Professional Documents
Culture Documents
208197
208197
የ ፌዴራል ጠቅላ ይ ፍር ድ ቤት
ሰበር ሰሚችሎት
የሠ/መ/ቁጥር 208197
ፍ ር ድ
ጉዳዩ አንደኛዉ ተጋቢ የፈጸሙን የብድር ዉል ሌላኛዉ ተጋቢ አዉቋል ሊባል የሚችልበትን አግባብ
የሚመለከት ነዉ፡፡ ተጠሪ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች እና በስር 2ኛ ተከሳሽ ላይ
በመሰረቱት ክስ ከአመልካች ጋር ተጋብተዉ እየኖሩ ቆይተዉ በቀን 03/06/2009ዓ/ም በፌዴራል መጀመሪያ
ደረጃ ፍርድ ቤት በተሰጠ ዉሳኔ ጋብቻዉ ፈርሷል፡፡ አመልካች በጋራ ንብረት ክፍፍል ክርክር መልሳቸው
ላይ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በካርታ ቁጥር 32394/97 በአመልካች ስም ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት
የተሰራው ከስር 2ኛ ተከሳሽ በተገኘ ብድር እና እዳውም አልተከፈለም በማለት መልስ የሰጠ ቢሆንም የብድር
ውሉ ተጠሪ ሳያውቁት የተደረገ ነው፡፡ በቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 68(1/መ) መሰረት ከብር 500 በላይ ለማበደርም
ሆነ ለመበደር ተጋቢዎች የጋራ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ተጠሪ የብድር ውል ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ በብድር
ተገኘ የተባለውም ገንዘብም ለትዳር ጥቅም አልዋለም፡፡ ውሉ ከቅን ልቦና ውጪ ተጠሪን ለመጉዳት የተደረገ
በመሆኑ የብድር ውሉ ሊፈርስ ይገባል እንዲሁም የብድር ውሉ ተጠሪ ላይ የሚያመጣው ግዴታ የለም
ተብሎ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
አመልካች በቀን 23/09/2013 ዓ/ም የተጻፈ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡትም ከላይ በተመለከተዉ መሰረት በተሰጠ
ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ሲሆን የአቤቱታቸዉ ይዘት በአጭሩ፡- የብድር ውል
ግዴታ የተገባው በ07/10/2007 ዓ/ም ነዉ፡፡ ተጠሪ በቀን 28/09/2009ዓ/ም ክስ የመሰረቱት ብድሩ መኖሩን
ካወቁ ከስድስት ወር በኋላ መሆኑን አመልካች ከተጠሪ የተሻለ ማስረጃ በማቅረብ አስረድቻለሁ፡፡ የስር
የፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 69/2 ስር የተደነገገዉ የ6 ወር ይርጋ ራሱን ችሎ
የቆመ ይርጋ እንጅ ከሁለት አመት ፍጹማዊ ይርጋ ጋር ግንኙነት የሌለዉ ሆኖ እያለ ጉዳዩን ከሁለት አመት
ይርጋ አንጻር በማየት የተጠሪ ክስ የማቅረብ መብት በይርጋ አልታገደም በሚል አለአግባብ የአመልካችን
መቃወሚያ ዉድቅ አድርጓል፡፡ይግባኝ ሰሚዉ ፍርድ ቤትም የስር ፍርድ ቤትን ስህተት ማረም ሲገባዉ
አለአግባብ ማስረጃ ምዘና ዉስጥ በመግባት ብድር ዉል ግዴታ መገባቱን ተጠሪ ልታዉቅ አትችልም የሚል
ድምዳሜ ላይ በመድረስ የሰጠዉ ዉሳኔ የክርክር አመራር በተመለከተ በሰ/መ/ቁጥር 36979 የተሰጠዉን
የሕግ ትርጉም የሚቀረን ነዉ፡፡በብድር ዉሉ ላይ በግለጽ ገንዘቡ በብድር የተወሰደዉ በባህር ዳር ከተማ
ለምናስገነባዉ ቤት ለማዋል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡በዚህ አግባብ በብድር ዉሉ ላይ ተመልክቶ እያለ
በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2006/1 ስር የተደነገገዉን በሚቃረን አኳኋን በምስክሮች ለማረጋገጥ የተደረገዉ የክርክር
አመራር ስህተት ቢሆንም አመልካች በምስክሮች ገንዘቡ ለትዳር ጥቅም እንደዋለ አስረድቻለሁ፡፡ተጠሪ ግን
ገንዘብ ለትዳር ጥቅም አለመዋሉን በማስረጃ ማስረዳት አልቻሉም፡፡የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ የብድር ዉሉ
መኖሩን አታዉቅም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱት በማስረጃ የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች ወደጎን በመተዉ
በመሆኑ ገንዘቡ ለጋራ ጥቅም ዉሏል ተብሎ እንዲወስንላቸዉ እና የተጠሪ ክስ የማቅረብ መብት በይርጋ ቀሪ
የሆነ ነዉ ተብሎ የስር ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ በመጠየቅ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
የሰበር አጣሪ ችሎት አቤቱታውን መርምሮ አመልካች ከስር 2ኛ ተከሳሽ ጋር ያደረጉት የገንዘብ ብድር ውል
መኖሩን ተጠሪ ካወቁ ከስድስት ወር በኋላ የብድር ውሉ እንዲፈርስ ክስ እንዳቀረቡ የስር ፍርድ ቤት በቀን
10/03/2011 ዓ/ም በሰጠው ብይን ላይ በገለፀበት ሁኔታ አመልካች በስር ፍርድ ቤት ያቀረቡት የይርጋ
መቃወሚያ ውድቅ ተደረገበትን አግባብነት ከቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀፅ 69/2 ጋር
በማገናዘብ ለመመርመር ትዕዛዝ በመስጠቱ ተጠሪ በቀን 07/03/2014 ዓ/ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በላይ አጠር ባለመልኩ የተመለከተዉ የግራ ቀኙ ክርክርና በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ዉሳኔዎች
ይዘት ሲሆን እኛም የሰበር አጣሪ ችሎት የያዘዉን ማስቀረቢያ ጭብጥ ከግምት በማስገባት በስር ፍርድ
ቤቶች በተሰጠ ዉሳኔ የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን አግባብነት ካለዉ ሕግ ጋር
በማገናዘብ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡
ሌላዉ የዚህን ችሎት ትርጉም የሚሻዉ ነጥብ በአንደኛዉ ተጋቢ የዉል ግዴታ ሲገባ ተካፋይ ያልሆነ ተጋቢ
ግዴታዉ መገባቱን አወቀ የሚባለዉ መቼ ነዉ? የሚለዉን የሚመለከት ነዉ፡፡ ከላይ እንደተመለከተዉ
የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69/2 ስር የተጠቀሰዉ የ6 ወር የይርጋ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነዉ የዉል ግዴታ
በአንደኛዉ ተገቢ መገባቱን ለሚያዉቅ ተገቢ ነዉ፡፡ ጊዜዉም ያጠረበት ምክንያትም ያለእሱ ተሳትፎ ግዴታ
መገባቱን እስካወቀ ድረስ ሁለት ዓመት እስኪሆን መጠበቅ ሳያስፈልግ ግዴታ ያመጣዉ ዉል እንዲፈርስ
መጠየቅ ይችላል በሚል እምነት ነዉ፡፡እንግዲህ ይህ ይርጋ ዉል ይፍረስልኝ በሚል ክስ የማቅረብ መብት
ቀሪ የሚያደርግ እስከሆነ ድረስ በስምምነቱ ተሳታፊ ያልሆነ[ዉ]ችዉ ተጋቢ ዉል ይፍረስልኝ ክስ ለማቅረብ
በሚያስችል ልክ ስለዉሉ መኖር የተሟላ እዉቀት ሊኖረዉ(ልኖራት) ይገባል፡፡በዚህ መሰረት በአንደኛዉ
ተጋቢ የተደረገ የገንዘብ ብድር ዉል መኖሩን ሌላዉ/ዋ ተጋቢ አወቀ/አወቀች ሊባል/ልትባል
የሚችለዉ/የምትችለዉ ቢያንስ የገንዘብ ብድር ዉሉ ከማን ጋር እንደተደረገ፣ የምን ያህል ገንዘብ ብድር ዉል
እንደሆነ፣ መቼ የተደረገ የብድር ዉል እንደሆነ ማወቅ ሲችል/ስትችል ነዉ፡፡እነዚህን ፍሬ ነገሮች ያላወቀ
ተጋቢ የገንዘብ ብድር ዉሉ ይፍረስልኝ ክስ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ይቸገራል፡፡ምክንያቱም የገንዘብ ብድር ዉል
ይፍረስልኝ ዳኝነት በመጠየቅ ክስ የሚያቀርበዉ ተጋቢ በሌላኛዉ ተጋቢ የብድር ዉል ግዴታ መገባቱን
በጥቅሉ ከማወቅ ባለፈ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ በቁጥር 33(2 እና 3) ፣ 80(2-4)፣85 እና 222/1
እንደተደነገገዉ የተከሳሹን ማንነት እና የክሱን ምክንያት (ለክሱ አስፈላጊ የሆኑ ፍሬ ነገሮችን) በክሱ
እንዲገልጽ ሕጉ ስለሚያስገድደዉ ሌላኛዉ ተጋቢ ከማን ጋር የምን ያህል ገንዘብ ብድር ዉል እንደተዋዋለ
እና የብድር ዉሉ መቼ እንደተደረገ ማወቅና በክስ አቤቱታዉ ላይ በፍሬ ነገር ደረጃ መግለጽ ስለሚኖርበት
እና ሥልጣን ያለዉን ፍርድ ቤት ከብድሩ ገንዘብ መጠን አንጻር ለይቶ ገልጾ ክሱን ማቅረብ ስለሚኖርበት
ነዉ፡፡
እንዲሁም አንድን ፍሬ ነገር ማስረጃ አቅርቦ የማስረዳት ሸክምን ከሚመለከተዉ መሠረታዊዉ መርህ (Basic
Principle of Burden of Proof) መረዳት እንደሚቻለዉ አንድ አከራካሪ ፍሬ ነገር አለ ብሎ የሚከራከር ሰዉ
ፍሬ ነገሩ መኖሩን በማስረጃ የማስረዳት ሸክም(ግዴታ) አለበት፡፡ (የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 258-260 እና
የፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2001/1 ይመለከቷል)፡፡በዚህ መሰረት ግዴታ መገባቱን አዉቋል ብሎ በቤተሰብ ሕጉ
በያዝነዉ ጉዳይ ተጠሪ ይፈርስ ዘንድ ዳኝነት በመጠየቅ በስር ፍርድ ቤት በአሁን አመልካች እና በስር 2ኛ
ተከሳሽ ላይ ክስ የመሰረቱበት የገንዘብ ብድር ዉል አመልካች ከተጠሪ ጋር በጋብቻ ዉስጥ ተሳስረዉ
በነበሩበት ጊዜ ከስር 2ኛ ተከሳሽ ጋር ተዋዉለዋል የተባለዉን ዉል ነዉ፡፡በዚህ የብድር ዉል ላይ ተጠሪ
በተዋዋይነት አለመሳተፋቸዉ እና ከክርክሩ እንደተገነዘብነዉም የብድር ግዴታ የተገባበት የገንዘብ መጠን ብር
450,000.00 መሆኑ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ፡፡ አመልካች የገንዘብ ብድር ዉል ግዴታ መገባቱን ተጠሪ
ክሱ ከመቅረቡ ከ6 ወር በፊት ታዉቅ ነበር ያሉትን ለማስረዳት ያቀረቧቸዉ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት
ቃል አመልካች ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ብድር እንደተበደሩ ለተጠሪ ነግረዋቸዋል የሚል እንደነበር የስር
ፍርድ ቤቶች በሕግ የተሰጣቸዉን የምስክሮችን ቃል የመመዘን ሥልጣን በመጠቀም ያረጋገጡት ፍሬ ነገር
ነዉ፡፡ በዚህ መልኩ አመልካች በምስክሮቻቸዉ በጥቅሉ ያስረዱት አመልካች ከማን ጋር ምን ያህል ገንዘብ
ለመበደር መቼ በተደረገ የብድር ዉል እንደተዋዋሉ ተጠሪ ዉል ይፍረስልኝ ክስ ለመመስረት በሚያስችላቸዉ
በተሟላ መልኩ አዉቀዋል የሚያሰኝ ማስረጃ ወይም ምስክርነት ቃል አይደለም፡፡
በሌላ በኩል የስር ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተጠሪ ክስ የማቅረብ መብት በይርጋ ቀሪ
አልሆነም ሲል የደረሰበት ደምዳሜ ከዉጤት አንጻር ተገቢ ቢሆንም ተጠሪ የብድር ዉል መገባቱን ከ6 ወር
ሲጠቃለል ለክሱ መነሻ የሆነዉ የገንዘብ ብድር ዉል የተደረገዉ በቀን 07/10/2007ዓ/ም ሲሆን ተጠሪ ክስ
የመሰረቱት ደግሞ የብድር ዉል ግዴታ ከተገባ ሁለት አመት ሳይሞላዉ በቀን 28/09/2009ዓ/ም
ነዉ፡፡አመልካች ከስር 2ኛ ተከሳሽ ጋር የገንዘብ ብድር ዉል ሲያደርጉ ተጠሪ በተዋዋይነት እንዳልተሳተፉ
ከመረጋገጡም በተጨማሪ ተጠሪ ክስ ከማቅረባቸዉ ከ6 ወር በፊት የገንዘብ ብድር ዉል ግዴታ መገባቱን
ተጠሪ ከላይ በተመለከተዉ አግባብ በተሟላ መልኩ እንደሚያዉቁ አመልካች አለማስረዳታቸዉ ተረጋግጧል፡፡
ስለሆነም የ6 ወር ይርጋ ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት የለዉም፡፡ በመሆኑም ከላይ እንደተመለከተዉ የስር ፍርድ
ቤቶች ዉሳኔ ላይ የተለያዩ ጉድለቶች ቢኖሩም ተጠሪ ክስ የመሰረቱት በተዋዋይነት ያልተሳተፉት ወይም
ፈቃዳቸዉን ያልገለጹበት ዉል እንዲፈርስላቸዉ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ እና በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 69/2
መሰረት የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ መሰረት በማድረግ ሲታይ የተጠሪ ክስ የማቅረብ መብት በይርጋ ቀሪ
አልሆነም በማለት በሰጡት ዉሳኔም ሆነ ከተጠሪ አንጻር የብድር ዉሉ እንዲፈርስ (ተጠሪን
አይመለከታቸዉም ሲሉ) በሰጡት ዉሳኔ ከዉጤት አንጻር ሲታይ በዚህ ችሎት ደረጃ ሊታረም የሚችል
የተፈጸ ስህተት ባለመኖሩ ተከታዩን ወስነናል፡፡
ዉ ሳ ኔ
1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 63059 ላይ በቀን 10/03/2011ዓ/ም የሰጠዉ
ብይን እና በቀን 17/04/2012ዓ/ም የሰጠዉ ዉሳኔ እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ
ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 251127 ላይ በቀን 06/06/2013ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር
348/1 መሰረት ፀንተዋል፡፡
2. ግራ ቀኝ በዚህ ችሎት ያወጡትን ወጭ የየራሳቸዉን እንዲችሉ ተወስኗል፡፡