You are on page 1of 62

መንፈሳዊ የህይወት ክህሎት

በማኅበረ ቅዱሳን ደቡብ ማስተባበርያ

ሀዋሳ

መስከረም 7 – 8፣ 2012 ዓ.ም.


የሥልጠናው ዓላማዎች
ከዚህ ሥልጠና በኋላ ተሳታፊዎች፡ -
የህይወት ክህሎትን ይተረጉማሉ፡፡
የህይወት ክህሎቶችን በህይወታቸው ውስጥ ለማልማት ይወስናሉ፡፡
የህይወት ክህሎቶችን ዓይነቶች ይለያሉ ይተነትናሉ
ራሳቸውን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት የሚያስችሉ ክህሎቶችን
ይለማመዳሉ፡፡
ከሰዎች ጋር በፍቅር የመኖር ክህሎቶችን ይለማመመዳሉ፣
ያዳብራሉ፡፡
ችግሮችን የማስተዋልና የመፍታት ክህሎቶችን ይለማመመዳሉ
ያዳብራሉ፡፡
የሥልጠናው ይዘቶች
የሥልጠናው ዋና ዋና ይዘቶች፡ -
የህይወት ክህሎት ትርጉም
የህይወት ክህሎት ልማት አስፈላጊነት
የህይወት ክህሎት ዓይነቶች
ራስን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት የሚያስችሉ ክህሎቶች፡፡
ከሰዎች ጋር በፍቅር የመኖር ክህሎቶች፡፡
ችግሮችን የማስተዋልና የመፍታት ክህሎቶች፡፡
መግቢያ
መንፈሳዊ የሆነ ሰው (አማኝ) አራት ነገሮችን ሟሟላት አለበት፡ -
እግዚአብሔርን ማመን፡ - እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ ይችላል፣ የሚሳነው
ነገር የለም ብሎ ከልብ መቀበል ነው፡፡ ዮሐ ፩፡፫፡
በእግዚአብሔር መታመን፡ - ታማኝ አገልጋይ መሆን ማለት ነው፡፡ አንድም
ትውክልት ነው (ዕምነትን በግብር መግለጽ ማለት ነው፡፡ ኣንድም እግዚአብሔር
የሚያስፈልገኝን ሁሉ ያደርግልኛል ባያደርግ እንኳ ያላደረገው ኣለማድረጉ
ትክክል ስለሆነ ነው ብሎ መቀበል ነው፡፡ ዳን. ፩፡ ፰፤ ዳን. ፫፡ ፲፫ - ፴፣
መመስከር፡ - ያመኑትን ለሌሎች መግለጽ ነው፤ የማይመሰክር ሰው ለማመኑ
እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
መተግበር፡ - ባመንበት መኖር ማለት ነው፡፡
የህይወት ክህሎትን የምንማረው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑ መታወቅ
አለበት፡፡
መግቢያ
የህይወት ክህሎትን የምንማረው በተጠቀሱት እውነታዎች ውስጥ ነው የምንለው፡
-
እግዚአብሔርን ሳናምን የህይወት ክህሎት አዳበርን ኣላዳበርን ትርጉም
የለውም፤ ምክንያቱም የመንፈሳዊነት ዓላማው ሰማያዊ መንግስትን መውረስ
እንጂ ምድራዊ ውጤታማነት ኣይደለም፡፡
በእግዚአብሔር ሳንታመንም የህይወት ክህሎት አዳበርን ኣላዳበርን ትርጉም
የለውም፤ ምክንያቱም ወደ ራስ ትምክህትና ክህደት ያመራናልና፡፡
ማመናችን መገለጫው ምስክርነታችን ነውና የሁሉ አድራጊ እግዚአብሔርን
ኣምነን ሥራውን ካልመሰከርን ትርጉም የለውም፡፡
በእግዚአብሔር ኣጋዥነት የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት በህይወት
መኖራችንን ያረጋግጣል፡፡ ሕያው መሆናችን መገለጫው ማመናችን ብቻ
ሳይሆን ግብራችን መሆኑ የታወቀ ነውና፡፡
የህይወት ክህሎት ትርጉም
የህይወት ክህሎት የሚባሉት
ሰዎችን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተገቢ የሆኑ
ሁኔታዎች እና አጣብቂኝ የሆኑ ችግሮች በሚገባ ተቋቁመን በአሸናፊነት
እንድንወጣ የሚያስችሉ መንፈሳዊ ብቃቶች ናቸው፡፡
በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ደስታዎች ወይም ሃዘናት፣ ስኬቶች
ወይም ውድቀቶች እንደ አመጣጣቸው በተገቢው መንገድ በማስተናገድ
የተሻለ ዛሬን የምንፈጥርባቸው እና ለተሻለ ነገ (ለምድራዊም ሆነ ሰማያዊ
ህይወት) የምንዘጋጅባቸው ውጤታማም የሚያደርጉ ችሎታዎች ናቸው፡፡
በምድር ላይ የምንኖረውን ህይወት በፈቃደ እግዚአብሔር በመምራት
ለገነት ለመንግስተ-ሰማያት የሚያበቃ ግብር የምንይዝባቸው ክህሎቶች
ናቸው፡፡
የህይወት ክህሎት ልማት አስፈላጊነት
እነኝህ ክሂሎች
የአዕምሮን ጤንነትንና ብቃትን የሚያሣድጉ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት ክሂሎቹን
በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ውስጥ (በማኅበራዊ ህይወት፣ በሙያችን፣ ወዘተ) መጠቀም
ይቻላል፡፡
በሰዎች መካከል ከፍ ሲልም በሀገራት መካከል የሚከሰትን ግጭት ለመከላከል ብሎም
ለማስወገድ፣
ሃብትን በአግባቡ እና በተገቢው መልኩ በውጤታማነት ለመጠቀም፣ ወዘተ የህይወት
ክህሎት ወሳኝ ናቸው፡፡
በአጭሩ ሰዎች በተለይም ወጣቶች ራሣቸውን በመጠበቅ እና ጤናማ እና ውጤታማ
ማህበራዊ ግንኙነት በመመስረት በህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላሉ፡፡
በመሆኑም አንድም ህይወታችንን በሁለት እግሯ እንድትቆም ስለሚያደርጉ
በተጨማሪም በህይወት ውስጥ በልምምድ የሚዳብሩ በመሆናቸው የህይወት ክሂሎች
ተብለዋል፡፡
የህይወት ክህሎት ልማት አስፈላጊነት
በዚህ መሠረት የህይወት ክህሎት መማር፡-
ተገቢ ወይም ጤናማ የህይወት ምርጫ ማድረግ ያስችላል
ተገቢ እና የታለመበት ውሣኔ መውሰን ያስችላል
ጤናማ የሆነ ጠባይን ለመጐናፀፍ ያበቃል
አደገኛ የሆኑ የጤና ሁኔታዎችን እና ጠባያትን ለመረዳት እና
ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት ያስችላል፤ ወዘተ፡፡
የምድር ኑሮአችን ተገቢ እና ለሰማያዊ ሃብትና በረከት
የሚያበቃ እንዲሆን ያስችላል
የህይወት ክህሎት ዓይነቶች
በዋናነት ሦስት ዓይነት አጠቃላይ የህይወት
ክህሎቶች አሉ፡፡ እነሱም፡ -
ራስን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት
የሚያስችሉ ክህሎቶች፡፡
ከሰዎች ጋር በፍቅር የመኖር ክህሎቶች፡፡
ችግሮችን የማስተዋልና የመፍታት
ክህሎቶች፡፡
፩. ራስን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት
የሚያስችሉ ክህሎቶች፡፡
ይህ ምድብ በውስጡ የሚከተሉትን ኪሂሎች ይዟል፡
ራስን ማወቅና መረዳት
ራስን መውደድና ማክበር (ለራስ ዋጋ መስጠት)
በፈጣሪ ሃሳብ ከፈጣሪ በታች በራስ መተማመን (ለራስ
በራስ ኃላፊነትን መውሰድ)
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር
ጭንቀትን መቋቋም
ራስን ማወቅና መረዳት
ራስን መረዳት ማለት ተሰጥኦን መለየት፣ ስሜትን እና ፍላጐትን ማወቅ፣ የህይወት
ፍልስፍናችንን መረዳት፣ ራሳችን ለራሳችን ብሎም ሰዎች ለእኛ የሚሰጡንን ቦታ
በማህበረሰብ ውስጥ መገንዘብ፣ ድክመት እና ጥንካሬአችንንም ማጤን …. ማለት ነው፡፡
በሌላ አባባል ‘እኔ ማን ነኝ?’ ለሚለው ጥያቄ በቂ እና ግልጽ መልስ መስጠት መቻል
ነው፡፡
ራስን ማወቅ የሚከተሉትን ክሂሎቶች (ሁኔታዎች) ያጠቃልላል፡ -
የአካል ክፍሎቻችንን ማወቅ
የራስን አመለካከት (እምነት) ማወቅ
የራስን ጥንካሬ እና ተሰጥኦ መለየትና ማዳበር
የራስን ጉድለት (ደካማ ጐን) መረዳት እና ለማሸነፍ መትጋት
በህብረተሰብ ውስጥ ያለንን ቦታ ማወቅ (መረዳት)፡-
ተግባር ፩፡ - ራስን የመለየት ተግባር
ራስን ማወቅና …
ስንወለድ ንጹህና እጅግ መልካም ሆነን ነበር፡፡ ዘፍ፡ ፩፡ ፴፩
ነገር ግን አሁን ላለን ማንነታችን መሠረት የሆኑን፡-
አስተዳደጋችን እና ቤተሰቦቻችን፣ ዘመዶቻችን እና ሌሎች በህብረተሰባችን ውስጥ
ቦታ የሚሰጣቸው ታላላቅ ሰዎች ያላቸው አመለካከት፣ ባህል፣ ሥርዓት፣ ….
በሃይማኖታችን ውስጥ በቃልም፣ በንባብም፣ በምልከታም፣ ወዘተ የምንማራቸው
ነገሮች እና ሁኔታዎች፡፡
የጓደኞቻችን አመለካከት፣ አስተሣስብ፣ ዕምነት ….
የምንማርበት ት/ቤት አጠቃላይ ሁኔታ
የቤተሰቦቻችን ወይም የራሣችን ኢኮኖማያዊ ሁኔታ
ያደግንበት (የምንኖርበት) ማህበራዊ እና ተፈጥሮአዊ አካባቢ
የህብረተሰባችን ልምድና ባህል፤ ወዘተ ናቸው
ራስን ማወቅና …
አሁን ላለን ማንነታችን መሠረት የሆኑን …
በህይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ልምዶች እና ተሞክሮዎች
የምናዳምጣቸው ወይም የምናነባቸው የመረጃ (የዜና) ምንጮች
የራሣችን ሥነ ህይወታዊ (ተፈጥሮአዊ) ሁኔታዎች (ቅንብር) በሌላ አባባል
በሰውነታችን ውስጥ የሀብለ በራሂያን (hormons) ሁኔታ፤ ወዘተ
እነኝህ የዘረዘርናቸው ነጥቦች ራስን በማወቅ ሂደት ውስጥ ወይም በእኛ ህይወት ውስጥ
ወሣኝ የሚባሉ ነገሮች (ነጥቦች) መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ የእነኝህ ተጽዕኖ
በህይወታችን ውስጥ ግዙፍ ነውና!
እነኝህን ሁኔታዎች በመረዳት ሁኔታዎችን በተገቢው መንገድ መጠቀም ብልህነት ሲሆን
በማንነነታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያደርሱ (ያደረሱ) ሁኔታዎችን ተጽዕኖ መቀነስ
ከተቻለም ማጥፋት ተገቢ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ራስን ማወቅና …
በመጨረሻም የራስን ማንነት የተመለከቱ ሁለት መገለጫዎች እንዳሉ መታወቅ ኣለበት፡ -
እኔነት በሁለት መልክ (መገለጫዎች) ሲታይ
ሃሳባዊ እኔነት
እውነተኛ እኔነት
እኔነት በኣራት መልክ (መገለጫዎች) ሲታይ
እኔ የማውቀው ሰዎች የማያውቁኝ እኔነት
እኔ የማላውቀው ሰዎች የሚያውቁኝ እኔነት
እኔም ሰዎችም የሚያውቁኝ እኔነት
እኔም ሰዎችም የማያውቁኝ እኔነት
እነኝህ እኔነቶች ሲራራቁ (ሲለያዩ) ጥሩ አይደልም ማንነት ተምታቶብናል ማለት
ነውና!!!
ከእግዚአብሔር በታች ራስን መውደድና ማክበር
(ለራስ ዋጋ መስጠት)
ራሳችንን የምንወደውና የምናከብረው ከእግዚአብሔር በታች መሆኑ በቅድሚያ
መታወቅ ኣለበት
ይህ ክህሎት ሰዎች ለእነሱ የተከፈለላቸውን ዋጋ እንዲሁም በራሳቸው ውስጥ
ያሉትን ጥሩ ነገሮች በመረዳት ለራሳቸው ዋጋ ወይም ክብር የመስጠት ክህሎት
ነው፡፡
እኛ በደም የተገዛን መሆናችን መታመን ኣለበት፡፡ የሐ. ሥራ ፳፡፳፰
ከፍተኛ የሆነ ለራስ ዋጋ የመስጠት ብቃት ለተሻለ የህይወት ምርጫና ስኬት
(ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ክብር) መሰረት ነው፡፡
በአንጻሩ ዝቅተኛ የሆነ ለራስ ዋጋ የመስጠት ብቃት (ደረጃ) ለተዛባ እና ጐጂ
ለሆነ የህይወት ምርጫ (ውሣኔ) በር ከፋች መሆኑን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡
ተግባር ፪፡ - ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ እንለይ
ራስን መውደድና ማክበር …

ከፍተኛ ራስን የማክበር ክህሎት ያዳበረ ሰው፡ -


በራሱ ይተማመናል፣ ራሱን ይመራል፣ ወቃሽ ኣይሆንም
የራሱን ጥንካሬ ያውቃል፡፡
የራሱን ድክመት ያውቃል ለማሻሻልም ጥረት ያደርጋል፡፡
ስህተት ሲሰራ ይማርበታል እንጂ ይበልጥ ኣይወድቅበትም
ከሰዎች ጋር በደስታ፣ በፍቅር እና በትብብር በመረዳዳት ይኖራል፡፡
እግዚአብሔርን ያምናል በእርሱም ሌሎች ሰዎችን ያምናል
ራሱን ይጠብቃል፣ ይንከባከባል፤ ኣላስፈላጊ ነገሮችን ኣይሆንም
ይላል፡፡
ራስን መውደድና ማክበር …
ለራስ ዋጋ የመስጠት ክህሎት ለማዳበር የሚከተሉትን ነጥቦች ማጤን ይገባል፡-
ከሚወዱን እና ለእኛ ከሚጨነቁ ሰዎች ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሣለፍ
ከሚንቁንና ለእኛ መልካም ነገር ከማያስቡ ሰዎች ራሣችንን እናርቅ
ደስ የሚያሰኙንን፣ እርካታ የሚሰጡንን … ተግባራትን እናከናዉን
ራሳችንን እናበረታታ እንሸልም
ተሰጥኦአችንን እናዳብር እናሣድግ
ለራሣችን ጥሩ እና መልካም ጓደኞች እንሁን
ጥሩ እና ተገቢ ነው የምንላቸውን ምርጫዎች ለራሣችን በራሣችን እንምረጥ፤ ሰዎች
እንዲመርጡልን አናድርግ፡፡
ለራሣችን፣ ለምርጫችንም ሆነ ለተግባራችን ኃላፊነትን እንውሰድ
ሁሌም ትክክል ነው ብለን የምናምናቸውን ተግባራት ብቻ እንሥራ
ለራሣችንም ለዕምነታችንም ታማኝ እንሁኑ፡፡
ሌሎችን እናክብር በተገቢውም መንገድ እንቅረባቸው፡፡
ርዕይ ይኑረን፣ ርዕያችንንም ለማሳካት እንትጋ፡፡
ከፈጣሪ በታች ፈጣሪን በማመን በራስ
መተማመን
በራስ መተማመን ማለት የምንፈልገው ምን እንደሆነ እና ለምን
እንደፈለግነው በመረዳት የፈለግነው ይፈፀም ዘንደ ባለንበት ተጨባጭ
ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ተገቢ እርምጃ መውሰድ መቻል ነው፡፡
በራስ መተማመን ማለት ለራስ እና ለምናምነው ጉዳይ (ለሃይማኖት)
በተገቢው መንገድ ጽኑ ሆኖ መገኘት ማለት ነው፡፡
በራስ መተማመን ማለት የራስን ስሜት፣ ፍላጎት፣ አመለካከት እና ግምት
በትክክል ራስን በሚገልጽ መልኩ (የሌሎችን ስሜት፣ ፍላጎት፣ አመለካከት
እና ግምት ባለመጫን) ያለፍርሃት የመግለጽ ክህሎት ነው፡፡
ከፈጣሪ በታች ፈጣሪን በማመን …

በራስ መተማመን ማለት እንደ ጴጥሮስ ሦስቴ ከመካድ መታቀብ ወይም መዳን ማለት
ነው፡፡ ማቴ ፳፮፡ ፸
በዚህ ትርጉም መሰረት በራስ የመተማመን ክህሎት የሚከተሉትን ደረጃዎች ተግባራዊ
ማድረግ ይጠይቃል፡-
የምንፈልገውን ነገር ምን እንደሆነ እና ለምን እንደፈለግነው መረዳት
የፈለግነው ጉዳይ በእርግጥ አስፈላጊ መሆኑን ማረጋገጥና ማመን፡፡
ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ተገቢ እና ህጋዊ የመፍትሄ እርምጃ
(የፈለግነውን ነገር የማግኛ መንገድ) መምረጥ
የመፍትሄ እርምጃውን ያለምንም ፍርሃት ተግባራዊ ማድረግ
ከፈጣሪ በታች ፈጣሪን በማመን …
በራስ መተማመን ሲባል ከሁለት ጠባያት ራስን ማራቅ ነው፡ - ይሉኝታ እና
አምባገነን ከሆኑ ጠባያት
ይሉኝታ (ፈሪነት)፡ - የምንፈልገው ምን እንደሆነ እና ለምን
እንደፈለግነው እያወቅን ይሣካልን ዘንድ ምንም ዓይነት እርምጃ
አለመውሰድ፡፡
አምባገነን (በራስ መመካት)፡ - የምንፈልገው ምን አንደሆነ እና ለምን
እንደፈለግነው እያወቅን የፈለግነው ነገር (ጉዳይ) ይሳካልን ዘንደ
ሁኔታውን (ቦታውን፣ ሰዎችን፣ ወዘተ) ያላገናዘበ ተገቢ ያልሆነ ወይም ህገ
ወጥ እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ምሣሌ በድብድብ፣ በማስፈራራት፣
በማታለል (በብልጠት)፣ ወዘተ የፈለጉትን ለማሳካት መጣር፡፡
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር
የሰው ልጅ እንደ እንስሳነቱ እንስሣዊ ጠባያት ያለው ቢሆንም እንደ ሰውነቱ ሰዋዊ
ጠባያት ይጐላበታል፡፡
በዚህ ረገድ እንስሳዊ የሚያሰኘው ጠባዩ በስሜት መጓዙ ነው፡፡
በመሰረቱ ስሜታዊ መሆን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ስሜታዊነት
ከሚጠበቀው በላይ ሲገን ተገቢ ስሜት ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ መፍራት ተገቢ
ሊሆን ይችላል ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ፍርሃት ተገቢ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ይህን
ዓይነት ጠባይ እግዚአብሔርን መርሳት ወይም አለማመን ነው፡፡ በተመሳሳይ መውደድ፣
መናደድ፣ መቆጨት፣ ማዘን፣ መደሰት፣ ወዘተ በልክ እስከሆነ ድረስ ተገቢ ነው፡፡
ነገር ግን ልክ አጥቶ ራስን ሊጎዳ በሚችል ደረጃ በውስጣችን ከነገሰ የቱም ይሁን የቱ
ተገቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ነው ጥልቅ ስሜት የሚባለው፡፡
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር

በሌላ በኩል ደግሞ ያየችውን ወንድ ሁሉ የኔ ካላደረኩ፣ ድምጻዊ ተመልክቶ ድምጻዊ


እሆናለሁ (ካልሆንኩ)፣ አትሌቶች ሲወዳደሩ ተመልክቶ አትሌት ካልሆንኩ የሚል
(የምትል) ከሆነ … በዚህም ራሷን ካስጨነቀች ይህ ጤናማ ስሜት ነው ማለት
አይቻልም፤ ይልቁንም በጥልቅ ስሜት ውስጥ ገብታለች ማለት ነው፡፡ ቲቶ ፪፡ ፲፪ - ፲፫
ሰው ያየው ሁሉ ካማረው፣ የሰማው ሁሉ ካዋለለው፣ በዚህ ሁሉ ሳይገታ ያማረውን
ሁሉ ያዋለለውን ሁሉ ለማግኘት ሁሉንም እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ባለመሣካቱም
የሚበሳጭ ከሆነ በጥልቅ ስሜት ተመርቷል ማለት ነው፤ ለፈተናም ተጋልጧል ያዕ ፩፡ ፲፬
ይህን ዓይነት ሁኔታ ነው የሰውን ልጅ እንስሳዊ ጠባይ ተላብሷል የሚያሰኘው፡፡
ጥልቅ ስሜት የሰውነትን ለውጥ የሚያነሳሳ አጋጣሚ ነው፡፡
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር

የሰው ልጅ ጥልቅ ስሜቱን መቆጣጠር መቻል አለበት፡፡ ይህንን ማድረጉም


ከእንስሳዊነቱ በላይ ስብዕናው መጉላቱን ይገልጻል፡፡
ከፍ ብሎ እንደተገለፀው ስሜት ስንል የመፈለግ (የመጓጓት)፣ የፍርሃት፣
የመውደድ (የፍቅር)፣ የዓይናፋርነት፣ የብስጭት፣ የመደንገጥ ወዘተ ያካትታል፡፡
እነኝህሁኔታዎች ሊገመቱ የማይችሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ወደ አልተጠበቀ
እርምጃ ሊያመሩን የሚችሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነኝህን ስሜቶች መለየት፣
ቀጥሎም ምክንያታቸውን መረዳት፣ በመጨረሻም በስሜቶቹ በማይጐዱበት መሰረት
ሁኔታዎችን (ጊዜን፣ ቦታን፣ ሀብትን፣ ወዘተ) ያገናዘበ ተገቢ ምርጫ (እርምጃ)
መውሰድ ስሜትን መቆጣጠር ይባላል፡፡
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር

ጥልቅ ስሜትን ለመቆጣጠር የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ እናድርግ፡ -


ለራሳችን ታማኝ በመሆን የስሜት መጐዳት ከሚያስከትሉ ነገሮችና ሁኔታዎች መጠበቅ
ለሚቀርቡን ሰዎች ስሜታችንን መግለፅ
ስሜታችንን አንዘንጋ ምክንያቱም ሊነግረን የሚችለው ነገር አለው
የማይመች ስሜት ሲገጥመን ከዚህ ስሜት ለመውጣት የሚያስችሉ ጥሩ እና ተገቢ
አማራጮችን አሰላስለን በመምረጥ ተግባራዊ እናድርጋቸው
ሌሎችንም ሆነ ራሳችንን የማይጐዳ ገንቢ የሆነ ንዴትን እና ሀዘንን መግለጽ የሚያስችል መንገድ
መፈለግ
ምንም ይሰማን ምንም ብቻችንን እንዳልሆንን አንዘንጋ
ሁኔታዎች መሻሻላቸው አይቀርምና የተጐዳን አንሁን
ጉዳተኝነት ከተሰማን እርዳታ እንፈልግ፡፡
ጭንቀትን መቋቋም
ለጭንቀት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች የተለያዩ ከመሆናው ባሻገር በህይወታችን ውስጥ እነኝህ
ምክንያቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው፡፡
ለጭንቀት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ምከንያቶች፡ - የዘመድ መሞት፣ የቤተሰብ መለያየት፣
በቤተሰብ ውስጥ የሚከሰት ግጭት፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚከሰት ችግር (የጤና፣ የማህበራዊ
ህይወት፣ የኢኮኖሚ፣ ወዘተ)፣ ፈተና በሚፈጥረው ጫና፣ ወዘተ..፡፡
እነኝህ ሁኔታዎች በዝቅተኛ ደረጃ ተከስተው ግለሰቡ መቋቋም የሚችላቸው ከሆኑ በመሰረቱ
መልካም ናቸው፤ ምክንያቱም የህይወት ክህሎትን ያዳብራሉ ችግርን የመቋቋም ብቃትንም
ያሳድጋሉ፡፡
በአንጻሩ የገጠመን ችግር ከፍተኛ ሆኖ መቋቋም የማንችለው ሲሆን አደገኛ ነው፡፡
በመሆኑም ማንኛችንም ብንሆን ጭንቀት ሲከሰትብን ልንገነዘበው፣ የጭንቀቱን ምክንያት እና
ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ልንረዳ ብሎም ጭንቀታችንን ልናስወግድ (ልንቋቋም)
የምንችልባቸውን መንገዶች ለራሳችን ልናመለክት እና ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል፤ ጭንቀትን
መቋቋም ማለት ይህ ነው፡፡
ጭንቀትን መቋቋም
ጭንቀት ለመቋቋም የሚከተሉትን እርምጃዎች በየደረጃው ይውሰዱ፡ -
አረፍ ማለት (አረፍ ብሎ ራስን ማዝናናት)
ለአጭር ጊዜ ሌላ ተግባር ማከናወን፤ ለምሣሌ፡- መጽሐፍ ማንበብ፣ መዝሙር ማዳመጥ፣ ቀለል ያሉ
የጉልበት ስራዎችን ማከናወን፣ ወዘተ
ለሚቀርቡን ሰዎች ጉዳዩን ማጫወት
እርዳታ መጠየቅ (እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ)
በአዲስ መንገድ ችግሩን ማስተዋል፣ አማራጭ የመፍትሄ መንገዶችንም መፈለግ፡፡
ራስን ከሚገባው በላይ አለመውቀስ፣ አለመኮነን፤
የቀደሙ ስኬቶችን ማስተዋል ወይም ጥሩነትን ወይም ጥሩ ጐንን ማስተዋል፤
ድክመትን መለየት፤ ነገር ግን ማስተካከል ከሚቻለው በላይ መዘርዘር አያስፈልግም፡፡
ችግሮችና ጭንቀት ማለፋቸው አይቀርም
የመዝናናት ስሜትን እና የሚያዝናኑ ሁኔታዎችን መፍጠርና መጠቀም፤ …
ራስን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት የሚያስችሉ
ክህሎቶች፡፡
ለማጠቃለል ያህል፡ -
እስከ አሁን ራስን መረዳት፣ ማክበርና መግዛት የሚያስችሉ ክህሎቶች
ተመልክተናል፡፡
እነኝህ ክህሎቶች በውስጣቸው የሚከተሉትን ይዘዋል
ራስን ማወቅና መረዳት
ራስን መውደድና ማክበር (ለራስ ዋጋ መስጠት)
በፈጣሪ ሃሳብ ከፈጣሪ በታች በራስ መተማመን
በፈጣሪ ማመንና መታመን
ጥልቅ ስሜትን መቆጣጠር
ጭንቀትን መቋቋም
፪. ከሰዎች ጋር በፍቅር የመኖር ክህሎቶች፡፡

በአጠቃላይ እኛ ሰዎች ማህበራዊ በመሆናችን ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረጋችን


አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ትልቁ ተፈላጊው ነገር ይህን ግንኙነት መልካም፤ የውጤታማነት
መሰረት፣ ለስኬት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችል ማድረግ ላይ ነው፡፡
በዚህ የህይወት ክህሎት ዘርፍ ውሰጥ የሚከተሉትን የህይወት ከሂሎች ተመልክከተናል፡ -
የተግባቦት ክህሎት
ጓደኝነት መመስረትና ማጽናት
የጓደኛን ተጽዕኖ (የአቻን ግፊት) መቋቋም
ያለ አደጋ ግጭትን (አለመግባባትን) መፍታት
ለሰዎች መራራት
የመደራደር ክህሎት
የተግባቦት ክህሎት
የተግባቦት ክህሎት በውስጡ ከሌሎች የቋንቋ ክሂሎች (ማንበብ፣ መናገር እና መጻፍ) ጎን
ለጎን የማዳመጥ ክህሎትን እና የመረዳት ክህሎትን ያካትታል፡፡
ማዳመጥ፡- ሰዎች ለእኛ የገለጹልንን (በቃል ወይም በምልክት) መልዕክት እነርሱ ከገለጹልን
እውነታ አንጻር ተገቢ ትርጉም መስጠት ነው፡፡
መረዳት፡ - መረዳት ማዳመጥን መሰረት ያደርጋል፡፡ ይሁንና መረዳት ከማዳመጥ ባሻገር የሌላውን
ሰው ስሜት በመጋራት ያለበትን (የነበረበትን) እውነታ መገንዘብ ይጠይቃል
ይህም መወያየትና በውይይትም የጋራ ትርጉም መስራት ይሻል፡፡
በእንዲህ ዓይነት መልኩ በተለያዩ አካላት መካከል በሚደረግ ውይይት የሚፈጠረውን ትርጉም
የዘርፉ ባለሙያዎች Negotiated Meaning ይሉታል፡፡ (በውይይት ወይም በድርድር የተገኘ
የሚያስማማ ትርጉም) ማለት ነው፡፡
ይህ አይነት የጋራ ትርጉም በሁለቱ መካከል ሲገነባ ነው መረዳት ተፈጠረ የምንለው፤ ተግባቦትም
ይኸው ነው፡፡
ጓደኝነት መመስረትና ማጽናት
ጓደኛ የህይወት ማጣፈጫ ቅመም ነው፡፡ ይህ እውነት የሚሆነው በእርግጥም
ጓደኛ ጓደኛ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡
ጓደኝነት የህይወት ማጣፈጫ ቅመም የሚሆነው የሚከተሉት ጥቅሞች ስላሉት
ነው፡-
ተግባራትን እና ኃላፊነትን በመተጋገዝ ለመወጣት፣
ፍርሃትን፣ ጭንቀትን በመጋራት፣ ከጭንቀት የምንወጣበትን መንገድ
ለማመላከት፣ በሂደትም ለመረዳዳት፣
ስሜታችንን፣ ፍላጐታችንን ብሎም ተስፋችንን በመጋራት ተገቢ እርምጃ
ለመውሰድ፣
መጻኤ እድላችንን ስኬታማ ለማድረግ አስፈላጊ እና ተገቢ ድጋፍ
ለመሰጣጣት፣ ወዘተ፡፡
ጓደኝነት መመስረትና ማጽናት
ጥሩ ጓደኛ ለመመስረት በቅድሚያ ራስን ጥሩ ጓደኛ አድርጎ ማስገኘት ግድ ነው፡፡ ራስህ(ሽ) ጥሩና
መልካም ሣትሆን(ኝ) ሌሎች ላንተ(ቺ) ጥሩና መልካም እንዲሆኑ ማድረግ አይቻልም ወይም ይከብዳል፡፡
ጥሩና መልካም ጓደኛሞች የሚከተሉት ባህርያቶች አሏቸው፡ -
እርስ በእርሳቸው ይደማመጣሉ
አይናናቁም በስሜትም አይጐዳዱም
አንዳቸው የሌላቸውን ስሜትና ያሉበትን ሁኔት ይረዳሉ፤ በዚህ መሰረት ላይ ይረዳዳሉ፤
ጓደኛቸው ያጋጠማቸውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል ተገቢ መንገድ ይጠቁማሉ፤ ችግሩ
እንዲቀረፍም የበኩላቸውን ጥረት ያደረጋሉ፡፡
እርስ በእርሳቸው ገንቢ አስተያየት ይሰጣጣሉ
አንዳቸው ሌላውን በማይጐዳ መልኩ ይከራከራሉ፣ ይወያያሉ
እርስ በአርስ ታማኝና የሚደገፉባቸው ናቸው
እርስ በእርሳቸው ይከባበራሉ፣ ይደጋገፋሉ፣ ለለውጥና ዕድገትም ይተጋሉ፤ ወዘተ፡፡
ጓደኝነት መመስረትና ማጽናት
በአጠቃላይ የጥሩ ጓደኝነት መሰረቱ ራስን ጥሩና መልካም አድርጐ ማስገኘት ነው፡፡
ሌሎች ለእኛ (ለእኔ) ጥሩና መልካም እንዲሆኑ ከመጠበቅ በፊት ራስን ጥሩና
መልካም አድርጐ መቅረጽ ይገባል፡፡ ለዚህም ከላይ በዝርዝር በቀረቡት የመልካም እና
ጥሩ ጓደኛ መስፈርት መሰረት ራስን በየጊዜው መመዘን እና ማብቃት ብልህነት ነው፡፡
ለራስህ(ሽ) እንዲደረግ የምትፈልገውን(ጊውን) መልካም ነገር ሁሉ ለሌሎች
አድርግ/ጊ/፡፡ በአንጻሩ በራስህ(ሽ) ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን (ጊውን) መጥፎ
ነገር ሁሉ በሌሎች ላይ አትድርግ(ጊ)፡፡
እንዲህ ለማድረግ ታዲያ አስቀድሞ ሂሣብ ወይም ዋጋ መጠየቅ ተገቢ አይደለም
ወይም አይገባም፡፡ ምክንያቱም ጓደኝነት ሸቀጥ አይደለምና!
የጓደኛን ተጽዕኖ (የአቻን ግፊት) መቋቋም

ጓደኛ በህይወት ውስጥ ቅመም ቢሆንም ጓደኝነት በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባው ግንኙነት መሆኑ
መጤን አለበት፡፡
በጓደኞቻችን አማካይነት የሚደረግብን ተጽዕኖ (ግፊት) ብዙውን ግዜ መልካም እና ተገቢ
ቢሆንም አልፎ አልፎ ያልተገባ እና ጎጂ ሊሆን ይችላል፡፡
እናጥና፣ መጠጥ ጎጂ ነው መጠጣት የለብንም፣ ከሰው ጋር መጣላት ጉዳት እንጂ
ጥቅም የለውም፣ ሰው ክቡር ነው ሰው ማክበር ይገባናል፣ መስረቅና ማታለል ፀያፍ ነው፣
ወዘተ ዓይነት ግፊቶች እጅግ መልካም ተጽዕኖዎች ናቸው፡፡
በአንጻሩ የሌሎችን ንብረት መዝረፍ፣ ሳይሰሩ ለመበልፀግ የሚደረግ ጥረት፣ ሌሎችን
ጎድቶ ራስን ማስደሰት ወይም ማበልፀግ፣ ሌሎችን ለአደጋ መዳረግ፣ መስረቅ፣ ወዘተ
ዓይነት ግፊቶች ያልተገቡ ጎጂ የአቻ ግፊቶች ናቸው፡፡
የአቻን ግፊት መቋቋም …
በአጭሩ የአቻ ግፊት ማለት በመልካምም ይሆን በጎጂ ጎኑ የራሳችንን አቋም ትተን
የጓደኛችንን አቋም እንድንከተል የሚደረግ ግፊት ወይም ተጽዕኖ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ የራሳችን የምንለውን አመለካከት፣ እምነት እና ጠባይ
እንድንለውጥ የሚያደርግ ተጽዕኖ ነው፡፡
የአቻ ግፊት በበጎ ጎን ሲሆን ጠቃሚ የሚሆነውን ያህል ባልተገባ መልኩ ሲሆን ደግሞ
ይብዛም ይነስም ጎጂ ነው፡፡
በዚህ መሰረት አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቻችን የምናምነውን ትተን የማናምነውን፣ የሚገባውን
ትተን የማይገባውን እንድንሰራ ሊገፋፉን እንደሚችሉ በመገመት እና በማመን ያለንን
ግንኙነት በጥንቃቄ ልንመራ ይገባል፡፡ ለዚህ ሚዛን መሆን ያለበት ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡
ለዚህም ሲባል የጓደኛን ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል ክህሎት ልናዳብር ይገባል፣ ይህም
እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
የአቻን ግፊት መቋቋም …
የጓደኛን ተጽዕኖ መቋቋም ማለት ያመንባቸውንና መሆን ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች
በተመለከተ በማይስማማ መልኩ እንድንጥስ ሲገፋፉን አይሆንም ብሎ መከላከል ነው፡፡ ቲቶ
፫፡ ፲ - ፲፩
ለምንወዳቸው ጓደኞቻችን ‘አይሆንም’ ማለት እጅግ ከባድ መሆኑ እውን ነው፡፡
ምክንያቱም አይሆንም ስንላቸው ስለእኛ የሚፈጥሩት ግምት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ
በራሱ ያስጨንቃልና ነው፡፡
ከጓደኛችን ጋር በማያጣላንና የጓደኛችንን ክብር በማያሳጣን መልኩ ‘አይሆንም’ ማለት
የሚያስችለን ጥሩ መንገድ (ደረጃዎች) እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እነኝህም ደረጃዎች
የሚከተሉትን አማራጮች ይይዛሉ፡ -
የግፊቱን ወይም ህገ ወጥ ተግባሩን በግልጽ ለጓደኛችን መንገርና ስህተትነቱን (ህገ
ወጥነቱን) እንዲያስተውሉ ማስቻል
በግፊቱ ምክንያት የሚከሰተውን ስህተት ሊያስከትል የሚችላቸውን አደገኛ
ውጤቶች መግለጽ (ግልጽ እንዲሆንላቸው ማድረግ)
የአቻን ግፊት መቋቋም …
ሊከናወን የታሰበው ተግባር ራስንም ሆነ ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ ተግባራዊ
ሊደረግ የሚችልባቸው ሌሎች መንገዶች ካሉ መግለጽ (ማሣየት)
ይህን ሁሉ ገልጸን ጓደኛችን አይሆንም ብሎ(ላ) መጀመርያ ባሰበው(ችው) አደገኛ
መንገድ ካልሄድኩ የሚል(የምትል) ከሆነ መብቱ(ቷ) መሆኑን በመግለጽ መተው
ተገቢ ነው፡፡
ይሁንና በማንኛውም ሰዓት ወደ እኛ አስተሳሰብ መምጣት የሚፈልግ(የምትፈልግ)
ከሆነ ግን በደስታ የምንቀበላቸው መሆኑን መግለጽ ተገቢ ነው፡፡
ልብ በሉ ጓደኛችን (ጓደኞቻችን) መብታቸውን አክብረን ከእኛ ፍላጎት (ዕምነት)
ውጭ ወደ ሌላ መንገድ ሲሄዱ እንደተውናቸው (እንደፈቀድንላቸው) ሁሉ እነሱም
እኛ ወደ አመነው ተግባር እንድናመራ ይፈቅዳሉ ተብሎ ይታመናል፤ መብታችንንም
ማክበር ይጠበቅባቸዋልና፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምኑን ጓደኛ ሆኑ!
የአቻን ግፊት መቋቋም …
በአጭሩ እኛ መብታቸውን እናከብራለን እና እነርሱም የእኛን መብት ሊያከብሩ ይገባል
(ያከብራሉም)፡፡ ካላከበሩ ግን ጓደኞቻችን መሆን አይችሉምና በግልጽ ልንነግራቸው
ይገባል፡፡
ይህንንም አልረዳ ካሉንም ጓደኝነታችንን ልናቋርጥ ይገባል፡፡ ጓደኝነታችንን ችግር
ከተፈጠረ በኋላ በጥል ከምናጣ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ሣንጣላ በስምምነት ብንለያይ
ይሻላል፡፡ ተግባር ፬
አንዳንድ ጊዜ በጓደኛ ተጽዕኖ አማካይነት ሊከሰት የሚችልን ችግር አስቀድሞ በመገመት ራስን
ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ቀላል መንገዶች መከተል ተገቢ ነው፡ -
ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መገመት
ችግሮቹ ቢከሰቱ ምን ማድረግ እንደምንችል አስቀድሞ መወሰን
የምንለያቸው የመፍትሄ መንገዶች ችግሮቹን በቁጥጥራችን ስር ማዋል የሚያስችሉን
ወይም ከነአካቴው የሚያስወግዱልን መሆኑን ማረጋገጥ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ‘ያልጠረጠረ
ተመነጠረ' እንዳሉት እንደሚገጥመን አይጠርጥሩ፡
ያለ አደጋ አለመግባባትን መፍታት
ሰዎች በጋራ በምንኖርበት አኗኗራችን ውስጥ በመካከላችን አለመግባባት እና
ግጭት ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ ምንም የሚያስገርም
አይደለም፡፡ ሌላ ቀርቶ በጣም ከምናፈቅረው ሰው ጋር ልንጋጭ እንችላለን፡፡
ትልቁ ቁም ነገር ከሰዎች ጋር የማያግባቡን ነገሮች ተጋንነው ከቁጥጥር ውጭ
እንዳይሄዱ መጠንቀቅ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ነው፡፡
በመሰረቱ ልዩነቶች እርስ በእርስ ለሞሞራረድ እና ከአንድ የስብዕና ደረጃ
ወደተሻለ የስብዕና ደረጃ ለመሸጋገር ጥሩ መሰረት ናቸው፡፡
ነገር ግን ከላይ እንደተገለፀው ከቁጥጥር ውጭ የመውጣት ዕድል ካገኙ ወደ
ከፋ አደጋ ሊያመሩ ይችላሉ፡፡
ያለ አደጋ አለመግባባትን …
ትንሿን ግጭት ‘ሣይቃጠል በቅጠል' እንደሚባል በእንጭጩ መቅጨት ብልህነት ነው፡፡ ይህ
ታዲያ ስሜትን የመቆጣጠር ክህሎትን፣ ጭንቀትን የመቋቋም ክህሎትን የድርድርን
ክህሎትን በተገቢው ቦታና መንገድ ተግባራዊ እንድናደርግ ይሻል፡፡
ያለ አደጋ አለመግባባትን ለመፍታት የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ ይመከራል፡-
ለሌላው ሰው ምን እንደሚያስጨንቅህ (ያለመግባባታችሁን ምክንያት) በጥሩና ፍቅር
በተመላበት መልኩ መግለጽ፡፡
ስሜትሽን ተቆጣጠሪው እንጂ እንዲቆጣጠርሽ ዕድል አትስጪው፡፡
ሌላውን ሰው በሚገባ አድምጠው በሚገባ ልትረዳውም ሞክር፡፡
በዚህ ረገድ ስም መጥራት፣ መስደብ፣ መቆጣት፣ መጮህ፣ ለመማታት መቃጣት
(መማታት) … ፈጽሞ አይገባም፡፡
ማቻቻል የሚያስችል መንገድን መፈለግ፡፡
ለሰዎች መራራት
መራራት (ማዘን) ማለት በሰዎች ችግር ውስጥ ራስን አስገብቶ ችግሩን እንደራስ ችግር አድርጎ
ለመቅረፍ ጥረት ማድረግን ያመለክታል፡፡
ይህ ማለት የሰዎችን ችግር በመረዳት ያሉበትንም ሁኔታ ከራስ ሁኔታ ጋር በማገናኘት (እኛም
እንደ እነርሱ ባለ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንደምንችል በማሰብ) ችግራቸውን በመጋራት
ችግራቸው የሚቀልበት (ከተቻለም ሙሉ በሙሉ የሚቀረፍበትን) ሁኔታ ማመቻቸት ማለት
ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ህይወት ሲጀመር አደጋ የበዛበትና ውስብስብ ሊሆን የሚችል ቢሆንም ውጤቱ
ግን እጅግ አርኪ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ለሰዎች ማዘን የህይወት ክህሎት በአጭሩ ሲጠቃለል ሰዎችን በመርዳት ራሣቸውን ችለው
ኑሮአቸውን መኖር እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡
ይህ በሰዎቹ ውስጥ የጥገኝነት ስሜት መፍጠርን አይሻም፡፡ ይልቁንም በሁለት እግራቸው
ቆመው በራሣቸው ጉዳይ ራሣቸው መወሰን የሚችሉ ማድረግ ነው፡፡
የመደራደር ክህሎት
የመደራደር ክህሎት የጓደኛን ተጽዕኖ ለመቋቋምና እርስ በእርስ ለመግባባት እጅግ
አስፈላጊ የሆነ የህይወት ክህሎት ነው፡፡
ይህ የህይወት ክህሎት በውስጡ በራስ የመተማመን ክህሎት፣ ለሰዎች የማዘን ክህሎት፣
እና ነገሮችን (ጉዳዮችን) ከራስ መርህ ጋር የማቻቻል ወይም የማጣጣም ችሎታ የሚጠይቅ
(በውስጡ የሚያካትት) የህይወት ክህሎት ነው፡፡
ይህ ክህሎት የራስን ጥቅም አሣልፎ ባለመስጠት የሌሎችንም ጥቅም አሣልፎ
ባለመውሰድ ወይም የራስን ጥቅም ሊከሰት ካለ (ከተከሰተ) ችግር አንጻር አሣልፎ ወይም
ከፍሎ በመስጠት (ዋጋ በመክፈል) ከችግር ራሣችንን የምናወጣበት (የምንታደግበት)
የህይወት ክህሎት ነው፡፡
ምድራዊ በሆነ በማንኛውም ነገር መደራደር ይቻላል፤ ነገር ግን የማንደራደረው አንድ
ወሳኝ ነገር አለ - ክርስትናችን፡፡
፫. ችግሮችን የማስተዋልና የመፍታት ክህሎቶች፡፡
ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ችግርን አታምጣብኝ ማለት
ይከብዳል፤ ምክንያቱም የችግር መግቢያ ቀዳዳዎቹ ብዙ ናቸውና፡፡ ይልቁንም ችግርን
የምቋቋምበት አቅምና የማሸንፍበትን ጥበብ አድለኝ ማለት የተሻለ ፀሎት ነው፡፡
ችግርን ለመቋቋም ብሎም በአሸናፊነት ለመዝለቅ የዚህ የህይወት ክህሎት ዘርፍ
ውስጥ የሚመደቡትን የህይወት ክሂሎች በራስ ውስጥ ማልማት እጅግ በጣም አስፈላጊ
እና ጠቃሚ ነው፡፡
በዚህ የህይወት ክህሎት ዘርፍ ውስጥ የሚመደቡትን የህይወት ክሂሎች በዝርዝር
እንመለከታለን፡፡ እነሱም
በጥልቀት የማሰብ (አርቆ የማስተዋል)
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ክህሎት
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት
ችግር የመፍታት ክህሎት
በጥልቀት የማሰብ (አርቆ የማስተዋል)
አርቆ የማስተዋል ክህሎት በአንድ ሃሳብ፣ ጉዳይ፣ ነገር፣ ሁኔታ፣ ወዘተ ላይ የሚደረግ
ምክንያታዊ ግምገማን ያመለክታል፡፡
እንዲህ ዓይነት ግምገማ ሲደረግ መስፈርት መጠቀም ተገቢ ብቻ ሣይሆን ግድም
ነው፡፡
ከዚህ አንጻር አርቆ የማስተዋል ክህሎት የአንድን ሃሳብ፣ ነገር፣ ሁኔታ፣ ወይም ጉዳይ
ብቃት በጥንቃቄ መመዘን የምንችልበት ብልህነትን መሰረት ያደረገ የግምገማ እና
የማስተዋል ስርዓት ወይም ጥበብ ሲሆን ሰዎች ምን ማመን እና እንዴት መስራት
እንዳለባቸው የሚወስኑበት መንገድ ነው፡፡
በጥልቀት ማሰብ ከምክንያታዊነት ጋር ወይም እኛ ካለን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር
ይያያዛል፡፡ ምክንያታዊነት ማለት አንድን ነገር ለማመን ወይም ላለማመን ወይም
ተግባራዊ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ወይም ችግርን ለመፍታት ምክንያትን
(ምክንያቶችን) መጠቀም ማለት ነው፡፡
በጥልቀት የማሰብ (አርቆ የማስተዋል)
ምክንያታዊነት ደግሞ የሚጀምረው ከራሳችን መሆኑ መታወቅ አለበት:: ይህም በውስጡ
የሚከተሉትን ያካትታል፡ -
ለምናምነው እና ለምንሰራው ምክንያት እንዲኖረን ማድረግና ምክንያቶቹንም መረዳት
የራሳችንን ዕምነት እና ሥራ በጥልቀት መመርመር
ለዕምነታችን እና ለተግባራችን ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች ለሌሎች ማስረዳት
መቻል፡፡
ተግባር ፭፡ - ለምን የማ/ቅ ኣባል ሆናችሁ?
አርቆ የማስተዋል ክህሎት በሚገባ የታለመና በግለሰብ ደረጃ የተቀነባበረ የአስተሣሰብ
ሂደት ሲሆን መረጃዎችን፣ ዘዴዎችን፣ መስፈርቶችን፣ ሁኔታዎችን፣ ወዘተ
የምናብራራበት፣ የምንተነትንበት፣ የምንገመግምበት ብሎም ያንን ተከትሎ ሊመጣ
የሚችለውን ሁኔታ የምንገምትበት ሂደት ነው፡፡
በጥልቀት የማሰብ (አርቆ የማስተዋል)
አርቆ የሚያስብ ሰው ዘወትር መጠየቅ፤ መመርመር ለሚነሱ (ለሚያነሳቸው) ጥያቄዎች መልስ
ለመስጠት የሚተጋ፣ ሚዛናዊ የሆነ አዕምሮ ያለው፣ ነገሮችንም በዚህ መሰረት የሚመዝን፣ ተገቢና
አስፈላጊ መረጃዎችን በመፈለግ ረገድ ትጉህ (ታታሪ) የሆነ፣ አጥጋቢ የሆኑ መስፈርቶችን ሚዛናዊ
በሆነ መልኩ የሚለይ፣ ነገሮችን ወይም ሁኔታዎችን ለመመርመር (ለመመልከት) ፈቃደኛ የሆነ፣
ለውጤት እስከመጨረሻው የሚፀና፣ ….. ጠባይ አለው፡፡
በዚህ መሰረት በጥልቀት የሚያስብ ሰው ጥያቄ ይጠይቃል፣ መልስ ይፈልጋል፣ አማራጭ
መፍትሄዎችን ያነጻጽራል፤ ይህንንም ተከትሎ የማይፀፅተውን ውሣኔ ይወስናል፡፡
በጥልቀት የማሰብ ክህሎት በውስጡ ተያያዥ የሆኑ በርካታ ግቦችን የያዘ እንጂ እሱ ብቻውን ለራሱ
ያለቀለት ግብ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በዚህ መሰረት ሰዎች በጥልቀት የማሰብ ክህሎትን ሲያዳብሩ ከሱ ጋር በተያያዘም ሣይንሳዊ
የምርምር ባህርይን፣ የፈጠራዊ አስተሳሰብ ክህሎት፣ ውሣኔ የመስጠት ክህሎት ብሎም ችግር
የመፍታት ክህሎትም አብረው ይዳብራሉ፡፡
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ክህሎት
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ክህሎት በጥልቀት የማሰብ የህይወት ክህሎትን ተያይዞ (ተከትሎ)
የሚያድግ የህይወት ክህሎት ሲሆን ወደ አዲስ አመለካከት፣ አዲስ አማራጭ መንገድን
የመለየት፣ ነገሮችን በአዲስና ለየት ባለ መንገድ መረዳትን የሚያመጣና የሚያካትት
ነው፡፡
በሌላ አገላለጽ ፈጠራዊ አስተሳሰብ ክህሎት ነገሮችን በሚደነቅ መልኩ የምናይበት
ወይም የምንሰራበት መንገድ ሲሆን በአራት ይዘቶች ወይም ጠባያት ይገለጻል፤ እነሱም፡
-
አንደበተ ርቱዕነት (አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ)፣
ተለማጭነት (አስተሳሰብን በቀላሉ መቀየር)፣
የመጀመርያነት (አዲስ ነገር መፀነስ) እና
ማብራራት (በሌሎች ሃሳብ ላይ መገንባት ወይም ማዳበር) ናቸው፡፡
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ክህሎት
በመሰረቱ አለማችን በአንድ ቦታ የቆመች የረጋች አይደለችም፡፡ ይልቁንም ዘወትር
በለውጥ ላይ የምትገኝ እንጂ፡፡
በዚህ መሰረት የሰዎች ህይወትም ዘወትር በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ አዳዲስ
ከሆኑ ሁኔታዎች ጋር መጋፈጥ ግድ ይላታል፡፡
ህይወት በየጊዜው የሚገጥሟትን ያልተገመቱ እና ያልተለመዱ ሁኔታዎችን
ተቋቁማና አሸንፋ መዝለቅ እንድትችል ይህ ፈጠራዊ አስተሣሰብ የህይወት ክህሎት
ጥቅሙ ጉልህ እና በህይወት ውስጥም ወሳኝ ነው፡፡
ይህ የህይወት ክህሎት በውስጣችን ካልዳበረ በሚገጥሙን ያልተጠበቁና ያልተለመዱ
ችግሮች ተጠላልፈን መውደቃችን በአብዛኛው አይቀሬ ነው -
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ክህሎት
ፈጠራዊ አስተሣሰብ ከላይ እንደተገለፀው ራሱን ችሎ ብቻውን
የሚከሰት ሳይሆን እንደ ቀስተ ደመና በውስጡ በጥልቀት ማሰብ፣ ውሣኔ
የመስጠት ክህሎት እና ችግር የመፍታት ክህሎት አቆራኝቶ ይዟል፡፡
በሌላ አባባል እነኝህ የህይወት ክህሀሎቶች እርስ በእርሳሰቸው
የተቆራኙ ናቸው ማለት ነው፡፡
የተጠቀሱት የህይወት ክህሎቶች ያላቸውን ተያያዥነት መረዳት
ያቻለን ዘንድ የተቀሩትን የህይወት ክህሀሎቶች እንመለከታለን፡ -
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት ይህ ይሻላል፣ ይህ አይሻልም፣ ይህ ይበጃል፣ ይህ ተገቢ አይደለም፣
ወዘተ ማለትን የሚጠይቅ የህይወት ክህሎት ነው፡፡
በሌላ አባባል ውሳኔ የመስጠት ክህሎት ሊሆኑ ከሚችሉ የተለያዩ አማራጮች ወይም
ምርጫዎች መካከል የተሻለውን የመምረጥ ክህሎት ነው፡፡
በመሰረቱ ውሣኔ የሚሹ (ምርጫ እንድንመርጥ የሚያስገድዱን) በርካታ ጉዳዮች በየዕለቱ፣
በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው፣ በየሰከንዱ ይገጥሙናል፡፡ ይሁንና አንዳንዶቹ በባህርያቸው በጣም ተራ
በመሆናቸው ሌላ ቀርቶ ስሜትም ላይሰጡን ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግና እጅግ ትኩረት የሚሹና
ህይወታችንን የሚያናጉ በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ፡፡
ምንም ይሁን ምን የምንወስነው ውሳኔ ውጤታማ በሆነ ደረጃ (ፀፀት በማያስከትል መልኩ)
መወሰን አለበት፡፡
ለዚህም ውሳኔ ከመወሰናች በፊት የውሣኔዎቻችንን ቀጣይ ውጤት በጥንቃቄ መተንበይ ወይም
መመዘን አስፈላጊ ነው፡፡
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት

ውሣኔ የመስጠት ሂደት ጥንቃቄ የሚሻ ተግባር ነው፡፡


በመሰረቱ ውሳኔ የሚሰጠው መጥፎውን ትቶ ትክክለኛውን በመምረጥ ከሆነ ይህ
ሂደት ግራ ቀኙን፣ ፊት ኋላውን ማየት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጥሩውን
(ትክክለኛውን) መምረጥ የሂሊና ጉዳይና ራስንም የማክበር ጉዳይ ነው፡፡
ራሱን የሚያከብርና የሚወድ ሰው ሁል ጊዜ ራሱን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያወጣ
ውሣኔ ይወስናልና፡፡ ተጠያቂነት ሲባል ሁለት ዓይነት ገፅታዎች አሉት፡ -
ከሂሊና (መንፈስ ቅዱስ) ተጠያቂነትና
ከህግ ተጠያቂነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት
ተገቢየሆነ ውሣኔ መወሰን እንችል ዘንድ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ማጤን እና
ከውሣኔያችን በፊትም መከተል ተገቢ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ልቤም አዕምሮዬም የሚነግሩኝን ምንድነው?
ይህ ጉዳይ እኔን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን ይጎዳል?
እውን ጉዳዩ ተገቢ ነው?
ይህን ዓይነት ነገር ሌላ ሰው በኔ ላይ ቢያደርግ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማኛል?
ከወሰንኩና ተግባራዊ ካደረኩ በኋላ ስለራሴ ምን ስሜት ይሰማኝ ይሆን?
የማከብራቸውና የሚያከብሩኝ ሰዎችስ ከውሣኔዬ በኋላ ምን ይሉኝ ይሆን?
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት
እነኝህን እና እነኝህን መሰል ጥያቄዎች ከውሣኔያችን በፊት በምንወስነው ጉዳይ ዙርያ
ራሣችንን ጠይቀን ተገቢ መልስ ልንሻላቸው ይገባል፡፡
በመልሶቹም ላይ ተንተርሰን እውነተኛውን እና ትክክለኛ የሆነውን አማራጭ ለይተን
ብንወስን ራሣችንን ከዘወትር ፀፀት እንደምናድን ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ከላይ በዝርዝር ያየነው የምንወስንበት ጉዳይ እውነት ወይም ሃሰት፣ ትክክል ወይም
ስህተት በሚል ሁለት አማራጮች ውስጥ ሊለዩ ለሚችሉ ጉዳዮችን እና እነዚህን ዓይነት
ጉዳዮች በተመለከተ ውሣኔ እንዴት ማስተላለፍ እንደሚገባን የሚጠቁመንን መንገድ ነው፡፡
በመሰረቱ እውነት ወይም ሃሰት፣ ትክክል ወይም ስህተት ሊባሉ ከሚችሉ ጉዳዮች ባሻገር
እውነት ወይም ሀሰት ማለት የማንችላቸው (የሚከብዱ)፣ ትክክል ወይም ስህተት ሊባሉ
የማይችሉ ጉዳዮች መኖራቸው ሊጤን ይገባል፡፡
ውሣኔ የመስጠት ክህሎት
አንዳንድ ጉዳዮችን ጥሩና ትክክል ብሎ መወሰን ይከብድ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ጥሩና
ተገቢ ውሣኔ መወሰን ይቻል ዘንድ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች መከተሉ ተገቢ ነው፡፡
ከሚያምኗቸው ሰዎች በጉዳዩ ዙርያ ላይ በቂና ጥሩ የሆነ መረጃ ይሰብስቡ
በጉዳዩ ላይ ስለሚሰማዎ ስሜት ከሚቀርቡት ሰዎች በተለይም ከቤተሰቦችዎ ጋር ይወያዩበት፤
ምንአልባት ቤተሰቦችዎ በቂ ባልሆነ ምክንያት ያልተገባ አቅጣጫ እየመርዎት ከመሰልዎት ሌሎች
አዋቂ ሰዎችን (ባለሞያዎችን) ያማክሩ፡፡
በአካልም ሆነ በስሜት ሊደርስቦት የሚችሉ ውጤቶችን በሙሉ ለመለየት ጥረት ያድርጉ ወይም
ይረዱ
የህይወትዎን ዓላማ ያስቡ
የራስዎን ፍልስፍና እና ግለ ዕምነት ያስቡ
የሚመርጡት የውሳኔ ሃሳብ ከህይወት ዓላማዎ እንዲሁም ከራስዎ ፍልስፍና እና ግለ ዕምነት ጋር
የማይጋጭ መሆኑን ያረጋግጡ
ወደ አልተዘጋጁበት ነገር እንዲያመሩ የሚገፋፍዎትን ማንኛውንም ሰዎች ገፋፍቶዋት ወደ
አልፈለጉት መንገድ እንዳይከትዎት ፍጹም ዕድል አይስጡ፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
ችግር የመፍታት ክህሎት ራሱን ችሎ የሚቆም ሣይሆን ከላይ በዝርዝር ያየናቸውን
የህይወት ክሂሎች መሰረት ያደረገና ገቢራዊ ማድረግ የሚሻ የህይወት ክህሎት ነው፡፡
በእርግጥም ችግርን ለመፍታት
በቅድሚያ በችግሩ (በጉዳዩ) ዙርያ በጥልቀት ማሰብ ይገባል፣
ቀጥሎም ከችግሩ ማውጣት የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችን በጥንቃቄ
መፍጠር (መለየት) ይገባል፡፡
ከዚያም ከቀረቡት አማራጭ መንገዶች ውስጥ አደጋ ያልበዛበትን (ቢቻል አደጋ
የማያደርሰውን) እና/ወይም ውጤታማ ሊያደርግ የሚችለውን (ወደ ምንፈልገው
ግብ የሚያደርሰንን) መንገድ ለይቶ እሱን መከተል ይገባል፡፡
እዚህ ላይ ነው አራቱን የ “መ” ህጎች (ማሰብ፣ አማራጮችን መለየት፣ የተሻለውን
መምረጥ እና መወሰን) መከተል የሚገባን፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
እስቲ አራቱን የ “መ” ህጎች በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
መ 1፡ - ማሰብ፡ - ችግርን ለመፍታት የመጀመርያው መጀመርያ የሆነው ደረጃ የችግሩን ችግርነት
መረዳት በመሆኑ ችግሩን በእርግጥም በችግርነት ለመረዳት በጥልቀት ማሰብ ይገባናል፡፡
ያለንባቸው ሁኔታዎች፣ የገጠሙን ገጠመኞች፣ ወዘተ ችግር መሆን አለመሆናቸውን ወይም
ችግር ማስከተል አለማስከተላቸውን የምንረዳው በሁኔታዎቹ ላይ በጥልቀት ስናስብና ስሜት
ሲሰጡን ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ችግር መሆናቸውን (ችግር ሊያደርሱ እንደሚችሉ) እንኳ
አንረዳቸውም፡፡
ማሰብ በሌላ አባባል በስሜት ከመጓዝ መውጣት እና ምክንያታዊም በሆነ መልኩ ሁኔታዎችን፣
ገጠመኞችን፣ ወዘተ መመርመር ማለት ነው፡፡
ብዙዎቻችን ችግር ውስጥ እየገባን እንኳ ወደ ችግር ውስጥ መግባታችን አይታወቀንም፡፡
ለዚህ ዋናው ምክንያት ጉዳዩን ባለማሰብ (በደመ ነፍስ) በመመራታችን (በመያዛችን) ነው፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
እስቲ አንድ ጊዜ ቆም ብለው አሁን እያደረጉ ያሉትን ተግባር ተገቢ ነው ወይስ ተገቢ
አይደለም? አደጋ ያመጣል ወይስ ምንም አደጋ የለውም ወይም ይጠቅማል? ... ብለው
ራስዎን ይጠይቁ፡፡
አሁን ያሉበትን የሕይወት ጉዞ እንዲሁ ይጠይቁ፡፡ የትናንትናውንም ሁኔታዎን በዚህ
መልኩ ይገምግሙ፡፡ በየጊዜው የሚገጥሞትን ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ይገምግሙ፡፡
በየጊዜው የሚገጥሞትን ሁኔታዎች እንዲህ እያስተዋሉ፤ እየመዘኑ ይጓዙ፡፡
እንዲህ ካደረጉ ይህንንም ተግባር ካዳበሩ በእግርጠኝነት ራስዎን ከችግር እየታደጉ
መሆንዎን አይዘንጉ፡፡
ይሁንና ይህ ተግባር የመጀመርያው እርምጃ መሆኑንም አይዘንጉ፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
መ 2: - መምረጥ፡ - ከችግሩ መውጣት የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችን መለየት፡፡
ከገባንበት ችግር የምንወጣበት መንገድ ብዙውን ጊዜ አንድ እና አንድ ብቻ ነው ብሎ
ማሰብ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ይልቁንም በርካታ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶች
እንዳሉ መረዳት ይገባል፡፡ በመሆኑም ቀጥታ ወደ ውሣኔ ከመግባታችን በፊት አሉ
የምንላቸውን አማራጭ መንገዶች በሙሉ አሟጠን ልንለይ ይገባል፡፡
እነኝህንም አማራጭ መንገዶች ከተቻለ በጽሁፍ አሊያም በአእምሮአችን 1፣ 2፣ 3፣
….. እያልን እስከ መጨረሻው ልንዘረዝር ይገባል፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በፈጠራ የማሰብ ክህሎት በአያሌው አስፈላጊ የሚሆነው፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
መ 3: - መለየት፡ - የተሻለውን አማራጭ መለየት
አሁን በሁለተኛ ደረጃ በዝርዝር ያስቀመጧቸውን አማራጮች አንድ በአንድ
የሚመዝኑበት ደረጃ ነው፡፡
ልብ በሉ እያንዳንዱ አማራጭ የራሱ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ሊኖሩት ይችላል፡፡
ስለዚህ በዚህ ደረጃ የእያንዳንዱን አማራጭ መንገድ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በዝርዝር
በመለየት ካሉበት ሁኔታ አንጻር ደካማ ጎኑ ዝቅተኛ የሆነውን (ከተቻለም ምንም ደካማ
ጎን የሌለውን) በአንጻሩ ጠንካራ ጎኖቹ የበዙለትን (ወይም ሙሉ በሙሉ ጠንካራ ጎኖች
ብቻ ያሉትን) አማራጭ መለየት ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡
አንድ በአንድ እያሉ የሁሉንም አማራጭ መንገዶች ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት
የተሻለውን አማራጭ መንገድ መወሰን ወይም መለየት የዚህ ደረጃ ትልቁ ተግባር ነው፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
መ 4: - መተግበር፡- የተሻለውን አማራጭ መንገድ ከለየን በኋላ የመጨረሻ ተግባራችን
የለየነውን የተሻለ አማራጭ መሰረት አድርገን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰን እና ተግባራዊ
እርምጃ ውስጥ መግባት ነው፡፡
እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን መረዳት ይገባናል፡፡
የመጀመሪያው፡- ከዘረዘርናቸው አማራጭ መንገዶች ውስጥ ካለንበት ሁኔታ አንጻር፣
ካለን አቅም አንጻር የተሻለ ነው ብለን የመረጥነውን አማራጭ ወስነን ስንጓዝ
ትኩረታችን በአተገባበራችን እና በመጨረሻው ውጤታችን ላይ እንጂ በተቻለ መጠን
በጥርጣሬ ሌሎችንም መንገዶች ለመሞከር መጣር የለብንም፡፡
ሁለተኛው፡- መርጠን ተግባራዊ ልናደርገው የወሰንነው አማራጭ መንገድ በራሱ
በርካታ ዝርዝር አማራጮች እና/ወይም ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ዝርዝር
ደረጃዎች ሊኖሩት እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡
ችግር የመፍታት ክህሎት
ስለሆነም ከዝርዝር አማራጮች መካካል የተሻለውን አማራጭ
በመለየት በዚያ አማራጭ ውስጥ ያሉትን ዝርዝር ተግባራቶችን
በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡
በመሰረቱ እያንዳንዱን ደረጃ ተግባራዊ ስናደርግ ሊከሰቱ የሚችሉ
ውጣ ውረዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ መገመትም ብልህነት
ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ሊከሰት ይችላል የምንለው ችግር ቢከሰት ምን
እንደምናደርግ አስቀድሞ መወሰን እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ማጠቃለያ
*የህይወት ክህሎት የምንላቸው በእርግጥም ህይወትን የተሳካ እንድትሆን የሚያደርጉ
በኑሮ ውስጥ እየዳበሩ እና እየጎለመሱ የሚሄዱ ክሂሎች ናቸው፡፡
*እነኝህ ክሂሎች በሚፈለገው ደረጃ በስብዕናችን ውስጥ እንዲጎለምሱ ጥረት ማድረግ
ተገቢ ነው፡፡
*በተለይም ማህበራዊ ግንኙነታችን እየላላ እና የሉላዊነት ተጽዕኖ እየበረታ በሄደበት
በአሁኑ ወቅት ብልህነትን ማዳበር ተገቢነቱ አያጠራጥርም፡፡
*ለዚህም ሲባል የህይወት ክህሎት ትምህርት በተገኘው አጋጣሚ መማር ይገባል፡፡
*አሊያ በችግሮች ተጠላልፈን ለነፍስም ሆነ ለሥጋ በማይበጅ ኑሮ ውስጥ መዘፈቃችን
አይቀሬ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር
አይለየን!!!

You might also like