You are on page 1of 9

ግብረአበር ነኝ!

ገቢር አንድ
(መድረኩ ላይ አንድ ግንብ ሥር ድንጋይ ላይ የተቀመጠ እና ሄድሴት(Headset) ጆሮው ላይ አጥልቆ ስልኩን በአትኩሮት
የሚጎረጉር ወጣት (ዮሐንስ) ይታያል። አለባበሱ ቄንጠኛ ነው። ከላይ ቅጥነቱን የሚያሳይ ቲሸርት ከታች ደግሞ ወደላይ
ታፋው ድረስ የተሰበሰበ ጠባብ ጂንስ ለብሷል። የተጫማው ነጠላ ጫማ አቧራ የቃመ እግሩን ያሳያል። ስልኩን እየጎረጎረ
ብቻውን ያወራል... ብቻውን ይስቃል። አንዳንዴም እንደመደነቅ ...አንዳንዴም እንደመደንገጥ ያደርገዋል። ተመልሶ
ደግሞ ስልኩ ላይ ያቀረቅራል። በዚህ ጊዜ አንድ እርጅና የተጫጫናቸው ዓይነስውር የኔ ቢጤ ወደመድረኩ በበትራቸው
እየተመሩ ይገባሉ። ጥቁር መነጽር ዓይናቸው ላይ ሰክተው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያለበት የሹራብ ኮፍያ አድርገዋል። ቁሽሽ
ካለ ኮታቸው ላይ የደረቡት የመነቸከ ኩታቸው በአንድ ወቅት ነጭ እንደነበር ያስታውቃል። በትራቸውን ባልያዙበት
እጃቸው በኩል ካርቶን ፌስታል እና ሌሎች ኮተቶችን ጉያቸው ሥር ወሽቀዋል። በበትራቸው እየተመሩ ልጁ
ወደተቀመጠበት ይሄዳሉ። ልጁ አላየቸውም ኖሮ ከተቀመጠበት ሳይነሳ ሥልክ መጎርጎሩን ቀጥሏል። ድንጋዩ ጎን ሲደርሱ
ሰው መኖር አለመኖሩን ለማጣራት በሚመስል መልኩ የወጣቱን እግር በበትራቸው ነካ ያደርጋሉ። ልጁ በመመሰጡ የተነሳ
ቀና ብሎም ሳያያቸው እግሩን ዞር አድርጎ ሥልክ መጎርጎሩን ይቀጥላል። አሁንም ጥቂት ጠጋ ብለው በበትራቸው እግሩን
ነካ ሲያደርጉት በተመሳሳይ ዞር ብሎ ሥልኩን ይጎረጉራል። በመጨረሻ ትንሽ ተጠግተው በበትራቸው ሾጥ ሲያደርጉት
ድንገት ብድግ ይልና ደንግጦ ይሸሻል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አሂሂ....አንት ወስላታ!! (ዱላቸውን እርሱ በሌለበት እየወዘወዙ) ደህና አድርጌ አቀመስኩህ አይደል?
(የፌዝ ሳቅ ይስቃሉ)

ጆኒ - እንዴ ...እርስዎ ነዎት እንዴ ጋሽ ቢያድግልኝ (የተመታበትን ቦታ እያሻሸ በማለቃቀስ ድምጽ) ... እኔ ደግሞ ሌላ ነገር
መስሎኝ!( በስጋት ግራ ቀኝ መላልሶ እየቃኘ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ምን ሌላ ነገር ይመስልሃል? ወሮበላ!...እዚህ ደርቀህ በተቀመጥክበት ጥንብ አንሳ መጥቶ እንዳይወስድህ
ነው የደነበርክ? አዪ...እንደው መድኃኔዓለም... እንዴት ያለውን ጉድ ነው የጣለብኝ እናንተዬ። ዓይን እያለው የማያይ
ከንቱ (ጉያቸው ስር ያለውን ኮተታቸውን እያራገፉ) አንደኛውን እንደኔ ቢለይለህማ ተዚህ ግንብም አትሻል! እግዚኦ...

(ይህን እያሉ ሳንቲም የሚቀበሉበትን ፌስታል እና የሚቀመጡበትን ካርቶን አስተካክለው ልጁ ተቀምጦበት የነበረበት ቦታ
ላይ ይቀመጣሉ። ጎረምሳውም እየተቅለሰለሰ ከእርሳቸው እልፍ ብሎ ሌላ ድንጋይ ላይ ይቀመጣል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ማነህ ልጅ.. ማ ነበር እቴ ስምህ? ...ምን የዘንድሮ ልጆች ስም አይያዝ! (ከተቀመጡ እና ከተደላደሉ
በኋላ ለመለመን ብለው የሆነ ነገር እንደረሱ ሁሉ ወደ ወጣቱ ዞረው)

ጆኒ - ጆኒ ነዋ.... ጋሼ ደግሞ! ጆኒ ነው ስሜ....

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኧረግ! ብለህ ብለህ ጂኒ ሆነህ አረፍከው? እግዚኦ... እግዚኦ.... !ወይ ስምንተኛው ሺህ (እጆቻቸውን
እርስ በ'ርስ በየተራ እያማቱ) የለም! ጂኒማ አይሆንም ስምህ! የለም! የለም! ሌላ ካለህ ወዲህ በል እንጂ የሥላሴን ፍጡር
በጋኔን ስምማ አልጠራም። ሆሆ...

ጆኒ- አይ ጋሼ... (በማላገጥ ድምጽ እየሳቀ) ስሜማ ዮሐንስ ነው። ሲያቆላምጡኝ እኮ ነው ጆኒ ጋሼ ...እ... አለ አይደለ ጆኒ
ያራዳው ልጅ... ጭሱ ምናምን... (በመቀናጣት ድምጽ እንደዘመኑ ልጆች እጁን ወደታች ዘቅዝቆ እያወራጨ )
ጋሽ ቢያድግልኝ - አዪዪዪ... አንተን ብሎ ያራዳ ልጅ (ይስቃሉ) እንደው ዮሐንስን የመሰለ ስም ይዘህ ነው ጂኒ ነኝ
የምትል...ሆሆ.... እንዴት ያለ ዘመን ላይ ደረስን እናንተዬ (ዮሐንስ ፊቱ ላይ የነበረው ፈገግታ ጠፍቶ አኩርፎ ፊቱን
ያዞራል) ይልቅ ... ናማህ... ቀረብ በል (ይሉትና ሲቀርብ በሹክሹክታ) ዛሬ ዕለቱ ስንት ነው በል? ንሳማ ንገረኝ! እኔማ
ይኼው እርጅናው እየተጫጫነኝ ሁሉ ተዘንግቶኝ መቅረቱ ነው። በልማ... ንገረኝ እንጂ... ምነው ዘገየህ።

ጆኒ- (በማመንታት ድምጽ ቀኑ የጠፋበት ይመስል) ዛሬ? ዛ...ሬማ ጋሼ... (ሲል ይቆይና ድንገት እንደተገለጸለት) እህህህ...
ዛሬማ ቀኑ ሰኞ ነው። ጋሽ ቢያድግልኝ ደግሞ... አሁን ይህች ትጠፋብኛለች ብለው ነው። (በእርካታ ስሜት ተጥለቅልቆ
ደጋግሞ እጁን ከጉልበቱ ጋር እያጋጨ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኤድያ አንተን ብሎ የተስተማረ... ዕለቱ ስንት ነው አልኩህ እንጂ መቸ ቀኑን ጠየቅኩህ? እ? መላም የለህ
አንተው ... እንደው በየዕለቱ እዚህ እየተጎለትክ ቀንና ሌቱም ሳይምታታብህ አይቀር።

ጆኒ - ጋሼ ደግሞ ሁሌ ስህተቴን እንዳጎሉ ነው። (በማጉረምረም ድምጽ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እርሱንስ ተወው ይልቅ ዕለቱ ስንት ነው? ...ንሳ ንገረኝማህ!

ጆኒ - (ጣቱን ሲቆጥር ይቆይና) ዘጠኝ...አስር... አስራ...አንድ (በለሆሳስ ለራሱ ቆጥሮ) አ....ዎ ዛሬ አስራ ሁለት ነው ጋሼ!
ሰኔ አስራ ሁለት....

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኧረግ! (ደንግጠው ከተቀመጡበት በትራቸውን ጥለው ሲነሱ ልጁም ድንግጥ ብሎ ይነሳል።)

ጆኒ - ምነው? ምን ተፈጠረ ጋሽ ቢያድግልኝ? (ግራ ቀኙን በፍጥነት ዞር ዞር ብሎ አይቶ ለመሮጥ እያኮበኮበ) ፓ... ፓሊሶች
መጡ እንዴ?

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኤድያ (እጃቸውን እያወናጨፉ) የምን ፎሊስ ነው የምትል አንት ወንበዴ ...ፎሊስ እንዳንተ ሥራ ፈት
መሰለህ እንዴ መንደር ለመንደር ሲዞር የሚውል ....ዛሬ አቅለብልቦኻል እንደው....''ያቡዬን ግብር የበላች ፍየል... ለፍልፊ
ለፍልፊ ይላታል" ነው ነገሩ... (በመጠራጠር ድምጽ እርሱ በሌለበት እየገላመጡት)

ጆኒ - ታዲያ ምንድነው ጋሼ?(ትንሽ ተረጋግቶ በትራቸውን ከወደቀበት አንስቶ እያስያዛቸው)

ጋሽ ቢያድግልኝ - የጻድቁን መታሰቢያ ረሳሁ... ያ'ባቴን እረፍት ረሳሁ ልጄ... የዓመቱ እኮ ነው... ቅዱስ ላሊበላ ዛሬ
ይነግሳል እኮ (ለማልቀስ በሚዳዳው ድምጽ ሙሾ እንደሚደረድር ሰው እያጎነበሱ)

ጆኒ - ኧ..... ለዚህ ነው እንዴ? (ይላል በማቃለል ድምጽ) ታዲያ ምን ጣጣ አለው ጋ...ሼ...(እያለ ሊቀመጥ ሲል
ሳይጨርሰው ድንገት በጩኸት ተቆጥተው ያስነታል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - (በድንገተኛ ቁጣ) አንተ ምን ጣጣ አለው ነው ያልክ? (ብለው ሲቆጡ መቀመጡን ትቶ በድንጋጤ ቆሞ
ያያቸዋል።) ምን ጣጣ አለው? እንዴት እንዴት ብትደፍረኝ ነው አንተ ? (የቆመበትን ስላላወቁ በትራቸውን ጠበቅ
አድርገው ይዘው በመጠራጠር ዙርያ ገባቸውን ያያሉ። ዮሐንስ እንዳይመቱት ፈርቶ በመርበትበት ቆሟል።)

ጆኒ - አይደለም እኮ ጋሼ( ጸጉሩን እያፍተለተለ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ዝም በል ...ወትሮም እኔው ነኝ ጥፋተኛ (የመነቸከ ኩታቸውን እያስተካከሉና ለመቀመጥ ድንጋዩን


በእጃቸው እየፈለጉ) "ከልጅ አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት" ነው ከነተረቱ። እንደው የማያምርብኝን አላቻዬ ...ኤድያ!

(ቁጭ ይላሉ! ፈራ ተባ ሲል ቆይቶ አንዴ ግራ ቀኙን በጥርጣሬ ከተገላመጠ በኋላ ዮሐንስም ቁጭ ይላል። ለአፍታ ዝም
ተባብለው ይቆዩና ... እርሱም ስልክ ወደመጎርጎሩ እርሳቸውም ወደ ልመናቸው ይገባሉ።)
ጋሽ ቢያድግልኝ - ስለጻድቁ ንጉሥ... ስለቅዱስ ላሊበላ እናቶቼ.... ስለጻድቁ ንጉሥ

(አንዲት ነጠላ የለበሰች ሴት ምንቅር ምንቅር እያለቼ መጥታ ሳንቲም በንቀት ወርውራላቸው ስትሄድ ዮሐንስ ስልክ
መጎርጎሩን ትቶ በትዝብት ይመለከታታል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እግዚሃር ይስጥልኝ እናቶቼ.... እግዚሃር ይስጥልኝ ...ውሎ ያግባችሁ... የሰው ፊት አያሳችሁ (ይላሉ
ወዳልሄደችበት በኩል ዞረው... ይሄኔ ዮሐንስ ሳቁ ያመልጠውና ቡፍ ብሎ ይስቃል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አንት ወስላታ...ምንድነው የሚያስቅህ? (ይላሉ በሌሉበት በኩል ዞረው... ተጣልተው ቂም አይዙም)

ጆኒ - አይ ልጅቱ ባልሄደችበት በኩል ዞረው ሲመርቁ ገርሞኝ ነው።

ጋሽ ቢያድግልኝ - እሰየው... አበጀሁ... ደግ አደረግኩ... (ይላሉ አሁንም እርሱ ወደሌለበት ዞረው)

ጆኒ- አይ ጋሼ ...(ሳቁን ለማፈን እየሞከረ) እኔም በዚህ በኩል ነው እኮ ያለሁት! (ይስቃል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አዪ.....(ይላሉ በረዥሙ አገጫቸውን በእጃቸው ደግፈው) አረጀሁ ማለት ነው። (በሐዘን እና በመጸጸት
ድምጽ)

(ጥቂት ሲተክዙ ቆይተው አዪዪዪ እያሉ ወደልመናቸው ይመለሳሉ። ትንሽ ቆይቶ)

ጆኒ - ጋሼ?(በመቅለስለስ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አቤት (በመሰልቸት ድምጽ ፊታቸውን ሳያዞሩ)

ጆኒ - ለምንድነው ግን የሚለምኑት? (ከተቀመጠበት ተነስቶ ነው እየተንጎራደደ የሚጠይቃቸው)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ካካካካ (ከት ብለው ይስቃሉ። ሲስቁ እንደዚያ ተክዘው የቆዩ አይመስሉም)

ጆኒ - እህህህህ ምነው? (ይላል በማኩረፍ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አይ ወዲህ ነው... እህ እህህ አሂሂሂ(ሳቃቸውን ለመግታት እየሞከሩ) ሆሆ... አይ መድኃኔዓለም ...ዛሬ
ደግሞ ምኑን ጣልክብኝ ...መቼም የማታሰማኝ የለ! ሆሆ(ይሄኔ ዮሐንስ አኩርፎ ጀርባውን ሰጥቷቸው ይቀመጣል!)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ይልቅ ጨዋታውን ታመጣኸው አይቀር ... መቼም "አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው" አይደለ
ነገሩ? ... እኔም የምጠይቅህ አለኝ። (ይሉታል ወደርሱ እየዞሩና ኩታቸውን እያስተካከሉ)

ጆኒ - የምር (ይላል በመገረም ወደእርሳቸው እየዞረ...)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እንዴታ (ቀረብ እያሉ)

ጆኒ - ለ'ኔ?

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኋላስ?

ጆኒ - ይጠይቁኛ ይጠይቁኝ ጋሼ (በጉጉት ድንጋዩን አስጠግቶ ፊትለፊታቸው ይቀመጣል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ጥያቄው ምንድነው... (አፋቸውን በሁለት ጣታቸው እየጠረጉ)


ጆኒ - እ ?(በጣም በመጓጓት)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ለምንድነው ግን አንተ የማትለምነው?

(ይሄኔ ዮሐንስ ጉጉቱ ጠፍቶ ከተቀመጠበት ይነሳና በተስፋ መቁረጥ አጁን ወገቡ ላይ አድርጎ ይቆማል።)

ጆኒ - እህ...? ጋሽ ቢያድግልኝ ደግሞ ቁም ነገር አያውቁም። (ይላል በመብሸቅ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኧረግ የምሬን እኮ ነው አንት ኩታራ ....ጠዋት ማታ እዚሁ ተጎልተህ ነው የማገኝህ... ለስሙ
ኡምበርስቲ በጥሰሃል... እንደው እዚያም የሚያስተምሯችሁ መጎለት ነው እንዴ? እንደዚያ ተሆነ አንደኛዬን ይህቺን
የምቀመጥባትን ቦታና ኮተቴን ላውርስህና ጡረታ ልውጣ። መቼም የኡምበርስቲ ምሩቅ ባለሞያ ለማኝ እያለ እኔ
አልለምንም!(በማሾፍ ድምጽ) ደግሞ ማነው ይህቺ ስሟ እቴ (ወደላይ እየጠቆሙ)... ዋይ ዋይ ነው ዋይ ላይ....

ጆኒ - ዋይ ፋይ (ብሎ ያርማቸዋል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እ....ርሷ እርሷ ከመጣች ጀመሮ አንተም ሰርክ ቦታዬ ላይ ተጎልተህ ነው የማገኝህ...ሰውም
መመጽወቱን ተወ መሰለኝ ገበያዬም ቀነሰ። እምልህ ይህቺ ዋይ ዋይ ያልካት ነገር...

ጆኒ - ዋይ ፋይ (ብሎ መልሶ ያርማቸዋል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እ....ርሷ ...ስሟም አያምር ታልጠፋ ስም ዋይ ዋይ...

ጆኒ - ዋይ ፋይ (መልሶ ለሦስተኛ ጊዜ ያርማቸዋል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ምነው ላውራበት እንጂ ልጅ ዮሐንስ ...እንደው ትልቅ ሰው ሲያወራ ልጅ ጥልቅ ይላል እንዴ?

ጆኒ - አይልም ጋሼ አይልም

ጋሽ ቢያድግልኝ - አ...ዎ እንደርሱ ነው! ምን እያልኩህ ነበር ልጄ... አ.....ዎ! ምንድነው ታዲያ ተግባሯ ይህቺ ዋይ ዋይ
የሚሏት ነገር። እንደው ገበያ የምታባርር ነገር ትሆን እንዴ?

ጆኒ - አይ ጋሼ ዋይ ፋይዋን ነው ገበያ የምታባርር የሚሉት? (ፊቱን ፈገግታ አልብሶት ለማስረዳት በኩራት ስልኩን ከኪሱ
አውጥቶ ይጠጋል!)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እ... እንደሆነች ብዬ እኮ ነው።

ጆኒ - የለም! ይ'ቺ የምትታይ ነገር አይደለችም። ኔትወርክ ናት ጋሼ። አንዴ ከሞባይሌ ጋር ካገናኘኋት በኋላ ከዓለም ሁሉ
ጋር ታገናኘኛለች። ሳሉት ጋሼ ...በሞባይል ብቻ ዓለምን ሀሉ ማግኘት

ጋሽ ቢያድግልኝ - እግዚኦ እግዚኦ እግዚኦ... በዚች በሞባይሏ?(ይላሉ በመገረም)

ጆኒ - አዎን ጋሼ በሞባዮሏ

ጋሽ ቢያድግልኝ - ታለም ሁሉ መገናኘት?(ይላሉ አሁንም ይበልጥ ተገርመው ባለማመን ድምጽ)

ጆኒ - አዎን ከዓለም ሁሉ ታገናኛለች።

ጋሽ ቢያድግልኝ - ግሩም ነው! ግሩም ነው! እንዲህ ቁም ነገር ኖራለች ለካ!


ጆኒ - ታዲያስ (በኩራት ይመልስና ስልኩን ወደመጎርጎሩ ይመለሳል። ለአፍታ ዝም ተባብለው ይቆዩና)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እምልህ?(ይላሉ ጠጋ ብለው)

ጆኒ - (ስልኩን ከሚጎረጉርበት ቀና ሳይል) ወዬ ጋሼ...

ጋሽ ቢያድግልኝ - ይህቺ ዋይዋይ ያልካት...

ጆኒ - ...እ...

ጋሽ ቢያድግልኝ - ተእግዜርም ታገናኝ ይሆን እንዴ

ጆኒ - አይ አታገናኝም (በማመንታት)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እንደዚያ ተሆነ ትቅርብኝ። ታለም ወዳጅነት የእግዚሃር ወዳጅነት ይበልጥብኛል። (ዮሐንስ ስልኩን
በመጎሮጎር ተጠምዶ አይሰማቸውም። ወደልመናቸው ይመለሳሉ።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ስለጻድቁ ንጉሥ... ስለቅዱስ ላሊበላ እናቶቼ.... ስለጻድቁ ንጉሥ

(ሌላ ጎረምሳ ነጠር ነጠር እያለ መጥቶ ሳንቲም ወርውሮላቸው ይሄዳል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እግዚሃር ይስጥልኝ እናቶቼ.... እግዚሃር ይስጥልኝ ...ውሎ ያግባችሁ... የሰው ፊት አያሳችሁ (ይላሉ።
ይሄን ጎረምሳ ዮሐንስ ከተቀመጠበት ተነስቶ ከዓይኑ እስኪጠፋ ድረስ ያየውና ተመልሶ ለመጠየቅ ጋሽ ቢያድግልኝ ስር
ይቀመጣል።)

ጆኒ - ጋሽ ቢያድግልኝ?

ጋሽ ቢያድግልኝ - አቤት (በመሰላቸት ድምጽ)

ጆኒ - ቅድም ግን ለምንድነው የተበሳጩት ....ጣጣ የለውም ስል

(ጋሽ ቢያድግልኝ ወድያው ፊታቸውን ሃዘን ይሞላዋል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ይኸውልህ ልጄ...ታገሬ ስወጣ ልጅ ነበርኩ ...ትዝ ይለኛል ባ'ስራ አምስት ዓመቴ ለብሔራዊ ውትድርና
ስመለመል... በጦርነቱ የዓይኔን ብርሃን ካጣሁ ኋላ አገሬ ተመልሼ አልገባሁም። ታዲያ አሁን እንዲህ አርጅቼ ነገር መርሳት
ሳልጀምር በፊት ስለልጅነቴ ጥቂት ጥቂት ትዝ ይለኛል። (አሉና ተክዘው ሩቅ ሩቅ ማየት ጀመሩ) ላስታ ሲባል ሰምተህ
ታውቃለህ መቼም...

ጆኒ- አዎ(ይላል በጉጉት ጨዋታቸውን እንዲቀጥሉ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ምን ተማርኩ ነው ያልከኝ ልጄ... ይ...ንጅነር... ይንጅነርነት

ጆኒ - አዎ ጋሼ !

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኋላስ...ድልድይ መገንባት ሕንጣ ማቆም አይደለም ይንጅነርነት?

ጆኒ - አዎን አዎን ጋሼ እንደዚያ ነው


ጋሽ ቢያድግልኝ - እኮ (ይላሉ በትክክለኝነት ስሜት) ይገርምሃል ታዲያ ጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እንዴት ያለ ይንጅነር ነበረ
መሰለህ።

ጆኒ - የምር!

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኋላ...ስ! ይንጅነር ነኝ አላልክም? ስንት ዓመት ተማርክ በል ሕንጻ ማቆም?

ጆኒ - አምስት...

ጋሽ ቢያድግልኝ - ታዲያ አምስት ዓምት ሙሉ ተምረህ ምን ሰራህ? የታለ ያቆምከው ሕንጻ? የታለ ያቅምከው ድልድይ?

ጆኒ - ሥራ ጠፋ እንጂ እኮ... (ያጉረመርማል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ታዲያ መፍትሔው እዚህ ተጎልቶ መዋል ነው? እንከፍ... (ይሉታል አባባሉ ገርሟቸው)

ጆኒ - በአቋራጭ ካልሆነ ጋሼ እዚህ አገር ላይ ሰርቶ መለወጥ አይቻልም። የዘረፉት የተደላደለ ኑሮ ሲኖሩ ታታሪው ሕዝብ
ሁሌም ከእጅ ወደአፍ ነው ኑሮው።

ጋሽ ቢያድግልኝ - እሱስ ልክ ነህ! እርሱስ ልክ ነህ! ልጄ... (ጥቂት እንደመተከዝ ይላሉ)

ጆኒ - ይቀጥሉልኝ እንጂ ታሪኩን

ጋሽ ቢያድግልኝ - ጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ ግን ምንም የአስኳላ ትምህርት አልተስተማረም። ታዲያ እጀታ እንኳ በሌለው
መዶሻ የሰራቸው ሕንጻዎች ግን ጉድ ጉድ ያሰኛሉ።

ጆኒ - ያለምንም መሳርያማ ሊሆን አይችልም ጋሼ...ለዚያውም ምንም ሳይማር! እንደተለመደው ዝም ብለው መላዕክት
ሰሩት አይሉኝም? (ይላል ተስፋ በቆረጠ ድምጽ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ይኽ እኮ ነው ችግራችሁ ያሁን ዘመን ልጆች!(በቁጣ ድምጽ... ይሄኔ በድንገተኛ ቁጣቸው ደንግጦ
ዮሐንስ ከተቀመጠበት ይነሳና በስጋት ግራ ቀኙን ገላምጦ ማንም እንዳልመጣ ሲያውቅ ይቀመጣል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ይሄ ነው ችግራችሁ። መድገም ቢያውቅችሁ እንዴት ማድነቅ ያቅታችኋል? ሰው ራሱን ባይወድ


እንኳን እንዴት ራሱን ይጠላል? በልማህ መልስልኝ... ያለማሽን ሕንጣ ከማቆምና ከመላዕክት ጋር ከመተባበር የቱ
ይበልጣል?

ጆኒ - እኔንጃ...(ያመነታል)

ጋሽ ቢያድግልኝ - አየህ የሚበልጠውን ስለማታዩ ክብራችሁን ውርደት ታደርጉታላችሁ። በክብር ኒሻናችሁ ...
በሜዳልያችሁ ለአንገታችሁ መታነቂያ ሸምቀቆ ታበጃላችሁ። ሰው እንዴት ምስጋናውን ስድብ ያደርገዋል?

ጆኒ - አልገባኝም ጋሼ(ይበልጥ እያመነታ)

ጋሽ ቢያድግልኝ - በል ተወው... ወደፊት ይገባኻል ....በመላዕክት እጅ መገንባቱን እንደጉድለት መቁጠር ስትተው...


በመላዕክት እጅ መገንባቱን ለስንፍናህ፣ ከአንድ ዓለት ፈልፍለህ ውቅር ሕንጻ ከላይ ወደታች ላለመስራትህ ምክንያት
ማድረግህን ስትተው... ያኔ ይገባኻል።

(ዮሐንስ አንገቱን ሰብቆ በምን ቸገረኝነት ይተወዋል። ጋሽ ቢያድግልኝ በትካዜ ይቀጥላሉ።)


ጋሽ ቢያድግልኝ - እዚያ ነበር የተወለድኩት ...ድንጋይ አፍ አውጥቶ በሚናገርበት ላሊበላ። ትዝ ይለኛል ቤተ ማርያም...
ለልደት መርጌቶቹ ዙርያውን ቆመው ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ ሲሉ... ትዝ ይለኛል ቤተ ጊዮርጊስ.... ዙርያውን
ለፈረንጅ ስናስጎበኝ፣ በአፍሮ አይገባም ስንታሽ ... ቤተ ደናግል፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ መድኃኔዓለም፣ የዮርዳኖስ ጸበል...
ይኸ ሁሉ ትዝ ይለኛል። ይገርምሃል... ብዙ ወንድሞችና እህቶች ነበሩኝ። ተብዛታቸው የተነሳ የአንዳንዶቹን መልክ ዛሬ
ዛሬ አላስታውስም። ላሊበላ ዙርያ ገባዋ ግን አትረሳኝም።

(ይህን እያሉ ዮሐንስ ድንገት ቀና ብሎ የሆነ ነገር ካየ በኋላ በፍጥነት ሹልክ ብሎ ከመድረኩ ይወጣል።)

አየህ... ዛሬ ዛሬ ዕለቱ እንኳ አይታወሰኝም...ግን ልጅነቴን ልቅም አድርጌ አስታውሳለሁ! ዛሬ ዛሬ አቅጣጫ ሁሉ


ጠፍቶኛል... ግን ታውሬም ቢሆን ላስታ ላሊበላ መንገዱ አይጠፋኝም። ብፈልግ በእግሬ እሄዳለሁ እኔ አባትህ... ሙት!
መውጫ መግቢያውን ጥንቅቅ አድርጌ ነው የማውቀው። እየሰማኸኝ ነው...አሁን ግን አረጀሁ። ሰኔ አስራ ሁለት...
የቅዱስ ላሊበላ እረፍት እንኳ ተረሳኝ። ሰማህ? ምን ዋጋ አለኝ ተእንግዲህ? ምን ዋጋ አለኝ ይኼን ይኼን ከረሳሁ? እ?
ምን ዋጋ አለው የአባቱን ሞት የሚረሳ ልጅ? አንድ የኔ ብጤ ዕለቱን በዓሉን ረሳ ማለት እንጀራውን አጣ ማለት
አይደለም?

(በትካዜ ይኼን ለብቻቸው ሲያወሩ ሁለት ፓሊሶች ወደመድረኩ ይገባሉ። ብቻቸውን እያወሩ ሲያዩዋቸው እብድ
ስለመሰሏቸው እርስ በርስ እየተያዩ እየተጠቃቀሱ ይጠጓቸዋል።)

ፖሊስ 1 - ሰላም አረፈዱ ጋሼ?

(ጋሼ ከተከዙበት መምጣቱን እንኳ ያላወቁት ድምጽ አስደንብሯቸው ይነሳሉ።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - እግዚሃር ይመስገን... እግዚሃር ይመስገን... ማናችሁ?

ፖሊስ 2 - ምነው ብቻዎትን የሚያወሩ?

ጋሽ ቢያድግልኝ - ኧረግ የምን ብቻዎትን ነው... እኔማ ተልጄ ነው የማወጋ ...ተ... ማን ነበር ስሙ እቴ(ይላሉ ተቀምጦበት
ወደነበረበት እየጠቆሙ)

ፖሊስ 1 - ማንም የለም እኮ

ጋሽ ቢያድግልኝ - አትቀልድ እንጂ ጌታው... አሁን እያወራን እየተጨዋወትን?... ምነው ኮቴሞ የለው ሲሄድ?.... ምን
የዘንድሮ ልጅ እንደሁ ጥላ ቢስ ነው... ይልቅ ምን ልርዳችሁ?

ፖሊስ 2 - ዮሐንስ የሚባል ልጅ ያውቁ ይሆን... ሰዎች እዚህ አካባቢ አይጠፋም ብለውን ነው።

ጋሽ ቢያድግልኝ - አ...ዎ! ተባረክ ልጄ! ዮ...ሐንስ! ትዝ አለኝ ስሙ... እንዴት ያለ የተባረከ ጥሩ ልጅ መሰለህ ጌታው።
ኡምበርስቲ ሁሉ በጥሷል። እንደው ሥራ ፈትቶ ቤት ሲቀመጥ ጊዜ እዚህ ብቅ እያለ ያጨዋውተኛል። አሁንም እዚሁ
ስንጨዋወት ነው ያረፈድነው። እንደው መሄዱንም ሳይነግረኝ ነው የሄደ። ምናልባት አይቷችሁ ይሆናል። ምነው በሰላም
ፈለጋችሁት? ፎሊሶች ናችሁ እንዴ?

(ይሄኔ ፖሊሶቹ እርስበርስ ይተያዩና)

ፓሊስ 1 - የለም! የለም! አባቴ ጓደኞቹ ነን። እንደው ከተገናኘን ቆይተናል። ቤቱን በምልክት እንኳ ቢነግሩንና ብናገኘው
ጥሩ ነበር። ይኼውሎት እርሱ ጓደኛዬ ወደአሜሪካ ሊሄድ ስለሆነ እንደው ሳያገኘው እንዳይሄድ ብለን ነው።
ጋሽ ቢያድግልኝ - ነ...ው! በጀ! በዚህ በኩል ውረዱ። አዎ... ቤቱ በዚህ በኩል ነው። አዎ የመጀመርያው ግቢ ...በሉ
ይቅናችሁ! በሰላም ያግባህ አንተም።

ፖሊስ 2 - አሜን አሜን አባባ! እግዜር ይስጥልን... ይህቺን ይያዙ....ይያዙ ግዴለም። (ብሎ አስር ብር ያስጨብጣቸዋል።)

(መጨረሻ ላይ ጋሽ ቢያድግልኝ በትራቸውን እንደያዙ መሃል መንገድ ላይ ለብቻቸው ቆመው አንዴ ወደግራ አንዴ ወደቀኝ
እየዞሩ መጋረጃው ይዘጋል።)

ገቢር ሁለት
(መጋረጃው ሲከፈት ጋሽ ቢያድግልኝ በትራቸውን እንደያዙ መሃል መንገድ ላይ ለብቻቸው በድንጋጤ ቆመው ወደአንድ
አቅጣጫ (ወደፊት ለፊት) አፍጥጠዋል። እጃቸው ይንቀጠቀጣል። ደብዘዝ ያለ ብርሃን አለ። ከኋላ አንጀት የሚበላ
የዋሽንት ዜማ ይሰማል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ልጄን አሰሩት።

ሥራ መፍታት ጥፋት ሆኖበት ልጄን አሰሩት።

ሥራ መፍታት ወደእጅ አመል እንደሚመራ አያውቁም?

ረሃብ ወደሌብነት እንደሚመራ አያውቁም?

ደሞ.... እኔው ነኝ እኮ የመራኋቸው! (በሲቃ ድምጽ)

ለወትሮው አቅጣጫ እንኳን በውሉ እማላውቅ ሰው... ሰተት አድርጌ ወደቤቱ መራኋቸው።

ልጄን ሸጥኩት! (በሚንቀጠቀጠጥ እጃቸው ቅድም ከፓሊሱ የተቀበሉትን አስር ብር ከፍ አድርገው እያሳዩ)

ልጄን በአስር ብር ሸጥኩት!

አይ ኪሳራዬ...

አይ አንቺ አገር ኪሳራሽ...

ተቸግረሽ ያስተማርሽውን ልጅሽን ወደችግር ለመዶል የማትቸገሪ(ሳግ እየተናነቃቸው)

ከዚህ በላይ ምን ክህደት አለ?

(እጃቸው ላይ ያለውን ሳንቲም ያንቻቻሉ)

እባካችሁ ተዘከሩኝ

ስላላዳንኩት... ባለማዳኔም ከገዳዮቹ ጋር ስለተባበርኩበት ልጄ ተዘከሩኝ!

በተሳሳተ መንገድ ሰለሰደድኩት... በማይሆን አቅጣጫ ስለመራሁት ልጄ ተዘከሩኝ!

ስለራሴ ዓይን መታወር ሳይሆን በመታወሬ ከክፉ ስላልጠበቅኩት ትውልድ ተዘከሩኝ!

ስላጠፋሁት ትውልድ ተዘከሩኝ!


ከአያቶቹ ስላኳረፍኩት....የጣር ጩኸት ዋይ ዋይ ውስጥ ስለከተትኩት ልጄ ተዘከሩኝ!

እግዚሃር ምነው ምህረትህ በዛብኝ... (ወደላይ ቀና ለማለት እየሞከሩ)

የአባት ጥፋት ለልጅ ቅጣት አልነበረ ሕጉ

ግን እኮ... በልጅ ጥፋት አባትን መቅጣት ነው ወጉ

ማን አሳየውና ጥፋትን?

ማን አሳየውና ክፋትን?

አለመግደል ብቻ እኮ... ከገዳይነት ፍዳ... አያነጻም ነበር

ማዳን ሲችሉ ማሳከም... አለማዳንም ወንጀል ነው... ከገዳይ ጋር መተባበር።

ታዲያ የማትቀጣኝ ምነው?

ጥፋተኛ አይደለሁም? የልጄ ገዳይ ግብረአበር?

አለማዳንም እኮ ወንጀል ነው ከገዳይ ጋር መተባበር?

ማነህ ፎሊስ... (ዞር ዞር ለማለት እየሞከሩ) እኔንም አብረህ እሰረኝ!

የልጄ ገዳይ እኔ ነኝ!

የጥፋቱ ግብረአበር ነኝ! (በሲቃ ድሞጽ)

(ጋሽ ቢያድግልኝ ተመልሰው ድንጋዩ ላይ ቁጭ ብለው ልመናቸውን ይቀጥላሉ። የዋሽንቱ ድሞጽ ይቆማል።)

ጋሽ ቢያድግልኝ - ስለቅዱስ ላሊበላ.... ስለጻድቁ ንጉስ እናቶቼ..... (መጋረጃው ይዘጋል።)

ተፈጸመ!

You might also like