You are on page 1of 40

እናት ፓርቲ

መተዳደሪያ ደንብ
እንደ ተሻሻለ

2015 ዓ.ም.
ማውጫ
ክፍል አንድ መግቢያ ........................................................................................................................................ 3

ክፍል ሁለት ጠቅላላ ድንጋጌዎች ........................................................................................................................ 5

አንቀጽ አንድ፡-አጭር ርዕስ ........................................................................................................................... 5

አንቀጽ ኹለት፡- የፓርቲው ስያሜ፣ ርዕይ፣ ተልእኮና ዓላማ .............................................................................. 5

አንቀጽ ሦስት፡- ትርጉም ............................................................................................................................... 6

አንቀጽ አራት የፓርቲው አርማ (ሎጎ) ትርጉም ................................................................................................ 7

አንቀጽ አምስት፡- የፓርቲው የሥራ ቋንቋ ...................................................................................................... 8

አንቀጽ ስድስት፡- የፓርቲው ጽ/ቤት .............................................................................................................. 8

አንቀጽ ሰባት፡- የፆታ አገላለጽ ........................................................................................................................ 8

ክፍል ሦስት የፓርቲ አባልነት ....................................................................................................................... 8

አንቀጽ ስምንት፡- የፓርቲ አባልነት................................................................................................................. 8

አንቀጽ ዘጠኝ፡- የአባልነት መብት ................................................................................................................ 10

አንቀጽ አስር፡- የአባልነት ግዴታ .................................................................................................................. 10

አንቀጽ አስራ አንድ፡- የአባልነት መዋጮ እና የገቢ ምንጭ ............................................................................. 10

አንቀጽ አስራ ሁለት፡- አባልነት የሚቋረጥበት ሁኔታዎች ................................................................................ 11

ክፍል አራት የፓርቲው አወቃቀር እና አደረጃጀት ............................................................................................... 13

አንቀጽ አስራ ሦስት ፡- የፓርቲው አወቃቀር እና አመራር አባላት .................................................................... 13

አንቀጽ አስራ አራት፡- የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አመሠራረት፣ ሥልጣንና ተግባር ............................................. 14

አንቀጽ አሥራ አምስት፡- የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ................................................................................ 16

አንቀጽ አስራ ስድስት፡- የፓርቲው የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ...................................................................... 16

አንቀጽ አስራ ሰባት፡- የፓርቲው የሒሳብና ክዋኔ ቁጥጥር ኮሚሽን ................................................................ 17

አንቀጽ አሥራ ስምንት፡- የፓርቲው አርትኦት /ኤዲቶሪያል/ ቦርድ ኃላፊ ......................................................... 18

አንቀጽ አስራ ዘጠኝ፡- የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት አመሠራረት፣ ሥልጣንና ተግባር ..................................... 18

አንቀጽ ሃያ፡- የፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ................................................................................. 21

አንቀጽ ሃያ አንድ፡- የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመሠራረት፤ ተግባርና ኃላፊነት ..................... 21

አንቀጽ ሀያ ኹለት፡- የፓርቲው ፕሬዝዳንት .................................................................................................. 24

አንቀጽ ሀያ ሦስት፡- የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ..................................................................................... 25

አንቀጽ ሀያ አራት፡- የፓርቲው ጠቅላይ ጸሐፊ............................................................................................... 25

አንቀጽ ሀያ አምስት፡- የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ....................................................................... 26


አንቀጽ ሀያ ስድስት፡- የፓርቲው የአባላት ምልመላና አደረጃጀት ክፍል ኃላፊ .................................................. 27

አንቀጽ ሀያ ሰባትት፡- የፓርቲው የፖለቲካ ትንተና ክፍል ኃላፊ፡-..................................................................... 28

አንቀጽ ሀያ ስምንት ፡- የውጭ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ..................................................................................... 29

አንቀጽ ሀያ ዘጠኝ ፡- የፓርቲው የሴቶችና ወጣቶች ክፍል ኃላፊ ...................................................................... 29

አንቀጽ ሰላሣ ፡- የፓርቲው የፋይናንስና ገቢ ማሰባሰብክፍል ኃላፊ (ትሬዠረር)፡- ............................................. 30

አንቀጽ ሰለሣ አንድ ፡- የፓርቲው ፖሊሲ፣ ምርምርና እቅድ ክፍል ሓላፊ ......................................................... 31

አንቀጽ ሠላሣ ኹለት፡- የፓርቲው የመረጃና የግኑኝነት ቴክኖሎጂ አገልግሎት ኃላፊ፡- ...................................... 32

አንቀጽ ሠላሳ ሦስት፡- የአካል ጉዳተኞች ክፍል ኃላፊ ...................................................................................... 32

አንቀጽ ሠላሳ አራት፡- የሥልጠና ማብቃት /አቅም ግንባታ/ክፍል ኃላፊ .......................................................... 33

አንቀጽ ሠላሳ አምስት፡- የማስተባበሪያ ምክር /ቤት ሓላፊነት፣ ውሳኔ አሰጣጥ እና ተጠሪነት............................ 34

አንቀጽ ሠላሳ ስድስት ፡- የፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት ....................................................................................... 35

አንቀጽ ሠላሳ ስባት ፡- የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ..................................................................................... 35

አንቀጽ ሠላሳ ስምንት፡- የፓርቲው መሰረታዊ ድርጅት ................................................................................. 36

አንቀጽ ሠላሳ ዘጠኝ ፡- የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባና ውሳኔ አሰጣጥ.......................................... 37

ክፍል አምስት ሌሎች ድንጋጌዎች .............................................................................................................. 37

አንቀጽ አርባ፡- ፓርቲው ከሌላ ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ቅንጅት ወይም ግንባር ስለሚፈጥርበት ሂደቶች .......... 37

አንቀጽ አርባ አንድ፡- የፓርቲው አባላት ለአገር አቀፍና በየደረጃው ላሉ አገራዊ ምርጫዎች የሚታጩበት ሥርዓት
................................................................................................................................................................ 37

አንቀጽ አርባ ኹለት፡- የፓርቲው የፋይናንስ ሥርዓት ..................................................................................... 38

አንቀጽ አርባ ሦስት፡- የፓርቲው የሰው ሀብት አስተዳደር ስርዓት ................................................................... 38

አንቀጽ አርባ አራት፡- የፓርቲው የኦዲት ስርዓት ............................................................................................ 38

አንቀጽ አርባ አምስት፡- የፓርቲው አቅርቦት እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ................................................... 38

አንቀጽ አርባ ስድስት፡- የፓርቲው የገንዘብ ማስገኛ አሰራር ............................................................................ 38

አንቀጽ አርባ ሰባት፡- የፓርቲው ውስጥ አለመግባባቶች አፈታት ሥርዓትና የሥነ ሥርኣት እርምጃ አወሳሰድ ..... 39

አንቀጽ አርባ ስምንት፡- የፓርቲ መፍረስ ...................................................................................................... 39

አንቀጽ አርባ ዘጠኝ፡- ስለ ፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሻሻል ...................................................................... 39

አንቀጽ ሃምሳ፡- የመተዳደሪያ ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ .................................................................................... 39


ክፍል አንድ መግቢያ
ኢትዮጵያ ሀገራችን ሉዐላዊ ማንነት እና ቁመና ያላት የሕዝቦቿ ህብረ ቀለም፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣

ባህል፣ ክብርና የተሟላ ጀግንነት በዓለም የስልጣኔ ማማ ላይ ተቀምጣ የኖረች እና ታፍራ ተከብራ ከብዙ

ሺህ ዘመናት በላይ የመንግስትነትን ታሪክ የምትቆጥር ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለንበት በ21ኛው

ክፍለ ዘመን የህዝቧ ልዕልና ከነሙሉ ክብሯ ሳይቀጥል ይልቁንም የረሀብ፣ የችግርና የኋላ ቀርነት ተምሳሌት

ተደርጋ እስክትቆጠር ድረስ ማንነቷ እያሽቆለቆለ ህዝቧም በዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ይዛ ትገኛለች።

የሀገራችን ዜጎች ለፈርጀ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግር የተጋለጡ ቢሆንም እንኳን

ሀገራቸውን በቅንነት በታማኝነት እና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ አገልግለው ለማለፍ ፍላጎት ያላቸው በርካታ

ዓላማ ያነገቡ ዜጎች አሉ፡፡ እነዚህ በተወደደ ስብእና የታነጹ ወጣቶች የኢትዮጵያ ክብር የሚያንገበግባቸው

ግን ደግሞ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ሀገራችን የተመራችበት የሥነ መንግስት ርእዮት ያገለላቸው እና

ድርሻ ያልሰጣቸው ለለውጥ አርግዘው የሚኖሩ ናቸው። ነገር ግን የእነዚህን ወጣት ምሁራን ፍላጎት

አስተባብሮ በታቀደና ግልጽ በሆነ ሀገራዊ ርእይ ሊመራ የሚችል ቁርጠኛ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩ ደግሞ

ኢትዮጵያ ከልጆቿ እንዳትጠቀም አድርጓት ኖሯል ፡፡

በሌላም በኩል በኢትዮጵዊነት መርህና እሴቶች ላይ ያልተመሠረተ ስሜት እየተስፋፋ በመምጣቱ በዚህ

የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት ውድ የሆነች ሃገራችን መስቀልኛ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ እንዲሁም መላው

የሀገራችን ህዝቦች በተለያየ የኃይል አሰላለፍ ላይ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ይህን ኃይል በአንድ አስተባብሮ ትውልድ ተሻጋሪ የለውጥ ችቦ ማቀጣጠል ግድ የሚልበት ጊዜው

ዛሬ ነው። ለዚህ መሥራትና ለዚህ ክብር መሥራት መታደል መሆኑን አምኖ መንቀሳቀስ ለነገ የማይባል

አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ርዕይ ከግብ ለማድረስ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያታግል የሚችል

አደረጃጀት መፍጠር የግድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም እናት ፓርቲ ይህን የተበታተነ ወጣት

በማስተባበር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግሎ ለማታገል የተቋቋመ ፓርቲ ነው፡፡

የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በዓለም ላይ ተቀባይነት እያገኘ መምጣት ለሕዝቦች ተጠቃሚነትና

የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሥልጣን፣ በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን

አስተዋጽኦ ለማድረግ ያስቻለ ዘመናዊ ስርዓተ መንግስት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ዴሞክራሲ በአጠቃላይ ሀሳቡ
ከሕዝብ የተመረጠ፣ በሕዝብ የሚጠየቅ እና ለሕዝብ የሚያገለግል ስርዓት ማለት ሲሆን በሀገራችንም ይህንን

ዓይነት ስርዓት ለማስፈን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያልተቋረጠ ትግል አድርገዋል።

የዲሞክራሲ ሥርዓት መሰረታዊ መገለጫ ባህርያት ከሆኑት አንዱና ዋነኛው በሕዝብ የተመረጠ

መንግሥታዊ አስተዳደርን መመሥረት ነው፡፡ እናት ፓርቲ ለመቋቋምና በምርጫ ለመሳተፍ የወሰነው አሁን

ያለው የፖለቲካ ምህዳር የተመቻቸ ሁኔታዎች ያሉት ሆኖ ሳይሆን ይህ ተጫባጭ እውነታ በህዝቡ የተባበረ

ትግልና በቁርጠኛ አመራር ሊለወጥ ይገባል የሚል ፅኑ እምነት ስላለው ነው፡፡ ስለዚህ ፓርቲው

የሚመሠረትበትን ሕገ-ደንብ ለመቅረጽ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይህ መተዳደሪያ ደንብ በዋናነት በአምስት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ጠቅላላ

የእናት ፓርቲን የፖለቲካ ድንጋጌዎችን በተመለከተ የተዘረዘሩ እንደ አርማ (ሎጎ) የፓርቲው የስራ ቋንቋ እና

የጽ/ቤት ቦታዎችን ይተነትናል፡፡ በሁለተኛ ክፍል የፓርቲው የአባልነት መስፈርትና ሌሎች አባላትን

በተመለከተ በዝርዝር ተነትኗል በሦስተኛው ክፍል የእናት ፓርቲ የአደረጃጀት ሥርዓቶችን ይዘረዝራል

በአራተኛ ክፍል የእናት ፓርቲ አወቃቀር እና አደረጃጀት እንዲሁም የሥራ ድርሻ እና በመጨረሻም በክፍል

አምስት እናት ፓርቲ የሚመራበት ሌሎች ድንጋጌዎችን እና እናት ፓርቲ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር

ስለሚኖረው ውሕደት፣ ቅንጅት እና ግንባር መፍጠር በምን መልኩ እንደሆነ እና በተጨማሪም የእናት ፓርቲ

የውስጥ ሥርዓቶችን፣ ደንቦችን እና አደረጃጀቶችን ያሳያል፡፡


ክፍል ሁለት ጠቅላላ ድንጋጌዎች
አንቀጽ አንድ፡-አጭር ርዕስ

ይህ ሰነድ የእናት ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

አንቀጽ ኹለት፡- የፓርቲው ስያሜ፣ ርዕይ፣ ተልእኮና ዓላማ


2.1 የፓርቲው ስያሜ

2.1.1 የፓርቲው ስያሜ “እናት ፓርቲ” ነው።


2.1.2 እናት ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር
1162/2011 መሠረት በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የተመዘገበ ፓርቲ ነው።

2.2 የፓርቲው ርእይ፣ ተልእኮ እና ዓላማ

ርእይ

በሥነ ምግባር የታነጸ እና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የተላበሰ የሕዝብ ተመራጭ ሆኖ የመንግስትን ስልጣን

በመያዝ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ልዕልና ከፍ የሚያደርግ ፓርቲ መሆን ነው፡፡

ተልዕኮ

ሀገር በቀል እውቀቶችንና እሴቶችን አክብሮ ከሌሎች እውቀቶች ጋር በማዋሐድ፤ ሰውነትን መሠረት ያደረገ

ሁሉን አቃፊ ፖለቲካ በማራመድ፤ የችግሮቻችን መንስዔ የሆኑትን ስሁት አስተሳሰቦች በመቅረፍ፤

ኢትዮጵያውያን በሕይወት የመኖር ዋስትናቸው እንዲሁም ተዘዋውሮ ሀብት የማፍራት መብታቸው

ተከብሮ፤ በእኩልነትና በፍትሐዊ ሥርዓት እየተመሩ የሚኖሩበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡

ዓላማ

1. በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ምርጫን አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን በመጨበጥ ኢትዮጵያ

አገራችንን ወደ ላቀ ከፍታ ማምጣት

2. የገዢውን ፓርቲ ድክመት ነቅሶ በማውጣት፣በመተቸትእና አማራጭ ሃሳቦችን በማመንጨት አገር

በአግባብ እንድትመራ የማያቋርጥ አወንታዊ ተጽእኖ ማሳደር

3. የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲዳብር ማድረግ


4. ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ

5. የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲሰፋ መስራት

6. በሀገር ደረጃ የተዛቡ ስሑት ፖለቲካ አስተሳሰቦችን መሞገትና ማጋለጥ

7. በዜጎች ላይ የሚደርሱ ሰብዓዊ፣ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ በደሎችን በማጋለጥ

ድምጽ መሆን

8. ዜጎች የሃገራቸው ጉዳይ ያገባኛል ብለው ለሃገር አንድነት እንዲቆሙ ማስተባበር

አንቀጽ ሦስት፡- ትርጉም


3.1 ጠቅላላ ጉባኤ ማለት፡- የፓርቲው አባላት በሙሉ በሕጋዊ ተወካዮች በሙሉ ወይም ሁሉም

አባላት በአንድ ላይ መሰብሰብ ስለማይቻል ቢያንስ 500 በየዘርፉ ያሉ ተወካዮቻቸው

የሚሳተፉበትና የፓርቲው አጠቃላይ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት እና የፓርቲው የበላይና

የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ማለት ነው።

3.2 ላዕላይ ምክር ቤት ማለት ፡- ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛ የፓርቲው የሥልጣን አካል

ሲሆን ከእየንዳንዱ ማስተባበሪያ በሚወከሉ አንድ አንድ አባላት የሚመሠረት እና በወቅቱ

ባሉ ማስተባበሪያዎች ቁጥር ልክ አባላት ያሉት ሆኖ የፓርቲውን አጠቃላይ አሰራር

በበላይነት የሚመራ ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤ የሆነ አካል ነው።

3.3 ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ማለት፡- በሥሩ የሚገኙ የወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች

የሚፈጽሙትን ሥራ የሚያቀናጅ ፣የሚያስተባብር እና የሚከታተል፤ተጠሪነቱ

ለማስተባበሪያ ምክር ቤት እና ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ የሆነ የፓርቲውን ሥራ

የሚያስተባብር እና የሚመራ አካል ማለት ነው፡፡

3.4 የማስተባበሪያ ምክር ቤት ማለት፡- ከእያንዳንዱ በማስተባበሪያው ሥር ካሉ ወረዳ/ከተማ

ቅ/ጽቤቶች በሚወከሉ ተወካዮች የሚመሠረት እና በማስተባበሪያው ሥር ባሉ

ወረዳዎች/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የፓርቲውን እንቅስቃሴ በበላይነት የሚመራ አካል

ማለት ነው፡፡

3.5 የወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ማለት፡- በወረዳ/ከተማ የሚገኙ የፓርቲው አባላት

በየመሠረታዊ ድርጅቶቻቸው የሚፈጽሙትን ሥራ የሚያቀናጅ የሚያስተባብር እና

የሚከታተል ተጠሪነቱ ለማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሆነ የፓርቲውን ሥራ የሚያስተባብር እና

የሚመራ አካል ማለት ነው፡፡


3.6 የፓርቲው ፕሬዝደንት ማለት፡- በጠቅላላ ጉባኤ በቀጥታ የሚመረጥ ተጠሪነቱ ለላዕላይ

ምክር ቤት እና ለሥራ አስፈጻሚ ኪሚቴ የሆነ የፓርቲው ፕሬዚዳንት የሆነ ነው።

3.7 የፓርቲው ምክትል ምክትል ፕሬዝደንት ማለት፡- በጠቅላላ ጉባኤ በቀጥታ የሚመረጥ

ተጠሪነቱ ለላዕላይ ምክር ቤት እና ለሥራ አስፈጻሚ ኪሚቴ የሆነ የፓርቲው ምክትል

ፕሬዝዳንት ማለት ነው።

3.8 የፓርቲው ጠቅላይ ጸሐፊ ማለት፡- በጠቅላላ ጉባኤ በቀጥታ የሚመረጥ ተጠሪነቱ ለላዕላይ

ምክር ቤት እና ለሥራ አስፈጻሚ ኪሚቴ የሆነ የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊና ሙሉ ጊዜውን

በፓርቲ ሥራ ላይ የሚያውል ማለት ነው።

3.9 ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማለት፡- በጠቅላላ ጉባኤ በቀጥታ የሚመረጥ እና

ተጠሪነቱ ለላዕላይ ምክር ቤት የሆነ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካል ማለት ነው።

3.10 የፓርቲው ሙሉ አባል ማለት፡- በፓርቲው በማንኛውም የእውቀት የአመለካከት እና

የክህሎት ዝንባሌ በሚጠይቅ በፓርቲው የሥራ ዘርፍ ወይም በአባልነት ተመዝግቦ የሚገኝ

ግለሰብ ማለት ነው።

3.11 የፓርቲው ተባባሪ አባል ማለት፡- ፓርቲውን በእውቀቱ፣ በገንዘቡ እና በማንኛውም የድጋፍ

እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነገር ግን የመምረጥና የመመረጥ መብት የሌለው የፓርቲው ደጋፊ

ማለት ነው።

አንቀጽ አራት የፓርቲው አርማ (ሎጎ) ትርጉም


4.1 የዓርማው ዙሪያ ክበብ ዓለምን የሚያሳይ ነው

4.2 የተለያዩ ቀለማት ያሉት ሐረጉ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት እሴት ፤ ኅብርና

መተሳሰር ያሳያል ፡፡

4.3 በቢጫ ቀለም የሚታየው የብርሃን ጨረር ለዓለም የሚተርፈውን የኢትዮጵያን መጻኢ

እድገትና ብሩህ ተስፋን ያሳያል ፡፡

4.4 በጥቁር ቀለም የተቀለመው የኢትዮጵያ ካርታ አፍሪካዊነታችንን ያሳያል፡፡

4.5 የጸነሰች እና ልጇን የታቀፈችው እናት ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን በእኩልነት የምታይ

መሆኗን ያሳያል፡፡

4.6 የካርታው ነጩ መደብ ሰላምን የሚገልጽ ነው፡፡


አንቀጽ አምስት፡- የፓርቲው የሥራ ቋንቋ
ሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት በሀገራችን የሥራ ቋንቋነት የተገለፀው አማርኛ ቋንቋ የፓርቲውም

የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሌሎች ተጨማሪ የሥራ

ቋንቋዎችን ይጠቀማል።

አንቀጽ ስድስት፡- የፓርቲው ጽ/ቤት


የእናት ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አዲስ አባባ ሲሆን በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እንደ አግባብነቱ

የማስተባበሪያ፤ የወረዳ እና የከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚኖረው ይሆናል፡፡

አንቀጽ ሰባት፡- የፆታ አገላለጽ


በዚህ መመሪያ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትን ፆታ ያካትታል።

ክፍል ሦስት የፓርቲ አባልነት


አንቀጽ ስምንት፡- የፓርቲ አባልነት
8.1 እጩ አባል

8.1.1 በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥልቅ ስሜት ያለው።

8.1.2 ሀገራዊ ፍልስፍና ማወቅና ማስጠበቅ፣ መተግበር የሚችል።

8.1.3 ሀገራዊ እሴቶችን መጠበቅ እና ማስጠበቅ የሚችል።

8.1.4 ህዝብን ለማገልገል ሙሉ ተነሳሽነት ቁርጠኝነት እና ፍቃደኝነት ያለው፡፡

8.1.5 የሚያገጥሙ ተግዳሮቶችን ሁሉ ከፓርቲው አባላት ጋር በፍጹም ታማኝነት

ለመወጣት በጥብቅ ቃል ኪዳን ለመተሳሰር ፍቃደኛ የሆነ፡፡

8.1.6 ለፓርቲው ሕግና ደንብ ተገዢ የሆነ።

8.1.7 የፓርቲውን ተልእኮና ፕሮግራም ለማስፈጸም ዝግጁ የሆነ።

8.1.8 በጋራ ለመስራት ለመወያየት በሃሳብ ልእልና የሚያምን።

8.1.9 ራሱን ለማብቃት ሙሉ ፍቃደኝነት ያለው።

8.1.10 ምስጢር ጠባቂ የሆነ።

8.1.11 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፓርቲው አባል ለመሆን ሲጠይቅ በእጩ አባልነት

ይመዘገባል።

8.1.12 እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ በፖለቲካ ለመሳተፍ የሕግ ገደብ

ያልተጣለበት።
8.1.13 የሌላ የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ።

8.1.14 የፓርቲውን የአባላት መዋጮ ለመክፈል እና ሌሎች ግዴታዎችን ለመወጣት

ፈቃደኛ የሆነ።

8.1.15 የዕጩ አባልነት ጊዜ ሦስት ወር ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ ለተጨማሪ ሦስት ወራት

ሊራዘም ይችላል ፡፡

8.1.16 የፓርቲው ሙሉ አባል ለመሆን የሚፈልግ ግለሰብ በፓርቲው መመልመያ

መስፈርት መሰረት አባል ለመሆን በሚያቀርበው ጥያቄ ላይ ተንተርሶ የእጩነት

ጊዜውን እንደ ጨረሰ ወይም አስፈላጊ መሆኑ ሲታመን በጊዜአዊ አባልነት ዘመኑ

በሚሰጠው ተልዕኮ አፈጻጸም ተመዝኖ በተዋረድ ባለ ሥራ አስፈጻሚ ሲጸድቅ ብቻ

ሙሉ አባል ይሆናል፡፡

8.2 ሙሉ አባል

8.2.1 የፓርቲው አባላት ከፓርቲው መስራች ጉባኤ በፊት ተመዝግበው በመስራች

አባልነት ከምስረታ በኃላ የእጩ አባልን መስፈርት ወይም ግዴታቸውን በአግባቡ

የተወጡ ፓርቲውን በአባልነት የተቀላቀሉትን ሁሉ ያካተተ ነው።

8.2.2 የእናት ፓርቲ አባልነት በውርስም ሆነ በሌላ በማናቸውም መንገድ ለሌላ ተላልፎ

የማይሰጥ በአባሉ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ነው።

8.2.3 የአባልነት መብት የሚቆየው የአባልነት ግዴታቸውን ለተወጡ አባላት ብቻ ነው፡፡

8.3 ተባባሪ / ደጋፊ አባል

8.3.1 በፓርቲው ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ የግል ሁኔታቸው የማይፈቅድላቸው

ኢትዮጵያውያን ሁሉ የፓርቲው ተባባሪ አባል ሊሆኑ ይችላሉ።

8.3.2 ተባባሪ አባል ለፓርቲ ኃላፊነት ቦታ ለመምረጥና ለመመረጥ እንዲሁም በፓርቲው

ውሳኔዎች ላይ ድምጽ ለመስጠት ካለመቻል በስተቀር ሌሎች የአባልነት መብቶች

ሆሉ ይኖረዋል።
አንቀጽ ዘጠኝ፡- የአባልነት መብት
9.1 ማንኛውም አባል ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት ንቁ ተሳታፊ የመሆን መብት አለው፡፡

9.2 ማንኛውም የፓርቲው አባል በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በሚመለከተው

የፓርቲው ስብሰባዎች የመሳተፍ፣ ሀሳቡንና አስተያየቱን በነፃ መግለጽ፣ ድምጽ የመስጠት

መብት አለው።

9.3 ማንኛውም አባል በፓርቲው ውስጥ የመመረጥ እና የመምረጥ መብት አለው፡፡

9.4 ማንኛውም አባል በደንቡ መሠረት ጥያቄ የመጠየቅ እና በወቅቱ መልስ የማግኘት መብት

አለው፡፡

9.5 ማንኛውም እጩ አባል በፓርቲው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው

ሆኖም የመምረጥ የመመረጥ እና በፓርቲው ውሳኔዎች ላይ ድምጽ የመስጠት መብት

የለውም።

አንቀጽ አስር፡- የአባልነት ግዴታ


10.1 የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ የማክበር እና የማስከበር፤

10.2 በተመሳሳይ ጊዜ የሌላ ፓርቲ አባል መሆን አይችልም፤

10.3 ከሌላ ፓርቲ ሥልጠና መውሰድና ለሌላ ፓርቲ ሥልጠና መስጠት አይችልም፤

10.4 የፓርቲውን የአሠራር ምስጢር መጠበቅ ፤

10.5 በጠቅላላ ጉባኤ እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሚመጡ እቅዶችን እና ፖሊሲዎችን የሥራ

ክንውኖች ላይ በመተባበር ትእዛዞችን የመፈፀምና የማስፈፀም ፤

10.6 አባል ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ወርሀዊ መዋጮ የመክፈል ፤

10.7 በተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ፓርቲው በሚጠራቸው የተለያዩ ሥልጠናዎች መሳተፍ ፤

10.8 በፓርቲው የሚሰጠውን ማንኛውም ሕጋዊ ተልእኮ የመፈጸም ግዴታ ፡፡

አንቀጽ አስራ አንድ፡- የአባልነት መዋጮ እና የገቢ ምንጭ

11.1 ማንኛውም የፓርቲው አባል በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ወይም ፓርቲው በወሰነው

መሠረት ከሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝ ወይም ገቢ 1.0% /አንድ መቶኛ/ ለፖለቲካ

ፓርቲው ዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ በየወሩ የአባልነት መዋጮ ይከፍላል፡፡ ክፍያው በጥሬ

ገንዘብ በአካል ወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመቅረብ ወይንም በፓርቲው የባንክ

ሂሣብ ቁጥር በማስገባት ይፈፀማል፡፡ ገንዘቡን የተቀበለው የወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት


ለከፋዩ በብሔራዊ ጽ/ቤት የታተመና ተከታታይ ቁጥር ያለው የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ

ቆርጦ ይሰጣል፡፡

11.2 የምርጫ ቦርዱ አጥንቶ በሚያስቀምጠው ጣሪያ መሠረት በኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች

ወይም ኢትዮጵያዊያን በሚቆጣጠሯቸው ኩባንያዎች የሚደረግ ስጦታ ወይም ዕርዳታ

የፓርቲው የገቢ ምንጭ ነው።

11.3 ከመንግስት የሚሰጠው ድጋፍና ዕርዳታ የፓርቲው ገቢ ይሆናል፡፡

11.4 የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ እናት ፓርቲ የገንዘብ አቅሙን ለማጎልበት የሚያግዙ

የገቢ ማስገኛ ኮንፍረሶችን እና ግብዣዎችን በማዘጋጀት የተለያዩ ጉባኤዎችን በማስመልከት

የሚያዘጋጃቸውን አልባሳት፣ መጽሔቶችን እና መጽሐፍቶችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የምርምር

ውጤቶችን በመሸጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ሌላው የፓርቲው የገቢ ምንጭ ይሆናል።

አንቀጽ አስራ ሁለት፡- አባልነት የሚቋረጥበት ሁኔታዎች


12.1 ማንኛውም የፓርቲው አባል የፓርቲውን ሕግ እና ደንብ ተላልፎ ሲገኝ እንዲሁም ፓርቲውን

አደጋ ላይ በሚጥሉ ተግባራት ላይ መሠማራቱ ከተረጋገጠ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ

መሠረት በቅድሚያ የቃል፣ ቀጥሎም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ እንደአስፈላጊነቱ

እንደ ፓርቲያችን እሴት በሽምግልና እንዲታረም ሊደረግ ይችላል፤ በመጨረሻ በፓርቲያችን

አባሉ በነበረበት የበላይ መዋቅሮች ከአባልነት ሊሰናበት ይችላል፤ በየመዋቅሩ ያሉ አመራሮች

ከሆኑ በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ውሳኔ ከአባልነት ሊሰናበት ይችላል፡፡

12.1.1 የቃል ማስጠንቀቂያ የሚያሰጡ ጥፋቶች

ከፓርቲው የተቀበለውን ሐላፊነት በወቅቱ አለመወጣት፣ በቸልተኝነት የሚፈጸሙ


ጥፋቶች፣ ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር ተግባብቶ አለመስራት እና መሰል ጥፋቶች

12.1.2 የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የሚያሰጡ ጥፋቶች

የፓርቲውን ምስጢር ለሶስተኛ ሰው አሳልፎ መስጠት፣ የፓርቲው አመራሮች

የሚሰጢትን ውሳኔ አለመቀበል/ግዳጅ አለመፈጸም፣ የፓርቲውን መዋቅር ለግል

ጥቅም መጠቀም፣ ከፓርቲው ለሥራ የተወሰደ ገንዘብ በተገቢው ጊዜ

አለማወራረድ፤ ከፓርቲውን እውቅና ካለው ሶሻል ሚዲያ ውጪ የፓርቲውን አርማ

ተጠቅሞ በግል መክፈት እና ያልተገባ የፓርቲው አቋም ያልሆነን ነገር መፃፍ ወይም
በግል ሶሻል ሚዲያ ፓርቲውን/አባላትን የሚጎዱ ጽሁፎችን ወይም ምስሎችን

መፃፍ/ማጋረት እና መሰል ጥፋቶች

12.1.3 ያለ ማስጠንቀቂያ ከፓርቲው የሚያሰናብቱ ጥፋቶች

የፓርቲውን አባላትን የመከፋፈል ሥራ ወይም በፓርቲው መደበኛ መዋቅር ላይ

ለአመጽ ማነሳሳት ሲሰራ የተገኘ ማንኛውም አባል እንደጥፋቱ ደረጃ ያለ

ማስጠንቀቂያ ሊሰናበት ይችላል፤ የፓርቲውን ንብረት/ገንዘብ የስርቆት ሥራ ላይ

ተሳትፎ መገኘት፤ የሙስና ጥፋቶች ከተገኙበት፣ ከፓርቲው አመራሮች ውሳኔ ውጪ

የሐገርን ሰላም ወይም የሕብረተሰብን ተስማምቶ መኖር ሊያጠፋ የሚችል ቅስቀሳ

ወይም አመጽ ማነሳሳት፤ እና መሰል ጥፋቶች

12.2 የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሲያምንበት እና እንደጥፋቱ ደረጃ ከላይ

የተቀመጡትን ደረጃዎች ሳይጠብቅ ለፓርቲው ሕልውና አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምንበትን

እርምጃ መውሰድ ይችላል፡

12.3 ከፓርቲ አባልነት የተሰናበተ አባል በውሳኔው ላይ ቅሬታ ካለው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ

መሠረት ውሳኔውን ካሳለፈው ውሳኔ ሰጪ አካል ቀጥሎ ላለው የበላይ አካል ቅሬታውን

ማቅረብ ይችላል።ቅሬታውን የተመለከተው አካል ውሳኔ አባሉን ካላረካው ውሳኔው

በይግባኝ እንዲታይለት የፓርቲውን መዋቅር ተከትሎ እስከ ላዕላይ ምክር ቤት ድረስ

ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት ላዕላይ ምክር ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻው

ውሳኔ ይሆናል፡፡

12.4 የአባሉ የስንብት ሁኔታ ለምርጫ ቦርድና በሁሉም የፓርቲው መዋቅሮች እንዲታወቅ

ማድረግና ሥንብቱ አባሉ በተመዘገበበት ወረዳ የሚከናወን ይሆናል።

12.5 በሥነ ምግባር ግድፈት (ሙስና፣ የፓርቲውን ምስጢር በታወቀ መልኩ በማባከን)

ከተገኘበት ይህ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ተብሎ በሕጉ አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል።

12.6 የእምነት፣ የጎሳ፣ የቋንቋ ልዩነት የፈጠረ እንደሆነ ይህ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ተብሎ በሕጉ

አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል።

12.7 በተሰጠው ሓላፊነት ተጠቅሞ ለፓርቲው ሕልውና ሥጋት መሆኑ በማስረጃ የተደረሰበት

አካል ይህ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ተብሎ በሕጉ አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል።

12.8 የሓላፊነትን ሥልጣን ከፓርቲው ውጪ ለሌላ ጉዳይ የተጠቀመ ይህ የሥነ ሥርዓት ጉድለት

ተብሎ በሕጉ አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል።


12.9 የእናት ፓርቲ አባል የሆነ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ ሲገኝና

ይህም በሰው ወይም በሰነድ ማስረጃ ሲረጋገጥ በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በሚሰጠው

ውሳኔ ከፓርቲው አባልነት ይሰናበታል፡፡ ይሁን እንጂ አባሉ በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚው

ውሳኔ ካልተስማማ ቅሬታውን ለላዕላይ ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የፓርቲው ላዕላይ

ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የሚያሳልፈው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡

12.10 ማንኛውም የእናት ፓርቲ አባል ወይም አመራር ለፓርቲው በጹሑፍ በቅድሚያ በማቅረብ

ከፓርቲው ሊሰናበት ይችላል።

12.11 እናት ፓርቲ መልቀቂያ ያደረሰውን አባል በ15 ቀናት ውስጥ ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ

አለበት።

12.12 በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ

(1162/2012) ስለ ፓርቲዎች መቀናጀት ውህደት እና ስለ ፓርቲ መተካት የተደነገገው

እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የእናት ፓርቲ አባል ወይም አመራር ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ

የመመሥረት ወይም ለመመሥረት ሂደት ውስጥ የተሳተፈ ወይም የተቀላቀለ ወይም የሌላ

የፖለቲካ ፓርቲን መመሥረት አስመልክቶ በይፋ የቀሰቀሰ ወይም የሌላ ፓርቲ ፕሮግራም

ፍላጎት የሚያስፋፋ ከሆነ መልቀቂያ ባያቀርብም ከእናት ፓርቲ እንደለቀቀ ይቆጠራል፤

ክፍል አራት የፓርቲው አወቃቀር እና አደረጃጀት

አንቀጽ አስራ ሦስት ፡- የፓርቲው አወቃቀር እና አመራር አባላት


ፓርቲው የሚከተሉት የድርጅት አካላት ይኖሩታል።

1) የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ፣

2) የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት፣

3) የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ

4) የፓርቲው የሕግና የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ

5) የፓርቲው የሒሳብና ክዋኔ ቁጥጥር ኮሚሽን

6) የፓርቲው አርትኦት ቦርድ

7) የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት

8) የፓርቲው ማስተባበሪያ ምክር ቤት

9) የፓርቲው ማስተባበሪያ ጽ/ቤት


10) የፓርቲው ወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት

11) የፓርቲው መሠረታዊ ድርጅት

12) የፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት

አንቀጽ አስራ አራት፡- የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አመሠራረት፣ ሥልጣንና ተግባር


14.1 የጠቅላላ ጉባኤ አመሠራረት

14.1.1 ማንኛውም ለጠቅላላ ጉባኤ የተወከለ የፓርቲ አባል በጠቅላላ ጉባኤ ላይ አንድ

ድምጽ አለው፤ ማንኛውም አባል እኩል ድምፅ አለው፡፡

14.1.2 የድምጽ አሰጣጥ ሥነ- ሥርዓት ፍትሃዊ ነጻና ግልጽ በሆነ መንገድ ድጋፍ፣

ተቃውሞና ድምጸ ተዐቅቦ በሚጠይቅ ጉዳይ እጅ በማውጣት በሚሰጥ ድምጽ

የአባላት ድምጽ እንዲንፀባረቅና ውሳኔ እንዲተላለፍ ይደረጋል፡፡

14.1.3 በጠቅላላ ጉባኤ የሚደረግ የፓርቲው አመራር አካላት እና ልዩ ልዩ ኮሚቴ አባላት

ምርጫ የሚካሄደው ለዚሁ ተግባር በዕለቱ በጠቅላላ ጉባኤው በሚመረጡና

አምስት አባላት ባሉት ጊዜያዊ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ አማካይነት ነፃና

ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ በድምጽ መስጫ ወረቀትና

በድምጽ መስጫ ሳጥን አማካኝነት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት

ከተጠናቀቀ በኋላ የድምፅ ቆጠራው በዕለቱ ተጠናቅቆ ውጤቱ በኮሚቴው

አማካይነት ለጉባዔው ይገለፃል፡፡

14.1.4 የጠቅላላ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ በፓርቲው

ፕሬዝደንት መሪነት የሚካሄድ ይሆናል፡፡

14.1.5 ፓርቲው አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ የጠቅላላ ጉባኤውን መደበኛ የስብሰባ ጊዜ

ሳይጠብቅ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካሄድ ይችላል፡፡

14.1.6 በጠቅላላ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ ከ7 (ሰባት) የሥራ ቀናት በፊት ለአባላት

የስብሰባው ቦታ፣ ቀኑንና ሰዓት እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡

14.1.7 ከፓርቲው አባላት ቢያንስ 500 ከተገኘ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡ የጠቅላላ ጉባኤ

ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውሳኔዎች የሚተላለፉት ከተገኙት አባላት

አብላጫ ድምጽ ማግኘት ሲችሉ ነው፡፡


14.1.8 በጠቅላላው ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች እንደ ሁኔታዎቻቸው

በአጀንዳነት ተይዘው ይቀርባሉ፣ ማንኛውም ጉዳይ በአጀንዳ እንዲያዝለት

የሚፈልግ መዋቅር ጠቅላላ ጉባኤ ከመሰብሰቡ ቢያንስ ከአምስት የሥራ ቀናት

በፊት ለፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በጽሁፍ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

14.1.9 የጠቅላላ ጉባኤው የስብሰባ የጊዜ ቆይታ ከአንድ እስከ አምስት ቀናት እንደ

አስፈላጊነቱ ይከናወናል።

14.1.10 በውጭ ሀገር የተቋቋሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ወይም ደጋፊ ድርጅቶች

የሚጋበዙና ለአባልነት የማይበቁ ደጋፊ አባላት ያለ ድምጽ ሊካፈሉ ይችላሉ።

14.1.11 ከአቻ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሕዝባዊ ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ ከሆኑ

ድርጅቶች እና ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች (ዝግ ባልሆኑ ስብሰባዎች) ሊጋበዙ

ይችላሉ።

14.2 የጠቅላላ ጉባኤ ስልጣንና ተግባር

14.2.1 የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ ያፀድቃል፣ አስፈላጊም ሲሆን

ያሻሽላል፡፡

14.2.2 የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን፣ የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባላትን፣ የፓርቲውን

የሒሳብ ክዋኔ ቁጥጥር ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ የፓርቲውን የሕግና ሥነ ሥርዓት

ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የፓርቲውን አርትኦት /የኤዲቶሪያል / ቦርድ ሰብሳቢን

በምስጢራዊ ድምፅ አሠጣጥ ግልጽ፣ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይመርጣል

ይሽራል፡፡

14.2.3 ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት ወይም የፖለቲካ ፓርቲ መተካት አስፈላጊነቱን

ካመነበት ውሳኔ ይሰጣል፡፡

14.2.4 የፓርቲውን አጠቃላይ ጉዳዮችን ይወስናል።

14.2.5 የፓርቲውን አጠቃላይ ሂደትንና ሥራዎችን በበላይነት ይገመግማል እንዲሁም

የማስተካከያ አቅጣጫ ያስቀምጣል።

14.2.6 የጉባኤውን የመወያያ አጀንዳዎችን ያጸድቃል ፡፡

14.2.7 የፓርቲውን ስልታዊ እቅድ ያጸድቃል።

14.2.8 የፓርቲውን የሂሳብ ሪፖርቶች ያጸድቃል።


14.2.9 በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ የፓርቲው አመራሮች ቃለ መሐላ እንዲፈጽሙ

ያደርጋል ፡፡

አንቀጽ አሥራ አምስት፡- የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ

15.1 የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ ከመድረሱ ስድስት ወራት ቀደም ብሎ የጠቅላለ ጉባኤ አዘጋጅ

ኮሚቴ እንዲዋቀር ይደረጋል፡፡

15.2 የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ አምስት አባላት የሚኖሩት ሲሆን ሰብሳቢ፣ ምክትል

ሰብሳቢ፣ ፀሐፊና ሁለት የኮሚቴ አባላት ይኖሩታል፡፡

15.3 ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስቱ አባላት በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ተጠቁመው ጉባዔውን

እንደሚያሳኩ ሲታመንባቸው ዝርዝራቸው ለላዕላይ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡

15.4 የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሥራ ምቹነትና ከብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ

የሚያስፈልገውን ድጋፍ እና እግዛ ለማግኘት እንዲያስችለው ከብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ

ኮሚቴ ውስጥ አንዱ እንዲሆን ይደረጋል፡፡

15.5 የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው በሥሩ ለዓላማው ስኬታማነት የሚረዱ

ንዑሳን ኮሚቴዎችን ከብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ጋር በመነጋገር ሊያቋቁም ይችላል፡፡

15.6 የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ በጉባዔው ቀን የሚመረጡ የፓርቲው አመራሮችን

ከተሰናባች አመራረሮች ጋር ርክክብ እንዲያደርጉ በማድረግና ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ

ያከናወናቸውን ተግባራት የጽሑፍ ሪፖርት አዘጋጅቶ ለተመራጭ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ

በማስገባት የአገልግሎት ዘመኑን ይጨርሳል፡፡

አንቀጽ አስራ ስድስት፡- የፓርቲው የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ

16.1 በፓርቲው የተለያዩ አካላት የቀረቡለትን ከሕግ እና ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች

ይመለከታል።

16.2 በፓርቲው አመራሮች የሚቀርቡ ማንኛውም ሕግ ነክ ጉዳዮችን ጥያቄዎችን ተቀብሎ

የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፤ በሚጠየቀው መሰረት የሥነ-ምግባር ደንብ እና ሌሎች

መመሪያዎች አዘጋጅቶ እንዲጸድቅ ያስደርጋል ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤


16.3 በአንቀጽ 12 ሥር የተገለጹት የሥነ ሥርዓት ጉድለቶች መፈፀማቸው በፓርቲው አመራሮች

ሲታመን እንደአስፈላጊነቱ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት የሥነ ሥርዓት ጉዳዮችን መርምሮ

ተገቢው ቅጣት ምን መሆን እንዳለበት የውሳኔ ምክረ-ሐሳብ ያቀርባል፤

16.4 ኮሚቴው ከፓርቲው ፕሮግራምና ደንብ ስህተቶች ወይም የአሠራር መዛባት

መፈጸማቸውን ሲያረጋግጥ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በወቅቱ እንዲታረም ያደርጋል፤

16.5 የፓርቲውን መብት ለማስከበር አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ በጽ/ቤት ወይም በመንግስት

አካላት ፊት ፓርቲውን በመወከል ክስ በማቅረብ ይከራከራል፤

16.6 በላዕላይ ምክር ቤት ወይም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከፓርቲው ጋር በተያያዘ

ለሚቀርብለት የሕግ ጉዳይ ምክር ይሰጣል፤

16.7 በፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት እና የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ላይ ያለ

ድምጽ የመሳተፍ መብት አለ፤

16.8 ሦስት አባላት የሚኖረው ሲሆን ሰብሳቢው በጠቅላላ ጉባኤ ይመረጣል ቀሪ ሁለቱ የኮሚቴ

አባላት በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ተጠቁመው በላዕ ላይ ምክር ቤት የሚፀድቅ ይሆናል ።

አንቀጽ አስራ ሰባት፡- የፓርቲው የሒሳብና ክዋኔ ቁጥጥር ኮሚሽን


17.1 አጠቃላይ የፓርቲውን የሥራ አፈጻጸም ሂደት ይከታተላል፣ ቁጥጥርም ያደርጋል፡፡

17.2 የፓርቲውን አጠቃላይ የሒሳብ ሥራዎች እና ንብረት አያያዝ በአግባቡ መሠራቱን

ለማረጋገጥ ክትትል ያደርጋል።

17.3 የተበላሹ የሒሳብ አሰራሮችን የማስተካከያ ሥራ እንዲወሰድ ያስደርጋል።

17.4 አጠቃላይ የፓርቲውን የሒሳብ እና ክዋኔ ቁጥጥር እንቅስቃሴ ለጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት

ያደርጋል። አስፈላጊና አጣዳፊ ሆኖ ሲያገኘው ለላዕላይ ምክር ቤት የቁጥጥር ሪፖርት

ያቀርባል፡፡

17.5 በቀረቡት የሒሳብና ክዋኔ ቁጥጥር ግኝቶች መሠረት በሚመለከተው አካል መፍትሔና

እርምት ማግኘታቸውን ይከታተላል

17.6 የውስጥ አሰራሮችን መሰረት ባደረገ የፓርቲውን ወጪና ገቢ ሰነዶችን ይመረምራል።

17.7 የኮሚሽኑ አባላት ቁጥር ሦስት ሲሆን ሰብሳቢው በጠቅላላ ጉባኤ ይመረጣል ቀሪ ሁለቱ

የኮሚቴ አባላት በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ተጠቁመው በላዕላይ ምክር ቤት የሚፀድቅ


ይሆናል፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤ ይሆናል፡፡የላዕላይ ምክር ቤት እና የፓርቲው ብሔራዊ

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ያለ ድምጽ የመሳተፍ መብት አለው።

አንቀጽ አሥራ ስምንት፡- የፓርቲው አርትኦት /ኤዲቶሪያል/ ቦርድ ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔና ለላዕላይ ምክር ቤት ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

18.1 የቦርዱ ኃላፊ በጠቅላላ ጉባኤ ይመረጣል፡፡

18.2 ሦስት አባላት የሚኖረው ሲሆን ሰብሳቢው በጠቅላላ ጉባኤ ይመረጣል ቀሪ ሁለቱ የኮሚቴ

አባላት በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ተጠቁመው በላዕ ላይ ምክር ቤት የሚፀድቅ ይሆናል ።

18.3 የፓርቲውን አርትኦት ፖሊሲና የሥራ መመሪያ አዘጋጅቶ በላዕላይ ምክር ቤት ሲጸድቅ

በሥራ ላይ ያውላል።

18.4 የፓርቲውን ማንኛውም የአቋም መግለጫዎች፣ የድምጽና ምስል ፣ የጹሑፍ

ሥራዎች…ወዘተ ለሕዝብ ከመቅረባቸው በፊት ተስተካክለው እንዲወጡ ያደርጋል።

18.5 የአርትኦት ቦርዱ ኃላፊ እና አባላት የሥራ ዘመናቸው ሦስት ዓመት ይሆናል፡፡

አንቀጽ አስራ ዘጠኝ፡- የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት አመሠራረት፣ ሥልጣንና ተግባር


19.1 የላዕላይ ምክር ቤት አመሰራረት እና የአገልግሎት ዘመን

19.1.1 ከየማስተባበሪያው በሚወከሉ እና በጠቅላላ ጉባዔ በሚመረጡ 25 አባላት

እነዲሁም ከብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በቀጥታ በሚገቡ ሦስት አባላት በድምሩ

28 ዓባላት የላዕላይ ምክር ቤት ይመሠረታል፡፡ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት

የሚመረጡት ከላይ በአንቀጽ 14.1.3 በተጠቀሰው መሠረት ግልፅ፤ ነፃና ፍትሃዊ

በሆነ መንገድ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ ይሆናል፡፡

19.1.2 ከዚህ በታች የተገለጹት ሦስቱ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በቀጥታ

የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ይሆናሉ፡፡

1. የፓርቲው ፕሬዝዳንት

2. የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት

3. የፓርቲው ጠቅላይ ጸሐፊ

19.1.3 በጠቅላላ ጉባኤ የሚሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ከየማስተባበሪያው የቀረቡትን

ሁለት ሁለት የላዕላይ ምክር ቤት እጩዎች ዝርዝር ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርባል፡፡

ጉባኤው ለእያንዳንዱ የምክር ቤት ወንበር ከሚቀርቡለት ሁለት እጩዎች አንዱን


ይመርጣል፡፡ አንዳንድ ማሰተባበሪያዎች ቀድመው ያልተደራጁ በሚሆኑበት ጊዜ

ለላዕላይ ምክር ቤት እጩ ሊያቀርቡ ካልቻሉ ለእያንዳንዱ የላዕላይ ምክር ቤት

ወንበር ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ የሚያምንባቸውን ሁለት ሁለት እጩዎች

በማቅረብ ምርጫውን በማካሄድ ምክር ቤቱ እንዲሟላ ይደረጋል፡፡

19.1.4 በጠቅላላ ጉበኤው የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ስለ እጩ አባላቱ ገለጻ

በመስጠት ድጋፍና ተቃውሞ ይጠይቃል ፡፡

19.1.5 ከየማስተባበሪያው ከተጠቆሙ እጩዎች ከፍተኛውን ድምፅ ያገጁ 25

ተመራጮች የፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ፡፡

19.1.6 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት(3) ይሆናል፡፡

19.1.7 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት መልካም የሆነ የሥራ እንቅስቃሴ መሠረት

በማድረግ የስልጣን ዘመናቸው የጨረሱ የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን ሁሉንም

ወይንም በከፊል በዕጩነት ቀርቦ በድጋሚ ለቀጣይ አንድ የሥራ ዘመን ብቻ

ሊመረጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንድ የምርጫ ዘመን አርፈው በድጋሚ እንደ አዲስ

በእጩነት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

19.2 የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት እና ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መመልመያ

መስፈርት

19.2.1 በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው፤ ሆኖም አባሉ

በመደበኛ ትምህርት ዲግሪ ባይኖረውም የተመሰከረለት ስብዕና ያለውና ለምክር

ቤቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ከታመነበት ይኸው ለጉባኤው አባላት ተገልጾ

በእጩነት ቀርቦ ሊመረጥ ይችላል፡፡

19.2.2 የፓርቲውን ዓላማ እስከ ፍጻሜው ማድረስ የሚችል፤

19.2.3 ምንም ዓይነት የስነምግባር ችግር የሌለበት፤

19.2.4 በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እና አርአያነት ያለው፤

19.2.5 አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨትና ማስተናገድ የሚችል፤

19.2.6 በዜጎች እኩልነት የሚያምን እና ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበል፤

19.3 የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር፡-

19.3.1 የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ወክሎ የፓርቲውን እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል።


19.3.2 በጠቅላላ ጉባኤ የተወሰኑ ጉዳዮች በትክክል መፈጸማቸውንና በሥራ ላይ

መዋላቸውን ይገመግማል ያረጋግጣል።

19.3.3 የፓርቲውን ዓላማ ለማስፈጸምና በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የሥራ

መመሪያዎችንና የውስጥ ደንቦችን መርምሮ ያጸድቃል አፈጻጸማቸውን

ይገመግማል ይከታተላል።

19.3.4 የፓርቲውን አባላት እንደ አስፈላጊነቱ ለመደበኛም ሆነ ለድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ

ይጠራል።

19.3.5 በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ የቀረቡለትን የፓርቲውን አርትኦት /ኤዲቶሪል/ ቦርድ

ምክትል ሰብሳቢና ፀሐፊ መርምሮ ያጸድቃል፡፡

19.3.6 በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ የቀረቡለትን የፓርቲውን የሕግ እና ሥነ ሥርዓት

ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና ፀሐፊ መርምሮ ያጸድቃል፡፡

19.3.7 በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ የቀረቡለትን የፓርቲውን የሒሳብ እና ክዋኔ ቁጥጥር

ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢና ፀሐፊ መርምሮ ያጸድቃል፡፡

19.3.8 የፓርቲውን የሒሳብ ስራዎች በውጭ ኦዲተሮች ያስመረምራል።

19.3.9 ተጠሪነታቸው ለላእላይ ምክር ቤት የሆኑ አመራሮች የሥነ ምግባር ጉድለት

የታየባቸውን ወይም የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ካልቻሉ እንዲሰናበቱና

በምትካቸው ሌሎች አመራር አባላትን ይመርጣል።

19.3.10 የፓርቲውን የወደፊት እቅድና በጀት ያጸድቃል አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ ።

19.3.11 የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚያቀርብለትን ልዩ ልዩ ቡድኖችና ቋሚ

ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ያጸድቃል ።

19.3.12 በፓርቲው ፕሮግራም ላይ በዝርዝር ለተገለጹት የፓርቲው አላማ፣ መርሆዎች እና

እሴቶች ከግብ መድረስ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ግንባር ለመፍጠር ወይም

የፖለቲካ ፓርቲዎች መቀናጀት አስፈላጊነቱን ካመነበት በላዕላይ ምክር ቤት 2/3

ድምጽ በመወሰን ተግባራዊ ማድረግ ይችላል፡፡

19.3.13 ለፓርቲው አመራር ምርጫ በጠቅላላ ጉባዔ ለሚሰየም አስመራጭ ኮሚቴ

እጩዎችን መልምሎ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እጩዎችን መልምሎ ለጠቅላላ ጉባኤ

የሚያቀርብ ኮሚቴ ይሰይማል።

19.4 የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባና ውሳኔ አሰጣጥ


19.4.1 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት መደበኛ ስብሰባ በሦስት ወር አንድ ጊዜ የሚከናወን

ሆኖ አስቸኳይ ስብሰባ የሚያስፈልግበት ምክንያት ሲኖር ልዩ ስብሰባ ሊደረግ

ይችላል፡፡ የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ አመቺ በሆነ መንገድ /በበይነ መረብ

ወይንም በአካል/ የሚከናወን ሲሆን ምክር ቤቱ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ

በአካል ተገናኝቶ ስብሰባ ያደርጋል

19.4.2 የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ እርሱ በሌለበት በምክትል

አፈ ጉባዔው ይመራል

19.4.3 አስቸኳይ ስብሰባው በአፈ ጉባዔው፣ በፕሬዝዳንቱ አሳሳቢነት ወይም ከላዕላይ

ምክር ቤት አባላት አምስት ያህል በጋራ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሊጠራ ይችላል፤

19.4.4 ከአባላቱ ውስጥ 51% ከተገኘ ምልዓተ ጉባኤው እንደተሟላ ይቆጠራል፣

19.4.5 ውሳኔዎች የሚወሰኑት በስምምነት ወይም በአብላጫ ድምጽ ይሆናል ድምጽ

እኩል ሲሆን በሰብሳቢው የሚደገፈው የውሳኔ ሃሳብ አሸናፊ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ሃያ፡- የፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ


ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔና ለላዕላይ ምክር ቤት ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል።

20.1 የፓርቲውን የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባዎችን በአፈጉባኤነት ይመራል።

20.2 በምክር ቤቱ የተወሰኑ ውሳኔዎች እና የፀደቁ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ለብሔራዊ ሥራ

አስፈፃሚው ያሳውቃል፡፡

20.3 አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የላዕላይ ምክር ቤት አመራርን ለአስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል።

20.4 የላዕላይ ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዋናው አፈ ጉባኤ ከሌለ ተክቶ የአፈጉባኤውን ሥራ

ይሰራል፤ አፈ ጉባኤው ተገኝተው የም/ቤቱን ስብሰባ ሲመራ ቃለ ጉባኤ ይይዛል፡፡

አንቀጽ ሃያ አንድ፡- የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመሠራረት፤ ተግባርና


ኃላፊነት
21.1 የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

1. ፕሬዚደንት

2. ምክትል ፕሬዚደንት

3. ጠቅላይ ጸሐፊ
4. የፋይናንስና ገቢ ማሰባሰብ /ትሬዠሪ/ ክፍል ኃላፊ

5. የፖለቲካ ትንተና ክፍል ኃላፊ

6. የሴቶችና ወጣቶች ክፍል ኃላፊ

7. የአካል ጉዳተኞች ክፍል ኃላፊ

8. የውጪ ግኙኝነት ክፍል ኃላፊ

9. የፖሊሲ፣ ምርምርና እቅድ ክፍል ኃላፊ

10. የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ

11. የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ክፍል ኃላፊ

12. የአባላት ምልመላና አደረጃጀት ክፍል ኃላፊ

13. የሥልጠና ማብቃት /አቅም ግንባታ/ ክፍል ኃላፊ

21.2 የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አመራረጥ ሥነ ሥርዓት

21.2.1 የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለየሥራ ኃላፊነታቸው በእጩነት

ከሚቀርቡ አባላት መካከል ከላይ በአንቀጽ 14.1.3 በተገለጸው መሠረት

በሚስጢር ድምፅ አሰጣጥበጠቅላላ ጉበኤ ይመረጣሉ፡፡ ለእያንዳንዱ የብሔራዊ

ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቦታ ቢያንስ ሁለት እጩዎች ለውድድር እንዲቀርቡ

ይደረጋል፡፡

21.2.2 በማንኛውም አካል የሚደረግ የእጩ ጥቆማ የተጠቋሚውን ይሁንታ ማግኘት

ይኖርበታል

21.2.3 እጩዎች በፓርቲ ኃላፊነት ቦታዎች በተደራራቢነት ሌሎች ቦታዎች ላይ እጩ

ሆነው መቅረብ አይችሉም ፡፡

21.2.4 ሁሉም የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በአስመራጭ ኮሚቴ በተዘጋጀው የድምጽ መስጫ

ወረቀት አማካኝነት በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ ድምጽ ይሰጣሉ፤ የሰጡት ድምጽ

ተቆጥሮ ውጤቱ ለጉባኤው አባላት ይፋ ይደረጋል፡፡

21.2.5 ድምጽ የመስጠትና ድምጽ ቆጠራውን የማስተባበር ኃላፊነት በጉባኤው

በተመረጡ አስመራጭ ኮሚቴ አባላት ይሆናል ፡፡

21.3 የፓርቲው መሪ

21.3.1 የፓርቲው መሪ ከፓርቲው የፓርላማ ተመራጭ አባላት መካከል በፓርቲው

የፓርላማ አባላት ይመረጣል


21.3.2 ከተመረጠ በኃላ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ይሆናል ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ጋር በመሆን ኃላፊነቶችን ይመራል

21.3.3 ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል

21.3.4 በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ፣ የካቢኔ አባላትንና ሌሎች በሹመት የሚያዙ የሚኒስቴር

መሥሪያ ቤት ሥልጣኖችን እና የመንግሥት ተጠሪዎችን ይሰይማል

21.3.5 ፓርቲው ሥልጣን ላይ ካልወጣ የፓርላማ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪ ይሆናል መሪ

ኮሆነ በኃላ ከሁለት ተከታታይ የፓርላማ ዘመን በላይ ማገልገል አይችልም

21.4 የሥራ አስፈጻሚው ተግባርና ኃላፊነት

ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔና ላዕላይ ምክር ቤት ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት

ይኖሩታል።

21.4.1 ፓርቲው በተዋረድ ባሉት መዋቅሮች የሚገኙ አመራሮች ተግባራቸውን በበቂ

ሁኔታ ማከናወናቸውን ይገመግማል፣ ያስተባብራል እንዲሁም ይከታተላል።

21.4.2 የላዕላይ ምክር ቤት ጉባኤ የሚወስነውን ውሳኔ ተግባራዊ ያደርጋል። የሥራ

አስፈፃሚ አባል የሚሆኑት መደበኛ መኖሪያቸው የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት

መቀመጫ ከተማ ወይም በተመላላሽ ለመስራት ፈቃደኛ የሆኑ እጩዎች ብቻ

ናቸው ፡፡

21.4.3 የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባላት መመልመያ መስፈርት

21.4.3.1 በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው፡፡

21.4.3.2 በተለያዩ የፓርቲው የአመራር እርከኖች ውስጥ ያለፈ፤

21.4.3.3 የፓርቲውን ዓላማ እስከ ፍጻሜው ማድረስ የሚችል፤

21.4.3.4 ምንም ዓይነት የስነምግባር ችግር የሌለበት፤

21.4.3.5 በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እና አርአያነት ያለው፤

21.4.3.6 አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨትና ማስተናገድ የሚችል፤

21.4.3.7 በዜጎች እኩልነት የሚያምን እና ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበል፤

21.4.4 በተዋረድ ላሉ መዋቅሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል የሥራ

መመሪያ ያስተላልፋል።
21.4.5 ፓርቲው በየዓመቱ የሚሠራቸውን ሥራዎች እቅድ፣የሚፈጽበትን በጀት እና

የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ገምግሞ ለላእላይ ምክር ቤት እንዲቀርብ ያደርጋል።

21.4.6 የፓርቲው የሒሳብ መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት ለተለያዩ ሥራዎች የሚውሉ

ወጪዎችን በሥራ ላይ እንዲውሉ ይፈቅዳል።

21.4.7 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ካልቻሉ

ለላዕላይ ምክር ቤት አመራር በማቅረብ በምትካቸው ሌሎች አባላት እንዲመደቡ

ያስደርጋል።

21.4.8 የፓርቲውን የቀን ተቀን ሥራ ክንውን ይመራል፣ ያስተባብራል እንዲሁም

በተቀመጠለት ሕግና ደንብ መሰረት ይወስናል።

21.4.9 የፓርቲውን ሥራ ለማጠናከር የሚያስችል እርዳታ የሚገኝበትን መንገድ

ያመቻቻል ተግባራዊነቱን ይከታተላል።

21.4.10 ለፓርቲው አላማ ተግባራዊ መሆን አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ቋሚ እና ጊዜያዊ

ሰራተኞች እንዲቀጠሩ ይወስናል፤

21.4.11 በተዋረድ ካሉ አመራሮች ጋር በየወቅቱ በሚወሰን የጊዜ ሰሌዳ ስብሰባ ያደርጋል፡፡

አንቀጽ ሀያ ኹለት፡- የፓርቲው ፕሬዝዳንት


ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔ፣ ለላዕላይ ምክር ቤት እና ለብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ የሚከተሉት

ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል።

22.1 የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል።

22.2 የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ በሊቀ መንበርነት ይመራል።

22.3 ፓርቲውን በማንኛውም ጉዳይ ይወክላል፡፡

22.4 የሥራ አስፈጻሚ እንቅስቃሴን በበላይነት ይመራል።

22.5 የጠቅላላ ጉባኤውን፣ የላዕላይ ምክር ቤት እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎችን

በፊርማው ለሚመለከታቸው ሁሉ ያስተላልፋል አፈጻጸማቸውን ይከታተላል።

22.6 የፓርቲውን አጠቃላይ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል።

22.7 አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የላዕላይ ምክር ቤት ለአስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ለምክር ቤቱ

አፈ ጉባዔ ያሳስባል።
22.8 ፕሬዚደንቱ ወይንም ጠቅላይ ፀሐፊው ከሒሳብ /ትሬዠሪ/ ክፍል ኃላፊ ጋር በጣምራ

የፓርቲውን ገንዘብ ያንቀሳቅሳሉ።

አንቀጽ ሀያ ሦስት፡- የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት


ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔ ላዕላይ ምክር ቤት እና ለሥራ አስፈጻሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና

ኃላፊነት ይኖሩታል።

23.1 የፓርቲው ፕሬዝዳንት በማይኖርበት ጊዜ የፓርቲውን ሥራዎችን ተክቶ ይሰራል።

23.2 የሥራ አስፈጻሚ የሥራ እንቅስቃሴን በቅርበት ይከታተላል።

23.3 ከፓርቲው ፕሬዝዳንት ተለይቶ የሚሰጠውን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሀያ አራት፡- የፓርቲው ጠቅላይ ጸሐፊ


ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔ ላዕላይ ምክር ቤት እና ለሥራ አስፈጻሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና

ኃላፊነት ይኖሩታል።

24.1 የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እና ሥራ አስፈጻሚ የሚወያዩባቸውን አጀንዳዎች ከፕሬዝደንቱ

ጋር በመመካከር ያዘጋጃል።

24.2 በጠቅላላ ጉባኤው እና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተላለፉትን ውሳኔዎች በቃለ ጉባኤ

አዘጋጅቶ በማስፈረም ለሚመለከታቸው ያስተላልፋል።

24.3 የጠቅላላ ጉባኤውንና የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚውን ልዩ ልዩ መዛግብትና ሰነዶችን

በጥንቃቄ ይይዛል።

24.4 የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ሙሉ ጊዜውን ለፓርቲው ሥራ በማዋል የብሔራዊ ሥራ

አስፈጻሚ አባላትን የሥራ እንቅስቃሴ በቅርበት ይከታተላል፣ ይደግፋል።

24.5 ከፓርቲው ጠቅላላ ጉበኤ፣ላዕላይ ምክር ቤት እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በውሳኔ የሚወጡ

ጉዳዮችን እያዘጋጀ ፕሬዝደንቱን በማስፈረም ወይም በማሳወቅ ለሚመለከታቸው ሁሉ

እንዲደርሱ ያደርጋል።

24.6 የፓርቲውን የደብዳቤ ልውውጦችን ያከናውናል፤ የጽ/ቤት ሰነዶችን እና ማህተም በሥርዓት

መያዛቸውን መጠበቃቸውን ያረጋግጣል።

24.7 የፓርቲውን ጽ/ቤት ያደራጃል፤ በኃላፊነት ይመራል ሌሎች ጽ/ቤቶች እንዲደራጁ ያደርጋል።

24.8 በመደበኛነት ሊቀጠሩ የሚችሉ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች እንዲቀጠሩ በእጩነት ለሥራ አስፈጻሚ

ያቀርባል።
24.9 የመደበኛ ሠራተኞችን የእለት ተእለት ሥራ ይከታተላል።

24.10 ሥራ አስፈጻሚ በሰጠው የስራ መመሪያ መሰረት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን

እንዲያገኙ ያስደርጋል።

24.11 የመደበኛ ሠራተኞች ሙሉ መረጃዎችን አጠናቅሮ ይይዛል።

24.12 ሠራተኞች ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል፤ በሥራ አስፈጻሚ

አስወስኖ ተግባራዊ ያደርጋል።

24.13 በፓርቲው የውስጥ ደንብ መሠረት መደበኛ ሠራተኞች የሥራ ክፍተት ከተገኘባቸው

አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል።

24.14 ሌሎች ከፓርቲው ጽ/ቤት የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል።

አንቀጽ ሀያ አምስት፡- የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

25.1 የተሠሩ ወይም ሊሰሩ የታሰቡ ሥራዎችን በሥራ አስፈፃሚው ለሕዝብ እንዲገለጽ ሲፈለግ

የፓርቲው የአሠራር ደንብ በሚያስቀምጠው መሠረት ከመረጃና ግንኑነት ቴክኖሎጂ

አገልግሎት ጋር በመሆን የተለያዩ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶችን በመጠቀም ያሳውቃል፡፡

25.2 ፓርቲው አቋም በያዘባቸው ጉዳዮች ላይ በመገናኛ ብዙኃን አካላት አስቸኳይ መረጃ ሲጠየቅ

ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፡፡

25.3 የፓርቲውን የአቋም መግለጫዎች፣ የድምጽ፣የድምጽና ምስል እና የጹሑፍ ሥራዎችን

አዘጋጅቶ ለሕዝብ እና ለአባላት ከመቅረባቸው በፊት በአርትኦት ቦርድ ተስተካክለው

እንዲወጡ ያደርጋል።

25.4 ከፓርቲው የፖለቲካ ትንተና ክፍል ኃላፊ እና የውጭ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ጋር በቅርበት

ይሠራል።

25.5 የፓርቲውን የፕሬስ መግለጫዎችን ፕሬስ ኮንፍረሶችን ያዘጋጃል ያስተባብራል ፓርቲውን

በመወከል በሌሎች ዝግጅቶች ላይም ይገኛል።

25.6 ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳን የሚመለከቱ እንቅስቃሴዎችን ያቅዳል።

25.7 ፓርቲው የሚያከናውናቸውን ልዩ ልዩ ተግባራትን ለሕዝብ ያሳውቃል።

25.8 የፓርቲውን ልሳን ዘጋጃል


25.9 በፓርቲው ድረ ገጽ እና ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚለቀቁ ማንኛውም ጉዳዮች

በፓርቲው አርትኦት ቦርድ ተገምግመው ያለፉትን ብቻ ይለቃል።

25.10 የቅስቀሳ ሥነ ጹሑፎች፣ ጋዜጦች ፣በራሪ ወረቀቶች ፣ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ወዘተ አዘጋጅቶ

እና በአርትኦት ቦርድ አሳርሞ ለሕዝብ እንዲሰራጩ ያደርጋል።

25.11 የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ክፍልን በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

25.12 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሀያ ስድስት፡- የፓርቲው የአባላት ምልመላና አደረጃጀት ክፍል ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

26.1 በሀገሪቱ ያሉትን አጠቃላይ አባላትን ያደራጃል ፣ፕሮፋይላቸውን ይይዛል።

26.2 አዳዲስ አባላትን ወደ ድርጅቱ መልምሎ በእጩነት ለሥራ አስፈጻሚ ያቀርባል።

26.3 ድርጅቱ ባዋቀረው መዋቅር መሠረት በተላያዩ ቦታዎች ያሉትን አባላት መረጃ ያጠናቅራል።

26.4 በተዋረድ ባሉ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታምኖበት ሙሉ አባል እንዲሆን የተመለመለን አባል

መረጃ ይይዛል።

26.5 ከአባላት በኩል የሚደርሱ መረጃዎችን ለሥራ አስፈጻሚ በሰዓቱ ያቀርባል፡፡

26.6 አባላት እና እጩ አባላት የአባልነት ድርጅታዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን ይከታተላል፡፡

26.7 የእለት ተእለት የክፍሉን ሥራዎችን ይከታተላል፣ ይገመግማል እንዲሁም የእርምት

አቅጣጫ ይሰጣል።

26.8 ከአቅሙ በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ያቀርባል እንዲሁም አፈጻጸሙን

ይከታተላል።

26.9 አባላት የፓርቲውን የሥነ ሥርዓት እና የሥነ ምግባር መመሪያዎች እንዲተገብሩ ያደርጋል።

26.10 የፓርቲውን ሕዝባዊ ስብሰባዎች ያስተባብራል አባላትና ተሳታፊዎች እንዲገኙ ያደርጋል።

26.11 በምርጫ ምልመላ ወቅት ከምርጫ አስተባባሪ ጋር በመሆን ተገቢውን የአባላት መረጃ

ያጠናቅራል።

26.12 የአባላትን ደኅንነት እና የሥራ እንቅስቃሴን ለመከታተል የሚያስችሉ መዋቅሮችን ይዘረጋል፡፡

26.13 የፓርቲውን የአባላት ምልመላና አደረጃጀት ክፍል በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

26.14 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡


አንቀጽ ሀያ ሰባት፡- የፓርቲው የፖለቲካ ትንተና ክፍል ኃላፊ፡-
ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

27.1 ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ፖለቲካና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ላይ በአትኩሮት ይሠራል።

27.2 አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ዘርፍ ረቂቅ ሀሳቦችን ይቀምራል እንዲሁም ለሥራ አመራር

ለውይይት ያቀርባል።

27.3 ማንኛውንም ድርጅቱን ሊገዳደሩ የሚችሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከፖለቲካ አንጻር ይተነትናል

እንዲሁም ከሚመለከታቸው የፓርቲው አመራር ጋር በመሆን ምላሽ ይሰጣል።

27.4 ፖለቲካ ነክ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ተንትኖ ለድርጅቱ ያቀርባል፡፡

27.5 በፕሬዝዳንቱ እውቅና ድርጅቱን ወክሎ ማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ

ስብሰባዎችን ይካፈላል ።

27.6 የፓርቲውን ውስጠ ድርጅታዊ ባሕል ረቂቅ ፖሊሲ ይቀርጻል።

27.7 ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲደረግ ለፖሊስ ምርምርና ዕቅድ ሃሳብ

ያቀርባል

27.8 ከጥናት እና ምርምር ጋር የተያያዙ የፓርቲውን ሰነዶችን ያደራጃል።

27.9 ብቃትና ጥራት ያላቸውን የፓርቲ አባላትን በአወያይነት በመመልመል እንዲሁም በምርጫ

አካባቢዎች የፓርቲ እጩዎች በምርጫ መድረክ ላይ በስፋት በማወያየት የፓርቲውን

ሕዝባዊ ተቀባይነት ያጠናክራል።

27.10 ፓርቲውና የፓርቲው ፕሮግራም በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ከፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት

(ቃል አቀባይ) እና ከመረጃና የግኑኝነት ቴክኖሎጂ አገልግሎት ጋር በጋራ ይሰራል።

27.11 በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲው መዋቅሮች የሚገኙ አባላት የውይይትና የጥናት ቡድኖችን

እንዲኖራቸውና ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖራቸው ሥርዓት ይዘረጋል የመተግበሪያ ፖሊሲዎችን

ያዘጋጃል።

27.12 የፓርቲውን ሥልታዊ እቅድና የምርጫ ማኒፌስቶ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር

ያዘጋጃል፡፡

27.13 የፖለቲካ ትንተና ክፍልን በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

27.14 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡


አንቀጽ ሀያ ስምንት ፡- የውጭ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ
ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

28.1 ፓርቲው ከውጭ አገር ደጋፊዎቹ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በሚመለከት በአትኩሮት

ይሰራል፡፡

28.2 የሀገራችን ጂኦፖለቴካል ጉዳዮችን በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት

ይከታተላል፤ ለሥራ አስፈፃሚ መረጃ ይሰጣል።

28.3 የፓርቲውን የውጭ ፖሊሲ መረጃዎችን ያሰባስባል፡፡

28.4 ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ አባላትን ጉዳይ ይከታተላል በሚገኙባቸው አካባቢዎች

እንዲደራጁ ያደርጋል ፓርቲውን እንዲደግፉ ያደርጋል።

28.5 ከተለያዩ መንግሥታዊ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዲፈጠር

ያደርጋል ስለ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጥያደርጋል።

28.6 የሀገር ውስጥ የፓርቲውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በውጭ ሀገር ለሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች

ያሳውቃል።

28.7 በውጭ አገራት ባሉ የፓርቲው መዋቅሮች የሚገኙ አባላትን የውይይት እና የጥናት ቡድኖች

እንዲኖራቸውና ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖራቸው ሥርዓት ይዘረጋል የመተግበሪያ ፖሊሲዎችን

ያዘጋጃል፡፡

28.8 የውጪ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴን /ክፍልን/ ቻፕተሮችን በሰብሳቢነት

ይመራል ።

28.9 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሀያ ዘጠኝ ፡- የፓርቲው የሴቶችና ወጣቶች ክፍል ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

29.1 ፓርቲው ሴቶችን በሚመለከት ሊሰራቸው የሚገቡ ሥራዎችን ያቅዳል ተግባራዊነታቸውን

ይከታተላል፡፡

29.2 የፓርቲው ሴት አባላትን ለከፍተኛ አመራርነት ለማብቃት ሥራዎችን ይሰራል፡፡

29.3 ፓርቲው ሴት አባላት እንዲኖሩት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፡

29.4 ፓርቲው ህፃናት እና ወጣቶችን በሚመለከት ሊሰራቸው የሚገቡ ሥራዎችን ያቅዳል

ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል፡ ፡
29.5 ፓርቲው ወጣት አባላትን ለከፍተኛ አመራርነት ለማብቃት ሥራዎችን ይሰራል፡፡

29.6 ፓርቲው ወጣት አባላት እንዲኖሩት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፡

29.7 የፓርቲው ሴት አባላትን ለከፍተኛ አመራርነት ለማብቃት ሥራዎችን ይሰራል፡፡

29.8 ፓርቲው ሴት አባላት እንዲኖሩት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፡፡

29.9 ህፃናት እና ወጣቶችን በሚመለከት ሊሰራቸው የሚገቡ ሥራዎችን ያቅዳል

ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል፡፡

29.10 ወጣት አባላትን ለከፍተኛ አመራርነት ለማብቃት ሥራዎችን ይሰራል፡፡ ፓርቲው ወጣት

አባላት እንዲኖሩት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፡፡

29.11 ክፍሉን በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

29.12 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሰላሣ ፡- የፓርቲው የፋይናንስና ገቢ ማሰባሰብክፍል ኃላፊ (ትሬዠረር)፡-


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

30.1 የፓርቲውን ማንኛውንም ሒሳብ ነክ ጉዳዮችን ገቢና ወጪ ይቆጣጠራል፡፡

30.2 ከፕሬዝዳንቱ ወይንም ከጠቅላይ ጸሐፊ ጋር በመሆን የተከፈተውን ሒሳብ ያንቀሳቅሳል

በሁሉም ወጪዎች ላይ ይፈርማል፡፡

30.3 የፓርቲውን ረቂቅ በጀት ያዘጋጃል የበጀት አጠቃቀምን ይከታተላል።

30.4 አጠቃላይ የፓርቲውን የወጪ እና የገቢ ሒሳብ ሒደት ሪፖርት በየወቅቱ አዘጋጅቶ

ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚና ለሚመለከታቸው ያቀርባል።

30.5 የፓርቲውን አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት ለላዕላይ ምክር ቤት ያቀርባል።

30.6 የፓርቲውን ፋይናስ እና ንብረት በአግባቡ መጠበቁንና ሥራ ላይ መዋሉን ይከታተላል።

30.7 የፓርቲውን ሰነዶች በማንኛውም ጊዜ ለኦዲት ሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋል።

30.8 የፓርቲውን የፋይናስ ሥራዎች መመሪያ አዘጋጅቶ ለላዕላይ ም/ቤት በማቅረብ አፀድቆ

በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል።

30.9 የድርጅቱን ገንዘብ በሓላፊነት ይይዛል፣ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሲታዘዝ ወጪ

ያደርጋል፡፡

30.10 ከአባላት ወርኃዊ አስተዋጽዖ ክፍያን ይሰበስባል የአሰባሰብ ሥርዓት ይዘረጋል።


30.11 ከበጎ አድራጊዎች እና ፓርቲውን ከሚደግፉ አካላት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በገቢ

መሰብሰቢያ ደረሰኝ ገቢ ያደርጋል።

30.12 የፓርቲው የፋይናንስ አቅም እንዲጎለብት ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን ይቀይሳል

በሥራ አስፈፃሚው ሲፀድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

30.13 እለታዊውን ገቢን አቅራቢያው በሚገኝ ባንክ በየዕለቱ በድርጅቱ በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር

ገቢ ያደርጋል።

30.14 በመደበኛነት ሊቀጠሩ የሚችሉ ልዩ ልዩ ባለሙዎችን እንዲቀጠሩ በእጩነት ለሥራ አስፈጻሚ

ያቀርባል።

30.15 ማንኛውንም ሒሳብ ነክ ጉዳዮችን ገቢና ወጪ ይቆጣጠራል፡

30.16 የሂሣብ ክፍል በሰብሳቢነት ይመራል።

30.17 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሰለሣ አንድ ፡- የፓርቲው ፖሊሲ፣ ምርምርና እቅድ ክፍል ሓላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

31.1 ለፓርቲው ፖሊሲ ምርምር ስራ የሚሆኑ መረጃዎችን ያሰባስባል፣

31.2 በፓርቲው ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲዎች ላይ ጥናትና ምርምር ያካሂዳል፣ሰነዶች ያዘጋጃል፡

31.3 ፓርቲው ሲያሸንፍ በሀገሪቱ የሚተገብረው የተለያዩ ፖሊሲዎችን ያዘጋጃል፣ለላይ ላይ

ምክር ቤት እንዲቀርብ ለሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ያስገባል ።

31.4 የፓርቲውን የተለያዩ ደንብና መመሪያዎችን ያዘጋጃል ለሥራ አመራር ያቀርባል።

31.5 ልዩ ልዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ

የተሻሉ ሀሳቦች እንዲተገበሩ ለሥራ አስፈጻሚ ያቀርባል።

31.6 የፓርቲውን የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ፣ ስልትና ስትራቴጂ በማዘጋጀት በስራ አስፈጻሚ

ኮሚቴው እንዲፀድቅ ያደርጋል፤ ተፈፃሚነቱንም ይከታተላል፣

31.7 በፓርቲ እንቅስቃሴና የትግል ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ

ሁኔታዎችን በመለየትና በክብደታቸውም ቅደም ተከተል በማስቀመጥ የተለያዩ ስልቶችና

አቅጣጫዎችን ይቀይሳል፣

31.8 የተለያዩ አለማቀፋዊ፣ አካባቢያዊና አገራዊ ሁኔታዎችን የኃይል አሰላለፎችን በመገምገም

በፓርቲ እንቅስቃሴና የትግል ውጤት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ ይተነትናል፤


ፓርቲው ራሱን በገንዘብ፣በሰው ኃይልና በቁሳቁስ የሚያጠናክርበትን እንዲሁም የትግል

አድማሱን ማስፋፋት የሚችልበትን ስልትና ስትራቴጂ ይቀይሳል፣

31.9 የፓርቲውን የየሩብ ዓመቱ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያዘጋጃል ግብረ መልስ ይሰጣል

31.10 የፓርቲውን የሩብ ዓመት እና ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሥራ አስፈጻሚ

ያቀርባል

31.11 የፓርቲውን የሥራ አስፈጻሚ እቅድ ክትትልና ግምገማ ያደርጋል

31.12 የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አሰፈጻሚ ዓመታዊ እቅድ እንዲያቅዱ አስፈላጊውን ድጋፍ

ያደርጋል ።

31.13 የፓርቲውን የአምስት ዓመት ሥልታዊ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ

ያደርጋል ሥልጠና ይሰጣል።

31.14 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሠላሣ ኹለት፡- የፓርቲው የመረጃና የግኑኝነት ቴክኖሎጂ አገልግሎት ኃላፊ፡-


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባራት ያከናውናል

32.1 የፓርቲውን ኢሜይል፤ ድረገጽ (ዌብ ሳይትና) ማኅበራዊ ሚዲዎችን በመክፈት እና

ደኅንነታቸውን በመጠበቅ ያስተዳድራል፡፡

32.2 ከተለያዩ ከታመኑ የመገናኛ ብዙኃን ምንጮች ላይ የሚገኙ ጠቃሚ የጽሑፍና የድምጽ

መረጃዎችን ለሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ የሚደርስበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

32.3 የፓርቲውን የመረጃ መረብ ዝርጋታ (Instalation)፣ የሶፍት ዌር ዲዛይን ያዘጋጃል፤

የመረጃ መጠባበቂያዎች (Back up) እንዲኖር ያደርጋል።

32.4 የመረጃ መረብ ተጠቃሚ የሆኑ የፓርቲው አካላት አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ

የአጠቃቀም ማኑዋሎችን እና ስልጠናዎችን በመቅረጽ ያሰለጥናል።

32.5 የመረጃ መረቡን መተግበሪያ ቁልፍ ከፓርቲው ጽ/ቤት ጋር በመሆን ይቆጣጠራል ።

32.6 የመረጃ ማዕከል ያቋቁማል፣

32.7 የፓርቲውን የመረጃ እና የግንኙነት ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

32.8 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሠላሳ ሦስት፡- የአካል ጉዳተኞች ክፍል ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል።
33.1 አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞችን በሚመለከት ሥራዎችን ያቅዳል ተፈፃሚነታቸውን

ይከታተላል፡፡

33.2 የአካል ጉዳተኞችን ጉዳዮችን በሚመለከት ፖሊሲዎችን እስትራቴጂ እና ዓመታዊ ዕቅዶችን

ከፖሊሲ ጥናትና ዕቅድ ክፍል ጋር በመሆን ያዘጋጃል፡

33.3 አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የፓርቲውን ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች (ሥራዎች) ከደጋፊ

አካላት በጀት በማፈላለግ ስራዎችን ይሰራል፡፡

33.4 አካል ጉዳተኞች የፓርቲው አባል እንዲሆኑ ያሳልጣል ፡፡

33.5 በመዋቅሩ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የተመጣጠነ እንዲሆን አመቺ ሁኔታዎችን

እንዲፈጠሩ ያደርጋል።

33.6 በፓርቲው አባላት ላይ የሚደርስባቸውን ማኅበራዊ ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉበትን

መንገድ ይቀይሳል በትኩረት ይከታተላል።

33.7 በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ እየደረሰ ያለውን አስተዳደራዊ ችግሮችን ይመረምራል ለስራ

አስፈጻሚው ያቀርባል

33.8 አካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት የፓርቲው የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ ሁነው

እንዲቀርቡ ይሰራል

33.9 የአካል ጉዳተኞች ክፍልን በሰብሳቢነት ይመራል፡፡

33.10 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሠላሳ አራት፡- የሥልጠና ማብቃት /አቅም ግንባታ/ክፍል ኃላፊ


ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል።

34.1 የአጭር እና የረጅም ጊዜ የሥልጠና ጉዳዮችን ይለያል፣ ለሚመለከተዉ ክፍል ያቀርባል፤

ያጸድቃል፣ ይተገብራል።

34.2 የሥልጠና ፖሊሲ፣ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን እንዲሁም የሥልጠና ማንዋሎችን ያዘጋጃል

የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን ይሰጣል እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

34.3 የሥልጠናው ማኅበረሰባዊ ለዉጥ/በጎ ተጽእኖ/ ዳሰሳ ያደርጋል፣ በውጤቱ መሠረት ማሻሻያ

እና እርምት ይወስዳል

34.4 ለትምህርት እና ሥልጠና አጋር የሚሆኑ ተቋማትን ግለሰቦችን በመለየት በዘላቂነት አብሮ

መሥራት የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፡፡


34.5 የአመራሩን አቅም ሊያጎለብቱ የሚችሉ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ የትምህርት እድሎችን

ያመቻቻል

34.6 የፓርቲው አባላት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው

የሚያስችሉ የተለያዩ የስልጠናና የአቅም ግንባታ ስልቶችን ይቀይሳል፤ በሥራ አስፈጻሚ

ኮሚቴው ሲፈቀድም ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

34.7 የክፍሉ አጠቃላይ የሥራ ሂደት ያቅዳል፣ አፈጻጸሙን በበላይነት ይመራል።

34.8 ሌሎች በፕሬዚደንቱ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

አንቀጽ ሠላሳ አምስት፡- የማስተባበሪያ ምክር /ቤት ሓላፊነት፣ ውሳኔ አሰጣጥ እና ተጠሪነት
የማስተባበሪያ ምክር ቤት በሥሩ ካሉ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የፓርቲው ቅርንጫፍ

ጽ/ቤቶች /ከእያንዳንዳቸው አንድ ሰው/ በሚወከሉ አባላት የሚመሠረትና የማስተባበሪያውን

ሥራ በላይነት አቅጣጫ የሚመራ አካል ሲሆን በሚከተለው መልኩ ይደራጃል ሥራውንም

ያከናውናል፡፡

35.1 የማስተባበሪያውን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ እና ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የማስተባበሪያ ሥራ

አስፈጻሚ አባላት፣ የኦዲት ክፍል ሓላፊ እና የሕግ ክፍል ሓላፊን ይመርጣል፡፡

35.2 በፓርቲው የተወሰኑትን እና አቋም የተያዘባቸውን ጉዳዮች በትክክል መፈጸማቸውንና

በሥራ ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል።

35.3 የማስተባበሪያ ዓመታዊ የሥራ እና የበጀት እቅድ ያጸድቃል።

35.4 የማስተባበሪያውን ሥራ አስፈጻሚ አሠራር ይከታተላል፡፡

35.5 የፓርቲው ስልታዊ እቅድ በተያዘለት ጊዜና አኳኋን በሥሩ ባሉ ወረዳዎች መተግበራቸውን

ይከታተላል፡፡

35.6 ሪፖርት አድምጦ አስፈላጊ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡

35.7 የአሠራር መዛነፎችና የግልጽነት ችግሮች ሲያጋጥሙት ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚው ጽ/ቤት

ጋር በመገናኘት ሊፈታ ይችላል፡፡

35.8 ከላይ በአንቀጽ 33.7 ከተገለጸው በመለስ ያሉ የአሠራር ግንኙነቶችን በማስተባበሪያ ጽ/ቤት

በኩል ያስፈጻማል፡፡

35.9 በዓመት ኹለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡ አስቸኳይ ጉባኤ ቢያስፈልገው ሊጠራ ይችላል፡፡


35.10 በማስተባበሪያው ሥር ያሉ የማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ፣ የወረዳ/ከተማ ቅ/ጽ ቤት

አመራሮች ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸውን ወይም የተጣለባቸውን ሓላፊነት

መወጣት ያልቻሉትን በማሰናበት በምትካቸው ሌሎች አመራር አባላትን ይመርጣል።

35.11 የማስተባበሪያውን የሒሳብ እንቅስቃሴ ኦዲት ያደርጋል፡፡

አንቀጽ ሠላሳ ስድስት ፡- የፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት


36.1 የፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት የሚባሉት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የሙያ ማኅበራት ክንፍ፣ የባለ

ሀብቶች ክንፍ፣ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ፣የሕዝብ ተመራጭ ሸንጎ እና የአማካሪዎች ሸንጎ

እና ሌሎችም እንደ አስፈላጊነቱ የሚቋቋሙ ናቸው፡፡

36.2 የሚቋቋሙበት ዝርዝር የአደረጃጀትና የአሠራር ሰነድ በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው

ተዘጋጅቶ በላዕላይ ምክር ቤት ሲጸድቅ ተግባራዊ ይደረጋል።

አንቀጽ ሠላሳ ስባት ፡- የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት


ፓርቲው ማስተባበሪያዎች፣ የወረዳ/ የከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና መሠረታዊ ድርጅት ይኖሩታል፡፡

የፓርቲ መሠረታዊ ድርጅት እንደ አግባብነቱ የከተማ አስተዳደር ሥር ያለ ከሆነ ለከተማው ካልሆነ

ለሚገኝበት ወረዳ ተጠሪ ይሆናል፡፡ የወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በበኩሉ ተጠሪነቱ ከበላዩ ላለው

ማስተባበሪያ ይሆናል፡፡ ማስተባበሪያዎች ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ እና ለማስተባበሪያው ምክር ቤት

ተጠሪ ይሆናሉ፡፡ በሥዕላዊ አገላለጽ ለመግለጽ ቀጣዩን ሥዕል መመልከት ይቻላል፡፡


ሥዕል 1. የእናት ፓርቲ አወቃቀር

ጠቅላላ ጉባዔ

ላዕላይ ምክር ቤት

ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ

የማስተባበሪያ ምክር ቤት ማስተባበሪያ

የወረዳ/ከተማ ቅርንጫፍ
ጽ/ቤት

መሠረታዊ ማኅበር

አንቀጽ ሠላሳ ስምንት፡- የፓርቲው መሰረታዊ ድርጅት


የፓርቲው መሠረታዊ ድርጅቶች በአባላት የሥራና የመኖሪያ ቦታ የሚደራጁ ሲሆን፣ በቀበሌ፣

በወረዳ እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ እንዲሁም አስፈላጊ ሆነ በተገኘበት ደረጃ ይቋቋማሉ።


የአደረጃጀት የአሰራር ሰነድ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ በላዕላይ ምክር ቤት ሲጸድቅ

ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

አንቀጽ ሠላሳ ዘጠኝ ፡- የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባና ውሳኔ አሰጣጥ


39.1 የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የስብሰባ ጊዜ ቢያንስ በአስራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ

ይሆናል፡፡ ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኮሚቴው ልዩ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ

ይችላል፡፡

39.2 ከአመራር አካላቱ 51 በመቶ ከተገኙ መደበኛ ስብሰባው ሊካሔድ ይችላል።

39.3 የፓርቲው ማስተባበሪያ፣ የወረዳ/የከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስብሰባ ስነ ሥርዓቶች

በፓርቲው የውስጥ መመሪያ ይወሰናል።

39.4 ውሳኔዎች በስምምነት ወይም በአብላጫ ድምጽ የሚወሰኑ ሲሆን ድምጽ እኩል ሲሆን

በሰብሳቢው የሚደገፈው ሃሳብ አሸናፊ ይሆናል፡፡

ክፍል አምስት ሌሎች ድንጋጌዎች

አንቀጽ አርባ፡- ፓርቲው ከሌላ ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ቅንጅት ወይም ግንባር


ስለሚፈጥርበት ሂደቶች
40.1 ፓርቲው የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት የሚያስችለው መሆኑን ካመነበት ከሌላ

ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ቅንጅት ወይም ግንባር መፍጠር ይችላል፤

40.2 ፓርቲው ከሌላ ፓርቲ ጋር ውህደት ለመፍጠር በቅድሚያ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው

አብላጫ ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ በመቀጠል በላእላይ ምክር ቤት 2/3 ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ

እና በጠቅላላ ጉባኤ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ከተቻለ ብቻ ይሆናል፡፡

አንቀጽ አርባ አንድ፡- የፓርቲው አባላት ለአገር አቀፍና በየደረጃው ላሉ አገራዊ ምርጫዎች
የሚታጩበት ሥርዓት
41.1 ፓርቲው ለአገር አቀፍ እና በየደረጃው ላሉ አገራዊ ምርጫዎች እጩዎችን የምርጫ ክልሉ

ከሚገኝበት የፓርቲው መዋቅር ከሚገኙ አባላት በጥቆማ ይቀበላል፡፡ የተጠቋሚዎች መረጃ

እዚያው ባለ መዋቅር ሥራ አመራር ተመርምሮ ተገቢ እና ለቦታው ብቁ ሆነው ከተገኙ

ከትምህርት፣ የሥራ ልምድ እና ግላዊ ባሕርያት መግለጫ ጋር ለብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ


ተልኮ በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ሲፀድቅ አግባብ ባለው መንገድ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

41.2 የሕዝብን ጥያቄና ኃላፊነት እና የፓርቲውን አላማ ከግብ ማድረስ የሚችሉትን በመምረጥ

በመወዳደሪያው ጣቢያ አባላት እና ደጋፊ አካላት ጋር በሚደረግ ምክክር ከፓርቲው አባላት

ለቦታው የሚመጥነውን አባል በማስመረጥ ይሆናል፡፡

አንቀጽ አርባ ኹለት፡- የፓርቲው የፋይናንስ ሥርዓት


42.1 የፓርቲው የፋይናንስ ስርዓት የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በሚያወጣው እና ላዕላይ

ምክር ቤት በሚያፀድቀውው መመሪያ መሰረት የሚተዳደር ይሆናል፤

42.2 ፓርቲው የተሟሉና ትክክለኛ የሒሳብ መዛግብት ይይዛል፣ በውጭ ኦዲተር በየዓመቱ

ያስመረምራል፡፡

አንቀጽ አርባ ሦስት፡- የፓርቲው የሰው ሀብት አስተዳደር ስርዓት

የፓርቲው የሰው ሀብት አስተዳደር ስርዓት የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በሚያወጣው እና ላዕላይ

ምክር ቤት በሚያፀድቀውው መመሪያ መሰረት የሚተዳደር ይሆናል፤

አንቀጽ አርባ አራት፡- የፓርቲው የኦዲት ስርዓት


44.1 የፓርቲው የኦዲት ስርዓት የፓርቲው የሒሳብና ክዋኔ ቁጥጥር ኮሚሽን በሚያዘጋጀው እና

የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት በሚያፀድቀው መመሪያ መሠረት የሚተዳደር ይሆናል፤

44.2 የኦዲት ሪፖርቱ ለጠቅላላ ጉባኤ አባላት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

አንቀጽ አርባ አምስት፡- የፓርቲው አቅርቦት እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት


የፓርቲው የገንዘብና ንብረት አስተዳደር ስርዓት የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በሚያወጣው

እና ላዕላይ ምክር ቤት በሚያፀድቀውው መመሪያ መሰረት የሚተዳደር ይሆናል፤

አንቀጽ አርባ ስድስት፡- የፓርቲው የገንዘብ ማስገኛ አሰራር


የፓርቲው የፋይናንስ ምንጮች ከአባላት መዋጮ፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከፓርቲው ደጋፊዎች እና

ወዳጆች ከሚገኝ ድጋፍ እንዲሁም መንግሥት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት ለፖለቲካ

ፓርቲዎች ከሚያደርገው ድጋፍ ይሆናል።


አንቀጽ አርባ ሰባት፡- የፓርቲው ውስጥ አለመግባባቶች አፈታት ሥርዓትና የሥነ ሥርኣት
እርምጃ አወሳሰድ
47.1 በፓርቲው አካላት ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዚህ ደንብ ውስጥ በተደነገጉ

የአሰራር ሥርዓት ማለትም በቅድሚያ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይቀርባሉ በሥራ አስፈጻሚ

ኮሚቴ የማይወሰን ከሆነ ለላዕላይ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡

47.2 በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (1) መሰረት መፍታት ካልተቻለ በአገሪቱ የምርጫ፣ የፖለቲካ

ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግና በሌሎች ሕጎች መሰረት ይፈታል፡፡

አንቀጽ አርባ ስምንት፡- የፓርቲ መፍረስ


48.1 የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት ፓርቲው እንዲፈርስ በሁለት ሦስተኛ (2/3) ድምጽ ውሳኔ

ካስተላለፈ እና ውሳኔው ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ በተመሳሳይ ሁለት ሦስተኛ (2/3) ድምፅ

ከፀደቀ ፓርቲው እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡

48.2 በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት በምርጫ ቦርድ ወይም በፍርድ ቤት እንዲፈርስ ውሳኔ

ከተላለፈበት፡፡

አንቀጽ አርባ ዘጠኝ፡- ስለ ፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሻሻል


49.1. ይህ መተዳደሪያ ደንብ የሚሻሻለው ወይም የሚቀየረው በፓርቲው የጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል ፡፡

49.2 የመተዳደሪያ ደንቡ የማሻሻያ ሃሳብ ሊቀርብ የሚችለው በላዕላይ ምክር ቤት 1/3 ድምጽ

ድጋፍ ሲያገኝ እና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አብላጫ ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡

49.3 በዚህ መሠረት በላዕላይ ምክር ቤት የቀረበውን የማሻሻያ ሀሳብ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ

በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ሊሻሻል ወይም ሊቀየር ይችላል።

አንቀጽ ሃምሳ፡- የመተዳደሪያ ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ


ይህ የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ በፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ከጸደቀበት ከየካቲት 26 ቀን 2015

ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።

2015 ዓ.ም

You might also like