You are on page 1of 4

ከመንፈሳዊ ዝለት ለመውጣት ምን ላድርግ?

ክርስትና ሕይወት ነው። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ብዙ መሰናክሎቻችን ክርስትና በሕይወት የሚተገበር መልካም
ልምምድ መሆኑን በመርሳታችን ምክንያት የሚመጡብን ናቸው። አንዳንዶቻችን ክርስትናን የሆነ ድርጅት አባልነት
አድርገን እናየዋለን። ሕግጋቱም የመኖርና የመሞት ፤ የመዳን እና ያለመዳን ጉዳይ ሳይሆኑ ከአንዳች ድርጅት አባልነት
ላለመባረር የምንተገብራቸው ይመስለናል። ሕግጋቱን መጣስ ከመልካሙ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኪዳን ማፍረስ
በዚህም የጠቅላላው ክፋት ግብረ አበር ወደመሆን የሚያደርስ መሆኑን እንረሳዋለን። መዋሸት ከመግደል ጋር
የሚያገናኘው መሰረታዊ የጥፋት ክር አይታየንም። በአጠቃላይ ክርስቲያን ከመሆን ይልቅ ክርስቲያን ናቸው መባል
ያስደስተናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ታሪክ አለ። ሁለት ሰዎች ቤት ለመስራት ይወጣሉ። የመጀመርያው ቤቱን በጠንካራ መሠረት
ላይ ለመመሥረት አስቦ አጥልቆ ይቆፍራል። በታላቅ ዓለት ላይም ይመሠርተዋል። አጥልቆ በቆፈረ ቁጥር መሠረቱ
እየጠነከረ ቤት ለመሥራት የተመቸ እየሆነ የሚመጣ ነው። ጎረቤቱ ግን እንደ'ርሱ ያለ ትዕግስተኛ አልነበረም። ቤቱን
ያለጥልቅ መሠረት አሸዋ ጫር ጫር አድርጎ ይሰራዋል። የሁለቱ ቤቶች ጥንካሬ የሚታየው መከራ በመጣ ጊዜ ነው።
ዝናብም ይዘንባል፤ ጎርፍም ይጎርፋል፤ ነፋስም ይነፍሳል። ያንን ቤት ይገፋዋል። ቤቱን በዓለት ላይ የመሰረተው ሰው
አይነዋወጽም። በጠንካራ መሠረት ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም። በአሸዋ ላይ ቤቱን የገነባው ግን ወደቀ፤ አወዳደቁም
ታላቅ ሆነ። ማቴ 7:24-27

የብዙዎቻችን ሃይማኖት መሠረቱ ቢመረመር ይኼ እምነት የተሰኘ ጠንካራ ዓለት ይገኝ እንደሆን እርግጠኛ አይደለንም።
አብዛኞቻችን ክርስትያን የሆንነው እናትና አባቶቻችን ክርስቲያን ስለሆኑ ነው። በቤቱም የምንጸናው ከእኛ ትጋት ይልቅ
በእናት በአባቶቻችን ጸሎት ጥንካሬ ነው። ይኼ በራሱ መጥፎ አልነበረም። ነገር ግን በጣም ከመለመዱ የተነሳ ክርስትናን
እንደአንድ ሊኖሩት እንደሚገባ ጣፋጭ ሕይወት ከማየት ይልቅ ከወላጆቻችን እንደወረስነው አይነኬ የድሮ ቅርስ
እንድናየው አድርጎናል። ለአፍታ ተግ ብለን ራሳችንን ችለን ለራሳችን ክርስትያን መሆን አለብን። 'ለምንድነው ግን
ክርስቲያን የሆንኩት?' ብለን መጠየቅ አለብን። በእርግጥ 'እናት እና አባቴ ክርስትያን ስለነበሩ ነው።' የሚለው በቂ መልስ
ሊሆን ይችላል። ግን አጥልቀን መቆፈር አለብን። ቤተክርስቲያንን፣ ክርስትናን ለማወቅ መታተር ያሻል። ይኼኔ የበለጠ
የክርስትና ሕይወት ጥፍጥና እየተገለጠልን፣ እየጣፈጠን፣ ይበልጥ ርየጣፈጠን ንምነታችን በማይነቃነቅ መሠረት ላይ
እየሠራን እንመጣለን። ሌሎቻችን ክርስትያን የሆንነው ተአምር ፍለጋ ይሆናል። ክርስቶስን ይከተሉ የነበሩ ሰዎች ሁሉ
ለትምህርቱ፣ ለእውነተኛ አምላክነቱ የሚከተሉት አልነበሩም። ተአምር ሲሰራ ለማየት ብቻ የሚከተሉት ብዙዎች ነበሩ።
ፈሪሳውያኑም ምልክት እንዲያሳያቸው ደጋግመው ጠይቀውታል። ማቴ 12:38-39፤ 16:1-4፤ ማር 8:11-12፤ ሉቃ
11:16፣ 29-30፤ ዮሐ 2:18 ሔሮድስ ክርስቶስ ፊቱ ሲቀርብ መጀመርያ የጠየቀው አንዳች ምልክት እንዲያሳየው ነበር።
"ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥
ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም።" ሉቃ
23 : 8 እኛም ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር ለአፍታ ምልክት ማሳየቱን ቢያቆም፥ በብዙ ቃልም ጠይቀነው አንዳች እንኳ
ባይመልስልን እምነት የተባለ ቤታችን የሚወድቅ፥ አወዳደቁም ታላቅ የሚሆን የአሸዋ ላይ ቤቶች ብዙዎች ነን።
በአጠቃላይ ክርስትና ውስጥ እንጂ ክርስትና ሕይወት ውስጥ እንደሌለን የሚያሳዩ እንዲህ ያሉ ብዙ ምሳሌዎችን
ማምጣት ይቻላል።

እነዚህን ነገሮች ካጠራን በኋላ ነው በክርስትና ሕይወት መዛል ስለሚባለው ነገር ማውራት የምንችለው። ጡብ እየደረደረ
ግንብ የሚገነባ ግንበኛ ከታች የሚደረድራቸው ጡቦች በተቻለ አቅም ጥራት ያላቸውና ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረግ
አለበት። ከታች የማይረቡ ጡቦችን ደርድሮ ሳለ ከላይ የሚደረደራቸው የፈለገ ጠንካራና ውብ ቢሆኑ ግንቡ መፍረሱ
አይቀርም። ይልቁን ከታች ያሉትን በጠንካራ ጡቦች ቢሠራቸውና ከላይ ያሉት የማይረቡ ጡቦች ቢሆኑ ለመቀየርም
ለማስተካከልም ቢሉ ይመቻል። ክርስትና ሕይወት ነው በሚለው ላይ መግባባት አለብን። መሠረታችንን በዓለት ላይ
መመሥረት አለብን። ከዚያ በኋላ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ስለሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ማውራት ዕዳው ገብስ ነው።
ለዛሬ ደግሞ ልናነሳው ያሰብነው ተግዳሮት መንፈሳዊ ዝለት የሚባለውን ነው።

መንፈሳዊ ዝለት በዘመናችን አገልጋዮች ዘንድ ተደጋግሞ የሚታይ ከመሆኑም በላይ መገለጫዎቹ ከመብዛታቸው የተነሳ
እንዲህ ነው ብሎ ለመበየንም አስቸጋሪ የሆነ ነገር ነው። በአንዳንዶቻችን ውስጥ በ'ሁሉንም አውቄዋለሁ! ምንም አዲስ
ነገር የለውም!' መልክ ሊመጣ ይችላል። ለአንዳንዶቻችን 'እኔ ለዚያ የተገባሁ አይደለሁም! ስለዚህ ባልፈጽመው ይሻላል!'
ከሚል ትህትና መሰል ስንፍና የሚመጣ ሊሆን ይችላል። ብቻ ከመልካም ክርስትያናዊ ልምምዶች በኋላ የሚያጋጥም
የመታከት፣ እና የመዶልዶም ስሜት ነው። አዲስ ነገር የማጣት፣ በአጠቃላይ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱ ውስጥ ትርጉም
ያለማግኘት ስሑት መንፈስ ነው። ይኼ ደግሞ በተለይ በወጣኒያን ላይ በተደጋጋሚ የሚታይ እንደሆነ አበው ይናገራሉ።
በሆነ መልኩ እምነታቸው በየነፋሱ፣ በየጎርፉ ከሚፈተን ወጣት የሠንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ጀምሮ መነኮሳት
ድረስ ይኼ ችግር ሊደርስ ይችላል።

ችግሩ ቅድም ያነሳነው ክርስትናን የሕይወት ልምምድ አድርጎ ካለማሰብ የሚመዘዝ ነው። ክርስትና ሕይወት ነው ስንል
የሕይወት ምንጭ የሆነ ክርስቶስ ነው የመሰረተው ማለታችን ነው። በዚህም ክርስቲያኖች የሕይወት መንፈስ መገኛዎች
ይሆናሉ። ይህ የሚመጣው በምስጢራት በኩል በሚፈጸም ሱታፌ አምላክ ወይም የመለኮትና የሰው ኅብረት በኩል ነው።
በአጭሩ ስናስቀምጠው ሥጋ ወደሙን የማይቀበል፥ በንስሐ ሕይወት ውስጥ የማይመላለስ አገልጋይ የክርስትና ሕይወትን
እየኖረ ነው ለማለት ይቸግረናል ማለት ነው። ሕይወትን ከሚያስገኘው ከክርስቶስ ተገልሎ ሕይወት አለኝ ማለት
አይቻልም። እንዲህ ማለት በአሸዋ ላይ የተሠራ ቤት ምልክት ነው።

የመንፈሳዊ ዝለት መንስኤም ይኼ ነው። ብዙዎቻችን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ያለውን ጥፍጥና እንረሳዋለን።
ጥፍጥናው ያለው ክርስቲያን ነኝ ብሎ ማተብ በማንጠልጠሉ ላይ ብቻ ይመስለናል። ለጥምቀት አሸብርቆ ታቦት
በመሸኘት ውስጥ፤ ወይ ምንጣፍ ተሸክሞ በማገልገል ውስጥ፤ ወይ ደግሞ በመዘመር ውስጥ፣ በማስተማር ውስጥ ብቻ
ይመስለናል። አዎን በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ውስጥ ጥፍጥና አለ። ነገር ግን ይሄ ጥፍጥና የሚገለጠው ማስተማራችንም፣
መዘመራችንም፣ ማገልገላችንም ከክርስቶስ ጋር ያለንን ኅብረት በማጠንከራችን የመጣ ሲሆን ነው። ከውስጥ ሞልቶ
የተረፈ ነው በውጪ መታየት ያለበት። ማቴ 9:21፤ ሉቃ 6:45 ይህ ካልሆነ ግን የሆነ ጊዜ እነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ
አዲስ ነገር እናጣለን። እነርሱ የሚሰጡንን አዲስ ነገር ስለጨረሱ አይደለም። እኛ ስልቹና ታካች ስለሆንን ነው እንጂ።
ቅዳሴው ሠርክ አዲስ ነው የምንለው፣ የያሬድ መዝሙር ሁሌም ይናፈቃል የምንለው፣ ጸሎት ሁሌም አይሰለችም
የምንለው ሠርክ አዲስ የሚያደርጋቸው ክርስቶስ ስላለባቸው ነው። ስለዚህ እኛ መንፈሳዊ ዝለት ቢያጋጥመን እና ጸሎቱ
አሰልቺ ቢሆንብን፣ ቅዳሴው ቢረዝምብን፣ የያሬድ ዜማ ኋላ ቀር ቢመስለን ይህ ያለመለወጥ የሠርክአዲስነት መንፈስ
የሆነው ክርስቶስ በውስጣችን ስለታጣ ነው። ስለዚህ መፍትሔው መሆን ያለበት አገልግሎቶች ሁሉ ንስሐ መር እና ሥጋ
ወደሙ ተኮር መሆን አለባቸው የሚለው ነው። መጀመር ያለብንም ከመዘመርና ከመስበክ ሳይሆን ንስሐ ከመግባትና ሥጋ
ወደሙ ከመቀበል ነው።

ወደዚህ ደረጃ ለመሔድ የሚያገለግሉ ዘዴዎች ደግሞ አሉን። እነዚህ ክርስትያን የሆንንበትን ምክንያት የሚያስታውሱን፥
በውስጣችን ያለውን መንፈሳዊነት የሚያድሱና ወደንስሐ በዚህም ወደሥጋ ወደሙ የሚመሩን ናቸው። ስንጀምር
ቤታችንን ዓለት ላይ መመሥረታችን ላይ መስማማት አለብን ያልነው የሚያገለግለው እዚህ ጋር ነው። እናት እና አባቱ
ክርስትያን ስለሆኑ ብቻ ክርስትያን የሆነ ሰው እንዲህ ያለ ዝለት ባጋጠመው ጊዜ አስቀድሞ ወደክርስትና የሳበውን ውብ
ብርሃን ማሰብ አይችልም። በቃ ድንገት ሲነቃ እዚህ የጠበቀ ሕግ ያለበት ወኅኒ ቤት ውስጥ የተገኘ እና ከዚያ ሌላ አማራጭ
ስለሌለው ብቻ እዚህ የእናትና የአባቱ እምነት ውስጥ የቆየ ሊመስለው ይችላል። ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ከቀየሩ በኋላ
ነጻ ወጣን ዓይነት ንግግር የሚናገሩት ለዚህ ነው። የኖሩት ብቻ ናቸው በዚህ ከጭራ በቀጠነ ሕግ እና ከባድ በሚመስል
ሥርዓት ውስጥ የሚገኘውን ጣፋጭ ነጻነት የሚያውቁት። በአንደበት ለማስረዳት ሊከብድ ይችላል። አንዳንድ ዝም
ተብለው የሚኖሩ ነገሮች አሉ። የማይነገሩ፥ ለመነገር የማይመቹ፤ ቢነገሩ እንኳ ከአንደበታችን ትባት ማነስ የተነሳ፥
ከቋንቋችን አንካሳነት የተነሳ ቅርፊታቸውን፥ ውጪያቸውን እንኳ በተገቢ ሁኔታ አንስተን የማንጨርሳቸው ነገሮች አሉ።
ክርስትና እንደዚያ ነው። አባቶቻችን እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ ያሬድ፣ እነአባ እንጦንስ፣ እነ አባ መቃርስ ብለው
ብለው ያልቻሉትን እኛ በአንድ የመጽሔት ጽሑፍ ተንትነን መጨረስ የምንችለው አይደለም።

ከዚያ ይልቅ በዚህ የክርስትና ሕይወት ውስጥ ሊያጋጥመን ከሚችለው ዝለት ለመውጣት ያገለግላሉ ያልናቸውን መልካም
ልምምዶችን እንጠቁማለን።

መጀመርያ የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች መገንዘብ አለብን። አንድ ይሄ የመንፈሳዊነት ዝለት በአገልግሎት ሕይወት ውስጥ
የሚጠበቅ እና ተፈጥሯዊ መሆኑን መገንዘብ ነው። ያለነው እኮ መንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ ነው። ይሄ ዝለት ደግሞ
ዲያብሎስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደሆንን እንዲሰማን እያደረገ፣ ክርስትያኖች የሆንን ርንዲመስለን እያደረገ የ'ርሱ
ተገዢዎችና የኃጢኣት ባርያዎች መሆናችንን እንዳናስተውል የሚያደርግበት አስቀያሚ ወጥመድ ነው። ይህን
ካልተገነዘብን ከዚህ ዝለት መውጫ መፍትሔ የሌለ ሊመስለን ይችላል። በዚህም ምንም አዲስ ነገር የለውም ካልነው
መንፈሳዊ ሕይወት ወጥተን አዲስ ነገር ፍለጋ... መለወጥ፣ መጥፋት እና መፍረስ መገለጫው ወደሆነው ዓለም
እንመለሻለን። ብዙዎቹ መዘምራን ዘፋኝ የሚሆኑት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው። ሁለተኛ መገንዘብ ያለብን ከዚህ
መንፈሳዊ ዝለት በእግዚአብሔር እርዳታና በእኛ ትጋት መውጣት እንደሚቻል ነው። ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን
እንዳልነው ክርስትና በመንፈሳዊ ልምምድ የሚዳብር ሕይወት እንጂ በመታወቂያ የሚገለጽ የድረጅት አባልነት
አይደለምና ቀስ በቀስ እነዚህን ልምምዶች በማዘውተር ክርስቲያን ከመባል ክርስቲያን ወደመሆን ማደግ እንችላለን።

ለዚህ የሚያግዘን የመጀመርያው ነገር ተገቢ የትኅትና መንፈስ ነው። ወጣኒያን ላይ የሚታየው ችግር ይሄ ነው። በአፍላነት
ጉልበት አንድ ጊዜ በፍጥነት ሁሉን ካላወቅሁ፣ ሁሉን ካልጨበጥሁ እንላለን። እዩኝ እዩኝ እንላለን። እዩኝ እዩኝ በኋላ
ደብቁኝ ደብቁኝን ያመጣል። ደርሶ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ሥርዓት አስከባሪ የምንሆነው ነገር አለ። አለእኛ በቀር
እግዚአብሔር ሰው የሌለው ይመስለናል። 'ጀማሪ እረኛ ከብት አያስተኛ' ይባላል ከነተረቱ። 'ጀማሪ ዲያቆኖ ከጳጳስ
ይበልጣል' ይላሉ አበውም። በዚህ መነሻው መልካም በሚመስል ተግባር ውስጥ ብዙ ክርስቲያኖችን ከቤተክርስቲያን
እናስቀራለን። እግዚአብሔርንም እናሳዝናለን። ማራቶን ውድድር ላይ ሁልጊዜ ገና ሩጫው እንደተጀመረ ፊት ፊት
የሚመሩት ሯጮች ብዙ ጊዜ ውድድሩን ለመጨረስ አቅም አጥተው እንደሚያቋርጡ የታወቀ ነው።። ይኼ ችግር
የሚስተካከለው ቅድም ባነሳነው መልካም የትሕትና ባሕል ነው።

መልካም ትሕትና ያልንበት ምክንያት መንፈሳዊ ዝለት ከሚለብሳቸው ጭንብሎች መካከል ስሑት የሆነው የትኅትና
መንፈስ አንዱና ዋነኛው ስለሆነ ነው። ብዙዎቻን ለምን ሥጋ ወደሙ እንደማንቀበል ብንጠየቅ መልሳችን የሚሆነው
'ለዚያ የተገባሁ አይደለሁም! ክብሩን መቀነስ ይሆናል!' ምናምን የሚል ምስጢሩን ማክበር መሠል ትኅትና ለበስ
ማስተባበያ ነው። አንደኛ መቼም ቢሆን በራሳችን ጥረት ለዚያ የተገባን ሆነን አንገኝም። ምስጢረ ቁርባን ራሱ
የተመሠረተው በእኛ የተገባን ሆኖ መገኘት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ ነው። ሁለተኛ ራስን ወደዚህ ከፍታ
ከመውሰድ ይለቅ ይህን ከፍታ ወደራስ ዝቅታ ለመሳብ መሞከር በራሱ ተገቢ አይደለም። ንስሐ ገብቶ ሥጋ ወደሙን
በመቀበላችን ውስጥ ንስሐ ከገባንበት ኃጢኣት ይልቅ ንስሐ ሳንገባ ሥጋ ወደሙንም ሳንቀበል ቤተክርስቲያን በየዕለቱ
የክርስቶስን ሥጋ እና ደም ፈትታ አዘጋጅታ ጠርታን አንታደምም፣ አንመገብም ብለን መመለሱ የበለጠ ክብሩን የሚቀንስ
ነው።

ትህትና ስንል ይህን ማለታችን እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳል። ትህትና ስንል ቤተክርስቲያን ውሰጥ ሁሌም ከምናውቀው ነገር
ይልቅ የማናውቀው፤ ከምናየው ነገር ይልቅ የማናየው ነገር እንደሚበዛ መገንዘብ ማለታችን ነው። ይኼ ከእኛ አላዋቂነት
ወይም ወጣኒነት ብቻ የሚመጣ አይደለም። ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ከመገኘቷም ጭምር የሚነሳ ነው። ታውቃ
ልትጨረስ አትችልም። አይደለም እኛ ቀርቶ አበው ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ኖረውባት አወቅናት በቃችን አላሉም።

ሌላኛው ከመንፈሳዊ ዝለት እንድንወጣ ሊረዳን የሚችለው ነገር የፀሎት ልምድ ነው። ልብ ይበሉ! ጸሎት ብቻ
አልተባለም! የጸሎት ልምድ እንጂ። ብዙዎቻችን የምንጸልየው የሆነ የምንፈልገው ነገር ሲኖር ብቻ ነው። በራሱ ችግር
የለውም ይሄ። ጸሎት ልምድ ቢሆን ግን የበለጠ ጠቃሚነቱ ይጨምራል። አለመጸለይ የማንችልበት ደረጃ እስክንደርስ
ድረስ መልመድ አለብን። ጥፍጥናው ሊገባን ይገባል። አባቶቻችን ሲቀመጡ፣ ሲነሱ፣ በመንገድ ሲሔዱም ፣ ሌላም ሥራ
ሲሰሩ ጸሎት የማያስታጉሉት የሰይጣንን ፈተና በየቦታው ለመዋጋት ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከፀሎቱ ጋር በፍቅር ስለወደቁም
ጭምር ነው። ማለት እንደው ሰይጣን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይፈትናችሁ ከዓለም ጠፍቷል ቢባሉ እንኳ
መጸለያቸውን አያቆሙም። እግዚአብሔርን ከማመስገን ጋር ፥ ከእግዚአብሔር ጋራ ከመነጋገር ጋር ፍቅር ይዟቸዋል።
በምስጋና ብቻ እየረኩ የገነት ኑሯቸውን በምድር እየኖሩት ነው። እኛም እነርሱ የደረሱበት ከፍታ ላይ ለመድረስ መጣር
አለብን።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የምናነሳው የመጨረሻው ሃሳብ መንፈሳዊ አውድ ነው። በዙርያችን መንፈሳዊ አውድ መፍጠር ካነሳነው
መንፈሳዊ ዝለት ለመውጣት ሊያገለግለን ይችላል። ዙርያችንን በመንፈሳዊ መጻሕፍት መሙላት፤ የቅዱሳንን
የሰማዕታትን የተጋድሎ ሕይወት የሚያስታውሱን ነገሮችን በየቦታው ማኖር ክርስትና ውስጥ ያለውን ጥፍጥና እኛም
ክርስትያን የሆንንበትን ምክንያትሊያስታውሰን ይችላል። የዩትዩብ አልጎሪዝማችንን በመንፈሳዊ ቪድዮዎች መሙላት፤
መዝሙሮች፣ ስብከቶችን ማዳመጥ፤ መንፈሳዊ ፊልሞችን ማየት፤ ማንበብ፣ ማንበብ፤ ማንበብ... ከዚህም በኋላ ስለነዚህ
ነገሮች ከመንፈሳዊ ባልንጀሮቻችን ጋር መወያየት። መልካም ጓደኞች የዚህ መንፈሳዊ አውድ ወሳኝ አካላት ናቸው።
ስንደክም የሚያበረቱን፣ ስንተኛ የሚቀሰቅሱን፣ ለኪዳን ለቅዳሴ የሚያተጉን፣ ስለመንፈሳዊ ነገር ማውራት የሚቀናቸው
ጓደኞች ማግኘት መታደል ነው። ቢላዋ ቢላዋን ይበልጥ ስል ያደርገዋል እንደሚባለው ሁሉ እኛም ለእነርሱ መጠንከር
ስንል መትጋት አለብን። በአጠቃላይ በእነዚህ መንፈሳዊ ነገሮች አካባቢያችንን መሙላት ከመንፈሳዊ ዝለት ጎትቶ
ከማውጣቱ በላይ አዕምሯችንን ከኃላፊው ዓለማዊ ነገር ለማቀብ እንዲሁም በዙርያችን ያሉ ወንድምና እኅቶች ላይ
መልካም ተጽእኖ ለማሳደር ያገለግለናል።

በአጠቃላይ ግን በእውነተኛው ክርስትና ውስጥ ሁሉንም አዲስ የሚያደርግ ክርስቶስ እስካለ ድረስ መንፈሳዊ ዝለት
የሚባል ነገር እንደሌለ (ትርጉምም እንደማይሰጥ) ተረድተን በአገልግሎታችን ውስጥ መንፈሳዊ ዝለት ባጋጠመን ጊዜ
ክርስቲያን ከመምሰል በአማን ክርስቲያን ወደመሆን የሚጋብዝ ዕድል እንደሆነ በመገንዘብ ከላይ ያነሳናቸውን እና ሌሎች
መሰል ክርስቲያናዊ ልምምዶችን በማዘውተር መትጋት እንዳለብን መርሳት የለብንም። ለዚህም እነአባ እንጦንስን፣ እነአባ
መቃርስን በመልካም ተጋድሏቸው ውስጥ ያበረታቸው አምላከ ቅዱሳን ይርዳን። አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

You might also like