You are on page 1of 3

FastMereja.

com - "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን


በሚመጥን መልኩ በዓሉን ማክበር...
facebook.com/fastmereja/posts/pfbid0AtRcx7usZREXCrHxk6xPYWRtPvNurwUBUvjhBrRy2T1GUsqQ9L99SPYmVkuLL2F
Al

"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚመጥን መልኩ በዓሉን ማክበር ያስፈልጋል" ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከታቸው ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

የብፁዕነታቸው ሙሉ መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“ ወኪያነኒ ይእዜ ያድኅነነ በአርኣያሁ በጥምቀት ።” ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ አሁን ያድነናል ። 1ኛ ጴጥ 3፥ 21

በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንና ምእመናት

የሰላም አለቃ ፣ የዘለዓለም አባት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሰላም ጠብቆ
ለ2016 ዓ.ም በዓለ ጥምቀት በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።

የጥምቀት በዓል ነጻነታችን የታወጀበት ፣ የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበት የባርነት ቀንበር የተሰበረበት ፣ የሚናፈቀው
የእግዚአብሔር ድምፅ የተሰማበት ፣ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ፣ ልጅነትን የምንቀበልበት ጸጋ የተመሠረተበት
ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ድምቀት ይከበራል።

ይኸውም በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር እና ታላቁ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ
ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ
ተክለሃይማኖት በተገኙበት በጃን ሜዳ ባሕረ ጥምቀት የሚከበረው በዓል እንደተጠበቀ ሆኖ በጠቅላላ በከተማዋ
ውስጥ ከ78 ያላነሱ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሥፍራዎች ይገኛሉ። በዚህም መሠረት በዓሉ በተቀናጀ መልኩ
ለማስኬድ ሲባል በእያንዳንዱ ክ/ከተማ ላይ ግብረ ኃይል በማደራጀት እና ተጠሪነታቸውንም ለሃገረ ስብከቱ ሥራ
አስኪያጅ በማድረግ በሰፊው ዝግጅት ተደርጓል በየባሕረ ጥምቀቱም በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን
ይሳተፉበታል።

ሀገረ ስብከቱም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያካሄደውን ሰፊ ዝግጅት
አጠናቅቋል።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

ምእመናንና ምእመናት

1/3
ሰላም የጌታ ድንቅ ስጦታ እንደሆነና ደግሞም ማንም እንዳይወስድብን አጽንተን ልንይዘው የሚያስፈልገን የሁሉም
መሠረት ነው ፣ ሰላም ከሌለ በዓላትን ማክበር ይቅርና ወጥቶ መግባት ፣ ሠርቶ መብላት የማይቻልበት ሁኔታ
ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት በተግባር ያየነው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ እና ለሰላም ዘብ በመቆም ቀዳሚ መሆኗ
ይታወቃል።

ከላይ እንደተገለጸው በሰላም አምላክ የተመሰረተን እና የተሰጠን ጸጋ ማስጠበቅ የእያንዳንዱ አማኝ ግዴታ ነው።
እንዲሁም የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ሰላምን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ድርሻ
በእያንዳንዳችን ላይ እንዳለ በመገንዘብ ሐዋርያዊት ፣ ብሔራዊት እና ዓለምአቀፋዊት ለሆነችው የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚመጥን መልኩ በዓሉን ማክበር ያስፈልጋል።

ስለሆነም ይህንን በዓል በምናከብርበት ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ሰላም
በመንከባከብ እና በመተግበር ፍፁም ክርስቲያናዊ በሆነ ሥነ ምግባር እና አካሄድ በዓላችንን ልናከብር ይገባናል።

ይህ በእንዲህ እያለ

1. መንፈሳዊ ሰልፋችን ከነአለባበሳችን የጉዞውን ቅደም ተከተል በጠበቀ መልኩ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማዕከል
ያደረገ እና ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጥ እንዲሆን

2. ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚደረገው ጉዞ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ፤ ከልዕልና
ወደ ትህትና መውረዱን የሚያሳይ መንፈሳዊ እሴት ያለበት እንደሆነ የታወቀ በመሆኑ በጉዞው ላይ የሚደረግ
እያንዳንዱ ክንውን አስተማሪ ሊሆን ይገባል። ሰልፉም ውበትና መስመር እንዲኖረው ይጠበቃል። በመሆኑም
የአምልኮ መርሐግብር እያከናወኑ ዋዛ ፈዛዛ በመከወን የሚደረግ ጉዞ ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ጋር ፈጽሞ
የሚጣረስ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዚህ ረገድ ከካህናት አባቶች የሚሰጡ መመሪያዎችን በመቀበል የበዓሉን
አከባበር በደመቀ መልኩ ማከናወን እንዲቻል እንዲደረግ።

3. ሰዓትን በተመለከተ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ታቦታተ ምሥዋዕ ከመንበረ ክብር ስለሚነሱበት ሰዓት በወጣው
መርሐ ግብር መሠረት ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ዋዜማ ስብሐተ እግዚአብሔር ይቆማል። በማስቀጠል 7 ሰዓት ሲሆን
በመላዋ አዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ለ10 ደቂቃ የደወል ድምፅ ይሰማና መነሻ ሰዓት ይሆናል።

- የጥር 11 የጥምቀት በዓልና የጥር 12 የቃና ዘገሊላ በዓልን በተመለከተም መነሻ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት እንዲሆንና
መድረሻውም ከ 7 - 10 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲሆን እያሳሰብን በዓሉ የትህትና እና የፍቅር እንደመሆኑ መጠን ከእኛ
የሚጠበቁ ክንውኖችን በመፈፀም ለበዓሉ በድምቀት መከበር አስተዋጽኦ ልናደርግ ይገባል።

4. አገልግሎታችን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ መሆን ስለሚገባው አስፈላጊውን ግብዓት ከማቅረብ በቀር
ከአበው ካህናት ውጭ በየትኛውም መልኩ በሌሎች አካላት የሚደረግ ማዕጠንት ተገቢነት የሌለው እና ከቀኖና ቤተ
ክርስቲያን ውጭ በመሆኑ እንዳይፈፀም የሚመለከታቸው አካላትም ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም
በማዕጠንት አገልግሎቱ በካህናት አባቶች በሰፊው እንዲሰጥ ይሁን።

5. በረከተ ጥምቀቱን የማድረስ እና የመርጨት ክንውን የሚፈጸመው በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በካህናት
ብቻ መሆኑ ይታወቃል በዚሁ መሠረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ባለማወቅ ምክንያት ሥርዓቱ እንዳይፈርስ ወጣት
ልጆቻችንም ይህን አውቃችሁ ሥርዓቱን እንድትጠብቁና አገልጋዮች ካህናትም ድርሻችሁን እንድትወጡና ሕዝቡን
እንድታገለግሉ እናሳስባለን ።

2/3
6. ከልክ ያለፉ እና በተደጋጋሚ የተስተዋሉ ከሥርዓት ውጭ በሆነ መልክ ለታቦታቱ ክብር በማይመጥኑ ሥፍራዎች
ላይ እንዲቆሙ የሚደረገው ልምድ እንዲታረምና ሁሉም በሕግና በሥርዓት እንዲመራ።

7. ምእመናን እንደተለመደው ራሳችሁን ከሁከትና አላስፈላጊ ነገሮች በማራቅ በትዕግሥት እና በሆደ ሰፊነት በዓሉን
እንድናከብር እያሳሰብን ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተናበበ መልኩ
እልባት እንዲሰጣቸው ሊደረግ ይገባል።

በመጨረሻም ፦

በዓለ ጥምቀትን ስናከብር በፍፁም ወንድማዊ ፍቅር የተራቡትን በማብላት ፣ የተጠሙትን በማጠጣት ፣ የታረዙትን
በማልበስ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ፤ የመድኃኒታችን የኢየሱስ
ክርስቶስን ትህትና አብነት በማድረግ በመተሳሰብና በመደጋገፍ እንዲሆን እናሳስባለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ አሜን

አባ ሄኖክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

3/3

You might also like