You are on page 1of 6

ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል


ገዳምና ገዳማዊ ሕይወት በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አስተምህሮ
ይህ ጽሁፍ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ምንም እንኳን
በመንፈሳዊ ኮሌጅነቱ አስቀድሞ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴፍሎስ የተመሠረተ ቢሆንም በልዩልዩ ምክንያት
ከተቋረጠ በኋላ በአዲስ መልክ መሥራችና መሪ የነበሩት አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ባላቸው ጥልቅ አስተምህሮ
ውስጥ በገዳምና ገዳማዊ ሕይወት በሚል ርዕስ ለ30ኛ ዓመት የበረከት መታሰቢያ ለማያውቃቸው
ማንነታቸውን ለማሳወቅ ለሚያውቃቸውም ትዝታቸውን እንደገና ለመቀስቀስ የተዘጋጀ ነው፡፡
እኒህ ታላቅ ባለራእይ አባት በዚህ ርዕስ ውስጥ ማንነታቸው ሲዳሰስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለአጭር ግዜ ብቅ ብለው ሳይጠገቡ ለትውልዱ ጥቂት የወንጌል ፋናን እንዲሁም
ገዳማዊ ሕይወትን ሙሉ አድርገው አሳይተው ዳግም ላይታዩ የተሰወሩ የአጥቢያ ኮኮብ ናቸው፡፡
በማስተማርና በጽሑፍ ዘይቤያቸው በአባታዊና በሐዋርያዊ አቋማቸው ይህ ቀረዎት የማይባሉ የማይጠገቡ
ሰው ፍለጋ ዓይኑ ለሚከራተተው አዲስ ትውልድ የስስት እንጀራ ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓለማችንም ጭምር አልፎ አልፎ በዘመናት
በስጦታ ከእግዚአብሔር ለበረከት ከሚሰጡት ጥቂት እውነተኞች አባቶች አንዱ ነበሩ፡፡በተለይም
ራዕያቸውን ስናስብ አዲሱን ትውልድ ከነበረበት ሥልጣኔ ከሚመስለው ከምዕራቡ ዓለም የልብ ወለድ
የራስ ወዳድነት ፍልስፍና ነገር ግን ውስጥ ውስጡ ሰይጣናዊ ልምምድ ከሆነው እየጠፋበት ከነበረው
የሲኦል መንገድ መልሰው ሃሳቡን አቃንተውና የጉዞዉን አቅጣጫ አስቀይረው አሻግሮ የእግዚአብሔርን
ክብር እንዲመለከት አይነልቡናውን ለመክፈት የቻሉ ረቂቅ የማስተዋል ቁልፍ ነበሩ፡፡ጽውዐን አበው ሁሉ
የተለያየ ጸጋ አላቸው፡ብፁዕነታቸው ግን በተሰጣቸው ልዩ መንፈሳዊ ጸጋ በሃገራችን ዛሬ ላለው አዲስ
ትውልድ የተሰጡ የመጀመሪያ ሐዋርያው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ብፁዕ አባታችንን አባትነታቸውን ቀና ብሎ በነበሩበት የአባትነት ደረጃ ማንነታቸውን ለሚመለከት
ሰው ልዩ ፀጋቸው ሃሳብን ከንግግራቸው በላይ በእንቅስቃሴያቸው በአኗኗራቸውም ጭምር ሊገልጡ
የሚችሉ የነበሩ የተለዩ ሊቅነት ከሕይወት ጋር የተሳካላቸው አባት ነበሩ፡፡በዚህም በኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታላላቅ ተብለው የሚጠሩትን ሊቃውንት የቤተክርስቲያን ጠበቆች የተባሉትን እነ
ቅዱስ ቂርሎስን ቅዱስ አትናትዮስ ቅዱስ ባስልዮስ ሁለቱ ጎርጎርዮሶችን በታሪክ የምናውቃቸውን
በሕይወታቸው ገልጠዋቸው አሳይተውናል፡፡
በተለምዶ ሰዎች ሰው ሞቶ ቀብረው ሲመለሱ የታደለ ከሆነ ይረሱታል፣ከባሰም ደግሞ ይወቅሱታል፡፡
ብፁዕነታቸው ግን ለሚወዷት ሁልግዜ እድገቷንና መንፈሳዊ ጥንካሬዋን ለሚያልሙላት ቤተክርስቲያናችን
እንኳን ኖረው “አቤል ሞቶ ሳለ በመስዋዕቱ እስከዛሬ ይናገራል እንደተባለ” ከእረፍታቸው እንኳን
ለሚያውቃቸው ድምፃቸውም በእዝነ ልቡና የሚሰማ አስተማሪ የሆነው መላ እንቅስቃሴያቸው ከዓይነ
ኅሊና የማይጠፋ ነው፡፡ እንኳን የመከሩት ያስተማሩት የገሰጹት ቀርቶ ያላያቸው ያልሰማቸው
የማያውቃቸው ሁሉ ታሪካቸው ሲነገር እየሰማ ያያቸውና የሰማቸው ያክል በፊቱ እየሳለ የሚያያቸው
እንደ ሚያውቃቸው ሆኖ የሚናፍቃቸው ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለነገውም ትውልድ ቤተክርስቲያንን
ሃይማኖቱን ለሚወድ የአእምሮ ማረፊያ የእውነትም ትክክልኛ አባት ናቸው፡፡
ወደ ዋናው ርእሳችን እንመለስና ገዳምና ገዳማዊነትን ስንመለከት ብፁዕነታቸው የራዕያቸው አንዱ ክፍል
በመሆኑ የነበራቸውን ተምኔት ከሥራቸውና ከትምህርታቸው የሰማነውንና የተረዳነውን በአቅማችን
ለመግለጥ እንሞክራለን
ገዳምና ገዳማዊነት/ምንኩስና/ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አስተምህሮ
ስለገዳም ሲነሳ ጥንቱንና መሠረቱን አብነት አድርጎ መነሳት የበለጠ የተነሳንበትን የብፁዕነታቸውን ዓላማ
ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ በታላቁ እንጦንስ ገዳማዊ ሕይወት ሲመሠረት ዓላማው ከዓለም ፈተና ርቆ
እግዚአብሔርን በመላካዊ ሕይወት ማገልገልና ዓለምንም ግዜ አግኝቶ በጸሎት ለመርዳት ነው፡፡
ገዳምና ዓላማው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 10፣37᎓40 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
እርሱን ማገልገል ስለሚችል አንድ አገልጋይ ምን አይነት አቋም ሊኖረው እንደሚገባ እንደተናገረው ፦
“ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም
ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን
አይገባውም።ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።”የሚለውን አምላካዊ
ጥሪ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ ነው፡፡ይህ ጉዞ እውነተኛውን
የክርስቶስንም ትምህርት ገልጦ ያሳያል፡፡
ከዚህም ጋር ገዳማዊ ሕይወት የጎላ ጥቅሙ በዓለም ውስጥ ሲኖር ብዙ ይሰማል ይታያልና
በልምምድ በመስማት በማየት ወደሃልዮነት የተቀየረውን የገቢር ዋዜማ ክፉና መጥፎ የሥጋ አስተሳሰብና
ልማደ ሥጋ ለማስወገድና መንፈሳዊውንም ሕይወት ለመገንባት ልምምድ ለማድረግ የሚያስችል የተቀደሰ
አካሄድ ነው፡፡

ይህን የተረዱ በየትኛውም ጾታ ያሉ መናኞችም ይሁኑ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ለማጠንከር


የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሁሉ በገዳም ሲኖሩም ይሁን ለተወሰነ ግዜ ቆይታ ሲያደርጉ ዕለት በዕለት
በጸሎትም ግዜ ይሁን በትምህርት ግዜ እንዲሁም በማናቸውም የአገልግሎት ዘርፍ በሚያዩትና በሚሰሙት
የቅዱሳን ዜና ሕይወት በሚያሳየው የገዳማውያን ትጋትና ተጋድሎ እምነታቸውን ያሳድጋሉ፣የሥጋ
ፍላጎታቸን መግደል ባይችል መቆጣጠርና ራሳቸውን መግዛት የሚያስችል አቅም ይኖራቸዋል፡፡ማየትም
ማመን ነውና በነገረ ቅዱሳን ላይ ያላቸውን ጥርጥር ይወገድላቸዋል፣ማሕበራዊ ሕይወታቸውም የሰፋ
ይሆናል፣ለሌላው ማካፈልን ሌላውን እንደራስ ማየትና የሰው ልጆች እኩልነትን ያረጋግጣሉ፣ኣለምና በኣለም
ያለው ሁሉ ኃላፊ መሆኑን አውቀው እግዚአብሔርን በማስቀደም በኣለም ዘንድ ሲኖሩ ነቀፌታቸውን
ያስወግዳሉ፣የሚገባቸውን ድርሻቸውን ያውቃሉ፣የሰውን አይከጅሉም የራሳቸውንም አሳልፎ አይሰጡም፡
ይህ ሃሳብ በታላቁ አባት አቡነ ጎርጎርዮስ ከቃላቸውም ከሕይወታቸውም የተገኘ ነው፡፡
ገዳምና ገዳማዊ ሕይወትን በተመለከተ እንደ ብፁዕነታቸው አስተምህሮ ሲገለጽ በሁለት ከፍለን ማየት
እንችላለን

1ኛ ስለነበረው፣ስላለውና ወደፊት ስለሚሆነውን ይመለከታሉ ያስባሉ ያልማሉ

• ይህ ማለት

ሀ. የነበረው ሲባል ገዳምና ገዳማዊ ሕይወት በኢትዮጵያ ሃገራችን መቼና እንዴት ተጀመረ? ከተጀመረ
ጀምሮ ዛሬ እስከ አለንበት ዘመን ምን አተረፈ የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡በብፁዕነታቸው ዘንድ
ለቤተክርስቲያን ማሰብ የማይቋረጥ ከሕይወታቸው ጋር የተቆራኘ የሕይወታቸው አካል ነው፡፡ሲያስቡም
ለቀደሙት ልዩ ክብር ስለነበራቸው ምን ግዜ የሃሳባቸው መነሻ የቀደሙት አበው ናቸው፡፡

ለ. ያለው ማለት ዛሬ ባለንበት ዘመን ገዳማት ምን ይመስላሉ?የተጀመሩበትን ዓላማ እያከናወኑ የገኛሉ


ወይ? ከነዚህ ገዳማት የሚወጡ መናያን በሥራቸውና በኗኗራቸው ቤተክርስቲያንን ምን ያክል ጥያቄዋን
እየመለሱ ነው? የሚለውን ጥያቄ አጉልቶ ያሳያል፡፡ቤተክርስቲያን በልምድ ከመጓዝ ሁልግዜ አካሄዷን
መፈተሽ ስላለባት ምን ነበር?ምንስ አለ? ምን አናቆይ? የሚሉት ጥያቂዎች በየዘመናቱ የሚመልስ አካሄድ
ነው፡፡
ሐ. ወደፊት የሚሆነው የሚለውን ስንመለከት መቼም እንኳን እንደ እርሳቸው ያለ ባለራዕይ
የቤተክርስቲያን አባት ቀርቶ ማንኛውም ሰርቶ አደር የነገን ማሰብ የግድ ነውና የብፁዕነታቸውን ውሎና
አዳር ለሚያውቅ ሁሉ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ እንደሚሰጡት ይታወቃል፡፡ዛሬ
ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ዛሬ መዘጋጀት ያስፈልጋል የሚል የጠነከረ ንግግር ዘወትር ሲናገሩ
ይሰሙ ነበር፡፡በዚያን ግዜ ሲናገሯቸው የነበሩት ሁሉ ዛሬ በየግዜው ሲፈጸሙ ስንመለከት የሰማነውም
የበለጠ እንድናስብበት ያደርገናል፡፡

2ኛ በገዳምና በገዳማዊ ሕይወት ልዩና አገር በቀል የሆነው ሊጠበቅ የሚገባው ምንድነው? እኛ ዘንድ
የሌለው ከሌሎች የምንማረው ምንድን ነው? በሚል ማየት ይቻላል

ሀ. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነት ትውፊቱ የሚጀምረው ከዘመነ ብሉይ


በመሆኑ በተለይም በስነምግባር ደረጃ ለየት ያለ ለእግዚአብሔር የመታዘዝና ትሑትነት ከሌላው ክፍለ ዓለም
በተለየ ዘመናት ሊለውጡት ያላቻሉት አይነኬ ልዩ መታወቂያ ነው፡፡ይህንና ይህን የመሳሰሉትና ከሥርዓተ
ቤተክርስቲያን ጋር አይነኬዎች በመሆናቸው ይህ ተጠንቶ እንዲጠበቅ የማድረግ ትልቅ ራዕይ ነበራቸው
ለ. ብፁዕነታቸው ገዳማት እንደወታደራዊ ማሰልጠኛዎች የባለራዕዮች የመንፈሳዊም የሥጋዊም መሪዎች
መፍለቂያ ነው ብለው ስለሚያምኑ የሥራ ፈትና የወሬ ከችግር የመሸሻ፣የጥቅማጥቅም ቦታዎች ሣይሆኑ
ዓላማ ያላቸው የትምህርትና የሥራ ቦታዎች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ለዚህም ብዙ ግዜ በዓለም አቀፍ
ደረጃ ተዘዋውረው ያዩአቸውን ለምሳሌ በግሪክ በኢየሩሳሌምና በግብፅ ያሉትን ገዳማት ትጋታቸውንና
የሥራ ባህላቸውን እያነሱ ያደንቁም ያንን ባህል በሃገራቸው ገዳማት ላይም ለመተግበር ይመኙም ነበር፡፡
በብፁዕነታቸው ራእይ ውስጥ የምንኩስና ሕይወት ሲዳሰስ
የብፁዕነታቸው ፍጹም የሆነው ነቅዕ የሌለው ኦርቶዶክሳዊ እውቀታቸውና አባታዊ አቋማቸውና
መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሲዳሰስ ለአምላካቸው ቀናእያን ከነበሩት ከነቅዱስ ኤልያስ ና ቅዱስ የሐንስ
መጥምቅ ጀመሮ በብዙ መከራ ውስጥ አልፈው ለዘመናት ሕይወታቸው ትምህርታቸው ከሁሉ በላይ ደግሞ
አገልግሎታቸው ልክ እንደ ዕንቈጳዝዮን እንደሚያበሩት የነበሩትን ቀደመት መንፈሳውያን አርበኞችን ማሳያ
መስታወት እንደነበሩ ምስክሮች ነን፡፡
ስለዚህም ምንኩስና በብፁዕነታቸው አስተምህሮ ቃል በቃል ሲገለጽ የሥጋ ፍላጎቶችን ገድሎ
በመንፈስም በሥጋም የቀደሙትን አባቶች ለመምሰል የሚጣርበት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙበት መንኖ
ጥሪት ያልተለየው የዓላማ ሕይወት እንደሆነ ከቃላቸው ባሻጋር የእለት ተእለት የአኗኗር ሁኔታቸው
ያስተምራል፡፡እዚህ ላይ አንድ እናት ስለብፁዕነታቸው ሲወራ ሰምተው ያሉንን ብናስታውስ ይጠቅመናል፡፡
ቀደም ባለው ግዜ ከእንግሊዝ ሃገር አንድ አባት ገንዘብ ሰጥተውኝ መጻህፍትና ሌሎች የሚያስፈልጉ
ነገሮችን አስገዝተው እንዲልኩኝ ከማስታወሻ ጋር ላኩኝ፡፡አግኝቼም ነገርኳቸው፡፡በኋላ መንግሥት በውጭ
ሃገር ሁሉን አሟልቶ በውጭ ሃገር ኤምባሲ ይከፍታል፡፡ደግሞ ይሄም በዝቶ ብለው ሁሉን አስገዚተው
ሰጥተውኝ ገንዘቡን ግን አልቀበልም ብለው መለሱት ብለው አጫወቱን፡፡”ይህ እንግዲህ ማንነታቸውን
አጉልቶ ያሳያል፡፡
በዚህ ረገድ ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ ሰው የሚያውቀውንና የሚሠራውን ሲናገር ያምርበታል የሚል
ጠንካራ ብሂል ስለነበራቸው ንግግራቸው እንደ እምነታቸው፣እምነታቸውም በሥራቸው የሚያሳዩ ነበሩ፡፡
ይህንን ህይወታቸውን የተመለከተ ሁሉ ወደዚህ ሕይወት እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሠሉ
እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ማንም ሰው እርሳቸውን ለመምሰል ይጥራል፡፡የሰሙትን ከማየት በላይ ምንስ አለ?
በዚያም ላይ አምላካዊ መመሪያውም “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም
አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል
የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።”ይላልና ማቴ 19፥29 ብፁዕነታቸውም ያሳዩን የነበረው ይሕንን ነበር፡፡
በዚህ መሠረት በዚህ ዓላማ የተሰሰለፍን ልንመስላቸውና ልንከተላቸው ይገባል፡፤
በገዳም ውስጥ በሁሉ አሳቢ በመሆናቸው በመንፈሳዊ አባትነት ትጉህ ዘኢይነውም ስለሆኑ አንድ ደቀ
መዝሙር ወደ ገዳሙ ከገባበት ግዜ ጀምረው ጥቂት የምናኔ ሁኔታ ካዩበት ዓላማውን በምክርና በክትትል
ያሳድጉለታል፡፡ለዚህች ቤተክርስቲያን ሰው ስለሚያስፈልጋት ራስህን ስጣት፣ዓለምና በዓለም ያለው ሁሉ
ኃላፊ ስለሆነ ሩጫዋን ለማፋጠን ምንኩስና አንዱ ነውና በርታ እያሉ መንፈሳዊ እንክብካቤ ያደርጉ ነበር፡፡
በዚህ መንገድ ያፈሯቸው አባቶች በሁለንተናዊ አገግሎት እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት የደረሱ
የመሰሏቸው ብፁዐን አቦቶችን ከዲያቆናት ጀምሮ እስከ ስመጥር መምህራነ ወንጌል አበው ቆሞሳትና
ካህናት ነበሩ አሉም፡፡ይህም ወላዴ ዐእላፍ አሰኝቷቸዋል፡፡
በዓላማ ተነስቶ በዓላማ መፈጸም ማለት እንግዲህ እንደዚህ ነው፡፡ከልጆቻቸው መካከል አንደኛው
ታላቅ አባት ገና የረፍታቸው ሰሞን ለአገግሎት አንድ ስመጥር ቦታ ተመድበው አመታዊ የረፍት በአላቸው
ሲከበር መጥተው በሁሉ ሙሉ ስለመሆናቸው ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉን “አሁን እኔ ምን አውቄ ነው
እዚያ ትልቅ ቦታ ሄጄ ክብር ያገኘሁት?በርሳቸው ስምና ዝና እንጂ” አሉ፡፡ እንደዚሁም ከአንጋፋ
ልጆቻቸው መካከል የሆኑት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ንብ የሚያሰኝ ተልእኳቸውን ሲመሰክሩ “እኛ
ግሪክም ጎንደርም ጎጃምም አልሄድንም፣የእኛ ግሪክ ጎንደርና ጎጃማችን እርሳቸው ናቸው ያሉት
አይረሳም”ትጉህ በመሆናቸው ሌላ ሃሳብ ስለሌላቸው እራሳቸዉን ሙሉ ለሙሉ ለቤተክርስቲያን
በመስጠታቸው እስከዚህ ድረስ የተሳካላቸው መናኝ፣ገዳማዊ፣የቤተክርስቲያን ጠበቃ፣ሐዋርያዊ ተከብረው
ቤተክርስቲያናችንን ያስከበሩ የእምነት አርበኛ ነበሩ፡፡
በዚህ አቋማቸውና አስተማሪነታቸው ብዙ የሃይማኖት ልጆችን በምክር በተግሳጽ በቁጣም ጭምር’ተም
ኡ ወኢተአብሡ ነውና” ወልደውና አሳድገው አስተምረውም በዓለም ሁሉ ላይ አሰማርተዋል፡፡የቅዱስ
ሲኖዶስ አባላት ሆነው ፈለጋቸውን የተከተሉ አሁንም በልዩ ልዩ ክፍለ ኣለም በቤተክርስቲያን ላይ
ተሰማርተው ያሉ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል፡፡
የብፁዕነታቸው በረከት በኛ ላይ እጥፍ ድርብ ሆኖ ሁላችንም የጀመርነውን አገግሎታችንን በአግባቡ
ፈጽመን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን ጸሎታቸው ይርዳን፡፡

You might also like