You are on page 1of 2

የሥነምግባር መርሆዎች

መስከረም 07/2014 ዓ.ም


==============
1. ቅንነት (ምሉዕነት)
የተሟላ ስብዕና፣ ያልተዛባ ህሊና፣ ጽኑ አቋምና ሃቀኝነትን የሚያሳይ ነው፡፡ ቅንነት ያለው የመንግሥት
ሠራተኛ ሥራውን በራሱ ተነሳሽነት የሚሰራ፣ የራሱን ስሜትና ፍላጎት የሚቆጣጠር፣ ሥራውን
በሚያከናውንበት ወቅት ኃላፊነት የሚሰማው፣ በሚሰራበት ተቋም ውስጥ ህብረተሰቡ ያለውን እምነት
ሊያስጠብቅና ሊያጎለብት የሚችል ነው፡፡
ከፍተኛ የሙያ ሥነምግባርና ችሎታ ያለው ሠራተኛ ሥራውን በጥንቃቄ፣ በትጋት፣ በሙሉ አቅሙ እና
ውጤታማ በሆነ መልኩ ያከናውናል፡፡ ቅንነት ያለው ሠራተኛ ከማታለል፣ ከማጭበርበር፣ ባለው ኃላፊነት
ከመነገድ እና ከሥራው ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆኑ ጥቅሞችን ከመጠየቅና ከመቀበል የራቀ ነው፡፡
2. ታማኝነት
የገቡትን ቃል መጠበቅ፣ የአገሪቱ ህገ-መንግሥት፣ ህጎችና ደንቦች እንዲሁም ለሚሰራበት መ/ቤት ታማኝ
መሆንን ያመለክታል፡፡ ይህ መርህ ኃላፊው ወይም ሠራተኛው ለሥራና ለሥራ ባልደረቦቹ ታማኝ፣
በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ህገ-ወጥ እና ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙ በቸልታ የማያልፍ፣ ከመደበኛ
ሥራው ጋር የጥቅም ግጭት የሚፈጥሩ ተግባራት ከመፈፀም የታቀበ ሊሆን እንደሚገባው ያመለክታል፡፡
3.ግልፅነት
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖች በተሠጣቸው ሥልጣን የመሥራት እና የመንግሥትን ሀብትና
አገልግሎት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለዜጎች ማከፋፈል ወይም ማዳረስ አለባቸው፡፡ ውሳኔዎችን በተቻለ
መጠን ግልጽ እና ምክንያታዊ በማድረግ ሊሰጡ ይገባል፡፡ አንድ መረጃ በሚስጢር ሊጠበቅ የሚገባው
ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡
4. ምስጢር መጠበቅ
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖች ህዝቡ የሚያውቀውን ወይም ሊያገኘው የሚገባውን መረጃ
መደበቅ የለባቸውም፡፡ ሆኖም የመንግሥት ሠራተኞችና ባለስጣኖች በሥራ አጋጣሚ ያወቁትን ምስጢራዊ
ወይም ግላዊ ባህርይ ያለውን መረጃ መግለፅ የለባቸውም፡፡
5. ሐቀኝነት
ሕዝብ በመንግሥት ላይ ለሚኖረው እምነትና ከበሬታ እንደ ምሰሶ የሚያገለግለው የመንግሥት
ሠራተኞችና ባለስልጣኖች ሀቀኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት የገቡትን ቃል
ማክበር፣ ከማታለል፣ ከማጭበርበር ወይም ከሙስና የፀዱ መሆን አለባቸው፡፡
የሀቀኝነትን መርህ ተግባራዊ የሚያደርግ የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን በቅንነት፣ ቃሉን በመጠበቅና
በማክበር ያከናውናል፡፡ ከማጭበርበር፣ ከማታለልና በሥልጣን ከመንገድ የራቀ ነው፡፡ ስጦታን ወይም
መስተንግዶን ለመቀበል የሚያበቃ በቂ ምክንያት ከሌለ ስጦታን አይቀበልም፡፡
6. ተጠያቂነት
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖች ለሚሰጧቸው ውሳኔዎችና ለሚያከናውኗቸው ሌሎች ሥራዎች
በሕዝቡ ይጠየቃሉ፡፡ በተጨማሪም ለሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ማብራሪያ ለመስጠትና በመሥሪያ
ቤታቸው ለሚደረግባቸው ተገቢ ለሆነ ምርመራ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡

7. የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ


የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖች የሚሰጡት ውሳኔና የሚያከናውኑት ሥራ የሕዝቡን ጥቅም እንጂ
የራሳቸውን ወይም የሌላ ሰውን የግል ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን የለበትም፡፡ የመንግስት ሥራና ሥልጣን
ለግል ጥቅም መዋል የለበትም፡፡
8. ሕጋዊ በሆነ ሥልጣን መገልገል
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት የመወሰን ሥልጣን አላቸው፡፡ በሥልጣናቸው መወሰን የሚችሉት
ለመሥሪያ ቤቱ በሕግ ተወስኖ በተሰጣቸው ሥልጣን ብቻ መሆን አለበት፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችና
ባለሥልጣኖች በስልጣናቸው ያለአግባብ መገልገል አይገባቸውም፡፡
9. አድልዎ አለመፈፀም
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት ተገቢና ፍትሃዊ በሆነ አሠራር ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡
የሠራተኛ ቅጥርና ምደባ በችሎታ ወይም በብቃት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ማንኛውም
የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን የሚሰጠው ምክር እና አስተያየት በፍራቻ ወይም በውለታ
መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግሥት መ/ቤቶች ሁሉንም ዜጎች በሕጉ መሠረትና ያለአድልዎ
ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
10. ሕግን ማክበር
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለስልጣናት ሕገ መንግሥቱን የማብከር በመንግሥት የወጡና የሚወጡ
አዋጆችን ደንቦችንና መመሪያዎችን የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡
11. ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት ባለጉዳዮችን በጥሞና በማዳመጥ በማክበርና በትህትና
ለጥያቄዎቻቸው በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ ወይም መፍትሄ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ የመንግሥት
መ/ቤቶች የተገልጋዩን ሕብረተሰብ ፍላጎትና አስተያየት ከግምት በማስገባት አገልግሎታቸውንና
ፕሮግራማቸውን ማሻሻል ማስፋፋት ወይም ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡
12. አርዓያ መሆን
የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት ሥራቸውን ከማንም በላይ አርአያ በመሆን ማከናወን
ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውንም ውጤት በተግባር በማሳየት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ምሳሌ
በመሆን እነዚህን መርሆች ማጎልበትና መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት

You might also like