You are on page 1of 4

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

"አሐደ አእትት ለዘመን፤

አንዱን ለዘመን ተው!"


መርሐ እውር

"አዲስ" ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ እንጂ ጠቢቡ እንዳለው "ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡" መክ 1÷9 ለምሳሌ አዲስ ነው ብለን
የገዛነው ነጠላ ከሆነ ጊዜ በፊት የደረሰ ጎረምሳ የጥጥ ዛፍ ነበረ፡፡ የሆነ ጊዜ ደግሞ ያለቀለት ባዘቶ፡፡ ኅልውናውን ቀይሮ ነጠላ
ሆኖ ሲመጣ አዲስ ይባላል እንጂ አዲስ አይደለም፡፡ ከእርሱ በፊት እልፍ ነጠላዎች በምድር ላይ ተሰርተው ተለብሰዋል፡፡
የሚሸጥላችሁ ሸማኔም ከዚህ በፊት በሺህ የሚቆጠሩ ነጠላዎችን ሰርቶ ሸጧል፡፡ እናንተም ከዚህ በፊት ቀላል የማይባል
ቁጥር ያላቸውን ነጠላዎች ገዝታችሁ ለብሳችኋል። 'ታዲያ ይህን ነጠላ አዲስ የሚያሰኘው ምንድነው?' ካላችሁ መልሱ
ስለእንግዳ ኅላዌው ያለን እሳቤ ነው እላችኋለሁ፡፡ ምንድነው እንግዳ ኅላዌ ማለት? ምንም እንኳ ከዚህ በፊት በዓለም ላይ
አእላፍ ነጠላዎች ተሰርተው ቢሆንም፣ እናንተም ብዙ ነጠላዎች ቢኖሯችሁና ነጠላ ለሚባለው ነገር እንግዳ ባትሆኑም ግን
ለዚህ ለገዛችሁት ነጠላ እናንተም፣ የምትኖሩባት ዓለምም ምናልባት ደግሞ የሰራው ሸማኔም ራሱ እንግዳ ናችሁ፡፡
(በዓለም ላይ ምንም አዲስ ነገር ባይኖርም ሁሉም ነገር ደግሞ በራሱ አዲስ ነው እንደማለት) በምድር ላይ በኖራችሁበት
እድሜ ከዚህ ሸማኔ ይህንን ነጠላ በዚህ ቦታ፣በዚህ ጊዜና በዚህ ሁኔታ ገዝታችሁት አታውቁም፤ የመጀመሪያችሁም
የመጨረሻችሁም ነው፡፡ ሸማኔውም ይህን ነጠላ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ቦታ፣ጊዜና ሁኔታየሚሸጠው
ለእናንተ ነው፡፡ ያ ነው አዲስነት፤ የተመሰረተው በቦታ፣በጊዜና በሁኔታ ላይ ነው፡፡ ለዛሬ የምናየው ከአዲስ ዓመት መምጣት
ጋር አያይዘን ሊኖረን ስለሚገባው በጎ ለውጥ ለመረዳት በዋናነት በጊዜ ላይ የተመሰረተውን አዲስነት ነው፡፡

በጊዜ ላይ የተመሰረተውን የአዲስነት ጽንሰ ሃሳብ በደንብ መረዳትችን ከጊዜ ሂደት ጋር ሊኖረን ስለሚገባው በጎ ለውጥ
ያለንን አመለካከት ለመቅረጽ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ እኔን ተመልከቱኝ፡፡ ከዚህ በፊት ያለውን አረፍተ ነገር
ስጽፍ የነበርኩት እኔና አሁን ያለሁት እኔ አንድ አይደለንም፡፡ ቅድም 'አሁን ያለሁት እኔ' የተባልኩት እኔም አሁን የለሁም፡፡
ከእግዚአብሔር ውጪ በምድር ላይ ብቸኛ የማይለወጥ ነገር ቢኖር ራሱ ለውጥ ብቻ ነውና ብገነዘበውም ባልገነዘበውም
ጊዜ እስካለ ድረስ በእያንዳንዱ ቅጽበት በምኖረው ህይወት ውስጥ በማካብተው ልምድ ምክንያት በየሰከንዱ ሌሎች ብዙ
እኔዎች ይፈጠራሉ፡፡ በዚህ የቅጽበታት ለውጥ ውስጥ ደግሞ ሁሉም ፍጥረት ያልፋል፡፡ ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት ደግሞ
እግዚአብሔር በሰጣቸው እውቀት ይህን ለውጥ ለመረዳትና ወደበጎ ለመቀየር የታደሉ ይሆናሉ፡፡

ዘመን ሲቀየርም "አዲስ" ዓመት የሚለውን እሳቤ በዚህ መልኩ መቃኘት አለብን፡፡ እንደምታውቁት ሁላችንም ለውጥ
እንፈልጋለን፤ ወይም ያስፈልገናል፡፡ ችግራችን ለለውጥ ጊዜ መጠበቃችን ብቻ ነው፡፡ በተለይ ለውጡ ለበጎ ሲሆን
አስቀድመን ምክንያቶችንና ቅድመ ሁኔታዎችን መደርደር እናበዛለን፡፡ ብዙዎች "በአዲሱ ዓመትማ ንስሃ ገብቼ ለሥጋ
ወደሙ እበቃለሁ!" እያሉ ያስባሉ፡፡ ሰዎች ያለባቸውን የቁማር፣ የመጠጥ፣ የጫት ወይም የትንባሆ ሱስ ለመተው አዲስ
ዓመትን ሲጠብቁ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ ሲገቡበት ግን አዲስ ዓመትን ጠብቀው አልገቡበትም፡፡ መስከረም አንድ
የመጠጥ ሱሱን ለመተው ያቀደ ሰው ጳጉሜን አምስት የመጨረሻ ነው ወይም ዓመት በዓል ነው በሚል ሰበብ በአልኮል
ተነክሮ ሲያመሽ ታገኙታላችሁ፡፡ ችግሩ ያለው በምዕመናን ዘንድ ብቻ አይደለም፡፡ በአንዳንድ የቤተክርስቲያን
መምህራንም ዘንድ ይስተዋላል፡፡ ለውጡን ቅጽበታዊ አድርገው የሚያስቡ መምህራን አሉ፡፡ ኃጢኣት ማለት መጥፎ
ልምድ ማለት ነው፡፡ በአንዴ አይገባበትም፡፡ በተለይ ሱስ ሲሆን ደግሞ ይብሳል፡፡ ሲወጣም ደግሞ በቅጽበት አይወጣም፡፡ ቀስ
በቀስ አንዱን እየተዉ ቀጥሎ ሌላውን እያሉ በሂደት ነው እንጂ፡፡ በዓሉን የለውጥ መነሻ ነጥብ አድርጎ መውሰዱ ባይከፋም
ለመለወጥ ግን የግድ በዓሉን መጠበቅ የለብንም፡፡ “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፤በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥
የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ አሁንን የሚያክል ጊዜ የለም፡፡ 2 ኛ
ቆሮ 6፥2 ይህ ችግር ደግሞ የሚመነጨው ከላይ እንደጠቀስኩት በየሰከንዱ በየቅጽበቱ መለወጣችንን ባለመረዳታችን
ብቻም ሳይሆን ለአዲስና ለለውጥ ባለን የተጣመመ መረዳት ምክንያት ነው፡፡

ጊዜ ኃያል ነው፡፡ አይነኩም፣ አይገፉም ተብለው ለዘመናት ሲፈሩ የነበሩ ኃይላት እንደኢያሪኮ ግንብ በእልልታ ብቻ እጅ
ሳይካቸው ዶግ አመድ ሲሆኑ ያየነው በጊዜ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቀን የጣላቸው እግዚአብሔር ግን ያልረሳቸው ከትቢያ
ተነስተው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሲገኑና በክብር ዙፋን ላይ ሲቀመጡ ያየነውም በጊዜ ነው፡፡ የጊዜ ኃያልነት ከላይ
ባሉት አንቀፆች ለማብራራት ከሞከርኩት ዘለለታዊ የአዲስነትና የአሮጌነት ምንታዌነቱ በተጨማሪ ከእግዚአብሔር
የፍርድ መሳሪያነቱም የመነጨ ነው፡፡ ጊዜ እግዚአብሔር ከሚፈርድባቸው መሳሪያዎች ውስጥ ዋነኛውና ትልቁ ነው፡፡
ለዚህ ነው "ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር" ያለው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፡፡ 'ለእግዚአብሔር ሥራውን የሚሰራበት ጊዜ
ነው፡፡' እንደማለት፡፡ መዝ 118፥126 አንዳንዶች "እግዚአብሔር በዓለም ላይ ያሉትን ክፋ ሰዎች ሁሉ አንድ ጊዜ በመብረቅ
ወይም በቸነፈር ወይም በሆነ ነገር መትቶ ማጥፋት ተስኖት ነው?" ይላሉ፡፡ እኔም በግሌ ለእኔ በግልጽ የታየኝ እውነት
ከሌሎች ወንድም እህቶቼ ተሰውሮባቸው ሳይ "እግዚአብሔር ለኢ-አማንያን ሁሉ አንዴ በማያሻማ መልኩ ኅልውናውንና
ወደእርሱ የሚያደርሰውን ትክክለኛ መንገድ በሆነ ተአምር መግለጽ ተስኖት ነው?" ብዬ ጠይቄ አውቃለሁ፡፡ ጥያቄዎቹ
እውነትነት ያላቸው ይመስላሉ፤ በጎውን በማሰብ እንጂ በምንፍቅና ወይም በሌላ የጥፋት ሃሳብ ምክንያት የተጠየቁ
አይደሉም፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ መነሻ አሁን በዓለም ላይ የሚታየው ኢ-ፍትሐዊነት ነው፡፡ ደግና ጻድቅ፣ ሃቀኛና ለጋስ
ሰዎች እንደሌሎች ባለመዝረፋቸው፣ ደመወዛችን ብቻ ይበቃናል በማለታቸውና ንጹህ ሕሊናቸውን በኃጢኣት ምክር
ባለማቆሸሻቸው ምክንያት በከባድ ምድራዊ ችግር ውስጥ ሲጣሉ፣ ሲራቡ፣ ሲታረዙና ሲቸገሩ በአንጻሩ የዘረፉትና የሰው
ሃቅ የበሉት ተደላድለው የተመቻቸ ምድራዊ ህይወት ሲኖሩ መመልከት የተለመደ ነውና፡፡ ሁለተኛውም እንደዚያው
ሁሉም የራሱን እውነት እያጎላና የሌሎችን እያኮሰሰ ከሚያወናብድ እግዚአብሔር ሃቀኛውን መንገድ መግለጹ የተሻለና
ተገቢ ይመስላል በሚል በጎ አመለካከት የተነሳ ነው፡፡ በጥያቄ ደረጃ ተመልክተን ለሁለቱም መልስ ብንሰጥ ደግሞ መልሱ
'እግዚአብሔር ተስኖት አይደለም!' የሚለው ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና፤ ሁሉም ይቻለዋል፡፡ ዘፍ
18÷14፤ ሉቃ 1፥37 ታዲያ ለምን አያደርገውም ቢሉ መልሳችን የሚሆነው እግዚአብሔር ከመብረቅና ከቸነፈር
በሚበልጠውና ጊዜ በሚባለው የፍርድ መሳርያው ፍርዱን እየሰጠ ነው የሚለው ነው፡፡ ጠቢቡ "ለሁሉም ጊዜ አለው" ሲል
የተናገረው ይህንኑ ነው፡፡መክ 1፥1-8 ይህንን እውነት መጽሐፍ ቅዱስም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሳያል፡፡ ደብረ ሲና ስር
ሕዝበ እስራኤል ጣዖት ሰርተው ሲሰግዱ አስርቱን ተአምራት በፈርዖን ፊት አሳይቶ ከባርነት ነጻ ያወጣቸው
እግዚአብሔር አምላክ መብረቅ አውርዶ ወይም በዚያ ጭልጥ ያለ በረሃ ላይ ደራሽ ውሃ አምጥቶ እነርሱን እዚያው
አምላካችን ብለው የሰገዱለት የላም ጣዖት ስር በመግደል መቅጣት ተስኖት አይደለም፤ ጊዜ የሚባለውን ትልቁን የፍርድ
መሳሪያውን እየተጠቀመ ነበር እንጂ፡፡ ዘጸ 32፤ 4፤ 5 ከግብጽ ከተነሱት እልፍ አዕላፍ ሕዝበ እስራኤል መካከል በሕይወት
ወደተስፋይቱ ምድር ወደከነዓን የገቡት ሁለት ብቻ መሆናቸው ይህንን ያሳያል፡፡ከእነርሱ ጋር አብረው ከነዓን የገቡት
ብዙዎቹ ወላጆቻቸውን በመንገድ ያጡና በመንገድ ላይ ተወልደው ያደጉ ናቸው እንጂ ከግብጽ የወጡት ዋነኞቹ
አልነበሩምና፡፡ ዘኁ 26፥63-64 የህልቃና ሚስት ፍናና ጣውንቷን ቅድስት ሐናን በመጥፎ ቃል ስትናገራት እግዚአብሔር
እንደ ቅዱስ ዘካርያስ ዲዳ እንደ ኤልማስ ዕውር ማድረግ ተስኖት አልነበረም፡፡ ሉቃ 1፥20፤ ሐዋ 13፥7 በኋላ ላይ
ሳሙኤልን የመሰለ ልጅ ሰጥቶ በጊዜው ሊፈርድ ነው እንጂ፡፡ "እስመ መካን ወለደት ሰብዓተ፣ ወወላድሰ ስዕነት ወሊደ፤
መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፣ ብዙም የወለደችው ደክማለች።” ብላ ቅድስት ሃና ያመሰገነችው ለዚያ ነው፡፡1 ኛ ሳሙ 2፥5
አፍኒንና ፊንሐስ ካህናት ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያልተገባ ነውር ሲፈጽሙ እግዚአብሔር በንዳድ ወይም
በአንዳች መቅሰፍት እነርሱን መቅጣት ተስኖት አልነበረም፤ በጊዜው ለመፍረድ እንጂ፡፡ በኋላ በጠላቶቻቸው
በፍልስጤማውያን እጅ እንዲወድቁ ከማድረጉም በላይ አባታቸውም በእነርሱ ጦስ እንዲሞት ሆኗልና፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ
የእስራኤላውያን መመኪያና ክብር የነበረችው እግዚአብሔር የሚያድርባት ታቦተ ጽዮን የተማረከችው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
ይህም ክብራቸው፣ ኃይላቸውና መመኪያቸው እግዚአብሔር እንደተዋቸው ማሳያ ነው፡፡ 1 ኛ ሳሙ 1-4 ደግሞ
እንደክፋታችን እግዚአብሔር ወዲያው የሚቀጣን ቢሆን ኖሮ ምድር ባዶ በሆነችም አልነበር? ስለዚህ ጊዜ እግዚአብሔር
ቸርነቱንና ፈራጅነቱን በአንድነት አዋሕዶ የሚገልጽበት ኃያል ሥራው ነው፡፡
ይህን ሁሉ ስለ ጊዜ ኃያልነት የገለጽኩት ከመሬት ተነስቼ አይደለም፡፡በጊዜ፣ በዘመን ሂደት የሚከሰት ለውጥ ምን ያህል
ትልቅ እንደሆነና በእኛና በአካባቢያችን ላይም ትልቅ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ለማስረገጥ ነው፡፡አሁን ስለ አዲስነት እና ስለ
ጊዜ (እንዲሁም በጊዜ ላይ ስለሚመሰረተው የአዲስነት ጽንሰ ሃሳብ) ይህን ያህል ጊዜ ወስደን ካየን ለውጥ የሚለውን
እሳቤ ለመቀበል ጠንካራ መሠረት አኑረናል ማለት ነው፡፡ለውጥ እኛ የምናመጣው ነገር እንዳልሆነ ተግባብተናል ብዬ
አስባለሁ፡፡ ወደድንም ጠላንም በእያንዳንዷ ሰከንድ ለውጥ ላይ ነን፡፡ አለመለወጥ የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም
ያለነው፡፡ማድረግ የምንችለው ብቸኛ ነገርና እግዚአብሔር የሰጠን ልዩ ፀጋ ይህን የለውጥ ሂደት መገንዘብና ወደበጎ ለውጥ
መቀየር ነው፡፡

ወደ በጎ ለውጥ መቀየር ያልኩት መጥፎ ለውጦች ስላሉ ነው፡፡ብዙዎቻችን ለውጥ ሲባል አዕምሮዋችን ላይ የሚከሰተው
አዎንታዊ ጎኑ ነው፡፡ለዚህ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው ደግሞ በጎ የምንለው ለውጥ ከባድ መሆኑ ነው፡፡ መጥፎው ለውጥ
ወይም አሉታዊው ለውጥ በጣም አታላይ፣ ጣፋጭና እንደመንሸራተት ያለ ነው፡፡እያሳሳቀ ነው የሚወስደው፡፡ ስለዚህ
ብዙዎቻችን ልብ አንለውም፡፡ ቅድም እንዳልኩት ሱስ ሲጀመር አያስጨንቅም፡፡ከሱስ መውጣት ግን በጎ ለውጥ ነውና ብዙ
ፈተና አለው፡፡ ለምን?

ዘመን ሲለወጥ፣ ጊዜ ሲለወጥ ሁላችንም ብንለወጥም ሁላችንም ግን መለወጣችንን ቆም ብለን ለመረዳትና ወደበጎ
ለውጥ ለመቀየር አንሞክርም፡፡ ብዙ መለወጣቸውን ያልተረዱ ሰዎች አሉ፡፡ መለወጣችንን ካልተረዳን ደግሞ ለውጡን
የበጎ ልናደርገው አንችልምና እንጎዳለን፡፡ ዘመን እንዲህ ያሉትን ዝንጉዎች ጥሎ ይነጉዳል፡፡ ዘመን ሲቀየር መለወጣችንን
የማንረዳና ለበጎ ነገር የማናውለው ከሆነ ዘመን ዓይኑን ሳያሽ ጥሎን ይሄዳል፡፡ ዘመን ጥሎን የሄደ ብዙዎች አለን፡፡
ስላልተቀየርን ግን አይደለም፡፡ መቀየራችንን፣ መለወጣችንን ለበጎ ስላላደረግነው ነው እንጂ፡፡ “ባረጀ አቁማዳም አዲስ
የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም
ይጠፋል። አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፡፡ ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡" እንዳለው ነው ቅዱስ ሉቃስ፡፡
ሉቃ 5፥37 አሮጌውን ማንነት በአዲሱና በተለወጠው ሰውነታችን ውስጥ ለማስገባት መጣር የለብንም፡፡ ታዲያ ዘመን
ጥሎን እንዳይሄድ ምን ማድረግ ያለብን ይመስላችኋል? ለውጣችንን መረዳት ነው ያለብን፡፡ ለውጣችንን ስንረዳ ብዙ
የተሸከምናቸው የማይረቡን ሸክሞች እንዳሉን እንረዳለን፡፡ እነርሱን በመተው ነው ጥሎን የሄደው ዘመን ላይ
የምንደርስበት፡፡

በውጊያ ላይ ወታደር በፍጥነት እንዲያጠቃ በታዘዘ ጊዜ ስንቁን፣ አንዳንዴም ደግሞ ከበድ ያሉ የጦር መሳርያዎቹንም
ቢሆን ለመሮጥና ቀጣይ ድሉን ለመቀዳጀት ስለማይረዱት ትቶ ይሄዳል፡፡ ለምን ቢሉ የእነዚያ ቁሶች ዋጋ ከእርሱ ሕይወት
ነፍስ ዋጋ ጋር የማይለካኩ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከመጎተትና ወደኋላ ከማስቀረት በተረፈ ለወደፊቱ ድል
የሚበጁት ስላልሆነ ነው፡፡ እኛም በዘመናት ሂደት ውስጥ እርድና እየመሰሉን፣ ብልጠት እየመሰሉን ይዘናቸው የመጣናቸው
አጓጉል ልምዶች ካሉን ከነፍሳችን መትረፍ ዋጋቸው ስለማይተካከል ልንተዋቸው ይገባል፡፡ እንደሃገርም ወደፊት
ለመራመድ ብዙ የምናራግፋቸው ኮተቶች የምንተዋቸው ነገሮች ይበዛሉ፡፡ ገንዘብ እንደፈጣሪ የሚመለክበት ዘመን ላይ
ደርሰናል፡፡ ወደፊት ለመራመድ የአልፐራሲም ሰዎች በዳዊት ፊት ጣዖቶቻቸውን እንደተዉ፣በእሳትም እንዳቃጠሏቸው
እኛም የዘመኑን ጣዖት ገንዘብን መተው አለብን፡፡ 1 ኛ ዜና 14፥11-12፤ 2 ኛ ሳሙ 5፥20-21 ያዕቆብ ለቤተሰቦቹ እንዳለው
እኔም "እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፡፡ ንጹሐንም ሁኑ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ!" እላችኋለሁ፡፡ ዘፍ 35፥2
ቅሚያና ዝርፊያ በዝቷል፡፡ የእኔ የአንተ መባባል ገዝፏል፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ ቃል "ይብቃችሁ፤ ግፍንና ብዝበዛን
አስወግዱ!" ብሏልና ዝርፊያችንን ክፋታችንን እንተው፡፡ ሕዝ 45፥9 ዳግመኛም እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ
“እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፣ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ
የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፣ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፣ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።”ብሏልና፡፡ ኤር 4፥4
ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን ሌዋውያኑን ካህናት ሰብስቦ “...ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት
ቀድሱ፤ ርኩሱን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።” እንዳላቸው እኔም መልእክቴ ይኸው ነው፡፡2 ዜና 29፥5 ሰውነታችሁም
እግዚአብሔር የሚያድርበት ቤተመቅደስ ነውና ቀድሱት፡፡ርኩሱን ነገር አስወግዱ፣ ሸክም ከማብዛት በስተቀር ሌላ ጥቅም
የሌለውን ነገር ተዉት፡፡ በአጠቃላይ “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው
አስወግዱ" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ አሮጌውን ሰው አስወግዱ፡፡ ኤፌ 4፥22

ለዚያ ነው የጽሑፉን ርዕስ "አሐደ አእትት ለዘመን፤ ለዘመን አንዱን ተው!" ብዬ የሰየምኩት፡፡ ሁሌ አዲሱ ዓመት
መጀመሩን መስከረም አንድ ቀን የሚያበስሩን ሊቃውንት የዓመቱን በዓላትና አጽዋማት የሚያሳወቀውን ባሕረ ሐሳብን
ሲያውጁ ከሚያውጇቸው አዋጆች መሃል አንዱ ነው፡፡ መጥቅዕና አበቅቴ ለማግኘት የሚያገለግለውን ወንበር የተሰኘ
ቁጥር ለማስላት ይጠቀሙበታል፡፡ መደብ የተባለውን ቁጥር ካገኙ በኋላ "ስለተጀመረ ቆጠርነ፣ ስላልተፈጸመ አተትነ
(ተውን)" በማለት ከመደብ ላይ አንድ ይቀንሱና ወንበሩን ያገኛሉ፡፡ ይህ መቀነስ ነው አንዱን ለዘመን ተው የሚባለው፡፡ ይህ
ራሱን የቻለ ቀመር ያለው ስለሆነ ባትቸገሩበት (ይልቁን ወደ ሊቃውንቱ ቀረብ ብላችሁ ብትማሩ) እመክራለሁ፡፡ ታዲያ
በየአዲስ ዓመቱ ይህንን አዋጅ ስሰማ ይደንቀኛል፡፡ለዚያ ነው ለእናንተ ለማካፈል የፈለግኩት፡፡ እኛ ስንት ለዘመን
የምንተወው ነገር አለ መሰላችሁ? ሁሉን ግን በአንዴ መተው አይቻልምና ቢያንስ በየዓመቱ አንድ አንዱን ሸክማችሁን
ብትተዉ ጓዛችሁ ስለሚቀላችሁ ወደፊት ለሚጠብቃችሁ የጽድቅ መንገድ ዝግጁ ትሆናላችሁ፤ ለውጡን ለበጎ
ታደርጉታላችሁ፡፡

ስለዚህ አንዱን ለዘመን ተዉ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

You might also like