You are on page 1of 4

የሠበር መ/ቁ 43166

ታህሳስ 13 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

አመልካች፡- የባሕርትራንዚት አገልግሎት ድርጅት፡- ነ/ፈጅ ትዕግስት ንጉሴ ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡- አቶ ካሣዬ ወንድሙ - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የተጀመረው የአሁን አመልካች በስር 1 ኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ

መክብብ ጌታነህ የአመልካች ድርጅት የኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ የአሁን ተጠሪ ደግሞ ረዳት የክፍል

ኃላፊ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት አመልካች የመርከብ ወኩል ከሆነበት ፖርት ሰርብ ካናዳ ከተባለ

የመርከብ ድርጅት የክፍያ የዕቃ ግዢ ወይም የሥራ ትዕዛዝ ሳይሰጥ በስር 1 ኛ ተከሳሽ በተሰጠ ትእዛዝ

የአሁን ተጠሪ በሁለት ቼኮች ብር 5‚976 ከአመልካች ካዝና አውጥተው ከወሰዱ በኋላ ሂሳብ

ለማወራረድ ያቀረቡት ደረሰኝ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የስር ተከሳሾች የተጠቀሰውን ገንዘብ

ከነወለዱ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ፌ/መጀ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ

ነው፡፡

በስር 2 ኛ ተከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ደግሞ በበኩላቸው በሰጡት መልስ ከሳሽ ክርክር

በተነሳበት ገንዘብ ላይ መብት ወይም ጥቅም ስለሌለው ክስ ሊያቀርብ አይችልም፣ ክሱም

በፍ/ብ/ህ/ቁጥር 2143 እና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 161 መሠረት በይርጋ ቀሪ ነው በማለት

የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበው በፍሬ ጉዳዩም በወቅቱ የዕቃ ምዝገባና ድልደላ ሠራተኛ

1
ስለነበርኩና ገንዘቡም ወጪ እንዲሆን የታዘዘው በስር 1 ኛ ተከሳሽ በመሆኑ ከባለመርከቡ ጋር ቀጥተኛ

ግንኙነት እንዳልነበረኝ ታውቆና የቀረበብኝ ከስ ውድቅ ተደርጐ በነፃ ልሰናበት በማለት ተከራክረዋል፡፡

ፍ/ቤቱም ከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ደንበኛው ከሆነው የመርከብ ድርጅት በውክልና

የተቀበለ ቢሆንም ገንዘቡን በራሱ ስም ባንክ አስገብቶ ራሱ የሚያዝበት በመሆኑ የስር ተከሳሾች

ይህንን ገንዘብ አውጥተው ከወሰዱ ከከሳሽ ውጩ ሊጠይቃቸው የሚችል ማንም የለም፡፡ ስለዚህ

የአሁን አመልካች ከሂሳቡ ተወሰደ በተባለው ገንዘብ ላይ መብትና ጥቅም አለው ይርጋውን በተመለከተ

ክሱ ያለአግባብ መበልፀግን የተመለከተ እንደመሆኑ የ 2 ዓመቱ ይርጋ ተፈፃሚ እንደማይሆንበት

በፍ/ብ/ህ/ቁጥር 2143(3) ስለተደነገገና የይረጋው ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1845 መሠረት 10 ዓመት በመሆኑ

ይርጋው አላለፈም በማለት ፍ/ቤቱ መቃወሚያውን ባለመቀበል ተከሳሽ በመልሳቸው ገንዘቡ ወጩ

መደረጉንና የወጪ ትእዛዙም በጽሁፍ አለመሰጠቱን በማመን በቃልም ሊሰጥ ይችላል ቢሉም

እንደዚህ አይነት አሰራር እንደነበረ ያቀረቡት ማስረጃ ካለመኖሩም በላይ እንደዚ አይነት ትእዛዝ በቃል

የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳልነረ ፍ/ቤቱ በከሳሽ ከቀረቡት ማስረጃዎች ተረድቷል፡፡ ገንዘቡ የወጣው

ለመርከብ ድርጅቱ ነው እንዳይባልም ድርጅቱ የሰጠው ደረሰኝ አልቀረበም የስር 2 ኛ ተከሳሽ ገንዘቡን

ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ስለተረጋገጠ ገንዘቡን ለከሳሽ ይመልሱ በሌላ በኩል የከሳሽ ድርጅት

የሠራተኞቹን የሥራ ድርሻና የኃላፊነት ወሰን የተመለከተ ደንብ የሌለው መሆኑንና 2 ኛ ተከሳሽ

ገንዘብ በስማቸው ወጪ እንዲሆን ሲታዘዝ ወጪ አድርገው ለአለቃቸው መስጠት የሚሠራበት

የመ/ቤቱ ልማዳዊ አሠራር መሆኑን ፍ/ቤቱ አረጋግጧል 2 ኛ ተከሳሽ ገንዘቡን ለ 1 ኛ ተከሳሽ

መስጠታቸው በከሳሽ ታምኗል፣ በዚህ ምክንያት 2 ኛ ተከሳሽ ያለአግባብ በልጽገዋል ለማለት

አይቻልም በመሆኑም 2 ኛ ተከሳሽ ያለአግባብ በልጽገዋል ተብሎ የቀረበባቸውን ክስ ፍ/ቤቱ ውድቅ

አድርጐታል በማለት ወስኗል፡፡

የአሁን አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ

የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348(1) መሠረት አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ

የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

2
የአመልካች ነገረ ፈጅ ታህሳስ 09 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች

ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው

አቅርበዋል፡፡ የአቤቱታው ይዘት በአጭሩ ተጠሪ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን በተለያዩ ቼኮች አመልካች

የባንክ ሂሳብ ወጪ ማድረጋቸውም ሆነ ይህንኑ ገንዘብ አለማወራረዳቸው አልካዱም ገንዘቡን

ባለማወራረዳቸው ወይም ለአመልካች ባለመመለሳቸው በአመልካች ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚባል

እና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2027(1.2) መሠረት የሚያስጠይቅ ሆኖ እያለ ተጠሪ ያላግባብ በልጽገዋል

በማለት አመልካች አቤቱታ ባላቀረበበት ሁኔታ ተጠሪ አላግባብ ስለመበልፀጋቸው አልተረጋገጠም

ተብሎ ክሱ ውድቅ የሆነው መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ስለሆነ ሊታም ይገባዋል በማለት

መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የስር ፍርድ ቤት ተጠሪ ገንዘቡን ወጭ

አድርጐ በስር አንደኛ ተከሳሽ ለነበረ ሰጥቷል በሚል ምክንያት ገንዘቡን የመክፈል ኃላፊነት የለበትም

በማለት የተሰጠው ውሳኔ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት

እንዲቀርብ ተደርጐ ተጠሪ ነሐሴ 07 ቀን 2001 ዓ.ም በሠጡት መልስ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ

መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ የአመልካች ነገረ ፈጅ

በበኩላቸው የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ጥቅምት 09 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ

የመልስ መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር

ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ

ለሰበር ችሎት ቀርቦ ሊመረመር ይገባል ተብሎ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ በሚከተለው መልኩ

መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ የአመልካች ሰራተኛ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት

በቅርብ አለቃቸው ትእዛዝ መሠረት ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ገንዘብ በተለያዩ ቼኮች ከባንክ

አውጥተው በስር 1 ኛ ተከሳሽ ለነበሩትና ገንዘቡ እንዲወጣ ላዘዙት አለቃቸው መስጠታቸው

መረጋገጡን ነው፡፡ ይህ ገንዘብ በህጋዊ አግባብ ያልተወራረደ መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡

3
እንግዲህ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ያለው ግንኙነት የአሰሪና ሰራተኛ ሲሆን ሰራተኛ

በአሰሪው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳትም ሊከተል የሚገባው ኃላፊነት መታየት ያለበት በመካከላቸው

ያለውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ተጠሪ አከራካሪውን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለስር 1 ኛ

ተከሳሽ መስጠታቸው በአመልካች ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልካች ጠቅሶ የሚከራከር ሲሆን ተጠሪ

የስር 1 ኛ ተከሳሽ የቅርብ ታዛዥ ሰራተኛ ስለመሆናቸውን ግን ያስተባበለው ነገር የለም፡፡ ተጠሪ

የቅርብ አለቃቸውን ትእዛዝ ላለማክበር ወይም ተገቢነቱን ማወቅ የነበረባቸው ስለመሆኑ

ሃላፊነታቸውንና የስራ ድርሻ በመግለጽ አመልካች በስር ፍ/ቤት ያረጋገጠው ነገር የለም፡፡ አመልካች

ተጠሪ የፈፀሙት ጥፋት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2027 እና 2028 ድንጋጌዎች መንፈስ በሚጠይቀው አኳኋን

ያረጋገጠው ጉዳይ አለመሆኑን ከመዝገቡ ተገንዝበናል፡፡ በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ

መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል፡፡

ውሳኔ

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 18243 ግንቦት 17 ቀን 1999 ዓ.ም

ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 58247 ህዳር 02 ቀን 2001 ዓ.ም የፀናው

ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሠረተ ፀንቷል፡፡

2. ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

3. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የሦስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

You might also like