You are on page 1of 12

ለመሆኑ ፈተና ምንድን ነው?

ሃይማኖት ስለእግዚአብሔር ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሚሰበሰቡበት ጉባኤ ወይም ድርጅት ሳይሆን

ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖራቸው ሕይወት ነው። ይህንን ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ስለምንተነፍሰው አየር ካለን

እውቀት ጋር በማነጻጸር በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ሰዎችን በሕይወት የሚያኖራቸው ስለኦክስጅን ያላቸው

ዕውቀት ተመሳሳይ ሆኖ በዚያ ዙሪያ መሰባሰባቸው ሳይሆን በየራሳችው አቅም እና ሁኔታ ወደ ውሳጣቸው

የሚያስገቡት ኦክስጅን ነው። ይህን ወደ ውስጥ የምንተነፍሰውን አየር ኦክስጂን ይባል አይባል የማያውቁ ሰዎች

ይኖራሉ። አለማወቃቸው ግን እንዳይተነፍሱት እና በሕይወት እንዳይኖሩ አልከለከላቸውም። ልክ እንዲሁ

ሃይማኖት የሚባለውም ስለእግዚአብሔር ያለን ዕውቀቱ ሳይሆን እንደ ኦክስጅኑ ወደ ራሳችን የምናስገባው

እግዚአብሔር ወይም ከእርሱ ጋር ያለን ሕይወቱ ነው።

ኦክስጅን መውሰድ የማይችል ወይም የመተንፈስ ችግር የገጠመው ሰው ማለት በሕይወት የመኖር ችግር የገጠመው

ማለት ነው። ታዲያ መተንፈስ ችግር የገጠመውን ሐኪሞች ረድተውት ወደ ጤንነት ተመልሶ ያለ ችግር

መውሰዱን ካልቀጠለ በሕይወት መኖር እንደማይችለው ሁሉ ሰዎችም እግዚአብሔርን በሕይወታችን ውስጥ

ማኖር ካልቻልን በእግዚአብሔር ዘንድ ሙታን እንሆናለን። ምንም ያህል ስለሃይማኖት ዕውቀት ቢኖረንም ዕውቀቱ

ሕይወት ሊሆነን አይችልም። በዚህ ጊዜ በሥጋ ብንኖርም ጠባያችን ፣ ምግባራችን፣ ሕይወታችን በአጠቃላይ

ለዐለም እና ለሰይጣን ይጋለጣል። ከጸናም ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል።

በእንዲህ ያለው ጊዜ ስሙን ብንጠራም አንሰማም ይሆናል። አንዳንድ ሃይማኖታዊ ተግባራትንም ብንፈጽም

የምንፈልገውን ላናገኝ እንችላለን። በዚህ ምክንያት ደግሞ እንታወካለን። ባዶነት ይሰማናል። ጥያቄዎች

ይፈጠሩብናል፣ እንረበሻለን፣ ብዙ ነገሮች ይፈራረቁብናል። ከዚህ ነጽተን እና ተላቅቀን የምንፈልገውን ወይም

የምንመኘውን ማለት በቅዱሳን እንደተገለጠ እና እንደታየ የምናምነውንና የምናውቀውን ዓይነት ሕይወት ለመኖር

ብንፈልግም አይሳካልንም። መጥፎ ነው ብለን የተራዳነውን ጠባያችንን ወይም ያጎሳቆለንን መጥፎ ድርጊታችንን

ወይም የተረዳነውን ውድቀታችንንም ሆነ ያልተረዳነውን ትተን ነጽተን ተቀድሰን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር

ስነነሣም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ተመልሰን ከነበርንበት ወድቀን ራሳችንን እናገኘዋለን። ለዚህ ዐይነት መከራ አሳልፈ

የሰጡን ደግሞ ፈተናዎቻችን ወይም እኩያት ፍትወታት (ክፉ ክፉ ፍላጎቶቻችን) ናቸው። እንዚህን በአግባቡ

ተረድተን ታግለን ከእነርሱ ከተላቀቅን የምንመኘውን ሕይወት ለመኖር እንችላለን።

በርግጥ ፈተና የሚባለው ግን ምንድን ነው?

ነጻ ለመውጣት የምንችለው መጀመሪያ እነዚህን እኩያት ፍትወታት እና ፈተናዎችን ( passions) ምን እንደሆኑ፣

ዋና ዋናዎቹንም ለይተን ስናውቃቸው ነው። ያን ጊዜ እንዴት መታገል እና ማስወጣት እንደምንችልም ለመረዳት

ይቻለናልና ማንነታቸውን ከማየት እንጀምር።


ፍትወታት እኩያት ወይም በተለምዶ ፈተናዎቻችን የምንላቸው ከየት ነው የሚመጡት? ከኃጢአት ጋር ያላቸው

አንድነት እና ልዩነትስ ምንድን ነው ከሚል እንነሣ።

ፈተናዎች ወይም ክፉ ፍላጎቶች መነሻቸው ስሜት ነው። በተለይም ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ የምንወዳቸው

እና የማንወዳቸው ነገሮች ለእነዚህ ክፉ ክፉ ፍላጎቶች ዋና መብቀያዎች ናቸው። ስሜታችን ደግሞ ከባሕርያችን

ወይም ከሰውነታችን የሚመነጭ ስለሆነ ስሜት አልባ ልንሆን አንችልም። ስሜትም በራሱ ችግር አይደለም። ችግር

ወደ መሆን የሚያድገው ስሜታችንን የምንረዳበት እና እርሱን የምናሳድገበት፣ የምንገራበት ወይም አቅጣጫ

የምንሰጥበት መንገድ ላይ ነው። ለምሳሌ እስካልበላን ድረስ የረሀብ ስሜት አይቀሬ ነው። ከሰውነታችን ጋር በጥብቅ

የተሳሰረ ነውና። ወይም ሥጋችን ያለ ምግብ እንዳይኖር ሆኖ የተፈጠረ ነውና። ሆኖም የረሀብ ስሜታችንን

የምንቆጣጠርበት፣ ምግብም ካገኘን በኋላ የምንበላበት መንገድ ፈተናን ወይም ቅድስናን ሊያስከትል ይችላል

ማለት ነው።

እንዲያውም አንድ ሰው ይህን በተመለከተ ሲናገር ይህ ነገር እንደቤት እንስሳት ልንወስደው እንችላለን ይላል።

ለምሳሌ ያህል ያሁን ዘመን ውሾችን ብናያቸው ሁኔታቸው ባለቤታቸው እንዳሰለጠናቸው ነው። ባለቤቱ በአግባቡ

እየተንከባከበ እና እንዲለምዱለት እና እንዲያውቁለት የፈለገውን በተገቢው መንገድ እያስለመደ ያሳደጋቸው

ውሾች በተፈለጉ ጊዜ ያን የለመዱትን አገልግሎት ለሰዎቹ ይሰጣሉ። ከዚያም ውጭ ሕይወት አይኖራቸውም፣

እንዲያ እንዲሆኑ ተደርገው ተቀርጸዋል ወይም ሰልጥነዋልና። ከዚያ በተቃራኒው ካደጉ ደግሞ ባለቤታቸውን

ሳይቀር የሚነክሱ አውሬዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ፈተናዎች ወይም ክፉ ክፉ ፍላጎቶች ማለት ስሜቶቻችን

በአግባቡ ሳንገራ እና ሳናስተካክል በእኛ ውስጥ በማሳደጋችን ምክንያት ራሳችንን እንዲበሉን ወይም እንዲጎዱን

ያደረግናቸው ስሜቶቻችን ወይም ተፈጥሮአዊ ማንነቶቻችን ናቸው ማለት ነው። ይህም ማለት አውቀንም ይሁን

ሳናውቅ ራሳችንን በማስለመድ ለራሳችን ከሠራነው ሰብእና የሚመነጩ ፍላጎቶች እንጂ ከሌላ ቦታ ወይም ከከባቢ

አየር ላይ እንደ ባክቴሪያ እና ቫይረስ የተጣበቁብን ተሐዋስያን አይደሉም ማለት ነው። ስለዚህ ካውቅን በኋላ ሁሉ

ቶሎ ለማስለቀቅ የምንቸገረው ሳናውቅ በውስጣችን እንዲያ እንዲሆኑ አድረገን ካሳደግናቸው በኋላ

የተለማመዱትን አስትተን ሌላ ሳናስለምዳቸው እኛ የምንፈልገውን እንዲሆኑ በመፈለጋችን ምክንያት የተፈጠረ

ችግር ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ልክ በእኛ ሀገር ያለን ሌባ እንዲጠብቅ ተብሎ አንዲት ትንሽዬ ሳጥን መሰል

ክፍል ውስጥ ተዘግቶበት ሰው ሳይለምድና እና ሥልጠና ሳያገኝ የኖረን ውሻ በገመድ እየጎተቱ ወስዶ የተቀበረ ድራግ

ፈልግ እንደማለት ያለ የሞኝ ድርጊት ነው እየፈጸምን ያለነው እንደማለት ነው።

ፈተናዎቻችን ለስሜቶቻችን በምንሰጠው መልስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ያልነውም የምንሰጠው ተግባራዊ ምላሽ

የሚፈጥረውን እንድናውቅ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ምግብ ባማረው ሁሉ ጊዜ እየቀያየረ ፣ እያማረጠ፣

እያጣጠመ እስኪጠግብ እየበላ እና እየጠጣ ሰብአዊ ስሜቶችን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዴት ይችላል? በልቶ ጠጥቶ

መጸዳጃ ቤት ሳይሔድ ሊቀር እንደማይችለው ሁሉ የበላው የጠጣው ነገር በውስጣዊ ማንነቱም ላይ ቀጥተኛ

ተጽእኖ ያመጣበታል። ወደ ውጭ እንደወጣው ሁሉ ወደ ውስጥም የሚሔድ አለና። ስለዚህ አመጋገቡን መቆጣጠር


ሳይጀምር እና ስለዚያም በአግባቡ ሳያስብ ምግቡ የሚያመጣውን ትኩሳት ለመቆጣጠር አይችልም ማለት ነው።

ለዚያም ነው ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ጾምን የነገር ሁሉ መጀመሪያ ያደረገው። ነገሮች ሁሉ ሊጀምሩ የሚችሉት

ራስን ከመግዛት ፣ ስሜትን ከመቆጣጠር እና ነገሮችን በአግባቡ ከመረዳት መሆኑን ለማስተማር ነውና የጾመው።

በጾሙ መጨረሻን ምን ምን ፈተናዎችን ድል እንደነሣበት አንረሳውምና።

ስለዚህ ፍትወታት እኩያት ማለት እኛው ስሜቶቻችንን በአግባቡ ሳንቆጣጠር እና ከእግዚአብሔር ጋር ላለን

ሕይወት እንዲረዱን አድርገን ሳንቀርጽ እኛው ውስጥ ያሳደኛቸው ልማዶች ማለት ናቸው። እነዚህ ልማዶች

አድገው ሲቆጣጠሩን እና ስንደጋግማቸው ደግሞ ፈተናዎች ይባላሉ። ፈተና ደረጃ ከደረሱ በኋላ ደግሞ እኛ

እነርሱን መቆጣጠር አቁመን እነርሱ እኛን መቆጣጠር ይጀምራሉ ማለት ነው። መውጣት እየፈለግን የሚያቅተን

በዚህ ጊዜ ነው። እየቆዩ ሲሔዱ ደግሞ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ገዢዎቻችን ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ “ሰው

ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና” /1 ኛ ጴጥ 2 ፤ 19/ ሲል ቅዱስ ጴጥሮስ የገለጸው ባርነት በሕይወታችን

ይደርሳል ።

በዚህ ጊዜ ነገሮች ሁሉ እጂግ ከባድ ይሆናሉ። በሁለት መንገድ ሊከብዱብን ይችላሉ። አንደኛው እና በጣም

መጥፎው እኛ የምናደርጋቸው ሁሉ ተፈጥሮአዊ እና ትክክል እስኪመስለን በቁጥጥር ውስጥ ስለሚያደርጉን ችግሩ

የሌሎች ሰዎች እንጂ የራሳችን አይመስለንም። ሌላው ቀርቶ መንፈሳዊ ነገሮችን እንኳ የምንቀበለው ለእኛ ስሜት

ሲስማሙን ብቻ ይሆናል። ልክ ልብስ ምግብ እና የመሳሰሉት ላይ ለስሜታችን ባላቸው ተስማሚነት (ቴስታችን)

ተከትለን እንደምንከተለው ለዚህኛውም እውነቱ ሳይሆን ለእኛ የማይስቡን እና ከቴስታችን የማይሔዱ ሁሉ ችግሩ

የእነርሱ እንጂ የእኛ እንደሆነ አይታየንም። ለምሳሌ ያህል የመዝሙር ምርጫዎቻችን ውስጣችን በተገነባው

የሙዚቃ ቴስት ላይ በጥብቅ የተመሠረተ ይሆናል። ለዚህም ነው የከተማ ልጆች እና የገጠር ልጆች የመዝሙር

ምርጫችን ሳይቀር የሚለያየው። አንዳንድ ኦርቶዶክሶች የፕሮቴታንቶችን ድለቃ የሚወድዱት በትትክክልነቱ

ሳይሆን ለራሳቸው ሰሜት እናፍላጎት በመስማማቱ ነውና። ይህኛው ስሜት ግን ከዚህም የከፋ ብዙ ችግሮች አሉት

። የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎች፣ ሥርዓቶች ሁሉ ከእኛ ፍላጎት እና ከዘመኑ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙ እንድንፈለግ

ያደርገናል እንጂ እኛን ከሕጉ እና ከሥርዓቱ ጋር ለማስማማት አይፈቅድልንም። ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን

ሰዎች ኋላቀር እና የማይገባቸው አድረገን እንድንወስድ ውስጣችንን ያሳምነዋል እንጂ እኛ የራቅን እና በችግር

ውስጥ መኖራችንን እንድናይ ፈጽሞ አይፈቅድልንም።

ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ችግሮቹን የእኛ መሆናቸውን እናውቃለን። ኃጢአቱን ከሠራነው በኋላ ራሳችን

እስከመጥላት ድረስ እንደርሳለን። እንዲያውም እንዳንዴ በራሳችን ከማዘናችን የተነሣ ራሳችንን እስከመጥላት

አንዳንዴም ተስፋ ቆርጠን ራሳችንን ምንም የማንጠቅም አድርገን በማሰብ የባሰ ክፉ እንድናስብ ሁሉ ያደርገናል።

እንደምንም ከዚህ ስሜት እንደተላቀቅን ወዲያ ልንቆጣጠረው በማንችለው ስሜት ውስጥ እንገባና ያንኑ

የምንጠላውን እና ራሳችንን ለመጥላት የሚገፋንን ድርጊት አሁንም ሳናስበው እናደርገዋለን። አንዳንድ መንፈሳዊ

ምክሮችንን ሰምተን ሌላም ሌላም ሞክረን የተሻለን ይመስለን እና አሁንም እንደገና ራሳችንን እዚያው ድርጊት
ውስጥ እናገኘዋለን። ሰውነታችን ለምዶታልና ሳናስበው እስኪመረን ድረስ ደጋግመን እዛው ቦታ እንገኛለን።

ትክክለኛው ፈተና ማለት ይህ ነው። ስለዚህ ፈተና ማለት ራሳችን ውስጥ ያለውን ስሜት በአግባቡ ካለመግራት

የተነሣ የተፈጠረ ክፉ ተግባር ተደጋግሞ ከመደረጉ የተነሣ በእኛ ላይ ሥልጣን እስኪኖረው ድረስ ሲደርስ ማለት

ነው። ለዚህ ነው ከባድ የሚሆነው። ክብደቱን ደግሞ “ልማድ ከሰይጣን ይከፋል” በሚለው አባባላችን ሳይቀር

እናውቀዋለን። በሕይወት ውስጥ ልማድ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነገር ነው። መጥፎ ልማድ ከሆነ እጂግ ይጎዳናል።

ጥሩ ልማድ ከሆነ ደግሞ እጂግ ይጠቅመናልና።

ታዲያ እንዲህ ያለው የመጥፎ ልማድ ድርጊት አንድ እና ተመሳሳይ አይደለም። እጅግ ብዙ ዐይነት ነው። በአንድ

ሰውም በርከት ያሉ መጥፎ ልማዶች ወይም ፈተናዎች ሊኖሩበት ይችላሉ። ሆኖም ብዙ በሽታዎች ጭንቅ ውስጥ

የከተቱን በሽተኛ ብልህ ሐኪም ከየትኛው መጀመር እንዳለበት በአግባቡ አጥንቶ እና መርምሮ በመጀመር ቀስ በቀስ

ወደ ጤንነቱ እንደሚመልሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወትም የሚደረገው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ

በሽታዎች ዋናውን እና ለሌሎች ምክንያት የሆነውን ስንታከም እንደሚጠፉት ሁሉ በዚህም ተመሳሳይ ነው።

አንዳንድ ፈተናዎችን ማስወገድ ስንችል ሌሎቹም አብረው ይጠፋሉ። እንዲህ ከሆነ ዋና ዋና ፈተናዎች የሚባሉት

የትኞች ናቸው? መፍትሔዎቻቸውስ ምን ምን ናቸው? ይቀጥላል።

የ ፍትዎቶቻችን ዐይነቶች

(ካለፈው የቀጠለ)

በመጀመሪያ ደረጃ ፈተናዎቻችን ወይም ፍትወቶቻችን በሁለት ይከፈላሉ። ተፈጥሮአዊ የሆኑ እና ያልሆኑ

ተብለው። ተፈጥሮአዊ የሚባሉት ከምግብ ጋር በተገናኘ ያለው ሆዳምነት (እንደ ስስት ፣ መጎምጀት፣ ምግብን

የማጣጣም እና የመብላት ፍላጎት ሁሉ በዚህ ሥር ይካተታሉ)፣ ፍርሐት፣ እና ሐዘን እንደሆኑ የነገረ መልኮት

መምህራን ይገልጻሉ። እነዚህ ነገሮች በተፈጥሮ ከእኛ ጋር ያሉ፣ ፈጽሞ ልናስወግዳቸው የማንችላቸው ብቻ

ሳይሆን በአግባቡ ጥቅም ላይ እስከዋሉ ድረስ ለባሕርያችንም አስፈላጊ ናቸው። አስፈላጊነታቸውን እና

ጠቀሜታቸውን በዐራቱ ባሕርያተ ሥጋ (መሬት፣ ውኃ፣ ነፋስ እና እሳት) አንጻር ልናየው እንችላለን። ለምሳሌ

ባሕርየ እሳትን ወይም ሙቀትን ብናየው እርሱ የሌለው ሕይወት ያለው ሰው ሊኖር አይችልም። ይህን ያክል

መሠረታዊ ነው። ሆኖም ከመጠኑ ሲወርድ ስንቀዘቅዝ ወይም ሲያልፍ ስንቃጠል በሁለቱም ጊዜ ጽኑ በሽታ

መሆኑን እናውቃለን። ከላይ የጠቀስናቸው ተፈጥሮአዊ ያልናቸው ሦስቱም እንዲሁ ናቸው።

ለምሳሌ ያለ ምግብ እና ያለ ምግብ ፍላጎት መኖር አይቻልም። ነገር ግን የሰውነታችን ሙቀቱ ሲጨምር

አእምሮአችንን እንደሚያስተን ሁሉ ሰውነታችን ለርኩሰት አሳልፎ የሚሰጠው ዋናው መግቢያው ምግብ እና


አመጋገብ ነው። ስለዚህ እያነሣን ያለነው ጉዳይ የመብላትን ነገር በአጠቃላይ ሳይሆን የሆዳምነትን ጉዳይ ነው

ማለት ነው። መጀመሪያ ላይ እንዳልነው እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ቅድስና የሌለው ሰው

ከእግዚአብሔር ጋር መኖር አይችልም። ለዚህ አስፈላጊው ንጽሕናን አጽንቶ ለመያዝ ያለን አማራጭ

ሆዳምነትን መታገል ይሆናል ማለት ነው። ንጽሕናችንን አጥፍቶ ሰውነታችንን የሚያረክሰው ነፍሳችን

የሚያሳድፋት የመጀመሪያው ነገር ሆዳምነት መሆኑ ተደጋግሞ የተረጋገጠ ነው። ሆዳምነት ማለት ስለምግብ

ከመጠን በላይ በመጨነቅ ለመኖር ወይም ለመሥራት ከሚያስፈልገን በላይ መመገብን ፣ ጣዕም አማርጦ

ለማጣጣም ብዙ መጨነቅን ፣ ለምግብ መሳሳትን ፣ መጎምጀትን ሁሉ የሚመለከት ነው። ይህ ጉዳይ እንኳን

የአልኮል መጠጥን የፍራፍሬ ጭማቂዎችንና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ መቼም አይዘነጋም

ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ስለዚህ በአጠቃላይ የምግብ ነገር አንዳንዶቻችን ላናስተውለው እንችላለን እንጂ ሌሎች ጉዳዮች ባላነሰ ሱስ

ይሆናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ብዙ ነገር ውስጥ የሚከትተን ሰዎች አለን። ሆዱን ያልተቆጣጠረ አብዛኛዎቹ

ሰውነታችንን የሚያረክሱ ነገሮች በሙሉ ይቆጣጠሩታል። ከዚህ የተነሣ በአንዳንዶችን ዝሙት ይሰለጥናል፤

በሌሎቻን ደግሞ ተሳዳቢነት፣ ልበ ደንዳናነት፣ ትምክህተኝነት፣ ሰው ናቂነት፣ ተሳዳቢነት፣ በተለይም ደግሞ

ተደባዳቢነት እና ገዳይነት ሁሉ ከዚህ ይበቅላሉ። ከሆዳምነት ወይም ከስስታምነት ጋር በተገናኘ ብዙ ጣጣዎች

ስላሉ ነው እኔም ከፍርሐት እና ከሐዘን ይልቅ ትኩረት ሰጥቼ ያብራራሁት ። የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል

የሚባለው አባባላችንም የጉዳዩን ትልቅነት የሚያስታውስ ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አባታችን

አዳም የወደቀው ያው ለበለሲቱ በመጎምጀት እና ብሎም በመብላት መሆኑን አንረሳውም ጌታችንም በገዳመ

ቆሮንቶስ ስለእኛ ሲጾም ሰይጣን ካቀረበለት ሦስት ፈተናዎች መካከል ሁለቱ ለምግብ ስስት ለመፍጠር እና

ለዚህ ዓለም ሀብት መጎምጀትን ለማስጎምጀት በመጣር ነበር። ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና

ጌታችን እነዚህን ድል ፈተናዎች በጾም እና በትእግሥት ድል ብንነሣው ሰይጣንን በማንኛውም ነገር ድል

መንሣት እንደምንችል ለማስተማርም ጭምር ነበር በዚያ መንገድ ድል ያደረገልን። ለዚህ ነው በቤተ

ክርስቲያናችንም ሆነ በእውነተኞች ክርስቲያኖች ዘንድ ጾም ትልቅ ልጓም ሆኖ የሚያገለግለው።

ሆኖም ሆዳምነት ከተቆጣጠረን ብንጾም እንኳ ተጨንቀን የፍስክ ምግብ የሚያስንቅ የጾም ምግብ እንድንበላ

ያደርገናል። ስለዚህ ሆዳምነት መሠረታዊ ፍትወት መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ሆኖም በሚያስፈልገን

በተመጋቢነታችን በኩል የመጣ ስለሆነ ወይም ያንን ያለአግባብ ለጥጦ መውሰድ ያመጣው ጉዳይ ስለሆነ

ተፈጥሮአዊ ነው ይባል እንጂ ሆዳምነትን ወይም ፈሪነትን ወይም ሐዘንተኝነት እግዚአብሔር ፈጥሮብናል

ማለት አይደለም። ይልቁንም ልክ አረም ሳይዘራ እንደሚበቅለው ከአዳም ውድቀት በኋላ ከውስጣችን

ከባሕርያችን በቅለው የተገኙ ናቸው ለማለት ነው።


በአጭሩ እነዚህ ተፈጥሮአዊ የሚባሉት የሰው እንሥሣዊ ባሕርይ መገለጫዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም

ማለት የሰውነታችን ሙቀት በተገቢው መጠን ሲሆን ምንም ችግር እንደሌለው ሁሉ እነዚህንም በመጠናችን

እና በአስፈላጊነታቸው ልክ ብቻ ከተጠቀምንባቸው በራሳቸው ችግሮች አይሆኑም ማለት ነው። ከመጠናቸው

ሲለዋወጡ ግን ወይ ወደ ጥሩ ወይም ወደ መጥፎ ይወስዱናል ማለት ነው። ለምሳሌ እየጾመ እና እየጸለየ

የምግብን ጉዳይ ወደ መንፈሳዊ ምግብና መሻት እየለወጠው እርካታውንም ከዚህ ዓለም ምግብ ይልቅ ወደ

መንፈሳዊ ምግብ መፈለግ እያሳደገው ቢሔድ ባሕርዩን ከሰውነት ወደ መልአክነት እየለወጠው ሊሔድ

ይችላል። በአንጻሩ እርካታውን ከምግብእና ከዚህ ዓለም ነገር ብቻ እየፈለገ በበላው እና በጠጣው፣ በለበሰው

ባጌጠው፣ በገዛው በነዳው እየተመሰጠ እየረካ ስለዚያም እያሰበ ወይም ትልቅ ቦታ እየሰጠ ሲሔድ በውስጡ

ያለው እንስሳዊነት ወደ አውሬነት እየተቀየረ ይሔዳል። ለዚህም ነው ጥጋበኛ ሰው የሰው መዋረድ ይቅርና

ሞቱ እንኳ የማይገድደው ወደ መሆን የሚደርሰው። የሌሎቹን የሁለቱንም በዚሁ መንገድ እንረዳው እና ወደ

ሌሎቹ ልለፍ።

ተፈጥሮአዊ ያልሆኑ የሚባሉት ደግሞ ተፈጥሮአዊ የሆኑትን በመጥፎ አቅጣጫ ስንጠቀም እነዚያ ወደ

እነዚህኞቹ ይለወጣሉ። ይለውጧቸዋል ማለትም ሰው ዘላለማዊ ሆኖ ለመኖር የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን

እነዚህ ፍላጎቶቻችን ሲሰለጥኑ ነፍሳችን ላይ ወሰን ወደ ሌለው ወይም በቃኝ ወደማንለው ፍላጎት ይለወጣሉ።

ይህም ማለት ከስስት ወደ ስግብግብነት ማለትም ርካታ አግኝተን በቃን ወደማንልበት ስሜት ይለወጣሉ። ይህ

ነው እንግዲህ ሰዎች በሀብት ላይ ሀብት ቢያገኙ ወይም በሥልጣን ላይ ሥልጣን ወይም ቢጠጡ ቢጠጡ እና

ቢሰክሩ፣ በዝሙትም ቢሆን በምንም ያህል ሰው የማይረኩ በምንም ነገር ላይ በቃኝ ማለት የማያውቁ

ወደመሆን ስለሚለወጡ ነው። ከዚህ የተነሣ ጥቅማችን፣ ክብራችን የተነካ የሚመስለን በቀላሉ ነው፣

የምንቆጣው በቀላሉ ነው። ለማንኛውም ኃጢአት እና ግብር በቀላሉ እንጋለጣለን። ከዚያም እነዚህ ሁሉ

ድርጊቶች በብዙ መንገድ ሰውነታችንን ያረክሱታል። ከላይ በሆዳምነት እንዳየነው ሆዳምነትን ተከትለው

ዝሙት፣ ስካር፣ ጸብ ክርክር፣ ... ይመጣሉ እንዳልነው ፍርሕትን ተከትለው ገና የሆነ ነገር ሊያደርጉብኝ ነው

በማለት እጅግ በርካታ ኃጢአቶችን እንሠራለን። በሐዘንተኝነትም ስሜት ውስጥ ጥላቻው፣ በቀሉ፣ ዘረኝነቱ፣

... ብዙ ኮተቶች ይወርሱናል። እነዚህ ከተፈጥሯችን ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባይኖራቸውም፣ ነገር ግን

ተለውጠው እና እነዚያን በር አድርገው ከገቡ በኋላ ሰውነታችንን በመቆጣጠር ለራሳቸው ተገዢዎች

የሚያደርጉን ጉዳዮች ናቸው። እግዚአብሔር ነጻ ያውጣን ፤ አሜን። ይቀጥላል።


የምንመኘውን ዓይነት ክርስቲያን ለመሆን
ከፍትወታት ለመዳን ልናደርገው የሚገባን ምንድን ነው? (የመጨረሻው ክፍል)

በክርስትና ሕይወት ውስጥ በጣም መጥፎ ኃጢአት የሚባለው ተስፋ መቁረጥ ነው። ሰይጣን ተረባርቦ ብዙ ነገር

ካሠራን በኋላ ራሳችንን እንድንጠላ እና በራሳችን ተስፋ ቆርጠን በቃ ለውጥ ማምጣል አልችልም፣ የማልረባ ሰው
ነኝ፣ መኖሬ ትርጉም የለውም፣ እግዚአብሔር እኔን አይምረኝም ዓይነት ሀሳቦችን ወደ ኅሊና ውስጥ እያስገባ ተስፋ

ለማስቆረጥ ይታገላል። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታመነ ተስፋ እና ወሰን የሌለው አዛኝ ሆኖ

እያለ አንተም (አንቺማ) ይቅር አትባሉም እያለ ይወተውተናል። ነገር ግን ጌታችን የታመነ ተስፋ፣ ሳይክፋ

የሚወድድ ፍጹም ፍቅር፣ ይቅር ለማለትም ትንሽ ምክንያት የሚፈልግ በቃላት ሊገለጽ የማይችል መሐሪ ነው።

እኛም ቢሆን ኃጢአተኝነት፣ ጎስቋላነት እና የመሳሰለው በተሰማን ጊዜ በራሳችን ላይ ተስፋ መቁረጥ ወይም ራስን

መጥላት የለብንም። ይልቁንም ደግሞ ለምሕረት እና ለዕርቅ ጥረት በምናደርግበት ወይም ንስሐ በምንገባበት

ጊዜም ቢሆን ሰውነታችን መጉዳት አይጠበቅብንም። አባ ቦይመን (ጴሜን) “እኛ ፍትወቶቻችንን እንጂ

ሰውነታችን እንድንገድል አልተማርንም” እንዳለው ማተኮር ያለብን ፍትወቶቻችን ላይ መሆን አለበት ። ስለዚህም

ከፍትወቶቻችን ለመላቀቅ ልናደርጋቸው የሚገባንን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው በአጭሩ

እንመለክታቸዋለን።

1) ራስን ማወቅ
ከሁሉ በፊት አስፈላጊው ነገር ይህ ነው። በሽታውን ያላወቀ ሐኪም ማከም እንደማይችለው ሁሉ አንድ

ክርስቲያንም የነፍሱን በሽታዎች ወይም ደግሞ ፍትወቶቹን እና መነሻ ምክንያቶቹን ማወቅ በጣም አስፈላጊ

ነው። ለምሳሌ በዝሙት የተቸገረ እና በሐሰት ወይም በቁጣ የሚቸገሩ ሰዎች ከእነዚህ ከእያንዳንዳቸው ጋር

አብረው ሊያውቋቸው የሚገቧቸው ነገሮች ይኖራሉ። በምን ምክን ያት በተደጋጋሚ የምፈጽመው፣ ወደዚህ ጉዳይ

የሚመሩኝ ነገሮች ምን ምን ናቸው? ... የመሳሰሉትን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እንደማንኛውም

ሕክምና የነፍስ ድኅነትም የራስን ድክመቶች በተገቢው መጠን ከማወቅ ነው። ቀደም ብዬ የፍተወት ዓይነቶችን እና

ሁኔታዎቻቸውን እጅግ በትንሹም ቢሆን ለማቅረብ የሞከርሁት ራሳችንን ለማወቅ እንዲረዳን በማሰብ ነው።

ለምሳሌ ዝሙትን የሚገፉት ምክንያቶች አንደኛው እና ዋናው ደስታን መፈለግ ነው። ይህን የሚያባብሰው እና

እንደ ነዳጅ የሚያቀጣጥለው ደግሞ አመጋገብ ነው። ከእነዚህ ቀጥሎ ደግሞ የምናያቸው እና የምንሰማቸው ነገሮች

(በፊልም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በመሳሰሉት) በአሁኑ ጊዜ ወሲብ ቀስቃሽ የሆነ እጅግ ብዙ ይዘቶች ይሰራጫሉ።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ውሎአችን (ለምሳሌ ለፈተናው ከሚዳርገን አካል ጋር በተደጋጋሚ ብቻን መገናኘት)

የመሳሰሉት በደንብ መታወቅ ያለባቸው ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው ስሜቱን የሚያነሳስቱትን በሙሉ ባወቀ እና

ከእነዛ ጋር በተገናኘ ትክክለኛ ውሳኔዎችን በወሰነ ቁጥር ወደ ፈውስ እና ድኅነት ለመሔድ ቀላል ይሆንለታል።

ለሁሉም ፈተናዎቻችን በዚህ መንገድ ራሳችንን መፈተሽ እና ጉድለታችንን ማወቅ አስፈላጊ ነው። በተለይ ደግሞ

ልክ በላብራቶሪ እገዛ እንደሚታወቁ የጤና ችግሮች በነፍስም በጣም ድብቅ እና በቀላሉ እንዳሉብን የማናውቃቸው

አደገኛ ድከመቶች አሉብን። ሥጋዊ ደስታን መፈለግ፣ ትዕቢት፣ ምቀኝነት ከንቱ ወዳሴን መሻት፣ መጎምጀት ከነዚህ

ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። ስለዚህ ራስን በአግባቡ በተለይም ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበ ራሱን የሚመረምር

ሰው ማለት አልትራ ሳውንድ፣ ሲቲ እስካን እና የመሳሰሉትን ተጠቅሞ በውስጥ የሰውነቱ አካል ያሉ ቁስለቶችን
ጉዳቶችን እንደሚያስፈልግ ታካሚ ብዙ ደኅና የሚመስሉ ችግሮቹን ለመመልከት ይቻለዋል። በሽታውን ማወቅ

ደግሞ ለድኅነታችን ምን ያህል ፈውስ እንደሆነ የታወቀ ነው።

ይህ ራስን ማወቅ ማጠቃለያው ደግሞ ንስሐ እና ጸጸት ነው። በደልን እያሰቡ ከልብ ጌታን እንደበደሉት ማሰብ እና

መናዘዝ እጂግ አስፈላጊው ነገር ነው። ንስሐችን እና ኑዛዜያችንም ከተለመደው ሪፖርት የማድረግ አካሔድ የራቀ

ነገር ግን ከውስጥ ስሜት በሚመነጭ ሁኔታ ሆኖ አምላክን መለመን መሆን ይገባዋል። ይህም ማለት ኃጢአተኝነትን

እና ደካማነትን ከልብ ተቀሎ በፊቱ ራስን በንስሐ ዝቅ ማድረኝ ይይዛል ማለት ነው። ስለዚህ ንስሐ መነሻው ራስን

በአግባቡ ማወቅ ስለሆነ በዚሁ ውስጥ የተካተተ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።

2) እምነት
ሌላው በጣም አስፈላጊ ነገር እምነት ነው። ምንም ያህል ደካሞች ብንሆን የጌታችንን ሰውን ወዳጅነት፣ ስለእኛ

ብሎ ያን ሁሉ መከራ በሥጋ መቀበሉን፣ ይቅር ባይ እና ድኅነታችን የሚሻ መሆኑን እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ

ሊምረን ሊረዳን የሚችል መሆኑን ማመን አስፈላጊ ነው። ስንጸልይ እንደሚሰማን ማመን በጣም አስፈላጊ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ ወይም ስንሰማ ጌታችን የፈወሳቸው ብዙዎቹ ሰዎች ከፍተኛ ኃጢአትን የሰሩ እና ብዙ

ድካም የነበረባቸው ናቸው። ሰባት አጋንንት ያወጣላት መግደላዊት ማርያምን፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት

ኖሮ ያዳናትን፣ እና የመሳሰሉትን ብንመለክት ጌታ ለማንም ሰው ምን ያህል አዛኝ እና ፈዋሽ እንደሆነ እንረዳለን።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉንም የፈወሳቸው እና ኃጢአታቸውን ይቅር ያላቸው ስለእምነታቸው እንጂ

ስለምግባራቸው አልነበረም። እምነትህ አድኖሃል፣ እምነትሽ አድኖሻል፣ እንደ እምነትህ ይሁንልህ፣ እንደ እምነትሽ

ይሁንልሽ የሚሉት ቃላት ሁሉ የሚያመለክቱት ዋናው ነገር እምነት መሆኑን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ አምኖ

መሔድ ያስፈልጋል። አምኖ ወደ ጌታችን ቀርቦም እርዳታውን ሳያገኝ የቀረ አንድም ሰው ኖሮ አያውቅም።

የሚያስምር ምግባር አለኝ የሚል ሰውም ሊኖር አይችልም። እንደዚያ የሚል ካለ ከትዕቢትም እጂግ በከባዱ

ትዕቢት የተያዘ ነው ማለት ነው።

3) ተስፋ
ተስፋ ሰይጣንን ከሚያሸሹት ነገሮች አንዱ ነው። ሲጀመር ተስፋ የሚደረገው ራሱ ጌታችን ስለሆነ በተለይም

በወንጌል ትርጓሜያችን ላይ ሊቃውንት ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ እያሉ ደጋግመው እንደሚገልጹት እርሱ ይቅር

ይለኛል፣ ይረዳኛል የሚል ተስፋ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው። ስለዚህ አንድ ድርጊት እየጠላነው ማቆም ባንችል እንኳ

ጌታችን እንደሚረዳን እና አንድ ቀን ከዚያ ነጻ እንደምንወጣ ተስፋ መያዝ ለምንመኘው ነጻነት የሚያበቃ ታላቅ

ጉልበት ነው።

4) መንፈሳዊ ምግባራትን እንደየአግባቡ መፈጸም


ከዚህ ቀጥሎ ልናደርጋቸው የሚገቡን እንደፈተናዎቻችን ወይም ፍትወቶቻችን የሚለያዩ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም

ዋናዋናዎቹን በአጭር በአጭሩ ለመጠቆም ልሞክር።

ሀ) ጾም
ጾምና ጸሎት አስፈላጊነታቸው የታወቀ ነው። ቢሆንም ደግሞ ጉልበታቸው ምን ያህል ብርቱ እንደሆነ ደጋግሞ

ማስታወሱ አሁንም አስፈላጊ ነው። ጌታችን ጾሞ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውዕ ድል መንሣት እንደሚቻል በተግባር

አሳይቶናል። እነዚያ ደግሞ በጣም መሠረታዊ ፍትወታት ናቸው። ስለዚህ አንድ ሰው ይጹም ሲባል በሕግ

የታዘዙትን ብቻ አይደለም። በዝሙት፣ በትዕቢት፣ በልበ ደነዳናነት እና በመሳስለው ኅሊናው የጨለመ ሁሉ ወደ

ብርሃን ብልጭታ ብቅ ሊል ከሚችልባቸው ሕክምናዎች አንዱና ዋናው ጾም ነው። ከበዓለ ኃምሳ በቀር መጾም

ይቻላል። ያም ባይሆን በተመቸ ሁኔታ ላይ ሁሉ በራስ ላይ ሆእነ ብሎ የምግብ ፍላጎት ላይ ማዕቀብ መጣል፣

ምርጫን ውሱን ማድረግ፣ የምንመገበውን መጠኑን መቀነስ እና የመሳሰሉት በጣም ጠቃሚ ነገሮች ናቸው።

ለመጾም የማያስችል በሽታ ያለበት ሰው ደግሞ ሌሎቹን ሁኔታዎች በጥብቅ መፈጸም ሊበቃው ይችላል።

ለ) ጸሎት

ጸሎት እንደ አየር ሳንተነፍሰው ልንውልና ልናድር የማንችለው ነገር መሆኑ የታወቀ ነው። ስለዚህ እንደ ክርስቲያን

ጸሎት እንደምንጸልይ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከፍትወታት ለመላቀቅ ለየት ያሉ ጸሎቶች ያስፈልጋሉ።

የሚያስፈልጉት ጸሎቶች አጫጭር እና በቃል የሚያዙ ሆነው ልክ ኅሊናችን ውስጥ የሆነ ነገር ሲርመሰመስ ኅሊናን

መልሶ በቃል ደጋግሞ የሚጸልዩት ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነት ጸሎቶች ሥራ እየሠራንም ሆነ ሰው

ቤት ውስጥ ሆነን ወይም ሌላ ሥራ ላይ እያለን ልንጸልያቸው የምንችላቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ኦ እግዚእየ

ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ሥረይ ኩሎ ኃጢአትየ” ፟ ‘የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ

ክርስቶስ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር በለኝ” የሚሉ ጸሎቶች በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። እንዲህ ያሉ ጸሎቶች

የሚያስቸግረንን ፍትወት በመጥራት ከዚህ ነጻ አውጣኝ በማለት መጸለይን ያጠቃልላል። በተለይም ደግሞ ከዳዊት

መዝሙር ውስጥ ለፈተናችን መድኃኒትነት የሚስማሙትን በማምጣት ማለትም “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ”

፣ በቁጣህ አትቅሰፈኝ፣ የመሳሰሉትን ደጋግሞ መጸለይ ተገቢ ነው። የተመረጡ የዳዊት መዝሙሮችን እና የሰባቱን

ቀን (በቅርብ ጊዜ በመምህር ተስፋሚካኤለ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተተረጎመውን ሰፊውን) ውዳሴ አምላክን

መጸለይ ለማንም ሰው የምመክረው ነገር ነው። ይህን የጸሎት መጽሐፍ የሚጠቀም ሰው በግሉም እንዴት መጸለይ

እንደሚገባው የሚያስተምር የእነ ቅዱስ ባስልዮስ፣ ቅዱስ ኤፍሬም፣ አባ ሲኖዳ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ ስምዖን ዘአምድ

እና የመሳሰሉት ቅዱሳን የጸለዩት የጸሎት እስግቡእ ነው። እውነቱን ለመናገር ይህን ጸሎት የሚጸልይ ሰው

የቅዱሳኑን ንስሐ በማስተዋል ንስሐ ገባሁ ብሎ ካለመመጻድቅ ጀምሮ ብዙ ነገሮችን እንደሚገበይ አምናለሁ።

ሐ) የትሕትና ሥራዎችን መሥራት

በተለይ እንደ ስንፍና እና ዝሙት ያሉትን ለመላቀቅ ሥራዬ ብሎ የጉልበት ሥራዎች መሥራት ይመከራል።

ይልቁንም ደግሞ እጂግ ዝቅ ያሉ የትሕትና ሥራዎችን መሥራት ፍቱን መድኃኒት ነው። በስንክሳር ላይ

እንደተገለጸው በቅድስና በገዳም ይኖር የነበረ አንድ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ወደ ሲመት ከመጣ በኋላ ዝሙት

ባስቸገረው ጊዜ ገዳማውያን አበው በመከሩት መሠረት ሌሊት ሌሊት ተደብቆ የገዳማውያኑን ቆሻሻ እየጠረገ

በመድፋት ሁለት ዓመት ያህል ካገለገለ በኋላ ጌታ ትዕግሥቱን አይቶ ፈተናውን እንዳራቀለት ተገለጿል። ስለዚህም
ይህን የመሰሉ የትሕትና ሥራዎችን ከመሥራት ጋር ሥራዬ ብሎ በጸሎት ጊዜ ስግደት መስገድ እና መሬት ላይ

መተኛት እንደዝሙት ካሉት ለመላቀቅ ጠቃሚ ነገር መሆኑን ብዙ ቅዱሳን ጽፈዋል።

መ) ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ

ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለይም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ፈተናን አንዱ መታገያ መንገድ ነው። ይልቁንም ደግሞ

ፊልሙን የማይገባውን የቴሌቪዥን እና የፊልም እይታዎችን ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ስሜት ቀስቃሽ ነገሮችን ቢቻል

አቁሞ ካልሆነም በጣም ቀንሶ መጻሕፍትን ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው። ስሜቱን መቆጣጠር የቻለ ሰው ከብዙ

ጥፋት ይድናል። ይህም ማለት ኃጢአትን ሳይድግ እና ሳይጎለምስ መቅጨት ማለት ነው። በዚህ ጊዜ የሚተጋውን

ሰው እግዚአብሔርም ይረዳዋል። በነፍሳችን ውስጥ ስላለችው የኃጢአት ከተማ ነቢዩ ሲናገር ‘ሕፃናቶችሽን በዓለት

የሚቀጠቅጣቸው የተመሰገነ ነው’ ተብሎ የተነገረው ይፈጸምለታል። ሕጻናቶች ማለት ኃጢአት ገና ከመጎልመሱ

አእምሮን ከመቆጣጠሩ በፊት ተቀዳድሞ ገና በስሜትነት እያለ በቃለ እግዚአብሔር በጸሎት አእምሮን እንደጥሩ

ጥበቃ ተግቶ እንዳይዘናጋ በመጠብቅ ማሸነፍ ይቻላል። ኃጢአትን ገና በሀሳብነቱ መዋጋት የእግዚአብሔርን ርዳታ

ያስገኛል፤ ከዚያም በዚያው እንዲቀጩ እና አእምሮአችንን ነጻ ያወጣዋል። ያን ጊዜ ሥጋችን ከእድፈት ነፍሳችንም

ከርስኩሰት ይነጻሉ።

ማጠቃለያ

ከላይ የጠቀስኳቸው በጣም ትንሽ እና ለማነሣሣት ያህል ብቻ የተድረጉ እንጂ በጉዳዩ ላይ ሥራዬ ብሎ መማር፣

ማንበብ እና ልክ እንደ ስፖርት አዘውትሮ ሰዐት ጠብቆ ተገቢውን ማድረግ ያስፈልጋል። በእነዚህና በመሰሉት

መንገዶች ከተጓዝን ደግሞ ሳንቸኩል በቀስታ የምንፈልገው ቦታ ላይ እንደርሳለን ። ይህ እንደሚሆንም ምንም

ጥርጥር የለውም። ታዲያ የመፈወሳችን ምልክቱ ምንድን ነው ልንል እንችላለን።

በነገራችን ላይ ከፍትወታት ፈጽሞ ለመላቀቅ ረጂም እና ያልተቋረጠ ትግል ይፈልጋል። ይህ መላቀቅ ስንል

ስለኃጢአት ሥርየት ማግኘትን በተመለከተ እየተናገርን አይደለም። ስላለፈው ኃጢአት በተናዘዝን ቁጥር ይቅርታ

በጠየቅን ቁጥር ሥርየት እናገኛለን። ስለማቆም የምንናገረው ፍትወቶቹን ከውስጣችን ስለመለየት እና ኃጢአትን

ስለማቆም ነው። ተጋድሎው ያስፈለገውም ወደዚህ የነፍስ ጤንነት ስለመመለስ ነው። ለዚህም ነው ከመናዘዝ እና

ንስሐ ከመግባት ያለፈ ተጋድሎ የሚጠይቀው። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ደም እስከማፍሰስ ድረስ ለመጋደል ገና

አልደረሳችሁም” እንዳለው ደም እስከማፈሰስ ወይም ደም ማፍሰስ ጋር የሚተካከል ተጋድሎ የሚፈልጉ ናቸውና።

ይህ ተጋድሎ እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።

የሆነው ሆኖ እውነተኛ ድል መነሣት ላይ ስንደርስ አንደኛ ኃጢአትን በገቢር መሥራት ይልቁንም ደግሞ ፈልጎ

መሥራት እናቆማለን። ይህ የመጀመሪያው እና በተለይ ወጣንያን የሚደርሱበት ከፍትወታት የመላቀቅ ጅማሮ

ነው። ለእኛ ዓይነቶቹ ደግሞ ከፍተኛ ውጤት ነው። ከዚህ ሳይደረስ ወደ ሌላው መሸጋገር አይቻልምና። ሁለተኛው

ደረጃ ደግሞ ኃጢአት አቁመው ጸጋ ማግኘት የጀመሩት ደግሞ ፍትወታት ወደ አእምሮ ሲደርሱ ቶሎ ማስወገድ

መቻል ላይ የሚደርሱበት ደረጃ ነው። ይህም ማለት በአእምሮ ውስጥ በሀሳብነት የመጣውን ልክ ጥበቅ አልፎ የገባን
ሰው ቶሎ ይዘው እንደሚመልሱት ሀሳቡን በአእምሮ ውስጥ አለማቆየት ፣ አለማዋል፣ አለማሳደር ማለት ነው።

ስለዚህ ሁለተኛው ደረጃ ፍትወታትን ከአእምሮ በየደቂቃው ነቃቅሎ የማውጣት ደረጃ መድረስ ነው። ሦስተኛው

ደረጃ የሚደርሱት ደግሞ ከፍትወት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ በአእምሮአቸው ከማሰብ ያቆማሉ። በዚህ

ጊዜ እንኳን አዲስ ሊያስቡ ይቅርና በንስሐ ያለፉት እንኳ እንዴት ድርጊቱ ምን ይመስል እንደነበር እስከመርሳት

ይደርሳሉ። ለምሳሌ ያህል በቀደመ ሕይወቱ በዝሙት የነበረ ሰው እንኳ ቢሆን ዝሙት ራሱ ግብሩ ምን እንደነበረ

ከአእምሮው ይጠፋለታል። ይህም ማለት ግብረ ሥጋን የማያውቀው ሰው ዓይነት ይሆናል። ንስሐ ዘማዊውን

ድንግል ታደርጋለች የሚለው ቃል እዚህ ደረጃ ለደረሰ የሚነገር ነው። በስንክሳራችንም ላይ ታሪካቸውን በዝሙት

ጀምረው በተጋድሎ ከጨረሱ በኋላ ጸሐፊው ራሱ ከዚህች ድንግል በረከት ይክፈለን እያለ የጸፈላቸው አሉ።

አራተኛው እና የመጨረሻው ደግሞ ከፍትወታት ጋር የተገናኘ ቅዥትም ሆነ ሕልም ሁሉ ያለማየት ደረጃ መድረስ

ነው። የፍጹማኑ ንጽሕና የሚባለው ይኼኛው ደረጃ ነው። እንግዲህ የምንታገለው ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ነው

ማለት ነው።

በመጀመሪያው ጽሑፌ በአዲሱ ዓመት የምንመኘው ዓይነት ሰው ለመሆን ማድረግ የሚገባን ምንድን ነው የሚል

ጥያቄ ጠይቄ የተነሣሁት ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ለማናውቃቸው ለማሳወቅ ፣ ለሚያውቋቸውም ለማስታወስ

ነው። እነዚህም እኛ ያለንበትን ማወቅ፣ ልንደርስበት የሚገባንን ማወቅ፣ ሦስተኛው እና እኩል አስፈላጊው ነገር

ደግሞ ካለንበት ወደምንመኘው እና ወደ ምንፈልገው ሕይወት የሚያደርሰንን መንፈሳዊ ሕይወት ፣ ተጋድሎ

ወይም መንገድ ማወቅ ናቸው። ስለዚህ በመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ለመነካካት የሞከርኩት ችግሮቻችንን ወይም

ያለንበትን የሕይወት ደረጃ ለማሳየት ያህል ብቻ ነው። ዛሬ ደግሞ የመፍትሔ መንገዶቹንና እና በተጋድሏችን

ልንደርስበት የሚገባውን የሕይወት ደረጃ በጣም በትንሹ ለመጠቆም ሞክሪያለሁ። በእግዚአብሔር ቸርነት እና

ኃይል ተጉዘን ወደዚህ እውነተኛ አዲስ ሕይወት ለመድረስ ያብቃን። ያን ጊዜ ዘመናችን ሁሉ እንደ ስሙ ዓመተ

ምሕረት ሁል ጊዜም አዲስ ዓመት ይሆንልናል።

መሆን የምንፈልገው ድል ነሺ ክርስቲያን መሆኑ የታወቀ ነው። ድል የምንነሳው ደግሞ መጀመሪያ ኃጢአትን ቀጥሎ

ደግሞ የኃጢአትን በሮች ፍትወታትን ነው። ድል የምንነሣው በጌታችን ኃይል ነው። ያለ እኔ ምንም ምን ልታደርጉ

አትችሉም ብሎናልና። ስለዚህ እርሱን አምነን በቅዱሳኑ ይልቁንም የባሕርያችን መመኪያ በሆነች በእመቤታችን

አማልጅነት እየተማጸንን አሁን ከተቀመጥንበት የኃጢአት ቦታ ተነሥተን ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

እያልን እጅ ወደ ምንነሣት የድል ነሺዎች ጉባኤ እና ኅብረት ለመቀላቀል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንነሣ። ሁሌም

ተንሥኡ አይደል የምንባለው። እንግዲያውስ የትንሣኤውን ኃይል ገንዘብ አድርገን በቸርነቱ እንነሣ። እግዚአብሔር

(በእኔ ሕይወት ውስጥ) ይነሣ፤ ጠላቶቹም (አጋንንት እና ፍትወታትም) ይበተኑ የሚለውን የዳዊትን መዝሙር
እየዘመርን በመንፈስ እንነሣ። በመንፍሳዊቷ መቅደስም በቅዳሴ እና በቁርባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ ከነቢያት እና

ከሐዋርያት ጋር አብረን እንሠራ።

እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ አደረሳችሁ።


ዘመነ ዮሐንስ በግል እና በማኅበራዊ ሕይወታችን ያሉት በሽታዎች ብቻ ሳይሆኑ እነዚህ ተደማምረው ሀገራችንን

በከባድ ሰቆቃ ፣ ሐዘን ፣ ልዩነት እና ዕልቂት ወጥሮ የያዘው መንፈስ ተሸንፎ ከግለሰባዊውም ሆነ ከሀገራዊ

ችግሮቻችን ነጻ የምንወጣበት ያድርግልን። ዘመነ ዮሐንስ ሆይ ከአስደናቂ ተአምራቶችህ ጋር ግባልን፤ አሜን።

መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን።

You might also like