You are on page 1of 9

ምናሴ(ማስረሻ)

ትዕይንት አንድ

መጋረጃው ሲከፈት ሙሉ ሳሎን ይታያል። ከሳሎኑ ግራና ቀኝ ሁለት በሮች ይታያሉ። ሳሎኑ ውስጥ ያደፉ ሶፋዎች ይታያሉ።
ሩሃማ ከእቃ ቤቱ ወደሳሎን ትመጣለች። ናሆም ሶፋ ላይ ተቀምጦ ይታያል። በሁለቱም ባልና ሚስት ጥሩ ስሜት
አይነበብባቸውም። ተኮራርፈው በጥላቻ ዓይን እየተሰራረቁ ይተያያሉ። በድንገት ዓይን ለዓይን እንደተያዩ፣

ናሆም፡- ምን ታፈጫለሽ?

ሩሃማ፡- አንተስ ምን ታፈጣለህ?

ናሆም፡- እኔማ ስላስጠላሽኝ ነው።

ሩሃማ፡- ምን? ስላስጠላሽኝ ነው?.......’’ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል አለች አያቴ’’ ሆሆ እንግዲያውስ እኔም ስላስጠላኸኝ
ነው…….እጅ እጅ ነው ያልከኝ።

ናሆም፡- (ዓይኑን እያጉረዘረዘ) ምኔ ነው እጅ እጅ ያለሽ? ሰርቼ ባበላሁሽ ጠገብሽ አንቺ ድሪቶ።

ሩሃማ፡- እኔስ ብሆን ካንተ በምን አንሳለሁ? አንተ እየሰራህልኝ ነው? ካንተማ አላንስም፣ የፈሰሰ ውሃ የማታቃና፤ ደግሞ
አንተ ወንድ ተብለሃል።

ናሆም፡- እኔ? አንቺ ሴትዮ ዛሬ ምንሽም አልጣመኝ፤ ነገሬን አታምጪው።

ሩሃማ፡- (በስላቅ ሳቅ እየሳቀች) አረ እኔስ ምንህም ጥሞኝ አያውቅ፤ ምን የሚጥም አለህ? አሁን አንተ ባል ነህ? ሂዲና ባሎችን
ምን እንደሚሰሩ እያቸው ።

ናሆም፡- (የስላቅ ሳቅ እየሳቀ) ከኔ በላይ ባልስ ላሳር ነው……….ቆይ አንቺ ሚስት ነሽ ምስጥ? በልተሽ በልተሽ ጨረስሺኝ አንቺ
ጋለሞታ።

ሩሃማ፡- በስድብማ ተመርቀሃል። አንደበትህ መልካም ነገር መቼ ያፈሳል? (ምርር ብላ) አረ አረ አሁንስ መረርከኝ….አረ
ፈጣሪዬ ምን አደረኩህ ከነጭናጫ ባል ጋር ያጣመርከኝ? አረ በቃኝ በቃኝ!(ታፈጠበታለች) በቅቶኛል!

ናሆም፡- ምን? በቃኝ…….እኔም በቃኝ አላልኩ…..እ……እኔም አልተማረርኩ…….አንቺ ምን አለብሽ? ትበያለሽ፣ ትጠጫለሽ፣


ትተኛለሽ….. እኔ ነኝ እንጂ ወይ የምትሰሪው አይጥም። (ከትንሽ ፋታ በኋላ ጣራ ጣራውን ሲያይ ቆይቶ ድንገት
በንዴት) ውጪ ውጪ ካስመረርኩሽ ጉልት (በጥፊ ይመታታል)

ሩሃማ፡- (በሃዘን ስሜት) አይ የፍቅር መቀዝቀዝ ደፍረህ መታኸኝ? ቤታችን የደፈረሰበት ምክንያት ነው አልገባ ያለኝ።
ታስታውሳለህ ገና ስንፋቀር ያኔ የነበረን ፍቅር? ዛሬ ወዴት ገባ? ምን በላው? ምን ዓይነት ምትሃት ሰወረብኝ? ትዝ
ይልሃል ንጹህ ፍቅር የሰፈረበት ዘመን? ይሳኮር እያልክ ስትጠራኝ እኔም ምናሴ እያልኩ አጸፋውን እምስልህ ነበር።
ዛሬ እጆችህ በኔ ላይ የጨከኑት ምን ተገኘ? ያን ጣፋጭ ፍቅር ምን አዳፈነው?.....ንገረኛ…….
ናሆም፡- አታለቃቅሽቢኝ………ዳግም እንዳያበራ አድርገሽ ያዳፈንሺው አንቺ ነሽ……..መተላለፍ፣ መወያየት፣ ይቅርታ በኛ ዘንድ
ጠፋቷል። ለኔ ክብር የለሽም……ያቺ የማቃት ይሳኮር ባንቺ ዘንድ የለችም…….ሞታለች። ያኔ ከደግነትሽና ከጥንካሬሽ
የተነሳ ልቤን ሰጠሁሽ። ምን ዋጋ አለው ያንቺ አስመሳዩ ቅርፊት ተቀርፍቶ ድብቅ ማንነትሽ ሲወጣ እምነት ከኔ
ራቀ……..ተይኝ ተይኝ አታቁስይኝ፡

ሩሃማ፡- አዎ ልክ ነህ አንተም መልካም ባል ትመስለኝ ነበር። ሁለታችንም የተሸነፍነው በመልካምነታችን ነው። ነገር ግን
ተሳስቻለሁ የማውቅህን ናሆም አልመስለኝ አልክ። ሁሌ ጭቅጭቅ ሁሌ ንትርክ ነው። በዚህ ሁኔት የቀደመው
ፍቅራችን እንዴት መመለስ ይቻለናል? የሚገርመው ደግሞ ቤተ-ክርስትያን መሳለሙን ትተኸዋል።

ናሆም፡- አታመጪው የለ ደግሞ ከፈጣሪዬ ጋር ኣጣይኝ። የሰው ልጅ ፈራጅ ቢሆን ፈርደሽብኝ ነበር። ባንቺ ዘንድ የኔ
እጣፈንታ ሲኦል ነበር።

ሩሃማ፡- አንተኮ አታፍርም ልትክድ ይሆናል…….እስኪ አዲስ የመጡት ጠንቋይ ቤት ይመስክር።

ናሆም፡- አረ ጥንቁል ያርግሽ የጭቃ እሾህ…….ስሙም ሲጠራ አልወድ እንኳን ልሄድ።

ሩሃማ፡- አይ ናሆም ዋሸኸኝ…..ውሸት እኮ መራራ ናት……እውነት ተደብቃ ላትቀር ለምን ትደብቀዋለህ? እውነት
ለእውነተኞች አንድ ቀን ማብራቷ አይቀርም።

ናሆም፡- መድሐኒዓለምን….ጊዮርጊስን እያልኩሽ ምን ልሰራ እሄዳለሁ? ቆይ አንቺ ምን ልትሰሪ ሂደሽ ነው?

ሩሃማ፡- አረ እኔስ እግር ጥሎኝ ነው……..እግር ጥሎኝ…….

ናሆም፡- አይ አንቺ ዘመን ጥሎኝ አትዪም? እንደው አደራሽን ከጠንቋይ ቤት ታየች ተብለሽ እንዳታሰድቢኝ………አስበሽዋል?
ጠንቋይ እኮ ነው…….የሰው ዓይን መጠንቆል…….ዓይን ሲጠነቆል መዘዙ ማልቀስ ነው፡

ሩሃማ፡- ልክ ነህ…..ምን ላወራ እሄዳለሁ ብለህ ነው? ያንተን እንጃ እንጂ እኔማ አልቅሼ ስነግራት በኪዳኗ ጎዶሎየን
ትሞላዋለች……ውይ ጠንቋይ(ያንገፈግፋታል) አረ ተው ስሞትልህ ስሙም ሲጠራ ያንገፈግፈኛል…….ስለነሱ ከምሰማ
ምን አለ ይህች ምድር ዋጥ ባደረገችኝ።

ናሆም፡- ለመግባት ያብቃሽ እንጂ ኢኔ እቆፍርልሻለሁ። ለማንኛውም ተጠመቂ እንዲሂ የሚያደርግሽ በላይሽ የሰፈረው ጋኔን
ነው፡

ሩሃማ፡- አረ ባክህ (ትስቅበታለች) እኔስ (እያማተበች) በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ስለው
ነው ድራሹ የሚጠፋው። እንኳን ለኔ ለጎረቤትም እተርፋለሁ…….አሄሄ እኔ ባልኖር ምን ይውጥህ ነበር?(ወደ መኝታ
ቤት ትገባለች)

ናሆም፡- አቤት አቤት ጡጥም ከፈስ ተቆጠረች? ደግሞ እንደሰዎች ታወራለች……ቱልቱላ……ቆይ አሳይሻለሁ አፈር ካላገባሁሽ
እኔ የደባልቄ ልጅ አይደለሁም። ሆሆ ምን ስትል አየችኝ? ይቺ አጥማዣም የጎረቤት ቡና ለማንቃረር ሂዳ ይሆናል።
አሁንስ መረረኝ ሞታ ትገላገለኝ።

ሩሃማ፡- (ድንገት ትገባለች። ደንገጥ ብላ) ምን ሙታ ትገላገለኝ?


ናሆም፡- (እየተርበደበደ) አ…አ…አዎ…አዎ ትሙትና ትረፍ።

ሩሃማ፡- ማን? እኔን? ሞቴን ተመኘኽልኝ?(ታለቅሳለች)

ናሆም፡- (የፌዝ ሳቅ እየሳቀ) አረ ምን በወጣሽ ጠላትሽ እዛው ክርር ይበልልሽ። ዶሮዋን እየቀዘነች አይቻት ነው። ዶሮዋን
ነው ዶሮዋን….

ሩሃማ፡- የምን ዶሮ? ምን ዶሮ አለንና ነው?

ናሆም፡- እ..…እንዴ ተዪ እንጂ (ወደ ውጭ እያመላከታት) የጎረቤት ዶሮ የኛ ማለት አየደል? አጥብቆ ጠያቂ እናቱን ይረዳል
አሉ። በይ ለማንኛውም ቤቱን ለቀሽ የትም እንዳትሄጂ፣ ቤት ሰብረው የሚሰርቁ ሌቦች መጥተዋል ሲባል
ሰምቻለሁ።

ሩሃማ፡- ምን መሄጃ አለኝ ዛሬስ ስራም በዝቶብኛል። እህሉንም አላበጠርኩት። (ዓይን ለዓይን እየተያዩ ይወጣል) አምላኬ
ይቅር በለኝ ዋሽቻለሁ…..መቼም ያንተ ይቅርታ አያልቅም። (በሃሳብ ከወድያ ወዲህ ትመላለሳለች) እኔማ መሄዴ
አይቀርም…..ትራክተር እንደፈነገለው እነደ አቶ ደበበ ባህር ዛፍ ከስሩ ተፈንገሎ እንዲወዲቅ ነው የምፈልገው።
እንደውም እነሱ ካላጠፉልኝ አይጠፋም እድሜው ረጅም ነው……..አባቴ ሚካኤል ስራቸው እውን ከሆነ እቅዴ
ከሰመረ ላንተም ሻማ አመጣልሃለሁ…….ውይ ይሄ ክርፋታም ይገላገለኝ ምርር ብሎኛል። (ናሆም ድንገት ይገባል።
በፍርሃትና በድንጋጤ) ም…..ም….ምን አመጣህ?

ናሆም፡- አይ ቦርሳዬን ረስቼ ሂጄ ነው። (ቦርሳውን እያነሳ) እኔ እምልሽ ክርፋታም፣ ይገላገለኝ፣ ምርር ብሎኛል ከማን ነው
የተበደርሻቸው ባክሽ? ማነው የሚገላገልሽ? ማነው ክርፋታሙ? (ያፈጣባታል)

ሩሃማ፡- (ለመረጋጋት እየሞከረች) አይሸትህም እንዴ ቤቱ ሁሉ ጠረኑ ተቀይሮ? ምነው እቴ ገና የጎረቤት ዶሮ የኛ ነው ማለት
ነው ተብሎ የሱ ቅዘን ጠራጊ ልሁን እንዴ? ቅድም ሴቷ ዶሮ አሁን ደግሞ አውራ ዶሮው…….እህ አረ አሁንም
ይገላገለኝ። (አፍንጫዋን ትይዛለች)

ናሆም፡- እንደዛ ነው? ባለቤቴ እንደዚህ የተማረረችብኝ ምን ባስቀይማት ነው ብዬ ተንበርክኬ ይቅርታ ልጠይቅሽ ምንም
አልቀረኝም ነበር። (ፊቱን አዙሮ እያሾፍ ወደበሩ መሄድ ይጀምራል)

ሩሃማ፡- አረ….አረ ጠላትህን ምን አድርገኸኝ? (ይወጣል)…….አፍ ያጠፋል አፍ ይክሳል አሉ አይ አንች አፌ አዋርደሺኝ


ነበር….ይገርማል ይህ የጎረቤት ዶሮ ባይኖር ምን ይውጠኝ ነበር? ማምለጫ ነው የሆንከኝ። ከዚህ ጉድ ስላወጣኸኝ
ጥሬ ላመጣልህ። (ወደ ጓዳ ትገባለች)

መጋረጃው ይዘጋል

ትዕይንት ሁለት

መጋረጃው ሲከፈት ሙሉ መድረክ ይታያል። ከመድረኩ መሃል ላይ የጠንቋዩ ከስጋጃ የተሰራ ትንሽ ክፍል ትታያለች። በቀኝ
በኩል ስጋጃ አንጥፎ የተቀመጠ የጠንቋዩ ተላላኪ ያታያል። ከጠንቋዩ ክፍል ምረኩን በሙሉ አዳርሶታል። ፊት ለፊት
የተጎነበሱ ሰዎች ይታያሉ። ናሆም የሚያደርገው ቅጡ ጠፍቶት ከወድያ ወዲህ ይመላለሳል።
ጠንቋይ፡- ማነው አንተ ያዙረውና የሚዞረኝ? እንዴት ቢንቀኝ ነው? ኡረህ አምጣው…….አሰግደው……አሰግደው ለመጀናችን።

ተላላኪ፡- አንተ ወራዳ በራስህ ጊዜ ትዋረድ? ቶሎ ብለህ ስገድለት ንጉሳችንን አስቀየምከው…….የተከበረው ቦታ ዘውብለህ
ትገባለህ?

ናሆም፡- (እየተንበረከከ) አጥፍቻለሁ ጌታዬ ጨንቆኝ ነው ይቅር ይበሉኝ…….

ጠንቋይ፡- (ያጓራና) ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?

ናሆም፡- ሚስቴ እስምርራኛለች እንድትሞትልኝ እፈለጋለሁ……..እንደው ድራሿ እንዲጠፋ እፈልጋለሁ።

ጠንቋይ፡- ካሁን በፊት ትዋደዱ ነበር…….ይሳኮርና ምናሴ እየተባባላችሁ ትጠራሩ ነበር…….ተሳሳትኩ

ናሆም፡- አረ በፍጹም ጌታዬ በፍጹም……

ጠንቋይ፡- (ያጓራል) ወሎ መጀን……አምጣት……..አምጣት አመድ አድርጋት…….(ያጓራል) በስማችሁ መጠራራቱን ቀጥሉበት።


ወዳጅ ብሉ ናና ስጠው (ተላላኪው ወደ ጠንቋዩ ቀርቦ በሃይላንድ ውሃ እንዲሁም በትንሽ ፌስታል አፈር ነገር
ይቀበለዋል። የተቀበለውን ኣፈርና ውሃውን ይደባልቀዋል።) እንዳታውቅብህ በደንብ ተንከባከባት።

ተላላኪ፡- (ውሃውንና አፈሩን ካደባለቀው በኋላ) ትሰማለህ ሳምንት ያህል መታመም አለባት። ጎረቤት ምታመሟን
ስለሚያውቁ ብትሞትም አንተ ገደልካት አትብልም። በደንብ አስረግጬ የምነግርህ እንድትንከባከባት ነው። ካልሆነ
ግን መዳህኒቱን ስራ በቀጥታ ከጀመርክ ወድያውኑ ትሞታለች። አንተም ሚስቱን ገደለ ተብለህ ትታሰራለህ……..

ናሆም፡- (ያቋርጠዉና) እ…..ት…….ትታሰራለህ?

ተላላኪ፡- አታቋርጠኝ (ሁለቱም ያጓራሉ) ከተንከባከብካት፣ ጥሩ ስጦታ ከገዛህላት፣ ፍቅር ከሰጠሃት እሷም ቀስ እያለች
በሳምንት ውስጥ ትገላገላታለህ፤ ተግባባን?

ናሆም፡- አዎ ጌታዬ ገብቶኛል። (ኪሱን እየዳበሰ) ምን ያህል ነው መክፈል ያለብኝ?

ተላላኪ፡- እሱን ምኞትህ ሲሳካ ደስ ያለህን ለመጀናችን ታመጣለህ።(ያጓራል)

ናሆም፡- እሺ ጌታዬ (ሰግዶ የተሰጠውን መድሃኒት ይዞ ይወጣል።)

ጠንቋይ፡- (እያጓራ ይቆይና) የጣናው ተራራው መጀን መጣ ገሰገሰ እንባዋን አበሰ (ሩሃማ በመሃል ትገባለች)

ተላላኪ፡- ጎዶሎሽ ምንድን ነው? ምን ትፈሊጊያለሽ?

ሩሃማ፡- ባሌቤቴ አስመርሮኛል እንዲሞት እፈልጋለሁ።

ጠንቋይ፡- (በሃይል እያጓራ) ያለተስማማች ገላ ልላሰች ወለላ አስገባት…….አሰገባት

ተላላኪ፡- አረጋ ምን ዓይነት ጥሩ እድል ነው ያለሽ በይ? ቶሎ ነው የውደዱሽ…….በዪ ጠጋ በዪና አመስግኛቸው።

ሩሃማ፡- እሺ…..እሺ ጌታዬ (ከጠንቋዩ ፊት ተደፍታ) እባክዎ ጌታዬ ወሎ መጀን የልቤን መሻት ይፈጽሙልኝ።
ጠንቋይ፡- (እያጓራ) አ.…አ…..አ…አምጣው……እ….እ….እ…..ከባልሽጋ ትዋደዱ ነበር።

ሩሃማ፡- አዎ ጌታዬ አዎን

ጠንቋይ፡- ይሳኮርና ምናሴ እየተባባላችሁ ትጠራሩ ነበር……….

ሩሃማ፡- አረ…..አረ…..ምን ያሉ የልብ አዋቂ ናቸው? በደንብ በደንብ ነው አልተሳሳቱም…….

ጠንቋይ፡- ባልሽን ተንከባከቢው፣ ፖሊስ ገደለችው ብለው እንዳያስሩሽ የተወሰነ ጊዜ መታመም አለበት……ፍቅር
ስጪው……የምሰጥሽን መዳህኒት ደግሞ በሚበላውና በሚለብሰው ላይ እንዲሁም በሚተኛበት ላይ
በትኚው……ወዳጄ በሉ ናና ስጣት (ተላላኪው መጥቶ ለናሆም የሰጠውን ዓይነት ለሷም በጥብጦ ይሰጣታል። እሷም
ተቀብላ ትወጣለች። ሁለቱም ያጓራሉ።)

መጋረጃው ይዘጋል

ትዕይንት ሶሥት

መጋረጃው ሲከፈት በትዕይንት ኣንድ የነበሩት ሶፋዎች ይታያሉ። ሩሃማ ከወድያ ወዲህ ትመላለሳለች። ቤቱ ሻማ
በርቶበታለ። ከጠረጴዛው ላይ ድፎ ዳቦ ይታያል። በግራን በቀኝ ጠላና አረቂ ተቀጧል። የመቸኮል ባህሪ ይታይባታል።
ጠንቋዩ የሰጣትን መድሃኒት ወንበሩን ትረጫጨዋለች።

ናሆም፡- እንዴት አመሸሽ የኔ ውድ? (በፈገግታ ይገባል። እሷንም እቅፍ አድርጎ ይስማታል። በእጁ ፌስታል አንጠልጥሎ
ይዟል። ቤቱን በግርምት ይመለከትና) ዛሬ ምን ተገኘ?

ሩሃማ፡- ዉዱ ባሌቤቴ ረሳሁት ልትለኝ ባትሆን?

ናሆም፡- አልኩት እንጂ…….የኔ ውድ ከስጦታዎች ሁሉ የላቅሽው ስጦታዬ አንቺ ነሽ።

ሩሃማ፡- ምናስዬ እኔስ ካላንተ ምን ውድ ስጦታ አለኝ?

ናሆም፡- (ሳቅ እያለ) ይሳኮርዬ እንዴት በዚህ ስም ልትጠሪኝ ቻልሽ?

ሩሃማ፡- እየነገርኩህ…..አንተ እውነትም ረስተሀዋል……ዛሬኮ ፍቅር የጀመርንባት ቀን ናት….የልደታችን ቀን፣ ስም


የተውጣጣንባት ቀን…….

ናሆም፡- አሃ……አስታወስኩት……አይ አንቺ ምን ዓይነት አስተዋይ ልብ ነው ያለሽ? እንኳንም የኔ አደረገሽ።

ሩሃማ፡- እኔም እንኳን የኔ አደረገህ……በል ራት ላቅርብ እስከዛው ዪሄን ዳቦ ቁረሰውን እቀማመስክ ጠብቀኝ (ወደ ጓዳ
ትገባለች)

ናሆም፡- እሺ የኔ ስጦታ። (ሩሃማ እንደገባች ዳቦውን ቆርሶ ጠንቋዩ ሰጡ መድሃኒት ቀብቶ ይጠብቃታል። እሷም ምግብ
ከውስጥ ይዛ በፈገግታ ትገባለች። በአክብሮት ከተቀመጠበት ተነስቶ የቀባውን ዳቦ አንስቶ እያጎረሰ) አስታዋሼ
ይችን ብዪልኝ…..ብቻሽን እኮ ደከምሽ።
ሩሃማ፡- እሺ ሸግዬ (ምግቡን ወደፊቱ እያቀረበች) በል በላ ዛሬ እንዴት ያለ ወጥ ሰርቻለሁ መሰለህ…..

ናሆም፡- አይ አንቺ ለሴትነቱማ ማን ችሎሽ? ካንቺ ወዲያ ሴትነትስ አይገኝም።

ሩሃማ፡- የኔ ውድ እንዳንተ አይነቱ ወንድስ የት ተገኝቶ? በስራም በለው በሌላው የልብ አድርስ እኮ ነህ…….እንደው
ጠን……(ደንግጣ አፏን ትይዝና ወድያውኑ) እግዚአብሔር እድሜህን ያርዝመው።

ናሆም፡- ልክ ብለሻል እድሜ ይስጠን። ለማንኛዉም ይህን ጫማና ልብስ ለብሰሽ ነይ……..አሄሄ የልደታችን ቀን አንቺ ብቻ
ያሰታወሺው መሰለሽ?.....እያበሳጨሺኝ ነው አንጂ እኔምኮ አስታውሰዋለሁ።

ሩሃማ፡- አረ ካሁን በኋላማ መጨቃጨቅ ደህና ሰንብት ልንለው ይገባል። (ፊቷን አዙራ እያሾፈች “ደህና ሰንብት” ትልና
ወደሱ ዙራ) አዲስ ሒወት ነው ከዚሁ በኋላ የሚገጥመን።(አየተፍለቀለቀች ለብሱን ይዛ መኝታ ክፍል ትገባለች)

ናሆም፡- (የሷን መግባት አይቶ) አረ ምን ጉድ ውስጥ ነው የገባሁ? እጄን በጄ….ሚሰቴን ልገላት ነው?.....ዳቦዉን፣ ልብሷንና
ጫማውን ሳይቀር ቀባብቸዋለሁ……ያ የተዳፈነ ጣፋጭ ፍቅር የተመለሰው ማን መካሪ አግኝታ ነው? እንደዚህ
እንክብካቤዋ የሚቀጥል ከሆነማ ምቾቱ ታየኝ የደለበ በሬ መስዬ መኖሬ ነው። (በጭንቀት ይንጎራደዳል) አረ
መከራዬ ልትሞት እኮ ሳምት ነው የቀራት…….አንድ ዓይኔ መጥፋቱ ነው……አረ የምን አንድ ዓይን እሷ ከሞተች ሁለት
ዓይኔ ጠፋ እነጂ…….ወይኔ ፈገግታዋ ብቻ ይቃኝ ነበር…..ዛሬ ደግሞ አምሮባታል…..አምላኬ እባክህን እባክህን……..

ሩሃማ፡- (ድንገት ልብሱን ለብሳ ትገባለች) ምነው ዉዴ ልመናው ምንድን ነው?

ናሆም፡- ዛሬ ጠዋትም ማታም ቤተ-ክርስትያን ስላልሄድኩ እዚሁ ላመስግን ብዬ ነው…….ደገሞስ ለዚህ ላደረሰን ምስጋና
ሲያንስበት ነው…….ፐፐፐፐ ንግስት ሳባ በየት መጣች? ዳገማዊት ሳባ ብዬሻለሁ……ንግስት ሆይ(ብሎ በርከክ ይላል)

ሩሃማ፡- (እጁን ይዛ እያነሳች) አይገባም ንጉስ ሆይ……እንዴት ያማረ ልብስና ጫማ ነው የገዛህልኝ ባክህ……(ፊቷንም
ኋላዋንም እያየች) እንዴት ነው አምሮብኛል?

ናሆም፡- በጣም….በጣም…..በጣም ነው ያማረብሽ። ፈጣሪና ልብስ ሰፊው ተገናኝተው ያስዋቡሽ ነው የምትመስዪው……ነይ


ቁጭ እንበልና እንጠጣ (እጇን ይዞ ያስቀምጥና ከጠላው በፍቅር ዓይን እየተዩ ይጠጣሉ። ድንገት ናሆም ተነስቶ)
መጸዳጃ ቤት ደርሼ ልምጣ…..(ብሎ ይወጣል)

ሩሃማ፡- እሺ ቶሎ ና (ከወጣ በኋላ ተነስታ በሃሳብ ትንቆራጠጥና) ያልታደች ሒወት…..ጉዴ ፈላ ዛሬ…..ለመግደል ሳጠምደው
ያፈቀርኩት መሰለው……እኔ ሞቱን ሳጎርሰው እሱ ሒወትን ያጠጣኛል……እንደዚህ የሚያስብልኝ፣ የሚወደኝ፣
የሚነከባከበኝ መሆኑን ባውቅ እዚህ መዘዝ ውስጥ መች እጄን አሰገባ ነበር……ቤተሰቦችን፣ ጓደኞቼን አረ ምኑ ቅጡ
ሁሉንም የተውኩብትን ማስረሻዬን በገዛ እጄ ላጣው……እመቤቴ እባክሺን የሞቱን ጽዋ ከሱ አርቂልኝ…..አረ ቶሎ
በነጋ…….

ናሆም፡- (ድንገት ይገባል) ወዴት ለመሄድ ነው በነጋ ያልሽው ውዴ?

ሩሃማ፡- (ተደናግጣ) እ…..የት እሄዳለሁ? ቤተ-ክርስትያን ነዋ……ነገ ዕሁድም አይደል በመቅደሱ ፊት ቁመን እናመስግነው
እንጂ…….
ናሆም፡- ልክ ብለሻል ስለተደረገልን፣ ስላለተደረገልን፣ እንዲሁም እንዲደረግልን ስለምንፈልገው ሁሉ ልናመሰግነው ይገባል።
ዛሬማ የእውነት አኮራሽኝ።

ሩሃማ፡- አንተም የእውነት አኮራኸኝ። (ተያይዘው ወደውስጥ ይገባሉ።)

መጋረጃው ይዘጋል

ትዕይንት አራት

መጋረጃው ሲከፈት መድረኩ በጭስ ታፍኖ ይታያል። ተላላኪው በነበረበት ቦታ ተቀምጦ ይታያል። አንድ ናሆም ተጎንብሶ
ይታያል።

ጠንቋይ፡- (እያጓራ) ምንድን እንድናደርግልህ ትፈልጋለህ? ምን ቀረህ? የሰጠንህ መድሃኒት አልሰራም?

ናሆም፡- አረ ስር ሰዷል፤ ሊያጠፋት ነው።

ጠንቋይ፡- ፋህ መጥፋቷን አይደል የምትፈልገው?

ናሆም፡- አረ ጌታዬ ይለፋት……ይቅር……የፈለጉትን ነገር ይውሰዱ እሷ ግን አትሙትብኝ፤ ጥሩ ፍቅር እየመገበችኝ ነው።


(ያለቅሳል)

ተላላኪ፡- ዝምበል! የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም።

ጠንቋይ፡- (እያጓራ) አንዴ ሁኗል…..እሷ በሕይወት እንድትኖር ከፈለክ አንተ ግዴታ መሞት አለብህ…..ይህን ደግሞ ማድረግ
አትችልም…..ምን አይነት ፍቅር አለህና ነው ነፍስህን አሳልፈህ የምትሰጥ? (ጮክ ብሎ) ትሰማለህ….ከነገወድያ
መሞቷ ስለማይቀር ቤትህን ለቀህ ውጣ።

ናሆም፡- ምን? ከነገወድያ…….አረ ወይኔ ባለቤቴ ይሳኮር ዋጋዬ ስጦታዬን ላጣት አልፈልግም…..(ሩሃማ መጥታ ትንበረከካለች)

መንቋይ፡- ነገርኩሃ መሰለኝ(ያጓራል) በራስህ ጊዜ የበጠስከውን ትዳር እንደገና ለመቀጠል አትሞክር…..ከዚህ በላይ
የሁለታችሁም ታሪክ አብሮ መዝለቅ አይችልም…….ስሚ አንቺ ደግሞ ምን አመጣሽ? መቼም ኮተታችሁ አያልቅ…..

ሩሃማ፡- ባሌቤቴን ልወስድ ናፈቀኝ……ጭቅጭቁ ይሻለኛል……

ጠንቋይ፡- (እየሳቀ) ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆሰ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማለቀስ አሉ…….እውነት
ነው….ባልሽ የሚሞተው ዛሬ…..አስከሬኑን ለመውሰድ ፈልገሽ ነው? ቀልደኛ ለመሆኑ ምን ተገኘ?

ሩሃማ፡- ፍቅር ፍቅር ነው የተገኘው ጌታዬ……ቤታችን ሰላም ሰፍኗል…..ምናልባት የሰጡኝ የሚያፋቅረውን ከሆነ ደስታዬ
ገደብ የለውም፤ የሚገድለውን ከሆነ ግን እባክዎ ይቅርብኝ ባለቤቴን እፈልገዋለሁ። በትናትናዏ ምሽት ብቻ ሺ
ዘመን ያሳለፍኩ ያክል ነው የተሰማኝ እባክዎ ጌታዬ (ታለቅሳለች)
ተላላኪ፡- የምን መነፋረቅ ነው ወሎመጀኑ የሚነፋረቅበት አይወድም! ዝም በይ! እንዳይሞትባችሁ የምትፈልጉ ከሆነ አንቺም
ባልሺን ይዘሽ ነይ አንተም ሚስትህን ይዘህ ና…..ካልሆነ ግን ከመሞት አይድኑም።

ናሆም፡- ይዘህ ና?.....አይሆንም ጌታይ….ልዋረድ ብለው ነው?

ሩሃማ፡- ጌታዬ ባለቤቴ እንኳን ሊመጣ ጠንቋይ የሚባል ሲጠራም አይወድ……እባክዎ የሞቱን ማለፊያ ማስረሻውን ስጡኝ።

ጠንቋይ፡- ተነሱ የምላእሁን ታደርጋላችሁ (አንገታቸውን እንዳቀረቀሩ ይነሳሉ)…..ዛሬ አንቺ ከባልሽ ጋር ማደር
የለብሽም…..አንተም ከሚስትህ ጋር ልታድር አይገባም……በሒወት መኖር አደል የምትፈልጉት? ሞት እንዲደመሰስ
ከፈለጋችሁ ሁለታችሁም አብራችሁ ልታድሩ ግድ ነው…..ካልሆነ ግን ይሞታሉ (ያጓራል)

ተላላኪ፡- እንግዲህ ለዛሬዋ ምሽት ባልና ሚስት ናችሁ። ሰላም ተባባሉ

(አንገታቸውን ደፍተው ፊትለፊት ይጠጋጋሉ። እጅ ለእጅ አንደተጨባበጡ ሑለቱም እኩል ይተያያሉ፤


ተደናግጠውም ያላቀቁና ወደኋ ይሸሻሉ።)

ናሆም፡- (በድንጋጤ) ይሳኮር እዚህ ምን ትሰራለሽ?

ሩሃማ፡- (በድንጋጤ) አንተስ ምን ትሰራለህ?

ናሆም፡- ለካ ተያይዘናል……ይሳኮር አንቺም?

ሩሃማ፡- ምንውስጥ ነው የገባሁት ዛሬ…..አንተም ምናሴ?

ናሆም፡- የትናትናው ማታ ደስታችን የዛሬው የሞታችን ዋዜማ ነበር ማለት ነው? ተላልቀናል በይኛ…..

ሩሃማ፡- ምናሴ ተው እንጂ ለምን እንሙት አዲስ ቀን መጥቷል…..ጭቅጭቅና ንትርኩ ከጨለማው ጋራ አብሮ ጠፍቷል። የኛ
ንጹህ ፍቅርና ሰላም እንደማለዳዋ ጮራ በርቷል። አንተ ውስጥ ማግኘት የሚገባኝን ፍቅር ስላጣሁ ነው ይህን
ያደረኩት። (ተጠጋግተው እጅ ለእጅ ይያያዛሉ) እጣፈንታችን ሞት ከሆነ አብረን እንሙት።

ናሆም፡- አየሽ ሁለታችንም ስህተት ውስጥ ገብተናል……ብንወያይበት ምስጢራችን ከቤት አይወጣም ነበር……ይህች ቀን ለኔና
ላንቺ የመጨረሻ የሒወት ምዕራፋችን ናት። ነገ እንሞታለን…….ይሳኮር ባለችን አጭር ደቂቃ ውስጥ የተዳፈነውን
ምስጢር እንመለሰው።

ጠንቋይ፡- (ጠንቋዩ ከተሸፈነበት መጋረጃ ውስጥ ይወጣል።) ሞት ነው የሚያስጨንቃችሁ?

ናሆምና ሩሃማ፡- (እኩል በጭንቀት) አዎ

ጠንቋይ፡- ታላቁ መጽሓፍ እንዲህ ይላል “እርሱ ስለናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላያ ጣሉት”....”ሞት ሆይ
መውጊያህ የት አለ?” መባሉንስ አላነበባችሁም?......እናንተ የሚያስጨንቃችሁን ነገር ለኛ ነገራችሁን፤ ትክክል ግን
አልነበራችሁም፤ እኛ የናንተን ሸክም መሸከም አንችልም። ችግራችሁን ለክርስቶስ ብትነግሩታ ባረፋችሁ ነበር፤
ዓለም ያረፈችው በርሱ ክንድ ላይ ነውና።
ተላላኪ፡- አዎ ስንቶቻችን ከቤተ-ክርስትያን ይልቅ ለጠንቋይ ተንበርክከን፣ ሰግደን፣ በጠንቋይ አምነን ይሆን? ፈጣሪን
ብትለምኑት መች ሰላምና ፍቅር ይነሳችሁ ነበር? ውሃውን ወደ ወይን የቀየረ አምላክ የናንተን ፍቅር መመለስ
ያቅተዋል ብላችሁ ታስባላችሁ? ብዙዎቻችን ልባችን ለክርስቶስ ሳይሆን ለጠንቋዮች ነው አሳልፈን የሰጠነው፤
ከጠንቋይ ቤት ሞት እንጂ ሒወት የለም።

ናሆም፡- እውነት ነው ሒወት ያለው በክርስቶስ ውስጥ ስንኖር ነው።

ሩሃማ፡- እና አንሞትም ማለት ነው? ሞታችን ተሻረ?

ጠንቋይ፡- አትሞቱም…..እኛ እናንተን አናውቃችሁም፤ እናንተም አታውቁንም። ጎርቤታችሁ የሚገኘው ጓደኛችን ስለእናንተ
የቀድሞ ፍቅራችሁ እና አሁን ስላላችሁበት ሁኔታ ሲነግረን እኛም ያን የጠፋውን ፍቅራችሁን ተመልሶ ለማየት
ልናስታርቃችሁ ወሰንን፤ ይህንንም አደረግን። ካስቀየምናችሁ ይቅረታ። የሰጠናችሁ መድሃኒትም እምነትና ጠበል
ነው።

ናሆም፡- መልካም ነገር ነው ያደረጋችሁት። ጥሩ ዘይዳችኋል።

ሩሃማ፡- አቤቱ ኀጥያቴ ምንኛ በዛ…..(ወደላይ እያየች) እንደኀጥያቴ ብዛት አትመልከተኝ። ይቅርታና ምሕረት ከሚያፈልቀው
መዳፍህ አኑረኝ። (እየተንበረከከች) ምናሴ ይቅር በለኝ።

ናሆም፡- ይቅረታ ከሰማይ ነው። እርሱ ስለበደላችንና ስለመተላለፋችን ይቅር ይበለን፤ እኔንም ይቅር በዪኝ። (ይተቃቀፋሉ)

ተላላኪ፡- ካሁን በኋላ በመሃላችሁ ፍቅርና ግልጽነት ይኑር፤ በንሰኃ ሒወት እየተመላለስን፣ ከምስጢሩም ተካፋይ እየሆንን
በሓይማኖታችን ጸንተን እንኑር።

“እንደ ቸርነትህ” የሚለው መዝሙር በጥቂቱ እየዘመሩ መድረኩ ይዘጋል።

መጋረጃው ይዘጋል

አለማየሁ ሲሳይ

፬ኛ ዓመት

ቴአትር ጥበባት

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ-ሓቂ ግቢ-ጉባኤ

የስነ-ጽሁፍ ንኡስ ክፍል

ኅዳር-2008

ወስበሐት ለእግዚአብሔር

You might also like