You are on page 1of 3

ጭውውት ሦስት

(መብራት ሲበራ በአዘነ ጎጃም ወይ በፎጣ ተከናንበው የሚሳሳሙ ኮረዳና ጎረምሳ ይታያሉ። ከኋላ ሃገርኛ የእረኞች
ዋሾንንት ይሰማል! ይኼኔ ጥቂት ትንሽ ሲላፉ፣ ሲጎነታተሉ ፣ ሲሳሳቁ ይቆዩና ድንገት እርስዋ ብድግ ብላ ትነሳለች።
እርሱም በርገግ ብሎ ጋቢውን ሰብሰብ አድርጎ ዱላውን ከወደቀበት ፈልጎ ይንጎራደዳል።)

እርሱ - ምነው? ምን አይተሽ ነው ዓይንዬ!

እርሷ - ምንም (እየተሽኮረመመች)

እርሱ - ታዲያ ምነው እንዲህ እንደእንቁራሪት ፊንን ብለሽ መነሳትሽ። ጥሩ እየተጨዋወትንም አልነበር።

እርሷ - አሳመምከኝ! (እየተሽኮረመመች)

እርሱ - አሳመምኸኝ?

(ራሷን ላይ ታች ትነቀንቃለች)

እርሷ - ደግሞ አበዬ ይቆጣኛል ልኽድ!

(ሄዶ አፈፍ ያደርጋታል እጇን)

እርሱ - ነገሰ ብቅ የማትዪ! እንዴት አድረጌ ልጥራሽ

እርሷ - እስከመቼ ግን ርንዲህ ተደብቀን! ተሰው ዓይን ተሸሽገን! ምናለበት ጠቅልለህ ብትወስደኝ። እዚያ የንጉሥ አገር
አዲስ አበባ የሚሉት አግብቼ እወስድሻለሁ ብለኸኝ አልነቀር?

እርሱ - ነበር! አባትሽ በጀ አላሉም እንጂ!

እርሷ - አበዬ ደግሞ ምን አደረገ?

እርሱ - ልጅዎን ይዳሩልኝ! ብዬ ሽማግሌ ብልክ ሽማግሌዎቼን ውሻ አድርገው አባረው የመለሱብኝ እርሳቸው አይደሉም
እንዴ። እርሳቸው አይደሉ እንዴ ጥሎሹን ከየት አምጥቶ ይከፍላል ብለው አስወርተው የሰፈሩ ሁሉ መቀለጃ ያደረጉኝ።

እርሷ - ታድያ እርሳቸው ስላሉ ነው የማትወስደኝ። ወንድ ስላልሆንህ ነው እንጂ! (ጀርባዋን ሰጥታ ታኮርፋለች)

እርሱ - የኔ ወንድነት ምን ያደርጋል ብለሽ ነው።

ተሟግተህ ተሟግተህ ዳኛው ሲያደላብህ

ብርና ወንድ ልጅ አይልም ወይ ልብህ አለ ዘፋኙ። ተይው እስኪ ። ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ነው ነገሩ።

እርሷ - ምነው ይኸው የባላምባራስ ባያብል ልጅ ሎሚሽታ የከንፈር ወዳጇ ጠልፎ ወሰዳት አይደል እንዴ?

እርሱ - ይኼ ማነው አገኘሁ!

አርሷ - ታድያስ

እርሱ -አያደርገውም
እርሷ - አደረገው እንጂ!

እርሱ -እስቲ ሙት በዪ (እጁን እየዘረጋላት)

እርሷ - ልሙትልህ! (እጁን እየመታች)

እርሱ - አገኘሁም ወንድ ሆና ሴት ጠለፈች።

እርሷ - ይኸው አሁን ባላምባራስ! በተከበርኩበት ሰፈር አታዋርደኝ። ቢያንስ በወግ ልዳራችሁ ብለው መልዕክት ላኩበት
አሉ።

(ለአፍታ ዝም ይባባላሉ)

እርሱ - ታዲያ አሁን ምን ይሁን ነው የምትዪ

እርሷ - እንደው በወንድነት ታገኘሁ የምታንስ አይመስለኝም

እርሱ - እናሳ

እርሷ - እስከምለው ለምን ትጠብቃለህ

እርሱ - በይው እንጂ

እርሷ - ነገ ለማኝ ሳያራ በይህ በጓሮው በኩል ትመጣና ኩኩ መለኮቴ ኩኩ መለኮቴ ብለህ ጩህ! እመጣለሁ!

እርሱ - (በስጨት ብሎ ወደኋላ ይመለስና) ኤድያ ሌላ ምልክት ስጭኝማ

ባለፈው በዚህ በጓሮ በኩል እምቧ በል! እምቧ ስትል ጊዜ እናቱ የመጣች መስሎት ጥጃው በጥሶ ሲያመልጥ እርሱን
ለመመለስ እመጣለሁ!' ብለሽኝ እንደከብት እምቧ ብል እምቧ ብል በየት በኩል

በስተጓሮ ሆኜ እምቧ ስል እምቧ ስል

እንደጥጃ ፈትተው ይለቁሽ ይመስል

በስተጓሮ ሆኜ ባነጥስ ባነጥስ

ወይ አንቺ ብቅ አትይ ወይ ጥጃው አይበጥስ አለ ዘፋኙ

እርሷ - ግድ የለህም ጥራኝ እሰማለሁ ነገ!

(ይኼኔ ከመድረክ ጀርባ ትጠራለች!)

እናቷ - አንቺ ዓይንዬ! የት ሄደሽ ነው። አበዬ እየጠራሽ ነው።

(የእናቷን ድምጽ እንደሰማ እርሱ ደንግጦ ጨርቁን ሁሉ ጥሎ እየሮጠ ይወጣል።)

እርሷ - እመት መጣሁ መጣሁ እመምዬ መጣሁ

(ይህን ብላ ልትሰናበተው ዞር ስትል ከተቀመጠበት የለም! እንደማሽሟጠጥ ብላ አፏን ታሞጠሙጣለች! ከዚያ 'መጣሁ'
እያለች ትወጣለች።)

You might also like