You are on page 1of 4

ስለዘፈን እና መዝሙር የቤተክርስቲያን አስተምህሮ

ዜማን ለእግዚአብሔር የምስጋና አገልግሎት የመጠቀም ነገር ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በአይሁድ እምነት የነበረ ነው።
የማርያም እኅተ ሙሴ ምስጋና አንዱ ማሳያ ነው። ዘጸ 15፥21 መዝሙረ ዳዊት ሌላ ማስረጃ ይሆናል። መዝ 9፥11፤
30፥4፤ 33፥2-3፤ 47፥6-7፤ 66፥2፤ 68፥4፣ 32-33፤ 105፥2 በሌላ መልኩ ሊቃነ ካህናቱ ተራ ገብተው እግዚአብሔርን
በዜማ እንዲያመሰግኑ ሥርዓት የሰራው መዝሙረኛው ዳዊት ነበር። 1 ዜና 15፥21፤ 16፥5፤ 25፥6፤ 2 ዜና 20፥21፤
23፥13 እርሱም በቃልኪዳኑ ታቦት ፊት በዝማሬ አመስግኗል። 2 ሳሙ ምዕራፍ 6 ይህም ሥርዓት ለጊዜው በሰሎሞን
በተሰራው ቤተመቅደስ ለፍጻሜው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸንቷል። እነእዝራ
በመሰንቆ ቅዱሳን መላዕክቱም በጣፋጭ ዝማሬ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።

በክርስቶስም ዘመን በዝማሬ እግዚአብሔርን ማመስገን የተለመደ ነገር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ማቴ
26፥30፤ ማር 14፥26 የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችም በመዝሙር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። ለዚህ አሪፉ ማሳያ
ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ነው። ሐዋ 16፥25 በዘመናት የክርስትና ታሪክ ውስጥም ስለዜማና ስለዝማሬ ሥርዓት ብዙ ብዙ
ክርክሮች ተካሂደዋል። አብዛኞቹ ክርክሮች መነሻቸው የዜማ መሳሪያዎችን መጠቀም አለብን ወይስ የለብንም በሚለው
ላይ ያተኮረ ነበር። በመዝሙርና በዘፈን መካከል ውዝግብ እንዲፈጠር መነሻ የሆነው የአስራ ስድስተኛ መቶ ክፍለ ዘመኑ
ተሐድሶ (Reformation) የተሰኘ ፕሮቴስታንቶች የቀሰቀሱት የሃይማኖት እንቅስቃሴ ነው። የዚህ እንቅስቃሴ መስራች
ነው የሚባለው ማርቲን ሉተር ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ከተቃወመባቸው ነገሮች አንዱ በላቲን ቋንቋ ላይ ብቻ
የተወሰነው የዝማሬ ሥርዓቷ አንዱና ዋነኛው ነበር። መነሻው ክርስትናን ከአንድ ሰዋዊ ቋንቋ ነጻ ማውጣት ቢሆንም
በዘመኑ የነበሩ የተሐድሶው እንቅስቃሴ መሪዎች ይህን ለማሳካት የተከተሉት መንገድ ግን ይለያያል። ይህም አሁን ድረስ
ዘልቆ በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መሰረታዊ የአስተምህሮ ውዝግብ ፈጥሯል። በዘመናችን ያለውን
ከማየታችን በፊት ነገሩን ከሥሩ ከመነሻው ማየቱ ጥሩ ነው በሚል በተሐድሶው እንቅስቃሴ መስራቾች መካከል ያለውን
የአመለካከት ልዩነት እንመልከት። ቤተክርስቲያንን ከላቲን ተጽዕኖ ነጻ ማውጣት በሚል መሰረታዊ ሐሳብ የተነሳው ሉተር
ይህንን ለማስፈጸም የሄደበት ርቀት የሚገርም ነው። በወቅቱ በሕዝቡ መካከል የተለመዱ ሃገረሰባዊ ሙዚቃዎችን
(Popular Songs) ጭምር ግጥሞቻቸው እየተቀየሩ ለዝማሬ መዋል አለባቸው የሚል ሐሳብ አመጣ። ሌላኛው
የፕሮቴስታንታዊው እንቅስቃሴ መሪ ጆን ካልቪን የላይኛውን የሉተር ሐሳብ ይቃወም ነበር። ለዚህ መነሻው
ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርቡ ግጥም እና ዜማዎች ያለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ካልተጻፉ ምዕመኑን ወዳልተፈለገ
አቅጣጫ ይመራሉ የሚል ስጋት ስለነበረበት ነው። ስለዚህም መዝሙራቱ ቀጥታ ከመዝሙረ ዳዊት መወሰድ አለባቸው
የሚል ሐሳብ ነበረው። ሌላኛው ስዊዘርላንዳዊው የተሐድሶው መሪ ዝወንግሊ ደግሞ ያለምንም የሙዚቃ መሳርያ የሰው
ልጅ በድምጹ ብቻ እግዚአብሔርን ማመስገን አለበት በሚል ሉተርን ሐሳዊ መምህር እስከማለት ደርሷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በ 19 ኛው መክዘ መጨረሻና በ 20 ኛው መክዘ መባቻ ላይ ከተፈጠረው


ፕሮቴስታንታዊ አመጽ በቀር በዜማ ሥርዓቷ ላይ ይህ ነው የሚባል ችግር ተፈጥሮ አይታወቅም። ቅዱስ ያሬድ ዜማውን
የተማረው ከመላዕክት መሆኑ በጥብቅ ስለሚታመን ያንን ለመዳበር እንጂ ለመለወጥ የተደረገ ሙከራ አልነበረም።
በእርግጥ በዘመነ ሱስንዮስ ካቶሊኮች የቅዳሴ ዜማውን በራሳቸው ሥርዓት ተክተዉት ያሬዳዊው ዝማሬ ላይ ችግር
ተጋርጦ ነበር። ከዚያም በፊት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ በዘመናቸው ሰዎች በየራሳቸው የቅዳሴ መጽሐፍ እየደረሱ መሆኑን
ጠቅሰው በጻፉት መጽሐፍ ላይ ይህንን ተቃውመዋል። እነዚህ በሙሉ ግን ዛሬ ልናነሳው ከወደድነው የዘፈን እና የመዝሙር
ብያኔ ጋር ግንኙነት ስለሌላቸው በጥልቀት አናያቸውም።

በዘመናችን ባሉ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተፈጠረው "የዘፈን ኃጢኣት ነው? ወይስ አይደለም?"
ንትርክ ቅርጹ ከላይ ካነሳነው የአባቶቻቸው የአመለካከት ልዩነት የተነሳ ነው። ዮናስ ጎርፌ የተባለ ሰው በቅርቡ "ቤት ያጣ
ቤተኛ" በሚል ባሳተመው መጽሐፉ ላይ ዘፈን ኃጢኣት አይደለም ሲል በብርቱ ይሞግታል። በቅርቡ ዘፋኞችም ዘፋኝ
አትበሉኝ፤ ዘማሪ ነኝ ዓይነት ንግግር መናገር እንዲሁም መዝሙር ይሁን ዘፈን የማይለዩ ነገሮችን መስራት ከጀመሩ
ሰነባብተዋል። በሌላኛው ጽንፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ዘፈንን የማትከለክል የአዝማሪዎች
ኅብረት አድርገው ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት ደግሞ ያስደንቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን ያላትን አስተምህሮ ለማየት ከመሞከራችን በፊት አስተምህሯቸው ውስጥ ያለውን መሰረታዊ ችግር
ለመመልከት እንሞክር።

በ 20 ኛው መክዘ አጋማሽ የተነሱ የፕሮቴስታንት መዘምራን እንደመሰንቆ እና ከበሮ ያሉ ባሕላዊ የዜማ መሳሪያዎችን
በየአዝማሪ ቤቱ ለውዳሴ ከንቱ የሚያገለግሉ እርኩሳን ናቸው በሚል ከቤተክርስቲያን አገልግሎት አገዷቸው። እነዚህን
መሳርያዎች መጠቀም ነውር ሆኖ እስከሚታይ ድረስ ተወገዙ። እዚህ ተግባር ላይ የሚታየው መሰረታዊ ችግር ሁለት
ነው። አንደኛው "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ!" የሚል መፈክር ያላቸው ፕሮቴስንታንቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
የተጠቀሱትን መሰንቆና ክራርን የአዝማሪ መሳሪያዎች ናቸው በሚል ከልክለው ካስወገዱ በኋላ በእነርሱ ምትክ
ያመጧቸው እንደኦርጋንና እንደጊታር ያሉ ምዕራባውያን መሳርያዎች ራሳቸው ለዘመናት በዓለማዊው ሙዚቃ ውስጥ
ለኃጢኣት ማስፈጸምያነት ሲያገለግሉ የነበሩ መሆናቸውን መርሳታቸው ነው። ይህ ነገር ካለው ግልጽ አመክንዮአዊ
ተቃርኖ በዘለለ የሚገልጸው አንዳች ታላቅ እውነት አለ። ይህም ዓላማቸው ለዘመናት ሥርዓት ሰርታ እግዚአብሔርን
ስታመሰግን የኖረችውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሻርና መቃረን እንጂ እግዚአብሔርን
በንጽኅና የማመስገን ጉዳይ አለመሆኑን ማሳየቱ ነው። ሁለተኛው ችግር ደግሞ በጊዜ ሂደት የተገለጠ ነው። መጀመርያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የአዝማሪዎች ኅብረት ሲሉ የነበሩ ሰዎች በኋላ ብዙዎቹ ዘፋኞች እና
የሙዚቃ አቀናባሪዎች ፕሮቴስታንት በሆኑበት የኢትዮጵያውያን ሚሊንየም መባቻ ላይ "ዘፈን እኮ ኃጢኣት አይደለም!"
የሚል ክርክር ማምጣታቸው ነው። ለእነርሱ ጊዜ ጽድቅ ለሌሎች ጊዜ ኃጢኣት የሚሆንበት መንገድ ዓይንህን ጨፍንና
በጥፊ ልምታህ ዓይነት የጅል ተግባር ይመስላል። ከዚህም በዘለለ ዘፈን ኃጢኣት አይደለም ለማለት ራሱ የሚያቀርቡት
ምክንያት ውኃ አያነሳም። ተራ የቃላት ጨዋታ ነው ባይ ነኝ። አንደኛው ሙዚቃ ተሰጥኦ ነውና እንደማንኛውም ሞያ
ይህንን ተሰጥኦ ለመጥፎ ተግባር መጠቀም ነው የሚያስቀጣው የሚል ነው። ልክ አንድ ዳኛ ጉቦኛ በመሆኑ እንጂ ዳኛ
በመሆኑ ብቻ እንደማይቀጣ ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በገላትያ ላይ የሥጋ ተግባራት ተብለው ከተጠቀሱት መሐል
በጽርዕ በተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘፋኝነት የለም የሚል ነው። መነሻ ቃሉ "ኮሞይስ" ሲሆን ይህም ዘፈንን
ሳይሆን በአምልኮ ወቅት ዝሙት ሳይቀር የሚፈጸምበትን ጭፈራና ዳንኪራ ለመግለጽ የገባ ነው ባዮች ናቸው።
ሦስተኛው መሟገቻው ዘፋኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበጎም በመጥፎም ተጠቅሶ ሳለ በመጥፎ ብቻ ማንሳቱ ተገቢ
አይደለም የሚል ነው። የያዙት የግለሰቦችን ጥፋት ተንተርሰው ቃላትን በመጠምዘዝ ቤተክርስቲያን የምትለውን በሌላ
ቋንቋ የራሳቸው አስመስለው መድገም ነው። እኛ ትክክለኛውን የዜማ አገልግሎት መዝሙር፣ የተሳሳተውን ደግሞ ዘፈን
አልነው። ዘፈን የሚለውን ኮሞይስ ካሉት ወደዝሙት ከሚነዳ ሙዚቃ እና ጭፈራ ጋር አቆራኘነው። መዝሙር የሚለውን
ደግሞ እግዚአብሔርን ለማመስገን ከምንጠቀምበት ዜማ ጋር አገናኘነው። በዚህ ካልተስማሙ መጽሐፍ ቅዱስ
በሚጠቀምበት የቃላት ብያኔ ሄደን ዘፈን እና መዝሙርን ለእግዚአብሔር ምስጋና ለሚቀርብ ዝማሬ ኮሞይስን ደግሞ እኛ
አሁን ዘፈን ለምንለው ዝሙታዊ ዜማ መጠቀም እንችላለን። ማለት ሐሳቡ ላይ ከተግባባን የምንወክልበት ቃል ችግር
የለውም ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን ዝሙታዊ የሆነውን ዜማ (ወይም በእኛ ብያኔ ዘፈን ያልነውን
ማለት ነው) እግዚአብሔር ከሚመሰገንበት የዝማሬ አገልግሎት (መዝሙር ከምንለው) ለመለየት የምትጠቀምበት
መስፈርት ግልጽ ነው። አንደኛው የዚያ ዜማ እሳቤ ነው። አዚያሚው ዜማውን የሚያዜምበት እሳቤ የዜማውን ውጤት
ይወስናል። እሳቤው ዓለማዊ ከሆነ ወደዝሙት፣ እሳቤው መንፈሳዊ ከሆነ ደግሞ ወደእግዚአብሔር ይመራል። ይህ ግጥም
ተጽፎላቸው ለሚዜሙት ብቻ ሳይሆን በመሳርያ ብቻ ለተቀነባበሩት ዜማዎች በሙሉ ያገለግላል። ምክንያቱም ጥሩ
ዜመኛ በመሳሪያዎቹ ብቻ አንድም ቃል ሳይናገር ሥጋዊም ይሁን መንፈሳዊ መልዕክቱን የማስተላለፍ እና አዳማጩን
ወደጥፋትም ሆነ ወደልማት የመምራት አቅም አለው። ይህ የመጀመርያው መስፈርት ብዙ ለመወሰን የሚያስቸግሩ
ዜማዎችን ለመለየት የማያስችል ቦታ ላይ ቢያስቀምጣቸውም ለእግዚአብሔር አገልግሎት መዋል ያለበት ዜማ ላይ ግን
ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ያስቀምጣል። ያ ዜማ እሳቤዎቹ መንፈሳዊ ስለሆኑ አዳማጮቹን ወደእግዚአብሔር ብቻ
የሚያደርሱ መሆን አለባቸው። ይህንን አጽንዖት ልሰጠው እወዳለሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ብቻ! ይህ ብያኔ ለጾታዊ ፍቅር
የተቀነቀኑትን ሥጋዊ ዜማዎች ብቻ ሳይሆን ስለሃገር፣ ስለእናት ወይም ስለሆነ ቡድን የተዜሙትን ምኑናት ዜማዎች
(የተናቁ፣ የማይጎዱ የማይጠቅሙ ዜማዎች) በሙሉ ከጨዋታው ውስጥ ያወጣቸዋል። የሚቀሩት አሁን ዘፈን
የምንላቸው ነገር ግን ፍጹም መንፈሳዊ መልዕክት ያላቸው ዜማዎች ናቸው። ይሄ ደግሞ ወደ ሁለተኛው መስፈርት
ይመራናል።

ሁለተኛው መስፈርት ሥርዓት ነው። ከላይ በበየነው መሰረት ለእግዚአብሔር አገልግሎት በሚውለው ዜማ እና
ወደዝሙት በሚመራው ዓለማዊ ዜማ መካከል ያለውን ልዩነት ለመቆጣጠርም በግልጽ ለመለየትም የሚያገለግለው
ሥርዓት ነው። የሥርዓት ቤት የምትባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም በዚህ አትታማም። የራሷ የሆነ
የዜማ ሥርዓት ሰርታ እግዚአብሔርን በሚገባ ታመሰግነዋለች። ሥርዓቱ እንዲሁ እንደውኃ ፈሳሽ እንደእንግዳ ደራሽ
የተገኘ አይደለም። ከላይ እንደ መጀመሪያ መስፈርት ካስቀመጥነው እሳቤው የመጣ ነው። ለምን በኪቦርድ አትዘምሩም
የሚሉን ይህንን ስለማያውቁ ነው። የቅዱስ ያሬድን ዝማሬ ቤተክርስቲያን የምትጠቀመው በጣም ስለሚያምር ወይም
ከአባቶቻችን የወረስነው ጥንታዊ ሃብታችን ስለሆነ ብቻ አይደለም። የሚዜሙት ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወጣጡ
ምንባቦች ከመሆናቸው በላይ ዜማው ራሱ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያስታውሱ ሆነው
የተቀረጹ ናቸው። ይዘት የክርስቶስን መያዝ፣ ርክርክ የክርስቶስን መንገላታት ያጠይቃሉ። ከበሮ የአዝማሪ ቤት እቃ
የመሰላቸው ስለማይጠይቁ ነው። ከበሮውን መምታት ክርስቶስ በጥፊ መመታቱን ለማስታወስ የሚደረግ ተግባር ነው።
ክርስቲያኖች በከበሮው ውስጥ ክርስቶስ መገረፉን እና መሞቱ እንዲያስታውሱ በቀይ ከለሜዳ ተሸፍኖ ዙሪያውን ገመድ
ተተብትቦበታል። ስለሰው ልጆች መከራ ለመቀበል አምላክ ሰው መሆኑን ሲያጠይቅ ከበሮ በመለኮትና በትስብዕት ምሳሌ
አንድ ሰፊና አንድ ጠባብ መምቻዎች አሉት። ከበሮ የሚመታው ሰው ቀጥ ብሎ እንዲቆም የማይፈቀድለት የክርስቶስን
መንገላታት እንዲያስታውስ ስለሚፈለግ ነው። መቋሚያ አናቱ የበግ ቀንድ (ቀርነ በግዕ) ቅርጽ እንዲኖረው የሚደረገው
የክርስቶስ ምሳሌ ስለሆነ ነው። ሊቃውንቱ በየወረቡ ከፍ ዝቅ የሚያደርጉት መንገላታቱን ሲያስታውሱ ነው። እንዲህ
እንዲህ እያልን እያንዳንዱን የቤተክርስቲያን የዜማ መሳሪያና ስርዓት መተንተን እንችላለን። እንዲህ ባለ ሥርዓት ውስጥ
ተሁኖ ለሞተልን ጌታ ከሚቀርብ ከመንፈሳዊው የእግዚአብሔር አገልግሎት ውጪ እንዴት ስለዓለማዊው ነገር ማሰብ
ይቻላል? የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ወደዓለማዊው ዝሙታዊ ሙዚቃና ዳንኪራ ሄደው እንዳይጠፉ ይህን ሁሉ
አጥር ሥርዓት ሰርታ ልጆቿን ትጠብቃለች። ቤት አጥር ስላለው ሊነቀፍ ይገባል? እያሉን ያሉት እኮ አጥራችሁን አፍርሱና
እንዝረፋችሁ ነው። አንዳንዴ በጸጋችን ሊያሸማቅቁን ሲሞክሩ ያበሳጫል። እውነት እውነት እንነጋገር ከተባለ "ኮሞይስ"
ለሚባለው ዝሙታዊ የአምልኮ ጭፈራ የሚቀርበው የትኛው ሥርዓት ነው? አሁንም በፕሮቴስታንት አብያተ
ክርስቲያናት ውስጥ የሚጎድለው ይሄ ሥርዓት ነው። ምዕመናን ዜማውን ሲያዜሙ ከተነሱበት መንፈሳዊ እሳቤ
እንዳይወጡ የሚያደርግ ሥርዓት ያሻል። በእርግጥ ሲመሰረቱ ጀምሮ "በነጻነት ማምለክ" በሚል መፈክር ሥር ሥርዓት
የሚባለውን አጥር ንደዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም እንደገባው ይተርጉም የሚለው የዚያ ማሳያ ነው። ነገር ግን እነርሱ
ሥርዓት ስላጡ ሁሉም ሥርዓት አልባ መሆን አለበት ማለት አያስኬድም። እኔ አጥሬን አፍርሻለሁና መንደርተኛው ሁሉ
አጥሩን ያፍርስ እንደሚል ነገረኛ ጎረቤት መሆን ነው።

በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእኛው ቤተክርስቲያን ውስጥም ትልቅ የሥርዓት መፋለስ እየተከሰተ ነው። በያሬዳዊው
የዝማሬ ስልት የሚዘምሩ ዘማሪያን ቁጥር እየቀነሰ ሃገረ ሰባዊውን ዜማ (Pop Culture) የሚጠቀሙት እየበዙ ነው።
ከዚያም በላይ መዝለል እና መጨፈር የሚያበዙ ዘማርያን ሞልተዋል። መዝሙር በድምቀቱ እና በእልልታው ብዛት
እየተመዘነ ነው። ከበሮ የክርስቶስ ምሳሌ ነው ብላ በምታስተምር ቤተክርስቲያን ውስጥ እየሳቀ ከበሮ የሚመታ ምዕመን
ክርስቶስን በጥፊ እየመቱ ካላገጡበት አይሁድ በምን ይተናነሳል።

ይህ የእሳቤ እና የሥርዓት ጉዳይ ለዝማሬ ብቻ የሚያገለግል አይደለም። ረሐብ እና ጾም መካከል ያለው ልዩነት
ምንድነው? አንድም እሳቤው ነው። የክርስቶስን መራብና መጠማት እያሰብን ነው የምንራበው ወይስ ሥላጣን ነው?
ከዚያ ቀጥሎ የምንጾምበት ሥርዓት ያሻናል። ቤተክርስቲያን በጾም ወቅት ጥሉላት ምግቦችን የምትከለክለው ለዚህ ነው።
ጾመን ጾመን ውለን ኋላ በዘፈቀደ ስናግበሰብስ ብንውል ሥርዓት የለንምና ከረሐብተኛ የሚለይ ሥራ አልሰራንም።
ረሐብተኛም የማይበላው የሚበላው ስላላገኘ ነው። ጾመኛ ግን በፈቃዱ ስለሚራብ ለቁመተ ሥጋ ብቻ እየበላ
የክርስቶስን ረሐብ ያስባል።

በአጠቃላይ ይህ የእሳቤና የሥርዓት አመክንዮ ለብዙ ነገሮች የሚያገለግል ነው።

You might also like