You are on page 1of 4

የግብፅ ስስ ብልት

በዘመናት የታሪክ ሂደት ውስጥ ከሀገራችን ጋር በብዙ መልኩ ግንኙነት ከነበራቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ግብፅ ናት፡፡ ሁለቱ
ሀገራት ከፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነታቸው በላይ ሀይማኖታዊ ግንኙነታቸው ሚዛን ደፍቶ ይስተዋላል፡፡በዛሬው ፅሁፍ
በሁለቱ ሀገራት መሀል ስለነበረው ሀይማኖታዊ ግንኙነት በተለይም ደግሞ በጳጳሳት ሹመት ዙርያ በንጉስ ጃን ስዩም እና
በንጉስ ይምርሀነ ክርስቶስ ዘመነ መንግስት ወቅት የነበሩ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመንግስት ወደ ላስታ ከዞረ በኃላ በዮዲት ጉዲት በደረሰው ጉዳት የተደናገጠው ህዝብ የሀይማኖት
ስሜቱ ድጋሚ ተቀሰቀሰ፡፡በወቅቱ የነገስታቱና የመኳንንቱ ልጆች በለጋ እድሜያቸው መመነን በመጀመራቸው በወቅቱ
የምንኩስና ህይወት እጅግ ተስፋፍቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ከ 925 ጀምሮ የነበረው ጠጠውድም የተባለው ንጉስም በዮዲት
ጊዜ የፈረሰውን የአክሱም ፅዮንን ቤተ ክርሰቲያን እንዲሁም የፈራረሱትን ሀውልቶች በድጋሚ አሰራ፡፡በዚህም ዘመን
በግብፅ የነበሩ ክርስቲያኖች በሀገራቸውያለውን የሙስሊሞች ጫና በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ታሪክ ያወሳል፡፡
ከ 965 እስከ 1005 ዓ.ም የነበረው የኢትዮጵያ ንጉስ ጃን ስዩም በዘመኑ የእስክንድርያ ሊቀጳጳስ ለነበሩት ለአባ ፊላታዎስ
አንድ መልዕክት ላኩ በመልክቱም በቤተክርስቲያኒቱ ላይ በደረሰው መከራ ምክንያት በርካታ ችግሮችን ማሳለፋቸውን
ገልፀው ህዝቡን ከፈጣሪው የሚያስታርቅና የሚባርክ ጳጳስ እንዲልኩላቸው ጠየቁ፡፡በዚህም መሰረት ከአባ መቃርስ ገዳም
አባ ዳንዔል የተባሉ ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ መጡ ህዝቡም ናፍቆት በተቀላቀለብት ደስታ እና እንባ ተቀበላቸው፡፡ጳጳሱም
የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትን በማሰራትና ያዘኑ ህዝቦችን በማፅናናት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን በሀገራችን ሲፈፅሙ
ቆዩ፡፡
በወቅቱ ግብፅን ይመሩ ከነበሩ ኢስላማዊ መሪዎች አንዱ ከሊፋ አል ሀኪም የእስክንድርያ ሲኖዶስ ወደ ኢትዮጵያ
ለሚልካቸው ጳጳሳት ግብር አይከፍሉም በማለት ብዙ ጊዜ ጳጳሳቱን ያስርና ያሰቃይ ነበር፡፡በዚህም በርካታ መምህራንና
ምዕመናን ሌላ የሚሄዱበት ሀገር ስላልነበራቸው በወቅቱ የሀይማኖት ወንድሞቻቸው ወደነበሩት ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ
መጡ ህዝቡም በደስታና በፍቅር ተቀበላቸው፡፡

ሙስሊሙ ጳጳስ
በኢትዮጵያ የነበሩት ጳጳስ አባ ዳንኤል ህይወታቸው ሲያልፍ ጳጳስ እንዲላክልን የሚል መልዕክት ወደ ግብፅ ሐገር ተላከ
ነገር ግን በወቅቱ የእስክንድርያ ለቀ ጳጳስ አባ ክሪስቶ በኑቢያ እና በኢትዮጵያ የሚገኙ መስጊዶች እንዲፈርሱ አድርገዋል
በሚል ክስ ወህኒ ወርደው ስለነበር ኢትዮጵያውያኑ መልእክተኞች ሳይሳካለቸው ቀረ ፡፡ በዚህም መሀል አብዱም የሚባል
ሙስሊም ግብፃዊ የሀሰት ድብዳቤ ይዞ አባ ቄርሎስ ነኝ በማለት ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ህዝቡም የተለመደውን ታላቅ
አቀባበል አደረገለት ፡፡ ነገር ግን በግብፅ ይህ ዜና እንደተሰማ የግብፅ መንግስት ወዲያው እንዲያዝ ወደ ኢትዮጵያ
መልዕክት በመላክ ካስያዙት በኃላ ወደ ግብፅ ተወስዶ አንገቱ በሰይፍ ተቀልቶ ተገደለ፡፡
በግብፅ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አባ ክርስቶዶልም ሲሞቱ በምትካቸው አባ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ከዚህ ሹመት
በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ጳጳስ ለመላክ ዝግጅት ተደረገ፡፡ነገር ግን በወቅቱ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው በድርእል ጀማል ተፅዕኖ
በማድረግ ሲኖዶሱ የመረጣቸው ሳይሆኑ የኢስላማዊው መንግስት ወዳጅ የነበሩት አቡነ ሳዊሮስ ወደ ኢትዮጵያ ተላኩ፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት ንጉስ ግርማ ስዩም እና ህዝቡ ደማቅ አቀባበል አደረገላቸው ፡፡ነገር ግን አቡኑ
ወደኢትዮጵያ ከገቡ በኃላ የቤተክርስቲያንን ስራ ከመጀመራቸው በፊት በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሙስሊሞች በርካታ
ድጋፎችን ያደርጉ ነበር፡፡ለሙስሊም ማህበረሰቡ ሀይማኖቱን እንያስፋፋ ምክረ ሀሳብም ይሰጡ ነበር፡፡

ሐበሻዊ ዛቻ

አቡኑ በኢትዮጵያ በቆዩበት ጊዜ 7 መስጂዶችን ማሰራታቸውን እና ከሀገራቸው ሲመጡ ለ በድርእል ጀማል የገቡትን
ቃል ለመፈፀም ሲሰሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ይህም ነገር ሲበረታ ህዝቡ በአቡኑ ላይ በመቆጣቱ ንጉሱ ጳጳሱ ወደ ማረፍያ
እንዲገቡና ያሰሯቸውም ሁሉም መስጂዶች እንዲፈርሱ ተደረገ፡፡ይህ ሲሆን ከጳጳሱ ጋር አብ መጥቶ የነበረው
ወንድማቸው የሆነውን ነገር ሁሉ ለ በድርእል ጀማል ነገረው፡፡በዚህ ጊዜ በድርእል ጀማል በኃይሉ ይመካ ነበርና እንዲህ
ሲል መልዕክት ላከ‹‹ በሀገርህ የፈረሱት መስጂዶች ካልተሰሩ እኔም በግብፅ የሚገኙትን የቅብጥ/ ኮፕት / ቤተክርስቲያን
አፈራርሳለው ›› ብሎ የዛቻ እና የማስፈራርያ መልዕክት ላከ፡፡ነገር ግን ንጉሱ ዛቻውን ከጥፍ ሳይቆጥሩ ይህን ምላሽ
ሰደዱለት ‹‹ ከግብፅ ቤ/ክ አንዲት ደንጊያ ብታነሳ መካ ተሻግሬ የከአባን ደንጊያ አመድ አድርጌ ትቢያውን ካይሮ
እልክልሀለው ›› ብለው እንደመለሱለት ይነገራል፡፡
በግርማ ስዩም ዘመነ መንግስት በመካከለኛው ምስራው የመስቀል ጦርነት ተጀምሮ ስለነበር ግብፃውያኑ ትኩረታቸው
ወደዚያ ሲዞር የኢትዮጵያኑ ትኩረት ደግሞ ወደ ግብፅ ሆነ፡፡ግርማ ስዩም አርፈው ልጃቸው ንጉስ ይምርሀነ ክርስቶስ
ነገሱ፡፡ነገር ግን በግብፅና ኢትዮጵያ መሀል ያለው ግንኙነት ግን በኢስላማዊው የግብፅ መንግስት አማካኝነት የሻከረ ነበር፡፡
በግርማ ስዩም ዘመን እስር ቤት ገብተው ከነበሩት ከአቡነ ሳዊሮስ ጀምሮ ጳጳስ ተልኮ አያውቅ ስለነበር ይምርሀነ
ክርስቶስ ወደ ግብፅ መልዕክተኞችን ልኮ አቡነ ጊዮርጊስ የተባሉ ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ነገር ግን አቡኑ
ስግብግብነታቸው የበዛና በንግድ ገንዘብ እንደሰበሰቡ ሲታወቅ ወደ ግብፅ እንዲሄዱ ተደረገ፡፡

አባይ - ግብፅን ማስፈራርያ

ይምርሀነ ክርስቶስ በዘመናቸው ከሰሩት ስራዎች መሀል አንዱ በአባይ ግብፅን ማስፈራራታቸው ዋነኛው ነው፡፡በዘመኑ
በግብፅ ሐገር በኢስላማዊ የሀገሪቱ መሪዎች የተነሳ በርካታ ክርስቲያኖች በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡ይህን የተደረዳው
ይምርሀነ ክርስቶስ የግብፅ ስስ ብልት የሆነውን የአባይን ወንዝ ለመገደብ ሞከረ፡፡በዚህም ወደ ግብፅ የሚወርደው የዓባይ
ውሀ መቀነስ ያስደነገጣቸው የግብፅ ነገስታት የአባይ ውሀ ከቀነሰ ህዝቡ በውሀ ጥም እነደሚሞት በመረዳታቸው
ውሀውን ያስለቅቁ ዘንድ አማላጅ አድርገው አቡነ ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ፡፡አቡኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ይህን
ተማፅኖ አቀረቡ ‹‹ የአባይን ውሀ በማስቆማቹ የሚጎዱት ሙስሊም ግብፃውያን ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁ
ስለሆኑ ይህን አስረድቼ ልመናዬን ለህዝቡና ለንጉስ ይምርሀነ ክርስቶስ ለማቅረብ ነው የመጣውት ›› ብለው
መልዕክታቸውን አደረሱ ፡፡ በዚህ ጊዜ ውሀው ተለቀቀ ሊቀ ጳጳሱም ደስ ብሏቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ግብፅን ያስተዳድረ የነበረው መንግስት ሀገራችን ላይ በበርካታ ጊዜያት በተለይም ደግሞ ሀገራችን
የራሷ የሆነ ጳጳስ እንዳይኖራትና ሁሌም ግብፅን ለጳጳስ ሹመት በመለመን ጥገኛ እንድትሆን እንዲሁም ጳጳስ እንዲሾም
በሚል የሚላክን ወርቅን ጨምሮ እጅግ ብዙ የሀገር ሀብት ለዘመናት ለመበዝበዝ በርካታ ሴራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል
ከነዚህ መሀል የተወሰኑትን በሚቀጥለው ፅሑፍ ይዘን እንመለሳለን፡፡

You might also like