You are on page 1of 4

ወጣትነት እና እጮኝነት

በዲ/ን ኢያሱ መስፍን


ክፍል አንድ

ይህ ርእሰ ጉዳይ በጥንታውያን እንዲሁም በዘመናችን ባሉ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የተባለለት እና በጥልቀት

ማብራሪያ የተሰጠበት ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ ጠለቅ ያሉትን ትምህርቶች አቆይተን ግቢ ጉባኤያት ከዚህ ጉዳይ ጋር

በተገናኘ በብዛት የሚፈተኑባቸውን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሚገኙበት ዕድሜ ትኩስ የወጣትነት ዘመን እንደ መሆኑ ተፈልጎም ይሁን ሳይፈለግ ዕድሜን

ተከትሎ የሚመጣ ሁሉም ሰው የግድ የሚያልፍበትን አንድ ጥያቄ ያስተናግዳሉ። ይህም ለክርስቲያኖች ከተፈቀዱልን

ከሁለቱ የሕይወት መንገዶች የእኔ ምርጫ የትኛው ነው? የሚል ነው። እነዚህ ሁለቱ መንገዶች የድንግልና ሕይወት እና

የጋብቻ ሕይወት መሆናቸው ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት አዲስ መረጃ ላይሆን ይችላል። (1ቆሮ 7፤1-2) ጌታችን እንዳለ

እስከ ሕይወት ፍጻሜ ሳያገቡ ድንግልናን ጠብቆ መኖር ተከትሎት የሚመጣውን ፈተና መቋቋም የሚችሉበት ጸጋ

ለተሰጣቸው ሰዎች ብቻ የሚሆን ተጋድሎ ነው (ማቴ 19፤11)። በዚህ የተጋድሎ ሕይወት ያጌጠ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ

ጋብቻ እና የድንግልና ሕይወት በስፋት ባስተማረበት መልእክቱ ክፍል ደጋግሞ እንደተናገረው ሰው ሁሉ በዚህ የተጋድሎ

ሕይወት ቢኖር መልካም እንደሆነ ጠቅሶ ይህንን መቋቋም የማይችሉ ግን ቢጋቡ የሚያስመሰግን እንጂ ነውር የሌለበት

መሆኑን አስተምሯል። (፩ቆሮ. ፯፥፩) እኛ ባለንበት በዚህ ዘመን ወደ ጋብቻ ለመሄድ የወሰነ ሰው ቀድሞ የሚያልፍበት

የእጮኝነት ጊዜ የሚባል እጅግ ወሳኝ ደረጃ አለ።

የእጮኝነት ጊዜ

የእጮኝነት ጊዜ በቅርቡ ለመጋባት ዝግጁ የሆኑ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ወደ ትዳር ሕይወት ከመግባታቸው በፊት

አንዳቸው ለሌላኛው የሚመቹ አጋር መሆናቸውን እና ቢጋቡ በጋራ የትዳርን ዓላማዎች ያሳካ ትዳር ሊኖራቸው መቻሉን

የሚያጠኑበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ላደረጉ እና ዓላማውን ለተረዱ እጅግ ጠቃሚ

የመሆኑን ያህል፥ ፈተና የበዛበት እና ላልተጠነቀቁ ሰዎች ደግሞ መሰናከያ ወጥመድ ሊሆን የሚችል ነው። ቤተ

ክርስቲያን ‘የእጮኝነት ጊዜ’ ብላ የምትጠራው ሁለቱ ሰዎች የፍቅር ግንኙነት ከጀመሩበት አንሥቶ እስኪጋቡ ያለውን

የመጠናናት ጊዜ ሲሆን ከጋብቻ እና ከእጮኝነት ውጪ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና የሰጠችው ሌላ የጾታዊ ግንኙነት

ሂደት የለም።

እጮኝነት መቼ?

አንድ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ወደ ጋብቻ የሚመራውን የእጮኝነት ሕይወት መች መጀመር አለበት የሚለውን መረዳት

ወደ ሕይወታችን ሊመጡ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎችን ለማስቀረት አልያም ለመሻገር እጅግ ጠቃሚ ነው። የእድሜ እና

የአካል ጉልምስና ብቻውን ወደዚህ ሕይወት ለመግባት በቂ አይደለም። የእጮኝነት እንዲሁም የጋብቻ ሕይወት

ከእድሜ ባሻገር መንፈሳዊ፣ አእምሮአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዝግጅትን የሚጠይቅ ነው።


ሀ. መንፈሳዊ ዝግጅት

መንፈሳዊ ዝግጁነት ማለት አንድ ወጣት ሕይወቱን ከሌላ ሰው ጋር ከመጋራቱ በፊት ከአምላኩ ጋር የሚሆንበት ጊዜ

ያስፈልገዋል ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ማለት እያንዳንዱ ክርስቲያን ከአምላኩ ጋር ያለውን ጥብቅ

ትስስር የሚመለከት ነው። ከእጮኝነት በፊት ያለው የወጣትነት የብቸኝነት ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ

ለሚደረግ ተጋድሎ እጅግ የተመቸ ነው። መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ “ያላገባ ጌታውን እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ

የጌታን ነገር ያስባል፣ ያገባ ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ የሚስቱን ነገር ያስባል፤ ልቡም ተከፍሏል” (1ቆሮ

7፡32-33) እንዳለ በትዳር ሐሳብ ሳንያዝ እግዚአብሔር አምላካችንን ደስ የምናሰኝበትን ምግባር ገንዘብ ለማድረግ

መታገል ያስፈልጋል። ጾም፣ ጸሎት እና ስግደትን ማዘውተር እንዲሁም ሕይወትን ንስሓ እና የቅዱስ ቁርባን ሕይወትን

መምራት ለብቻችን በሆንበት ጊዜ ሊደረጉ የሚገባቸው ናቸው። እንደዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ልምምዶች ከትዳር በኋላ

የምንሞክራቸው ሳይሆን የትዳር ኃላፊነቶችን ከመቀበላችን በፊት ገንዘብ ልናደርጋቸው የሚገቡ ናቸው። ለዚህም ነው

ፈረንጆቹ ‘your relationship is as good as your singleness’ የሚሉት። በብቸኝነት ጊዜ ያልነበሩንን ምግባራት ከሌላ ሰው

ጋር ከሆንን በኋላ መላመድ አስቸጋሪ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በተጨማሪም ልቡናችን ሳይከፈል ከእግዚአብሔር በተቀበልነው ጸጋማ ዓቅማችን የፈቀደውን ያህል በእግዚአብሔር

ቤት አገልግሎት በመጠመድ ከዕድሜአችን አሠራት መክፈል ያስፈልጋል። ከትዳር በኋላ አገልግሎት የሚቋረጥ

ባይሆንም እንኳ እንደ ልብ ለማገልገል የሚመቸው የብቸኝነት ጊዜ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

ሐሳቡን ስንጠቀልለው የእጮኝነት ጊዜ ይዞት የሚመጣውን ኃላፊነት ከመቀበላችን በፊት መንፈሳዊ ምግባራትን

በመለማመድ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በኩል ራስን ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ይህ

መንፈሳዊ ዝግጁነት ሳይኖረው ወደ እጮኝነት ሕይወት ባለመግባት ራሱን ከፈተና ሊጠብቅ ይገባዋል።

ለ. አእምሮአዊ ዝግጅት

አእምሮአዊ ዝግጁነት ወጣቶች ወደ እጮኝነት ሕይወት ከመግባታቸው በፊት ከራሳቸው ጋር የሚያደርጉት ውይይት

ነው። ከራስ ጋር መሆን ማለትም ራስን ማወቅ፣ ፍላጎትን መለየት፣ ደካማ ጎኖችን ማሻሻል፣ ጥንካሬን ማስቀጠል እና

በአጠቃላይ “ሰው ሆኖ” ለመገኘት መሥራት ማለት ነው። ይህ ከራስ ጋር የሚደረግ ውይይት ከትዳር እና ከድንግልና

ሕይወት የትኛውን እንደምንፈልግ፣ ለምን ያንን ሕይወት እንደ መረጥን አጥርቶ ከመለየት ይጀምራል። በመቀጠልም

ለመረጥነው ሕይወት የተገባን እንድንሆን ራስን ማዘጋጀት ይገባል። ሁሉም ሰው የሚፈልገው የትዳር አጋር ‘ጥሩ ሰው’

ተብሎ ሊገለጽ የሚችል መሆኑ እሙን ነው። ጥሩ ሰዎችን የምንፈልገውን ያህል እኛም ለአጋሮቻችን ጥሩ ሰዎች ሆነን

ልንገኝ እንደሚገባን ማሰብ ያስፈልጋል። የመጽሐፉም ትእዛዝ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ወደድ’ (ዘሌ ፲፱፥፲፰)

እንደመሆኑ ሰው ራሱን ሳይወድ ባልንጀራውን ሊወድድ አይችልም። ስለሆነም የራሳችንን ሰብእና ዐውቀን እና

ተረድተን፣ ደካማ አርመን እና አሻሽለን መገኘት ይኖርብናል። ያን ጊዜ ጥሩ ሰው እንዲሰጠን እግዚአብሔርን

ለመጠየቅም የሞራል ብቃቱ ይኖረናል።


ብዙዎች በሚጀምሯቸው ጾታዊ ግንኙነቶች መጽናት ሳይችሉ የሚቀሩት እና ከብዙ ሰዎች ጋር በእንደዚህ ያሉ ግንኙነቶች

ውስጥ እየገቡ የሚወጡት ከአጋሮቻቸው የሚፈልጉትን ነገር አስቀድመው ባለማወቃቸው ነው። ፍላጎትን መለየት

መቻል ከምን ዓይነት ሰው ጋር መሆን እንደምንፈልግ እና እንደምንችል ለማወቅ እና ለመወሰን ይረዳል። ፍላጎቱን

ሳይለይ ወደዚህ ሕይወት የሚገባ ሰው ግን የማያስደስቱትን እና ሊቋቋማቸው የማይችላቸውን ጠባያት እና ድርጊቶች

በአጋሩ ላይ ሲያገኝ ለመለያየት ይገደዳል። የሰዎችን ጠባይ ከውጭ አይተን በአንዴ ማወቅ ባይቻልም እኛ የምንፈልገው

ጠባይ ያለቸው ሰዎችን በመጠኑ መረዳት ግን ይቻላል፡፡ ስለሆነም መለያየትን ለመቀነስና ተያይዞ የሚመጣውን ጉዳት

ለማስቀረት ወደ እጮኝነት ከመግባት አስቀድሞ ከራስ መክሮ፣ ስሜትን አድምጦ የራስን ፍላጎት መለየት ይገባል።

ሐ. ኢኮኖሚያዊ ዝግጁነት

ይህ በዋናነት ከገንዘብ እና ራስን እንዲሁም ቤተሰብን ለማስተዳደር ካለን ዓቅም ጋር የሚገናኝ ዝግጅት ነው። አንድ

ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ወደ እጮኝነት ሲገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትዳር ለመግባት ዝግጁ መሆኑን እና

የሚመሠርተውን ቤተሰብ ለማስተዳደር ዓቅም ያለው መሆኑን አስቀድሞ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህም ሌሎች

ዝግጅቶች ሁሉ ወደ እጮኝነት እና ትዳር ኃላፊነት ከመገባቱ በፊት አስቀድሞ የሚታሰብበት እንጂ ከገቡበት በኋላ

የሚነሣ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ዝግጁ መሆን ማለት ከትዳር በፊት ባለጸጋ መሆን አልያም

ቤት እና መኪና መግዛት የሚል ዝርዝር መሥፈርትን ማስቀመጥ ማለት ሳይሆን ራስን እና ቤተሰብን ማስተዳደር

መቻላችንን እርግጠኞች መሆን ማለት ነው። ይህም ብዙዎች እንደሚያስቡት ወንዶችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን

እኅቶችም ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ከእነዚህ እንጠበቅ!

የእጮኝነት ሕይወት ከላይ ያነሣናቸውን እና የመሳሰሉትን መንገዶች ተጠቅሞ ዝግጁነትን ካረጋገጡ በኋላ ብቻ

ሊገባበት የሚገባ ሕይወት ነው። ከዚህ ባለፈ ብዙዎች ወደዚህ ከሚገቡባቸው የተሳሳቱ ምክንያቶች ራስን መጠበቅ

ያስፈልጋል። እነዚህም ሁሉም ጓደኞቼ የፍቅር አጋር አላቸው፣ እድሜዬ ገፍቷል፣ ብቸኝነት ይሰማኛል እና የመሳሰሉት

ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

በአንድ ዓይነት ዕድሜ ወይም አካባቢ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ዓይነት ዝግጁነት አላቸው ማለት ስላልሆነ እና ሁሉም

ወደዚህ ሕይወት የገቡ ሰዎች አስበውበት እና ተገቢውን ዝግጅት አድርገው ስለማይገቡ የሌሎች ይህንን ሕይወት

መጀመር እኛም እንድንገባበት በቂ ምክንያት ነው ማለት አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አትሳቱ! ክፉ ባልንጀራ

መልካሙን አመል ያበላሻል” (፩ቆሮ ፲፭፥፴፫) እንዳለ ተገቢውን ዝግጅት ሳናደርግ ከጓደኞቻችን ያነስን እና የተበለጥን

መስሎን አልያም በእነርሱ ግፊት ወደ እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት እንዳንገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

እንኳን ሳንዘጋጅ ዝግጁ በሆንበት ጊዜ ላይ እንኳ ተገቢው ሰው ወደ ሕይወታችን ካልመጣ በትዕግሥት እና በእምነት

ሆኖ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠበቅ ይገባል እንጂ ዕድሜን ምክንያት አድርጎ ወደ እጮኝነት አልያም ወደ ትዳር

ሕይወት መግባት አይገባም። “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ ዐውቃለሁ” (ኤር.፳፱፥፲፩) እንዳለ እግዚአብሔር በጎውን
ነገር እንዲያደርግልን ምልጃ እና ጸሎታችንን ከምስጋና ጋር ለእርሱ ማሳወቅ እንጂ በአንዳች መጨነቅ አይገባንም። (ፊል.

፬፥፮)።

ዕድሜአችንን ተከትለው በሚመጡ የሆርሞን ለውጦች እንዲሁም ባለን ማኅበራዊ መስተጋብር ምክንያት በየጊዜው

የሚሰሙን እንደ ብቸኝነት፣ ያለመወደድ እና ያለመፈለግ ስሜት፣ ፍትወት እና የመሳሰሉት ወደ እጮኝነት እና ትዳር

እንዳይገፋፉን ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እጮኛ መያዝ ለጊዜው ችግሮቹን የፈታ መስሎ ቢሰማንም የችግሩ

ምንጭ ከእግዚአብሔር እና ከራስ ጋር አለመሆን እንጂ እጮኛ ማጣት አይደለምና ጊዜውን ጠብቆ ማገርሸቱ አይቀርም።

በዚህ ጊዜ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን አብሮን የሆነውን ያንን ሰውም እንጎዳለን። ክርስቲያን አዘውትሮ በሚቀበለው ቅዱስ

ቁርባን ምክንያት እግዚአብሔር ሁሌም አብሮት አለ። ዕለት ዕለት በሚሳተፍበት የማኅበር ጸሎት (ቅዳሴ) አማካኝነት

ከቅዱሳኑ ጋር ኅብረት አለውና አንዳች ጓደኛ ባይኖረው እንኳ መቼም ብቸኛ አይሆንም። የራበው ሰው ምግብ

እንደማይመርጥ ሁሉ አንዳች ጉድለት በተሰማው ጊዜ የፍቅር ጓደኛ የሚመርጥ ሰውም ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ

አይቻለውም። ጎዶሎአችንን ለመሙላት ብቻ ብለን ወደ እጮኝነት መግባት እጅግ የከፋ ስሕተት ነው።

ፍትወትን ለማስታገስ፣ ሌሎች ሲያወሩ የሰማናቸውን፣ በየፊልሙ ያየናቸውን፣ በመጻሕፍት ያነበብናቸውን ድርጊቶች

ለመሞከር እና ለማወቅ ወደ እጮኝነት መግባት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስንቀን፣ ከመንግሥቱም የሚያርቀን

ከመሆኑም በላይ እኛንም ሆነ ለዚህ ርኩሰት ተባባሪ ያደረግናቸውን ወዳጆቻችንን ለልብ ስብራት ለሚዳርግ መጠላላት

ያጋልጣልና ለእንደዚህ ዓይነት የኃጢአት ግቦች ወደ እጮኝነት መግባት ነውር ነው።

ይቆየን፡፡

You might also like