You are on page 1of 4

የግል የህይወት ታሪክ

እኔ አቶ ያለው አሰፋ ከአባቴ አቶ አሰፋ በላይነህ እና ከእናቴ ከወ/ሮ እቴቴ ላቀ ጥር 16 ቀን 1978 ዓ.ም በአማራ ክልል
ሰ/ሸዋ ዞን መርሀቤቴ ወረዳ ኮራ ወንጭት ቀበሌ ልዩ ስሙ ደብር በምትባል ቦታ ተወለድኩ። እኔ ለቤተሰቦቼ 4ኛ ልጅ
ስሆን በአጠቃላይ 4 ወንድምና 4 እህቶች ማለተም ከእኔ በላይ 2 ወንድምና 1 እህት እንድሁም ከእኔ በታች ደግሞ 2
ወንድም እና 3 እህቶች አሉኝ። እኔ ዕድሜዬ ገና 11 ዓመት እያለሁ ነበር አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን። ታዲያ
አባታችን ከመታመሙ በፊት እስከ ሰኔ 1989 ዓ.ም ያዘመረው አዝመራ እንክብካቤ ሳያገኝ በተለይ በወቅቱ አብሮን
የነበረው የኔ ታላቅ ወንድም ደምሰው ገና ብዙም ለስራ ስላልደረሰ እናታችንም አባታችንን በማስታመም አዝመራው
ዉድማ በልቶት ቀረ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጣም ከባድ ድህነት በቤታችን ገባ፤ በጣም ከባድ። በአካባቢው ባህል መሰረት
ከበርቴ ወይም ሃብታም ከሚባል ሰው ቀጣይ እከፍላለሁ እየተባለ ብድር እየተወሰደ ክፉ ቀል ይታለፍ ነበር ነገር ግን
የእኛ አባት በህይወት ስለሌለ እንድሁም ማን ሰርቶ ይከፍለናል በማለት ፍራቻ እናታችን ብድር ለመጠየቅ ስትሄድ ጨርሰን
ለሰው ሰጠነው አሁን የለንም ምናምን በማለት ይመልሷት ነበር። እኛም ይዛ ትመጣለች እያልን ስንጠብቅ ባዶ እጇን ፊቷ
ተለውጦ፣ ጠቁሮ እና አዝና ትመለሳለች። ያ ፊቷ ዛሬም ይታየኛል እኛን ለማስደግ ያልገባችበት ቤት፣ ያልወጣችው ተራራ፣
ያልሄደችበት መንገድ አልነበረም። በዚህ መሃልም ደግሞ ከስንት አንድ መቼም አይጠፋም ነበርና በሰፈራችን ደበበ
እንግዳወቅ በአሁኑ ስሙ ነገሰ እንግዳወርቅ የሚባል ለኛ በአባታችን በኩል የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው ነበረ፤ ሁሌ
የማያሳፍረን፤ ስታገኙ ትከፍላላችሁ፣ በጉልበታችሁ የምትችሉትን ያህል ታግዙኛላችሁ፣ ፍየሎቹን እናንተ የርቢ ያዟቸው፣
ወዘተረፈ እያለ ያንን ክፉ ቀን እንድናልፍ ያደረገው ነገር ይህ ነው ተብሎ በዚች ጽሁፍ ለመጻፍ የሚቻል አይደለም፤
በጣም ብዙ ነገር ነው ያደረገልን፤ በጣም ብዙ። እንዳው እኔ እንኳን በበኩሌ በግል በዚያን ዕድሜዬ አንድ ቀን
ያደረግሁትንና የማልረሳውን ላንሳ፤ ዓመት በዓል እየደረሰ ነበር እናም ልብሴ በሙሉ ላዬ ላይ ተበጫጭቆ አልቋል
ደበበ/በአሁኑ ስሙ ነገሰ/ እስኪመጣ መንገድ ላይ ጠበቅሁትና “አበይ” አልኩት(ታላቅን አበይ፣አብዬ፣ጋሽዬ ወዘተ በማለት
ነውና የምንጣራው አበይ እለው ነበር) አቤት አለኝ ልብስ የለኝም ይሄ የምታየው ነው ያለኝ ግዛልኝ አልኩት፤ ምንም
ሳያቅማማ እሺ አለኝ፣ ሌላ ጊዜ ገበያ ሄዶ ልብሱን ገዝቶ አምጥቶ ሰጠኝ ደስ አለኝና አመሰገንኩት ፍየሎቹን በደንብ ጠብቅ
እንድረቡና ብዙ እንዲሆኑ እሽ? አለኝ እሺ አልኩት። እናም እኛ ምንም እንኳን ያንን ሁሉ ዉለታ የመክፈል አቅም
ባይኖረንም ሁሉን ሰጭ የሆነው ፈጣሪ ዉለታውን እየከፈለዉ እሱንም በሞገስ አኑሮት እስካሁን በሰፈሩ በክብር ምንም
ሳይጎድልበት ይኖራል፤ አሁንም ፈጣሪ በሰላም ቀሪ ዘመኑን ባርኮ ቀጣይ ይህወቱን እንደተስተካከለ መጨረሻዉን
እንዳሳምርለት ወደ ፈጥሪዬ እጸልያለሁ። ስንቱን ልጻፍ ብቻ ከባድ ጊዜ ነበር። ሌላም አንድ ሰው ነበረ የደበበ/የነገሰ/
እንግዳወርቅ የአያቱ ወንድም ልጅ አባቡ ጉልላት የሚባል እሱም ብዙዉን ጊዜ በጉልበት ስራ ማለትም በቀን ስራ ሂሳብ
ታላቅ ወንድሜና እናቴ እርሱ ጋር እንድሰሩ እያደረገ ሲያበድረን ነበረ፤ ምክንያቱም በወቅቱ የቀን ስራ እንኳን የጠፋበት
ወቅት ስለነበረ በጣም ከባድ ወቅት ነበር። እናታችን እኔ አሁን በልቻለሁ እናንተ ብሉ እያለች ያገኘቻትን ሁሉ ለኛ ለልጆቿ
ነበር የምታካፍለን፤ እሷ ግን ጾሟን ነበር ለካ የምታድረው። አይ እኩል እናት ሁሉም እናት እናት ነው፤ እኛ ልጆቿ
እንዳንጎዳባት አንዱ ፈጥኖ በልቶ ሌላውን እንዳይጎዳ በማለት ያገኘቻትን አዘጋጅታ ለየብቻ ነበር የምትሰጠን፤ ንፍሮም
እንኳን በስኒ እየለካች ታካፍለን ነበር። ስንቱን እዚህ በጽሁፍ ማስፈር እችላለሁ? እንዳው ልተወው እና ወደ ሚቀጥለው
ጉዞዬ ልቀጥል።
ከዚያም የማይነጋ ሌሊት የማያልፍ ክረምት እንዲሉ አበው ሁሉም በጊዜው አለፈና፤ ታላቅ ወንድሜ ደምሰውም ለስራ
ደረሰ፤ ጎረመሰ፤ እኔም ትንሺ ትንሺ አግዘው ጀመር፤ ጥሩ አመረትን ከዓመት እስከ ዓመት የሚያደርስ እህል ማግኘት
ቻልን። ያን ጊዜ እኔ ብዙውን ጊዜ ከብት ጠባቂ ነበርኩ። ጓደኞቼ ሲማሩ፣ ደብተር ይዘው ወደ ት/ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ
እመለከት ነበር። ከዚያም የትምህርት ፍላጎቱ ዝም ብሎ አደረብኝ። የፊደል ገበታ ከቤታችን አይጠፋም ነበረና ፊደልን
ከታልቅ ወንድሜ ተማርኩ ምክያቱም እሱ የቄስ ትምህርት ከአያታችን ቄስ ላቀ ገብሬ ጋር ትንሽ ጀምሮ ስለነበረ በደንብ
ያውቃል። ትምህርቱን ሙሉ በሙሉ የተወውም አባታችን ከዚህ አለም ሲለየን ነበር። እንግሊዘኛ ፊደልን ሳይቀር (ከ A
እስከ Z) ት/ቤት ሳልገባ ጨርሸ አወቅሁ። ከዚያም ት/ቤት ካልገባሁ ብዬ እናትና ወንድሜን መጨቅጨቅ ጀመርኩ። ነገር
ግን እነሱ ደግሞ ት/ቤት መግቢያ ወቅቱ መስከረምና ጥቅምት ስራ የሚበዛበት ወቅት ነውና እንዳግዛቸው ቆይ አሁን ስራ
በዝቷል ወደ ፊት ትገባለህ ትንሺ አግዘን እንጂ እኛስ ብቻችንን ምን እናድርገዋለን? እያሉኝ ሁለት ዓመት ያህል አለፈ።
አሁንም እኔ መወትወቴን እንደቀጠልኩ ነዉ ነገር ግን መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር፣ታህሳስ አለፈ። ታህሳስ 30 ቀን 1993
ዓ.ም እኛ ቤት ድግስ ነበረ። ጎረቤታችን የነበረች በአባታችን በአሰፋ በላይነህ በኩል ዘመድ የሆነች ጉርዶ ዘዉዴ የምትባል
ከድግሱ ጋር በተያያዘ እኛ ቤት አድራ ነበር። ነጋ፤ ጥር 1 ቀን 1993 ዓ.ም ሆነ፤ እኔም ጥር እንኳን ቢሆን ትምህርት እገባለሁ
ብዬ ተነሳሁ፣ እናቴ አይ አሁን እኮ ጥር ነው የትምህርት ዓመቱ አሁን ላይ ተጋምሷል ቀጣይ አመት ትገባለህ ስትለኝ ወደ
ውጭ ወጣሁና አለቀስኩ። ያች እንግዳ ሆና እኛ ቤት ያደረችው ጉርዶ ዘዉዴ ምን ሆኖ ነው የሚያለቅሰው? አለች።
ትምህርት ቤት ካልሄድኩ ብሎ ነው አለቻት እናቴ፤ ታዲያ አሁን አዝመራ ገብቷል ምን ይሰራላችኋል? ለምን አይገባም
አለችልኝ። ያን ጊዜ እናቴ እኔ እኮ ልከለክለው ፈልጌ ሳይሆን ቀኑ አልፏል ቀጣይ ይገባል ብዬ ነው አለችና ና ቁርስህን
ብላና ሂድ አለችኝ። እኔ ግን ፈቃዷን ብቻ ነበረና የምጠብቀው ቁርስ በማለት ብድግ ብዬ እየሮጥኩ ወደ ት/ቤት
ሄድኩአልፈልግም(በወቅቱ በልቤ ነው እንጂ በቃላት ቁርስ አልፈልግም ብዬ ቃል አውጥቼ አልተናገርኩም)። ት/ቤት
ስደርስ ረፍዷል፣ ተማሪዎች ወደ ክፍል ገብተዋል፣ ርዕሰ መምህሩ መ/ር ተስፋዬ ይባላል፣ በአጋጣሚ ውጭው ላይ ጸሐይ
እየሞቀ አገኘሁትና ተጠጋሁት፤ ምን ፈልገህ ነው? አቡሽ አለኝ፣ ትምህርት ልገባ ነበር አልኩት፤ ያኔ ልክ እናቴ እንዳለችው
አይ አሁን እኮ ጥር ነው ትምህርት እኮ የሚጀመረው በመስከረም ነው እናም በመስከረም ተመልሰህ ና አለኝ፤ ትምህርት
በመስከረም እንደሚጀመር አውቃለሁ ግን ያን ጊዜ አንተም አካባቢውን ታውቀዋለህ ስራ ይበዛል፣ ስራ ስለሚበዛም
ቤተሰቦቼ አልቅም ብለዉኝ ነው እስከ አሁን ድረስ የቆየሁት፣ ወደፊትም ቢሆን መስከረም ላይ ያው ነው፣ እባክህ አሁን
ልግባ መማር እፈልጋለሁ አንዴዬ ከገባሁ አልቀርም እባክህ አልኩት። ሁኔታዬን በደንብ አየኝና አሁን ባስገባህ ከእንግድህ
አትቀርም? አለኝ፣ የሆነ የደስታ ስሜት እየተሰማኝ አንዴየ ብቻ ልግባ እንጂ አልቀርም አልኩት(እንዳዛ ሲለኝ በዉስጤ
የነበረው ስሜት አሁንም ባሰብኩት ቁጥር ይሰማኛል ከዚያን ወዲህ እንደዚያ አይነት የልብ የደስታ ስሜት የተሰማኝ
አይመስለኝም)። እሺ ብሎ 1ኛ ክፍል ወሰደኝና መምህሯ ገብታ እያስተማረች እያለ አንኳኳና ሺታዬ ይሄን ልጅ መዝግቢው
አላት(እያስተማረች ያለችው መ/ርት ሺታዬ ነበረች የክፍል ኃላፊዋ)፤ እሺ ብላ ከሮስተሩ መጨረሻ ስሜን መዘገበች።
ትምህርቴን አንድ ብዬ ጀመርኩ፤ ትልቅ ደስታ፣የሆነ የተለየ ስሜት በቃ ሁሉ ነገር የተሳካልኝ ሰው አይነት ስሜት ተሰማኝ፤
ትምህርቴን ጨርሸ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ዲግሪ ስመረቅ እንኳን እንደዚያ አይነት ስሜት አልነበረኝም።
በነገራችን ላይ በገባሁ በዚያው ዓመት በሰኔ ለወላጆች ቀን ለርዕሰ መምህሩ ልክ አልቀርም እንዳልኩት ከጥር እስከ ሰኔ
አንድም ቀሪ የሌለበት በሚል ተሸላሚ እንድሁም ከክፍል በትምህርት 1ኛ በመውጣት ተሸላሚ ሆኘ ዓመቱን አጠናቀቅሁ።
ከዚያ በኋላ እናቴም ወንድሜም ለስራ ከትምህርትህ ቀርተህ አግዘን ብለዉ ብዙም አያስጨንቁኝም፣ እንድማር ወሰኑ፤
እኔም ቀጠልኩ። በሚቀጥለው አመት ዴብል አለፍኩ ከዚያ በኋላ ግን ደብል እንዳልፍ ት/ቤቱ ቢፈቅድልኝም በአጎቴ
በአስታወሰኝ ላቀ ምክር ዴብል ማለፍ ተዉኩ። ምክያቱም ቀስ እያልክ ሁሉን እያወቅህ ብትማር ይሻላል ብሎኝ ስለነብር
ነው። እንድህ እንድህ እያልኩ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን በ1999 ዓ.ም፣ የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በ2001
ዓ.ም እንድሁም የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን በ2003 ዓ.ም ጨርሸ በ2004 ዓ.ም አምቦ ዩኒቨርስቲ
በኮምፑተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ትቀላቀልኩ። በዩኒቨርስቲ ቆይታየም ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፌ በ2007 ዓ.ም በጥሩ
ዉጤት ተመርቄ ወደ ቤተሰቦቼ ተመለስኩ፤ (በነገራችን ላይ በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፌአለሁ ብልም
እናቴንና ወንድሜን ላለማስቸገር እያልኩ ብር እንላክልህ ሲሉኝ ኧረ ምንም አይቸግረኝም የምበላው የምጠጣው ከት/ቤቱ
ምንም ለኔ አታስቡ እያልኩ ብር ሲያስፈልገኝ እንኳን አልጠይቃቸውም ነበር፣ ምክንያቱም የቤተሰቦቼን ቤት
ስለማዉቀው። በዓል ሲመጣ ዛሬ ዉጭ ወጥተን እንድህ እንድህ... እናድርግ ትንሽ ዘና እንበል ሲሉኝ የሆነ ስበብ እፈጥርና
ተለይቻቸው ቤተ መጻህፍት ቤት እገባና የምደበቅበት ጊዜ ነበር)። ከዚያም ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ እስከ ጥቅምት 2008
ዓ.ም ስራ ሳፈላልግ ቆየሁ(በነገራችን ላይ ከመርሃቤቴ አ.አ መጥቶ ስራ ማፈላለግ በጣም ከባድ ነበር፦ቤት አልከራይ ብር
የለም፣ ዘመድ ጋር ትንሽ ሞከርኩት አይሆንም፣ የቅርብ ዘመድም አንድ ሰናይት ላቀ ነበርች እሷም እሰው ቤት ነበረች፣ እነ
አበሩና አብርሃምም ያኔ አ.አ አልነበሩም)። በዚህም ምክንያት ወደ ገጠር ተመለስኩና በአይ.ሲ.ቲ መምህርነት ጥቅምት 20
ቀን 2008 ዓ.ም በሰ/ሸዋ ዞን በቀወት ወረዳ ሸዋሮቢት ከተማ ስር በምትገኝ ተሬ ሁለተኛና አጠቃላይ መሰናዶ ት/ቤት
ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ (እዚህ ላይ አብሮኝ አጎራባች ት/ቤት የተቀጠረ ወንድወሰን እሸቴ የሚባለው አብሮኝ አምቦ
ዩኒቨርስቲ በአንድ ክፍል የተማርን ጓደኛዬ አልፈልግም ብሎ ት/ቤቱን አይቶ ተመልሷል እኔ ግን የአ.አን ጉዳይ ስላየሁትና
ያለ ስራ መቀመጥም ስለከበደኝ እንመለስ ሙቀቱም ከባድ ነው፤ ወባም አለ ለኛ አይሆንም ሲለኝ እምቢ ብዬ እዛው
ቀረሁ)። በዚህ ት/ቤት ለአንድ ዓመት ከአንድ ወር ከ21 ቀን ያህል ከአስተማርኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታህሳስ
13 ቀን 2009 ዓ.ም ገባሁ(ማስታወቂያዉን የነገረኝ አስጨናቂ አቢ የሚባል ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል አብረን የተማርን ጓደኛየ
የነበረ ነው)። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታየም በአራት ስራ አስኪያጆች ስር ማለትም በዮናስ ወርቁ፣
በዳንኤል ረታ፣ በአብዱራሂም ጀማል እና በብሩክ ጌታቸው ስር ሆኘ ሰርቻለሁ። አሁንም እዚሁ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
መ/ቤት ውስጥ እየሰራሁ እገኛለሁ።
የትዳር ህይወቴ አጀማመር ደግሞ እንድህ ነበር፦ ሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ.ም አ.አ ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ለመማር አስቤ
ስቱደንት ኮፒ ለማስላክ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ሄድኩ፤ ልክ እንደ እኔ እሷም ስቱደንት ኮፒ ልታስልክ ሄዳ የልጆቼን እናት
ዉዷ ባለቤቴን ሰላማዊት አለማየሁን ተመርቀን ከተለያየን ከ 3 ዓመት ቆይታ በኋላ ተገናኘን። ልክ እንዳየችኝ ያለው ብላ
ስትጠራኝ እኔ ለጊዜው ስሟን መጥራት አልችሃልኩም ነበር ምክንያቱም ትንሽ ጊዜው ቆይቶ ስለነበር ስሟ አልመጣልህ
አለኝ። በነገራችን ላይ አራት ዓመት አብረን እንማር እንጂ አንድ ቀን እንኳን ተቀራርበን ያወራንበት ቀን አልነበረም። ግን
ፈጣሪ ሲፈቅድ በዚች ዕለት ዳግም ተገናኝተን ይሄው ለዚህ በቃን፤ ጥሩ የሚባል ህይወትም እየመራን የሁለት ወንድ ልጆች
ባለጸጋ ሆነናል። ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለአ.አ ዩኒቨርሲቲ ስቱደንት ኮፒየን አስላክሁ፤ የማስተርስ ትምህርቴን ከ 1 ዓመት
በኋል መስከረም ላይ በ2012 ዓ.ም በኢንፎርሜሽን ሳይንስ የትምህርት መስክ ጀምሬ በሰኔ 2014 ዓ.ም ተመርቅሁ።
ወደ 1989/90ዎቹ ዓ.ም መለስ ልበልና የማይረሱና በህይወቴ እስከ አሁን ተጽዕኖ ያሳደሩብኝን ነገሮች በትንሹ ለመጥቀስ
ያህል የሚከተለውን ተጨማሪ ጽሁፍ ለማስቀመጥ ወደድኩ። አባታችን አዝመራውን አዝምሮ ጨርሶ የመጨረሻውን ዕለት
ቦነን የሚባል ቦታ ነበር እርሻ ውሎ ማታ ቤቱ ሲገባ ዛሬ አሞኛል ብሎ የተኛው፤ በሰኔ ወር 1989 ዓ.ም ክፉኛ ተለከፈ።
በዚያው እንደተኛ ሳይነሳ ክረምቱን ሙሉ በከባድ ህመም አሳልፎ ጳጉሜ ላይ ግን ጭንቅ ሆነ። ብዙ ወዳጅ ዘመድ
እየተሰበሰበ ያድር ነበር። ጳጉሜ 5 ቀን 1989 ዓመተ ምህረትም በሱ ህመም ምክያት እንደ ሰሞኑ ሁሉ ብዙ ወዳጅ ዘመድ
ተሰብስቦ ቁጭ ብሎ እየተጠባበቁ እና እየተጨዋወቱ ነበር። በዚች ዕለት በግምት ከሌሊቱ 5፡00 አካባቢ ወላጅ አባቴ
ይችን ዓለም ሲሰናበት ወላጅ እናቴ “እሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪ እንግድህ ምኑ ይያዘው” ብላ ያወጣችው የጩኸት ድምጽ
ዛሬም ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል፤ እኔ እንዴ ልጅ ዋይ አባቴ ብዬ ሳላለቅስ ያንን የእናቴን የመጀመሪያ የጩኸት ድምጽ ብቻ
እየሰማሁ፣ እያወጣሁ እያወረድኩ፣ እያሰላሰልኩ እንባዬ ብቻ እየወረደ ደርቅ ብዬ አደርኩ። ሲነጋም እንኳን ድምጽ
አዉጥቼ አባቴ አባቴ ብየ ላለቅስ ጭራሽ ከብት ጥበቃዬን ቀጠልኩ፤ እንባ የለም፣ለቅሶ የለም፣ ብቻ ዉስጥ ዉስጡን ወይኔ
አባቴ ከዚህ በኋላ እንዴት ነው የምንሆነው? ከዚህ በኋላ የምንይዘው የምንጨብጠው የለም ማለት ነው? ከእንግድህ
አባት የለኝም ማለት ነው? ከዚህ በኋላ ሁሉም ነገር አበቃ ማለት ነው? እራሴን እጠይቃለሁ፤ አዎ አበቃ ሁሉም ነገር
ጨለማ ሆነ እልና እማረገውን አጣና መሬቱን በእጄ መደብደብ፣ መምታት፣ መንከባለል ግን አሁንም ድምጽ አዉጥቶ
ማልቀስ የለም። ዝም ብዬ ዉስጥ ዉስጡን መንገብገብ፣ ማብሰልሰል ብቻ። አባቴን ምን ያህል እንደምወደዉ እናቴ ብቻ
ታዉቃለች፣ ከሱ ተለይቼ መተኛት እንኳን አልችልም ነበር። ጠረኑ ዛሬም በአፍንጫዬ አለ። ታዲያ እሱን ሳጣ ዋይ ብዬ
ድምጽ አዉጥቼ ማልቀስ ያልቻልኩበት ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ አላወቅሁትም። አሁን ላይ ሆኘ ሳስብ ያን ጊዜ
የነበረኝ የበዛ እፍረት ምን ያህል ቢሆን ነው? ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ከዚያ ዉጭ ሌላ ምንም አይኖርማ። ጥንካሬ
ነዉ አይባል በዚያን ስዓት አይታሰብም፣ አለማወቅ ነዉ አይባል አስራ አንድ ዓመት ሞልቶኝ ሁሉን ነገር አውቃለሁ፤
እናደዳለሁ፣ እንገባገባለሁ፣…
አሁን ላይ የተረዳሁትና የጎዳኝ ትልቅ ነገር ያኔ ድምጽ አዉጥቼ ዋይ ብዬ አልቅሸ አባቴን ባለመቅበሬ ሀዘኑ አልወጣልህ
ብሎኝ ይኸዉ ሃዘኔን በጭንቅላቴ ይዤ በህይወቴ ጎዳና ሙሉ በማሰላሰልና በመቆዘም እኖራለሁ፤ ስስቅ እንኳን ከአንጀቴ
ሳልስቅ እኖራለሁ። ምክንያቱም ምንም ጥሩ ነገር ሆኖልኝ እንኳን አያስደስተኝም፤ አንድ ጥሩ ነገር ሲሳካልኝ ይህን ጊዜ
አባቴ ቢያየኝ እያልኩ ነው የማስበዉ። ቀልድና ጨዋታ ተነስቶ እንኳን የሚያስቅ ነገር ሲወራ ለሰዉ ብዬ እስቃለሁ እንጂ
ሳቄ ከልቤ መጥቶ አይፈነቅለኝም። እናም አንዳንድ ሰዎች ኧረ እንዳውም ብዙ ሰዎች በዚህ የተነሳ ኩራተኛ ነዉ፣ የሰዉ
ነገር ስለሚንቅ ነዉ ብለዉ እንደሚፈርጁኝ በጣም ከምወደው ከቅርብ ጓደኛዬ እንዲሁም ከቅርብ ቤተሰቦቼ ከተረዳሁ
ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። እርግጥ ይህን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ሞክሬ አውቃለሁ ግን ነገሩ ውስጣዊ ስሜትና የጭንቅላት ስራ
ከባድ ስለሆነ ብዙም ልቀርፈው እንዳልቻልኩ አውቃለሁ። ይህን ነገር በራሴ ዕይታ ሳየው ደግሞ የፈጣሪን ስራ ያለመቀበል
ችግር አለብኝ ማለት ነው እያልኩ ራሴን እንድወቅስና ዕምነተ-ቢስነት እንድሰማኝ እያደረገኝ ያለ ጉዳይ ሆኖብኛል፤
የተምታታ ሃሳብ፤ የተምታታ አመለካከት፤ የተምታታ ዕይታ በህሊናዬ ይመጣብኛል። ህይወትን እንድጠላና ትርጉም አልባ
ያደርግብኛል። በህይወቴም ከዚህ በላይ ስኬታማ እንዳልሆን ያደረገኝ አንዱ ይህ ጉዳይ እንደሆነም ይሰማኛል። ነገር ግን
ከዚህ በላይ በእንደዚህ አይነት ስሜት ላለመጓዝ ወስኘ ራሴን ለመለወጥ እይታገልኩ ነው፤ ፈጣሪም ሁሌም የምፈልገውን
አሳጥቶኝ አያውቅም፤ አሁንም የምፈልገውን እያደረገልኝ ነው፤ ለወደፊቱም ሁሉን እሱ እንደሚያደርግልኝ እግጠኛ ነኝ፤
በእርሱም እተማመናለሁ።

ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ጤና ሰጥቶ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በቅርቡ እንድናይ ከልቤ እመኛለሁ!
ያለው አሰፋ
ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ

You might also like