You are on page 1of 12

አምልኮ

በነቢዩ ኢሳይያስ
በዓለም ላይ ብዙ ኃይማኖቶች አሉ። ሁሉም እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት የየራሳቸው መንገድ አላቸው። ብዙዎች የአምልኮ
መለኪያውን የራሳቸው አምልኮ በማድረግ በእነርሱ አምልኮ እግዚአብሔር ደስ እንደሚሰኝ፣ በሌሎች ግን ደስ እንደማይሰኝ
በድፍረት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ የብሉያትን መጽሓፍ ስንመረምር በቀደመው ኪዳን ይኖሩ የነበሩ
የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምልኮአቸው በአጠቃላይ በሕጉ መጽሓፍ ከተቀመጠው ሓሳብ በወጣ ጊዜ ያህዌ በነቢያቱ በኩል እንዲህ
ይላቸውና ይገስጻቸው ነበር፣ “ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም።
የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን
የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም። የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም” (አሞጽ 5፡ 21-
23)።
እግዚአብሔርን ከማወቅ መንገድ ርቀው በሚያቀርቡት መስዋዕት ብቻ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ይጥሩ ለነበሩት ለእነዚሁ
የእስራኤል ልጆች በሌላ ጊዜ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ የሚል መልዕክት መጥቶላቸው ነበር፤ “እናንተ የሰዶም አለቆች
ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ
ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤የበሬና የበግ
ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ
የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን
በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤
ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም
ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” (ኢሳ 1፡10-15)። ከእነዚህ ሁለት የመጽሓፍ ቅዱስ ክፍሎች
እግዚአብሔር አንዳንድ አምልኮዎችን እንደሚቀበል፣ አንዳንዶችን ደግሞ እንደማይቀበል እንረዳለን።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስመልክቶ ስለ “አምልኮ” ይህንን መልዕክት ስጽፍ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማው፣
እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለብን አቅጣጫን ከማሳየት ይልቅ፣ አምልኮን በሰው ሕይወት የሚፈጥረው ራሱ
እግዚአብሔር መሆኑን ማሳየት ነው (ፊል 2፡13)፤ ወይም በ 16 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተክርስቲያን ተሓድሶአውያን
አገላለጽ፣ “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ የሚወሰነው እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በገለጠውና ባደረገው ነገር ላይ
እንጂ በእኛ ኃይማኖታዊ ስሜት ወይም አሳብ አይደለም። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው አምልኮ የሚመነጨውም ሆነ
የሚካሄደው በራሱ በእግዚአብሔር ነው።” ይህንን በወንጌላት ከተገለጸው እውነት ማስተዋል እንደምንችል አስባለሁ። እኛም
በዚህ ዘመን የምንገኝ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምልኮን በተመለከተ ከወንጌላት ልንማረው የምንችለው በርካታ ነገር ስላለ
ወደዚያው ሓሳብ እንሄዳለን፦
1. አምልኮ በእረኞቹ ሕይወት። የአምልኮአቸው ምክንያት የምሥራቹ ቃል ነበረ። በሰው ሕይወት ውስጥ አምልኮን የሚፈጥር
እግዚአብሔር አምላክ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ ከምናይባቸው የወንጌላት ክፍሎች ውስጥ አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡8-
14 ያለው ታሪክ ነው። በዚህ ክፍል የምሥራቹ ቃል የተበሠረላቸው እረኞች ሲሆኑ፣ እግዚአብሔር መድህን እንደ ተወለደ
ያበስሩላቸው ዘንድ መላእክቱን ወደ እነርሱ ላከ። እረኞቹም በመልእክቱ የታወጀውን የምሥራች ቃል እንደ ሰሙ፣ “ስለ
ሰሙትና ስላዩት ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።” እነዚህ እረኞች በመላእክቱ አማካይነት የመጣውን
ይህን የምሥራች ቃል ባይሰሙ ኖሮ፣ እግዚአብሔርን በማምለክ ደስታ አይጥለቀለቁም ነበር። ስለዚህም ከሰሙት የምሥራች ቃል
የተነሳ አዳኙን ለማየት ወደ ቤተ ልሔም ተጣደፉ፣ እግዚአብሔርም በመላእክቱ በተነገረው የምሥራች ቃል አማካይነት
እረኞቹን እንዲያመልኩት አደረገ። ሉቃስ ስለዚህ ሁኔታ ሲተርክልን “ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና
እያከበሩ ተመለሱ” ይለናል (ሉቃስ 2፡20)። እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያነሳሳው አምልኮ
እውነተኛ ከመሆኑም በላይ እርሱ ደስ የሚሰኝበትና ትክክለኛ አምልኮ ነው። እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት አምልኮ ሁሉ
ከወንጌሉ ቃል ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በዚሁ የወንጌል ቃል እንዲህ ዓይነቱንም አምልኮ በሰው ሕይወት ውስጥ እንዲፈጠር
የሚያደርገው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ከዚህ እውነት ስንነሳ በሰው ሕይወት የሚፈጠር የእውነተኛ አምልኮ ምንጭና መገኛ
እግዚአብሔር ነው ማለት እንችላለን። መልአኩ “ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና … ዛሬ
መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋልና” ሲል ባበሠረላቸው የወንጌል ኃይል ምክንያት እረኞቹ እግዚአብሔርን
አመሰገኑት (ሉቃስ 2፡10-11)። ሰዎችን በሰማያዊ ደስታ እንዲጥለቀለቁ የሚያደርግና እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑት
(እንዲያመልኩት) የሚያስችለው ብቸኛ ኃይል የማዳኑ ወንጌል ነው። ሕያው ቃሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ ሲያገኝና ሲሠራ
ሰዎች በደስታ ሊጥለቀለቁ፣ እግዚአብሔርንም ሊያመልኩት ይችላሉ።
2. መግደላዊት ማርያም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የአምልኮ ምሳሌ ነች (ሉቃስ 7፡38፤48-50)። የዚች ሴት ታሪክ
የሚገኝበትን ዐውደ ምንባብ በጥልቀት ካልመረመርነው ምናልባትም ድርጊቷ ሊያሳስተን እንደሚችል አስባለሁ። ከእኛ እይታ
አንፃር ምንም እንኳ ይህች ሴት ጌታን አንድ ነገር በማድረግ እያመለከችው ያለች ቢመስለንም፣ “ኃጢአትሽ ተሠረዬልሽ…
እምነትሽ አድኖሻል… በሰላም ሂጂ’’ የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር ግን፣ ከእርሷ ድርጊት ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይህች ሴት
ወደ ኢየሱስ የመጣቸው የኃጢአት ይቅርታ በእርሱ እንደሚገኝ በማመን ነው። ይህ እግዚአብሔርን የማምለክ ከፍተኛ ደረጃ
ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የወንጌል አማኞች እንደ ተነሳንበት የእምነት አቋም፣ አምልኮ ማለት እኛ በራሳችን ተነሳሽነት
ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር ሳይሆን፣ ይልቁንም እርሱ በሕያው ቃሉ አማካይነት በእኛ ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው ነገር
ነው። መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ የመጣቸው የኃጢአት ይቅርታን ሽታ ነበር። ጌታም ይህን ሊሰጣት እንደሚችል ስለ
እርሱ ቀድማ ከሰማችው ነገር አምናለች። ይህች ሴት ስለ ኢየሱስ መሲህነቱን ከመቀበልና የኃጢአትን ይቅርታ እንደሚሠጣት
ከማመን ውጭ ስለ እርሱ ልታውቀው የምትችለው ነገር አልነበረም። ለእኛም ቢሆን ከዚህ የተለየ ነገር የለም። ጌታ ኢየሱስ
እርሱ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚሰጥ በማመን በእምነት ወደ እርሱ መጠጋት የአምልኮ ከፍተኛው ደረጃ ነው። መግደላዊት
ማርያም ኢየሱስን ሽቱ በመቀባቷና በማልቀሷ እርሱ ድርጊቷን አድንቆታል፤ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ በእርሱ ላይ ያላት የእምነት
ምልክትና መግለጫ እንዲሁም ከእርሱ የኃጢአት ይቅርታ ለመቀበል ያደረገችው አንድ ዓይነት ኑዛዜ ነበር። ወደ እርሱ
ከመምጣቷ በፊት ስለ እርሱ ዝና ሰምታለች (ሉቃስ 7፡17)። ወደ እርሱም የመጣችውና እርሱን ማምለክ የጀመረችው የእርሱ
ምህረቱና የኃይሉ ዝና በመውጣቱ ምክንያት በሰማችው የምሥራች እንጂ እንዲሁ ከሜዳ በመነሳት አልነበረም። የወንጌሉን ክፍል
ልብ ብለን እንመልከት። ኢየሱስ መግደላዊት ማርያም ባሳየችው የፍቅር ሥራ የኃጢአት ይቅርታን እንዳገኘች መናገር አልፈለገም፤
ስለዚህ “እምነትሽ አድኖሻል” በማለት መለሰላት። ከዚህ እውነት ስንነሳ የኃጢአት ይቅርታን እንደምናገኝ በማመን ወደ ኢየሱስ
ክርስቶስ መምጣት፣ የአምልኮአችን ከፍተኛው ደረጃ ነው። ይህም እርሱን በማመን የሚጀመር ይሆናል። ሰው የኃጢአትን ሥርየት
የሚያገኘው በእምነት እንጂ በአምልኮው ወይም በድርጊቱ ብዛት አይደለም። የአምልኮአችን መነሻ በእምነት ያገኘነው የኃጢአት
ይቅርታ ነው። ከዚህ እውነት ስንነሳ አምልኮን በውስጣችን የሚፈጥረው ስለ እርሱ የምንሰማው ሕያው እውነት እንደሆነ
እንረዳለን።
አምልኮ ከመስጠት ይልቅ መቀበል ላይ ያመዝናል። በወንጌላት የተገለጸው የአምልኮ የመጀመሪያው ምዕራፍ በእምነት አማካይነት
በሰው ሁኔታ ላይ ባልተመረኮዘው የእግዚአብሔር ጸጋ የኃጢአት ይቅርታንና ያለ ሥራ የሚገኝን ጽድቅ ለመቀበል መዘጋጀት
ይሆናል። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ ጥያቄ ይነሳል። ይኸውም በዚህ የወንጌል ክፍል ተገልጻ የምናገኛት የዚህች ሴት ድርጊት፣ ዛሬ
ለእኛ ምን ፋይዳ አለው? የሚለው ነው። እንደ እኔ አመለካከት የዚች ሴት ድርጊት ለእኛ አንድ ጥሩ ፋይዳ እንዳለው
አስባለሁ። ይህም ስለ አምልኮ ሊኖረን የሚገባውን አሳብና አመለካከት ለማስተካከል እንደ መስተዋት የሚሆን ምሳሌ የሚሰጠን
መሆኑ ነው። እኛ ዛሬ እንደ ሴትዬዋ በኢየሱስ ክርስቶስ እግር ላይ እንባችንን እያፈሰስን እግሩን ማጠብ ባንችልም፣ነገር ግን
ለማምለክ የተለያዩ ነገሮችን እናደርግ ይሆናል። እግዚአብሔርን በማምለክ ሂደት ውስጥ የዚች ሴት ድርጊት የሚያሳየን ዋናው
ትኩረት፣ አምልኮ እርሱ ለእኛ ካደረገልን ነገር የሚመነጭ እንጂ እኛ በራሳችን ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር እንዳልሆነ
ነው። የእኛ የአምልኮ ተግባር እግዚአብሔር በእኛ ላይ ምህረቱን፣ ፍቅሩንና ጸጋውን ከማፍሰሱ የተነሳ የሚመጣ ነው።
በአምልኮአችን ውስጥ ዋናው ነገር የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሲሆን፣ ይህም በመስቀል ሞቱ ያስገኘልንና እኛ በእርሱ በማመን
የተቀበልነውን የኃጢአት ይቅርታ ነው (1 ዮሐ 4፡19)። እግዚአብሔርን እንድናመልከው የሚያነሳሳን ነገር ቢኖር ይኽ ነው።
አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁና ይህንን ሓሳብ ላጠቃልለው፣ እግዚአብሔርን ስናመልክ በጣም ግድ የሚለን እኛ ለእርሱ የምናደርግለት
ነገር ነው? ወይስ እርሱ ለእኛ ያደረገልን ነገር? ይህንን ሓሳብ መለየት በጣም ጠቃሚ ነገር እንደ ሆነ አስባለሁ። የዚች ሴት
ታሪክ ስለ አምልኮ ያለንን አመለካከት እንዲያስተካክልልን እንፍቀድ፤ ከዚያም አምልኮአችን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ
ይሆናል። ኢየሱስን ያስደስተዋል ብለን አንድ ነገር በመያዝ ወደ ፊቱ ከመምጣት ይልቅ ይህች ሴት የኃጢአትን ይቅርታ
ለመቀበል በእምነት ወደ ኢየሱስ እንደ መጣች፣ እኛም ምህረትንና ጸጋውን ለመቀበል እለት እለት በእምነት ወደ ፊቱ እንምጣ።
ይህ እርሱን ያስደንቀዋል። የአምልኮአችን ጅማሬ የሚመነጨው ከዚህ ውስጥ ነው።
3. አምልኮ በማርያምና ማርታ ሕይወት (ሉቃስ 10፡42)። አምልኮ ማለት ኢየሱስን መስማት እንጂ ለኢየሱስ አንድ ነገር
ማድረግ አይደለም። እ. ኤ. እ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በኮፕን ሃገን ዴንማርክ አንድ ትልቅ የሙዚቃ ትርዒት ቀርቦ
ነበር። ትርዒቱን የተከታተሉ ሰዎች በቀረበው የሲንፎኒ ሙዚቃ ትርዒት ተመስጠው እንደ ነበር ተናግረዋል። አሁን አሁን
አንዳንድ ኃይማኖታዊ ፕሮግራሞች እንዲህ ዓይነት ይዘት አላቸው። በዚህ ዘመን በትልልቅ ካቴድራሎችና የስብሰባ አዳራሾች
የሚቀርቡ እንዲህ ዓይነት ረቂቅ ሙዚቃዎች፣ የሰውን ቀልብ የመጎተትና ነፍስን በማባበል ወደ ውስጡ እንዲያዘነብል የማድረግ
ባህርይ አላቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ረቂቅ የሙዚቃ ቅንብሮሽ በቤተ ክርስቲያን በሚከናወን አምልኮ ውስጥ እየተለመደ መጥቷል።
በተለይም እንዲህ ዓይነቱ ኃይማኖታዊ የሙዚቃ ኮንሰርትና ፌስቲቫል በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ፣በሰሜን አሜሪካና በአፍሪካ
አንዳንድ አገሮች ውስጥ እየተከናወነ ያለ ነገር በመሆኑ በትንንሽ ቤተ ክርስቲያን ከሚካሄዱ የአምልኮ ፕሮግራሞች ይልቅ ሰዎችን
የሚመስጡ እየሆኑ መጥተዋል። ወደ ወንጌል ትምህርት ስንመጣ ግን፣ የምንመለከተው የዚህን ድርጊት ተቃራኒ ነገር ነው።
በሉቃስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን የማርያምንና የማርታን ታሪክ ልብ እንበል። ማርያም ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ
በማለት እርሱ የሚያስተምረውን በአንክሮ ትከታተላለች። የማርያምን ሕይወትና ድርጊት ወደ እዚህ ዘመን ድርጊትና ልምምድ
ብናመጣው ብዙዎቻችን መነቃቃት የምንለውን የአምልኮ ሕይወት አይገልጽም፤ ይሁን እንጂ ከማርታ ድርጊት ይልቅ ኢየሱስ ደስ
ተሰኝቶበታል። ኢየሱስ ማርያምንና ማርታን ለመጎብኘት ወደ ቤታቸው በመጣ ጊዜ፣ ማርታ ኢየሱስን ለማስደሰት ስትል ራሷን
አባተለች፤ ማርያም ግን ሕይወት ሰጭ በሆነው ጌታ እግር ሥር በመቀመጥ ነፍሷን ትመግብ ነበር። ፈቃዷንም ለዚህ ነገር
አስገዛች። በዚህ የማርያም ድርጊት ማርታ በማጉረምረሟ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፣ “ማርታ ማርታ በብዙ ነገር
ትጨነቂያለሽ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም እድልን መርጣለች፣ ከእርስዋም
አይወሰድባትም” (ሉቃስ 10፡41-42)።
አምልኮ የሚጀምረው በመቀበል እንጂ በመስጠት አይደለም። ማርታ ለመስጠት ስትነሳ ማርያም ግን ለመቀበል ተቀምጣለች።
ኢየሱስ እየተናገረ እያለ ማርታ ለኢየሱስ የሚሰጥ ነገር ለማቅረብና እርሱን ለማስደሰት ደፋ ቀና ትላለች። ማርያም ግን የአምልኮ
መገኛና ሕይወት ሰጭ የሆነውን ሕያው ቃሉን ዝም ብላ ትመገብ ነበር። ምንም እንኳ እርሱን የምናምን እኛ በአምልኮ ለእርሱ
በርካታ ነገሮችን የምንሰጥበት ጊዜ ቢኖረንም፣ ይህንን ምላሽ ከመስጠታችን በፊት ግን በእርሱ ሕይወት ሰጭ ቃል እለት እለት
አዲስና የተለወጠ ሕይወት ልንቀበል ይገባል (ዮሐ 6፡63)። በዚህ ዘመን ብዙዎች ስለ አምልኮ ያላቸው መረዳት ከመቀበል
ይልቅ መስጠት ላይ ያተኩራል፤ ስለዚህ ሕይወታቸው የማርያም ሳይሆን የማርታ፣ ጸጋ አደር ሳይሆን ወዝ አደር ነው።
እግዚአብሔርን በአምልኮ ለማስደሰት ሞቅ ባለ ሁኔታ መዘመር ወይም እንቅስቃቄ ማድረግ ብቻ አለብህ የሚለው አስተሳሰብ
ለሕዝብ ስሜት የሚመችና በአንድ በኩል ብቻ ረዝሞ የጸነፈ አመለካከት ነው። እንዲያውም የተሳሳተ አመለካከት እንዳይሆን
ያስፈራል። በአምልኮ ጊዜ ከእግዚአብሔር ከምንቀበለው በረከት ይልቅ ለእርሱ በምንሰጠው ነገር ፈተና ውስጥ መውደቅ አዲስ
ነገር አይደለም። እንደ ተሓድሶአውያን አባባል፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውና “ለሰው ልጅ ታላቅ መጽናናት የሚያመጣው
ከፍተኛ አምልኮ፣ በወንጌል ውስጥ ከተቀመጠልን የኃጢአት ይቅርታና የጸጋ ትምህርት የሚነሳ ነው።” ወደ ቤተ ክርስቲያን
ለመሄድ ስንነሳ የሚታሰበን እግዚአብሔርን ለማምለክ ያለብን ግዴታ ነው? ወይስ እርሱ ነፍሳችንን ሊመግባት ያዘጋጀልን
ግብዣ? በእርግጥ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ አምልኮን በይበልጥ እኛ ለእርሱ የምናደርግለት ነገር መሆኑን የሚያስመስሉ ሓሳቦች
አሉ። ለምሳሌ ሮሜ 12፡1-2 አንዱ ነው። ይህ ጥቅስ ከአጠቃላይ የሮሜ መልእክት ዐውድ አኳያ ሲታይ ምዕራፉ
“እንግዲህ” ብሎ በመጀመሩ አምልኮ እግዚአብሔር ለእኛ ካደረገልን ነገር የሚጀምር መሆኑን አመልካች ሲሆን፣ ይኸውም እኛን
ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ማምጣቱ ነው። ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድን ስናስብ እርሱ ለእኛ የሚያደርግልን ሳይሆን፣
እኛ ለእርሱ የምናደርግለት ነገር አእምሮአችንን የሚገዛ ከሆነ፣ አሁንም ደግሜ እላችኋለሁ፣ ሕይወታችን የሚሆነው ጸጋ አደር
ሳይሆን ወዝ አደር ነው። እኛ ለእርሱ የምናቀርብለት አምልኮ ከእኛ እንዲወጣ አስቀድሞ እርሱ በሕያው ቃሉና በጸጋው ወደ
እኛ መምጣት አለበት። በኃጢአተኛው ሰው ሕይወት መፈለግንና ማድረግን የሚሠራ እርሱ ነው (ፊል 2፡13)።
የአምልኮ ዋና ነጥብ ጌታን መስማት ነው (ማቴ 17፡5)። ኢየሱስን በመስማትና ለኢየሱስ አንድ ነገር በማድረግ መካከል
ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ልብ ብለን ካላወቅን ሕግና ጸጋ ሊቀላቀልብን ይችላል። ከዚህ አኳያ የወንጌሉን አምልኮ ከሕግ
አምልኮ መለየት መቻል አለብን። የወንጌል አምልኮ ኢየሱስን በመስማት መጀመር አለብህ ሲለን፣ በሰብዓዊ ጥረት ላይ
የተመሠረተው (የሕጉ) አምልኮ ግን ለኢየሱስ አንድ ነገር በማድረግ ጀምር ይለናል። በዚህ ጊዜ አምልኮ ሥራ ይሆናል።
የወንጌሉ አምልኮ ከእግዚአብሔር መልካም ነገሮችን መቀበል ሲሆን፣ የሕግ አምልኮ ግን የእኛን መልካም ነገሮች ለእግዚአብሔር
ማቅረብ ነው። እግዚአብሔር አምልኮአችን ከወንጌሉ ቃል የወጣ እንዲሆን ይፈልግብናል። ይኸውም ኢየሱስን መስማት ነው።
በዚህ መስማት ውስጥ ኃያልና ሕያው የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን ታላቅ የሆነን ሥራ ይሠራል (1 ተሰ 2፡13)።
ከዚህ ውጭ ግን እንቅስቃሴያችንን የአምልኮአችን መጀመሪያ እንድናደርገው አይፈልግም። እግዚአብሔርን ለአምልኮ ወደ ፊቱ
ስንመጣ፣ እንደ ማርታ ለኢየሱስ አንድ ነገር ለማድረግ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ እንደ ማርያም ቃሉን በመስማት ላይ እና እርሱ
ለእኛ ባደረገው ነገር ላይ ትኩረት እናድርግ። “እርሱን ስሙት” እንደ ተባለ፣ እርሱን ለመስማት እንዘጋጅ። ዛሬም ከዚህ ሓሳብ
እግዚአብሔር አንድ ነገር እንድናውቅ ይፈልጋል። ይህም አንድ ነገር ቃሉን ከመስማትና ልብ ከማለት የበለጠ እርሱን
የምናክበርበት ነገርና ፍቅራችንን ለእርሱ የምንገልጥበት እንዲሁም እርሱን ለማምለክ ከፍ ያለ ሁኔታና መንገድ ያለ መኖሩን ነው።
ለእግዚአብሔር በመዝሙርና በመንፈሳዊ ቅኔ በልባችን የምንቀኘው የእግዚአብሔር ቃል በልባችን ሲኖር ብቻ ነው (ቆላ 3፡
16)። ሕይወት ሰጭና አስተላላፊ ከሆነው የእግዚአብሔር ቃል ጋር እየተጣብቅን ስንመጣ ከኢየሱስ ጋር ያለን ሕይወት ሰጭ
መያያዝ ውጤታማ ይሆናል (ዮሐ 6፡63)። በቃሉ የማይኖር ሕይወት ይቋረጥበታል (ዮሐ 15፡6)።
4. የአምልኮ ጽንሰ ሓሳብና ሳምራዊቷ ሴት (ዮሐ 4፡20)። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው አምልኮ በቦታ የሚወሰን
አይደለም። በዓለማችን ላይ የታወቁ የአምልኮ ሥፍራዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የነበረበት ሥፍራ፣
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ብሔራዊ ካቴድራል፣ በሎንደን የሚገኘው ዌስትሚንስተር ካቴድራል፣ በሜክሲኮ ከተማ የሚገኘው
ጓዳሉፕ ሂዳልጎ፣ በሮም የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራልና እንዲሁም በአገራችን የሚገኙት የላሊበላና የአክሱም ጽዮን ቤተ
ክርስቲያን በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህን በምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ ዝርዝሩ ከዚህ በላይ ሊያልፍ እንደሚችል እውቅ
ነው፤ ይሁን እንጂ በተለያየ አገር የሚኖሩ የሰው ልጆች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ወደ እነዚህ የታወቁ የአምልኮ
ሥፍራዎች መጓዝ ይናፍቃሉ። የዘመናችን ሰው በእነዚህ የተቀደሱ ሥፍራዎች በመገኘቱ ብቻ በጣም መንፈሳዊነት ሊሰማው
እንደሚችል እገምታለሁ፤ ምክንያቱም ሥፍራዎቹ ለመንፈሳዊ ነገር ታስበው ስለተለዩና ተጓዡም ሰው ገንዘቡን ከፍሎ በሥፍራው
ተገኝቷልና ነው። ኢየሱስ ግን ለሳምራዊቷ ሴት እግዚአብሔር በሰው አምልኮ ደስ ከተሰኘ ደስ የሚሰኘው በአምልኮው ይዘት
እንጂ በሥፍራ እንዳልሆነ አስረዳት። ይህች ሴት እግዚአብሔርን ለማምለክ ሥፍራ ቁም ነገር ነው ብላ የምታምን ነበረች። ይህን
የምታምን መሆኗ “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፣ አንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ”
ከሚለው ንግግሯ መረዳት እንችላለን (ዮሐ 4፡20)። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ ከሥፍራ ጋር የተያያዘ
ሳይሆን፣ራሱን በልጁ በመግለጡ ላይ የሚያተኩር ነው። አምልኮአችን እግዚአብሔር አምላክ ራሱን በልጁ በኩል በመግለጡ ላይ
ከመሠረተ፣ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ብሔራዊ ካቴድራል እስከ ጦር ሜዳ ውስጥ እስካለች ትንሽ ድንኳን ሊከናወን ይችላል፤
እግዚአብሔርን ማምለክ ቦታ አይወስነውም። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህችን ሳምራዊ ሴት፣ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ፣ ለአብ
በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኗአል፣ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና’’ በማለት
ሲመልስላት በእርሱ መምጣት ወደ ፊት ሊከናወን ስላለው አምልኮ መናገሩ ነበር [ዮሐ 4፡23]። እግዚብሔርን የሚያስደስተው
አምልኮ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ላይ ያተኩራል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት እንዴት እንዳዳነንና ሥጦታውን
በመስቀሉ በኩል በተከናወነው ነገር እንደለቀቀልን ብርሃን ስናገኝ፣ እግዚአብሔር በአምልኮአችን እጅግ ይደሰታል።
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ በእውነት ላይ የተመሠረተ፣ በኢየሱስ ማንነት ዙሪያ የሚያተኩርና እርሱን ማዕከል
የሚያደርግ ነው። ኢየሱስ እውነት ነው (ዮሐንስ 14፡6)። እንዲሁም ቃሉ ሕይወት ሰጭና እውነት ነው (ዮሐንስ 6፡63)።
አምልኮአችን እውነት በሆነው በኢየሱስና እውነት በሆነው ሕያው ቃሉ ላይ ተመስርቶ ሲከናወን፣ ሰዎች ከጥማታቸው
ይረኩበታል፤ እግዚአብሔርም ደስ ይሰኝበታል (ዮሐ 14፡4)። ሀልዎቱንም በቅርበት እንለማመዳለን። እግዚአብሔርን ደስ
በሚያሰኝ አምልኮ ውስጥ በስብከትና በትምህርት አማካይነት ሕይወት ሰጭ የሆነው የቃሉ ውኃ በነፃ የሚፈስበት የእውነት
ምንጭ አለ (ዮሐንስ 4፡14)። የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ሰው ሁሉ በእውነትና በመንፈስ እንዲሰግዱለት ነው (ዮሐንስ 4፡
23)። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምልኮ ከሳምራዊቱ ሴት ጋር ያደረገው ንግግር በታወቁ ኃይማኖታዊ ቦታዎች ማምለክ
እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኘው አምልኮ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር የሚመለከው
በእውነትና በመንፈስ ነው። ይህም እውነት ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰበት፣ የኃጢአት ሥርየት ያስገኘበት ሞትና ትንሳኤው ነው።
ኢየሱስ ለሳምራዊቱ ሴት አብ ጥንታዊ የአምልኮ መንገዶችን ሁሉ የሚተውበት “ጊዜ ይመጣል” ሲል ገለጸላት። በመቀጠል
“አሁንም ሆኗል” አላት። እግዚአብሔር በጥንቱ ፈንታ ኢየሱስን ለዓለም ሰጥቷል። እርሱንም ስሙት ተብለናል። እርሱን በሕያው
ቃሉ በኩል ስንሰማው በአምልኮአችን እግዚአብሔር ይበልጥ ይደሰታል። ይህንን በማወቅና በመረዳት እናመልከው ዘንድ ሁሉን
የሚችል አምላክ ጸጋውን ይስጠን። መልካም የልደት በዓል!!!
ወንድም ነቢዩ ኢሳይያስ በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የመሐልና ምዕራብ አጥቢያ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪና የአዲስ
አበባ ክልል የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቨርጂንያ በምትገኘዋ አንጾኪያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት

አምልኮና የአምልኮ መልክ


በገዛኸኝ ሙሴ
[የመጨረሻው ክፍል]

_____________________________________
የግል አምልኮ ማለት ሰው አየኝ አላየኝ እኔ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ነኝ የሚል እምነት ይዞ መመላለስ ነው። እንዲህ ሲሆን
ሕይወት አንድ ረዥም አምልኮ ሆነች ማለት ነው፡፡
አምልኮ ምንድነው?አምልኮን በቅጡ ለመረዳት ከሁለት ከፍሎ ማየቱ ይመረጣል፡፡ አምልኮ ቢያንስ ከሁለት ትልልቅ ምድቦች ይ
ከፈላል፡፡ የግል አምልኮና የጉባኤ አምልኮ ተብሎ፡፡ እስቲ የሁለቱን ብያኔ እንመልከት፡፡
የግል አምልኮ። በቀን ለ 24 ሰዓት፣ በሳምንት ለ 7 ቀናት፣ በዓመት ለ 365/366 ቀናት በሁሉም ቦታ በእግዚአብሔር ፊት
እንዳለን በማወቅና በመረዳት የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ ይህን ስናሳጥረው፡- የግል አምልኮ ሁል ጊዜ በሁሉም ቦታ በእግዚአብሔር
ፊት እንዳለን በማወቅና በመረዳት የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ ለግል አምልኮ ጥሩ ግንዛቤ ካላቸው የብሉይ ኪዳን ወጣቶች መካከል
ዮሴፍ አንዱ ነው፡፡ የጲጢፋራ ሚስት ላቀረበችለት የነውር ግብዣ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢዓት እሠራለሁ›› (ዘፍ 39፡
9)? የሚል ቆፍጣና ምላሽ ነው የሰጣት፡፡ ዮሴፍ ከእስራኤል ምድር ርቆ፣የእስራኤል አምላክና የእስራኤላውያን አምልኮ በማይ
ታወቅበትና ከእርሱ በስተቀር ማንም ዕብራዊ በሌለበት በግብፅ ምድር ቢገኝም እንኳን ያህዌ በአንድ ጊዜ በሁሉ ቦታ እንደሚገኝ
እርሱም በዚህ ቅዱስ አምላክ ፊት ሁል ጊዜ እንዳለ ያምን ነበር፡፡ እናም የግል አምልኮ ማለት ሰው አየኝ አላየኝ እኔ ሁል ጊዜ በእ
ግዚአብሔር ፊት ነኝ የሚል እምነት ይዞ መመላለስ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሕይወት አንድ ረዥም አምልኮ ሆነች ማለት ነው፡፡
የጉባኤ አምልኮ። የጉባኤ አምልኮ አማኞች በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት፣ ለተወሰኑ ሰዓታት፣ በተወሰኑ ቦታዎች (እንደ ቤተ ክርስ
ቲያን ባሉ) በአንድነት በመሆን እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት፣ እርስ በርሳቸው የሚተናነጹበትና ለዓለም ምስክርነታቸውን የ
ሚሰጡበት አገልግሎት ነው፡፡
የግል አምልኮ የጉባኤ አምልኮ መሠረት ነው፡፡ የግል አምልኮ ከሌለ የጉባኤ አምልኮ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የግል አምልኮ የጉባኤ አ
ምልኮን አይተካም፡፡ የጉባኤ አምልኮም የግል አምልኮን አይተካም፡፡ ለጤናማ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁለቱንም በሚዛናዊነ
ት መያዝ ያስፈልጋል፡፡
የብዙ መሪዎችና አገልጋዮች ትልቁ ትኩረት የጉባኤ አምልኮው ነው፡፡ ምእመናን ልብሳቸውንና ጸባያቸውን አሳምረው ለሰንበቱ
አምልኮ ብቅ ካሉ፣ ዝማሬውንና ስብከቱን ከተከታተሉ፣ ዐሥራታቸውን፣ መባቸውንና የፍቅርና የሌላም ስጦታቸውን ከሰጡ ም
እምናንም አገልጋዮችም ትልቁን ኃላፊነታቸውን የተወጡ ይመስላቸው ይሆናል፡፡ በእርግጥ በእሑዱ የጉባኤ አምልኮ ወቅት በብ
ዙ መቶ ወይም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አምልኮ አዳራሽ ሲገቡ ሲያይ ልቡ የማይሞቅ መጋቢ አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ መጠየ
ቅ ያለበት ትልቅ ጥያቄ ግን ይህ ብዙ ሕዝብ በአዘቦቱ ቀናት በግልና በሥራ ሕይወቱ፣ በቤቱ፣ በጎረቤቱ፣ በመሥሪያ ቤቱ፣ በንግዱ
ሥራ እንዴት ከርሞ ነው የመጣው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አገልጋዮች የምዕመናናቸውን የአዘቦት ሕይወት ምን ያህል ያውቃ
ሉ? ወይስ ዘመኑ የዲሞክራሲ ስለሆነ ምእመናን እሑድ ብቅ ይበሉ እንጂ የግል፣ የቤት፣ የመስሪያ ቤት ሕይወት የራሳቸው ጉዳ
ይ ነው? ከቶ እንዲህ ሊሆን አይገባም፡፡
መጀመሪያ የመጠቀስ መርሆ/ሕግ። ቃለ እግዚአብሔር የሁሉ መፈተኛ ነውና ከላይ ያነሳነውን ነገር ቃሉ
ይደግፈዋል? በእርግጥ! መጀመሪያ በመጠቀስ መርሆ መሠረት እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ በአቤልና በቃየን የቀረበለትን
መሥዋዕት አስመልክቶ የሰጠው ምላሽ ዛሬም እግዚአብሔር የሚቀበለውን አምልኮ አስመልክቶ ትልቅ መሠረታዊ መርሆ ይሰ
ጠናል፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ ለእግዚአብሔር የቀረበለትን (የጉባኤ?) አምልኮ በሚመለከት ቃለ አግዚአብሔር የሰጠው አስተያየት
የሚከተለው ነው፡-
‹‹እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም›› (ዘፍ 4፡4)፡፡
በዚህ ቦታ ላይ አምልኮን አስመልክቶ ቃለ እግዚአብሔር የሚሰጠንን መሠረታዊ መርሆ የምናገኘው ‹‹እግዚአብሔር የአቤልን
መሥዋዕት ተቀብሎ የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለበት ምክንያት ምንድነው?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ስናገኝ ነው፡፡ አንዳን
ዶች ትኩረታቸውን መሥዋዕቱ ላይ ያደርጋሉ፡፡ እንዲያውም የቃየን መሥዋዕት የደም መሥዋዕት ስላልነበረ ነው በእግዚአብሔ
ር ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘው የሚል መልስ ያቀርባሉ፡፡ የሆነ ሆኖ እግዚአብሔር በቅድሚያ የተመለከተው ያቀረቡትን መሥዋዕ
ት ሳይሆን ሕይወታቸውን ነበር፡፡ ቃሉ ይህን ይላል? አዎ!
‹‹እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም›› ይላል፡፡ ይህን ኃይለ
ቃል ስናነብ ብዙ ጊዜ ልብ የማንለው አንድ ወሳኝ መስተጻምር አለ፡፡ ይህም ‹‹እና›› የሚለው ነው፡- ወደ አቤል እና ወደ መሥዋ
ዕቱ…ወደ ቃየን እና ወደ መሥዋዕቱ፡፡ እናም እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት የተቀበለው በቅድሚያ የአቤልን ሕይወት ስለ
ተቀበለ ነው፡፡ እግዚአብሔር የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለው በቅድሚያ የቃየንን ሕይወት ስላልተቀበለ ነው፡፡ ከዚህ የምናወጣ
ው መርሆ እነሆ፡-
‹‹እግዚአብሔር መሥዋዕትን የሚቀበለው መሥዋዕት አቅራቢውን ሲቀበል ነው፤ መሥዋዕት አቅራቢውን ካልተቀበለ እግዚአብ
ሔር መሥዋዕቱን አይቀበልም፡፡›› እግዚአብሔር አምልኮን የሚቀበለው አምላኪውን ሲቀበል ነው፡፡ አምላኪውን ካልተቀበለ እግ
ዚአብሔር አምልኮውን አይቀበልም፡፡ እግዚአብሔር ዝማሬን የሚቀበለው ዘማሪውን ሲቀበል ነው፤ ዘማሪውን ካልተቀበለ እግዚ
አብሔር ዝማሬውን አይቀበልም…፡፡
ይህ መርሆ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ጥቂት ጥቅሶችን ለአብነት እንጥቀስ፡፡ በ 1 ኛ ሳሙኤል 15፡17 ላይ
ሳሙኤል ለሳዖል ‹‹እግዚአብሔር ቃሉን በሚሰሙት ሰዎች የሚደሰተውን ያህል በሚታረድና በሚቃጠል መሥዋዕት ደስ ይለዋ
ልን?›› መልሱ አይለውም ነው፡፡ እንዲሁም በኢሳይያስ 1፡10 ላይ የየዕለቱ ኑሯቸውና የሰንበቱ አምልኳቸው ለየቅል የሆነው
ን ሕዝቡን እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፡-
‹‹የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?...መባቻችሁን፣ ሰንበታችሁን፣ በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድም…መባቻችሁንና
በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ ልታገሳቸውም ደክሜያለሁ…›› ምናልባት ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ት
ጠይቁ ይሆናል፡፡ መልሱ ቁጥር 16 ላይ ይገኛል፡-
‹‹እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል፡፡ ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተ
ዉ፤ መልካም መሥራትን ተማሩ…›› ወደ ሌላ ጥቅስ እንሸጋገር፡፡ ሆሴዕ 6፡6
‹‹ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና›› ይላል፡፡ እንዲሁም በአሞፅ
5፡21 ላይ ‹‹ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ፤ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤያችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡ … የዝማሬህን
ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም፡፡ ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፤ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍ
ሰስ›› ይላል፡፡ በሚልክያስ ዘመንም የቤተ መቅደሱ የሰንበት አምልኳቸውና የአዘቦቱ ኑሯቸው ፈጽሞ ተቃራኒ ስለ ነበረ እግዚአብ
ሔር ‹‹ምርር ብሎት›› ይመስላል እንዲህ ይላቸዋል፡-
‹‹በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ (የቤተ መቅደሱን) ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናን
ተ ደስ አይለኝም፤ ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም›› (ሚል 1፡10)፡፡
ጌታ ስለ እኛ ዘመን አምልኮ እንዲናገር ዕድል ብንሰጠው ምን ይል ይሆን? የመነቃቂያ ኮንፍረንሶቻችሁን፣ ራሳችሁን የምታዝና
ኑባቸውን የሙዚቃ ኮንሰርቶቻችሁን፣ የኪቦርዳችሁንና የጊታራችሁን፣ የሳክስፎናችሁንና የድረማችሁን ድምፅ አላደምጥም፡፡ ባ
ዶ ጩኸትና ጭፈራችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፡፡ ይልቁን በሳምንቱ ኑሯችሁ በጽድቅ፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በ
ይቅርታና በፍቅር፣ በመካከላችሁ ላሉት ችግረኞች በመቁረስና በመቆረስ አገልግሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ዝማሬያችሁን፣ ሽብሸባችሁን፣
የሞቀ የደመቀ ሙዚቃችሁን አቅርቡልኝ…የሚለን መስለኛል፡፡ በሳምንት ስድስት ቀን በዓለም ውስጥ እንደ ዓለማውያን ስንኖር
ሰንብተን፣ እግዚአብሔር ተለዩ ካለን ነገር ሳንለይ፣ እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን ሳናደርግ ቆይተን በሳምንት አንድ ቀን በምናደ
ርገው አምልኮ ብለን በምንጠራው ፐርፎርማንስ/ ኢንተርቴይመንት እግዚአብሔርን ልንሸነግለው አንችልም፡፡ እግዚአብሔር የ
ብሉይ ኪዳን አምላኪዎችን ከሕይወትና ከኑሮ የተፋታ አምልኮ አልቀበልም ካለ የእኛን የአዲስ ኪዳን አምላኪዎችን ከቶ እንዴ
ት የሚቀበል ይመስለናል?

የአምልኮ መልክ ምንድነው?


የአምልኮ መልክ ማለት አምልኮ የሚመስል ግን ያልሆነ ማለት ነው፡፡ የአምልኮ መልክ የሚለውን ቃል የምናገኘው ሐዋርያው ጳ
ውሎስ የመጨረሻውን ዘመን ምልክቶች በሚዘረዝርበት በ 2 ኛ ጢሞቲዎስ 3፡6 ላይ ነው፡፡ በዚያ ስፍራ ጳውሎስ የመጨረሻ
ውን ዘመን ክፉ የሚያደርጉ ምልክቶችን መዘርዘር ይጀምራል፡- ‹‹ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ…
ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፤ ይሆናሉ›› ካለ በኋለ ‹‹የአምልኮ መልክ አላቸው፣ ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ
ራቅ›› ይላል፡፡ ሰው ራሱን፣ ገንዘብንና ተድላን ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚወድ ከሆነ የሚያመልከው እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሱ
ን ነው፡፡ ታላቁ ትእዛዝ እግዚአብሔርን በፍጹም ሁለንተናህ አምልክ/ ውደድ የሚል ነው፤ ሰይጣን ለ 21 ኛው መቶ ክፍለ ዘመ
ን ሰው የሚሰብከው ስብከት ራስህን በፍጹም ሁለንተናህ ውደድ የሚል ነው፡፡
እግዚአብሔር በዘፍጥረት 4 በአቤልና በቃየን ከቀረበለት መሥዕት ጀምሮ የአምልኮን መልክ እንደ ተቃወመ አለ፡፡ የአምልኮ መ
ልክ ማለት ይዘት የሌለው ሜዳዊ እንቅሥቃሴ ብቻ ማለት ነው፡፡ ይዘት ስንል ሌላ ሳይሆን የአምላኪው ሁለንተና ማለት ነው፡፡
አምልኮን አምልኮ የሚያደርገው የአምላኪው ሁለንተና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምልኮን የሚቀበለው ከሰው ውስጣዊ ማንነት እን
ጂ ከሜዳዊው ፐርፎርማንስ አይደለም፡፡ የአምልኮ መልክ ኃይል አልባ የሆነበት ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ‹‹የአምልኮ መልክ አላቸው፤
ኃይሉን ግን ክደዋል፡፡››
አንዳንድ ሰዎች ‹‹በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ሞልቷል፤ የጠፋው ቅድስና ነው›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ አባባሉ ትክክል ባይሆን
ም ምን ለማለት እንደ ፈለጉ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ቦታ አምልኮ የተባለው ውዳሴ፣ ማለትም ዝማሬ፣ ሽብሸባ፣ ሙዚቃ…ነው፡፡ በእ
ርግጥ እያሸበሸቡ፣ እየሞዘቁ፣ እየዘመሩ አለመቀደስ ይቻላል፤ እያመለኩ ግን አለመቀደስ አይቻልም፡፡ ማምለክ ማለት ወደ ቅዱ
ስ አምላክ መቅረብ ማለት ከሆነ ቅዱሱን አምላክ እያመለኩ አለመቀደስ አይቻልም፡፡ አምልኳችን ወደ ቅድስና የማያመጣን ከ
ሆነ አምልኮ ብለን ልንጠራው አንችልም፡፡ ወይም እያመለክን ያለነው ቅዱሳን ፍጥረታት በቅዱስነቱ ፊት መቆም ፈርተው በሁ
ለት ክንፎቻቸው፣ ፊታቸውን፣ በሁለት ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን ሸፍነው በሁለት ክንፎቻቸው እየበረሩ ያለ ማቋረጥ ቅዱስ
! ቅዱስ! ቅዱስ! በሚሉት ቅዱስ ነበልባል በሆነ አምላክ ፊት መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ ሰዎች የሚያመልኩትን ነገር ይመስላ
ሉና እያመለኩ ነኝ እያሉ በእርኩሰት የሚመላለሱ ካሉ የሚያመልኩት የሚቀድሰውን ሳይሆን የሚያረክሰውን ርኩስ መንፈስ ነ
ው ማለት ይቻላል፡፡
እናም እውነተኛው ክርስቲያናዊ አምልኮ ኃይል አለው፡- ከኃጢአትና ከኃጢአተኝነት፣ ከዓለምና ከዓለማዊነት ሕይወት የሚያ
ወጣ ኃይል አለው፡፡ አምልኳችን ኃይል ከሌለው አምልኮ ሳይሆን የአምልኮ መልክ ነው፡፡ ከቃሉ እንዳየነው የአምልኮ መልክ ውስጥ
ኃይል የለም፤ እውነተኛ አምልኮ ውስጥ ግን ኃይል አለ፡፡
ይህን ሰፊ ርእስ እንዲህ በአንድ መጣጥፍ አንጨርሰውም፤ ሐሳቦችን እናጭራለን እንጂ፡፡ በዚህ ዘመን ስለ ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ
ብዙ ችግሮች ብዙ ሲባል እንሰማለን፡፡ የችግሩ ሥር እታች ድረስ ተሂዶ ቢመዘዝ የእውነተኛ አምልኮ መጓደል መሆኑን ማወቅ ይ
ቻላል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ሲያመልክ ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር ይኖራል፤ ታጋሽ ይሆናል፣ ለጋስ ይሆናል፣ ይቅር ባይ ይሆናል፣ ት
ጉ ይሆናል፣ ከዓለምና ከዓለማዊነት ይወጣል፤ በጽድቅና በቅድስና ሕይወት ይመላለሳል፡፡ ወደ እውነተኛ አምልኮ መመለስ ማለት
ሁለንተናዊ በረከትና ሙላት ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር መመለስ ማለት ነው፡፡ እስቲ ከኢያሱ ጋር ይህን ውሳኔ እንወስን፡-
‹‹…የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፡፡ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› (ኢያሱ 24፡15)፡፡

ሕያው አምልኮ ለሕያው አምላክ!

የአምልኮ መርሖዎች (ማቴ. 6፡1-18)


Leave a Comment / የማቴዎስ ወንጌል / By ወንጌል በድረ-ገጽ
ዮሐንስ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነበር። እርሱም በጸሎቱ የታወቀ አገልጋይ ነበር። በየእሑዱ
«ሃሌሉያ» እያለ ረዥም ጸሎት ያቀርባል። ዮሐንስ በረዥም ጸሎቱ መንፈሳዊነቱን ለሰዎች እንደሚያሳይ ያስብ
ነበር። ብዙነሽ ክርስቲያን ነጋዴ ነበረች። አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያኗ ለአዲስ የሕንጻ ግንባታ ገንዘብ ታሰባስብ ነበር።
ብዙነሽ መሪው በምእመናኑ ፊት እያንዳንዱ ሰው የሰጠውን የገንዘብ ልክ እንደሚናገር ታውቅ ነበር። ስለሆነም
ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቃ ብዙ ስጦታ ይዛ ገባች። ለእግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ ለመስጠት ሰዎችን ማስደነቅ መቻሏ
ያስደስታታል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ነገሮችን በራስ ወዳድነት አመለካከት ማድረግ የሚቀልለው እንዴት ነው? ለ)
መንፈሳዊ የሚመስሉ ነገሮችን የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ባለን ፍላጎት ልናደርግ የምንችልባቸውን መንገዶች
ዘርዝር።

ኤርምያስ በ 17፡9 ላይ የሰው ልብ ክፉና ተንኮለኛ ማንም የማያውቀው እንደሆነ ይናገራል። በልባችን እራሳችንን
ከምናታልልባቸው እጅግ አደገኛ መንገዶች አንዱ አምልኮ ነው። የሐሰት አምልኮ ሊመጣ የሚችለው የውሸት ጣዖት
በማምለክ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ባለማመን ብቻ አይደለም። ለእግዚአብሔር ሕዝብ፥ በምናከናውናቸው
የአምልኮ ተግባራት ሁሉ የሐሰት አምልኮ መፈጸሙ ቀላል ነው። ስለሆነም ክርስቶስ የተሳሳተ አመለካከት በሚኖረን
ጊዜ፥ ሊከሰቱ የሚችሉትን የተለመዱ የአምልኮ ተግባራት ገልጾአል። እነዚህ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ለሌሎች
መንፈሳዊ መስለን ለመታየት በምንፈልጋቸው ጊዜያት ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ማምለክ አቁመናል ማለት ነው።
በኳየር (በኅብረ ዝማሬ) ውስጥ የምንዘምረው የኳየር ልብሳችንን ለማሳየት፥ ዓይኖቻችንን በመጨፈን ወደ ሰማይ
በማየትና በመወዛውዝ መንፈሳዊነታችንን ለማሳወቅ፥ ወይም ሃሌሉያ እያልን በመጮህ የሕዝቡን ስሜት
ለማነሣሣት ከሆነ፥ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የማይጠቅሙ ይሆናሉ። እውነተኛ አምልኮ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ
የልባችን መግለጫ ነው። ከዚህ ውጭ የምናደርገው ሁሉ የሐሰት አምልኮ ነው።

በክርስቶስ ዘመን ሌሎችን ለማስገረም የሚካሄዱ የአምልኮ ተግባራት በፈሪሳውያን ሕይወት ውስጥ ይታዩ ነበር።
አለባበላቸው፥ በሕዝቡ ፊት የነበራቸው አክብሮትን ሰዎች ልብ ብለው እንዲያዩዋቸው መፈለጋቸው ሁሉ
አምልኳቸው እንዲበላሽ አድርገዋል። ክርስቶስ እነዚህን አደጋዎች በመረዳት፥ ደቀ መዛሙርቱ አምልኳቸው
ተቀባይነትን እንዲያገኝና ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው «ምጽዋታችሁን» በፊታቸው እንዳታደርጉ
ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ፊት ዋጋ የላችሁም።» ሲል አስጠነቀቃቸው ክርስቶስ
«ምጽዋታችሁን» ሲል በእግዚአብሔር ፊት «ትክክለኛ ነገሮችን» እንድናደርግ ማሳሰቡ ነው።

1. ለድሆች በመመጽወት ማምለክ (ማቴ. 6፡1-4)። ለድሆች መስጠት እግዚኣብሔር ከልጆቹ ሁሉ የሚጠብቀው
ተግባር ነው። የወንጌል አማኝ ክርስቲያኖች፥ ሌሎች ወገኖች የሚሰጡበትን ምክንያት በመንቀፍ የሕይወት
ማዕበል ለሚያንገላታቸው ወገኖች ርኅራኄን ማሳየት ኣቁመዋል። ነገር ግን ከመስጠት የሚበልጠው
በምንሰጥበት ጊዜ በልባችን ውስጥ ያለው አመለካከት ነው። በመስጠት ዙሪያ አራት አመለካከቶች
ይንጸባረቃሉ።
በመጀመሪያ፥ «ለድሃ ብሰጥ እግዚአብሔር እኔን ወደ መንግሥተ ሰማይ ያስገባኛል፤ ኃጢአቴንም ይሰርዝልኛል»
የሚል አመለካከት አለ። አንድ መልካም ነገር በማድረግ ኃጢአታችንን ልናስወግድ ወይም ወደ መንግሥተ ሰማይ
ልንገባ አንችልም። አንድ ሰው የኃጢአትን ይቅርታ አግኝቶ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሊያገኝ የሚችለው፥
የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።

ሁለተኛው፥ በመስጠት እግዚአብሔር ሀብታም እንዲያደርገን ለማስገደድ እንችላለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኣሉ።
«ለእግዚኣብሔር ብዙ ገንዘብ ስጠው። ይህም እግዚአብሔር ከሰጠኸው የበለጠ እንዲመልስልህ ያደርገዋል።
ለእግዚአብሔር 100 ብር ብትሰጠው፥ እርሱ 1000 ብር ይሰጥሃል። ብዙ ከሰጠኸው ሀብታም ትሆናለህ።»
እግዚአብሔር በትክክለኛ አመለካከት ከሰጠነው ይባርከናል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚሰጠን
የበረከት ተስፋ የግድ በምድር ላይ ብዙ ገንዘብ የምናገኝበት ሳይሆን፥ በመንግሥተ ሰማይ የምንቀበለው ነው።
ከእግዚአብሔር ዘንድ እንድ ነገር ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ ስጦታ የራስ ወዳድነት ተግባር ነው። ይህ በርኅራኄ
ሳይሆን አንድን ነገር በአጸፋው ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር የሚያከብረው ዓይነት ስጦታ
ኣይደለም።
ሦስተኛው፥ «ሌሎች አይተው በችሮታዩ ሊያመሰግኑኝ በሚችሉበት መንገድ ለድሃ መስጠት አለብኝ» የሚሉ ሰዎች
አሉ። ይህ የርኅራኄ መግለጫ ሳይሆን፥ በሌሎች ፊት ታዋቂ ለመሆን የሚደረግ ስጦታ ነው። ክርስቶስ የዚህ ዓይነቱ
መስጠት የሰዎችን ምስጋና ከማስከተል ያለፈ፥ ሌላ ማዕረግ እንደማያስገኝ ተናግሯል። ይህ እግዚአብሔርን
የማያስደስት በመሆኑ፥ ከእርሱ ዘንድ ምንም ምሥጋና አያስገኝም። ፈሪሳውያን የሚያደርጉት ይህንኑ ነበር። በቤተ
መቅደስ ገንዘብ በሚሰጡበት ጊዜ ሕዝቡ ምን ያህል እንደሰጡ እንዲያውቁላቸው ይፈልጉ ነበር። እንዲያውም
አንዳንዶች ሰዎች እንዲያዩላቸው መለከት እየነፉ ይሰበስቧቸው ነበር።

አራተኛው፥ ከርኅራኄና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ የተነሣ ለተጎዱ ሰዎች የሚበረከት ስጦታም አለ። ይህ ስጦታ
በሚለገስበት ጊዜ ተመልካች ስለመኖር አለመኖሩ ሳንጨነቅ የምናደርገው ነው። መንፈሳዊ ልብ ለእውቅና
አይጣደፍም። ስሙ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጠራት አለመጠራቱም አይጨነቅም። ክርስቶስ በመስጠት ጊዜ
የሚከሰተውን አደጋ በማጤኑ፥ ቀኝ እጃችን የሚሰጠውን ግራው እንደማያውቅ ያህል በምሥጢር እንድናደርገው
እዝዞናል። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የዚህ ዓይነቱ ልግስና ብቻ ነው። እግዚአብሔር ትልቅ ግምት
የሚሰጠው የዚህ ዓይነቱን ልግስና ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርሱን እንድናገለግለው በምድር ብዙ ሀብት
በመስጠት ቢባርከንም፥ ከሁሉም የሚበልጠው በሰማይ የሚገኘው በረከት ነው። (አሁንም ቢሆን በሰማይ ትልቅ
ስጦታ ለማግኘት ስንል፥ በራስ ወዳድነት ዓላማ አለመስጠታችንን ማረጋገጥ አለብን። እግዚአብሔር ከሰው ምንም
ነገር ለማግኘት ሳይሆን፥ ከፍቅሩና ከርኅራኄው የተነሣ እንደሚሰጥ፥ የእኛም ስጦታ ከርኅራኄ ልብ ሊመነጭ
ይገባል።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በእነዚህ አራት መንገዶች ሊሰጡ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ግለጽ። ለ) በቤተ
ክርስቲያንህ ሰዎችን ወደ ተሳሳቱ አቅጣጫዎች ሊመሩ የሚችሉ እንዳንድ ልምምዶች ምንድን ናቸው? ሐ)
ምእመናን እግዚአብሔርንና ሰዎችን በመውደዳቸው ምክንያት፥ ከራስ ወዳድነት በጠራ መንፈስ በልግስና እንዲሰጡ
ለማገዝ፥ ሊለወጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

2. አምልኮ በጸሎት (ማቴ. 6፡5-15)። ጸሎት ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል? ክርስቶስ፥
«አዎን» ብሏል። ክርስቲያኖች የአምልኮ ግብዝነታቸውን ከሚያሳዩባቸው ዐበይት መንገዶች ኣንዱ ጸሎት ነው።
ክርስቶስ ካስተማራቸው ዐበይት የአምልኮ ተግባራት አንዱ ጸሎት ነው። ብዙ ሰባኪዎች ሰዎችን ለማስደሰት
ሲሉ ረዥም በሆኑ ወይም በስሜት ጸሎቶች ይጠቀማሉ። እንዲሁም ለስብከት የጸሎት ጊዜን ይጠቀማሉ።
ጸሎት ከሰዎች ጋር ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት መሣሪያ ነው። ሌሎች መሪዎች የተወሰኑ
ቃላትን በመደጋገም መንፈሳዊነታቸውን ለማሳየት ይፈልጋሉ። አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ወይም የክርስቶስን
ስሞች ይደጋግማሉ። ሌሎች ደግሞ ሃሌሉያ የሚለውን ቃል ይደጋግማሉ።
በኢየሱስ ዘመን ፈሪሳውያን መንፈሳዊነታቸውን በጸሎት ለማሳየት ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም በአምልኮ ዕለት ወደ
ምኩራብ ገብተው ከፊት በመቀመጥ ረዥም ጸሎቶችን ያቀርባሉ። ያም ባይሆን ሕዝብ ወደሚሰበሰብባቸው
አካባቢዎች ሄደው ሁሉም ሰው እስኪሰማቸው ድረስ፥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጸልያሉ። ክርስቶስ፥ «ይኼ
ምን እርባና ኣለው?» ሲል ነቅፎአቸዋል። ብድራታቸው የእግዚአብሔር ሳይሆን፥ የሰዎች አድናቆት ነበር።

የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑ የጸሎት አመለካከት ፍጹም የተለየ ሊሆን ይገባል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር
የምናደርገው ንግግር ስለሆነ፥ የሰዎች መኖር አለመኖር ሊያሳስበን አይገባም። (ክርስቶስ በኅብረት መጸለይ
የለብንም ኣላለም። ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ስፍራዎች ጸልየዋል። ነገር ግን ክርስቶስ
በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ አመለካከታችን ትክክለኛ መሆን እንዳለበት አስገንዝቧል። ኢየሱስ ተከታዮቹ
በትክክለኛ መንገድ እንዲጸልዩ የተወሰኑ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል።
ሀ. ክርስቶስ ጸሎትን ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ለመጠበቅ፥ አብዛኛውን ጸሎታችንን እግዚአብሔር ብቻ
በሚሰማባቸው ስውር ስፍራዎች እንድናደርግ አስተምሮናል። እግዚአብሔር ከመናገራችን በፊት ጸሎታችንን
ስለሚያውቅ፥ ስለ ጸሎታችን መናገሩ የግድ አስፈላጊ አይደለም። ጮክ ብሎ መጸለዩ ተጨማሪ በረከት አያስገኝም።
ጮክ ብለን መጸለያችን እግዚአብሔር በተሻለ ሁኔታ እንዲያደምጠን አያደርገውም። እግዚአብሔር ደንቆሮ ስላልሆነ
መጮኽ አያስፈልገንም። ጮክ ብለን የምንጸልይ ከሆነ፥ አነሣሽ ምክንያታችንን መመርመር ይኖርብናል። ክርስቶስ
ከእርሱ ጋር ከተነጋገርን፥ ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን ተናግሯል።

ለ. ጸሎት በቃላት አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለሆነም ቀጥተኛ የሆነ አነጋገር ለጸሎት
ተስማሚ ነው። ክርስቶስ ቀጥተኛ ከሆነ የጸሎት ቃላት ውጪ ሳይታሰቡ የሚወረወሩ ቃላት ለጸሎት ሊያገለግሉ
እንደማይገባ አስጠንቅቋል። ስሙን በመደጋገማችን ወይም ሃሌሉያ እያልን በመጮኻችን ብቻ እግዚአብሔር
ጸሎታችንን በተሻለ ሁኔታ እያደምጥም። ይህንን የምናደርግ ከሆነ፥ «ለምንድን ነው የማደርገው?» ብለን ራሳችንን
መጠየቅ አለብን። ያለልማድ የምንጠቀምባቸው ቃላት ብዙውን ጊዜ ለሌሎች እንደምንጸልይ ወይም ሳናስብ
በልማድ እንደምንጸልይ ያሳያሉ።

ሐ. ረዥም ጸሎት የግድ አፈላጊ አይደለም። ክርስቶስ ብዙ ቃላት መደጋገም እንደማያስፈልግ ገልጾኣል። ብዙ
በጸለይን ቁጥር ትክክለኛ ጸሎት እናደርጋለንን? አናደርግም። ጥርት ባለ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንና
ለእግዚአብሔር ለመናገር የምንፈልጋቸውን ነገሮች የሚገልጽልን የሁለት ደቂቃ ጸሎት በቂ ነው። በተለይ በሌሎች
ሰዎች ፊት ረጅም ጸሎት የምንጸልይ ከሆነ፥ ለሰዎች ሳይሆን ለእግዚኣብሔር እየጸለይን መሆናችንን በልባችን
መመርመር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ባስጠነቀቀባቸው በእነዚህ መንገዶች የጸለይህባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ።

እነዚህ ደቀ መዛሙርት ጸሎት ምን እንደሆነ በትክክል እንዲረዱ ለማገዝ፥ ክርስቶስ የጸሎት መመሪያ ሰጥቷቸዋል።
ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው የአባታችን ጸሎት፥ (እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የደቀ መዛሙርት ጸሎት) ቤተ
ክርስቲያን የአምልኮ ፕሮግራም ለመፈጸም እንድትጠቀምበት አልነበሩም። ጸሎቱ የተሰጠው እንዴት ልንጸልይ
እንደሚገባን ለማሳየት ነበር። በዚህ ጸሎት ውስጥ አስፈላጊው ነገር በውስጡ የተጻፉት ቃላት ሳይሆኑ፥ በቃላቱ
ውስጥ የተካተቱት አመለካከቶች ናቸው። በዚህ የጸሎት መመሪያ በመጠቀም ብዙ ነገሮችን ልንማር እንችላለን።

ሀ. የጸሎት መሠረቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት መረዳት ስለ መሆኑ። አይሁዶች እግዚአብሔርን


«አባታችን» ብለው ሊጠሩት አይችሉም ነበር። እንዲያውም ከክርስቶስ በፊት ማንም ሰው እግዚአብሔርን አባ
አባት በሚል ዓይነት የግል መጠሪያ መጥራቱን የሚያመለክት መረጃ አልተገኘም። («አባ» የሚለው የአማርኛ ቃል
አባትነትን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፥ የፍቅርም መግለጫ ነው – ልክ ትንሽ ልጅ «አባዬ» እያለ እንደሚጠራው)
ማለት ነው። ለአይሁዶች እግዚአብሔር የሩቅ አምላክ ነበር። እርሱ እጅግ ቅዱስ አምላክ በመሆኑ፥ በጸሎት ውስጥ
ስሙን ለመጥራት የሚደፍር አልነበረም። ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር ያን ያህል ሩቅ እንዳልሆነና ጸሎታችውን
ለመስማት እንደሚፈልግ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። እግዚአብሔር ልጁ ኣንዳች ነገር በፍቅርና በመተማመን
ቢጠይቀው እንደሚፈቅድ ሰብአዊ ኣባት ይመስላል።

ለ የጸሉት አነሣሽ ምክንያት የእግዚአብሔር ክብር ነው። ከእግዚአብሔር አንድን ነገር ለመቀበል ጸሎትን ለራስ
ወዳድነት ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ፥ የእግዚአብሔርን ክብር ልንሻ እንደሚገባን ክርስቶስ አስተምሯል።
እግዚአብሔር በሕይወታችን፥ በቤተ ክርስቲያናችንና በዓለማችን እንዲከበር ልንሻ ይገባል። እያንዳንዱ
የእግዚአብሔር ልጅ የሚጸልየው ጸሎት ሁሉ እግዚአብሔርን የማክበር ፍላጎት ሊያንጸባርቅ ይገባል።
ሒ ራእያችን የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋት መሆን ኣለበት። እግዚአብሔር በሰማይ ሆኖ በፍጹማዊ ሥልጣኑ
ስለሚገዛ፥ አልታዘዝህም የሚለው ማንም የለም። ወደ እግዚአብሔር የሚጸልየው ግለሰብ ቁጥጥሩ ምድርንም
እንደሚያካትት መገንዘብ ይኖርበታል። የእግዚአብሔር ግዛት በሚጸልየው ግለሰብ ልብ፥ በቤተ ክርስቲያንና
በዓለም ጉዳዮች ሁሉ ላይ መስፋፋት አለበት። ክፋትና ዓመፅ ባለበት ሁሉ እግዚአብሔር የክርስቶስን አገዛዝ
እንደሚያመጣ ሊናፈቅ ይገባል።

መ. በጸሎት የራስ ወዳድነት አመለካከትን ልናንጸባርቅ አይገባም። ጸሎት የራስ ወዳድነት አመለካከትን ሊያንጸባርቅ
ስለማይገባ፥ መሠረታዊ ያልሆኑትን ነገሮች ከእግዚአብሔር ልንጠይቅ አይገባም። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን
ያስተማራቸው ለሕይወት መሠረታዊ የሆነውን ዕለታዊ እንጀራ እንዲጠይቁ ነበር። የጸሎት ድፍረታችን የሚመጣው
ከእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር ነው። ለሕይወት መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮችን በምንጠይቅበት ጊዜ አነሣሽ
ምክንያቱ የእግዚአብሔር ክብር ሊሆን ይገባል። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የጸሎት ጥያቄያችንን እንደሚመልስ
እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ሠ. የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው፥ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት በንጽሕና መመላለስን ይሻል። ኃጢኣትን
በምንሠራበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅ ሕይወታችንን እናጠራለን። ከሰዎችም ጋር በስምምነት
ለመኖር እንፈልጋለን። የሚበድሉንን ይቅር ማለት አለብን። ይህ አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር
ይቅርታ እኛ ሌሎችን ይቅር ለማለት ባለን ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ሁለት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ
ተናግሯል። የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት የማንፈልግ ከሆነ፥ በልባችን ውስጥ መራርነት እንዳለ ግልጽ ነው።
ስለሆነም እግዚአብሔር ይቅር አይለንም። ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ግንኙነት ከሌለን፥ ጸሎታችን መልስ ስለ
ማግኘቱ ድፍረት ሊኖረን አይችልም። በጸሎታችን ልንገፋ ብንችልም፥ እግዚአብሔር አይሰማንም።

ኣንድ ሰው የሌሎችን በደል ይቅር ለማለት የሚችለው፥ እግዚኣብሔር የራሱን ኃጢአት ይቅር በማለት ያሳየውን
ምሕረት ሲረዳ ብቻ ነው። የልቡን ኃጢአተኛነትና ከእግዚአብሔርም ፍርድ እንጂ በረከትን መቀበል
እንደማይገባው ሲገነዝብ ሌሎችን ይቅር ይላል። ሌሎችን ይቅር ለማለት አለመፍቀድ፥ በልባችን ውስጥ ትዕቢት
መኖሩንና ከሌሎች እንደምንበልጥ ማሰባችንን ያሳያል።

ረ. ልባችንንና የኃጢኣት ዝንባሌውን ለማወቅ መፈለግ አለብን። ስለሆነም በፈተና ጊዜ እግዚአብሔር እንዲረዳን
እንጠይቀዋለን። ይሄኛው የጸሎት ምሳሌ አካል በምሑራኑ ዘንድ ብዙ ክርክሮችን አስነሥቷል።

በመጀመሪያ፥ «ፈተና» የሚለው ቃል በግሪክ ሁለት ትርጉሞች አሉት። ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር


እምነታችንን ለመፈተንና ለማሳደግ የሚጠቀምባቸውን መከራዎችና ችግሮች ያመለክታል። ወይም ደግሞ ሰውን
በኃጢአት ለመጣል የሚደረገውን የሰይጣን ፈተና ሊያመለክት ይችላል። እግዚኣብሔር ኃጢአትን እንድናደርግ
እንደማይፈትነን በያዕቆብ 1፡13 ላይ በግልጽ ስለሚታይ፥ እዚህ ላይ የቀረበው ጸሎት እግዚአብሔር በቀጥታ ወደ
ኃጢአት እንዳይመራን የሚጠይቅ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰይጣንን ጥቃት በመከላከል
ከኃጢአት እንዲጠብቀን ለመለመን የቀረበ ጸሎት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ይህ ጸሎት እግዚኣብሔር
በመከራው ጊዜ ኢየሱስን ከመስቀሉ የመከራ መንገድ እንዲያድነው እንደ ለመነ ሁሉ የምናቀርበው ጸሎት ይሆናል።

(ማስታወሻ፡- በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ክርስቶስ፥ «ፈቃድህ ቢሆን» ብሏል። ምንም እንኳ ይህ የጸሎት
መንፈስ ቢሆንም፥ የጸሎት ኣመለካከታችን ግን መገዛትን ያካተተ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር
የምንፈልገውን ይሰጠን ዘንድ እንድናዝዘው አይፈቅድልንም። ሁልጊዜ እንደ ፍጡራን ሁሉ ከፈጣሪያችን ጋር ያለን
ግንኙነት፥ የመገዛትንና የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጸም የመፈለግን ስሜት ማንጸባረቅ አለበት። ስለሆነም፥
የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ስለማናውቅ ለነገሮች በምንጸልይበት ጊዜ፥ ሁልጊዜ ልመናችን፥ «ጸሎቴ እንደ
ዕቅድህ ከሆነ» ማለት አለበት።ሁለተኛው፥ «ማዳን» የሚለውም ቃል ሁለት ፍቺዎች ስላሉት አከራክሯል። ይህ
ቃል ማንኛውም ዓይነት ክፋትና መከራ ወደ እኛ እንዳይመጣ መከልከልን ሊያመለክት ይችላል። እንደዚሁም
«በመከራ ጊዜ በሰላም ጠብቀን» ማለትም ይሆናል። በ 1 ኛ ቆሮ. 10፡13 ላይ እግዚኣብሔር ሁልጊዜ
የሚያጋጥሙንን ችግሮችና ፈተናዎች የምንጋፈጥበት ኃይል እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። በተጨማሪም
እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ለክርስቲያኖች ለበጎ እንደሚያደርግ ይናገራል (ሮሜ 8፡28)። ስለሆነም ክርስቶስ
ችግሮቻችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድንቀበልና ፈተናውን እንድናልፍ ይፈልጋል። ከዚህም
በስተቀር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተፈለገውን ትምህርት እስክናገኝ ድረስ በእምነታችን እንድንጸና የሚያስፈልገንን
ኃይል ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን እንድንማጠን ያሳስበናል።

ሦስተኛው፥ «ክፉ» የሚለው ቃል ምን ትርጉም ኣለው? በግሪኩ ይህ ቃል «ክፉ» ወይም «ክፉው» ተብሎ
ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ቃሉ ኃጢአትን ወይም ኃጢአትን እንድንሠራ የሚፈትነንን ሰይጣንን ሊያመለክት
ይችላል። ስለሆነም ይህ ጸሎት ድክመታችንን በመናዘዝ፥ ሰይጣን እንድንፈጽም ከሚፈልገው ኃጢአት ለመራቅ
ኃይልን የምንጠይቅበት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጸሎታችን ክፍሎች ሊሆኑ የሚገባቸውን መንፈሳዊ መርሖዎች ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ
መርሖዎች ብዙውን ጊዜ በጸሎትህ ውስጥ የማትጠቀምበት መርሕ የትኛው ነው? ሐ) ከእነዚህ መርሖዎች
ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማይጠቀሙባቸው የትኞቹ ናቸው?

እንደምታስታውሰው፣ «መንግሥት ያንተ ነውና፥ ኃይል ምስጋና ክብርም ለዘላለሙ አሜን» ስለሚለው
የመጨረሻው የጸሎቱ ክፍል፥ ማብራሪያ አልሰጠንም። ለዚህ ምክንያቱ ምሑራን ይህ በመጀመሪያው ጽሑፍ ውስጥ
የሌለና በኋላ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተጨመረ መሆኑን በማመናቸው ነው። ምሑራን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን
ይህንን ጸሎት ወደ ዝማሬ እንደ ለወጠችና በራእይ 5፡13 መሠረት ጸሎቱን ሲጨርሱ ይህንን ሐረግ
እንደጨመሩበት ያምናሉ።

3. በጾም አማካይነት ስለ ማምለክ (ማቴ. 6፡16-18)። ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ይጾማሉ። አንዳንዶች የቤተ
ክርስቲያናቸውን ትእዛዝ ለማክበር ሲሉ በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ይጾማሉ። (ለምሳሌ፥ ፈሪሳውያን ሰኞና
ሐሙስ ቀን ሲጾሙ፥ የኦርቶዶክስ አማኞች ደግሞ ረቡዕና ዓርብ ይጾማሉ።) ሌሎች ደግሞ የተወሰኑ ምግቦችን
ትተው የተቀሩትን እየተመገቡ ይጾማሉ። ሌሎች ደግሞ (ሙስሊሞች በረመዳን ጾም እንደሚያደርጉት) በተወሰኑ
ሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት አንዳንድ ምግቦችን አይበሉም፥ ጨርሰው ምንም ዓይነት ምግብ የማይበሉበት ጊዜ
አለ። ክርስቶስ ስለ እነዚህ ጾሞች የተናገረው ነገር አልነበረም።
ኣይሁዶች ሦስት ዓይነት አጽዋማት (ጾሞች) ነበሯቸው። በመጀመሪያ፥ የመታሰቢያ ጸሎት ነበር። አይሁዶች አሳዛኝ
ታሪኮችን ወይም እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ለእነርሱ የሠራባቸውን ጊዜ እያስታወሱ ከምግብ ርቀው
የሚያከብሯቸው በዓላት ነበሩ። (ለምሳሌ፥ የስርየት ቀን።) ሁለተኛው፥ እንደ ፈሪሳውያን ያሉ አንዳንድ አይሁዶች
በተወሰኑ የሳምንት ቀናት ውስጥ አይመገቡም ነበር። መጀመሪያ ይህ ጾም የታቀደው በእነዚህ ቀናት በጸሎትና
በአምልኮ ላይ እንዲያተኩሩ ለማገዝ ነበር። በኋላ ይህ ወደ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተለወጠ። ሦስተኛው፥ አይሁዶች
ከምግብ ርቀው በግላቸው ይጾሙ ነበር። የግል ጾሞች ዓላማ ግለሰቡ በጸሎት ላይ እንዲያተኩር ለማገዝ ነበር (አስ.
4፡16)። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በጉዳዩ ላይ ለማተኮር የሚጸልየው ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ነበር። ይሁንና
ይህንን ጸሎት ልማድ አድርገው ሥጋቸውን እንደሚያሸንፉና ፈሪሳውያን እንደሆኑ ለማሳየት የሚሞክሩ ወገኖች
ነበሩ።
ብዙ ፈሪሳውያን የተሳሳተ የጾም አመለካከት ነበራቸው። በጸሎት ላይ መሆናቸውን ለሰዎች ለማሳየት ሲሉ የተወሰኑ
ልብሶችን ይለብሱ ነበር። እንዲሁም ፊታቸውን ከመታጠብ ይቆጠቡና እንዲህ ዓይነት ብዙ ተግባራትን ያከናውኑ
ነበር። ፈሪሳውያን ጹዋሚነታቸውን ሰዎች አይተው በመንፈሳዊነታቸው እንዲያከብሩዋቸው ይፈልጉ ነበር።

ክርስቶስ በቀዳሚነት የጠቀሰው ይህንኑ ሦስተኛውን ግላዊ የጸሎት ዓይነት ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ
እንዲጾሙ ቢያበረታታም፥ የግል ጸሎት በሚይዙበት ጊዜ፥ ትክክለኛ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ
ሳያስጠነቅቃቸው አላለፈም። መንፈሳዊነታችንን ለማሳየት ስንል ልንጾም አይገባንም። በምንጾምበት ትክክለኛ
ምክንያት ላይ ለማተኮር እንችል ዘንድ፥ ስለ ጾማችን ማወጅ ሳያስፈልገን በስውር መጾም አለብን (ለምሳሌ፥ ልዩ
ልብሳችንን ሳንለብስና ፊታችንን ሳናኮማትር) ለሌሎች መንፈሳዊነታችንን ሳናሳይ በምንጸልይበት ጊዜ፥
እግዚአብሔር ልባዊ ጸሎታችንን እንደሚያዳምጥ ልንተማመን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ አማኞች የሚጸልዩት ለምንድን ነው? ለ) ይህ ጾም ትርጉም የሌለው ልማድ ሊሆን
የሚችልበትን ሁኔታ በምሳሌዎች አስረዳ። ሐ) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በጾም ሊጠቀም
የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎችን ለማስደሰት ወይም ለመታወቅ ሲባል የሚደረጉ ሌሎች የአምልኮ ተግባራትን
ዘርዝር። ለ) ለእግዚኣብሔር ብቻ በሚቀርብና ሰዎችን ለማስደሰት በሚካሄድ ኣምልኮ መካከል ያለው ልዩነት
ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው
መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

You might also like