You are on page 1of 8

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

ቅድስት
ርዕስ፡ "እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ!" 1ጴጥ 1፡ 13-15

ዓብይ ጾም በገባ በሁለተኛው ሳምንት "ቅድስት" በመባል ይሰየማል፣ ሥያሜውንም


ቅዱስ ያሬድ ነው የሰየመው፥ በዚህም መሰረት ከዋዜማው እሁድ ጀምሮ ስለ ቅድስት
ሰንበት በቤተክርስትያን ይቆማል፣ በዚህም መሰረት ቤተክርስትያን ሳምንቱን ስለ ቅድስና
ለልጆቿ ታስተምራለች፣

ቅዱስ ማለት የቃሉ ትርጓሜ የተለየ፣ የተመረጠ፣ የሚለዉን ትርጉም ይይዛል፣ ከሁሉ
አስቀድሞ እግዚአብሔር አምላክ በባህሪው ቅዱስ ነው፣ (ጥቅስ) እርሱም ቅዱስ እንደሆነ
የእርሱ የሆነ ሁሉ ቅዱስ ነው፣ ማደርያው ቅድስት ቤተክርስትያን፣ እናታችን ቅድስተ
ቅዱሳን ንፅህተ ንፁሃን ድንግል ማርያም፣ መገልገያዎቹ ቅዱሳት ነዋያት፣ ቅዱሳን
መላዕክት፤ ቅዱሳን ዕለታት፣ ቅዱስ ቦታዎች፣ ቅዱሳን ሰዎች፤ የተቀደሱ ፀበል ቦታዎች፣
እነዚህ ሁሉ ቅድስናቸው የፀጋ የስጦታ ቅድስናቸውም ከእግዚአብሔር ነው፣ የእግዚአብሔር
አምላክ ቅዱስ የባህሪው የሆነ ነው፣

እግዚአብሔር አምላክ "እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፡" ብሎ እኛን


ልጆቹን ልጆቹ የሚያስብለንን ቅድስና የታዘዝነው ነው። እግዚአብሔር ከምዕመናንም
ከአገልጋዮቹ ካህናትም ንፅህና ቅድስና ይፈልጋል። ከሶስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር
ወልድ ከእናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ንፅህተ ንፁሃን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ፍፁም
ሰው ሆኖ በዚህ ምድር በሚመላለስባት ወቅት ወንጌልን ሲያስተምረን ብዙዉን ግዜ
የክርስትና ተጋድሎ ህይወትን፤ ቅድስናን በፍሬ መስሎ አስተምሯል።

የዘሪውን ምሳሌ ማር (4፡ 1-9)


የበለሷን ፍሬ ሉቃ (13፡ 6-10)
ፍሬ ያልተገኘባት ቅርንጫፍ ተቆርጦ ለእሳት እንደሚጣል (ማቴ 7:24)
ፍሬ የተባለች ቅድስና ነው። እግዚአብሔር በፍሬ የመሰለልን፡ ከእኛ ፍሬ እጠብቃለሁ ሲል
ቅድስናን ከእናንተ እፈልጋለሁ ማለቱ ነው። የቤተክርስትያን ሊቃውንት ሲያስተምሩ
ሐይማኖትን ልክ እንደ ዛፍ ፍሬ ይመስሏታል። የዛፍ ፍሬ በእጅ የምትያዝ ማዳፍ ያማታክል
ትንሽ ብትሆንም፤ በአፈር ተክለዋት፡ ኮትኩተዋት፡ በማዳበርያ ተንከባክበዋት ትልቅ ዋርካ
ትሆናለች። ለብዙ ህዝብ መጠለያም ትሆናለች። ልክ እንደዚህ በፍሬ የተመሰለች በአርባ ቀን
እና በ ሰማንያ ቀን የተቀበልናት ሐይማኖት ናት። በምግባር ማለትም በፆም፤ በፀሎት፡
በስግደት፡ ሚስጥራትን በመካፈል፡ በምፅዋት እና የተለያዩ መከራዎች ሲመጡብን
በመታገስ እና በእግዚአብሔር ኃይል ስናልፍ፡ የፅድቅን ስራ በመስራት ኮትኩተናት ፍሬዋ
ትልቅ ዛፍ እንደምትሆን እኛም ሐይማኖታችን በምግባር ቅድስናን እናፈራለን። ዋርካው
መጠለያ እንደሆነ የእኛም ምግባር ፍሬ ከእኛ አልፎ ለሰው መዳኛ ይተርፋል። ይህ ሁሉ
የእግዚአብሔር ፍፁም ቸር ስጦታ ነው። አምላክነቱን በፀጋ ሰጥቶናል፡ እኛ በምግባር
ትዕዛዙን ስንጠብቅ እግዚአብሔር ማደርያው እንሆናለን። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ
ስራውን ይሰራል፡ ለተቀደስውም አገልግሎት ተሳታፊ እንሆናለን።
ጌታችን በምሳሌ ሲያስተምር ሙሽራው እስኪመጣ እየጠበቁ የነበሩትን 10ሩን ሚዜዎች
ምሳሌ እንመልከት። 10ሩም መብራትን ይዘዋል። 5ቱ ከመብራታቸው ጋር ዘይትን
ጨምረው ይዘዋል። 5ቱ ግን መብራት ብቻ ነበር የያዙት። ሙሽራውም በድንገት መጣ
ዘይት የያዙት 5ቱ፡ ዘይት በመያዛቸው መብራታቸው አልጠፋባቸውም፡ ዘይት ያልያዙት 5ቱ
ግን መብራታቸው ዘይት ባለመያዛቸው ጠፋባቸው። ባለቀ ሰዓትም ዘይት ፍለጋ ሲዘዋወሩ
ቆይተው ዘግይተው ሲመጡ ሙሽራውም በሩን ዘጋባቸው። አላውቃችሁም አላቸው። በነሱ
ቦታ ሆነን እናስባው ምን ያህል ያስፈራ እና የሚያስጨንቅ ይሆን። መብራት የተመሰለ
ሐይማኖት ሲሆን ዘይት ደግሞ ምግባር ነው። አሁንም በዚህ ምሳሌ ሐይማኖት ያለ
ምግባር የሚያስፈርድ እንደሆነ ወይንም ሐይማኖት ብቻውን እንደማያድነን ሲያስገነዝበን
ነው። እነዛን ዘይት ያልያዙት አምስቱ ሚዜዎች ሰነፎች ይላቸዋል። ስንፍና እጅጉን
እግዚአብሔርን የምያስቆጣ የኃጥያት መሰረት ነው። በተራራው ስብከትም ስለ ሰነፍ ሰው
"... ቃሌን የሚያደርገው ቤቱን በዓለት ላይ የሰራ ጎበዝ ሰው ይመስላል። ነፋስ ነፈሰ
ጎርፍም መጣ ማእበልም ቢነሳ ቤቱ አይፈርስም ብሎ የጎበዝ ሰውን ምሳሌ ከተናገረ
በኋላ የሰነፉን ደግሞ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሰራ ይመስላል አለን፡ በነፋስ በማእበል
ቢመታ እንደማይፀና እና እንደሚፈርስ" ማቴ 7፡ 27 ብሏል፡
ስንፍና በጣም መጥፎ ኃጥያት እንደሆነ ልንረዳ እና ክፋቱ ለንስሓ ተነሳስተን እንኳን
እንዳንጥር ጥፋታችንንም እንዳይሰማን ስለሚያደርግ፡ ኃጥያት ብንሰራም ምንም ያህል
አይሰማንም ። ይሄ ታድያ እግዚአብሔርን እጅጉን ያሳዝነዋል፡ እንዳንጠፋ የሚፈልገው ቸሩ
አምላክ ግን በዚሁ ኃጥያት ወድቀን እንዳንቀር በተላያየ መከራ በህይወታችን እንዲመጣ
ይፈቅዳል። እንድንነቃ እና በእዉነተኛ ሃዘን እና ፀፀት እንዲሰማን የተሰወረብንን ኃጥያት
እስኪታየን ድረስ መከራውን ያፀናዋል። ልክ እንደ ፃድቁ እዮብ
ፃድቁ እዮብ "እንደርሱ ያለ ፃድቅ የለም" ተብሎ እስኪመሰከርለት ድረስ ነበር፡ ነገር ግን
በአንድ ፈተና ይፈተን ነበር፡ እርሱም ፃድቅ ነኝ የሚል ሃሳብ በውስጡ ነበረች፡ ለራሱም
ታስታብየው ነበር ....
"ፅድቅን ለበስኩ፣ ቅንንነትንም እንደመጎናጸፍያ ተሽለምኩ" ኢዮ 29:14

"እዮብም በፊታቸው እራሱን ፃድቅ አድርጎነበር እና እነዝያ ሦስት ወዳጆቹ ለእዮብ


ለመመለስ ዝም አሉ" ኢዮ 32:1
እግዚአብሔርንም እኔ ምን አጥፍቼ ነው እያለ ይጠይቀውም ነበር። የልባችንን የኩላሊት
ማመላለስ የሚያውቅ ችር አምላክ ስለሆነ እዮብም ይቺን ኃጥያቱን የምያይለት እርሱ
ስለሆነ ያንን ምንም እንኳ በሰይጣን ከሳሽነት ቢመጣበት የፈቀደው ግን ፍፁም
ሊያደርገው ያቺን እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ እንዳያይ የከለከለችውን ኃጥያት
እንዲያጥብለት አድርጎታል።
እዮብም የእግዚአብሔርን ከስነ ፍጥረት ጀምሮ እያነሳለት ነፋሳትን ከዋክብትን ሚስጥር
አሳይቶ ወቀሳውን ካሳየው በኋላ እንዲህ አለ .... "..አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ ስለዚህ
እራሴን እንቃለሁ፤ ሰዉነቴም ቀለጠ፣ እኔ አፈር እና ዓመድ እንደሆንኩ አውቃለሁ"
ኢዮ 42:6
ብሎ የታደለችዋን የልብ መሰበር አግኝቶ መከራው ሁሉ ከዛች ሰዓት ጀምሮ ቀጥ እንዳለ
እንረዳለን።
ስለዚህ ከሚሰወር ኃጥያት እስክንድን ድረስ እግዚአብሔር አምላክ መከራውን እና
ፈተናውን ያጸናዋል። ዞሮ እንግዲህ መከራ ሁሉ ለበጎ ነው። የሚጠብቅን ነው። ሁሉም
የእርሱ ቸርነት ስራ ነው እና ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን።

ዘይት ያልያዙት ሚዜዎች በአሁኑ ሰዓት ያለነውን በደንብ ይመስለናል። የመኪና ታርጋ
መልዮ ይመስል "እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ" ከሚል ሐይማኖታችን እንደ ብሔር ብሔረሰብ የማልያ
ቲፎዞ ያላላለፈ የሆነብን ስንቶቻችን ነን? የተሰጠችንን የሥላሤ ልጅነት ሳንረዳው ወይንም
ንቀነው በዓለም በምትሰጠን ትምህርት አስተሳሰብ ከሐይማኖታችን ትምህርት
አስበልጠን በስመ ሥልጣኔ ወጀብ ወደ ሞት እየተወሰድን ያለን ስንቶቻችን ነን?
"ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል" እንዲል እኛ በቃል ባናወጣውም፡ ባንናገርውም
በህይወት ስለማንኖረው እግዚአብሔር የለም ለሚሉት ዉስጥ መኖራችንን የማናቅ
ስንቶቻችን ነን? መታመናችን ሁሉ በራሳችን ላይ፡ በገንዘብ፡ በስልጣን፡ በሰው ላይ፡
በእዉቀታችን ላይ፡ በዉበታችን ላይ፡ በዝናችን ላይ፡ በዘራችን ላይ፡ በፖለቲካ ድርጅት ላይ፡
በምናደንቀው ግለሰብ ላይ፡ ስለሆነ ጣዖት ሆኖብን እግዚአብሔርንም አሳዝነነዋል። በስም
ኦርቶዶክስ እንባል እንጂ ምንም ክርስቶስ በእኛ ዉስጥ አይሸትም።

• በቤተክርስታያን መገኘት እንደ ባህል ምናየው፡ እንደ ማህበራዊ ህይወት አካል


የምናየው፡ ብዚዎች አለን።

• እንዲሁም ደግሞ ከባድ ችግር ዉስጥ ስንሆን፡ ወይንም ትልቅ እንዲሳካልን


የምንፈልገው ሲኖር፡ የምንፈልገው ነገር እስክናገኝ ድረስ በቤተክርስትያን ደጅ
እንጠናለን፡ አፅዋማትን እንፆማለን፡ የምንፈልገውን ካገኘን ብኋላ ያ ደጅ መጥናት ያ
ሁሉ ትጋት ያ ሁሉ ገዳማት እየዞሩ በረከትን ማግኘት እንደ ትዝታ የሆነብን
ብዙዎች አለን።

• ሌሎቻችን ደግሞ በቤቱ እንመላለሳለን፡ አገልግሎት እንካፈላለን፡ አስራት


እናወጣለን፡ ወዘተ ግን በመንፈሳዊ ህይወት ምንም ለዉጥ አናመጣም።
ምክንያቱም ብዙ ግዜ ቤተክርስትያን ስለመጣን ፡ ብዙ ትላልቅ መምህራን አባቶች
ጓዶቻችን ስለሆኑ፡ እራሳችንን እንደ ንፁህ ስለምናይ እግዚአብሔር ግን ከእኛ
እንዳልሆነ እንኳን ስለማንመረምር ድንዘን በዝለት በከንቱ እግር መመላለስ
የሆነብን ብዙዎች አለን። እንዲህ አይነቱ ደግሞ ክፋቱ ኃጥያታችንን ስለሚሰዉርብን
(አይደለሁም ብለን ስለምናስብ) ለንስሃ እንኳን አንነሳም። እንዲህ አይነቱ ልብ ደፋር
ስለሆነ ቤተክርስትያንን በዘር ለመከፋፈል ልክ እስኪመስል ድረስ ያደርሰናል።
እነዚህን እና የመሳሰሉትን የሚያሰራውም ሁሉ መንስኤው ስንፍና ነው።
ስንፍና የትዕቢት እናቷ ነች። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ከመገዛት ይልቅ፡
ለህሊናችን ለእራሳችን እንገዛለን። ከእራሳችን አልፎ ደግሞ ነገሮችን በስጋ አስተሳሰብ
ስለምናስብ፡ ሁሉን ነገር በገንዘብ እንደሚሰራ፡ በስልጣን እንደሚሰራ፡ በዘር
እንደሚሰራ ማመን እንጀምራለን። ቤተክርስትያን የክርስቶስ ቤት መሆኑ
ይሰወርብናል። ከዚህ በላይ የከፋ ሞት የት አለ ይሆን? በእውነት በሐይማኖት እያለን
ከዚህ ዓለም የምንሞትው ይሻላል።
ይህ ጉዳይ ከምዕመን ጀምሮ እስከ ላይ ካህናት ድረስ ይፈትነናል በእውነት ቸሩ
አምላክ ይመልሰን።
ስንፍና መከራን የሚያመጣብን ከዋንኛዎቹ ኃጥያት አንዱ ነው። አንድ ክርስትያን
ሰነፍ ነው የሚባለው፡ እንዴት ነው ቢሉ።

በመንፈሳዊ ህይወት ለማደግ ፍላጎት አለመኖር፡

አንድ ክርስትያን ሰነፍ የሚሆነው ዘወትር እራሱን በመንፈሳዊ ደረጃ የት እንዳለ


የማይመረምር፡ ማለት ነው። ባለበት በምቾት የሚቀጥል ማለት ነው።
"ለቅድስና ለመኖር ትሹ ዘንድ" ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል፡ "ማንም የቆመ
የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ" ይላል። አንድ ክርስትያን ዘወትር እራሱን
ለካህን እያስመረመረ፡ እራሱንም በመንፈሳዊ መፃህፍት እያነበበ እየመረመረ፡
የቅዱሳንን ገድል በማንበብ እራሱን እየመረመረ፡ ከዛሬ ነገ የተሻለ ትጋት ሊያደርግ
ይገባል።

ኃጥያትንም ሰይጣንንም የማይቃወም

ከአዳም ጀምሮ ዘወትር የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ለመለየት፡ በኃጥያት ጥሎ


ወደ ዘላለም ሞት የሚወስደን እጅግ ጨካኝ ጠላት እንዳለን አንረዳም። ይህን
ጠላትነት እግዚአብሔር እራሱ " " ብሎ አኑሮታል፡ ታድያ ይህን ጥላትነት
ልናከብረው እና ልንጠቀምበት ይገባል። የሰይጣን አንዱ ተንኮል እንደሌለ እንደራቀን
እንዳሸነፍነው አስመስሎ አዘናግቶ ይጥለናል። ምክንያቱም ዘወትር ስለማንመረምር
ስንፍናችንን ተጠቅሞ ይጥለናል። የሚዋጋን ያማይተኛልን እኛ ግን የምንተኛ ሆነን
ልንገናኝ አልቻልንም። አባቶች ይህንን ተረድተው እስከ ፍፃሜ ድረስ ይዋጉታል
ኃይላቸዉም እግዚአብሔርን ስለሚያደርጉ ድል ያደርጉታል። ሰነፍ ክርስትያን ግን
አይቃወምም።
ኃጥያትንም እንደዛው፡ አንዳንዱን አብሮ አደግ ባህርዬ ነው በሚል ምክንያት
ለመቃወም ጥረት አናደርግም። በጣም ከባድ አድርጎ ስለሚስልብን ለማሰብ እንኳን
አንፈልግም፡ እስከ ባህሪ ኃጥያታችን በቤተክርስትያን እንመላለሳለን። ነገር ግን
"ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ" የሚለዉን ይዘነጉታል። ይሄ ደግሞ
ከእግዚአብሔር ጋር እንዳልሆንን ትልቁ ምስክር ነው። በኃጥያታችን ላይ እርሱ
ስልጣን እንዳለው እና እንደሚያስተወን ማመኑን አንፈልግም ሰነፎች ነን።
እግዚአብሔርም ጥረታችንን ስለሚፈልግ እስክንረዳ እና እስክንጀምር ታግሶ
ይጠብቀናል፡ አልፎም በመከራ እና በፈተና እንድንነቃ ያደርገናል።

እራስ ወዳድነት፡ የራሳችን ስኬት፤ ምቾት ብቻ መጨንቅ ስለሌላው ሰው ግድ


አለመስጠት

ይሄ በሽታ በእውነት አደገኛነቱ ያልተደረሰበት በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን


በልቡ ተጠርንፎ የተያዝበት ነው። ዛሬ በቤታችን የጣፈጠ የለማ እየበላን ከቤቱ
ተፈናቅሎ የሚበላውን አጥቶ በየመንገዱ በስደት መከራ የሚያሳልፈውን አለማሰብ፡
ለይምሱላ ከመመፅወት ይልቅ ከልብ እያዘኑ እያለቀሱ ለእግዚአብሔር አምላክ
መማፀን። እኔ ልራብ እኔ ልጠማ እኔ ልሰደድ እኔ ልዘን እያሉ ሃዘናቸውን እየተሰማን
መካፈል ነው በእውነት ከእግዚአብሔር ዘድ ይቅርታን የሚያሰጥ፤ ፀሎቱም
የሚሰማው። "እናንተ የከርስቶስ አካላት እንደሆናቹህ አታዉቁምን?" እንዲል
ቅዱስ ጳውሎስ
ከሁሉ የሚያስፈራው ደግሞ ከታች እየመጣ ያለው ትውልድ ምንም አይቶ
ስለማያድግ ምን ያህል ከፍቶ እንደሚመጣ ማሰብ እራሱ በጣም ከባድ ነው!

ማጠቃለያ
ክርስትና የተጋድሎ ህይወት ነው። እስከፍፃሜ ድረስ በተጋድሎ የምንሮጠው ህይወት
ነው። ለዚህም የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞትዮስ የጻፈለት መልክት
ላይ በግልጽ አስቀምጦልናል።

"መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጥብቄአለሁ‹ ወደ ፊት


የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለኔ ያስረክባል፤
ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም" 2ጢሞ 4:7 ብሎ በግልጽ
አስተምሮናል።
1፡ የተጋድሎ ህይወት እንደሆነ፡
ከምን ከምን?
- ከራስ ኃጥያት ፡
- ከአዳም ጀምሮ እንደሚያገሳ አንበሳ እይዞረ የማይተኛልን ጨካኝ ጠላት ዲያብሎስ
(1ጴጥ 5:8-10)
- ከሰው የሚመጣ
ከእናዚህ ሁሉ ከሚመጣ ፈተና ኃይላችን እና ብርታታችን እግዚአብሔርን ይዘን ተጋድለን፡
የምናልፈው ህይወት ነው።

2- እስከ ፍፃሜ ድረስ የምንጋደለው ህይወት እንደሆነ


3- ዋጋዉም ሰማያዊ እንደሆነ
4- ለእሱ ብቻ እንዳልሆነ እና መገለጡን ለሚያምኑ ለእኛ ምዕመናን ሁሉ እንደሆነ በግልፅ
ነግሮናል።

ክርስትና ህይወቱን በተግባር የሚኖር አንድ ክርስትያን አኗኗሩ በነብዩ ነህሚያ ግዜ


የኢየሩሳሌምን ግንብ የሚገነቡ እስራኤላውያንን ይመስላል። እነኚህ እስራኤላውያን በአንድ
እጃቸው ጥላትን ተወግተው እራሳቸውን የሚከላከሉበትን መሳርያ ይዘው፡ በአንድ እጃቸው
ደግሞ ግንቡን እየገነቡ ነበር ሰርተው የጨረሱት። ይህም ምሳሌነቱ የአንድ መንፈሳዊ የሆነ
ክርስትያንን ህይወቱን ይገልፃል። በአንድ እጁ መሳርያ መያዙ እና ከጠላት መዋጋቱ የእኛ
ከጠላት ዲያብሎስ የምንዋጋውን ይመስላል። በአንድ እጁ መገንባቱ ደግሞ በንስሃ፡ በፆም፡
በጸሎት፡ በስግደት፡ ሰጋውን በልቶ ደሙን ጠጥቶ ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆኖ በምጽዋት
መንፈሳዊ ህይወቱን የማበልፀጉን ምሳሌ እንደሆነ አበው ሊቃውንት አስረደተውናል።

እኛም ይህን ተረድተን የቀረዉን ግዜያችንን በንስሃ ተመልሰን፡ ለስጋወደሙ ተቀብለን


ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን፡ ተጋድሎዉን እይተጋደልን፡ የፅድቅን ፍሬ የምናፈራ ያድርግልን።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር፡ ወለወላዲቱ ድንግል፡ ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን

You might also like