You are on page 1of 3

›››የሐበሻ ጀብዶ›››የኢትዮጵያውን የነፃነት ተጋድሎ›››

ኢትዮጵያዊ ነህ? ሐበሻ ነህ? ሐበሻ ከሆንክ መጀመሪያ የሐበሻ ጀብዶንና ቀይ አንበሳን አንብብ፡፡ የቅድመ
አያትህ፣ የአያትህና የአባትህ ታሪክ ነው፡፡ ዘመን የማይሽረው የሀበሻ ወኔ፣ ችግር ማይበግረው ጀግንነት፣
ሀገር ወዳድነትና ዘላለማዊ የሆነ የወገን ፍቅር በቀይ ቀለም የተከተቡበት ድንቅ መፅሐፍ፡፡ ስለማንነትህና
ስለ ዘርህ አትጨነቅ ብቻ ሀባሻ ሁን፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ትግሬ የትኛውንም የኢትዮጵያ ዘር
ብትሆንም ይህ ያንተ የሀበሻው ታሪክ ነው፡፡ ቅድመ አያትህ፣ አያትህ፣ አባትህ ወይም ከወገኖችህ አንዱ
አድዋ ነበር፤ ማይጨው ነበር፣ አቢ አዲ ነበር፣ መቀሌ ነበር፣ ኮረም ነበር፣ ተከዜ በረሃ ነበር፤ ኢትዮጵያን
ከጠላት ሊታደግና ያልተበረዘ ማንነት ሊያወርስህ፡፡ አንተ የነዚያ ጀግኖች ውጤት ነህ፡፡ አጥንታቸውን
ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍሰው በከፈሉልህ መስዋትነት ቀና ብለህ የምትጓዝ ነፃ ትውልድ! አንበው ቢያንስ
ማንነትህና ታሪክህ ነው! ማንነቱን በትክክል የተረዳና ታሪኩን የሚያውቅ ትውልድ ማንም በደነፋ ቁጥር
አይበረግግም፤ ታሪክ ጠቅሶ መፅሐፍ አስደጉሶ ስለማንነቱ ይከራከራል እንጂ፡፡

መጽሐፏ የቼክ ተወላጅ በሆኑትና በኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት አብረው በተዋጉት አዶልፍ ፓርለሳክ የተጻፈ
ነበር። “ሐበሽስካ ኦዴሳ” (Habesska Odyssea) በሚል ርዕስ በተለያዩ ጊዜያት የተታተመችው ይህቺው
መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን ከኢጣሊያን ጋር ያደረጉትን መራር ጦርነት የምትተርክ
እውነተኛ የታሪክ ማስታወሻ ናት። ክብር ይግባቸውና አቶ ተጫኔ ጆብሬ ይህንን መፅሐፍ “የሐበሻ ጀብዱ”
በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉመው በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬስ ለህትመት ብርሃን አብቅተውታል፡፡

መጽሐፏን የጻፉት አዶልፍ ፓርላሳክ ሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ቆይታ አድርገዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የአባይን ወንዝ ፈለግ ለመከተል ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የተመለሱት ሀገሪቱ በጦርነት ዋዜማ
ላይ ሆና ነበር። በመዲናይቱ የነበራቸውን ቆይታ እና የያኔዋ አዲስ አበባ ኑሮ እና ሁኔታ ምን ይመስል
እንደነበር የታዘቡትን በመጽሀፋቸው አቅርበዋል። ጸሀፊው ለሰሜኑ ጦር አዛዥ ራስ ካሳ የጦር አማካሪነት
በንጉሱ በመሾም ነበር የኢትዮጵያን አርበኞች የተቀላቀሉት። ከፍተኛውን የኢትዮጵያ የጦር መኮንን ማዕረግ
የተሾሙት ፓርለሳክ በማይጨው ጦርነት ላይ ከመሳተፋቸው በፊት ለወራት ያህል ከራስ ካሳ ጦር ጋር
በመሆን ጋራ ሸንተረሩን እያቋረጡ በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ላይ ውለዋል።

የያኔውን ንጉስ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንንን (ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን) እንዲህ በማለት ያወድሷቸዋል፡፡
“በ1930 ከነገሱበት ቀን ጀምሮ ዘላለማዊ እንቅልፍ የተኛች የምትመስለውን ውዷን ሀገራቸውን ከዚህ
እንቅልፏ ለመቀስቀስና ወደፊት መራመድ እንድትችል የውጪ ዲፕሎማሲ ምን ያህል ከፍተኛ ሚና
እንደሚጫወት ጠንቅቀው ያወቁት ንቁው እና ብልሁ ንጉስ የዲፕሎማሲ ስራውን ከሁሉም ነገር በፊት
አስቀድመው አጠናከሩት” ይላሉ፡፡ ንጉሱ ረጅም ሰዓት ያለማቋረጥ ይሰሩ የነበሩ ታታሪ እንደነበሩም
በዓይናቸው ያዩትን ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

በጦርነት ዋዜማ ንጉሱ የነበሩበትን ሁኔታ ሲገልጹ “ቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ፣ እድል
ለዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የመረጣቻቸው መሪ፣ በቁመናቸው አጠርና ከሳ ያሉ ናቸው። ይሄ ረዘም ያለ ፊታቸው
በጥንቃቄ የተከረከመው ሙሉ ጥቁር ጢማቸው፣ ምናልባት ለሳይንቲስት፣ ለፈላስፋ ወይም ለደራሲ
እንደሆነ እንጂ አገሩን በደሙና በአጥንቱ ለመከላከል ቆርጦ ለተነሳ መሪ የሚሆን አይመስልም” ይላሉ፡፡
አክለውም “ምንም እንኳ ንጉሰ ነገስቱ ፈረንሳይኛም እንግሊዘኛም አቀላጥፈው ቢናገሩም የኢትዮጵያውያን
የነገስታት ሕግ ከውጭ ዜጎች ጋር ሲገናኙ በአማርኛ ብቻ እንዲናገሩ ስለሚያስገድድ የግድ አስተርጓሚ
አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲህ ለስልጣኔ ሌት ተቀን የሚለፉት ንጉሰ ነገስት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እንኳን የጥንቱን
የጠዋቱን የኢትዮጵያውያንን ባህልና ወግ አልረሱም” ሲሉ ያደንቋቸዋል፡፡

እንደ ፓርለሳክ አባባል አጼ ኃይለ ስላሴ ከሀገር መሪነታቸው ባሻገር በወታደራዊ መስክም “ጀግና” ነበሩ።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ንጉሱ ኮረም በምትገኝ ትንሽ የዋሻ ቤተ መንግስት እንደቆዩና በመጨረሻም
ማይጨው ጦርነት ሲጀመር ገብተው እንደተዋጉ ይገልፃሉ፡፡ “ንጉሰ ነገስቱ እንደማንም ተራ ወታደር
በጦር ሜዳ ውለው፤ ታግለው አታግለዋል። ተዋግተው አዋግተዋል። አዎ በማይጨው የጦር ሜዳ
ከእሳቸው በፊት እንደነበሩት ነገስታት ሁሉ ትልቁን ኃላፊነት ወስደው፣ ጠቅላላውን የሀገሪቱን ጦር እየመሩ
ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ተዋግተዋል። ይሄም ታላቅ ጀግና ሊያስብላቸው ይገባል” ይላሉ
በማይጨው ጦርነት ላይ የተሳተፉት ፓርለሳክ። ንጉሱ ማይጨው ጦርነት በአካል ገብተው እንደተዋጉ
የሚያውቅ ኢትዮጵያዊን ቁጥር ምንያህል ይሆን?

ንጉሱን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን፤ የሚያደንቋቸው ንጉስ ይሰሯቸው የነበሩትን ስህተቶችን ጭምር በድፈረት
ተችተዋል። የኢትዮጵያ ጦር የአድዋውን ድል በኢጣሊያኖች ላይ ለመድገም ያስችለው የነበረውን ተደጋጋሚ
እድል ያጣው በአጼ ኃይለ ስላሴ ምክንያት እንደነበር እንዲህ ሲሉ ተችተዋል፡፡ “ንጉሰ ነገስቱ ለሁሉም
የጦር አበጋዞቻቸው በሰጡት ጥብቅ ትዕዛዝ ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሰራዊት ከመከላከል አልፎ ቀድሞ
ጥቃት እንዳይሰነዘር ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። ኃይለ ስላሴ አሁንም የመንግስታቱ ህብረት የጣልያንን
ወራሪ ሰራዊት ያቆምልናል ብለው ያምናሉ። ንጉሰ ነገስቱ በዚህ ስህተት በተሞላበት እምነታቸው ከባድ
ጥፋት ሰርተዋል። ልክ እንደገናናው ምኒልክ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰራዊት የጣልያንን ሰራዊት ልክ ሊያስገባው
የሚችልበትን ብዙ ዕድል አሳጥተውታል።” ይላሉ፡፡

ወታደራዊ ዩኒፎርም በቅጡ ያለበሰውንና በምትኩ እንደማንኛውም ባላገር ሸማ የለበሰውን ዘማች እንዲህ
ሲሉ ይገልፁታል፡፡ “አብዛኛው ሰራዊታችን ከየጥሻውና ከየአምባው የመጣና ጦርና ጎራዴ ብቻ የታጠቀ፣
በመጀመሪያው ቀን ውጊያ ጠላት ገድሎ ጥሩ መሳሪያ ለመታጠቅ በጽኑ እምነት የቆመ ጀግናና ጉጉ ጦር
ነበር” ይህ ወደ ሃምሳ ሺህ እንደሚጠጋ የሚገመተው የሰሜኑ ጦር ከኢጣሊያን አውሮፕላኖች
የሚደርስበትን የማያቋርጥ የቦምብ ድብደባ ተቋቁሞ እስከ ተንቤን በመጓዝ በእርግጥም ጀብዱ ፈጽሟል።

እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ ጦር በማይጨው ጦርነት ብርቱ ተጋድሎ አድርጎ ነበር። በሶስት ራሶች እና
በአንድ የደጃዝማቾች ስብስብ የሚመራው ጦር ሶስት ጊዜ ያህል ማይጨውን ለመያዝ ጦርነት አድርጎ
በስተመጨረሻ የተሰካላት መስሎ ነበር። ጣሊያኖችን ማሸነፍ የቻለው ጦር ከጣሊያን ጋር ባበሩት ራያዎች
እና አዘቦዎች ባንዳነት በደረሰበት ጉዳት መሸነፉን ፓርለሳክ መስክረዋል። ራያዎች እና አዘቦዎች የኢትዮ-
ጣሊያን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከጣሊያኖች በተቀበሉት አዳዲስ መሳሪያ ታግዘው ለኢትዮጵያ ጦር የጎን
ውጋት ሆነው የቆዩ ነበሩ። በስተመጨረሻም የኢትዮጵያ ጀግኖች ከፊት ጣሊያኖችን ከኋላ ባንዳዎችን
ሲዋጉ ውለው ጦርነቱን በሽንፈት ተጠናቀቀ፡

ከመሪ ደጃዝማቾች መካከል በደጃዝማች አበራ ይመራ የነበረው የሰላሌ ጦር ለየት ያለ ታሪክ ነበረው።
የሰሜኑ ጦር አዛዥ የሆኑት ራስ ካሳ ልጅ የሆነው ደጃዝማች አበራ በማይጨው ጦርነት በወጉ እንኳ
ጺም ያላበቀለ ለግላጋ ወጣት ነበር። ከዚህ ጦር ጋር አንድ ድንቅ የሆነ የጦር መሪ ብላቴና ታሪክ
የፀሐፊውን ቀልብ ወስዷል፡፡የወረጃርሶው አቢቹ፡፡ አዲስ አበባ ትምህርቱን የተከታተለው አቢቹ
በቀጣዩ ዓመት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ ለመጓዝ እየተዘጋጀ እያለ ነበር የኢጣሊያ ወራራ
የመጣው። ትምህርት ቀርቶ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ሆነና አቢቹም ሁለት ወንድሞቹን ተከትሎ
ነበር የዘመተው። ይህ ብላቴና ለማመን የሚከብድ ፤ እጅን ከአፍ ላይ የሚያስጭን ጀብድ ፈፅሟል፡፡ ጀግናው
አቢቹ፡፡ የሚኒሊክ፣ የባልቻ አባነፍሶ፣ የገበየሁ፣ የዲነግዴ፣ የበላይ ዘለቀ፣ የአብዲሳ አጋ፣ የጃገማ ኬሎ፣ የቅዱስ
ጴጥሮስ ዘር፡፡ ምርጥ የሀበሻ ልጅ! ያልተዘመረለት የሰላሌ ጀግና፡፡ የት ነህ አቢቹ?
አቢቹ ደራ ደራ
አቢቹ ደራ ደራ…………….
Zelalemtilahun.blogspot.com
ዘላለም ጥላሁን፣ ሰኔ 1፣ 2007 ዓ.ም
ሻሎም፣ መልካም ንባብ!

You might also like