You are on page 1of 2

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡አሜን፡፡

እውነት ማለት ትክክለኛና ስህተት የሌለበት የሐሰት ተቃራኒ ማለት ነው፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ
እውነት ተብሎ የተገለጠው ቃል አንደኛ ባህርይው እውነት የሆነውና የእውነት ምንጭ የሆነውን ልዑል እግዚአብሔርን
የሚያመለክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣውንና በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈውን
ቅዱሱን ቃል ያመለክታል፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የተያያዘና ሰውን ወደዘላለማዊ ህይወት የሚያደርሰውን
መንገድ እንጂ ፍልስፍናዊው እውቀት አያመለክትም፡፡

እግዚአብሔር እውነት ነው፡፡እውነት በመሆኑም

1- ሐሰትን አይናገርም ሐሰት ከቶ በእርሱ ዘንድ የለምና፡፡ (ዘኁ.23÷19)

2- የታመነ ነውና ለሰው የሰጠውን የተስፋ ቃል ይፈጽማል፡፡ (2ጢሞ.2÷11-13፤ዕብ.10÷23)

• ለአባቶቻችን ለአዳም፣ለአብርሐም፣ለይስሐቅ፣ለዳዊት … የሰጠውን ታላቅ ተስፋ የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን


በመስጠት የተስፋ ቃሉን ፈጽሟል፡፡

• ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላም ከዕርገቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱን “አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ
እልክላችኋለሁ፣እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” በማለት መንፈስ ቅዱስን
እንደሚልክላቸው የሰጣቸው ተስፋ ጌታችን ባረገ በአሥረኛው ቀን ተፈጽሟል፡፡(ሐዋ.2÷ )

3- እውነትንም ለሰው ይሰጣል (ይገልጣል)፡፡ (ሮሜ.1÷18-20)

እውነት ምንድን ነው?

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሁለት አበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ እነርሱም እውነትና ምስክርነት ናቸው፡፡ ወንጌላዊው
እውነትን እውነት ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማያያዝ ይጽፋል፡፡ (ዮሐ.1÷9፤14÷6) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
እውነት ምንድነው? ለሚለውና ዓለም ለዘመናት ስትጠይቀው ለኖረችው የህይወት ጥያቄ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች
መልስ ሰጥቷል፡፡

1- በትምህርት ወይም በቃል

 “እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ”፡፡(ዮሐ.14፥6)


 “ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋችሁ፡፡”(ዮሐ.8፥40)
 “እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለሆንሁ አታምኑኝም፡፡”(ዮሐ.8፥45)
 “እኔ ግን እውነት ነገርኳችሁ፡፡”(ዮሐ.16፥7)
 “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ … ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምጼን ይሰማኛል፡፡”(ዮሐ.18፥3)

ጌታችን ራሱ እውነት በመሆኑ በእርሱ የተገለጠውን እውነት ማለትም የወንጌሉን ቃል በእምነት ተቀብሎ
የሚታዘዝ ሁሉ እውነትን ያውቃል ፤እውነትም ነጻ ታወጣዋለች፡፡
2- በቃል ብቻም ሳይሆን በህይወት ፣በንግግር ሳይሆን በዝምታ፣ በብዙ ቃል ሳይሆን በፍጹም ርህራሄና ምህረትን
በማድረግ የተሰጠ መልስም ነው፡፡ይህ መልስ በመስቀል ሰሌዳነት በደሙ ቀለምነት በሞቱ ተጽፎ ለአለሙ ሁሉ
የተገለጠ ፣ የብዙዎችን የህይወት አቅጣጫ ከሐሰት ወደ እውነት፣ ከሞት ጎዳና ወደ ዘላለማዊ ህይወት ፣ከጨለማ ወደ
ሚደነቅ ብርሐን የለወጠ መልስ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለሚያምኑበት ሁሉ የሰጠ፣ የሞት ፍርሀትንና የኃጢአት ባርነትን ቀንበር ከጫንቃ
ሰብሮ ነጻ የሚያወጣ፣ የጨለማን ሥልጣን የሚያስወግድ የህይወትና የብርሐን መልስ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን
አባቶቻችን የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ያህል ወደልዑል እግዚአብሔር ይጸልዩ
የነበረው ጸሎትና የነፍሳቸው ጥማት የነበረው ጥያቄና መሻት በተለይም

• በጎውን ማን ያሳየናል?(መዝ.4፥6)

• እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም፡፡(መዝ.143፥7)

• አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ፡፡(መዝ.21፥1)

ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ (ኢሳ.64፥1) የሚለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኒህ ቅዱሳን አባቶቻችን
የጸሎታቸውና የጥያቄያቸው ሁሉ መልስ፤ የተስፋቸውም ፍጻሜ ሆኖ መጣ፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአለምን
ሽንገላና የሰይጣንን ሐሰት ያሸነፈ፤ የሐሰትን አባት ዲያብሎስን ከዙፋኑ ያዋረደ ፤ለዘመናት ከእግዚአብሔር ለይቶን
የነበረውን የኃጢአት ግድግዳ በመስቀሉ ያፈረሰ ፤የሐሰትንና የጨለማን መጋረጃ ከልባችን በብርሀንነቱ ጉልበት የቀደደ
ወደባህርይ አባቱ ሊያቀርበን የተገለጠ፤ ድል የማይነሳ እውነት የብርሐን መንገድ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለታላቁ ተልዕኮ ሳንፋጠን ወይም ወንጌልን በጨለማው ዐለም ውስጥ ለመስበክ
ሳንንቀሳቀስ ሰይጣን በፊታችን ያስቀመጠውን የሐሰት እንቅፋት በመስቀሉ ያስወገደልን በአለም የምንመላለስበት
የህይወት እውነት ነው፡፡ከጨለማው አለም ገዢዎች ከክፉ መንፈሳዊያን ሰራዊቶች ጋር ስንዋጋ ወገባችንን
የምንታጠቅበት የእውነት መታጠቂያችን ድል የምንነሳበት መሳሪያችን እርሱ ነው፡፡(ኤፌ.6፥10-17)

እናም በአለም ላይ እውነት ከሌለ፦

• እውነተኛና ዘላቂ ሰላም በፍጹም አይኖርም

• ንጹህ ፍቅር ፣ነጻ አዕምሮ ፣ቅን ፍርድ አይታሰብም

• ከሌብነት ወይም ከሙስና የጸዳ ማህበረሰብ … ወዘተ እንዲኖሩ ማሰብም ሆነ መጣር

ያለዝናብ ወይም ያለመስኖ ውሃ እህል ዘርቶ ለማምረት እንደመሞከር ነው፡፡በአለማችን ላይ ሰላም፣ፍቅር ፣ቅን ፍርድ
… ወዘተ እንዲኖር ከተፈለገ የእነዚህን ሁሉ ምንጭ የሆነውን እውነት ኢየሱስ ክርስቶስን እያንዳንዱ ሰው በልቡ
ሊያነግሰው ይገባል፡፡እውነትን የሚፈልግ ሁሉ በቅንነት ቢመረምር የፍለጋው መጨረሻ ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ
ይደመድማል፡፡

You might also like