You are on page 1of 16

አክሊለ ሃይማኖት

ዘኢትዮጵያ።

ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አቡነ ባስልዮስ በአኤሮፕላን ጣቢያ
ለግርማዊት እቴጌ መነን መስቀል ሲያሳልሙ።

በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ታተመ።


አክሊለ ሃይማኖት

ዘኢትዮጵያ

ለኢትዮጵያ ጸጋውን አከታትሎ መስጠት ልማዱ የሆነ ልዑል እግዚአብሔር፤ አንድ ሺህ ስድስት መቶ
ዘመን በረቂቅ ጥበቡ ጠብቆ ያኖረው የኢትዮጵያ የእስክንድርያ ሃይማኖታዊ አንድነትና ግንኙነት፤ በደገኛው ንጉሠ
ነገሥት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትጋትና እድለኛነት የበለጠ መከባበርን፤ መፈርቃቀርን መተባበርን እንዲያገኝ እነሆ
አደረገ።

የዚሁ አደራ በታማኙና በመንፈሳዊው ሐዋርያ በብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአቡነ ባስልዮስ
እንዲጠበቅ ቅዱስ ፈቃዱ ሆነ። ስለዚህ፤ ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ፈቃድ የታደሰላትን ይህን የሃይማኖት መሠረት
ከቀድሞው በበለጠ የሥራዋ ሁሉ ድጋፍ ልታደርገው ትችላለች።

አዲስ አበባ ሐምሌ ፱ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም

በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ታተመ።

ከትልቅ ትግል በኋላ የተገኘ

መንፈሳዊ ድል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብፁዕ ፓትሪያርኩን ለመቀበል የቻለው ሐምሌ ፬ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም ቢሆንም፤ መላው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንፈሳዊ ታሪኩ ታላቅ ጌጥና ክብሩ፤ ለመጪው ትውልድ ትምክህቱ የሆነውን ይህን ታላቅ
ሥልጣን ለወገኑ ሊያስገኝ የቻለውን ሰኔ ሐያ አንድን የሚያከብረው ወደር በማይገኝለት የደስታ ስሜት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሙሉ መብትና ነፃነት ሊቀ ጳጳስዋ ፓትርያርክ ተብለው ሊቀ


ጳጳሳትና ጳጳሳትን ለመሾም የሚያስችላቸውን መብት ያገኙት በዚህች በማትረሳ ቀን ነው።
ለሰው ልጅ የኖሩ መሠረት ሃይማኖት እንደ መሆኑ መጠን፤ የኢትዮጵያም ከብዙ ሺህ ዘመናት ጀምሮ ያለ
አንዳች መናወጽ፤ ጸንቶ ለኖረ ሃይማኖቷ የክብር አክሊል የሆነውን የመጨረሻ ሥልጣን ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ
ክርስቲያኗ ስታስገኝ የሚሰማት ሙሉ ደስታ ታላቅ ነው።

የኢትዮጷ ዘወትር እምነቷ በእግዚአብሔር ሥልጣን ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም በመሆኑ በመንፈሳዊ
ሆነ፤ በሥጋዊ በኩል በየጊዜው ተጠቅማበታለች።

በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድካም ይህ ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ነፃነት በመገኘቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ
በዚህ ቀን ለፈጣሪው ምሥጋና ያቀርባል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ

ፓትርያርክ።

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰኔ ፳ ቀን ከእኩለ ቀን በኋላ ለእስክንድርያው ፓፓና
ለመንበረ ቅዱስ ማርቆስ ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ ሳድሳዊ አንድ ላንቃ አንድ የወርቅ መስቀልና
አንድ የወርቅ ወንጌል ልከውላቸዋል። ይህንንም ስጦታ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ስም ለብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ
ያስረከቡ ልዑል ደጃዝማች አሥራተ ካሣ ናቸው።

ሰኔ ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስ ስላሴ በሁለት ሰዓት የክብር
ተከታዮቻቸውን አስከትለው በካይሮ ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኢትዮጵያ ሊቀ
ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ተብለው የተሾሙበትን መብትና ሥልጣን በተቀበሉበት ሥነ ሥርዓት ላይ
ተገኝተዋል።

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ከኩቤ ቤተ መንግሥት ተነሥተው በምስር፤ በሱዳን በላምሴና በአልሹምሕሪያ
መንገዶች በኩል አልፈው ወደ በትረካናው በሚያልፉበት ጊዜ ማለድ ብሎ እንደተለመደው በየመንገዱ ተሰብስቦ
የሚጠባበቀው ሕዝብ ደስታውን በጭብጨባ ገለጡላቸው።

ወደ በትረካናው ግቢ በደረሱ ጊዜ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕዝብ ውጭውንና ግቢውን ሞልቶት


የግርማዊነታቸውን ስም እየጠራ ልብ የሚነካ አቀባበል አደረገላቸው።

ወደ በትረካናው ውስጥ እንደ ገቡ የእስክንድርያው ፓፓና የመንበረ ቅዱስ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ
ወቅዱስ አባ ቄርሎስ፤ የእስክንድርያ ቤተ ክርስትያን ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የቤተ ክህነት አላፊዎችና ሌሎችም
ሹማምንቶች በክብር ተቀበሉዋቸው።

ወዲያው፤ ከብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ ጋር ወደ ፎቅ ወጥተው ትቂት ደቂቃዎች ያህል በወዳጅነት


ከተነጋገሩ በኋላ፤ ለአባ ቄርሎስ ታላቁን የሰሎሞንን ኮርዶኒ ኒሻን ከነፕላኩ ሸለሙዋቸው።

እንደዚሁም ስማቸው ከዚህ ግርጌ ለተዘረዘረው ጳጳሳት ልዩ ልዩ ሽልማት አደረጉ።

ለአቡነ ሉቃስ የኢትዮጵያን የክብር ኮከብ ኮርዶን።

ለአቡነ ዮሐንስ ሀብቶን የኢትዮጵያን የክብር ኮከብ ኮርዶን።

ለአቡነ ብኒሜን የምኒልክን ካርዶን ያንገት ከነ ፕላኩ።

ለአቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያን የክብር ኮከብ ከነፕላኩ።

ከዚህ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ የራሳቸውን ሥዕል ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መታሰቢያ ሰጡ።
እንደዚሁም ለልዕልት ሣራ ግዛውና ለልዕልት አይዳ ደስታ፤ እልቀሩትም የክብር ተከታዮች ሥዕላቸውን
አበረከቱ።

በበትረ ካናው ፎቅ ላይ የሚደረገው የኒሻን ሽልማት ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት፤
ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፤ ሌሎቹን ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳትን፤ አስከትለው በዚያው ግቢ
ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሲያመሩ፤ የተሰበሰበው ሕዝብ አሁንም ያለማቋረጥ
እያጨበጨበና የጃንሆይን ስም እየጠራ ደስታውን ገለጠ።

ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብተው በቅዱስ ማርቆስ መንበር ፊት ለፊት በተለይ በተዘጋጀው ዙፋን ላይ እንደ
ተገኙ፤ ስለ ሹመቱ የሚደረገው ሥርዓት ተጀመረ።

በሥርዓተ ጸሎቱም ውስጥ ከግብጽ ጳጳሳትና ዲያቆናት ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያን


ጳጳሳትና መነኰሳት ተባብረው ይሠሩ ነበር።

በጥንታዊው በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኤሮፓ አብያተ ክርስቲያናት እንደራሴዎች፤ የውጪ
አገር መንግሥታት እንደራሴዎች የዓረብ አንድነት ሬፑብሊክ ባለሥልጣኖች፤ ታላላቅ ሰዎች፤ ሴት ወይዛዝሮችና
በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎች ይታዩ ነበር። በአጭሩ የቤተ ክርስቲያኑ ፎቁም ምድር ቤቱም በሕዝብ
ብዛት ተመልቶ ይታይ ነበር። አራት ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስ በትሕትናና በአክብሮ
ራሳቸውን ወደደፉት ወደ ብፁዕ አባታችን አቡነ ባስልዮስ ዘንድ ቀርበው በኮፕት ልሳን አጭር ቃል ከተናገሩ
በኋላ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትሪያርክ የሚያሰኛእችውን ዘውድ
ጫኑላቸው።

በዚችም በማትረሳ ደቂቃ ውስጥ ጥቂት ጸጥታ ሆኖ ነበር። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አባ
ባስልዮስ፤ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ብርቱ ትግልና ድካም ይህን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን
የደረሳትን ታላቅ ክብርና የዚህም ክብር የአደራ ጠባቂነት ለሳቸው መድረሱን በማስታወስ ልባቸው በጥብቅ ስለተነካ
ዐይናቸው ዕንባ አዝሎ ይታይ ነበር።

ከዚህ በኋላ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቄርሎስና ብፁዕ ወቅዱስ አባ ባስልዮስ በመንበራቸው ላይ እንደ
ተቀመጡ፤ ከብፁዓን ጳጳሳት መካከል አንዱ ተነሥተው፤ የኢትዮጵያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትሪያርክ ወደ ፊት
ያለባቸውን ኃላፊነት ከባድ መሆኑን በማስታወስ ይህን ከባድ ኃላፊነት እያሰቡ በሚሰሩበት ጊዜ ሁሉ፤ ከቅዱስ
ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረገው ሥርዓት እንደ ተፈጸመ፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ብፁዕ ወቅዱስ አባ
ቄርሎስና ብፁዕ ወቅዱስ አባ ባስልዮስ ሌሎቹን ጳጳሳት አስከትለው እንደ ገና ወደ በትረካናው ሔዱ።

በዚሁም በበትረካናው ውስጥ ታላላቆችን ሰዎች በየተራ እየተቀበሉ አነጋገሩ። የቍርስም ግብዣ በዚያው
ተደረገ።

በግብዣውም ላይ፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ በበትረካናው አማካይነት


ለሚተዳደሩት ለነዳያን ልጆችና ለሆስፒታሎች መርጃ 1000 ፓውንድ ስተርሊንግ፤ ለቍስቋም ገዳም 300 ፓውንድ
ስተርሊንግ፤ ለሶርያ ገዳም 300 ፓውንድ ስተርሊንግ ስጦታ አደረጉ።

በበትረካናው ውስጥ የሚደረገው ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በጥንታዊ ካይሮ
ከተማ የሚገኘው የኮፕትን ሙዚዬም ለመጐብኘት ሔዱ።…….

ከእኩለ ቀን በኋላ፤ በዓሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ብፁዕ ወቅዱስ አባ ባስልዮስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ስለ አዲሱ ሹመታቸው በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ፊት ደንበኛውን ሥርዓተ መሐላ
ፈጽመዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አባ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቀ ጳጳሳትና ፓትርያርክ
ሰኔ ፳፩ ቀን ከእኩለ ቀን በኋላ፤ በ፲፩ ሰዓት በኩቤህ ቤተ መንግሥት ስለ አዲሱ ሹመታቸው በግርማዊ ንጉሠ
ነገሥት ፊት ሥርዓት መሐላን ሲፈጽሙ የተናገሩት።

ቃለ በረከት።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

በግርማዊነትዎ መሪነት ሁልጊዜ ከክብር ወደ ክብር በመሸጋገር ላደገችው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህ


የፓትርያርክነት ማዕርግ ዛሬ ስለተፈጸመላትና ለዚሁ ማዕርግ የኔ ደካማ ሰውነት፤ ቀዳሚነትን ለማግኘት ስለ ታደለ፤
ከሁሉ አስቀድሜ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ።

ወደዚህ ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ለመድረስ ሲፈቅድልኝ ለግርማዊነትዎ ያለኝን የታማኝነት ቃል ኪዳን


በፊትዋ ቆሜ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ምክንያት አግኝቻለሁ።

ግርማዊነትዎ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለማሳደግ ይህ ዛሬ የተገኘው ማዕርግ ከነመብቱ ለኢትዮጵያ


እንዲሆን፤ ባለፉት ፴፩ ዓመታት ውስጥ ያደረገው ድካምና ትጋት ይህን ፍሬ ለማፍራት በቅቷል። እስከዛሬም ድረስ
ወደዚህ ግብ ለመድረስ በግርማዊነትዎ ለተደረገው ሰላማዊ ትግል መደምደሚያው ይሆናል።

ያንድ ነፃ መንግሥትና ያንድ ነፃ ሕዝብ እናት፤ መሠረታዊቱ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን


በመንፈሳዊ ረገድ ራስዋን ችላ የምትተዳደር እንድትሆን፤ ግርማዊነትዎ ያደረገው ድካም ከታሪክ በላይ ስለሆነ፤
ዘመንዎ ዘመነ ሰላም እንዲሆንና ትውልደ መንግሥትዎ እንዲባረክ፤ እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ፤ ወጽድቀከኒ
ለወልደ ንጉሥ አግግር ፀሮ ታሕጠ እገሪሁ ዕቀብ ንግሦ ወሠራዊቶ ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ እያለች
ቤተ ክርስቲያን ባለማቋርጥ ወደ እግዚአብሔር ትጸልያለች።

ግርማዊነትዎ ምድረ ግብጽን በሚጐበኙበት በዚህ በአሁኑ ጊዜ አጋጣሚ ሆኖ በተገኙበት በመንበረ ማርቆስ
ቤተ ክርስቲያን አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ የተፈጸመው ይህ የፓትርያርክነት ሥነ በዓል ለመጪው ትውልድ መታሰቢያ
ይሆን ዘንድ፤ በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የታሪክ ምዕራፍ የያዘ ይሆናል። ይህንኑም ጉዳይ ወደ ፍጻሜ ለማድረስ
በእግዚአብሔር መንፈስ ለተመሩትና እድል ላገኙት ለመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ለቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ
ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።

ልዑል እግዚአብሔር፤ ግርማዊነትዎን በሰላምና በጤንነት ጠብቆ ለብዙ ዘመናት ያኑር። የአብ የወልድ
የመንፈስ ቅዱስ በረከትና ረድኤት በግርማዊነትዎና በግርማዊነት እቴጌ ላይ በልዑል አልጋ ወራሽና በንጉሣዊ
ቤተሰብ ሁሉ ላይ ይደር። የኢትዮጵያን ሕዝብ ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ኢትዮጵያ በነፃነት ትኑር።

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የመለሱት።

የደስታ መግለጫ ቃል።

በአፍሪካ መካከል የክርስቲያን ደሴት ሆና የኖረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፤ የሚገባትን ትልቅነትና


ክብር እንድታገኝ፤ በዘመናችን ደክመንበታል። ድካማችንን ባርኮ ይህንን ፍሬ እንዲያፈራ ላደረገልንና ኢትዮጵያዊ
ፓትርያርክ ለኢትዮጵያ የተገኘበትን ይህን ቀን ለማየት ላበቃን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናችንን እናቀርባለን።

በሐዋርያው በቅዱስ ማርቆስ ልጆች መካከል፤ ዛሬ የተገኘው ይህ መልካም መግባባትና መከባበር፤ ሁለቱ
ቤተ ክርስቲያኖቻችን በመደጋገፍ የሚፈጽሙትን መንፈሳዊ አገልግሎት ከፍ የሚያደርገውና ለብዙ ፍሬ የሚያበቃው
ነው።

ከዚህም በቀር፤ ከሦስት መቶ ሠላሳ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ የኖረው የሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ
ግንኙነት ወደ ፊት ጸንቶ እንዲኖር፤ ላደረግነው ጥረት መተማመኛ የሚሆን ጽኑዕ መሠረት ነው።
ይህ ከፍተኛ ሥራ በዘመናችን ተጀምሮ በዘመናችን እንዲፈጸም እድል ስላገኘን ለእግዚአብሔር
የምናቀርበው ምስጋና ከፍ ያለ ነው።

ለጉዳዩ አፈጻጸም፤ መልካም አስተያየት ለሰጡትና በብርቱ ፈቃድ ለደከሙበት አባታችን ለእስክንድርያ
ፓፓና ለመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ለቅዱስ አባ ቄርሎስ ሳድሳዊ ያለንን ታላቅ አክብሮት ስንገልጽ ደስ ይለናል።

የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጊዜ ለሆነው ለዚህ ማዕርግ
በቅተው አደራ ያለንበትን የፓትርያርክነት ተግባርዎን ሲጀምሩ፤ ሥራዎን ለማከናወን እግዚአብሔር ይርዳዎት።

ኢትዮጵያ፤ ከነፃ መንግሥቱ ጋር ነፃ ቤተ ክርስቲያን ይኖራት ዘንድ የተደረገላት ትግል ዛሬ ፍጹም ድል


አገኘ። ለሁሉ ጊዜ አለው የተባእልው ሰሎሞናዊ ቃል ዘወትር በፍሬ ንባቡ ሲታሰብ ይኖራል፤ ከዚህ ቀደም ጊዜ
ነበረን፤ አሁን ደግሞ በግርማዊነታቸው የተሻሻለና ከፍተኛ ደረጃን ያስከተለና የተከተለ ጊዜ አገኘን።

በዘመናችን እንደ ዕብነ እልአስአል ያሉ መከልዓን ሳይኖሩ፤ ጉዳዩ በስምምነት መፈጸሙ የእውነተኛ
መንፈሳዊ ሥራ መሆኑን ያስረዳል፤ በጢሮሳዊ ተወላጅ በፍሬምናጦስ የተመሠረተው ሢመተ ጵጵስና በታላቁ
ሐዋርያ በአቡነ ባስልዮስ የመጨረሻውን አክሊለ ክህነት በቤተ ክርስቲያናችን ጉልላት ላይ አኖረ።

በለስን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል እንደተባለው ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ አመሠራረት
ጥልቅ በሆነው በክርስቶስ እምነት ላይ ስለሆነ፤ የትዕግሥቷ እርምጃ ሁሉ የተፈጸመው ከክርስቶስ ባስመረኰዛት
በትረ ሃይማኖት ነው ከከሣቴ ብርሃን ሰላማ ጀምሮ ያሳለፈቻቸው ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት በረዥምነታቸው
ከእስክንድርያ ጋር ያላንት መገናኛ ሊያቋርጡት አልቻሉም ፡

በነዚህ ዘመናት መካከል ምንም አንዳንድ መሰናክል ባይታጣም፤ መሰናክሉን በትዕግሥት ለማለፍ
አላስቸገራትም፤ ይልቁንም የገናናው ንጉሠ ነገሥታችን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብሩህ አስተያየት በእግዚአብሔር
ከሃሊነትና በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ተመሥርቶ አስደናቂውን ጽናት ካገኘ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
የተከፈለላት አዲስ እድል ከፍ ያለ መንፈሳዊ አድናቆት የተጐናጸፈ መሆኑ በቀደምትነት ሳይታወስ የሚታለፍ
አይደለም።

በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ከኢትዮጵያ መምህራን፤ ጳጳሳት እንዲሾሙ በታሰበ ጊዜ፤ ብዙ ክርክር መነሣቱ አልቀረም
ነበር፤ የዚህም ክፍል ክርክር መነሻ፤ ይገባናል፤ አይገባንም ማለት ሲሆን፤ ከባድ ወገን ደግሞ ስጡን አንሰጥም
በማለት ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር የነበረው ክርክር ነበር።

ይህን ሁሉ የግርማዊነታቸው ትዕግሥት ድል አደረገና አምስት ጳጳሳት ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ


መምህራን በመሾማቸው አንድ አረፍተ መሠረት ሊመሠረት ተቻለ።

እንዲሁም፤ እግዚአብሔር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን በቀኝ አውሎ ጠላትን ድል እንዲያደርጉ ረዳት ሆኖ
ወደ ዙፋናቸው ከተመለሱ በኋላ በ፲፱፻፵ ዓ.ም እንደ ገና ደግሞ በፊተኞቹ እግር አምስት ጳጳሳት ተሾመው ፫ ዓመት
ያህል ከቆዩ በኋላ፤ በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም እድለኛው ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተብለው በማዕርግ ላይ
ማዕርግ ተጨመረላቸው፤ በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም ሰኔ ፳፩ ቀን ዛሬ ደግሞ ሙሉ መብትን በማግኘት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ ሁነው በእስክንድርያው ፓፓና ፓትርያርክ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ
ተቀብለው በመሾማቸው የተገኘው የመጨረሻው መንፈሳዊ ክብር የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑ የማይገነዘብ
አይገኝም።

ይልቁንም የሚያስደንቀውና ከታሪኮች ሁሉ የበለጠ ታሪክ እንዳለው የሚገመተው፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን የሹመቱ ሥነ ሥርዓት መፈጸሙ ነው።
ይህ ታሪክ፤ ታላቅ አድናቆትን የተጐናጸፈ በመሆኑ፤ የግርማዊነታቸው መንበረ መንግሥት ለሆነችው
ለውዲቱ ሀገራችን ለኢትዮጵያና ለእኛ ለሕዝቦቻቸው ምን ያህል ደስታና ኵራት መሆኑን የያንዳንዳችን ስሜት
ያመዛዝነዋል።

የግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት በሙሉ የታሪክና የተአምር ዘመን እንደ ሆነ ከዚህ የበለጠ ሌላ ማስረጃ
አይኖርም፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ማናቸውም ነገር ከመደረጉ ወይም ከመቅረቱ በፊት ጉዳዩን አስታመው በጸሎት
ወደ እግዚአብሔር አመልክተው፤ በሃይማኖት ስለሚፈጽሙት፤ የመጨረሻው ውጤት አጥጋቢ ፍሬ እያስገኘ ደስ
ከማሰኘት የቀረበት ጊዜ የለም።

ዛሬ ለመላው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፤ በጣም ከፍ ያለ ታላቅ ደስታ የተገኘበትና ታሪካዊ ሥራ


የተፈጸመበት ቀን ስለሆነ፤ ይህንኑ በዛሬዪቱ ቀን የተፈጸመውን ታሪካዊ እድልና ድል ለመቀበል የተዘጋጀን እንሁን።
ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በካይሮ የተደረገላቸውን ከፍ ያለ የክብር አቀባበልና በአገሩ ውስጥ የተደረጉትን ንግግሮች
በሁለት አገሮች መካከል ከጥንት ጀምሮ ለኖረው ግንኙነት የጠበቀ አዲስ መሠረት እንደሰጠው ከካይሮ የሚደርሱት
ወሬዎች፤ እንደዚሁም ይህ ጕብኝት በዓለም ሕዝቦች አስተያየት ዘንድ የፈጠረው ከፍ ያለ ስሜት ያስረዳል።

እነዚህ ሁለቱ አገሮች፤ ለወደፊት እድገታቸውና ለጋራ ጥቅማቸው አብረው ሊፈጽሟቸው ካሰቡዋቸው
ታላላቅ ተግባሮች ጋር ለቀረውም ለአፍሪካ ሕዝብ ድኅንነትና ሰላም የሚሠሩዋቸው ታላላቅ ሥራውዎች
ስለሚጠብቋቸው፤ ይህ ጕብኝት ከፍ ያለ ፍሬ ሰጥቷል፤ በዚህ ጉብኝት ጊዜ ከተገኙት ከፍ ያለ ዋጋ ካላቸው
ጉዳዮች ውስጥ አንደኛውን መሥመር ይዞ የሚገኘው ትልቁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ፩ሺ ፮፻ ዓመት
ጀምሮ በትዕግሥት ትጠባበቀው የነበረው ከልጆቿ መካከል ከፍተኛውን የመንፈሳዊ መሪነት የሚይዝ ፓትሪያርክ
የመሾም ጉዳይ እንደ ነበረ የሚያስተውል የለም።

በዚህ ረገድ የተደከመው ድካምና የተገኘው ፍሬ ሲመዛዘን፤ ባለፈው ጊዜ ለተደረገው ድካም ተገቢውን
ዋጋ የሚሰጥና ለወደፊቱ የኢትዮጵያን ትውልድ የሚያኰራ ታላቅ የሆነ ታሪካዊ ሥራ ተፈጽሟል።

ይህን የምሥራችና ታላቅ መንፈሳዊ ድል ለማግኘት የበቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ደስ እያለው ለዚህ
ያደረሱትን ታላቁን ንጉሠ ነገሥቱን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዘለዓለም ያኑርልን በማለት ጸሎቱን ባለማቋረጥ
በአንድነት ፍጹም በሆነው የኅብረት መንፈስ በዚያው በቦታው ላይ ተገኝቶ በሕሊናው የበዓሉ ተካፋይ ሆኖ
እንደሚውል የሚታመን ነው።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክነት ማዕርግ የኢትዮጵያ ንጉሠ
ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት በመንበረ ማርቆስ ተቀብለው አዲስ አበባ በገቡበት ቀን
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያደረገችው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት።

(ፕሮግራም)።
ሀ. የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል

ለ. የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል

ሐ. የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ካህናት ከየአንዳንዳቸው ፳፬ ፳፬ መዘምራን ድርብ ለብሰው ልዑካኑ
ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተው እንዲሁም

፩. የቀራንዮ መድኃኔ ዓለም

፪. የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ

፫. የመካነ ሰማዕት ቂርቆስ


፬. የደብረ ገሊላ አማኑኤል

፭. የማኅደረ ስብሓት ልደታ

፮. የወጨጫ ማርያም

፯. የጌቴሴማኒ ማርያም

፰. የረጴ መድኃኔ ዓለም

የአቃቄ ገብረ ክርስቶስ ካህናት የማዕርግ ልብሳቸውን፤ መዘምራኑም ፀዓዳ ልብስ፤ ልዑካኑ በሙሉ ልብሰ
ልዑካኑ በሙሉ ለብሰ ተክህኖ ለብሰው አዕጹቀ በቀልት «ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ» የሚለውን
ስብሓተ እግዚአብሔር በከበሮና በጸናጽል እየዘመሩ ተቀበሉ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስም፤ ቀደም ብለው ለዚህ መልዕክት ወደ እስክንድርያ ሔደው የነበሩትን
ልዑል ደጃዝማች አሥራተ ካሣን፤ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን፤ ክብር ብላታ መርስዔ ኅዘን ወልደ ቂርቆስን፤ የክብር
ተከታዮቻቸውን፤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን አስከትለው ከአኤሮፕላኑ
ደረጃ ላይ ብቅ ብለው፤ ለተሰበሰበው ሕዝብ በቅዱስ መስቀላቸው ቡራኬ አደረጉ፤ ከአኤሮፕላኑ እንደወረዱ፤
ግርማዊት እቴጌ መነን ልዑል አልጋ ወራሽ ወደ አኤሮፕላኑ አጠገብ ሔደው ብፁዕ ፓትርያርክን ተቀበሉ።

ከዚህ በኋላ፤ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ ክብር፤ በቀዳማዊ ኃይለ
ሥላሴ አኤሮፕላን ጣቢያ የተሰለፈው የጦር ሠራዊት የክብር ዘብ ሰላምታ አቀረበ፤ ብፅዕ አባታችን ለሰልፉ
መመልከቻ ወደ ተዘጋጀላቸው ከፍተኛ ሥፍራ ከልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ሒደው እንደቆሙ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ
መዝሙር በሙዚቀኞች ተዘመረ፤ ቀጥሎም ብፁዕ ፓትርያርኩ ጸሎት በማድረግ የክብር ዘቡን ከባረኩ በኋላ፤
ለመቀበያ ወደተዘጋጀው ድንኳን ገብተው መሳፍንቱንና መኳንንቱን ተቀበሉ።

በዚህም ጊዜ፤ ግርማዊት እቴጌ መነን የክብር ተከታዮቻቸውን አስከትለው ወደ ቤተ መንግሥት ሔዱ፤
ብፁዕ አባታችን መሳፍንቱንና መኳንንቱን ተቀብለው መስቀል ካሣለሙ በኋላ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት
አልጋ ወራሽ ከልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ጋር በግልጽ አውቶሞቢል ሆነው በፖሊስ ሞተር ብስክሊተኞች
ታጅበው፤ በፊልድ ማርሻል እስመት መንገድ፤ በቸርቸል ጎዳና፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና በኪንግ ጆርጅ
መንገድ፤ በአስፋ ወሰን መንገድ አድርገው በየመንገዱ የተሰለፉት ተማሪዎች የየሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት
ባልደረቦችና የከተማው ሕዝብ በደስታ የሚያቀርብላቸውን አቀባበል እየተመለከቱ ወደ ገነተ ልዑል መንግሥት
አመሩ፤ ከዚያም የተሠለፈውን የክብር ዘብ ሰላምታ ከተቀበሉ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር በሙዚቀኞች
ተዘመረና፤ ብፁዕ አባታችን የክብር ዘቡን ባረኩ፤ በቤተ መንግሥቱም ዐውደ መርህብ የተሰበሰቡት

የአዲስ ዓለም ማርያም፤

የእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ማርያም፤

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ፤

የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤

የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል፤

የታዕካ ነገሥት በኣታ፤

የደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም፤

የደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል፤


የመናገሻ ቅዱስ ማርቆስ፤

የገነተ ኢየሱስ ካህናትና አለቆቻቸው፤ የማዕርግ ልብሳቸውን ልዑካኑ በሙሉ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው
ከላይኛው ቤተ መንግሥት በየካቲት ፲፪ ቀን አደባባይ ከሚገኘው በር አንሥቶ እስከ ከገነተ ልዑል ቤተ
መንግሥት፤ ከዚያም በአደባባዩ ዙሪያ ተሰልፈው በከበሮ በጸናጽል «ተቀደሲ ወንሥኢ ኃይለ ኦ ቤተ እግዚአብሔር
ኢትዮጵያ ሀገረ ቅዱስ ባስልዮስ እስመ ናሁ በጽሐ እስክንድርያ ንጉሥኪ ኃይለ ሥላሴ ዘያበርህ ለኪ። እያሉና
እንዲሁም እምርት ዕለት ዕለት በዓልነ ነያ፤ ኃይለ ሥላሴ አብርሃም ዘተመነያ እያሉ በማሸብሸብ ደስታቸውን
ገልጸዋል።

በዚህም ጊዜ፤ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሲገቡ፤ ልብሰ
ተክህኖ ካባ ላንቃ የለበሱና በራሳቸው የወርቅ አክሊል እይድፉ ፳፬ ካህናት ከነዚሁ ውስጥ ሰባት ካህናት መብራት
ይዘው ወደ ማረፊያ ሳሎን አጅበዋቸው ገቡ። ብፁዕ አባታችን ጥቂት ደቂቃዎች ያህል በማረፊያ ሳሎን ቆይተው
ብፁዓን ጳጳሳት ታጅበው ግርማዊት እቴጌ ወደሚገኝቡበት ዙፋን አዳራሽ ከገቡ በኋላ በግርማዊት እቴጌ ዙፋን
ፊት፤

ያሰሙት ቃለ በረከት።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለፓርትያርካዊ እምንበር እንድትበቃና በዚህ ማዕርግ እንድትከበር ላደረገ፤


እንዲሁም ይህ ታላቅ ሥራ ርቱዐ ሃይማኖት በሆኑት ንጉሠ ነገሥታችን በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን
እንዲፈጸም ለፈቀደና ለባረከ ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው።

ግርማዊት እቴጌ ሆይ።

በእግዚአብሔር ቸርነት፤ የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ድካምና ትጋት ያዘጋጀው ይህ በዓል በቤተ ክርስቲያናችን
ታሪክ፤ ከፍተኛውን ሥፍራ ይዞ የሚገኝና መታሰቢያነቱ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፤ ከጌታችንና ከመድኅኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በ፫፻፴ኛው


ዓመት በቅዱሳን ነገሥታቶችዋ በአብርሀና አጽብሐ መሪነትና በመምህርዋ በፍሬ ምናጦስ ሳበኪነት ተመሠረተች።
ዛሬ ደግሞ ከሺ፮፻፳፩ ዓመት በኋላ፤ በትጉሁና በእድለኛው ንጉሠ ነገሥትዋ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሪነት
ለፓትርያርካዊ መንበር በቃች። እስከ ዛሬ የነበሩትም ነገሥታቶችዋ፤ (እግዚአብሔር ሁሉንም በመካነ ዕረፍት
በመንግሥተ ሰማያት ይቀበላቸውና ወደዚህ ዓላማ ለመድረስ ደክመዋል።

ድካማቸውም ማዕርገ ጵጵስና ለኢትዮጵያዊ እንዲሆን እስከመመኘት ድረስ ነበር። ይሁን እንጂ ከምኞት
በላይ የሆነው ይህን አሁን የተገኘውን የፓትርያርክነት ማዕርግ በሰላማዊ ትግልና በመንፈሳዊ ስምምነት በኢትዮጵያ
ለመመሥረት እድሉ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብቻ ሆነ። እንዲሁም የእኔ ደካማ ሰውነት ለዚህ ከፍተኛ ማዕርግ
መሸጋገሪያ ሆኖ እንዲያገለግል የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ሆነ።

በዚህ ታሪካዊ ቀንና ሰዓት፤ ከታላቁ ጻድቅ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክና ሥራ ጥቂቱን ሳልጠቅስና
ሳልናገር አላልፍም። በሀገረ ጽላልሽ (እቲሳ የተወለዱት አባታችን ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ በስብከታቸው፤
በትምህርታቸው በጸሎታቸው በትሩፋታቸው ሐዲስ ሐዋርያ ዘኢትዮጵያ ተብለውበታል፤ ከዚህም በላይ በችግር
ምክንያት በእስክንድርያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው መገናኛው መንገድ ተቋርጦ ነገሥታቱ እንደተለመደው ጳጳስን
ለማስመጣት ባልቻሉበት በዚያ ጊዜ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ፈቃድ ለጵጵስና ተመርጠው
በጳጳስነት ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል። ለጵጵስናውም ማዕርግ አረቦን የተውልን ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
መሆናቸው የማይጠረጠር ነው።
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ የታሪክን መሥመር መከታተልና ሥራን በሥራ ላይ ማዋል
የተፈጥሮ ስጦታቸው ስለሆነ፤ ይህ የፓትርትያርክነት ማዕርግ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር ጋር እንዲጣመርና
የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወራሽ ዕጨጌ እንዲሆን በማድረግ በመልካም መሠረት ላይ መስርተውታል።

ይልቁንም፤ እግዚአብሔር ቸር ፈቃዱ ሆኖ፤ ይሆናል ተብሎ ባልታሰበበትና ባልተጠረጠረበት ሰዓት


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ከፍ ያለውን የፓትርያርክነት መንፈሳዊ ሥልጣን በምትጐናጸፍበት ሰዓት ግርማዊ
ንጉሠ ነገሥት በዚሁ በዓል ቀን ሥፍራው ላይ መገኘታቸው፤ ዕፅፍ፤ ድርብ ታስታ ከመሆኑ በላይ፤ አንድ የታሪክ
ዐምድ ይዞ የሚኖር ነው።

ይህንንም ሁሉ በትድግናው ያከናወነው የገዢዎች ገዥ የንጉሦች ንጉሥ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን።

እግዚአብሔር ለዓለሙ ሁሉ ሰላምን ይስጥ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅርንና አንድነት፤ በሁሉ ነገር
ብልጽግናንና ምቾትን አብዝቶ ይስጥ።

እግዚአብሔር፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥታችንን እንደ ዓይን ብለኔ ይጠብቅልን። ከሔዱበትም አገር በሰላም
መልሶ በመካከላችን ያስገኝልን።

እግዚአብሔር፤ ንጉሠ ነገሥታችንንና ግርማዊት እትጌን ልዑል አልጋ ወራሽንና ንጉሣዊ ቤተ ሰብን ሁሉ
ለብዙ ወራት፤ ለረጅም ዘመናት በሕይወት ጠብቆ ያኑርልን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይባርክ ይቀድስ። ኢትዮጵያ
ለዘለዓለም በነፃነት ትኑር።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ንግግር ሲፈጸም፤ ብፁዓን ጳጳሳት፤ ልዑላን መሳፍንት፤ ክቡራት
ሚኒስትሮችና መኳንንቶች ባሉበት በዙፋን አዳራሽ ስለ ፓትርያርኩ ክብር የሻምፓኝ ግብዣ ተደረገ።

በግብዣውም መጨረሻ፤ ብፁዕ ፓትርያርኩ ቡራኬ አድርገው፤ በመጡበት አኳኋን ታጅበው ወደ መንበረ
ፓትርያርኩ ሔዱ።

በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢም፤

የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል።

የደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት

የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም

የገነት ኪዳነ ምሕረት

የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት

የመናገሻ ማርያም

የመካነ ሕይወት ገብረ መንፈስ ቅዱስ።

የናዝሬት ዮሴፍ

የመንበረ ንግሥት ቍስቋም

የገነት መድኃኔ ዓለም

የፉሪ ቅድስት ሐና

የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት


የፋሌ መድኃኔ ዓለም።

የመንበረ ሥላሴ አድባራት ካህናትና ሹማምንት የማዕርግ ልብሳቸውን መዘምራኑ ፀዓዳ ልብስ፤ ካህናቱ
(ልዑካኑ) ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በመንበረ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርክ ግቢ በመገኘት በስተ ምሥራቅ ካለው
በር እስከ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በሚወስደው መንገድ ግራና ቀኝ፤ የቤተ ክህነት ሠራተኞችና የቅዱስ ጳውሎስ፤
የቅድስት ሥላሴ፤ የታዕካ ነገሥት በአታ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርት ከፓትርያርኩ ግቢ ፩ኛ በር ጀምሮ እስከ
ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በር ድረስ፤ ፲፪ ልዑካን ሙካሽ ካባ ላንቃ ለብሰው በየራሳቸው አክሊል ደፍተው መብራት
ይዘው፤ በአዳራሹ በር ግራና ቀኝ ተሰልፈው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርኩ ከዋናው በር ሲደርሱ መዘምራን
ካህናቱ ንሴብሖ እያሉ፤ ደቀ መዛሙርቱ ለበዓሉ የተዘጋጀውን መዝሙር እየዘመሩ ተቀበሏቸው።

መንበረ ፓትርያርኩ ደስ በሚያሰኝ ሥነ ሥርዓት አምሮ ከመዘጋጀቱ በላይ፤ ከ፩ኛው መግቢያ በር ጀምሮ
«ንዑ ንትፈሣሕ በእግዚአብሔር ወንየብብ ለአምላክነ ወመድኃኒነ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ
ጼዴቅ። ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልው አኅው ኅቡረ የሚሉ ጥቅሶች አልፎ አልፎ በቅስት ላይ ተጽፈው
ነበር።

ብፁዕ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለአቀባበሉ በተሰናዳው በስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንደተገኙ የሻምፓኝ ግብዣ
ተደረገ።

በሻምፓኙም ግብዣ ሰዓት፤ የመናገሻ ማርቆስ አለቃ ወልደ ማርያም ሀብቴ ግጥምና መወድስ ሲያበረክቱ፤
እንዲሁ ለበዓሉ የተዘጋጀው ኮከበ ክብር መንፈሳዊ የተባለው መጽሕፈ ታደለ። ከዚህ በኋላ፤ ለ፱ ሰዓት ሩብ ጉዳይ
ሲሆን፤ የግብዣው ፍጻሜ ሆኖ በሥነ በዓሉ ላይ የነበሩት ሁሉ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እየተሰናበቱ ከሔዱ
በኋላ፤ ብፁዐ አባታችን በመንበረ ፓትርያርክ ወደ ምትገኘው ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሒደው
ወደዚህ ላደረሳቸው አምላክ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመለሱ።

ኢትዮጵያ «እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ሃይማኖት ቢኖራችሁ፤ ይህንን ተራራ
ከዚህ ወደዚያ ተነሣ ብትሉት ይነሣል» የተባለውን አምላካዊ ቃል አክብራ በመጠበቋ፤ በየጊዜው ማሸነፍ እንጂ
መሸነፍ፤ ማግኘት እንጂ ማጣት የሌለባት ቅድስት ሀገር ናት።

ይን ቀን ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ደስታ ሰጠ፤ ይህ ቀን ሃይማኖታችን ያስገኘው ታላቅ ጸጋ ነው፤ ይህ


ቀን እምነታችን ደስ የሚያሰኝ ክብርን የተቀዳጀበት ቀን ነው፤ የዚህ ቀን መታሰቢያነት ለታሪክ ሙሽራው ነው፤
ስለዚህ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት የሚያከብሩት ከልብ ነው።

ከመምህርነት ዕጨጌነት፤ ከዕጨጌነት ጳጳስነት፤ ከጳጳስነት ሊቀ ጳጳስነት፤ ከሊቀ ጳጳስነትም፤


ፓትርያርክነትን ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንችን ለመቀበል በእናታቸው ከርሠ ማሕጸን በመንፈስ ቅዱስ
የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፤ ይህን ከባድ መንፈሳዊ ኃላፊነት ለመውሰድ፤
መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው እድላቸው ታላቅ ነው።

ጋሻና ጦራችን ለሆነው ሃይማኖታችን የመጨረሻ ክብር ያገኘንበት ሰኔ ፳፩ ቀን ነው፤ ሰኔ ፳፩ ቀን ወደ


ፊት በኢትዮጵያ ታላላቅ የሕዝብ በዓላት ተብለው ከሚጠሩት ቀኖች አንዱ ሆኖ እንደሚከበር የሚታመን ነው፤
በሰኔ ፳፩ ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሢመተ ፓትርያርክነትን ማዕርግ ያገኘበት እድለኛ
ቀን በመሆኑ ለታሪካችን ቅርሱ ነው።

በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለአንድ ታላቅና ዝነኛ መንግሥት የእምነት መሠረት ለሆነው ለኦርቶዶክስ
ሃይማኖት የመጨረሻ ሥልጣን ማግኘት የምሥራች ምሥራች ነው።

ይልቁንም፤ የብዙ ዓመት ታሪል ለአለው ለአንድ ነፃ መንግሥትና ለአንድ ነፃ ሕዝብ ሙሉ ሥልጣን ያለው
የሃይማኖት መሪ ማግኘት ይበልጥ የሚያስደስተው ታሪካዊ ነው ታሪክ ዝናውን እያሽሞነሞነ የሚያሞግሠው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የመሰለ ዝነኛ ታሪክ በታሪኩ ላይ ሲታከልለት፤ የታሪክ ገጾች ምልአትንና ስፋትን
ለማግኘት ጥሩ እድል ገጥሟቸዋል።

ቀጥተኛውንና እውነተኛውንም መንገድ ስንከተል ኢትዮጵያ በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ታሪኳ እጅግ


የሚያስደንቅ እርምጃ ለማድረግ የቻለችው በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በቀዳማዊ፤ ኃይለ ሥላሴ ጥረትና ድካም
በመሆኑ፤ በዘመነ መንግሥታቸው ይህና ይህን የመሳሰለው ሥራ ሲፈጸም ለማየት የቻሉት ጃንሆይ የታደሉ ናቸው።

በሥጋዊው ነፃነታችን ድልን በድል ላይ እያደራረቡ ነፃነታችንን ይዘውልን የመጡት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት
ሲሆኑ፤ በመንፈሳዊውም ነፃነታችን ቀን ብፁዕ አባታችን የመጨረሻውን ሥልጣን ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ
ክርስቲያናችን ሲቀበሉ፤ ጃንሆይ በሥነ በዓሉ መገኘት ለሀገራችን እርምጃ ወጣኝነትና ፈጻሚነት ከልዑል
እግዚአብሔር የታዘዙት ግርማዊነታቸው መሆናቸውን ያስረዳል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ብርቱ
ትግልና ድካም ይህን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የደረሳትን ታላቅ ክብር ለመቀበልና፤ የዚህንም
ክብር አደራ ጠባቂነት ለመውረስ በመቻላቸው እድላቸው ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ተአምራታዊ ሥራ ጋር የተያያዘ
ሆኖ ይገኛል።

በተአምራት ተመልቶ የሚገኘው የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዘመነ መንግሥት በፈቃደ እግዚአብሔር ብዙ ከፍ
ያለ ሥራ ለማከናወን ችሏል። የተደራረበ ደስታ ካስገኙትም ታሪካዊ ሥራዎች መካከል የታላቁ ሐዋርያ የቅዱስ
ማርቆስ መንበር ባለበት በእስክንድርያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን
መካከል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የቆየው የሃይማኖት ግንኙነታችን መተሳሰባቸውና መቀራረባቸው እንዳለ ሆኖ ይህን
ታላቅ ሥልጣን ለወገን ማስገኘት ነው።

«ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር» ሲል ዳዊት የተናገረውን ቃልና «ቦ ጊዜ ለኵሉ» በማለት ሰሎሞን የገለጸውን
አሳብ በጥብቅ ለመረመረው አስደናቂና የማይዛባ ውሳኔ ያለው ሆኖ ይገኛል።

የሰው ልጅ ምንም ቢጨነቅ፤ ምንም ቢያስብ፤ ምንም ቢመኝ፤ ምንም አሳቡን በገቢር ለመፈጸም
ቢታገል፤ እግዚአብሔር ይሁን ካላለው አንድም ነገር የሚፈጸም የለም። ይሁን ሲልም ከወሰነው፤ አንድ እንኳ
የማይሆን አይገኝም። ሁሉም በሱ ፈቃድ ይደረጋል። ሁሉም በሱ ከሃሊነት የውሳኔ መልክ ለማግኘት ይችላል።

ኢትዮጵያ እንኳንስን የፓትርያርክነትና እንኳንስ የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትንና የኤጲስ ቆጶስነትም ነገር አስቸግሮ
ይኖር ነበር፡ በሺ፮፻ ዘመናት ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተወላጆችዋ ሳይሆን በሌሎች መንፈሳዊ መብት
ስትተዳደር ምን ዓይነት ጕዳት እንደ ደረሰባትና ከወገኖችዋ መንፈሳዊ አባት ጳጳስ እንዲሆንላት እንዴት ያለ
ነበልባላዊ ስሜት እንደ ነበረባት የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም።

ከቶውንም እንግብጋቦትና ጸጸት የሆነባት «ወሰብኦ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እማእምራኒሆሙ» ተብሎ


በፍትሐ ነገሥት ጣልቃ ገብ ሆኖ በተጻፈው ሰው ሠራሽ ብትብ እንደነበረ ግልጽ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፤ እስከዚህ ድረስ ትዕግሥት ማድረጓ፤ መሠረት እንዳይጠፋ፤ ከመንበረ ማርቆስ
ጋር ያላት ጥንታዊ መገናኛ እንዳይቋረጥና፤ በትሕትና ረገድ ይገባኛል ከባለት ይገባታል በማለት አመዛዛኝ
እንዲያስብበት ስትል ነው እንጂ፤ እንደ ሌሎቹ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ራስዋን በራስዋ በእግዚአብሔር ፈቃድ
ለመሾም ባላቃታትም ነበር።

ይህን ሁሉ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ጊዜውን ጠብቃ ጊዜ ባለ እድሉንና ለዚህ ለተባለው መንፈሳዊ
አመሠራረት ተገቢውን ፈለገ። ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመብት
እንደተከለከለች እንዳትቀር፤ እከስክንድርያም ጋራ ያላት ወዳጅነት እንዳለ እንዲኖር፤ በትዕግሥት፤ በፍቅር ነገሩን
በዘዴ መልክ መሥራት ባደረጉት መንፈሳዊ ትግል በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም የመጀመሪያው የጵጵስና ማዕርግ በአምስት
ኢትዮጵያውያን የመምህራን ሊመሠረት ተቻለ።
ይህም የሆነበት ምክንያት፤ ከላይ እንደተገለጸው፤ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር የተባለውና ቦ ጊዜ ለኵሉ
ተብሎ የተነገረው የአባቱ የዳዊትና የልጁ የሰሎሞን ቃል የነገሩ ዓላማ መግለጫ ስለደረሰ ነው።

ከዚህስ በኋላ፤ የደረጃው ጥርጊያ ራሱ እየፈቀደ፤ ከጳጳስነት ወደ ሊቀ ጳጳስነት ማዕርግ እየተራመደ


በመሔዱ ምክንያት፤ የሊቀ ጳጳስነቱ እድገት ደግሞ ወደ ርእሰ ሊቃነ ጵጵስነትና ወደ ፓትርያርክነት ከፍተኛ ስያሜ
በመድረሱ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በንጉሠ ነገሥቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በፓትርያርኳ በብፁዕ ወቅዱስ
አቡነ ባስልዮስ ያገኘቻቸው የብዙ ጊዜ እድሎች የሚገኙት ታሪካዊ በሆነ በአዲስ ገጽና በአዲስ ምዕራፍ ላይ
እንደሆነ ሁላችንም የምንመለከተው በታላቅ ደስታ ነው።

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተደረገ

መንፈሳዊ በዓል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ የፓትርያርክነት ዘውዳቸውን
አድርገው፤ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው ለሕዝብ የሚታዩበትና ዋናው የሢመተ ፓትርያርክነት በዓል የሚከበርበት
ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ስለ ነበር፤ ሐምሌ ፬ ቀን በተደረገው
የአቀባበል ሥነ በዓል ላይ የተገኙት የሠላሳ ስምንት አድባራት ካህናት በየቤተ ክርስቲያናቸው የተለመደውን ስብሓተ
እግዚአብሔር፤ ዝማሬና ማኅሌትን ሲያደርሱ አድረው ከሌሊቱ በ፲ ሰዓት ተኩል ልዑካኑ ልብሰ ተክህኖ አለቆቹ
የማዕርግ ልብሳቸውን፤ መዘምራኑ ድብርና ነጭ ልብስ ለብሰው አዕጹቀ በቀልትን ይዘው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት
ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በየተወሰነላቸው ሥፍራ ሁነው የብፁዕ ፓትርያርኩን መምጣት ይጠባበቁ ነበር።

እንዲሁም ከጧቱ ፲፪ ሰዓት ተኩል ጀምሮ የክብር ዘበኛ ወታደሮች ከመግቢያው በር ጀምሮ በቤተ
ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ዙርያ በብረት ተሰልፈው ነበር። ብፁዕ ፓትርያርክ ከንጋቱ ፩ ሰዓት ሲሆን፤ በፁዓን ጳጳሳትን
አስከትለው፤ በሞተር ቢስክሌተኞችም ታጅበው፤ ወደ መንበረ ፀባዖት፤ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ፤
በዚያ የተሰለፉት የክብር ዘበኛ ወታደሮች በብረት ሰላምታ አቀረቡ። ከዚያም ፩ ሰዓት ከ፭ ደቂቃ ሲሆን ጸሎተ
ቅዳሴው ተጀመረ።

በጸሎተ ቅዳሴውም ላይ፤ ግርማዊት እቴጌ መነን፤ የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ
ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰንን፤ ልዕልት ተናኘ ወርቅን ልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅን፤ ልዑለ ሣህለ
ሥላሴን፤ ልዕልት ማኅጸንተንና ሌሎቹንም የክብር ተከታዮቻቸውን አስከትለው ተገኝተው ነበር።

ልዑላን መሳፍንት፤ ክቡራን ሚኒስትሮችና መኳንንቶች፤ ታላላቅ የጦር አለቆችና ክቡራት ሴት ወይዛዝርም
በጸሎተ ቅዳሴው ተገኝተው ነበር። ለ፫ ሰዓት ፲ ደቂቃ ጉዳይ ሲሆን፤ የጸሎተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ተፈጽሞ፤
ግርማዊት እቴጌ መነን በመጡበት አኳኋን ወደ ቤተ መንግሥታቸው ተመለሱ።

ከዚያም በኋላ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በቤተ መቅድሱ
ዓውደ ምሕረት በተሰናዳው መንበረ ፓትርያርክ ሲቀመጡ፤ ለበዓሉ የተሰናዳው፤ ሣህለ ወርትዕ ተራከባ፤ ጽድቅ
ወሰላም ተሰዐማ፤ ርትዕሰ እምድር ሠረፀት የሚለው መዝሙር ከተሰበከ በኋላ፤ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ወፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ወንጌሉን አሰሙ።

ቀጥሎም፤ መዘምራኑ አንገርጋሪው መርተው፤ መኑ አምጽአ ለጽድቅ በተፋቅሮ ንንበር በሰላም ምስለ
እስክንድርያ የሚለውን እስመ ለዓለምና ግሥ በማድረግ አቅርበው በመጨረሻው ለኰኵሐ ሃይማኖት ርእሰ ሊቃነ
ጳጳሳት ባስልዮስ ርእሰ ትስምዮ ኢትዮጵያ» በሚለው ግሥ እያሸበሸቡ ዘመሩ።

በመጨረሻም፤ ብፁዕ አባታችን ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተው፤ ብፁዓን ጳጳሳትን፤ ክቡራን ሚኒስትሮችንና
መኳንንቶች አስከትለው፤ በሞተር ቢስኪሊተኞች ታጅበው፤ በግልጽ አውቶሞቢል ሆነው ወደ መንበረ ፓትርያርክ
በሔዱ፤ ጊዜ ለ፬ ሰዓት ፳፭ ደቂቃ ጕዳይ ሲሆን ሠርሆተ ሕዝብ ሆነ።
/
ከኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ ቤት።

የተሰጠ መግለጫ።

ከብዙ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያና በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና
ለቀረው ዓለም የተሰጠው መንፈሳዊ ነፃነት ለኢትዮጵያም እንዲሰጣት፤ ግራምዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ
ሥላሴ ረጂም ዘመናት የድከሙበት መንፈሳዊ ትግል ወደ መልካም ፍጻሜ ደርሶ ሰኔ ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም
ግርማዊነታቸው ወዳጅ አገሮችን ለመጐብኘት ሔደው በእስክንድርያ በተገኙበት፤ ብፁዕ ወቅዱስ የእስክንድርያ
አቡነ ቄርሎስና የመላው ግብጽ ሊቃነ ጳጳሳት በአሉበት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ
ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ባስልዮስ ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ቅዱስ ማርቆስ የተፈጸመበትንና ይህን ታላቅ የሆነ
መንፈሳዊ ነፃነት የተገኘበትን ታሪካዊ ዕለት ምክንያት በማድረግ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ
አብያተ ክርስቲያናት ሥነ በዓል እንዲደረግ ተወስኗል።

ሥነ በዓሉም የሚፈጸመው በይባቤ፤ በዝማሬና በዑደት ነው።

ቴሌግራም።

ለ……………………………………….

ሐምሌ ፲፪ ቀን እሑድ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁሉ፤ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ
ባስልዮስ የፓትርያርክነት ሥርዓተ ሢመት፤ በመላው በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲከበር ስለተወሰነ፤
በዚሁ ቀን ለበዓሉ የሚገባው ሥርዓተ ጸሎትና አክብሮ በሚገባ እንዲፈጸም ለሁሉም ትእዛዝ እንዲሰጥ
እናስታውቃለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ጠቅላይ ጽ/ቤት

You might also like