You are on page 1of 5

የፍስክ ጾም

ከምሳ በኋላ እንደተለመደው በአበራ ወጌሻ መውጫ በኩል ቡና


የምንጠጣበት ቦታ ጋ ተቀምጠናል። ግቢ ከገባን ጀምሮ ቡና
የምንጠጣው እዚህች ቦታ ስለኾነ ከሰፈሩ ወጣቶች ጋር በጣም
እንግባባለን። እንደ አጋጣሚ ኾኖ ዛሬ ባለቡናዋ ማርታ ከጎን ወጥ
እየሠራች ነበር። አንደኛው የሰፈሩ ልጅ ፈጠን እያለ መጥቶ ሰላም
ካለን በኋላ "እናቴ ትሙት ማርቲ የሽሮሽ ሽታ ነው የጠራኝ" አላት።
እሷም ፈገግ እያለች አታስብ በሽ'ታ ብቻ አትቀርም ምሳ አብረን
እንበላለን አለችው። ሰምታችኋል ምስክሮች ናችሁ አለን ወንበር
ስቦ እየተቀመጠ። ችግር የለውም እኛ እያለን አትከዳህም አለው
አብሮኝ የመጣው ጓደኛዬ። የማርቲን ሽሮ አንድ ጊዜ ብትቀምሱትኮ
ልክ ለቡና እንደምትመላለሱት ለምሳም ከዚህ አትጠፉም ነበር
አለን። አይይ ገና ለገና ጋበዘችኝ ብለህ ነው እንዲህ የምትክባት
አለው ሌላኛው የሰፈር ልጅ። አይ የምሬን ነው በማርቲ ሽሮማ
ቀልድ የለም። በተለይ ለጾም ጊዜ የምትኾን ምርጥ ሽሮ ናት
እንደውም ይህችን ጾም አንቺ ጋ ነኝ ማርቲ አላት ወደሷ ዞሮ። ጾም
የሚለውን ስሰማ ግራ ገባኝ። ባየሁት ነገር ሰው የመገመት አባዜ
ይዞኝ የዚህን ሰፈር ወጣቶች ሲጋራና ጫት ይዘው ስለማያቸው
ስለጾም የሚያውቁ አይመስለኝም ነበር ጭራሽ የግል ጾም
የኾነችውን ጾመ ዮዲት መጾማቸው ደነቀኝ። የራሴ የችኮላና
የስኅተት ግምት አሳፍሮኝ ዝም አልኩ። ትንሽ ዝም ብለን ከቆየን
በኋላ አብሮኝ የነበረው ጓደኛዬ ወጥ የምትሠራዋን ልጅ "እኔ
የምልሽ የጾም ነው እያለ ቅቤ የምትጨምሪው ለምንድነው አላት።
ኧረ የጾም ነው አለችው። ምኑ? ቅቤው? አላት ግራ ተጋብቶ። አዎና
አለች ፈርጠም ብላ። ጓደኛዬ ነገሩ እንዳልገባው ያየ ሌላኛው
የሰፈር ልጅ የጾም ቅቤ እንዳለ አታርፊም እንዴ ጀለስ ዘመኑ እኮ
ተቀይሯል የጾም ቅቤ የጾም አይብ ሌላም ሌላም ብዙ ነገር አለ
ያድርሰን እንጂ እድሜ ለሳይንስ ገና ወደፊት የጾም በግ እና በሬም
መኖሩ አይቀርም ያኔ ቀለል ያለ ጾም እንጾማለን ብሎ ዘለግ ያለ
ማብራሪያ ሰጠው። ቆይ ግን እንዴት? አለው ጓደኛዬ። ሆ ሆ እሱን
እኔ ምን አውቃለሁ የሠራውን ሰውዬ ጠይቀው እኔ customer ነኝ
man አለው። ጓደኛዬ ከዚህ በላይ መቀጠል የፈለገ አይመስልም
ዝም አለ። እኔም በራሴ ሃሳብ ተዋጥኩ ኹኔታው ግን በዚህ
ከቀጠለ ድሮ ልጆች ኾነን ፍልሰታ ጾም ላይ ብስኩት ስንገዛ
ማሸጊያው ላይ "የጾም" የሚል ጽሑፍ እንደምንፈልገው ለቅቤ
ለአይብ እና ሥጋ እንደዛ መፈለጋችን እንደማይቀር ሳስብ አስፈራኝ።
ግና ይህንን ባለማወቃችን ከዘመኑ በጣም ኋላ የቀረን
እንዳይመስላቸው ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጠብኹ።
በዚህ ኹኔታ የቡና ሰዓታችን አልቆ ወደ ዶርማችን ተመለስን።
እንደአጋጣሚ በዚሁ ዕለት ሰርክ ሰዓት ከንስሐ አባታችን ጋር
ሳምንታዊ ቀጠሮ ነበረን። ጓደኛዬም ይህን አስታውሶ ቡና ቦታ
የተነገረው ነገር ስላልተዋጠለት ከቀጠሮ ሰዓት ቀደም ብለን ሄደን
እንድንጠይቃቸው ሃሳብ አመጣ እኔም ንግግራቸው ብዙም ምቾት
ስላልሰጠኝ በሃሳቡ ተስማማሁ። ኹል ጊዜ እሳቸው ጋር ስንሄድ
የሚሰማኝ የደስታ ስሜት ዛሬም አልተለየኝም። ስንደርስ
በተለመደው አባታዊ ፈገግታቸውና ፍቅራቸው ተቀበሉን እኛም
መስቀል ተሳልመን ጉልበታቸውን ስመን ተቀመጥን።
ስለጤንነታችን ስለቤተሰብ ስለትምህርት አጠቃላይ ሳምንቱ
እንዴት እንዳለፈ ሲጠይቁንና ስንጨዋወት ከቆየን በኋላ ጓደኛዬ
ያብከነከነውን ጉዳይ አነሣ። ስላየው ነገር የሰፈሩ ልጆች
የነገሩትንም ነገር በዝርዝር ነገራቸው። አባ ይህንን በሚሰሙበት
ሰዓት አልፎ አልፎ ፈገግ ከማለት በስተቀር ፊታቸው ላይ ምንም
መለዋወጥ አይታይም። በዚህም ነገሩ የሚያውቁት እንጂ አዲስ
እንዳልኾነባቸው ገባኝ። ጓደኛዬ ነገሩን አስረድቶ ከጨረሰ በኋላ
ታዲያ አባ ይህ ነገር ትክክል ነው? አላቸው። አባ አዎን ወይም
አይደለም ሳይሉ ጥቂት ዝም ብለው ቆዩና የፍስክ ጾም
ታውቃላችሁ ልጆቼ አሉን? ግራ ገባኝ። አነዚህ ኹለት ቃላት ከካፌ
ውጭ ወዳሉት ምግብ ቤቶች በገባን ቁጥር የሚያስጨንቁን፣
ለመለየት መከራ የኾኑብን ቃላት ነበሩ። እኔ በበኩሌ ብዙ ሰው
አስረድቶኝ ከብዙ ልፋት በኋላ የፍስክ የሚለውን ከፋሲካ ጋር
አገናኝቼ የጾምና የፍስክ ሲባል መለየት ጀምሬ ነበር ። ዛሬ ግን አባ
ያን ኹሉ ልፋት ገደል ከተቱት የፍስክ ጾም ብለው ደባለቁብኝ! ዝም
ስንልባቸው አንተ አታውቅም? አሉት ጓደኛዬን። አላውቅም አላቸው።
አንተስ? አሉኝ ወደእኔ ዞረው። እኔም አንገቴን ግራ ቀኝ በመነቅነቅ
አለማወቄን ነገርዃቸው። አይይ ይህን የዘመናችሁን ፍልስፍናማ
ማወቅ ነበረባችሁ አሉ እስከ አንገታቸው የወረደውን ነጭ
ጢማቸውን እየዳበሱ። የፍስክ ጾም ማለት ያ ባልንጀራችሁ የጾም
ቅቤ የጾም አይብ እንዳለው ቀለል ያለ ጾም ማለት ነው። መናፍቃኑ
መጽሐፍ ቅዱስን ለሥጋቸው ፍላጎት እንዲመች "ቀለል ባለ
አማርኛ" ተርጉመው እንደ ቀለሉ እኛም ለሥጋችን ፍላጎት
እንዲመች ቀለል ያለ ጾም እየጾምን ቀልለናል። አንደው እናንተ
ይህችን ትንሿን የምግብ ጉዳይ አያችሁ እንጂ ብዙ ነገራችን እኮ
ተበላሽቷል ልጆቼ። በጾም ወቅት ከምግብ ተከልክለን ጆሮአችን
ከአሉባልታና ከዘፈን ተጠብቆ ቃለ እግዚአብሔር ካላደመጠ፣
ዓይናችን የማይገቡ ነገሮችን ከማየት ተከልክሎ ቅዱሳት መጻሕፍት
ካላነበበ፣ አንደበታችን ከሃሜት ርቆ ስብሐተ እግዚአብሔር
ካላቀረበ፣ እጃችን ከሥርቆት ተከልክሎ ካልመጸወተ ምን ዋጋ
አለው? ጾማችን እንዲህ ምሉዕ ካልኾነ "ከሥጋው ጾመኛ ነኝ
ከመረቁ አውጡልኝ"እንደሚባለው ይኾንብናል። ሆዳችን ብቻ ጹሞ
"የማይጾመውን ጾመኛ" ድል አናደርገውም። የማይጾመው ጾመኛ
ማነው አባ? አልኳቸው። እሱማ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ነው።
ጾም ከምግብ መከልከል ብቻ ቢኾን ከዲያብሎስ በላይ ጾመኛ
አይኖርም ነበር ። ምክንያቱም እኛ ብንጾም ጥቂት ሰዓታት ወይም
ቀናት ብቻ ነው እሱ ግን ዓለም ከተፈጠረ በልቶ አያውቅም ግና
የጾም መንፈሳዊ ትርጉም ምግብ ከመከ'ልከል ከፍ ይላልና
ዳያብሎስ ጾመኛ ተብሎ ሰምተንም አይተንም አናውቅም። ለዚያ
ነው የማይጾመው ጾመኛ የሚባለው። አባ ሕርያቆስ ቅዳሴ ማርያም
ላይ ስለምሥጢረ ሥላሴ ያለውን ታስታውሳላችሁ "አንድነትን
ሳንለይ የተለየ እንዳይኾን የተቀላቀለ እንዳይኾን እንለይ" ነበር
ያለው። እኛ ግን ጾም ማለት በግዘፍ የምናየው ሥጋችን ሲራብ
የማናያት ረቂቅ ነፍሳችን የምትጠግብበት ትልቅ ምሥጢር መኾኑ
ጠፍቶን ቀላቀልነው። ጾም ለጥቂት ሰዓታት መከልከል ብቻ ሳይኾን
የጾም ጊዜ እስኪያልፍ አንዳንድ ምግቦችን ሙሉ በሙሉ
መተወንም ይጨምራል። ወደጥያቄህ ስመጣልህ ከጾም ድንጋጌ
አንጻር የጾም ቅቤ የጾም አይብ ወዘተ በቀጥታ ከእንስሳት ተዋጽኦ
ስላልኾኑ እነዚህን እየበሉ መጾም ይቻላል። ግን ከጾም መንፈሳዊ
ትርጉም አንጻር ትክክል አይደሉም። የጾማችንን ወጋ ያሳንሱብናል።
የምንጾመው ሥጋችን ደክሞ ለነፍሳችን እንዲገዛ ነው እንጂ ለሌላ
አይደለም። ጾማችን ፍጹም የሚኾነውም ስንራብና ያንን ረሃብ
ለማሸነፍ በምናደርገው ትግልና በዚያውም ሥጋዊ ፍላጎታችንን
ለመግታት በምናደርገው ልምምድ ነው። ጾም ማለት መዝሙረኛው
ቅዱስ ዳዊት "ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ" እንዳለ ፈቃድንም ጭምር
የምንሠዋበት እንጂ ለፈቃዳችን የጾም የሚል የዳቦ ስም እየሰጠን
ፈቃዳችንን የምንፈጽምበት አይደለም። መቼስ የህክምና
ተማሪዎችም አይደላችሁ ሳይንስ የት እንደደረሰ አይጠፋችሁም
ከእንስሳት ከሚገኘው ቅቤ የበለጠ ሰው ሠራሽ ስቦች ብዙ ኃይል
ሰጪ ነገሮች እንዳላቸው፤ ከሥጋም ከፍ ያለ ፕሮቲን ያላቸው
የፋብሪካ ምግቦች እንዳሉ ግልጽ ነው። ታዲያ ከእንስሳት
ስላልተገኙ ብቻ "የጾም" የሚል ቅጽል በመስጠት ጾምን የፍስክ
ማድረግ ተገቢ ይመስላችኋል? ሊኾን አይችልም! ይህ ራስንም
መንፈስቅዱስንም ለማታለል መሞከር ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን
ብርሃን ከጨለማ ምን ኅብረት አለው እንዲል ቅቤ አይብና ሌሎች
ሥጋዊ ፍላጎቶቻችን ከጾም ጋር ኅብረት የላቸውም። ፋሲካ ከጾም
በኋላ እንጂ በጾም ወቅት አይኖርምና የፍስክ ጾም የለም። አባ
በሚጣፍጥ አንደበታቸው ይህን ሲሉ በተመስጦ ኾነን መምሸቱን
አላወቅንም ነበር። አባ ሰዓታቸውን አይተው አይ የኔ ነገር ወሬ
አብዝቼ አስመሸሁባችሁ አይደል ይቅር በሉኝ እያሉ ሊሸኙን ተነሡ።
እኛም አመስግነን መስቀል ተሳልመን ተሰናብተን ወጣን። ትንሽ
እንደተጓዝን ወልደ ገብርኤል እያሉ ተከተሉን አቤት አባ ብለን
ወደሳቸው ዞርን። እንግዲህ ይህች የሰማችኋትን ነገር ሰፈር ካሉት
እነዚያ ልጆች ጋር ስትገናኙ መጨዋወት እንዳትረሱ አደራ እሺ
ልጆቼ አሉን። እሺ አባታችን እሱ ቢረሳም እኔ ፈልጌያቸው ነው
የምነግራቸው አለ ጓደኛዬ። አባም ፈገግ ብለው እግዘብሔር
ይባርካችሁ በሉ እንግዲህ መሽቶባችኋል ፈጠን እያላችሁ ሂዱ
አሉን። እኛም አሜን! ብለን ተሰናበትናቸው።

You might also like