You are on page 1of 1

<ዕለቱ_አርብ_ነው>

በቤተ ክርስቲያን በጥበብ መንፈሳዊ እያደጋችሁ በግቢ ጉባዔያችን ውስጥ ለአገልግሎት የምትፋጠኑ ወንድም
እህቶቻችን ሆይ የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ፍፁም ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን። የአንድነትና
የወንድምነት እና የእህትነት ሰላምታችን ባላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ
ክርስቶስ በዓለ ስቅለት በሰላም አደረሳችሁ፡፡

የዛሬዋ ዕለት በክርስቶስ ጽንሰት የጀመረው የአዳም መዳን ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀበት ዕለት በመሆኑ የዘመናት
ተስፋው የተፈጸመለት አዳም አባታችንን ስናስታውሰው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ቀን ሆኖ እናገኘዋለን።

#ዛሬ_ዕለቱ_አርብ_ነውና

ሰማይና ምድርም በውስጣቸው የሚኖሩትን ሁሉ በገዛ ስልጣኑ የፈጠረ አምላክ በምድራዊ ባለስልጣን ፊት ለፍርድ
የቆመበት ዕለት ነች።

#ዛሬ ዕለቱ አርብ ነውና

ይሁዳም ገንዘቡን ኒቆዲሞስም በሌሊት ወደ ጌታው ሲመላለስ የተቀበለውን የሃይማኖት ዘር አብቅሎ ያሳየበት ዕለት
ነው።

#ዛሬ_ዕለቱ_አርብ_ነውና

የቀሬና ሰው ሆነው ስምዖን ሁሉን ቻዩን አምላካችንን መስቀሉን በመሸከም አገዘው።

#ዛሬ_ዕለቱ_አርብ_ነውና

የመልካም ስራዎች ሁሉ ባለቤት የሆነው ጌታችን በሁለት ወንበዴዎች መካከል እንደ የበላይ ወንበዴ ተደርጎ ተቆጥሮ
ተሰቀለ።

#ዛሬ_ዕለቱ_አርብ_ነውና

ጌታችን በስቃይ ውስጥ ሁኖ ለሚጨክኑበት ከአባቱ ዘንድ ምህረትን ለመነ እንዲህ እያለ“አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን
አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ።”(ሉቃስ ፳፫÷፴፬)

አንደ አርብ ዕለት እጅግ የምትጨንቅ ቀን የለም።በእኩል ሰዓት ሀዘን እና ደስታ፤ክህደት እና መታመን፤ኃጢአት እና
ንስሐ፤ውሸት እና እውነት፤ትእቢት እና ትህትና በአንድ ላይ የቆሙበት ዕለት ነው።

ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ዕለተ አርብ ላይ ነው ያለችው።


ሀሰተኛው ከእውነተኛው፤ከሀዲው ከተአማኒው መለየት የማይቻልበት።እንደ የአስቆሮቱ ሰው ይሁዳ
ብዙ“መጨረሻቸው ጥፋት፥ ሆዳቸው አምላካቸው ፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ”(ፊልጵስዩስ
፫÷፲፱) የሆኑ አገልጋዮችን እያየን ነው።

እነሆ እንደ ሰምዖን ቀሬናዊ እኛም ከምንሄድበት መንገድ ተመልሰን ጥበብ መንፈሳዊ እና ስጋዊ ያለአንዳች ዋጋ
የሰጠችንን እናት ቤተክርስቲያናችንን የተሸከመችው መስቀል እናግዛት ዘንድ አደራችን ነው።እነሆ ከአርብ በኋላ
ቀጣይ የሚመጣው ትንሳኤ ነውና “እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥
ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና”ለቤተክርስቲያን ማድረግ
የምንችለውን ሳይሆን ማድረግ ያለብንን ፈጽመን በመጨረሻ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን
ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው
ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል”ብለን መናገር እስክንችል ድረስ በአገልግሎታችን አንጽና።(ዕብራውያን ፮÷፲) (፪ኛ
ጢሞቴዎስ ፬÷፰)

“ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ”በጸሎታችሁ አስቡኝ (፩ኛ ቆሮንቶስ ፱÷፳፯)

መልካም የስቅለት በዓል። ተመጉ ዘፖሊ

You might also like