You are on page 1of 11

#በፌደራል_የመንግስት_ሰራኞች_አዋጅ_የተካተቱ_የመንግስት_ሰራተኞች_መብቶችና_ግዴታዎች

በዚህ ጹሁፍ በመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኝነት ለመቀጠር መሟላት ያለባቸው መስፈርቶችና


የመንግስት ሰራተኛ መብቶች እና ግዴታዎች፣የሥነ ምግባርና ዲሰፕሊን እርምጃዎች እና የቅሬታ
አቀራረብ እንዲሁም አገልግሎት ስለሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች በፌደራል የመንግስት ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር
1064/2010 ስራ እንደተደነገገው እንመለከታለን፡፡
1. #የፌደራል_የመንግስት_ሰራተኞች_ትርጉም
የመንግስት ሰራተኞች መብታቸው የሚከበርበትን የተቀላጠፈ የፍትህ ስርዓት ለማጠናከር እና የሲቪል
ሰርቪስ ማሻሸያ ፕሮግራም በሰው አስተዳደር ማሻሻያ ረገድ ያካሄዳቸው ለውጦች በበቂ ሁኔታ
የሚያካትት ህግ ማውጧት ለማስፈለጉ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010
ታወጇል፡፡
በፌደራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 2(1) ስር እንደተደነገገው የመንግስት
ሰራተኛ ማለት በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ነው፡፡ከዚህ
ትርጉም የምንረዳው አንድ ሰው የመንግስት ሰራተኛ ነው የሚባለው በመንግስት መስሪያ ቤት ማለትም
ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመ እና ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ከመንግስት በሚመደብለት
በጀት የሚተዳደር ሆኖ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚወጣው የመንግስት መስራያ ቤቶች ዝርዝር ውስጥ
የተካተተ የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤት ሲሰራ ነው፡፡በተጨማሪ በየክልሉ ባሉ የመንግስት መስሪያ ቤት
ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችም የመንግስት ሰራተኛ ይባላሉ፡፡ይሁንና በፌደራል የመንግስት
መስሪያ ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ቢሆንም የሚከተሉትን አይጨምርም፡-
• ሚኒስተር ዴኤታዎች፣ ምክትልና ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በተመሳሳይ ደረጃ እና ከዚያ በላይ የሆኑ
ሃላፊዎች
• የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት
• የፌ/ፍ/ቤት ዳኞች እና ዐቃቤያን ህግ
• የመከላኪያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላትን እንዲሁም በመከላኪያ ወይም በፖሊስ ደንብ
የሚተዳደሩ ሌሎች ሰራተኞች
• አግባብ ባለው ሌላ ህግ በዚህ አዋጅ እንዳይሸፈኑ የተደረጉ የመንግስት ሰራተኞች አይጨምርም፡፡ ይህ
ሲባል እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ሰራተኞች የመንግሰት ሰራተኛ ቢሆኑም በፌደራል የመንግስት ሰራተኞች
አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አይተዳደሩም ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ሁሉም የየራሳቸው የተለያየ መተዳደሪያ
ህግ እና ደንብ ይኖራቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰዎች በጊዜያዊ ሰራተኝነት በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው ሊሰሩ የሚችሉባቸው
ሁኔታዎች በአዋጁ ተካቷል፡፡በአዋጁ እንደተደነገገው አንድ ሰራተኛ ጊዜያዊ ሰራተኛ የሚባለው በመንግስት
መስራያ ቤት ውስጥ ዘላቂነት ባህሪ በሌለው ስራ ወይም ሁኔታዎች ሲያስገድዱ በቋሚ የስራ መደብ ላይ
በጊዜያዊነት ተቀጠሮ የሚሰራ ሰው ነው፡፡ ሆኖም የሚከተሉትን አያካትትም፡-
• በቀን ሂሳብ እየተከፈላቸው የሚሰሩ የቀን ሰራተኞች
• ከመንግስት መስራያ ቤት ጋር በገቡት ውል ዋጋ እየተከፈላቸው በራሳቸው የንግድ ስራ ወይም የሙያ
ሃላፊነት የሚሰሩ ተቋራጮች
• በመንግስት መስራያ ቤት ውስጥ የሙያ መልመጃ ወይም ለስልጠና የተመደቡ ተለማማጆች
• ባላቸው ልዩ እውቀት አና ችሎታ ምክንያት ከመስሪያ ቤቱ ጋር በገቡት ውል መሰረት እየተከፈላቸው
በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ ባለሙያዎችን አይጨምርም፡፡
2 #የመንግስት_ሰራተኛ_ለመሆን_የሚያስፈልጉ_መስፈርቶች
ሰዎች የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በሰራተኝነት ለመቀጠር ከሚስፈልጋቸው ሙያና ሙያዊ ብቃት
በተጨማሪ ማሟላት የሚጠበቅባቸው መስፈርቶች በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 ስር ተቀምጠዋል፡፡
እነዚህም
#እድሜ
በመንግስት ሰራተኝነት ለመቀጠር አንድ ሰው እድሜው 18 አመት መሙላት አለበት፡፡ 18 አመት
ያልሞላው ሰው በመንግስት ሰራተኝነት መቀጠር አይችልም፡፡ ነገር ግን እድሜያቸው ከ 14 አመት በላይ
የሆናቸው እና 18 አመት ያልሞላቸው ወጣቶች ስለሚቀጠሩበትና ስለ ስራ ሁኔታዎች የፌደራል ሲቭል
ሰርቪስ ኤጀንሲ መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል አዋጁ ይደነግጋል፡፡በሌላ በኩል በዚህ አዋጅ የማይተዳደሩ
ለምሳሌ የዳኞች የመቀጠሪያ ትንሹ እድሜ 25 አመት ነው፡፡
#ዜግነት
በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 21(2) ስር እንደተቀመጠው አንድ የመንግስት መ/ቤት ከፍተኛ ባለሞያ
ለሚጠይቅ ማናቸውም ክፍት የስራ መደብ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር ወይም በቅጥር ኢትዮጵያዊ
ባለሙያ ለማግኘት አለመቻሉን በማረጋገጠ የውጪ ሀገር ዜጋ በጊዜያዊነት ሊቀጥር ይችላል፡፡ይህ ማለት
ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው በመንግስት ሰራተኝነት በቋሚነት አይቀጠርም፡፡ነገር ግን ትውልደ ኢትዮጵዊ
የሆነ የውጪ አገር ዜጋ፣ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጪ ዜጎች በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች
ተጠቃሚ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 270 አንቀጽ 5(2) መሰረት በመንግስት ሰራተኝነት ሊቀጠሩ
ይችላል፡፡
ስለዚህ በመንግስት ሰራተኝነት ለመቀጠር ኢትዮጵያዊ ዜግነት አንዱ መስፈርት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ
የውጪ አገር ዜጋ በጊዜያዊ ሰራተኝነት እና ትውልድ ኢትዮጵያዊ የውጪ ዜጎች በመንግስት ሰራተኝነት
ሊቀጥሩ እንደሚችሉ አዋጁ ይደነግጋል፡፡
ከወንጀል ነጻ መሆን የእምነት ማጉደል፣ የስርቆት እና የማጭበርበር ወንጀል ፈጽሞ ስልጣን ባለው ፍ/ቤት
የተፈረደበት ማንኛውም ሰው በመንግስት ሰራተኝነት ሊቀጠር አይችልም፡፡ በተጨማሪም ከማንኛውም
የመ/ቤት በስነምግባር ጉድለት ምክንያት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ ከስራ ከተሰናበተበት ጊዜ ጀምሮ
አምስት አመት ከመሙላቱ በፊት በመንግስት ሰራተኝነት ሊቀጠር አይችልም፡፡ይህ ማለት ከወንጀል ነጻ
መሆን እና ዲሲፕሊን ያለው ሰራተኛ መሆን በመንግስት ሰራተኝነት ለመቀጠር መሟላት ያለባቸው
መስፈርቶች ናቸው፡፡ለዚህ ነው ወደ ቅጥር ውል ከመገባቱ በፊት ከላይ ከተጠቀሱት ወንጀሎች ነጻ መሆንን
የሚገልጽ ማስረጃ ከፖሊስ ማቅረብ ግዴታ የሆነው፡፡ በተጨማሪም በመንግስት ስራ ተቀጥሮ ለማገልገል
ብቁ ለመሆኑ ከኤች.አይቪ.ኤድስ ምርመራ በስተቀር የጤንነት ማረጋገጫ የሕክምና ምርመራ ዉጤት
ማቅረብ እንዳለበት የአዋጁ አንቀጸ 14 (3) ስር በግልጽ ሰፍሯል፡፡
#ቃለ_መሐላ
በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 17 ስር እንደተደነገገው የተመረጠው እጩ የስራ መደቡ መጠሪያ፣
የተመደበበትን ደረጃ፣ ደሞዙ እና ስራውን የሚጀምርበትን ቀን የሚገልጽ በአሰሪው መስሪያ ቤት የበላይ
ሃለፊ ወይም ሰራተኛን ለመቅጠር ውክልና በተሰጠው የስራ ሃላፊ የተፈረመ የሙከራ የቅጥር ደብዳቤ
ከሚያከናውነው የስራ ዝርዝር መግለጫ ጋር ይሰጠዋል፡፡ነገር ግን የተቀጠረው የመንግስት ሰራተኛ ስራ
ከመጀመሩ በፊት የሚከተለውን ቃለ መሐላ መፈጸም አለበት፡፡“እኔ------------ በመንግሰት ሰራተኝነቴ
ከሁሉም በላይ አድርጌ በእውነት እና በታማኝነት ህዝቡን ለማገልገል፣በማንኛውም ግዜ ህገ መንግስቱ እና
የሀገሪቱን ዜጎች ለማክበር እና በስራዬ ምክንያት ያወኩትና በህግ ወይም አሰራር በሚስጥርነት
የተመደቡትን ለሌላ ማንኛውም ወገን ላለመግለጽ እንዲሁም የመንግስትን ፖሊሲዎች ለመፈጸም ቃል
እገባለሁ” በማለት ቃለ መሐላ መፈጸም አለበት፡፡
በሌላ በኩል አንድ ሰራተኛ በቋሚ የመንግስት ሰራተኝነት ለመቀጠር የተቀመጠውን የሙከራ ግዜ
ማጠናቀቅ አለበት፡፡የሙከራ ግዜ አላማ አዲስ የተቀጠረ የመንግስት ሰራተኛ ሰለስራው ክትትል እየተደረገ
ብቃቱን ለማረጋገጥ ይሆናል፡፡የሰራተኛው የሙከራ ግዜ በተቀጠረበት የስራ መደቡ ላይ ለስድስት(6) ወራት
ሆኖ የስራ አፈጸጻም ውጤቱ ከአጥጋቢ በታች ሆኖ ከተገኘ የሙከራው ግዜው ለተጨማሪ ሶስት ወር
ይራዘማል፡፡ከዚህ በኃላ የሙከራው ግዜ ሰራተኛው አጥጋቢ የስራ አፈጻጸም ውጤት ካላገኘ ከስራ
ይሰናበታል፡፡
የመንግስት ሰራተኞች የሙከራ ጊዜ 6 ወር ሲሆን ለግል ሰራተኞች ግን የግል ሰራተኞች የሚገዛው የአሰሪና
ሰራተኛ ህግ 1156/2011 ስር እንደተደነገገው የሙከራ ግዜ 60 ቀን ነው፡፡ በሌላ በኩል በአዋጁ በሌላ አኳኋን
ካልተደነገገ በስተቀር በሙከራ ላይ ያለ የመንግስት ሰራተኛ የሙከራ ግዜውን የጨረሰ ቋሚ የመንግስት
ሰራተኛ ያለው መብት እና ግዴታ ይኖረዋል፡፡
ከላይ ተገለፁት መስፈርቶች እንዳሉ ሆነው በክፍት የስራ መደብ ላይ ሰራተኛ የሚመደባው በስራ መደቡ
የሚጠየቀውን ተፈላጊ ችሎታ የሚያሟላ እና ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድሮ ብልጫ ያለው ሆኖ
ሲገኘ ብቻ ነው፡፡ይሁንና የመንግስት ሰራተኞች ቅጥር፣ የደረጃ እድገት እና ድልድል ሲፈጸም በውድድር
ውጤታቸው እኩል ወይም ተቀራራቢ ሲሆን
• ሴት አመልካቾች
• አካል ጉዳተኞች
• በአንጻራዊ ሁኔታ በመንግስት መስሪያ ቤቱ ውስጥ አነስተኛ ብሄራዊ ተዋጾ ላላቸው ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
3.#የመንግስት_ሰራተኛ_መብቶች
ሰዎች በመንግስት ሰራተኝነት ሲቀጠሩ የሰራ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ጎን ለጎን ለነርሱ ደግሞ በህግ
የሚጠበቁላቸው ወይም የሚከበሩላቸው መብቶች አሉ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 42/2 ስር ባጠቃላይ
እንደተደነገገው በአግባቡ የተወሰነ የሰራ እረፍት፣ የመዝናኛ ግዜ፣በየገዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የእረፍት
ቀኖች፣ ደሞዝ የሚከፈልባቸው የህዝብ በዓላት እንዲሁም አደጋን የማያስከትል የስራ አካባቢን የማግኘት
መብት አላቸው፡፡
ከዚህ በመቀጠል በአዋጁ ስራ የተካተቱ የመንግስት ሰራተኞችን መብቶች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
#ደሞወዝ
ማንኛውም ሰራተኛ ለሰራበት ስራ ክፍያ ወይም ደመወዝ የማግኘት መብት አለው፡፡ እኩል ዋጋ ያላቸው
ስራዎች እኩል የመነሻ ደሞወዝ ይኖራቸዋል፡፡ ማንኛውም የመንግስት መ/ቤት በየወሩ መጨረሻ
ለሰራተኞቹ ወይም ለህጋዊ ወኪሎቻቸው የደሞዝ ክፍያ እንደሚፈፅም አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ እንዲሁም
የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ የሚያገኙት በስራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ላይ በመመስረት
መሆኑን ያክላል፡፡አጥጋቢ እና ከዛ በላይ የስራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ላገኘ የመንግስት ሰራተኞች
የሚሰጠው የደሞዝ ጭማሪ በየሁለት አመቱ ይደረጋል፡፡በተጨማሪ የትርፍ ሰዓት ስራ ለሰራ ማንኛውም
የመንግስት ሰራተኛ በሰራተኛው ምርጫ መሰረት የማካካሻ እረፍት ወይም የትርፍ ሰዓት ክፍያ ይሰጠዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዋጁ የተካተተው ሌላ ጉዳይ የደሞዝ ክፍያ ስለሚያዝበት እና ስለሚቆረጥበት ሁኔታ
ነው፡፡በአዋጁ አንቀጽ 9 (2) ስር እንደተቀመጠው የማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ደሞወዝ ሊቆረጥ
ወይም ሊያዝ የሚችለው
 ሰራተኛው ስምምነቱን በጹሁፍ ሲገልጽ
 በፍርድ ቤት ትእዛዝ
 በህግ በተደነገገው መሰረት ብቻ ነው
በፍርድ ቤት ትእዛዝ እና በህግ በተደነገገው መሰረት ደሞዝ ሲቆረጥ ከሰራተኛው ደሞዝ በየወሩ
የሚቆረጠው ከደሞዙ አንድ ሶስተኛ መብለጥ አይችልም፡፡
#የደረጃ_እድገት
የደረጃ እድገት አላማ የመስሪያ ቤቱን የስራ ውጤት ለማሻሻል እና ሰራተኛውን ለማበረታታት ነው፡፡
ለደረጃ እድገት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ያሟላ ሰራተኛ ለደረጃ እድገት የመወዳደር እና የደረጃ እድገት
የማግኘት መብት አለው፡፡የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግስት ሰራተኛ በደረጃ እድገት ዝርዝር
አፈፃጸም መመሪያ ውስጥ ለውድድር የሚያበቁ ሁኔታዎች ከሌሉ በመንግስት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ለወጣ
ክፍት የስራ መደብ በደረጃ እድገት ለመወዳደር ይችላል፡፡
ሌላ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ዝውውርን የሚመለከት ነው፡፡የሙከራ ግዜውን ያጠናቀቀ
የመንግስት ሰራተኛ በጤናው ምክንያት በያዘው የስራ መደብ ወይም ባለበት የስራ ቦታ ላይ ሊሰራ
አለመቻሉ በህክምና ማስረጃ ሲረጋገጥ
 በተመሳሳይ ደረጃ ሊመደብበት የሚችል የስራ መደብ ካለ በያዘው ደረጃ
 በተመሳሳይ ደረጃ ሊመደብበት የሚችልበት ክፍት የስራ መደብ ከሌለና ሰራተኛው ዝቅ ባለ ደረጃ
ለመስራት ፍቃደኛ ከሆነ ደረጃውን ቀንሶ የሚስማማውን የስራ መደብ ወይም የስራ ቦታ የመዘዋወር
መብት አለው፡፡እንዲሁም አንድ የመንግስት ሰራተኛ የስራ መደብ የተሰረዘ እንደሆነ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ
ተመሳሳይ ደረጃ ወዳለው መደብ ይዛወራል፡፡
#ልዩ_ልዩ_ፈቃዶች
ፍቃዶች ለሰራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች የሚሰጡ ሲሆን ሰራተኞች በአዋጁ የተካተቱ ልዩ ልዩ
ፍቃዶችን በህጉ አግባብ የመውሰድ መብት አላቸው፡፡ከዚህ በመቀጠል በአዋጁ የተካተቱ ፍቃድ አይነቶችን
እንለከታለን፡፡
የዓመት ፍቃድ
በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 36/1 ስር እንደተደነገገው የአመት አረፍት ፍቃድ የሚሰጠው መንግስት
ሰራተኛው ለተወሰነ ጊዜ በማረፍ አገልግሎቱን በታደሰ መንፈስ እንዲቀጥል ለማስቻል ነው፡፡
ማንኛውም አዲስ ተቀጣሪ የመንግስት ሰራተኛ የአስራ አንድ ወራት አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት የአመት
ፍቃድ ለማግኘት መብት የለውም፡፡በመርህ ደረጃ የአመት እረፍት በገንዘብ አይለወጥም፡፡ሆኖም ሰራተኛው
አገልግሎቱ በመቋረጡ ምክንያት ያልተወሰደ የአመት እረፍት ካለ በገንዘብ እንዲለውጥ ይደረጋል፡፡ይህም
ለምሳሌ ሰራተኛው ስራውን ቢለቅና ያልተጠቀመበት ወይም ያልወሰደው የአመት እረፍት ቢኖረው የስራ
ቀናቶች ብቻ ታስበው በገንዘብ ተቀይሮ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት አለው ማለት ነው፡፡
አንድ አመት ያገለገለ የመንግስት ሰራተኛ 20 የስራ ቀናት የአመት እረፍት ፍቃድ ያገኛል፡፡ከአንድ አመት
በላይ ያገለገለ ሰራተኛ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ አመት አንድ የስራ ቀን እየታከለበት የአመት ፍቃድ ያገኛል፡፡
ሆኖም የሚሰጠው የአመት እረፍት ፍቃድ ከ 30 የስራ ቀናቶች ሊበልጥ አይችልም፡፡ሰራተኛው በሌላ
የመንግስት መስሪያ ቤት ቀደም ሲል የሰጠው አገልግሎት ለአመት እረፍት ስሌቱ የሚታሰብለት ይሆናል፡፡
የአመት እረፍት ለሰራተኛው በበጀት አመቱ ውስጥ የሚሰጠው የመስሪያ ቤቱን እቅድ መሰረት በማድረግ
እና በተቻለ መጠን የሰራተኛውን ፍላጎት በማመዛዘን በሚዘጋጀው ስራተኛውም እንዲያውቀው
በሚደረገው ፕሮግራም መሰረት ይሆናል፡፡ሰራተኛው ፍቃድ በሚወስድበት ጊዜ በእረፍት ላይ የሚቆይበትን
ወር ደመወዝ በቅድምያ ሊወስድ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል የስራ ሁኔታ በማስገደዱ ምክንያት መ/ቤቱ የአመት እረፍት ፍቃድ በበጀት አመቱ ውስጥ ሊሰጥ
ያልቻለ እንደሆነ የመስሪያ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ከሁለት የበጀት አመት ላልበለጠ ጊዜ ሊያስተላልፈው
ይችላል፡፡ሆኖም ያልተጠቀመበት የአመት እረፍት ፍቃድ በሶስተኛው የበጀት አመት ለሰራተኛው መሰጠት
አለበት፡፡ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የአመት ፍቃዱ ለሚተላለፍለት ሰራተኛ ፍቃዱ በገንዘብ
ተለውጦ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ሰራተኛውም በጀት በቅድሚያ በማስያዝ ከተላለፈው አመት ፍቃድ
የመጀመሪያውን አንዱን አመት የስራ ቀናቶች ብቻ በገንዘብ ተለውቶ እንዲሰጠው ማድረግ አለበት፡፡
#የወሊድ_ፍቃድ
የወሊድ ፍቃድ በመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ውስጥ ከተካተቱ የፍቃድ አይነቶች አንዱ ነው፡፡ነፍሰ ጡር
የሆነች የመንግስት ሰራተኛ ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ ሀኪም በሚያዘው መሰረት
ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣታል፡፡እንዲሁም ከመውለዷ በፊት እረፍት እንድታደርግ ሀኪም ካዘዘ
ደመወዝ የሚከፈልበት እረፍት ይሰጣታል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 42 ስር እንደተደነገገው ነፍሰጡር የሆነች ሴት
መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ካሰበችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ እንዲሁም
ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት በአጠቃላይ 120 ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት
የወሊድ ፍቃድ ይሰጣታል፡፡
ሰራተኛዋ የወሊድ ፍቃዷን ከጨረሰች በኃላ ብትታመም እና ተጨማሪ ፍቃድ የሚያስፈልጋት መሆኑ
በሀኪም ከተረጋገጠ በዚህ አዋጅ በተደነገገው መሰረት የህመም ፍቃድ መውሰድ ትችላለች፡፡
የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ከአሰሪና ሰራተኛ ህግ በተለየ ወይም በግል ሰራተኞች ህግ ያልተካተተ
ለመንግስት ሰራተኛ ፍቃድን ተመልክቶ የሰጠው መብት የአባትነት የወሊድ ፍቃድ (paternal leave) ነው፡፡
የመንግስት ሰራተኛው የትዳር ጓደኛው ከወሊድ ጋር በተያያዘ ቤተሰቡንና ባለቤቱን ለመንከባከብ ደመወዝ
የሚከፈልበት 5 የስራ ቀናት ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡
#የህመም_ፍቃድ
ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በህመም ምክንያት ስራውን መስራት ያልቻለ እንደሆነ የህመም ፍቃድ
ይሰጠዋል፡፡የሙከራ ጊዜውን ላጠናቀቀ የመንግስት ሰራተኛ የሚሰጥ የህመም ፍቃድ በተከታታይ ወይም
በተለያየ ጊዜ ቢወሰድም ህመም ከደረሰበት መጀመሪያ ቀን አንስቶ ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከ 8
ወር ወይም በ 4 አመት ውስጥ ከአንድ አመት አይበልጥም፡፡በዚህ መሰረት የህመም ፍቃድ ሲሰጥ
ለመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት ከግማሽ ደመወዝ ጋር እና
ለመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት ያለ ደመወዝ ይሆናል፡፡የሙከራ ጊዜውን ያላጠናቀቀ የመንግስት ሰራተኛ
ደግሞ የህክምና ማስረጃ ሲያቀርብ የአንድ ወር ህክምና ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡
#ለግል_ጉዳይ_የሚሰጥ_ፍቃድ
ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ለሀዘን፣ለጋብቻ፣ለፈተና እና ለመሳሰሉት በአንድ የበጀት ዓመት ውስጥ
የ 7 ቀናት ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡
#ከደወመዝ_ጋር_የሚሰጥ_ልዩ_ፍቃድ
ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ
• ከፍርድ ቤት ወይም ከሌሎች ስልጣን ካላቸው አካላት መጥሪያ ሲደርሰው የተጠራበት ጉዳይ
ለሚጠየቀው ጊዜ
• በህዝብ ምርጫ ስልጣን የሚይዙ የመንግስት ሀላፊዎችን ለመምረጥ ሲሆን ምርጫው ለሚወስድበት ጊዜ
ከደመወዝ ጋር ልዩ ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡
#ያለደመወዝ_የሚሰጥ_ልዩ_ፍቃድ
 የሙከራ ጊዜውን ያጠንቀቀ የመንግስት ሰራተኛ በበቂ ምክንያት ደመወዝ የማይከፈልበት ልዩ ፍቃድ
እንዲሰጠው ሲጠይቅ መስሪያ ቤቱን የማይጎዳ ሲሆን የመስሪያ ቤቱ ሀላፊ ሊፈቅድ ይችላል፡፡
 የሙከራ ጊዜውን ያጠንቀቀ የመንግስት ሰራተኛ በህዝብ ምርጫ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ሲቀርብ የምርጫ
ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅት ምርጫው በሚከናወንበት ጊዜ ያለደመወዝ ፍቃድ እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
4. #የመንግስት_ሰራተኛ_ግዴታዎች
የመንግስት ሰራተኞች ግዴታዎች ምን ምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 66 ስር በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ፡-
 ለህዝብና ለመንግስት ታምኝ መሆን
 መላ ጉልበቱንና ችሎታውን ለህዝቡ አገልግሎት የማዋል
 በስራ ዝርዝር መሰረት የሚሰጡትን የስራ አቅዶችና ሌሎች በህጋዊ መንገድ የሚሰጡትን ትዕዛዞች
መፈጸም
 የመንግስትን ስራ የሚመለከቱ ህጎች፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማክበር
 የመንግስት ፖሊሲ በብቃት የመፈፀም ግዴታ አለበት፡፡እንዲሁም
 ደህንነቱንና ጤንነትን ለመጠበቅ የወጡ መመሪያዎችን የማክበር
 የተሰጡ የአደጋ መከላከያ መሳሪዎችንና ቁሳቁሶችን በአግባቡ የመጠቀም
 አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ሲገምት ለሚመለከተው የመስሪያ ቤቱ ሃለፊ
ወዲያውኑ የማሳወቅ ግዴታ አለበት
 ለህክምና ምርመራ የመቅረብ ግዴታ፡- ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምርመራ
በስተቀር ከምርመራ ጋር በተያየዘ በበቂ ምክንያት የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ በመንግስት መስሪያ
ቤቱ ሲጠየቅ ለምርመራ የመቅረብ ግዴታ
 የንብረት አያያዝና አጠቃቀም :- ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ለስራው ማከናወኛ የተሰጡትን
መሳሪያዎችና መገልገያዎች በአግባቡ የመጠበቅና የመጠቀም ሃላፊነት አለበት
 በእዳ የመጠየቅ ሃላፊነት :- ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ለስራው ማከናወኛ በተሰጡት
መሳሪያዎችና መገልገያዎች ላይ በሚደርስ ጉዳት ወይም ጥፋት በእዳ ተጠያቂ የሚሆነው ጉዳቱ ወይም
ጥፋቱ በሰራተኛው ቸልተኝነት ወይም ሆን ተብሎ በተፈፀመ ድርጊት ምክንያት የደረሰ እንደሆነ ነው፡፡
በአጠቃላይ የመንግሰት ሰራተኞች ተቀጥረው በሚሰሩበት መስሪያ ቤት መብት እንዳላቸው ሁሉ
የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡
5.#የዲስፕሊን_ጥፋቶች_እርምጃዎች_እና_ቅሬታ_አቀራረብ
የዲስፕሊን ቅጣት አላማ የመንግስት ሰራተኛው በፈፀመው የዲሲፕሊን ጉድለት ተፀፅቶ እንዲታረምና
ብቁ ሰራተኛ እንዲሆን ለማስቻል ወይም የማይታረም ሆኖ ሲገኝ ለማሰናበት ነው፡፡በአዋጁ ስር
የዲስፕሊን ቅጣት አይነቶችና አመዳደባቸው በዝርዝር ተቀምጧል፡፡በአዋጁ አንቀፅ 69 ስር የዲስፕሊን
ጉድለት የፈፀመ የመንግስት ሰራተኛ እንደ ጥፋቱ ክብደት ከሚከተሉት ቅጣቶች አንዱ ሊወሰንበት
ይችላል፡፡
1. የቃል ማስጠንቀቂያ
2. የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ
3. እስከ አስራ አምስት ቀን ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ
4. እስከ 3 ወር የሚደረስ የደሞዝ መቀጮ
5. እስከ 2 አመት ድረስ ለሚደርስ ጊዜ ከስራ ደረጃና ከደመወዝ ዝቅ ማድረግ
6. ከስራ ማሰናበት ናቸው፡፡
ከአንድ እስከ ሶስት ያሉት የቅጣት አይነቶች ቀላል የዲስፕሊን ቅጣቶች ተብለው ሲመደቡ የተቀሩት
ደግሞ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ተብለው ተመድበዋል፡፡አንድ ሰራተኛ በዲስፕሊን ከተቀጣ በኃላ ቅጣቱ
በሪከርድነት ሊቆይና ሊጠቀስ የሚችለው ፡-
• ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለሁለት አመታት
• ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለአምስት አመታት ይሆናል፡፡
ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ምን ምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 70 ስር በዝርዝር
ተቀምጠዋል፡፡እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-
 ትእዛዝ ባለማክበር፣በቸልተኝነት፣በመለገም ወይም ሆን ብሎ የአሰራር ሥነ ስርዓትን ወይም የመንግስት
ፖሊሲን ባለማክበር ሥራ ላይ በደል ማድረስ
 ጉዳዮችን ሆን ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት
 ስራ እንዳይሰራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩ ጋር መተባበር
 በቀላል የዲስፕሊን ቅጣት እርምጃዎች ባለመታረም ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ ከስራ መቅረት
ወይም የስራ ሰዓት አለማክበር
 በስራ ቦታ በጠብ አጫሪነት መመደብ
 በልማዳዊ ስካር ወይም በአደንዛዥ እፅ ሱስ በመመረዝ ስራን መበደል
 ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ
 በስራ ቦታ ለህዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈፀም
 የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈፀም
 የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈፀም
 በመስሪያ ቤቱ ላይ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ
 በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም
 በስራ ቦታ ላይ ፆታዊ ጥቃት መፈፀም እና እነዚህን ከላይ ከተዘረዘሩት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለው ሌላ
የዲስፕሊን ጉድለት መፈፀም ከባድ የዲስፕሊን ጉድለት ተብለው ተመድበዋል፡፡በሌላ በኩል አዋጁ ቀላል
የዲስፕሊን ቅጣት አይነቶችን ቢዘረዝርም ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ግን ምን ምን
እንደሆኑ በግልፅ አላስቀመጠም፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ በአዋጁ የተካተተው ጉዳይ የዲስፕሊን
እርምጃዎች አወሳሰድ ነው፡፡
ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሰራተኞችን የዲስፕሊን ክስ አጣርቶ የውሳኔ ሀሳብ ለሚመለከተው
የስራ ሀላፊ የማቅረብ እና የዲስፕሊን ኮሚቴ ማቋቋም እንዳለበት አዋጁ ያስቀምጣል፡፡የዲስፕሊን ቅጣት
የማንኛውንም ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠብቅ ወይም ሳይከተል ሊወሰን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡በአንድ
መንግስት ሰራተኛ ላይ የዲስፕሊን ክስ ከቀረበበት ሰራተኛው ከስራ ታግዶ እንዲቀይ የሚደረገው
 ከተጠረጠረበት ጉዳይ ጋር አግባብነት ያላቸው ማስረጃዎችን በማበላሸት፣በመደበቅ ወይም በማጥፋት
ምርመራውን ያሰናክላል ወይም
 በመንግስት ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል
 ከተከሰሰበት ጥፋት ክብደት አንፃር የሌሎችን ሰራተኞች ሞራል የሚነካ ወይም ተገልጋይ ሕዝብ
በመስሪያ ቤቱ ላይ ሊኖረው የሚገባውን እምነት ያዛባል ወይም
 ተፈፀመ የሚባለው ጥፋት ከስራ ያስወጣል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡
አንድ ሰራተኛ ከስራና ከደመወዝ ታግዶ ሊቆይ የሚችለው ከሁለት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሲሆን የመንግስት
ሰራተኛው በተከሰሰበት የዲሲፕሊን ጥፋት ምክንያት ከስራ እንዲሰናበት ካልተወሰነበት በስተቀር በእግዱ
ወቅት ሳይከፈለው የቀረው ደመወዝ ያለወለድ ይከፈለዋል፡፡
ሰራተኛው የተለያዩ መብቶችን በሚመለከት እንዲሁም የዲሲፕሊን ክስ ቀርቦባቸው የተሰጡት ውሳኔዎች
በተመለከተ ቅሬታ ሲኖራቸው ቅሬታቸውን በማጣራት የውሳኔ ሀሳብ ለመስሪያ ቤቱ ሃላፊነት የሚያቀርብ
የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ እንደሚቋቋም አዋጁ ይደነግጋል፡፡በቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ የሚታዩ ጉዳዮች ምን ምን
እንደሆኑ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡እነዚህም
 ከህጎችና መመሪያዎች አተረጓጎም ወይም አፈጻጸም
 ከመብቶችና ጥቅሞች አጠባበቅ
 ከስራ አከባቢ ጤንነትና ደህንነት ሁኔታዎች
 ከስራ ምደባና ደረጃ አሰጣጥ
 ከስራ አፈጻጸም ምዘና
 በስራ ሃላፊ ከሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ተጽኞዎች
 በዲሲፕሊን ኮሚቴ በተወሰኑ ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣቶች ላይ ቅሬታ ሲኖር
 የስራ ሁኔታዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመንግስት ሰራተኛ የሚያቀርበውን ቅሬታ
አጣርቶ የወሰኔ ሃሳብ የማቅረብ ሃላፊነት የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴው ነው፡፡
በአንድ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ የሰራተኞችን የዲሲፕሊን ክስ የሚያጣራ የዲሲፕሊን ኮሚቴ
እንዲሁም ሰራተኞች ቅሬታ ሲኖራቸው ቅሬታቸውን የሚመረምር የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ መቋቋም
እንዳለበት ከላይ ተመልክተናል፡፡ከዚህ በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር
አይቶ የሚወሰን የአስተዳደር ፍ/ቤት በአዋጁ ተቋቁሟል፡፡የአስተዳደር ፍ/ቤቱ ይግባኝ የተባሉ አስተዳደራዊ
ውሳኔዎችን ከመረመረ በኃላ ውሳኔውን ለማጽናት ለመሻር ወይም ለማሻሻል ይችላል፡፡ፍርድ ቤቱ በፍሬ
ነገር ክርክር የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ሆኖም የአስተዳደር ፍ/ቤቱ ውሳኔ የህግ ስህተት አለው
ብሎ የሚያምን ወገን ፍ/ቤቱ ውሳኔ በሰጠ በሰላሳ (30) ቀናት ውስጥ ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ማቅረብ ይችላል፡፡የፍሬ ነገር (matter fact)ክርክር ማለት ምስክሮች በሰሜት ህዋሳቸው በመገንዘብ
ስለነገሩ መኖር ወይም አለመኖር ሊያረጋግጡ የሚችሉት እውነታ ሲሆን የህግ ነገር(matter of law) ደግሞ
ፍርድ ቤቶች የህግ መርሆችን እና አንቀፆችን በመተርጎም ውሳኔ ላይ የሚደረሱበት ሁኔታ ነው፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 81 ስር እንደተቀመጠው በአስተዳደር ፍ/ቤቱ የሚታዩት የሚከተሉት ጉዳዮች ናቸው።
• ከህግ ውጪ ከስራ መታገድ ወይም አገልግሎት መቋረጥ
• ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት የተወሰነበት በመሆኑ
• ከህግ ውጪ ደመወዝ ወይም ሌሎች ክፍያዎች የተያዘበት ወይም የተቆረጠበት በመሆኑ
• በስራው ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት ጋር በተያያዘ መብቱ በመጓደሉ
• ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣቶችን ከተመለከተ በስተቀር በቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ታይተው ውሳኔ የተሰጠባቸው
ጉዳዮች
• በስራ መልቀቂያና አገልግሎት ማስረጃ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ተመልክቶ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን
ይኖረዋል፡፡
6.#አገልግሎት_ስለማቋረጥ
አንድ ሰራተኛ በመንግስት ሰራተኛነት በመንግስት መስሪያ ቤት የሚሰጠው አገልግሎት ወይም ስራ
በተለያየ ምክንያት ሊቋረጥ ይችላል፡፡በአዋጁ ስር አገልግሎት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ምክንያቶች ወይም
ሁኔታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል::እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡
#በገዛ_ፈቃድ_ከስራ_መልቀቅ
አንድ ሰራተኛ ስራውን በተለያየ ምክንያት በገዛ ፈቃዱ ሊለቅ ይችላል፡፡ይሁንና በህግ ወይም በውል
የተቀመጡ ግዴታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በማንኛውም ጊዜ
#የአንድ_ወር_ቅድሚያ_ማስታወቂያ በመስጠት ስራውን በገዛ ፈቃዱ ሊለቅ ይችላል፡፡ስለሆነም
ሰራተኛው ስራ መልቀቅ ሲፈልግ ከአንድ ወር በፊት አስቀድሞ ለመስሪያ ቤቱ ማሳወቅ አለበት ማለት
ነው፡፡ይሀውም ተጀምረው የነበሩ ስራዎች እንዲጠናቀቁ ወይም ሰራተኛው በእጅ ያሉትን ስራዎች አጠናቆ
እንዲያስረክብ እንዲሁም ተተኪ ሰራተኛ እንዲቀጠር መስሪያ ቤቱ ማድረግ ያለበትን እንዲያደርግ
የሚያስችል ይሆናል፡፡
የአንድ ወር በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግቱን ያቋረጠ የመንግስት ሰራተኛ ግዴታውን
ባለመወጣቱ ለሚደርሰው ጉዳት በፍትሐ ብሄርና በወንጀል ህግ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡የመንግስት
ሰራተኛው እጅግ አስፈላጊና በቀላሉ ለመተካት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ የመ/ቤቱ የበላይ ሀላፊ
የመልቀቂያውን ጥያቄ ሰራተኛው ካመለከተበት ጊዜ ጀምሮ ከ 3 ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሊያራዝ ይችላሉ፡፡
#በህመም ምክንያት አገልግሎት ማቋረጥ
ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በአዋጁ መሰረት በህመም ፈቃድ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ማለትም
የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ ሰራተኛ ከሆነ በህመም ፈቃድ በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ ቢወሰድም
ህመሙ ከደረሰበት ከመጀመሪያ ቀን አንስቶ አስራ ሁለት ወር(1 አመት)ጊዜ ውስጥ ለ 8 ወር ወይም
በአራት አመት ውስጥ ለ 1 አመት ጊዜ በላይ ወደ ስራ መመለስ ካልቻለ በህመም ምክንያት አገልግሎቱ
ይቋረጣል፡፡በተጨማሪ በስራ በመጣ ጉዳት ምክንያት ለዘለቄታው መስራት አለመቻሉ በህክምና ማስረጃ
ከተረጋገጠ የጉዳት አበል እና የጉዳት ዳረጎት መብቶች ተጠብቀው በህመም ምክንያት አገልግሎት
እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡
#ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከስራ መሰናበት
የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግስት ሠራተኛ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በስራ ገበታው ላይ
ካልተገኘ ምክንያቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመስሪያ ቤቱ ማሳወቅ አለበት፡፡በዚህ መሰረት ሪፖርት
የተደረገለት የመንግስት መስሪያ ቤት ሠራተኛው ከሥራ ገበታው ላይ የተለየበት ምክንያት የመ/ቤቱ የበላይ
ሃላፊ ወይም ተወካይ ከአቅም በላይ መሆኑን ካረጋገጠ የመንግስት ሠራተኛው ይዞት የነበረውን የሥራ
መደብ ለስድስት ወር ክፍት አድርጎ መጠበቅ አለበት፡፡ሆኖም የመንግስት ሠራተኛው በስድስት ወር ጊዜ
ውስጥ ወደ ሥራው ካልተመለሰ ከሥራ ማሰናበት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል አንድ ሰራተኛ ባልታወቀ ምክንያት ለተከታታይ 10 ቀናት ከመደበኛ የሥራ ቦታው ላይ ከተለየ
በየአስር ቀናት ልዩነት በተከታታይ ለሁለት ጊዜ በማስታወቂያ ተጠርቶ ለመስሪያ ቤቱ ሪፖርት ካላደረገ
ከሥራ ይሰናበታል፡፡የሙከራ ጊዜውን ያላጠናቀቀ የመንግስት ሠራተኛ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት
ከአንድ ወር በላይ በሥራ ገበታው ላይ ካልተገኘ ያለተጨማሪ ሥነ ሥርዓት ከሥራ እንዲሰናበት ይደረጋል፡፡
#በችሎታ_ማነስ_ምክንያት_ከሥራ_መሰናበት
የሥራ አፈጻጸም ምዘና አላማ ሠራተኞች ስራቸውን በሚጠበቀው መጠን የጥራት ደረጃ ጊዜና ወጪ
ቆጣቢነት በተሞላበት ሁኔታ እንዲያከናውኑ ለማድረግና ተከታታይ የሥራ አፈጻጸም ምዘና በማካሄድ
የሠራተኞችን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየት ቀጣዩ የሥራ አፈጻጸማቸው እንዲሻሻል በማድረግ
ውጤታማ እንዲሆኑ ለማብቃት ነው፡፡ይሁንና የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግስት ሠራተኛ ያለውን
እውቅትና ችሎታ እየተጠቀመ በተመደበበት ሥራ ላይ የሥራ አፈጻጻም ውጤቱ በተከታታይ ለሁለት ጊዜ
ከአጥጋቢ በታች ከሆነ በችሎታ ማነስ ምክንያት ከሥራ ማሰናበት ይቻላል።
#የሠራተኛ_ቅነሳ
ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ
 የሥራ መደቡ ሲሰረዝ
 መስሪያ ቤቱ ሲዘጋ
 ትርፍ የሰው ሃይል ሲኖር ወይም ሠራተኛው ዝቅ ባለ የሥራ ደረጃ ላይ ለመስራት ፈቃደኛ ካልሆነ
በሰራተኛ ቅነሳ ምክንያት ከሥራ ይሰናበታል፡፡ትርፍ የሰው ሀይል ሲኖር ቅነሳ የሚደረገው በመስሪያ ቤት
ውስጥ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ላይ ካሉ የመንግስት ሠራተኞች ጋር ሲወዳደር በሥራ ውጤቱና ባለው
ችሎታ ዝቅተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡በሰራተኛ ቅነሳ ምክንያት አገልግሎት ሲቋረጥ ሰራተኛው ከስራ
ከተሰናበተበትና የስራ ውሉ በተቋረጠበት እለት የጡረታ አበል የማይከፈለው ከሆነ ለመጀመሪያው አንድ
ዓመት የሶስት ወር ደመወዝ እና በተጨማሪ ለአገለገለበት ለእያንዳንዱ ዓመት የወር ደመወዙ አንድ ሶስተኛ
እየታከለ ይከለዋል፡፡ሆኖም የሚሰጠው ክፍያ ከሰራተኛው የአስራ ሁለት ወር ደመወዙ መብለጥ የለበትም፡፡
#በዲሲፕሊን ምክንያት ከሥራ መሰናበት
አንድ ሠራተኛ የዲሲፕሊን ክስ ቀርቦበት ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ማጥፋቱ ተረጋግጦ ከሥራ እንዲሰናት
የዲሲፕሊን ቅጣት የተወሰነበት እንደሆነና በዚህ ውሳኔ ላይ ለአስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ቅጣት
ያልተሰረዘለት እንደሆነ አገልግሎቱ ይቋረጣል፡፡
#በዕድሜ ምክንያት አገልግሎት ማቋረጥ
የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግስት ሠራተኛ በህግ የተወሰነው የመጦሪያ ዕድሜ ከደረሰነት የመጨረሻ
ቀን ጀምሮ ያለተጨማሪ ሥነ-ሥርዓት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ነገር ግን የሠራተኛው
• ትምህርት ፣ልዩ ዕውቅና ችሎታ ለመሥሪያ ቤቱ ሥራ ጠቃሚ ሆኖ ሲገኝ
• በዕድገት በዝውውር ወይም በቅጥር ተተኪ ሠራተኛ ለማግኘት አለመቻሉ ሲረጋጥ
• ሠራተኛው ለሥራው ብቁ መሆኑ በሕክምና ሲረጋገጥ
• ሠራተኛው አገልግሎቱን ለመቀጠል ሲስማማና
• የአገልግሎቱ መራዘም ለፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ቀርቦ ሲፈቀድ የመጦሪያ ዕድሜው ከደረሰ በኃላ በአንድ
ጊዜ እስከ አምስት ዓመት በጠቅላላው ከአስር ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ አገልግሎቱ ሊራዘም ይችላል፡፡
በኢትዮጽያ ህግ የመንግስት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ስድሳ 60 ዓመት ነው፡፡አንድ የመንግስት
ሠራተኛ ጡረታ ከመውጣቱ ከሶስት ወር በፊት በጽሁፍ እንዲያውቀው መደረግ አለበት፡፡
#በሞት ምክንያት አገልግሎት መቋረጥ
ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ ከሞተበት ቀን ጀምሮ አገልግሎት ይቋረጣል፡፡አገልግሎቱ በሞት ምክንያት
የተቋረጠበት የመንግስት ሠራተኛ የሞተበት ወር ሙሉ ደመወዝ ለትዳር አጋሩ ወይም ለህጋዊ ወራሾቹ
ይከፈላል፡፡በተጨማሪ አግባብ ባለው የጡረታ ህግ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የመንግስት
ሠራተኛ በሞት ምክንያት አገልግሎቱ ሲቋረጥ ለሚሰራበት መስረያ ቤት በጽሁፍ ላሳወቃቸው የትዳር
ጓደኛው ወይም በስሩ ይተዳደሩ ለነበሩ ቤተሰቦቹ የሶስት ወር ደመወዝ በአንድ ጊዜ ይከፈላል፡፡ሆኖም
የትደር ጓደኛውን ወይም በስሩ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹን ሳያስመዘግብ የሞተ እንደሆነ ሥልጣን ካለው አካል
ወይም በፍርድ ቤት በሚሰጥ ማስረጃ ክፍያው ይፈፀማል፡፡
ሳሙኤል ግርማ
የሕግ አማካሪና ጠበቃ

You might also like