You are on page 1of 53

ዕቅበተ እምነት ምንድን ነው?

• ዕቅበተ እምነት የቃሉ መነሻ “አፖሎጊያ - (Apologi የሚል


የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ቃላዊ መከላከል/መልስ ማለት
ነው፡፡
• በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት “አፖሎጊያ - (Apologia)”
የሚለውን የግሪክ ቃል ብዙ ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
• “እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ
ስሙኝ- Men, brethren, and fathers, hear ye my
defence which I make now unto you” (ሐዋ. ፳፪፡
፩)፤ “እኔም፦ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም
ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም
ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ
መለስሁላቸው” (ሐዋ. ፳፭፡፲፮)፤
• “ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው” (1ኛ ቆሮ. ፱፡፫)፤
“በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ
ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ
ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል” (ፊል. ፩፡፯)፤
• “በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ
እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው” (፪ኛ ጢሞ. ፬፡፲፮) የሚሉት
ጥቂት ማሳያዎች ናቸው፡፡
• አፖሎጊያ “አፖሎጊያ - (Apologia)” የሚለው ቃል
በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ “መልስ፣ ክርክር፣ መመከቻ፣
ሙግት፣ ነገር፣ ወዘተ” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡
• ስለዚህ ዕቅበተ እምነት ማለት በእምነት ላይ ለሚነሡ
ጥያቄዎች መልስ በመስጠት እምነትን መጠበቅ ማለት ነው፡፡
• ዕቅበተ እምነት ብዙ ጊዜ መናፍቃንንና ከሐድያንን ተከራክሮ
ከመርታት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ተደርጎ ቢታይም ሥራው ግን ዘርፈ
ብዙ ነው፡፡
• በፍልስፍና፣ በታሪክ፣ በሌሎች ቤተ እምነቶች፣ በሳይንስና መጽሐፍ
ቅዱስን ባለመረዳት ምክንያት በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ
የሚነሡትን ከፍ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ በእምነትና በዕውቀት በማፍረስ
አእምሮን የመማረክ ሥራ ነው፡፡
• በነገረ ሃይማኖት ውስጥ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት
ምእመናን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት እንዲኖራቸው
ማድረግ፣ መናፍቃን ምእመናንን እንዳይነጥቁ ብቻ ሳይሆን እነርሱም
የድኅነት ተካፋዮች እንዲሆኑ ማድረግ፣ መከላከል ብቻ ሳይሆን
ሌሎችን መሳብ የዕቅበተ እምነት ዋና ተግባራት ናቸው፡፡ .
• በአጠቃላይ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን ትክክለኛነት ወይም
እውነትነት የሌሎችን “እምነቶች” ሐሰተኝነት በማስረጃ በማስደገፍ
ኦርቶዶክሳውያን በእምነታቸው እንዲጸኑ ሌሎች ደግሞ ወደ ኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲመጡ ለማድረግ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡
• ብዙ ሰው መዳን ከሚገኝበት እውነተኛ የሕይወት መንገድ በዕውቀትም
ይሁን በየዋሕነት ይወጣል፡፡
• በየዋህነት የሚወጣውን ሰው ሃይማኖትን በምድራዊና በሰው ሠራሽ አሳብ
ላይ እንዳይገነባ ማድረግ፣ ዐውቄያለሁ ብሎ የሚክደውን ደግሞ እምነት
በሥጋዊ ዕውቀትና ጥበብ ተመሥርቶ የሚሻሻል አስተሳሰብ አለመሆኑን
ማስረዳት ዕቅበተ እምነት ነው፡፡
• በትክክለኛው መሠረት ላይ የቆመውን ሰው በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ
እንዲያምን ማድረግም በተመሳሳይ ዕቅበተ እምነት ነው፡፡
• እምነት የሚጠበቀው ከምንድን ነው ከተባለ
• ከሥጋዊ ፍላጎት/አስተሳሰብ፣
• ከሥርዓት አልበኝነት አካሔድ፣
• ከዓለም ፍልስፍና፣
• ከመናፍቃን ቅሰጣ፣
• ከኢአማንያን ክሕደት፣ ወዘተ ነው፡፡
• እነዚህ አስተሳሰቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰውን
ከተመሠረተበት መሠረትና ከተጣበቀበት የሕይወት ግንድ የሚለዩ
ናቸው፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ላይ
“እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና
እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና
በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ”
(ቆላ. ፪፡፰) በማለት እምነታችንን ከዓለም ፍልስፍናና
ከዓለማዊ አስተሳሰብ መጠበቅ እንዳለብን ነግሮናል።
• ከሥርዓት አልባ አካሔድ ስለመጠበቅም “ወንድሞች ሆይ፥
ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ
ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
እናዛችኋለን” (፪ኛ ተሰ. ፫፡፮) ካለ በኋላ
• “ወንድሞች ሆይ፣ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት
የሚሄዱትን ገሥጹአቸው” (፩ኛ ተሰ. ፭፡፲፬) በማለት ደግሞ
ያለ ሥርዓት የሚሔዱትን ስለመመለስ መክሮናል።
ዕቅበተ እምነት ለምን ያስፈልጋል?

1. እግዚአብሔር ስለሚያዝ፡-

• ማንኛውም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል እንዲያምን ብቻ ሳይሆን በቃሉ እንዲኖርና እምነቱን ከዓለማዊ


ፍልስፍናና ከመናፍቃን ትምህርት እንዲጠብቅ እንዲሁም ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ
ይጠበቅበታል፡፡

• ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት
እንጠብቅ” (ዕብ. ፲፡፳፫) እንዳለን፤

• እምነትን ከቀሳጥያን መጠበቅ የእያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ግዴታ እንጂ ለተወሰነ የቤተ ክርስቲያን
አካል ብቻ የሚሰጥ ሓላፊነት አይደለም፡፡
• ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም “በእናንተ ስላለ ተስፋ
ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር
የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋሕነትና በፍርሃት ይሁን” (፩ኛ
ጴጥ. ፫፡፲፭) በማለት እያንዳንዳችን ስለ እምነታችን
የምንጠየቀውን ለመመለስ ብቁና ዝግጁ ሆነን መኖር
እንደሚገባን ነግሮናል።
• በሌሎች ትምህርት እንዳንወሰድና የራሳችንን አጥብቀን
እንድንይዝ ታዘናል፡፡
• እግዚአብሔር መከራከሪያ ማስረጃችንን እንድናቀርብ
አዞናል፡፡ ከእርሱ ጋር ኑ እንዋቀስ ብሎ፣ ከሌሎች ጋር ደግሞ
“ክርክራችሁን አቅርቡ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን
አምጡ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። ያምጡ፤ የሚሆነውንም
ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ
ዘንድ፤ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፤
የሚመጡትንም አሳዩን።” (ኢሳ. ፵፭፡፳፩-፳፪)
• ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን በሥጋዌው ወራት ከተለያዩ አካላት
ለተነሡ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፤
• ሐዋርያት፣ ሐዋርያውያን አበው፣ የእምነት ጠበቆች የሚባሉት እነ
ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሰማዕቱ ቅዱስ ዮስጢኖስ፣ ቅዱስ ቴዎፍሎስ
ዘአንጾኪያና ሌሎችም፣ ከእነርሱ ቀጥለው በዘመነ ሊቃውንት የተነሡ
ቅዱሳን አባቶች ሁሉ የዕቅበተ እምነት ሥራ ሠርተዋል፡፡
• እኛ ደግሞ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን
አስቡ፣ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት
ምሰሏቸው” (ዕብ. ፲፫፡፯) ስለተባልን በስም ያይድለ በግብር
እነርሱን መከተል ያስፈልገናል፡፡
• ቤተ ክርስቲያን ይህን ሥራ የሚሠራ መዋቅር እንዲኖራት
ከማድረግ ጎን ለጎን ልጆቿ በእምነታቸው ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን
ለመመለስ የሚችሉ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ዕቅበተ እምነት
መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡
2.

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ማወቅ የሚገባንን ያህል


ለማወቅ፡-
• “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” (ሆሴ. ፬፡፮)፤
ተብሎ እንደተነገረ የዕውቀት ማጣት ሰውን ወደ ክሕደት
ይመራል፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚኖረው በሚያውቀው ልክ ነው፡፡
• በክርስትና ታሪክ አላዋቂዎችም ሆኑ ዐውቆ አጥፊዎች ቤተ
ክርስቲያንን ሲጎዷት እንደኖሩ ግልጽ ነው፡፡
• እንዲያውም ዐውቆ ከሚያጠፋ በላይ በዕውቀት ማጣት ምክንያት
የሚያጠፋው ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ይጎዳታል፡፡
• በእምነታችን ጥርጥር ላይኖርብን ይችላል፤ እግዚአብሔርን
በፍጹም ልባችን እንወድ፣ ትእዛዛቱንም በፍጹም ልባችን እንፈጽም
ይሆናል፤
• ነገር ግን ያላመኑት ለማመን፣ የማያምኑት ለማደናገር ጥያቄ
ሲያቀርቡልን እምነታችንን በትክክል ማብራራት ካቻልን ሌሎቹ
የፈለጉትን ሊሞሉብን ይችላሉ፡፡
• የዕውቀት ማጣት ባዶነትን ያስከትላል፡፡

• ባዶነት ደግሞ ለሌሎች አሳብ ተገዥ ለመሆንና ማንኛውንም አሳብ ለማስተናገድ

ተመቻችቶ መገኘት ነው፡፡

• እንዲህ ዐይነቱ ሰው ኀጢአተኛውም ጻድቁም የሚመላለስበትን መንገድን፣ የተሞላበትን

ሁሉ የሚያሳውን ባዶ ብርጭቆን ይመስላል፡፡

• ሌሎች የሞሉት እንጂ የራሴ የሚለው አሳብ የለውምና፡፡ የቄርሎስን ትምህርት ነው

የምከተለው የሚለው የአውጣኪ ግለሰባዊ ማብራሪያ እንዳይገጥመን የቤተ ክርስቲያንን

አስተምህሮ ማወቅ ይገባናል፡፡

• ለዚህ ደግሞ ዕቅበተ እምነት ታላቅ መሣሪያ ነው፡፡


• ቤተ ክርስቲያን ፈላስፎች እና መናፍቃን ለሚያነሧቸው
ጥያቄዎች መልስ ስትሰጥ ኖራለች፣ እየሰጠችም ነው፡፡
• ይህ ማለት እምነትን መጠበቅ ለሊቃውንቱ ብቻ የተተወና
ምእመናንን የማይመለከተን ተግባር ነው ማለት አይደለም፡፡
• በተለይ የኑፋቄ አሳቦች በበረቱበት በዚህ ዘመን “በገበሬ
አስደንግጥ ጥቅስ” ላለመበርገግ ነቅቶ መጠበቅ ይገባል፡፡
• ስለምናምነው እምነት ግን በቂ ዕውቀት የሌለንና መልስ
ለመስጠት የምንቸገር ክርስቲያኖች መሆን የለብንም፡፡
• ስለዚህ ከራሳችን አልፈን ለሚጠይቁን አካላት መልስ
ለመስጠት የተዘጋጀን ሆነን ከኖርን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን
እና አስተምህሮዋን ጠንቅቀን ዐወቅን ማለት ነው፡፡
• ሃይማኖትን በትክክል ተረድቶ በክርስትና ሕይወት ጸንቶ
በመኖር እምነትን ለመጠበቅ ዕውቀት የግድ አስፈላጊ ነውና፡፡
3. ራስን ከክሕደት ለመጠበቅና ሌሎችን ወደ ድኅነት መንገድ
ለመምራት፡-
• የክርስትና ዋናው ዓላማ ሰውን ለመንግሥተ ሰማያት ማዘጋጀት
ነው፡፡
• ሰውን ከሲዖል ጨለማ ወደ ብርሃን መመለስ የሚቻለው
በትምህርት ነው፡፡
• ክሕደት የስንፍና ጫፍ ነው፡፡
• ለዚህ ነው መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “ሰነፍ በልቡ
እግዚአብሔር የለም ይላል” (መዝ. ፲፬፡፩) ያለው፡፡
• ቅጠሏ የማይረግፍ፣ ፍሬዋ የማይነጥፍ ተብሎ እንደተነገረላት
በውኃ ዳር እንደበቀለች ዛፍ ራስን በቃለ እግዚአብሔር ማለምለም
ብቻ በቂ አይደለም፡፡
• ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞች ሆይ፤ ምናልባት
ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ
ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ” (ዕብ. ፫፡፲፪)
ብሎ ራስንም ሌላውንም ከክሕደት የመጠበቅ ሓላፊነት
ሰጥቶናልና፡፡
• ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ስለ ወንድሙ መዳን የማይገደው
እርሱ ድኗል ብዬ አላምንም” በማለት ሌሎችን ከክሕደት ወደ
እምነት፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መመለስ
አንደሚገባ ነግሮናል፡፡
• ሰውን ከዚህ የድንቁርና ክሕደት አውጥቶ ወደ ትክክለኛው
መንገድ መምራት የማንኛውም ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡
• ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ዕቃ
ጦር ብሎ የጠቀሳቸውን እውነትን፣ የጽድቅን ጥሩር፣ የሰላምን ወንጌል፣
የእምነትን ጋሻ፣ የመዳንን ራስ ቁር፣ የመንፈስን ሰይፍ (ቃለ
እግዚአብሔር) (ኤፌ. ፮፡፲፬-፲፯) ገንዘብ በማድረግ ነው፡፡
• ድኅነት ደግሞ ሌላ አማራጭ መንገድ የለውም፡፡
• መንገዷ አንድ ያውም ጠባብ ናት፡፡
• እርሷም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ናት፡፡
• ክሕደትና ኀጢአት መሥራት ከዚች መንገድ ያስወጡናል፣
ከእግዚአብሔር ይለዩናል፡፡
• ክፉ መሥራት ብቻ ሳይሆን በጎ አለመሥራት ኀጢአትና በእግዚአብሔር
ላይ ማመጽ ነው፡፡
• የራስን አስተምህሮ ማወቅ አንድ ነገር ነው፤ ሌሎች አማራጮች
እንደሌሉ ማመን ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡
• ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አማራጮች አለመኖራቸውን
በማመን ላይ ትክክለኛ አስተምህሮዎች አለመሆናቸውን
በአመክንዮ ማስረዳትም ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡
• እንዲህ ስናደርግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎች ወገኖቻችንን
እናድናለን፡፡
• “አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ደግሞ
ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ” (ይሁ. ፳፪) የተባልነውም ወደ ሞት
ከሚወስድ የተሳሳተ መንገድ ወደ ቀደመችዋ መንገድ
እንድንመልሳቸው ነው፡፡
• በብዙ ሰው ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይን እውነት አድርጎ መውሰድ
እየተለመደ መጥቷል፡፡
• አንድን ጉዳይ በተደጋጋሚ በተለያዩ ዘዴዎች በማቅረብ እውነት
እንዲመስልና ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ መሞከርም
እንዲሁ፡፡
• እውነት እውነትነቱ የሚታወቀው በነገሩ ጭብጥ እንጂ በአብላጫ
ድምጽ አይደለም፡፡
• በአብላጫ ሕግ እውነትን ሐሰት፣ ሐሰትንም እውነት ማድረግ
አይቻልም፡፡
• በሃይማኖት ውስጥ እውነት ወይም ሐሰት እንጂ የተሻለ የሚባል
ነገር የለም፡፡
• ማመንና መካድ የተሻለ ወይም መጥፎ የሚባል ደረጃ የላቸውም፡፡
• እገሌ የተሻለ ያምናል፣ እገሊት የባሰች ከሐዲት ናት
አይባልም፡፡
• ማመን ማመን ነው፤ አለማመን ደግሞ ክሕደት፡፡ ከዚህ
ውጪ ሌላ ምርጫ የለም፡፡
• ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዘው፣ ቅዱሳን አባቶቻችን
ካስተማሩት አንዱን ማጉደል ክሕደት መሆኑን መረዳት ተገቢ
ይሆናል፡፡
• ዕቅበተ እምነት ያስፈለገውም ይህን ለይተን ለማወቅ ነው፡፡
4. ከዘመን አመጣሽ የማንነት ወረራዎች ለመጠበቅ፡-
• በሥጋዊ ዐይን ሲታዩ በጎ የሚመስሉ፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ
የመራመድ ምልክት ተደርገው የሚቆጠሩ ብዙ የጥፋት
መንገዶች ተፈጥረዋል፡፡
• ጥበበኛው ሰሎሞን “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤
ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” (ምሳ. ፲፬፡፲፪) ብሎ
የጠቀሳት ዐይነት ብዙ መንገዶች ተፈጥረዋል።
• ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ፣ ክርስትናን የሚያዋርዱ፣
የዘመናዊነት መገለጫ፣ መብት፣ ግለሰባዊ ነጻነት፣ ወዘተ
በሚል መጽሐፍ ቅዱስን እንቀበላለን በሚሉ ቤተ እምነቶች
ጭምር ዕውቅና የተሰጣቸው ብዙ የጥፋት ርኩሰቶች
በዓለማችን በዝተዋል፡፡
• ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ በወቅቱ ከእግዚአብሔር
ይልቅ በራሳቸው መንገድ ይሔዱ ለነበሩት እስራኤላውያን
“ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ
ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጕድጓዶች፥ ውኃውን
ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል”
(ኤር. ፪፡፲፫) በማለት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደወቀሰ
ይነግረናል።
• ዛሬ ላይ በቃየን መንገድ የሚሔዱ፣ በበለዓም ስሕተት የጸኑ፣
በቆሬ መቃወም መጥፋት የሚሹ ኀጢአተኞች፣ ክፉዎችና
ዘባቾች በዝተዋል፡፡
• ቅዱስ ይሁዳ በመልእቱ “በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት
እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ … እነዚህ
የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ
ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ
ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን
ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ”
በማለት ከእነርሱ እንድንጠበቅ መክሮናል (ይሁ. ፲፰፡፳፩)።
• እነዚህ አካሔዶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆናቸውን፣
ከሰብአዊነት ደረጃ የሚያወርዱ የሲዖል መንገዶች መሆናቸውን
ለመሞገትና ሰውነትን ነውር የሌለበት ንጹሕ መሥዋዕት አድርጎ
ለማቅረብ ነውር በሌለበት ሃይማኖት ጸንቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡
5. በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነገሩ መጥፎ ገጽታዎችን
ለመከላከል፡-
• ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሁልጊዜ ቀስቱን አዘጋጅቶ
የሚጠብቀው ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያንን ያለስሟ ስም
መስጠት ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ የሚጠቀምባቸው
ብዙ አፎች አሉት፡፡
• የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመንቀፍ፣ በመሳደብና
በማጥላላት፣ መንፈሳዊ ክንዋኔዎችን ሁሉ በማቃለል
ምእመናንን ለማደናገር የሚሠሩ አካላት ብዙ ናቸው፡፡
• ቤተ ክርስቲያን በዓላትን በማብዛት ለአገር ድህነት ተጠያቂ
ናት ከሚለው የምግብ ጥያቄ ጀምሮ ክርስቶስን አታውቀውም
እስከሚለው የክሕደት ውንጀላ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን በብዙ
መልኩ የሚወቅሱት ብዙ ናቸው፡፡
• የግለሰቦችን የምግባር ድቀት የቤተ ክርስቲያን የአስተምህሮ
ስሕተትነት ማሳያ አስመስሎ ማቅረብ የተለመደ ሆኗል፡፡
• ሁሉም ባዶ ውንጀላዎች ናቸው፡፡
• ነገር ግን ለእነዚህ ሁሉ ውንጀላዎች መፍትሔ መስጠት
የምንችለው በዕቅበተ እምነት አቅማችንን ስናሳድግ ነው፡፡
ዕቅበተ እምነት ስንል በአጠቃላይ እነዚህን አራት
ዋና ዋና ተግባራት በቅደም ተከተል ማከናወን ነው፡፡

1. አስተምህሮን መግለጽ (ማረጋገጥ)፡-


• ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሐዋርያት የሰበኳት ሃይማኖት
መሆኗን ከታሪክ፣ ከትውፊትና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጠቅሶ
ማስረዳት ነው፡፡
• ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ ጌታችን
በሥጋዌው ወራት እንዳስተማረው ወደ ሕይወት የሚወስደው
መንገድ አንድ ያውም ጠባብ ነው፡፡
• ይህ ሁሉም ሰው የሚቀበለው እውነት ነው፡፡
• በዓለም ላይ ብዙ “ሃይማኖቶች” እንዳሉ ቢነገርም ብዙዎቹ
በሐሰት ሃይማኖት የተባሉ ናቸው፡፡
• ማንም ሰው በስም ሃይማኖት የተባሉት ሁሉ ትክክል
እንደሆኑ አያምንም፣ ሁሉም የእኔ ትክክል ነው የሚለው፡፡
ስለዚህ መጽሐፍ “የቀደመችዋን መንገድ ጠይቁ፣ በእርሷም
ላይ ሒዱ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ኤር. ፮፡፲፮)
እንዳለ ትክክለኛዋን መንገድ የማግኘት ጉዳይ እንጂ
ሃይማኖት አንድ መሆኗን ማንም ያምናል፡፡
• ይህችውም ሃይማኖት ነቅ የሌለባት ንጽሕት ኦርቶዶክሳዊት
ሃይማኖት ናት፡፡
• አስተምህሮዋ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ያለፈ ነው፡፡
• ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ነቢያት ትንቢት
የተናገሩላት፣ ክርስቶስ በሥጋዌው ወራት ያስተማራት፣
ሐዋርያት ዞረው የሰበኳት፣ የእምነት ጠበቆችና ሊቃውንት
ከኑፋቄ ከክሕደት የተከላከሉላት፣ ሰማዕታት ደማቸውን
አፍሰሰው፣ መራራ ሞትን ታግሠው፣ በጥብዐት የመሰከሯት
ሃይማኖት ናት፡፡
• ቀጥተኛ የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ በመግለጽ
እምነትን ማጽናት የመጀመሪያው የዕቅበተ እምነት ተግባር
ነው፡፡
2. ጥያቄዎችን መመለስ (ማቀብ/መጠበቅ)፡-
• በዓለም እንዲህ በዝተው የምናገኛቸው ቤተ እምነቶች
የተፈጠሩት ወይም የተስፋፉት በግለሰቦች አስተሳሰብ ነው፡፡
• ሃይማኖት የሰው አስተሳሰብ ውጤት ሳይሆን ራሱ
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የገለጠው እውነት ነው፡፡
• ሐዋርያው ይሁዳ በመልእክቱ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ
ስለተሰጠች ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ
እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” (ይሁዳ ፫) በማለት የገለጸው
ሃይማኖት እንዲት እንጂ ሌላ አማራጭ እንደሌላት ነው፡፡
• እምነት ማለትም እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት መቀበል
ማለት ነው፡፡
• እግዚአብሔር ከገለጠው እውነት ውጪ ሰዎች በይሆናል፣
በይመስለኛልና በግል መረዳት የፈጠሩት “እውነት”
ሃይማኖት ሊባል አይችልም፡፡
• ስለዚህ በምድራዊ ፍልስፍና፣ በመናፍቃን ቅሳጣ፣
በኢአማንያን ክሕደት ምክንያት በሰዎች አእምሮ ውስጥ
የተፈጠሩ ጥያቄዎችን በመመለስ ምእመናንን በበረታቸው
ማጽናት ሁለተኛው የዕቅበተ እምነት ሥራ ነው፡፡
• ይህ በአብዛኛው በመምህራነ ወንጌል የሚፈጸም ነው፡፡
• “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን
ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ
ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ. ፳፡
፳፰) በማለት ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመናንን ብሎም
ሃይማኖትን ለመጠበቅ ለተሾሙ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት
መጻፉም ለዚህ ነው፡፡
• ይህ ተግባር ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት
ባለመረዳትም ይሁን በተሳሳተ ትርጓሜ የሚነሡ
ተቃውሞችን፣ ጥያቄዎችን እና ትችቶችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ
በሆነ መንገድ መልስ በመስጠት በቤተ ክርስቲያን ላይ
የሚነሡ ክሶችን መመለስን ያጠቃልላል፡፡
• በአጭሩ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ምክንያታዊና
ከአመክንዮንም በላይ መሆኗን ማስረዳት ማለት ነው፡፡
3. የሰውን አእምሮ መጠበቅ፡-
• ተዋሕዶ ሃይማኖት ትክክል መሆኗን ከማስረዳት ጎን ለጎን
ሌሎች አስተሳሰቦች ትክክል እንዳልሆኑ ማስረዳት ይገባል፡፡
• የሰው ልጅ አምሮታዊ ነው፡፡ አዲስ የመሰለውን ወይም
በእርሱ ዕውቀት ትክክል ነው ብሎ የገመተውን መከተል
ይወዳል፡፡
• ነገር ግን ምድራዊ ፍልስፍናዎች ሁሉ በኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ሃይማኖት ፊት ጸንተው መቆም የማይችሉ፣ እንደ
ጉም ተነው የሚጠፉ ግላዊ አሳቦች ናቸው፡፡
• ተዋሕዶ ሃይማኖት ሃይማኖትን በመቃወም የተነሡ ፈላስፎችን
ፍልስፍና፣ አስተምህሮን ለመቀየር የተነሡ መናፍቃንን
ምንፍቅና መልሳ ከዚህ የደረሰች ናት፡፡
• ከእኛ ጉድለት ካልሆነ በስተቀር አባቶቻችን መልስ ያልሰጡበት
ጥያቄ፣ ያላወገዙት ኑፋቄ የለም፡፡
• ዐዲስ ጥያቄ ወይም ኑፋቄ ስለሌለ ዐዲስ ትምህርት እንድናመጣ
አይጠበቅብንም፡፡
• አባቶቻችን ከሃይማኖታችን ውጪ ያሉት አስተሳሰቦች ሁሉ
ከንቱና ነፋስን እንደመከተል መሆናቸውን በአፍም በመጽሐፍም
ስለገለጹልን እነርሱን በማስማትና በማየት ሌሎች “መንገዶች”
ሁሉ ትክክል አለመሆናቸውን በማጋለጥ የሰዎችን አእምሮ
ከክሕደት፣ ከኑፋቄና ከዓለማዊ አስተሳሰብ መጠበቅ ተገቢ
ይሆናል፡፡
• ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የሰውንም አሳብ
በእግዚአብሔርም ዕውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር
ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ
እንማርካለን” (፪ኛ ቆሮ. ፲፡፭) በማለት የጠቀሰው ስለዚህ
ነው፡፡
• የሰውን አእምሮ መጠበቅ ማለት ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ
ሃይማኖት ውጪ ያሉት አስተሳሰቦች ሁሉ ትክክል
አለመሆናቸውን ሰዎች እንዲረዱ ማድረግ ማለት ነው፡፡
4. እምነትን ማጽናት፡-
• ከክርስትና ውጪ ያሉት አስተሳሰቦች ትክክል አለመሆናቸውን
ማሳወቅ ወይም ክርስትና ትክክለኛና ብቸኛዋ መንገድ መሆኗን
ማስረዳት ብቻ ሰውን ለድኅነት አያበቃውም፡፡
• ሰው የሚድነው ቃሉን በመስማት ሳይሆን ቃሉ የሚለውን
በመኖር ነው፡፡
• የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም በእርሱ እንዲያምኑ፣ ትእዛዛቱን
ጠብቀው ምግባር ትሩፋት ሠርተው መንግሥቱን እንዲወርሱ
ነው፡፡
• የተሳሳተው ከስሕተት መንገዱ እንዲመለስ፣ የወደቀው እንዲነሣ፣
የተነሣው እንዲጸና፣ የጸናው እንዲቀደስ ማድረግ የዕቅበተ እምነት
አንዱና ዋነኛው ሥራ ነው፡፡
• ስለዚህ ሃይማኖት አንዲትና ብቸኛ መሆኗን በማረጋገጥ የተጀመረው
የዕቅበት እምነት ሥራ ሰዎች እምነታቸውን አጠንክረው፣ በምግባር
በትሩፋት አጊጠው ለጽድቅ የተዘጋጁ ሙሽሮች በማድረግ ይጠናቀቃል
ማለት ነው፡፡
• በአጠቃላይ የዕቅበተ እምነት ሥራ በሃይማኖት ውስጥ ያሉት
በእምነታቸው እንዲጸኑ ያላመኑትና ነፍሳትን ለማጥፋት የተነሡት
ከስሕተታቸው ተመልሰው አምነውና ተጠምቀው የክርስቶስ አካላት
እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
• ዕቅበተ እምነት የሚፈለገውን ውጤት አመጣ የሚባለው የራስን
መክሊት በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በመማረክ ነው፡፡
• በተለይ ሥጋዊ ፍልስፍናቸው እግዚአብሔርን ከማምለክ
የከለከላቸውን ሰዎች ከፍልስፍና እስራታቸው ተፈትትተው
በእግዚአብሔር እንዲያምኑ ማድረግ የዕቅበተ እምነት ግብ ነው፡፡
በዕቅበተ እምነት አገልግሎት ውስጥ ጥበቃ
የሚደረግላቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
• በዋናነት ዕቅበተ እምነት ስሙም እንደሚናገረው ጥበቃ
የሚያደርገው ለሃይማኖት ነው፡፡
• ሃይማኖት ሲባል ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት መንገድ
ስለሆነ በውስጡ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡
• በሃይማኖት ውስጥ አምልኮትን የሚፈጽሙ ግእዛን ያላቸው
ፍጥረታት፣ አምልኮት መፈጸሚያዎች፣ አገልጋዮችና በሃይማኖቱ
ሥርዓት ውስጥ በዘመናት የበለጸጉ እሴቶች አሉ፡፡
• ስለዚህ ዕቅበተ እምነት ስንል የእነዚህን ሁሉ መጠበቅ
የሚያጠቃልል ነው፡፡
1. ምእመናን፡-
• ዕውቀት በማጣት ምክንያት እንዳይጠፉ መጠበቅ ያለባቸው
የመጀመርያዎች ተጠባቂዎች ምእመናንን ናቸው፡፡
• ክርስቶስ የሞተላቸው፣ በክቡር ደሙ የዋጃቸው ምእመናን
በኑፋቄ መርዝ እንዳይጠቁ፣ በነጣቂ ተኩላ እንዳይነጠቁ
ለትምህርት የደረሱትን ራሳቸውን እንዲጠብቁ በማስተማር፤
ለትምህርት ያልደረሱትን ደግሞ ተግቶ በመጠበቅ
የመንግሥተ ሰማያት ሙሽሮች ማድረግ ከእያንዳንዱ ሰው
ይጠበቃል፡፡
• ከሐሰተኛ መምህርና ከሐሰት ትምህርት ተጠብቀው፣ ቤተ
ክርስቲያንን እና አስተምህሮዋን አውቀው፣ የበግ ለምድ
ለብሰው የሚመጡ የውስጥ ጠላቶች በመከላከል በሃይማኖት
በምግባር ጸንተው ድርሻቸውን ተወጥተው እንዲኖሩ ማድረግ
ያስፈልጋል፡፡
• “ንቁ፣ በሃይማኖት ቁሙ፣ ጎልምሱ ጠንክሩ” (፩ኛ ቆሮ. ፲፮፡
፲፫) ተብሎ ተነገረው ለሁላችን ነውና በሃይማኖት መጽናት፣
በምግባር መጎልበት ያሻል፡፡
2. አገልጋዮች፡-
• ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ ባለው መዋቅሯ ከብፁዓን አበው
ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ አፀውተ አናቅጽ ድረስብዙ አገልጋዮች
አሏት፡፡
• እነዚህ አገልጋዮች ራሳቸውን ከኑፋቄ የመጠበቅ አቅም
እንዳላቸው ግምት ይወሰዳል፡፡
• ክፍተቶች ካሉ የራሳቸውን መንፈሳዊ ዕውቀት የሚያዳብሩባቸው
ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት አንዱ ዘዴ ነው፡፡
• ከዚህ በተጨማሪ ግን ከሐሰተኛ ውንጀላ መከላከል፣ በተለያዩ
ፈተናዎች ከሚገጥማቸው ድካም ማገዝ፣ ተርበውና ተጠምተው
ከሃይማኖታቸው እንዳይናወጹ መደገፍ የማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ
ግዴታዊ የዕቅበተ እምነት ተግባሩ ነው፡፡
• “ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል
ትጉ” (ሮሜ ፲፪፡፲፫) ተብሎ የታዘዘ ክርስቲያን ሁሉ መንፈሳዊ
አባቱን ማገልገልና መርዳት አለበት።
• አብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳማትን አለመጠበቅ፣ ለቤተ
ክርስቲያን ሊቃውንትና ለደቀ መዛሙርት ክብካቤ
አለማድረግ ዕውቀትን ለማጥፋት እንደመሥራት ይቆጠራል፡፡
• ዕቅበተ እምነት የሚሰፋው መንፈሳዊ ሊቃውትን በማብዛት
ነው፡፡
• ስለዚህ በእምነት ጸንተን፣ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን
ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትን ለመምራት የሚያስተምሩንንና
የሚያቆርቡንን ካህናት መጠበቅ ይገባናል፡፡
3. ቅዱሳት መጻሕፍት፡-
• “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን
ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ
ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው
ምክር ደግሞ ይጠቅማል” (፪ኛ ጢሞ. ፫፲፮) እንደተባለ
ቅዱሳት መጻሕፍት የሰውን ልብ ለማቅናት የሚጠቅሙ
መምህራን ናቸውና መጠበቅ አለባቸው።
• ያልተተረጎሙትን መተርጎም፣ የተቆነጻጸሉትን ማከም፣
የስሕተት ትምህርት እንዳይጨመርባቸው መጠበቅ ዋና
የዕቅበተ እምነት ተግባር ነው፤
• በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በኢአማንያንና በመናፍቃን ለሚነሡ
ጥያቄዎች መልስ መስጠትም እንዲሁ፡፡
4. የቤተ ክርስቲያን እሴቶች:-
• ቅድስት ቤተ ክርስቲን በዘመናት የሕይወት ጉዞዋ ውስጥ
ያፈራቻቸው መልካም እሴቶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ
ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
• ለምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያን በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላት
ተሰሚነት፣ ካህናት በሁሉ ፊት የነበራቸው ሞገስና ክብር፣
አርአያ ክህነትና መንፈሳዊ ልዕልና፣ ኦርቶዶክሳውያን
ምእመናንን ለአገርና ለሃይማኖት ያላቸው የነደደ ፍቅር
በዘመናዊነት ስም እንዳይሸረሸር ማድረግ ዕቅበተ እምነት
ነው፡፡
• እምነታችንን እስካሁን ድረስ ተጠብቆ የዘለቀው በብዙ ተጋድሎ ነው፡፡
• በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱት ፈተናዎች ክርስትናችንን እንድናጠብቅ
እንጂ እንድንጥል አላደረጉንም፡፡
• የእነዚህ ፈተናዎች መከሰት ጉዳት ቢኖረውም ቤተ ክርስቲያን ቋሚና
ዓለም አቀፋዊ መገለጫዎች የሆኑ እሴቶችን እንድታዳብር አድርገዋል፡፡
• የሰማዕትነት፣ የመንፈሳዊነት፣ የጥብዓት፣ የእውነተኛነት፣ የአንድነት፣
የፍቅርና የመጥወተ ርእስ እሴቶችን ማስቀጠል ካልቻልን ክርስትና ግላዊ
አስተሳሰብ ይሆናል፡፡
• እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች የመሆናችን መገለጫዎች ናቸው፡፡
• በጥምቀት የተጀመረ ክርስትና ለሌሎች ራስን በመስጠት ይጠናቀቃል፡፡
ለዚህ ነው ፍቊረ እግዚእ የተባለው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “ነፍሱን
ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም
የለውም” (ዮሐ. ፲፭፡፲፫) በማለት የነገረን።
5. የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሀብቶች፡-
• የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ብቻ
ሳይሆን ለአገር ያበረከተቻቸው አያሌ አስተዋጽኦዎች አሉ፡፡
• አገራችን የራሳቸው ፊደል ካላቸው ጥቂት አገራት ውስጥ
አንዷ ናት፡፡
• ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ፊደል ቀርጻ፣ ብራና ዳምጣ ሥነ
ጽሑፍን አስፋፍታለች፡፡
• ለመሸከም እንኳን የሚከብዱ ብዙ የብራና መጻሕፍት
አሏት፡፡
• በኪነ ሕንፃ ውበታቸው አስደናቂ የሆኑ ብዙ አብያተ
ክርቲያናት አሏት፡፡
• ያሬዳዊ ዜማ፣ የዜማ መሣሪያዎች፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ
ቅርሶች፣ ግዙፍነት ያላቸውና ግዙፍነት የሌላቸው ትውፊቶች፣
የራሷ የዘመን መቁጠሪያ ያላት ስንዱ እመቤት ናት፡፡
• እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ሀብቶች ሕጋዊ ጥበቃ
እንዲደረግላቸው፣ ለሌሎች አካላት ለዓለማዊ መጠቀሚያ
እንዳይውሉ ወይም ተመሳስለው በሚያደናግሩ ቀሳጢያን
እንዳይዘረፉና የቤተ ክርስቲያን ሀብትነታቸው እንዲረጋገጥ
ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
• እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም
ኀይሉ እንዲወድ፣ ባልንጀራውን እንደ ራሱ እንዲወድ የታዘዘ
ክርስቲያን በሁለንተናዊ ሕዋሳቱ ሁሉ የዕቅበተ እምነት
መሥራት አለበት፡፡
• የምንችል በአንድነትም ሆነ በተናጠል፣ በዕውቀት፣ በአሳብ፣
በጉልበት በአገልግሎቱ በመሳተፍ ይህን ማድረግ የማንችል
ደግሞ ወደዚህ ደረጃ ራሳችንን ለማሳደግ ራሳችን ላይ
የምንሠራው ሥራ እንደተጠበቃ ሆኖ የሚሠሩትን በገንዘብ
በመደገፍ የጠፉትንና አጥፊዎችን ወደ በረታቸው መመለስ
ይገባናል፡፡
• ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ሙሉ ድል አገኘን ወይም
የዕቅበተ እምነት ሥራ ሠራን ማለት የሚቻለው፡፡

እግዚአብሔር ቤቱን እድንጠብቅ ይርዳን!

You might also like