You are on page 1of 16

ምዕራፍ አንድ

መልካም ምግባራት

የምዕራፉ ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምረው ካገባደዱ በኋላ
፩ ከክርስቲያኖች የሚጠበቁ መልካም ምግባራትን ይለያሉ፡፡
፪ ለማንና እንዴት መታመን እንዳለባቸው በታሪክ ይማራሉ፡፡
፫ ቅን ስለመሆን በቅንነትም ስለሚገኝ ጥቅም አውቀው ቅን ለመሆን ይጥራሉ፡፡
፬ ታዛዥ ልጆች መሆን እንዳለባቸው በታሪክ ይማራሉ፡፡

(የመክፈቻ ጥያቄዎች)
.፩ ልጆች መልካም ምግባራት ብላችሁ የምታስቡአቸውን ለመምህራችሁ ተናገሩ?
፪ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምታውቁአቸው ታዛዥ ልጆች መካከል የአንዱን ተራሪክ
ለመምህራችሁ ተናገሩ?

በቃል የሚጠና ጥቅስ


“ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ ይህ የሚገባ ነውና” ኤፌ ፮፥፩

ጥያቄ፦ ልጆች መልካም ምግባር ማለት ምን ማለት ነው?


መልስ፦ መልካም ምግባራት ማለት እግዚአብሔር አምላክን መውደዳችንን ለእርሱም መገዛታችንን
የምንገልጥበት የክርስቲያኖች ሁሉ መገለጫ ምግባራት ናቸው፡፡
ጥያቄ፦ መልካም ምግባራት የሚፈጽም ክርስቲያን ምንን ይገልጣል?
መልስ፦ መልካም ምግባርን የሚፈፅም ክርስቲያን ከሥራው የተነሣ የእግዚአብሔር ልጅነቱ በሰዎች
ዘንድ የተገለጠ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፦ መልካም ምግባር ሁል ጊዜ በሰዎች ዘንድ የተገለጠ ሊሆን ይገባዋል?
መልስ፦ አዎ እኛ ክርስቲያች ሁልጊዜ መልካም ምግባሮቻችን በሰዎች ፊት የተገለጠ መሆን ይገባል፡
፡ ልጆችዮ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ፦ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን
እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ማቴ ፭፥፲፮ በማለት ተናግሮአል፡፡ ስለዚህ ልጆች
መልካም ሥራ በመስራት እግዚአብሔር የሚደሰትብን ልንሆን ይገባል፡፡

ጥያቄ፦ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቁ መልካም ምግባራት ምን ምን ናቸው?

መልስ፦ አንደኛ ታማኝነት ነው?

ጥያቄ፦ ታማኝነት ማለት ምን ማለት ነው?


መልስ፦ ታማኝነት ማለት አደራ መጠበቅ፤ የታዘዙትን ነገር ማድረግ መፈፀም (ሰዎች የጣሉብንን
እምነት መጠበቅ) ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ሰው ታማኝ ሊሆን የሚገባው ለማን ነው?
መልስ፦ ፩. ለራሱ
፪. ለእግዚአብሔር
፫. ለሰዎች ነው፡፡
ጥያቄ፦ ለራሱ ሲባል ምን ማለት ነው?
መልስ፦ ለቃሉ ለአንዲት ነፍሱ ታምኖ ራስን ከክፉ ነገር መጠበቅ ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ለእግዚአብሔር ሲባል ምን ማለት ነው?
መልስ፦ እግዚአብሔር አምላክ እንደ አምላክነቱ ያዘዘንን ትዕዛዝ የሰጠን ህግጋትን በመጠበቅ መኖር
ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ምሳሌ የምናደርገው ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ለዚህም ትልቅ ምሳሌ የሚሆኑት አዳምና ሔዋን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ፈጥሮ
ወደ ገነት ካስገባቸው ሁሉን ነገር ካቀረበላቸው በኋላ አንዲት እፅ ይህችውን እፀ በለስን እንዳትበሉ
አላቸው ይህም ታማኝነታቸው፣ አደራ ጠባቂነታቸውን ከመግለጥ ይልቅ ሠይጣን በነገራቸው የጠሳሳተ
ቃል ተታለው አትብሉ የተባሉትን እፀ በለስ በመመገብ ታማኝነታቸውን አጎደሉ፤ ከእግዚአብሔርና
ከፍጥረታት ጋር ታጣሉ ከገነትም ተባረሩ፡፡ (ዘፍ ፪)
ጥያቄ፦ ለሰዎች መታመን ሲባል ምን ማለት ነው?
መልስ፦ ሰዎች የሰጡንን አደራ ጠብቆ መኖር፣ የራስ ያልሆነን ነገር አለመንካት፣ የሰዎች የሆነ ነገርንም
አለመመኘት ማለት ነው፡፡ በቤት ውስጥ፣ በአካባቢያች እንዲሁም በምንማርበት ትምህርት ቤት የእኛ
ያልሆነ ማንኛውም ነገር ባለቤቱ ሳያሳውቅና ሳይፈቅድ መንካት ወይም መውሰድ አለመታመን ነው፡፡
ጥያቄ፦ ምሳሌ የምናደርገው ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ቅዱስ የአባታችን የዮሴፍ ታሪክ እንመልከት፡- ያዕቆብ አሥራ ሁለት ልጆች የነበሩት ከእነዚህም
ልጆች መካከል እጅግ የሚወደው ዮሴፍ የተባለ ልጅ ነበረው፡፡ በአባቱ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው
ከወንድሞቹ በተለየ መልኩ መልካምና ታማኝ ስለሆነ ነው፡፡ አንድ ቀን ወንድሞቹ የአባታቸውን በጎች
ይዘው ለእረኝነት ወደሜዳ ወጡ ዮሴፍም ለወንድሞቹ ምሳ እንዲያደርስላቸው ተላከ፡፡ እነርሡ የነበሩት

በጣም ሩቅ ቦታ ነበርና ሲፈልጋቸው ውሎ ደከመው ለእርሱ የተሰጠው (ምግብ) አለቀበት፡፡ ከድማኩም


የተነሣ ርሀብ ተሰማው፡፡ ዮሴፍ ግን ለወንድሞቹ የሚሰጠውን ምግብ ይዞ ሳለ እየራበው ሳይበላባቸው
ቆየ ይህም ታማኝነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም ታማኝነቱ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትትና
“ድንጋዩን በተአምራት ዳቦ እንዲሆን አደረገለት ከዚያም በላና ጠነከረ የወንድሞቹን ምግብ በታማኝነት
ምንም ሳይነካ ይዞላቸው ሄደ፡፡ (ዘፍ ፴፯፥፩-፲፯) ማቴ ፬፥፫(ትርጓሜ)
ጥያቄ፦ የዮሴፍ ታሪክ ለኛ ምን ያስተምረናል?
መልስ፦ ይህ የዮሴፍ ታሪክ እኛም ለሠዎች ምን ያህል ታማኝ ልንሆን እንደሚገባን የሚያስተምረን ነው፡
፡ እኛም ከእርሱ ተምረን ለራሳችን፣ ለፈጠረን አምላክ ለልዑል እግዚአብሔር እንዲሁም ለቤተሰቦቻችን
እንዲሁ ለሠዎች ሁሉ ታማኞ ሆነን ልንኖር ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሁለተኛው መልካም ምግባር ምንድን ነው?
መልስ፦ ቅንነት

ጥያቄ፦ ቅንነት ምን ማለት ነው?

መልስ፦ ቅንነት ከክርስቲያናዊ ስነ ምግባራት መካከል አንዱ ሲሆን ኅሊና መሞላት፣ መልካምነት፣
ተንኮል የሌለበት ትክክለኛ እሳቤ ማሰብ በድርጊትም መፈፀም ነው፡፡
ጥያቄ፦ ቅን ሰው ምን ያያል?
መልስ፦ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ፊት ያያል
ጥያቄ፦ ማስረጃ ጥቅስ ብትነግረን?
መልስ፦ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና ጽድቅንም ይወድዳል ቅንነት ግን ፊቱን
ታየዋለች” በማለት ተናግሯል፡፡ መዝ ፲፩፥፯
ጥያቄ፦ ቅን ልብ ያለው ልጅ ምን ያደርጋል?
መልስ፦ ቅንልብ ያለው ልጅ በቀና አዕምሮ በንፁህ ልብ ሲጠሩት ይሄዳል ሲልኩት ይታዘዛል፡፡
ጥያቄ፦ ሌላ ምን ያደርጋል?
መልስ፦ ቅን ልብ ያለው ሰው ለሰዎች ብቻ አይደለም ለእንስሳም ጭምር ያዝናል፡፡
ጥያቄ፦ ማስረጃ ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ቅን ልብ ያላት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ታሪክ በአንድ ወቅት እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ሳለች ውኃ ቀድታ ስትመለስ አንድ የተጠማ ውሻ ከመንገድ
አገኘች ውኃን ሊጠጣ ቢፈልግ ሌሎች ሰዎች በቅንንት ውኃ መስጠት ሲገባቸው ሲያባርሩት ተመለከተች

እርሷ ግን ቅን ልቡና ያላት ናትና ካያዘችው ማድጋ (እንስራ) በወርቅ ጫማዋ ውኃ አድራበት ውኃ
እንዲጠጣ አደረገችው፡፡
ጥያቄ፦ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
መልስ፦ እኛም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምንማረው ትልቁ ነገር በቅንነት መኖር ቅን
ነገርን ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት መፈፀም እንዳለብን ነው፡፡
ጥያቄ፦ ሌላ የቅን ሰው ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ሌላው የቅንነትን ታላቅነት የምንማርበት ታሪክ የአባታችን የአባ አጋቶን ታሪክ ነው፡፡ አባታችን
ከቅንነታቸው የተነሣ በረከትን አግኝተዋል፡፡ ታሪካቸውም በአንድ ገዳም ውስጥ ሰሌን እየሰፉ የሚሸጡ
አባት ነበሩ፡፡ ሰሌኑን ሸጠው በገዳሙ ውስጥ ለሚኖሩ መነኮሳት ነው ምግብ የሚገዙበት ይሄ ትልቅ
ቅንነት ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሰሌኑን ሊሸጡ ከገዳሙ እንደወጡ አንድ የኔ ቢጤ ሰው ‹‹አባቴ ወዴት
ነው የምትሄደው?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ‹‹ገበያ ነው የምሄደው›› አሉት የኔ ቢጤውም ‹‹ገበያ የምትሄደው
ለምንድን ነው?›. አላቸው፡፡ መነኩሴው ‹‹ይህንን ሰሌን ልሸጥ›› አሉት የኔቢጤውም ‹‹እኔም ገበያ መሄድ
እፈልጋለሁ ግን መራመድ ስለማልችል አዝለኸኝ ገበያ ውሰደኝ›› ሲላቸው እሺ ብለው አዝለውት ገበያ
ወሰዱት ገበያ ከደረሱ በኋላም ሰሌኑን ሲሸጡ የኔ ብጤው ‹‹ሰሌን ሸጥክ?›› ሲላቸው ‹‹አዎ›› አሉት፡፡
‹‹በስንት ብር ሸጥክ?›› ሲላቸው ‹‹በዚህን ያህል ብር ሸጥኩት›› ሲሉት የኔቢጤው ‹‹ዳቦ ግዛልኝ?
ርቦኛል›› አላቸው እርሳቸውም ቅንነት ስላላቸው ሳያንጎራጉሩ ለኔብጤው ዳቦ ገዝተው ሰጡት፡፡ ሁሉንም
ሰሌን ሸጠው ዳቦ ግዛልኝ ሲላቸው እየገዙለት መጨረሻ ላይ ሰሌኑን ሸጠው ከጨረሱ በኋላ ምንም ብር
እጃቸው ላይ አልቀረም፡፡ ለኔብጤው ዳቦ ሲገዙለት አልቋል፡፡ የኔ ብጤውም ‹‹ዳቦ ግዛልኝ?›› ሲላቸው
‹‹ገንዘቡ አለቀበኝ›› አሉት እርሱም ‹‹አሁን ታዲያ ምን ልታደርግ ነው?›› ሲላቸው ‹‹አሁን ወደ በአቴ
ወደ ገዳሜ ልመለስ ነው›› አሉት የኔ ብጤውም ‹‹በቃ እኔንም አዝለኸኝ ውሰደኝና ጠዋት ካነሳኸኝ ቦታ
አድርሰኝ?›› አላቸው፡፡ እሳቸውም እሺ ብለውት አዝለውት ወደ ጠዋቱ ቦታ የገዳሙ በር ላይ ሲደርሱ
‹‹በል አሁን አውርደኝ ደርሻለሁ›› ሲላቸው እሺ ብለው አወረዱት ለካስ ያ የኔ ብጤ መስሎ የተገለጠው
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ነበር እና መርቋቸው ባርኳቸው ሄደ፡፡
ጥያቄ፦ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
መልስ፦ እኛም ለሌላው በጎ ስናደርግ ለእግዚአብሔር እንደምናደርግ አንጠራጠር፡፡ተማሪዎች ሁል ጊዜ
ቅን ሆነን የምንጓዝ ከሆነ አምላክችን እግዚአብሔር መልካም የምንለውን ነገር ለእኛ ይሰጠናል፡፡ ክፉንም
ነገር ያርቅልናል፡፡ “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” እንዲል መዝ
፹፬፥፲፩
ጥያቄ፦ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሦስተኛ መልካም ምግባር ምንድን ነው?
መልስ፦ ታዛዥነት

ጥያቄ፦ ታዛዥነት ምን ማለት ነው?

መልስ፦ እሺ ብሎ መልካሙን ቃል መቀበል ማለት ነው፡፡


ጥያቄ፦ የምንታዘዘው ለማን ነው?
መልስ፦ ፩ ለእግዚአብሔር
፪ ለወላጆቻችን
፫ ለመንፈሳዊ አባቶቻችን ነው፡፡
ጥያቄ፦ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፦ እርሱ እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪና አስገኝ አምላክ እንደመሆኑ ለእርሱ ቃል ሕግጋት ታዛዥና
ፈጻሚ መሆን ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ለእግዚአብሔር በመታዘዛችን ምን እናገኛለን?
መልስ፦ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ለእኛ በረከትን የሚያመጣ ለሀገርም ሰላም ይሰጣል
ጥያቄ፦ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ምን ያስከትላል?
መልስ፦ ለእርሡ አለመታዘዝ በራሳችንእና በሀገር ላይ መከራና ስቃይን ያመጣል፡፡
ጥያቄ፦ የታዛዥ ሰው ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በረከትን ካገኙ ሰዎች መካከል አበ ብዙሃን አብርሃም አንዱ ነው፡፡
እግዚአብሔር አብርሃም አብርሃም ከእናት ከአባትህ ከዘመዶችህ ሀገር ጣዖት ከሚመለክበት ፣ኃጢአት
ክፋት ከሚሰራበት ምድር ውጣ መልካም ሥራ ወደሚሰራበት ሀገር ሂድ ሲለው አብርሃምም እሺ ብሎ
በመታዘዝ ወደ ተባለው ሀገር ሄዷል፡፡
ጥያቄ፦ ከታሪኩ ምን እንማራለን?
መልስ፦ እንደ አብርሃም እግዚአብሔር ላዘዘን ትዕዛዝ ታማኝ ሆነን መፈጸም እንዳለብን ደእንማራለን፡፡
ጥያቄ፦ ለወላጅ መታዘዝ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፦ ከእግዚአብሔር በታች በመታዘዝ ሊያገለግሉአቸው የሚገቡ ወላጆች ናቸውና እነርሱን
በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ማገልገል ማለት ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ በአጽንኦት የሚናገረው
ነው፡፡ “ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ ይህ የሚገባ ነውና” ኤፌ ፮፥፩

ጥያቄ፦ ለወላጆቻችን መታዘዛችን ምንን ይገልጣል?


መልስ፦ ለወላጆቻችን በመታዘዝ ውስጥ ለእርሱ ያለንን ፍቅርና አክብሮት እንገልጣለን

ጥያቄ፦ ለወላጆቹ የማይታዘዝ ልጅ ምን ይሆናል?

መልስ፦ ለወላጆች የማይታዘዝ ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ፣ በሰዎችም ዘንድ መወደድ የሌለው ይሆናል፡፡
ጥያቄ፦ ለወላጆቹ የሚታዘዝ ልጅ ምን ያገኛል?
መልስ፦ ወላጆቹን የሚያከብር ለእነርሱም የሚታዘዝ ልጅ እግዚአብሔር እድሜን ይሰጠዋል፡፡
ጥያቄ፦ ማስረጃ ጥቅስ?
መልስ፦ “አባትና እናትህን አክብር እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር እድሜህ እንዲረዝም” ዘጸ ፳፥፲፪
ጥያቄ፦ ለወላጅ መታዘዝ እንዲገባ ምሳሌ የሚሆነን ማን ነው?
መልስ፦ ለወላጆች መታዘዝ እንዲገባ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቆመት
በጠባብ ደረት ተገልጦ በተመላለሰበት የልጅነቱ ወራት ለእናቱ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
እየታዘዘ በማገልገል አስተምሮናል፡፡

ጥያቄ፦ ለመንፈሳዊ አባቶች መታዘዝ ማለት ምን ማለት ነው?


መልስ፦ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሚያገለግሉ አካህናት አባቶች፣ ለወንድሞች ዲያቆናት፣ እንዲሁ
ቃለ እግዚአብሔር ለሚያስተምሩን መምህራን ቤተ ክርስቲያን መታዘዝ፣ ቃላቸውን መፈጸም ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ዮሐንስ ሐፂር የሚባል በአንድ ገዳም የሚኖር አንድ ጻድቅ ሰው ነበር፡፡ ምንኩስናን ለመቀበል
/ለመመንኮስ/ ወደ ገዳም ሄደ፡፡ ከመመንኮሱ በፊት ግን የገዳሙ አስተዳዳሪ አንድ ሥራ እንዲሠራ
ለዮሐንስ ነገረው ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ እርሱም ሥር የሌለው ወድቆ የኖረ ደረቅ እንጨት አስመጥቶ ‹‹በል
ይሄን ደረቅ እንጨት ተክለህ ውኃ አጠጥተህ ተንከባክበህ አሳድገህ ለፍሬ አድርሰው (ፍሬ እንዲያፈራ)
አድርግ›› አለው፡፡ ዮሐንስም ታዛዥ ነበርና ይሄ እኮ ደረቅ እንጨት ነው ሥር የለውም ከዚያ ላይ
ወድቆ የቆየ ነው ፍሬ ሊያፈራ አይችልም ስለዚህ አይሆንም አላለም እሺ ብሎ ደረቁን እንጨት ተክሎ
አፈር አስታቅፎት ውኃ ጧት እና ማታ እያጠጣው በሦስት ዓመት ያ የደረቀ እንጨት ሥር አውጥቶ
መሬት ይዞ ቅጠል አውጥቶ ለምልሞ አበባ አውጥቶ ፍሬ አፍርቷል፡፡ ከዚያ ይሄን የዮሐንስን ትህትና
ትዕግስት እና ታዛዥነት ያየ እና ያደነቀው የገዳሙ አለቃ “አንተ ታላቅ ታዛዥ ቅዱስ ሰው ነህ”
ምንኩስና ይገባሃል ብሎት አመንኩሶታል፡፡ ዮሐንስ ሐፂርም (አጭሩ ዮሐንስም) በዚያ ገዳም አለቃ
ሆኖ ድውያንን እፈወሰ በፆም እና በጸሎት ፀንቶ ብዙ ተዓምራት እያደረገ ኖሯል፡፡
ጥያቄ፦ ከታሪኩ ምን እንማራለን?
መልስ፦ ሰው ለመልካም ነገር ቢታዘዝ ትዕግስት ካለው ብዙ ድንቅ ነገሮችን ማድረግ ይችላል፡፡ የማርቆስ
ወንጌል ማር ፱:፳፫ ‹‹ለሚያምን ሁሉ ቻለዋል›› እንዲል
ጥያቄ፦ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ አራተኛ መልካም ምግባር ምንድን ነው?
መልስ፦ ላጠፉት ይቅርታ መጠየቅ እና ሰዎች ይቅር ሲሉን መቀበል ነው፡፡

ጥያቄ፦ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ፦ ይቅርታ መጠየቅ ማለት አንድን ሰው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመናገር በመስራት በድለነው
ተናግረነው አስቀይመነው ከሆነ ወንድሜ ይቅር በለኝ እኅቴ ይቅር በይኝ ይቅርታ አድርጊልኝ በድያለሁ
ብሎ ጥፋትን ማመን ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ይቅርታ ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፦ ይቅርታ ማድረግ ማለት የበደለን ያስቀየመን ሰው ወደኛ መጥቶ ማረኝ ወንድሜ ማሪኝ እኅቴ
ብሎ ይቅርታ ሲጠይቀን እኛ ደግሞ ችግር የለውም ይቅር ለእግዚአብሔር በመባባል ሰላም ማውረድ እና
ወደ ቀድሞ ፍቅር ወንድማማችነትና ታማኝነት መመለስ ነው፡፡
ጥያቄ፦ ይቅርታ መባባል እንዲገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
መልስ፦ ‹‹እርስ በርሳችሁ ትዕግስትን አድርጉ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር
ተባባሉ፡፡ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፡፡›› ቆላ ፫፥፲፫
ጥያቄ፦ ይቅርታ ስለመባባል የሚያስረዳ ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩ፡፡ ከእነርሱም ታናሹ አባቱን ‹‹አባቴ ሆይ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን
ክፍል ስጠኝ›› አለው አባትየውም ገንዘቡንም አካፈላቸው፡፡ ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን
ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ፡፡ ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች ሀገር
ጽኑ ርሀብ ሆነ እርሱም ይጨነቅ ጀመር፡፡ ሄዶም ከዚያች ሀገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ እርሱም
እሪያ እንዲያሰማራ ወደ ሜዳ ላከው፡፡ እሪያዎችም ከሚበሉት ምግብ ይበላና ይጠግብ ዘንድ ይመኝ
ነበር ነገር ግን የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ ‹፣እንጀራ የሚተርፋቸው
የአባቴ ባለሙያዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በርሀብ እጠፋለሁ ተነስቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁ
አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም ከሙያተኞችህ እንደ አንዱ
አድርገኝ እለዋለሁ›› አለ ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ፡፡ እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለትሮጦም
አንገቱን አቀፈውና ሳመው፡፡ ልጁም ‹‹አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልሁ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል
አይገባኝም›› አባቱ ግን በታላቅ ደስታ ሆኖ ባርያዎቹን አለ
የማጠቃልያ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ጥያቄዎች እውነት ወይም ሀሰት በማለት መልሱ

፩ መልካም ምግባራት የምንላቸው እግዚአብሔር አምላክን መውደዳችን ለእርሡም መገዛታችንን


የምንገልጽባቸው የክርስቲያኖች ሁሉ መገለጫ ነው፡፡
፪ ሰዎች የሰጡትን አደራ ጠብቆ መኖር የራስ ያልሆነን ነገር አለመንካት ታማኝነት ይባላል፡፡
፫ አንድ ክርስቲያን ለሠዎች ሊታዘዝ አይገባውም፡፡

ከሚከተሉት ጥያቄቆች መካከል ትክክለኛውን መልስ ምረጡ


፬ ክርስቲያን ታማኝ ሊሆን የሚገባው ለማን ነው?
ሀ. ለእግዚአብሔር ሐ. ለሰዎች
ለ. ለራስ መ. ሁሉም መልስ ነው

፭ በቅንነት ለሠዎች በመታዘዝ በረከትን ያገኘ አባት


ሀ. አባ አጋቶን ሐ. ይሁዳ
ለ. ማርታ መ. መልስ የለም

፮ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቁ መልካም ምግባራት ምን ምን ናቸው?


ሀ. ታዛዥነት ሐ. ቅንነት

ለ. ይቅርታ መጠየቅና መድረግ መ. ሁሉም መልስ ነው


ምዕራፍ ሁለት

ታታሪነት
የምዕራፉ ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምረው ካገባደዱ በኋላ
፩- በነገር ሁሉ ታታሪ ስለመሆንና እንዴት መሆን እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡
፪- ቤተሰብን በስራ ማገዝ እንደሚገባቸው ይረረዳሉ በማገዝም ያገለግላሉ፡፡
፫- በአለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ትምህርታቸው እንዴት ውጤታማ መሆን
እንዳለባቸው ይረዳሉ፡፡
፬- መጻሕፍትን የማንበብ ልማድ ሊኖራቸው እንዲገባ በማወቅ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡
፭- ጊዜያቸውን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡

በቃል የሚጠና ጥቅስ

‹‹ልጆች ሆይ በጌታ ደስ የሚያሰኘው ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ›› (ቆላ፫፥፳)

(የመክፈቻ ጥያቄዎች)

.፩ ልጆች መጽሐፍ ታነባላችሁ? መልሳችሁ አዎ ከሆነ ምን አይነት መጽሐፍ


ታነባላችሁ?
፪ ልጆች ቤተሰቦቻችሁን በምን መንገድ ታግዛላችሁ? ለመምህራችሁ ተናገሩ?
ታታሪነት
ጥያቄ፦ ልጆች ታታሪነት ማለት ምን ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፦ታታሪነት ወይም ትጋት ስንል ለተሰጠን ኃላፊነት ወይም ሥራ በቁርጠኝነት የተሰጠንን ለመፈጸም
አላማችንንም ለማሳካት የምንሄድበት ወጥነት ያለው መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያኖች በኑሮአቸው ሁሉ
ትጉህና ታታሪ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ጥያቄ፦ ልጆች ትጉህ መሆን ያለብን በምን በምንድን ነው?
መልስ፦ አንደኛ ቤተሰቦቻችንን በስራ ለማገዝ
ጥያቄ፦ ቤተሰብ ማለት ምን ማለት ነው?
መልስ፦ ቤተሰብ ማለት በአንድ ቤት ውስጥ አባት እናት ወንድምና እህት ሌሎችም ዘመዶች የሚገኙበት
የዘመድ ስብስብ ነው፡፡
ጥያቄ፦ ለወላጅ መታዘዝ እንዲገባ ማን አዘዘን?
መልስ፦ እግዚአብሔር ‹‹ልጆች ሆይ በጌታ ደስ የሚያሰኘው ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ››
(ቆላ፫፥፳)
ጥያቄ፦ ቤተሰብን እንዴት በሥራ እናግዝ?
መልስ፦ ያለ መሰልቸት በፍጹም ትጋት
ጥያቄ፦ ለወላጆቻቸው በትጋት የታዘዙ ልጆች ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ይስሐቅ አባቱ አብርሃም እናቱ ደግሞ ሳራ ትባላለች፡፡ እናትና አባቱ ለብዙ አመታት በጋብቻ
አብረው ሲኖሩ ልጅ አልነበራቸውም ነበር፡፡ ይህን ጉድለታቸውን የሚያውቅ እግዚአብሔር ስለ
እምነታቸው ጽናት ልጅን እንደሚወልዱ ቃል ገባላቸው፡፡ እነርሱም በትዕግስት የእግዚአብሔርን
ቃል ጠብቀው ይስሐቅን በእስተ እርጅናቸው ወለዱ፡፡ ይስሐቅ ማለት ይስቃል ማለት ሲሆን በእናቱ
በሳራ በእግዚአብሔር ፊት በመሳቋ ምክንያት የተሰጠው ስም ነው፡፡ ይስሐቅ በጥበብና በሞገስ እያደገ
ለእናት ለአባቱ እየታዘዘ እነርሱንም እያከበረና እያገለገለ ያድግ ነበር፡፡ ለአባቱ ለአብርሃም ለአምላኩ
ለእግዚአብሔር የተናገረውን ቃል በማጠፍ እንዳይበድል ራሱን እስከ መስዋዕት ድረስ በማድረስ ታዛዥ
ሆኖአል፡፡
ጥያቄ፦ ሌላ ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ሌላው ቤተሰብን በሥራ ማገዝ እንዲገባ አብነት የሆነን የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነ የሰው
ልጆችን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ለእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም በሚያስፈልገው ሁሉ ውኃን እየቀዳ እንጨትን
እየለቀመ ይራዳትና ያግዛት ነበር፡፡ ይህም ለእኛ አብነት ይሆን ዘንድ ነው፡፡

ጥያቄ፦ ከታሪኮቹ ምን እንማራለን?


መልስ፦ እንደነ ይስሐቅ በታታሪነት ለወላጆቻችን በመታዘዝ እግዚአብሔርን እና ወላጆቻችንን ልናስደስት
እንዲገባ ያስተምረናል፡፡
ጥያቄ፦ ልጆች ሌላው ትጉህ መሆን ያለብን በምንድን ነው?
መልስ፦ በትምህርት ውጤታማ በመሆን፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በሁሉ መስክ ውጤታማ ሊሆኑ ይገባል፡፡
አስኳላ ብለን በምንጠራው በዓለማዊው ትምህርታችን በአግባቡ በመማርና በማጥናት ውጤታማ
ልንሆን ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ ውጤታማ መሆን እንዴት ይገኛል?
መልስ፦ ተግቶ በመማርና በማጥናት ነው፡፡
ጥያቄ፦ ሥራችንን ሁሉ በጸሎት በመጀመር፡ ልጆች መንፈሳዊ ሰው ሥራውን ሁሉ በጸሎት ጀምሮ
በጸሎት ይፈጽማል፡፡
ጥያቄ፦ ይህንንም የሚያደርገው ለምንድን ነው?
መልስ፦ ያለ እግዚአብሔር በራሳችን ምንም ማድረግ ስለማንችል ነው፡፡ አምላካችን ‹‹ያለ እኔ ምንም
ማድረግ አይቻላችሁም›› እንዳለን እግዚአብሔር እንዲረዳን የተሰወረውንም ምስጢር እንዲገልጽልን
ቅዱስ ስሙን ዘወትር እየጠራን ልንለምነው ይገባል፡፡ (ዮሐ ፲፭፥፭)
ጥያቄ፦ ውጤታማ መሆን እንዴት ይገኛል?
መልስ፦ የጥናት ጌዜ በማበጀት በአግባቡ ማጥናት፡፡ ልጆች ሌላኛው በትምህርታችን ውጤታማ እንድንሆን
አጋዥ የሚሆነን መንገድ በትምህርት ቤት መምህራኖቻችን ሲያስተምሩ በአግባቡ መማርና መከታተል
እንዳለብን ሁሉ ለራሳችን ደግሞ የተማርነውን ደግመን የምናነብበት የራሳችን ግዜ በማበጀት የምናጠና
ከሆነ በትምህርታችን ውጤታማ እንሆናለን፡፡
ጥያቄ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ለትምህርትና ለጥናት የተመቸ ግዜ የቱ ነው?
መልስ፦ የሌሊቱ ጌዜ ነው፡፡ ለምን ካላችሁ ሰው ሁሉ የሚተኛበት ጸጥታ የሰፈነበት ግዜ ስለሆነ በዚህ
ጌዜ ብናነብ ብንማርበት ስለሚገባን እጅግ ተመራጭ ነው፡፡
ልጆች በትምህርቱ ውጤታማ የሆነ ታታሪ ልጅ ቤተሰቦቹንና መምህራኖቹን ያስደስታል፡፡ ቤተሰቦቹን
የሚያስደስት ልጅ ደግሞ እግዚአብሔር ይወደዋል፡፡ በተጨማሪ በትምህርቱ ውጤታማ የሆነ ልጅ
ለቤተ ክርስቲያን ማድረግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማድረግ ይችላል፡፡
ጥያቄ፦ ልጆች ሌላ ትጉህ መሆን ያለብን በምንድን ነው?
መልስ፦ መጻሕፍት አንባቢ በመሆን
ጥያቄ፦ መጻሕፍት ምንድን ናቸው?
መልስ፦ ልጆች መጻሕፍት ለሰው ልጅ መንፈሳዊም ሆነ አለማዊ እውቀት የሚሰጡ ናቸው፡፡
ጥያቄ፦ መጻሕፍትን እንዴት ማንበብ ይገባል?
መልስ፦ መጻሕፍትን በእድሜያችንና ጠቃሚነታቸውን ቤተሰብ እየጠየቅን ልናነብና ልንጠቀምባቸው
ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ መጻሕፍትን አንባቢ ልጅ ምን ይሆናል?
መልስ፦ አንባቢ ልጅ ከመጻሕፍት በሚያገኘው እውቀት ራሱን ጠቅሞ ቤተሰቡን የሚያኮራ ሀገሩንም
የሚጠቅም ይሆናል፡፡
ጥያቄ፦ መጻሕፍትን የማያነብ ልጅ ምን ይሆናል?
መልስ፦ መጻሕፍትን የሚያነብ ልጅ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲሁም ሀገሩን ሊጠቅም አይችልም ይያቄ፦
የንባብ ልምድን እንዴት ማዳበር እንችላለን?
መልስ፦ የመጀመርያው ለንባብ ጊዜና ቦታ በማዘጋጀት፡፡ ይህም መጻሕፍት ከማንበባችን አስቀድሞ
የምናነብበት የራሳችን የሆነ ቦታና ሰዓት መምረጥ ይኖርብናል፡፡ ይኸውም ቤተሰቦቻችንን በስራ ካገዝን
ከትምህርታችንም በኋላ በሚኖረን ግዜ ሊሆን ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ አንባቢነቱ የሚታወቅ ሰው ማን ይባላል?
መልስ፦ ኢትዮጲያዊው ጃንደረባ ወይም ባኮስ፡፡ ባኮስ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሰግድ ሄዶ በሰረገላው ላይ ሳለ
እንኳን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ አንብቦም ከመጽሐፉ ያልገባውን ፊሊጶስ በሚገባ አስረድቶት
አጥምቆታል፡፡(ሐዋ ፰፥፳፯-፴፪) ልጆች ከኢትዮጲያዊው ጃንደረባ የምንማረው ትልቁ ነገር ምንም እንኳ
ትልቅ መአረግ ላይ ቢሆንም ቦታው ሳይገድበው መጽሐፍ ማንበቡ እንዲሁ ያነበበውን እንዲገባውና
እንዲያስተውለው መምህር የሆነውን ፊሊጶስን መጠየቁ ነው፡፡ እኛም እንደ እርሱ አንባቢዎች ያልገባንንም
የምንጠይቅ ጠያቂዎች ልንሆን ይገባል፡፡
ጥያቄ፦ ልጆች ሌላው ትጉህ መሆን ያለብን በምንድን ነው?
መልስ፦ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም
ጥያቄ፦ ልጆች ጊዜ ምንድ ነው?
መልስ፦ ጊዜ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ትልቅ ስጦታ ነው፡፡

ጥያቄ፦ እግዚአብሔር ጊዜን የሰጠን ለምንድን ነው?


መልስ፦ በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ እንጠቀምበት ዘንድ ሥራ እንድንሰራበት ነው፡፡
ጥያቄ፦ በጊዜው ያልተጠቀመ ልጅ ምን ያጋጥመዋል?
መልስ፦ በተሰጠው ጊዜ መልካም ነገሮችን ከመስራት ይልቅ በአልባሌ ነገሮች ማለትም በዋዛ በፈዛዛ፣
በጨዋታ የሚያሳልፍ ልጅ ጊዜውን አልተጠቀመምና ይጎዳል ማግኘት ያለበትንም ነገር ሳያገኝ ይቀራል፡፡
ጥያቄ፦ በጊዜው ያተጠቀመ ልጅ ምን ያገኛል?
መልስ፦ በጊዜው ደግሞ መልካም ነገርን የሠራ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲሁ ሀገሩን የሚጠቅም ይሆናል፡፡
ጥያቄ፦ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን ትልቅ ትምህርት የሚሆነን አንድ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ
ንገረን?
መልስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሽራ የተባለ ክርስቶስን ሊቀበሉ መብራታቸውን ይዘው የወጡ አሥር
ቆነጃጅት ነበሩ፡፡ ከእነዚህም አምስቱ ሰነፎች ሲሆኑ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ በተሰጣቸው
ጊዜ ሳይጠቀሙ ቀርተው መብራታቸውን ይዘው መብራቱን ረጅም ሰዓት እንዲበራ የሚያደርገውን ዘይት
አልያዙም ነበር፡፡ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር ቨበማሰሮዋቸው ዘይትን ያዙ፡፡ ሙሽራውም በዘገየ
ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ፡፡ እኩለ ሌሊትም ሲሆን ‹‹እነሆ ሙሽራው ይመጣል
ትቀበሉት ዘንድ ውጡ›› የሚል ሁካታ ሆነ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን
አዘጋጁ ሰነፎቹ ልባሞቹን ‹‹መብራታችን ሊጠፋብን ነው ከዘይታችሁ ስጡን›› አሏቸው፡፡ ልባሞቹ ግን
‹‹ምናልባት ለእኛና ለእናነተ ባይበቃስ ይልቅስ ወደ ሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ›› አሏቸው፡፡
ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፡፡ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሠርግ ገቡደጁም ተዘጋ፡
፡ በኋላም ደግሞ ጊዜያቸውን በአግባቡ ያልተጠቀሙት አምስቱ ሰነፎች መጡና ‹‹ጌታ ሆይ ክፈትልን››
አሉ እርሱ ግን መልሶ ‹‹እውነት እላቹኃለሁ አላውቃችሁም›› አላቸው፡፡ (ማቴ ፳፭፥፩-፲፪)
ጥያቄ፦ ከቃሉ ምን እንማራለን?
መልስ፦ በተሰጠው ጊዜ ተግቶ የሚሰራ መልካም ነገርን የሚያደርግ ለክብር እንደሚበቃ፡፡

የማጠቃልያ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ጥያቄዎች እውነት ወይም ሀሰት በማለት መልሱ


፩ ከሚከተሉት ቤተሰቡን በታታሪነት የታዘዘ ማን ነው?
ሀ/ቃየል ሐ/ይስሐቅ
ለ/ አቤል መ/መልስ የለም

፪ በትምህርታችን ውጤታማ እንድንሆን ማድረግ ያለብን ነገር ምንድን ነው?


ሀ/ስራችንን ሁሉ በጸሎት መጀመር ሐ/ ሀእናለ መልስ ናቸው፡፡
ለ/ለጥናት ጊዜ ማበጀት መ/ መልስ የለም

፫ በመጽሐፍ ቅዱስ በአንባቢነቱ የሚታወቅ ኢትዮጲያዊ ሰው ማን ይባላል?


ሀ/ አቤሚሊክ ሐ/ ሙሴ
ለ/ ባኮስ መ/ መልስ የለም

ምዕራፍ ሦስት

ትዕግሥት
የምዕራፉ ዓላማ
ተማሪዎች ይህን ትህርት ተምረው ባገባደዱ ጊዜ
፩ የትዕግሥትን ምንነት ይረዳሉ፡፡
፪ በመታገሥ የሚገኘውን ጥቅም በማወቅ ለመተግበር ይለማመዳሉ፡፡
፫ ባለመታገሥ ጠንቅ የሚመጣውን ጉዳት ያውቃሉ ይጠነቀቃሉ፡፡
(የመክፈቻ ጥያቄዎች)
፩ ልጆች ትዕግሥት ማለት ምን ማለት ነው? የምታውቁትን ለመምህራችሁ
ተናገሩ?
፪ ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ በመታገሣቸው ብዛት የተጠቀሙ ሰዎችን ለመምህራችሁ
ተናገሩ?

በቃል የሚጠና ጥቅስ


‹‹ በመታገሣችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ››(ሉቃ፳፩፥፲፱)

ትዕግሥት
ጥያቄ፦ ትዕግሥት ምንድን ነው?

መልስ፦ ፩ ትዕግሥት መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ሊያደርጋቸው ከሚገቡ የመንፈስ
ፍራ ብሎ ከጠቀሳቸው መልካም ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ (ገላ ፭፥፳፪)
፪ ትዕግሥት መከራን ወይንም ችግርን እንዲሁ የትኛውንም የሚገጥመን ውጣ ውረድ ያለ
ምንም መሰላቸትና ብስጭት መቀበል መቻል
፫ ትዕግሥት መልካም ልመናችንን የምንቀበልባት ታላቅ ሥጦታችን ናት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ
ጻድቁ አባታችን አብርሃም ከእግዚአብሔር ዘንድ ‹‹ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት
አበዛልሃለሁ›› ተብሎ የተነገረውን የተስፋውን ቃል ምኞቱ የተፈጸመለት ሃያ አምስት ዓመታት ጠብቆ
በመቶ አመቱ ይስሐቅን በመውለድ ነው፡፡ ይህም የሆነለት ትዕግሥትን በማብዛቱ ነው፡፡
ጥያቄ፦ የትዕግሥት ጥቅም ምንድን ነው?
መልስ፦ ዋነኛውና መሠረታዊው ነገር የነፍስ ድኽነት ነው፡፡ ትዕግሥተኛ ሰው ትዕግስቱ ነፍስና ሥጋውን
ያድናል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹በመታገሳችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ›› ሲል ይነግረናል፡፡
(ሉቃ፳፩፥፲፱)
ጥያቄ፦ ለዚህ አብነት የሚሆነን ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ አብነት የሚሆነን ታሪክ ታላቁ አባታችን ኢዮብ ነው፡፡ ኢዮብ ላይ ሰይጣን ቀንቶበት በእግዚአብሔር
ፈቃድ በልጆቹ፣ በሀብት በንብረቱ፣ እንዲሁ በገዛ ሰውነቱ ላይ እያፈራረቀ ፈተና ቢያመጣበት እርሱ
ግን የሚስቱን ምክር ሰምቶ አምላኩን ከመስደብ ይልቅ ትዕግሥትን አበዛ እንጂ ለአንዲት ቀንም
የምሬት ቃልን አልተናገረም፡፡ እግዚአብሔር ደግ አምላክ ነውና ለኢዮብ ከፊተኛው ይልቅ በኋለኛው
በታላቅ በረከት ጎበኘው ይህም በረከት እጥፍ ድርብ ሆነለት፡፡ ይህን ሁሉ ያገኘው ግን በመታገሱ ነው፡፡

ጥያቄ፦ ያለመታገሥ ጉዳት ምንድን ነው?

መልስ፦ ባለመታገሳቸው ጠንቅ በራሳቸው እና በሌሎች ላይ ጉዳትን ያመጡብዙ ሰዎች አሉ፡፡


ከጉዳቶቹም መካከል ያለመታገስ እንደ ኤሳው ብኩርናን ያሳጣል፡፡ ታሪኩም በመጽሐፍ ቅዱስ
ተመዝግቦ እንደምናገኘው የያዕቆብ ወንድም ኤሳው ብኩርናውን የማጣቱ ምክንያት መብልን መውደዱ
ነው፡፡ ይኸውም እናቱ ርብቃን ጠብቆ መመገብ እየተቻለው ተዕግሥት ከማጣጡ የተነሳ ለሚጠፋው
መብል ሲል ብኩርናውን ሸጠ (አጣ)፡፡ ኤሳው ዳግመኛ የማያገኛትን ብኩርናወን በክብር አልያዛትምና
ተወሰደችበት፡፡ (ዘፍ ፳፭)

ጥያቄ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ የትዕግሥት ምሳሌ እነማን ናቸው?


መልስ፦ የእግዚአብሔር ትዕግሥት፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ ነው እንደ እርሱ ትዕግሥት ባይሆን
የሰው ልጅ ሁሉ በኃጢአቱ ምክንያት በጠፋ አኗኗሩም ባልታወቀ ነበር፡፡
ጥያቄ የእግዚአብሔር ትዕግሥት ከምን የተነሳ ነው?
መልስ፦ ከምህረቱና ከርህራሄው የተነሳ ነው፡፡ ይህንንም መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ሲናገር
‹‹እግዚአብሔር መኃሪና ይቅር ባይ ነው ከቁጣ የራቀ የራቀ ምህረቱም የበዛ›› ሲል ገልጾታል፡፡ (መዝ
፻፫፥፫)
ጥያቄ፦ የእግዚአብሔር ትዕግሥት ይበልጥ የሚገለጠውና የተገለጠው በማን ላይ ነው?
መልስ፦ በኃጢአተኞች ላይ ነው፡፡ አሕዛብ ከጣዖት አምልኮ ተመልሰው ንስሐ እስኪገቡ፣ የነነዌ ሰዎችን
ራሳቸውን በእርሱ ፊት ትሁት እስኪያደርጉ ድረስ በትዕግሥት ጠብቋል፡፡ እንዲሁ የፈርዖንን ጭካኔ
በማየት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከመቅጣት ይልቅ ሊመለስ የሚችልበት አስር መቅሰፍቶች በእርሱ
ላይ በመማምጣት እግዚአብሔር ፈርኦንን እጅግ ታገሶት ነበር፡፡ በእያንዳንዱም መቅሰፍት ፈርዖን
በደልኩ በማለት የተመለሰ ቢመስልም ዳግመኛ ግን ቢበድልም እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቀው
ነበር፡፡ (ዘጸ ፳፯፥፲)
ጥያቄ፦ ሎላኛው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ የትዕግሥት ምሳሌ ማን ነው?
መልስ፦ የነቢዩ ኤልያስ ትዕግሥት፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥተኛና መሐሪ እንደመሆኑ ልጆቹ ደግሞ
ታጋሽ እንዲሆኑ ያስተምራል ያሰለጥናቸዋልም፡፡ ኤልያስ ለሦስት ዓመት ተኩል ርሃብ በኋላ ዝናብ
እንዲዘንብ ለጠየቀው ጥያቄ እግዚአብሔር ሰምቶታል፡፡ ነገር ግን ነብዩ ኤልያስ ይህ እንዲሆን አንድ ግዜ
ሳይሆን ለስድስት ጊዜያትም እንኳን ዝናብን አላዘንብም እስከሚል ድረስ ጸልዮአልተስፋም ሳይቆርጥ
በትግሥት ጸንቶ ነበር፡፡ በሰባተኛውም ግዜ የሰው ልጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባህር ወጣች ስለዚህ

ኤልያስ እግዚአብሔር ለጸሎቱ መልስ እንደሰጠው አወቀ፡፡ ፩ነገ ፲፰፥፵፬

ማጠቃለያ ጥያቄዎች

በተማራችሁት መሠረት ትክክለኛውን መልስ ምረጡ


፩ በትዕግሥቱ ብዛት በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቅ ሰው ማን ነው?
ሀ/ኤሳው ሐ/ አቤል
ለ/ኢዮብ መ/ መልስ የለም

፪ ባለመታገሣቸው ጠንቅ ከተጎዱ ሰዎች መካከል አንዱ ማን ነው?


ሀ/ ያዕቆብ ሐ/ ኡሳው
ለ/ አብርሃም መ/መልስ የለም

፫ ‹‹…………………. መሐሪና ይቅር ባይ ነው ከቁጣ የራቀ ምህረቱ የበዛ ነው?


ሀ/ዳንኤል ሐ/ ቅዱስ ጴጥሮስ
ለ/እግዚአብሔር መ/ መልስ የለም

፬ ……………………. በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱትና የመንፈስ ፍሬ ከተባሉት መልካም ምግባራት


መካከል አንዱ ነው?
ሀ/ ትዕግሥት ሐ/ ምዕዋት
ለ/ ቁጣ መ/ለእና ሐ/መልስ ናቸው

ምዕራፍ አራት
ጾም
የምዕራፉ ዓላማ
ተማሪዎች ይህን ትህርት ተምረው ባገባደዱ ጊዜ
፩ የጾም ምንነትን እንዲሁ ተገቢነትን በሚገባ ይረዳሉ፡፡
፪ እንዴት መጾም እንዳለባቸው በሚገባ ይረዳሉ፡፡
፫ በጾም ስለሚያገኙት ጥቅም አውቀው ይጾማሉ፡፡

(የመክፈቻ ጥያቄዎች)
፩ ስለ ጾም የምታውቁትን ተናገሩ?
፪ በጾም ከማናገኛቸው ጥቅሞች መካከል የምታውቁትን ተናገሩ?

በቃል የሚጠና ጥቅስ

“ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ ሥጋዬም ቅቤን በማጣት ከሳ” መዝ ፻፬፥፳፩

ጾም

ጥያቄ፦ ልጆች ጾም ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ፦ ጾም ማለት ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት ውኃም ከመጠጣት መከልከል ከጥሉላት (ከፆም)
ምግቦች መከልከል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ጾም ማለት ራስን መግዛት ፣ ሥጋዊ ስሜትን ማሸነፍ
ለሥጋ ፍላጎት በመከልከል ለነፍስ ፍላጎት እንድትገዛ ማድረግ ነው፡፡

ጥያቄ፦ ልጆች ጾም ምንድን ነው?

መልስ፦ በአዳምና በሔዋን በኩል የጠቀበልነው የመጀመሪያ ትዕዛዝ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ
የሰውን ልጅ ከፈጠረ በኋላ በኤዶም ገነት እንዲኖሩ አደረጋቸው ለዛም ሦስት እፅዋትን ሠጥቷቸው
የነበረ ሲሆን አንደኛው እንዲበሉ የተሰጣቸው ሁለተኛው ብሉም አትብሉም ያልተባሉት እንዲሁም
ሦስተኛ ደረጃ እንዳይበሉ የጠነገራቸው እፀ በለስ ነበረች እግዚአብሔር እፀ በለስን እንዳይበሉ ስለምን
ከለከላቸው (አዘዛቸው) ከተባለ ፆምን መተው መከልከልን ሲያስተምራቸው ነው፡፡
ጥያቄ፦ የጾም ጥቅም ምንድን ነው?
መልስ፦ በነፍስና በሥጋ ድኅነትን እናገኛለን፡፡
ጥያቄ፦ በፆም ድኅነተ ሥጋን ካገኙ ሰዎች መካከል ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ ተጠቅሶ የምናገኛት አስቴር አንዷ ናት፡፡ አስቴር በወገኖቿ ላይ
የተላለፈውን የሞት ፍርድ ይሻር ዘንድ ያደረገችው ትልቅ ነገር ሁሉም ወገኖችዋ እንዲፆሙና እንዲጸልዩ
ነበር፡፡ በዚህም ፆም ምክንያት በወገኖቿ ላይ የተላለፈው የሞት ውሳኔ ወደ ሕይወት እንዲቀየር
አድርጓል፡፡ (መ.አስ ፬፥፲)
ጥያቄ፦ በፆም ድኅነተ ነፍስ ካገኙ ሰዎች መካከል ታሪክ ብትነግረን?
መልስ፦ ሌላው በፆም ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ካገኙ ሕዝች መካከል የነነዌ ሕዝቦች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እግዚአብሔር ሊያመጣባቸው ካለው መከራ በፍፁም መፀፀት በንስሐ፣ በመፆም፣ በመጸለይ ከመቅሰፍት
ድነዋል፡፡ (ት.ዮናስ ፫)

ጥያቄ፦ የጾም ሌላኛው ጥቅም ምንድን ነው?

መልስ፦ ራሳችንን እንድንገዛ (ከክፉ ነገር እንድንጠብቅ) ያደርገናል፡፡ ጾም በኑሮአችን ወደ ክፉ ሥራ


ወደ ኃጢአት እንዳንጓዝ መጠበቂያ ሆና ያገገለገለች የማይፆም ሠው ራሱን ከክፉ ሥራዎች መከላከል
ይከብደዋልና ይወድቃል በተቃራኒው ሰውነቱን ጾም ያስለመደ ክርስቲያን በሚያደርጋቸው ሥራዎች
ሁሉ ቁጥብና ጥንቁቅ ስለሚሆ ከኃጢአት፣ አእምሮውን ከክፉ ሐሳብ ዘወትር ሲጠብቅ ይኖራል፡፡
ጥያቄ፦ የጾም ሌላኛው ጥቅም ምንድን ነው?
መልስ፦ ምስጢር ይገለጥልናል፡፡ በፆም ራሱን ያስለመደ ዘወትርም የሚተጋ ሰው በሰዎች ዘንድ
የተሰወረ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ የሚገልጠው ምስጢር ይገለጽለታል፡፡ ለዚህም ምሳሌ የምናደርገው
ነቢዩ ዳንኤል ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ምግብን በመተው በመፆምና በጸሎት ኃይል ምስጢር እንደተገለጠለት
ራሱ በትንቢቱ መጽሐፍ ላይ አስፍሮት ይገኛል፡፡ (ት.ዳን ፲፥፪-፬)
ጥያቄ፦ እንዴት እንጹም?
መልስ፦ አንደኛ ንስሐ በመግባት፡፡ በሰሩት በደከል በማዘን በፍፁም ከክፉ ሥራችን ወደ እግዚአብሔር
በመመለስ ራስን ለካህን በማሳየት በፍፁም ንስሐ ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላክን ንስሐ ገብተን
በጾም በጸሎት ማረን ይቅር በለን ብለን ብንጠይቀው ሊምረን የጎደለንን ነገር ሊሞላ የታመነ አምላክነ ነው፡፡
ሁለተኛ መልካም ምግባራትን በመሥራት፡፡ፆምና ጸሎታችን ፍፁም ተቀባይነት የሙኖረው አብሮ
መልካም ምግባራትን መፈፀም ስንችል ነው፡፡
ጥያቄ፦ እነዚህ መልካም ምግባራት የምንላቸው እነማን ናቸው?
መልስ፦ ስግደት፣ ምፅዋት፣ ናቸው፡፡ እነዚህ ከፆምና ከጸሎት ጋር በአንድን የሚሄዱ ናቸው፡፡ (ማቴ
፮) እየጾምን የተራቡትን ማብላት፣ የታረዙትን ማልበስ ከሁሉም ክርስቲያን የሚገባ መልካም ምግባር ነው፡፡
ጥያቄ፦ ጾም በስንት ይከፈላል?
መልስ፦ በሁለት የፈቃድ ጾም እና የአዋጅ አጽዋማት
ጥያቄ፦ የአዋጅ አጽዋማት እነማን ናቸው?
መልስ፦ ፩ ጾመ ድኅነት /ረቡዕና ዓርብ/
፪ ጾመ ገሀድ
፫. ጾመ ፍልሰታ
፬. ጾመ ነነዌ
፭. ጾመ ሐዋርያት
፮. ጾመ ነቢያት
፯. ዓቢይ ጾም ናቸው፡፡

ማጠቃለያ ጥያቄዎች
በተማራችሁት መሠረት ትክክለኛውን መልስ ምረጡ

፩ በፆም ድኅነተ ሥጋ እንደሚገኝ ማስረጃ ከምናደርጋቸው መካከል


ሀ. ሩትና ህዝቦቿ ሐ. ኑኃሚንና ህዝቦቿ
ለ. አስቴርና ህዝቦቿ መ.ሁሉም መልስ ነው፡፡

፪ ክርስቲያን እንዴት ሊፆም ይገባዋል


ሀ. ንስሐ በመግባት ሐ. ሀ እናለ መልስ ነው
ለ. መልካም ምግባራትን በመሥራት መ. መልስ የለም

፫ ፆም ለክርስቲያኖች ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል


ሀ. ምሥጢር ይገለጥላቸዋል ሐ. ለነፍስና ለሥጋ ድኅነትን እናገኝበታለን
ለ. ከክፉ ነገር እንድንጠበቅ ያደርገናል መ. ሁሉም መልስ ነው፡፡

ምዕራፍ አምስት
ጸሎት
የምዕራፉ ዓላማ
ተማሪዎች ይህን ምዕራፍ ተምረወስ ሲጨርሱ
፩ ስለ ጸሎት ምንነት ይረዳሉ፡፡
፪ ጸሎት በማድረግ የሚያገኙትን ጥቅሞች ያውቃሉ፡፡
፫ እንዴትና ስለምን መጸለይ እንዳለባቸው ይለያሉ እነርሱም ጸሎትን የሚያረጉ
ይሆናሉ፡፡

(የመክፈቻ ጥያቄዎች)
፩ ልጆች እስቲ በጸሎታችሁ ስለ ምን እንደምትጸልዩ ለመምህራቹ ተናገሩ ?

በቃል የሚጠና ጥቅስ

“አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” ማቴ ፳፩፥፳፪


ጸሎት

ጥያቄ፦ ጸሎት ማለት ምን ማለት ነው?


መልስ፦ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡
“ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገርባት ነገር ናት” (ፍ.ነገ አንቀጽ ፲፬)

ጥያቄ፦ ጸሎት ምንድን ነው?

መልስ፦ ፩. ከሰማያዊ ንጉሥ ፊት ቀርበን የምንቆምበት ከእርሱም ጋር የምንነጋገርበት መንፈሳዊ


ድልድይ ነው፡፡ “በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዛሬ በእርሡ እገለጣለሁ፡
፡” ፩ኛ ነገ ፲፰፥፲፭
፪. ጸሎት እግዚአብሔር ሕይወት እንዲመራ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡
“እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሡ ላይ ጣሉት” እንዲል በሕይወታችን
ከባድ መስለው የሚታዩንን ነገሮች ሁሉ ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠትና የእርሱን አምላካዊ እይታና
ጥበቃ ከልብ መሻትና መጠየቅ ነው፡፡ ፩ጴጥ ፭፥፯
ጥያቄ፦ የጸሎት ጥቅም ምንድን ነው?
መልስ፦ ፩. ምስጢር ይገልፅልናል፡፡ ጸሎትን የሚያዘወትር ሰው ሁልጊዜ ንግግሩ ከእግዚአብሔር ጋር
ነውና እግዚአብሔር ረቂቅና ሽሽግ የሆኑ የማይታዩ ምስጢሮችን ይገልፅለታል፡፡ ከጸሎት ሕይወት የራቀ
ሰው ግን ምስጢራት ይሰወሩባታል አይገለጡለትም ምክንያቱም ምስጢርን ከሚገልጥ ከእግዚአብሔር
ጋር በጸሎት መነጋገርን ትቷልና በዚህም ምንም ነገር ማድረግ አይቻላቸውም መጽሐፍ “ያለ እኔ
ምንም ልታደርጉ አትችሉም” እንዲል ዮሐ ፲፭፥፭
፪.ከፈተና እንድናለን፡፡ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ፈተና በተለያያ መንገድ በስጋቸውና በነፍሳቸው
ላይ ይመጣል፡፡ ይህንን ፈተና ማምለጫና መውጫ መንገድ ደግሞ ጸሎት ነው፡፡ ጸሎትን የማያቋርጥ
ክርስቲያን ዲያብሎስ ከሚያመጣበት ፈተና ይድናል፡፡
፫. የጎደለንን እናገኛለን፡፡ የሰው ልጅ ቢዚህ ምድር ላይ አንዱ ሲመላለት ሌላው ሲጎድለው በደካማም
ይኖራል፡፡ የጎደለውን ለማግኘትም ይሠራል ይወጣል፣ ይወርዳል ይህ ስህተት ባይሆንም እግዚአብሔርን
ካልያዙ ከንቱ ልፋትና ድካም ነው፡፡

ጥያቄ፦ ስለምን መጸለይ አለብን?

መልስ፦ ክርስቲያን ስለሚጸልየው ነገር አስቀድሞ ማወቅና ማዘጋጀት አለበት፡፡ ስለምን እንደምንጸልይ
የማያውቅ ሰው ፍላጎቱን የማያውቅ ደካማ ሰው ነው ስለዚህ ለጸሎት በቆምን ጊዜ
ሀ. ስለራሳችን እንጸልይ
ስለ ራሳችን ስለ ምንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታችን ማለትም ትምህርታችንን እንዲገልጥልን፣ ሥራችንን
እንዲባርክልን፣ጤና እንዲሰጠን፣ ኃይል ጉልበት እንዲሆንነን አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል፡፡
ለ. ስለ ቤተሰቦቻችን እንጸልይ
እግዚአብሔር ቤተሰቦቻችንን ማለትም እናትና አባታችንን እህት ወንድሞቻችንን በእድሜ በጤና
እንዲጠብቅልን ሰላምና ፍቅርን እንዲያድልልን ሥራቸው እንዲቃናላቸው፣በመንፈሳዊ ሕይወት

እንዲበረቱ በንስሐ በሥጋ ወደሙ ታትመው እንዲኖሩ መጸለይ ይገባል፡፡

ሐ. ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
እግዚአብሔር ማደሪያው የምትሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃት ዘንድ አገልጋዮቿ የሚሆኑ
ካህናትን ሁሉ ይጠብቅ ዘንድ ስለ ፍፁም አንድነቷ፣ ስለ ሥርዓቷ መጠበቅ ዘወትር ሊለምኑ ይገባል፡፡

መ. ስለ ሀገር
የሁሉ መኖሪያ ስለሆነች ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ስለ ህዝቦቿ አንድነትና ፍቅር እንዲሁ እግዚአብሔር
ሰላሟን ይጠብቅ ዘንድ መለመን ይገባል፡፡ በተጨማሪ ሰላሟን ለመጠበቅ በየድንበሩ ላሉ ሠራዊቶች
ህዝቦቿን ይመግቡ ዘንድ ስለሚታትሩ ስለ ገበራዎች ዝናብን ይሰጥ ዘንድ አብዝ መጸለይ ይገባል፡፡

ሠ. ስለ ዓለም
ክርስቲያን ሁሉ ወገኑ ለሁሉም የየሚያስ ነውና እግዚአብሔር ዓለምን በውስጧ ያሉ ህዝቦቿን ሁሉ
ከርሀብ፣ ከቸነፈር፣ ከተፈጥሮና ከድንገተኛ አደጋ፣ ከእርስ በእርስ ጦርነት ይጠብቅ ዘንድ ዘወትር
ለጸሎት በቆምን ጊዜ ልንጸልይ ያስፈልጋል፡፡
ጥያቄ፦ እንዴት እንጸልይ?
መልስ፦ ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ማንኛውም ክርስቲያን ጸሎቱን እንዴት ማቅረብ
እንዳለበት ሊያውቅና አውቆ ሊቆም ይገባዋል፡፡ አንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባለማወቅ ብዙዎች
እግዚአብሔርን አሳዝነዋል ጸሎታቸውም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ክርስቲያች ግን እንዴት እንጸልይ ቢሉ?

ሀ. በእምነት መጸለይ
እግዚአብሔር አምላካችን ስለሚደንና ስለሚያስብልን ልመናችንን ስለሚሰማንና የሚጠቅመንን ነገር
እንደሚያደርግልን የተሻላንም ነገር እንደሚሰጠን በፍፁም ልባችን አምነን ንልጸልይ ይገባል፡፡ መጽሐፍ
ቅዱስ “አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” ማቴ ፳፩፥፳፪ እንዲል በእምነት ከጸለይን
የለመነው ይሳካልናል የፈለግነውም ይሰጠናል፡፡

ለ. በማስተዋል መጸለይ
ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ሁሉ ከውስጣችን የምናወጣው ማናቸውም ቃልና
የምናደርገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በማወቅና በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ይህምእንዲሆን
ዘወትር “አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነት ምራኝ አስተምረኝም ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ
አድርጌያለሁ” ልንለው ይገባል፡፡ መዝ ፳፭፥፭

ሐ. በትሕትና
አንድ ክርስቲያን በክርስቲያንነቱ ሊያሟላቸው ከሚገቡ መልካም ምግባራት መካከል ትሕትና እጅግ
አስፈላጊ ነው፡፡
ታዲያ በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት የሚቆም ሠው ትሁት ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ትህትና
ዲያቢሎስን ድል ማድረጊያ መንፈሳዊ መሳሪያ ነውና፡፡

ማጠቃለያ ጥያቄ

የሚከተሉትን በተማራችሁት መሠረት ትክክለኛውን መልስ ምረጡ

፩ የጸሎት ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?


ሀ. ምስጢርን ይገልጻል ሐ. የገጎደለንን እናገኝበታለን
ለ. ከፈተና እንድንድን ያደርጋል መ. ሁሉም መለስ ነው

፪ አንድ ክርስቲያን ስለምን ሊጸልይ ይገባዋል?


ሀ. ስለ ራሱ ሐ. ስለ ሀገሩ ሠላም
ለ. ስለ ቤተሰቡ ጤንነት መ. ሁሉም መልስ ነው

፫ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው?


ሀ. እውነት ለ. ሀሰት

You might also like