Professional Documents
Culture Documents
ቅዱስ ትውፊት
አስቀድመን እንግዲህ ቀጥታ ትውፊት የሚለውን ነገር ለመረዳት ያህል በአጭሩ ቅብብሎሽ ማለት ነው። ለምሳሌ የሆነ ትምህርት
ከሆነ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ በተለያየ መንገድ እየተላለፍ ሲሄድ ይሄ ቅብብሎሽ ትውፊት ይባላል። ትውፊትን በዋናነት
ለሁለት መክፈል እንችላለን.. ይህም የእግዚአብሔር መገለጥ ያለበት ቅዱስ ትውፊት እና የእግዚአብሔር መገለጥ የሌለው ተራ
ትውፊት ነው። መገለጥ የሌለው ትውፊት ብዙ ጊዜ ሰዋዊ ትውፊት ነው.. ስለዚህም መነሻው ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች
ብቻ ነው። ይህ ሰዋዊ ትውፊት የተለያየ ቅርጽ ሊኖረው ቢችልም እኛ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ከተቀመጠልን ከአይሁዳውያን
ትውፊት አንጻር ከሁለት በኩል ልናየው እንችላለን.. ይህም አንደኛው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውና
ከእለት እለት ኑሮዋቸው ጋር ሊገናኝ የሚችል ትውፊት ብቻ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የምንመለከተው ሰዋዊ ትውፊት
የእግዚአብሔርን ቃል የሚሽረውን ነው።
በማርቆስ ወንጌል 7 ላይ ካለው ተነስተን የተወሰነች ማብራሪያ እናስቀምጥ፡
1. በአይሁዳውያን ዘንድ ለምሳሌ እጅን ታጥቦ መብላት የሽማግሌዎች ወግ(ትውፊት) እንደሆነ ይነገራል.. ይህ ከመገለጥ ጋር
ምንም የማያገናኘው የሰዎች ሥርዓት ብቻ ነው.. ታድያ ግን አንዳንድ ጊዜ አይሁዳውያን ይህንን ሰዋዊ ትውፊት አጥብቀው
ሲይዙ በጎን ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል ይሉም ነበር። ለማንኛውም ከትውፊትነቱ አንጻር ይሄ ቢደረግ ሥጋን የሚጠቅም
መልካም ነገር ነው ግን ሁሉን በአግባቡ ሲሆን መልካም ይሆናል። እንዳልኳቹ ግን ከሃይማኖት ጋር ምንም አያገናኘውም።
2. ታድያ እዛው የማርቆስ ወንጌል ምእራፍ ላይ ጌታ ኢየሱስ አይሁዳውያንን ሌላ የራሳቸውን ትውፊት በመጥቀስ
የእግዚአብሔርን ቃል እንደሻሩ ሲናገራቸው እንመለከታለን። ይህም አባትህን እና እናትህን አክብር የሚለውን ትእዛዝ ልጆች
ሁሉ አባቶቻቸውን እናቶቻቸውን በመርዳትም(በገንዘብ) ጭምር ሊተገብሩት የሚገባ ሲሆን በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት
እነርሱ ግን ለእናት ለአባት የሚገባውንም ወደ እነርሱ ለመሳብ ሕግን ያስቀምጡ ነበር። ያው ወደ ቤተ መቅደስ የሚገባው ሁሉ
ለአገልጋዮቹ ስለሚሆን ማለት ነው። ስለዚህም የራሳቸውን ኪስ ለማወፈር የራሳቸውን ትውፊት በመያዝ ዋናውን
የእግዚአብሔርን ቃል ሲሽሩበት እንመለከታለን። ቅዱስ ትውፊት ስንል ደግሞ በተለየ መልኩ ምንጩ እግዚአብሔር ሆኖ
ከእግዚአብሔር ለሰዎች ሲሰጥ.. የተቀበሉትም ሰዎች ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሲያስተላልፍ ይህንን ቅብብሎሽ(ትውፊት) ቅዱስ
ትውፊት እንለዋለን።
ቅዱስ ትውፊት የቤተ ክርስቲያን ሕይወቷ ነው(Tradition and Orthodoxy, Fr Tadros Malaty) እናም ከቅዱስ
ትውፊት ውጪ የሆነ ሕይወት የላትም። ቅዱስ ይሁዳ በመልእክቱ ሲናገር “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት”
በማለት ይናገራል። ይህም የተሰጠው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሆን የተሰጠውም ወደ ቀጣዩ ትውልድ እየተላለፈ እስከ አለም
ፍጻሜ ይሄዳል ማለት ነው። የቅብብሎሹ መነሻ ራሱ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነው.. ስለዚህም ይህ ቅብብሎሽ ቅዱስ ነው። ልክ
መጽሐፍ ቅዱስን “ቅዱስ” የሚያስብለው ምንጩ ቅዱሱ መንፈስ መሆኑ እንደሆነ ሁሉ ማለት ነው። እስቲ ይህንን ቅብብሎሽ
የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አንስተን እንመልከት፡
ይሁዳ 1: 3 - ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ
ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። (በዚህ ክፍል ላይ እንደምንመለከተው
ሃይማኖት(እምነት) በራሱ የተሰጠ ነው። ትውፊት ደግሞ መቀበል እና ማቀበል ወይም ቅብብሎሽ እንደሆነ ተመልክተናል)
ገላ 1፡ 11-12 - ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል
እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። (እዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ግልጽ እንደሚያደርገው ወጌልን ወይም
ትምህርትን ከሰው አልተቀበለም ይልቁንም ከጌታ እንጂ። ስለዛ ቅብብሎሹ ከሰው አይጀምርም ከጌታ እንጂ)
1 ቆሮንቶስ 11፡ 23 - ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና (ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታ የተቀበለውን
ትምህርት አሳልፎ ደግሞ ለሌሎች ይሰጣል። ከጌታ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከጳውሎስ ደግሞ ወደ ሌሎች። ቅብብሎሽን
አስተዋልክ..??)
2 ጢሞቴዎስ 2፡ 2 - ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች
አደራ ስጥ። (እዚህ ላይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን እሱ ደግሞ ለሌሎች ለታመኑ ሰዎች አደራ እንዲሰጥ
ሲነግረው እንመለከታለን። ስለዚህም ከጌታ ወደ ጳውሎስ፤ ከጳውሎስ ወደ ጢሞቴዮስ፤ ከጢሞቴዎስ ደግሞ ወደሌሎች
የታመኑ ሰዎች። ዛሬ ላይ የደረሰው ሃይማኖት እንዲሁ አይደለም.. ይልቁንም እንዲህ ባለ ቅብብሎሽ ውስጥ አልፎ ነው። ያለ
ትውፊት ቤተ ክርስቲያን ሕይወት የላትም የሚለውን አስተዋልክበት..??)
1 ቆሮንቶስ 11፡ 2 - ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን(ትውፊትን) ፈጽማችሁ ስለ
ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። (ይህ የሚተላለፈው ትውፊት ደግሞ ጅማሬው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነውና ይህንን ትውፊት
አሳልፎ እንደሰጣቸው ፈጽመው በመያዛቸው ያመሰግናቸዋል። የትውፊትን ወሳኝነት አስተዋልክበት..??)