You are on page 1of 2

በትግራይ 28 አባላት የሚኖሩት የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት

ተወሰነ
ethiopianreporter.com/116483

March 5, 2023

ዜናበትግራይ 28 አባላት የሚኖሩት የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ተወሰነ

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሕወሓት ይሰየማል

በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ለሁለት ቀናት የተካሄደው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ
ፓርቲዎችና ሕዝብን ከሚወክሉ ተቋማት የሚውጣጡ 28 አባላትን የሚይዝ ካቢኔ እንዲመሠረት ተወሰነ። ይህ
ውሳኔ ወደ ትግበራ የሚገባው የፌዴራል መንግሥትን ይሁንታ ካገኘ በኋላ ነው ተብሏል።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ሐሙስ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፣
ኮንፈረንሱ በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መክሮ መግባባት ላይ መድረሱ ተገልጿል። 

ዋነኛ የተባሉት አራቱ አጀንዳዎችም፣ በትግራይ የሚቋቋመው ጊዚያዊ አስተዳደር ተልዕኮ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ
የሥልጣን ዘመን፣ የጊዚያዊ አስተዳደሩ መዋቅርና የሥልጣን ክፍፍልን የተመለከቱ መሆናቸው ታውቋል። 

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዓበይት ተልዕኮዎችኧ የትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ
እንዲመልሱ ማድረግና የትግራይ ሕዝብን አንድነት ማጠናከር እንደሚሆን ተገልጿል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመንም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ
ወቅትም በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት ሕዝባዊ ምርጫ
ተካሂዶ ቋሚ መንግሥት እንደሚቋቋም የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ያወጡት መግለጫ ያመለክታል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ
በሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ስለሚኖረው የሥልጣን ክፍፍልም ውሳኔ አሳልፏል። 

በዚህም መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር 28 አባላት እንዲኖሩት የተወሰነ ሲሆን፣ በካቢኔው ውስጥም
የሕወሓት፣ የትግራይ ሠራዊት፣ ሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት እንደሚወከሉበት
ምንጮቹ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ አደረጃጀትን በተመለከተም ኮንፍረንሱ ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን የገለጹት እነዚሁ ምንጮች፣
ጊዜያዊ አስተዳደሩ አንድ ፕሬዚዳንት፣ ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሚሾሙ
አራት የዘርፍ አመራሮች እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር 17 የቢሮ ኃላፊዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ
28 አባላትን የያዘ ካቢኔ እንዲደራጅ መወሰኑን ገልጸዋል።

ከተገለጸው የካቢኔ አባላት ቁጥር ውስጥ 50 በመቶው ከሕወሓት የሚወከሉ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ
ፕሬዚዳንትና የካቢኔው ሰብሳቢ ከሕወሓት እንዲወከል መወሰኑንም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሁለት ፕሬዚዳንቶች እንዲኖሩት መወሰኑን መሠረት በማድረግም ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች
ከትግራይ ሠራዊትና ከሲቪክ ተቋማት እንዲመረጡ መወሰኑን ከምንጮቹ ለመረዳት ተችሏል። 

1/2
ሕወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው፣ የተቀረው 50 በመቶ ደግሞ ለትግራይ
ሠራዊት፣ ለሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ለትግራይ ሲቪክ ተቋማት መደልደሉን ምንጮቹ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ሌሎች የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በድምሩ በ21 በመቶ ውክልና የካቢኔ አባል እንዲሆኑ፣
በተቀረው 29 በመቶ ካቢኔ ወንበር ላይ ደግሞ የትግራይ ሠራዊትና የሲቪክ ተቋማት በእኩል እንዲወከሉ
መወሰኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሕዝባዊ ኮንፍረንስ የተላለፉ ውሳኔዎች ወደ ትግበራ የሚገቡት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣
የፌዴራል መንግሥትን ይሁንታ ሲሰጥ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቹ፣ ይህንን ይሁንታ ለማግኘትም የትግራይ
ተደረዳሪ ቡድን በጥቂት ቀናት ውስጥ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተገናኝቶ እንደሚወያይ አስረድተዋል።

የካቲት 23 ቀን የተጠናቀቀው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ባወጡት የአቋም መግለጫም ይህንኑ


አመላክተዋል።

‹‹በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ ውሳኔ ለሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኢፌዴሪ መንግሥት፣ መላው
የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የዓለም ማኅበረሰብ ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፤›› ሲል የአቋም
መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ 401 ተሳታፊዎች የተጋበዙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 351 የሚሆኑት በድምፅ እንዲሳተፉ
የተጋበዙ ናቸው። በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ የተወከሉት ተሳታፊዎች ስብጥር ሲታይ ደግሞ፣ ሕወሓት 30 በመቶ፣
25 በመቶ የትግራይ ሠራዊት 25 በመቶ፣ የትግራይ ሲቪል ተቋማት 30 በመቶና ሌሎች የትግራይ ፖለቲካ
ፓርቲዎች 15 በመቶ ነው። ይሁን እንጂ 15 በመቶ ውክልና ከተሰጣቸው የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ
ሦስቱ ሒደቱን በመቃወም በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ አለመሳተፋቸው ታውቋል፡፡

የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ለመቋቋም የተካሄደውን ይህንን ሕዝባዊ ኮንፈረንስ የመሩት አባላት አምስት ሲሆኑ፣
እነዚህም የሕወሓቱ ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ጄነራል ታደሰ ወረድ፣ ዘውዱ ኪሮስ፣ ወ/ሮ ሊያ
ካሳና ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ናቸው።

ስለጊዜያዊ አስተዳደሩ አደረጃጀትና አጠቃላይ ሒደትን በተመለከተ ከሕወሓት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና
የፌዴራል መንግሥትን አስተያየት ለማከል ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ይመዝገቡ

2/2

You might also like