You are on page 1of 3

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

" ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።"

ዮሐ 19፥27

ከአስራ ሁለቱ የጌታችን ደቀመዛሙርት መካከል የሚስጥር እና የፍቅር ሐዋርያት የሚባሉት ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ
ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ ናቸው። ለእነዚህ ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸው ምክንያት
ቢኖራቸውም አንድ የሚያደርጋቸው ግን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ኃያል ፍቅር ነው። ቅዱስ
ጴጥሮስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ጥልቅ ፍቅር በምሴተ ሐሙስ የማልኮስን ጆሮ በመቁረጡ
ታይቷል። ምንም የጦርነት ልምድ ሳይኖረው እና ከሐዋርያት መካከል በዕድሜ ትልቁ እና ያረጀው እርሱ ሆኖ ሳለ ያ ሁሉ
ሠራዊት በይሁዳ መሪነት የመጡት ጌታችንን ለመያዝ እንደሆነ ሲረዳ አንድ ብቻውን ሆኖ እንኳ ሰይፉን መዝዞ ጌታውን
ለመከላከል ሞክሯል። ይህ ለጌታችን ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል። አንድም በምሴተ ሐሙስ ጌታችን ከሐዋርያት መካከል
አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው በተናገረ ጊዜ "ሁሉ ቢክዱህ እኔ አልክድህም" በማለቱ ለጌታችን ያለው ጥልቅ ፍቅር
ታውቋል ይላሉ አበው። ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ ግን ቅዱስ ዮሐንስ እና ወንድሙ ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ
ዘብዴዎስ ለጌታችን ያላቸው ፍቅር በምን ታውቋል ቢሉ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ ታሪክ አለ። ታሪኩ እንደዚህ
ነው። ማቴ 20:20፤ ማር 10፥32፤ ሉቃ 18፥31

የቅዱስ ያዕቆብ እና የቅዱስ ዮሐንስ እናት የሆነችው ማርያም ባውፍልያ (እንደአንዳንድ ትውፊቶች ሰሎሜ) ጌታችን
ወደኢየሩሳሌም በአህያ ውርንጭላ ላይ ተጭኖ ከመግባቱ በፊት እየወደቀች እየተነሳች በነገሠ ጊዜ ልጆቿን በቀኝ እና
በግራ እንዳያስቀምጣቸው ወይም እንዲሾማቸው ለመነችው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቃል ሲተረጉሙ በነገሠ
ጊዜ እንዲሾማቸው ዮፈልጉ የነበሩት ወንዳማማቾቹ የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ ነውና በነገሠ ጊዜ
እንዲሾመን ሄደሽ ጠይቂልን ብለዋት እንደሆነ ያስተምራሉ። ለዚህ ምክንያቱ በዚያን ጊዜ በሐዋርያት መካከል ተነስቶ
የነበረው የእኔ እበልጣለሁ እኔ እበልጣለሁ የፉክክር መንፈስ እንደሆነ ከዚህ ጥያቄያቸው በኋላ የመጣው የሌሎቹ ሐዋርያት
መናደድና ትንሽ ወረድ ብሎ ጌታችን ለሁሉም የሰጣቸው ተግሳጽ ያመላክታል። ማቴ 20፥24-25 ጌታችን ግን "አንቺ ሴት
የምትለመኝውን አታውቂም " አላት። መልሶ ደግሞ ሐሳቡ የእነርሱ እንደሆነ ያውቃልና ዞር ብሎ ለነቅዱስ ዮሐንስ
"ኢተአምሩ ዘትስእሉ፤ የምትለምኑትን አታውቁም። ትክሉኑ ሰትየ ጽዋዕ ዘአነ እሰቲ ወጥምቀትኒ ዘአነ እጠመቅ
ትጠመቁኑ፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁን? እኔ የምጠመቀውንስ መስቀል ትሸከማላችሁን?" ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም ሳያመነቱ "አዎን አንተ የጠጣኸውን ጽዋ እንጠጣለን። አንተ የተጠመቅከውን ጥምቀት እነሰጠመቃለን። "
በማለት መለሱለት። ጽዋ ያለው ሞትን ነው። ጥምቀትም የሞቱ ትዕምርት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ " ሞቱንም
በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤" እንዲል።
ሮሜ 6:5 በዚህ መልሳቸውም ለጌታችን ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ተገልጿል። በዚህም ከፍቅር ሐዋርያት ውስጥ ይቆጠራሉ።
በ'ርግጥ ጥምቀት የሞት ብቻ ሳይሆን የትንሣኤም ትዕምርት ነው። ይህንንም ጌታችን "ጽዋዕየሰ ትሰትዩ፥ ወጥምቀትየኒ
ትጠመቁ፤ ጽዋዬን ትጠጣላችሁ፥ ጥምቀቴንም ትጠመቃላችሁ።" በማለት ከሞቱም ሆነ ከትንሳኤው ጋር እንደሚተባበሩ
ነግሯቸዋል። በኋላም ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ነጎድጓድ ከሐዋርያት መካከል የመጀመርያው ሰማዕት ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ግን
ሞት ሳያገኘው ቢሰወርም ከምጽኣት በፊት መጥቶ ከሐዋርያት መካከል የመጨረሻው ሰማዕት እንደሚሆን አበው
ይናገራሉ። ሐዋ 12:2፤ዮሐ 21:21-23

ይህ ሁሉ ከሆነ ከአንድ ሳምንት በኋላ ጌታችን ወደኢየሩሳሌም በአህያ እና በውርንጭላዋ ላይ ተጭኖ ገብቶ፣ በዕለተ
ሐሙስ በይሁዳ መሪነት በመጡት ወታደሮች ተይዞ፣ የግፍ ፍርድ ተፈርዶበት በተሰቀለ ጊዜ አስቀድሞ በነቢይ "...
እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ።" ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሐዋርያቱ በሙሉ ፈርተው ሲሸሹ እስከ
እግረ መስቀሉ ድረስ በጽናት ለተከተለው ቅዱስ ዮሐንስ የሚወዳትን እናቱን እናት ትሆነው ዘንድ "እናትህ እነኋት" ብሎ
ሰጠው። ዘካ 13:7፤ ዮሐ 19:25-27
ለቅዱስ ዮሐንስ ተለይታ የተሰጠችበት ምክንያት ድንቅ ነው። የመጀመርያው ምክንያት ከላይ እንዳየነው የቅዱስ ዮሐንስ
ወላጅ እናት የሆነችውን ማርያም ባውፍልያን ክርስቶስ የምትለምኚውን አታውቂም ብሏት ነበርና ልመና የምታውቅ ደግ
እናት ሰጠሁህ ሲለው ነው። ማርያም ባውፍልያ ጌታችንን እየለመነችው የነበረው በነገሠ ጊዜ ልጆቿን በቀኝ እና በግራ
እንዲያነግስላት ነው። ክርስቶስም ስለእርሱ ብለው መከራ እንደሚቀበሉ ቢነግራቸውም በግራ እና በቀኙ
እንደማይቀመጡ ግን አስረግጦ ነገሯቸዋል። ምክንያቱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የንግሥና ዙፋኑ
የተሰቀለበት መስቀል ነውና። ማርያም ባውፍልያም ልጆቼን አንዱን በቀኝህ አንዱን በግራህ አንግሥልኝ በማለት
ስትለምን እየጠየቀችው ያለው አንዱ ልጇ በስተቀኙ አንዱ ልጇ በስተግራው አብረውት እንዲሰቀሉ ነው። ለዚያ ነው
የምትለምኑትን አታውቁም ብሎ ጌታ የገሰጻቸው። ከክርስቶስ ጎን መሰቀል ኃሳር ሆኖ ሳይሆን ሲጀመርም አንግስልኝ
ማለቷ አብረውህ ይሙቱ ማለት መሆኑን አለማወቋ ነው ስህተቷ። ለዚህ ነው ልመና የምታውቅ እናት ሰጠሁህ ብሎ
በወላጅ እናቱ ፈንታ ድንግል ማርያምን የሰጠው። ዮሐንስ ለምዕመናን ሁሉ ወካይ ሆኖ ተቀበላት እንጂ የተሰጠችውስ
ለክርስቲያኖች በሙሉ ነው ይላሉ አበው። ስለዚህ ልመና የምታውቅ እናት የተባለች እመቤታችን በቅዱስ ዮሐንስ በኩል
ተሰጥታናለች። ይህችን እናት ነው ዮሐንስ ወደቤቱ አስገብቶ ያገለገላት።

በሁለተኛነት የምናነሳው የምትወደውን እናቱን ለሚወደው ደቀመዝሙሩ መስጠቱ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላት ፍቅር ከቃላት በላይ ነው። በቤተክርስቲያናችን ሰቆቃወ ድንግል በሚል
የሚታወቀው መጽሐፍ እመቤታችን ለክርስቶስ ያላትን ፍቅር በተሰቀለ ጊዜ ባለቀሰችው አንጀት የሚበላ ለቅሶ
ይገልጸዋል። ሰኔ ጎልጎታ የተባለውም መጽሐፍ ክርስቶስ ከተቀበረ በኋላ ድንግል ማርያም ዕለት ዕለት ወደመቃብሩ
እየሄደች ታለቅስ እንደነበር ተጽፏል። ስምዖን አረጋዊውም በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል በማለት ትንቢት የተናገረው ክርስቶስ
በዋለበት እየዋለች ባደረበት እያደረች ይገድሉብኝ ይሆን ስትል ያሳለፈቻቸውን አምስት መራራ ሐዘናት ሲያወሳ ነው።
ለልጇ ባላት ፍቅርም የተነሳ ሄሮድስ ሊገድለው በፈለገ ጊዜ እስከግብጽ ድረስ ይዛው መሰደዷ ይታወሳል። ፍቅሯ በዚህ
ይታወቃል ይላሉ አበው። በተሰቀለ ጊዜም ልጄን ሰቀሉብኝ ብላ እጅጉን አዝና ስታለቅስ ጌታችን በመስቀል ላይ እንደልጇ
ሆኖ ያጽናናት ዘንድ የሰጣት የሚወደውን ደቀመዝሙሩን ነበር። የተወደደው ሐዋርያ የጌታችንን ውድ እናት በአደራ
ከተቀበለ በኋታ በሚገባ ስላገለገላት እርሷም አብልጣ ትወደው፣ በልቧ ደብቃ ያኖረችውንም የመለኮትንም ነገር ደጋግማ
ትነግረው ነበር። ሉቃ 2:51 በዚህም ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ፍቁረ እግዚእ ብቻ ሳይሆን ፍቁረ ድንግልም እየተባለ
ይጠራል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል ድረስ የተከተለችውን እናቱን እስከ መስቀል ድረስ ለተከተለው
ደቀመዝሙሩ በአደራ ሰጠ። በደረቷ አስጠግታ ያሳደገችውን እናቱን በምሴተ ሐሙስ በደረቱ ተጠግቶ አሳልፎ የሚሰጥህ
ማነው ብሎ ለጠየቀው ደቀ መዝሙሩ እናት ትሆነው ዘንድ ሰጣት። ከመለኮት ወይም ከሰማይ እና ከምድር ንጉሥ ደረት
መጠጋት የባለሟልነት ምልክት ነውና። ድንግል በክልኤ የተባለችውን እናቱን መልአክ ዘበምድር እየተባለ በንጽሕናው
ለሚወደሰው ደቀመዙሙሩ እናት ትሆነው ዘንድ ሰጣት። መለኮትን በማኅጸኗ የተሸከመች፣ በእጇ ያቀፈች፣ የመለኮትንም
ነገር በልቧ ትጠብቅ የነበረች እናቱን ነባቤ መለኮት ለተባለ የመለኮትን ነገር አምልቶ አስፍቶ ለሚናገር ደቀመዝሙሩ አደራ
ሰጠው።

እንደው በዮሐንስ ቦታ ተገብተን አደራ ተሰጠው እያልን እንናገራለን እንጂ ለድንግል ማርያም አደራ ሆነን የተሰጠነውስ
እኛ ክርስትያኖች ነበርን። በአማልጅነቷ፣ በጸሎቷ፣ በማያልቀው ምህረቷ ከሲኦል ቅጣት ታድነን ዘንድ አደራ የተሰጠነው
ለርሷ ነው።

ይሄኔ ነው ዮሐንስ በወንጌሉ ስለትሕትና ራሱን አርቆ በሦስተኛ ወገን "ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደቤቱ
ወሰዳት።" በማለት የጻፈው። እዚህ ጋር ልናነሳው የሚገባን ጥያቄ አለ። ወደቤቱ ወሰዳት ማለት ምን ማለት ነው?

በብሉይ ኪዳን ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ የበሬ ሰረገላ በካህናቱ አስጭኖ ወደከተማው መመለስ ጀምሮ
ነበር። ከርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብም በሙሉ በበገናና በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር። ዖዛ የሚባል ሰው የሚፋንኑትን በሬዎች
ለማስተካክል ሲሞክር ተሳስቶ የእግዚአብሔርን ታቦት በእጁ ስለነካ ተቀስፎ ሞተ። ይህንን የተመለከቱት ሕዝቡም ፈሩ።
" በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? አለ። " 2 ሳሙ 6:9 በዚህ
ምክንያት የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዳዊት ከተማ መውሰዳቸውን ተዉትና አቢዳራ የሚባል ሰው ቤት አስገቧት።
በአቢዳራም ቤት ለሦስት ወር ያህል ጊዜ ተቀመጠች። "የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር
ያህል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። " እንዲል። 2 ሳሙ 6:11 ተሳስቶ የነካት ዖዝ በመቀሰፉ
ምክንያት አስቀድሞ ወደከተማው ለማስገባት ፈርቶ የነበረው ንጉሥ ዳዊት በአቢዳራ ቤት ታቦተ ጽዮን ያመጣችውን
በረከት በተመለከተ ጊዜ በደስታ ወደከተማው ለማስገባት ፈቀደ። በታላቅ በዓልም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደከተማው
አስገባ።

አማናዊቷ ታቦተ ጽዮን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና አቢዳራ የቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌ ይሆናል። በቃልኪዳኑ
ታቦት ውስጥ የእግዚአብሔር አስርቱ ቃላት የተጻፉበት ጽላት እንደሚገኝ ሁሉ በእመቤታችንም ማኅጸን የአብ ቃል ወልድ
ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል። ይህንን ነው ወንጌላዊው ወደቤቱ ወሰዳት በማለት የገለጸው። በሌላ መልኩ ቤት የሕይወት
ትእምርት ነው። ወደቤቱ ወሰዳት ማለት ወደሕይወቱ አስገባት ማለት ነው። ወደቤቱ ማስገባት ብቻ በቂ አይደለም።
ቅዱስ ዮሐንስ ድንግል ማርያምን ወደቤቱ ወስዶ እንደልጇ እየታዘዘ የምትለውን እየፈጸመ አስራ አምስት ዓመት
አገልግሏታል። ወደቤቱ ወደሕይወቱ ያስገባት እንደልጇ ሊታዘዛት ይገባል። በብሉይ ኪዳን አቢዳራ የቃልኪዳኗን ታቦት
በቤቱ ተቀብሎ ቤቱን በረከት ከሞላው አማናዊቷን ታቦት ድንግል ማርያምን ወደሕይወቱ ያስገባ የበለጠ በበረከት
ይሞላል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

You might also like