Jhonson, S. (2012). Early christianity in Asia minor. Journal of Biblical Literature, 15-16.

newadvent. (2015, ህዳር 15). newadvent.org. Retrieved from church fathers:


https://www.newadvent.org/fathers/3811.htm

Philip Henry, P. S. (1900). Nicene and Post-Nicene Fathers. New york: Christian
Literature Publishing Co.

ZA Blog. (2018, Nov). zondervan. Retrieved from zondervanacademic:


https://zondervanacademic.com/blog/council-of-chalcedon

ኅሩይ ኤርሚያስ, መ. (2010 ዓ/ም). መዝገበ ታሪክ ክፍል 1. አዲስ አበባ: ፋር ኢስት ማተሚያ ትሪዲንግ.

ሉሌ መላኩ. (1986 ዓ/ም ). የቤተክርስቲያን ታሪክ. አዲስ አበባ: ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት .

ማህበረቅዱሳን. (2015, ታህሳስ 10). https://eotcmk.org. Retrieved from eotcmk.org:


https://eotcmk.org/a/አውጣኪ፣-ቅዱስ-ዲዮስቆሮስ-እና-የኬልቄዶ/

ቤተ ሃዋርያት. (2006, Feb). Bete hawariyat. Retrieved from bete hawariyat:


https://betehawariat.blogspot.com/2017/01/blog-post_91.html)

አቡነ ጎርጎርዮስ. (2015). የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ. አዲስ አበበ: ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት.

ኤፍሬም, ባ. ዲ. (2013). መንበረ ፕትርክና ፥ ሐዋርያዊ ሥርዓቱ. አዲስ አበባ.

ዊኪፔድያ. (2015, ታህሳስ 12). wikipedia.org. Retrieved from wikipedia:


https://en.wikipedia.org/wiki/Council_of_Chalcedon

Holy Trinity University Group Assignment 28

You might also like