You are on page 1of 19

TITLE

Written by

Author's Name

Copyright (c) 2023

Draft
information
Contact
information
ምህረት

ክፍል - 4

ደራሲ ዳይሬክተር

ዓለምሰገድ አሰፋ ማቲያስ ባዩ


(CONT'D)

Teaser

1.ውስጥ, ክለብ በር ላይ /የአማን መኪና ውስጥ/ - ምሽት

አማን ክለቡ ፊት ለፊት መኪናው ውስጥ ተቀምጦ ሲብሰለሰል ስልኩ ይጮሀል በፍጥነት ያነሳውና ከስልኩ ውስጥ
የሚነገረውን መረጃ ካዳመጠ በኋላ፡-

አማን
እርግጠኛ ነህ ምንም አልሆነችም?.....ጥሩ የሚፈጠረውን ሁሉ በትኩረት
ተከታተል...ታውቃለህ ጫፏ እንዲነካ አልፈልግም

አማን ስልኩን እያወራ ቤቲ ከክለቡ ወጥታ ዙሪያዋን ታማትርና ወደ እሱ መኪና ፈጠን እያለች ስትመጣ አማን
ስልኩን ይዘጋል ቤቲም የጋቢናውን በር ከፍታ ትገባና በንዴት እየተቀመጠች፡-

ቤቲ
ምን ማድረግህ ነው?

አማን
አንበሲት ተረጋጊና ሲት ቤልትሽን እሰሪ?

የመኪናውን ሞተር ሊያስነሳ ሲል ቤቲ እጁን ይዛ ታስቆመውና፡-

ቤቲ
ጓደኛዬን የት እንዳደረካት ሳትነግረኝ ከዚ ንቅንቅ አንልም!

አማን
ደህነቷን ካወቅሽ አይበቃሽም!...ደርሶ ለጓደኛሽ ተቆርቋሪ አትምሰይ!!

አማን ተኮሳትሮ እጇን ሲያይ ቤቲ በፍርሀት ተውጣ ትለቀውና ሲት ቤልቷን እያሰረች፡-

ቤቲ
ቆይ ደህና መሆኗን በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?

አማን
ቤቴልሄም....አድርጊ የምልሽን ከማድረግ ውጭ ነገሮች ለማወቅ
የምታደርጊውን ጥረት አቁሚ! ይሄን ማድረግ የማትችይ ከሆነ አደጋ
ውስጥ ትወድቂያለሽ! ከዚህ በኋላ ደግሜ አልነግርሽም!!!

ቤቲ
(በፍርሀት)
እሺ እሺ...

አማን
ይልቅ ሲነጋ ሰናይት ፖሊስ ጣቢያ ማመልከቷ ስለማይቀር አንቺ ማለት
ያለብሽን ብጠይቂኝ ይሻላል!
ቤቲ ምንም መልስ ሳትሰጠው ታየዋለች አማንም የመኪናውን ሞተር ያስነሳና ከአካባቢው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።

End of teaser

2. ውስጥ, የነቴዲ ቤት /ሳሎን/ - ምሽት

ምህረት ቀስ እያለች አይኗን ትገልጥና ራሷን ከሳተችበት ስትነቃ ቴዲ ከፊት ለፊቷ ቆሞ የዘውትር ፀሎት ሲያነብ
ታየውና በድንጋጤ ተስፈንጥራ ትነሳለች ቴዲም ደንግጦ እያማተበ፡-

ቴዲ
በስመ አብ ወወልድ...በስመ አብ ወወልድ...አይዞሽ እሺ ሲስቱ አይዞሽ

ምህረት
የት ነኝ...ምን ሆኜ ነው...ማነህ አንተ

ቴዲ
እኔ ቴዲ እባላለሁ የዚህ ቤት ባሉካ ነኝ...መንገድ ላይ ላቦሮዎች
ሲተናኮሉሽ አስጥዬሽ ነው እራስሽን ስትስቺብኝ ግራ ገብቶኝ ወደዚህ
ያመጣሁሽ

ምህረት በድንጋጤ ውስጥ ሆና ከሶፋው ላይ ለመነሳት እየሞከረች፡-

ምህረት
ስለረዳኸኝ አመሰግናለሁ አሁን ግን ወደ ቤቴ መሄድ አለብኝ

ቴዲ
አረ አረጋጊው ነፍሴ ሰአቱን አይተሸዋል ከለሊቱ 8 ሰአት እኮ ነው በዚህ
ሰአት በምንሽ ነው የምትሄጂው

ምህረት
ወይኔ ምህረት ምን ውስጥ ነው የገባሁት

ምህረት ተመልሳ ሶፋው ላይ የምትቀመጥ ሲሆን ቴዲ ከሻንጣ ውስጥ ልብስ መፈለግ ሲጀምር እሷ ደግሞ የቤቱን
ዙርያ ታያለች ቴዲ ከሻንጣው ሺቲ ያወጣና ወደ ምህረት እየወረወረላት፡-

ቴዲ
ሲስቱ እንኳን ነቃሽልኝ እንጂ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም እኔ መኪና
ስጠብቅ ስለማድር ልወጣ ነው ስለዚህ በሩን ከውስጥ ቆልፈሽ ደቅሺና
ጠዋት ወደ ቤትሽ ትነኪዋለሽ

ምህረት የሰጣትን ሺቲ እንደያዘች በእሺታ አንገቷን ትነቀንቃለች ቴዲም በትኩረት ያያትና፡-

ቴዲ (CONT'D)
ምግብ ምናምን መፈወስ ትፈልጊያለሽ?

ምህረት
አይ ምንም አልፈልግም

ቴዲ
ጎሽ እንኳንም አልፈለክሽ በድንጋጤ ወንጌል መድገሜ ሳያንስ በዚህ ደረቅ
ለሊት ምግብ ልታሰሪኝ ነው ብዬ ሀሳብ ይዞኝ ነበር.

ምህረት ምንም ምላሽ ሳትሰጠው ስትቀር ስልኩን ከኪሱ አውጥቶ ፊት ለፊቷ እያስቀመጠው፡-

ቴዲ (CONT'D)
ስልኬ ባትሪ ስለዘጋ ቻርጅ አርጊውና የምትፈልጊው ቦታ
ደውይ....ፓተርን ምናምን የለውም...ደህና እደሪ በቃ...እና ደግሞ ሸኖ
ምናምን ካስቸገረሽ እዛ ላይ መጠቃቀም ትችያለሽ

ምህረት ወደ ሚጠቁማት ቦታ ስታይ ማስታጠቢያ በማየቷ እንደ መገረም ትላለች ቴዲም ፈገግታውን ያሳያትና ቤቱን
ለቆ ሲወጣ ምህረት በፍጥነት ትነሳና በሩን ከቆለፈች በኋላ እዛው በሩን ተደግፋ ተንሸራታ መሬት ላይ ትቀመጥና
በረጅሙ ትተነፍሳለች፡፡

መሸጋገሪያ 1፡- የጠዋቷ ፀሀይ ያረፈችበትን የነምህረት ቤት ውጪያዊ ገፅታ እንመለከታለን፡፡

3. ውስጥ, የነምህረት ቤት /ደረጃና ኮሪደር ላይ/- ጠዋት

ሰናይት በፈገግታ ተሞልታ ቁርስ አቀራርባ እንደጨረሰች ምህረትን ለመቀስቀስ ወደ መኝታ ቤቷ ትሄድና በሩን
ስትከፍት ታጣታለች ግራ እየተጋባች በሩን ትዘጋና ወደ ስእል ስቱዲዮዋ በማምራት በሩን ከፍታ ስታይ እዛም
ታጣታለች ግራ እየተጋባች ወደ መመገቢያ ጠረቤዛው ትመለስና ከተቀመጠች በኋላ ከጠረቤዛው ላይ ስልኳን
አንስታ ‹‹ትንሿ›› ብላ ሴቭ ወዳደረገችው ቁጥር ትደውልና ስልኩ በተደጋጋሚ ከጠራ በኋላ ሲነሳ፡-

ሰናይት
አንቺ በጠዋት ወዴት ሄደሽ ነው?

ዌይተር (V.O)
ይቅርታ የኔ እህት የዚህ ስልክ ባለቤት ትላንት ክለባችን ውስጥ ስልኳን
እና ቦርሳዋን ጥላ ወጥታ ነው ምናልት.......

ሰናይት በድንጋጤ ተሞልታ ከተቀመጠችበት ትነሳች።

4. ውስጥ, የቴዲ ቤት /ሳሎን/ - ጠዋት

ምህረት ልብሷ ላይ ሺቲውን እንደደረበች አልጋው ላይ ተኝታለች የቤቱ በር ሲንኳኳ ግን ባና ትነሳና ወደ በሩ ፈራ


ተባ እያለች ሄዳ ልትከፍት ትልና መልሳ ታመነታለች በሩ በድጋሚ በሀይል ሲንኳኳ ግን የበሩን መክፈቻ ይዛ፡-

ምህረት
ማ..ማ...ማነው?

5. ውጪ, የቴዲ ቤት /ግቢ ውስጥ/ - ጠዋት

ቲጂ የተባለች ሴት በሩ ላይ የቆመች ሲሆን የሴት ድምፅ ስትሰማ ግራ በመጋባት ተሞልታ፡-

ቲጂ
እ? ማነሽ?...አንቺ ራስሽ ማነሽ ባክሽ?....

ምንም ምላሽ ባለመስማቷ በንዴት ተሞልታ፡-


ቲጂ (CONT'D)
ሄይ ሴትዮ እያናገርኩሽ እኮ ነው....ወይኔ ቲጂ ጭራሽ ማነሽ
ታስብልልኛለህ?...ና ውጣ አንተ ደፋር ዛሬ አለቅህም

ምህረት ከውስጥ እንደቆመች በፍርሀት ውስጥ ሆና፡-

ምህረት
እረ እናት እኔ ?....

ቲጂ
እናት አትበይኝ አንቺ ውሻ ነይ ውጩ ብዬሻለሁ ዛሬ? እሱንም ውጣ
በይው!

ምህረት የምትመልሰው ጠፍቷት ዝም ትላለች ቲጂ ግን ይበልጡን ተናዳ ድንጋይ ታነሳና በሩን በሀይል መደብደብ
ስትጀምር ቴዲ ደግሞ ዳቦና እንቁላል ይዞ ወደ ግቢው ሲገባ የቲጂን ሁኔታ ሲያይ ተደናግጦ፡-

ቴዲ
ቲጂ...ምንድን ነው ምን ሆነሻል?

ቲጂ ቴዲን ስታየው ግራ ተጋብታ ታፈጥበትና፡-

ቲጂ
ማናባህን ነው አስተኝተህ የወጣህልኝ ባክህ

ቴዲ ቲጂ ነገሩን በሌላ መልኩ እንደተረዳችው ይገባውና መሳቅ ይጀምራል ቲጂም ይበልጥ ግራ ይገባታል፡፡

6. ውስጥ, ፖሊስ ኮሚሽን /የመርማሪ ቢሮ/- ጠዋት

ቤቲና ሰናይት አብርሀም ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው ለፍራኦል ቃላቸውን እየሰጡ ሲሆን አብርሀም ፈንጠር ብሎ ቆሞ
የሚወራውን በትኩረት ይሰማል፡-

ፍራኦል
ይሄ ጉዳይ ከአቶ አማን ጋር ግንኙነት ይኖረዋል ብለሽ ታስቢያለሽ?

ሰናይት
ያለምንም ጥርጥር እሱ ነው ሌላ ሊያስጠፋት የሚችል ምክንያት የለም!

ፍራኦል
ሰናይት አቶ አማን ከተፈታ በኋላ በተፈጠረው ነገር እህትሽ መረበሽ
ውስጥ ገብታ ስለነበር ምናልባት በጭንቀት ምክንያት ለመጥፋት አስባ
ቢሆንስ ብዙ ሰዎች እንደዚህ ያደርጋሉ ብዬ ነው።

ሰናይት
እህቴ በጣም ጤነኛ ልጅ ናት! በጭራሽ እንደዚህ አይነት ተራ ነገር
አታደርግም።

ፍራኦል
ምን ያህል እርግጠኛ ነሽ?
ሰናይት
በጣም እርግጠኛ ነኝ!

አብርሀም በንዴት ተሞልቶ መንቆራጠጥ ይጀምራል ፍራኦልም ቀና ብሎ አብርሀምን ካየ በኋላ ወደ ቤቲ በመዞር፡-

ፍራኦል
ስንት ሰዓት ላይ ነበር ከቤት የወጣችሁት?

ቤቲ
በግምት ወደ 4 ሰዓት አካባቢ።

ፍራኦል
ምክንያታችሁ ምን ነበር?

ቤቲ
በጣም ተጨንቃ እንቅልፍ እንቢ ብሏት ነበር ከዛም ደወለችልኝና ወጥተን
እንድንጠጣና ከጭንቀቷ መገላገል እንደምትፈልግ ነገረችኝ በጣም
የደከመኝ ቢሆንም ሁኔታዋ ስላሳዘነኝ እሺ አልኳት!

ፍራኦል
ምን እንዳስጨነቃት አልነገረችሽም?

ቤቲ
በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆና ስሜቷን ከመጠበቅ ውጪ ልጠይቃት አልፈለኩም

ፍራኦል
ስትገምቺው ግን ምን ያስጨነቃት ይመስልሻል!

ቤቲ
እኔንጃ መገመት ይከብደኛል።

ፍራኦል
መጨረሻ እንዴት ነው የተለያያችሁት?

ቤቲ
ሁለታችንም በጣም ጠጥተንና ሰክረን ነበር በመሀል ከዚ በፊት
የማውቀው የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ የነበረን ሰው አገኘሁ ከሱ ጋር ብዙ
ጠጣን እስከዛ ሰዓት ድረስ አብረን እንደነበርን አስታውሳለሁ...ከራሴ
ይልቅ ለሷ ትኩረት ልሰጥ ይገባ ነበር.....ወይኔ ጓደኛዬ

ድንገት ተንሰቅስቃ ስታለቅስ ሰናይትም እንባዋ ይመጣል ፍራኦልም በሀዘኔታ ተሞልቶ፡-

ፍራኦል
አይዞሽ....መለያያታችሁን ያወቅሽው መቼ ነው።

ቤቲ
ጠዋት ያልኩህ ሰው ቤት ራሴን አገኘሁት ከዛ ሰኒ ደውላ መጥፋቷን
ነገረቺኝ እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ እንደዚህ አይነት ምሽት አሳልፌ
ስለማላውቅ ራሴን እስክረሳ ነው ነገሮችን ሳደርግ የነበረው እባካችሁ
ጓደኛዬን አግኙልኝ አለዛ ፀፀቱን አልችለውም!
ቤቲ መልሳ ማልቀስ ስትጀምር አብርሀም በንዴት ተሞልቶ ክፍሉን ለቆ ይወጣል፡፡

7. ውጪ, ፖሊስ ኮሚሽን /ኮሪደር ላይ/ - ጠዋት

አብርሀም በንዴት ተሞልቶ ከክፍሉ ከወጣ በኋላ ኮሪደሩ ላይ ቆሞ ሲብሰለሰል ሰናይት ከምርመራው ክፍል ትወጣና
ወደ አብርሀም ተጠግታ እየቆመች፡-

ሰናይት
አብርሽ ለምን አታምነኝም ከእሱ ውጪ ማንም እንደዚህ ሊያደርግ
አይችልም!

አብርሀም
እኔም እንዳንቺ ነው የማስበው ግን ከዚህ በኋላ ይሄን ሰው
የምንታገልበትን መንገድ መቀየር ይኖርብናል እጁ ረጅም ስለሆነ ፊት
ለፊት ልንፋለመው አንችልም

ሰናይት
(በንዴት ተሞልታ)
እኛ ነን ፊት እየሰጠን የሌለውን አቅም አለው እያልን እዚህ
ያደረስነው...ወይኔ ሰናይት!...እውነቴን ነው የምልህ ጫፏን ነክቷት ከሆነ
የመጨረሻው ነው የሚሆነው ለእህቴማ መሆን ካቃተኝ የውብዳር ተፈሪ
አልወለደችኝም!

አብርሀም
ሰኒ ተረጋጊ አንቺ ራስሽን መጉዳት የለብሽም

ሰናይት በንዴት ተሞልታ በምትብሰለሰልበት ግዜ ቤቲ ከፍራኦል ጋር በመሆን ከምርመራ ክፍሉ ይወጣሉ፡፡

8. ውስጥ, የቴዲ ቤት /ሳሎን/ - ጠዋት

ምህረትና ቲጂን በቤቱ ውስጥ የምንመለከት ሲሆን ቲጂ ቡና እያፈላች ምህረትን አፈር ብላ በማየት፡-

ቲጂ
እንዴት ብዬ ይቅርታ እንደምጠይቅሽ አላውቅም?

ምህረት
እረ ምንም አላጠፋሽም

ቲጂ
እርሜን ቤተሰቦቼ ጋር ላድር ብሄድ ሌላ ሴት ደርቦ ጠበቀኝ ብዬ እኮ ነው
እንደዛ ላብድ የደረስኩት...ታውቂያለሽ ቴዲን ከልክ በላይ ነው
የማፈቅረው በሱ የመጣ ምንም ነገር ቢሆን መቋቋም አልችልም!

ምህረት
ደስ ይላል!

ቲጂ
የሚገርምሽ ነገር ግን በፊት እንደዚህ አልነበርኩም....አሁን ሳስበው
በጣም ይገርመኛል!

ምህረት
እንዴት?

ቲጂ
በፊት የሰፈሩ ጉልበተኛ ስለነበር በጡንቻው ብቻ የሚያስብ አድርጌ
ስለማስበው በጣም ነበር የምጠላው...አቤት እኔን ለማግኘት የከፈለው
ዋጋ....ህንድ ፊልም ታያለሽ?

ምህረት
አይ አይቼ አላውቅም።

ቲጂ
ውይ ተበድለሻላ የምታይ ቢሆን ኖሮ የምልሽ ይገባሽ ነበር ብቻ ግን ምን
አለፋሽ ባጭሩ የኔ እና የሱ ህይወት የህንድ ፊልም ነበር የሚመስለው!

ምህረት
እንዴት?

ቲጂ
ከስንት ጎረምሳ እ...ከወንድሞቼ...ከፖሊሶች ሳይቀር እየተፋለመ ነው
የራሱ ሊይደርገኝ ሲሞክር የነበረው።

ምህረት
በጉልበት? ይሄ እኮ ልክ አይደለም? እውነት ለመናገር መብትሽን መጣስ
ነው!

ቲጂ
ልክ ነሽ! እኔም ፍቅር በጉልበት እንደማይሆን እንዲያውቅ እፈልግ
ስለነበር ጭራሽ እልህ ውስጥ እየከተትኩ እንደ እብድ ነበር የማደርገው

ቲጂ ሰትስቅ ምህረትም አብራት ስትስቅ ትቆይና፡-

ምህረት
እና እንዴት አብራችሁ ሆናችሁ!

ቲጂ
ነገሮች ሲባባሱ እራሱን መጉዳት ጀመረ ያኔ ቀርቤ ላረጋጋው ሞከርኩ
ታውቂያለሽ ሴት ልጅ ብልሀተኛ ናት የሚባለው እውነት ነው ስፈልግ
ውሀ ስፈልግ እሳት አደርገው ጀመር ከዛ አሳዘነኝ ጉልበት ብቻ እንዳልሆነ
ገባኝ የሆነ የማላውቀውን ነገሩን አገኘሁት ከዛ ቅድም እንዳየሽው
እስክሆን ድረስ ከንፌልሽ ቁጭ

ምህረት መሳቅ ትጀምራለች ቲጂም በራሷ እየሳቀች ባለበት ግዜ ቴዲ ከውጭ ይገባና፡-

ቴዲ
ቡናውን ትታችሁ ቀደዳ ጀመራችሁ አይደል?

ቲጂ
ትንሽ ፈታ ላርጋት ብዬ እኮ ነው

ቴዲ
በይ ቶሎ አጠጪንና ወደ ቤቷ እንሸኛት

ቲጂ ቡናውን መቅዳት ትጀምራለች።

9. ውስጥ, መንገድ ላይ /የአብርሀም መኪና/ -ረፋድ

አብርሀም ከጎኑ ሰናይትን ከጀርባ ደግሞ ቤቲን አስቀምጦ መኪናውን እያሽከረከረ ሲሆን ሰናይት መንገድ መንገዱን
እያየች ሀሳብ ውስጥ ትገባና ንግስትን ያገኘቻት ቀን ያወሩትን ማስታወስ ትጀምራለች፡-
Flash back start

F 9.A. ውስጥ, ጭለማ ቦታ /የንግስት መኪና ውስጥ/ - ምሽት

ንግስት ሰናይት ላይ አፍጥጣ፡-


ንግስት
ከወሰንሽና ስራችንን ከጀመርን በኋላ ግን ወደኋላ መመለስ በፍጹም
አትችይም።
ሰናይት
ለምን ወደ ኋላ እላለሁ?
ንግስት
እንደነገርኩሽ ስራውን የምንሰራው በተለየ መንገድ ነው ይሄን ለማድረግ
ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል! ባለን ልምድ መሰረት ብዙ እርግጠኛ ያልሆኑ
ስሜታዊ ሰዎች ይመጡና ከ 15 ቀን በኋላ ሀሳባቸውን ሊቀይሩ
ይሞክራሉ ይሄን ማድረግ ደግሞ አይቻልም... ምክንያቱም ለኛ አደጋ
አለው!
ሰናይት
ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል?
ንግስት
እሱ በሰውዬው ማንነትና ላይ ይመሰረታል...የሰውዬው አቅም ከፍተኛና
የመገኝት እድሉ ጠባብ ከሆነ ጊዜ ይፈጃል! አቅሙ ካነሰና በቀላሉ
የሚገኝ ተራ ሰው ከሆነ ደግሞ በተቃራኒው ቶሎ ያበቃል። ግን ማንም
ቢሆን ከ 2 ወር በላይ አይፈጅም።
ሰናይት
ጊዜው አልበዛም?
ንግስት
ስራችን ንጹህ እና እጅግ ተፈጥሮአዊ ነው። ብዙውን ጊዜ የሚወስደው
የሰውዬውን ማንነት እና ምንነት በማጣራት ላይ ነው። ምን ይወዳል?
ምን ይጠላል? ምን ይፈልጋል? የጤናው ሁኔታ? ሊያጠፋው ይችላል
ብለን የምናስበው ድክመቱ የቱ ነው የሚለውን ቀርበን ማጥናት
ያስፈልጋል። ያን ጊዜ ስራው ንጹህ ይሆናል እንኳን ፖሊስ ሟቹም
ድጋሜ መነሳት ቢችልና ቢጠየቅ ጉዳዩ በሰው እጅ እንደተፈጸመ
አያውቅም።
ንግስት ስልኳ ሲጠራ ንግግሯን አቁማ ወደ ስልኳ ታያለች።
Flash back end

የሰናይት ስልኳ እየጠራ ቢሆንም እሷ ግን ሀሳብ ውስጥ በመሆኗ አትሰማውም አብርሀምም ሁኔታዋ ግራ አጋብቶት
ነካ በማድረግ ከነበረችበት ሀሳብ ያነቃትና ስልኳን ያሳያታል ሰናይትም ስልኳ እየጠራ መሆኑን ስታውቅ ፈጠን ብላ
ታነሳውና፡-

ሰናይት
ሄሎ

ምህረት V.O
ሄሎ ሰኒ!

ሰናይት
ምሩ!...የኔ እናት አለሽ? ምን ሆነሽ ነው ግን?...ቆይ የት ሆነሽ ነው?
አስጨነቅሽኝ እኮ! ደህና ነሽ ግን አይደል?

ምህረት
ደህና ነኝ እህቴ ተረጋጊ ......

ሰናይት በደስታ ተሞልታ ትፍለቀለቃለች።

10. ውስጥ, የአማን ድርጅት /ቢሮው ውስጥ/ - ቀን

አማን ፋይል እያገላበጠ በሚመለከትበት ግዜ አብይ ሌላ ፋይል ይዞ በሩን ያንኳኳና ይገባል አማንም በፈገግታ
ተሞልቶ እያየው፡-

አማን
እንኳን ደህና መጣህ?

አብይ
እንኳን ደህና ቆየህኝ!!

አማን
አረፍ በል!

አብይ
(ፋይሉን ሰጥቶት እየተቀመጠ)
ይሄ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ለተከናወኑ ግዢዎችን የወጣውን ወጪ
የሚያሳይ ዝርዝር ነው

አማን
በጣም ጥሩ በኋላ በደንብ አያቸዋለሁ።

ፋይሉን ያስቀምጥና ቀና ሲል አብይ ሀሳብ ውስጥ መሆኑን ያየውና፡-


አማን (CONT'D)
ምነው?....ፊትህ ልክ አይደለም

አብይ
እንቅልፍ አጥቼ ነው ያደርኩት።

አማን
በሰላም?

አብይ
ትላንት ብዙ ጥያቄ ነው የፈጠርክብኝ እ…ጊዜ ካለህ አንዳንድ ነገሮችን
ብናወራ ብዬ ነበር

አማን
እምነት ብቻ አይበቃም? ለሁሉም ጥያቄዎችህ መልስ ልሰጥህ አልችልም!

አብይ በልመና አይን ያየዋል አማንም አሰብ አድርጎ፡-

አማን (CONT'D)
እሺ በቃ ማታ ላይ ተረጋግተን እናወራለን!...ግን
ብዙ ነገር ይነግረኛል ብለህ እንዳጠብቅ።

አብይ
(በፈገግታ ከተቀመጠበት ይነሳና)
እኔም ብዙ ማወቅ አልፈልግም ማታ እንገናኝ መልካም ስራ

አማን በፈገግታ ተሞልቶ ሲያየው አብይ ከቢሮው ይወጣል፡፡

11. ውስጥ, የምህረት ቤት /ግቢ ውስጥ/ - ቀን

ሰናይት አብርሀምና ቤቲን በግቢው ውስጥ የምንመለከታቸው ሲሆን ሰናይት አላስችል ብሏት ወዲህ ወድያ ትላለች
ድንገት ግን የግቢው በር ሲንኳኳ ሰናይት በፍጥነት ሮጣ ሄዳ በሩን ስትከፍት ምህረት ሺቲ እንደለበሰች ቴዲና ቲጂን
አስከትላ ወደ ግቢው ትገባለች። ሰናይትም በደስታ ተሞልታ ትጠመጠምባትና አገላብጣ በስስት እያየቻት፡-

ሰናይት
ደህና ነሽልኝ አይደል...እውነት ምንም አላደረጉሽም?

ምህረት
አዎ ደህና ነኝ ምንም አልሆንኩም!

ሰናይት
እርግጠኛ ነሽ ምሩዬ? ወይ ሀኪም ቤት እንሂድ?

ምህረት
ደህና ነኝ አልኩሽ እኮ ሰኒ ይልቅ ተዋወቂያቸው
(ወደ ቴዲ ዞራ እየጠቆመች)
ቴዲ ይባላል እሱ ነው ማታ ከብዙ ነገር አድኖኝ ቤቱ ያሳደረኝ እሷ ደግሞ
ቲጂ ትባላለች ሚስቱ ናት
ሰናይት
ሰናይት እባላለሁ የምህረት እህት ነኝ ስላደረጋችሁላት ነገር ሁሉ
እግዚአብሔር ውለታችሁን ይክፈለው

ሁለቱንም አቅፋ ሰላም ትላቸዋለች አብርሀምና ቤቲ ሁኔታቸውን ይመለከታሉ።

መሸጋገሪያ 2፡- በምሽት የከተማዋን ገፅታ እንመለከታለን፡፡

12. ውስጥ. ባርና ሬስቶራንት /ባር ውስጥ/- ምሽት

በዘመናዊው ባር ውስጥ አብይ አማንን በጥያቄ አይን እየተመለከተው ሲሆን አማን እየጠጡት ካለው ውስኪ ላይ
አይኑን ሳያነሳ፡-

አማን
ተጨማሪ ማወቅ የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው?

አብይ
መጀመሪያስ ምን ያወኩት ነገር አለ? ጭንቅላቴን እንደሆነ በጥያቄ
ሞልተህዋል!

አማን
አሁን መስማት የምትፈልገውን ብቻ ጠይቀኝ ከዚህ በኋላ ስለዚህ ጉዳይ
አንስተን ማውራት የለብንም

አብይ
መጀመሪያ እንደማትዋሸኝ ቃል ግባልኝ!!

አማን
መመለስ የማልችለውን ጥያቄ አንስተህ እንድነግርህ ልታስገድደኝ
እንዳትሞክር እንጂ አልዋሽህም

አብይ
እሺ!....የመጀሪያው ጥያቄ ከምህረት የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው?

አማን
(ፈገግ ይልና)
ከከባዱ ጀመርክ....እሱን ባታውቀው ይሻላል።

አብይ
(ኮስተር ብሎ)
አማን...ይሄንን እንድትደብቀኝ አልፈልግም...ምህረትን የቀረብካት ከሷ
ለምትፈልገው ጥቅምህ ብቻ ብለህ ነው? እውነት ምንም አይነት ፍቅር
ውስጥህ የለም?

አማን ስሜቱ እጅግ ይለወጣል ምን መገናገር እንዳለበት ግራ ይጋባል አብይም ስሜቱን አስተውሎ፡-

አብይ (CONT'D)
ለምን አልወዳትም ብለህ ዋሸኸኝ?
አማን
ምክንያቱም ልቀበለውና ልታረቀው የምፈልገው እውነት እሱ ስለሆነ
ምህረትን በማፍቀሬ ብዙ የማጣው ነገር አለ...አብይ ከራሴ እና ከአላማዬ
ጎትቶ ያስቀረኝ የእሷ ፍቅር ነው

አብይ
ምን ማለት ነው?

አማን
የመጀመሪያ ሰሞን ፍላጎቴ ፍቅር አልነበረም ከዛ ይልቅ ከሷ የምፈልገውን
ማግኘት ላይ ነበር ትኩረቴ...ቅርርባችን በጨመረ ቁጥር ነገሮች
እየተለወጡ ሄዱ!

አብይ በሚሰማው ነገር ግራ ተጋብቶ አማንን እያየ፡-

አብይ
ቆይ ግልፅ አርግልኝ...አውነቱ የትኛው ነው ትላንት የነገርከኝ ወይስ?...

አማን
እውነቱ ምህረትን አሁንም ድረስ አፈቅራታለሁ። ፍቅሯ ግን ከራሴ
እያጣላኝ ልተካው የማልችለውን ነገር እያሳጣኝ ነው!

አብይ
ምንድን ነው እሱ ልትተካው የማትችለው ነገር?

አማን
ብነግርህ ሚስጥር መጠበቅ ትችላለህ!

አብይ
አማን!!...እኔ እኮ ጓደኛህ ብቻ አይደለሁም ወንድምህ ነኝ! ይሄን ሁሉ
ነገር የምጠይቅህ ያንተን ሚስጥር የማወቅ ጉጉት ኖሮኝ ሳይሆን ችግርህን
ለመካፈልና በቻልኩት አቅም አንተን ለማገዝ ስለምፈልግ ነው! አንተ
እንደዚህ እየሆንክ ደስተኛ የምሆን ይመስልሀል?

አማን
(ትኩር ብሎ አይቶት)
ደግመህ አስብ ይሄን ነገር ከነገርኩህ በኋላ ከጎኔ ከመቆም ውጭ አማራጭ
አይኖርህም!

አብይ
ከጎንህ ለመቆም ሁለቴ ማሰብ አይጠበቅብኝም!

አማን በአይኑ ዙሪያውን ይቃኝና ድምፁን ቀነስ አድርጎ፡-

አማን
ወላጅ አባቴ አልሞተም በህይወት አለ!

አብይ
(በድንጋጤ ፈጦ)
ምን?
አማን
(አይኑ እንባ እያቀረረ)
አዎ መኖር ከተባለ በህይወት አለ...በከፋ ህመም እየተሰቃየ አይኑ
ውጪውን ሳያይ የፀሀይን ብርሃን እንደናፈቀ ብቻውን ቤት ውስጥ
ተዘግቶ በህይወት አለ

አማን አይኑ እንባ ያቀርና ከተቀመጠበት ተነስቶ እራሱን ለማረጋጋት እየሞከረ ወደ መታጠቢያ ቤት ያመራል፡፡

13. ውስጥ, የነምህረት ቤት /ሳሎን ውስጥ/ - ምሽት

በሳሎኑ ሶፋ ላይ ሰናይት ምህረትን እግሯ ላይ ጋደም እንድትል አድርጋት ፀጉሯን እየደባበሰቻት ፊልም የሚያዩ ሲሆን
ምህረት አይኗ ቴሌብዥኑ ላይ ቢሆንም ሀሳቧ ግን እነቴዲ ቤት በነበረችበት ግዜ ከቲጂ ጋር ያወሯቸው ነገሮች
ያስታውሳል፡-

ቲጂ
ከስንት ጎረምሳ እ...ከወንድሞቼ...ከፖሊሶች ሳይቀር እየተፋለመ ነው
የራሱ ሊይደርገኝ ሲሞክር የነበረው።
ምህረት
በጉልበት? ይሄ እኮ ልክ አይደለም? እውነት ለመናገር መብትሽን መጣስ
ነው!
ቲጂ
ልክ ነሽ! እኔም ፍቅር በጉልበት እንደማይሆን እንዲያውቅ እፈልግ
ስለነበር ጭራሽ እልህ ውስጥ እየከተትኩ እንደ እብድ ነበር የማደርገው

ቲጂ ሰትስቅ ምህረትም አብራት ስትስቅ ትቆይና፡-


ምህረት
እና እንዴት አብራችሁ ሆናችሁ!
ቲጂ
ነገሮች ሲባባሱ እራሱን መጉዳት ጀመረ ያኔ ቀርቤ ላረጋጋው ሞከርኩ
ታውቂያለሽ ሴት ልጅ ብልሀተኛ ናት የሚባለው እውነት ነው ስፈልግ
ውሀ ስፈልግ እሳት አደርገው ጀመር ከዛ አሳዘነኝ ጉልበት ብቻ እንዳልሆነ
ገባኝ የሆነ የማላውቀውን ነገሩን አገኘሁት ከዛ ቅድም እንዳየሽው
እስክሆን ድረስ ከንፌልሽ ቁጭ
ምህረት በምታስበው ነገር እየተገረመች ባለችበት ግዜ የሰናይት ስልክ ይጮህና ከሀሳቧ ያባንናታል ሰናይት በፍጥነት
ስልኩን ታነሳና፡-

ሰናይት
ሄሎ...እሺ አሁኑኑ መጣሁ

ስልኩን ትዘጋና ከተቀመጠችበት መነሳት ስትጀምር ምህረት ግራ ተጋብታ እያየቻት፡-

ምህረት
ወዴት ልትሄጂ ነው?
ሰናይት
እዚሁ ነኝ መጣሁ

ሰናይት የምህረትን ቀጣይ ምላሽ ሳትሰማ ከሳሎኑ ትወጣለች፡፡

14. ውስጥ, የአብይ ቤት አካባቢ /የአማን መኪና ውስጥ/ - ምሽት

የአማን መኪና የአብይ ቤት አካባቢ መጥቶ ይቆማል ሁለቱም ለጥቂት ቆይታ ዝም ተባብለው ይቆዩና አማን በረጅሙ
ተንፍሶ፡-

አማን
ቆይ አንተ ብትሆን የቱን ትመርጣለህ?

አብይ
(አሰብ አድርጎ)
ምርጫው ከባድ ነው ግን ሁለቱንም ማግኘት የምችልበትን መንገድ
እፈልጋለሁ!

አማን
እሱን ለማድረግ ስሞክር ነው ራሴን ያጣሁት!

አብይ
ያልሞከርከው ነገር እንዳለ ይሰማኛል።

አማን
ምን?

አብይ
ለምህረት ግልጽ ሁንላት! ከሷ የምትፈልገውን ነገር ምንም ይሁን ምን
ፊት ለፊት ጠይቀህ ለማግኘት ሞክር! ላደረስከው ጥፋት ለሄድክበት
መንገድ ሁሉ ይቅርታ በል! ያኔ እሷንም ማግኘት አባትህንም ማትረፍ
የምትችል ይመስለኛል

አማን
ይሄን አድርጌ ነገሮች ባይሆኑስ?

አብይ
ቢያንስ ራስህን አታጣም!

አማን በረጅሙ ይተነፍሳል።

15. ውጪ, መንገድ ላይ /ጭር ያለ ቦታ/ - ምሽት

ሰናይት ፊቷን በሻሽ ሸፋፍና አንድ ሳምሶናይት ነገር ይዛ አስፋልቱ ዳር ቆማ የምንመለከታት ሲሆን ከዚህ በፊት
ንግስትን ያገኘችበት Rava4 መኪና እሷ ወዳለችበት መጥቶ ይቆምና የኋላው በር ይከፈትላታል ሰናይትም ፈራ ተባ
ብላ ስትገባ መኪናው መንቀሳቀስ ይጀምራል።

16. ውስጥ, ባርና ሬስቶራንት /ሬስቶራንት ውስጥ/ - ምሽት


ቤቲ ብቻዋን ተቀምጣ እየተብሰለሰለች ወይን ስትጠጣ የምናያት ሲሆን ደበቅ ያለ ቦታ ላይ የተቀመጠው አብርሀም
ኮፍያውን ደፍቶ በርቀት እየተመለከታት እናየዋለን ቤቲ ቴክስት ሲገባላት ስልኳን አንስታ ትመለከትና ሂሳብ ከፍላ
ትወጣለች አብርሀምም ይከተላታል።

17. ውስጥ, ጭር ያለ ቦታ /RAVA4 መኪና ውስጥ/ - ምሽት

ሰናይት ይዛው የነበረውን ሳምሶናይት ጋቢና ያለው ሹፌር ማንነቱ ሳይታይ ከፍቶ እያየው ሲሆን ውስጡ በገንዘብ
ተሞልቷል ፊቱን ሳያዞር ብሩን እያየ፡-

ሰውየው
አለቃ ገንዘቡ ልክ ነው።

ንግስት
(ለሰናይት እጇን ዘርግታላት)
ስራው ተጀምሯል በአጭር ጊዜ አማን የሚባል ሰው ከመኖር ወዳለመኖር
እንቀይረዋለን

ሰናይት ደስታና ፍርሀት በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ ሆና የንግስትን እጅ ትጨብጣለች።

18. ውስጥ, መንገድ ዳር /አማን መኪና ውስጥ/ - ምሽት

ቤቲ ከባሩ ወጥታ ወደ አማን መኪና ውስጥ ትገባና፡-

ቤቲ
እንደዚህ በአደባባይ መገናኘቱ ጥሩ ነው ትላለህ? የምትፈልገውን ነገር
በስልክ ልትነግረኝ ትችል ነበር እኮ!

አማን
ከዚህ በኋላ ካንቺ ምንም አልፈልግም።

ቤቲ
ምን?...ማለት?...ምን አጠፋሁ?

አማን
ምንም አላጠፋሽም...ግን ምህረትን ምን ያህል እንደማፈቅራት
ታውቂያለሽ! ስለዚህ ከዚህ በላይ ላስጨንቃት አልፈልግም የሚሆን ከሆነ
የምፈልገውን ነገር በፍቃዷ ለመውሰድ ወስኛለሁ።

ቤቲ ግራ በመጋባት ተሞልታ አማን ላይ ታፈጣለች፡፡

CLIFF HANGER

19. ውጪ, መንገድ ዳር /የአማን መኪና የቆመበት አካባቢ/ - ምሽት

አብርሀም ቤቲና አማን መኪና ውስጥ ሲያወሩ በማየቱ ሲገረም ይቆይና ስልኩን አውጥቶ ፎቶ ሲያነሳቸው ይታያል።

You might also like